ሁለተኛ ነገሥት
1 አክዓብ ከሞተ በኋላ ሞዓብ+ በእስራኤል ላይ ዓመፀ።
2 በዚህ ወቅት አካዝያስ በሰማርያ በሚገኘው ቤቱ ሰገነት ላይ ካለው ክፍል በርብራቡ ሾልኮ በመውደቁ ጉዳት ደርሶበት ነበር። በመሆኑም “ከደረሰብኝ ጉዳት እድን እንደሆነና እንዳልሆነ ማወቅ እንድችል ሄዳችሁ የኤቅሮንን+ አምላክ ባአልዜቡብን ጠይቁልኝ” በማለት መልእክተኞች ላከ።+ 3 የይሖዋ መልአክ ግን ቲሽባዊውን ኤልያስን*+ እንዲህ አለው፦ “ተነስተህ የሰማርያን ንጉሥ መልእክተኞች ለማግኘት ውጣ፤ እንዲህም በላቸው፦ ‘የኤቅሮንን አምላክ ባአልዜቡብን ለመጠየቅ የምትሄዱት በእስራኤል አምላክ ስለሌለ ነው?+ 4 ስለዚህ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “ከተኛህበት አልጋ ላይ አትነሳም፤ በእርግጥ ትሞታለህ።”’” ከዚያም ኤልያስ ሄደ።
5 መልእክተኞቹ ወደ እሱ ተመልሰው ሲመጡ አካዝያስ “ለምን ተመልሳችሁ መጣችሁ?” አላቸው። 6 እነሱም እንዲህ አሉት፦ “እኛን ለማግኘት የመጣ አንድ ሰው ነበር፤ እሱም እንዲህ አለን፦ ‘ሂዱ፣ ወደላካችሁ ንጉሥ ተመልሳችሁ እንዲህ በሉት፦ “ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘የኤቅሮንን አምላክ ባአልዜቡብን ለመጠየቅ መልእክተኛ የምትልከው በእስራኤል አምላክ ስለሌለ ነው? ስለዚህ ከተኛህበት አልጋ ላይ አትነሳም፤ በእርግጥ ትሞታለህ።’”’”+ 7 በዚህ ጊዜ አካዝያስ “እናንተን ለማግኘት የመጣውና ይህን የነገራችሁ ሰው ምን ይመስላል?” ብሎ ጠየቃቸው። 8 እነሱም “ሰውየው ፀጉራም ልብስ የለበሰ+ ሲሆን ወገቡም ላይ የቆዳ ቀበቶ ታጥቋል”+ አሉት። እሱም ወዲያውኑ “ይሄማ ቲሽባዊው ኤልያስ ነው” አለ።
9 ከዚያም ንጉሡ አንድ ሃምሳ አለቃ በሥሩ ካሉት 50 ሰዎች ጋር ላከ። ሃምሳ አለቃው ወደ እሱ ሲወጣ ኤልያስ ተራራው አናት ላይ ተቀምጦ ነበር። ሃምሳ አለቃውም “አንተ የእውነተኛው አምላክ ሰው፣+ ንጉሡ ‘ና ውረድ’ ብሎሃል” አለው። 10 ኤልያስ ግን ሃምሳ አለቃውን “እኔ የአምላክ ሰው ከሆንኩ እሳት ከሰማይ ወርዶ+ አንተንና ከአንተ ጋር ያሉትን 50 ሰዎች ይብላ” አለው። ከዚያም እሳት ከሰማይ ወርዶ እሱንና 50ዎቹን ሰዎች በላ።
11 በመሆኑም ንጉሡ እንደገና ሌላ ሃምሳ አለቃ በሥሩ ካሉት 50 ሰዎች ጋር ወደ ኤልያስ ላከ። እሱም ሄዶ ኤልያስን “አንተ የእውነተኛው አምላክ ሰው፣ ንጉሡ ‘ና ፈጥነህ ውረድ’ ብሎሃል” አለው። 12 ኤልያስ ግን “እኔ የእውነተኛው አምላክ ሰው ከሆንኩ እሳት ከሰማይ ወርዶ አንተንና ከአንተ ጋር ያሉትን 50 ሰዎች ይብላ” አላቸው። ከዚያም የአምላክ እሳት ከሰማይ ወርዶ እሱንና 50ዎቹን ሰዎች በላ።
13 ከዚያም ንጉሡ እንደገና ለሦስተኛ ጊዜ አንድ ሃምሳ አለቃ በሥሩ ካሉት 50 ሰዎች ጋር ላከ። ሆኖም ሦስተኛው ሃምሳ አለቃ ወጥቶ በኤልያስ ፊት በጉልበቱ ተንበርክኮ ሰገደ፤ ሞገስ እንዲያሳየውም እየለመነ እንዲህ አለው፦ “አንተ የእውነተኛው አምላክ ሰው፣ እባክህ የእኔም ሕይወት ሆነ የእነዚህ 50 አገልጋዮችህ ሕይወት በፊትህ የከበረ ይሁን።* 14 ከዚህ በፊት እሳት ከሰማይ ወርዶ ሁለቱን ሃምሳ አለቆችና አብረዋቸው የነበሩትን ሃምሳ ሃምሳ ሰዎች በልቷል፤ አሁን ግን ነፍሴ በፊትህ የከበረች ትሁን።”
15 በዚህ ጊዜ የይሖዋ መልአክ ኤልያስን “አብረኸው ውረድ። አትፍራው” አለው። በመሆኑም ኤልያስ ተነስቶ አብሮት ወደ ንጉሡ ወረደ። 16 ከዚያም ኤልያስ ንጉሡን እንዲህ አለው፦ “ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘የኤቅሮንን+ አምላክ ባአልዜቡብን ለመጠየቅ መልእክተኞች ልከሃል። ይህን ያደረግከው በእስራኤል አምላክ ስለሌለ ነው?+ ለምን የእስራኤልን አምላክ አልጠየቅክም? ስለዚህ ከተኛህበት አልጋ ላይ አትነሳም፤ በእርግጥ ትሞታለህ።’” 17 በመሆኑም ይሖዋ በኤልያስ አማካኝነት በተናገረው ቃል መሠረት ሞተ፤ አካዝያስ ወንድ ልጅ ስላልነበረው ኢዮራም*+ በምትኩ ነገሠ፤ ይህ የሆነው የይሁዳ ንጉሥ የኢዮሳፍጥ ልጅ ኢዮራም በነገሠ+ በሁለተኛው ዓመት ነው።
18 የቀረው የአካዝያስ+ ታሪክ፣ ያደረገው ነገር በእስራኤል ነገሥታት ዘመን ስለተፈጸሙት ነገሮች በሚተርከው የታሪክ መጽሐፍ ውስጥ ተጽፎ ይገኝ የለም?
2 ይሖዋ ኤልያስን+ በአውሎ ነፋስ ወደ ሰማይ የሚወስድበት ጊዜ ሲደርስ+ ኤልያስና ኤልሳዕ+ ከጊልጋል+ ተነስተው ጉዞ ጀመሩ። 2 ኤልያስም ኤልሳዕን “ይሖዋ ወደ ቤቴል እንድሄድ ስለላከኝ እባክህ አንተ እዚህ ቆይ” አለው። ኤልሳዕ ግን “ሕያው በሆነው በይሖዋና በሕያውነትህ* እምላለሁ፣ ከአንተ አልለይም” አለው። በመሆኑም አብረው ወደ ቤቴል+ ወረዱ። 3 ከዚያም በቤቴል የነበሩት የነቢያት ልጆች* ወጥተው ኤልሳዕን “ይሖዋ በአንተ ላይ ራስ የነበረውን ጌታህን ዛሬ ሊወስደው እንደሆነ አውቀሃል?”+ አሉት። እሱም “አዎ፣ አውቄአለሁ። ዝም በሉ” አለ።
4 ኤልያስም “ኤልሳዕ፣ ይሖዋ ወደ ኢያሪኮ+ እንድሄድ ስለላከኝ እባክህ አንተ እዚህ ቆይ” አለው። ኤልሳዕ ግን “ሕያው በሆነው በይሖዋና በሕያውነትህ* እምላለሁ፣ ከአንተ አልለይም” አለው። በመሆኑም አብረው ወደ ኢያሪኮ መጡ። 5 ከዚያም በኢያሪኮ የነበሩት የነቢያት ልጆች ወደ ኤልሳዕ ቀርበው “ይሖዋ በአንተ ላይ ራስ የነበረውን ጌታህን ዛሬ ሊወስደው እንደሆነ አውቀሃል?” አሉት። እሱም “አዎ፣ አውቄአለሁ። ዝም በሉ” አለ።
6 ኤልያስም ኤልሳዕን “ይሖዋ ወደ ዮርዳኖስ እንድሄድ ስለላከኝ እባክህ አንተ እዚህ ቆይ” አለው። ኤልሳዕ ግን “ሕያው በሆነው በይሖዋና በሕያውነትህ* እምላለሁ፣ ከአንተ አልለይም” አለው። በመሆኑም አብረው ሄዱ። 7 ከነቢያት ልጆች መካከል 50ዎቹ ተከትለዋቸው በመሄድ ራቅ ብለው ቆመው ያዩአቸው ነበር፤ በዚህ ጊዜ ሁለቱ ዮርዳኖስ አጠገብ ቆመው ነበር። 8 ከዚያም ኤልያስ የነቢይ ልብሱን+ አውልቆ በመጠቅለል ውኃውን መታው፤ ውኃውም ግራና ቀኝ ተከፈለ፤ ሁለቱም በደረቅ መሬት ተሻገሩ።+
9 ዮርዳኖስን እንደተሻገሩ ኤልያስ ኤልሳዕን “ከአንተ ከመወሰዴ በፊት እንዳደርግልህ የምትፈልገውን ጠይቀኝ” አለው። ኤልሳዕም “እባክህ፣ መንፈስህ+ በእጥፍ* ይሰጠኝ”+ አለው። 10 ኤልያስም “የጠየቅከው አስቸጋሪ ነገር ነው። ከአንተ ስወሰድ ካየኸኝ እንዳልከው ይሆንልሃል፤ አለዚያ ግን አይሆንልህም” አለው።
11 ሁለቱ እየተጨዋወቱ በመሄድ ላይ ሳሉ የእሳት ሠረገላና የእሳት ፈረሶች+ ድንገት መጥተው ለያዩአቸው፤ ኤልያስም በአውሎ ነፋስ ውስጥ ሆኖ ወደ ሰማይ ወጣ።+ 12 ኤልሳዕ ይህን ሲመለከት “አባቴ፣ አባቴ፣ እነሆ የእስራኤል ሠረገላና ፈረሰኞቹ!”+ በማለት ጮኸ። ኤልያስ ከዓይኑ ሲሰወርበትም የራሱን ልብስ ይዞ ለሁለት ቀደደው።+ 13 ከዚያም ከኤልያስ ላይ የወደቀውን የነቢይ ልብስ+ አነሳ፤ ተመልሶም በዮርዳኖስ ዳርቻ ቆመ። 14 እሱም ከኤልያስ ላይ በወደቀው የነቢይ ልብስ ውኃውን መታና እንዲህ አለ፦ “የኤልያስ አምላክ ይሖዋ የት አለ?” ውኃውንም ሲመታው ግራና ቀኝ ተከፈለ፤ ኤልሳዕም ተሻገረ።+
15 በኢያሪኮ የሚኖሩ የነቢያት ልጆች ኤልሳዕን ከሩቅ ሲመለከቱት “የኤልያስ መንፈስ በኤልሳዕ ላይ አርፏል”+ አሉ። በመሆኑም እሱን ለማግኘት ሄዱ፤ በፊቱም መሬት ላይ ተደፍተው እጅ ነሱት። 16 እነሱም እንዲህ አሉት፦ “እነሆ፣ ከአገልጋዮችህ ጋር ብቁ የሆኑ 50 ሰዎች አሉ። እባክህ ይሂዱና ጌታህን ይፈልጉት። ምናልባት የይሖዋ መንፈስ* ወደ ላይ አንስቶት ከተራሮቹ በአንዱ ላይ ወይም ከሸለቆዎቹ በአንዱ ውስጥ ጥሎት ይሆናል።”+ እሱ ግን “አትላኳቸው” አላቸው። 17 ሆኖም እነሱ እስኪያፍር ድረስ ወተወቱት፤ እሱም “እሺ፣ ላኳቸው” አለ። እነሱም 50ዎቹን ሰዎች ላኩ፤ ሰዎቹም ለሦስት ቀን ያህል ፈለጉት፤ ሆኖም ሊያገኙት አልቻሉም። 18 ወደ ኤልሳዕ በተመለሱም ጊዜ ኤልሳዕ በኢያሪኮ+ ነበር። እሱም “‘አትሂዱ’ ብያችሁ አልነበረም?” አላቸው።
19 ከጊዜ በኋላም የከተማዋ ሰዎች ኤልሳዕን “ጌታዬ፣ ይኸው እንደምታየው ከተማዋ የምትገኘው ጥሩ ቦታ ላይ ነው፤+ ሆኖም ውኃው መጥፎ ነው፤ ምድሪቱም ፍሬ አትሰጥም”* አሉት። 20 እሱም “አነስ ባለ አዲስ ጎድጓዳ ሳህን ጨው ጨምራችሁ አምጡልኝ” አለ። እነሱም አመጡለት። 21 ከዚያም ውኃው ወደሚመነጭበት ቦታ ሄዶ ጨው ረጨበትና+ “ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘ይህን ውኃ ፈውሼዋለሁ። ከእንግዲህ ለሞት ምክንያት አይሆንም፤ ምድሪቱንም ፍሬ እንዳትሰጥ* አያደርጋትም’” አለ። 22 ኤልሳዕ በተናገረውም ቃል መሠረት ውኃው እስከ ዛሬ ድረስ እንደተፈወሰ ነው።
23 እሱም ከዚያ ተነስቶ ወደ ቤቴል ወጣ። በዚህ ጊዜ ከከተማዋ የወጡ ልጆች “አንተ መላጣ፣ ውጣ! አንተ መላጣ፣ ውጣ!” እያሉ ያፌዙበት ጀመር።+ 24 በመጨረሻም ዞር ብሎ ተመለከታቸውና በይሖዋ ስም ረገማቸው። ከዚያም ሁለት እንስት ድቦች+ ከጫካው ወጥተው 42 ልጆችን ቦጫጨቁ።+ 25 እሱም ጉዞውን በመቀጠል ወደ ቀርሜሎስ ተራራ+ ሄደ፤ ከዚያ ደግሞ ወደ ሰማርያ ተመለሰ።
3 የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሳፍጥ በነገሠ በ18ኛው ዓመት የአክዓብ ልጅ ኢዮራም+ በሰማርያ ሆኖ በእስራኤል ላይ ነገሠ፤ እሱም ለ12 ዓመት ገዛ። 2 ኢዮራም በይሖዋ ፊት መጥፎ የሆነውን ነገር አደረገ፤ ሆኖም አባቱ ወይም እናቱ ያደረጉትን ያህል ክፉ ድርጊት አልፈጸመም፤ አባቱ የሠራውን የባአል የማምለኪያ ዓምድ አስወግዶ ነበርና።+ 3 ይሁንና የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም እስራኤላውያን ኃጢአት እንዲሠሩ በማድረግ+ የተከተለውን የኃጢአት ጎዳና የሙጥኝ አለ። ከዚያ ፈቀቅ አላለም።
4 የሞዓብ ንጉሥ ሜሻ በግ አርቢ ነበር፤ እሱም ለእስራኤል ንጉሥ 100,000 የበግ ጠቦቶችንና 100,000 ያልተሸለቱ አውራ በጎችን ይገብር ነበር። 5 አክዓብ እንደሞተ+ የሞዓብ ንጉሥ በእስራኤል ንጉሥ ላይ ዓመፀ።+ 6 በዚህ ጊዜ ንጉሥ ኢዮራም ከሰማርያ ወጥቶ በመሄድ እስራኤልን ሁሉ አሰለፈ። 7 በተጨማሪም ወደ ይሁዳ ንጉሥ ወደ ኢዮሳፍጥ “የሞዓብ ንጉሥ ዓምፆብኛል። ሞዓብን ለመውጋት አብረኸኝ ትሄዳለህ?” የሚል መልእክት ላከበት። እሱም “አብሬህ እሄዳለሁ።+ እኔ ማለት እኮ አንተ ማለት ነህ። ሕዝቤ፣ ሕዝብህ ነው። ፈረሶቼም ፈረሶችህ ናቸው” አለው።+ 8 ከዚያም “ታዲያ በየትኛው መንገድ ብንወጣ ይሻላል?” ብሎ ጠየቀው። እሱም “ወደ ኤዶም ምድረ በዳ በሚወስደው መንገድ” አለው።
9 በመሆኑም የእስራኤል ንጉሥ ከይሁዳ ንጉሥና ከኤዶም+ ንጉሥ ጋር አብሮ ሄደ። ለሰባት ቀን ያህል በሌላ አቅጣጫ ዞረው ከሄዱ በኋላ ለሠራዊቱም ሆነ እየተከተሏቸው ለነበሩት የቤት እንስሳት የሚሆን ውኃ አጡ። 10 ከዚያም የእስራኤል ንጉሥ “በጣም አስደንጋጭ ነው! ይሖዋ እነዚህን ሦስት ነገሥታት የጠራው ለሞዓብ አሳልፎ ለመስጠት ነው!” አለ። 11 በዚህ ጊዜ ኢዮሳፍጥ “በእሱ አማካኝነት ይሖዋን ልንጠይቅ የምንችልበት የይሖዋ ነቢይ እዚህ የለም?” አለ።+ ከእስራኤል ንጉሥ አገልጋዮች አንዱ “ኤልያስን+ እጅ ያስታጥብ የነበረው* የሻፋጥ ልጅ ኤልሳዕ+ እዚህ አለ” ሲል መለሰ። 12 ከዚያም ኢዮሳፍጥ “የይሖዋ ቃል እሱ ዘንድ ይገኛል” አለ። በዚህም መሠረት የእስራኤል ንጉሥ፣ ኢዮሳፍጥና የኤዶም ንጉሥ ወደ እሱ ወረዱ።
13 ኤልሳዕም የእስራኤልን ንጉሥ “እኔና አንተን ምን የሚያገናኘን ነገር አለ?+ ወደ አባትህ ነቢያትና ወደ እናትህ ነቢያት ሂድ”+ አለው። የእስራኤል ንጉሥ ግን “ይሄማ አይሆንም፤ ይሖዋ እኮ እነዚህን ሦስት ነገሥታት ጠርቶ በሞዓብ እጅ አሳልፎ ሊሰጣቸው ነው” አለው። 14 በዚህ ጊዜ ኤልሳዕ እንዲህ አለ፦ “በማገለግለውና* ሕያው በሆነው በሠራዊት ጌታ በይሖዋ እምላለሁ፣ ለማከብረው ለይሁዳ ንጉሥ ለኢዮሳፍጥ+ ብዬ ነው እንጂ ዓይንህን አላይም፣ ጉዳዬም አልልህም ነበር።+ 15 በሉ አሁን በገና የሚደረድር ሰው*+ አምጡልኝ።” በገና የሚደረድረውም ሰው መጫወት ሲጀምር የይሖዋ እጅ በኤልሳዕ ላይ መጣ።+ 16 እሱም እንዲህ አለ፦ “ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘በዚህ ሸለቆ* ውስጥ ብዙ ቦዮች ቆፍሩ፤ 17 ይሖዋ እንዲህ ይላልና፦ “ነፋስም ሆነ ዝናብ አታዩም፤ ይሁንና ይህ ሸለቆ* በውኃ ይሞላል፤+ እናንተም ሆናችሁ ከብቶቻችሁ እንዲሁም ሌሎች እንስሶቻችሁ ከዚያ ትጠጣላችሁ።”’ 18 ይህ ለይሖዋ በጣም ቀላል ነገር ነው፤+ ሞዓብንም በእጃችሁ አሳልፎ ይሰጣችኋልና።+ 19 እናንተም እያንዳንዱን የተመሸገ ከተማና+ እያንዳንዱን የተመረጠ ከተማ ትመታላችሁ፤ ጥሩውንም ዛፍ ሁሉ ትቆርጣላችሁ፤ የውኃ ምንጮችን በሙሉ ትደፍናላችሁ፤ ጥሩውንም መሬት ሁሉ በድንጋይ ታበላሻላችሁ።”+
20 በነጋታውም የጠዋት የእህል መባ+ በሚቀርብበት ጊዜ በድንገት ውኃ ከኤዶም አቅጣጫ መጣ፤ ምድሪቱም በውኃው ተጥለቀለቀች።
21 ሞዓባውያንም ነገሥታቱ ሊወጓቸው እንደመጡ ሲሰሙ የጦር መሣሪያ መታጠቅ የሚችሉ* ሰዎችን ሁሉ ሰብስበው ድንበሩ ላይ ቆሙ። 22 በማለዳ ሲነሱም ፀሐይዋ በውኃው ላይ ታንጸባርቅ ነበር፤ ማዶ ለነበሩት ሞዓባውያንም ውኃው እንደ ደም ቀልቶ ታያቸው። 23 እነሱም “ይሄማ ደም ነው! ነገሥታቱ ያለጥርጥር እርስ በርሳቸው በሰይፍ ተራርደዋል። ስለዚህ ሞዓብ ሆይ፣ ወደ ምርኮህ+ ሂድ!” አሉ። 24 እነሱም ወደ እስራኤል ሰፈር ሲመጡ እስራኤላውያን ተነስተው ሞዓባውያንን መምታት ጀመሩ፤ እነሱም ከፊታቸው ሸሹ።+ እስራኤላውያንም ሞዓባውያንን እየመቱ ወደ ሞዓብ ገሰገሱ። 25 ከተሞቹንም ደመሰሱ፤ እያንዳንዱም ሰው ድንጋይ እየጣለ ጥሩውን መሬት ሁሉ በድንጋይ ሞላው፤ የውኃ ምንጮቹን በሙሉ ደፈኑ፤+ ጥሩውንም ዛፍ ሁሉ ቆረጡ።+ በመጨረሻም የቂርሃረሰት+ የድንጋይ ግንቦች ብቻ ቆመው ቀሩ፤ ወንጭፍ የሚወነጭፉትም ዙሪያዋን ከበው መቷት።
26 የሞዓብ ንጉሥ በውጊያው እንደተሸነፈ ባየ ጊዜ ወደ ኤዶም ንጉሥ+ ጥሶ ለመግባት ሰይፍ የታጠቁ 700 ሰዎችን ወሰደ፤ ሆኖም አልተሳካላቸውም። 27 ስለዚህ በእሱ ምትክ የሚነግሠውን የበኩር ልጁን ወስዶ ቅጥሩ ላይ የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጎ አቀረበው።+ በእስራኤልም ላይ ታላቅ ቁጣ ሆነ፤ በመሆኑም አካባቢውን ለቀው ወደ ምድራቸው ተመለሱ።
4 ከነቢያት ልጆች+ መካከል የአንዱ ሚስት ወደ ኤልሳዕ መጥታ እንዲህ ስትል ጮኸች፦ “አገልጋይህ ባለቤቴ ሞቷል፤ አገልጋይህ ምንጊዜም ይሖዋን የሚፈራ ሰው እንደነበር በሚገባ ታውቃለህ።+ አሁን ግን አንድ አበዳሪ መጥቶ ሁለቱንም ልጆቼን ባሪያዎቹ አድርጎ ሊወስዳቸው ነው።” 2 በዚህ ጊዜ ኤልሳዕ “ታዲያ ምን እንዳደርግልሽ ትፈልጊያለሽ? ንገሪኝ፣ ቤት ውስጥ ምን አለሽ?” አላት። እሷም “አገልጋይህ ከአንድ ማሰሮ ዘይት በስተቀር ቤት ውስጥ ምንም ነገር የላትም”+ ብላ መለሰችለት። 3 ከዚያም እንዲህ አላት፦ “እንግዲያው ሂጂና ከጎረቤቶችሽ ሁሉ ባዶ ዕቃዎች ለምኚ። የቻልሽውን ያህል ብዙ ዕቃ ለምኚ። 4 ከዚያም ገብተሽ በሩን በአንቺና በልጆችሽ ላይ ዝጊው። ዕቃዎቹንም ሁሉ በዘይት ሙዪ፤ የሞሉትንም ለብቻ አስቀምጫቸው።” 5 እሷም ወጥታ ሄደች።
በሩን በራሷና በልጆቿ ላይ ከዘጋች በኋላ ልጆቿ ዕቃዎቹን ሲያቀርቡላት እሷ ትቀዳባቸው ጀመር።+ 6 ዕቃዎቹ ሲሞሉ ከልጆቿ መካከል አንዱን “ሌላ ዕቃ አምጣልኝ”+ አለችው። እሱ ግን “የቀረ ዕቃ የለም” አላት። በዚህ ጊዜ ዘይቱ መውረዱን አቆመ።+ 7 እሷም ሄዳ ለእውነተኛው አምላክ ሰው ነገረችው፤ እሱም “ሂጂ፤ ዘይቱን ሸጠሽ ዕዳሽን ክፈዪ፤ የተረፈው ደግሞ ለአንቺና ለልጆችሽ መተዳደሪያ ይሁን” አላት።
8 አንድ ቀን ኤልሳዕ ወደ ሹነም+ ሄደ፤ በዚያም አንዲት ታዋቂ ሴት ነበረች፤ እሷም ምግብ እንዲበላ አጥብቃ ለመነችው።+ እሱም በዚያ ባለፈ ቁጥር ምግብ ለመብላት ወደዚያ ጎራ ይል ነበር። 9 በመሆኑም ሴትየዋ ባሏን እንዲህ አለችው፦ “ይህ በየጊዜው በዚህ መንገድ የሚያልፈው ሰው ቅዱስ የአምላክ ሰው እንደሆነ አውቃለሁ። 10 እባክህ በሰገነቱ ላይ ትንሽ ክፍል+ ሠርተን አልጋ፣ ጠረጴዛ፣ ወንበርና መቅረዝ እናስገባለት። ከዚያም ወደ እኛ በሚመጣበት ጊዜ ሁሉ እዚያ ማረፍ ይችላል።”+
11 ኤልሳዕም አንድ ቀን ወደዚያ መጣ፤ ጋደም ለማለትም በሰገነቱ ላይ ወዳለው ክፍል ሄደ። 12 ከዚያም አገልጋዩን ግያዝን+ “እስቲ ሹነማዊቷን+ ሴት ጥራት” አለው። እሱም ጠራት፤ እሷም መጥታ ፊቱ ቆመች። 13 ከዚያም ኤልሳዕ ግያዝን እንዲህ አለው፦ “እባክህ እንዲህ በላት፦ ‘እንግዲህ ለእኛ ስትዪ ብዙ ተቸግረሻል።+ ታዲያ ምን እንዲደረግልሽ ትፈልጊያለሽ?+ ንጉሡን ወይም የሠራዊቱን አለቃ የማነጋግርልሽ ነገር አለ?’”+ እሷ ግን “እኔ እኮ የምኖረው በገዛ ወገኖቼ መካከል ነው” ብላ መለሰች። 14 እሱም “ታዲያ ምን ቢደረግላት ይሻላል?” አለ። ግያዝም “ለነገሩማ ሴትየዋ ወንድ ልጅ የላትም፤+ ባሏ ደግሞ አርጅቷል” አለው። 15 ኤልሳዕም ወዲያውኑ “በል ጥራት” አለው። እሱም ጠራት፤ እሷም በራፉ ላይ ቆመች። 16 ከዚያም “የዛሬ ዓመት በዚሁ ጊዜ ወንድ ልጅ ትታቀፊያለሽ” አላት።+ እሷ ግን “የእውነተኛው አምላክ ሰው ጌታዬ ሆይ፣ ይሄማ አይሆንም! አገልጋይህን መዋሸት እንዳይሆንብህ” አለችው።
17 ይሁንና ሴትየዋ ፀነሰች፤ ኤልሳዕ በነገራትም መሠረት በቀጣዩ ዓመት በዚያው ጊዜ ወንድ ልጅ ወለደች። 18 ልጁም አደገ፤ ከዚያም አንድ ቀን ከአጫጆቹ ጋር ወደነበረው ወደ አባቱ ወጣ። 19 አባቱንም “ራሴን! ወይኔ ራሴን!” አለው። ከዚያም አባቱ አገልጋዩን “ተሸክመህ ወደ እናቱ ውሰደው” አለው። 20 እሱም ተሸክሞ ወደ እናቱ ወሰደው፤ ልጁም እስከ እኩለ ቀን ድረስ እናቱ ጭን ላይ ተቀመጠ፤ ከዚያም ሞተ።+ 21 እሷም ወደ ላይ ወጥታ ልጁን በእውነተኛው አምላክ ሰው አልጋ+ ላይ አስተኛችው፤ በሩንም ዘግታ ሄደች። 22 ባሏንም ጠርታ “እባክህ አንድ አገልጋይና አንድ አህያ ላክልኝና ወደ እውነተኛው አምላክ ሰው በፍጥነት ደርሼ ልመለስ” አለችው። 23 እሱ ግን “ዛሬ ወደ እሱ መሄድ ለምን አስፈለገሽ? አዲስ ጨረቃ+ ወይም ሰንበት አይደለም” አላት። እሷ ግን “ግድ የለም፣ ደርሼ ልምጣ” አለችው። 24 ስለዚህ አህያዋን ከጫነች በኋላ አገልጋይዋን “ቶሎ ቶሎ ሂድ። እኔ ቀስ በል እስካላልኩህ ድረስ ለእኔ ብለህ ፍጥነትህን እንዳትቀንስ” አለችው።
