የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
የኢትዮጵያ ምልክት ቋንቋ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • nwt 1 ሳሙኤል 1:1-31:13
  • 1 ሳሙኤል

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • 1 ሳሙኤል
  • አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ
አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ
1 ሳሙኤል

አንደኛ ሳሙኤል

1 በኤፍሬም+ ተራራማ አካባቢ በምትገኘው በራማታይምጾፊም+ የሚኖር ሕልቃና+ የተባለ አንድ ሰው ነበር፤ ይህ ሰው ኤፍሬማዊ ሲሆን የጹፍ ልጅ፣ የቶሁ ልጅ፣ የኤሊሁ ልጅ፣ የየሮሃም ልጅ ነበር። 2 እሱም ሁለት ሚስቶች ነበሩት፤ የአንደኛዋ ስም ሐና ሲሆን የሌላኛዋ ደግሞ ፍናና ነበር። ፍናና ልጆች ነበሯት፤ ሐና ግን ምንም ልጅ አልነበራትም። 3 ያም ሰው አምልኮ ለማቅረብና* ለሠራዊት ጌታ ለይሖዋ መሥዋዕት ለመሠዋት በየዓመቱ ከከተማው ወደ ሴሎ ይወጣ ነበር።+ በዚያም ሁለቱ የኤሊ ልጆች ሆፍኒ እና ፊንሃስ+ ለይሖዋ ካህናት ሆነው ያገለግሉ ነበር።+

4 አንድ ቀን ሕልቃና መሥዋዕት ሲያቀርብ ለሚስቱ ለፍናና እንዲሁም ለወንዶች ልጆቿና ለሴቶች ልጆቿ በሙሉ ድርሻቸውን ሰጣቸው፤+ 5 ሆኖም ሐናን ይወዳት ስለነበር ልዩ የሆነ ድርሻ ሰጣት፤ ይሁንና ይሖዋ ለሐና ልጅ አልሰጣትም ነበር።* 6 በተጨማሪም ይሖዋ ልጅ ስላልሰጣት ጣውንቷ እሷን ለማበሳጨት ዘወትር ትሳለቅባት ነበር። 7 እሷም በየዓመቱ እንዲህ ታደርግባት ነበር፤ ሐና ወደ ይሖዋ ቤት+ በወጣች ቁጥር፣ እስክታለቅስና መብላት እስኪያቅታት ድረስ ጣውንቷ ትሳለቅባት ነበር። 8 ባሏ ሕልቃና ግን “ሐና፣ ለምን ታለቅሻለሽ? ለምንስ አትበይም? ልብሽስ ለምን ያዝናል? ከአሥር ወንዶች ልጆች እኔ አልበልጥብሽም?” አላት።

9 ከዚያም ሐና በሴሎ ከበሉና ከጠጡ በኋላ ተነሳች። በዚህ ጊዜ ካህኑ ኤሊ በይሖዋ ቤተ መቅደስ*+ መቃን አጠገብ ወንበር ላይ ተቀምጦ ነበር። 10 እሷም በጣም ተማርራ* ነበር፤ ስቅስቅ ብላም እያለቀሰች ወደ ይሖዋ ትጸልይ ጀመር።+ 11 እንዲህም ስትል ተሳለች፦ “የሠራዊት ጌታ ይሖዋ ሆይ፣ አገልጋይህ እየደረሰባት ያለውን መከራ ተመልክተህ ብታስበኝና አገልጋይህን ሳትረሳት ወንድ ልጅ ብትሰጣት+ በሕይወት ዘመኑ ሁሉ ለይሖዋ እሰጠዋለሁ፤ ራሱንም ምላጭ አይነካውም።”+

12 ሐና በይሖዋ ፊት ለረጅም ሰዓት ስትጸልይ ኤሊ አፏን ይመለከት ነበር። 13 ሐና የምትናገረው በልቧ ነበር፤ በመሆኑም ከንፈሯ ሲንቀጠቀጥ ቢታይም ድምፅዋ አይሰማም ነበር። በመሆኑም ኤሊ የሰከረች መሰለው። 14 ስለዚህ “ስካሩ የማይለቅሽ እስከ መቼ ነው? የወይን ጠጅሽን መጠጣት ተዪ” አላት። 15 ሐናም መልሳ እንዲህ አለች፦ “አልሰከርኩም ጌታዬ! እኔ ብዙ ጭንቀት ያለብኝ ሴት* ነኝ፤ የወይን ጠጅም ሆነ ሌላ የሚያሰክር መጠጥ አልጠጣሁም፤ ይልቅስ ነፍሴን* በይሖዋ ፊት እያፈሰስኩ ነው።+ 16 እኔ እስካሁን ድረስ እየተናገርኩ ያለሁት በውስጤ ካለው ብሶትና ጭንቀት የተነሳ ስለሆነ አገልጋይህን እንደማትረባ ሴት አትቁጠራት።” 17 ከዚያም ኤሊ “በሰላም ሂጂ፤ የእስራኤል አምላክ የለመንሽውን ነገር ይስጥሽ” አላት።+ 18 እሷም “አገልጋይህ በፊትህ ሞገስ ታግኝ” አለችው። ከዚያም ተነስታ ሄደች፤ ምግብም በላች፤ ዳግመኛም በፊቷ ላይ ሐዘን አልታየም።

