መክብብ
1 በኢየሩሳሌም የነገሠው+ የሰብሳቢው*+ የዳዊት ልጅ ቃል።
3 ሰው ከፀሐይ በታች በትጋት ከሚያከናውነውና ከሚለፋበት ሥራ ሁሉ
የሚያገኘው ጥቅም ምንድን ነው?+
6 ነፋስ ወደ ደቡብ ይነፍሳል፤ ወደ ሰሜንም ዞሮ ይሄዳል፤
ክብ እየሠራ ያለማቋረጥ ይሽከረከራል፤ ደግሞም ነፋሱ ዑደቱን ይቀጥላል።
7 ጅረቶች* ሁሉ ወደ ባሕር ይፈስሳሉ፤ ሆኖም ባሕሩ አይሞላም።+
ጅረቶቹ እንደገና ይፈስሱ ዘንድ ወደሚነሱበት ወደዚያው ቦታ ተመልሰው ይሄዳሉ።+
8 ሁሉ ነገር አሰልቺ ነው፤
ሁሉንም ነገር ሊገልጽ የሚችል ሰው የለም።
ዓይን አይቶ አይጠግብም፤
ጆሮም ሰምቶ አይሞላም።
10 አንድ ሰው “ተመልከት፣ ይህ አዲስ ነገር ነው” ሊል የሚችለው ነገር ይኖራል?
ከጥንት ጀምሮ የነበረ ነው፤
ከእኛ ዘመን በፊት የነበረ ነው።
11 በቀድሞ ዘመን የነበሩትን ሰዎች ማንም አያስታውሳቸውም፤
ከጊዜ በኋላ የሚመጡትንም የሚያስታውሳቸው አይኖርም፤
ከእነሱ በኋላ የሚነሱት ሰዎችም እንኳ አያስታውሷቸውም።+
12 እኔ ሰብሳቢው በኢየሩሳሌም፣ የእስራኤል ንጉሥ ነበርኩ።+ 13 ከሰማይ በታች የተሠራውን ነገር ሁሉ ይኸውም አምላክ የሰው ልጆች እንዲጠመዱበት የሰጣቸውን አሰልቺ ሥራ በጥበብ+ ለማጥናትና ለመመርመር ከልቤ ጥረት አደረግኩ።+
14 ከፀሐይ በታች የተሠራውን ሥራ ሁሉ ተመለከትኩ፤
እነሆ፣ ሁሉም ከንቱ ነፋስንም እንደማሳደድ ነው።+
15 የተጣመመ ነገር ሊቃና አይችልም፤
የሌለም ነገር በምንም መንገድ ሊቆጠር አይችልም።
16 እኔም በልቤ እንዲህ አልኩ፦ “እነሆ፣ ከእኔ በፊት በኢየሩሳሌም ከነበሩት ሁሉ እጅግ የላቀ ጥበብ አገኘሁ፤+ ልቤም ከፍተኛ ጥበብና እውቀት አገኘ።”+ 17 እኔም ጥበብንና እብደትን* እንዲሁም ሞኝነትን ለመረዳት ከልቤ ጥረት አደረግኩ፤+ ይህም ቢሆን ነፋስን እንደማሳደድ ነው።
18 ጥበብ ሲበዛ ብስጭትም ይበዛልና፤
በመሆኑም እውቀትን የሚጨምር ሁሉ ሥቃይንም ይጨምራል።+
2 እኔም በልቤ “እስቲ ደስታን ልፈትንና ምን መልካም ነገር እንደሚገኝ ልይ” አልኩ። ይሁንና ይህም ከንቱ ነበር።
2 ሳቅ “እብደት ነው!”
ደስታም “ምን ይጠቅማል?” አልኩ።
3 በገዛ ጥበቤ እየተመራሁና ራሴን በወይን ጠጅ እያስደሰትኩ+ በጥልቀት መረመርኩ፤ ሰዎች አጭር በሆነው የሕይወት ዘመናቸው ከሰማይ በታች ሊያደርጉት የሚችሉት ከሁሉ የተሻለ ነገር ምን እንደሆነ ለማወቅ በሞኝነት እንኳ ሳይቀር ተመላለስኩ። 4 ታላላቅ ሥራዎችን አከናወንኩ።+ ለራሴ ቤቶችን ሠራሁ፤+ ወይንም ተከልኩ።+ 5 ለራሴ የአትክልት ስፍራዎችንና መናፈሻዎችን አዘጋጀሁ፤ በእነዚህም ቦታዎች ሁሉንም ዓይነት የፍራፍሬ ዛፎች ተከልኩ። 6 በእርሻው መሬት ላይ እያደጉ ያሉትን ዛፎች* ለማጠጣት የውኃ ማጠራቀሚያዎችን ሠራሁ። 7 ወንድና ሴት አገልጋዮች አስመጣሁ፤+ በቤቴ የተወለዱ አገልጋዮችም* ነበሩኝ። በተጨማሪም ከእኔ በፊት በኢየሩሳሌም ከነበሩት ሁሉ ይበልጥ ብዛት ያላቸው እንስሶች፣ ከብቶችና መንጎች ነበሩኝ።+ 8 ለራሴም ብርና ወርቅ፣+ የነገሥታትንና የአውራጃዎችን ውድ ሀብት* አከማቸሁ።+ ወንድና ሴት ዘፋኞችን እንዲሁም የሰው ልጆች እጅግ የሚደሰቱባቸውን ብዙ ሴቶች* ሰበሰብኩ። 9 በመሆኑም ከእኔ በፊት በኢየሩሳሌም ከነበሩት ሁሉ ይበልጥ ታላቅ ሰው ሆንኩ።+ ደግሞም ጥበቤ ከእኔ አልተለየችም።
10 የተመኘሁትን ነገር ሁሉ ራሴን አልነፈግኩም።*+ ልቤንም ደስ የሚያሰኘውን ነገር ሁሉ አልከለከልኩትም፤ ልቤ በትጋት በማከናውነው ሥራ ሁሉ ደስ ይሰኝ ነበርና፤ ብዙ ለደከምኩበት ሥራ ሁሉ ያገኘሁት ወሮታ* ይህ ነበር።+ 11 ሆኖም እጆቼ የሠሩትን ሥራ ሁሉና ዳር ለማድረስ የደከምኩበትን ሥራ+ ሁሉ መለስ ብዬ ሳስብ፣ ሁሉ ነገር ከንቱ፣ ነፋስንም እንደማሳደድ መሆኑን አስተዋልኩ፤+ ከፀሐይም በታች እውነተኛ ፋይዳ* ያለው አንዳች ነገር አልነበረም።+
12 ከዚያም ትኩረቴን ወደ ጥበብ፣ እብደትና ሞኝነት አዞርኩ።+ (ከንጉሥ በኋላ የሚመጣው ሰው ምን ሊያደርግ ይችላል? ሊያደርግ የሚችለው ቀደም ሲል የተደረገውን ነገር ብቻ ነው።) 13 እኔም ብርሃን ከጨለማ የተሻለ ጥቅም እንዳለው ሁሉ ጥበብም ከሞኝነት የተሻለ ጥቅም እንዳለው ተገነዘብኩ።+
14 የጥበበኛ ሰው ዓይኖች ያሉት በራሱ ላይ ነው፤*+ ሞኝ ሰው ግን በጨለማ ውስጥ ይሄዳል።+ ደግሞም የሁለቱም ፍጻሜ* አንድ እንደሆነ ተገነዘብኩ።+ 15 እኔም በልቤ “በሞኙ ላይ የሚደርሰው በእኔም ላይ ይደርሳል” አልኩ።+ ታዲያ እጅግ ጥበበኛ በመሆኔ ምን አተርፋለሁ? በልቤም “ይህም ከንቱ ነው” አልኩ። 16 ጥበበኛውም ሆነ ሞኙ ለዘለቄታው አይታወሱምና።+ ሁሉም በሚመጡት ዘመናት ይረሳሉ። ለመሆኑ ጥበበኛው የሚሞተው እንዴት ነው? ልክ እንደ ሞኙ ሰው ይሞታል።+