25 በመሆኑም በቀርሜሎስ ተራራ ወደሚገኘው ወደ እውነተኛው አምላክ ሰው ሄደች። የእውነተኛውም አምላክ ሰው ከሩቅ እንዳያት አገልጋዩን ግያዝን እንዲህ አለው፦ “ተመልከት! ሹነማዊቷ ሴት ያቻትና። 26 እባክህ ሮጠህ ወደ እሷ ሂድና ‘ምነው፣ ደህና አይደለሽም? ባልሽ ደህና አይደለም እንዴ? ልጁስ ደህና አይደለም?’ በላት።” እሷም “ሁሉም ነገር ደህና ነው” አለች። 27 ተራራው ላይ ወዳለው ወደ እውነተኛው አምላክ ሰው እንደደረሰች እግሩ ላይ ተጠመጠመች።+ በዚህ ጊዜ ግያዝ ሊያስለቅቃት ሲመጣ የእውነተኛው አምላክ ሰው “ተዋት፣ እጅግ ተጨንቃለች፤* ይሖዋም ነገሩን ከእኔ ደብቆታል፤ የነገረኝ ነገር የለም” አለው። 28 እሷም “ለመሆኑ ጌታዬ ልጅ እንዲሰጠኝ ጠይቄ ነበር? ደግሞስ ‘የማይሆን ተስፋ አትስጠኝ’ አላልኩም?” አለችው።+
29 እሱም ወዲያውኑ ግያዝን “ልብስህን ወገብህ ላይ ታጠቅ፤+ በትሬን ያዝና ሩጥ። መንገድ ላይ ሰው ብታገኝ ሰላም አትበል፤ ማንም ሰው ሰላም ቢልህም መልስ አትስጠው። ሂድና በትሬን በልጁ ፊት ላይ አድርገው” አለው። 30 በዚህ ጊዜ የልጁ እናት “ሕያው በሆነው በይሖዋና በሕያውነትህ* እምላለሁ፣ ፈጽሞ ትቼህ አልሄድም” አለችው።+ ስለሆነም ተነስቶ አብሯት ሄደ። 31 ግያዝ ቀድሟቸው በመሄድ በትሩን በልጁ ፊት ላይ አደረገው፤ ሆኖም ድምፅም ሆነ ምላሽ አልነበረም።+ እሱም ወደ ኤልሳዕ ተመልሶ በመምጣት “ልጁ አልነቃም” አለው።
32 ኤልሳዕ ወደ ቤት ሲገባ ልጁ ሞቶ በእሱ አልጋ ላይ ተጋድሞ አገኘው።+ 33 ከዚያም ወደ ውስጥ ገብቶ በሩን በራሱና በልጁ ላይ ከዘጋ በኋላ ወደ ይሖዋ መጸለይ ጀመረ።+ 34 ከዚያም አልጋው ላይ ወጥቶ ልጁ ላይ በመተኛት አፉን በአፉ፣ ዓይኑን በዓይኑ እንዲሁም መዳፉን በመዳፉ ላይ አድርጎ ላዩ ላይ ተደፋበት፤ የልጁም ሰውነት መሞቅ ጀመረ።+ 35 ኤልሳዕ ተነስቶ ቤቱ ውስጥ ወዲያ ወዲህ ይል ጀመር፤ ደግሞም እንደገና አልጋው ላይ ወጥቶ ላዩ ላይ ተደፋበት። ልጁም ሰባት ጊዜ ካስነጠሰው በኋላ ዓይኖቹን ገለጠ።+ 36 ኤልሳዕም ግያዝን ጠርቶ “ሹነማዊቷን ሴት ጥራት” አለው። እሱም ጠራት፤ እሷም ወደ እሱ ገባች። ከዚያም ኤልሳዕ “ልጅሽን አንሺው” አላት።+ 37 እሷም ገብታ እግሩ ሥር በመውደቅ ወደ መሬት ለጥ ብላ እጅ ነሳች፤ ልጇንም አንስታ ወጣች።
38 ኤልሳዕ ወደ ጊልጋል ሲመለስ በምድሪቱ ላይ ረሃብ ነበር።+ የነቢያት ልጆች+ በፊቱ ተቀምጠው ነበር፤ አገልጋዩንም+ “ትልቁን ድስት ጣደውና ለነቢያት ልጆች ወጥ ሥራላቸው” አለው። 39 አንድ ሰው ቅጠላ ቅጠል ለማምጣት ወደ ሜዳ ወጣ፤ እሱም ዱር በቀል ሐረግ አገኘ፤ ከሐረጉም ላይ የዱር ቅል ለቅሞ በልብሱ ሙሉ ይዞ ተመለሰ። ከዚያም ምንነታቸውን ሳያውቅ ከትፎ ድስቱ ውስጥ ጨመራቸው። 40 በኋላም ሰዎቹ እንዲበሉ አቀረቡላቸው፤ እነሱ ግን ወጡን ገና እንደቀመሱት “የእውነተኛው አምላክ ሰው ሆይ፣ ድስቱ ውስጥ ገዳይ መርዝ አለ” ብለው ጮኹ። ሊበሉትም አልቻሉም። 41 እሱም “ዱቄት አምጡልኝ” አለ። ዱቄቱንም ድስቱ ውስጥ ከጨመረው በኋላ “ለሰዎቹ አቅርቡላቸው” አለ። በድስቱም ውስጥ ጉዳት የሚያስከትል ምንም ነገር አልተገኘም።+
42 ከበዓልሻሊሻ+ የመጣ አንድ ሰው ነበር፤ እሱም ለእውነተኛው አምላክ ሰው ከፍሬው በኩራት የተዘጋጁ 20 የገብስ ዳቦዎችና+ አንድ ከረጢት የእሸት ዛላዎች ይዞለት መጣ።+ ከዚያም ኤልሳዕ “ሰዎቹ እንዲበሉ ስጣቸው” አለው። 43 ሆኖም አገልጋዩ “ይህን እንዴት አድርጌ ለ100 ሰው አቀርባለሁ”+ አለው። በዚህ ጊዜ ኤልሳዕ “ሰዎቹ እንዲበሉ ስጣቸው፤ ይሖዋ እንዲህ ይላልና፦ ‘ይበላሉ፤ ደግሞም ይተርፋቸዋል’”+ አለው። 44 ከዚያም አቀረበላቸው፤ እነሱም በሉ፤ ይሖዋም በተናገረው መሠረት ተረፋቸው።+
5 የሶርያ ንጉሥ የሠራዊት አለቃ የሆነው ንዕማን በጌታው ፊት የተከበረና ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ሰው ነበር፤ ምክንያቱም ይሖዋ ለሶርያ ድል ያጎናጸፈው* በእሱ አማካኝነት ነበር። ይህ ሰው የሥጋ ደዌ በሽተኛ* ቢሆንም ኃያል ተዋጊ ነበር። 2 ሶርያውያን በአንድ ወቅት ወረራ ሲያካሂዱ ከእስራኤል ምድር አንዲት ትንሽ ልጅ ማርከው ወስደው ነበር፤ እሷም የንዕማን ሚስት አገልጋይ ሆነች። 3 ይህች ልጅ እመቤቷን “ጌታዬ በሰማርያ ወዳለው ነቢይ+ ቢሄድ እኮ ጥሩ ነው! ከሥጋ ደዌው ይፈውሰው ነበር”+ አለቻት። 4 እሱም* ወደ ጌታው ሄዶ ከእስራኤል ምድር የመጣችው ልጅ ያለችውን ነገረው።
5 የሶርያም ንጉሥ “እንግዲያው ሂድ! እኔም ለእስራኤል ንጉሥ ደብዳቤ እልክለታለሁ” አለ። እሱም አሥር ታላንት* ብር፣ 6,000 ሰቅል ወርቅና አሥር ቅያሪ ልብሶች ይዞ ሄደ። 6 ለእስራኤልም ንጉሥ “አገልጋዬን ንዕማንን ከሥጋ ደዌው እንድትፈውሰው ከዚህ ደብዳቤ ጋር ወደ አንተ ልኬዋለሁ” የሚለውን ደብዳቤ ሰጠው። 7 የእስራኤልም ንጉሥ ደብዳቤውን እንዳነበበ ልብሱን ቀደደ፤ ከዚያም “ይህን ሰው ከሥጋ ደዌው እንድፈውስ ወደ እኔ የሚልከው እኔ መግደልና ማዳን የምችል አምላክ ሆኜ ነው?+ እንግዲህ ነገር ሲፈልገኝ እዩ” አለ።
8 ይሁንና የእውነተኛው አምላክ ሰው ኤልሳዕ የእስራኤል ንጉሥ ልብሱን እንደቀደደ ሲሰማ ወዲያውኑ “ልብስህን የቀደድከው ለምንድን ነው? በእስራኤል ነቢይ መኖሩን እንዲያውቅ እባክህ ወደ እኔ ላከው”+ የሚል መልእክት ወደ ንጉሡ ላከ። 9 በመሆኑም ንዕማን ፈረሶቹንና የጦር ሠረገሎቹን ይዞ መጣ፤ በኤልሳዕም ቤት ደጃፍ ላይ ቆመ። 10 ሆኖም ኤልሳዕ “ሄደህ ዮርዳኖስ ውስጥ ሰባት ጊዜ+ ታጠብ፤+ ሥጋህም ይፈወሳል፤ ንጹሕም ትሆናለህ” ብሎ እንዲነግረው መልእክተኛ ላከ። 11 በዚህ ጊዜ ንዕማን ተቆጥቶ ለመሄድ ተነሳ፤ እንዲህም አለ፦ “እኔ እኮ ‘ወደ እኔ መጥቶ በመቆም የአምላኩን የይሖዋን ስም እየጠራ ቁስሉ ያለበትን ቦታ በመዳሰስ ከያዘኝ የሥጋ ደዌ ይፈውሰኛል’ ብዬ አስቤ ነበር። 12 ለዚህ ለዚህማ የደማስቆ+ ወንዞች አባና እና ፋርፋር በእስራኤል ከሚገኙ ውኃዎች ሁሉ የተሻሉ አይደሉም? እነሱ ውስጥ ታጥቤ መንጻት አልችልም ነበር?” ከዚያም በቁጣ ተመልሶ ሄደ።
13 አገልጋዮቹም ቀርበው “አባቴ ሆይ፣ ነቢዩ ያልተለመደ ነገር እንድታደርግ ቢነግርህ ኖሮ አታደርገውም ነበር? ታዲያ ‘ታጠብና ንጻ’ ቢልህ ምኑ ከበደህ?” አሉት። 14 በዚህ ጊዜ ንዕማን የእውነተኛው አምላክ ሰው በነገረው መሠረት ወርዶ ዮርዳኖስ ውስጥ ሰባት ጊዜ ጠለቀ።+ ከዚያም ሥጋው እንደ ትንሽ ልጅ ሥጋ ሆነ፤+ ደግሞም ነጻ።+
15 ከዚያ በኋላ አጃቢዎቹን አስከትሎ ወደ እውነተኛው አምላክ ሰው ተመለሰ፤+ በፊቱም ቆሞ “በእስራኤል እንጂ በምድር ላይ በሌላ በየትኛውም ቦታ አምላክ እንደሌለ አሁን አውቄአለሁ።+ እባክህ ከአገልጋይህ ስጦታ* ተቀበል” አለው። 16 እሱ ግን “በማገለግለውና* ሕያው በሆነው በይሖዋ እምላለሁ፣ ምንም ነገር አልቀበልም”+ አለው። ንዕማን እንዲቀበለው ቢወተውተውም ፈቃደኛ አልሆነም። 17 በመጨረሻም ንዕማን እንዲህ አለው፦ “እንግዲያው የማትቀበለኝ ከሆነ፣ አገልጋይህ ከአሁን በኋላ ለይሖዋ እንጂ ለሌሎች አማልክት የሚቃጠል መባም ሆነ መሥዋዕት ስለማያቀርብ እባክህ ለአገልጋይህ ከዚህ ቦታ የሁለት በቅሎ ጭነት አፈር ይሰጠው። 18 ይሁንና ይሖዋ ስለ አንድ ነገር ብቻ አገልጋይህን ይቅር ይበለው፤ ይኸውም ጌታዬ ለመስገድ ወደ ሪሞን ቤት* በሚገባበት ጊዜ ክንዴን ይደገፋል፤ እኔም በሪሞን ቤት መስገዴ አይቀርም። በሪሞን ቤት በምሰግድበት ጊዜ ይሖዋ ይህን ነገር አገልጋይህን ይቅር ይበለው።” 19 በዚህ ጊዜ ኤልሳዕ “በሰላም ሂድ” አለው። ከእሱ ተለይቶ የተወሰነ ርቀት እንደተጓዘ 20 የእውነተኛው አምላክ ሰው+ የኤልሳዕ አገልጋይ የሆነው ግያዝ+ ‘ጌታዬ ሶርያዊው ንዕማን+ ያመጣውን ነገር ሳይቀበለው እንዲሁ አሰናበተው። ሕያው በሆነው በይሖዋ እምላለሁ፣ ተከትዬው ሮጬ የሆነ ነገር እቀበለዋለሁ’ ብሎ አሰበ። 21 ስለዚህ ግያዝ ንዕማንን ተከተለው። ንዕማንም አንድ ሰው በሩጫ እየተከተለው እንዳለ ሲያይ ሰውየውን ለማግኘት ከሠረገላው ላይ ወርዶ “በደህና ነው?” አለው። 22 በዚህ ጊዜ ግያዝ እንዲህ አለው፦ “አዎ፣ በደህና ነው። ጌታዬ ‘ከነቢያት ልጆች መካከል ሁለት ወጣቶች ከተራራማው ከኤፍሬም አካባቢ አሁን ድንገት ወደ እኔ መጡ። ስለሆነም እባክህ አንድ ታላንት ብርና ሁለት ቅያሪ ልብስ ስጣቸው’+ ብዬ እንድነግርህ ልኮኝ ነው።” 23 ንዕማንም “እባክህ፣ ሁለት ታላንት ውሰድ” አለው። አጥብቆም ለመነው፤+ ከዚያም ሁለት ታላንት ብር በሁለት ከረጢት ጠቅልሎ እንዲሁም ሁለት ቅያሪ ልብስ ጨምሮ ለሁለቱ አገልጋዮቹ ሰጣቸው፤ እነሱም ተሸክመው ከፊት ከፊቱ ሄዱ።
24 እሱም ኦፌል* በደረሰ ጊዜ ዕቃዎቹን ከእጃቸው ላይ ወስዶ ቤት ውስጥ ካስቀመጠ በኋላ ሰዎቹን አሰናበታቸው። እነሱም ከሄዱ በኋላ 25 ገብቶ ጌታው አጠገብ ቆመ። ኤልሳዕም “ግያዝ፣ ከየት ነው የመጣኸው?” አለው። እሱ ግን “ኧረ አገልጋይህ የትም አልሄደም” አለ።+ 26 ኤልሳዕም እንዲህ አለው፦ “ሰውየው አንተን ለማግኘት ከሠረገላው ላይ ሲወርድ ልቤ በዚያ ከአንተ ጋር አልነበረም? ለመሆኑ ጊዜው ብር ወይም ልብስ፣ የወይራ ወይም የወይን እርሻ፣ በግ ወይም ከብት አሊያም ደግሞ ወንድ ወይም ሴት አገልጋዮች የሚቀበሉበት ነው?+ 27 ስለሆነም የንዕማን የሥጋ ደዌ+ በአንተና በዘርህ ላይ ለዘላለም ይጣበቃል።” ግያዝም በሥጋ ደዌ የተነሳ እንደ በረዶ ነጭ ሆኖ ወዲያውኑ ከፊቱ ወጣ።+
6 የነቢያት ልጆች+ ኤልሳዕን እንዲህ አሉት፦ “ይኸው እንደምታየው አብረንህ የምንኖርበት ስፍራ በጣም ጠቦናል። 2 እባክህ ወደ ዮርዳኖስ እንሂድ። እያንዳንዳችን ከዚያ እንጨት እንቁረጥ፤ በዚያም የምንቀመጥበት መኖሪያ እንሥራ።” እሱም “እሺ ሂዱ” አላቸው። 3 ከመካከላቸው አንዱ “አንተስ ከአገልጋዮችህ ጋር ለመሄድ ፈቃደኛ ነህ?” አለው። እሱም “እሺ እሄዳለሁ” አለ። 4 ስለዚህ አብሯቸው ሄደ፤ ወደ ዮርዳኖስም መጥተው ዛፍ መቁረጥ ጀመሩ። 5 ከእነሱ አንዱ ዛፍ እየቆረጠ ሳለ የመጥረቢያው አናት ወልቆ ውኃው ውስጥ ወደቀ። ሰውየውም “ወየው ጌታዬ፣ ተውሼ ያመጣሁት መጥረቢያ እኮ ነው!” በማለት ጮኸ። 6 የእውነተኛው አምላክ ሰውም “የት ነው የወደቀው?” አለው። ሰውየውም ቦታውን አሳየው። እሱም እንጨት ቆርጦ ውኃው ውስጥ በመጣል የመጥረቢያው አናት እንዲንሳፈፍ አደረገ። 7 ከዚያም “በል አውጣው” አለው። ሰውየውም እጁን ዘርግቶ ወሰደው።
8 በዚህ ጊዜ የሶርያ ንጉሥ እስራኤልን ለመውጋት ዘምቶ ነበር።+ ከአገልጋዮቹ ጋር ከተማከረ በኋላ “እዚህ እዚህ ቦታ አብሬያችሁ እሰፍራለሁ” አለ። 9 ከዚያም የእውነተኛው አምላክ ሰው+ “ሶርያውያን በዚህ እየወረዱ ስለሆነ በዚህ በኩል እንዳታልፍ ተጠንቀቅ” በማለት ወደ እስራኤል ንጉሥ መልእክት ላከ። 10 የእስራኤልም ንጉሥ፣ የእውነተኛው አምላክ ሰው እንዳይሄድ ወዳስጠነቀቀው ስፍራ መልእክት ላከ። በዚህ መንገድ ኤልሳዕ ንጉሡን በተደጋጋሚ ጊዜ* ያስጠነቅቀው የነበረ ሲሆን ንጉሡም ከዚያ አካባቢ ይርቅ ነበር።+
11 ይህ ጉዳይ የሶርያን ንጉሥ* እጅግ አበሳጨው፤ በመሆኑም አገልጋዮቹን ጠርቶ “ከመካከላችን ከእስራኤል ንጉሥ ጋር የወገነ ካለ ንገሩኝ!” አላቸው። 12 ከዚያም ከአገልጋዮቹ መካከል አንዱ “ንጉሡ ጌታዬ ሆይ፣ ኧረ ማንም የለም! አንተ መኝታ ቤትህ ውስጥ ሆነህ የምትናገረውን ነገር ለእስራኤል ንጉሥ የሚነግረው በእስራኤል ያለው ነቢዩ ኤልሳዕ ነው”+ አለው። 13 ንጉሡም “በሉ ሰዎች ልኬ እንዳስይዘው ሄዳችሁ የት እንደሚገኝ አጣሩ” አላቸው። በኋላም “ዶታን+ ነው ያለው” የሚል ወሬ ደረሰው። 14 እሱም ወዲያውኑ ፈረሶችን፣ የጦር ሠረገሎችንና ብዙ ሠራዊት ወደዚያ ላከ፤ እነሱም በሌሊት መጥተው ከተማዋን ከበቡ።
15 የእውነተኛው አምላክ ሰው አገልጋይ በማለዳ ተነስቶ ወደ ውጭ ሲወጣ በፈረሶችና በጦር ሠረገሎች የተጠናከረ ሠራዊት ከተማዋን መክበቡን አየ። አገልጋዩም ወዲያውኑ “ወየው ጌታዬ! ምን ብናደርግ ይሻላል?” አለ። 16 ኤልሳዕ ግን “አይዞህ፣ አትፍራ!+ ከእነሱ ጋር ካሉት ከእኛ ጋር ያሉት ይበልጣሉ”+ አለው። 17 ከዚያም ኤልሳዕ “ይሖዋ ሆይ፣ እባክህ ያይ ዘንድ ዓይኖቹን ክፈትለት”+ በማለት ጸለየ። ይሖዋም ወዲያውኑ የአገልጋዩን ዓይኖች ከፈተ፤ እሱም አየ፤ እነሆ የእሳት ፈረሶችና የጦር ሠረገሎች+ በኤልሳዕ ዙሪያ ተራራማውን አካባቢ ሞልተውት ነበር።+
18 ሶርያውያኑ ወደ ኤልሳዕ መውረድ ሲጀምሩ ኤልሳዕ “እባክህ፣ ይህን ሕዝብ አሳውረው”+ በማለት ወደ ይሖዋ ጸለየ። እሱም ኤልሳዕ በጠየቀው መሠረት አሳወራቸው። 19 ኤልሳዕም “መንገዱ ይሄ አይደለም፤ ከተማዋም ይህች አይደለችም። ወደምትፈልጉት ሰው መርቼ እንዳደርሳችሁ እኔን ተከተሉኝ” አላቸው። ይሁን እንጂ ኤልሳዕ የወሰዳቸው ወደ ሰማርያ+ ነበር።
20 እነሱም ሰማርያ ሲደርሱ ኤልሳዕ “ይሖዋ ሆይ፣ እንዲያዩ ዓይኖቻቸውን ክፈት” አለ። ስለዚህ ይሖዋ ዓይኖቻቸውን ከፈተላቸው፤ እነሱም ሰማርያ ውስጥ መሆናቸውን አዩ። 21 የእስራኤል ንጉሥ ባያቸው ጊዜ ኤልሳዕን “አባቴ ሆይ፣ ልግደላቸው? ልፍጃቸው?” አለው። 22 እሱ ግን እንዲህ አለው፦ “አትግደላቸው። ለመሆኑ በሰይፍህ ወይም በቀስትህ ማርከህ የወሰድካቸውን ሰዎች ትገድላለህ? በል አሁን እንዲበሉና እንዲጠጡ ምግብና ውኃ ስጣቸው፤+ ከዚያም ወደ ጌታቸው ይመለሱ።” 23 በመሆኑም ታላቅ ግብዣ አደረገላቸው፤ እነሱም በሉ፣ ጠጡም፤ ከዚያም ወደ ጌታቸው እንዲመለሱ አሰናበታቸው። ከዚያ በኋላ የሶርያውያን+ ወራሪ ቡድን ወደ እስራኤል ምድር ተመልሶ አልመጣም።
24 ከጊዜ በኋላ የሶርያ ንጉሥ ቤንሃዳድ ሠራዊቱን ሁሉ ሰብስቦ በመውጣት ሰማርያን ከበበ።+ 25 በመሆኑም በሰማርያ ታላቅ ረሃብ ተከሰተ፤+ ከተማዋን ከበው በነበረበት ጊዜም አንድ የአህያ ጭንቅላት+ 80 የብር ሰቅል እንዲሁም አንድ አራተኛ የቃብ መስፈሪያ* የርግብ ኩስ 5 የብር ሰቅል እስኪያወጣ ድረስ ረሃቡ ጸንቶ ነበር። 26 የእስራኤል ንጉሥ በቅጥሩ ላይ ሲያልፍ አንዲት ሴት “ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፣ እርዳን!” በማለት ወደ እሱ ጮኸች። 27 ንጉሡም “ይሖዋ ካልረዳሽ እኔ ከየት አምጥቼ ልረዳሽ እችላለሁ? ከአውድማው ነው ወይስ ከወይኑ ወይስ ከዘይት መጭመቂያው?” አላት። 28 ከዚያም “ለመሆኑ ችግርሽ ምንድን ነው?” ሲል ጠየቃት። እሷም እንዲህ ስትል መለሰች፦ “ይህች ሴት ‘ዛሬ የአንቺን ልጅ እንድንበላው አምጪው፤ ነገ ደግሞ የእኔን ልጅ እንበላለን’ አለችኝ።+ 29 በመሆኑም ልጄን ቀቅለን በላነው።+ በማግስቱ ‘የአንቺን ልጅ እንድንበላው አምጪው’ አልኳት። እሷ ግን ልጇን ደበቀችው።”
30 ንጉሡ ሴትየዋ ያለችውን ሲሰማ ልብሱን ቀደደ።+ በቅጥሩም ላይ በሚያልፍበት ጊዜ ሕዝቡ ንጉሡ ከልብሶቹ ሥር ማቅ መልበሱን አየ። 31 ከዚያም “የሻፋጥ ልጅ የኤልሳዕ ጭንቅላት ዛሬ አንገቱ ላይ ካደረ አምላክ እንዲህ ያድርግብኝ፤ ከዚህ የባሰም ያምጣብኝ!” አለ።+
32 ኤልሳዕ ቤቱ ውስጥ ተቀምጦ ነበር፤ ሽማግሌዎቹም አብረውት ተቀምጠው ነበር። ንጉሡ አንድ ሰው ከፊቱ አስቀድሞ ላከ፤ ሆኖም መልእክተኛው ከመድረሱ በፊት ኤልሳዕ ሽማግሌዎቹን እንዲህ አላቸው፦ “ይህ የነፍሰ ገዳይ ልጅ+ ጭንቅላቴን ሊያስቆርጥ ሰው እንደላከ ታያላችሁ? በሉ መልእክተኛው ሲመጣ በሩን ዝጉት፤ ደግሞም እንዳይገባ በሩን ዘግታችሁ ያዙት። የጌታው ኮቴ ድምፅ ከኋላው ይሰማ የለም?” 33 እሱም ገና ከእነሱ ጋር እየተነጋገረ ሳለ መልእክተኛው ወደ እሱ ደረሰ፤ ንጉሡም “ይህ ከይሖዋ የመጣ ጥፋት ነው። ታዲያ ከዚህ በላይ ይሖዋን ለምን እጠብቃለሁ?” አለ።
7 ኤልሳዕም እንዲህ አለ፦ “የይሖዋን ቃል ስሙ። ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘ነገ በዚህ ሰዓት ገደማ በሰማርያ በር* ላይ አንድ የሲህ መስፈሪያ* የላመ ዱቄት በአንድ ሰቅል* እንዲሁም ሁለት የሲህ መስፈሪያ ገብስ በአንድ ሰቅል ይሸጣል።’”+ 2 በዚህ ጊዜ ንጉሡ የሚተማመንበት የጦር መኮንን የእውነተኛውን አምላክ ሰው “ይሖዋ የሰማይን የውኃ በሮች ቢከፍት እንኳ እንዲህ ያለ ነገር* ሊፈጸም ይችላል?”+ አለው። ኤልሳዕም “ይህን በገዛ ዓይኖችህ ታያለህ፤+ ሆኖም ከዚያ ምንም አትቀምስም”+ አለው።
3 በከተማዋ መግቢያ በር ላይ በሥጋ ደዌ የተያዙ አራት ሰዎች ነበሩ፤+ እነሱም እርስ በርሳቸው እንዲህ ተባባሉ፦ “እስክንሞት ድረስ እዚህ ቁጭ የምንለው ለምንድን ነው? 4 ‘ወደ ከተማዋ እንግባ’ ብንል ከተማዋ ውስጥ ረሃብ+ ስላለ እዚያ መሞታችን አይቀርም። እዚህም ብንቀመጥ ያው የሚጠብቀን ሞት ነው። ስለዚህ ዝም ብለን ወደ ሶርያውያን ሰፈር እንሂድ። ካልገደሉን ሕይወታችን ይተርፋል፤ ከገደሉንም ያው ሞቶ መገላገል ነው።” 5 ከዚያም ጨለምለም ሲል ተነስተው ወደ ሶርያውያን ሰፈር ሄዱ። ወደ ሶርያውያን ሰፈር ዳርቻ በደረሱ ጊዜ በዚያ አንድም ሰው አልነበረም።
6 ምክንያቱም ይሖዋ የሶርያውያን ሰፈር የጦር ሠረገሎችን ድምፅ፣ የፈረሶችን ድምፅና የታላቅ ሠራዊት ድምፅ እንዲሰማ አድርጎ ነበር።+ በመሆኑም እርስ በርሳቸው “የእስራኤል ንጉሥ እኛን ለመውጋት የሂታውያንንና የግብፅን ነገሥታት ቀጥሮብናል!” ተባባሉ። 7 እነሱም ወዲያውኑ ተነስተው በምሽት ሸሹ፤ ድንኳኖቻቸውን፣ ፈረሶቻቸውንና አህዮቻቸውን እንዲሁም ሰፈሩን እንዳለ ትተው ሕይወታቸውን* ለማዳን እግሬ አውጪኝ አሉ።
8 በሥጋ ደዌ የተያዙት እነዚህ ሰዎች ወደ ሰፈሩ ዳርቻ ከደረሱ በኋላ ወደ አንዱ ድንኳን ገብተው መብላትና መጠጣት ጀመሩ። ከዚያም ብር፣ ወርቅና ልብስ ይዘው በመሄድ ደበቁት። ከዚያም ተመልሰው መጥተው ወደ ሌላ ድንኳን በመግባት የተለያዩ ነገሮችን ወሰዱ፤ እነዚህንም ይዘው በመሄድ ደበቁ።
9 በመጨረሻም እርስ በርሳቸው እንዲህ ተባባሉ፦ “እያደረግን ያለነው ነገር ትክክል አይደለም። ይህ ቀን እኮ ምሥራች የሚነገርበት ቀን ነው! የምናመነታና እስኪነጋ ድረስ የምንጠብቅ ከሆነ መቀጣታችን አይቀርም። በመሆኑም አሁን ወደ ንጉሡ ቤት ሄደን ይህን ነገር እንናገር።” 10 ስለሆነም ሄደው የከተማዋን በር ጠባቂዎች በመጥራት እንዲህ አሏቸው፦ “ወደ ሶርያውያን ሰፈር ገብተን ነበር፤ ሆኖም በዚያ አንድም ሰው አልነበረም፤ የአንድም ሰው ድምፅ አልሰማንም። እዚያ የነበሩት የታሰሩ ፈረሶችና አህዮች ብቻ ናቸው፤ ድንኳኖቹም እንዳሉ ነበሩ።” 11 የከተማዋ በር ጠባቂዎችም ወዲያውኑ ይህን አስተጋቡ፤ ወሬውም በንጉሡ ቤት ተሰማ።
