የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
የኢትዮጵያ ምልክት ቋንቋ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • nwt ሥራ 1:1-28:31
  • ሥራ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ሥራ
  • አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ
አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ
ሥራ

የሐዋርያት ሥራ

1 ቴዎፍሎስ ሆይ፣ ኢየሱስ ስላደረገውና ስላስተማረው ነገር ሁሉ በመጀመሪያው መጽሐፍ ላይ ጽፌልሃለሁ፤+ 2 ታሪኩም አምላክ እስከወሰደው ቀን ድረስ ያለውን ያካትታል።+ ለመረጣቸው ሐዋርያት በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት መመሪያዎች ከሰጣቸው በኋላ አረገ።+ 3 መከራ ከተቀበለ በኋላ ሕያው መሆኑን በብዙ አሳማኝ ማስረጃዎች አሳያቸው።+ እነሱም ለ40 ቀናት ያዩት ሲሆን እሱም ስለ አምላክ መንግሥት ይነግራቸው ነበር።+ 4 ከእነሱ ጋር ተሰብስቦ ሳለ እንዲህ ሲል አዘዛቸው፦ “ከኢየሩሳሌም አትውጡ፤+ ከዚህ ይልቅ አብ ቃል የገባውንና እኔም ስለዚሁ ጉዳይ ስናገር የሰማችሁትን ቃል ፍጻሜ ተጠባበቁ፤+ 5 ዮሐንስ በውኃ አጥምቆ ነበርና፤ እናንተ ግን ከጥቂት ቀናት በኋላ በመንፈስ ቅዱስ ትጠመቃላችሁ።”+

6 እንደገና ተሰብስበው ሳሉ “ጌታ ሆይ፣ ለእስራኤል መንግሥትን መልሰህ የምታቋቁመው በዚህ ጊዜ ነው?” ሲሉ ጠየቁት።+ 7 እሱም እንዲህ አላቸው፦ “ጊዜያትንና ወቅቶችን የመወሰን ሥልጣን ያለው አብ ብቻ ስለሆነ* እናንተ ይህን ማወቅ አያስፈልጋችሁም።+ 8 ሆኖም መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በሚወርድበት ጊዜ ኃይል ትቀበላላችሁ፤+ በኢየሩሳሌም፣+ በመላው ይሁዳና በሰማርያ+ እንዲሁም እስከ ምድር ዳር ድረስ+ ምሥክሮቼ ትሆናላችሁ።”+ 9 ይህን ከተናገረ በኋላም እያዩት ወደ ላይ ወጣ፤ ደመናም ከዓይናቸው ሰወረው።+ 10 እሱ ወደ ላይ እየወጣ ሳለ ትኩር ብለው ወደ ሰማይ ሲመለከቱ ነጫጭ ልብስ የለበሱ ሁለት ሰዎች+ ድንገት አጠገባቸው ቆሙ፤ 11 እንዲህም አሏቸው፦ “እናንተ የገሊላ ሰዎች፣ ወደ ሰማይ እየተመለከታችሁ የቆማችሁት ለምንድን ነው? ይህ ከእናንተ ወደ ሰማይ የተወሰደው ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሲሄድ ባያችሁት በዚሁ ሁኔታ ይመጣል።”

12 ከዚያም ደብረ ዘይት ከተባለው ተራራ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፤+ ይህ ተራራ በኢየሩሳሌም አቅራቢያ የሚገኝ ሲሆን ርቀቱ የሰንበት መንገድ* ያህል ብቻ ነበር። 13 እዚያ በደረሱ ጊዜ ያርፉበት ወደነበረው ደርብ ወጡ። እነሱም ጴጥሮስ፣ ዮሐንስ፣ ያዕቆብና እንድርያስ፣ ፊልጶስና ቶማስ፣ በርቶሎሜዎስና ማቴዎስ፣ የእልፍዮስ ልጅ ያዕቆብና ቀናተኛው ስምዖን እንዲሁም የያዕቆብ ልጅ ይሁዳ ነበሩ።+ 14 እነዚህ ሁሉ ከአንዳንድ ሴቶችና+ ከኢየሱስ እናት ከማርያም እንዲሁም ከወንድሞቹ+ ጋር በአንድ ልብ ተግተው ይጸልዩ ነበር።

15 በዚያው ሰሞን 120 የሚያህሉ ሰዎች አንድ ላይ ተሰብስበው ሳለ ጴጥሮስ በወንድሞች መካከል ቆሞ እንዲህ አለ፦ 16 “ወንድሞች፣ ኢየሱስን የያዙትን ሰዎች እየመራ ስላመጣው ስለ ይሁዳ+ መንፈስ ቅዱስ በዳዊት በኩል በትንቢት የተናገረው የቅዱስ መጽሐፉ ቃል መፈጸሙ የግድ ነበር።+ 17 ምክንያቱም እሱ ከእኛ እንደ አንዱ ተቆጥሮ የነበረ+ ከመሆኑም በላይ በዚህ አገልግሎት የመካፈል አጋጣሚ አግኝቶ ነበር። 18 (ይኸው ሰው ለዓመፅ ሥራው በተከፈለው ደሞዝ+ መሬት ገዛ፤ በአናቱም ወድቆ ሰውነቱ ፈነዳ፤* ሆድ ዕቃውም ተዘረገፈ።+ 19 ይህም በኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ሁሉ ዘንድ ታወቀ፤ በመሆኑም መሬቱ በቋንቋቸው አኬልዳማ ተብሎ ተጠራ፤ ትርጉሙም “የደም መሬት” ማለት ነው።) 20 በመዝሙር መጽሐፍ ላይ ‘መኖሪያው ወና ይሁን፤ በውስጡም ማንም ሰው አይኑርበት’+ እንዲሁም ‘የበላይ ተመልካችነት ሹመቱን ሌላ ሰው ይውሰደው’ ተብሎ ተጽፏልና።+ 21 ስለዚህ ጌታ ኢየሱስ በእኛ መካከል ሆኖ ሥራውን ያከናውን በነበረበት* ጊዜ ሁሉ ከእኛ ጋር ከነበሩት ወንዶች መካከል በአንዱ እሱን መተካት ያስፈልጋል፤ 22 የሚተካው ሰው ኢየሱስ በዮሐንስ ከተጠመቀበት ጊዜ አንስቶ+ ከእኛ እስከተወሰደበት ጊዜ+ ድረስ አብሮን የነበረ መሆን ይኖርበታል። በተጨማሪም ከእኛ ጋር የትንሣኤው ምሥክር መሆን ያስፈልገዋል።”+

23 ስለዚህ ሁለት ሰዎችን ዕጩ አድርገው አቀረቡ፤ እነሱም በርስያን ተብሎ የሚጠራው ዮሴፍ (ኢዮስጦስ ተብሎም ይጠራል) እና ማትያስ ነበሩ። 24 ከዚያም እንዲህ ብለው ጸለዩ፦ “የሰውን ሁሉ ልብ የምታውቀው ይሖዋ* ሆይ፣+ ከእነዚህ ሁለት ሰዎች መካከል የመረጥከውን አመልክተን፤ 25 ይሁዳ ወደ ገዛ ራሱ ስፍራ ለመሄድ ሲል የተወውን ይህን የአገልግሎትና የሐዋርያነት ቦታ የሚወስደውን ሰው ግለጥልን።”+ 26 ከዚያም በሁለቱ ሰዎች ላይ ዕጣ ጣሉ፤+ ዕጣውም ለማትያስ ወጣና ከአሥራ አንዱ ሐዋርያት ጋር ተቆጠረ።*

2 በጴንጤቆስጤ* በዓል ቀን+ ሁሉም በአንድ ቦታ ተሰብስበው ነበር። 2 ድንገትም እንደ ኃይለኛ ነፋስ ያለ ድምፅ ከሰማይ መጣ፤ ተቀምጠውበት የነበረውንም ቤት ሞላው።+ 3 የእሳት ምላሶች የሚመስሉም ታዩአቸው፤ ተከፋፍለውም በእያንዳንዳቸው ላይ አረፉ፤ 4 ሁሉም በመንፈስ ቅዱስ ተሞሉ፤+ መንፈስም እንዲናገሩ ባስቻላቸው መሠረት በተለያዩ ቋንቋዎች* ይናገሩ ጀመር።+

5 በዚያን ጊዜ በምድር ዙሪያ ካለ አገር ሁሉ የመጡ ለአምላክ ያደሩ አይሁዳውያን በኢየሩሳሌም ነበሩ።+ 6 ስለዚህ ይህ ድምፅ በተሰማ ጊዜ ብዙ ሕዝብ ተሰበሰበ፤ እያንዳንዱም ሰው ደቀ መዛሙርቱ በገዛ ቋንቋው ሲናገሩ በመስማቱ ግራ ተጋባ። 7 ደግሞም ሕዝቡ እጅግ ተደንቀው እንዲህ አሉ፦ “እንዴ፣ እነዚህ እየተናገሩ ያሉት የገሊላ ሰዎች አይደሉም?+ 8 ታዲያ እያንዳንዳችን በአገራችን ቋንቋ* ሲናገሩ የምንሰማው እንዴት ነው? 9 እኛ ከጳርቴና፣ ከሜዶን፣+ ከኤላም፣+ ከሜሶጶጣሚያ፣ ከይሁዳ፣ ከቀጰዶቅያ፣ ከጳንጦስ፣ ከእስያ አውራጃ፣+ 10 ከፍርግያ፣ ከጵንፍልያ፣ ከግብፅ፣ በቀሬና አቅራቢያ ካሉት የሊቢያ አውራጃዎችና ከሮም የመጣን አይሁዶችና ወደ ይሁዲነት የተለወጥን ሰዎች፣+ 11 የቀርጤስና የዓረብ ሰዎች ሁላችን ስለ አምላክ ታላቅ ሥራ በየቋንቋችን ሲናገሩ እየሰማናቸው ነው።” 12 ስለዚህ ሁሉም ተገርመውና ግራ ተጋብተው እርስ በርሳቸው “ይህ ነገር ምን ይሆን?” ይባባሉ ነበር። 13 ይሁን እንጂ ሌሎች “ያልፈላ የወይን ጠጅ* ተግተው ነው” በማለት አፌዙባቸው።

14 ጴጥሮስ ግን ከአሥራ አንዱ+ ጋር ተነስቶ በመቆም ድምፁን ከፍ አድርጎ እንዲህ ሲል ለሕዝቡ ተናገረ፦ “እናንተ የይሁዳ ሰዎችና የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ሁሉ፣ አንድ ማወቅ ያለባችሁ ነገር ስላለ ንግግሬን በጥሞና አዳምጡ። 15 ጊዜው ገና ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት ስለሆነ እነዚህ ሰዎች እናንተ እንዳሰባችሁት አልሰከሩም። 16 ከዚህ ይልቅ ይህ የሆነው በነቢዩ ኢዩኤል በኩል እንዲህ ተብሎ በተነገረው መሠረት ነው፦ 17 ‘አምላክ እንዲህ ይላል፦ “በመጨረሻው ቀን በሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ ከመንፈሴ አፈሳለሁ፤ ወንዶች ልጆቻችሁና ሴቶች ልጆቻችሁም ትንቢት ይናገራሉ፤ ወጣቶቻችሁ ራእዮችን ያያሉ፤ ሽማግሌዎቻችሁም ሕልም ያልማሉ፤+ 18 በዚያ ቀን በወንዶች ባሪያዎቼና በሴቶች ባሪያዎቼ ላይ ሳይቀር ከመንፈሴ አፈሳለሁ፤ እነሱም ትንቢት ይናገራሉ።+ 19 በላይ በሰማይ ድንቅ ነገሮች፣ በታች በምድር ደግሞ ተአምራዊ ምልክቶች አሳያለሁ፤ ደም፣ እሳትና የጭስ ደመናም ይታያል። 20 ታላቁና ክብራማው የይሖዋ* ቀን ከመምጣቱ በፊት ፀሐይ ወደ ጨለማ፣ ጨረቃም ወደ ደም ይለወጣሉ። 21 የይሖዋን* ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናል።”’+

22 “የእስራኤል ሰዎች ሆይ፣ ይህን ቃል ስሙ፦ እናንተ ራሳችሁ እንደምታውቁት፣ አምላክ በኢየሱስ አማካኝነት በመካከላችሁ የፈጸማቸው ተአምራት፣ ድንቅ ነገሮችና ምልክቶች የናዝሬቱ ኢየሱስ በአምላክ የተላከ ሰው እንደሆነ የሚያሳዩ ማስረጃዎች ናቸው።+ 23 ይህ ሰው ለሞት አልፎ ተሰጠ። ይህም አምላክ አስቀድሞ የወሰነው ፈቃዱና* የሚያውቀው ነገር ነበር።+ እናንተም በክፉ ሰዎች እጅ በእንጨት ላይ ሰቅላችሁ ገደላችሁት።+ 24 አምላክ ግን ከሞት ጣር* አላቆ አስነሳው፤+ ምክንያቱም ሞት ይዞ ሊያስቀረው አልቻለም።+ 25 ዳዊትም ስለ እሱ እንዲህ ይላል፦ ‘ይሖዋን* ሁልጊዜ በፊቴ* አደርገዋለሁ፤ እሱ በቀኜ ስለሆነ ፈጽሞ አልናወጥም። 26 ስለዚህ ልቤ ደስ አለው፤ አንደበቴም ሐሴት አደረገ። እኔም በተስፋ እኖራለሁ፤* 27 ምክንያቱም በመቃብር* አትተወኝም፤* ታማኝ አገልጋይህም መበስበስን እንዲያይ አትፈቅድም።+ 28 የሕይወትን መንገድ አሳውቀኸኛል፤ በፊትህ በታላቅ ደስታ እንድሞላ ታደርገኛለህ።’+

29 “ወንድሞች፣ ከቀድሞ አባቶች አንዱ የሆነው ዳዊት እንደሞተና እንደተቀበረ+ እንዲሁም መቃብሩ እስከ ዛሬ ድረስ በእኛ ዘንድ እንደሚገኝ ለእናንተ በግልጽ እንድናገር ፍቀዱልኝ። 30 እሱ ነቢይ ስለነበረና አምላክ ከዘሮቹ አንዱን* በዙፋኑ ላይ እንደሚያስቀምጥ በመሐላ ቃል እንደገባለት ስላወቀ+ 31 አምላክ ክርስቶስን በመቃብር* እንደማይተወውና ሥጋውም እንደማይበሰብስ* አስቀድሞ ተረድቶ ስለ ትንሣኤው ተናገረ።+ 32 ይህን ኢየሱስን አምላክ ከሞት አስነሳው፤ እኛ ሁላችንም ለዚህ ነገር ምሥክሮች ነን።+ 33 ስለዚህ ወደ አምላክ ቀኝ ከፍ ከፍ ስለተደረገና+ ቃል የተገባውን ቅዱስ መንፈስ ከአብ ስለተቀበለ+ ይህን የምታዩትንና የምትሰሙትን አፈሰሰው። 34 ዳዊት ወደ ሰማያት አልወጣምና፤ ሆኖም እሱ ራሱ እንዲህ ሲል ተናግሯል፦ ‘ይሖዋ* ጌታዬን እንዲህ ብሎታል፦ “በቀኜ ተቀመጥ፤ 35 ጠላቶችህን ለእግርህ መርገጫ እስከማደርግልህ ድረስ በቀኜ ሁን።”’+ 36 ስለዚህ ይህን እናንተ በእንጨት ላይ የሰቀላችሁትን ኢየሱስን+ አምላክ ጌታም+ ክርስቶስም እንዳደረገው የእስራኤል ቤት ሁሉ በእርግጥ ይወቅ።”

37 ሰዎቹም ይህን በሰሙ ጊዜ ልባቸው እጅግ ተነክቶ ጴጥሮስንና የቀሩትን ሐዋርያት “ወንድሞች፣ ታዲያ ምን ብናደርግ ይሻላል?” አሏቸው። 38 ጴጥሮስም እንዲህ አላቸው፦ “ንስሐ ግቡ፤+ እያንዳንዳችሁም ለኃጢአታችሁ ይቅርታ እንድታገኙ+ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ፤+ የመንፈስ ቅዱስንም ነፃ ስጦታ ትቀበላላችሁ። 39 ምክንያቱም የተስፋው ቃል+ ለእናንተና ለልጆቻችሁ እንዲሁም ይሖዋ* አምላካችን ወደ ራሱ ለሚጠራቸው በሩቅ ላሉ ሁሉ ነው።”+ 40 በሌላ ብዙ ቃልም በሚገባ* መሠከረላቸው፤ “ከዚህ ጠማማ ትውልድ ዳኑ” እያለም አጥብቆ አሳሰባቸው።+ 41 ስለዚህ ቃሉን በደስታ የተቀበሉ ተጠመቁ፤+ በዚያም ቀን 3,000 ገደማ የሚሆኑ ሰዎች* ተጨመሩ።+ 42 የሐዋርያቱንም ትምህርት በትኩረት መከታተላቸውን ቀጠሉ፤ አንድ ላይ ይሰበሰቡ፣* ምግባቸውንም አብረው ይበሉ+ እንዲሁም በጸሎት ይተጉ ነበር።+

43 ሰው ሁሉ* ፍርሃት አደረበት፤ ሐዋርያቱም ብዙ ድንቅ ነገሮችና ተአምራዊ ምልክቶች ያደርጉ ጀመር።+ 44 ያመኑትም ሁሉ አብረው ነበሩ፤ ያላቸውም ነገር ሁሉ የጋራ ነበር፤ 45 በተጨማሪም ያላቸውን ሀብትና ንብረት በመሸጥ+ ገንዘቡን ለሁሉም አከፋፈሉ። ለእያንዳንዱም ሰው የሚያስፈልገውን ያህል ሰጡ።+ 46 በየዕለቱም በአንድ ልብ ሆነው በቤተ መቅደሱ አዘውትረው ይገኙ ነበር፤ ምግባቸውንም በተለያዩ ቤቶች ይበሉ የነበረ ሲሆን የሚመገቡትም በታላቅ ደስታና በንጹሕ ልብ ነበር፤ 47 አምላክንም ያወድሱ የነበረ ከመሆኑም በላይ በሰው ሁሉ ፊት ሞገስ አግኝተው ነበር። ይሖዋም* የሚድኑ ሰዎችን በየዕለቱ በእነሱ ላይ ይጨምር ነበር።+

3 አንድ ቀን ጴጥሮስና ዮሐንስ በጸሎት ሰዓት ይኸውም ከቀኑ በዘጠኝ ሰዓት ወደ ቤተ መቅደሱ እየወጡ ነበር፤ 2 ሰዎችም ከተወለደበት ጊዜ አንስቶ ሽባ የሆነ አንድ ሰው ተሸክመው በማምጣት ወደ ቤተ መቅደሱ ከሚገባው ሰው ምጽዋት* እንዲለምን “ውብ” በተባለው የቤተ መቅደሱ በር አጠገብ በየዕለቱ ያስቀምጡት ነበር። 3 ይህ ሰው ጴጥሮስና ዮሐንስ ወደ ቤተ መቅደሱ ሊገቡ ሲሉ አያቸውና ምጽዋት እንዲሰጡት ይለምናቸው ጀመር። 4 ጴጥሮስና ዮሐንስ ግን ትኩር ብለው አዩት፤ ከዚያም ጴጥሮስ “ወደ እኛ ተመልከት” አለው። 5 ሰውየውም የሆነ ነገር ሊሰጡኝ ነው ብሎ በማሰብ ትኩር ብሎ ተመለከታቸው። 6 ይሁንና ጴጥሮስ “እኔ ብርና ወርቅ የለኝም፤ ያለኝን ግን እሰጥሃለሁ። በናዝሬቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተነስና ተራመድ!” አለው።+ 7 ከዚያም ቀኝ እጁን ይዞ አስነሳው።+ ወዲያውም እግሩና ቁርጭምጭሚቱ ጠነከረ፤+ 8 ዘሎም ተነሳ፤+ መራመድም ጀመረ፤ ደግሞም እየተራመደና እየዘለለ እንዲሁም አምላክን እያወደሰ ከእነሱ ጋር ወደ ቤተ መቅደሱ ገባ። 9 ሰዎቹም ሁሉ ሲራመድና አምላክን ሲያወድስ አዩት። 10 ይህ ሰው “ውብ በር” በተባለው የቤተ መቅደሱ መግቢያ አጠገብ ተቀምጦ ምጽዋት ይለምን የነበረው ሰው መሆኑን ስላወቁ በእሱ ላይ በተፈጸመው ሁኔታ እጅግ ተገረሙ፤+ በአድናቆትም ተዋጡ።

11 ሰውየው ጴጥሮስንና ዮሐንስን ይዟቸው ሳለ በዚያ የነበሩት ሰዎች ሁሉ እጅግ ተደንቀው እነሱ ወዳሉበት “የሰለሞን መተላለፊያ”+ ወደሚባለው ስፍራ ግር ብለው እየሮጡ መጡ። 12 ጴጥሮስ ይህን ባየ ጊዜ ሰዎቹን እንዲህ አላቸው፦ “የእስራኤል ሰዎች ሆይ፣ በዚህ ለምን ትደነቃላችሁ? ደግሞስ በእኛ ኃይል ወይም እኛ ለአምላክ ያደርን በመሆናችን የተነሳ ይህን ሰው እንዲራመድ ያስቻልነው ይመስል ለምን ትኩር ብላችሁ ታዩናላችሁ? 13 የአባቶቻችን አምላክ ይኸውም የአብርሃም፣ የይስሐቅና የያዕቆብ አምላክ+ እናንተ አሳልፋችሁ የሰጣችሁትንና+ ጲላጦስ ሊፈታው ወስኖ የነበረ ቢሆንም በእሱ ፊት የካዳችሁትን አገልጋዩን ኢየሱስን አከበረው።+ 14 አዎ፣ እናንተ ይህን ቅዱስና ጻድቅ ሰው ክዳችሁ ነፍሰ ገዳይ የሆነን ሰው እንዲፈታላችሁ ጠየቃችሁ፤+ 15 በአንጻሩ ግን የሕይወትን “ዋና ወኪል”*+ ገደላችሁት። አምላክ ግን ከሞት አስነሳው፤ እኛም ለዚህ ነገር ምሥክሮች ነን።+ 16 የኢየሱስ ስምና እኛ በስሙ ላይ ያለን እምነት ይህን የምታዩትንና የምታውቁትን ሰው አጠነከረው። በኢየሱስ አማካኝነት ያገኘነው እምነት ይህ ሰው በሁላችሁም ፊት ፍጹም ጤናማ እንዲሆን አደረገው። 17 አሁንም ወንድሞች፣ ገዢዎቻችሁ እንዳደረጉት ሁሉ እናንተም ይህን ያደረጋችሁት ባለማወቅ እንደሆነ አውቃለሁ።+ 18 ይሁንና አምላክ፣ ክርስቶስ መከራ እንደሚቀበል በነቢያት ሁሉ አፍ አስቀድሞ ያሳወቀው ነገር በዚህ መንገድ እንዲፈጸም አድርጓል።+

19 “ስለዚህ ኃጢአታችሁ እንዲደመሰስ+ ንስሐ ግቡ፣+ ተመለሱም፤+ ከይሖዋም ዘንድ* የመታደስ ዘመን ይመጣላችኋል፤ 20 እንዲሁም ለእናንተ የሾመውን ክርስቶስን ይኸውም ኢየሱስን ይልክላችኋል። 21 እሱም አምላክ በጥንቶቹ ቅዱሳን ነቢያቱ አፍ የተናገራቸው ነገሮች ሁሉ የሚታደሱበት ዘመን እስኪመጣ ድረስ በሰማይ መቆየት* ይገባዋል። 22 ደግሞም ሙሴ እንዲህ ብሏል፦ ‘አምላካችሁ ይሖዋ* ከወንድሞቻችሁ መካከል እንደ እኔ ያለ ነቢይ ያስነሳላችኋል።+ እሱ የሚነግራችሁንም ነገር ሁሉ ስሙ።+ 23 ያንን ነቢይ የማይሰማ ሰው ሁሉ* ከሕዝቡ መካከል ተለይቶ ይጠፋል።’+ 24 ከሳሙኤል ጀምሮ በተከታታይ የተነሱት ነቢያት ሁሉ ስለ እነዚህ ቀናት በግልጽ ተናግረዋል።+ 25 እናንተ የነቢያት ልጆች ናችሁ፤ እንዲሁም አምላክ ለአብርሃም ‘የምድር ቤተሰቦች ሁሉ በዘርህ አማካኝነት ይባረካሉ’+ ብሎ ከአባቶቻችሁ ጋር የገባው ቃል ኪዳን ወራሾች ናችሁ።+ 26 አምላክ አገልጋዩን ካስነሳ በኋላ እያንዳንዳችሁን ከክፉ ሥራችሁ በመመለስ ይባርካችሁ ዘንድ በመጀመሪያ ወደ እናንተ ላከው።”+

4 ጴጥሮስና ዮሐንስ ለሕዝቡ እየተናገሩ ሳሉ ካህናቱ፣ የቤተ መቅደሱ ሹምና ሰዱቃውያን+ ድንገት ወደ እነሱ መጡ። 2 እነሱም ሐዋርያቱ ሕዝቡን እያስተማሩና ኢየሱስ ከሞት እንደተነሳ በግልጽ እየተናገሩ+ ስለነበር እጅግ ተቆጡ። 3 በመሆኑም ያዟቸው፤ መሽቶም ስለነበር እስከ ማግስቱ ድረስ እስር ቤት አቆዩአቸው።+ 4 ይሁን እንጂ ንግግሩን ሰምተው ከነበሩት መካከል ብዙዎቹ አመኑ፤ የወንዶቹም ቁጥር 5,000 ገደማ ሆነ።+

5 በማግስቱም የሕዝቡ ገዢዎች፣ ሽማግሌዎችና ጸሐፍት በኢየሩሳሌም ተሰበሰቡ፤ 6 የካህናት አለቃው ሐና፣+ ቀያፋ፣+ ዮሐንስ፣ እስክንድርና የካህናት አለቃው ዘመዶችም ሁሉ ከእነሱ ጋር ነበሩ። 7 ጴጥሮስንና ዮሐንስን በመካከላቸው አቁመው “ይህን ያደረጋችሁት በምን ሥልጣን ወይም በማን ስም ነው?” ብለው ጠየቋቸው። 8 በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ+ እንዲህ አላቸው፦

“እናንተ የሕዝቡ ገዢዎችና ሽማግሌዎች፣ 9 ዛሬ በእኛ ላይ ምርመራ እየተካሄደ ያለው ለአንድ ሽባ ሰው በተደረገ መልካም ሥራ+ የተነሳ ከሆነና ይህን ሰው ያዳነው ማን እንደሆነ ማወቅ የምትፈልጉ ከሆነ፣ 10 ይህ ሰው ጤናማ ሆኖ እዚህ ፊታችሁ የቆመው፣ እናንተ በእንጨት ላይ በሰቀላችሁት+ ሆኖም አምላክ ከሞት ባስነሳው+ በናዝሬቱ ኢየሱስ ክርስቶስ ስም፣+ ይኸውም በኢየሱስ አማካኝነት እንደሆነ እናንተም ሆናችሁ መላው የእስራኤል ሕዝብ ይወቅ። 11 ‘እናንተ ግንበኞች የናቃችሁት፣ የማዕዘን ራስ የሆነው ድንጋይ’ እሱ ነው።+ 12 ደግሞም መዳን በሌላ በማንም አይገኝም፤ ምክንያቱም ልንድንበት የምንችል ከሰማይ በታች ለሰዎች የተሰጠ ሌላ ስም የለም።”+

13 ሰዎቹ ጴጥሮስና ዮሐንስ በድፍረት ሲናገሩ ባዩአቸው ጊዜ ያልተማሩና* ተራ ሰዎች+ መሆናቸውን ተረድተው ተደነቁ። ከኢየሱስ ጋር እንደነበሩም ተገነዘቡ።+ 14 የተፈወሰውንም ሰው ከእነሱ ጋር ቆሞ ሲያዩት+ ምንም መልስ መስጠት አልቻሉም።+ 15 ስለዚህ ከሳንሄድሪን ሸንጎ አዳራሽ እንዲወጡ አዘዟቸው፤ ከዚያም እርስ በርሳቸው ይማከሩ ጀመር፤ 16 እንዲህም ተባባሉ፦ “እነዚህን ሰዎች ምን ብናደርጋቸው ይሻላል?+ ምክንያቱም በኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ሁሉ ዘንድ የታወቀ አስደናቂ ነገር እንደፈጸሙ የማይታበል ሐቅ ነው፤+ ይህን ደግሞ ልንክድ አንችልም። 17 ይሁንና ይህ ነገር በሕዝቡ መካከል ይበልጥ እንዳይስፋፋ ከዚህ በኋላ በዚህ ስም ለማንም ሰው እንዳይናገሩ በማሳሰብ እናስፈራራቸው።”+

18 ከዚያም ጠርተዋቸው በኢየሱስ ስም ፈጽሞ እንዳይናገሩ ወይም እንዳያስተምሩ አዘዟቸው። 19 ጴጥሮስና ዮሐንስ ግን መልሰው እንዲህ አሏቸው፦ “አምላክን ከመስማት ይልቅ እናንተን መስማት በአምላክ ፊት ተገቢ እንደሆነና እንዳልሆነ እስቲ እናንተው ፍረዱ። 20 እኛ ግን ስላየነውና ስለሰማነው ነገር ከመናገር ወደኋላ ማለት አንችልም።”+ 21 በመሆኑም እንደገና ካስፈራሯቸው በኋላ ለቀቋቸው፤ ይህን ያደረጉት እነሱን ለመቅጣት የሚያስችል ምንም ተጨባጭ ነገር ስላላገኙና ሕዝቡን ስለፈሩ ነው፤+ ምክንያቱም ሕዝቡ ሁሉ በተፈጸመው ሁኔታ አምላክን እያከበረ ነበር። 22 በዚህ ተአምር* የተፈወሰውም ሰው ዕድሜው ከ40 ዓመት በላይ ነበር።

23 ከተለቀቁ በኋላ ወደ ወንድሞቻቸው ሄደው የካህናት አለቆቹና ሽማግሌዎቹ ያሏቸውን ሁሉ ነገሯቸው። 24 እነሱም ይህን በሰሙ ጊዜ በአንድ ልብ ሆነው ድምፃቸውን ከፍ በማድረግ እንዲህ ሲሉ ወደ አምላክ ጸለዩ፦

“ሉዓላዊው ጌታ ሆይ፣ ሰማይን፣ ምድርን፣ ባሕርንና በውስጣቸው ያሉትን ነገሮች ሁሉ የፈጠርክ አንተ ነህ፤+ 25 በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት በአገልጋይህ በአባታችን በዳዊት አፍ እንዲህ ብለሃል፦+ ‘ብሔራት ለምን ታወኩ? ሕዝቦችስ ለምን ከንቱ ነገር ያውጠነጥናሉ? 26 የምድር ነገሥታት ተሰለፉ፤ ገዢዎችም በአንድነት ተሰብስበው በይሖዋና* እሱ በቀባው* ላይ ተነሱ።’+ 27 በእርግጥም ሄሮድስና ጳንጥዮስ ጲላጦስ+ ከአሕዛብና ከእስራኤል ሕዝብ ጋር በዚህች ከተማ ተሰብስበው አንተ በቀባኸው+ በቅዱስ አገልጋይህ በኢየሱስ ላይ ተነሱ፤ 28 ይህም የሆነው እጅህና ፈቃድህ አስቀድመው የወሰኑት እንዲፈጸም ነው።+ 29 አሁንም ይሖዋ* ሆይ፣ ዛቻቸውን ተመልከት፤ ባሪያዎችህም ቃልህን በፍጹም ድፍረት መናገራቸውን እንዲቀጥሉ እርዳቸው፤ 30 ለመፈወስም የዘረጋኸውን እጅህን አትጠፍ፤ በቅዱስ አገልጋይህ በኢየሱስ ስም+ ተአምራዊ ምልክቶችና ድንቅ ነገሮች ማድረግህንም ቀጥል።”+

31 ምልጃ ካቀረቡም* በኋላ ተሰብስበውበት የነበረው ቦታ ተናወጠ፤ ሁሉም በመንፈስ ቅዱስ ተሞልተው+ የአምላክን ቃል በድፍረት መናገር ጀመሩ።+

32 በተጨማሪም ከፍተኛ ቁጥር የነበራቸው ያመኑት ሰዎች አንድ ልብና ነፍስ* ነበራቸው፤ አንዳቸውም ቢሆኑ ያላቸው ማንኛውም ንብረት የግላቸው እንደሆነ አድርገው አይቆጥሩም ነበር፤ ከዚህ ይልቅ ያላቸው ነገር ሁሉ የጋራ ነበር።+ 33 ደግሞም ሐዋርያቱ ስለ ጌታ ኢየሱስ ትንሣኤ በታላቅ ኃይል መመሥከራቸውን ቀጠሉ፤+ ሁሉም የአምላክን ታላቅ ጸጋ አግኝተው ነበር። 34 ከመካከላቸውም አንድም ችግረኛ አልነበረም፤+ ምክንያቱም መሬት ወይም ቤት የነበራቸው ሁሉ እየሸጡ ገንዘቡን በማምጣት 35 ለሐዋርያት ያስረክቡ ነበር።+ ከዚያም ለእያንዳንዱ ሰው በሚያስፈልገው መጠን ይከፋፈል ነበር።+ 36 የቆጵሮስ ተወላጅ የሆነ ዮሴፍ የሚባል አንድ ሌዋዊ ነበር፤ ሐዋርያት በርናባስ+ ብለውም ይጠሩት የነበረ ሲሆን ትርጉሙም “የመጽናናት ልጅ” ማለት ነው፤ 37 እሱም መሬት ስለነበረው መሬቱን ሸጦ ገንዘቡን በማምጣት ለሐዋርያት አስረከበ።+