17 እኔም ከፀሐይ በታች የሚሠራው ሥራ ሁሉ አስጨናቂ ሆኖ ስለታየኝ ሕይወትን ጠላሁ፤+ ሁሉም ከንቱ፣+ ነፋስንም እንደማሳደድ ነውና።+ 18 ከኋላዬ ለሚመጣው ሰው ትቼው ስለምሄድ+ ከፀሐይ በታች እጅግ የደከምኩበትን ሥራ ሁሉ+ ጠላሁ። 19 ጥበበኛ ወይም ሞኝ እንደሚሆን የሚያውቅ ማን ነው?+ ሆኖም ከፀሐይ በታች በድካሜና በጥበቤ ያፈራሁትን ነገር ሁሉ ይወርሰዋል። ይህም ቢሆን ከንቱ ነው። 20 በመሆኑም ከፀሐይ በታች በለፋሁበት አድካሚ ሥራ ሁሉ ልቤ ተስፋ መቁረጥ ጀመረ። 21 ሰው በጥበብ፣ በእውቀትና በብልሃት እየተመራ ሥራውን በትጋት ሊያከናውን ይችላል፤ ይሁንና ድርሻውን* ምንም ላልደከመበት ሰው ያስረክባል።+ ይህም ከንቱና እጅግ አሳዛኝ* ነው።
22 ሰው ከፀሐይ በታች ከደከመበት ሁሉና ተግቶ እንዲሠራ ከሚገፋፋው ብርቱ ፍላጎት* የሚያገኘው ትርፍ ምንድን ነው?+ 23 በሕይወት ዘመኑ ሁሉ ሥራው የሚያስገኝለት ነገር ቢኖር ሥቃይና ብስጭት ነው፤+ በሌሊትም እንኳ ልቡ አያርፍም።+ ይህም ከንቱ ነው።
24 ሰው ከመብላትና ከመጠጣት እንዲሁም ተግቶ በመሥራት እርካታ ከማግኘት* የሚሻለው ነገር የለም።+ ይህም ቢሆን ከእውነተኛው አምላክ እጅ የተገኘ መሆኑን ተገንዝቤአለሁ፤+ 25 ደግሞስ ከእኔ የተሻለ የሚበላና የሚጠጣ ማን ነው?+
26 አምላክ እሱን ለሚያስደስት ሰው ጥበብ፣ እውቀትና ደስታ ይሰጣል፤+ ኃጢአተኛ ለሆነው ግን እውነተኛውን አምላክ ለሚያስደስት ሰው ይሰጥ ዘንድ የመሰብሰብና የማከማቸት ሥራ ሰጥቶታል።+ ይህም ከንቱና ነፋስን እንደማሳደድ ነው።
3 ለሁሉም ነገር ጊዜ አለው፤
ከሰማይ በታች ለሚከናወን ነገር ሁሉ ጊዜ አለው፦
2 ለመወለድ ጊዜ አለው፤* ለመሞትም ጊዜ አለው፤
ለመትከል ጊዜ አለው፤ የተተከለውን ለመንቀልም ጊዜ አለው፤
3 ለመግደል ጊዜ አለው፤ ለመፈወስም ጊዜ አለው፤
ለማፍረስ ጊዜ አለው፤ ለመገንባትም ጊዜ አለው፤
4 ለማልቀስ ጊዜ አለው፤ ለመሳቅም ጊዜ አለው፤
ለዋይታ ጊዜ አለው፤ ለጭፈራም* ጊዜ አለው፤
5 ድንጋይ ለመጣል ጊዜ አለው፤ ድንጋይ ለመሰብሰብም ጊዜ አለው፤
ለማቀፍ ጊዜ አለው፤ ከማቀፍ ለመቆጠብም ጊዜ አለው፤
6 ለመፈለግ ጊዜ አለው፤ ጠፍቷል ብሎ ለመተውም ጊዜ አለው፤
ለማስቀመጥ ጊዜ አለው፤ አውጥቶ ለመጣልም ጊዜ አለው፤
7 ለመቅደድ ጊዜ አለው፤+ ለመስፋትም ጊዜ አለው፤
ዝም ለማለት ጊዜ አለው፤+ ለመናገርም ጊዜ አለው፤+
8 ለመውደድ ጊዜ አለው፤ ለመጥላትም ጊዜ አለው፤+
ለጦርነት ጊዜ አለው፤ ለሰላምም ጊዜ አለው።
9 ሠራተኛ ከልፋቱ ሁሉ የሚያገኘው ጥቅም ምንድን ነው?+ 10 አምላክ የሰው ልጆች እንዲጠመዱበት የሰጣቸውን ሥራ ተመለከትኩ። 11 አምላክ ሁሉንም ነገር በወቅቱ ውብ* አድርጎ ሠርቶታል።+ ደግሞም ዘላለማዊነትን በልባቸው ውስጥ አኑሯል፤ ይሁንና የሰው ልጆች እውነተኛው አምላክ ከመጀመሪያው አንስቶ እስከ መጨረሻው ድረስ ያከናወነውን ሥራ በምንም ዓይነት መርምረው ሊደርሱበት አይችሉም።
12 ለሰው በሕይወት ዘመኑ ከመደሰትና መልካም ከማድረግ የተሻለ ነገር የለም ብዬ ደመደምኩ፤+ 13 ደግሞም ለሰው ከመብላትና ከመጠጣት እንዲሁም ተግቶ በሚሠራው ሥራ ሁሉ ደስታ ከማግኘት የተሻለ ነገር የለም። ይህ የአምላክ ስጦታ ነው።+
14 እውነተኛው አምላክ የሚሠራው ነገር ሁሉ ለዘላለም ጸንቶ እንደሚኖር ተረድቻለሁ። በእሱ ላይ የሚጨመር ምንም ነገር የለም፤ ከእሱም ላይ የሚቀነስ ምንም ነገር የለም። እውነተኛው አምላክ በዚህ መንገድ የሠራው ሰዎች ይፈሩት ዘንድ ነው።+
15 አሁን የሚሆነው ነገር ሁሉ ከዚህ በፊት የሆነ ነው፤ ወደፊት የሚመጣው ነገር ከዚህ በፊት የነበረ ነው፤+ ሆኖም እውነተኛው አምላክ፣ ሲያሳድዱት የነበረውን* አጥብቆ ይሻዋል።
16 ደግሞም ከፀሐይ በታች ይህን አየሁ፦ በፍትሕ ቦታ ክፋት፣ በጽድቅም ቦታ ክፋት ነበር።+ 17 እኔም በልቤ እንዲህ አልኩ፦ “እውነተኛው አምላክ በጻድቁም ሆነ በኃጢአተኛው ላይ ይፈርዳል፤+ ማንኛውም ድርጊትና ማንኛውም ተግባር ጊዜ አለውና።”
18 እኔም በልቤ፣ እውነተኛው አምላክ የሰው ልጆችን ይፈትናቸዋል፤ እንደ እንስሳት መሆናቸውንም ያሳያቸዋል አልኩ፤ 19 የሰው ልጆች ፍጻሜና* የእንስሳት ፍጻሜ ተመሳሳይ ነውና፤ የሁሉም ፍጻሜ አንድ ነው።+ አንዱ እንደሚሞት ሌላውም እንዲሁ ይሞታል፤ የሁሉም መንፈስ አንድ ዓይነት ነው።+ በመሆኑም ሰው ከእንስሳ ብልጫ የለውም፤ ሁሉም ከንቱ ነውና። 20 ሁሉም ወደ አንድ ቦታ ይሄዳሉ።+ ሁሉም የተገኙት ከአፈር ነው፤+ ሁሉም ወደ አፈር ይመለሳሉ።+ 21 የሰው ልጆች መንፈስ ወደ ላይ ይወጣ እንደሆነ፣ የእንስሳት መንፈስ ደግሞ ወደ ታች ወደ ምድር ይወርድ እንደሆነ በእርግጠኝነት የሚያውቅ ማን ነው?+ 22 ሰው በሥራው ደስ ከመሰኘት የተሻለ ነገር እንደሌለው አስተዋልኩ፤+ ምክንያቱም ይህ ወሮታው* ነው፤ እሱ ካለፈ በኋላ የሚከናወነውን ነገር ተመልሶ እንዲያይ ሊያደርገው የሚችል ማን ነው?+