12 ንጉሡም ወዲያውኑ በሌሊት ተነስቶ አገልጋዮቹን እንዲህ አላቸው፦ “ሶርያውያን ምን እንዳደረጉብን ልንገራችሁ። እንደተራብን+ ያውቃሉ፤ በመሆኑም ‘እነሱ ከተማዋን ለቀው ይወጣሉ፤ እኛም በሕይወት እንዳሉ እንይዛቸዋለን፤ ወደ ከተማዋም እንገባለን’ በማለት በዱር ለመደበቅ ከሰፈሩ ወጥተው ሄደዋል።”+ 13 ከዚያም ከአገልጋዮቹ አንዱ እንዲህ አለ፦ “የተወሰኑ ሰዎች በከተማዋ ውስጥ ከቀሩት ፈረሶች አምስቱን ይዘው ይሂዱ። እነዚህ ሰዎች እንደሆነ እዚህ ከሚቀረው የእስራኤል ሕዝብ ሁሉ የተለየ ምንም አይደርስባቸውም። የሚጠብቃቸው ነገር ቢኖር በዚህ እንዳለቁት እስራኤላውያን መሆን ነው። ስለሆነም እንላካቸውና የሚሆነውን እንይ።” 14 ስለዚህ ሁለት ሠረገሎችን ከፈረሶች ጋር ወሰዱ፤ ንጉሡም “ሄዳችሁ እዩ” በማለት ወደ ሶርያውያን ሰፈር ላካቸው። 15 እነሱም ዮርዳኖስ ድረስ ተከትለዋቸው ሄዱ፤ ሶርያውያን በድንጋጤ ሲሸሹ ጥለዋቸው የሄዱት ልብሶችና ዕቃዎች መንገዱን ሁሉ ሞልተውት ነበር። መልእክተኞቹም ተመልሰው በመምጣት ሁኔታውን ለንጉሡ ነገሩት።
16 ከዚያም ሕዝቡ ወጥቶ የሶርያውያንን ሰፈር በዘበዘ፤ በመሆኑም ይሖዋ በተናገረው መሠረት አንድ የሲህ መስፈሪያ የላመ ዱቄት በአንድ ሰቅል እንዲሁም ሁለት የሲህ መስፈሪያ ገብስ በአንድ ሰቅል ተሸጠ።+ 17 ንጉሡ፣ የሚተማመንበትን የጦር መኮንን የከተማዋ በር ኃላፊ አድርጎ ሾመው፤ ይሁንና ሕዝቡ በሩ ላይ የጦር መኮንኑን ረጋገጠው፤ የእውነተኛው አምላክ ሰው ንጉሡ ወደ እሱ በወረደ ጊዜ በተናገረው መሠረት ሞተ። 18 የእውነተኛው አምላክ ሰው “ነገ በዚህ ሰዓት በሰማርያ በር ላይ ሁለት የሲህ መስፈሪያ ገብስ በአንድ ሰቅል እንዲሁም አንድ የሲህ መስፈሪያ የላመ ዱቄት በአንድ ሰቅል ይሸጣል”+ በማለት ለንጉሡ የተናገረው ነገር ተፈጸመ። 19 የጦር መኮንኑ ግን የእውነተኛውን አምላክ ሰው “ይሖዋ የሰማይን የውኃ በሮች ቢከፍት እንኳ ይህ የተባለው ነገር* ይፈጸማል?” ብሎት ነበር። በዚህ ጊዜ ኤልሳዕ “ይህን በገዛ ዓይኖችህ ታያለህ፤ ሆኖም ከዚያ ምንም አትቀምስም” ብሎት ነበር። 20 የጦር መኮንኑ፣ ሕዝቡ በሩ ላይ ረጋግጦት ስለሞተ ልክ እንደተባለው ደረሰበት።
8 ኤልሳዕ፣ ልጇን ከሞት ያስነሳላትን+ ሴት “ተነስተሽ ከቤተሰብሽ ጋር የባዕድ አገር ሰው ሆነሽ መኖር ወደምትችዪበት ቦታ ሂጂ፤ ይሖዋ ረሃብ እንደሚከሰት ተናግሯልና፤+ ደግሞም ረሃቡ በምድሪቱ ላይ ለሰባት ዓመት ይቆያል” አላት። 2 በመሆኑም ሴትየዋ ተነስታ የእውነተኛው አምላክ ሰው እንደነገራት አደረገች። እሷም ከመላ ቤተሰቧ ጋር ሄደች፤ በፍልስጤማውያንም+ ምድር ለሰባት ዓመት ተቀመጠች።
3 በሰባቱ ዓመት ማብቂያ ላይ ሴትየዋ ከፍልስጤማውያን ምድር ተመልሳ መጣች፤ ከዚያም ስለ ቤቷና ስለ መሬቷ ለንጉሡ አቤቱታ ለማቅረብ ሄደች። 4 በዚህ ጊዜ ንጉሡ የእውነተኛው አምላክ ሰው አገልጋይ የሆነውን ግያዝን “እስቲ ኤልሳዕ ያደረጋቸውን ታላላቅ ነገሮች በሙሉ ተርክልኝ” እያለው ነበር።+ 5 እሱም ኤልሳዕ የሞተውን ልጅ እንዴት እንዳስነሳው+ ለንጉሡ እየተረከለት ሳለ ኤልሳዕ ልጇን ከሞት ያስነሳላት ሴት ስለ ቤቷና ስለ መሬቷ ለንጉሡ አቤቱታ ለማቅረብ መጣች።+ ግያዝም ወዲያውኑ “ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፣ ሴትየዋ ይህች ናት፤ ኤልሳዕ ያስነሳው ልጇም ይሄ ነው” አለው። 6 በዚህ ጊዜ ንጉሡ ሴትየዋን ጠየቃት፤ እሷም ታሪኩን ነገረችው። ከዚያም ንጉሡ ከቤተ መንግሥት ባለሥልጣናቱ አንዱን “የእሷ የሆነውን በሙሉ እንዲሁም መሬቷን ከለቀቀችበት ቀን አንስቶ እስካሁን ድረስ መሬቱ ያፈራውን ምርት ሁሉ መልስላት” የሚል መመሪያ በመስጠት መደበላት።
7 የሶርያ ንጉሥ ቤንሃዳድ+ ታሞ ሳለ ኤልሳዕ ወደ ደማስቆ+ መጣ። በመሆኑም “የእውነተኛው አምላክ ሰው+ ወደዚህ መጥቷል” ተብሎ ተነገረው። 8 በዚህ ጊዜ ንጉሡ ሃዛኤልን+ “ስጦታ ይዘህ ወደ እውነተኛው አምላክ ሰው+ ሂድ። በእሱም አማካኝነት ይሖዋን ‘ከዚህ በሽታ እድናለሁ?’ ብለህ ጠይቀው” አለው። 9 ሃዛኤልም በደማስቆ ከሚገኘው ምርጥ ነገር ሁሉ 40 የግመል ጭነት ስጦታ ይዞ ሊያገኘው ሄደ። እሱም መጥቶ በፊቱ በመቆም “ልጅህ የሶርያ ንጉሥ ቤንሃዳድ ‘ከዚህ በሽታ እድናለሁ?’ በማለት ወደ አንተ ልኮኛል” አለው። 10 ኤልሳዕም “ሂድና ‘በእርግጥ ትድናለህ’ በለው፤ ሆኖም መሞቱ እንደማይቀር ይሖዋ አሳይቶኛል”+ ሲል መለሰለት። 11 ደግሞም እስኪያፍር ድረስ ትኩር ብሎ ተመለከተው። ከዚያም የእውነተኛው አምላክ ሰው አለቀሰ። 12 ሃዛኤልም “ጌታዬ የሚያለቅሰው ለምንድን ነው?” በማለት ጠየቀው። እሱም እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “በእስራኤል ሕዝብ ላይ ምን ዓይነት ጉዳት እንደምታደርስ ስለማውቅ ነው።+ የተመሸጉ ስፍራዎቻቸውን በእሳት ታቃጥላለህ፤ ምርጥ የሆኑ ሰዎቻቸውን በሰይፍ ትገድላለህ፤ ልጆቻቸውንም ትፈጠፍጣለህ፤ ነፍሰ ጡር የሆኑ ሴቶቻቸውንም ሆድ ትቀድዳለህ።”+ 13 ሃዛኤልም “ለመሆኑ ተራ ውሻ የሆነው አገልጋይህ እንዲህ ያለ ነገር እንዴት ሊያደርግ ይችላል?” አለው። ኤልሳዕ ግን “አንተ በሶርያ ላይ ንጉሥ እንደምትሆን ይሖዋ አሳይቶኛል” አለው።+
14 ከዚያም ከኤልሳዕ ተለይቶ በመሄድ ወደ ጌታው መጣ፤ ቤንሃዳድም “ለመሆኑ ኤልሳዕ ምን አለህ?” አለው። እሱም “በእርግጥ እንደምትድን ነግሮኛል” ሲል መለሰለት።+ 15 በማግስቱ ግን ሃዛኤል የአልጋ ልብስ ወስዶ ውኃ ውስጥ ከነከረ በኋላ የንጉሡን ፊት ሸፈነው፤ ንጉሡም ሞተ።+ ሃዛኤልም በምትኩ ነገሠ።+
16 የእስራኤል ንጉሥ የአክዓብ ልጅ ኢዮራም+ በነገሠ በአምስተኛው ዓመት የይሁዳ ንጉሥ የኢዮሳፍጥ ልጅ ኢዮራም ነገሠ፤+ በዚህ ጊዜ ኢዮሳፍጥ በይሁዳ ንጉሥ ሆኖ ይገዛ ነበር። 17 ኢዮራም በነገሠ ጊዜ ዕድሜው 32 ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌምም ሆኖ ስምንት ዓመት ገዛ። 18 የአክዓብን ልጅ አግብቶ+ ስለነበር ከአክዓብ ቤት የሆኑት እንዳደረጉት+ ሁሉ እሱም በእስራኤል ነገሥታት መንገድ ሄደ፤+ በይሖዋም ፊት መጥፎ የሆነውን ነገር አደረገ።+ 19 ሆኖም ይሖዋ ለአገልጋዩ ለዳዊት ሲል ይሁዳን ማጥፋት አልፈለገም፤+ ምክንያቱም ለእሱና ለልጆቹ ለሁልጊዜ የሚኖር መብራት እንደሚሰጥ ቃል ገብቶ ነበር።+
20 በእሱ ዘመን ኤዶም በይሁዳ ላይ ዓምፆ+ የራሱን ንጉሥ አነገሠ።+ 21 በመሆኑም ኢዮራም ሠረገሎቹን ሁሉ ይዞ ወደ ጻኢር ተሻገረ፤ በሌሊትም ተነስቶ እሱንና የሠረገሎቹን አዛዦች ከበው የነበሩትን ኤዶማውያን ድል አደረገ፤ ሠራዊቱም ሸሽቶ ወደየድንኳኑ ሄደ። 22 ሆኖም ኤዶም እስከ ዛሬ ድረስ በይሁዳ ላይ እንዳመፀ ነው። ሊብናም+ በዚሁ ጊዜ ዓመፀ።
23 የቀረው የኢዮራም ታሪክ፣ ያደረጋቸው ነገሮች ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት ዘመን ስለተፈጸሙት ነገሮች በሚተርከው የታሪክ መጽሐፍ ውስጥ ተጽፈው ይገኙ የለም? 24 በመጨረሻም ኢዮራም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ ከአባቶቹም ጋር በዳዊት ከተማ ተቀበረ።+ በእሱም ምትክ ልጁ አካዝያስ+ ነገሠ።
25 የእስራኤል ንጉሥ የአክዓብ ልጅ ኢዮራም በነገሠ በ12ኛው ዓመት የይሁዳ ንጉሥ የኢዮራም ልጅ አካዝያስ ነገሠ።+ 26 አካዝያስ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው 22 ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌምም ሆኖ አንድ ዓመት ገዛ። እናቱም ጎቶልያ+ የተባለች የእስራኤል ንጉሥ የኦምሪ+ የልጅ ልጅ* ነበረች። 27 እሱም ከአክዓብ ቤተሰብ ጋር በጋብቻ ተሳስሮ ስለነበር የአክዓብን ቤት መንገድ ተከተለ፤ እንዲሁም የአክዓብ ቤት እንዳደረገው ሁሉ በይሖዋ ፊት መጥፎ የሆነውን ነገር አደረገ።+ 28 በመሆኑም አካዝያስ ከአክዓብ ልጅ ከኢዮራም ጋር ሆኖ ከሶርያ ንጉሥ ከሃዛኤል ጋር ለመዋጋት ወደ ራሞትጊልያድ+ ሄደ፤ ሆኖም ሶርያውያን ኢዮራምን አቆሰሉት።+ 29 ስለዚህ ንጉሥ ኢዮራም ከሶርያ ንጉሥ ከሃዛኤል ጋር በተዋጋበት ጊዜ ሶርያውያን በራማ ካቆሰሉት ቁስል ለማገገም ወደ ኢይዝራኤል+ ተመለሰ።+ የይሁዳ ንጉሥ የኢዮራም ልጅ አካዝያስ፣ የአክዓብ ልጅ ኢዮራም ቆስሎ* ስለነበር እሱን ለማየት ወደ ኢይዝራኤል ወረደ።
9 ከዚያም ነቢዩ ኤልሳዕ ከነቢያት ልጆች አንዱን ጠርቶ እንዲህ አለው፦ “ልብስህን በወገብህ ታጠቅና ይህን የዘይት ዕቃ ይዘህ ወደ ራሞትጊልያድ+ በፍጥነት ሂድ። 2 እዚያም ስትደርስ የኒምሺን ልጅ፣ የኢዮሳፍጥን ልጅ ኢዩን+ ፈልገው፤ ከዚያም ገብተህ ከወንድሞቹ መካከል አስነሳውና ወደ ውስጠኛው ክፍል ውሰደው። 3 የዘይቱንም ዕቃ ወስደህ ዘይቱን በራሱ ላይ አፍስ፤ እንዲህም በለው፦ ‘ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “አንተን በእስራኤል ላይ ንጉሥ አድርጌ ቀብቼሃለሁ።”’+ ከዚያም በሩን ከፍተህ በፍጥነት ሽሽ።”
4 በመሆኑም የነቢዩ አገልጋይ ወደ ራሞትጊልያድ አቀና። 5 እዚያም ሲደርስ የሠራዊቱ አለቆች ተቀምጠው አገኛቸው። እሱም “አለቃ ሆይ፣ የምነግርህ መልእክት አለኝ” አለ። ኢዩም “ለማናችን ነው?” ሲል ጠየቀው። እሱም “አለቃ ሆይ፣ ለአንተ ነው” አለው። 6 በመሆኑም ኢዩ ተነስቶ ወደ ቤት ገባ፤ አገልጋዩም ዘይቱን በኢዩ ራስ ላይ በማፍሰስ እንዲህ አለው፦ “የእስራኤል አምላክ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘አንተን በይሖዋ ሕዝብ፣ በእስራኤል ላይ ንጉሥ አድርጌ ቀብቼሃለሁ።+ 7 አንተም የጌታህን የአክዓብን ቤት ትመታለህ፤ እኔም የአገልጋዮቼን የነቢያትን ደምና በኤልዛቤል እጅ የሞቱትን የይሖዋን አገልጋዮች ሁሉ ደም እበቀላለሁ።+ 8 የአክዓብም ቤት በጠቅላላ ይጠፋል፤ ደግሞም በእስራኤል ውስጥ ያለውን ምስኪኑንም ሆነ ደካማውን ጨምሮ ከአክዓብ ቤት ወንድ የተባለውን ሁሉ* ጠራርጌ አጠፋለሁ።+ 9 የአክዓብንም ቤት እንደ ናባጥ ልጅ እንደ ኢዮርብዓም ቤትና+ እንደ አኪያህ ልጅ እንደ ባኦስ ቤት+ አደርገዋለሁ። 10 ኤልዛቤልን ደግሞ ኢይዝራኤል ውስጥ በሚገኝ የእርሻ ቦታ ውሾች ይበሏታል፤+ የሚቀብራትም አይኖርም።’” ይህን ከተናገረም በኋላ በሩን ከፍቶ ሸሸ።+
11 ኢዩ ወጥቶ ወደ ጌታው አገልጋዮች ሲሄድ “ሁሉም ነገር ደህና ነው? ይህ እብድ ወደ አንተ የመጣው ለምንድን ነው?” ብለው ጠየቁት። እሱም “መቼም ሰውየውንም ሆነ የሚናገረውን ነገር ታውቁታላችሁ” አላቸው። 12 እነሱ ግን “ይሄ እንኳ ትክክል አይደለም! ይልቅስ እውነቱን ንገረን” አሉት። ከዚያም ኢዩ “እንግዲህ የነገረኝ ይህ ነው፤ ደግሞም እንዲህ ብሏል፦ ‘ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “በእስራኤል ላይ ንጉሥ አድርጌ ቀብቼሃለሁ።”’”+ 13 በዚህ ጊዜ እያንዳንዳቸው ቶሎ ብለው ልብሳቸውን በማውለቅ ደረጃዎቹ ላይ አነጠፉለት፤+ ቀንደ መለከትም ነፍተው “ኢዩ ነግሦአል!” አሉ።+ 14 ከዚያም የኒምሺ ልጅ፣ የኢዮሳፍጥ ልጅ ኢዩ+ በኢዮራም ላይ አሴረ።
ኢዮራም ከሶርያ ንጉሥ ከሃዛኤል+ የተነሳ ከእስራኤል ሁሉ ጋር ሆኖ ራሞትጊልያድን+ እየጠበቀ ነበር። 15 በኋላም ንጉሥ ኢዮራም ከሶርያ ንጉሥ ከሃዛኤል ጋር በተዋጋበት ጊዜ ሶርያውያን ካደረሱበት ቁስል ለማገገም ወደ ኢይዝራኤል+ ተመለሰ።+
ኢዩም “እንግዲህ ከተስማማችሁ* ወደ ኢይዝራኤል ሄዶ ይህን ወሬ የሚያቀብል ሰው እንዳይኖር ማንም ሰው ከከተማዋ ሾልኮ እንዳይወጣ ጠብቁ” አለ። 16 ከዚያም ኢዩ ሠረገላው ላይ ወጥቶ ወደ ኢይዝራኤል ሄደ፤ ምክንያቱም ኢዮራም ቆስሎ በዚያ ተኝቶ ነበር፤ የይሁዳ ንጉሥ አካዝያስም ኢዮራምን ለመጠየቅ ወደዚያ ወርዶ ነበር። 17 ጠባቂውም በኢይዝራኤል ማማ ላይ ቆሞ ሳለ የኢዩ ሰዎች ግር ብለው ሲመጡ አየ። ወዲያውኑም “ሰዎች ግር ብለው ሲመጡ ይታየኛል” አለ። ኢዮራምም “አንድ ፈረሰኛ ጠርተህ ወደ እነሱ ላክ፤ እሱም ‘የመጣችሁት በሰላም ነው?’ ይበላቸው” አለ። 18 ስለሆነም አንድ ፈረሰኛ ወደ ኢዩ ሄዶ “ንጉሡ ‘የመጣችሁት በሰላም ነው?’ ይላል” አለው። ኢዩ ግን “አንተ ስለ ‘ሰላም’ ምን ይመለከትሃል? ይልቅስ ከኋላዬ ተሰለፍ!” አለው።
ጠባቂውም “መልእክተኛው እነሱ ጋ ደርሷል፤ ሆኖም አልተመለሰም” በማለት ተናገረ። 19 በመሆኑም ሁለተኛ ፈረሰኛ ላከ፤ እሱም እነሱ ጋ ሲደርስ “ንጉሡ ‘የመጣችሁት በሰላም ነው?’ ይላል” አለ። ኢዩ ግን “አንተ ስለ ‘ሰላም’ ምን ይመለከትሃል? ይልቅስ ከኋላዬ ተሰለፍ!” አለው።
20 ጠባቂውም “መልእክተኛው እነሱ ጋ ደርሷል፤ ሆኖም አልተመለሰም፤ ሰውየው ሠረገላ አነዳዱ የኒምሺን የልጅ ልጅ* የኢዩን ይመስላል፤ የሚነዳው ልክ እንደ እብድ ነውና” በማለት ተናገረ። 21 ኢዮራምም “ሠረገላዬን አዘጋጁልኝ!” አለ። በመሆኑም የጦር ሠረገላው ተዘጋጀለት፤ የእስራኤል ንጉሥ ኢዮራምና የይሁዳ ንጉሥ አካዝያስም+ በየራሳቸው የጦር ሠረገላ ሆነው ኢዩን ለመገናኘት ወጡ። በኢይዝራኤላዊው በናቡቴ የእርሻ ቦታ+ ላይ ከእሱ ጋር ተገናኙ።
22 ኢዮራምም ኢዩን እንዳየው “ኢዩ፣ የመጣኸው በሰላም ነው?” አለው። እሱ ግን “የእናትህ የኤልዛቤል+ ምንዝርና መተት+ እያለ ምን ሰላም አለ?” አለው። 23 ኢዮራምም ለመሸሽ ወዲያውኑ ሠረገላውን አዙሮ አካዝያስን “አካዝያስ ተታለናል!” አለው። 24 ኢዩም ቀስቱን አስፈንጥሮ ኢዮራምን በትከሻዎቹ መካከል ወጋው፤ ቀስቱም በልቡ በኩል ወጣ፤ ኢዮራምም እዚያው ጦር ሠረገላው ውስጥ ወደቀ። 25 ኢዩም የጦር መኮንኑን ቢድቃርን እንዲህ አለው፦ “አንስተህ በኢይዝራኤላዊው በናቡቴ የእርሻ ቦታ ላይ ጣለው።+ እኔና አንተ በሠረገሎች ሆነን አባቱን አክዓብን እንከተለው በነበረ ጊዜ ይሖዋ ራሱ በእሱ ላይ ይህን ፍርድ እንዳስተላለፈ አስታውስ፦+ 26 ‘“ትናንት የናቡቴን ደምና የልጆቹን ደም እንዳየሁ ሁሉ”+ ይላል ይሖዋ፣ “በዚህ የእርሻ ቦታ ላይ ዋጋህን እከፍልሃለሁ”+ ይላል ይሖዋ።’ በመሆኑም ይሖዋ በተናገረው ቃል መሠረት አንስተህ እርሻው ላይ ጣለው።”+
27 የይሁዳ ንጉሥ አካዝያስ+ ይህን ሲያይ በአትክልት ቤቱ በኩል ባለው መንገድ ሸሸ። (በኋላም ኢዩ እሱን እያሳደደው “እሱንም ግደሉት!” አለ። እነሱም በይብለአም+ አጠገብ ወደምትገኘው ወደ ጉር ሽቅብ በሚያስወጣው መንገድ ላይ ሠረገላው ውስጥ እንዳለ አቆሰሉት። እሱ ግን ወደ መጊዶ ሸሸ፤ በዚያም ሞተ። 28 ከዚያም አገልጋዮቹ በሠረገላ ጭነው ወደ ኢየሩሳሌም ወሰዱት፤ በዳዊት ከተማ+ ከአባቶቹ ጋር በራሱ መቃብር ቀበሩት። 29 አካዝያስ+ በይሁዳ ላይ የነገሠው የአክዓብ ልጅ ኢዮራም በነገሠ በ11ኛው ዓመት ነበር።)
30 ከዚያም ኢዩ ወደ ኢይዝራኤል+ መጣ፤ ኤልዛቤልም+ ይህን ሰማች። በመሆኑም ዓይኖቿን ተኩላና ፀጉሯን አሰማምራ በመስኮት ቁልቁል ትመለከት ጀመር። 31 ኢዩም በቅጥሩ በር በኩል ሲገባ ኤልዛቤል “ጌታውን የገደለው ዚምሪ ምን እንደደረሰበት አታውቅም?” አለችው።+ 32 እሱም ወደ መስኮቱ ቀና ብሎ በመመልከት “ከእኔ ጎን የቆመ ማን ነው? ማን ነው?”+ አለ። ወዲያውኑ ሁለት ወይም ሦስት የሚሆኑ የቤተ መንግሥት ባለሥልጣናት ቁልቁል ተመለከቱት። 33 እሱም “ወደ ታች ወርውሯት!” አላቸው። እነሱም ወረወሯት፤ ደሟም በግድግዳውና በፈረሶቹ ላይ ተረጨ፤ ኢዩም በፈረሶቹ ረጋገጣት። 34 ከዚያም ገብቶ በላ፤ ጠጣም። በኋላም “እባካችሁ ይህችን የተረገመች ሴት አንስታችሁ ቅበሯት። ምንም ቢሆን የንጉሥ ልጅ ናት”+ አላቸው። 35 ሊቀብሯት ሲሄዱ ግን ከራስ ቅሏ፣ ከእግሮቿና ከእጆቿ መዳፍ በስተቀር ምኗንም አላገኙም።+ 36 እነሱም ተመልሰው በነገሩት ጊዜ እንዲህ አላቸው፦ “ይህ እኮ ይሖዋ በአገልጋዩ በቲሽባዊው በኤልያስ አማካኝነት እንዲህ በማለት የተናገረው ቃል ፍጻሜ ነው፦+ ‘በኢይዝራኤል በሚገኘው የእርሻ ቦታ ውሾች የኤልዛቤልን ሥጋ ይበላሉ።+ 37 ሰዎች “ይህች እኮ ኤልዛቤል ናት” እንዳይሉ የኤልዛቤል በድን በኢይዝራኤል የእርሻ ቦታ ላይ እንደ ፍግ ይሆናል።’”
10 አክዓብ+ በሰማርያ 70 ወንዶች ልጆች ነበሩት። በመሆኑም ኢዩ ደብዳቤዎች ጽፎ በሰማርያ ወደሚገኙት የኢይዝራኤል መኳንንትና ሽማግሌዎች እንዲሁም ወደ አክዓብ ልጆች ሞግዚቶች* ላከ፤+ መልእክቱ እንዲህ የሚል ነበር፦ 2 “አሁን ይህ ደብዳቤ ሲደርሳችሁ የጌታችሁ ወንዶች ልጆች ከእናንተ ጋር ይሆናሉ፤ እንዲሁም የጦር ሠረገሎች፣ ፈረሶች፣ የተመሸገች ከተማና የጦር መሣሪያ ይኖራችኋል። 3 በመሆኑም ከጌታችሁ ወንዶች ልጆች መካከል የተሻለውንና ብቃት ያለውን* መርጣችሁ በአባቱ ዙፋን ላይ አስቀምጡት። ከዚያም ለጌታችሁ ቤት ተዋጉ።”
4 እነሱ ግን በፍርሃት ተውጠው “ሁለት ነገሥታት በፊቱ ሊቆሙ ካልቻሉ+ እኛ እንዴት ልንቆም እንችላለን?” አሉ። 5 በመሆኑም የቤተ መንግሥቱ ኃላፊ፣* የከተማዋ ገዢ፣ ሽማግሌዎቹና ሞግዚቶቹ “እኛ የአንተ አገልጋዮች ነን፤ አንተ ያልከንን ሁሉ እናደርጋለን። ማንንም አናነግሥም። አንተ ራስህ መልካም መስሎ የታየህን አድርግ” በማለት ወደ ኢዩ መልእክት ላኩ።
6 ከዚያም ኢዩ “የእኔ ከሆናችሁና እኔን ለመታዘዝ ፈቃደኛ ከሆናችሁ የጌታችሁን ወንዶች ልጆች ራስ ቆርጣችሁ ነገ በዚህ ሰዓት ወደ ኢይዝራኤል ይዛችሁልኝ ኑ” የሚል ሁለተኛ ደብዳቤ ጻፈላቸው።
በዚህ ጊዜ 70ዎቹ የንጉሡ ልጆች አሳዳጊዎቻቸው ከሆኑት ታዋቂ የከተማዋ ሰዎች ጋር ነበሩ። 7 እነሱም ደብዳቤው እንደደረሳቸው 70ዎቹን የንጉሡን ልጆች ወስደው አረዷቸው፤+ ከዚያም ጭንቅላታቸውን በቅርጫቶች ውስጥ አድርገው ወደ ኢይዝራኤል ላኩለት። 8 መልእክተኛውም ገብቶ “የንጉሡን ልጆች ጭንቅላት አምጥተዋል” አለው። እሱም “በከተማዋ መግቢያ በር ላይ ሁለት ቦታ ቆልላችሁ እስከ ጠዋት ድረስ አቆዩአቸው” አለ። 9 ከዚያም ጠዋት ላይ ሲወጣ በሕዝቡ ሁሉ ፊት ቆሞ እንዲህ አላቸው፦ “እናንተ ንጹሐን* ናችሁ። በጌታዬ ላይ ያሴርኩትና የገደልኩት እኔ ነኝ፤+ እነዚህን ሁሉ ግን የገደላቸው ማን ነው? 10 እንግዲህ ይሖዋ በአክዓብ ቤት ላይ ከተናገረው የይሖዋ ቃል አንዱም እንኳ ሳይፈጸም እንደማይቀር* እወቁ፤+ ይሖዋ በአገልጋዩ በኤልያስ አማካኝነት የተናገረውን ቃል ፈጽሟል።”+ 11 በተጨማሪም ኢዩ በኢይዝራኤል ከአክዓብ ቤት የቀሩትን ሁሉ እንዲሁም ታዋቂ የሆኑ ሰዎቹን፣ ወዳጆቹንና ካህናቱን አንድም ሳያስቀር ገደላቸው።+