5 ሐናንያ የሚባል አንድ ሰው ከሚስቱ ከሰጲራ ጋር መሬት ሸጠ። 2 ይሁንና ከገንዘቡ የተወሰነውን ደብቆ አስቀረ፤ ሚስቱም ይህን ታውቅ ነበር፤ የቀረውንም አምጥቶ ለሐዋርያት አስረከበ።+ 3 ጴጥሮስ ግን እንዲህ አለ፦ “ሐናንያ፣ ሰይጣን መንፈስ ቅዱስን እንድትዋሽና+ ከመሬቱ ሽያጭ የተወሰነውን ደብቀህ እንድታስቀር ያደፋፈረህ ለምንድን ነው? 4 ሳትሸጠው በፊት ያንተው አልነበረም? ከሸጥከውስ በኋላ ገንዘቡን የፈለግከውን ልታደርግበት ትችል አልነበረም? እንዲህ ያለ ድርጊት ለመፈጸም በልብህ ለምን አሰብክ? የዋሸኸው ሰውን ሳይሆን አምላክን ነው።” 5 ሐናንያ ይህን ቃል ሲሰማ ወደቀና ሞተ። ይህን የሰሙ ሁሉ እጅግ ፈሩ። 6 ወጣት ወንዶችም ተነስተው በጨርቅ ከጠቀለሉት በኋላ ተሸክመው አውጥተው ቀበሩት።

7 ይህ ከሆነ ከሦስት ሰዓት ገደማ በኋላ ደግሞ የተፈጸመውን ነገር ያላወቀችው ሚስቱ መጣች። 8 ጴጥሮስም “እስቲ ንገሪኝ፣ መሬቱን የሸጣችሁት በዚህ ዋጋ ነው?” አላት። እሷም “አዎ፣ በዚሁ ዋጋ ነው” አለች። 9 በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ “ሁለታችሁ የይሖዋን* መንፈስ ለመፈተን የተስማማችሁት ለምንድን ነው? እነሆ፣ ባልሽን የቀበሩት ሰዎች እግር ደጃፍ ላይ ነው፤ እነሱም ተሸክመው ያወጡሻል” አላት። 10 ወዲያውም እግሩ ሥር ወድቃ ሞተች። ወጣቶቹ ሲገቡም ሞታ አገኟት፤ ተሸክመው አውጥተውም ከባሏ አጠገብ ቀበሯት። 11 በመሆኑም መላው ጉባኤ እንዲሁም ይህን የሰሙ ሰዎች ሁሉ በከፍተኛ ፍርሃት ተዋጡ።

12 በተጨማሪም ሐዋርያት በሕዝቡ መካከል ብዙ ተአምራዊ ምልክቶችና ድንቅ ነገሮች መፈጸማቸውን ቀጥለው ነበር፤+ ሁሉም አንድ ላይ ሆነው መጠለያ ባለው “የሰለሞን መተላለፊያ”+ ይሰበሰቡ ነበር። 13 እርግጥ ከሌሎቹ መካከል ከእነሱ ጋር ሊቀላቀል የደፈረ አንድም ሰው አልነበረም፤ ሆኖም ሕዝቡ ያሞግሳቸው ነበር። 14 ከዚህም በላይ በጌታ ያመኑ እጅግ በርካታ ወንዶችና ሴቶች በየጊዜው በእነሱ ላይ ይጨመሩ ነበር።+ 15 ደግሞም ጴጥሮስ በዚያ ሲያልፍ በአንዳንዶቹ ላይ ቢያንስ ጥላው ቢያርፍባቸው በማለት ሕመምተኞችን አውራ ጎዳናዎች ላይ አውጥተው በትናንሽ አልጋዎችና በምንጣፎች ላይ ያስተኟቸው ነበር።+ 16 በተጨማሪም በኢየሩሳሌም ዙሪያ ከሚገኙ ከተሞች ብዙ ሰዎች ሕመምተኞችንና በርኩሳን መናፍስት የሚሠቃዩ ሰዎችን ተሸክመው መምጣታቸውን ቀጠሉ፤ የመጡትም ሁሉ ይፈወሱ ነበር።

17 ይሁንና ሊቀ ካህናቱና አብረውት የነበሩት የሰዱቃውያን ሃይማኖታዊ ቡድን አባላት ሁሉ በቅናት ተሞልተው ተነሱ። 18 ሐዋርያትንም ይዘው እስር ቤት ከተቷቸው።+ 19 ይሁን እንጂ ሌሊት የይሖዋ* መልአክ የእስር ቤቱን በሮች ከፍቶ+ አወጣቸውና እንዲህ አላቸው፦ 20 “ሂዱና በቤተ መቅደሱ ቆማችሁ ስለዚህ ሕይወት የሚገልጸውን ቃል ሁሉ ለሕዝቡ መናገራችሁን ቀጥሉ።” 21 እነሱም በተነገራቸው መሠረት ንጋት ላይ ወደ ቤተ መቅደሱ ገብተው ያስተምሩ ጀመር።

ሊቀ ካህናቱና ከእሱ ጋር የነበሩት በመጡ ጊዜም የሳንሄድሪንን ሸንጎና መላውን የእስራኤል ልጆች ሽማግሌዎች ጉባኤ በአንድነት ሰበሰቡ፤ ሐዋርያቱንም ወደ እነሱ እንዲያመጧቸው ሰዎችን ወደ እስር ቤቱ ላኩ። 22 የቤተ መቅደሱ ጠባቂዎች እዚያ በደረሱ ጊዜ ግን እስር ቤቱ ውስጥ አላገኟቸውም። ስለዚህ ተመልሰው መጥተው ነገሯቸው፤ 23 እንዲህም አሏቸው፦ “እስር ቤቱ በሚገባ ተቆልፎ ጠባቂዎቹም በሮቹ ላይ ቆመው አገኘናቸው፤ በሮቹን ስንከፍት ግን ውስጥ ማንንም አላገኘንም።” 24 የቤተ መቅደሱ ሹምና የካህናት አለቆቹም ይህን ሲሰሙ ‘የዚህ ነገር መጨረሻ ምን ይሆን?’ በማለት በነገሩ ግራ ተጋቡ። 25 በዚህ ጊዜ አንድ ሰው መጥቶ “እስር ቤት ያስገባችኋቸው ሰዎች በቤተ መቅደሱ ቆመው ሕዝቡን እያስተማሩ ነው” ብሎ ነገራቸው። 26 ከዚያም የቤተ መቅደሱ ሹም ከጠባቂዎቹ ጋር ሄዶ አመጣቸው፤ ሆኖም ሕዝቡ በድንጋይ እንዳይወግራቸው ስለፈሩ ያመጧቸው በኃይል አስገድደው አልነበረም።+

27 አምጥተውም በሳንሄድሪን ሸንጎ ፊት አቆሟቸው። ከዚያም ሊቀ ካህናቱ ይጠይቃቸው ጀመር፤ 28 እንዲህም አለ፦ “በዚህ ስም ማስተማራችሁን እንድታቆሙ በጥብቅ አዘናችሁ ነበር፤+ እናንተ ግን ኢየሩሳሌምን በትምህርታችሁ ሞልታችኋታል፤ የዚህንም ሰው ደም በእኛ ላይ ለማምጣት ቆርጣችሁ ተነስታችኋል።”+ 29 ጴጥሮስና ሌሎቹ ሐዋርያትም እንዲህ ሲሉ መለሱ፦ “ከሰው ይልቅ አምላክን እንደ ገዢያችን አድርገን ልንታዘዝ ይገባል።+ 30 እናንተ በእንጨት* ላይ ሰቅላችሁ የገደላችሁትን ኢየሱስን የአባቶቻችን አምላክ አስነሳው።+ 31 እስራኤል ንስሐ እንዲገባና የኃጢአት ይቅርታ እንዲያገኝ+ አምላክ እሱን “ዋና ወኪል”+ እና “አዳኝ”+ አድርጎ በቀኙ ከፍ ከፍ አደረገው።+ 32 ለዚህም ጉዳይ እኛ ምሥክሮች ነን፤+ እንዲሁም አምላክ እሱን እንደ ገዢያቸው አድርገው ለሚታዘዙት የሰጠው መንፈስ ቅዱስ ምሥክር ነው።”+

33 እነሱም ይህን ሲሰሙ እጅግ ተቆጡ፤ ሊገድሏቸውም ፈለጉ። 34 ሆኖም በሕዝቡ ሁሉ ዘንድ የተከበረ፣ የሕግ አስተማሪ የሆነ ገማልያል+ የሚባል አንድ ፈሪሳዊ በሳንሄድሪኑ ሸንጎ መካከል ተነስቶ ሰዎቹን ለጊዜው ወደ ውጭ እንዲያስወጧቸው አዘዘ። 35 ከዚያም እንዲህ አላቸው፦ “የእስራኤል ሰዎች ሆይ፣ በእነዚህ ሰዎች ላይ ልታደርጉ ያሰባችሁትን ነገር በተመለከተ ልትጠነቀቁ ይገባል። 36 ለምሳሌ ያህል፣ ከዚህ ቀደም ቴዎዳስ ራሱን እንደ ታላቅ ሰው በመቁጠር ተነስቶ ነበር፤ ወደ 400 የሚጠጉ ሰዎችም ከእሱ ጋር ተባብረው ነበር። ነገር ግን እሱም ተገደለ፤ ተከታዮቹም ሁሉ ተበታትነው እንዳልነበሩ ሆኑ። 37 ከእሱ በኋላ ደግሞ የሕዝብ ቆጠራ በተካሄደበት ወቅት የገሊላው ይሁዳ ተነስቶ ተከታዮች አፍርቶ ነበር። ይሁንና እሱም ጠፋ፤ ተከታዮቹም ሁሉ ተበታተኑ። 38 ስለዚህ አሁን የምላችሁ፣ እነዚህን ሰዎች አትንኳቸው፤ ተዉአቸው። ይህ ውጥን ወይም ይህ ሥራ ከሰው ከሆነ ይጠፋል፤ 39 ከአምላክ ከሆነ ግን ልታጠፏቸው አትችሉም።+ እንዲያውም ከአምላክ ጋር ስትጣሉ ትገኙ ይሆናል።”+ 40 እነሱም ምክሩን ተቀበሉ፤ ሐዋርያትንም ጠርተው ገረፏቸው፤*+ ከዚያም በኢየሱስ ስም መናገራቸውን እንዲያቆሙ አዘው ለቀቋቸው።

41 እነሱም ስለ ስሙ ውርደት ለመቀበል ብቁ ሆነው በመቆጠራቸው ደስ እያላቸው+ ከሳንሄድሪን ሸንጎ ወጡ። 42 ከዚያም በየቀኑ በቤተ መቅደስም ሆነ ከቤት ወደ ቤት+ እየሄዱ ስለ ክርስቶስ ይኸውም ስለ ኢየሱስ የሚናገረውን ምሥራች ያለማሰለስ ማስተማራቸውንና ማወጃቸውን ቀጠሉ።+

6 በዚያን ወቅት የደቀ መዛሙርቱ ቁጥር እየጨመረ ሲሄድ ግሪክኛ ተናጋሪ የሆኑ አይሁዳውያን በየዕለቱ በሚከናወነው ምግብ የማከፋፈል ሥራ መበለቶቻቸው ቸል ስለተባሉባቸው ዕብራይስጥ ተናጋሪ በሆኑት አይሁዳውያን ላይ ቅሬታ ማሰማት ጀመሩ።+ 2 ስለዚህ አሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ደቀ መዛሙርቱን በሙሉ ጠርተው እንዲህ አሏቸው፦ “በማዕድ ምግብ ለማከፋፈል ስንል የአምላክን ቃል የማስተማር ሥራችንን ብንተው ተገቢ አይሆንም።+ 3 ስለዚህ ወንድሞች፣ ለዚህ አስፈላጊ ጉዳይ እንድንሾማቸው ከእናንተ መካከል መልካም ስም ያተረፉ፣*+ በመንፈስና በጥበብ የተሞሉ+ ሰባት ወንዶች ምረጡ፤+ 4 እኛ ግን በጸሎትና ቃሉን በማስተማሩ ሥራ* ላይ ሙሉ በሙሉ እናተኩራለን።” 5 የተናገሩት ነገር ሁሉንም ደስ አሰኛቸው፤ ስለሆነም ጠንካራ እምነት የነበረውንና በመንፈስ ቅዱስ የተሞላውን እስጢፋኖስን እንዲሁም ፊልጶስን፣+ ጵሮኮሮስን፣ ኒቃሮናን፣ ጢሞንን፣ ፓርሜናስንና ወደ ይሁዲነት ተለውጦ የነበረውን አንጾኪያዊውን ኒቆላዎስን መረጡ። 6 ሐዋርያትም ፊት አቀረቧቸው፤ እነሱም ከጸለዩ በኋላ እጃቸውን ጫኑባቸው።+

7 ከዚህም የተነሳ የአምላክ ቃል መስፋፋቱን ቀጠለ፤+ በኢየሩሳሌምም የደቀ መዛሙርቱ ቁጥር በፍጥነት እየጨመረ ሄደ፤+ በጣም ብዙ ካህናትም ይህን እምነት ተቀበሉ።+

8 እስጢፋኖስም ጸጋና ኃይል ተሞልቶ በሕዝቡ መካከል ታላላቅ ድንቅ ነገሮችና ተአምራዊ ምልክቶች ይፈጽም ነበር። 9 ይሁን እንጂ ‘ነፃ የወጡ ሰዎች ምኩራብ’ ተብሎ የሚጠራው ቡድን አባላት የሆኑ አንዳንድ ሰዎች ከተወሰኑ የቀሬና፣ የእስክንድርያ፣ የኪልቅያና የእስያ ሰዎች ጋር መጥተው እስጢፋኖስን ተከራከሩት። 10 ይሁንና ይናገርበት የነበረውን ጥበብና መንፈስ መቋቋም አልቻሉም።+ 11 ስለዚህ “ይህ ሰው በሙሴና በአምላክ ላይ የስድብ ቃል ሲናገር ሰምተነዋል” ብለው እንዲናገሩ አንዳንድ ሰዎችን በድብቅ አግባቡ። 12 በተጨማሪም ሕዝቡንና ሽማግሌዎችን እንዲሁም ጸሐፍትን ቀሰቀሱ፤ ከዚያም ድንገት መጡና በኃይል ይዘው ወደ ሳንሄድሪን ሸንጎ ወሰዱት። 13 የሐሰት ምሥክሮችም አቀረቡ፤ እነሱም እንዲህ አሉ፦ “ይህ ሰው ይህን ቅዱስ ስፍራና ሕጉን የሚቃወም ነገር ከመናገር ሊቆጠብ አልቻለም። 14 ለምሳሌ ያህል፣ የናዝሬቱ ኢየሱስ ይህን ስፍራ እንደሚያፈርሰውና ሙሴ ያስተላለፈልንን ወግ እንደሚለውጥ ሲናገር ሰምተነዋል።”

15 በሳንሄድሪን ሸንጎ ተቀምጠው የነበሩትም ሁሉ ትኩር ብለው ሲያዩት ፊቱ እንደ መልአክ ፊት ሆኖ ታያቸው።

7 ሊቀ ካህናቱም “ይህ የተባለው ነገር ልክ ነው?” አለው። 2 እስጢፋኖስም እንዲህ ሲል መለሰ፦ “ወንድሞችና አባቶች ሆይ፣ ስሙ። አባታችን አብርሃም በካራን መኖር ከመጀመሩ በፊት በሜሶጶጣሚያ ሳለ የክብር አምላክ ተገለጠለት፤+ 3 እንዲህም አለው፦ ‘ከአገርህ ወጥተህ፣ ከዘመዶችህም ተለይተህ እኔ ወደማሳይህ ምድር ሂድ።’+ 4 እሱም ከከለዳውያን አገር ወጥቶ በካራን መኖር ጀመረ። አባቱ ከሞተ+ በኋላ ደግሞ አምላክ ከዚያ ተነስቶ አሁን እናንተ ወደምትኖሩበት ወደዚህ ምድር እንዲዛወር አደረገው።+ 5 ሆኖም በወቅቱ በዚህ ምድር ምንም ርስት፣ ሌላው ቀርቶ እግሩን ሊያሳርፍ የሚችልበት መሬት እንኳ አልሰጠውም፤ ይሁንና ገና ልጅ ሳይኖረው ለእሱም ሆነ ከእሱ በኋላ ለዘሮቹ ምድሪቱን ርስት አድርጎ እንደሚሰጣቸው ቃል ገባለት።+ 6 ከዚህም በላይ አምላክ፣ ዘሮቹ በሰው አገር ባዕዳን ሆነው እንደሚኖሩ እንዲሁም የአገሩ ሰዎች ለ400 ዓመት በባርነት እንደሚገዟቸውና እንደሚያጎሳቁሏቸው* ነገረው።+ 7 ደግሞም አምላክ ‘በባርነት የሚገዛቸውን ብሔር እፈርድበታለሁ፤+ ከዚያም በኋላ ከነበሩበት አገር ወጥተው በዚህ ስፍራ ቅዱስ አገልግሎት ያቀርቡልኛል’ ሲል ተናግሯል።+

8 “በተጨማሪም አምላክ ከእሱ ጋር የግርዘት ቃል ኪዳን አደረገ፤+ አብርሃምም ይስሐቅን ወለደ፤+ በስምንተኛውም ቀን ገረዘው።+ ይስሐቅም ያዕቆብን ወለደ፤* ያዕቆብም 12ቱን የቤተሰብ ራሶች* ወለደ። 9 የቤተሰብ ራሶቹም በዮሴፍ ቀንተው+ ወደ ግብፅ ሸጡት።+ ሆኖም አምላክ ከእሱ ጋር ነበር፤+ 10 ከመከራውም ሁሉ ታደገው፤ በግብፅ ንጉሥ በፈርዖንም ፊት ሞገስና ጥበብ አጎናጸፈው። ፈርዖንም በግብፅና በቤቱ ሁሉ ላይ ገዢ አድርጎ ሾመው።+ 11 ይሁንና በግብፅና በከነአን አገር ሁሉ ታላቅ መከራ ያስከተለ ረሃብ ተከሰተ፤ አባቶቻችንም የሚበሉት ነገር አጡ።+ 12 ሆኖም ያዕቆብ በግብፅ እህል መኖሩን ሲሰማ አባቶቻችንን ለመጀመሪያ ጊዜ ወደዚያ ላካቸው።+ 13 ለሁለተኛ ጊዜ ሲሄዱ ዮሴፍ ማንነቱን ለወንድሞቹ ነገራቸው፤ ፈርዖንም ስለ ዮሴፍ ቤተሰብ ሰማ።+ 14 ስለዚህ ዮሴፍ መልእክት ልኮ አባቱን ያዕቆብንና ዘመዶቹን ሁሉ ከዚያ አገር አስጠራ፤+ እነሱም በአጠቃላይ 75 ሰዎች* ነበሩ።+ 15 ያዕቆብም ወደ ግብፅ ወረደ፤+ በዚያም ሞተ፤+ አባቶቻችንም በዚያ ሞቱ።+ 16 አፅማቸውም ወደ ሴኬም ተወስዶ አብርሃም በሴኬም ከኤሞር ልጆች በብር ገንዘብ* በገዛው መቃብር ውስጥ ተቀበረ።+

17 “አምላክ ለአብርሃም የተናገረው የተስፋ ቃል የሚፈጸምበት ጊዜ ሲቃረብ ሕዝባችን በግብፅ እየበዛና እየተበራከተ ሄደ፤ 18 ይህም የሆነው ዮሴፍን የማያውቅ ሌላ ንጉሥ በግብፅ እስከተነሳበት ጊዜ ድረስ ነው።+ 19 ይህ ንጉሥ በወገኖቻችን ላይ ተንኮል በመሸረብ ሕፃናት ልጆቻቸውን ለሞት አሳልፈው እንዲሰጡ አባቶቻችንን አስገደዳቸው።+ 20 በዚህ ወቅት በአምላክ ፊት እንኳ ሳይቀር እጅግ ውብ የነበረው ሙሴ ተወለደ። በአባቱም ቤት ሦስት ወር በእንክብካቤ ኖረ።*+ 21 በተጣለ ጊዜ+ ግን የፈርዖን ልጅ ወስዳ እንደ ራሷ ልጅ አድርጋ አሳደገችው።+ 22 ሙሴም የግብፃውያንን ጥበብ ሁሉ ተማረ። በንግግሩና በተግባሩም ብርቱ ሆነ።+

23 “ሙሴ 40 ዓመት በሞላው ጊዜ ወንድሞቹ የሆኑት የእስራኤል ልጆች ያሉበትን ሁኔታ ለማየት* በልቡ አሰበ።*+ 24 እሱም አንድ ግብፃዊ በአንድ እስራኤላዊ ላይ በደል ሲፈጽም አየ፤ ለእስራኤላዊውም አግዞ ግብፃዊውን በመግደል ተበቀለለት። 25 ወንድሞቹ አምላክ በእሱ አማካኝነት እንደሚያድናቸው የሚያስተውሉ መስሎት ነበር፤ እነሱ ግን ይህን አላስተዋሉም። 26 በማግስቱም እርስ በርሳቸው ሲጣሉ አገኛቸው፤ እሱም ‘ሰዎች፣ እናንተ እኮ ወንድማማቾች ናችሁ። ለምን እርስ በርሳችሁ ትጣላላችሁ?’ በማለት ሊያስታርቃቸው ሞከረ። 27 ይሁንና በባልንጀራው ላይ ጥቃት እየፈጸመ የነበረው ሰው ገፈተረውና እንዲህ አለው፦ ‘አንተን በእኛ ላይ ማን ገዢና ፈራጅ አደረገህ? 28 ትናንት ግብፃዊውን እንደገደልከው እኔንም ልትገድለኝ ትፈልጋለህ እንዴ?’ 29 ሙሴ ይህን ሲሰማ ሸሽቶ በምድያም አገር ባዕድ ሆኖ ኖረ፤ በዚያም ሁለት ወንዶች ልጆች ወለደ።+

30 “ከ40 ዓመትም በኋላ በሲና ተራራ አቅራቢያ በሚገኝ ምድረ በዳ፣ በሚነድ ቁጥቋጦ ነበልባል ውስጥ አንድ መልአክ ተገለጠለት።+ 31 ሙሴም ባየው ነገር ተደነቀ። ሆኖም ሁኔታውን ለማጣራት ወደዚያ ሲቀርብ የይሖዋ* ድምፅ እንዲህ ሲል ሰማ፦ 32 ‘እኔ የአባቶችህ አምላክ፣ የአብርሃም፣ የይስሐቅና የያዕቆብ አምላክ ነኝ።’+ በዚህ ጊዜ ሙሴ ይንቀጠቀጥ ጀመር፤ ሁኔታውን ይበልጥ ለማጣራትም አልደፈረም። 33 ይሖዋም* እንዲህ አለው፦ ‘የቆምክበት ስፍራ ቅዱስ መሬት ስለሆነ ጫማህን አውልቅ። 34 በግብፅ ባለው ሕዝቤ ላይ እየደረሰ ያለውን ጭቆና በእርግጥ አይቻለሁ፤ የጭንቅ ጩኸታቸውንም ሰምቻለሁ፤+ ልታደጋቸውም ወርጃለሁ። አሁንም ና፣ ወደ ግብፅ እልክሃለሁ።’ 35 ‘አንተን ማን ገዢና ፈራጅ አደረገህ?’ ብለው የተቃወሙትን ይህንኑ ሙሴን+ አምላክ በቁጥቋጦው ውስጥ በተገለጠለት መልአክ አማካኝነት ገዢና ነፃ አውጪ አድርጎ ላከው።+ 36 ይህ ሰው በግብፅ፣ በቀይ ባሕርና+ በምድረ በዳ ለ40 ዓመት+ ድንቅ ነገሮችንና ተአምራዊ ምልክቶችን በመፈጸም+ ከግብፅ እየመራ አወጣቸው።+

37 “‘አምላክ ከወንድሞቻችሁ መካከል እንደ እኔ ያለ ነቢይ ያስነሳላችኋል’ ብሎ ለእስራኤል ልጆች የተናገረው ይኸው ሙሴ ነው።+ 38 በሲና ተራራ ካነጋገረው መልአክና+ ከአባቶቻችን ጋር በምድረ በዳ በጉባኤው መካከል የነበረው እሱ ነው፤+ ደግሞም ለእኛ ይሰጠን ዘንድ ሕያው የሆነውን ቅዱስ ቃል ተቀበለ።+ 39 አባቶቻችን ለእሱ ለመታዘዝ ፈቃደኞች አልሆኑም፤ ከዚህ ይልቅ እሱን በመቃወም በልባቸው ወደ ግብፅ ተመለሱ፤+ 40 አሮንንም ‘ፊት ፊታችን የሚሄዱ አማልክት ሥራልን። ከግብፅ ምድር መርቶ ያወጣን ያ ሙሴ ምን እንደደረሰበት አናውቅምና’ አሉት።+ 41 ስለሆነም በዚያን ጊዜ ጥጃ ሠርተው ለጣዖቱ መሥዋዕት አቀረቡ፤ በእጃቸውም ሥራ ይደሰቱ ጀመር።+ 42 በዚህ ጊዜ አምላክ ፊቱን ከእነሱ አዞረ፤ በነቢያትም መጻሕፍት እንዲህ ተብሎ በተጻፈው መሠረት የሰማይ ሠራዊትን እንዲያመልኩ ተዋቸው፦+ ‘የእስራኤል ቤት ሆይ፣ ለ40 ዓመት በምድረ በዳ መባና መሥዋዕት ያቀረባችሁት ለእኔ ነበር? 43 ይልቁንም ልታመልኳቸው የሠራችኋቸውን ምስሎች ይኸውም የሞሎክን+ ድንኳንና ሮምፋ የሚባለውን አምላክ ኮከብ ተሸክማችሁ ተጓዛችሁ። ስለዚህ ከባቢሎን ወዲያ እንድትሰደዱ አደርጋችኋለሁ።’+

44 “አባቶቻችን በምድረ በዳ የምሥክሩ ድንኳን ነበራቸው፤ ይህ ድንኳን የተሠራው አምላክ ሙሴን ባነጋገረው ወቅት በሰጠው ትእዛዝና ባሳየው ንድፍ መሠረት ነበር።+ 45 አባቶቻችንም ይህን ድንኳን በመረከብ ከኢያሱ ጋር ሆነው አምላክ ከአባቶቻችን ፊት ያባረራቸው ብሔራት ይኖሩበት ወደነበረው ምድር+ ይዘውት ገቡ።+ እስከ ዳዊት ዘመን ድረስም በዚህ ምድር ቆየ። 46 ዳዊትም በአምላክ ፊት ሞገስ አገኘ፤ ለያዕቆብ አምላክም መኖሪያ ስፍራ የማዘጋጀት መብት እንዲሰጠው ጠየቀ።+ 47 ይሁን እንጂ ቤት የሠራለት ሰለሞን ነበር።+ 48 ሆኖም ልዑሉ አምላክ የሰው እጅ በሠራው ቤት አይኖርም፤+ ይህም ነቢዩ እንዲህ ሲል በተናገረው መሠረት ነው፦ 49 ‘ሰማይ ዙፋኔ ነው፤+ ምድር ደግሞ የእግሬ ማሳረፊያ ናት።+ ለእኔ የምትሠሩልኝ ምን ዓይነት ቤት ነው? ይላል ይሖዋ።* ወይስ የማርፍበት ቦታ የት ነው? 50 እነዚህን ነገሮች ሁሉ የሠራው እጄ አይደለም?’+

51 “እናንተ ግትሮች፣ ልባችሁና ጆሯችሁ ያልተገረዘ፣ ሁልጊዜ መንፈስ ቅዱስን እንደተቃወማችሁ ነው፤ አባቶቻችሁ እንዳደረጉት እናንተም እንዲሁ ታደርጋላችሁ።+ 52 ከነቢያት መካከል አባቶቻችሁ ስደት ያላደረሱበት ማን አለ?+ አዎ፣ እነሱ የጻድቁን መምጣት አስቀድመው የተናገሩትን ገድለዋቸዋል፤+ እናንተም አሁን ይህን ጻድቁን አሳልፋችሁ ሰጣችሁት፤ ደግሞም ገደላችሁት፤+ 53  በመላእክት አማካኝነት የተላለፈውን ሕግ ተቀበላችሁ፤+ ነገር ግን አልጠበቃችሁትም።”

54 እነሱም ይህን ሲሰሙ ልባቸው በንዴት በገነ፤ ጥርሳቸውንም ያፋጩበት ጀመር። 55 እሱ ግን በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ ትኩር ብሎ ወደ ሰማይ ሲመለከት የአምላክን ክብር እንዲሁም ኢየሱስ በአምላክ ቀኝ ቆሞ አየ፤+ 56 ከዚያም “እነሆ፣ ሰማያት ተከፍተው የሰው ልጅም+ በአምላክ ቀኝ ቆሞ አያለሁ” አለ።+ 57  በዚህ ጊዜ በኃይል እየጮኹ ጆሯቸውን በእጃቸው ደፍነው በአንድነት ወደ እሱ ሮጡ። 58 ይዘውት ከከተማው ውጭ ካስወጡት በኋላ በድንጋይ ይወግሩት ጀመር።+ ምሥክሮቹም+ መደረቢያቸውን ሳኦል በተባለ ወጣት እግር አጠገብ አስቀመጡ።+ 59 እስጢፋኖስም እየወገሩት ሳለ “ጌታ ኢየሱስ ሆይ፣ መንፈሴን ተቀበል” ብሎ ተማጸነ። 60 ከዚያም ተንበርክኮ በታላቅ ድምፅ “ይሖዋ* ሆይ፣ ይህን ኃጢአት አትቁጠርባቸው” ብሎ ጮኸ።+ ይህን ከተናገረም በኋላ በሞት አንቀላፋ።

8 ሳኦልም በእሱ መገደል ተስማምቶ ነበር።+

በዚያ ቀን በኢየሩሳሌም በሚገኘው ጉባኤ ላይ ከባድ ስደት ተነሳ፤ ከሐዋርያት በስተቀር ደቀ መዛሙርቱ በሙሉ በይሁዳና በሰማርያ ክልሎች ሁሉ ተበተኑ።+ 2 ሆኖም ለአምላክ ያደሩ ሰዎች እስጢፋኖስን ወስደው ቀበሩት፤ ታላቅ ለቅሶም አለቀሱለት። 3 ሳኦልም በጉባኤው ላይ ከፍተኛ ጥቃት ማድረስ ጀመረ። በየቤቱ እየገባ ወንዶችንም ሆነ ሴቶችን ጎትቶ በማውጣት ወህኒ ቤት ያስገባቸው ነበር።+

4 ይሁን እንጂ የተበተኑት ደቀ መዛሙርት በሄዱበት ቦታ ሁሉ የአምላክን ቃል ምሥራች ሰበኩ።+ 5 በዚህ ጊዜ ፊልጶስ ወደ ሰማርያ+ ከተማ* ሄዶ ስለ ክርስቶስ ይሰብክላቸው ጀመር። 6 ሕዝቡ ፊልጶስ የሚናገረውን ሲሰሙና የፈጸማቸውን ተአምራዊ ምልክቶች ሲመለከቱ ሁሉም በአንድ ልብ በትኩረት ይከታተሉት ጀመር። 7 ርኩሳን መናፍስት ያደሩባቸው ብዙ ሰዎችም ነበሩ፤ ርኩሳን መናፍስቱም በከፍተኛ ድምፅ እየጮኹ ይወጡ ነበር።+ በተጨማሪም ሽባና አንካሳ የነበሩ በርካታ ሰዎች ተፈወሱ። 8 ከዚህም የተነሳ በዚያች ከተማ ታላቅ ደስታ ሆነ።

9 በዚያች ከተማ ስምዖን የሚባል አንድ ሰው ነበር፤ ይህ ሰው ከዚህ ቀደም አስማት እየሠራ የሰማርያን ሕዝብ ያስደምም የነበረ ሲሆን ታላቅ ሰው እንደሆነ አድርጎም ይናገር ነበር። 10 ከትንሹ አንስቶ እስከ ትልቁ ድረስ፣ ሰዎች ሁሉ “ይህ ሰው ታላቅ ተብሎ የሚጠራ ‘የአምላክ ኃይል’ ነው” በማለት ትልቅ ቦታ ይሰጡት ነበር። 11 ረዘም ላለ ጊዜ በአስማት ሥራው ሲያስደንቃቸው ስለቆየ የሚለውን ሁሉ ይቀበሉ ነበር። 12 ይሁንና ስለ አምላክ መንግሥትና ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ምሥራች እያወጀ የነበረውን ፊልጶስን ባመኑት ጊዜ+ ወንዶችም ሴቶችም ይጠመቁ ጀመር።+ 13 ስምዖን ራሱም አማኝ ሆነ፤ ከተጠመቀም በኋላ ከፊልጶስ+ አይለይም ነበር፤ ምልክቶችና ታላላቅ ተአምራት ሲፈጸሙ በማየት ይደነቅ ነበር።

14 በኢየሩሳሌም ያሉ ሐዋርያት የሰማርያ ሰዎች የአምላክን ቃል እንደተቀበሉ ሲሰሙ+ ጴጥሮስንና ዮሐንስን ላኩላቸው፤ 15 እነሱም ወደዚያ ወርደው መንፈስ ቅዱስን እንዲቀበሉ ጸለዩላቸው።+ 16 ምክንያቱም በጌታ ኢየሱስ ስም ተጠመቁ እንጂ መንፈስ ቅዱስ ገና በአንዳቸውም ላይ አልወረደም ነበር።+ 17 ከዚያም ጴጥሮስና ዮሐንስ እጃቸውን ጫኑባቸው፤+ እነሱም መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ።