4 ከፀሐይ በታች የሚፈጸመውን ግፍ ሁሉ በድጋሚ ተመለከትኩ። ግፍ የተፈጸመባቸውን ሰዎች እንባ ተመለከትኩ፤ የሚያጽናናቸውም ሰው አልነበረም።+ ግፍ የሚፈጽሙባቸውም ሰዎች ኃይል ነበራቸው፤ የሚያጽናናቸውም አልነበረም። 2 እኔም ‘ዛሬ በሕይወት ካሉት ሕያዋን ይልቅ በቀድሞ ዘመን የሞቱ ሙታን ይሻላሉ’ አልኩ።+ 3 ደግሞም ከሁለቱ ይልቅ ገና ያልተወለደው፣+ ከፀሐይ በታች የሚፈጸሙትንም አስጨናቂ ድርጊቶች ያላየው ይሻላል።+
4 እኔም በሰዎች መካከል ያለው ፉክክር፣ ከፍተኛ ጥረት እንዲያደርጉና* የተዋጣለት ሥራ እንዲያከናውኑ እንደሚያነሳሳቸው ተመለከትኩ፤+ ይህም ከንቱና ነፋስን እንደማሳደድ ነው።
5 ሞኝ ሰው ሥጋው እየመነመነ ሲሄድ፣* እጁን አጣጥፎ ይቀመጣል።+
6 ብዙ በመልፋትና ነፋስን በማሳደድ ከሚገኝ ሁለት እፍኝ ይልቅ ጥቂት እረፍት በማድረግ የሚገኝ አንድ እፍኝ ይሻላል።+
7 እኔም ከፀሐይ በታች ያለውን ሌላ ከንቱ ነገር እንደገና ተመለከትኩ፦ 8 ብቸኛ የሆነና ጓደኛ የሌለው ሰው አለ፤ ልጅም ሆነ ወንድም የለውም፤ ይሁንና የሚሠራው ሥራ ማብቂያ የለውም። ዓይኖቹ ሀብትን አይጠግቡም።+ ሆኖም ‘እንዲህ በትጋት የምሠራውና ራሴን* መልካም ነገር የምነፍገው ለማን ብዬ ነው?’ ብሎ ራሱን ይጠይቃል?+ ይህም ቢሆን ከንቱና አሰልቺ ሥራ ነው።+
9 አንድ ከመሆን ሁለት መሆን ይሻላል፤+ ምክንያቱም ሁለት ሆነው የሚያከናውኑት ሥራ ጥሩ ውጤት* ያስገኝላቸዋል። 10 አንዱ ቢወድቅ ሁለተኛው ባልንጀራውን ደግፎ ሊያነሳው ይችላልና። ይሁንና ደግፎ የሚያነሳው ሰው በሌለበት አንዱ ቢወድቅ እንዴት ይሆናል?
11 በተጨማሪም ሁለት ሰዎች አብረው ቢተኙ ይሞቃቸዋል፤ ሆኖም አንድ ሰው ብቻውን ሆኖ እንዴት ሊሞቀው ይችላል? 12 ደግሞም አንድ ሰው ብቻውን ያለን ሰው ሊያሸንፈው ይችል ይሆናል፤ ሁለት ከሆኑ ግን ሊቋቋሙት ይችላሉ። በሦስት የተገመደ ገመድም ቶሎ አይበጠስም።*
13 የተሰጠውን ማስጠንቀቂያ ተግባራዊ እንዳያደርግ ማስተዋል ከጎደለው በዕድሜ የገፋ ሞኝ ንጉሥ+ ይልቅ ድሃ የሆነ ጥበበኛ ልጅ ይሻላል።+ 14 በእሱ ግዛት ውስጥ ድሃ ሆኖ የተወለደ ቢሆንም* ከእስር ቤት ወጥቶ ንጉሥ ይሆናል።+ 15 እኔም ከፀሐይ በታች የሚመላለሱት ሕያዋን ሁሉ እንዲሁም በንጉሡ ቦታ የሚተካው ልጅ ምን እንደሚገጥማቸው አጤንኩ። 16 ስፍር ቁጥር የሌላቸው ደጋፊዎች ቢኖሩትም በኋላ የሚመጡት ሰዎች በእሱ አይደሰቱም።+ ይህም ቢሆን ከንቱና ነፋስን እንደማሳደድ ነው።
5 ወደ እውነተኛው አምላክ ቤት በምትሄድበት ጊዜ ሁሉ አካሄድህን ጠብቅ፤+ ሞኞች እንደሚያደርጉት መሥዋዕት ለማቅረብ ከመሄድ+ ይልቅ ለመስማት መሄድ ይሻላል፤+ እነሱ እየሠሩ ያሉት ነገር መጥፎ መሆኑን አያውቁምና።
2 በአፍህ ለመናገር አትጣደፍ፤ ልብህም በእውነተኛው አምላክ ፊት ለመናገር አይቸኩል፤+ እውነተኛው አምላክ በሰማያት፣ አንተ ግን በምድር ላይ ነህና። ስለዚህ የምትናገራቸው ቃላት ጥቂት ሊሆኑ ይገባል።+ 3 ሐሳብ ሲበዛ* ለቅዠት ይዳርጋል፤+ የቃላት ብዛትም ሞኝን ሰው ለፍላፊ ያደርገዋል።+ 4 ለአምላክ ስእለት በምትሳልበት ጊዜ ሁሉ ስእለትህን ለመፈጸም አትዘግይ፤+ እሱ በሞኞች አይደሰትምና።+ ስእለትህን ፈጽም።+ 5 ስእለት ተስለህ ሳትፈጽም ከምትቀር ባትሳል ይሻላል።+ 6 አፍህ ወደ ኃጢአት እንዲመራህ* አትፍቀድ፤+ በመልአክም* ፊት “ተሳስቼ ነው” አትበል።+ እውነተኛው አምላክ በተናገርከው ነገር ተቆጥቶ የእጅህን ሥራ ለምን ያጥፋ?+ 7 ሐሳብ ሲበዛ ቅዠት እንደሚያስከትል፣+ የቃላት ብዛት ደግሞ ከንቱነትን ያስከትላልና። አንተ ግን እውነተኛውን አምላክ ፍራ።+
8 በምትኖርበት ግዛት ውስጥ በድሃ ላይ ግፍ ሲፈጸም፣ ፍትሕ ሲጓደልና ጽድቅ ወደ ጎን ገሸሽ ሲደረግ ብታይ በዚህ ጉዳይ አትገረም።+ ይህን ባለሥልጣን፣ ከእሱ ከፍ ያለ ቦታ ያለው ይመለከተዋልና፤ ከእነሱም በላይ የሆኑ ሌሎች አሉ።
9 ከምድሩ የሚገኘውን ትርፍ ሁሉም ይከፋፈሉታል፤ ንጉሡ እንኳ የሚያስፈልገውን ነገር የሚያገኘው ከእርሻው ነው።+
10 ብርን የሚወድ ብርን አይጠግብም፤ ሀብትንም የሚወድ በሚያገኘው ገቢ አይረካም።+ ይህም ቢሆን ከንቱ ነው።+
11 መልካም ነገሮች ሲበዙ፣ በላተኛውም ይበዛል።+ ታዲያ በዓይኑ ብቻ ከማየት በቀር ይህ ለባለቤቱ ምን ይጠቅመዋል?+
12 የሚበላው ጥቂትም ሆነ ብዙ፣ የሠራተኛ እንቅልፍ ጣፋጭ ነው፤ ባለጸጋ ሰው ያለው ብዙ ሀብት ግን እንቅልፍ ይነሳዋል።
13 ከፀሐይ በታች ያየሁት እጅግ አሳዛኝ የሆነ ነገር* አለ፦ ይህም ባለቤቱ በገዛ ራሱ ላይ ጉዳት ለማምጣት ያከማቸው ሀብት ነው። 14 ይህ ሰው አደገኛ ነገር* ውስጥ በመግባቱ ሀብቱን አጥቷል፤ ልጅ በሚወልድበት ጊዜም ለልጁ የሚያወርሰው ምንም ነገር አይኖረውም።+
15 ሰው ከእናቱ ማህፀን ራቁቱን እንደወጣ ሁሉ፣ ልክ እንደዚያው ተመልሶ ይሄዳል።+ ደግሞም ከደከመበት ነገር ሁሉ ሊወስደው የሚችል አንዳች ነገር የለም።+