19 እነሱም በማለዳ ተነስተው በይሖዋ ፊት ሰገዱ፤ ከዚያም በራማ+ ወደሚገኘው ቤታቸው ተመለሱ። ሕልቃናም ከሚስቱ ከሐና ጋር የፆታ ግንኙነት ፈጸመ፤ ይሖዋም አሰባት።+ 20 ከዚያም በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ* ሐና ፀንሳ ወንድ ልጅ ወለደች፤ እሷም “ከይሖዋ የለመንኩት ነው” በማለት ስሙን+ ሳሙኤል* አለችው።

21 ከጊዜ በኋላም ሕልቃና ለይሖዋ ዓመታዊውን መሥዋዕት ለመሠዋትና+ የስእለት መባውን ለማቅረብ ቤተሰቡን ሁሉ ይዞ ወጣ። 22 ሐና ግን አልወጣችም፤+ ምክንያቱም ለባሏ “ሕፃኑ ጡት እንደጣለ አመጣዋለሁ፤ እሱም ይሖዋ ፊት ይቀርባል፤ ዕድሜውንም ሙሉ በዚያ ይኖራል” በማለት ነግራው ነበር።+ 23 ባሏ ሕልቃናም “መልካም መስሎ የታየሽን አድርጊ። ልጁን ጡት እስክታስጥዪው ድረስ ቤት ሁኚ። ይሖዋም ያልሽውን ይፈጽም” ብሏት ነበር። በመሆኑም ሐና ቤት ተቀመጠች፤ ልጇንም ጡት እስክታስጥለው ድረስ ተንከባከበችው።

24 እሷም ልክ ልጁን ጡት እንዳስጣለችው ከልጁ ጋር የሦስት ዓመት ወይፈን፣ አንድ የኢፍ መስፈሪያ* ዱቄትና አንድ እንስራ የወይን ጠጅ ይዛ ወጣች፤+ ልጁንም በሴሎ+ ወደሚገኘው ወደ ይሖዋ ቤት ይዛው መጣች። 25 እነሱም ወይፈኑን ካረዱ በኋላ ልጁን ወደ ኤሊ አመጡት። 26 እሷም እንዲህ አለች፦ “ጌታዬ ሆይ፣ በሕያውነትህ* እምላለሁ፤ ጌታዬ ሆይ፣ እኔ ወደ ይሖዋ ለመጸለይ ከአንተ ጋር እዚህ ቦታ ቆሜ የነበርኩት ሴት ነኝ።+ 27 ይህን ልጅ እንዲሰጠኝ ጸልዬ ነበር፤ ይሖዋም የለመንኩትን ሰጠኝ።+ 28 እኔ ደግሞ በበኩሌ ልጁን ለይሖዋ እሰጠዋለሁ።* በሕይወት ዘመኑም ሁሉ ለይሖዋ የተሰጠ ይሆናል።”