18 ስምዖንም ሐዋርያት እጃቸውን የጫኑበት ሰው ሁሉ መንፈስ ቅዱስ እንደሚቀበል አይቶ ገንዘብ እንደሚሰጣቸው ቃል በመግባት 19 “እጄን የምጭንበት ሰው ሁሉ መንፈስ ቅዱስን እንዲቀበል ይህን ሥልጣን ለእኔም ስጡኝ” አላቸው። 20 ጴጥሮስ ግን እንዲህ አለው፦ “የአምላክን ነፃ ስጦታ በገንዘብ ማግኘት እንደምትችል ስላሰብክ የብር ገንዘብህ ከአንተ ጋር ይጥፋ።+ 21 ልብህ በአምላክ ፊት ቀና ስላልሆነ በዚህ አገልግሎት ምንም ዓይነት ድርሻም ሆነ ዕድል ፋንታ የለህም። 22 ስለዚህ ከዚህ ክፋትህ ንስሐ ግባ፤ ምናልባት የልብህ ክፉ ሐሳብ ይቅር ይባልልህ እንደሆነ ይሖዋን* ተማጸን፤ 23 መራራ መርዝና* የክፋት ባሪያ እንደሆንክ አያለሁና።” 24 ስምዖንም መልሶ “ከተናገራችሁት ነገር አንዱም እንዳይደርስብኝ እባካችሁ ይሖዋን* ማልዱልኝ” አላቸው።

25 ጴጥሮስና ዮሐንስ የተሟላ ምሥክርነት ከሰጡና የይሖዋን* ቃል ከተናገሩ በኋላ የሰማርያ ሰዎች በሚኖሩባቸው በርካታ መንደሮች ምሥራቹን እያወጁ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ።+

26 ይሁንና የይሖዋ* መልአክ+ ፊልጶስን “ተነስተህ በደቡብ በኩል ከኢየሩሳሌም ወደ ጋዛ በሚወስደው መንገድ ሂድ” አለው። (ይህ መንገድ የበረሃ መንገድ ነው።) 27 እሱም ተነስቶ ሄደ፤ የኢትዮጵያ ንግሥት የህንደኬ* ባለሥልጣንና የገንዘቧ ሁሉ ኃላፊ የሆነ አንድ ኢትዮጵያዊ ጃንደረባም* አገኘ። ይህ ሰው ለአምልኮ ወደ ኢየሩሳሌም ሄዶ ነበር፤+ 28 እየተመለሰም ሳለ በሠረገላው ውስጥ ተቀምጦ የነቢዩ ኢሳይያስን መጽሐፍ ድምፁን ከፍ አድርጎ ያነብ ነበር። 29 መንፈስም ፊልጶስን “ሂድና ወደዚህ ሠረገላ ቅረብ” አለው። 30 ፊልጶስ ከሠረገላው ጎን እየሮጠ ጃንደረባው የነቢዩ ኢሳይያስን መጽሐፍ ጮክ ብሎ ሲያነብ ሰማና “ለመሆኑ የምታነበውን ትረዳዋለህ?” አለው። 31 እሱም “የሚመራኝ ሰው ሳይኖር እንዴት ልረዳው እችላለሁ?” አለው። ፊልጶስንም ሠረገላው ላይ ወጥቶ አብሮት እንዲቀመጥ ለመነው። 32 ያነበው የነበረው የቅዱስ መጽሐፉ ክፍል የሚከተለው ነበር፦ “እንደ በግ ለመታረድ ተነዳ፤ በሸላቹ ፊት ዝም እንደሚል ጠቦት እሱም አፉን አልከፈተም።+ 33 ውርደት በደረሰበት ወቅት ፍትሕ ተነፈገ።+ ስለ ትውልዱ ማን በዝርዝር ሊናገር ይችላል? ምክንያቱም ሕይወቱ ከምድር ላይ ተወግዷል።”+

34 ጃንደረባውም ፊልጶስን “እባክህ ንገረኝ፣ ነቢዩ ይህን የተናገረው ስለ ማን ነው? ስለ ራሱ ነው ወይስ ስለ ሌላ ሰው?” አለው። 35 ፊልጶስም መናገር ጀመረ፤ ከዚህ ቅዱስ መጽሐፍ አንስቶም ስለ ኢየሱስ የሚገልጸውን ምሥራች ነገረው። 36 እየተጓዙም ሳሉ ውኃ ወዳለበት ቦታ ደረሱ፤ ጃንደረባውም “ውኃ ይኸውና፤ እንዳልጠመቅ የሚከለክለኝ ምን ነገር አለ?” አለው። 37 *—— 38 ከዚያም ሠረገላው እንዲቆም አዘዘ፤ ሁለቱም ወርደው ውኃው ውስጥ ገቡ፤ ፊልጶስም ጃንደረባውን አጠመቀው። 39 ከውኃውም በወጡ ጊዜ፣ የይሖዋ* መንፈስ ወዲያውኑ ፊልጶስን ወሰደው፤ ጃንደረባውም ፊልጶስን ከዚያ በኋላ አላየውም፤ ይሁንና ደስ ብሎት ጉዞውን ቀጠለ። 40 በኋላ ግን ፊልጶስ በአሽዶድ ታየ፤ ቂሳርያም እስኪደርስ ድረስ በሚያልፍበት ክልል በሚገኙ ከተሞች ሁሉ ምሥራቹን ያውጅ ነበር።+

9 ሳኦል ግን አሁንም በጌታ ደቀ መዛሙርት ላይ በመዛትና እነሱን ለመግደል ቆርጦ በመነሳት+ ወደ ሊቀ ካህናቱ ሄደ፤ 2 የጌታን መንገድ የሚከተሉትን+ በዚያ የሚያገኛቸውን ወንዶችና ሴቶች ሁሉ አስሮ ወደ ኢየሩሳሌም ለማምጣት በደማስቆ ለሚገኙ ምኩራቦች ደብዳቤ እንዲጽፍለት ጠየቀው።

3 እየተጓዘም ሳለ ወደ ደማስቆ ሲቃረብ ድንገት ከሰማይ የመጣ ብርሃን በዙሪያው አንጸባረቀ፤+ 4 እሱም መሬት ላይ ወደቀ፤ ከዚያም “ሳኦል፣ ሳኦል ለምን ታሳድደኛለህ?” የሚል ድምፅ ሰማ። 5 ሳኦልም “ጌታዬ፣ አንተ ማን ነህ?” ሲል ጠየቀው። እሱም እንዲህ አለው፦ “እኔ አንተ የምታሳድደኝ+ ኢየሱስ ነኝ።+ 6 አሁን ተነስተህ ወደ ከተማዋ ግባ፤ ምን ማድረግ እንዳለብህም ይነገርሃል።” 7 አብረው እየተጓዙ የነበሩትም ሰዎች ድምፅ የሰሙ ቢሆንም ማንንም ባለማየታቸው የሚናገሩት ጠፍቷቸው ዝም ብለው ቆሙ።+ 8 ሳኦልም ከወደቀበት ተነሳ፤ ዓይኖቹ ቢገለጡም ምንም ነገር ማየት አልቻለም። በመሆኑም እጁን ይዘው እየመሩ ወደ ደማስቆ ወሰዱት። 9 ለሦስት ቀንም ምንም ሳያይ+ እንዲሁም ሳይበላና ሳይጠጣ ቆየ።

10 በደማስቆ ሐናንያ የሚባል አንድ ደቀ መዝሙር ነበር፤+ ጌታም በራእይ “ሐናንያ!” አለው። እሱም “ጌታ ሆይ፣ እነሆኝ” አለ። 11 ጌታም እንዲህ አለው፦ “ተነስተህ ‘ቀጥተኛ’ ወደተባለው መንገድ ሂድ፤ በይሁዳም ቤት ሳኦል የሚባለውን የጠርሴስ ሰው+ ፈልግ። እሱም አሁን እየጸለየ ነው፤ 12 ሐናንያ የሚባል ሰው እንደሚመጣና ዓይኑ ይበራለት ዘንድ እጁን እንደሚጭንበት በራእይ አይቷል።”+ 13 ሐናንያ ግን እንዲህ ሲል መለሰ፦ “ጌታ ሆይ፣ ይህ ሰው በኢየሩሳሌም ባሉ ቅዱሳን አገልጋዮችህ ላይ ምን ያህል ጉዳት እንዳደረሰ ከብዙዎች ሰምቻለሁ። 14 ወደዚህ ስፍራ የመጣው ስምህን የሚጠሩትን ሁሉ ለማሰር ከካህናት አለቆች ሥልጣን ተሰጥቶት ነው።”+ 15 ጌታ ግን እንዲህ አለው፦ “ይህ ሰው በአሕዛብ እንዲሁም በነገሥታትና በእስራኤል ልጆች ፊት ስሜን እንዲሸከም+ ለእኔ የተመረጠ ዕቃ+ ስለሆነ ወደ እሱ ሂድ። 16 እኔም ስለ ስሜ ሲል ምን ያህል መከራ መቀበል እንዳለበት በግልጽ አሳየዋለሁ።”+

17 ስለዚህ ሐናንያ ሄደ፤ ወደተባለውም ቤት ገባ፤ እጁንም በላዩ ጭኖ እንዲህ አለው፦ “ወንድሜ ሳኦል፣ ወደዚህ ስትመጣ መንገድ ላይ የተገለጠልህ ጌታ ኢየሱስ የዓይንህ ብርሃን እንዲመለስልህና በመንፈስ ቅዱስ እንድትሞላ እኔን ልኮኛል።”+ 18 ወዲያውም ከዓይኖቹ ላይ ቅርፊት የሚመስሉ ነገሮች ወደቁ፤ እሱም እንደገና ማየት ቻለ። ከዚያም ተነስቶ ተጠመቀ፤ 19 እንዲሁም ምግብ በልቶ ብርታት አገኘ።

በደማስቆ ካሉ ደቀ መዛሙርት ጋር የተወሰኑ ቀናት ቆየ፤+ 20 ወዲያውም ስለ ኢየሱስ እሱ የአምላክ ልጅ እንደሆነ በምኩራቦቹ ውስጥ መስበክ ጀመረ። 21 የሰሙት ሁሉ ግን እጅግ በመደነቅ እንዲህ ይሉ ነበር፦ “ይህ ሰው በኢየሩሳሌም ይህን ስም የሚጠሩትን ሲያጠፋ የነበረው አይደለም?+ ወደዚህስ የመጣው እነሱን እያሰረ ለካህናት አለቆች ለማስረከብ አልነበረም?”+ 22 ሳኦል ግን ይበልጥ እየበረታ ሄደ፤ በደማስቆ የሚኖሩ አይሁዶችን ኢየሱስ እሱ ክርስቶስ እንደሆነ አሳማኝ ማስረጃ እያቀረበ አፋቸውን ያስይዛቸው ነበር።+

23 በርካታ ቀናት ካለፉ በኋላ አይሁዳውያን እሱን ለመግደል አሴሩ።+ 24 ይሁን እንጂ ሳኦል ሴራቸውን አወቀ። እነሱም ሊገድሉት ስለፈለጉ ቀን ከሌት የከተማዋን በሮች ነቅተው ይጠብቁ ነበር። 25 ስለዚህ የእሱ ደቀ መዛሙርት ሳኦልን ወስደው በሌሊት በከተማዋ ቅጥር ላይ ባለ መስኮት በማሾለክ በቅርጫት አወረዱት።+

26 ኢየሩሳሌም በደረሰ ጊዜ+ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ለመቀላቀል ጥረት አደረገ፤ እነሱ ግን ደቀ መዝሙር መሆኑን ስላላመኑ ሁሉም ፈሩት። 27 ስለዚህ በርናባስ+ ረዳው፤ ሳኦልንም ወደ ሐዋርያት ወስዶ በመንገድ ላይ ጌታን እንዴት እንዳየውና+ እሱም እንዴት እንዳናገረው እንዲሁም በደማስቆ በኢየሱስ ስም እንዴት በድፍረት እንደተናገረ በዝርዝር ነገራቸው።+ 28 እሱም በኢየሩሳሌም በነፃነት እየተንቀሳቀሰና በጌታ ስም በድፍረት እየተናገረ አብሯቸው ቆየ። 29 ግሪክኛ ተናጋሪ ከሆኑ አይሁዳውያን ጋር ይነጋገርና ይከራከር ነበር፤ እነሱ ግን ሊገድሉት ሞከሩ።+ 30 ወንድሞች ይህን ሲያውቁ ወደ ቂሳርያ ይዘውት ወረዱ፤ ከዚያም ወደ ጠርሴስ ላኩት።+

31 በዚያ ወቅት በይሁዳ፣ በገሊላና በሰማርያ ያለው ጉባኤ+ ሁሉ ሰላም አገኘ፤ በእምነትም እየጠነከረ ሄደ፤ መላው ጉባኤ ይሖዋን* በመፍራትና መንፈስ ቅዱስ ከሚሰጠው ማጽናኛ+ ጋር በመስማማት ይኖር ስለነበር በቁጥር እየበዛ ሄደ።

32 ጴጥሮስም በየቦታው እየተዘዋወረ በነበረበት ወቅት በልዳ ወደሚኖሩት ቅዱሳን ደግሞ ወረደ።+ 33 በዚያም ሽባ በመሆኑ የተነሳ ለስምንት ዓመት የአልጋ ቁራኛ የሆነ ኤንያስ የተባለ አንድ ሰው አገኘ። 34 ጴጥሮስም “ኤንያስ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ይፈውስሃል።+ ተነሳና አልጋህን አንጥፍ” አለው።+ እሱም ወዲያውኑ ተነሳ። 35 በልዳ እና በሳሮን ሜዳ የሚኖሩ ሁሉ እሱን አይተው በጌታ አመኑ።

36 በኢዮጴ ጣቢታ የምትባል አንዲት ደቀ መዝሙር ነበረች፤ የስሟም ትርጉም “ዶርቃ”* ማለት ነው። እሷም መልካም በማድረግና ምጽዋት በመስጠት የምትታወቅ ነበረች። 37 በዚያን ጊዜም ታማ ሞተች። ሰዎችም አጠቧትና በደርብ ላይ በሚገኘው ክፍል ውስጥ አስቀመጧት። 38 ልዳ ለኢዮጴ ቅርብ ስለነበረች ደቀ መዛሙርቱ ጴጥሮስ በዚያች ከተማ እንዳለ ሲሰሙ “እባክህ ፈጥነህ ወደ እኛ ና” ብለው እንዲለምኑት ሁለት ሰዎች ወደ እሱ ላኩ። 39 በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ ተነስቶ አብሯቸው ሄደ። እዚያም ሲደርስ ደርብ ላይ ወደሚገኘው ክፍል ይዘውት ወጡ፤ መበለቶቹም ሁሉ በዙሪያው ቆመው እያለቀሱ ዶርቃ ከእነሱ ጋር በነበረችበት ጊዜ የሠራቻቸውን በርካታ ልብሶችና ቀሚሶች* ያሳዩት ነበር። 40 ጴጥሮስም ሁሉም እንዲወጡ ካደረገ በኋላ+ ተንበርክኮ ጸለየ። ከዚያም ወደ አስከሬኑ ዞር ብሎ “ጣቢታ፣ ተነሽ!” አለ። እሷም ዓይኖቿን ገለጠች፤ ጴጥሮስንም ባየች ጊዜ ቀና ብላ ተቀመጠች።+ 41 እሱም እጇን ይዞ አስነሳት፤ ቅዱሳኑንና መበለቶቹንም ጠርቶ ሕያው መሆኗን አሳያቸው።+ 42 ይህ ነገር በመላው ኢዮጴ ታወቀ፤ ብዙዎችም በጌታ አመኑ።+ 43 ጴጥሮስም በኢዮጴ ስምዖን በተባለ አንድ ቆዳ ፋቂ ቤት ለበርካታ ቀናት ተቀመጠ።+

10 በቂሳርያ “የጣሊያን ክፍለ ጦር”* ተብሎ በሚጠራ ሠራዊት ውስጥ ቆርኔሌዎስ የሚባል አንድ የጦር መኮንን* ነበር። 2 እሱም ከመላው ቤተሰቡ ጋር ለአምላክ ያደረና ፈሪሃ አምላክ የነበረው ሰው ሲሆን ለሰዎች ምጽዋት የሚሰጥና ዘወትር ወደ አምላክ የሚማልድ ሰው ነበር። 3 ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት+ ገደማ አንድ የአምላክ መልአክ ወደ እሱ ሲመጣ በራእይ በግልጽ አየ፤ መልአኩም “ቆርኔሌዎስ!” አለው። 4 ቆርኔሌዎስም በድንጋጤ ትኩር ብሎ እያየው “ጌታ ሆይ፣ ምንድን ነው?” በማለት ጠየቀው። እሱም እንዲህ አለው፦ “ጸሎትህና ምጽዋትህ በአምላክ ፊት መታሰቢያ እንዲሆን አርጓል።+ 5 ስለዚህ አሁን ወደ ኢዮጴ ሰዎች ልከህ ጴጥሮስ ተብሎ የሚጠራውን ስምዖንን አስጠራው። 6 ይህ ሰው፣ ቤቱ በባሕሩ አጠገብ በሚገኘው በቆዳ ፋቂው በስምዖን ቤት በእንግድነት አርፏል።” 7 ያነጋገረው መልአክ ተለይቶት እንደሄደ ከአገልጋዮቹ ሁለቱን እንዲሁም እሱን በቅርብ ከሚያገለግሉት ወታደሮች መካከል ለአምላክ ያደረ አንድ ወታደር ጠራ፤ 8 የሆነውንም ነገር ሁሉ ከነገራቸው በኋላ ወደ ኢዮጴ ላካቸው።

9 በማግስቱም የተላኩት ሰዎች ተጉዘው ወደ ከተማዋ ሲቃረቡ ጴጥሮስ ከቀኑ ስድስት ሰዓት ገደማ ሊጸልይ ወደ ሰገነት ወጣ። 10 ይሁን እንጂ በጣም ከመራቡ የተነሳ መብላት ፈለገ። ምግብ እየተዘጋጀ ሳለም ሰመመን ውስጥ ገባ፤+ 11 ሰማይም ተከፍቶ ትልቅ ጨርቅ የሚመስል ነገር በአራቱም ጫፍ ተይዞ ወደ ምድር ሲወርድ አየ፤ 12 በላዩም የተለያዩ በምድር ላይ የሚኖሩ አራት እግር ያላቸው እንስሳትና በምድር ላይ የሚሳቡ ፍጥረታት እንዲሁም የሰማይ ወፎች ነበሩ። 13 ከዚያም አንድ ድምፅ “ጴጥሮስ፣ ተነሳና አርደህ ብላ!” አለው። 14 ጴጥሮስ ግን “ጌታ ሆይ፣ በጭራሽ፤ ምክንያቱም እኔ ንጹሕ ያልሆነና የረከሰ ነገር በልቼ አላውቅም” አለ።+ 15 ያም ድምፅ እንደገና ለሁለተኛ ጊዜ “አምላክ ንጹሕ ያደረገውን ነገር ርኩስ ነው ማለትህን ተው” አለው። 16 ይህም ለሦስተኛ ጊዜ ተደገመ፤ ወዲያውኑም ጨርቅ የሚመስለው ነገር ወደ ሰማይ ተወሰደ።

17 ጴጥሮስ ‘የራእዩ ትርጉም ምን ይሆን’ በማለት በጣም ግራ ተጋብቶ እያለ ቆርኔሌዎስ የላካቸው ሰዎች የስምዖንን ቤት አጠያይቀው መጡና የውጭው በር ላይ ቆሙ።+ 18 ከዚያም ተጣርተው ጴጥሮስ ተብሎ የሚጠራው ስምዖን በዚያ በእንግድነት አርፎ እንደሆነ ጠየቁ። 19 ጴጥሮስ ያየውን ራእይ በሐሳቡ እያወጣና እያወረደ ሳለ መንፈስ+ እንዲህ አለው፦ “እነሆ፣ ሦስት ሰዎች ይፈልጉሃል። 20 ስለዚህ ተነስተህ ወደ ታች ውረድ፤ የላክኋቸው እኔ ስለሆንኩ ምንም ሳትጠራጠር አብረሃቸው ሂድ።” 21 ጴጥሮስም ሰዎቹ ወዳሉበት ወርዶ “የምትፈልጉት ሰው እኔ ነኝ። ወደዚህ የመጣችሁት ለምንድን ነው?” አላቸው። 22 እነሱም እንዲህ አሉ፦ “በአይሁዳውያን ሁሉ የተመሠከረለት ቆርኔሌዎስ+ የተባለ ጻድቅና አምላክን የሚፈራ አንድ የጦር መኮንን፣ ወደ አንተ መልእክተኞች ልኮ ወደ ቤቱ እንዲያስመጣህና የምትለውን ነገር እንዲሰማ አንድ ቅዱስ መልአክ መለኮታዊ መመሪያ ሰጥቶታል።” 23 እሱም ወደ ቤት አስገብቶ አስተናገዳቸው።

በማግስቱም ተነስቶ ከእነሱ ጋር ሄደ፤ በኢዮጴ ያሉ አንዳንድ ወንድሞችም አብረውት ሄዱ። 24 በሚቀጥለው ቀንም ወደ ቂሳርያ ገባ። ቆርኔሌዎስም ዘመዶቹንና የቅርብ ወዳጆቹን ሰብስቦ እየጠበቃቸው ነበር። 25 ጴጥሮስም በገባ ጊዜ ቆርኔሌዎስ ተቀበለውና እግሩ ላይ ወድቆ ሰገደለት።* 26 ጴጥሮስ ግን “ተነስ፣ እኔም እንደ አንተው ሰው ነኝ” ብሎ አስነሳው።+ 27 ከእሱ ጋር እየተነጋገረ ወደ ውስጥ ሲገባም ብዙ ሰዎች ተሰብስበው አገኘ። 28 እሱም እንዲህ አላቸው፦ “አንድ አይሁዳዊ ከሌላ ዘር ጋር ይወዳጅ ወይም ይቀራረብ ዘንድ ሕጉ እንደማይፈቅድ በሚገባ ታውቃላችሁ፤+ ሆኖም አምላክ ማንንም ሰው ንጹሕ ያልሆነ ወይም ርኩስ ማለት እንደማይገባኝ ገልጦልኛል።+ 29 በመሆኑም በተጠራሁ ጊዜ ምንም ሳላንገራግር መጣሁ። ስለዚህ ለምን እንዳስጠራችሁኝ ማወቅ እፈልጋለሁ።”

30 ቆርኔሌዎስም እንዲህ አለ፦ “ከአራት ቀን በፊት በዚሁ ሰዓት ይኸውም ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ላይ በቤቴ ሆኜ እየጸለይኩ ሳለ የሚያንጸባርቅ ልብስ የለበሰ ሰው ድንገት ፊቴ ቆሞ 31 እንዲህ አለኝ፦ ‘ቆርኔሌዎስ፣ ጸሎትህ ተሰምቶልሃል፤ ምጽዋትህም በአምላክ ፊት ታስቦልሃል። 32 ስለዚህ ወደ ኢዮጴ ሰዎች ልከህ ጴጥሮስ ተብሎ የሚጠራውን ስምዖንን አስጠራው። ይህ ሰው፣ ቤቱ በባሕሩ አጠገብ በሚገኘው በቆዳ ፋቂው በስምዖን ቤት በእንግድነት አርፏል።’+ 33 እኔም ወዲያውኑ ሰዎች ላክሁብህ፤ አንተም በመምጣትህ መልካም አድርገሃል። ስለዚህ አሁን እኛ ይሖዋ* እንድትናገር ያዘዘህን ነገር ሁሉ ለመስማት ይኸው ሁላችንም በአምላክ ፊት ተገኝተናል።”

34 በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ እንዲህ ሲል መናገር ጀመረ፦ “እነሆ፣ አምላክ እንደማያዳላ በእርግጥ አስተዋልኩ፤+ 35 ከዚህ ይልቅ ከየትኛውም ብሔር ቢሆን እሱን የሚፈራና ትክክል የሆነውን ነገር የሚያደርግ ሰው በእሱ ዘንድ ተቀባይነት አለው።+ 36 አምላክ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ለእስራኤል ልጆች የሰላም ምሥራች ለማወጅ ቃሉን ላከላቸው፤+ ይህም ምሥራች ኢየሱስ የሁሉ ጌታ+ እንደሆነ የሚገልጽ ነው። 37 ዮሐንስ ስለ ጥምቀት ከሰበከ በኋላ ከገሊላ አንስቶ በመላው ይሁዳ ይወራ ስለነበረው ጉዳይ ታውቃላችሁ፤+ 38 የተወራውም ስለ ናዝሬቱ ኢየሱስ ነው። አምላክ በመንፈስ ቅዱስ ቀባው፤+ ደግሞም ኃይል ሰጠው፤ ኢየሱስም አምላክ ከእሱ ጋር ስለነበር መልካም ነገር እያደረገና+ በዲያብሎስ ቁጥጥር ሥር የወደቁትን እየፈወሰ+ በዚያ አገር ሁሉ ተዘዋወረ። 39 እሱ በአይሁዳውያን አገርም ሆነ በኢየሩሳሌም ላደረጋቸው ነገሮች ሁሉ እኛ ምሥክሮች ነን፤ እነሱ ግን በእንጨት* ላይ ሰቅለው ገደሉት። 40 አምላክ እሱን በሦስተኛው ቀን አስነሳው፤+ ከዚያም ለሰዎች እንዲገለጥ* አደረገው፤ 41 የተገለጠው ግን ለሁሉም ሰው ሳይሆን አምላክ አስቀድሞ ለመረጣቸው ምሥክሮች ይኸውም ከሞት ከተነሳ በኋላ አብረነው ለበላንና ለጠጣን ለእኛ ነው።+ 42 በተጨማሪም አምላክ እሱን በሕያዋንና በሙታን ላይ ፈራጅ አድርጎ እንደሾመው+ ለሰዎች እንድንሰብክና በተሟላ ሁኔታ* እንድንመሠክር አዘዘን።+ 43 በእሱ የሚያምን ሁሉ በስሙ የኃጢአት ይቅርታ እንደሚያገኝ+ ነቢያት ሁሉ ስለ እሱ ይመሠክራሉ።”+

44 ጴጥሮስ ስለዚህ ጉዳይ ገና እየተናገረ ሳለ ቃሉን እየሰሙ በነበሩት ሁሉ ላይ መንፈስ ቅዱስ ወረደ።+ 45 ከጴጥሮስ ጋር የመጡት የተገረዙ አማኞች* የመንፈስ ቅዱስ ነፃ ስጦታ ከአሕዛብ ወገን በሆኑ ሰዎችም ላይ በመፍሰሱ ተገረሙ። 46 ምክንያቱም በባዕድ ቋንቋዎች* ሲናገሩና አምላክን ሲያወድሱ ይሰሟቸው ነበር።+ በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ እንዲህ አለ፦ 47 “እንደ እኛው መንፈስ ቅዱስ የተቀበሉትን እነዚህን ሰዎች በውኃ እንዳይጠመቁ ሊከለክላቸው የሚችል አለ?”+ 48 ይህን ካለ በኋላ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እንዲጠመቁ አዘዛቸው።+ ከዚያም የተወሰነ ቀን አብሯቸው እንዲቆይ ለመኑት።

11 በይሁዳ የነበሩት ሐዋርያትና ወንድሞች፣ አሕዛብም የአምላክን ቃል እንደተቀበሉ ሰሙ። 2 ስለዚህ ጴጥሮስ ወደ ኢየሩሳሌም በወጣ ጊዜ ግርዘትን የሚደግፉ ሰዎች+ ይተቹት* ጀመር፤ 3 “ወዳልተገረዙ ሰዎች ቤት ሄደህ ከእነሱ ጋር በልተሃል” አሉት። 4 በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ እንዲህ ሲል ጉዳዩን በዝርዝር አብራራላቸው፦

5 “በኢዮጴ ከተማ እየጸለይኩ ሳለ ሰመመን ውስጥ ሆኜ ራእይ አየሁ፤ አንድ ትልቅ ጨርቅ የሚመስል ነገር በአራቱም ጫፍ ተይዞ ከሰማይ ወረደና ወደ እኔ መጣ።+ 6 ይህን ነገር ትኩር ብዬ ስመለከት አራት እግር ያላቸው የምድር እንስሳት፣ የዱር አራዊት፣ በምድር ላይ የሚሳቡ ፍጥረታትና የሰማይ ወፎች አየሁ። 7 በተጨማሪም አንድ ድምፅ ‘ጴጥሮስ፣ ተነሳና አርደህ ብላ!’ ሲለኝ ሰማሁ። 8 እኔ ግን ‘ጌታ ሆይ፣ በጭራሽ፤ ምክንያቱም ንጹሕ ያልሆነ ወይም የረከሰ ነገር ወደ አፌ ገብቶ አያውቅም’ አልኩ። 9 ለሁለተኛ ጊዜ ከሰማይ የመጣው ድምፅ ‘አምላክ ንጹሕ ያደረገውን ነገር ርኩስ ነው ማለትህን ተው’ ሲል መለሰልኝ። 10 ይህም ለሦስተኛ ጊዜ ተደገመ፤ ከዚያም ሁሉም ነገር እንደገና ወደ ሰማይ ተወሰደ። 11 ልክ በዚያው ሰዓት ደግሞ ከቂሳርያ ወደ እኔ የተላኩ ሦስት ሰዎች እኛ ወደነበርንበት ቤት ደረሱ።+ 12 በዚህ ጊዜ መንፈስ፣ ምንም ሳልጠራጠር አብሬያቸው እንድሄድ ነገረኝ። እነዚህ ስድስት ወንድሞችም አብረውኝ ሄዱ፤ ወደ ሰውየውም ቤት ገባን።

13 “እሱም በቤቱ ውስጥ መልአክ ቆሞ እንዳየና እንዲህ እንዳለው ነገረን፦ ‘ወደ ኢዮጴ ሰዎች ልከህ ጴጥሮስ ተብሎ የሚጠራውን ስምዖንን አስጠራ፤+ 14 እሱም አንተና መላው ቤተሰብህ መዳን ልታገኙ የምትችሉበትን ነገር ሁሉ ይነግርሃል።’ 15 እኔም መናገር ስጀምር መንፈስ ቅዱስ በመጀመሪያ በእኛ ላይ እንደወረደው ሁሉ በእነሱም ላይ ወረደ።+ 16 በዚህ ጊዜ፣ ‘ዮሐንስ በውኃ አጠመቀ፤+ እናንተ ግን በመንፈስ ቅዱስ ትጠመቃላችሁ’+ እያለ ጌታ ይናገር የነበረውን ቃል አስታወስኩ። 17 እንግዲህ አምላክ በጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ላመንነው ለእኛ የሰጠውን ያንኑ ነፃ ስጦታ ለእነሱም ከሰጠ፣ ታዲያ አምላክን መከልከል* የምችል እኔ ማን ነኝ?”+

18 እነሱም ይህን በሰሙ ጊዜ መቃወማቸውን ተዉ፤* ደግሞም “እንዲህ ከሆነማ አምላክ አሕዛብም ሕይወት ማግኘት እንዲችሉ ንስሐ የሚገቡበት አጋጣሚ ሰጥቷቸዋል ማለት ነው” እያሉ አምላክን አከበሩ።+

19 ከእስጢፋኖስ ሞት በኋላ በተቀሰቀሰው ስደት የተነሳ የተበተኑት ደቀ መዛሙርት+ እስከ ፊንቄ፣ ቆጵሮስና አንጾኪያ ድረስ ሄዱ፤ ቃሉን ይናገሩ የነበረው ግን ለአይሁዳውያን ብቻ ነበር።+ 20 ይሁን እንጂ ከእነሱ መካከል የቆጵሮስና የቀሬና ሰዎች የሆኑ አንዳንዶች ወደ አንጾኪያ መጥተው ግሪክኛ ተናጋሪ የሆኑ ሰዎችን በማነጋገር የጌታ ኢየሱስን ምሥራች ይሰብኩላቸው ጀመር። 21 የይሖዋም* እጅ ከእነሱ ጋር ነበር፤ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎችም አማኝ በመሆን ጌታን መከተል ጀመሩ።+

22 በኢየሩሳሌም የሚገኘው ጉባኤ ስለ እነሱ የሚገልጸው ወሬ ደረሰው፤ በዚህ ጊዜ በርናባስን+ ወደ አንጾኪያ ላኩት። 23 እሱም እዚያ ደርሶ አምላክ ለደቀ መዛሙርቱ ያሳየውን ጸጋ ባስተዋለ ጊዜ በጣም ተደሰተ፤ ሁሉም በጽኑ ልብ ለጌታ ታማኞች ሆነው እንዲቀጥሉም አበረታታቸው፤+ 24 በርናባስ መንፈስ ቅዱስ የሞላበትና ጠንካራ እምነት ያለው ጥሩ ሰው ነበር። ብዙ ቁጥር ያላቸው ሰዎችም በጌታ አመኑ።+ 25 በመሆኑም ሳኦልን ፈልጎ ለማግኘት ወደ ጠርሴስ ሄደ።+ 26 ካገኘውም በኋላ ወደ አንጾኪያ አመጣው። ከዚያም አንድ ዓመት ሙሉ ከእነሱ ጋር በጉባኤ አብረው እየተሰበሰቡ ብዙ ሕዝብ አስተማሩ፤ ደቀ መዛሙርቱም በመለኮታዊ አመራር ለመጀመሪያ ጊዜ ‘ክርስቲያኖች’ ተብለው የተጠሩት+ በአንጾኪያ ነበር።

27 በዚያን ጊዜ ነቢያት+ ከኢየሩሳሌም ወደ አንጾኪያ ወረዱ። 28 ከእነሱም መካከል አጋቦስ+ የተባለው ተነስቶ በምድሪቱ ሁሉ ታላቅ ረሃብ እንደሚከሰት መንፈስ አነሳስቶት ትንቢት ተናገረ፤+ ይህም በቀላውዴዎስ ዘመን ተፈጸመ። 29 ስለዚህ ደቀ መዛሙርቱ እያንዳንዳቸው አቅማቸው በፈቀደ መጠን+ አዋጥተው በይሁዳ ለሚኖሩ ወንድሞች እርዳታ ለመላክ ወሰኑ፤+ 30 እርዳታውንም በበርናባስና በሳኦል እጅ ለሽማግሌዎቹ ላኩ።+