16 ይህም ደግሞ እጅግ የሚያሳዝን ነገር* ነው፦ ሰው በዚያው በመጣበት መንገድ ተመልሶ ይሄዳል፤ ለነፋስ የሚደክም ሰው የሚያገኘው ትርፍ ምንድን ነው?+ 17 ደግሞም በየቀኑ ጨለማ ውስጥ በከፍተኛ ብስጭት፣ በሕመምና በንዴት ይበላል።+
18 እኔ ያየሁት መልካምና ተገቢ የሆነ ነገር፣ ሰው እውነተኛው አምላክ በሰጠው አጭር የሕይወት ዘመን ሁሉ መብላቱና መጠጣቱ እንዲሁም ከፀሐይ በታች በደከመበትና በትጋት ባከናወነው ሥራ ሁሉ ደስታ ማግኘቱ ነው፤+ ይህ ብድራቱ* ነውና።+ 19 ደግሞም እውነተኛው አምላክ ለሰው ሀብትና ቁሳዊ ንብረት+ ብሎም በእነዚህ ነገሮች የመደሰት ችሎታ ሲሰጠው ብድራቱን* ተቀብሎ በትጋት በሚያከናውነው ሥራ መደሰት ይገባዋል። ይህ የአምላክ ስጦታ ነው።+ 20 እውነተኛው አምላክ ልቡን ደስ በሚያሰኙ ነገሮች እንዲጠመድ ስለሚያደርገው የሚያልፈውን የሕይወት ዘመኑን ፈጽሞ ልብ አይለውም።*+
6 ከፀሐይ በታች ያየሁት ሌላ አሳዛኝ ነገር* አለ፤ ይህም በሰው ልጆች ላይ በተደጋጋሚ ሲከሰት ይታያል፦ 2 እውነተኛው አምላክ፣ ሰው የሚፈልገውን ነገር* ሁሉ እንዳያጣ ሀብትን፣ ቁሳዊ ንብረትንና ክብርን ይሰጠዋል፤ ሆኖም እውነተኛው አምላክ በእነዚህ ነገሮች እንዲደሰት አያስችለውም፤ ከዚህ ይልቅ እንግዳ ሰው ይደሰትባቸዋል። ይህም ከንቱና እጅግ አስከፊ ነገር ነው። 3 አንድ ሰው መቶ ልጆች ቢወልድ፣ ብዙ ዓመት ቢኖርና ለእርጅና ቢበቃ፣ ወደ መቃብር ከመውረዱ በፊት ባሉት መልካም ነገሮች መደሰት ካልቻለ* ከእሱ ይልቅ ጭንጋፍ ይሻላል እላለሁ።+ 4 ከማህፀን የወጣው በከንቱ ነውና፤ በጨለማም ሄዷል፤ ስሙም በጨለማ ተሸፍኗል። 5 ፀሐይን ባያይና ምንም ነገር ባያውቅም እንኳ ከዚያኛው ይልቅ ይሄኛው ይሻላል።*+ 6 ሰው ደስታ ካላገኘ ሁለት ጊዜ ሺህ ዓመት ቢኖር ምን ይጠቅመዋል? ሁሉም የሚሄደው ወደ አንድ ቦታ አይደለም?+
7 የሰው ልጅ በትጋት የሚሠራው ሆዱን ለመሙላት ነው፤+ የምግብ ፍላጎቱ* ግን ፈጽሞ አይረካም። 8 ታዲያ ጥበበኛው ከሞኙ ሰው የሚሻለው በምንድን ነው?+ ድሃስ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንዴት መኖር እንደሚችል* ማወቁ የሚያስገኝለት ጥቅም ምንድን ነው? 9 በምኞት ከመቅበዝበዝ* ይልቅ ዓይን በሚያየው መደሰት ይሻላል። ይህም ቢሆን ከንቱና ነፋስን እንደማሳደድ ነው።
10 አሁን ያለው ነገር ሁሉ አስቀድሞ ስያሜ የተሰጠው ነው፤ ደግሞም የሰው ምንነት የታወቀ ነው፤ ከእሱ ከሚበረታም ጋር ሊከራከር* አይችልም። 11 ቃል ሲበዛ* ከንቱነት ይበዛል፤ ታዲያ ይህ ለሰው ምን ጥቅም ያስገኛል? 12 ሰው በሕይወት ሳለ ይኸውም ከንቱ በሆነውና እንደ ጥላ በሚያልፈው አጭር የሕይወት ዘመኑ ሊያደርገው የሚችለው የተሻለ ነገር ምን እንደሆነ የሚያውቅ ማን ነው?+ እሱ ካለፈስ በኋላ ከፀሐይ በታች የሚሆነውን ነገር ማን ሊነግረው ይችላል?
7 ጥሩ ስም* ከጥሩ ዘይት፣+ የሞትም ቀን ከልደት ቀን ይሻላል። 2 ወደ ግብዣ ቤት ከመሄድ ይልቅ ወደ ሐዘን ቤት መሄድ ይሻላል፤+ የሰው ሁሉ ፍጻሜ ሞት ነውና፤ በሕይወት ያለ ሰውም ይህን ልብ ማለት ይገባዋል። 3 ከሳቅ ትካዜ ይሻላል፤+ የፊት ሐዘን ለልብ መልካም ነውና።+ 4 የጥበበኞች ልብ በሐዘን ቤት ነው፤ የሞኞች ልብ ግን በደስታ* ቤት ነው።+
5 የሞኞችን መዝሙር ከመስማት ይልቅ የጥበበኛን ወቀሳ መስማት ይሻላል።+ 6 የሞኝ ሳቅ ከድስት ሥር እንደሚንጣጣ የእሾህ ማገዶ ነው፤+ ይህም ቢሆን ከንቱ ነው። 7 ግፍ ጥበበኛውን ሊያሳብደው ይችላል፤ ጉቦም ልብን ያበላሻል።+
8 የአንድ ነገር ፍጻሜ ከጅማሬው ይሻላል። ትዕቢተኛ ከመሆን ይልቅ ታጋሽ መሆን ይሻላል።+ 9 የሞኞች ቁጣ በጉያቸው ውስጥ ስለሆነ*+ ለቁጣ አትቸኩል።*+
10 “የቀድሞው ዘመን ከአሁኑ ዘመን ለምን ተሻለ?” አትበል፤ እንዲህ ብሎ መጠየቅ ጥበብ አይደለምና።+
11 ጥበብ ከውርስ ጋር መልካም ነገር ናት፤ የቀን ብርሃን ለሚያዩ ሰዎችም* ጠቃሚ ነች። 12 ገንዘብ ጥበቃ እንደሚያስገኝ+ ሁሉ ጥበብም ጥበቃ ታስገኛለችና፤+ የእውቀት ብልጫ ግን፣ ጥበብ የባለቤቷን ሕይወት ጠብቃ ማቆየት መቻሏ ነው።+
13 እውነተኛው አምላክ ያከናወነውን ሥራ ልብ በል፤ እሱ ያጣመመውን ማን ሊያቃና ይችላል?+ 14 በጥሩ ቀን አንተም ይህን ጥሩነት መልሰህ አንጸባርቅ፤+ በአስቸጋሪ* ቀን ግን ይሄኛውንም ሆነ ያኛውን ያደረገው አምላክ እንደሆነ አስተውል፤+ ይህም የሆነው ሰዎች ወደፊት የሚደርስባቸውን ማንኛውንም ነገር በተመለከተ እርግጠኞች መሆን* እንዳይችሉ ነው።+
15 ከንቱ በሆነው የሕይወት ዘመኔ+ ሁሉንም ነገር አይቻለሁ፤ ጻድቁ ሰው በጽድቁ ሲጠፋ፣+ ክፉው ሰው ደግሞ ክፉ ቢሆንም ረጅም ዘመን ሲኖር ተመልክቻለሁ።+
16 ከልክ በላይ ጻድቅ አትሁን፤+ እጅግም ጥበበኛ መስለህ ለመታየት አትሞክር።+ በራስህ ላይ ለምን ጥፋት ታመጣለህ?+ 17 እጅግ ክፉ አትሁን፤ ሞኝም አትሁን።+ ያለጊዜህ ለምን በሞት ትቀጫለህ?+ 18 አንደኛውን ማስጠንቀቂያ ሳትተው ሌላኛውንም አጥብቀህ መያዝህ የተሻለ ነው፤+ አምላክን የሚፈራ ሰው ሁለቱንም ይሰማልና።