እሱም* በዚያ ለይሖዋ ሰገደ።

2 ከዚያም ሐና እንዲህ ስትል ጸለየች፦

“ልቤ በይሖዋ ሐሴት አደረገ፤+

ቀንዴም* በይሖዋ ከፍ ከፍ አለ።

አፌ በጠላቶቼ ላይ ተከፈተ፣

በማዳን ሥራዎችህ ደስ ብሎኛልና።

 2 እንደ ይሖዋ ያለ ቅዱስ ማንም የለም፣

ያለአንተ ማንም የለም፤+

እንደ አምላካችን ያለ ዓለት የለም።+

 3 በትዕቢት መናገራችሁን ተዉ፤

የእብሪት ቃል ከአፋችሁ አይውጣ፣

ይሖዋ ሁሉን የሚያውቅ አምላክ ነውና፣+

ተግባርን ሁሉ በትክክል የሚመዝን እሱ ነው።

 4 የኃያላን ቀስቶች ተሰባብረዋል፣

የተንገዳገዱት ግን ብርታት አግኝተዋል።+

 5 ጠግበው የነበሩት ለምግብ ሲሉ ተቀጥረው ለመሥራት ተገደዱ፤

የተራቡት ግን ከእንግዲህ አይራቡም።+

መሃን የነበረችው ሴት ሰባት ልጆች ወለደች፤+

ብዙ ወንዶች ልጆች የነበሯት ግን ብቻዋን ቀረች።*

 6 ይሖዋ ይገድላል፤ ሕይወትንም ያድናል፤*

ወደ መቃብር* ያወርዳል፤ ከዚያም ያወጣል።+

 7 ይሖዋ ያደኸያል፤ እንዲሁም ያበለጽጋል፤+

እሱ ያዋርዳል፤ ከፍ ከፍም ያደርጋል።+

 8 ችግረኛውን ከአቧራ ላይ ያነሳል፤

ድሃውንም ከአመድ ቁልል* ላይ ያነሳል፤+

ከመኳንንትም ጋር ያስቀምጣቸዋል፤

የክብር ወንበርም ይሰጣቸዋል።

የምድር ምሰሶዎች የይሖዋ ናቸው፤+

ፍሬያማ የሆነችውን ምድር በእነሱ ላይ አስቀምጧል።

 9 እሱ የታማኞቹን እርምጃ ይጠብቃል፤+

ክፉዎች ግን በጨለማ ውስጥ ጸጥ እንዲሉ ይደረጋሉ፤+

ሰው የበላይ የሚሆነው በኃይሉ አይደለምና።+

10 ይሖዋ ከእሱ ጋር የሚዋጉትን ያደቃቸዋል፤*+

እሱም ከሰማይ ነጎድጓድ ይለቅባቸዋል።+

ይሖዋ እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ይፈርዳል፤+

ለንጉሡ ኃይል ይሰጣል፤+

የእሱ ቅቡዕ የሆነውንም ቀንዱን* ከፍ ከፍ ያደርጋል።”+

11 ከዚያም ሕልቃና በራማ ወደሚገኘው ቤቱ ሄደ፤ ልጁ ግን በካህኑ በኤሊ ፊት የይሖዋ አገልጋይ ሆነ።*+

12 የኤሊ ወንዶች ልጆች ምግባረ ብልሹ ነበሩ፤+ ለይሖዋ አክብሮት አልነበራቸውም። 13 ከሕዝቡ ላይ የካህናቱን ድርሻ በሚቀበሉበት ጊዜ እንዲህ ያደርጉ ነበር፦+ ማንኛውም ሰው መሥዋዕት በሚያቀርብበት ጊዜ ሥጋው እየተቀቀለ ሳለ የካህኑ አገልጋይ ሦስት ጣት ያለው ሹካ ይዞ ይመጣና 14 ሹካውን ወደ ሰታቴው ወይም ወደ ምንቸቱ ወይም ወደ አፍላሉ* ወይም ወደ ባለ አንድ ጆሮው ድስት ይከተዋል። መንሹ ይዞ የሚወጣውንም ካህኑ ለራሱ ይወስድ ነበር። ወደ ሴሎ በሚመጡት እስራኤላውያን ሁሉ ላይ እንዲሁ ያደርጉ ነበር። 15 ሌላው ቀርቶ መሥዋዕቱን የሚያቀርበው ሰው ስቡን ከማቃጠሉ+ በፊት የካህኑ አገልጋይ መጥቶ “ለካህኑ የሚጠበስ ሥጋ ስጠው። ጥሬ ሥጋ ብቻ እንጂ የተቀቀለ ሥጋ ከአንተ አይቀበልም” ይለው ነበር። 16 ሰውየውም “በመጀመሪያ ስቡን ያቃጥሉ፤+ ከዚያ በኋላ የፈለግከውን* ውሰድ” ይለው ነበር። እሱ ግን “አይሆንም፤ አሁኑኑ ስጠኝ፤ ካልሆነ ግን ነጥቄ እወስዳለሁ!” ይለዋል። 17 ሰዎቹ የይሖዋን መባ ያቃልሉ ስለነበር የአገልጋዮቹ ኃጢአት በይሖዋ ፊት እጅግ ታላቅ ሆነ።+

18 በዚህ ጊዜ ሳሙኤል ገና አንድ ፍሬ ልጅ የነበረ ቢሆንም ከበፍታ የተሠራ ኤፉድ+ ለብሶ* በይሖዋ ፊት ያገለግል ነበር።+ 19 እናቱም ዓመታዊውን መሥዋዕት ለማቅረብ ከባሏ ጋር ስትወጣ እጅጌ የሌለው ትንሽ ቀሚስ እየሠራች በየዓመቱ ታመጣለት ነበር።+ 20 ኤሊም ሕልቃናንና ሚስቱን እንዲህ ሲል ባረካቸው፦ “ለይሖዋ በተሰጠው* ልጅ ምትክ ይሖዋ ከዚህች ሚስትህ ልጅ ይስጥህ” አለው።+ እነሱም ወደ ቤታቸው ተመለሱ። 21 ይሖዋም ሐናን አሰባት፤ እሷም ፀነሰች፤+ ሌሎች ሦስት ወንዶችና ሁለት ሴቶች ልጆችም ወለደች። ብላቴናው ሳሙኤልም በይሖዋ ፊት እያደገ ሄደ።+