12 በዚያን ጊዜ ንጉሡ ሄሮድስ በአንዳንድ የጉባኤው አባላት ላይ ስደት ማድረስ ጀመረ።+ 2 የዮሐንስን ወንድም ያዕቆብን+ በሰይፍ ገደለው።+ 3 ይህ ድርጊቱ አይሁዳውያንን እንዳስደሰተ ባየ ጊዜ ጴጥሮስን ደግሞ በቁጥጥር ሥር አዋለው። (ይህም የሆነው በቂጣ* በዓል ሰሞን ነበር።)+ 4 ከያዘውና እስር ቤት ካስገባው+ በኋላ በአራት ፈረቃ፣ አራት አራት ሆነው እንዲጠብቁት ለተመደቡ ወታደሮች አስረከበው፤ ይህን ያደረገው ከፋሲካ* በኋላ ሕዝቡ ፊት ሊያቀርበው* አስቦ ነው። 5 ስለዚህ ጴጥሮስ እስር ቤት እንዲቆይ ተደረገ፤ ሆኖም ጉባኤው ስለ እሱ ወደ አምላክ አጥብቆ ይጸልይ ነበር።+

6 ሄሮድስ ጴጥሮስን ሕዝቡ ፊት ሊያቀርበው ካሰበበት ቀን በፊት በነበረው ሌሊት፣ ጴጥሮስ በሁለት ወታደሮች መካከል በሁለት ሰንሰለቶች ታስሮ ተኝቶ ነበር፤ በር ላይ ያሉ ጠባቂዎችም እስር ቤቱን እየጠበቁ ነበር። 7 ይሁንና የይሖዋ* መልአክ ድንገት መጥቶ ቆመ፤+ በክፍሉም ውስጥ ብርሃን በራ። ጴጥሮስን ጎኑን መታ አድርጎ ከእንቅልፉ ቀሰቀሰውና “ቶሎ ብለህ ተነሳ!” አለው። ሰንሰለቶቹም ከእጆቹ ላይ ወደቁ።+ 8 መልአኩም “በል ልብስህን ልበስ፤* ጫማህንም አድርግ” አለው። እሱም እንደተባለው አደረገ። ከዚያም “መደረቢያህን ልበስና ተከተለኝ” አለው። 9 እሱም ወጥቶ ይከተለው ጀመር፤ ይሁንና መልአኩ እያደረገ ያለው ነገር በእውን እየተከናወነ ያለ አልመሰለውም። እንዲያውም ራእይ የሚያይ መስሎት ነበር። 10 የመጀመሪያውንና ሁለተኛውን ዘብ አልፈው ከእስር ቤቱ ወደ ከተማዋ ወደሚያስወጣው የብረት መዝጊያ ደረሱ፤ መዝጊያውም በራሱ ተከፈተላቸው። ከወጡ በኋላ በአንድ ጎዳና አብረው ተጓዙ፤ ወዲያውም መልአኩ ተለይቶት ሄደ። 11 ጴጥሮስም የሆነውን ነገር ሲረዳ “ይሖዋ* መልአኩን ልኮ ከሄሮድስ እጅና አይሁዳውያን በእኔ ላይ ይደርሳል ብለው ካሰቡት ነገር ሁሉ እንደታደገኝ አሁን በእርግጥ አወቅኩ” አለ።+

12 ይህን ከተገነዘበ በኋላ ማርቆስ ተብሎ ወደሚጠራው ወደ ዮሐንስ+ እናት ወደ ማርያም ቤት ሄደ፤ በዚያም በርከት ያሉ ሰዎች ተሰብስበው ይጸልዩ ነበር። 13 የውጭውን በር ሲያንኳኳ ሮዳ የተባለች አንዲት አገልጋይ በሩን ለመክፈት መጣች። 14 የጴጥሮስ ድምፅ መሆኑን ባወቀች ጊዜ በጣም ከመደሰቷ የተነሳ በሩን ሳትከፍት ሮጣ ወደ ውስጥ በመግባት ጴጥሮስ በር ላይ መቆሙን ተናገረች። 15 እነሱም “አብደሻል እንዴ!” አሏት። እሷ ግን ያንኑ አስረግጣ መናገሯን ቀጠለች። እነሱም “ከሆነም የእሱ መልአክ ይሆናል” አሉ። 16 ጴጥሮስ ግን እዚያው ቆሞ ማንኳኳቱን ቀጠለ። በሩን ከከፈቱም በኋላ ሲያዩት በጣም ተገረሙ። 17 እሱ ግን ዝም እንዲሉ በእጁ ምልክት ከሰጣቸው በኋላ ይሖዋ* ከእስር ቤት እንዴት እንዳወጣው በዝርዝር ነገራቸው፤ ከዚያም “ይህን ነገር ለያዕቆብና+ ለወንድሞች ንገሯቸው” አላቸው። ይህን ካለም በኋላ ወጥቶ ወደ ሌላ ቦታ ሄደ።

18 በነጋም ጊዜ ወታደሮቹ ጴጥሮስ የት እንደደረሰ ግራ ስለተጋቡ በመካከላቸው ከፍተኛ ትርምስ ተፈጠረ። 19 ሄሮድስም ፈልጎ አፈላልጎ ባጣው ጊዜ ጠባቂዎቹን ከመረመረ በኋላ እርምጃ እንዲወሰድባቸው አዘዘ፤+ ከዚያም ከይሁዳ ወደ ቂሳርያ ወርዶ በዚያ የተወሰነ ጊዜ ተቀመጠ።

20 ሄሮድስ በጢሮስና በሲዶና ሰዎች ላይ በጣም ተቆጥቶ* ነበር። እነሱም በአንድ ልብ ሆነው ወደ እሱ በመምጣት የንጉሡ ባለሟል* የሆነውን ብላስጦስን ካግባቡ በኋላ ንጉሡን እርቅ ጠየቁ፤ ይህን ያደረጉት አገራቸው ምግብ የምታገኘው ከንጉሡ ግዛት ስለነበረ ነው። 21 አንድ ልዩ ዝግጅት በተደረገበት ቀን ሄሮድስ ልብሰ መንግሥቱን ለብሶ በፍርድ ወንበር ላይ ተቀመጠ፤ ከዚያም ለሕዝቡ ንግግር መስጠት ጀመረ። 22 የተሰበሰበውም ሕዝብ “ይህ የአምላክ ድምፅ ነው እንጂ የሰው አይደለም!” እያለ ይጮኽ ጀመር። 23 በዚህ ጊዜ፣ ለአምላክ ክብር ባለመስጠቱ ወዲያውኑ የይሖዋ* መልአክ ቀሰፈው፤ በትል ተበልቶም ሞተ።

24 የይሖዋ* ቃል ግን እየተስፋፋ ሄደ፤ ብዙ ሰዎችም አማኞች ሆኑ።+

25 በርናባስና+ ሳኦልም በኢየሩሳሌም እርዳታ ከሰጡ በኋላ ተመለሱ፤+ ማርቆስ ተብሎ የሚጠራውን ዮሐንስንም ይዘውት መጡ።+

13 በአንጾኪያ ባለው ጉባኤ ውስጥ ነቢያትና አስተማሪዎች ነበሩ፤+ እነሱም፦ በርናባስ፣ ኒጌር ማለትም ጥቁር ተብሎ የሚጠራው ሲምዖን፣ የቀሬናው ሉክዮስ፣ የአውራጃ ገዢ ከሆነው ከሄሮድስ ጋር የተማረው ምናሔና ሳኦል ናቸው። 2 እነዚህ ይሖዋን* እያገለገሉና* እየጾሙ ሳሉ መንፈስ ቅዱስ “በርናባስንና ሳኦልን አንድ ሥራ እንዲሠሩ ስለመረጥኳቸው ለዩልኝ”+ አለ። 3 እነሱም ከጾሙና ከጸለዩ በኋላ እጃቸውን ጫኑባቸው፤ ከዚያም አሰናበቷቸው።

4 ሰዎቹም በመንፈስ ቅዱስ ተልከው ወደ ሴሌውቅያ ወረዱ፤ ከዚያም በመርከብ ወደ ቆጵሮስ ደሴት ተጓዙ። 5 ስልማና በደረሱ ጊዜም የአምላክን ቃል በአይሁዳውያን ምኩራቦች ማወጅ ጀመሩ። ዮሐንስም እንደ አገልጋይ ሆኖ ይረዳቸው ነበር።+

6 ደሴቲቱን ከዳር እስከ ዳር አዳርሰው እስከ ጳፎስ ተጓዙ፤ በዚህ ጊዜ በርያሱስ የተባለ ጠንቋይና ሐሰተኛ ነቢይ የነበረ አንድ አይሁዳዊ አገኙ። 7 እሱም ሰርግዮስ ጳውሎስ ከተባለው አስተዋይ የሮም አገረ ገዢ* ጋር ነበር። ይህ አገረ ገዢ የአምላክን ቃል ለመስማት ስለጓጓ በርናባስንና ሳኦልን ጠራቸው። 8 ይሁን እንጂ ጠንቋዩ ኤልማስ* አገረ ገዢው ይህን እምነት እንዳይቀበል ለማከላከል ፈልጎ ይቃወማቸው ጀመር። (ኤልማስ የተባለው ስም ትርጉም ጠንቋይ ማለት ነው።) 9 በዚህ ጊዜ፣ ጳውሎስ ተብሎ የሚጠራው ሳኦል በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ ትኩር ብሎ ተመለከተው፤ 10 ከዚያም እንዲህ አለው፦ “አንተ ተንኮልና ክፋት ሁሉ የሞላብህ፣ የዲያብሎስ ልጅ፣+ የጽድቅም ሁሉ ጠላት! ቀና የሆነውን የይሖዋን* መንገድ ማጣመምህን አትተውም? 11 እነሆ፣ የይሖዋ* እጅ በአንተ ላይ ነው፤ ዓይነ ስውር ትሆናለህ፤ ለተወሰነ ጊዜም የፀሐይ ብርሃን አታይም።” ወዲያውኑም ጭጋግና ጨለማ ዓይኑን ጋረደው፤ እጁን ይዞ የሚመራው ሰው ለማግኘትም ዙሪያውን መፈለግ ጀመረ። 12 አገረ ገዢውም ስለ ይሖዋ* በተማረው ነገር ተደንቆ ስለነበር ይህን ባየ ጊዜ አማኝ ሆነ።

13 ጳውሎስና ባልደረቦቹ ከጳፎስ ተነስተው በባሕር ላይ በመጓዝ ጵንፍልያ ውስጥ ወዳለችው ወደ ጴርጌ ሄዱ። ዮሐንስ+ ግን ከእነሱ ተለይቶ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ።+ 14 እነሱ ግን ጉዟቸውን በመቀጠል ከጴርጌ ተነስተው በጵስድያ ወደምትገኘው ወደ አንጾኪያ መጡ። በሰንበት ቀንም ወደ ምኩራብ ገብተው+ ተቀመጡ። 15 የሕጉና የነቢያት መጻሕፍት በሕዝቡ ፊት ከተነበበ+ በኋላ የምኩራቡ አለቆች “ወንድሞች ሆይ፣ ሕዝቡን የሚያበረታታ የምትናገሩት ቃል ካላችሁ ተናገሩ” የሚል መልእክት ላኩባቸው። 16 ስለዚህ ጳውሎስ ተነስቶ በእጁ ምልክት በመስጠት እንዲህ አለ፦

“የእስራኤል ሰዎችም ሆናችሁ አምላክን የምትፈሩ ሌሎች ሰዎች ሁሉ፣ ስሙ። 17 የዚህ የእስራኤል ሕዝብ አምላክ አባቶቻችንን መረጠ፤ በግብፅ ምድር ባዕዳን ሆነው ይኖሩ በነበረበት ጊዜም ሕዝቡን ከፍ ከፍ አደረጋቸው፤ በኃያል ክንዱም ከዚያ አወጣቸው።+ 18 ለ40 ዓመት ያህልም በምድረ በዳ ታገሣቸው።+ 19 በከነአን ምድር የነበሩትን ሰባት ብሔራት ካጠፋ በኋላ ምድራቸውን ርስት አድርጎ ሰጣቸው።+ 20 ይህ ሁሉ የሆነው በ450 ዓመት ያህል ጊዜ ውስጥ ነው።

“ይህ ከሆነ በኋላ እስከ ነቢዩ ሳሙኤል ዘመን ድረስ መሳፍንትን ሰጣቸው።+ 21 ከዚያ በኋላ ግን ንጉሥ እንዲያነግሥላቸው ጠየቁ፤+ አምላክም ከቢንያም ነገድ የሆነውን የቂስን ልጅ ሳኦልን+ ለ40 ዓመት አነገሠላቸው። 22 እሱን ከሻረው በኋላ ‘እንደ ልቤ የሆነውን+ የእሴይን+ ልጅ ዳዊትን አገኘሁ፤ እሱ የምፈልገውን ነገር ሁሉ ያደርጋል’ ሲል የመሠከረለትን ዳዊትን ንጉሥ አድርጎ አስነሳላቸው።+ 23 አምላክ በገባው ቃል መሠረት ከዚህ ሰው ዘር ለእስራኤል አዳኝ የሆነውን ኢየሱስን አመጣ።+ 24 ዮሐንስ፣ ኢየሱስ ከመምጣቱ በፊት ለእስራኤል ሕዝብ ሁሉ የንስሐ ምልክት የሆነውን ጥምቀት በይፋ ሰብኮ ነበር።+ 25 ይሁንና ዮሐንስ ተልእኮውን በማጠናቀቅ ላይ ሳለ ‘እኔ ማን እመስላችኋለሁ? እኔ እኮ እሱ አይደለሁም። ይሁን እንጂ ከእኔ በኋላ ሌላ ይመጣል፤ እኔ የእግሩን ጫማ ለመፍታት እንኳ አልበቃም’ ይል ነበር።+

26 “ወንድሞች፣ እናንተ ከአብርሃም ዘር የተወለዳችሁ እንዲሁም በመካከላችሁ ያሉ አምላክን የሚፈሩ ሌሎች ሰዎች ሁሉ፣ ይህ የመዳን ቃል ለእኛ ተልኳል።+ 27 የኢየሩሳሌም ነዋሪዎችና የሃይማኖት መሪዎቻቸው* የእሱን ማንነት አልተገነዘቡም፤ በእሱ ላይ በፈረዱበት ጊዜ ግን በየሰንበቱ ከፍ ባለ ድምፅ የሚነበበውን ነቢያት የተናገሩትን ቃል ፈጸሙ።+ 28 ለሞት የሚያበቃ አንድም ምክንያት ባያገኙበትም እንኳ+ ያስገድለው ዘንድ ጲላጦስን ወተወቱት።+ 29 ስለ እሱ የተጻፈውን ነገር ሁሉ ከፈጸሙ በኋላም ከእንጨት* ላይ አውርደው መቃብር ውስጥ አኖሩት።+ 30 ሆኖም አምላክ ከሞት አስነሳው፤+ 31 እሱም ከገሊላ እስከ ኢየሩሳሌም ድረስ አብረውት ለሄዱት ሰዎች ለብዙ ቀናት ታያቸው። እነሱም አሁን ስለ እሱ ለሕዝቡ እየመሠከሩ ነው።+

32 “ስለሆነም እኛ ለአባቶቻችን ስለተገባው ቃል የሚገልጸውን ምሥራች እያወጅንላችሁ ነው። 33 አምላክ ኢየሱስን ከሞት በማስነሳት+ ለእነሱ የገባውን ቃል ለእኛ ለልጆቻቸው ሙሉ በሙሉ ፈጽሞታል፤ ይህም የሆነው በሁለተኛው መዝሙር ላይ ‘አንተ ልጄ ነህ፤ እኔ ዛሬ ወለድኩህ’ ተብሎ በተጻፈው መሠረት ነው።+ 34 አምላክ ኢየሱስን የማይበሰብስ አካል ሰጥቶ ከሞት አስነስቶታል፤ ይህን አስቀድሞ በትንቢት ሲናገር ‘ለዳዊት ቃል የተገባውን የማይከስም * ታማኝ ፍቅር አሳያችኋለሁ’ ብሏል።+ 35 ስለዚህ በሌላም መዝሙር ላይ ‘ታማኝ አገልጋይህ መበስበስን እንዲያይ አትፈቅድም’ ብሏል።+ 36 በአንድ በኩል፣ ዳዊት በሕይወት ዘመኑ አምላክን ካገለገለ* በኋላ በሞት አንቀላፍቷል፤ ከአባቶቹም ጋር ተቀብሮ መበስበስን አይቷል።+ 37 በሌላ በኩል ግን አምላክ ከሞት ያስነሳው ኢየሱስ መበስበስን አላየም።+

38 “ስለዚህ ወንድሞች፣ በእሱ በኩል የሚገኘው የኃጢአት ይቅርታ አሁን እየታወጀላችሁ እንዳለ እወቁ፤+ 39 በኢየሱስ የሚያምን ማንኛውም ሰው፣ በእሱ አማካኝነት ‘ከበደል ነፃ ነህ’ ሊባል ይችላል፤+ የሙሴ ሕግ ግን እናንተን ከበደል ነፃ ሊያደርጋችሁ አልቻለም።+ 40 ስለዚህ በነቢያት መጻሕፍት እንዲህ ተብሎ የተነገረው ነገር በእናንተ ላይ እንዳይደርስ ተጠንቀቁ፦ 41 ‘እናንተ ፌዘኞች፣ ተመልከቱ፤ ተደነቁ፤ ጥፉም፤ ማንም በዝርዝር ቢነግራችሁ እንኳ ፈጽሞ የማታምኑትን ሥራ በእናንተ ዘመን እያከናወንኩ ነውና።’”+

42 እየወጡ ሳሉም ሰዎቹ ስለዚሁ ጉዳይ በሚቀጥለው ሰንበትም እንዲነግሯቸው ለመኗቸው። 43 በምኩራቡ የተደረገው ስብሰባ ከተበተነ በኋላ ከአይሁዳውያንና ወደ ይሁዲነት ተለውጠው አምላክን ከሚያመልኩት መካከል ብዙዎች ጳውሎስንና በርናባስን ተከተሏቸው፤ እነሱም ሰዎቹን በማነጋገር የአምላክን ጸጋ አጥብቀው እንደያዙ እንዲቀጥሉ አሳሰቧቸው።+

44 በቀጣዩ ሰንበት የከተማዋ ሕዝብ ሁሉ ማለት ይቻላል፣ የይሖዋን* ቃል ለመስማት አንድ ላይ ተሰበሰበ። 45 አይሁዳውያንም ሕዝቡን ባዩ ጊዜ በቅናት ተሞልተው ጳውሎስ የተናገረውን ቃል በመቃወም ይሳደቡ ጀመር።+ 46 በዚህ ጊዜ ጳውሎስና በርናባስ በድፍረት እንዲህ አሏቸው፦ “የአምላክ ቃል በመጀመሪያ ለእናንተ መነገሩ አስፈላጊ ነበር።+ እናንተ ግን ወደ ጎን ገሸሽ እያደረጋችሁትና የዘላለም ሕይወት እንደማይገባችሁ በራሳችሁ ላይ እየፈረዳችሁ ስለሆነ እኛም ለአሕዛብ እንሰብካለን።+ 47 ይሖዋ* ‘እስከ ምድር ዳር ድረስ መዳንን እንድታመጣ ለብሔራት ብርሃን አድርጌ ሾሜሃለሁ’ በማለት ትእዛዝ ሰጥቶናልና።”+

48 ከአሕዛብ ወገን የሆኑት ይህን ሲሰሙ እጅግ በመደሰት የይሖዋን* ቃል አከበሩ፤ ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ያላቸው ሁሉ አማኞች ሆኑ። 49 ከዚህም በተጨማሪ የይሖዋ* ቃል በአካባቢው ባለው አገር ሁሉ እየተስፋፋ ሄደ። 50 ይሁንና አይሁዳውያን ፈሪሃ አምላክ ያላቸውን የተከበሩ ሴቶችና በከተማዋ የሚኖሩትን ታላላቅ ወንዶች በመቀስቀስ በጳውሎስና በበርናባስ ላይ ስደት አስነሱ፤+ ከክልላቸውም አስወጧቸው። 51 እነሱም የእግራቸውን አቧራ አራግፈው* ወደ ኢቆንዮን ሄዱ።+ 52 ደቀ መዛሙርቱም በደስታና+ በመንፈስ ቅዱስ ተሞሉ።

14 በኢቆንዮን ጳውሎስና በርናባስ አብረው ወደ አይሁዳውያን ምኩራብ ገቡ፤ በዚያም ጥሩ ንግግር ስለሰጡ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው አይሁዳውያንና ግሪካውያን አማኞች ሆኑ። 2 ሆኖም ያላመኑት አይሁዳውያን ከአሕዛብ ወገን የሆኑትን ሰዎች* በማነሳሳት በወንድሞች ላይ ጥላቻ እንዲያድርባቸው አደረጉ።+ 3 በመሆኑም ከይሖዋ* ባገኙት ሥልጣን በድፍረት እየተናገሩ በኢቆንዮን ረዘም ላለ ጊዜ ቆዩ፤ እሱም ተአምራዊ ምልክቶችና ድንቅ ነገሮች በእነሱ አማካኝነት እንዲከናወኑ በማድረግ ስለ ጸጋው የሚነገረው መልእክት ትክክል መሆኑን ያረጋግጥላቸው ነበር።+ 4 ይሁንና የከተማዋ ሕዝብ ተከፋፈለ፤ አንዳንዶቹ ከአይሁዳውያን ጎን ሲቆሙ ሌሎቹ ደግሞ ከሐዋርያት ጎን ቆሙ። 5 አሕዛብና አይሁዳውያን ከገዢዎቻቸው ጋር ሆነው ሊያንገላቷቸውና በድንጋይ ሊወግሯቸው በሞከሩ ጊዜ+ 6 ጳውሎስና በርናባስ ይህን ስላወቁ ልስጥራና ደርቤ ወደሚባሉት የሊቃኦንያ ከተሞች እንዲሁም በዙሪያቸው ወዳሉት መንደሮች ሸሹ።+ 7 በዚያም ምሥራቹን ማወጃቸውን ቀጠሉ።

8 በልስጥራም አንድ ሰው ተቀምጦ ነበር። እሱም ከተወለደበት ጊዜ ጀምሮ ሽባ የነበረ ሲሆን ፈጽሞ በእግሩ ሄዶ አያውቅም። 9 ይህ ሰው ጳውሎስ ሲናገር ያዳምጥ ነበር። ጳውሎስም ትኩር ብሎ አየውና ለመዳን የሚያበቃ እምነት እንዳለው ተመልክቶ+ 10 ከፍ ባለ ድምፅ “ተነስና በእግርህ ቁም” አለው። ሰውየውም ዘሎ ተነሳና መራመድ ጀመረ።+ 11 ሕዝቡም ጳውሎስ ያደረገውን ባዩ ጊዜ በሊቃኦንያ ቋንቋ “አማልክት በሰው አምሳል ሆነው ወደ እኛ ወርደዋል!” በማለት ጮኹ።+ 12 በርናባስን ዙስ፣ ጳውሎስን ደግሞ ዋና ተናጋሪ ስለነበር ሄርሜስ ብለው ይጠሯቸው ጀመር። 13 በከተማዋ መግቢያ ላይ ይገኝ የነበረው የዙስ ቤተ መቅደስ ካህን፣ ኮርማዎችና የአበባ ጉንጉን ወደ ከተማዋ መግቢያ በማምጣት ከሕዝቡ ጋር ሆኖ መሥዋዕት ሊሠዋላቸው ፈለገ።

14 ይሁን እንጂ ሐዋርያቱ በርናባስና ጳውሎስ ይህን ሲሰሙ ልብሳቸውን ቀደዱ፤ ሮጠውም ሕዝቡ መሃል በመግባት ድምፃቸውን ከፍ አድርገው እንዲህ አሉ፦ 15 “እናንተ ሰዎች፣ እንዲህ የምታደርጉት ለምንድን ነው? እኛም እንደ እናንተው ድክመት ያለብን ሰዎች ነን።+ ምሥራቹን እያወጅንላችሁ ያለነውም እነዚህን ከንቱ ነገሮች ትታችሁ ሰማይን፣ ምድርን፣ ባሕርንና በውስጣቸው ያሉትን ነገሮች ሁሉ የፈጠረውን ሕያው አምላክ እንድታመልኩ ነው።+ 16 ባለፉት ትውልዶች፣ ሕዝቦች ሁሉ በራሳቸው መንገድ እንዲሄዱ ፈቀደላቸው፤+ 17 ይሁንና ለራሱ ምሥክር ከማቅረብ ወደኋላ አላለም፤+ ከሰማይ ዝናብ በማዝነብና ፍሬያማ ወቅቶችን በመስጠት+ እንዲሁም የተትረፈረፈ ምግብ በማቅረብና ልባችሁን በደስታ በመሙላት መልካም ነገር አድርጓል።”+ 18 ይህን ሁሉ ተናግረው እንኳ ሕዝቡ እንዳይሠዋላቸው ያስጣሉት በብዙ ችግር ነበር።

19 ሆኖም አይሁዳውያን ከአንጾኪያና ከኢቆንዮን መጥተው ሕዝቡን አግባቡ፤+ ጳውሎስንም በድንጋይ ከወገሩት በኋላ የሞተ መስሏቸው ጎትተው ከከተማዋ አወጡት።+ 20 ደቀ መዛሙርቱ መጥተው በከበቡት ጊዜ ግን ተነስቶ ወደ ከተማዋ ገባ። በማግስቱም ከበርናባስ ጋር ወደ ደርቤ ሄደ።+ 21 በዚያች ከተማ ምሥራቹን ሰብከው በርካታ ደቀ መዛሙርት ካፈሩ በኋላ ወደ ልስጥራ፣ ወደ ኢቆንዮንና ወደ አንጾኪያ ተመለሱ። 22 በዚያም “በብዙ መከራ አልፈን ወደ አምላክ መንግሥት መግባት አለብን”+ እያሉ በእምነት ጸንተው እንዲኖሩ በማበረታታት ደቀ መዛሙርቱን* አጠናከሩ።+ 23 ከዚህም በተጨማሪ በየጉባኤው ሽማግሌዎችን ሾሙላቸው፤+ ከጾሙና ከጸለዩም በኋላ+ ላመኑበት ለይሖዋ* አደራ ሰጧቸው።

24 ከዚያም በጵስድያ በኩል አልፈው ወደ ጵንፍልያ+ መጡ፤ 25 በጴርጌ ቃሉን ካወጁ በኋላ ወደ አታሊያ ወረዱ። 26 ከዚያም ተነስተው በመርከብ ወደ አንጾኪያ ሄዱ፤ ጳውሎስና በርናባስ አሁን ያጠናቀቁትን ሥራ እንዲያከናውኑ ለአምላክ ጸጋ በአደራ የተሰጡት በአንጾኪያ ነበር።+

27 እዚያም ደርሰው ጉባኤውን ከሰበሰቡ በኋላ አምላክ በእነሱ አማካኝነት ያከናወናቸውን በርካታ ነገሮች እንዲሁም ለአሕዛብ የእምነትን በር እንደከፈተላቸው ተረኩላቸው።+ 28 በዚያም ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ረዘም ያለ ጊዜ አሳለፉ።

15 አንዳንድ ሰዎች ከይሁዳ ወደ አንጾኪያ ወርደው “በሙሴ ሥርዓት መሠረት ካልተገረዛችሁ+ በቀር ልትድኑ አትችሉም” እያሉ ወንድሞችን ያስተምሩ ጀመር። 2 በዚህ የተነሳ ጳውሎስና በርናባስ ከሰዎቹ ጋር የጦፈ ክርክርና ጭቅጭቅ ውስጥ ገቡ። በመሆኑም ጳውሎስና በርናባስ እንዲሁም አንዳንድ ወንድሞች ወደ ኢየሩሳሌም ወጥተው+ ጉዳዩን* በዚያ ለሚገኙት ሐዋርያትና ሽማግሌዎች እንዲያቀርቡ ተወሰነ።

3 በዚህም መሠረት ጉባኤው የተወሰነ መንገድ ከሸኛቸው በኋላ በፊንቄና በሰማርያ በኩል በማለፍ ከአሕዛብ ወገን የሆኑ ሰዎች ተለውጠው አምላክን ማምለክ እንደጀመሩ በዝርዝር ተናገሩ፤ ወንድሞችንም ሁሉ እጅግ ደስ አሰኟቸው። 4 ኢየሩሳሌም ሲደርሱም በዚያ የሚገኘው ጉባኤ እንዲሁም ሐዋርያትና ሽማግሌዎች ጥሩ አቀባበል አደረጉላቸው፤ የተላኩትም ወንድሞች አምላክ በእነሱ አማካኝነት ያከናወናቸውን በርካታ ነገሮች ተረኩላቸው። 5 ይሁንና ከፈሪሳውያን ሃይማኖታዊ ቡድን መካከል አማኞች የሆኑ አንዳንድ ሰዎች ከመቀመጫቸው ተነስተው “እነዚህን ሰዎች መግረዝና የሙሴን ሕግ እንዲጠብቁ ማዘዝ አስፈላጊ ነው” ሲሉ ተናገሩ።+

6 ሐዋርያትና ሽማግሌዎችም ይህን ጉዳይ ለመመርመር ተሰበሰቡ። 7 ከብዙ ክርክር በኋላ ጴጥሮስ ተነስቶ እንዲህ አላቸው፦ “ወንድሞች፣ አሕዛብ የምሥራቹን ቃል ከእኔ አፍ ሰምተው እንዲያምኑ አምላክ ገና ከመጀመሪያው ከእናንተ መካከል እኔን እንደመረጠኝ በሚገባ ታውቃላችሁ።+ 8 ልብን የሚያውቀው አምላክ+ ለእኛ እንዳደረገው ሁሉ ለእነሱም መንፈስ ቅዱስን በመስጠት መሠከረላቸው።+ 9 ደግሞም በእኛና በእነሱ መካከል ምንም ልዩነት አላደረገም፤+ ከዚህ ይልቅ በእምነታቸው የተነሳ ልባቸውን አነጻ።+ 10 ታዲያ አባቶቻችንም ሆኑ እኛ ልንሸከመው ያልቻልነውን+ ቀንበር በደቀ መዛሙርቱ ጫንቃ ላይ በመጫን+ አሁን አምላክን ለምን ትፈታተናላችሁ? 11 በአንጻሩ ግን እኛ የምንድነው በጌታ ኢየሱስ ጸጋ አማካኝነት እንደሆነ እናምናለን፤+ እነሱም ቢሆኑ ይህንኑ ያምናሉ።”+

12 በዚህ ጊዜ የተሰበሰበው ሰው ሁሉ ጸጥ አለ፤ በርናባስና ጳውሎስ፣ አምላክ በእነሱ አማካኝነት በአሕዛብ መካከል ያከናወናቸውን በርካታ ተአምራዊ ምልክቶችና ድንቅ ነገሮች ሲናገሩም ያዳምጥ ጀመር። 13 እነሱ ተናግረው ካበቁ በኋላ ያዕቆብ እንዲህ ሲል መለሰ፦ “ወንድሞች፣ ስሙኝ። 14 አምላክ ከአሕዛብ መካከል ለስሙ የሚሆኑ ሰዎችን ለመውሰድ ለመጀመሪያ ጊዜ እንዴት ለእነሱ ትኩረት እንደሰጠ ሲምዖን*+ በሚገባ ተርኳል።+ 15 እንዲህ ተብሎ የተጻፈው የነቢያት ቃልም ከዚህ ጋር ይስማማል፦ 16 ‘ከዚህ በኋላ ተመልሼ የፈረሰውን የዳዊትን ድንኳን* ዳግመኛ አቆማለሁ፤ ፍርስራሹንም አድሼ ዳግም እገነባዋለሁ፤ 17 ይህን የማደርገው የቀሩት ሰዎች፣ ከብሔራት ከመጡት በስሜ የተጠሩ ሰዎች ጋር አንድ ላይ ሆነው ይሖዋን* ከልብ እንዲፈልጉ ነው በማለት እነዚህን ነገሮች የሚያደርገው ይሖዋ* ተናግሯል፤+ 18 እነዚህም ነገሮች ከጥንት ዘመን ጀምሮ ይታወቃሉ።’+ 19 ስለዚህ እንደ እኔ ሐሳብ ከሆነ፣* ተለውጠው አምላክን ማምለክ የጀመሩትን አሕዛብ ባናስቸግራቸው ይሻላል፤+ 20 ከዚህ ይልቅ በጣዖት+ ከረከሱ ነገሮች፣ ከፆታ ብልግና፣*+ ታንቆ ከሞተ* እንስሳ ሥጋ እንዲሁም ከደም እንዲርቁ+ እንጻፍላቸው። 21 ምክንያቱም ከጥንት ዘመን ጀምሮ በየከተማው በሰንበት ቀናት ሁሉ በምኩራቦች ውስጥ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ከሙሴ መጻሕፍት በማንበብ በውስጡ የሰፈረውን ቃል የሚሰብኩ ሰዎች ነበሩ።”+

22 ከዚያም ሐዋርያትና ሽማግሌዎች ከመላው ጉባኤ ጋር ሆነው ከመካከላቸው የተመረጡ ሰዎችን ከጳውሎስና ከበርናባስ ጋር ወደ አንጾኪያ ለመላክ ወሰኑ፤ በወንድሞች መካከል ግንባር ቀደም የሆኑትን በርስያን የሚባለውን ይሁዳንና ሲላስን+ ላኩ። 23 ደግሞም የሚከተለውን ደብዳቤ ጽፈው በእነሱ እጅ ላኩላቸው፦