19 ጥበብ ጥበበኛውን ሰው፣ በአንድ ከተማ ካሉ አሥር ብርቱ ሰዎች ይበልጥ ኃያል ታደርገዋለች።+ 20 ሁልጊዜ ጥሩ ነገር የሚያደርግና ፈጽሞ ኃጢአት የማይሠራ ጻድቅ ሰው በምድር ላይ የለምና።+
21 በተጨማሪም ሰዎች የሚናገሩትን ነገር ሁሉ ትኩረት ሰጥተህ አትከታተል፤+ አለዚያ አገልጋይህ ስለ አንተ መጥፎ ነገር ሲናገር* ልትሰማ ትችላለህ፤ 22 አንተ ራስህ ስለ ሌሎች ብዙ ጊዜ መጥፎ ነገር እንደተናገርክ ልብህ በሚገባ ያውቃልና።+
23 ይህን ሁሉ በጥበብ ፈተንኩ፤ እኔም “ጥበበኛ እሆናለሁ” አልኩ። ይህ ግን ከአቅሜ በላይ ነበር። 24 የተከናወነው ነገር ሁሉ ሊደረስበት የማይቻል ከመሆኑም ሌላ እጅግ ጥልቅ ነው። ማንስ ሊረዳው ይችላል?+ 25 እኔም ጥበብንና የነገሮችን መንስኤ ለመረዳት፣ ለመመርመርና ለማጥናት እንዲሁም የሞኝነትን ክፋትና የእብደትን ቂልነት ለመገንዘብ ልቤን አዘነበልኩ።+ 26 ከዚያም የሚከተለውን ነገር ተገነዘብኩ፦ እንደ አዳኝ ወጥመድ የሆነች ደግሞም እንደ መረብ ያለ ልብ፣ እንደ እስር ቤት ሰንሰለትም ያሉ እጆች ያሏት ሴት ከሞት እጅግ የመረረች ናት። እውነተኛውን አምላክ የሚያስደስት ሰው ከእሷ ያመልጣል፤+ ኃጢአተኛ ግን በእሷ ይያዛል።+
27 ሰብሳቢው+ እንዲህ ይላል፦ “እነሆ፣ መርምሬ ያገኘሁት ነገር ይህ ነው። አንድ መደምደሚያ ላይ ለመድረስ እያንዳንዱን ነገር በሚገባ አጠናሁ፤ 28 ሆኖም ስፈልገው* የነበረውን ነገር ላገኘው አልቻልኩም። ከሺህ መካከል አንድ ወንድ* አገኘሁ፤ ከእነዚህ ሁሉ መካከል ግን አንዲትም ሴት አላገኘሁም። 29 ይህን አንድ ነገር ብቻ አገኘሁ፦ እውነተኛው አምላክ የሰውን ልጆች ቅን አድርጎ ሠራቸው፤+ እነሱ ግን ሌላ ብዙ ዕቅድ አወጡ።”+
8 እንደ ጥበበኛው ሰው ያለ ማን ነው? የአንድን ችግር መፍትሔ* የሚያውቅ ማን ነው? የሰው ጥበብ ፊቱ እንዲበራ እንዲሁም ኮስታራ ፊቱ እንዲፈታ ታደርጋለች።
2 እኔም እንዲህ እላለሁ፦ “በአምላክ ፊት በገባኸው መሐላ+ የተነሳ የንጉሥን ትእዛዝ አክብር።+ 3 ከንጉሡ ፊት ለመውጣት አትቸኩል።+ መጥፎ የሆነውን ነገር ሁሉ አትደግፍ፤+ እሱ ደስ ያሰኘውን ሁሉ ማድረግ ይችላልና፤ 4 ምክንያቱም የንጉሥ ቃል የማይሻር ነው፤+ ‘ምን ማድረግህ ነው?’ ሊለው የሚችል ማን ነው?”
5 ትእዛዛትን የሚጠብቅ ሰው ጉዳት አይደርስበትም፤+ ጥበበኛ ልብም ትክክለኛውን ጊዜና አሠራር* ያውቃል።+ 6 የሰው ልጆች ብዙ መከራ ቢኖርባቸውም ማንኛውም ጉዳይ ትክክለኛ ጊዜና አሠራር* አለው።+ 7 ወደፊት የሚሆነውን ነገር የሚያውቅ ሰው ስለሌለ ይህ እንዴት እንደሚሆን ሊነግረው የሚችል ማን ነው?
8 በመንፈስ* ላይ ሥልጣን ያለው ወይም መንፈስን መግታት የሚችል ሰው እንደሌለ ሁሉ በሞት ቀን ላይም ሥልጣን ያለው የለም።+ በጦርነት ጊዜ ከግዳጅ የሚሰናበት እንደሌለ ሁሉ ክፋትም ክፋት የመሥራት ልማድ ያላቸውን ሰዎች እንዲያመልጡ ዕድል አይሰጣቸውም።*
9 ይህን ሁሉ የተገነዘብኩት ከፀሐይ በታች የተሠራውን ሥራ ሁሉ በልቤ ከመረመርኩ በኋላ ነው። በዚህ ሁሉ ወቅት ሰው ሰውን የገዛው ለጉዳቱ* ነው።+ 10 ደግሞም ወደ ቅዱሱ ስፍራ ይገቡና ይወጡ የነበሩት ክፉዎች ሲቀበሩ አይቻለሁ፤ ይሁንና ይህን ባደረጉበት ከተማ ወዲያው ተረሱ።+ ይህም ቢሆን ከንቱ ነው።
11 በክፉ ሥራ ላይ በአፋጣኝ ፍርድ ስለማይሰጥ+ የሰው ልጆች ልብ ክፉ ነገር ለማድረግ ተደፋፈረ።+ 12 ኃጢአተኛ መቶ ጊዜ መጥፎ ነገር እየሠራ ረጅም ዘመን ቢኖር እንኳ እውነተኛውን አምላክ የሚፈሩ ሰዎች አምላክን በመፍራታቸው የኋላ ኋላ መልካም እንደሚሆንላቸው ተረድቻለሁ።+ 13 ክፉ ሰው ግን አምላክን ስለማይፈራ የኋላ ኋላ መልካም አይሆንለትም፤+ እንደ ጥላ የሆነውን የሕይወት ዘመኑንም ማራዘም አይችልም።+
14 በምድር ላይ የሚፈጸም አንድ ከንቱ* ነገር አለ፦ ክፉ እንደሠሩ ተደርገው የሚታዩ ጻድቃን አሉ፤+ ጽድቅ እንደሠሩ ተደርገው የሚታዩ ክፉ ሰዎችም አሉ።+ ይህም ቢሆን ከንቱ ነው እላለሁ።
15 በመሆኑም ደስታ መልካም ነው አልኩ፤+ ምክንያቱም ለሰው ከፀሐይ በታች ከመብላትና ከመጠጣት እንዲሁም ከመደሰት የተሻለ ነገር የለም፤ ከፀሐይ በታች እውነተኛው አምላክ በሚሰጠው የሕይወት ዘመን በትጋት ሲሠራ ይህ ደስታ ሊርቀው አይገባም።+
16 ቀንም ሆነ ሌሊት እንቅልፍ በዓይኔ ሳይዞር* ጥበብን ለማግኘትና በምድር ላይ ያለውን እንቅስቃሴ* ለማየት ከፍተኛ ጥረት አደረግኩ።+ 17 ከዚያም የእውነተኛውን አምላክ ሥራ ሁሉ አጤንኩ፤ የሰው ልጆች ከፀሐይ በታች የሚሆነውን ነገር ሁሉ መረዳት እንደማይችሉም ተገነዘብኩ።+ ሰዎች የቱንም ያህል ጥረት ቢያደርጉ ሊረዱት አይችሉም። ይህን ለማወቅ የሚያስችል ጥበብ አለን ቢሉም እንኳ ሊረዱት አይችሉም።+