12 ከዚያም ተነስቶ ወደ ሰማርያ አቀና። በመንገዱ ላይም የእረኞች ማቆያ ቤት* ይገኝ ነበር። 13 በዚያም ኢዩ የይሁዳን ንጉሥ የአካዝያስን+ ወንድሞች አገኛቸው፤ እሱም “እናንተ እነማን ናችሁ?” ሲላቸው “እኛ የአካዝያስ ወንድሞች ነን፤ የንጉሡን ልጆችና የንጉሡን እናት* ልጆች ደህንነት ለመጠየቅ እየወረድን ነው” አሉት። 14 እሱም ወዲያውኑ “በሕይወት እንዳሉ ያዟቸው!” አለ። በመሆኑም በሕይወት እንዳሉ ያዟቸው፤ በእረኞች ማቆያው ቤት አጠገብ በሚገኘው የውኃ ማጠራቀሚያ ጉድጓድ 42ቱን ሰዎች አረዷቸው። ከመካከላቸው አንድም ሰው አላስተረፈም።+
15 ከዚያ ተነስቶ ሲሄድ የሬካብን+ ልጅ ኢዮናዳብን+ ወደ እሱ ሲመጣ አገኘው። ኢዩም ሰላምታ ሰጥቶት* “የእኔ ልብ ከልብህ ጋር እንደሆነው ሁሉ የአንተስ ልብ ሙሉ በሙሉ* ከእኔ ጋር ነው?” አለው።
ኢዮናዳብም “አዎ ነው” ሲል መለሰለት።
ኢዩም “እንደዚያ ከሆነ እጅህን ስጠኝ” አለው።
እሱም እጁን ሰጠው፤ ኢዩም ጎትቶ ወደ ሠረገላው አወጣው። 16 ከዚያም “አብረኸኝ ሂድና ይሖዋን የሚቀናቀንን ማንኛውንም ነገር እንደማልታገሥ* እይ”+ አለው። እነሱም በጦር ሠረገላው አብሮት እንዲሄድ አደረጉ። 17 ከዚያም ወደ ሰማርያ መጣ፤ ደግሞም ይሖዋ ለኤልያስ በነገረው ቃል መሠረት+ ኢዩ በሰማርያ የሚገኙትን ከአክዓብ ቤት የቀሩትን በሙሉ ጠራርጎ እስኪያጠፋቸው ድረስ መታቸው።+
18 በተጨማሪም ኢዩ ሕዝቡን ሁሉ አንድ ላይ ሰብስቦ እንዲህ አላቸው፦ “አክዓብ ባአልን ያመለከው በትንሹ ነው፤+ ኢዩ ግን በላቀ ሁኔታ ያመልከዋል። 19 በመሆኑም የባአልን ነቢያት+ ሁሉ፣ አምላኪዎቹን ሁሉና ካህናቱን+ ሁሉ ጥሩልኝ። ለባአል ታላቅ መሥዋዕት ስለማቀርብ አንድም ሰው እንዳይቀር። የሚቀር ካለ በሕይወት አይኖርም።” ሆኖም ኢዩ ይህን ያለው የባአልን አምላኪዎች ለማጥፋት ተንኮል አስቦ ነው።
20 በመቀጠልም ኢዩ “ለባአል የተቀደሰ ጉባኤ አውጁ”* አለ። እነሱም ይህንኑ አወጁ። 21 ከዚያም ኢዩ በመላው እስራኤል መልእክት ላከ፤ የባአል አምላኪዎችም በሙሉ መጡ። ሳይመጣ የቀረ አንድም ሰው አልነበረም። እነሱም ወደ ባአል ቤት*+ ገቡ፤ የባአልም ቤት ከአፍ እስከ ገደፉ ሞላ። 22 ኢዩም የልብስ ቤቱን ኃላፊ “ለባአል አምላኪዎች ሁሉ ልብስ አውጣላቸው” አለው። እሱም ልብሶቹን አወጣላቸው። 23 ከዚያም ኢዩና የሬካብ ልጅ ኢዮናዳብ+ ወደ ባአል ቤት ገቡ። የባአልንም አምላኪዎች “ከባአል አምላኪዎች በስተቀር አንድም የይሖዋ አምላኪ እዚህ አለመኖሩን በሚገባ አረጋግጡ” አላቸው። 24 በመጨረሻም መሥዋዕቶችንና የሚቃጠሉ መባዎችን ለማቅረብ ገቡ። ኢዩም የራሱ የሆኑ 80 ሰዎችን ውጭ አቁሞ “በእጃችሁ አሳልፌ ከምሰጣችሁ ሰዎች መካከል አንድ ሰው ቢያመልጥ የእናንተ ሕይወት በዚያ ሰው ሕይወት* ይተካል” አላቸው።
25 ኢዩም የሚቃጠለውን መባ አቅርቦ እንደጨረሰ ጠባቂዎቹንና* የጦር መኮንኖቹን “ግቡና ጨፍጭፏቸው! አንድም ሰው እንዳያመልጥ!”+ አላቸው። ጠባቂዎቹና የጦር መኮንኖቹም በሰይፍ ጨፈጨፏቸው፤ ሬሳቸውንም ወደ ውጭ ጣሉ፤ እስከ ባአል ቤት ውስጠኛ መቅደስም * ድረስ ዘልቀው ገቡ። 26 ከዚያም የባአልን ቤት የማምለኪያ ዓምዶች+ አውጥተው አንድ በአንድ አቃጠሉ።+ 27 የባአልን የማምለኪያ ዓምድ ፈረካከሱ፤+ የባአልንም ቤት+ በማፈራረስ መጸዳጃ ቦታ እንዲሆን አደረጉ፤ እስከ ዛሬም ድረስ እንደዚያው ነው።
28 በዚህ መንገድ ኢዩ ባአልን ከእስራኤል አስወገደ። 29 ሆኖም የናባጥን ልጅ የኢዮርብዓምን ኃጢአት ይኸውም በቤቴልና በዳን ከነበሩት የወርቅ ጥጆች+ ጋር በተያያዘ እስራኤላውያን እንዲፈጽሙ ያደረገውን ኃጢአት ከመከተል ዞር አላለም። 30 ስለሆነም ይሖዋ ኢዩን “በአክዓብ ቤት ላይ በልቤ ያሰብኩትን+ ሁሉ በመፈጸም በፊቴ መልካምና ትክክል የሆነውን ነገር ስላደረግክ ልጆችህ እስከ አራተኛ ትውልድ ድረስ በእስራኤል ዙፋን ላይ ይቀመጣሉ”+ አለው። 31 ኢዩ ግን በሙሉ ልቡ በእስራኤል አምላክ በይሖዋ ሕግ ይሄድ ዘንድ አልተጠነቀቀም።+ ኢዮርብዓም እስራኤላውያን እንዲፈጽሙ ካደረጋቸው ኃጢአቶች ዞር አላለም።+
32 በዚያ ዘመን ይሖዋ የእስራኤልን ግዛት መቆራረስ* ጀመረ። ሃዛኤል በሁሉም የእስራኤል ግዛት ጥቃት ይሰነዝር ነበር፤+ 33 ይህም ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ ያለውን የጊልያድ ምድር ሁሉ ማለትም ጋዳውያን፣ ሮቤላውያንና ምናሴያውያን+ የሚኖሩበትን ምድር እንዲሁም ከአርኖን ሸለቆ* አጠገብ ካለው ከአሮዔር አንስቶ እስከ ጊልያድና እስከ ባሳን+ ድረስ ያለውን አካባቢ ያጠቃልላል።
34 የቀረው የኢዩ ታሪክ፣ ያደረጋቸው ነገሮች በሙሉና ኃያልነቱ ሁሉ በእስራኤል ነገሥታት ዘመን ስለተፈጸሙት ነገሮች በሚተርከው የታሪክ መጽሐፍ ውስጥ ተጽፈው ይገኙ የለም? 35 በመጨረሻም ኢዩ ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ እነሱም በሰማርያ ቀበሩት፤ ልጁ ኢዮዓካዝም+ በምትኩ ነገሠ። 36 ኢዩ በሰማርያ ሆኖ በእስራኤል ላይ የገዛበት ዘመን ርዝመት* 28 ዓመት ነበር።
11 የአካዝያስ እናት ጎቶልያ+ ልጇ መሞቱን+ ባየች ጊዜ ተነስታ የንጉሣውያኑን ቤተሰብ* በሙሉ አጠፋች።+ 2 ይሁንና የአካዝያስ እህት የሆነችው የንጉሥ ኢዮራም ልጅ የሆሼባ ሊገደሉ ከነበሩት የንጉሡ ልጆች መካከል የአካዝያስን ልጅ ኢዮዓስን+ ሰርቃ በመውሰድ እሱንና ሞግዚቱን በውስጠኛው መኝታ ክፍል አስቀመጠቻቸው። እነሱም ጎቶልያ እንዳታየው ደብቀው አቆዩት፤ በመሆኑም ሳይገደል ቀረ። 3 እሱም ከእሷ ጋር ለስድስት ዓመት በይሖዋ ቤት ተደብቆ ቆየ፤ በዚህ ጊዜ ጎቶልያ በምድሪቱ ላይ ትገዛ ነበር።
4 በሰባተኛው ዓመት ዮዳሄ መልእክት ልኮ ካራውያን ጠባቂዎቹንና የቤተ መንግሥቱን ዘቦች* የሚያዙትን መቶ አለቆች+ እሱ ወዳለበት ወደ ይሖዋ ቤት አስመጣ። ከዚያም ከእነሱ ጋር ስምምነት* አደረገ፤ እንዲሁም በይሖዋ ቤት ውስጥ አስማላቸው፤ ይህን ካደረገም በኋላ የንጉሡን ልጅ አሳያቸው።+ 5 እንዲህም ሲል አዘዛቸው፦ “እናንተም እንዲህ ታደርጋላችሁ፦ ከመካከላችሁ አንድ ሦስተኛ የምትሆኑት በሰንበት ቀን ገብታችሁ የንጉሡን ቤት*+ በተጠንቀቅ ትጠብቃላችሁ፤ 6 አንድ ሦስተኛ የምትሆኑት ደግሞ በመሠረት በር ላይ ትሆናላችሁ፤ ሌላው አንድ ሦስተኛ ከቤተ መንግሥቱ ዘቦች ኋላ ባለው በር ላይ ይሆናል። ቤቱን በየተራ ትጠብቃላችሁ። 7 ከመካከላችሁ በሰንበት ቀን ከሥራ ነፃ የሚሆኑት ሁለቱ ቡድኖች ንጉሡን ከጥቃት ለመከላከል የይሖዋን ቤት በተጠንቀቅ ይጠብቁ። 8 እያንዳንዳችሁ የጦር መሣሪያችሁን በእጃችሁ ይዛችሁ ንጉሡን ዙሪያውን ክበቡት። ረድፉን ጥሶ የገባ ማንኛውም ሰው ይገደላል። ንጉሡ በሚሄድበት ሁሉ* አብራችሁት ሁኑ።”
9 መቶ አለቆቹ+ ልክ ካህኑ ዮዳሄ እንዳዘዛቸው አደረጉ። እያንዳንዳቸውም በሰንበት ቀን ተረኛ የሚሆኑትንና በሰንበት ቀን ከሥራ ነፃ የሚሆኑትን የራሳቸውን ሰዎች ይዘው ወደ ካህኑ ወደ ዮዳሄ መጡ።+ 10 ከዚያም ካህኑ በይሖዋ ቤት የነበሩትን የንጉሥ ዳዊት ጦሮችና ክብ ጋሻዎች ለመቶ አለቆቹ ሰጣቸው። 11 የቤተ መንግሥቱ ዘቦችም+ እያንዳንዳቸው የጦር መሣሪያቸውን ይዘው በስተ ቀኝ በኩል ካለው የቤቱ ጎን አንስቶ በስተ ግራ በኩል እስካለው የቤቱ ጎን ድረስ በመሠዊያውና+ በቤቱ አጠገብ በንጉሡ ዙሪያ ቆሙ። 12 ከዚያም ዮዳሄ የንጉሡን ልጅ+ አውጥቶ አክሊሉን* ጫነበት፤ ምሥክሩንም*+ ሰጠው፤ በዚህም መንገድ አነገሡት፤ ደግሞም ቀቡት። እያጨበጨቡም “ንጉሡ ለዘላለም ይኑር!” ይሉ ጀመር።+
13 ጎቶልያ ሕዝቡ ሲሯሯጥ ስትሰማ ወዲያውኑ በይሖዋ ቤት ወዳለው ሕዝብ መጣች።+ 14 ከዚያም በነበረው ልማድ መሠረት ንጉሡ ዓምዱ አጠገብ ቆሞ አየች።+ አለቆቹና መለከት ነፊዎቹ+ ከንጉሡ ጋር ነበሩ፤ የምድሪቱም ሕዝብ ሁሉ እጅግ እየተደሰተና መለከት እየነፋ ነበር። በዚህ ጊዜ ጎቶልያ ልብሷን ቀዳ “ይህ ሴራ ነው! ሴራ ነው!” በማለት ጮኸች። 15 ካህኑ ዮዳሄ ግን በሠራዊቱ ላይ የተሾሙትን መቶ አለቆች+ “ከረድፉ መካከል አውጧት፤ እሷን ተከትሎ የሚመጣ ሰው ካለ በሰይፍ ግደሉት!” በማለት አዘዛቸው። ካህኑ “በይሖዋ ቤት ውስጥ እንዳትገድሏት” ብሎ ነበር። 16 በመሆኑም ያዟት፤ ፈረሶች ወደ ንጉሡ ቤት*+ የሚገቡበት ቦታ ላይ ስትደርስ ተገደለች።
17 ከዚያም ዮዳሄ የይሖዋ ሕዝብ ሆነው እንዲቀጥሉ ይሖዋ፣ ንጉሡና ሕዝቡ ቃል ኪዳን እንዲጋቡ አደረገ፤+ በተጨማሪም ንጉሡና ሕዝቡ ቃል ኪዳን እንዲጋቡ አደረገ።+ 18 ከዚህም በኋላ የምድሪቱ ሕዝብ ሁሉ ወደ ባአል ቤት* መጥቶ መሠዊያዎቹን አፈራረሰ፤+ ምስሎቹንም እንክትክት አድርጎ ሰባበረ፤+ የባአል ካህን የነበረውን ማታንንም በመሠዊያዎቹ ፊት ገደሉት።+
ከዚያም ካህኑ በይሖዋ ቤት ላይ የበላይ ተመልካቾችን ሾመ።+ 19 በተጨማሪም ንጉሡን አጅበው ከይሖዋ ቤት ወደ ታች እንዲያመጡት መቶ አለቆቹን፣+ ካራውያን ጠባቂዎቹን፣ የቤተ መንግሥት ዘቦቹንና+ የምድሪቱን ሕዝብ ሁሉ ሰበሰበ፤ እነሱም ወደ ቤተ መንግሥቱ ዘቦች በር በሚወስደው መንገድ በኩል ወደ ንጉሡ ቤት መጡ።* እሱም በነገሥታቱ ዙፋን ላይ ተቀመጠ።+ 20 በመሆኑም የምድሪቱ ሕዝብ ሁሉ እጅግ ተደሰተ፤ ጎቶልያንም በንጉሡ ቤት በሰይፍ ስለገደሏት ከተማዋ ጸጥታ ሰፈነባት።
21 ኢዮዓስ+ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ሰባት ዓመት ነበር።+
12 ኢዩ+ በነገሠ በሰባተኛው ዓመት ኢዮዓስ+ ነገሠ፤ እሱም በኢየሩሳሌም ሆኖ 40 ዓመት ገዛ። እናቱ ጺብያ የተባለች የቤርሳቤህ ተወላጅ ነበረች።+ 2 ኢዮዓስ ካህኑ ዮዳሄ ያስተምረው በነበረበት ዘመን ሁሉ በይሖዋ ፊት ትክክል የሆነውን ነገር አደረገ። 3 ይሁን እንጂ ከፍ ያሉት የማምለኪያ ቦታዎች+ አልተወገዱም፤ ደግሞም ሕዝቡ አሁንም ከፍ ባሉት የማምለኪያ ቦታዎች ላይ ይሠዋ እንዲሁም የሚጨስ መሥዋዕት ያቀርብ ነበር።
4 ኢዮዓስ ካህናቱን እንዲህ አላቸው፦ “ቅዱስ መባ+ ሆኖ ወደ ይሖዋ ቤት የሚመጣውን ገንዘብ በሙሉ ማለትም እያንዳንዱ ሰው የሚጠበቅበትን ገንዘብ፣+ አንድ ሰው* እንዲከፍል የተተመነበትን ገንዘብና እያንዳንዱ ሰው ልቡ አነሳስቶት ወደ ይሖዋ ቤት የሚያመጣውን ገንዘብ በሙሉ ውሰዱ።+ 5 ካህናቱ በግል ቀርበው ገንዘቡን ከለጋሾቻቸው* ላይ መቀበል ይችላሉ፤ ከዚያም በቤቱ ውስጥ የፈረሰውን* ሁሉ ለመጠገን ይጠቀሙበት።”+
6 ንጉሥ ኢዮዓስ በነገሠ በ23ኛው ዓመት ካህናቱ በቤቱ ውስጥ የፈረሰውን ነገር ገና አልጠገኑም ነበር።+ 7 በመሆኑም ንጉሥ ኢዮዓስ ካህኑን ዮዳሄንና+ ሌሎቹን ካህናት ጠርቶ “በቤቱ ውስጥ የፈረሰውን ነገር ያልጠገናችሁት ለምንድን ነው? ስለዚህ ገንዘቡ ቤቱን ለማደስ ሥራ ላይ እስካልዋለ ድረስ ከለጋሾች ላይ ከዚህ በላይ ገንዘብ አትቀበሉ” አላቸው።+ 8 በዚህ ጊዜ ካህናቱ ከሕዝቡ ላይ ተጨማሪ ገንዘብ ላለመቀበልና ቤቱን የማደሱን ኃላፊነት ላለመውሰድ ተስማሙ።
9 ከዚያም ካህኑ ዮዳሄ አንድ ሣጥን+ ወስዶ መክደኛው ላይ ቀዳዳ አበጀ፤ ሣጥኑንም አንድ ሰው ወደ ይሖዋ ቤት ሲገባ በስተ ቀኝ በኩል በሚያገኘው መሠዊያ አጠገብ አስቀመጠው። በር ጠባቂዎች ሆነው የሚያገለግሉት ካህናት ወደ ይሖዋ ቤት የሚመጣውን ገንዘብ በሙሉ እዚያ ይጨምሩት ነበር።+ 10 እነሱም ሣጥኑ ውስጥ ብዙ ገንዘብ መኖሩን በሚያዩበት ጊዜ ሁሉ የንጉሡ ጸሐፊና ሊቀ ካህናቱ መጥተው ይሰበስቡታል፤* ከዚያም ወደ ይሖዋ ቤት የመጣውን ገንዘብ ይቆጥሩታል።+ 11 የተቆጠረውን ገንዘብ በይሖዋ ቤት በሚከናወነው ሥራ ላይ ለተሾሙት ሰዎች ይሰጧቸዋል። እነሱ ደግሞ ገንዘቡን በይሖዋ ቤት ለሚሠሩት አናጺዎችና የግንባታ ባለሙያዎች ይከፍሉ ነበር፤+ 12 በተጨማሪም ለግንበኞችና ለድንጋይ ጠራቢዎች ይከፍሉ ነበር። ደግሞም በይሖዋ ቤት ውስጥ የፈረሰውን ለመጠገን የሚውሉ ሳንቃዎችንና ጥርብ ድንጋዮችን ለመግዛት እንዲሁም ቤቱን ለመጠገን የሚያስፈልጉትን ሌሎች ወጪዎች ለመሸፈን ያውሉት ነበር።
13 ይሁን እንጂ ወደ ይሖዋ ቤት ከገባው ገንዘብ ውስጥ ለይሖዋ ቤት የሚሆኑ የብር ገንዳዎችን፣ የእሳት ማጥፊያዎችን፣ ጎድጓዳ ሳህኖችን፣ መለከቶችን+ አሊያም ማንኛውንም ዓይነት የወርቅ ወይም የብር ዕቃ ለመሥራት የዋለ ገንዘብ አልነበረም።+ 14 ገንዘቡን የሚሰጡት ሥራውን ለሚሠሩት ሰዎች ብቻ ነበር፤ እነሱም በገንዘቡ የይሖዋን ቤት ጠገኑ። 15 ለሠራተኞቹ እንዲከፍሉ ገንዘብ በሚሰጧቸው ሰዎች ላይ ቁጥጥር አያደርጉም ነበር፤ ምክንያቱም ሰዎቹ እምነት የሚጣልባቸው ነበሩ።+ 16 ይሁን እንጂ ለበደል መባዎች+ የሚሰጠው ገንዘብና ለኃጢአት መባዎች የሚሰጠው ገንዘብ የካህናቱ ንብረት+ ስለሆነ ወደ ይሖዋ ቤት እንዲገባ አይደረግም ነበር።
17 የሶርያ ንጉሥ ሃዛኤል+ ጌትን+ ለመውጋት የወጣው በዚህ ጊዜ ነበር፤ እሱም በቁጥጥር ሥር አዋላት፤ ከዚያም በኢየሩሳሌም ላይ ጥቃት ለመሰንዘር ወሰነ።*+ 18 በዚህ ጊዜ የይሁዳ ንጉሥ ኢዮዓስ የይሁዳ ነገሥታት የነበሩት አባቶቹ ኢዮሳፍጥ፣ ኢዮራምና አካዝያስ የቀደሷቸውን ቅዱስ መባዎች ሁሉ፣ የራሱን ቅዱስ መባዎች እንዲሁም በይሖዋ ቤትና በንጉሡ ቤት* ግምጃ ቤቶች የተገኘውን ወርቅ ሁሉ ወስዶ ለሶርያ ንጉሥ ለሃዛኤል ላከለት።+ በመሆኑም ሃዛኤል ኢየሩሳሌምን ከመውጋት ተመለሰ።
19 የቀረው የኢዮዓስ ታሪክ፣ ያደረጋቸው ነገሮች በሙሉ በይሁዳ ነገሥታት ዘመን ስለተፈጸሙት ነገሮች በሚተርከው የታሪክ መጽሐፍ ውስጥ ተጽፈው ይገኙ የለም? 20 ይሁንና አገልጋዮቹ በኢዮዓስ ላይ በማሴር+ ወደ ሲላ ቁልቁል በሚወስደው መንገድ ላይ በጉብታው+ ቤት* ገደሉት። 21 ኢዮዓስን መትተው የገደሉት፣ አገልጋዮቹ የነበሩት የሺምዓት ልጅ ዮዛካር እና የሾሜር ልጅ የሆዛባድ ነበሩ።+ እነሱም በዳዊት ከተማ ከአባቶቹ ጋር ቀበሩት፤ በእሱም ምትክ ልጁ አሜስያስ ነገሠ።+
13 የይሁዳ ንጉሥ የአካዝያስ+ ልጅ ኢዮዓስ+ በነገሠ በ23ኛው ዓመት የኢዩ+ ልጅ ኢዮዓካዝ በእስራኤል ላይ ነገሠ፤ በሰማርያም ሆኖ ለ17 ዓመት ገዛ። 2 እሱም በይሖዋ ፊት መጥፎ የሆነውን ነገር አደረገ፤ እንዲሁም የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም እስራኤላውያን እንዲፈጽሙ ያደረገውን ኃጢአት መሥራቱን ቀጠለ።+ ከዚያም አልራቀም። 3 በመሆኑም የይሖዋ ቁጣ+ በእስራኤል ላይ ነደደ፤+ በዘመናቸውም ሁሉ በሶርያ ንጉሥ በሃዛኤል+ እጅና በሃዛኤል ልጅ በቤንሃዳድ+ እጅ አሳልፎ ሰጣቸው።
4 ከጊዜ በኋላ ኢዮዓካዝ የይሖዋን ሞገስ ለማግኘት ለመነ፤ ይሖዋም ሰማው፤ ምክንያቱም የሶርያ ንጉሥ በእስራኤላውያን ላይ ያደረሰውን ጭቆና አይቶ ነበር።+ 5 ስለሆነም ይሖዋ ለእስራኤላውያን ከሶርያውያን እጅ ነፃ የሚያወጣ አዳኝ ሰጣቸው፤+ እስራኤላውያንም እንደቀድሟቸው በየቤታቸው መኖር ጀመሩ።* 6 (እነሱ ግን የኢዮርብዓም ቤት እስራኤላውያን እንዲፈጽሙ ካደረገው ኃጢአት ዞር አላሉም።+ ይህን ኃጢአት መፈጸማቸውን ቀጠሉ፤* የማምለኪያ ዓምዱም*+ በሰማርያ እንደቆመ ነበር።) 7 ኢዮዓካዝ የቀረው 50 ፈረሰኞች፣ 10 ሠረገሎችና 10,000 እግረኛ ወታደሮች ብቻ ያሉት ሠራዊት ነበር፤ ምክንያቱም የሶርያ ንጉሥ በአውድማ ላይ እንዳለ እብቅ ረጋግጦ ደምስሷቸው ነበር።+
8 የቀረው የኢዮዓካዝ ታሪክ፣ ያደረጋቸው ነገሮች በሙሉና ኃያልነቱ በእስራኤል ነገሥታት ዘመን ስለተፈጸሙት ነገሮች በሚተርከው የታሪክ መጽሐፍ ውስጥ ተጽፈው ይገኙ የለም? 9 በመጨረሻም ኢዮዓካዝ ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በሰማርያም ቀበሩት፤+ ልጁም ኢዮዓስ በምትኩ ነገሠ።
10 የይሁዳ ንጉሥ ኢዮዓስ+ በነገሠ በ37ኛው ዓመት የኢዮዓካዝ ልጅ ኢዮዓስ በእስራኤል ላይ ነገሠ፤ በሰማርያም ሆኖ ለ16 ዓመት ገዛ። 11 እሱም በይሖዋ ፊት መጥፎ የሆነውን ነገር አደረገ፤ የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም እስራኤላውያን እንዲፈጽሟቸው ካደረጋቸው ኃጢአቶች ሁሉ ዞር አላለም።+ እነዚህን ኃጢአቶች መፈጸሙን* ቀጠለ።
12 የቀረው የኢዮዓስ ታሪክ፣ ያደረጋቸው ነገሮች በሙሉና ኃያልነቱ እንዲሁም ከይሁዳ ንጉሥ ከአሜስያስ ጋር እንዴት እንደተዋጋ+ በእስራኤል ነገሥታት ዘመን ስለተፈጸሙት ነገሮች በሚተርከው የታሪክ መጽሐፍ ውስጥ ተጽፈው ይገኙ የለም? 13 በመጨረሻም ኢዮዓስ ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ ኢዮርብዓምም*+ በዙፋኑ ተቀመጠ። ኢዮዓስም ከእስራኤል ነገሥታት ጋር በሰማርያ ተቀበረ።+
14 ኤልሳዕ+ ለሞት በዳረገው በሽታ ተይዞ በነበረበት ወቅት የእስራኤል ንጉሥ ኢዮዓስ ወደ እሱ ወርዶ “አባቴ፣ አባቴ! የእስራኤል ሠረገላና ፈረሰኞች!”+ በማለት ላዩ ላይ ተደፍቶ አለቀሰ። 15 ኤልሳዕም “በል ደጋንና ቀስቶች አምጣ” አለው። እሱም ደጋንና ቀስቶች አመጣ። 16 ከዚያም ኤልሳዕ የእስራኤልን ንጉሥ “ደጋኑን በእጅህ ያዝ” አለው። ንጉሡም ደጋኑን በእጁ ያዘ፤ በመቀጠልም ኤልሳዕ እጆቹን በንጉሡ እጆች ላይ ጫነ። 17 ከዚያም “በምሥራቅ በኩል ያለውን መስኮት ክፈት” አለው። እሱም ከፈተ። ኤልሳዕም “አስፈንጥር!” አለው። እሱም አስፈነጠረ። ኤልሳዕም “የይሖዋ የድል* ቀስት፤ በሶርያ ላይ የሚወነጨፍ የድል* ቀስት! ሶርያውያንን ድምጥማጣቸውን እስክታጠፋ ድረስ አፌቅ+ ላይ ትመታቸዋለህ”* አለው።
18 ኤልሳዕ በመቀጠል “ቀስቶቹን ያዝ” አለው፤ እሱም ያዘ። ከዚያም የእስራኤልን ንጉሥ “መሬቱን ውጋ” አለው። እሱም መሬቱን ሦስት ጊዜ ወግቶ አቆመ። 19 በዚህ ጊዜ የእውነተኛው አምላክ ሰው በእሱ ላይ ተቆጥቶ እንዲህ አለው፦ “መሬቱን አምስት ወይም ስድስት ጊዜ መውጋት ነበረብህ! እንደዚያ ብታደርግ ኖሮ ሶርያውያንን ሙሉ በሙሉ ድምጥማጣቸውን ታጠፋ ነበር፤ አሁን ግን ሶርያን የምትመታው ሦስት ጊዜ ብቻ ነው”+ አለው።
20 ከዚያም ኤልሳዕ ሞተ፤ ተቀበረም። በዓመቱ መጀመሪያ* ላይ ወደ ምድሪቱ ዘልቀው የሚገቡ የሞዓባውያን ወራሪ ቡድኖች+ ነበሩ። 21 የተወሰኑ ሰዎች አንድ ሰው ሊቀብሩ ሲሉ ወራሪውን ቡድን ተመለከቱ፤ ስለዚህ ሰውየውን ኤልሳዕ የተቀበረበት ቦታ ውስጥ ወርውረው እየሮጡ ሄዱ። ሰውየውም የኤልሳዕን አፅም በነካ ጊዜ ሕያው ሆነ፤+ በእግሩም ቆመ።