“ከወንድሞቻችሁ ከሐዋርያትና ከሽማግሌዎች፣ በአንጾኪያ፣+ በሶርያና በኪልቅያ ለምትኖሩ ከአሕዛብ ወገን ለሆናችሁ ወንድሞች፤ ሰላምታችን ይድረሳችሁ! 24 ከእኛ መካከል አንዳንዶች ወጥተው እኛ ምንም ሳናዛቸው በሚናገሩት ነገር እንዳስቸገሯችሁና+ ሊያውኳችሁ* እንደሞከሩ ስለሰማን 25 ሰዎች መርጠን ከተወደዱት ወንድሞቻችን ከበርናባስና ከጳውሎስ ጋር ወደ እናንተ ለመላክ በአንድ ልብ ወሰንን፤ 26 በርናባስና ጳውሎስ ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ስም ሕይወታቸውን* አሳልፈው የሰጡ ናቸው።+ 27 ስለዚህ ይህንኑ ነገር በቃልም እንዲነግሯችሁ ይሁዳንና ሲላስን ልከናል።+ 28 ከሚከተሉት አስፈላጊ ነገሮች በስተቀር፣ ሌላ ተጨማሪ ሸክም እንዳንጭንባችሁ መንፈስ ቅዱስና+ እኛ ወስነናል፦ 29 ለጣዖት ከተሠዉ ነገሮች፣+ ከደም፣+ ታንቆ ከሞተ እንስሳ* ሥጋና+ ከፆታ ብልግና* ራቁ።+ ከእነዚህ ነገሮች ሙሉ በሙሉ ከራቃችሁ መልካም ይሆንላችኋል። ጤና ይስጣችሁ!”*

30 የተላኩትም ሰዎች ከተሰናበቱ በኋላ ወደ አንጾኪያ ወረዱ፤ እዚያ የሚገኙትንም ደቀ መዛሙርት በአንድነት ሰብስበው ደብዳቤውን ሰጧቸው። 31 እነሱም ካነበቡት በኋላ ባገኙት ማበረታቻ እጅግ ተደሰቱ። 32 ይሁዳና ሲላስም ራሳቸው ነቢያት ስለነበሩ ብዙ ቃል በመናገር ወንድሞችን አበረታቷቸው፤ እንዲሁም አጠናከሯቸው።+ 33 በዚያም የተወሰነ ጊዜ ከቆዩ በኋላ ወደላኳቸው ሰዎች እንዲመለሱ ወንድሞች በሰላም አሰናበቷቸው። 34 *—— 35 ይሁን እንጂ ጳውሎስና በርናባስ እያስተማሩና ከሌሎች ብዙ ሰዎች ጋር ሆነው ምሥራቹን ይኸውም የይሖዋን* ቃል እየሰበኩ በአንጾኪያ ቆዩ።

36 ከተወሰኑ ቀናት በኋላ ጳውሎስ በርናባስን “የይሖዋን* ቃል ባወጅንባቸው ከተሞች ሁሉ ያሉት ወንድሞች በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ለማወቅ ተመልሰን እንጠይቃቸው”* አለው።+ 37 በርናባስ፣ ማርቆስ ተብሎ የሚጠራው ዮሐንስ+ አብሯቸው እንዲሄድ ወስኖ ነበር። 38 ጳውሎስ ግን ማርቆስ በጵንፍልያ ተለይቷቸው ስለነበረና ያከናውኑት ወደነበረው ሥራ ከእነሱ ጋር ስላልሄደ አሁን አብሯቸው እንዲሄድ አልፈለገም።+ 39 በዚህ ምክንያት በመካከላቸው ኃይለኛ ጭቅጭቅ ስለተፈጠረ ተለያዩ፤ ስለዚህ በርናባስ+ ማርቆስን ይዞ በመርከብ ወደ ቆጵሮስ ሄደ። 40 ጳውሎስ ደግሞ ሲላስን መረጠ፤ ወንድሞችም ለይሖዋ* ጸጋ በአደራ ከሰጡት በኋላ ከዚያ ተነስቶ ሄደ።+ 41 ጉባኤዎችንም እያበረታታ በሶርያና በኪልቅያ በኩል አለፈ።

16 ከዚያም ጳውሎስ ወደ ደርቤና ወደ ልስጥራ+ ሄደ። በዚያም አማኝ የሆነች አይሁዳዊት እናትና ግሪካዊ አባት ያለው ጢሞቴዎስ+ የሚባል አንድ ደቀ መዝሙር ነበር፤ 2 እሱም በልስጥራና በኢቆንዮን ባሉ ወንድሞች፣ በመልካም ምግባሩ የተመሠከረለት ነበር። 3 ጳውሎስ፣ ጢሞቴዎስ አብሮት እንዲሄድ እንደሚፈልግ ገለጸ፤ አባቱ ግሪካዊ መሆኑን ሁሉም ሰው ያውቅ ስለነበረም በእነዚያ አካባቢዎች ስላሉት አይሁዳውያን ሲል ወስዶ ገረዘው።+ 4 በየከተሞቹ ሲያልፉም በዚያ ለሚያገኟቸው ሁሉ በኢየሩሳሌም ያሉት ሐዋርያትና ሽማግሌዎች ያስተላለፏቸውን ውሳኔዎች እንዲጠብቁ ጉዳዩን ያሳውቋቸው ነበር።+ 5 ጉባኤዎቹም በእምነት እየጠነከሩና ከዕለት ወደ ዕለት በቁጥር እየጨመሩ ሄዱ።

6 ከዚህም ሌላ መንፈስ ቅዱስ ቃሉን በእስያ አውራጃ እንዳይናገሩ ስለከለከላቸው በፍርግያና በገላትያ አድርገው አለፉ።+ 7 ደግሞም ወደ ሚስያ በወረዱ ጊዜ ወደ ቢቲኒያ+ ሊገቡ ሞከሩ፤ ሆኖም የኢየሱስ መንፈስ አልፈቀደላቸውም። 8 ስለዚህ በሚስያ በኩል አልፈው* ወደ ጥሮአስ ወረዱ። 9 ጳውሎስም ሌሊት በራእይ አንድ የመቄዶንያ ሰው በዚያ ቆሞ “ወደ መቄዶንያ ተሻገርና እርዳን” ብሎ ሲለምነው አየ። 10 ጳውሎስ ይህን ራእይ እንዳየም ‘አምላክ ምሥራቹን እንድንሰብክላቸው ጠርቶናል’ የሚል መደምደሚያ ላይ ስለደረስን ወደ መቄዶንያ ለመሄድ ሞከርን።

11 ስለዚህ ከጥሮአስ መርከብ ተሳፍረን በቀጥታ ወደ ሳሞትራቄ ሄድን፤ በማግስቱ ደግሞ ወደ ኔያጶሊስ ተጓዝን፤ 12 ከዚያም ተነስተን የሮማውያን ቅኝ ግዛትና የመቄዶንያ አውራጃ ቁልፍ ከተማ ወደሆነችው ወደ ፊልጵስዩስ+ መጣን። በዚህች ከተማም ለተወሰኑ ቀናት ቆየን። 13 በሰንበት ቀን የጸሎት ስፍራ ይገኝበታል ብለን ወዳሰብነው ከከተማው በር ውጭ ወዳለ አንድ ወንዝ ዳር ሄድን፤ በዚያም ተቀምጠን ተሰብስበው ለነበሩት ሴቶች መናገር ጀመርን። 14 ከትያጥሮን+ ከተማ የመጣች፣ ሐምራዊ ጨርቅ የምትሸጥና* አምላክን የምታመልክ ሊዲያ የተባለች አንዲት ሴት እያዳመጠች ነበር፤ ይሖዋም* ጳውሎስ የሚናገረውን በማስተዋል እንድትሰማ ልቧን በደንብ ከፈተላት። 15 እሷና በቤቷ የሚኖሩ ሰዎች ከተጠመቁ+ በኋላ “ለይሖዋ* ታማኝ እንደሆንኩ አድርጋችሁ ከቆጠራችሁኝ ወደ ቤቴ ገብታችሁ እረፉ” ብላ ተማጸነችን። እንድንገባም አስገደደችን።

16 አንድ ቀን ወደ ጸሎት ስፍራ እየሄድን ሳለ መንፈስ ይኸውም የጥንቆላ+ ጋኔን ያደረባት አንዲት አገልጋይ አገኘችን። እሷም በጥንቆላ ሥራዋ ለጌቶቿ ብዙ ትርፍ ታስገኝላቸው ነበር። 17 ይህች ሴት ጳውሎስንና እኛን እየተከተለች “እነዚህ ሰዎች የመዳንን መንገድ የሚያውጁላችሁ የልዑሉ አምላክ ባሪያዎች ናቸው” በማለት ትጮኽ ነበር።+ 18 ለብዙ ቀናት እየደጋገመች ይህንኑ ትናገር ነበር። በመጨረሻም ጳውሎስ በዚህ ነገር በመሰላቸቱ ዞር ብሎ ያን መንፈስ “ከእሷ እንድትወጣ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አዝሃለሁ” አለው። መንፈሱም በዚያው ቅጽበት ወጣ።+

19 ጌቶቿ የገቢ ምንጫቸው መቋረጡን+ ባዩ ጊዜ ጳውሎስንና ሲላስን ይዘው እየጎተቱ ገዢዎቹ ወደሚገኙበት ወደ ገበያ ስፍራው* ወሰዷቸው።+ 20 ከዚያም የከተማዋ ሕግ አስከባሪዎች ፊት አቅርበዋቸው እንዲህ አሉ፦ “እነዚህ ሰዎች ከተማችንን ክፉኛ እያወኩ ነው።+ እነሱ አይሁዳውያን ናቸው፤ 21 ደግሞም እኛ ሮማውያን ልንቀበለውም ሆነ ልንፈጽመው የማይገባንን ልማድ እያስፋፉ ነው።” 22 ሕዝቡም በአንድነት በእነሱ ላይ ተነሳ፤ የከተማዋ ሕግ አስከባሪዎችም ልብሳቸውን ከገፈፏቸው በኋላ በበትር እንዲደበደቡ አዘዙ።+ 23 በጣም ከደበደቧቸው በኋላ እስር ቤት አስገቧቸው፤ የእስር ቤቱንም ጠባቂ በደንብ እንዲጠብቃቸው አዘዙት።+ 24 እሱም እንዲህ ያለ ትእዛዝ ስለተሰጠው ወደ እስር ቤቱ ውስጠኛ ክፍል አስገብቶ እግራቸውን በእግር ግንድ አሰረው።

25 ይሁንና እኩለ ሌሊት ገደማ ጳውሎስና ሲላስ እየጸለዩና አምላክን በመዝሙር እያወደሱ ነበር፤+ ሌሎቹ እስረኞችም ያዳምጧቸው ነበር። 26 ድንገት ከባድ የምድር ነውጥ በመከሰቱ የእስር ቤቱ መሠረት ተናጋ። በተጨማሪም በሮቹ ወዲያውኑ የተከፈቱ ሲሆን ሁሉም የታሰሩበት ማሰሪያ ተፈታ።+ 27 የእስር ቤቱ ጠባቂም ከእንቅልፉ ነቅቶ የእስር ቤቱ በሮች መከፈታቸውን ሲያይ እስረኞቹ ያመለጡ መስሎት ራሱን ለመግደል ሰይፉን መዘዘ።+ 28 ጳውሎስ ግን ድምፁን ከፍ አድርጎ “በራስህ ላይ ክፉ ነገር አታድርግ! ሁላችንም እዚህ አለን” ሲል ተናገረ። 29 በዚህ ጊዜ የእስር ቤቱ ጠባቂ መብራት እንዲያመጡለት ጠይቆ ወደ ውስጥ ዘሎ ገባ፤ እየተንቀጠቀጠም በጳውሎስና በሲላስ ፊት ተደፋ። 30 ወደ ውጭ ካወጣቸውም በኋላ “ጌቶቼ፣ ለመዳን ምን ማድረግ ይኖርብኛል?” አለ። 31 እነሱም “በጌታ ኢየሱስ እመን፤ አንተም ሆንክ ቤተሰብህ ትድናላችሁ” አሉት።+ 32 ከዚያም ለእሱና በቤቱ ላሉት ሰዎች ሁሉ የይሖዋን* ቃል ነገሯቸው። 33 ጠባቂውም ሌሊት በዚያው ሰዓት ይዟቸው ሄዶ ቁስላቸውን አጠበላቸው። ከዚያም እሱና መላው ቤተሰቡ ወዲያውኑ ተጠመቁ።+ 34 ወደ ቤቱም ወስዶ ማዕድ አቀረበላቸው፤ በአምላክ በማመኑም ከመላው ቤተሰቡ ጋር እጅግ ተደሰተ።

35 ሲነጋም የከተማዋ ሕግ አስከባሪዎች “እነዚያን ሰዎች ልቀቃቸው” ብለው እንዲነግሩት መኮንኖቹን ላኩበት። 36 የእስር ቤቱ ጠባቂ የላኩትን መልእክት እንዲህ ሲል ለጳውሎስ ነገረው፦ “የከተማዋ ሕግ አስከባሪዎች ሁለታችሁ እንድትፈቱ ሰዎች ልከዋል። ስለዚህ አሁን ወጥታችሁ በሰላም ሂዱ።” 37 ጳውሎስ ግን እንዲህ አላቸው፦ “እኛ የሮም ዜጎች+ ሆነን ሳለ ያለፍርድ በሕዝብ ፊት ገርፈው እስር ቤት ወረወሩን። ታዲያ አሁን በድብቅ አስወጥተው ሊጥሉን ይፈልጋሉ? እንዲህማ አይሆንም! እነሱ ራሳቸው መጥተው ይዘውን ይውጡ።” 38 መኮንኖቹም ይህን ነገር ለከተማዋ ሕግ አስከባሪዎች ነገሯቸው። እነሱም ሰዎቹ የሮም ዜጎች መሆናቸውን ሲሰሙ ፍርሃት አደረባቸው።+ 39 በመሆኑም መጥተው ለመኗቸው፤ ከእስር ቤቱም ይዘዋቸው ከወጡ በኋላ ከተማዋን ለቀው እንዲሄዱ ጠየቋቸው። 40 እነሱ ግን ከእስር ቤቱ ወጥተው ወደ ሊዲያ ቤት አመሩ፤ እዚያም ወንድሞችን አግኝተው ካበረታቷቸው+ በኋላ ከተማዋን ለቀው ሄዱ።

17 ከዚያም በአምፊጶሊስና በአጶሎንያ በኩል ተጉዘው የአይሁዳውያን ምኩራብ ወዳለበት ወደ ተሰሎንቄ መጡ።+ 2 ጳውሎስም እንደ ልማዱ+ ወደ ምኩራብ ገባ፤ ለሦስት ሰንበትም ከቅዱሳን መጻሕፍት እየጠቀሰ ከእነሱ ጋር ተወያየ፤+ 3 ክርስቶስ መከራ መቀበሉና+ ከሞት መነሳቱ+ አስፈላጊ እንደነበር ማስረጃ እየጠቀሰ በማብራራትና በማስረዳት “ይህ እኔ የማውጅላችሁ ኢየሱስ እሱ ክርስቶስ ነው” አላቸው። 4 ከዚህም የተነሳ ከእነሱ መካከል አንዳንዶቹ አማኞች በመሆን ከጳውሎስና ከሲላስ ጋር ተባበሩ፤+ ከግሪካውያንም መካከል አምላክን የሚያመልኩ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች እንዲሁም ቁጥራቸው ጥቂት የማይባል የታወቁ ሴቶች እንዲሁ አደረጉ።

5 ሆኖም አይሁዳውያን ቅናት ስላደረባቸው+ በገበያ ስፍራ የሚያውደለድሉ አንዳንድ ክፉ ሰዎችን አሰባስበው አሳደሙ፤ ከተማዋንም በሁከት አመሷት። ጳውሎስንና ሲላስንም አምጥተው ለረብሻ የተሰበሰበው ሕዝብ ፊት ለማቅረብ የያሶንን ቤት ሰብረው ገቡ። 6 ባጧቸው ጊዜም ያሶንንና አንዳንድ ወንድሞችን እየጎተቱ ወስደው የከተማዋ ገዢዎች ፊት በማቅረብ እንዲህ እያሉ ጮኹ፦ “ዓለምን ሁሉ ያናወጡት* እነዚያ ሰዎች እዚህም መጥተዋል፤+ 7 ያሶንም በእንግድነት ተቀብሏቸዋል። እነዚህ ሁሉ ሰዎች ኢየሱስ የሚባል ሌላ ንጉሥ አለ እያሉ የቄሳርን ሕግ የሚቃረን ነገር ያደርጋሉ።”+ 8 ሕዝቡና የከተማዋ ገዢዎች ይህን ሲሰሙ ተሸበሩ፤ 9 ያሶንን እና ሌሎቹን የዋስትና ገንዘብ እንዲያስይዙ ካደረጓቸው በኋላ* ለቀቋቸው።

10 ወንድሞችም እንደመሸ ጳውሎስንና ሲላስን ወደ ቤርያ ላኳቸው። እነሱም እዚያ እንደደረሱ ወደ አይሁዳውያን ምኩራብ ገቡ። 11 በቤርያ የነበሩት አይሁዳውያን በተሰሎንቄ ከነበሩት ይልቅ ቀና አስተሳሰብ ስለነበራቸው የሰሙት ነገር ትክክል መሆኑን ለማረጋገጥ በየዕለቱ ቅዱሳን መጻሕፍትን በሚገባ በመመርመር ቃሉን በታላቅ ጉጉት ተቀበሉ። 12 ስለዚህ ከእነሱ መካከል ብዙዎቹ እንዲሁም ቁጥራቸው ጥቂት የማይባል የተከበሩ ግሪካውያን ሴቶችና የተወሰኑ ወንዶች አማኞች ሆኑ። 13 ሆኖም በተሰሎንቄ ያሉት አይሁዳውያን ጳውሎስ የአምላክን ቃል በቤርያም እንዳወጀ ባወቁ ጊዜ ሕዝቡን ለማነሳሳትና ለማወክ ወደዚያ መጡ።+ 14 በዚህ ጊዜ ወንድሞች ወዲያውኑ ጳውሎስን ወደ ባሕሩ ዳርቻ ላኩት፤+ ሲላስና ጢሞቴዎስ ግን እዚያው ቀሩ። 15 ጳውሎስን የሸኙት ሰዎችም እስከ አቴንስ አደረሱት፤ ከዚያም ጳውሎስ ‘ሲላስና ጢሞቴዎስ+ በተቻለ ፍጥነት ወደ እኔ እንዲመጡ ንገሯቸው’ የሚል መመሪያ ሰጣቸው፤ ሰዎቹም ተመልሰው ሄዱ።

16 ጳውሎስ በአቴንስ እየጠበቃቸው ሳለ ከተማዋ በጣዖት የተሞላች መሆኗን አይቶ መንፈሱ ተረበሸ። 17 ስለዚህ በምኩራብ ከአይሁዳውያንና አምላክን ከሚያመልኩ ሌሎች ሰዎች ጋር እንዲሁም በየዕለቱ በገበያ ስፍራ* ከሚያገኛቸው ሰዎች ጋር ይወያይ ጀመር። 18 ሆኖም ከኤፊቆሮስና ከኢስጦይክ ፈላስፎች መካከል አንዳንዶቹ ይከራከሩት ጀመር፤ ሌሎቹ ደግሞ “ይህ ለፍላፊ ምን ሊያወራ ፈልጎ ነው?” ይሉ ነበር። “ስለ ባዕዳን አማልክት የሚያውጅ ይመስላል” የሚሉም ነበሩ። ይህን ያሉት ስለ ኢየሱስና ስለ ትንሣኤ የሚገልጸውን ምሥራች ያውጅ ስለነበር ነው።+ 19 ስለዚህ ይዘው ወደ አርዮስፋጎስ* ከወሰዱት በኋላ እንዲህ አሉት፦ “ይህ የምትናገረው አዲስ ትምህርት ምን እንደሆነ ልታስረዳን ትችላለህ? 20 ምክንያቱም ለጆሯችን እንግዳ የሆነ ነገር እያሰማኸን ነው፤ ይህ ነገር ምን ማለት እንደሆነ ማወቅ እንፈልጋለን።” 21 የአቴንስ ሰዎችና በዚያ የሚገኙ* የባዕድ አገር ሰዎች ትርፍ ጊዜያቸውን የሚያሳልፉት ስለ አዳዲስ ነገሮች በማውራትና በመስማት ብቻ ነበር። 22 በዚህ ጊዜ ጳውሎስ በአርዮስፋጎስ+ መካከል ቆሞ እንዲህ አለ፦

“የአቴንስ ሰዎች ሆይ፣ በሁሉም ነገር ከሌሎች ሰዎች ይበልጥ እናንተ አማልክትን እንደምትፈሩ* ማየት ችያለሁ።+ 23 ለአብነት ያህል፣ እየተዘዋወርኩ ሳለሁ የምታመልኳቸውን ነገሮች በትኩረት ስመለከት ‘ለማይታወቅ አምላክ’ የሚል ጽሑፍ የተቀረጸበት አንድ መሠዊያ አይቻለሁ። ስለዚህ ይህን ሳታውቁ የምታመልኩትን እኔ አሳውቃችኋለሁ። 24 ዓለምንና በውስጡ ያለውን ነገር ሁሉ የፈጠረው አምላክ፣ እሱ የሰማይና የምድር ጌታ+ ስለሆነ በእጅ በተሠሩ ቤተ መቅደሶች ውስጥ አይኖርም፤+ 25 በተጨማሪም ሕይወትንና እስትንፋስንም ሆነ ማንኛውንም ነገር ለሰው ሁሉ የሚሰጠው+ እሱ ስለሆነ የሚጎድለው ነገር ያለ ይመስል በሰው እጅ አይገለገልም።+ 26 በምድር ሁሉ ላይ እንዲኖሩም+ የሰውን ወገኖች በሙሉ ከአንድ ሰው ፈጠረ፤+ የተወሰኑትን ዘመናትና የሰው ልጆች የሚኖሩበትንም ድንበር ደነገገ፤+ 27 ይህን ያደረገው ሰዎች አምላክን እንዲፈልጉትና አጥብቀው በመሻት እንዲያገኙት ብሎ ነው፤+ እንዲህ ሲባል ግን እሱ ከእያንዳንዳችን የራቀ ነው ማለት አይደለም። 28 ምክንያቱም ከእናንተ ባለቅኔዎች አንዳንዶቹ ‘እኛም የእሱ ልጆች ነንና’ ብለው እንደተናገሩት ሁሉ ሕይወት ያገኘነው፣ የምንንቀሳቀሰውና የምንኖረው በእሱ ነው።

29 “እንግዲህ እኛ የአምላክ ልጆች+ ከሆንን አምላክ በሰው ጥበብና ንድፍ ከወርቅ፣ ከብር ወይም ከድንጋይ የተቀረጸን ነገር ይመስላል ብለን ልናስብ አይገባም።+ 30 እርግጥ አምላክ ሰዎች ባለማወቅ የኖሩበትን ጊዜ+ ችላ ብሎ አልፎታል፤ አሁን ግን በየቦታው ያሉ ሰዎች ሁሉ ንስሐ እንዲገቡ እያሳሰበ ነው። 31 ምክንያቱም በሾመው ሰው አማካኝነት በዓለም ሁሉ ላይ በጽድቅ ለመፍረድ+ ዓላማ ያለው ሲሆን ይህን ለማድረግም ቀን ወስኗል፤ እሱንም ከሞት በማስነሳት ለሰዎች ሁሉ ዋስትና ሰጥቷል።”+

32 እነሱም ስለ ሙታን ትንሣኤ በሰሙ ጊዜ አንዳንዶቹ ያሾፉበት ጀመር፤+ ሌሎቹ ግን “ስለዚሁ ጉዳይ በድጋሚ መስማት እንፈልጋለን” አሉት። 33 በዚህ ጊዜ ጳውሎስ ትቷቸው ሄደ፤ 34 አንዳንድ ሰዎች ግን ከእሱ ጋር በመተባበር አማኞች ሆኑ። ከእነሱም መካከል የአርዮስፋጎስ ፍርድ ቤት ዳኛ የሆነው ዲዮናስዮስና ደማሪስ የተባለች ሴት እንዲሁም ሌሎች ሰዎች ይገኙበታል።

18 ከዚህ በኋላ ከአቴንስ ተነስቶ ወደ ቆሮንቶስ መጣ። 2 በዚያም የጳንጦስ ተወላጅ የሆነ አቂላ+ የተባለ አይሁዳዊ አገኘ፤ ይህ ሰው ቀላውዴዎስ አይሁዳውያን ሁሉ ከሮም እንዲወጡ ባዘዘው መሠረት ከሚስቱ ከጵርስቅላ ጋር በቅርቡ ከጣሊያን የመጣ ነበር። ጳውሎስም ወደ እነሱ ሄደ፤ 3 ሙያቸው አንድ ዓይነት በመሆኑ እነሱ ቤት ተቀምጦ አብሯቸው ይሠራ ነበር፤+ ሙያቸውም ድንኳን መሥራት ነበር። 4 በየሰንበቱ+ በምኩራብ+ ንግግር እየሰጠ* አይሁዳውያንንና ግሪካውያንን ያሳምን ነበር።

5 ሲላስና+ ጢሞቴዎስ+ ከመቄዶንያ በወረዱ ጊዜ፣ ጳውሎስ ቃሉን በመስበኩ ሥራ በእጅጉ ተጠመደ፤ ኢየሱስ በእርግጥ ክርስቶስ መሆኑን እያስረዳ ለአይሁዳውያን ይመሠክር ነበር።+ 6 አይሁዳውያኑ እሱን መቃወማቸውንና መሳደባቸውን በቀጠሉ ጊዜ ግን ልብሱን አራግፎ*+ “ደማችሁ በራሳችሁ ላይ ይሁን።+ እኔ ንጹሕ ነኝ።+ ከአሁን ጀምሮ ወደ አሕዛብ እሄዳለሁ” አላቸው።+ 7 ከዚያም* ተነስቶ ቲቶስ ኢዮስጦስ ወደሚባል አምላክን ወደሚያመልክ ሰው ቤት ሄደ፤ የዚህ ሰው ቤት ምኩራቡ አጠገብ ነበር። 8 የምኩራብ አለቃው ቀርስጶስ+ ከቤተሰቡ ሁሉ ጋር በጌታ አመነ። መልእክቱን የሰሙ በርካታ የቆሮንቶስ ሰዎችም አምነው ይጠመቁ ጀመር። 9 ጌታም ሌሊት በራእይ ጳውሎስን እንዲህ አለው፦ “አትፍራ፣ መናገርህን ቀጥል፤ ደግሞም ተስፋ አትቁረጥ፤ 10 እኔ ከአንተ ጋር ስለሆንኩ+ ማንም አንተን ሊያጠቃና ሊጎዳህ አይችልም፤ በዚህች ከተማ ብዙ ሰዎች አሉኝና።” 11 ስለዚህ በመካከላቸው የአምላክን ቃል እያስተማረ ለአንድ ዓመት ተኩል እዚያ ቆየ።

12 የሮም አገረ ገዢ* የሆነው ጋልዮስ አካይያን ያስተዳድር በነበረበት ጊዜ አይሁዳውያን ግንባር ፈጥረው በጳውሎስ ላይ ተነሱበት፤ በፍርድ ወንበር ፊት አቅርበውትም 13 እንዲህ አሉ፦ “ይህ ሰው ሕጉን በሚጻረር መንገድ ሰዎች አምላክን እንዲያመልኩ እያሳመነ ነው።” 14 ይሁንና ጳውሎስ ሊናገር ሲል ጋልዮስ አይሁዳውያንን እንዲህ አላቸው፦ “አይሁዳውያን ሆይ፣ አንድ ዓይነት በደል ወይም ከባድ ወንጀል ተፈጽሞ ቢሆን ኖሮ በትዕግሥት ላዳምጣችሁ በተገባኝ ነበር። 15 ነገር ግን ክርክራችሁ ስለ ቃላትና ስለ ስሞች እንዲሁም ስለ ሕጋችሁ+ ከሆነ እናንተው ጨርሱት። እኔ እንዲህ ላለ ነገር ፈራጅ መሆን አልፈልግም።” 16 ከዚያም ከፍርድ ወንበሩ ፊት አስወጣቸው። 17 በዚህ ጊዜ የምኩራብ አለቃ የሆነውን ሶስቴንስን+ ይዘው በፍርድ ወንበሩ ፊት ይደበድቡት ጀመር። ጋልዮስ ግን እንዲህ ባሉ ጉዳዮች እጁን አያስገባም ነበር።

18 ይሁንና ጳውሎስ በዚያ ለተወሰኑ ቀናት ከቆየ በኋላ ወንድሞችን ተሰናብቶ ከጵርስቅላና ከአቂላ ጋር በመርከብ ወደ ሶርያ ሄደ። ስእለት ስለነበረበትም ክንክራኦስ+ በተባለ ቦታ ፀጉሩን በአጭሩ ተቆረጠ። 19 ኤፌሶን በደረሱም ጊዜ እነሱን እዚያው ተዋቸው፤ እሱ ግን ወደ ምኩራብ ገብቶ ከአይሁዳውያን ጋር ይወያይ ነበር።+ 20 ምንም እንኳ ረዘም ላለ ጊዜ እንዲሰነብት አጥብቀው ቢለምኑትም ፈቃደኛ አልሆነም፤ 21 ከዚህ ይልቅ “ይሖዋ* ከፈቀደ ተመልሼ እመጣለሁ” ብሎ ተሰናበታቸው። ከዚያም ከኤፌሶን መርከብ ተሳፍሮ 22 ወደ ቂሳርያ ወረደ። ወጥቶም * ለጉባኤው ሰላምታ ካቀረበ በኋላ ወደ አንጾኪያ ወረደ።+

23 በዚያም የተወሰነ ጊዜ ካሳለፈ በኋላ ከዚያ ወጥቶ በገላትያና በፍርግያ+ አገሮች ከቦታ ወደ ቦታ እየተዘዋወረ ደቀ መዛሙርቱን ሁሉ አበረታታ።+

24 በዚህ ጊዜ የእስክንድርያ ተወላጅ የሆነ አጵሎስ+ የሚባል አንድ አይሁዳዊ ወደ ኤፌሶን መጣ፤ እሱም ጥሩ የመናገር ተሰጥኦ ያለውና ቅዱሳን መጻሕፍትን ጠንቅቆ የሚያውቅ ሰው ነበር። 25 ይህ ሰው የይሖዋን* መንገድ የተማረ* ሲሆን በመንፈስ* እየተቃጠለ ኢየሱስን ስለሚመለከቱ ጉዳዮች በትክክል ይናገርና ያስተምር ነበር፤ ይሁን እንጂ እሱ የሚያውቀው ዮሐንስ ይሰብከው ስለነበረው ጥምቀት ብቻ ነበር። 26 እሱም በምኩራብ ውስጥ በድፍረት መናገር ጀመረ፤ ጵርስቅላና አቂላም+ በሰሙት ጊዜ ይዘውት በመሄድ የአምላክን መንገድ ይበልጥ በትክክል አብራሩለት። 27 በተጨማሪም ወደ አካይያ መሄድ ፈልጎ ስለነበር ወንድሞች በዚያ የሚገኙት ደቀ መዛሙርት ጥሩ አቀባበል እንዲያደርጉለት የሚያሳስብ ደብዳቤ ጻፉለት። እዚያ በደረሰ ጊዜም በአምላክ ጸጋ አማኞች የሆኑትን ሰዎች በእጅጉ ረዳቸው፤ 28 ከአይሁዳውያን ጋር በይፋ በመወያየት ከቅዱሳን መጻሕፍት ላይ እያሳያቸው ኢየሱስ እሱ ክርስቶስ እንደሆነ በመግለጽ ትክክል እንዳልሆኑ በጋለ ስሜት ያስረዳቸው ነበር።+

19 ከጊዜ በኋላ፣ አጵሎስ+ በቆሮንቶስ በነበረበት ጊዜ ጳውሎስ በመሃል አገር አቋርጦ ወደ ኤፌሶን ወረደ።+ በዚያም አንዳንድ ደቀ መዛሙርትን አገኘ፤ 2 እነሱንም “አማኞች በሆናችሁ ጊዜ መንፈስ ቅዱስ ተቀብላችሁ ነበር?” አላቸው።+ እነሱም “ኧረ እኛ ስለ መንፈስ ቅዱስ የሰማነው ነገር የለም” ሲሉ መለሱለት። 3 እሱም “ታዲያ ምን ዓይነት ጥምቀት ነው የተጠመቃችሁት?” አላቸው። እነሱም “የዮሐንስን ጥምቀት” አሉት።+ 4 ጳውሎስም እንዲህ አላቸው፦ “ዮሐንስ ያጠምቅ የነበረው የንስሐ ምልክት የሆነውን ጥምቀት ነበር፤+ ሰዎች ከእሱ በኋላ በሚመጣው+ ይኸውም በኢየሱስ እንዲያምኑ ይነግራቸው ነበር።” 5 እነሱም ይህን ሲሰሙ በጌታ ኢየሱስ ስም ተጠመቁ። 6 ጳውሎስም እጁን በላያቸው በጫነ ጊዜ መንፈስ ቅዱስ ወረደባቸው፤+ እነሱም በባዕድ ቋንቋዎች መናገርና መተንበይ ጀመሩ።+ 7 ሰዎቹም በአጠቃላይ 12 ገደማ ነበሩ።

8 ጳውሎስም ወደ ምኩራብ እየገባ+ ንግግር በመስጠትና ስለ አምላክ መንግሥት አሳማኝ በሆነ መንገድ በማስረዳት ለሦስት ወራት ያህል በድፍረት ሲናገር ቆየ።+ 9 ሆኖም አንዳንዶቹ ግትሮች ስለነበሩ ለማመን ፈቃደኞች አልሆኑም፤ የጌታን መንገድ+ በሕዝቡ ፊት ባጥላሉ ጊዜ ከእነሱ በመራቅ+ ደቀ መዛሙርቱን ለይቶ ወሰዳቸው፤ በጢራኖስ የትምህርት ቤት አዳራሽም በየዕለቱ ንግግር ይሰጥ ነበር። 10 ይህም ለሁለት ዓመት ያህል ቀጠለ፤ ከዚህም የተነሳ በእስያ አውራጃ የሚኖሩ አይሁዳውያንና ግሪካውያን ሁሉ የጌታን ቃል ሰሙ።