9 ስለዚህ ይህን ሁሉ በጥሞና ተመልክቼ ጻድቃንም ሆኑ ጥበበኞች እንዲሁም የሚያከናውኗቸው ሥራዎች በእውነተኛው አምላክ እጅ ናቸው ብዬ ደመደምኩ።+ ሰዎች ከእነሱ በፊት በነበረው ዘመን የታየውን ፍቅርና ጥላቻ አያውቁም። 2 ጻድቁና ክፉው ሰው፣+ ጥሩው ሰውም ሆነ ንጹሕ የሆነውና ንጹሕ ያልሆነው ሰው፣ መሥዋዕት የሚያቀርቡትም ሆኑ የማያቀርቡት ፍጻሜያቸው* ተመሳሳይ ነው።+ ጥሩው ሰው ከኃጢአተኛው ጋር አንድ ነው፤ የሚምለውም ሰው፣ ላለመማል ከሚጠነቀቀው ሰው ጋር አንድ ነው። 3 ከፀሐይ በታች የሚፈጸመው አስጨናቂ ነገር ይህ ነው፦ የሁሉም ፍጻሜ* አንድ ስለሆነ+ የሰዎችም ልብ በክፋት የተሞላ ነው፤ በሕይወታቸው ዘመን በልባቸው ውስጥ እብደት አለ፤ ከዚያም ይሞታሉ!*
4 በሕያዋን መካከል ያለ ማንኛውም ሰው ተስፋ አለው፤ ምክንያቱም በሕይወት ያለ ውሻ ከሞተ አንበሳ ይሻላል።+ 5 ሕያዋን እንደሚሞቱ ያውቃሉና፤+ ሙታን ግን ምንም አያውቁም፤+ ከእንግዲህም የሚያገኙት ብድራት* የለም፤ ምክንያቱም የሚታወሱበት ነገር ሁሉ ተረስቷል።+ 6 በተጨማሪም ፍቅራቸው፣ ጥላቻቸውና ቅናታቸው ጠፍቷል፤ ከዚህም በኋላ ከፀሐይ በታች በሚሆነው ነገር ሁሉ ፈጽሞ ድርሻ አይኖራቸውም።+
7 ሂድ፣ ምግብህን በደስታ ብላ፤ ልብህም ደስ ብሎት የወይን ጠጅህን ጠጣ፤+ እውነተኛው አምላክ በሥራህ ደስ ተሰኝቷልና።+ 8 ልብስህ ምንጊዜም ነጭ* ይሁን፤ ራስህንም ዘይት መቀባት አትዘንጋ።+ 9 አምላክ ከፀሐይ በታች በሰጠህ ከንቱ በሆነው የሕይወት ዘመንህ ሁሉ፣ ከንቱ በሆነውም ዕድሜህ ሁሉ ከምትወዳት ሚስትህ ጋር ተደስተህ ኑር፤+ በሕይወትህ እንዲሁም ከፀሐይ በታች በምትደክምበትና በትጋት በምታከናውነው ሥራ ዕጣ ፋንታህ* ይህ ነውና።+ 10 እጅህ የሚያገኘውን ሥራ ሁሉ በሙሉ ኃይልህ አከናውን፤ አንተ በምትሄድበት በመቃብር* ሥራም ሆነ ዕቅድ፣ እውቀትም ሆነ ጥበብ የለምና።+
11 እኔም ከፀሐይ በታች ሌላ ነገር ተመለከትኩ፤ ፈጣኖች በውድድር ሁልጊዜ አያሸንፉም፤ ኃያላን በውጊያ ሁልጊዜ ድል አይቀናቸውም፤+ ጥበበኞች ሁልጊዜ ምግብ አያገኙም፤ አስተዋዮች ሁልጊዜ ሀብት አያገኙም፤+ እውቀት ያላቸው ሰዎችም ሁልጊዜ ስኬታማ አይሆኑም፤+ ምክንያቱም ሁሉም መጥፎ ጊዜና ያልተጠበቁ ክስተቶች* ያጋጥሟቸዋል። 12 ሰው የራሱን ጊዜ አያውቅምና።+ ዓሣዎች በአደገኛ መረብ እንደሚጠመዱና ወፎች በወጥመድ እንደሚያዙ፣ የሰው ልጆችም ድንገት በሚያጋጥማቸው ክፉ ጊዜ* ይጠመዳሉ።
13 ደግሞም ከፀሐይ በታች ስላለች ጥበብ ይህን አስተዋልኩ፤ በእሷም እጅግ ተገረምኩ፦ 14 ጥቂት ሰዎች የሚኖሩባት አንዲት ትንሽ ከተማ ነበረች፤ አንድ ኃያል ንጉሥም መጥቶ ከበባት፤ በዙሪያዋም ትልቅ ቅጥር ገነባ። 15 በከተማዋ ውስጥ ጥበበኛ የሆነ አንድ ድሃ ሰው ነበር፤ እሱም በጥበቡ ከተማዋን አዳናት። ሆኖም ይህን ድሃ ማንም ሰው አላስታወሰውም።+ 16 እኔም ለራሴ እንዲህ አልኩ፦ ‘ጥበብ ከኃይል ትበልጣለች፤+ ይሁንና የድሃው ጥበብ ተናቀ፤ የተናገረውም ነገር ሰሚ አላገኘም።’+
17 ሞኞችን የሚገዛ ሰው ከሚያሰማው ጩኸት ይልቅ ጥበበኞች በዝግታ የሚናገሩትን ቃል መስማት ይሻላል።
18 ከጦር መሣሪያ ይልቅ ጥበብ ትሻላለች፤ አንድ ኃጢአተኛ ግን ብዙ መልካም ነገርን ሊያጠፋ ይችላል።+
10 የሞቱ ዝንቦች በጥሩ ቀማሚ የተዘጋጀውን ሽቶ እንዲበላሽና እንዲገማ እንደሚያደርጉት ሁሉ ትንሽ ሞኝነትም ጥበብንና ክብርን ዋጋ ያሳጣል።+
2 የጥበበኛ ሰው ልብ በትክክለኛ መንገድ ይመራዋል፤* የሞኝ ልብ ግን በተሳሳተ መንገድ ይመራዋል።*+ 3 ሞኝ ሰው በየትኛውም መንገድ ቢመላለስ ማስተዋል* ይጎድለዋል፤+ ሞኝ መሆኑንም ሰው ሁሉ እንዲያውቅ ያደርጋል።+
4 የገዢ ቁጣ* በአንተ ላይ ቢነድ ስፍራህን አትልቀቅ፤+ የረጋ መንፈስ ታላቅ ኃጢአትን ጸጥ ያደርጋልና።+
5 ከፀሐይ በታች ያየሁት አንድ የሚያስጨንቅ ነገር አለ፤ ይህም በሥልጣን ላይ ያሉ ሰዎች እንደሚሠሩት ያለ ስህተት ነው፦+ 6 ሞኞች በከፍተኛ የሥልጣን ቦታዎች ላይ ሲቀመጡ የናጠጡ ሀብታሞች* ግን በዝቅተኛ ቦታዎች ላይ ይገኛሉ።
7 አገልጋዮች በፈረስ ተቀምጠው ሲጓዙ፣ መኳንንት ግን እንደ አገልጋዮች በእግራቸው ሲሄዱ አይቻለሁ።+
8 ጉድጓድ የሚቆፍር ራሱ ሊገባበት ይችላል፤+ ግንብን የሚያፈርስም በእባብ ሊነደፍ ይችላል።
9 ድንጋይ የሚፈነቅል ሰው በፈነቀለው ድንጋይ ሊጎዳ ይችላል፤ ግንድንም የሚፈልጥ አደጋ ሊያደርስበት ይችላል።*
10 ከብረት የተሠራ መሣሪያ ቢደንዝ፣ ሰውም ባይስለው ብዙ ጉልበት መጠቀም ያስፈልገዋል። ጥበብ ግን ስኬታማ ለመሆን ይረዳል።
11 እባብ በድግምት ከመፍዘዙ በፊት ቢነድፍ፣ በድግምት የተካነው ሰው* ምንም ጥቅም አያገኝም።
12 ጥበበኛ ሰው ከአፉ የሚወጡት ቃላት ሞገስ ያስገኙለታል፤+ የሞኝ ሰው ከንፈር ግን ለጥፋት ይዳርገዋል።+ 13 ከአፉ የሚወጡት የመጀመሪያ ቃላት ሞኝነት ይንጸባረቅባቸዋል፤+ የንግግሩ ማሳረጊያም የከፋ እብደት ነው። 14 ይሁንና ሞኙ ማውራቱን ይቀጥላል።+