22 የሶርያ ንጉሥ ሃዛኤል+ በኢዮዓካዝ ዘመን ሁሉ እስራኤልን ይጨቁን ነበር።+ 23 ሆኖም ይሖዋ ከአብርሃም፣+ ከይስሐቅና+ ከያዕቆብ+ ጋር ስለገባው ቃል ኪዳን ሲል ሞገስና አሳቢነት አሳያቸው፤ ምሕረትም አደረገላቸው።+ ሊያጠፋቸው አልፈለገም፤ እስከ ዛሬም ድረስ ከፊቱ አላስወገዳቸውም። 24 የሶርያ ንጉሥ ሃዛኤል በሞተ ጊዜ ልጁ ቤንሃዳድ በእሱ ምትክ ነገሠ። 25 ከዚያም የኢዮዓካዝ ልጅ ኢዮዓስ፣ ሃዛኤል ከአባቱ ከኢዮዓካዝ ላይ በጦርነት የወሰዳቸውን ከተሞች ከሃዛኤል ልጅ ከቤንሃዳድ አስመለሰ። ኢዮዓስ ሦስት ጊዜ መታው፤*+ የእስራኤልንም ከተሞች መልሶ ያዘ።
14 የእስራኤል ንጉሥ የኢዮዓካዝ ልጅ ኢዮዓስ+ በነገሠ በሁለተኛው ዓመት የይሁዳ ንጉሥ የኢዮዓስ ልጅ አሜስያስ ነገሠ። 2 አሜስያስ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው 25 ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌምም ሆኖ ለ29 ዓመት ገዛ። እናቱ የሆዓዲን የተባለች የኢየሩሳሌም ተወላጅ ነበረች።+ 3 እሱም እንደ አባቱ እንደ ዳዊት ባይሆንም በይሖዋ ፊት ትክክል የሆነውን ነገር ፈጸመ።+ ሁሉንም ነገር አባቱ ኢዮዓስ እንዳደረገው አደረገ።+ 4 ሆኖም ከፍ ያሉት የማምለኪያ ቦታዎች አልተወገዱም ነበር፤+ ሕዝቡ አሁንም ከፍ ባሉት የማምለኪያ ቦታዎች ላይ ይሠዋ እንዲሁም የሚጨስ መሥዋዕት ያቀርብ ነበር።+ 5 እሱም መንግሥቱ በእጁ እንደጸናለት፣ ንጉሥ የነበረውን አባቱን የገደሉትን አገልጋዮቹን+ ገደላቸው። 6 ይሁንና “አባቶች በልጆቻቸው ኃጢአት መገደል የለባቸውም፤ ልጆችም በአባቶቻቸው ኃጢአት መገደል የለባቸውም፤ ይልቁንም እያንዳንዱ ሰው በገዛ ኃጢአቱ ይገደል”+ በሚለው በሙሴ የሕግ መጽሐፍ ላይ በተጻፈው የይሖዋ ትእዛዝ መሠረት የገዳዮቹን ልጆች አልገደላቸውም። 7 እሱም 10,000 ኤዶማውያንን+ በጨው ሸለቆ+ መታ፤ ተዋግቶም ሴላን በቁጥጥሩ ሥር አደረገ፤+ እሷም እስከ ዛሬ ድረስ ዮቅተኤል ተብላ ትጠራለች።
8 ከዚያም አሜስያስ የእስራኤል ንጉሥ ወደሆነው ወደ ኢዩ ልጅ ወደ ኢዮዓካዝ ልጅ ወደ ኢዮዓስ “ና፤ ውጊያ እንግጠም”* በማለት መልእክተኞች ላከ።+ 9 የእስራኤል ንጉሥ ኢዮዓስ ደግሞ ወደ ይሁዳ ንጉሥ ወደ አሜስያስ ይህን መልእክት ላከ፦ “በሊባኖስ የሚገኘው ኩርንችት በሊባኖስ ወደሚገኘው አርዘ ሊባኖስ ‘ሴት ልጅህን ለወንድ ልጄ ዳርለት’ የሚል መልእክት ላከ። ይሁን እንጂ በሊባኖስ የነበረ አንድ የዱር አውሬ በዚያ ሲያልፍ ያን ኩርንችት ረገጠው። 10 እርግጥ ኤዶምን መተሃል፤+ በመሆኑም ልብህ ታብዮአል። ክብርህን ጠብቀህ አርፈህ ቤትህ* ተቀመጥ። በራስህ ላይ ለምን ጥፋት ትጋብዛለህ? ደግሞስ ራስህንም ሆነ ይሁዳን ለምን ለውድቀት ትዳርጋለህ?” 11 አሜስያስ ግን አልሰማም።+
በመሆኑም የእስራኤል ንጉሥ ኢዮዓስ ወጣ፤ እሱና የይሁዳ ንጉሥ አሜስያስም በይሁዳ በምትገኘው በቤትሼሜሽ+ ተጋጠሙ።+ 12 ይሁዳ በእስራኤል ድል ተመታ፤ እያንዳንዳቸውም ወደየቤታቸው* ሸሹ። 13 የእስራኤል ንጉሥ ኢዮዓስ የአካዝያስ ልጅ፣ የኢዮዓስ ልጅ የሆነውን የይሁዳን ንጉሥ አሜስያስን ቤትሼሜሽ ላይ ያዘው። ከዚያም ወደ ኢየሩሳሌም መጡ፤ እሱም የኢየሩሳሌምን ቅጥር፣ ከኤፍሬም በር+ አንስቶ እስከ ማዕዘን በር+ ድረስ አፈረሰ፤ ርዝመቱም 400 ክንድ* ያህል ነበር። 14 በይሖዋ ቤትና በንጉሡ ቤት* ግምጃ ቤቶች የተገኘውን ወርቅ፣ ብርና ዕቃ ሁሉ እንዲሁም የታገቱትን ሰዎች ወሰደ። ከዚያም ወደ ሰማርያ ተመለሰ።
15 የቀረው የኢዮዓስ ታሪክ፣ ያደረጋቸው ነገሮችና ኃያልነቱ እንዲሁም ከይሁዳ ንጉሥ ከአሜስያስ ጋር እንዴት እንደተዋጋ በእስራኤል ነገሥታት ዘመን ስለተፈጸሙት ነገሮች በሚተርከው የታሪክ መጽሐፍ ውስጥ ተጽፈው ይገኙ የለም? 16 በመጨረሻም ኢዮዓስ ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ ከእስራኤልም ነገሥታት ጋር በሰማርያ ተቀበረ፤+ ልጁም ኢዮርብዓም*+ በእሱ ምትክ ነገሠ።
17 የእስራኤል ንጉሥ የኢዮዓካዝ ልጅ ኢዮዓስ+ ከሞተ በኋላ፣ የይሁዳ ንጉሥ የኢዮዓስ ልጅ አሜስያስ+ 15 ዓመት ኖረ።+ 18 የቀረው የአሜስያስ ታሪክ በይሁዳ ነገሥታት ዘመን ስለተፈጸሙት ነገሮች በሚተርከው የታሪክ መጽሐፍ ውስጥ ተጽፎ ይገኝ የለም? 19 ከጊዜ በኋላ ኢየሩሳሌም ውስጥ በእሱ ላይ ሴራ ተጠነሰሰ፤+ እሱም ወደ ለኪሶ ሸሸ፤ እነሱ ግን ተከታትለው እንዲይዙት ሰዎችን ወደ ለኪሶ ላኩ፤ በዚያም ገደሉት። 20 ከዚያም በፈረሶች ላይ ጭነው አመጡት፤ እሱም በዳዊት ከተማ ከአባቶቹ ጋር በኢየሩሳሌም ተቀበረ።+ 21 ከዚያም የይሁዳ ሕዝብ ሁሉ በወቅቱ የ16 ዓመት+ ልጅ የነበረውን አዛርያስን*+ ወስደው በአባቱ በአሜስያስ ምትክ አነገሡት።+ 22 እሱም፣ ንጉሡ* ከአባቶቹ ጋር ካንቀላፋ በኋላ ኤላትን+ መልሶ በመገንባት ወደ ይሁዳ መለሳት።+
23 የይሁዳ ንጉሥ የኢዮዓስ ልጅ አሜስያስ በነገሠ በ15ኛው ዓመት የእስራኤል ንጉሥ የኢዮዓስ ልጅ ኢዮርብዓም+ በሰማርያ ነገሠ፤ እሱም 41 ዓመት ገዛ። 24 በይሖዋ ፊት መጥፎ የሆነውን ነገር አደረገ። የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም እስራኤላውያን እንዲፈጽሙ ካደረጋቸው ኃጢአት ሁሉ ዞር አላለም።+ 25 የእስራኤል አምላክ ይሖዋ የጋትሔፌር+ ነቢይ በሆነው በአሚታይ ልጅ፣ በአገልጋዩ በዮናስ+ አማካኝነት በተናገረው ቃል መሠረት ከሌቦሃማት*+ አንስቶ እስከ አረባ ባሕር*+ ድረስ ያለውን የእስራኤልን ወሰን አስመለሰ። 26 ይሖዋ በእስራኤል ላይ እየደረሰ ያለውን ከባድ ሥቃይ ተመልክቶ ነበርና።+ በዚያም እስራኤልን ሌላው ቀርቶ ምስኪኑንና ደካማውን የሚረዳ አልነበረም። 27 ሆኖም ይሖዋ የእስራኤልን ስም ከሰማይ በታች ጠራርጎ እንደማያጠፋ ቃል ገብቶ ነበር።+ በመሆኑም በኢዮዓስ ልጅ በኢዮርብዓም አማካኝነት አዳናቸው።+
28 የቀረው የኢዮርብዓም ታሪክ፣ ያደረጋቸው ነገሮች ሁሉና ኃያልነቱ እንዲሁም እንዴት እንደተዋጋ ብሎም ደማስቆንና ሃማትን+ ለይሁዳና ለእስራኤል እንዴት እንዳስመለሰ+ በእስራኤል ነገሥታት ዘመን ስለተፈጸሙት ነገሮች በሚተርከው የታሪክ መጽሐፍ ውስጥ ተጽፈው ይገኙ የለም? 29 በመጨረሻም ኢዮርብዓም ከአባቶቹ ከእስራኤል ነገሥታት ጋር አንቀላፋ፤ ልጁም ዘካርያስ+ በእሱ ምትክ ነገሠ።
15 የእስራኤል ንጉሥ ኢዮርብዓም* በነገሠ በ27ኛው ዓመት የይሁዳ ንጉሥ የአሜስያስ+ ልጅ አዛርያስ*+ ነገሠ።+ 2 እሱም በነገሠ ጊዜ ዕድሜው 16 ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌምም ሆኖ ለ52 ዓመት ገዛ። እናቱ ይኮልያ የተባለች የኢየሩሳሌም ተወላጅ ነበረች። 3 እሱም አባቱ አሜስያስ እንዳደረገው ሁሉ በይሖዋ ፊት ትክክል የሆነውን ነገር አደረገ።+ 4 ሆኖም ከፍ ያሉት የማምለኪያ ቦታዎች አልተወገዱም ነበር፤+ ሕዝቡ አሁንም ከፍ ባሉት የማምለኪያ ቦታዎች ላይ ይሠዋ እንዲሁም የሚጨስ መሥዋዕት ያቀርብ ነበር።+ 5 ይሖዋ ንጉሡን ቀሰፈው፤ እስከ ዕለተ ሞቱም ድረስ የሥጋ ደዌ+ በሽተኛ ሆኖ ኖረ፤ በአንድ የተለየ ቤትም ውስጥ ተገልሎ ተቀመጠ፤+ በዚህ ጊዜ የንጉሡ ልጅ ኢዮዓታም+ በቤቱ* ላይ ተሹሞ በምድሪቱ በሚኖረው ሕዝብ ላይ ይፈርድ ነበር።+ 6 የቀረው የአዛርያስ ታሪክ፣+ ያደረጋቸው ነገሮች በሙሉ በይሁዳ ነገሥታት ዘመን ስለተፈጸሙት ነገሮች በሚተርከው የታሪክ መጽሐፍ ውስጥ ተጽፈው ይገኙ የለም? 7 በመጨረሻም አዛርያስ ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤+ እነሱም በዳዊት ከተማ ከአባቶቹ ጋር ቀበሩት፤ በእሱም ምትክ ልጁ ኢዮዓታም ነገሠ።
8 የይሁዳ ንጉሥ አዛርያስ+ በነገሠ በ38ኛው ዓመት የኢዮርብዓም ልጅ ዘካርያስ+ በሰማርያ፣ በእስራኤል ላይ ነገሠ፤ ለስድስት ወርም ገዛ። 9 አባቶቹ እንዳደረጉት በይሖዋ ፊት መጥፎ የሆነውን ነገር አደረገ። የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም እስራኤላውያን እንዲፈጽሟቸው ካደረጋቸው ኃጢአቶች ዞር አላለም።+ 10 ከዚያም የኢያቢስ ልጅ ሻሉም በእሱ ላይ በማሴር ይብለአም+ ላይ መትቶ ገደለው።+ ከገደለው በኋላ በእሱ ምትክ ነገሠ። 11 የቀረው የዘካርያስ ታሪክ በእስራኤል ነገሥታት ዘመን ስለተፈጸሙት ነገሮች በሚተርከው የታሪክ መጽሐፍ ውስጥ ተጽፏል። 12 ይህም ይሖዋ ለኢዩ “ልጆችህ+ እስከ አራተኛ ትውልድ ድረስ በእስራኤል ዙፋን ላይ ይቀመጣሉ” በማለት የተናገረው ቃል ፍጻሜ ነው።+ የሆነውም ልክ እንደዚሁ ነው።
13 የይሁዳ ንጉሥ ዖዝያ+ በነገሠ በ39ኛው ዓመት የኢያቢስ ልጅ ሻሉም ነገሠ፤ እሱም በሰማርያ ሆኖ ድፍን አንድ ወር ገዛ። 14 ከዚያም የጋዲ ልጅ መናሄም ከቲርጻ+ ወደ ሰማርያ መጥቶ የኢያቢስን ልጅ ሻሉምን ሰማርያ ላይ መትቶ ገደለው።+ ከገደለውም በኋላ በእሱ ምትክ ነገሠ። 15 የቀረው የሻሉም ታሪክና የጠነሰሰው ሴራ በእስራኤል ነገሥታት ዘመን ስለተፈጸሙት ነገሮች በሚተርከው የታሪክ መጽሐፍ ውስጥ ተጽፏል። 16 በዚያን ጊዜ መናሄም ከቲርጻ ወጥቶ ቲፍሳን እንዲሁም በውስጧና በዙሪያዋ የነበሩትን ሁሉ መታ፤ ይህን ያደረገው በሮቿን ለእሱ ለመክፈት ፈቃደኛ ባለመሆኗ ነው። እሱም ቲፍሳን መታት፤ የነፍሰ ጡሮቿንም ሆድ ቀደደ።
17 የይሁዳ ንጉሥ አዛርያስ በነገሠ በ39ኛው ዓመት የጋዲ ልጅ መናሄም በእስራኤል ላይ ነገሠ፤ በሰማርያም ሆኖ ለአሥር ዓመት ገዛ። 18 እሱም በይሖዋ ፊት መጥፎ የሆነውን ነገር አደረገ። በዘመኑም ሁሉ፣ የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም እስራኤላውያን እንዲፈጽሟቸው ካደረጋቸው ኃጢአቶች ዞር አላለም።+ 19 በዚህ ጊዜ የአሦር ንጉሥ ፑል+ ወደ ምድሩ መጣ፤ መናሄምም መንግሥቱን ለማጽናት ድጋፍ እንዲሰጠው ለፑል 1,000 የብር ታላንት* ሰጠው።+ 20 መናሄም ብሩን ያገኘው ከእስራኤላውያን ይኸውም ስመ ጥርና ሀብታም የሆኑ ሰዎች እንዲያዋጡ በማስገደድ ነው።+ በእያንዳንዱ ሰው 50 የብር ሰቅል* አስቦ ለአሦር ንጉሥ ሰጠው። ከዚያም የአሦር ንጉሥ ተመልሶ ሄደ፤ በምድሪቱም አልቆየም። 21 የቀረው የመናሄም+ታሪክ፣ ያደረጋቸው ነገሮች በሙሉ በእስራኤል ነገሥታት ዘመን ስለተፈጸሙት ነገሮች በሚተርከው የታሪክ መጽሐፍ ውስጥ ተጽፈው ይገኙ የለም? 22 በመጨረሻም መናሄም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ ልጁም ፈቃህያህ በእሱ ምትክ ነገሠ።
23 የይሁዳ ንጉሥ አዛርያስ በነገሠ በ50ኛው ዓመት የመናሄም ልጅ ፈቃህያህ በሰማርያ፣ በእስራኤል ላይ ነገሠ፤ ለሁለት ዓመትም ገዛ። 24 እሱም በይሖዋ ፊት መጥፎ የሆነውን ነገር አደረገ። የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም እስራኤላውያን እንዲፈጽሟቸው ካደረጋቸው ኃጢአቶች ዞር አላለም።+ 25 ከዚያም የረማልያህ ልጅ የሆነው የጦር መኮንኑ ፋቁሄ+ ከአርጎብ እና ከአርያ ጋር በማበር በእሱ ላይ አሴረ፤ በሰማርያ፣ በንጉሡ ቤት* በሚገኘው የማይደፈር ማማ ላይ ሳለም መትቶ ገደለው። ከእሱ ጋር 50 የጊልያድ ሰዎች ነበሩ፤ እሱን ከገደለ በኋላም በምትኩ ነገሠ። 26 የቀረው የፈቃህያህ ታሪክ፣ ያደረጋቸው ነገሮች በሙሉ በእስራኤል ነገሥታት ዘመን ስለተፈጸሙት ነገሮች በሚተርከው የታሪክ መጽሐፍ ውስጥ ተጽፈዋል።
27 የይሁዳ ንጉሥ አዛርያስ በነገሠ በ52ኛው ዓመት የረማልያህ ልጅ ፋቁሄ+ በሰማርያ፣ በእስራኤል ላይ ነገሠ፤ ለ20 ዓመትም ገዛ። 28 እሱም በይሖዋ ፊት መጥፎ የሆነውን ነገር አደረገ፤ የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም እስራኤላውያን እንዲፈጽሟቸው ካደረጋቸው ኃጢአቶች ዞር አላለም።+ 29 በእስራኤል ንጉሥ በፋቁሄ ዘመን የአሦር ንጉሥ ቴልጌልቴልፌልሶር+ ወረራ በማካሄድ ኢዮንን፣ አቤልቤትማዓካን፣+ ያኖአህን፣ ቃዴሽን፣+ ሃጾርን፣ ጊልያድን+ እንዲሁም ገሊላን ይኸውም መላውን የንፍታሌም+ ምድር ያዘ፤ ነዋሪዎቹንም በግዞት ወደ አሦር ወሰደ።+ 30 በመጨረሻም የኤላህ ልጅ ሆሺአ+ በረማልያህ ልጅ በፋቁሄ ላይ በማሴር መትቶ ገደለው፤ እሱም የዖዝያ ልጅ ኢዮዓታም+ በነገሠ በ20ኛው ዓመት በፋቁሄ ምትክ ነገሠ። 31 የቀረው የፋቁሄ ታሪክ፣ ያደረጋቸው ነገሮች በሙሉ በእስራኤል ነገሥታት ዘመን ስለተፈጸሙት ነገሮች በሚተርከው የታሪክ መጽሐፍ ውስጥ ተጽፈዋል።
32 የእስራኤል ንጉሥ የረማልያህ ልጅ ፋቁሄ በነገሠ በሁለተኛው ዓመት የይሁዳ ንጉሥ የዖዝያ+ ልጅ ኢዮዓታም+ ነገሠ። 33 እሱም በነገሠ ጊዜ ዕድሜው 25 ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌምም ሆኖ ለ16 ዓመት ገዛ። እናቱም የሩሻ ትባል ነበር፤ እሷም የሳዶቅ ልጅ ነበረች።+ 34 እሱም አባቱ ዖዝያ እንዳደረገው ሁሉ በይሖዋ ፊት ትክክል የሆነውን ነገር አደረገ።+ 35 ሆኖም ከፍ ያሉት የማምለኪያ ቦታዎች አልተወገዱም ነበር፤ ሕዝቡ አሁንም ከፍ ባሉት የማምለኪያ ቦታዎች ላይ ይሠዋ እንዲሁም የሚጨስ መሥዋዕት ያቀርብ ነበር።+ የይሖዋን ቤት የላይኛውን በር የሠራው እሱ ነበር።+ 36 የቀረው የኢዮዓታም ታሪክና ያደረጋቸው ነገሮች በይሁዳ ነገሥታት ዘመን ስለተፈጸሙት ነገሮች በሚተርከው የታሪክ መጽሐፍ ውስጥ ተጽፈው ይገኙ የለም? 37 በዚያ ዘመን ይሖዋ በይሁዳ ላይ የሶርያን ንጉሥ ረጺንን እና የረማልያህን ልጅ ፋቁሄን+ ላከ።+ 38 በመጨረሻም ኢዮዓታም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በአባቱ በዳዊት ከተማም ከአባቶቹ ጋር ተቀበረ። በእሱም ምትክ ልጁ አካዝ ነገሠ።
16 የረማልያህ ልጅ ፋቁሄ በነገሠ በ17ኛው ዓመት የይሁዳ ንጉሥ የኢዮዓታም ልጅ አካዝ+ ነገሠ። 2 አካዝ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው 20 ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌምም ሆኖ ለ16 ዓመት ገዛ። አባቱ ዳዊት እንዳደረገው በአምላኩ በይሖዋ ፊት ትክክል የሆነውን ነገር አላደረገም።+ 3 ከዚህ ይልቅ የእስራኤልን ነገሥታት መንገድ ተከተለ፤+ ይሖዋ ከእስራኤላውያን ፊት ያባረራቸው ብሔራት ይፈጽሙ የነበረውን አስጸያፊ ድርጊት በመከተል+ የገዛ ልጁን እንኳ ሳይቀር ለእሳት አሳልፎ ሰጠ።+ 4 ደግሞም ከፍ ባሉት የማምለኪያ ቦታዎች፣+ በኮረብቶቹና በእያንዳንዱ የለመለመ ዛፍ ሥር+ ይሠዋ እንዲሁም የሚጨስ መሥዋዕት ያቀርብ ነበር።
5 የሶርያ ንጉሥ ረጺንና የእስራኤል ንጉሥ የሆነው የረማልያህ ልጅ ፋቁሄ ኢየሩሳሌምን ሊወጉ የመጡት በዚህ ጊዜ ነበር።+ አካዝንም ከበቡት፤ ሆኖም ከተማዋን መያዝ አልቻሉም። 6 በዚህ ጊዜ የሶርያ ንጉሥ ረጺን አይሁዳውያንን* ከኤላት+ ካባረረ በኋላ ኤላትን ለኤዶም መለሰ። ኤዶማውያንም ወደ ኤላት ገቡ፤ እስከ ዛሬም ድረስ በዚያ ይኖራሉ። 7 በመሆኑም አካዝ ወደ አሦር ንጉሥ ወደ ቴልጌልቴልፌልሶር+ መልእክተኞች ልኮ “እኔ አገልጋይህና ልጅህ ነኝ። መጥተህ በእኔ ላይ ጥቃት ከሚሰነዝሩት ከሶርያ ንጉሥ እጅና ከእስራኤል ንጉሥ እጅ አድነኝ” አለው። 8 ከዚያም አካዝ በይሖዋ ቤትና በንጉሡ ቤት* ግምጃ ቤቶች ያለውን ብርና ወርቅ በመውሰድ ለአሦር ንጉሥ ጉቦ ሰጠ።+ 9 የአሦርም ንጉሥ ልመናውን በመስማት ወደ ደማስቆ ወጥቶ ከተማዋን ያዛት፤ ሕዝቧንም ወደ ቂር በግዞት ወሰደ፤+ ረጺንንም ገደለው።+
10 ከዚያም ንጉሥ አካዝ የአሦርን ንጉሥ ቴልጌልቴልፌልሶርን ለማግኘት ወደ ደማስቆ ሄደ። በደማስቆ የነበረውን መሠዊያ ባየ ጊዜ ንጉሥ አካዝ የመሠዊያውን ንድፍና እንዴት እንደተሠራ የሚያሳይ መግለጫ ለካህኑ ለዑሪያህ ላከለት።+ 11 ካህኑ ዑሪያህ+ ንጉሥ አካዝ ከደማስቆ በላከለት መመሪያ መሠረት መሠዊያውን ሠራ።+ ካህኑ ዑሪያህ ንጉሥ አካዝ ከደማስቆ ከመመለሱ በፊት ሠርቶ አጠናቀቀ። 12 ንጉሡ ከደማስቆ በተመለሰ ጊዜ መሠዊያውን አየው፤ ወደ መሠዊያውም ቀርቦ በላዩ ላይ መባ አቀረበ።+ 13 እንዲሁም በመሠዊያው ላይ የሚቃጠል መባውና የእህል መባው እንዲጨስ አደረገ፤ የመጠጥ መባውንም አፈሰሰ፤ የኅብረት መሥዋዕቶቹንም ደም ረጨ። 14 ከዚያም በይሖዋ ፊት የነበረውን የመዳብ መሠዊያ+ ከቤቱ ፊት ለፊት ከነበረበት ቦታ ይኸውም እሱ ከሠራው መሠዊያና ከይሖዋ ቤት መሃል አንስቶ ከእሱ መሠዊያ በስተ ሰሜን አስቀመጠው። 15 ንጉሥ አካዝም ካህኑን ዑሪያህን+ እንዲህ ሲል አዘዘው፦ “ጠዋት ላይ የሚቀርበውን የሚቃጠል መባ፣ ማታ ላይ የሚቀርበውን የእህል መባ፣+ የንጉሡን የሚቃጠል መባና የእህል መባ እንዲሁም የሕዝቡን ሁሉ የሚቃጠል መባ፣ የእህል መባና የመጠጥ መባ በታላቁ መሠዊያ ላይ አቅርብ።+ በተጨማሪም የሚቃጠለውን መባ ደም ሁሉና የሌሎቹን መሥዋዕቶች ደም ሁሉ በመሠዊያው ላይ እርጭ። የመዳቡን መሠዊያ በተመለከተ ግን ምን እንደማደርግ እወስናለሁ።” 16 ካህኑ ዑሪያህም ንጉሥ አካዝ ያዘዘውን ሁሉ አደረገ።+
17 በተጨማሪም ንጉሥ አካዝ የዕቃ ማጓጓዣ ጋሪዎቹን+ የጎን መከለያዎች ቆራረጠ፤ የውኃ ገንዳዎቹንም ከላያቸው ላይ አነሳ፤+ ባሕሩንም ከተቀመጠበት የመዳብ በሬዎች+ ላይ አውርዶ በድንጋይ ንጣፍ ላይ አስቀመጠው።+ 18 እንዲሁም በይሖዋ ቤት ውስጥ ሠርተውት የነበረውን ለሰንበት ቀን የሚያገለግለውን መጠለያና በውጭ ያለውን የንጉሡን መግቢያ በአሦር ንጉሥ የተነሳ ወደ ሌላ ቦታ ወሰደው።
19 የቀረው የአካዝ ታሪክ፣ ያደረጋቸው ነገሮች በይሁዳ ነገሥታት ዘመን ስለተፈጸሙት ነገሮች በሚተርከው የታሪክ መጽሐፍ ውስጥ ተጽፈው ይገኙ የለም?+ 20 በመጨረሻም አካዝ ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በዳዊት ከተማም ከአባቶቹ ጋር ተቀበረ፤ በእሱም ምትክ ልጁ ሕዝቅያስ*+ ነገሠ።
17 የይሁዳ ንጉሥ አካዝ በነገሠ በ12ኛው ዓመት የኤላህ ልጅ ሆሺአ+ በሰማርያ ሆኖ በእስራኤል ላይ ነገሠ፤ እሱም ለዘጠኝ ዓመት ገዛ። 2 ከእሱ በፊት የነበሩትን የእስራኤል ነገሥታት ያህል አይሁን እንጂ በይሖዋ ፊት መጥፎ የሆነውን ነገር አደረገ። 3 የአሦር ንጉሥ ሰልምናሶር በእሱ ላይ መጣ፤+ ሆሺአም አገልጋዩ ሆነ፤ ገበረለትም።+ 4 ሆኖም የአሦር ንጉሥ ሰልምናሶር ሆሺአ እንዳሴረበት አወቀ፤ ምክንያቱም ሆሺአ ወደ ግብፅ ንጉሥ ወደ ሶህ መልእክተኞች ልኮ ነበር፤+ ደግሞም ቀደም ባሉት ዓመታት ያደርግ እንደነበረው ለአሦር ንጉሥ መገበሩን አቁሞ ነበር። ስለሆነም የአሦር ንጉሥ እስር ቤት ውስጥ አስሮ አስቀመጠው።