11 አምላክም በጳውሎስ እጅ በጣም አስደናቂ የሆኑ ነገሮችን መፈጸሙን ቀጠለ፤+ 12 ሰዎችም የጳውሎስን ሰውነት የነኩ ጨርቆችንና ሽርጦችን ወደታመሙት ሰዎች ሲወስዱ+ ሰዎቹ በሽታቸው ይለቃቸው ነበር፤ ርኩሳን መናፍስትም ይወጡ ነበር።+ 13 ይሁንና እየዞሩ አጋንንትን ያስወጡ ከነበሩት አይሁዳውያን አንዳንዶቹም “ጳውሎስ በሚሰብከው በኢየሱስ ስም እንድትወጣ አጥብቄ አዝሃለሁ”+ እያሉ ክፉ መናፍስት በያዟቸው ሰዎች ላይ የጌታ ኢየሱስን ስም ለመጥራት ሞከሩ። 14 አስቄዋ የተባለ የአንድ አይሁዳዊ የካህናት አለቃ ሰባት ወንዶች ልጆችም ይህን ያደርጉ ነበር። 15 ክፉው መንፈስ ግን መልሶ “ኢየሱስን አውቀዋለሁ፤+ ጳውሎስንም አውቀዋለሁ፤+ እናንተ ደግሞ ማን ናችሁ?” አላቸው። 16 ከዚያም ክፉው መንፈስ ያደረበት ሰው ዘሎ ጉብ አለባቸው፤ አሸነፋቸውም፤ ስለዚህ ራቁታቸውን ሆነውና ቆስለው ከዚያ ቤት ሸሹ። 17 በኤፌሶን የሚኖሩት አይሁዳውያንና ግሪካውያን ሁሉ ይህን ሰሙ፤ በመሆኑም ሁሉም ፍርሃት አደረባቸው፤ የጌታ ኢየሱስ ስምም ይበልጥ እየገነነ ሄደ። 18 አማኞች ከሆኑት መካከል ብዙዎቹም እየመጡ ያደረጉትን ይናዘዙና በግልጽ ይናገሩ ነበር። 19 ደግሞም አስማት ይሠሩ ከነበሩት መካከል ብዙዎች መጽሐፎቻቸውን አንድ ላይ ሰብስበው በማምጣት በሰው ሁሉ ፊት አቃጠሉ።+ የመጽሐፎቹንም ዋጋ ሲያሰሉ 50,000 የብር ሳንቲሞች* ሆኖ አገኙት። 20 በዚህ መንገድ የይሖዋ* ቃል በኃይል እየተስፋፋና እያሸነፈ ሄደ።+

21 ይህ ሁሉ ከሆነ በኋላ ጳውሎስ በመቄዶንያና+ በአካይያ በኩል አልፎ ወደ ኢየሩሳሌም ለመሄድ ወሰነ።+ “እዚያ ከሄድኩ በኋላ ደግሞ ወደ ሮም ማቅናት አለብኝ” አለ።+ 22 ስለዚህ ከሚያገለግሉት መካከል ሁለቱን ማለትም ጢሞቴዎስንና+ ኤርስጦስን+ ወደ መቄዶንያ ላካቸው፤ እሱ ግን በእስያ አውራጃ ለተወሰነ ጊዜ ቆየ።

23 በዚህ ወቅት የጌታን መንገድ+ በተመለከተ ታላቅ ሁከት ተፈጠረ።+ 24 ምክንያቱም ድሜጥሮስ የተባለ አንድ የብር አንጥረኛ የአርጤምስን ቤተ መቅደስ የብር ምስሎች እየቀረጸ ለእጅ ጥበብ ባለሙያዎች ከፍተኛ ትርፍ ያስገኝ ነበር።+ 25 ድሜጥሮስ እነሱንና በተመሳሳይ ሙያ የተሰማሩ ሰዎችን ሰብስቦ እንዲህ አለ፦ “እናንተ ሰዎች፣ መቼም ብልጽግናችን የተመካው በዚህ ሥራ ላይ እንደሆነ ታውቃላችሁ። 26 አሁን ግን ይህ ጳውሎስ የተባለ ሰው በኤፌሶን+ ብቻ ሳይሆን በመላው የእስያ አውራጃ ማለት ይቻላል፣ በእጅ የተሠሩ አማልክት ሁሉ በፍጹም አማልክት አይደሉም እያለ ብዙ ሰዎችን አሳምኖ አመለካከታቸውን እንዳስለወጠ ያያችሁትና የሰማችሁት ጉዳይ ነው።+ 27 ከዚህም በላይ አሳሳቢ የሆነው ነገር የእኛ ሥራ መናቁ ብቻ ሳይሆን የታላቋ አምላክ የአርጤምስ ቤተ መቅደስ ዋጋ ቢስ ሆኖ ሊቀርና መላው የእስያ አውራጃም ሆነ ዓለም በሙሉ የሚያመልካት አርጤምስ ገናና ክብሯ ሊገፈፍ መሆኑ ጭምር ነው።” 28 ሰዎቹ ይህን ሲሰሙ በቁጣ ተሞልተው “የኤፌሶኗ አርጤምስ ታላቅ ናት!” እያሉ ይጮኹ ጀመር።

29 በመሆኑም ከተማዋ በረብሻ ታመሰች፤ ሕዝቡም የመቄዶንያ ሰዎች የሆኑትን የጳውሎስን የጉዞ ጓደኞች ይኸውም ጋይዮስንና አርስጥሮኮስን+ እየጎተቱ ግር ብለው ወደ ጨዋታ ማሳያው ስፍራ ገቡ። 30 ጳውሎስም ሕዝቡ ወዳለበት ሊገባ ፈልጎ ነበር፤ ደቀ መዛሙርቱ ግን ከለከሉት። 31 የጳውሎስ ወዳጆች የነበሩ አንዳንድ የበዓላትና የውድድር አዘጋጆች እንኳ ሳይቀሩ ወደ ጨዋታ ማሳያው ስፍራ በመግባት ራሱን ለአደጋ እንዳያጋልጥ መልእክት በመላክ ለመኑት። 32 በተሰበሰበው ሕዝብ መካከል ከፍተኛ ትርምስ ተፈጥሮ ስለነበር አንዳንዶቹ አንድ ነገር ሲናገሩ ሌሎቹ ደግሞ ሌላ ነገር እየተናገሩ ይጯጯኹ ነበር፤ አብዛኛው ሰው ለምን እዚያ እንደተገኘ እንኳ አያውቅም ነበር። 33 አንዳንዶች እስክንድርን ከሕዝቡ መካከል ባወጡት ጊዜ አይሁዳውያን ወደ ፊት ገፉት፤ እስክንድርም የመከላከያ ሐሳቡን ለሕዝቡ ሊያቀርብ ፈልጎ በእጁ ምልክት ሰጣቸው። 34 ሆኖም አይሁዳዊ መሆኑን ባወቁ ጊዜ ሁሉም በአንድ ድምፅ “የኤፌሶኗ አርጤምስ ታላቅ ናት!” እያሉ ለሁለት ሰዓት ያህል ጮኹ።

35 በመጨረሻ የከተማዋ ዋና ጸሐፊ ሕዝቡን ጸጥ አሰኝቶ እንዲህ አለ፦ “የኤፌሶን ሰዎች ሆይ፣ የታላቋ አርጤምስ ቤተ መቅደስና ከሰማይ የወረደው ምስሏ ጠባቂ የኤፌሶናውያን ከተማ እንደሆነች የማያውቅ ማን አለ? 36 ይህ ፈጽሞ የማይታበል ሐቅ ስለሆነ ልትረጋጉና የችኮላ እርምጃ ከመውሰድ ልትቆጠቡ ይገባል። 37 ምክንያቱም እነዚህ ያመጣችኋቸው ሰዎች ቤተ መቅደስ የዘረፉ ወይም የምናመልካትን አምላክ የሰደቡ አይደሉም። 38 ስለዚህ ድሜጥሮስና+ አብረውት ያሉት የእጅ ጥበብ ባለሙያዎች የሚከሱት ሰው ካለ ችሎት የሚሰየምባቸው ቀናት ያሉ ከመሆኑም ሌላ የሮም አገረ ገዢዎች* አሉ፤ እዚያ መሟገት ይችላሉ። 39 ከዚህ ያለፈ ልታቀርቡት የምትፈልጉት ክስ ካለ ግን በመደበኛ ጉባኤ መዳኘት ይኖርበታል። 40 አለዚያ ዛሬ በተፈጸመው ነገር የተነሳ ሕዝብ አሳድማችኋል ተብለን እንዳንከሰስ ያሰጋል፤ ለዚህ ሁሉ ሁከት መንስኤው ምን እንደሆነ ብንጠየቅ የምንሰጠው አጥጋቢ መልስ የለም።” 41 ይህን ከተናገረ በኋላ የተሰበሰበው ሕዝብ እንዲበተን አደረገ።

20 ሁከቱ ሲበርድ ጳውሎስ ደቀ መዛሙርቱን አስጠራቸው፤ ካበረታታቸውና ከተሰናበታቸው በኋላ ወደ መቄዶንያ ጉዞ ጀመረ። 2 በሚያልፍባቸው ስፍራዎች የሚያገኛቸውን ደቀ መዛሙርት በብዙ ቃል እያበረታታ ወደ ግሪክ መጣ። 3 በዚያ ሦስት ወር ቆየ፤ ይሁንና ወደ ሶርያ በመርከብ ለመሄድ ተነስቶ ሳለ አይሁዳውያን ሴራ ስለጠነሰሱበት+ ሐሳቡን ቀይሮ በመቄዶንያ አድርጎ ለመመለስ ወሰነ። 4 የጳይሮስ ልጅ የቤርያው ሶጳጥሮስ፣ የተሰሎንቄዎቹ አርስጥሮኮስና+ ሲኮንዱስ፣ የደርቤው ጋይዮስ፣ ጢሞቴዎስ+ እንዲሁም ከእስያ አውራጃ የመጡት ቲኪቆስና+ ጢሮፊሞስ+ አብረውት ነበሩ። 5 እነዚህም ወደ ጥሮአስ ቀድመውን በመሄድ እዚያ ጠበቁን፤ 6 እኛ ግን የቂጣ በዓል+ ካለፈ በኋላ ከፊልጵስዩስ በመርከብ ተነሳን፤ በአምስት ቀን ጊዜ ውስጥም እነሱ ወዳሉበት ወደ ጥሮአስ ደረስን፤ በዚያም ሰባት ቀን ቆየን።

7 በሳምንቱ የመጀመሪያ ቀን ምግብ ልንበላ አንድ ላይ ተሰብስበን ሳለን ጳውሎስ በማግስቱ ይሄድ ስለነበር ንግግር ይሰጣቸው ጀመር፤ ንግግሩንም እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ አስረዘመ። 8 በመሆኑም ተሰብስበንበት በነበረው ፎቅ ላይ ባለው ክፍል ውስጥ ብዙ መብራት ነበር። 9 ጳውሎስ ንግግሩን ባስረዘመ ጊዜ መስኮት ላይ ተቀምጦ የነበረ አውጤኪስ የሚባል አንድ ወጣት ከባድ እንቅልፍ ያዘው፤ እንቅልፍ ስለጣለውም ከሁለተኛ ፎቅ ላይ ወደቀ፤ ሲያነሱትም ሞቶ ነበር። 10 ጳውሎስም ከፎቅ ላይ ወርዶ በላዩ ላይ ተኝቶ አቀፈውና+ “በሕይወት ስላለ አትንጫጩ”* አላቸው።+ 11 ከዚያም ወደ ፎቅ ወጥቶ ማዕዱን ካስጀመረ* በኋላ በላ። እስከ ንጋትም ድረስ ሲነጋገር ቆየ፤ በኋላም ተነስቶ ሄደ። 12 ሰዎቹም ወጣቱን ወሰዱት፤ ሕያው በመሆኑም እጅግ ተጽናኑ።

13 እኛም ጳውሎስ በሰጠን መመሪያ መሠረት በመርከብ ተሳፍረን በቅድሚያ ወደ አሶስ ተጓዝን፤ ምክንያቱም ጳውሎስ በእግሩ ተጉዞ በዚያ ለመሳፈር አስቦ ነበር። 14 ስለዚህ አሶስ ላይ ከተገናኘን በኋላ አሳፍረነው ወደ ሚጢሊኒ ሄድን። 15 በነጋታውም ጉዟችንን በመቀጠል ከኪዮስ ትይዩ ወዳለው ስፍራ ደረስን፤ በሚቀጥለው ቀን ደግሞ ሳሞስ ላይ አጭር ቆይታ አደረግን፤ በማግስቱም ሚሊጢን ደረስን። 16 ጳውሎስ በእስያ አውራጃ ምንም መቆየት ስላልፈለገ ኤፌሶንን+ አልፎ ለመሄድ ወሰነ፤ ምክንያቱም ቢችል በጴንጤቆስጤ በዓል ቀን ኢየሩሳሌም ለመድረስ ቸኩሎ ነበር።+

17 ይሁን እንጂ ከሚሊጢን ወደ ኤፌሶን መልእክት ልኮ የጉባኤውን ሽማግሌዎች አስጠራ። 18 ወደ እሱም በመጡ ጊዜ እንዲህ አላቸው፦ “በእስያ አውራጃ እግሬ ከረገጠበት ከመጀመሪያው ቀን አንስቶ በመካከላችሁ እንዴት እንደተመላለስኩ ታውቃላችሁ፤+ 19 በአይሁዳውያን ሴራ ምክንያት ብዙ መከራ ቢደርስብኝም እንኳ በታላቅ ትሕትናና+ በእንባ ጌታን አገለግል ነበር፤ 20 ደግሞም የሚጠቅማችሁን ማንኛውንም ነገር ከመንገርም ሆነ በአደባባይና+ ከቤት ወደ ቤት+ ከማስተማር ወደኋላ ብዬ አላውቅም። 21 ከዚህ ይልቅ አይሁዳውያንም ሆኑ ግሪካውያን ንስሐ እንዲገቡና+ ወደ አምላክ እንዲመለሱ እንዲሁም በጌታችን በኢየሱስ እንዲያምኑ በተሟላ ሁኔታ* መሥክሬላቸዋለሁ።+ 22 አሁን ደግሞ እዚያ ምን እንደሚደርስብኝ ባላውቅም መንፈስ ወደ ኢየሩሳሌም እንድሄድ ግድ እያለኝ ነው፤ 23 እርግጥ ነው፣ እስራትና መከራ እንደሚጠብቀኝ መንፈስ ቅዱስ በደረስኩበት ከተማ ሁሉ በተደጋጋሚ ያሳስበኛል።+ 24 ይሁንና ሩጫዬን እስካጠናቀቅኩ+ እንዲሁም ስለ አምላክ ጸጋ የሚገልጸውን ምሥራች በተሟላ ሁኔታ በመመሥከር* ከጌታ ኢየሱስ የተቀበልኩትን አገልግሎት እስከፈጸምኩ ድረስ ሕይወቴ* ምንም አያሳሳኝም።*

25 “አሁንም እነሆ፣ የአምላክን መንግሥት የሰበክሁላችሁ እናንተ ሁላችሁ ዳግመኛ ፊቴን እንደማታዩ አውቃለሁ። 26 ስለዚህ ከሰው ሁሉ ደም ንጹሕ መሆኔን ለማሳየት በዚህች ቀን እናንተን ምሥክር አድርጌ መጥራት እችላለሁ፤+ 27 ምክንያቱም የአምላክን ፈቃድ* ሁሉ ለእናንተ ከመንገር ወደኋላ አላልኩም።+ 28 ለራሳችሁም ሆነ አምላክ በገዛ ልጁ ደም+ የዋጀውን ጉባኤውን እረኛ ሆናችሁ እንድትጠብቁ+ መንፈስ ቅዱስ የበላይ ተመልካቾች+ አድርጎ በላዩ ለሾማችሁ መንጋ ሁሉ ትኩረት ስጡ።+ 29 እኔ ከሄድኩ በኋላ ጨካኝ* ተኩላዎች በመካከላችሁ እንደሚገቡና+ መንጋውን በርኅራኄ እንደማይዙ አውቃለሁ፤ 30 ከእናንተ መካከል እንኳ ደቀ መዛሙርቱን ወደ ራሳቸው ለመሳብ ጠማማ ነገር የሚናገሩ ሰዎች ይነሳሉ።+

31 “ስለዚህ ነቅታችሁ ጠብቁ፤ ሦስት ዓመት ሙሉ+ ሌሊትና ቀን እያንዳንዳችሁን በእንባ ከማሳሰብ ወደኋላ እንዳላልኩ አስታውሱ። 32 አሁንም ለአምላክ እንዲሁም ሊያንጻችሁና በቅዱሳኑ ሁሉ መካከል ርስት ሊያወርሳችሁ ለሚችለው፣ ስለ እሱ ጸጋ ለሚገልጸው ቃል አደራ እሰጣችኋለሁ።+ 33 የማንንም ብር፣ ወርቅ ወይም ልብስ አልተመኘሁም።+ 34 እነዚህ እጆቼ ለእኔም ሆነ ከእኔ ጋር ለነበሩት የሚያስፈልጉንን ነገሮች ለማሟላት እንዳገለገሉ+ እናንተ ራሳችሁ ታውቃላችሁ። 35 እናንተም እንዲሁ እየሠራችሁ ደካማ የሆኑትን መርዳት እንዳለባችሁ በሁሉም ነገር አሳይቻችኋለሁ፤+ እንዲሁም ‘ከመቀበል ይልቅ መስጠት የበለጠ ደስታ ያስገኛል’+ በማለት ጌታ ኢየሱስ ራሱ የተናገረውን ቃል ማስታወስ ይኖርባችኋል።”

36 ይህን ተናግሮ ከጨረሰም በኋላ ከሁሉም ጋር ተንበርክኮ ጸለየ። 37 ከዚያም ሁሉም እጅግ አለቀሱ፤ ጳውሎስንም እቅፍ አድርገው* ሳሙት፤ 38 ከሁሉ ይበልጥ ያሳዘናቸው ከዚህ በኋላ ፊቱን እንደማያዩ የተናገረው ቃል ነው።+ ከዚያም እስከ መርከቡ ድረስ ሸኙት።

21 ከእነሱ በግድ ከተለያየን በኋላ በመርከብ ተሳፍረን በቀጥታ በመጓዝ ቆስ ደረስን፤ በማግስቱ ደግሞ ወደ ሮድስ አመራን፤ ከዚያም ወደ ጳጥራ ሄድን። 2 ወደ ፊንቄ የሚሻገር መርከብ ባገኘን ጊዜ ተሳፍረን ጉዟችንን ቀጠልን። 3 የቆጵሮስ ደሴት በታየችን ጊዜ በስተ ግራ ትተናት ወደ ሶርያ አመራን፤ መርከቡ ጭነቱን በጢሮስ ማራገፍ ስለነበረበት እኛም እዚያ ወረድን። 4 ደቀ መዛሙርቱን ፈልገን ካገኘን በኋላ በዚያ ሰባት ቀን ቆየን። እነሱም በመንፈስ ተመርተው ጳውሎስ ወደ ኢየሩሳሌም እንዳይሄድ ደጋግመው ነገሩት።+ 5 የቆይታ ጊዜያችን ባለቀ ጊዜ ከዚያ ተነስተን ጉዟችንን ጀመርን፤ ሴቶችንና ልጆችን ጨምሮ ደቀ መዛሙርቱ ሁሉ ከከተማዋ እስክንወጣ ድረስ ሸኙን። ከዚያም በባሕሩ ዳርቻ ተንበርክከን ጸለይን፤ 6 በኋላም ተሰነባበትን። ከዚያም እኛ ወደ መርከቡ ገባን፤ እነሱ ደግሞ ወደ ቤታቸው ተመለሱ።

7 ከጢሮስ ተነስተን በመርከብ በመጓዝ ጴጤሌማይስ ደረስን፤ እዚያም ለወንድሞች ሰላምታ ካቀረብን በኋላ አብረናቸው አንድ ቀን ቆየን። 8 በማግስቱ ከዚያ ተነስተን ቂሳርያ ደረስን፤ በዚያም ከሰባቱ ወንዶች አንዱ ወደሆነው ወደ ወንጌላዊው ፊልጶስ+ ቤት ገብተን እሱ ጋ አረፍን። 9 ይህ ሰው ትንቢት የሚናገሩ አራት ያላገቡ* ሴቶች ልጆች ነበሩት።+ 10 ለብዙ ቀናት እዚያ ከተቀመጥን በኋላ አጋቦስ+ የሚባል አንድ ነቢይ ከይሁዳ ወረደ። 11 ወደ እኛም መጥቶ የጳውሎስን ቀበቶ በመውሰድ የራሱን እግርና እጅ ካሰረ በኋላ እንዲህ አለ፦ “መንፈስ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ ‘አይሁዳውያን የዚህን ቀበቶ ባለቤት በኢየሩሳሌም እንዲህ አድርገው ያስሩታል፤+ ለአሕዛብም አሳልፈው ይሰጡታል።’”+ 12 ይህን ስንሰማ እኛም ሆንን በዚያ የነበሩት ደቀ መዛሙርት ጳውሎስ ወደ ኢየሩሳሌም እንዳይወጣ እንለምነው ጀመር። 13 በዚህ ጊዜ ጳውሎስ “እያለቀሳችሁ ልቤን ለምን ታባባላችሁ? እኔ ስለ ጌታ ኢየሱስ ስም በኢየሩሳሌም ለመታሰር ብቻ ሳይሆን ለመሞትም እንኳ ዝግጁ ነኝ” ሲል መለሰ።+ 14 እሱን ለማሳመን ያደረግነው ጥረት ሳይሳካ በመቅረቱ “እንግዲህ የይሖዋ* ፈቃድ ይሁን” ብለን ዝም አልን።*

15 ከዚህ በኋላ ለጉዞው ተዘጋጅተን ወደ ኢየሩሳሌም መጓዝ ጀመርን። 16 በቂሳርያ ከሚኖሩት ደቀ መዛሙርት አንዳንዶቹ ወደምናርፍበት ሰው ቤት እኛን ለመውሰድ አብረውን ሄዱ፤ ይህ ሰው ምናሶን የተባለ የቆጵሮስ ሰው ሲሆን ከቀድሞዎቹ ደቀ መዛሙርት አንዱ ነበር። 17 ኢየሩሳሌም በደረስን ጊዜ ወንድሞች በደስታ ተቀበሉን። 18 በማግስቱም ጳውሎስ ከእኛ ጋር ወደ ያዕቆብ ሄደ፤+ ሽማግሌዎቹም ሁሉ በዚያ ነበሩ። 19 ሰላምታ ካቀረበላቸውም በኋላ፣ እሱ ባከናወነው አገልግሎት አማካኝነት አምላክ በአሕዛብ መካከል የፈጸማቸውን ነገሮች በዝርዝር ይተርክላቸው ጀመር።

20 እነሱም ይህን ከሰሙ በኋላ አምላክን አመሰገኑ፤ እሱን ግን እንዲህ አሉት፦ “ወንድም፣ ከአይሁዳውያን መካከል በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ አማኞች እንዳሉ ታውቃለህ፤ ደግሞም ሁሉም ለሕጉ ቀናተኞች ናቸው።+ 21 እነሱም አንተ በአሕዛብ መካከል ያሉት አይሁዳውያን ሁሉ ልጆቻቸውን እንዳይገርዙም ሆነ የቆየውን ልማድ እንዳይከተሉ በመንገር የሙሴን ሕግ እንዲተዉ ስታስተምር እንደቆየህ ስለ አንተ የሚወራውን ወሬ ሰምተዋል።+ 22 እንግዲህ ምን ማድረግ ይሻላል? መምጣትህን እንደሆነ መስማታቸው አይቀርም። 23 ስለዚህ አሁን የምንነግርህን ነገር አድርግ፦ ስእለት ያለባቸው አራት ሰዎች በእኛ ዘንድ አሉ። 24 እነዚህን ሰዎች ይዘህ በመሄድ ከእነሱ ጋር የመንጻት ሥርዓት ፈጽም፤ ራሳቸውንም እንዲላጩ የሚያስፈልገውን ገንዘብ ክፈልላቸው። ይህን ካደረግክ በአንተ ላይ የተወራው ሁሉ ከንቱ መሆኑንና አንተም ሕጉን እያከበርክ በሥርዓት እንደምትኖር ሁሉም ሰው ያውቃል።+ 25 ከአሕዛብ የመጡትን አማኞች በተመለከተ ግን ለጣዖት ከተሠዋ፣+ ከደም፣+ ታንቆ ከሞተ* እንስሳ ሥጋና+ ከፆታ ብልግና* እንዲርቁ+ ወስነን ደብዳቤ ጽፈንላቸዋል።”

26 ከዚያም ጳውሎስ በማግስቱ ሰዎቹን ይዞ በመሄድ አብሯቸው የመንጻት ሥርዓቱን ፈጸመ፤+ የመንጻት ሥርዓቱ የሚያበቃበትን ቀንና ለእያንዳንዳቸው መባ የሚቀርብበትን ጊዜ ለማሳወቅም ወደ ቤተ መቅደሱ ገባ።

27 ሰባቱ ቀናት ሊጠናቀቁ በተቃረቡበት ጊዜ ከእስያ የመጡ አይሁዳውያን ጳውሎስን በቤተ መቅደሱ ውስጥ ሲያዩት ሕዝቡን ሁሉ ለሁከት በማነሳሳት ያዙት፤ 28 እንዲህ እያሉም ጮኹ፦ “የእስራኤል ሰዎች ሆይ፣ እርዱን! በሄደበት ቦታ ሁሉ ለሚያገኛቸው ሰዎች ሕዝባችንን፣ ሕጋችንንና ይህን ስፍራ የሚቃወም ትምህርት የሚያስተምረው ይህ ሰው ነው። በዚህ ላይ ደግሞ የግሪክ ሰዎችን ወደ ቤተ መቅደሱ ይዞ በመምጣት ይህን ቅዱስ ስፍራ አርክሷል።”+ 29 ይህን ያሉት ቀደም ሲል የኤፌሶኑን ሰው ጢሮፊሞስን+ ከእሱ ጋር ከተማው ውስጥ አይተውት ስለነበር ነው፤ ደግሞም ጳውሎስ ይህን ሰው ወደ ቤተ መቅደሱ ይዞት የገባ መስሏቸው ነበር። 30 በመሆኑም ከተማዋ በሙሉ ታወከች፤ ሕዝቡም ግር ብለው እየሮጡ በመምጣት ጳውሎስን ያዙት፤ እየጎተቱም ከቤተ መቅደሱ አወጡት፤ በሮቹም ወዲያው ተዘጉ። 31 ሊገድሉትም እየሞከሩ ሳለ መላዋ ኢየሩሳሌም እንደታወከች የሚገልጽ ወሬ ለሠራዊቱ ሻለቃ ደረሰው፤ 32 እሱም ወዲያውኑ ወታደሮችንና የጦር መኮንኖችን ይዞ እየሮጠ ወደ እነሱ ወረደ። እነሱም ሻለቃውንና ወታደሮቹን ሲያዩ ጳውሎስን መደብደባቸውን ተዉ።

33 በዚህ ጊዜ የሠራዊቱ ሻለቃ ቀርቦ በቁጥጥር ሥር አዋለውና በሁለት ሰንሰለት እንዲታሰር አዘዘ፤+ ከዚያም ማን እንደሆነና ምን እንዳደረገ ጠየቀ። 34 ከሕዝቡም መካከል አንዳንዶች አንድ ነገር ሲናገሩ ሌሎቹ ደግሞ ሌላ ነገር ይናገሩ ነበር። ስለዚህ ሻለቃው ከጫጫታው የተነሳ ምንም የተጨበጠ ነገር ማግኘት ስላልቻለ ወደ ጦር ሰፈሩ እንዲወሰድ አዘዘ። 35 ሆኖም ጳውሎስ ወደ ደረጃው በደረሰ ጊዜ ከሕዝቡ ዓመፅ የተነሳ ወታደሮቹ ተሸክመውት ለመሄድ ተገደዱ፤ 36 ብዙ ሕዝብም እየተከተለ “ግደለው!” እያለ ይጮኽ ነበር።

37 ጳውሎስ ወደ ጦር ሰፈሩ ሊያስገቡት በተቃረቡ ጊዜ ሻለቃውን “አንዴ ላናግርህ?” አለው። ሻለቃውም እንዲህ አለው፦ “ግሪክኛ መናገር ትችላለህ እንዴ? 38 አንተ ከዚህ ቀደም ዓመፅ አነሳስተህ 4,000 ነፍሰ ገዳዮችን ወደ ምድረ በዳ ያሸፈትከው ግብፃዊ አይደለህም?” 39 በዚህ ጊዜ ጳውሎስ “እኔ እንኳ በኪልቅያ የምትገኘው የታወቀችው የጠርሴስ+ ከተማ ነዋሪ የሆንኩ አይሁዳዊ ነኝ።+ ስለዚህ ለሕዝቡ እናገር ዘንድ እንድትፈቅድልኝ እለምንሃለሁ” አለ። 40 ከፈቀደለት በኋላ ጳውሎስ ደረጃው ላይ ቆሞ ለሕዝቡ በእጁ ምልክት ሰጠ። ታላቅ ጸጥታ በሰፈነ ጊዜ በዕብራይስጥ ቋንቋ+ እንዲህ ሲል ለሕዝቡ መናገር ጀመረ፦

22 “ወንድሞችና አባቶች፣ አሁን ለእናንተ የማቀርበውን የመከላከያ መልስ ስሙ።”+ 2 እነሱም በዕብራይስጥ ቋንቋ ሲናገር በሰሙ ጊዜ ይበልጥ ጸጥ አሉ፤ እሱም እንዲህ አለ፦ 3 “እኔ ኪልቅያ ውስጥ በምትገኘው በጠርሴስ+ የተወለድኩ አይሁዳዊ ነኝ፤+ ሆኖም የተማርኩት በዚህችው ከተማ በገማልያል+ እግር ሥር ተቀምጬ ሲሆን የአባቶችን ሕግ በጥብቅ እንድከተል የሚያስችል ትምህርት ቀስሜአለሁ፤+ ዛሬ እናንተ ሁላችሁ እንዲህ እንደምትቀኑ ሁሉ እኔም ለአምላክ እቀና ነበር።+ 4 ወንዶችንም ሆነ ሴቶችን በማሰርና ለወህኒ ቤት አሳልፌ በመስጠት የጌታን መንገድ የሚከተሉትን እስከ ሞት ድረስ ስደት አደርስባቸው ነበር፤+ 5 ይህን በተመለከተም ሊቀ ካህናቱና መላው የሽማግሌዎች ጉባኤ ሊመሠክሩ ይችላሉ። ከእነሱም በደማስቆ ላሉ ወንድሞቻችን የተጻፈ ደብዳቤ ተቀብዬ በዚያ ያሉትን አስሬ ወደ ኢየሩሳሌም በማምጣት ለማስቀጣት በጉዞ ላይ ነበርኩ።

6 “ሆኖም በጉዞ ላይ ሳለሁ ወደ ደማስቆ ስቃረብ፣ እኩለ ቀን ገደማ ላይ ድንገት ከሰማይ የመጣ ኃይለኛ ብርሃን በዙሪያዬ አንጸባረቀ፤+ 7 እኔም መሬት ላይ ወደቅኩ፤ ከዚያም ‘ሳኦል፣ ሳኦል ለምን ታሳድደኛለህ?’ የሚል ድምፅ ሰማሁ። 8 እኔም መልሼ ‘ጌታዬ፣ አንተ ማን ነህ?’ አልኩት። እሱም ‘እኔ አንተ የምታሳድደኝ የናዝሬቱ ኢየሱስ ነኝ’ አለኝ። 9 ከእኔ ጋር የነበሩት ሰዎች ብርሃኑን አይተዋል፤ ሆኖም እሱ ሲያነጋግረኝ ድምፁን አልሰሙም።* 10 በዚህ ጊዜ ‘ጌታ ሆይ፣ ምን ባደርግ ይሻላል?’ አልኩት። ጌታም ‘ተነስተህ ወደ ደማስቆ ሂድ፤ እዚያም ልታደርገው የሚገባህ ነገር ሁሉ ይነገርሃል’ አለኝ።+ 11 ይሁንና ከብርሃኑ ድምቀት የተነሳ ዓይኔ ማየት ስለተሳነው አብረውኝ የነበሩት ሰዎች እጄን ይዘው እየመሩ ደማስቆ አደረሱኝ።

12 “ከዚያም ሕጉን በሚገባ በመጠበቅ ለአምላክ ያደረ እንዲሁም እዚያ በሚኖሩት አይሁዳውያን ሁሉ የተመሠከረለት ሐናንያ የሚባል አንድ ሰው 13 ወደ እኔ መጣ። አጠገቤም ቆሞ ‘ወንድሜ ሳኦል፣ ዓይኖችህ ይብሩልህ!’ አለኝ። እኔም በዚያው ቅጽበት ቀና ብዬ አየሁት።+ 14 እሱም እንዲህ አለኝ፦ ‘የአባቶቻችን አምላክ ፈቃዱን እንድታውቅ፣ ጻድቁን እንድታይና+ ድምፁን እንድትሰማ መርጦሃል፤ 15 ይህን ያደረገው ስላየኸውና ስለሰማኸው ነገር በሰው ሁሉ ፊት ለእሱ ምሥክር እንድትሆን ነው።+ 16 ታዲያ አሁን ምን ትጠብቃለህ? ተነስና ተጠመቅ፤ ስሙንም እየጠራህ+ ኃጢአትህን ታጠብ።’+