ሰው ወደፊት የሚሆነውን ነገር አያውቅም፤ ከእሱ በኋላ የሚመጣውን ነገር ማን ሊነግረው ይችላል?+
15 ሞኝ ሰው የሚሠራው አድካሚ ሥራ እንዲዝል ያደርገዋል፤ ወደ ከተማ የሚወስደውን መንገድ ማግኘት እንኳ አይችልምና።
16 አንዲት አገር ንጉሧ ልጅ ቢሆን፣+ መኳንንቷ ደግሞ በጠዋት ግብዣ ላይ የሚገኙ ቢሆኑ ምንኛ አሳዛኝ ነው! 17 ከትልቅ ቤተሰብ የተወለደ ንጉሥ ያላት እንዲሁም ለስካር ሳይሆን ብርታት ለማግኘት በተገቢው ጊዜ የሚመገቡ መኳንንት ያሏት አገር ምንኛ ደስተኛ ናት!+
18 ስንፍና ሲበዛ ጣሪያ ይዘብጣል፤ እጆችም ካልሠሩ ቤት ያፈሳል።+
19 ምግብ* ለሳቅ ይዘጋጃል፤ የወይን ጠጅም ሕይወትን አስደሳች ያደርጋል፤+ ይሁን እንጂ ገንዘብ አስፈላጊውን ነገር ሁሉ ያሟላል።+
20 በሐሳብህ* እንኳ ንጉሡን አትርገም፤*+ በመኝታ ቤትህም ሆነህ ባለጸጋውን አትርገም፤ ቃሉን* ወፍ* ልትወስደው አሊያም ክንፍ ያላት ፍጥረት የተወራውን ደግማ ልትናገር ትችላለችና።
11 ቂጣህን በውኃ ላይ ጣል፤*+ ከብዙ ቀናት በኋላ መልሰህ ታገኘዋለህና።+ 2 ካለህ ነገር ላይ ለሰባት፣ እንዲያውም ለስምንት አካፍለህ ስጥ፤+ በምድር ላይ የሚመጣውን አደጋ* አታውቅምና።
3 ደመናት ውኃ ካዘሉ በምድር ላይ ዶፍ ያወርዳሉ፤ እንዲሁም ዛፍ በስተ ደቡብ ወይም በስተ ሰሜን ከወደቀ በዚያው በወደቀበት ይቀራል።
4 ነፋስን የሚጠባበቅ አይዘራም፤ ደመናትንም የሚመለከት አያጭድም።+
5 መንፈስ፣ በእርጉዝ ሴት ውስጥ በሚገኝ ሕፃን አጥንቶች* ላይ እንዴት እንደሚሠራ እንደማታውቅ ሁሉ፣+ ሁሉንም ነገር የሚያከናውነውን የእውነተኛውን አምላክ ሥራም አታውቅም።+
6 በማለዳ ዘርህን ዝራ፤ እስከ ምሽትም ድረስ እጅህ ሥራ አይፍታ፤+ ይህ ወይም ያ የትኛው እንደሚያድግ ወይም ደግሞ ሁለቱም ይጸድቁ እንደሆነ አታውቅምና።
7 ብርሃን ደስ ያሰኛል፤ ፀሐይንም ማየት ለዓይን መልካም ነው። 8 ሰው የቱንም ያህል ብዙ ዓመት ቢኖር በእያንዳንዱ ቀን ደስ ይበለው።+ ሆኖም በጨለማ የተዋጡት ቀናት ብዙ ሊሆኑ እንደሚችሉ መዘንጋት አይኖርበትም፤ የሚመጣው ሁሉ ከንቱ ነው።+
9 አንተ ወጣት፣ በወጣትነትህ ጊዜ ደስ ይበልህ፤ በወጣትነትህም ዘመን ልብህ ደስ ይበለው። የልብህን መንገድ ተከተል፤ ዓይንህ በሚመራህም መንገድ ሂድ፤ ሆኖም ስለ እነዚህ ነገሮች ሁሉ እውነተኛው አምላክ ወደ ፍርድ እንደሚያመጣህ* እወቅ።+ 10 ስለዚህ የሚያስጨንቁ ነገሮችን ከልብህ አስወግድ፤ ጎጂ ነገሮችንም ከሰውነትህ አርቅ፤* ወጣትነትና የለጋነት ዕድሜ ከንቱ ናቸውና።+
12 እንግዲያው አስጨናቂ የሆኑት ዘመናት*+ ከመምጣታቸው እንዲሁም “ደስ አያሰኙኝም” የምትላቸው ዓመታት ከመድረሳቸው በፊት በወጣትነትህ ጊዜ ታላቁን ፈጣሪህን አስብ፤+ 2 ፀሐይ፣ ብርሃን፣ ጨረቃና ከዋክብት ከመጨለማቸው በፊት+ እንዲሁም ዶፍ ከጣለ በኋላ ደመናት ተመልሰው* ከመምጣታቸው በፊት ፈጣሪህን አስብ፤ 3 በዚያን ጊዜ ቤት ጠባቂዎች* ይንቀጠቀጣሉ፤* ጠንካራ የነበሩ ሰዎች ይጎብጣሉ፤ የሚፈጩ ሴቶች ጥቂት በመሆናቸው ሥራቸውን ያቆማሉ፤ በመስኮት የሚያዩ ወይዛዝርትም ይጨልምባቸዋል፤+ 4 ወደ መንገድ የሚያወጡ በሮች ይዘጋሉ፤ የወፍጮ ድምፅ ይቀንሳል፤ ሰውም የወፍ ድምፅ ይቀሰቅሰዋል፤ ሴቶች ልጆችም ሁሉ ዝግ ባለ ድምፅ ይዘምራሉ።+ 5 በተጨማሪም ሰው ከፍታ ያስፈራዋል፤ በመንገድ ሲሄድም ይሸበራል። የአልሞንድ ዛፍ ያብባል፤+ ፌንጣም እየተጎተተ ይሄዳል፤ የምግብ ፍላጎት* ይጠፋል፤ ምክንያቱም ሰው ለረጅም ጊዜ ወደሚኖርበት ቤት ይሄዳል፤+ አልቃሾችም በጎዳና ይዞራሉ፤+ 6 የብር ገመድ ሳይበጠስ፣ የወርቅ ሳህን ሳይሰበር፣ እንስራ በምንጭ አጠገብ ሳይከሰከስ፣ ከጉድጓድ ውኃ ለማውጣት የሚያገለግለው መንኮራኩር* ሳይሰበር ፈጣሪህን አስብ። 7 አፈር ቀድሞ ወደነበረበት መሬት ይመለሳል፤+ መንፈስም* ወደ ሰጪው፣ ወደ እውነተኛው አምላክ ይመለሳል።+
8 ሰብሳቢው+ “የከንቱ ከንቱ* ነው! ሁሉም ነገር ከንቱ ነው!” ይላል።+
9 ሰብሳቢው ጥበበኛ ከመሆኑም በተጨማሪ ለሕዝቡ የሚያውቀውን ነገር ሁልጊዜ ያስተምር ነበር፤+ ብዙ ምሳሌዎችንም ማጠናቀር* ይችል ዘንድ አሰላሰለ እንዲሁም ሰፊ ምርምር አደረገ።+ 10 ሰብሳቢው ደስ የሚያሰኙ ቃላትን+ ለማግኘትና የእውነትን ቃል በትክክል ለመመዝገብ ጥረት አደረገ።
11 የጥበበኞች ቃላት እንደ በሬ መውጊያ ናቸው፤+ የሰበሰቧቸው አባባሎችም በሚገባ እንደተቸነከሩ ምስማሮች ናቸው፤ እነዚህ ቃላት ከአንድ እረኛ የተሰጡ ናቸው። 12 ልጄ ሆይ፣ ከዚህም ሌላ ይህን ማስጠንቀቂያ ልብ በል፦ ብዙ መጻሕፍት መጻፍ ማብቂያ የለውም፤ በእነሱ ዙሪያ ምርምር ማብዛትም ሰውነትን ያደክማል።+