5 የአሦር ንጉሥ መላ አገሪቱን ወረረ፤ ወደ ሰማርያም መጥቶ ከተማዋን ለሦስት ዓመት ከበባት። 6 ሆሺአ በነገሠ በዘጠነኛው ዓመት የአሦር ንጉሥ ሰማርያን ያዘ።+ ከዚያም የእስራኤልን ሕዝብ ወደ አሦር በግዞት+ በመውሰድ በሃላህ፣ በጎዛን+ ወንዝ አጠገብ በምትገኘው በሃቦርና በሜዶናውያን ከተሞች አሰፈራቸው።+
7 ይህ የሆነው የእስራኤል ሰዎች ከግብፅ ንጉሥ ከፈርዖን ቀንበርና ከግብፅ ምድር ነፃ ባወጣቸው በአምላካቸው በይሖዋ ላይ ኃጢአት ስለሠሩ ነው።+ እነሱም ሌሎች አማልክትን አመለኩ፤*+ 8 ይሖዋ ከእስራኤላውያን ፊት ያባረራቸውን ብሔራት ልማዶች ተከተሉ፤ ደግሞም የእስራኤል ነገሥታት ያቋቋሟቸውን ልማዶች ተከተሉ።
9 እስራኤላውያን በአምላካቸው በይሖዋ ፊት ትክክል ያልሆኑ ነገሮችን ያደርጉ ነበር። ከመጠበቂያው ግንብ አንስቶ እስከተመሸገው ከተማ ድረስ በሁሉም ከተሞቻቸው* ከፍ ያሉ የማምለኪያ ቦታዎችን ሠሩ።+ 10 በእያንዳንዱ ኮረብታ ላይና በእያንዳንዱ የለመለመ ዛፍ ሥር+ የማምለኪያ ዓምዶችንና የማምለኪያ ግንዶችን*+ ለራሳቸው አቆሙ፤ 11 ይሖዋ ከፊታቸው አሳዶ በግዞት እንዲወሰዱ ያደረጋቸው ብሔራት ያደርጉ እንደነበረው ከፍ ባሉት የማምለኪያ ቦታዎች ሁሉ የሚጨስ መሥዋዕት ያቀርቡ ነበር።+ ይሖዋን ለማስቆጣት ክፉ ነገሮችን ማድረጋቸውን ቀጠሉ።
12 ይሖዋ “አታድርጉ!”+ ያላቸውን ነገር በማድረግ አስጸያፊ የሆኑ ጣዖቶችን* አገለገሉ፤+ 13 ይሖዋ በነቢያቱ ሁሉና በእያንዳንዱ ባለ ራእይ+ አማካኝነት እስራኤልንና ይሁዳን “ከክፉ መንገዳችሁ ተመለሱ!+ አባቶቻችሁን ባዘዝኳቸውና በአገልጋዮቼ በነቢያት በኩል ለእናንተ በሰጠሁት ሕግ መሠረት ትእዛዛቴንና ደንቦቼን ጠብቁ” በማለት በተደጋጋሚ ያስጠነቅቃቸው ነበር። 14 እነሱ ግን አልሰሙም፤ በአምላካቸው በይሖዋ እንዳላመኑት አባቶቻቸው እነሱም ግትሮች ሆኑ።*+ 15 ሥርዓቶቹን፣ ከአባቶቻቸው ጋር የገባውን ቃል ኪዳንና+ እነሱን ለማስጠንቀቅ የሰጣቸውን ማሳሰቢያዎች ችላ አሉ፤+ ደግሞም ይሖዋ የእነሱን ምሳሌ እንዳይከተሉ ያዘዛቸውን+ በዙሪያቸው ያሉትን ብሔራት በመምሰል ከንቱ ጣዖቶችን ተከተሉ፤+ እነሱ ራሳቸውም ከንቱ ሆኑ።+
16 የአምላካቸውን የይሖዋን ትእዛዛት በሙሉ ተዉ፤ ለራሳቸውም ከብረት የተሠሩ ሁለት የጥጃ ሐውልቶችን* አበጁ፤+ የማምለኪያም ግንድ*+ ሠሩ፤ ለሰማያት ሠራዊት ሁሉ ሰገዱ፤+ እንዲሁም ባአልን አገለገሉ።+ 17 ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውንም ለእሳት አሳልፈው ሰጡ፤+ ሟርተኞችና ጠንቋዮች ሆኑ፤+ ይሖዋንም ያስቆጡት ዘንድ በእሱ ፊት መጥፎ የሆነውን ነገር ለማድረግ ራሳቸውን ሰጡ።*
18 በመሆኑም ይሖዋ በእስራኤል ላይ እጅግ ተቆጣ፤ ስለሆነም ከፊቱ አስወገዳቸው።+ ከይሁዳ ነገድ ሌላ ማንንም አላስቀረም።
19 የይሁዳም ሰዎች ቢሆኑ የአምላካቸውን የይሖዋን ትእዛዛት አልጠበቁም፤+ እነሱም እስራኤላውያን በተከተሏቸው ልማዶች ተመላለሱ።+ 20 ይሖዋም የእስራኤልን ዘሮች ሁሉ ተወ፤ ከፊቱም እስኪያስወግዳቸው ድረስ አዋረዳቸው፤ ለሚበዘብዟቸውም ሰዎች አሳልፎ ሰጣቸው። 21 እስራኤልን ከዳዊት ቤት ለየ፤ እነሱም የናባጥን ልጅ ኢዮርብዓምን አነገሡት።+ ሆኖም ኢዮርብዓም እስራኤላውያን ይሖዋን ከመከተል ዞር እንዲሉና ከባድ ኃጢአት እንዲሠሩ አደረገ። 22 የእስራኤልም ሰዎች ኢዮርብዓም የፈጸማቸውን ኃጢአቶች ሁሉ ሠሩ።+ ከዚያ ዞር አላሉም፤ 23 ይህም የሆነው ይሖዋ በአገልጋዮቹ በነቢያት ሁሉ አማካኝነት በተናገረው መሠረት እስራኤልን ከፊቱ እስኪያስወግድ ድረስ ነው።+ በመሆኑም እስራኤላውያን ከገዛ ምድራቸው ወደ አሦር በግዞት ተወሰዱ፤+ እስከ ዛሬም ድረስ በዚያ ይገኛሉ።
24 የአሦርም ንጉሥ ሰዎችን ከባቢሎን፣ ከኩታ፣ ከአዋ፣ ከሃማትና ከሰፋርዊም+ አምጥቶ በእስራኤላውያን ምትክ በሰማርያ ከተሞች አሰፈራቸው፤ እነሱም ሰማርያን ወርሰው በከተሞቿ መኖር ጀመሩ። 25 በዚያ መኖር እንደጀመሩ አካባቢ ይሖዋን አይፈሩም* ነበር። በመሆኑም ይሖዋ በመካከላቸው አንበሶችን ላከባቸው፤+ እነሱም የተወሰኑ ሰዎችን ገደሉ። 26 የአሦርም ንጉሥ እንዲህ ተብሎ ተነገረው፦ “በግዞት ወስደህ በሰማርያ ከተሞች እንዲሰፍሩ ያደረግካቸው ብሔራት የዚያች ምድር አምላክ እንዴት እንደሚመለክ* አላወቁም። ስለዚህ በመካከላቸው አንበሶችን ላከባቸው፤ አንዳቸውም የዚያች ምድር አምላክ እንዴት እንደሚመለክ ስለማያውቁ አንበሶቹ እየገደሏቸው ነው።”
27 በዚህ ጊዜ የአሦር ንጉሥ “ከዚያ በግዞት ከወሰዳችኋቸው ካህናት መካከል አንዱ ተመልሶ አብሯቸው በመኖር የዚያች ምድር አምላክ እንዴት እንደሚመለክ ያስተምራቸው” ሲል አዘዘ። 28 ስለሆነም ከሰማርያ በግዞት ከወሰዷቸው ካህናት መካከል አንዱ ተመልሶ በመምጣት በቤቴል+ መኖር ጀመረ፤ እሱም ይሖዋን እንዴት መፍራት* እንዳለባቸው ያስተምራቸው ጀመር።+
29 ይሁንና እያንዳንዱ ብሔር የየራሱን አምላክ* በመሥራት ሳምራውያን ከፍ ባሉት የማምለኪያ ቦታዎች ላይ በሠሯቸው ቤቶች ውስጥ አስቀምጦ ነበር፤ እያንዳንዱ ብሔር በሚኖርባቸው ከተሞች ውስጥ እንዲህ አደረገ። 30 በመሆኑም የባቢሎን ሰዎች ሱኮትቤኖትን፣ የኩት ሰዎች ኔርጋልን፣ የሃማት+ ሰዎች ደግሞ አሺማን ሠሩ፤ 31 አዋውያንም ኒብሃዝን እና ታርታቅን ሠሩ። ሰፋርዊማውያን+ ደግሞ አድራሜሌክና አናሜሌክ ለተባሉት የሰፋርዊም አማልክት ልጆቻቸውን በእሳት ያቃጥሉ ነበር። 32 ይሖዋን ይፈሩ የነበረ ቢሆንም ከሕዝቡ መካከል፣ ከፍ ባሉት የማምለኪያ ቦታዎች የሚያገለግሉ ካህናትን ሾሙ፤ እነዚህ ካህናትም ከፍ ባሉት የማምለኪያ ቦታዎች በሚገኙት የአምልኮ ቤቶች የእነሱ አገልጋዮች ሆኑ።+ 33 በአንድ በኩል ይሖዋን ይፈሩ ነበር፤ በሌላ በኩል ደግሞ ከመፈናቀላቸው በፊት የነበሩባቸው ብሔራት ያመልኩ እንደነበረው* የራሳቸውን አማልክት ያመልኩ ነበር።+
34 እስከ ዛሬ ድረስ አምልኳቸውን የሚያከናውኑት በፊት ያደርጉት እንደነበረው* ነው። ይሖዋን የሚያመልክ* ብሎም ደንቦቹን፣ ድንጋጌዎቹን እንዲሁም ይሖዋ እስራኤል የሚል ስም ላወጣለት ለያዕቆብ+ ልጆች የሰጣቸውን ሕግና ትእዛዝ የሚከተል አንድም ሰው አልነበረም። 35 ይሖዋ ከእነሱ ጋር ቃል ኪዳን በተጋባበት ወቅት+ እንዲህ ሲል አዟቸው ነበር፦ “ሌሎች አማልክትን አትፍሩ፤ አትስገዱላቸው፤ አታገልግሏቸው፤ አትሠዉላቸው።+ 36 ከዚህ ይልቅ መፍራት+ ያለባችሁ በታላቅ ኃይልና በተዘረጋ ክንድ ከግብፅ ምድር ያወጣችሁን ይሖዋን ነው፤+ መስገድ ያለባችሁ ለእሱ ነው፤ መሠዋት ያለባችሁም ለእሱ ነው። 37 የጻፈላችሁን ሥርዓቶች፣ ድንጋጌዎች፣ ሕግና ትእዛዛት ምንጊዜም በጥንቃቄ ጠብቁ፤+ ሌሎች አማልክትን አትፍሩ። 38 ደግሞም ከእናንተ ጋር የገባሁትን ቃል ኪዳን አትርሱ፤+ ሌሎች አማልክትንም አትፍሩ። 39 ይልቁንም ከጠላቶቻችሁ ሁሉ እጅ የሚታደጋችሁ እሱ ስለሆነ መፍራት ያለባችሁ አምላካችሁን ይሖዋን ነው።”
40 እነሱ ግን አልታዘዙም፤ አምልኳቸውንም የሚያከናውኑት በፊት ያደርጉት እንደነበረው* ነው።+ 41 እነዚህ ብሔራት ይሖዋን ይፈሩ+ የነበረ ቢሆንም የራሳቸውን የተቀረጹ ምስሎችም ያገለግሉ ነበር። ልጆቻቸውም ሆኑ የልጅ ልጆቻቸው እስከ ዛሬ ድረስ የሚያደርጉት አባቶቻቸው እንዳደረጉት ነው።
18 የእስራኤል ንጉሥ የኤላህ ልጅ ሆሺአ+ በነገሠ በሦስተኛው ዓመት የይሁዳ ንጉሥ የአካዝ+ ልጅ ሕዝቅያስ+ ነገሠ። 2 እሱም በነገሠ ጊዜ ዕድሜው 25 ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌምም ሆኖ ለ29 ዓመት ገዛ። እናቱ አቢ* ትባል ነበር፤ እሷም የዘካርያስ ልጅ ነበረች።+ 3 አባቱ ዳዊት እንዳደረገው ሁሉ እሱም በይሖዋ ፊት ትክክል የሆነውን ነገር አደረገ።+ 4 ከፍ ያሉትን የማምለኪያ ቦታዎች ያስወገደው፣+ የማምለኪያ ዓምዶቹን ያደቀቀውና+ የማምለኪያ ግንዱን* የቆራረጠው እሱ ነበር። በተጨማሪም ሙሴ ሠርቶት የነበረውን የመዳብ እባብ አደቀቀ፤+ የእስራኤል ሕዝብ እስከዚያ ጊዜ ድረስ ለእባቡ የሚጨስ መሥዋዕት ያቀርብ ነበርና፤ ይህም ጣዖት የመዳብ እባብ* ተብሎ ይጠራ ነበር። 5 እሱም በእስራኤል አምላክ በይሖዋ ታመነ፤+ ከእሱ በኋላም ሆነ ከእሱ በፊት ከተነሱት የይሁዳ ነገሥታት መካከል እንደ እሱ ያለ አልተገኘም። 6 ከይሖዋ ጋር ተጣበቀ።+ እሱንም ከመከተል ዞር አላለም፤ ይሖዋ ለሙሴ የሰጠውን ትእዛዝ ጠብቆ ኖረ። 7 ይሖዋም ከእሱ ጋር ነበር። የሚያደርገውንም ነገር ሁሉ በጥበብ ያከናውን ነበር። በኋላም በአሦር ንጉሥ ላይ ዓመፀ፤ እሱንም ለማገልገል ፈቃደኛ አልሆነም።+ 8 በተጨማሪም እስከ ጋዛና እስከ ክልሎቿ ድረስ በመዝለቅ ፍልስጤማውያንን+ ከመጠበቂያ ግንቡ አንስቶ እስከተመሸገው ከተማ* ድረስ ድል አደረገ።
9 ሕዝቅያስ በነገሠ በአራተኛው ዓመት ማለትም የእስራኤል ንጉሥ የኤላህ ልጅ ሆሺአ+ በነገሠ በሰባተኛው ዓመት የአሦር ንጉሥ ሰልምናሶር በሰማርያ ላይ ዘምቶ ከበባት።+ 10 በሦስተኛው ዓመት ማብቂያ ላይ ከተማዋን ያዟት፤+ ሕዝቅያስ በነገሠ በስድስተኛው ዓመት ይኸውም የእስራኤል ንጉሥ ሆሺአ በነገሠ በዘጠነኛው ዓመት ሰማርያ ተያዘች። 11 ከዚያም የአሦር ንጉሥ እስራኤላውያንን ወደ አሦር በግዞት ወስዶ+ በሃላህ፣ በጎዛን ወንዝ አጠገብ በምትገኘው በሃቦርና በሜዶናውያን ከተሞች አሰፈራቸው።+ 12 ይህ የሆነው የአምላካቸውን የይሖዋን ድምፅ ከመስማት ይልቅ ቃል ኪዳኑን ስላፈረሱ ይኸውም የይሖዋ አገልጋይ ሙሴ የሰጣቸውን ትእዛዝ በሙሉ ስላልጠበቁ ነው።+ አልሰሙም፤ ደግሞም አልታዘዙም።
13 ንጉሥ ሕዝቅያስ በነገሠ በ14ኛው ዓመት የአሦር ንጉሥ ሰናክሬም+ በተመሸጉት የይሁዳ ከተሞች ሁሉ ላይ ዘምቶ ያዛቸው።+ 14 በመሆኑም የይሁዳ ንጉሥ ሕዝቅያስ በለኪሶ ወደነበረው ወደ አሦር ንጉሥ “በድያለሁ። እባክህ ከእኔ ተመለስ፤ እኔም የምትጠይቀኝን ነገር ሁሉ እሰጣለሁ” የሚል መልእክት ላከ። የአሦርም ንጉሥ በይሁዳ ንጉሥ በሕዝቅያስ ላይ 300 የብር ታላንትና* 30 የወርቅ ታላንት ቅጣት ጣለበት። 15 በመሆኑም ሕዝቅያስ በይሖዋ ቤትና በንጉሡ ቤት* ግምጃ ቤቶች የተገኘውን ብር ሁሉ ሰጠው።+ 16 በዚህ ጊዜ የይሁዳ ንጉሥ ሕዝቅያስ ራሱ የለበጣቸውን*+ የይሖዋን ቤተ መቅደስ በሮችና+ መቃኖች ነቃቅሎ* ለአሦር ንጉሥ ሰጠው።
17 ከዚያም የአሦር ንጉሥ ታርታኑን፣* ራብሳሪሱንና* ራብሻቁን* ከብዙ ሠራዊት ጋር ከለኪሶ+ በኢየሩሳሌም ወደሚገኘው ወደ ንጉሥ ሕዝቅያስ ላካቸው።+ እነሱም ወደ ኢየሩሳሌም ወጥተው ወደ ልብስ አጣቢው እርሻ በሚወስደው አውራ ጎዳና ላይ በሚገኘው በላይኛው ኩሬ የውኃ መውረጃ ቦይ አጠገብ ቆሙ።+ 18 ንጉሡ እንዲመጣ በተጣሩ ጊዜ የንጉሡ ቤት* ኃላፊ የሆነው የኬልቅያስ ልጅ ኤልያቄም፣+ ጸሐፊው ሸብናህ+ እና ታሪክ ጸሐፊው የአሳፍ ልጅ ዮአህ ወደ እነሱ ወጡ።
19 ራብሻቁም እንዲህ አላቸው፦ “እስቲ ሕዝቅያስን እንዲህ በሉት፦ ‘ታላቁ ንጉሥ፣ የአሦር ንጉሥ እንዲህ ይላል፦ “ለመሆኑ እንዲህ እንድትተማመን ያደረገህ ምንድን ነው?+ 20 ‘የጦር ስልትና ለመዋጋት የሚያስችል ኃይል አለኝ’ ትላለህ፤ ይሁንና ይህ ከንቱ ወሬ ነው። ለመሆኑ በእኔ ላይ ለማመፅ የደፈርከው በማን ተማምነህ ነው?+ 21 እነሆ፣ ሰው ቢመረኮዘው እጁ ላይ ሊሰነቀርና ሊወጋው ከሚችለው ከዚህ የተቀጠቀጠ ሸምበቆ፣ ከግብፅ ድጋፍ አገኛለሁ ብለህ ተማምነሃል።+ የግብፅ ንጉሥ ፈርዖን ለሚታመኑበት ሁሉ እንዲሁ ነው። 22 ‘እኛ የምንታመነው በአምላካችን በይሖዋ ነው’+ የምትሉኝ ከሆነ ደግሞ፣ ሕዝቅያስ ይሁዳንና ኢየሩሳሌምን ‘መስገድ ያለባችሁ በኢየሩሳሌም በሚገኘው በዚህ መሠዊያ ፊት ነው’+ ብሎ የእሱን ከፍ ያሉ የማምለኪያ ቦታዎችና መሠዊያዎች አስወግዶ የለም?”’+ 23 በል እስቲ፣ አሁን ከጌታዬ ከአሦር ንጉሥ ጋር ተወራረድ፦ ጋላቢዎች ማግኘት የምትችል ከሆነ 2,000 ፈረሶች እሰጥሃለሁ።+ 24 አንተ የምትታመነው በግብፅ ሠረገሎችና ፈረሰኞች ነው፤ ታዲያ ከጌታዬ አገልጋዮች መካከል ዝቅተኛ ደረጃ ያለውን አንዱን አለቃ እንኳ እንዴት መመከት ትችላለህ? 25 ለመሆኑ ይህን አካባቢ ለማጥፋት የመጣሁት ይሖዋ ሳይፈቅድልኝ ይመስልሃል? ይሖዋ ራሱ ‘በዚህ ምድር ላይ ዘምተህ አጥፋው’ ብሎኛል።”
26 በዚህ ጊዜ የኬልቅያስ ልጅ ኤልያቄም፣ ሸብናህ+ እና ዮአህ ራብሻቁን+ እንዲህ አሉት፦ “እባክህ፣ እኛ አገልጋዮችህ ቋንቋውን ስለምናውቅ በአረማይክ* ቋንቋ+ አናግረን፤ በቅጥሩ ላይ ያለው ሕዝብ በሚሰማው በአይሁዳውያን ቋንቋ አታነጋግረን።”+ 27 ራብሻቁ ግን እንዲህ አላቸው፦ “ጌታዬ ይህን ቃል እንድናገር የላከኝ ለጌታህና ለአንተ ብቻ ነው? ከእናንተ ጋር የገዛ ራሳቸውን እዳሪ ለሚበሉትና የገዛ ራሳቸውን ሽንት ለሚጠጡት በቅጥሩ ላይ ለተቀመጡት ሰዎች ጭምር አይደለም?”
28 ከዚያም ራብሻቁ ቆሞ ከፍ ባለ ድምፅ በአይሁዳውያን ቋንቋ እንዲህ አለ፦ “የታላቁን ንጉሥ፣ የአሦርን ንጉሥ ቃል ስሙ።+ 29 ንጉሡ እንዲህ ይላል፦ ‘ሕዝቅያስ አያታላችሁ፤ እሱ ከእጄ ሊታደጋችሁ አይችልምና።+ 30 ደግሞም ሕዝቅያስ “ይሖዋ በእርግጥ ይታደገናል፤ ይህችም ከተማ በአሦር ንጉሥ እጅ አትወድቅም” እያለ በይሖዋ እንድትታመኑ አያድርጋችሁ።+ 31 ሕዝቅያስን አትስሙት፤ የአሦር ንጉሥ እንዲህ ይላልና፦ “ከእኔ ጋር ሰላም ፍጠሩ፤ እጃችሁንም ስጡ፤* እያንዳንዳችሁም ከራሳችሁ ወይንና ከራሳችሁ በለስ ትበላላችሁ፤ ከራሳችሁም የውኃ ጉድጓድ ትጠጣላችሁ፤ 32 ይህም የሚሆነው መጥቼ የእናንተን ምድር ወደምትመስለው፣ እህልና አዲስ የወይን ጠጅ፣ ዳቦና የወይን እርሻ፣ የወይራ ዛፍና ማር ወደሚገኝባት ምድር እስክወስዳችሁ ድረስ ነው።+ በዚያን ጊዜ በሕይወት ትኖራላችሁ እንጂ አትሞቱም። ሕዝቅያስን አትስሙት፤ ‘ይሖዋ ይታደገናል’ እያለ ያታልላችኋልና። 33 ከብሔራት አማልክት መካከል ምድሩን ከአሦር ንጉሥ እጅ ያስጣለ አለ? 34 የሃማትና+ የአርጳድ አማልክት የት አሉ? የሰፋርዊም፣+ የሄና እና የኢዋ አማልክትስ የት አሉ? ሰማርያን ከእጄ ማስጣል ችለዋል?+ 35 ከእነዚህ አገሮች አማልክት ሁሉ ምድሩን ከእጄ ማስጣል የቻለ የትኛው ነው? ታዲያ ይሖዋ ኢየሩሳሌምን ከእጄ ሊያስጥላት ይችላል?”’”+
36 ሕዝቡ ግን ንጉሡ “ምንም መልስ አትስጡት” ብሎ አዝዞ ስለነበር ዝም አለ፤ አንድም ቃል አልመለሰለትም።+ 37 ይሁንና የቤቱ* አስተዳዳሪ የሆነው የኬልቅያስ ልጅ ኤልያቄም፣ ጸሐፊው ሸብናህ እና ታሪክ ጸሐፊው የአሳፍ ልጅ ዮአህ ልብሳቸውን ቀደው ወደ ሕዝቅያስ መጡ፤ ራብሻቁ ያለውንም ነገሩት።
19 ንጉሥ ሕዝቅያስ ይህን እንደሰማ ልብሱን ቀደደ፤ ማቅ ለብሶም ወደ ይሖዋ ቤት ገባ።+ 2 ከዚያም የቤቱ* አስተዳዳሪ የሆነውን ኤልያቄምን፣ ጸሐፊውን ሸብናህን እንዲሁም የካህናቱን ሽማግሌዎች ማቅ ለብሰው ወደ አሞጽ ልጅ ወደ ነቢዩ ኢሳይያስ+ እንዲሄዱ ላካቸው። 3 እነሱም እንዲህ አሉት፦ “ሕዝቅያስ እንዲህ ይላል፦ ‘ይህ ቀን የጭንቀት፣ የዘለፋና* የውርደት ቀን ነው፤ መውለጃዋ ደርሶ* ለማማጥ የሚያስችል አቅም እንዳጣች ሴት ሆነናል።+ 4 ምናልባት አምላክህ ይሖዋ፣ ሕያው የሆነውን አምላክ እንዲያቃልል ጌታው የአሦር ንጉሥ የላከውን የራብሻቁን ቃል ሁሉ ይሰማ ይሆናል፤+ ደግሞም አምላክህ ይሖዋ፣ የተናገረውን ቃል ሰምቶ ተጠያቂ ያደርገው ይሆናል። ስለዚህ በሕይወት ለተረፉት ቀሪዎች ጸልይ።’”+
5 በመሆኑም የንጉሥ ሕዝቅያስ አገልጋዮች ወደ ኢሳይያስ ሄዱ፤+ 6 ኢሳይያስም እንዲህ አላቸው፦ “ጌታችሁን እንዲህ በሉት፦ ‘ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “የአሦር ንጉሥ አገልጋዮች እኔን በመሳደብ የተናገሩትን ቃል በመስማትህ አትፍራ።+ 7 እነሆ፣ በአእምሮው አንድ ሐሳብ አስገባለሁ፤* እሱም ወሬ ሰምቶ ወደ አገሩ ይመለሳል፤ በገዛ አገሩም በሰይፍ እንዲወድቅ አደርጋለሁ።”’”+
8 ራብሻቁም የአሦር ንጉሥ ለኪሶን+ ለቆ እንደሄደ ሲሰማ ወደ ንጉሡ ተመለሰ፤ ከሊብናም ጋር ሲዋጋ አገኘው።+ 9 ንጉሡ የኢትዮጵያው ንጉሥ ቲርሃቅ “ከአንተ ጋር ሊዋጋ ወጥቷል” የሚል ወሬ ሰምቶ ነበር። በመሆኑም ለሕዝቅያስ እንዲህ ብለው እንዲነግሩት በድጋሚ መልእክተኞች ላከ፦+ 10 “የይሁዳን ንጉሥ ሕዝቅያስን እንዲህ በሉት፦ ‘የምትታመንበት አምላክህ “ኢየሩሳሌም በአሦር ንጉሥ እጅ አትወድቅም” ብሎ አያታልህ።+ 11 እነሆ፣ የአሦር ነገሥታት ሌሎቹን አገሮች ሁሉ ፈጽመው በማጥፋት ያደረጉትን ነገር ሰምተሃል።+ ታዲያ አንተ ብቻ ከዚህ የምታመልጥ ይመስልሃል? 12 አባቶቼ ያጠፏቸውን ብሔራት አማልክታቸው ታድገዋቸዋል? ጎዛን፣ ካራን፣+ ረጼፍና በቴልአሳር የነበሩት የኤደን ሕዝቦች የት አሉ? 13 የሃማት ንጉሥ፣ የአርጳድ ንጉሥ፣ የሰፋርዊም ከተሞች ንጉሥ እንዲሁም የሄና እና የኢዋ+ ነገሥታት የት አሉ?’”
14 ሕዝቅያስ ደብዳቤዎቹን ከመልእክተኞቹ እጅ ተቀብሎ አነበበ። ከዚያም ወደ ይሖዋ ቤት ወጥቶ ደብዳቤዎቹን* በይሖዋ ፊት ዘረጋ።+ 15 ሕዝቅያስም በይሖዋ ፊት እንዲህ ሲል ጸለየ፦+ “ከኪሩቤል በላይ* የምትቀመጥ፣+ የእስራኤል አምላክ ይሖዋ ሆይ፣ የምድር መንግሥታት ሁሉ እውነተኛ አምላክ አንተ ብቻ ነህ።+ ሰማያትንና ምድርን ሠርተሃል። 16 ይሖዋ ሆይ፣ ጆሮህን አዘንብለህ ስማ!+ ይሖዋ ሆይ፣ ዓይንህን ገልጠህ እይ!+ ሰናክሬም ሕያው የሆነውን አምላክ ለማቃለል የላከውን ቃል ስማ። 17 ይሖዋ ሆይ፣ የአሦር ነገሥታት ሌሎቹን ብሔራትና ምድራቸውን እንዳጠፉ አይካድም።+ 18 አማልክታቸውንም እሳት ውስጥ ጨምረዋል፤ ምክንያቱም የሰው እጅ ሥራ፣+ እንጨትና ድንጋይ እንጂ አማልክት አይደሉም።+ ሊያጠፏቸው የቻሉት በዚህ ምክንያት ነው። 19 አሁን ግን አምላካችን ይሖዋ ሆይ፣ የምድር መንግሥታት ሁሉ፣ አንተ ብቻ አምላክ እንደሆንክ ያውቁ ዘንድ ይሖዋ ሆይ፣ እባክህ ከእጁ አድነን።”+
20 ከዚያም የአሞጽ ልጅ ኢሳይያስ እንዲህ የሚል መልእክት ወደ ሕዝቅያስ ላከ፦ “የእስራኤል አምላክ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘ስለ አሦር ንጉሥ ስለ ሰናክሬም ወደ እኔ ያቀረብከውን ጸሎት ሰምቻለሁ።+ 21 ይሖዋ በእሱ ላይ የተናገረው ቃል ይህ ነው፦
“ድንግሊቱ የጽዮን ልጅ ትንቅሃለች፤ ደግሞም ታፌዝብሃለች።
የኢየሩሳሌም ሴት ልጅ ራሷን ትነቀንቅብሃለች።
22 ያቃለልከውና የሰደብከው ማንን ነው?+
ድምፅህን ከፍ ያደረግከው፣+
እብሪተኛ ዓይንህንም ያነሳኸው በማን ላይ ነው?