17 “ሆኖም ወደ ኢየሩሳሌም ከተመለስኩ በኋላ+ በቤተ መቅደሱ ውስጥ እየጸለይኩ ሳለ ሰመመን ውስጥ ገባሁ፤ 18 ጌታም ‘ስለ እኔ የምትሰጠውን ምሥክርነት ስለማይቀበሉ ፍጠን፤ ከኢየሩሳሌም ቶሎ ብለህ ውጣ’ ሲለኝ አየሁት።+ 19 እኔም እንዲህ አልኩት፦ ‘ጌታ ሆይ፣ በየምኩራቡ እየዞርኩ በአንተ የሚያምኑትን አስርና እገርፍ እንደነበረ እነሱ ራሳቸው በሚገባ ያውቃሉ፤+ 20 ደግሞም የአንተ ምሥክር የነበረው የእስጢፋኖስ ደም ሲፈስ እኔ በድርጊቱ በመስማማት እዚያ ቆሜ የገዳዮቹን ልብስ ስጠብቅ ነበር።’+ 21 እሱ ግን ‘በሩቅ ወዳሉ አሕዛብ ስለምልክህ ተነስተህ ሂድ’ አለኝ።”+

22 ሕዝቡ ይህን እስኪናገር ድረስ ጸጥ ብለው ሲያዳምጡት ቆዩ። ከዚያም “ይህ ሰው መኖር የማይገባው ስለሆነ ከምድር ገጽ ይወገድ!” ብለው ጮኹ። 23 ደግሞም እየጮኹ መደረቢያቸውን ይወረውሩና አፈር ወደ ላይ ይበትኑ ስለነበር+ 24 የሠራዊቱ ሻለቃ ጳውሎስን ወደ ጦር ሰፈሩ እንዲያስገቡት ትእዛዝ ሰጠ፤ ደግሞም በጳውሎስ ላይ እንዲህ የሚጮኹት ለምን እንደሆነ በትክክል ማወቅ ስለፈለገ እየተገረፈ እንዲመረመር አዘዘ። 25 ሆኖም ሊገርፉት ወጥረው ባሰሩት ጊዜ ጳውሎስ አጠገቡ የቆመውን መኮንን “አንድን ሮማዊ* ሳይፈረድበት* ለመግረፍ ሕግ ይፈቅድላችኋል?” አለው።+ 26 መኮንኑ ይህን ሲሰማ ወደ ሠራዊቱ ሻለቃ ሄዶ “ምን ለማድረግ ነው ያሰብከው? ይህ ሰው እኮ ሮማዊ ነው” አለው። 27 ሻለቃውም ወደ ጳውሎስ ቀርቦ “ሮማዊ ነህ እንዴ?” አለው። እሱም “አዎ” አለው። 28 ሻለቃውም መልሶ “እኔ ይህን የዜግነት መብት የገዛሁት ብዙ ገንዘብ አውጥቼ ነው” አለው። ጳውሎስ ደግሞ “እኔ ግን በመወለድ አገኘሁት” አለ።+

29 ስለዚህ እያሠቃዩ ሊመረምሩት የነበሩት ሰዎች ወዲያውኑ ከእሱ ራቁ፤ የሠራዊቱ ሻለቃም በሰንሰለት አስሮት ስለነበር ሮማዊ መሆኑን ሲገነዘብ ፈራ።+

30 በመሆኑም በማግስቱ አይሁዳውያን የከሰሱት ለምን እንደሆነ በትክክል ማወቅ ስለፈለገ ፈታውና የካህናት አለቆቹ እንዲሁም መላው የሳንሄድሪን ሸንጎ እንዲሰበሰቡ አዘዘ። ከዚያም ጳውሎስን አውርዶ በመካከላቸው አቆመው።+

23 ጳውሎስ የሳንሄድሪንን ሸንጎ ትኩር ብሎ እየተመለከተ “ወንድሞች፣ እኔ እስከዚህ ቀን ድረስ በአምላክ ፊት ሙሉ በሙሉ ንጹሕ ሕሊና ይዤ ተመላልሻለሁ”+ አለ። 2 በዚህ ጊዜ ሊቀ ካህናቱ ሐናንያ፣ ጳውሎስ አጠገብ የቆሙት ሰዎች አፉን እንዲመቱት አዘዘ። 3 ጳውሎስም “አንተ በኖራ የተለሰንክ ግድግዳ! አምላክ አንተን ይመታሃል። በሕጉ መሠረት በእኔ ላይ ለመፍረድ ተቀምጠህ ሳለ አንተ ራስህ ሕጉን በመጣስ እንድመታ ታዛለህ?” አለው። 4 አጠገቡ የቆሙትም “የአምላክን ሊቀ ካህናት ትሳደባለህ?” አሉት። 5 ጳውሎስም “ወንድሞች፣ እኔ እኮ ሊቀ ካህናት መሆኑን አላወቅኩም። ምክንያቱም ‘በሕዝብህ ገዢ ላይ ክፉ ቃል አትናገር’ ተብሎ ተጽፏል” አላቸው።+

6 ጳውሎስ ግማሾቹ ሰዱቃውያን ግማሾቹ ደግሞ ፈሪሳውያን መሆናቸውን ስላወቀ በሳንሄድሪን ሸንጎ ውስጥ ድምፁን ከፍ አድርጎ “ወንድሞች፣ እኔ ከፈሪሳውያን የተወለድኩ ፈሪሳዊ ነኝ።+ ለፍርድ የቀረብኩት በሙታን ትንሣኤ ተስፋ በማመኔ ነው” ሲል ተናገረ። 7 ይህን በመናገሩ በፈሪሳውያንና በሰዱቃውያን መካከል ግጭት ተፈጥሮ ጉባኤው ለሁለት ተከፈለ። 8 ምክንያቱም ሰዱቃውያን ትንሣኤም፣ መልአክም፣ መንፈሳዊ ፍጥረታትም የሉም ይሉ የነበረ ሲሆን ፈሪሳውያን ግን በእነዚህ ነገሮች ያምኑ ነበር።+ 9 ስለዚህ ከፍተኛ ሁከት ተፈጠረ፤ ከፈሪሳውያን ወገን የሆኑ አንዳንድ ጸሐፍት ተነስተው እንዲህ ሲሉ አጥብቀው ተከራከሩ፦ “በዚህ ሰው ላይ ምንም ጥፋት አላገኘንም፤ መንፈስ ወይም መልአክ አናግሮት ከሆነ ግን+ . . . ።” 10 በመካከላቸው የተፈጠረው ግጭት እየከረረ ሲሄድ የሠራዊቱ ሻለቃ ጳውሎስን እንዳይገነጣጥሉት ፈርቶ ወታደሮቹ ወርደው ከመካከላቸው ነጥቀው እንዲያመጡትና ወደ ጦር ሰፈሩ እንዲያስገቡት አዘዘ።

11 ሆኖም በዚያኑ ዕለት ሌሊት ጌታ በጳውሎስ አጠገብ ቆሞ እንዲህ አለው፦ “አይዞህ፣ አትፍራ!+ ምክንያቱም በኢየሩሳሌም ስለ እኔ በሚገባ እንደመሠከርክ* ሁሉ በሮምም ልትመሠክርልኝ ይገባል።”+

12 በነጋም ጊዜ አይሁዳውያን በጳውሎስ ላይ በማሴር እሱን እስኪገድሉ ድረስ እህል ውኃ ላለመቅመስ ተማማሉ።* 13 ይህን ሴራ ለመፈጸም የተማማሉት ሰዎች ቁጥራቸው ከ40 በላይ ነበር። 14 እነሱም ወደ ካህናት አለቆቹና ወደ ሽማግሌዎቹ ሄደው እንዲህ አሉ፦ “ጳውሎስን እስክንገድል ድረስ አንዳች እህል ላለመቅመስ ጽኑ መሐላ ተማምለናል። 15 ስለዚህ እናንተ ከሳንሄድሪን ሸንጎ ጋር ሆናችሁ የጳውሎስን ጉዳይ ይበልጥ ማጣራት የምትፈልጉ በማስመሰል እሱን ወደ እናንተ እንዲያመጣው ለሠራዊቱ ሻለቃ ንገሩት። ይሁንና እኛ እዚህ ከመድረሱ በፊት እሱን ለመግደል ተዘጋጅተን እንጠብቃለን።”

16 ይሁን እንጂ የጳውሎስ የእህቱ ልጅ አድብተው ጥቃት ለመሰንዘር እንዳሰቡ በመስማቱ ወደ ጦር ሰፈሩ ገብቶ ጉዳዩን ለጳውሎስ ነገረው። 17 ጳውሎስም ከመኮንኖቹ አንዱን ጠርቶ “ይህ ወጣት ለሠራዊቱ ሻለቃ የሚነግረው ነገር ስላለው ወደ እሱ ውሰደው” አለው። 18 እሱም ወደ ሻለቃው ይዞት ሄደና “እስረኛው ጳውሎስ ጠርቶኝ ይህ ወጣት የሚነግርህ ነገር ስላለው ወደ አንተ እንዳቀርበው ጠየቀኝ” አለው። 19 ሻለቃውም እጁን ይዞ ለብቻው ገለል ካደረገው በኋላ “ልትነግረኝ የፈለግከው ነገር ምንድን ነው?” ሲል ጠየቀው። 20 እሱም እንዲህ አለ፦ “አይሁዳውያን ስለ ጳውሎስ ጉዳይ በዝርዝር ማወቅ የፈለጉ በማስመሰል ነገ ወደ ሳንሄድሪን ሸንጎ እንድታመጣው ሊጠይቁህ ተስማምተዋል።+ 21 አንተ ግን በዚህ እንዳትታለል፤ ምክንያቱም ከመካከላቸው ከ40 በላይ የሚሆኑ ሰዎች አድብተው በእሱ ላይ ጥቃት ለመሰንዘር እየጠበቁ ነው፤ ደግሞም እሱን እስኪገድሉ ድረስ እህልም ሆነ ውኃ ላለመቅመስ ተማምለዋል፤+ አሁንም ተዘጋጅተው የአንተን ፈቃድ እየተጠባበቁ ነው።” 22 በዚህ ጊዜ የሠራዊቱ ሻለቃ “ይህን ነገር ለእኔ መንገርህን ለማንም እንዳታወራ” ብሎ ካዘዘው በኋላ ወጣቱን አሰናበተው።

23 ከዚያም ከመኮንኖቹ መካከል ሁለቱን ጠርቶ እንዲህ አላቸው፦ “ከምሽቱ ሦስት ሰዓት ላይ ወደ ቂሳርያ የሚሄዱ 200 ወታደሮች እንዲሁም 70 ፈረሰኞችና ጦር የያዙ 200 ሰዎች አዘጋጁ። 24 በተጨማሪም ጳውሎስን ወደ አገረ ገዢው ወደ ፊሊክስ በደህና ለማድረስ የሚጓዝባቸው ፈረሶች አዘጋጁ።” 25 እንዲህ የሚል ደብዳቤም ጻፈ፦

26 “ከቀላውዴዎስ ሉስዮስ፤ ለክቡር አገረ ገዢ ለፊሊክስ፦ ሰላም ለአንተ ይሁን። 27 አይሁዳውያን ይህን ሰው ይዘው ሊገድሉት ነበር፤ ሆኖም የሮም ዜጋ መሆኑን ስላወቅኩ+ ወዲያውኑ ከወታደሮቼ ጋር ደርሼ አዳንኩት።+ 28 እሱን የከሰሱት ለምን እንደሆነ ለማወቅ ስለፈለግኩም ወደ ሳንሄድሪን ሸንጓቸው አቀረብኩት።+ 29 የተከሰሰውም ከሕጋቸው ጋር በተያያዘ በተነሳ ውዝግብ እንደሆነ ተረድቻለሁ፤+ ሆኖም ለሞት ወይም ለእስር የሚያበቃ አንድም ክስ አላገኘሁም። 30 ይሁንና በዚህ ሰው ላይ የተሸረበ ሴራ እንዳለ ስለተነገረኝ+ ወዲያውኑ ወደ አንተ ልኬዋለሁ፤ ከሳሾቹም ክሳቸውን በአንተ ፊት እንዲያቀርቡ አዝዤአቸዋለሁ።”

31 ስለዚህ ወታደሮቹ በታዘዙት መሠረት ጳውሎስን ይዘው+ በሌሊት ወደ አንቲጳጥሪስ ወሰዱት። 32 በማግስቱም ፈረሰኞቹ ከጳውሎስ ጋር ጉዟቸውን እንዲቀጥሉ በማድረግ እነሱ ወደ ጦር ሰፈሩ ተመለሱ። 33 ፈረሰኞቹም ቂሳርያ በደረሱ ጊዜ ደብዳቤውን ለአገረ ገዢው ሰጡት፤ ጳውሎስንም አስረከቡት። 34 እሱም ደብዳቤውን ካነበበ በኋላ የየትኛው አውራጃ ሰው እንደሆነ ጠየቀ፤ የኪልቅያ ሰው መሆኑንም ተረዳ።+ 35 ከዚያም “ከሳሾችህ ሲመጡ ጉዳይህን በደንብ አየዋለሁ” አለው።+ በሄሮድስም ቤተ መንግሥት ውስጥ በጥበቃ ሥር ሆኖ እንዲቆይ አዘዘ።

24 ከአምስት ቀን በኋላ ሊቀ ካህናቱ ሐናንያ+ ከተወሰኑ ሽማግሌዎችና ጠርጡለስ ከሚባል ጠበቃ ጋር ወደ ቂሳርያ ወረደ፤ እነሱም በጳውሎስ ላይ ያላቸውን ክስ ለአገረ ገዢው አቀረቡ።+ 2 በተጠራም ጊዜ ጠርጡለስ እንዲህ ሲል ይከሰው ጀመር፦

“ክቡር ፊሊክስ ሆይ፣ በአንተ አማካኝነት ብዙ ሰላም አግኝተናል፤ አስተዋይነትህም ለዚህ ሕዝብ መሻሻል አስገኝቷል፤ 3 በማንኛውም ጊዜና በየትኛውም ቦታ ለእነዚህ ነገሮች ሁሉ ታላቅ ምስጋና እናቀርባለን። 4 ይሁንና አሁን ጊዜህን እንዳልወስድብህ በአጭሩ የምንነግርህን ጉዳይ መልካም ፈቃድህ ሆኖ እንድትሰማን እለምንሃለሁ። 5 ይህ ሰው መቅሰፍት* ሆኖብናል፤+ በዓለም ባሉት አይሁዳውያን ሁሉ መካከል ዓመፅ ያነሳሳል፤+ ከዚህም ሌላ የናዝሬታውያን ኑፋቄ ቀንደኛ መሪ ነው።+ 6 በዚህ ላይ ደግሞ ቤተ መቅደሱን ለማርከስ ሲሞክር ስላገኘነው ያዝነው።+ 7 *—— 8 አንተ ራስህ ስትመረምረው በእሱ ላይ ያቀረብነው ክስ ትክክል መሆኑን ማረጋገጥ ትችላለህ።”

9 አይሁዳውያኑም የተባለው ነገር ሁሉ እውነት መሆኑን በመግለጽ በክሱ ተባበሩ። 10 አገረ ገዢውም እንዲናገር በጭንቅላቱ ምልክት በሰጠው ጊዜ ጳውሎስ እንዲህ ሲል መለሰ፦

“ለብዙ ዓመታት ለዚህ ሕዝብ ፈራጅ ሆነህ ስታገለግል መቆየትህን አውቃለሁ፤ በመሆኑም ስለ ራሴ የመከላከያ መልስ የማቀርበው በደስታ ነው።+ 11 ለአምልኮ ወደ ኢየሩሳሌም ከወጣሁ ከ12 ቀን እንደማይበልጥ አንተው ራስህ ማረጋገጥ ትችላለህ፤+ 12 እንዲሁም በቤተ መቅደሱ ከማንም ጋር ስከራከርም ሆነ በምኩራቦች ወይም በከተማው ውስጥ ሕዝቡን ለዓመፅ ሳነሳሳ አላገኙኝም። 13 በተጨማሪም አሁን ላቀረቡብኝ ክስ ሁሉ ምንም ማስረጃ ሊያቀርቡልህ አይችሉም። 14 ይሁን እንጂ በሕጉና በነቢያት የተጻፉትን ነገሮች ሁሉ+ ስለማምን እነሱ ኑፋቄ ብለው የሚጠሩትን የሕይወት መንገድ እንደምከተልና በዚህም መንገድ ለአባቶቼ አምላክ ቅዱስ አገልግሎት እንደማቀርብ አልክድም።+ 15 ደግሞም እነዚህ ሰዎች ራሳቸው ተስፋ እንደሚያደርጉት ጻድቃንም ሆኑ ጻድቃን ያልሆኑ ሰዎች+ ከሞት እንደሚነሱ+ በአምላክ ተስፋ አለኝ። 16 በዚህ የተነሳ በአምላክም ሆነ በሰው ፊት ንጹሕ* ሕሊና ይዤ ለመኖር ሁልጊዜ ጥረት አደርጋለሁ።+ 17 ከብዙ ዓመታት በኋላም ለወገኖቼ ምጽዋት ለመስጠትና+ ለአምላክ መባ ለማቅረብ መጣሁ። 18 በቤተ መቅደሱ ውስጥ ያገኙኝ የመንጻት ሥርዓት ፈጽሜ+ ይህንኑ ሳደርግ እንጂ ከብዙ ሕዝብ ጋር ሆኜ ሁከት ሳነሳሳ አልነበረም። ሆኖም ከእስያ አውራጃ የመጡ አንዳንድ አይሁዳውያን ነበሩ፤ 19 እነሱ እኔን የሚከሱበት ነገር ካላቸው እዚህ ፊትህ ተገኝተው ሊከሱኝ ይገባ ነበር።+ 20 ወይም እዚህ ያሉት ሰዎች በሳንሄድሪን ሸንጎ ፊት በቀረብኩበት ጊዜ ያገኙብኝ ጥፋት ካለ እነሱ ራሳቸው ይናገሩ፤ 21 በመካከላቸው ቆሜ በነበረበት ጊዜ ድምፄን ከፍ አድርጌ ‘ዛሬ በፊታችሁ ለፍርድ የቀረብኩት በሙታን ትንሣኤ በማመኔ ነው!’ ብዬ ከመናገር በቀር ያደረግኩት ነገር የለም።”+

22 ይሁን እንጂ ፊሊክስ ስለ ጌታ መንገድ+ በሚገባ ያውቅ ስለነበረ “የሠራዊቱ ሻለቃ ሉስዮስ ሲመጣ ለጉዳያችሁ ውሳኔ እሰጣለሁ” በማለት ያቀረቡትን ክስ ለሌላ ጊዜ አስተላለፈው። 23 ከዚያም ጳውሎስ በቁጥጥር ሥር እንዲቆይ፣ ይሁንና መጠነኛ ነፃነት እንዲሰጠው መኮንኑን አዘዘው፤ ደግሞም ወዳጆቹ የሚያስፈልገውን ነገር ለማድረግ ሲመጡ እንዲፈቅድላቸው መመሪያ ሰጠው።

24 ከተወሰኑ ቀናት በኋላ ፊሊክስ አይሁዳዊት ከሆነችው ሚስቱ ከድሩሲላ ጋር መጣ፤ ጳውሎስንም አስጠርቶ በክርስቶስ ኢየሱስ ስለ ማመን ሲናገር አዳመጠው።+ 25 ጳውሎስ ስለ ጽድቅ፣ ራስን ስለ መግዛትና ስለሚመጣው ፍርድ+ ሲናገር ግን ፊሊክስ ፈርቶ “ለአሁኑ ይበቃል፤ አጋጣሚ ሳገኝ ግን እንደገና አስጠራሃለሁ” አለው። 26 በዚሁ አጋጣሚ ጳውሎስ ጉቦ ይሰጠኛል ብሎ ተስፋ ያደርግ ስለነበር ብዙ ጊዜ እያስጠራ ያነጋግረው ነበር። 27 ይሁንና ሁለት ዓመት ካለፈ በኋላ ፊሊክስ በጶርቅዮስ ፊስጦስ ተተካ፤ በዚህ ጊዜ ፊሊክስ በአይሁዳውያን ዘንድ ተወዳጅነት ማትረፍ ስለፈለገ+ ጳውሎስን እንደታሰረ ተወው።

25 ፊስጦስም+ ወደ አውራጃው ከመጣና ኃላፊነቱን ከተረከበ ከሦስት ቀን በኋላ ከቂሳርያ ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ። 2 የካህናት አለቆችና አንዳንድ የታወቁ አይሁዳውያንም በጳውሎስ ላይ ያላቸውን ክስ ለእሱ አቀረቡ።+ ከዚያም ፊስጦስን ይለምኑት ጀመር፤ 3 ጳውሎስን ወደ ኢየሩሳሌም በማስመጣት እንዲተባበራቸው* ጠየቁት። ይህን ያሉት ግን መንገድ ላይ አድፍጠው ጳውሎስን ሊገድሉት አስበው ስለነበር ነው።+ 4 ይሁን እንጂ ፊስጦስ፣ ጳውሎስ እዚያው ቂሳርያ ታስሮ እንደሚቆይና እሱ ራሱም በቅርቡ ወደዚያ እንደሚመለስ ነገራቸው። 5 “በመሆኑም ከእናንተ መካከል ሥልጣን ያላቸው ከእኔ ጋር ይውረዱና ሰውየው ያጠፋው ነገር ካለ ይክሰሱት” አላቸው።+

6 ስለዚህ ፊስጦስ ከስምንት ወይም ከአሥር ቀን ያልበለጠ ጊዜ ከእነሱ ጋር ካሳለፈ በኋላ ወደ ቂሳርያ ወረደ፤ በማግስቱም በፍርድ ወንበር ላይ ተቀምጦ ጳውሎስን እንዲያመጡት አዘዘ። 7 ጳውሎስ በቀረበ ጊዜ ከኢየሩሳሌም የመጡት አይሁዳውያን በዙሪያው ቆመው በማስረጃ ያልተደገፉ በርካታ ከባድ ክሶች አቀረቡበት።+

8 ጳውሎስ ግን “እኔ በአይሁዳውያን ሕግ ላይም ሆነ በቤተ መቅደሱ ወይም በቄሳር ላይ ምንም የፈጸምኩት በደል የለም” ሲል የመከላከያ መልሱን ሰጠ።+ 9 ፊስጦስም በአይሁዳውያን ዘንድ ተወዳጅነት ማትረፍ ስለፈለገ+ ጳውሎስን “ወደ ኢየሩሳሌም ወጥተህ ስለዚህ ጉዳይ እዚያ እኔ ባለሁበት መዳኘት ትፈልጋለህ?” ሲል ጠየቀው። 10 ጳውሎስ ግን እንዲህ አለ፦ “እኔ ልዳኝበት በሚገባኝ በቄሳር የፍርድ ወንበር ፊት ቆሜአለሁ። አንተ ራስህ በሚገባ እንደተገነዘብከው በአይሁዳውያን ላይ የፈጸምኩት ምንም በደል የለም። 11 በእርግጥ ጥፋተኛ ሆኜ ከተገኘሁና ለሞት የሚያበቃ ነገር ፈጽሜ ከሆነ+ ከሞት ልዳን አልልም፤ እነዚህ ሰዎች ያቀረቡብኝ ክስ ሁሉ መሠረተ ቢስ ከሆነ ግን እነሱን ለማስደሰት ብሎ ማንም ሰው እኔን ለእነሱ አሳልፎ የመስጠት መብት የለውም። ወደ ቄሳር ይግባኝ ብያለሁ!”+ 12 በዚህ ጊዜ ፊስጦስ ከአማካሪዎቹ ጋር ከተመካከረ በኋላ “ወደ ቄሳር ይግባኝ ስላልክ ወደ ቄሳር ትሄዳለህ” ሲል መለሰለት።

13 የተወሰኑ ቀናት ካለፉ በኋላ ንጉሥ አግሪጳና* በርኒቄ ለፊስጦስ ክብር ይፋዊ ጉብኝት ለማድረግ ወደ ቂሳርያ መጡ። 14 በዚያም ብዙ ቀናት ስለቆዩ ፊስጦስ የጳውሎስን ጉዳይ ለንጉሡ በማቅረብ እንዲህ አለው፦

“ፊሊክስ እስር ቤት የተወው አንድ ሰው አለ፤ 15 ኢየሩሳሌም በነበርኩበት ጊዜ የካህናት አለቆቹና የአይሁዳውያን ሽማግሌዎች ይህን ሰው በመክሰስ+ እንዲፈረድበት ጥያቄ አቅርበው ነበር። 16 እኔ ግን ክስ የቀረበበት ሰው ከከሳሾቹ ጋር ፊት ለፊት ተገናኝቶ ለቀረበበት ክስ የመከላከያ መልስ መስጠት የሚችልበት አጋጣሚ ሳያገኝ እንዲሁ ሰውን ለማስደሰት ተብሎ ብቻ አሳልፎ መስጠት የሮማውያን ሥርዓት እንዳልሆነ ገለጽኩላቸው።+ 17 ስለዚህ ከሳሾቹ ወደዚህ በመጡ ጊዜ ምንም ሳልዘገይ በማግስቱ በፍርድ ወንበር ላይ ተቀምጬ ሰውየውን እንዲያመጡት አዘዝኩ። 18 ከሳሾቹም ቆመው በተናገሩ ጊዜ እኔ የጠበቅኩትን ያህል ከባድ በደል እንደፈጸመ የሚያሳይ ክስ አላቀረቡበትም።+ 19 ከዚህ ይልቅ ከእሱ ጋር ይከራከሩ የነበረው ስለ ገዛ አምልኳቸውና*+ ስለሞተው፣ ጳውሎስ ግን ሕያው ነው ስለሚለው ኢየሱስ ስለተባለ ሰው ነው።+ 20 እኔም ይህን ክርክር እንዴት እንደምፈታው ግራ ስለገባኝ ጳውሎስ ወደ ኢየሩሳሌም ሄዶ ስለዚህ ጉዳይ እዚያ መፋረድ ይፈልግ እንደሆነ ጠየቅኩት።+ 21 ጳውሎስ ግን አውግስጦስ* ውሳኔ እስኪሰጥ ድረስ ታስሮ እንዲቆይ ይግባኝ ጠየቀ፤+ በመሆኑም ወደ ቄሳር እስከምልከው ድረስ በእስር ቤት እንዲቆይ አዘዝኩ።”

22 በዚህ ጊዜ አግሪጳ ፊስጦስን “እኔም ይህ ሰው ሲናገር ብሰማው ደስ ይለኝ ነበር” አለው።+ እሱም “እንግዲያውስ ነገ ትሰማዋለህ” አለው። 23 ስለዚህ በማግስቱ አግሪጳና በርኒቄ በታላቅ ክብር ደምቀው እንዲሁም በሻለቃዎችና በከተማዋ ታላላቅ ሰዎች ታጅበው ወደ መሰብሰቢያ አዳራሹ ገቡ፤ ፊስጦስም ትእዛዝ በሰጠ ጊዜ ጳውሎስ እንዲቀርብ ተደረገ። 24 ፊስጦስም እንዲህ አለ፦ “ንጉሥ አግሪጳና ከእኛ ጋር እዚህ የተሰበሰባችሁ ሁሉ፣ ይህ የምታዩት ሰው በኢየሩሳሌምም ሆነ እዚህ፣ አይሁዳውያን ሁሉ ከእንግዲህ በሕይወት ሊኖር አይገባውም እያሉ በመጮኽ ለእኔ አቤቱታ ያቀረቡበት ሰው ነው።+ 25 እኔ ግን ለሞት የሚያበቃ ምንም ነገር እንዳልፈጸመ ተረድቻለሁ።+ በመሆኑም እሱ ራሱ ወደ አውግስጦስ ይግባኝ ስላለ ልልከው ወስኛለሁ። 26 ይሁንና ስለ እሱ ወደ ጌታዬ የምጽፈው ምንም የተረጋገጠ ነገር አላገኘሁም። ስለዚህ አሁን በችሎቱ ፊት ከተመረመረ በኋላ ልጽፈው የምችለው ነገር አገኝ ዘንድ በእናንተ ሁሉ ፊት በተለይ ደግሞ በአንተ በንጉሥ አግሪጳ ፊት አቀረብኩት። 27 ምክንያቱም አንድን እስረኛ የተከሰሰበትን ምክንያት ሳይገልጹ መላክ ተገቢ አልመሰለኝም።”

26 አግሪጳ+ ጳውሎስን “ስለ ራስህ እንድትናገር ተፈቅዶልሃል” አለው። በዚህ ጊዜ ጳውሎስ እጁን ዘርግቶ እንዲህ ሲል የመከላከያ መልሱን ይሰጥ ጀመር፦

2 “ንጉሥ አግሪጳ ሆይ፣ አይሁዳውያን በእኔ ላይ ያቀረቡትን ክስ+ ሁሉ በተመለከተ ዛሬ በአንተ ፊት የመከላከያ መልስ መስጠት በመቻሌ እጅግ ደስተኛ ነኝ፤ 3 በተለይ ደግሞ አንተ የአይሁዳውያንን ልማዶችና በመካከላቸው ያሉትን ክርክሮች ሁሉ ጠንቅቀህ ታውቃለህ። ስለዚህ በትዕግሥት እንድታዳምጠኝ እለምንሃለሁ።

4 “ገና ከልጅነቴ በሕዝቤ መካከልም ሆነ በኢየሩሳሌም እንዴት እንደኖርኩ አይሁዳውያን ሁሉ በሚገባ ያውቃሉ፤+ 5 ከድሮ ጀምሮ የሚያውቁኝ ሰዎች ሊመሠክሩ ፈቃደኞች ቢሆኑ ኖሮ በሃይማኖታችን ውስጥ ወግ አጥባቂ የሆነውን ቡድን በመከተል+ ፈሪሳዊ ሆኜ እንደኖርኩ ያውቃሉ።+ 6 አሁን ግን እዚህ ለፍርድ የቀረብኩት አምላክ ለአባቶቻችን የገባውን ቃል ተስፋ በማድረጌ ነው፤+ 7 ደግሞም 12ቱ ነገዶቻችን ለአምላክ ቀንና ሌሊት በትጋት ቅዱስ አገልግሎት በማቅረብ እየተጠባበቁ ያሉት የዚህኑ ተስፋ ፍጻሜ ነው። ንጉሥ ሆይ፣ አይሁዶች የከሰሱኝ በዚህ ተስፋ ምክንያት ነው።+

8 “አምላክ ሙታንን የሚያስነሳ መሆኑ ሊታመን የማይችል ነገር እንደሆነ አድርጋችሁ የምታስቡት* ለምንድን ነው? 9 እኔ ራሴ የናዝሬቱ ኢየሱስን ስም በተቻለኝ መጠን መቃወም እንዳለብኝ አምን ነበር። 10 ደግሞም በኢየሩሳሌም ያደረግኩት ይህንኑ ነው፤ ከካህናት አለቆችም ሥልጣን ተቀብዬ+ ብዙ ቅዱሳንን ወህኒ ቤት አስገብቻለሁ፤+ እንዲገደሉም የድጋፍ ድምፅ ሰጥቻለሁ። 11 ብዙ ጊዜም በየምኩራቡ እነሱን እየቀጣሁ እምነታቸውን በይፋ እንዲክዱ ለማስገደድ ሞክሬአለሁ፤ በእነሱ ላይ እጅግ ተቆጥቼ በሌሎች ከተሞች ያሉትን እንኳ ሳይቀር እስከ ማሳደድ ደርሻለሁ።

12 “ይህን እያከናወንኩ በነበረበት ወቅት ከካህናት አለቆች ሥልጣንና ተልእኮ ተቀብዬ ወደ ደማስቆ እየተጓዝኩ ሳለ 13 ንጉሥ ሆይ፣ እኩለ ቀን ሲሆን በመንገድ ላይ ከፀሐይ ብርሃን የበለጠ ድምቀት ያለው ከሰማይ የመጣ ብርሃን በእኔና አብረውኝ በሚጓዙት ሰዎች ዙሪያ ሲያበራ አየሁ።+ 14 ሁላችንም መሬት ላይ በወደቅን ጊዜ አንድ ድምፅ በዕብራይስጥ ቋንቋ ‘ሳኦል፣ ሳኦል ለምን ታሳድደኛለህ? መውጊያውን* መቃወምህን ከቀጠልክ ለአንተው የባሰ ይሆንብሃል’ ሲለኝ ሰማሁ። 15 እኔም ‘ጌታዬ፣ አንተ ማን ነህ?’ አልኩ። ጌታም እንዲህ አለኝ፦ ‘እኔ አንተ የምታሳድደኝ ኢየሱስ ነኝ። 16 ይሁንና አሁን ተነስተህ በእግርህ ቁም። የተገለጥኩልህ እኔን በተመለከተ ስላየኸው ነገርና ወደፊት ስለማሳይህ ነገር አገልጋይና ምሥክር እንድትሆን አንተን ለመምረጥ ነው።+ 17 ወደ እነሱ ከምልክህ ከዚህ ሕዝብና ከአሕዛብ እታደግሃለሁ፤+ 18 የምልክህም የኃጢአት ይቅርታ ያገኙና+ በእኔ ላይ ባላቸው እምነት አማካኝነት በተቀደሱት መካከል ርስት ይቀበሉ ዘንድ ዓይናቸውን እንድትገልጥ+ እንዲሁም ከጨለማ+ ወደ ብርሃን፣+ ከሰይጣን ሥልጣንም+ ወደ አምላክ እንድትመልሳቸው ነው።’