13 ሁሉ ነገር ከተሰማ በኋላ መደምደሚያው ይህ ነው፦ እውነተኛውን አምላክ ፍራ፤+ ትእዛዛቱንም ጠብቅ፤+ ይህ የሰው አጠቃላይ ግዴታ ነውና።+ 14 እውነተኛው አምላክ እያንዳንዱን የተሰወረ ነገር ጨምሮ ማንኛውንም ሥራ፣ ጥሩም ይሁን መጥፎ ወደ ፍርድ ያመጣዋልና።+
የዚህ መጽሐፍ ስያሜ በዕብራይስጥ ቆኼሌት ሲሆን ቃሉ “ሰብሳቢ፣ ሰዎችን አንድ ላይ የሚሰበስብ” የሚል ትርጉም አለው።
ወይም “ዋጋ ቢስ።”
ቃል በቃል “ትቆማለች።”
ወይም “ብርሃን ትፈነጥቃለች።”
ወይም “እያለከለከች ትመለሳለች።”
ወይም “የክረምት ጅረቶች፤ ወቅት ጠብቀው የሚፈስሱ ጅረቶች።”
ወይም “ከልክ ያለፈ ቂልነትን።”
ወይም “ጫካውን።”
ቃል በቃል “የቤቱ ወንዶች ልጆችም።”
ወይም “በነገሥታት እጅና በአውራጃዎች ውስጥ ብቻ የሚገኝ ንብረት።”
ወይም “እመቤቶች።”
ቃል በቃል “ዓይኖቼንም የፈለጉትን ነገር ሁሉ አልከለከልኳቸውም።”
ወይም “ድርሻ።”
ወይም “ጥቅም።”
ወይም “ዓይኖች ክፍት ናቸው።”
ወይም “ዕጣ ፋንታ።”
ወይም “ያለውን ሁሉ።”
ወይም “ታላቅ ኪሳራ።”
ቃል በቃል “ከልቡ ጥረት።”
ወይም “ነፍሱ መልካም ነገር እንድታገኝ ከማድረግ።”
ወይም “ለመውለድ ጊዜ አለው።”
ቃል በቃል “ለመዝለል፤ ለመፈንጨት።”
ወይም “በሚገባ የተደራጀ፤ ሥርዓታማ፤ ተስማሚ።”
“ያለፈውን” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “ዕጣ ፋንታና።”
ወይም “ድርሻው።”
ወይም “ጠንክረው እንዲሠሩና።”
ቃል በቃል “የገዛ ሥጋውን ይበላል።”
ወይም “ነፍሴን።”
ወይም “የተሻለ ጥቅም።”
ወይም “በቀላሉ አይበጠስም።”
ጥበበኛውን ልጅ የሚያመለክት ሊሆን ይችላል።
ወይም “ጭንቀት ሲበዛ።”
ቃል በቃል “ሥጋህን ወደ ኃጢአት እንዲመራ።”
ወይም “በመልእክተኛም።”
ወይም “ክፉ ነገር።”
ወይም “ሥራ።”
ወይም “ክፉ ነገር።”
ወይም “ድርሻው።”
ወይም “ድርሻውን።”
ወይም “አያስታውሰውም።”
ወይም “ክፉ ነገር።”
ወይም “ነፍሱ የምትሻውን ነገር።”
ወይም “ነፍሱ መደሰት ካልቻለች።”
ቃል በቃል “የተሻለ እረፍት አለው።”
ወይም “ነፍሱ።”
ቃል በቃል “በሕያዋን ፊት እንዴት መሄድ እንደሚችል።”
ወይም “ከነፍስ መቅበዝበዝ።”
ወይም “ሊሟገት።”
“ነገር ሲበዛ” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “መልካም ዝና።” ቃል በቃል “ስም።”
ወይም “ፈንጠዝያ ባለበት።”
“ቁጣ የሞኝ ሰው መለያ ስለሆነ” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ቃል በቃል “በመንፈስህ ለቁጣ አትቸኩል።”
በሕይወት ያሉትን ያመለክታል።
ወይም “በክፉ።”
ወይም “ማወቅ።”
ቃል በቃል “ሲረግምህ።”
ወይም “ነፍሴ ስትፈልገው።”
ወይም “ቅን ወንድ።”
ወይም “የአንድን ነገር ፍቺ።”
ወይም “ፍርድ።”
ወይም “ፍርድ።”
ወይም “በእስትንፋስ፤ በነፋስ።”
“ክፉዎች ክፋታቸው ሊታደጋቸው አይችልም” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “ለሥቃይ፤ ለጉስቁልና።”
ወይም “የሚያበሳጭ።”
“ሰዎች ቀንም ሆነ ሌሊት እንቅልፍ በዓይናቸው እንደማይዞር” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “የሚከናወነውን ሥራ።”
ወይም “ዕጣ ፋንታቸው።”
ወይም “ዕጣ ፋንታ።”
ቃል በቃል “ከዚያም በኋላ፣ ወደ ሙታን!”
ወይም “ደሞዝ።”
ነጭ ልብስ መልበስ የደስተኝነትን መንፈስ ያንጸባርቃል፤ የሐዘን ልብስ አይደለም።
ወይም “ድርሻህ።”
ወይም “በሲኦል።” የሰው ልጆችን ሁሉ መቃብር ያመለክታል። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ወይም “ያልታሰቡ ገጠመኞች።”
ወይም “የአደጋ ጊዜ።”
ቃል በቃል “በስተ ቀኙ ነው።”
ቃል በቃል “በስተ ግራው ነው።”
ቃል በቃል “ልብ።”
ቃል በቃል “መንፈስ፤ እስትንፋስ።”
ወይም “ብቃት ያላቸው።”
“ጥንቃቄ ሊያደርግ ይገባል” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ቃል በቃል “የምላስ ጌታ።”
ቃል በቃል “ዳቦ።”
“በመኝታህ ላይ” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “በንጉሡ ላይ ክፉ ቃል አትናገር።”
ወይም “መልእክቱን።”
ቃል በቃል “በሰማያት የምትበር ፍጥረት።”
ወይም “ስደድ።”
ወይም “ክፉ ነገር።”
ቃል በቃል “ማህፀን ውስጥ ባሉ አጥንቶች።”
ወይም “እንደሚጠይቅህ።”
ቃል በቃል “ከሥጋህ አርቅ።”
ወይም “የመከራ ቀናት።”
“ደመናት ዶፍ ይዘው” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “ዘበኞች።”
ወይም “ይብረከረካሉ።”
እዚህ ላይ የተሠራበት ቃል የምግብን ፍላጎት ለመቀስቀስ የሚያገለግልን ከእንጆሪ ጋር የሚመሳሰል ተክል ያመለክታል።
ወይም “መዘውር።”
ወይም “የሕይወት ኃይልም።”
ወይም “ዋጋ ቢስ።”
ወይም “በሥርዓት ማዘጋጀት።”