በእስራኤል ቅዱስ ላይ እኮ ነው!+
23 በመልእክተኞችህ+ በኩል ይሖዋን አቃለሃል፤+ እንዲህም ብለሃል፦
‘ብዛት ባላቸው የጦር ሠረገሎቼ፣
ወደ ተራሮች ከፍታ፣
ርቀው ወደሚገኙትም የሊባኖስ ስፍራዎች እወጣለሁ።
ረጃጅሞቹን አርዘ ሊባኖሶች፣ ምርጥ የሆኑትንም የጥድ ዛፎች እቆርጣለሁ።
ርቆ ወደሚገኘው ማረፊያ ቦታ፣ በጣም ጥቅጥቅ ወዳለው ጫካ እገባለሁ።
24 ጉድጓድ ቆፍሬ የባዕድ አገር ውኃዎችን እጠጣለሁ፤
የግብፅንም ጅረቶች* ሁሉ በእግሬ ረግጬ አደርቃለሁ።’
25 አልሰማህም? ይህ ከጥንት ዘመን ጀምሮ የተወሰነ* ነው።+
አሁን እንዲፈጸም አደርጋለሁ።+
አንተም የተመሸጉትን ከተሞች የፍርስራሽ ክምር ታደርጋለህ።+
26 ነዋሪዎቻቸው አቅመ ቢስ ይሆናሉ፤
ይሸበራሉ፤ ደግሞም ያፍራሉ።
እንደ ሜዳ ተክል፣ እንደ ለምለም ሣር፣+
እንዲሁም የምሥራቅ ነፋስ እንዳቃጠለው በጣሪያ ላይ የበቀለ ሣር ይሆናሉ።
27 ይሁንና መቼ እንደምትቀመጥ፣ መቼ እንደምትወጣና መቼ እንደምትገባ፣
እንዲሁም መቼ በእኔ ላይ እንደተቆጣህ በሚገባ አውቃለሁ፤+
29 “‘ይህም ምልክት ይሆንሃል፦* በዚህ ዓመት የገቦውን እህል* ትበላላችሁ፤ በሁለተኛውም ዓመት ከዚያው ላይ የበቀለውን እህል ትበላላችሁ፤+ በሦስተኛው ዓመት ግን ዘር ትዘራላችሁ፤ ታጭዳላችሁም፤ እንዲሁም ወይን ትተክላላችሁ፤ ፍሬውንም ትበላላችሁ።+ 30 ከይሁዳ ቤት ያመለጡትና በሕይወት የቀሩት ሰዎች+ ወደ ታች ሥር ይሰዳሉ፤ ወደ ላይም ያፈራሉ። 31 ከኢየሩሳሌም ቀሪዎች፣ ከጽዮን ተራራም በሕይወት የተረፉ ሰዎች ይወጣሉና። የሠራዊት ጌታ የይሖዋ ቅንዓት ይህን ያደርጋል።+
32 “‘ስለዚህ ይሖዋ ስለ አሦር ንጉሥ እንዲህ ይላል፦+
33 በመጣበት መንገድ ይመለሳል፤
ወደዚህች ከተማ አይገባም” ይላል ይሖዋ።
35 በዚያም ሌሊት የይሖዋ መልአክ ወጥቶ በአሦራውያን ሰፈር የነበሩትን 185,000 ሰዎች ገደለ።+ ሰዎችም በማለዳ ሲነሱ ሬሳውን አዩ።+ 36 በመሆኑም የአሦር ንጉሥ ሰናክሬም ከዚያ ተነስቶ ወደ ነነዌ+ ተመለሰ፤ በዚያም ተቀመጠ።+ 37 ሰናክሬም በአምላኩ በኒስሮክ ቤት* እየሰገደ ሳለ አድራሜሌክና ሳሬጸር የተባሉት የገዛ ልጆቹ በሰይፍ መትተው ገደሉት፤+ ከዚያም ወደ አራራት+ ምድር ሸሽተው ሄዱ። ልጁም ኤሳርሃደን+ በእሱ ምትክ ነገሠ።
20 በዚያ ጊዜ ሕዝቅያስ በጠና ታሞ ሞት አፋፍ ደርሶ ነበር።+ የአሞጽ ልጅ ነቢዩ ኢሳይያስ መጥቶ እንዲህ አለው፦ “ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘ከሕመምህ አትድንም፤ መሞትህ ስለማይቀር ለቤተሰብህ መመሪያ ስጥ።’”+ 2 በዚህ ጊዜ ፊቱን ወደ ግድግዳው አዙሮ ወደ ይሖዋ መጸለይ ጀመረ፦ 3 “እባክህ ይሖዋ ሆይ፣ በታማኝነትና በሙሉ ልብ በፊትህ እንዴት እንደተመላለስኩ እንዲሁም በዓይኖችህ ፊት መልካም የሆነውን ነገር እንዳደረግኩ እንድታስታውስ አጥብቄ እለምንሃለሁ።”+ ሕዝቅያስም ምርር ብሎ አለቀሰ።
4 ኢሳይያስ ገና ወደ መካከለኛው ግቢ ሳይወጣ የይሖዋ ቃል እንዲህ ሲል ወደ እሱ መጣ፦+ 5 “ተመልሰህ ሂድና የሕዝቤ መሪ የሆነውን ሕዝቅያስን እንዲህ በለው፦ ‘የአባትህ የዳዊት አምላክ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “ጸሎትህን ሰምቻለሁ። እንባህንም አይቻለሁ።+ ስለሆነም እፈውስሃለሁ።+ በሦስተኛው ቀን ወደ ይሖዋ ቤት ትወጣለህ።+ 6 እኔም በዕድሜህ* ላይ 15 ዓመት እጨምርልሃለሁ፤ ደግሞም አንተንና ይህችን ከተማ ከአሦር ንጉሥ እጅ እታደጋለሁ፤+ ስለ ራሴና ስለ አገልጋዬ ስለ ዳዊት ስል ከተማዋን እጠብቃታለሁ።”’”+
7 ከዚያም ኢሳይያስ “የደረቀ የበለስ ጥፍጥፍ አምጡ” አለ። ጥፍጥፉንም አምጥተው እባጩ ላይ አደረጉለት፤ እሱም ቀስ በቀስ እየተሻለው ሄደ።+
8 ሕዝቅያስ ኢሳይያስን “ይሖዋ እንደሚፈውሰኝና በሦስተኛው ቀን ወደ ይሖዋ ቤት እንደምወጣ ማወቅ የምችልበት ምልክት ምንድን ነው?”+ ሲል ጠየቀው። 9 ኢሳይያስም መልሶ “ይሖዋ የተናገረውን ቃል እንደሚፈጽም የሚያሳየው ይሖዋ የሰጠህ ምልክት ይህ ነው፦ ጥላው በደረጃው* ላይ አሥር ደረጃ ወደ ፊት እንዲሄድ ትፈልጋለህ ወይስ አሥር ደረጃ ወደ ኋላ እንዲመለስ?” አለው።+ 10 ሕዝቅያስም “ጥላው አሥር ደረጃ ወደ ፊት መሄዱ ቀላል ነገር ነው፤ አሥር ደረጃ ወደ ኋላ መመለሱ ግን ቀላል አይደለም” አለ። 11 ስለዚህ ነቢዩ ኢሳይያስ ወደ ይሖዋ ጮኸ፤ እሱም በአካዝ ደረጃ ላይ ወደ ታች ወርዶ የነበረው ጥላ አሥር ደረጃ ወደ ኋላ እንዲመለስ አደረገ።+
12 በዚያን ጊዜ የባላዳን ልጅ የሆነው የባቢሎን ንጉሥ ቤሮዳክባላዳን ሕዝቅያስ መታመሙን ሰምቶ ስለነበር ደብዳቤና ስጦታ ላከለት።+ 13 ሕዝቅያስም ለመልእክተኞቹ ጥሩ አቀባበል አደረገላቸው፤* ከዚያም ግምጃ ቤቱን ሁሉ ይኸውም ብሩን፣ ወርቁን፣ የበለሳን ዘይቱን፣ ሌላውን ምርጥ ዘይት፣ የጦር መሣሪያውንና በግምጃ ቤቶቹ ውስጥ ያለውን ንብረት በሙሉ አሳያቸው።+ ሕዝቅያስ በቤቱም* ሆነ በግዛቱ ሁሉ ያላሳያቸው ምንም ነገር አልነበረም።
14 ከዚያ በኋላ ነቢዩ ኢሳይያስ ወደ ንጉሥ ሕዝቅያስ መጥቶ “እነዚህ ሰዎች ምን አሉ? የመጡትስ ከየት ነው?” ሲል ጠየቀው። ሕዝቅያስም “የመጡት ከሩቅ አገር፣ ከባቢሎን ነው” አለው።+ 15 ቀጥሎም “በቤትህ* ያዩት ነገር ምንድን ነው?” ሲል ጠየቀው። ሕዝቅያስም “በቤቴ* ያለውን ነገር ሁሉ አይተዋል። በግምጃ ቤቶቼ ውስጥ ካለው ንብረት ሁሉ ያላሳየኋቸው ምንም ነገር የለም” ሲል መለሰለት።
16 በዚህ ጊዜ ኢሳይያስ ሕዝቅያስን እንዲህ አለው፦ “የይሖዋን ቃል ስማ፦+ 17 ‘እነሆ፣ በቤትህ* ያለው ሁሉና አባቶችህ እስካሁን ድረስ ያከማቹት ነገር ሁሉ ወደ ባቢሎን የሚጋዝበት ቀን ይመጣል።+ አንድም የሚቀር ነገር አይኖርም’ ይላል ይሖዋ። 18 ‘ከአንተ ከሚወለዱት ከገዛ ልጆችህ መካከልም አንዳንዶቹ ይወሰዳሉ፤+ በባቢሎን ንጉሥ ቤተ መንግሥትም ባለሥልጣናት ይሆናሉ።’”+
19 በዚህ ጊዜ ሕዝቅያስ ኢሳይያስን “የተናገርከው የይሖዋ ቃል መልካም ነው”+ አለው። አክሎም “በእኔ የሕይወት ዘመን* ሰላምና መረጋጋት* መኖሩ መልካም ነው” አለ።+
20 የቀረው የሕዝቅያስ ታሪክ፣ ኃያልነቱ ሁሉ እንዲሁም ኩሬውንና+ ቦዩን ሠርቶ ውኃው ወደ ከተማዋ እንዲመጣ ያደረገበት መንገድ+ በይሁዳ ነገሥታት ዘመን ስለተፈጸሙት ነገሮች በሚተርከው የታሪክ መጽሐፍ ውስጥ ተጽፎ ይገኝ የለም? 21 በመጨረሻም ሕዝቅያስ ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤+ በእሱም ምትክ ልጁ ምናሴ+ ነገሠ።+
21 ምናሴ+ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው 12 ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌምም ሆኖ ለ55 ዓመት ገዛ።+ የእናቱ ስም ሄፍጺባ ነበር። 2 እሱም ይሖዋ ከእስራኤል ሕዝብ ፊት ያባረራቸው ብሔራት ይፈጽሟቸው የነበሩትን አስጸያፊ ልማዶች በመከተል በይሖዋ ፊት መጥፎ የሆነውን ነገር አደረገ።+ 3 አባቱ ሕዝቅያስ አስወግዷቸው የነበሩትን ከፍ ያሉ የማምለኪያ ቦታዎች መልሶ ገነባ፤+ እንዲሁም የእስራኤል ንጉሥ አክዓብ እንዳደረገው ለባአል መሠዊያዎችን አቆመ፤+ የማምለኪያ ግንድም* ሠራ።+ ለሰማይ ሠራዊትም ሁሉ ሰገደ፤ እነሱንም አገለገለ።+ 4 በተጨማሪም ይሖዋ “ስሜን በኢየሩሳሌም አኖራለሁ”+ ብሎ በተናገረለት በይሖዋ ቤት ውስጥ መሠዊያዎችን ሠራ።+ 5 ደግሞም በይሖዋ ቤት በሚገኙት በሁለቱ ግቢዎች+ ውስጥ ለሰማይ ሠራዊት ሁሉ መሠዊያዎችን ሠራ።+ 6 የገዛ ልጁን ለእሳት አሳልፎ ሰጠ፤ አስማተኛና መተተኛም ሆነ፤+ መናፍስት ጠሪዎችንና ጠንቋዮችን ቀጠረ።+ ይሖዋን ያስቆጣው ዘንድ በእሱ ፊት በጣም ብዙ መጥፎ ነገሮችን ሠራ።
7 የሠራውንም የማምለኪያ ግንድ* የተቀረጸ ምስል ይሖዋ ለዳዊትና ለልጁ ለሰለሞን እንዲህ ብሎ በተናገረለት ቤት ውስጥ አስቀመጠው፦+ “በዚህ ቤትና ከእስራኤል ነገዶች ሁሉ በመረጥኳት በኢየሩሳሌም ስሜን ለዘለቄታው አኖራለሁ።+ 8 እነሱ ያዘዝኳቸውን ሁሉ ይኸውም አገልጋዬ ሙሴ እንዲከተሉት ያዘዛቸውን ሕግ በሙሉ በጥንቃቄ ይጠብቁ+ እንጂ ከእንግዲህ የእስራኤላውያን እግር ለአባቶቻቸው ከሰጠሁት ምድር ወጥቶ እንዲንከራተት አላደርግም።”+ 9 እነሱ ግን አልታዘዙም፤ ምናሴም ይሖዋ ከእስራኤላውያን ፊት ካጠፋቸው ብሔራት የበለጠ ክፉ ነገር እንዲሠሩ አሳታቸው።+
10 ይሖዋ አገልጋዮቹ በሆኑት ነቢያት አማካኝነት በተደጋጋሚ እንዲህ ይላቸው ነበር፦+ 11 “የይሁዳ ንጉሥ ምናሴ እነዚህን ሁሉ አስጸያፊ ነገሮች አድርጓል፤ ከእሱ በፊት ከነበሩት አሞራውያን+ ሁሉ ይበልጥ ክፉ ድርጊት ፈጽሟል፤+ አስጸያፊ በሆኑ ጣዖቶቹም* ይሁዳ ኃጢአት እንዲሠራ አድርጓል። 12 ስለዚህ የእስራኤል አምላክ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘ለሚሰማው ሰው ሁሉ ጆሮ የሚሰቀጥጥ* ጥፋት በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ላይ አመጣለሁ።+ 13 በሰማርያ ላይ ተጠቅሜበት የነበረውን የመለኪያ ገመድ+ በኢየሩሳሌም ላይ እዘረጋለሁ፤+ እንዲሁም በአክዓብ ቤት+ ላይ ተጠቅሜበት የነበረውን ውኃ ልክ* በእሷ ላይ እጠቀማለሁ፤ አንድ ሰው ሳህኑን እንደሚወለውል ሁሉ እኔም ኢየሩሳሌምን ከወለወልኩ በኋላ እገለብጣታለሁ።+ 14 የርስቴን ቀሪዎች እተዋቸዋለሁ፤+ በጠላቶቻቸውም እጅ አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ፤ እነሱም በጠላቶቻቸው ሁሉ ይበዘበዛሉ፤ እንዲሁም ለጠላቶቻቸው ምርኮ ይሆናሉ፤+ 15 ይህን የማደርገው አባቶቻቸው ከግብፅ ከወጡበት ቀን አንስቶ እስከ ዛሬዋ ዕለት ድረስ በፊቴ መጥፎ የሆነውን ነገር ስላደረጉና በተደጋጋሚ ስላስቆጡኝ ነው።’”+
16 ምናሴ፣ ይሁዳ በይሖዋ ፊት መጥፎ የሆነውን ነገር በመፈጸም ኃጢአት እንዲሠራ በማድረግ ከሠራው ኃጢአት በተጨማሪ ኢየሩሳሌም ከዳር እስከ ዳር በደም እስክትሞላ ድረስ እጅግ ብዙ ንጹሕ ደም አፍስሷል።+ 17 የቀረው የምናሴ ታሪክና ያደረጋቸው ነገሮች በሙሉ እንዲሁም የሠራው ኃጢአት በይሁዳ ነገሥታት ዘመን ስለተፈጸሙት ነገሮች በሚተርከው የታሪክ መጽሐፍ ውስጥ ተጽፈው ይገኙ የለም? 18 በመጨረሻም ምናሴ ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በቤቱም በሚገኘው የአትክልት ስፍራ ይኸውም በዑዛ የአትክልት ስፍራ ተቀበረ፤+ ልጁም አምዖን በእሱ ምትክ ነገሠ።
19 አምዖን+ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው 22 ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌምም ሆኖ ለሁለት ዓመት ገዛ።+ እናቱ ሜሹሌሜት ትባል ነበር፤ እሷም የዮጥባ ሰው የሆነው የሃሩጽ ልጅ ነበረች። 20 አምዖን አባቱ ምናሴ እንዳደረገው በይሖዋ ፊት መጥፎ የሆነውን ነገር አደረገ።+ 21 አባቱ በሄደበት መንገድ ሁሉ ተመላለሰ፤ ደግሞም አባቱ ያገለግላቸው የነበሩትን አስጸያፊ የሆኑ ጣዖቶች አገለገለ፤ ለእነሱም ሰገደ።+ 22 የአባቶቹንም አምላክ ይሖዋን ተወ፤ በይሖዋም መንገድ አልሄደም።+ 23 ከጊዜ በኋላም የንጉሥ አምዖን አገልጋዮች በእሱ ላይ አሲረው በገዛ ቤቱ ውስጥ ገደሉት። 24 ሆኖም የምድሪቱ ሕዝብ በንጉሥ አምዖን ላይ ያሴሩትን ሁሉ ገደላቸው፤ በእሱም ምትክ ልጁን ኢዮስያስን አነገሠው።+ 25 የቀረው የአምዖን ታሪክ፣ ያደረጋቸው ነገሮች በይሁዳ ነገሥታት ዘመን ስለተፈጸሙት ነገሮች በሚተርከው የታሪክ መጽሐፍ ውስጥ ተጽፈው ይገኙ የለም? 26 እሱንም በዑዛ የአትክልት ስፍራ በሚገኘው መቃብሩ ቀበሩት፤+ ልጁም ኢዮስያስ+ በምትኩ ነገሠ።
22 ኢዮስያስ+ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ስምንት ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌምም ሆኖ ለ31 ዓመት ገዛ።+ እናቱ ይዲዳ ትባል ነበር፤ እሷም የቦጽቃት+ ሰው የሆነው የአዳያህ ልጅ ነበረች። 2 ኢዮስያስም በይሖዋ ፊት ትክክል የሆነውን ነገር አደረገ፤ በአባቱም በዳዊት መንገድ ሄደ፤+ ወደ ቀኝም ወደ ግራም ፈቀቅ አላለም።
3 ንጉሥ ኢዮስያስ፣ በነገሠ በ18ኛው ዓመት የመሹላም ልጅ፣ የአዜልያ ልጅ የሆነውን ጸሐፊውን ሳፋንን እንዲህ ሲል ወደ ይሖዋ ቤት ላከው፦+ 4 “ወደ ሊቀ ካህናቱ ወደ ኬልቅያስ+ ሂድ፤ በር ጠባቂዎቹ ከሕዝቡ ላይ የሰበሰቡትንና ወደ ይሖዋ ቤት የገባውን ገንዘብ በአጠቃላይ እንዲሰበስብ አድርግ።+ 5 ገንዘቡን በይሖዋ ቤት የሚከናወነውን ሥራ እንዲቆጣጠሩ ለተሾሙት ሰዎች ይስጧቸው፤ እነሱ ደግሞ በይሖዋ ቤት ውስጥ የፈረሰውን* ለሚጠግኑት ሠራተኞች ይስጡ፤+ 6 ይኸውም ለእጅ ጥበብ ባለሙያዎቹ፣ ለግንባታ ባለሙያዎቹና ለግንበኞቹ ያስረክቡ፤ እነሱም ገንዘቡን ለቤቱ ጥገና የሚያስፈልጉትን ሳንቃዎችና ጥርብ ድንጋዮች ለመግዛት ይጠቀሙበታል።+ 7 ነገር ግን ሰዎቹ እምነት የሚጣልባቸው ስለሆኑ ለተሰጣቸው ገንዘብ ስሌት እንዲያቀርቡ መጠየቅ አያስፈልግም።”+
8 በኋላም ሊቀ ካህናቱ ኬልቅያስ ጸሐፊውን ሳፋንን+ “የሕጉን መጽሐፍ+ በይሖዋ ቤት ውስጥ አገኘሁት” አለው። ኬልቅያስም መጽሐፉን ለሳፋን ሰጠው፤ እሱም ያነበው ጀመር።+ 9 ከዚያም ጸሐፊው ሳፋን ወደ ንጉሡ ሄዶ “አገልጋዮችህ በቤቱ ውስጥ የተገኘውን ገንዘብ በሙሉ አውጥተው በይሖዋ ቤት የሚከናወነውን ሥራ እንዲቆጣጠሩ ለተሾሙት ሰዎች አስረክበዋል” አለው።+ 10 በተጨማሪም ጸሐፊው ሳፋን ንጉሡን “ካህኑ ኬልቅያስ የሰጠኝ አንድ መጽሐፍ+ አለ” አለው። ከዚያም ሳፋን መጽሐፉን በንጉሡ ፊት ማንበብ ጀመረ።
11 ንጉሡ የሕጉን መጽሐፍ ቃል ሲሰማ ልብሱን ቀደደ።+ 12 ከዚያም ንጉሡ ካህኑን ኬልቅያስን፣ የሳፋንን ልጅ አኪቃምን፣+ የሚካያህን ልጅ አክቦርን፣ ጸሐፊውን ሳፋንን እና የንጉሡን አገልጋይ አሳያህን እንዲህ ሲል አዘዛቸው፦ 13 “ሄዳችሁ በተገኘው በዚህ መጽሐፍ ላይ የሰፈረውን ቃል በተመለከተ እኔን፣ ሕዝቡንና መላውን ይሁዳ ወክላችሁ ይሖዋን ጠይቁ፤ ምክንያቱም አባቶቻችን በዚህ መጽሐፍ ላይ እኛን አስመልክቶ የሰፈረውን ቃል ስላልታዘዙ የይሖዋ ታላቅ ቁጣ በእኛ ላይ ነዷል።”+
14 በመሆኑም ካህኑ ኬልቅያስ፣ አኪቃም፣ አክቦር፣ ሳፋንና አሳያህ ወደ ነቢዪቱ ሕልዳና+ ሄዱ። ሕልዳና የሃርሐስ ልጅ፣ የቲቅዋ ልጅ፣ የአልባሳት ጠባቂው የሻሉም ሚስት ስትሆን ኢየሩሳሌም ውስጥ በሁለተኛው ክፍል ትኖር ነበር፤ እነሱም በዚያ አነጋገሯት።+ 15 እሷም እንዲህ አለቻቸው፦ “የእስራኤል አምላክ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘ወደ እኔ የላካችሁን ሰው እንዲህ በሉት፦ 16 “ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘በዚህ ቦታና በነዋሪዎቹ ላይ መከራ አመጣለሁ፤ የይሁዳ ንጉሥ ባነበበው መጽሐፍ+ ላይ የሰፈረውን ቃል ሁሉ እፈጽማለሁ። 17 እኔን በመተው በእጆቻቸው ሥራ+ ሁሉ ያስቆጡኝ ዘንድ ለሌሎች አማልክት የሚጨስ መሥዋዕት ስለሚያቀርቡ+ ቁጣዬ በዚህ ቦታ ላይ ይነዳል፤ ደግሞም አይጠፋም።’”+ 18 ይሖዋን እንድትጠይቁ ለላካችሁ ለይሁዳ ንጉሥ ግን እንዲህ በሉት፦ “የእስራኤል አምላክ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘የሰማኸውን ቃል በተመለከተ፣ 19 ይህን ቦታም ሆነ ነዋሪዎቹን መቀጣጫ እንደማደርግና እንደምረግም የተናገርኩትን ነገር ስትሰማ ልብህ ስለተነካ፣* በይሖዋም ፊት ራስህን ስላዋረድክ+ እንዲሁም ልብስህን ስለቀደድክና+ በፊቴ ስላለቀስክ እኔም ሰምቼሃለሁ ይላል ይሖዋ። 20 ወደ አባቶችህ የምሰበስብህ* በዚህ የተነሳ ነው፤ አንተም በሰላም በመቃብርህ ታርፋለህ፤ በዚህ ቦታ ላይ የማመጣውን መከራ ሁሉ ዓይኖችህ አያዩም።’”’” ከዚያም ሰዎቹ መልሱን ለንጉሡ አመጡለት።
23 ንጉሡም መልእክት ላከ፤ እነሱም የይሁዳንና የኢየሩሳሌምን ሽማግሌዎች ሁሉ ጠሩ።+ 2 ከዚያ በኋላ ንጉሡ ከይሁዳ ሰዎች፣ ከኢየሩሳሌም ነዋሪዎች፣ ከካህናቱ፣ ከነቢያቱ እንዲሁም ትልቅ ትንሽ ሳይባል ከሕዝቡ ሁሉ ጋር ወደ ይሖዋ ቤት ወጣ። እሱም በይሖዋ ቤት የተገኘውን+ የቃል ኪዳኑን+ መጽሐፍ+ ቃል ሁሉ የተሰበሰቡት ሰዎች እየሰሙ አነበበላቸው። 3 ንጉሡ ዓምዱ አጠገብ ቆሞ በዚህ መጽሐፍ ላይ የሰፈሩትን የዚህን ቃል ኪዳን ቃላት በመፈጸም በሙሉ ልቡና በሙሉ ነፍሱ* ይሖዋን ለመከተል እንዲሁም ትእዛዛቱን፣ ማሳሰቢያዎቹንና ደንቦቹን ለመጠበቅ በይሖዋ ፊት ቃል ኪዳን ገባ።*+ ሕዝቡም ሁሉ በቃል ኪዳኑ ተስማማ።+
4 ከዚያም ንጉሡ ሊቀ ካህናቱን ኬልቅያስን፣+ በሁለተኛ ማዕረግ ያሉትን ካህናትና በር ጠባቂዎቹን ለባአል፣ ለማምለኪያ ግንዱና* ለሰማይ ሠራዊት ሁሉ የተሠሩትን ዕቃዎች በሙሉ ከይሖዋ ቤተ መቅደስ እንዲያወጡ አዘዛቸው።+ ከዚያም ከኢየሩሳሌም ውጭ በቄድሮን ተዳፋት ላይ አቃጠላቸው፤ አመዱንም ወደ ቤቴል+ ወሰደው። 5 የይሁዳ ነገሥታት በይሁዳ ከተሞችና በኢየሩሳሌም ዙሪያ በነበሩት ከፍ ያሉ የማምለኪያ ቦታዎች ላይ የሚጨስ መሥዋዕት እንዲያቀርቡ የሾሟቸውን የባዕድ አምላክ ካህናት አባረረ፤ በተጨማሪም ለባአል፣ ለፀሐይ፣ ለጨረቃ፣ ዞዲያክ ለተባለው ኅብረ ከዋክብትና ለሰማይ ሠራዊት ሁሉ+ የሚጨስ መሥዋዕት ያቀርቡ የነበሩትን በሙሉ አባረረ። 6 የማምለኪያ ግንዱን* ከይሖዋ ቤት አውጥቶ+ ወደ ኢየሩሳሌም ዳርቻ ወደ ቄድሮን ሸለቆ በመውሰድ በዚያ አቃጠለው፤+ አድቅቆም አመድ አደረገው፤ አመዱንም በሕዝቡ መቃብር ላይ በተነው።+ 7 እንዲሁም በይሖዋ ቤት ውስጥ የነበሩትንና ሴቶች ለማምለኪያ ግንዱ* ቤተ መቅደስ የሚሆኑ ድንኳኖችን ይሸምኑባቸው የነበሩትን የቤተ መቅደስ ቀላጮች*+ ቤቶች አፈራረሰ።
8 ከዚያም ካህናቱን ሁሉ ከይሁዳ ከተሞች አስወጣ፤ እንዲሁም ካህናቱ የሚጨስ መሥዋዕት ያቀርቡባቸው የነበሩትን ከጌባ+ አንስቶ እስከ ቤርሳቤህ+ ድረስ የሚገኙትን ከፍ ያሉ የማምለኪያ ቦታዎች አረከሰ። በተጨማሪም የከተማዋ አለቃ በሆነው በኢያሱ መግቢያ በር ላይ ይኸውም አንድ ሰው በከተማዋ በር ሲገባ በስተ ግራ በኩል በሚያገኘው በር ላይ የነበሩትን ከፍ ያሉ የማምለኪያ ቦታዎች አፈራረሰ። 9 ከፍ ያሉት የማምለኪያ ቦታዎች ካህናት፣ በኢየሩሳሌም በሚገኘው የይሖዋ መሠዊያ አያገልግሉ+ እንጂ ከወንድሞቻቸው ጋር ቂጣ* ይበሉ ነበር። 10 እሱም በሂኖም ልጆች ሸለቆ*+ ውስጥ የነበረውን ቶፌትን+ አረከሰ፤ ይህን ያደረገው ማንም ሰው በዚያ ወንድ ልጁን ወይም ሴት ልጁን ለሞሎክ በእሳት አሳልፎ እንዳይሰጥ ነው።+ 11 ደግሞም የይሁዳ ነገሥታት ለፀሐይ የሰጧቸው ፈረሶች የቤተ መንግሥት ባለሥልጣን በሆነው በናታንሜሌክ ክፍል* ይኸውም በመተላለፊያዎቹ መሃል ባለው ክፍል በኩል አድርገው ወደ ይሖዋ ቤት እንዳይገቡ ከለከለ፤ የፀሐይንም+ ሠረገሎች በእሳት አቃጠለ። 12 እንዲሁም ንጉሡ የይሁዳ ነገሥታት በአካዝ ሰገነት ጣሪያ ላይ+ የሠሯቸውን መሠዊያዎችና ምናሴ በይሖዋ ቤት ሁለት ግቢዎች ውስጥ የሠራቸውን መሠዊያዎች አፈራረሰ።+ ከዚያም አደቀቃቸው፤ የደቀቀውንም በቄድሮን ሸለቆ ውስጥ በተነው። 13 በተጨማሪም ንጉሡ፣ የእስራኤል ንጉሥ ሰለሞን ለሲዶናውያን አስጸያፊ የሴት አምላክ ለአስታሮት፣ ለሞዓባውያን አስጸያፊ አምላክ ለከሞሽ እንዲሁም ለአሞናውያን አስጸያፊ አምላክ+ ለሚልኮም+ የሠራቸውን በኢየሩሳሌም ፊት ለፊት ከጥፋት ተራራ* በስተ ደቡብ* የነበሩትን ከፍ ያሉ የማምለኪያ ቦታዎች አረከሰ። 14 የማምለኪያ ዓምዶቹን ሰባበረ፤ የማምለኪያ ግንዶቹንም* ቆራረጠ፤+ ቦታውንም በሰው አፅም ሞላው። 15 በቤቴል የነበረውንም መሠዊያ ይኸውም እስራኤላውያን ኃጢአት እንዲሠሩ ያደረገው የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም የሠራውን ከፍ ያለ የማምለኪያ ቦታ አፈረሰ።+ ያን መሠዊያና ከፍ ያለ የማምለኪያ ቦታ ካፈረሰ በኋላ ቦታውን አቃጠለው፤ ፈጭቶም አመድ አደረገው፤ የማምለኪያ ግንዱንም* አቃጠለ።+
16 ኢዮስያስ ዞር ብሎ በተራራው ላይ ያሉትን መቃብሮች ባየ ጊዜ አፅሞቹን ከመቃብሮቹ ውስጥ አስወጥቶ በመሠዊያው ላይ በማቃጠል እነዚህ ነገሮች እንደሚሆኑ አስቀድሞ የተናገረው የእውነተኛው አምላክ ሰው ባወጀው የይሖዋ ቃል መሠረት መሠዊያውን አረከሰ።+ 17 ከዚያም “እዚያ ጋ የማየው የመቃብር ሐውልት የማን ነው?” አለ። በዚህ ጊዜ የከተማዋ ሰዎች “ከይሁዳ የመጣውና በቤቴል በሚገኘው መሠዊያ ላይ አንተ ያደረግካቸውን እነዚህን ነገሮች አስቀድሞ የተናገረው የእውነተኛው አምላክ ሰው+ መቃብር ነው” አሉት። 18 እሱም “በሉ ይረፍ ተዉት። ማንም ሰው አፅሙን አይረብሸው” አለ። በመሆኑም የእሱንም ሆነ ከሰማርያ የመጣውን ነቢይ አፅም ሳይነኩ ተዉት።+
19 በተጨማሪም ኢዮስያስ የእስራኤል ነገሥታት አምላክን ለማስቆጣት በሰማርያ ከተሞች ውስጥ የሠሯቸውን ከፍ ባሉ የማምለኪያ ቦታዎች ላይ የሚገኙ የአምልኮ ቤቶች በሙሉ አስወገደ፤+ በቤቴል ያደረገውንም ሁሉ በእነሱ ላይ አደረገ።+ 20 በዚህም መሠረት በዚያ የነበሩትን ከፍ ያሉ የማምለኪያ ቦታዎች ካህናት በሙሉ በመሠዊያዎቹ ላይ ሠዋ፤ በላያቸውም ላይ የሰው አፅም አቃጠለ።+ ከዚያም ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ።
21 ንጉሡም ሕዝቡን ሁሉ “በዚህ የቃል ኪዳን መጽሐፍ ላይ በተጻፈው መሠረት ለአምላካችሁ ለይሖዋ ፋሲካን* አክብሩ”+ ሲል አዘዘ።+ 22 መሳፍንት እስራኤልን ያስተዳድሩ በነበረበት ዘመንም ሆነ በእስራኤል ነገሥታትና በይሁዳ ነገሥታት ዘመን ሁሉ እንዲህ ያለ ፋሲካ ተከብሮ አያውቅም።+ 23 ንጉሥ ኢዮስያስ በነገሠ በ18ኛው ዓመት ግን ይህ ፋሲካ በኢየሩሳሌም ለይሖዋ ተከበረ።
24 በተጨማሪም ኢዮስያስ ካህኑ ኬልቅያስ በይሖዋ ቤት ውስጥ ባገኘው መጽሐፍ+ ላይ የተጻፈውን የሕጉን ቃል ይፈጽም ዘንድ+ መናፍስት ጠሪዎችን፣ ጠንቋዮችን፣+ የተራፊም ቅርጻ ቅርጾችን፣*+ አስጸያፊ የሆኑ ጣዖቶችን* እንዲሁም በይሁዳ ምድርና በኢየሩሳሌም የነበሩ አስጸያፊ ነገሮችን በሙሉ አስወገደ። 25 በሙሴ ሕግ መሠረት በሙሉ ልቡ፣ በሙሉ ነፍሱና*+ በሙሉ ኃይሉ ወደ ይሖዋ የተመለሰ እንደ እሱ ያለ ንጉሥ ከእሱ በፊት አልነበረም፤ ከእሱ በኋላም እንደ እሱ ያለ ንጉሥ አልተነሳም።
26 ይሁንና ይሖዋ፣ ምናሴ እሱን ያስቆጣው ዘንድ በፈጸማቸው አስጸያፊ ነገሮች ሁሉ የተነሳ በይሁዳ ላይ ከነደደው ቁጣው አልተመለሰም ነበር።+ 27 ይሖዋ “እስራኤልን እንዳስወገድኩ+ ሁሉ ይሁዳንም ከፊቴ አስወግዳለሁ፤+ የመረጥኳትን ይህችን ከተማ ኢየሩሳሌምን እንዲሁም ‘ስሜ በዚያ ይኖራል’+ ብዬ የተናገርኩለትን ቤት እተዋለሁ” አለ።