19 “በመሆኑም ንጉሥ አግሪጳ ሆይ፣ ከሰማይ ለተገለጠልኝ ራእይ አልታዘዝም አላልኩም፤ 20 ከዚህ ይልቅ በመጀመሪያ በደማስቆ+ ላሉ ቀጥሎም በኢየሩሳሌምና+ በመላው የይሁዳ አገር ሁሉ ለሚገኙ ከዚያም ለአሕዛብ ንስሐ እንዲገቡና ለንስሐ የሚገባ ሥራ+ በመሥራት ወደ አምላክ እንዲመለሱ የሚያሳስበውን መልእክት ማዳረሴን ቀጠልኩ። 21 አይሁዳውያኑ በቤተ መቅደሱ ውስጥ የያዙኝና ሊገድሉኝ የሞከሩት በዚህ የተነሳ ነው።+ 22 ይሁን እንጂ ከአምላክ እርዳታ በማግኘቴ እስከዚህ ቀን ድረስ ለትንሹም ሆነ ለትልቁ መመሥከሬን ቀጥያለሁ፤ ነቢያትና ሙሴ ይፈጸማል ብለው ከተናገሩት በስተቀር ምንም የተናገርኩት ነገር የለም፤+ 23 እነሱም የተናገሩት ክርስቶስ መከራ እንደሚቀበልና+ ከሙታን የመጀመሪያ ሆኖ በመነሳት+ ለዚህ ሕዝብም ሆነ ለአሕዛብ ስለ ብርሃን እንደሚያውጅ ነው።”+

24 ጳውሎስ የመከላከያ መልሱን እየሰጠ ሳለ ፊስጦስ ጮክ ብሎ “ጳውሎስ አሁንስ አእምሮህን ልትስት ነው! ብዙ መማር አእምሮህን እያሳተህ ነው!” አለ። 25 ጳውሎስ ግን እንዲህ አለ፦ “ክቡር ፊስጦስ ሆይ፣ አእምሮዬን እየሳትኩ አይደለም፤ እኔ እየተናገርኩ ያለሁት እውነተኛ እንዲሁም ከጤናማ አእምሮ የሚመነጭ ቃል ነው። 26 እንደ እውነቱ ከሆነ በነፃነት እያናገርኩት ያለሁት ንጉሥ ስለ እነዚህ ነገሮች በሚገባ ያውቃል፤ እነዚህ ነገሮች በድብቅ የተፈጸሙ ባለመሆናቸው አንዳቸውም ቢሆኑ ከእሱ የተሰወሩ እንዳልሆኑ እርግጠኛ ነኝ።+ 27 ንጉሥ አግሪጳ ሆይ፣ በነቢያት ታምናለህ? እንደምታምን አውቃለሁ።” 28 አግሪጳም ጳውሎስን “በአጭር ጊዜ ውስጥ አሳምነህ ክርስቲያን ልታደርገኝ እኮ ምንም አልቀረህም” አለው። 29 በዚህ ጊዜ ጳውሎስ “በአጭርም ሆነ በረጅም ጊዜ አንተ ብቻ ሳትሆን ዛሬ እየሰሙኝ ያሉት ሁሉ ከእስራቴ በስተቀር እንደ እኔ እንዲሆኑ አምላክን እለምናለሁ” አለ።

30 ከዚያም ንጉሡ ተነሳ፤ አገረ ገዢው፣ በርኒቄና አብረዋቸው ተቀምጠው የነበሩት ሰዎችም ተነሱ። 31 እየወጡ ሳሉም እርስ በርሳቸው “ይህ ሰው ለሞት ወይም ለእስራት የሚያበቃ ምንም ነገር አላደረገም” ተባባሉ።+ 32 ከዚያም አግሪጳ ፊስጦስን “ይህ ሰው ወደ ቄሳር ይግባኝ ባይል ኖሮ ሊፈታ ይችል ነበር” አለው።+

27 እኛም በመርከብ ወደ ጣሊያን እንድንሄድ ስለተወሰነ+ ጳውሎስንና የተወሰኑ እስረኞችን የአውግስጦስ ክፍለ ጦር አባል ለሆነ ዩልዮስ ለሚባል አንድ የጦር መኮንን አስረከቧቸው። 2 ከአድራሚጢስ ተነስቶ በእስያ አውራጃ የባሕር ዳርቻ ላይ ወደሚገኙት ወደቦች ሊሄድ በተዘጋጀ መርከብ ተሳፍረን ጉዞ ጀመርን፤ በተሰሎንቄ የሚኖረው የመቄዶንያው አርስጥሮኮስም+ አብሮን ነበር። 3 በማግስቱ ሲዶና ደረስን፤ ዩልዮስም ለጳውሎስ ደግነት* በማሳየት ወደ ወዳጆቹ እንዲሄድና እንክብካቤ እንዲያደርጉለት ፈቀደለት።

4 ከዚያም ተነስተን በባሕር ላይ ጉዟችንን ቀጠልን፤ ነፋሱ ከፊት ለፊታችን ይነፍስ ስለነበር ቆጵሮስን ተገን አድርገን አለፍን። 5 ከዚያም በኪልቅያና በጵንፍልያ ዳርቻ በኩል ያለውን ባሕር አቋርጠን በሊቂያ ወደሚገኘው የሚራ ወደብ ደረስን። 6 በዚያም መኮንኑ ወደ ጣሊያን የሚሄድ ከእስክንድርያ የመጣ መርከብ አግኝቶ አሳፈረን። 7 ከዚያም ለብዙ ቀናት በዝግታ ተጉዘን በስንት ችግር ቀኒዶስ ደረስን። ነፋሱ እንደ ልብ እንድንጓዝ ስላልፈቀደልን በስልሞና በኩል ቀርጤስን ተገን አድርገን አለፍን። 8 የባሕሩን ዳርቻ ይዘን በብዙ ችግር በመጓዝ በላሲያ ከተማ አቅራቢያ ወዳለው “መልካም ወደብ” ወደተባለ ስፍራ ደረስን።

9 ረጅም ጊዜ በመቆየታችንና የስርየት ቀን+ ጾም እንኳ ሳይቀር በማለፉ፣ ወቅቱ በባሕር ላይ ለመጓዝ አደገኛ ነበር፤ በመሆኑም ጳውሎስ አንድ ሐሳብ አቀረበ፤ 10 እንዲህም አላቸው፦ “እናንተ ሰዎች፣ ይህ ጉዞ በጭነቱና በመርከቡ ላይ ብቻ ሳይሆን በሕይወታችንም* ላይ እንኳ ሳይቀር ከፍተኛ ጉዳትና ጥፋት ሊያስከትል እንደሚችል ይታየኛል።” 11 ይሁን እንጂ መኮንኑ ጳውሎስ የተናገረውን ከመቀበል ይልቅ የመርከቡ መሪና የመርከቡ ባለቤት የተናገሩትን ሰማ። 12 ወደቡ የክረምቱን ጊዜ በዚያ ለማሳለፍ አመቺ ስላልነበረ አብዛኞቹ ከዚያ ተነስተው ጉዟቸውን በመቀጠል እንደ ምንም ፊንቄ ወደተባለው የቀርጤስ ወደብ ደርሰው ክረምቱን እዚያ ለማሳለፍ ሐሳብ አቀረቡ፤ ይህ ወደብ ወደ ሰሜን ምሥራቅም ሆነ ወደ ደቡብ ምሥራቅ ለመሄድ የሚያስችል ነበር።

13 የደቡብ ነፋስ በቀስታ እየነፈሰ እንዳለ ባዩ ጊዜ እንዳሰቡት የሆነላቸው መስሏቸው መልሕቁን ነቅለው የቀርጤስን የባሕር ዳርቻ ይዘው መጓዝ ጀመሩ። 14 ይሁንና ብዙም ሳይቆይ አውራቂስ* የሚባል ኃይለኛ አውሎ ነፋስ ከደሴቲቱ ቁልቁል ነፈሰ። 15 መርከቡ እንቅስቃሴው ስለተገታና ነፋሱን ሰንጥቆ መሄድ ስላልቻለ ዝም ብለን በነፋሱ እየተነዳን ሄድን። 16 ከዚያም ቄዳ የተባለችውን ትንሽ ደሴት ተገን አድርገን በፍጥነት ተጓዝን፤ ሆኖም በመርከቡ ኋለኛ ክፍል የነበረችውን ትንሿን ጀልባ* መቆጣጠር የቻልነው በብዙ ችግር ነበር። 17 ጀልባዋ ወደ ላይ ተጎትታ ከተጫነች በኋላ መርከቡን ዙሪያውን በማሰር አጠናከሩት፤ ከስርቲስ* አሸዋማ ደለል ጋር እንዳይላተሙ ስለፈሩም የሸራውን ገመዶች በመፍታት ሸራውን ዝቅ ካደረጉ በኋላ በነፋስ እየተነዱ ሄዱ። 18 አውሎ ነፋሱ ክፉኛ እያንገላታን ስለነበር በማግስቱ የመርከቡን ጭነት ያቃልሉ ጀመር። 19 በሦስተኛውም ቀን ለመርከቡ የሚያገለግሉትን ቁሳቁሶች በገዛ እጃቸው ወደ ባሕሩ ወረወሩ።

20 ለብዙ ቀናት ፀሐይንም ሆነ ከዋክብትን ማየት ስላልቻልንና ውሽንፍሩ ስለበረታብን በመጨረሻ በሕይወት የመትረፍ ተስፋችን እየተሟጠጠ ሄደ። 21 ሰዎቹ እህል ሳይቀምሱ ብዙ ቀን ከቆዩ በኋላ ጳውሎስ በመካከላቸው ቆሞ እንዲህ አለ፦ “እናንተ ሰዎች፣ ምክሬን ሰምታችሁ ቢሆን ኖሮ ከቀርጤስ ባልተነሳችሁና ይህ ጉዳትና ኪሳራ ባልደረሰ ነበር።+ 22 አሁንም ቢሆን አይዟችሁ! ምክንያቱም መርከቡ ብቻ እንጂ ከእናንተ አንድም ሰው* አይጠፋም። 23 ቅዱስ አገልግሎት የማቀርብለትና ንብረቱ የሆንኩለት አምላክ የላከው መልአክ+ ትናንት ሌሊት አጠገቤ ቆሞ 24 ‘ጳውሎስ ሆይ፣ አትፍራ። ቄሳር ፊት መቅረብ ይገባሃል፤+ አምላክ ለአንተ ሲል ከአንተ ጋር የሚጓዙት ሰዎች ሁሉ እንዲተርፉ ያደርጋል’ ብሎኛል። 25 ስለዚህ እናንተ ሰዎች፣ አይዟችሁ! ምክንያቱም ይህ የተነገረኝ ነገር በትክክል እንደሚፈጸም በአምላክ ላይ እምነት አለኝ። 26 ይሁን እንጂ ከአንዲት ደሴት ዳርቻ ጋር መላተማችን የግድ ነው።”+

27 በ14ኛው ሌሊት በአድርያ ባሕር ላይ ወዲያና ወዲህ እየተንገላታን ሳለ እኩለ ሌሊት ላይ መርከበኞቹ ወደ አንድ የብስ የተቃረቡ መሰላቸው። 28 ጥልቀቱንም ሲለኩ 36 ሜትር ገደማ* ሆኖ አገኙት፤ ጥቂት ርቀት ከተጓዙም በኋላ በድጋሚ ሲለኩ 27 ሜትር ገደማ* ሆኖ አገኙት። 29 ከዓለት ጋር እንላተማለን ብለው ስለፈሩ ከመርከቡ የኋለኛ ክፍል አራት መልሕቆች ጥለው የሚነጋበትን ጊዜ በጉጉት መጠባበቅ ጀመሩ። 30 ሆኖም መርከበኞቹ ከመርከቡ የፊተኛ ክፍል መልሕቅ የሚጥሉ አስመስለው ትንሿን ጀልባ ወደ ባሕር በማውረድ ከመርከቡ ለማምለጥ ሲሞክሩ 31 ጳውሎስ መኮንኑንና ወታደሮቹን “እነዚህ ሰዎች መርከቡን ጥለው ከሄዱ ልትድኑ አትችሉም” አላቸው።+ 32 በዚህ ጊዜ ወታደሮቹ የትንሿን ጀልባ ገመዶች ቆርጠው ብቻዋን ተንሳፋ እንድትቀር አደረጓት።

33 ሊነጋ ሲል ጳውሎስ እንዲህ በማለት ምግብ እንዲቀምሱ ሁሉንም አበረታታቸው፦ “እህል የሚባል ነገር ሳትቀምሱ እንዲሁ ልባችሁ ተንጠልጥሎ ስትጠባበቁ ይኸው ዛሬ 14ኛ ቀናችሁ ነው። 34 ስለዚህ ለራሳችሁ ደህንነት ስለሚበጅ እህል እንድትቀምሱ እለምናችኋለሁ፤ ምክንያቱም ከእናንተ መካከል ከራስ ፀጉሩ አንድ እንኳ የሚጠፋበት የለም።” 35 ይህን ካለ በኋላ ዳቦ ወስዶ በሁሉ ፊት አምላክን አመሰገነ፤ ቆርሶም ይበላ ጀመር። 36 በዚህ ጊዜ ሁሉም ተበረታተው ምግብ እየወሰዱ ይበሉ ጀመር። 37 መርከቡ ላይ በአጠቃላይ 276 ሰዎች* ነበርን። 38 በልተው ከጠገቡ በኋላ ስንዴውን ወደ ባሕሩ በመጣል የመርከቡን ጭነት አቃለሉ።+

39 ሲነጋም የደረሱበትን አገር ለይተው ማወቅ አልቻሉም፤+ ሆኖም አሸዋማ የሆነ የባሕር ወሽመጥ ተመለከቱ፤ ስለዚህ እንደ ምንም ብለው መርከቡን ወደ ባሕሩ ዳርቻ ለማድረስ ወሰኑ። 40 በመሆኑም መልሕቆቹን ቆርጠው ባሕሩ ውስጥ ጣሉ፤ በዚያው ጊዜም የመቅዘፊያዎቹን ገመዶች ፈቱ፤ የፊተኛውንም ሸራ ነፋስ እንዲያገኘው ከፍ ካደረጉ በኋላ ወደ ባሕሩ ዳርቻ አመሩ። 41 ሆኖም ድንገት በባሕር ውስጥ ካለ የአሸዋ ቁልል ጋር ተላተሙ፤ በዚህ ጊዜ መርከቡ መሬት ስለነካ የፊተኛው ክፍሉ ሊንቀሳቀስ በማይችል ሁኔታ አሸዋው ውስጥ ተቀረቀረ፤ የመርከቡ የኋለኛ ክፍል ግን በማዕበል እየተመታ ይሰባበር ጀመር።+ 42 በዚህ ጊዜ ወታደሮቹ ከእስረኞቹ አንዳቸውም እንኳ ዋኝተው እንዳያመልጡ ሊገድሏቸው ወሰኑ። 43 መኮንኑ ግን ጳውሎስን ለማዳን ቆርጦ ስለነበር ያሰቡትን እንዳይፈጽሙ ከለከላቸው። ከዚያም መዋኘት የሚችሉ ወደ ባሕሩ እየዘለሉ እንዲገቡና ቀድመው ወደ የብስ እንዲደርሱ አዘዘ፤ 44 የቀሩትም ሰዎች አንዳንዶቹ በሳንቃዎች፣ ሌሎቹ ደግሞ በመርከቡ ስብርባሪዎች ላይ እየተንጠላጠሉ እንዲወጡ አዘዘ። በዚህ መንገድ ሁሉም በደህና ወደ የብስ ደረሱ።+

28 እኛም በደህና ወደ የብስ ደረስን፤ ደሴቲቱም ማልታ ተብላ እንደምትጠራ አወቅን።+ 2 የአካባቢው ነዋሪዎችም* የተለየ ደግነት* አሳዩን። ዝናብ መዝነብ ጀምሮ ስለነበረና ብርድ ስለነበር እሳት በማቀጣጠል ሁላችንንም በደግነት አስተናገዱን። 3 ይሁን እንጂ ጳውሎስ ጭራሮ ሰብስቦ እሳቱ ውስጥ ሲጨምር ከሙቀቱ የተነሳ እፉኝት ወጥታ እጁ ላይ ተጣበቀች። 4 ባዕድ ቋንቋ የሚናገሩትም ሰዎች እፉኝቷ እጁ ላይ ተንጠልጥላ ባዩ ጊዜ እርስ በርሳቸው “ይህ ሰው ነፍሰ ገዳይ መሆን አለበት፤ ከባሕሩ ተርፎ በደህና ቢወጣም እንኳ ፍትሕ* በሕይወት እንዲኖር አልፈቀደለትም” ይባባሉ ጀመር። 5 እሱ ግን እፉኝቷን እሳቱ ላይ አራገፋት፤ አንዳችም ጉዳት አልደረሰበትም። 6 ሆኖም ሰዎቹ ከአሁን አሁን ሰውነቱ ያብጣል ወይም ድንገት ወድቆ ይሞታል ብለው ይጠባበቁ ነበር። ብዙ ጠብቀው ምንም ጉዳት እንዳልደረሰበት ባዩ ጊዜ ሐሳባቸውን ለውጠው ይህ ሰው አምላክ ነው ይሉ ጀመር።

7 በዚያ አካባቢ፣ ፑፕልዮስ የተባለ የደሴቲቱ አስተዳዳሪ ርስት ነበረው፤ እሱም በእንግድነት ተቀብሎን ሦስት ቀን በደግነት አስተናገደን። 8 የፑፕልዮስ አባት ትኩሳትና ተቅማጥ ይዞት ተኝቶ ነበር፤ ጳውሎስም ወደ እሱ ገብቶ ጸለየለት፤ እጁንም ጫነበትና ፈወሰው።+ 9 ይህ ከሆነ በኋላ በደሴቲቱ የሚኖሩ የታመሙ ሌሎች ሰዎችም ወደ እሱ እየመጡ ይፈወሱ ጀመር።+ 10 በተጨማሪም ብዙ ስጦታ በመስጠት አክብሮታቸውን ገለጹልን፤ በመርከብ ለመሄድ በተዘጋጀን ጊዜም የሚያስፈልጉንን ነገሮች ሁሉ ጫኑልን።

11 ከሦስት ወር በኋላም “የዙስ ልጆች” የሚል ዓርማ ባለው መርከብ ጉዞ ጀመርን። ይህ መርከብ ከእስክንድርያ የመጣ ሲሆን ክረምቱን ያሳለፈው በዚህች ደሴት ነበር። 12 በስራኩስ ወደሚገኘው ወደብ ከደረስን በኋላ በዚያ ሦስት ቀን ቆየን፤ 13 ከዚያም ተነስተን በመጓዝ ሬጊዩም ደረስን። ከአንድ ቀን በኋላም የደቡብ ነፋስ ስለተነሳ በሁለተኛው ቀን ፑቲዮሉስ ደረስን። 14 በዚያም ወንድሞችን አገኘን፤ እነሱም ሰባት ቀን አብረናቸው እንድንቆይ ለመኑን፤ እነሱ ጋር ከቆየን በኋላ ወደ ሮም አመራን። 15 በዚያ የነበሩ ወንድሞች ስለ እኛ በሰሙ ጊዜ እስከ አፍዩስ የገበያ ስፍራና ሦስት ማደሪያ* እስከሚባለው ቦታ ድረስ ሊቀበሉን መጡ። ጳውሎስም ባያቸው ጊዜ አምላክን አመሰገነ፤ እንዲሁም ተበረታታ።+ 16 በመጨረሻም ሮም በደረስን ጊዜ ጳውሎስ አንድ ወታደር እየጠበቀው ብቻውን እንዲኖር ተፈቀደለት።

17 ይሁን እንጂ ከሦስት ቀን በኋላ የአይሁዳውያንን ታላላቅ ሰዎች አንድ ላይ ጠራ። ሰዎቹም በተሰበሰቡ ጊዜ እንዲህ አላቸው፦ “ወንድሞች፣ ምንም እንኳ ሕዝቡን ወይም የአባቶቻችንን ልማድ የሚጻረር ነገር ያልፈጸምኩ+ ቢሆንም በኢየሩሳሌም አስረው ለሮማውያን አሳልፈው ሰጥተውኛል።+ 18 እነሱም ከመረመሩኝ+ በኋላ ለሞት የሚያበቃ ምንም ጥፋት ስላላገኙብኝ ሊፈቱኝ ፈልገው ነበር።+ 19 ሆኖም አይሁዳውያን ይህን በተቃወሙ ጊዜ ለቄሳር ይግባኝ ለማለት ተገደድኩ፤+ ይህን ያደረግኩት ግን ሕዝቤን የምከስበት ነገር ኖሮኝ አይደለም። 20 እናንተንም ለማየትና ለማነጋገር ጥያቄ ያቀረብኩት ለዚህ ነው፤ በዚህ ሰንሰለት የታሰርኩትም ለእስራኤል በተሰጠው ተስፋ ምክንያት ነው።”+ 21 እነሱም እንዲህ አሉት፦ “ስለ አንተ የተጻፈ ከይሁዳ የመጣ ምንም ደብዳቤ አልደረሰንም፤ ከዚያ ከመጡት ወንድሞች መካከልም ስለ አንተ ክፉ ነገር የተናገረ ወይም ያወራ አንድም ሰው የለም። 22 ሆኖም ስለዚህ ኑፋቄ+ በየቦታው መጥፎ ነገር እንደሚወራ ስለምናውቅ+ የአንተን ሐሳብ ደግሞ መስማት ተገቢ ይመስለናል።”

23 በጉዳዩ ላይ ለመነጋገር ከእሱ ጋር ቀን ከወሰኑ በኋላ ብዙ ሆነው ወደ መኖሪያ ስፍራው መጡ። እሱም በኢየሱስ እንዲያምኑ ለማድረግ+ ከሙሴ ሕግና+ ከነቢያት+ እየጠቀሰ ከጠዋት ጀምሮ እስከ ማታ ድረስ ስለ አምላክ መንግሥት በሚገባ* በመመሥከር ጉዳዩን አብራራላቸው። 24 አንዳንዶቹ የተናገረውን ነገር ሲያምኑ ሌሎቹ ግን አላመኑም። 25 እርስ በርስ ሊስማሙ ስላልቻሉም ለመሄድ ተነሱ፤ በዚህ ጊዜ ጳውሎስ የሚከተለውን የመጨረሻ ሐሳብ ተናገረ፦

“መንፈስ ቅዱስ በነቢዩ ኢሳይያስ በኩል ለአባቶቻችሁ እንዲህ ሲል የተናገረው ቃል ትክክል ነበር፦ 26 ‘ወደዚህ ሕዝብ ሄደህ እንዲህ በላቸው፦ “መስማቱን ትሰማላችሁ፤ ግን በፍጹም አታስተውሉም፤ ማየቱን ታያላችሁ፤ ግን በፍጹም ልብ አትሉም።+ 27 ምክንያቱም በዓይናቸው አይተው፣ በጆሯቸው ሰምተው እንዲሁም በልባቸው አስተውለው ወደ እኔ እንዳይመለሱና እንዳልፈውሳቸው የዚህ ሕዝብ ልብ ደንድኗል፤ በጆሯቸው ሰምተው ምላሽ አልሰጡም፤ ዓይናቸውንም ጨፍነዋል።”’+ 28 ስለዚህ አምላክ ሰዎችን ስለሚያድንበት መንገድ የሚናገረው ይህ መልእክት ለአሕዛብ እንደተላከ እንድታውቁ እፈልጋለሁ፤+ እነሱም በእርግጥ ይሰሙታል።”+ 29 *——

30 ጳውሎስም በተከራየው ቤት ሁለት ዓመት ሙሉ ኖረ፤+ ወደ እሱ የሚመጡትንም ሁሉ በደግነት ያስተናግዳቸው ነበር፤ 31 ያለምንም እንቅፋት በታላቅ የመናገር ነፃነት* ስለ አምላክ መንግሥት ይሰብክላቸው የነበረ ከመሆኑም በላይ ስለ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ያስተምራቸው ነበር።+

ቃል በቃል “(ጊዜያትንና ወቅቶችን) በራሱ ሥልጣን ሥር ስላደረገ።”

ይህ 890 ሜትር (2,000 ክንድ፤ 2,920 ጫማ) ገደማ ነው። ከኢያሱ 3:4 ጋር አመሣክር።

ወይም “ከመካከሉ ፈነዳ።”

ቃል በቃል “በገባበትና በወጣበት።”

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።

ወይም “ተደመረ።” እንደ ሌሎቹ 11 ሐዋርያት መሆኑን ያመለክታል።

በግሪክኛ ጴንጤቆስጤ ማለት “ሃምሳኛ” ማለት ነው። ይህ በዓል ኒሳን 16 በዋለ በ50ኛው ቀን ላይ ይከበራል።

ወይም “ልሳኖች።”

ወይም “በአፍ መፍቻ ቋንቋችን።”

ወይም “አዲስ የወይን ጠጅ።”

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።

ወይም “ምክሩና።”

“እስራት” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።

ወይም “በዓይኔ ፊት።”

ቃል በቃል “ሥጋዬም በተስፋ ይኖራል።”

ወይም “በሐዲስ።” የሰው ልጆችን ሁሉ መቃብር ያመለክታል። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

ወይም “ነፍሴን በመቃብር አትተዋትም።”

ቃል በቃል “ከወገቡ ፍሬ አንዱን።”

ወይም “በሐዲስ።” የሰው ልጆችን ሁሉ መቃብር ያመለክታል። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

ወይም “እንደማይፈርስ።”

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።

ወይም “በተሟላ ሁኔታ።”

ወይም “ነፍሳት።”

ወይም “ያላቸውን ነገር አብረው ይካፈሉ።”

ወይም “እያንዳንዱ ነፍስ።”

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።

ቃል በቃል “የምሕረት ስጦታ።” ወይም “ለድሆች የሚሰጥ ስጦታ።” የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

ወይም “ሕይወት እንዲሰጥ የተሾመውን መሪ።”

ቃል በቃል “ከይሖዋም ፊት።” ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።

ወይም “ሰማይ በውስጡ ሊይዘው።”

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።

ወይም “ነፍስ ሁሉ።”

ረቢዎች ትምህርት ቤት ገብተው አለመማራቸውን ያመለክታል እንጂ መሃይም መሆናቸውን አያሳይም።

ወይም “ምልክት።”

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።

ወይም “በእሱ ክርስቶስ።”

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።

ወይም “አጥብቀው ከጸለዩም።”

የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።

ወይም “በዛፍ።”

ወይም “ጠርተው ደበደቧቸው።”

ወይም “በመልካም የተመሠከረላቸው።”

ቃል በቃል “በአገልግሎቱ።”

ወይም “እንደሚያንገላቷቸው።”

“ይስሐቅም በያዕቆብ ላይ እንዲሁ አደረገ” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ወይም “ፓትሪያርኮች።”

ወይም “ነፍሳት።” ዘፍ 46:20, 27 ላይ የሚገኙትን የግርጌ ማስታወሻዎች ተመልከት።

ብር ከተባለው ማዕድን የተሠራ ገንዘብ።

ወይም “ሦስት ወር አደገ።”

ወይም “ለማጣራት።”

ወይም “ለማየት ወሰነ።”

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።

“ወደ አንዲት የሰማርያ ከተማ” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።

ቃል በቃል “መራራ ሃሞትና።”

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።

ለኢትዮጵያ ንግሥቶች ይሰጥ የነበረ የማዕረግ ስም።

ወይም “የቤተ መንግሥት ባለሥልጣንም።”

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ3ን ተመልከት።

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።

“ዶርቃ” ግሪክኛ ሲሆን “ጣቢታ” ደግሞ አረማይክ ነው፤ የሁለቱም ትርጉም “የሜዳ ፍየል” ማለት ነው።

ወይም “መደረቢያዎች።”

ወይም “የጦር ጓድ።” ወደ 600 የሚጠጉ ወታደሮችን ያቀፈ የሮም ሠራዊት።

ወይም “መቶ አለቃ።”

ወይም “እጅ ነሳው።”

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።

ወይም “በዛፍ።”

ወይም “እንዲታይ።”

ወይም “በሚገባ።”

ወይም “ታማኝ አገልጋዮች።”

ቃል በቃል “በልሳኖች።”

ወይም “ይሟገቱት።”

ወይም “ማገድ።”

ቃል በቃል “ዝም አሉ።”

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።

የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

ወይም “ከማለፍ በዓል።” የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

ወይም “ሊያስፈርድበት።”

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።

ወይም “ታጠቅ።”

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።

ወይም “ከጢሮስና ከሲዶና ሰዎች ጋር ተጣልቶ።”

ቃል በቃል “የንጉሡ መኝታ ቤት ሹም።”

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።

ወይም “ለይሖዋ ሕዝባዊ አገልግሎት እያቀረቡና።”

የሮም የአንድ አውራጃ ገዢ። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

ይህ ሰው ሥራ 13:6 ላይ በርያሱስ ተብሎም ተጠርቷል።

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።

ቃል በቃል “ገዢዎቻቸው።”

ወይም “ከዛፍ።”

ወይም “እምነት የሚጣልበት፤ አስተማማኝ የሆነ።”

ወይም “የአምላክን ፈቃድ ካገለገለ።”

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።

የእግርን አቧራ ማራገፍ ከኃላፊነት ነፃ መሆንን ያመለክታል።

ወይም “ከአሕዛብ ወገን የሆኑትን ሰዎች ነፍሳት።”

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።

ወይም “የደቀ መዛሙርቱን ነፍስ።”

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።

ወይም “ክርክሩን።”

የስምዖን ጴጥሮስ ስም ሌላ አጠራር ነው።

ወይም “ዳስ፤ ቤት።”

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።

ወይም “እንደ እኔ ውሳኔ ከሆነ።”

ግሪክኛ፣ ፖርኒያ። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

ወይም “ደሙ ሳይፈስ ከተገደለ።”

ወይም “ነፍሳችሁን ሊያውኩ።”

ወይም “ነፍሳቸውን።”

ወይም “ደሙ ሳይፈስ ከተገደለ እንስሳ።”

ግሪክኛ፣ ፖርኒያ። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

ወይም “ደህና ሁኑ።”

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ3ን ተመልከት።

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።

“ልንጠይቃቸው ይገባል” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።

ወይም “ሚስያን አቋርጠው።”

ወይም “ሐምራዊ ቀለም ያለው ማቅለሚያ የምትሸጥና።”

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።

ሰዎች የሚገበያዩበት እንዲሁም ሕዝባዊ ስብሰባ የሚካሄድበት ገላጣ ስፍራ።

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።

ወይም “ያወኩት።”

ወይም “ዋስ ተቀብለው።”

ሰዎች የሚገበያዩበት እንዲሁም ሕዝባዊ ስብሰባ የሚካሄድበት ገላጣ ስፍራ።

በጥንቷ አቴና የሚገኝ ኮረብታ ሲሆን በዚህ ቦታ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱም ይሰበሰብ ነበር።

ወይም “ለጉብኝት የመጡ።”

ወይም “ሃይማኖተኞች እንደሆናችሁ።”

ወይም “እያስረዳ።”

ልብስን ማራገፍ ከኃላፊነት ነፃ መሆንን ያመለክታል።

ምኩራቡን ያመለክታል።

የሮም የአንድ አውራጃ ገዢ። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።

ወደ ኢየሩሳሌም ሳይሆን አይቀርም።

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።

ወይም “በቃል የተማረ።”

የአምላክን መንፈስ ያመለክታል።

ብር ከተባለው ማዕድን የተሠራ ሳንቲም።

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።

የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

ወይም “ነፍሱ በውስጡ ስላለች አትንጫጩ።”

ቃል በቃል “ዳቦውን ከቆረሰ።”

ወይም “በሚገባ።”

ወይም “በሚገባ በመመሥከር።”

ወይም “ነፍሴ።”

ወይም “ለእኔ አንዳች ዋጋ የለውም።”

ወይም “ዓላማ።”

ወይም “ጨቋኝ።”

ቃል በቃል “ጳውሎስ አንገት ላይ ወድቀውም።”

ቃል በቃል “ድንግል የሆኑ።”

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።

ወይም “መቃወማችንን አቆምን።”

ወይም “ደሙ ሳይፈስ ከተገደለ።”

ግሪክኛ፣ ፖርኒያ። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

ወይም “ድምፅ ቢሰሙም ምን እንደተባለ አላስተዋሉም።”

ወይም “የሮም ዜጋ።”

ወይም “ችሎት ፊት ሳይቀርብ።”

ወይም “በተሟላ ሁኔታ እንደመሠከርክ።”

ይህን መሐላ ካልጠበቁ እርግማን እንደሚደርስባቸው ያምኑ ነበር።

ወይም “ችግር ፈጣሪ።”

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ3ን ተመልከት።

ወይም “እንከን የለሽ።”

ቃል በቃል “ለእነሱ እንዲያደላ።”

እዚህ ላይ የተጠቀሰው ዳግማዊ ሄሮድስ አግሪጳ ነው።

ወይም “ስለ ገዛ ሃይማኖታቸውና።”

ለሮም ንጉሠ ነገሥት የሚሰጥ የማዕረግ ስም ነው።

ቃል በቃል “የምትፈርዱት።”

መውጊያ አንድን እንስሳ ወደ ፊት እንዲሄድ ለመቀስቀስ የሚያገለግል ጫፉ ሹል የሆነ ዘንግ ነው።

ወይም “ሰብዓዊ ደግነት።”

ወይም “በነፍሳችንም።”

የሰሜን ምሥራቅ ነፋስን ያመለክታል።

ሕይወት አድን ጀልባ።

የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

ወይም “ነፍስ።”

በጥልቀት መለኪያ (ፋተም) ሃያ። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።

በጥልቀት መለኪያ (ፋተም) አሥራ አምስት። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።

ወይም “ነፍሳት።”

ወይም “ባዕድ ቋንቋ የሚናገሩት ሰዎችም።”

ወይም “ሰብዓዊ ደግነት።”

ግሪክኛ ዳይክ፣ የበቀል እርምጃ የምትወስድን ሴት አምላክ ወይም የፍትሕን ጽንሰ ሐሳብ ሊያመለክት ይችላል።

ሰዎች የሚመገቡበት እና የሚያርፉበት ቦታ ነው።

ወይም “በተሟላ ሁኔታ።”

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ3ን ተመልከት።

ወይም “በድፍረት።”

    የኢትዮጵያ ምልክት ቋንቋ ጽሑፎች (2011-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • የኢትዮጵያ ምልክት ቋንቋ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