28 የቀረው የኢዮስያስ ታሪክ፣ ያደረጋቸው ነገሮች በሙሉ በይሁዳ ነገሥታት ዘመን ስለተፈጸሙት ነገሮች በሚተርከው የታሪክ መጽሐፍ ውስጥ ተጽፈው ይገኙ የለም? 29 በእሱ ዘመን የግብፁ ንጉሥ ፈርዖን ኒካዑ ከአሦር ንጉሥ ጋር ለመገናኘት በኤፍራጥስ ወንዝ በኩል መጣ፤ ንጉሥ ኢዮስያስም ሊገጥመው ወጣ፤ ኒካዑም ባየው ጊዜ መጊዶ ላይ ገደለው።+ 30 በመሆኑም አገልጋዮቹ አስከሬኑን በሠረገላ ከመጊዶ ወደ ኢየሩሳሌም በማምጣት በራሱ መቃብር ውስጥ ቀበሩት። ከዚያም የምድሪቱ ሕዝብ የኢዮስያስን ልጅ ኢዮዓካዝን ቀብተው በአባቱ ምትክ አነገሡት።+
31 ኢዮዓካዝ+ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው 23 ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌምም ሆኖ ለሦስት ወር ገዛ። እናቱ ሀሙጣል ትባል ነበር፤+ እሷም የሊብና ሰው የሆነው የኤርምያስ ልጅ ነበረች። 32 አባቶቹ እንዳደረጉት ሁሉ እሱም በይሖዋ ፊት መጥፎ የሆነውን ነገር አደረገ።+ 33 ፈርዖን ኒካዑ፣+ ኢዮዓካዝ በኢየሩሳሌም ሆኖ እንዳይገዛ በሃማት ምድር በምትገኘው በሪብላ+ አሰረው፤ በምድሪቱም ላይ 100 የብር ታላንትና* አንድ የወርቅ ታላንት ቅጣት ጣለ።+ 34 በተጨማሪም ፈርዖን ኒካዑ የኢዮስያስን ልጅ ኤልያቄምን በአባቱ በኢዮስያስ ምትክ አነገሠው፤ ስሙንም ቀይሮ ኢዮዓቄም አለው፤ ኢዮዓካዝን ግን ወደ ግብፅ ወሰደው፤+ እሱም በመጨረሻ በዚያ ሞተ።+ 35 ኢዮዓቄም ብሩንና ወርቁን ለፈርዖን ሰጠው፤ ይሁንና ፈርዖን የጠየቀውን ብር ለመስጠት በምድሪቱ ላይ ቀረጥ መጣል አስፈልጎት ነበር። እሱም እያንዳንዱ የምድሪቱ ነዋሪ ለፈርዖን ኒካዑ እንዲሰጥ ተገምቶ በተጣለበት ቀረጥ መሠረት ብርና ወርቅ እንዲከፍል አደረገ።
36 ኢዮዓቄም+ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው 25 ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌምም ሆኖ ለ11 ዓመት ገዛ።+ እናቱ ዘቢዳ ትባል ነበር፤ እሷም የሩማ ሰው የሆነው የፐዳያህ ልጅ ነበረች። 37 አባቶቹ እንዳደረጉት+ ሁሉ እሱም በይሖዋ ፊት መጥፎ የሆነውን ነገር አደረገ።+
24 በኢዮዓቄም ዘመን የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነጾር+ ምድሪቱን ወረረ፤ ኢዮዓቄምም ለሦስት ዓመት የእሱ አገልጋይ ሆነ። ሆኖም ሐሳቡን ለውጦ ዓመፀበት። 2 ከዚያም ይሖዋ የከለዳውያንን፣+ የሶርያውያንን፣ የሞዓባውያንንና የአሞናውያንን ወራሪ ቡድኖች ይልክበት ጀመር። ይሖዋ አገልጋዮቹ በሆኑት በነቢያት አማካኝነት በተናገረው ቃል መሠረት+ ይሁዳን እንዲያጠፉ እነዚህን ቡድኖች ይልክባቸው ነበር። 3 ይህ ነገር ይሖዋ ባዘዘው መሠረት በይሁዳ ላይ የደረሰው ይሁዳን ከፊቱ ለማጥፋት ነው፤+ ይህም የሆነው ምናሴ በሠራቸው ኃጢአቶች ሁሉ የተነሳ ነው፤+ 4 ንጹሕ ደም በማፍሰስ ኢየሩሳሌም በንጹሕ ደም እንድትጥለቀለቅ በማድረጉ ነው፤+ ይሖዋም ይቅር ለማለት ፈቃደኛ አልሆነም።+
5 የቀረው የኢዮዓቄም ታሪክ፣ ያደረጋቸው ነገሮች በሙሉ በይሁዳ ነገሥታት ዘመን ስለተፈጸሙት ነገሮች በሚተርከው የታሪክ መጽሐፍ ውስጥ ተጽፈው ይገኙ የለም?+ 6 በመጨረሻም ኢዮዓቄም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤+ በእሱም ምትክ ልጁ ዮአኪን ነገሠ።
7 የባቢሎን ንጉሥ ከግብፅ ደረቅ ወንዝ*+ አንስቶ እስከ ኤፍራጥስ ወንዝ+ ድረስ የሚገኘውን የግብፅን ንጉሥ+ ምድር ሁሉ ወስዶ ስለነበር የግብፅ ንጉሥ ዳግመኛ ከምድሩ ለመውጣት አልደፈረም።
8 ዮአኪን+ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው 18 ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌምም ሆኖ ለሦስት ወር ገዛ።+ እናቱ ነሁሽታ ትባል ነበር፤ እሷም የኢየሩሳሌም ሰው የሆነው የኤልናታን ልጅ ነበረች። 9 አባቱ እንዳደረገው ሁሉ እሱም በይሖዋ ፊት መጥፎ የሆነውን ነገር አደረገ። 10 በዚህ ጊዜ የባቢሎን ንጉሥ የናቡከደነጾር አገልጋዮች በኢየሩሳሌም ላይ ዘመቱ፤ ከተማዋም ተከበበች።+ 11 የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነጾር አገልጋዮቹ ከተማዋን ከበው ሳሉ ወደ ከተማዋ መጣ።
12 የይሁዳ ንጉሥ ዮአኪን ከእናቱ፣ ከአገልጋዮቹ፣ ከመኳንንቱና ከቤተ መንግሥት ባለሥልጣናቱ+ ጋር ሆኖ ወደ ባቢሎን ንጉሥ+ ወጣ፤ የባቢሎንም ንጉሥ በነገሠ በስምንተኛው ዓመት ዮአኪንን ማርኮ ወሰደው።+ 13 ከዚያም በይሖዋ ቤትና በንጉሡ ቤት* የነበሩትን ውድ ዕቃዎች ሁሉ ወሰደ።+ የእስራኤል ንጉሥ የነበረው ሰለሞን ለይሖዋ ቤተ መቅደስ የሠራቸውን የወርቅ ዕቃዎች በሙሉ ሰባበራቸው።+ ይህ የሆነው ይሖዋ አስቀድሞ በተናገረው መሠረት ነው። 14 ኢየሩሳሌምን በሙሉ፣ መኳንንቱን በሙሉ፣+ ኃያላን ተዋጊዎቹን ሁሉ፣ የእጅ ጥበብ ባለሙያዎችንና አንጥረኞችን*+ በአጠቃላይ 10,000 ሰዎችን በግዞት ወሰደ። በጣም ድሃ ከሆኑት የምድሪቱ ነዋሪዎች በስተቀር በዚያ የቀረ አልነበረም።+ 15 በዚህ መንገድ ዮአኪንን+ ወደ ባቢሎን በግዞት ወሰደው፤+ በተጨማሪም የንጉሡን እናት፣ የንጉሡን ሚስቶች፣ የቤተ መንግሥት ባለሥልጣናቱንና በምድሪቱ ውስጥ ያሉትን ታላላቅ ሰዎች ከኢየሩሳሌም ወደ ባቢሎን በግዞት ወሰደ። 16 ደግሞም የባቢሎን ንጉሥ ኃያላን የሆኑና ለጦርነት የሠለጠኑ ወንዶችን በሙሉ ይኸውም 7,000 ተዋጊዎችን እንዲሁም 1,000 የእጅ ጥበብ ባለሙያዎችንና አንጥረኞችን* ወደ ባቢሎን በግዞት ወሰደ። 17 ከዚያም የዮአኪንን አጎት ማታንያህን+ በእሱ ምትክ አነገሠው፤ ስሙንም ቀይሮ ሴዴቅያስ+ አለው።
18 ሴዴቅያስ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው 21 ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌምም ሆኖ ለ11 ዓመት ገዛ። እናቱ ሀሙጣል ትባል ነበር፤+ እሷም የሊብና ሰው የሆነው የኤርምያስ ልጅ ነበረች። 19 ኢዮዓቄም እንዳደረገው ሁሉ እሱም በይሖዋ ፊት መጥፎ የሆነውን ነገር አደረገ።+ 20 እነዚህ ነገሮች በኢየሩሳሌምና በይሁዳ የተፈጸሙት ከይሖዋ ቁጣ የተነሳ ነው፤ በመጨረሻም ከፊቱ አስወገዳቸው።+ ሴዴቅያስም በባቢሎን ንጉሥ ላይ ዓመፀ።+
25 ሴዴቅያስ በነገሠ በዘጠነኛው ዓመት፣ በአሥረኛው ወር፣ ከወሩም በአሥረኛው ቀን የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነጾር+ ሠራዊቱን ሁሉ አስከትሎ በኢየሩሳሌም ላይ ዘመተ።+ በዙሪያዋም ሰፈረ፤ ደግሞም በዙሪያዋ የአፈር ቁልል ቆለለ፤+ 2 ከተማዋም እስከ ንጉሥ ሴዴቅያስ 11ኛ ዓመት ድረስ ተከበበች። 3 በአራተኛው ወር፣ ዘጠነኛ ቀን በከተማዋ ውስጥ ረሃቡ እጅግ ከፋ፤+ በምድሪቱ የሚኖሩትም ሰዎች የሚላስ የሚቀመስ አጡ።+ 4 የከተማዋ ቅጥር ተደረመሰ፤+ ከለዳውያን ከተማዋን ከበው ሳለም ወታደሮቹ ሁሉ በንጉሡ የአትክልት ቦታ አቅራቢያ ባለው መንገድ፣ በሁለቱ ቅጥሮች መካከል በሚገኘው በር በኩል በሌሊት ወጥተው ሸሹ፤ ንጉሡም ወደ አረባ በሚወስደው መንገድ ሄደ።+ 5 ይሁንና የከለዳውያን ሠራዊት ንጉሡን አሳደደ፤ እሱንም በኢያሪኮ በረሃማ ሜዳ ላይ ደረሱበት፤ ወታደሮቹም ሁሉ ጥለውት ተበታተኑ። 6 ከዚያም ንጉሡን ይዘው+ በሪብላ ወደነበረው የባቢሎን ንጉሥ አመጡት፤ ደግሞም ፈረዱበት። 7 የሴዴቅያስን ወንዶች ልጆች ዓይኑ እያየ አረዷቸው፤ ከዚያም ናቡከደነጾር የሴዴቅያስን ዓይን አሳወረ፤ በመዳብ የእግር ብረት አስሮም ወደ ባቢሎን ወሰደው።+
8 በአምስተኛው ወር፣ ከወሩም በሰባተኛው ቀን ይኸውም ንጉሥ ናቡከደነጾር በነገሠ በ19ኛው ዓመት፣ የዘቦች አለቃና የባቢሎን ንጉሥ አገልጋይ የሆነው ናቡዛራዳን+ ወደ ኢየሩሳሌም መጣ።+ 9 እሱም የይሖዋን ቤት፣+ የንጉሡን ቤትና*+ በኢየሩሳሌም የሚገኙ ቤቶችን በሙሉ አቃጠለ፤+ የታዋቂ ሰዎችንም ቤቶች ሁሉ በእሳት አጋየ።+ 10 ከዘቦቹ አለቃ ጋር የነበረው የከለዳውያን ሠራዊት በኢየሩሳሌም ዙሪያ ያለውን ቅጥር አፈረሰ።+ 11 የዘቦች አለቃ የሆነው ናቡዛራዳን በከተማዋ የቀሩትን በሕይወት የተረፉ ሰዎች፣ ከድተው ወደ ባቢሎን ንጉሥ የሄዱትን ሰዎችና የቀረውን ሕዝብ በግዞት ወሰደ።+ 12 ሆኖም የዘቦቹ አለቃ በምድሪቱ ከነበሩት ያጡ የነጡ ድሆች መካከል አንዳንዶቹ የወይን አትክልት ሠራተኞች ሆነው እንዲያገለግሉና የግዳጅ አገልግሎት እንዲሰጡ እዚያው ተዋቸው።+ 13 ከለዳውያኑም የይሖዋን ቤት የመዳብ ዓምዶች+ እንዲሁም በይሖዋ ቤት ውስጥ የነበሩትን የዕቃ ማጓጓዣ ጋሪዎችና+ የመዳብ ባሕር+ ሰባብረው መዳቡን ወደ ባቢሎን አጋዙ።+ 14 በተጨማሪም አመድ ማጠራቀሚያዎቹን፣ አካፋዎቹን፣ የእሳት ማጥፊያዎቹን፣ ጽዋዎቹንና ለቤተ መቅደስ አገልግሎት የሚውሉትን የመዳብ ዕቃዎች ሁሉ ወሰዱ። 15 የዘቦቹ አለቃ ከንጹሕ ወርቅና ብር የተሠሩትን መኮስተሪያዎችና ጎድጓዳ ሳህኖች ወሰደ።+ 16 ንጉሥ ሰለሞን ለይሖዋ ቤት ያሠራቸው ሁለቱ ዓምዶች፣ ባሕሩና የዕቃ ማጓጓዣ ጋሪዎቹ የተሠሩበት መዳብ ከብዛቱ የተነሳ ሊመዘን የሚችል አልነበረም።+ 17 የእያንዳንዱ ዓምድ ቁመት 18 ክንድ* ነበር፤+ በዓምዱ አናት ላይ ያለው ጌጥ ከመዳብ የተሠራ ሲሆን የጌጡ ርዝማኔ ሦስት ክንድ ነበር፤ በጌጡ ዙሪያ ያሉት ሮማኖችና መረቡ በሙሉ ከመዳብ የተሠሩ ነበሩ።+ ሁለተኛው ዓምድና መረቡም ከዚህ ጋር ተመሳሳይ ነበር።
18 በተጨማሪም የዘቦቹ አለቃ የካህናት አለቃ የሆነውን ሰራያህን፣+ ሁለተኛውን ካህን ሶፎንያስንና+ ሦስቱን የበር ጠባቂዎች ወሰዳቸው።+ 19 ደግሞም ከከተማዋ የወታደሮቹ ኃላፊ የሆነን አንድ የቤተ መንግሥት ባለሥልጣን፣ በከተማዋ ውስጥ የነበሩትን አምስቱን የንጉሡ የቅርብ ሰዎች፣ የምድሪቱን ሕዝብ የሚያሰልፈውን የሠራዊቱን አለቃ ጸሐፊ እንዲሁም ከተማዋ ውስጥ የተገኙትን በምድሪቱ የሚኖሩ 60 ተራ ሰዎች ወሰደ። 20 የዘቦች አለቃ የሆነው ናቡዛራዳን+ እነዚህን ሰዎች ይዞ በሪብላ ወዳለው ወደ ባቢሎን ንጉሥ አመጣቸው።+ 21 የባቢሎን ንጉሥ በሃማት+ ምድር ባለችው በሪብላ ሰዎቹን መትቶ ገደላቸው። በዚህ መንገድ ይሁዳ ከምድሩ በግዞት ተወሰደ።+
22 የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነጾር በይሁዳ ምድር በተዋቸው ሰዎች ላይ የሳፋን+ ልጅ፣ የአኪቃም+ ልጅ የሆነውን ጎዶልያስን+ አለቃ አድርጎ ሾመው።+ 23 የሠራዊቱ አለቆች በሙሉና አብረዋቸው ያሉት ሰዎች የባቢሎን ንጉሥ ጎዶልያስን አለቃ አድርጎ እንደሾመው ሲሰሙ ወዲያውኑ በምጽጳ ወደሚገኘው ወደ ጎዶልያስ መጡ። እነሱም የነታንያህ ልጅ እስማኤል፣ የቃሬሃ ልጅ ዮሃናን፣ የነጦፋዊው የታንሁመት ልጅ ሰራያህና የማአካታዊው ልጅ ያአዛንያህ እንዲሁም አብረዋቸው የነበሩት ሰዎች ናቸው።+ 24 ጎዶልያስ ለእነሱና አብረዋቸው ለነበሩት ሰዎች “የከለዳውያን አገልጋይ መሆን አያስፈራችሁ። በምድሪቱ ላይ ኑሩ፤ የባቢሎንንም ንጉሥ አገልግሉ፤ መልካምም ይሆንላችኋል”+ ሲል ማለላቸው።
25 በሰባተኛውም ወር፣ ከንጉሣውያን ቤተሰብ* የሆነው የኤሊሻማ ልጅ፣ የነታንያህ ልጅ እስማኤል+ ከሌሎች አሥር ሰዎች ጋር መጣ፤ እነሱም ጎዶልያስን መቱት፤ እሱም በምጽጳ አብረውት ከነበሩት አይሁዳውያንና ከለዳውያን ጋር ሞተ።+ 26 ከዚያ በኋላ የሠራዊቱን አለቆች ጨምሮ ትልቅ ትንሽ ሳይባል ሕዝቡ ሁሉ ተነስተው ወደ ግብፅ ሄዱ፤+ ከለዳውያንን ፈርተው ነበርና።+
27 የባቢሎን ንጉሥ ኤዊልሜሮዳክ በነገሠበት ዓመት የይሁዳን ንጉሥ ዮአኪንን+ ከእስር ቤት ፈታው፤* ይህም የሆነው የይሁዳ ንጉሥ ዮአኪን በግዞት በተወሰደ በ37ኛው ዓመት፣ በ12ኛው ወር፣ ከወሩም በ27ኛው ቀን ነበር።+ 28 በርኅራኄም አናገረው፤ ዙፋኑንም በባቢሎን ከእሱ ጋር ከነበሩት ከሌሎች ነገሥታት ዙፋን ይበልጥ ከፍ ከፍ አደረገለት። 29 በመሆኑም ዮአኪን የእስር ቤት ልብሱን አወለቀ፤ በሕይወት ዘመኑም ሁሉ በቋሚነት ከንጉሡ ማዕድ ይመገብ ነበር። 30 ንጉሡም ለዮአኪን በሕይወት ዘመኑ ሁሉ ሳያቋርጥ ቀለቡን በየዕለቱ ይሰጠው ነበር።
“አምላኬ ይሖዋ ነው” የሚል ትርጉም አለው።
ወይም “የእኔም ነፍስ ሆነች የእነዚህ 50 አገልጋዮችህ ነፍስ በፊትህ የከበረች ትሁን።”
የአካዝያስን ወንድም ያመለክታል።
ወይም “በሕያው ነፍስህ።”
“የነቢያት ልጆች” የሚለው አገላለጽ ነቢያት ትምህርት የሚቀስሙበትን ትምህርት ቤት ወይም የነቢያትን ማኅበር የሚያመለክት ሳይሆን አይቀርም።
ወይም “በሕያው ነፍስህ።”
ወይም “በሕያው ነፍስህ።”
ወይም “ሁለት እጅ።”
ወይም “ነፋስ።”
“ውርጃ እያስከተለች ነው” ማለትም ሊሆን ይችላል።
“ውርጃ እንድታስከትል” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “የኤልያስ አገልጋይ የነበረው።”
ቃል በቃል “ፊቱ በምቆመውና።”
ወይም “አንድ ሙዚቀኛ።”
ወይም “ደረቅ ወንዝ።”
ወይም “ደረቅ ወንዝ።”
ወይም “መታጠቂያ የታጠቁ።”
ወይም “ነፍሷ በውስጧ እጅግ ተመራለች።”
ወይም “በሕያው ነፍስህ።”
ወይም “መዳን ያስገኘው።”
ወይም “የቆዳ በሽታ የያዘው።”
ንዕማንን የሚያመለክት ሳይሆን አይቀርም።
አንድ ታላንት 34.2 ኪሎ ግራም ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
ቃል በቃል “በረከት።”
ቃል በቃል “ፊቱ በምቆመውና።”
ወይም “ቤተ መቅደስ።”
በሰማርያ የሚገኝ ቦታ ሲሆን ኮረብታ ወይም ምሽግ ሊሆን ይችላል።
ወይም “ከአንድ ወይም ከሁለት ጊዜ በላይ።”
ቃል በቃል “የሶርያን ንጉሥ ልብ።”
አንድ ቃብ 1.22 ሊትር ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
ወይም “ገበያ።”
አንድ ሲህ 7.33 ሊትር ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
አንድ ሰቅል 11.4 ግራም ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
ቃል በቃል “ይህ ቃል።”
ወይም “ነፍሳቸውን።”
ቃል በቃል “እንዲህ ያለ ቃል።”
ቃል በቃል “ሴት ልጅ።”
ወይም “ታሞ።”
ቃል በቃል “ግንብ ላይ የሚሸናውን ሁሉ።” ወንዶችን የሚያናንቅ የዕብራይስጥ አገላለጽ ነው።
ወይም “ነፍሳችሁ ከተስማማች።”
ቃል በቃል “ወንድ ልጅ።”
ቃል በቃል “ወደ አክዓብ ሞግዚቶች።”
ወይም “ቅን የሆነውን።”
ቃል በቃል “የቤቱ ኃላፊ።”
ወይም “ጻድቃን።”
ቃል በቃል “መሬት ጠብ እንደማይል።”
የሚሸለቱ በጎች የሚቆዩበትን ቦታ የሚያመለክት ይመስላል።
ወይም “የእመቤቲቱን።”
ወይም “ባርኮት።”
ቃል በቃል “በቅንነት።”
ወይም “ለይሖዋ ያለኝን ቅንዓት።”
ቃል በቃል “ቀድሱ።”
ወይም “ቤተ መቅደስ።”
ወይም “የእናንተ ነፍስ በዚያ ሰው ነፍስ።”
ቃል በቃል “ሯጮቹንና።”
ቃል በቃል “ከተማም።” እንደ ምሽግ ያለን ግንብ የሚያመለክት ሊሆን ይችላል።
ወይም “መቀናነስ።”
ወይም “ደረቅ ወንዝ።”
ቃል በቃል “የገዛባቸው ቀናት።”
ቃል በቃል “የመንግሥቱን ዘር።”
ቃል በቃል “ሯጮቹን።”
ወይም “ቃል ኪዳን።”
ወይም “ቤተ መንግሥት።”
ቃል በቃል “በሚወጣበትም ሆነ በሚገባበት ጊዜ።”
ወይም “ዘውዱን።”
የአምላክ ሕግ የሰፈረበት ጥቅልል ሊሆን ይችላል።
ወይም “ቤተ መንግሥት።”
ወይም “ቤተ መቅደስ።”
ወይም “ቤተ መንግሥት መጡ።”
ወይም “ነፍስ።”
ወይም “ከሚያውቋቸው ሰዎች።”
ወይም “ያሉትን ስንጥቆች።”
ወይም “ከረጢቶች ውስጥ ይጨምሩታል።” ቃል በቃል “ያስሩታል።”
ቃል በቃል “በኢየሩሳሌም ላይ ለመውጣት ፊቱን አቀና።”
ወይም “ቤተ መንግሥት።”
ወይም “በቤትሚሎ።”
ተረጋግተው በሰላም መኖራቸውን ያመለክታል።
ቃል በቃል “እሱ በዚያ ተመላለሰ።”
የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ቃል በቃል “በእነዚህ ኃጢአቶች መመላለሱን።”
ዳግማዊ ኢዮርብዓምን ያመለክታል።
ወይም “የማዳን።”
ወይም “የማዳን።”
ወይም “ታሸንፋቸዋለህ።”
ቃል በቃል “በዓመቱ መግቢያ።” በበልግ ወቅት ሊሆን ይችላል።
ወይም “አሸነፈው።”
ወይም “ፊት ለፊት እንገናኝ።”
ወይም “በቤተ መንግሥትህ።”
ቃል በቃል “ወደየድንኳናቸው።”
ወደ 178 ሜትር ገደማ ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
ወይም “ቤተ መንግሥት።”
ዳግማዊ ኢዮርብዓምን የሚያመለክት ነው።
“ይሖዋ ረዳ” የሚል ትርጉም አለው። በ2ነገ 15:13፣ 2ዜና 26:1-23፣ ኢሳ 6:1 እና ዘካ 14:5 ላይ ዖዝያ ተብሎም ተጠርቷል።
አባቱን አሜስያስን ያመለክታል።
ወይም “ከሃማት መግቢያ።”
ጨው ባሕርን ወይም ሙት ባሕርን ያመለክታል።
ዳግማዊ ኢዮርብዓምን የሚያመለክት ነው።
“ይሖዋ ረዳ” የሚል ትርጉም አለው። በ2ነገ 15:13፣ 2ዜና 26:1-23፣ ኢሳ 6:1 እና ዘካ 14:5 ላይ ዖዝያ ተብሎም ተጠርቷል።
ወይም “በቤተ መንግሥቱ።”
አንድ ታላንት 34.2 ኪሎ ግራም ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
አንድ ሰቅል 11.4 ግራም ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
ወይም “ቤተ መንግሥት።”
ወይም “የይሁዳን ሰዎች።”
ወይም “ቤተ መንግሥት።”
“ይሖዋ ያበረታል” የሚል ትርጉም አለው።
ቃል በቃል “ፈሩ።”
ጥቂት ሰዎች የሚኖሩባቸውን ቦታዎችም ሆነ ሰው የሚበዛባቸውን ቦታዎች ሁሉ ያመለክታል።
የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
እዚህ ላይ የገባው የዕብራይስጥ ቃል “ፋንድያ” ከሚለው ቃል ጋር ዝምድና ሊኖረው የሚችል ሲሆን ንቀትን ለማመልከት ተሠርቶበታል።
ቃል በቃል “እንደ አባቶቻቸው አንገት እነሱም አንገታቸውን አደነደኑ።”
ወይም “ቀልጠው የተሠሩ ሁለት የጥጃ ሐውልቶችን።”
የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ቃል በቃል “ሸጡ።”
ወይም “ይሖዋን አያመልኩም።”
ወይም “የዚያን ምድር አምላክ ሃይማኖታዊ ልማዶች።”
ወይም “ማምለክ።”
ወይም “አማልክት።”
ወይም “በነበሯቸው ሃይማኖታዊ ልማዶች መሠረት።”
ወይም “በፊት የነበሯቸውን ሃይማኖታዊ ልማዶች በመከተል።”
ቃል በቃል “የሚፈራ።”
ወይም “በፊት የነበሯቸውን ሃይማኖታዊ ልማዶች በመከተል።”
አቢያህ የሚለው ስም አጭር መጠሪያ ነው።
የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ወይም “ነሑሽታን።”
ጥቂት ሰዎች የሚኖሩባቸውን ቦታዎችም ሆነ ሰው የሚበዛባቸውን ቦታዎች ሁሉ ያመለክታል።
አንድ ታላንት 34.2 ኪሎ ግራም ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
ወይም “ቤተ መንግሥት።”
በወርቅ የተለበጡ መሆናቸውን ያመለክታል።
ቃል በቃል “ቆርጦ።”
ወይም “አዛዡን።”
ወይም “የቤተ መንግሥቱን ዋና ባለሥልጣንና።”
ወይም “የመጠጥ አሳላፊዎቹን አለቃ።”
ወይም “የቤተ መንግሥቱ።”
ወይም “በሶርያ።”
ቃል በቃል “ከእኔ ጋር ባርኩ፤ እንዲሁም ወደ እኔ ውጡ።”
ወይም “የቤተ መንግሥቱ።”
ወይም “የቤተ መንግሥቱ።”
ወይም “የስድብና።”
ቃል በቃል “ልጁ ወደ ማህፀኑ አፍ መጥቶ።”
ቃል በቃል “እነሆ፣ መንፈስ አስገባበታለሁ።”
ቃል በቃል “ደብዳቤውን።”
“በኪሩቤል መካከል” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “የአባይንም የመስኖ ቦዮች።”
ቃል በቃል “የተደረገ።”
ወይም “ሠርቻለሁ።”
ለሕዝቅያስ የተነገረ ነው።
ሰብል በሚሰበሰብበት ጊዜ ማሳው ላይ ረግፎ እንደገና የሚበቅለውን እህል ያመለክታል።
ወይም “ቤተ መቅደስ።”
ቃል በቃል “በቀኖችህ።”
እነዚህ ደረጃዎች በፀሐይ ጥላ አማካኝነት ሰዓትን ለመቁጠር ያገለግሉ የነበረ ይመስላል።
ወይም “መልእክተኞቹን ሰማቸው።”
ወይም “በቤተ መንግሥቱም።”
ወይም “በቤተ መንግሥትህ።”
ወይም “በቤተ መንግሥቴ።”
ወይም “በቤተ መንግሥትህ።”
ቃል በቃል “በቀኖቼ።”
ወይም “እውነት።”
የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
እዚህ ላይ የገባው የዕብራይስጥ ቃል “ፋንድያ” ከሚለው ቃል ጋር ዝምድና ሊኖረው የሚችል ሲሆን ንቀትን ለማመልከት ተሠርቶበታል።
ቃል በቃል “ጆሮ የሚነዝር።”
ወይም “ቱምቢ።”
ወይም “ያሉትን ስንጥቆች።”
ቃል በቃል “ልብህ ስለለሰለሰ።”
ይህ ሞትን የሚያመለክት ቅኔያዊ አነጋገር ነው።
የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ወይም “ቃል ኪዳኑን አደሰ።”
የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ግብረ ሰዶማውያን ሆነው የሴት ዓይነት ሚና ያላቸውን ወንዶች ያመለክታል።
የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
የቃላት መፍቻው ላይ “ገሃነም” የሚለውን ተመልከት።
ወይም “መመገቢያ አዳራሽ።”
የደብረ ዘይት ተራራ ሲሆን በተለይ ደግሞ የበደል ተራራ ተብሎም የሚጠራውን የተራራውን ደቡባዊ ጫፍ ያመለክታል።
ቃል በቃል “በስተ ቀኝ።” አንድ ሰው ፊቱን ወደ ምሥራቅ በሚያዞርበት ጊዜ ቦታው በስተ ደቡብ እንደሚገኝ ያመለክታል።
የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ወይም “የማለፍን በዓል።” የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ወይም “የቤት ውስጥ አማልክትን፤ ጣዖታትን።”
እዚህ ላይ የገባው የዕብራይስጥ ቃል “ፋንድያ” ከሚለው ቃል ጋር ዝምድና ሊኖረው የሚችል ሲሆን ንቀትን ለማመልከት ተሠርቶበታል።
የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
አንድ ታላንት 34.2 ኪሎ ግራም ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ወይም “ቤተ መንግሥት።”
“ምሽግ የሚገነቡ ሰዎችን” ማለትም ሊሆን ይችላል።
“ምሽግ የሚገነቡ ሰዎችን” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “ቤተ መንግሥትና።”
አንድ ክንድ 44.5 ሴንቲ ሜትር ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
ቃል በቃል “የመንግሥቱ ዘር።”
ቃል በቃል “የዮአኪንን ራስ ቀና አደረገው።”