22 በዚህ ጊዜ ኤሊ በጣም አርጅቶ ነበር፤ ሆኖም ወንዶች ልጆቹ በሁሉም እስራኤላውያን ላይ ምን እንደሚያደርጉ+ እንዲሁም በመገናኛ ድንኳኑ መግቢያ ላይ ከሚያገለግሉት ሴቶች ጋር እንደሚተኙ+ አንድም ሳይቀር ሰምቶ ነበር። 23 እሱም እንዲህ ይላቸው ነበር፦ “እንዲህ ያለ ነገር ለምን ታደርጋላችሁ? ሰዎች ሁሉ ስለ እናንተ መጥፎ ነገር ሲናገሩ እሰማለሁ። 24 ልጆቼ፣ ትክክል አይደላችሁም፤ በይሖዋ ሕዝቦች መካከል ሲናፈስ የምሰማው ወሬ ጥሩ አይደለም። 25 አንድ ሰው ሌላውን ቢበድል ሌላ ሰው ይሖዋን ይለምንለት ይሆናል፤* ሆኖም አንድ ሰው ይሖዋን ቢበድል+ ማን ሊጸልይለት ይችላል?” እነሱ ግን የአባታቸውን ቃል ለመስማት ፈቃደኞች አልሆኑም፤ ምክንያቱም ይሖዋ ሊገድላቸው ወስኖ ነበር።+ 26 ይህ በእንዲህ እንዳለ ብላቴናው ሳሙኤል በይሖዋም ሆነ በሰዎች ፊት በአካል እያደገና ይበልጥ ሞገስ እያገኘ ሄደ።+

27 አንድ የአምላክ ሰው ወደ ኤሊ መጥቶ እንዲህ አለው፦ “ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘የአባትህ ቤት በግብፅ በፈርዖን ቤት በባርነት ያገለግል በነበረበት ጊዜ ራሴን በይፋ ገልጬለት አልነበረም?+ 28 ካህን ሆኖ እንዲያገለግለኝ፣ መሥዋዕት ለማቅረብ ወደ መሠዊያዬ እንዲወጣ፣+ ዕጣን እንዲያጥንና* በፊቴ ኤፉድ እንዲለብስ ከእስራኤል ነገዶች ሁሉ መካከል ተመርጦ ነበር፤+ እኔም እስራኤላውያን* በእሳት የሚያቀርቧቸውን መባዎች በሙሉ ለአባትህ ቤት ሰጠሁ።+ 29 ታዲያ እናንተ በማደሪያዬ እንዲቀርብ ያዘዝኩትን መሥዋዕቴንና መባዬን የናቃችሁት* ለምንድን ነው?+ ሕዝቤ እስራኤል ከሚያመጣው ከእያንዳንዱ መባ ላይ ምርጡን ወስዳችሁ ራሳችሁን በማደለብ ከእኔ ይልቅ ልጆችህን ያከበርከው ለምንድን ነው?+

30 “‘ስለዚህ የእስራኤል አምላክ የይሖዋ ቃል እንዲህ ይላል፦ “የአንተ ቤትና የአባትህ ቤት ምንጊዜም በፊቴ እንደሚሄዱ ተናግሬ ነበር።”+ አሁን ግን ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “ይህ ፈጽሞ የማላስበው ነገር ነው፤ ምክንያቱም የሚያከብሩኝን አከብራለሁ፤+ የሚንቁኝ ግን ይናቃሉ።” 31 በቤትህ እስከ ሽምግልና ድረስ በሕይወት የሚቆይ ሰው እንዳይኖር የአንተንም ሆነ የአባትህን ቤት ብርታት* የምቆርጥበት ቀን ይመጣል።+ 32 ለእስራኤል በተደረገው ብዙ መልካም ነገር መካከል በማደሪያዬ ውስጥ ተቀናቃኝ ታያለህ፤+ በቤትህም ዳግመኛ አረጋዊ የሚባል አይገኝም። 33 በመሠዊያዬ ፊት እንዲያገለግል የምተወው የአንተ የሆነ ሰው ዓይኖችህ እንዲፈዙና ለሐዘን እንድትዳረግ* ያደርጋል፤ ከቤትህ ሰዎች መካከል ግን አብዛኞቹ በሰዎች ሰይፍ ይሞታሉ።+ 34 በሁለቱ ልጆችህ በሆፍኒ እና በፊንሃስ ላይ የሚደርሰው ነገር ምልክት ይሆንሃል፦ ሁለቱም በአንድ ቀን ይሞታሉ።+ 35 ከዚያም ለራሴ ታማኝ የሆነ ካህን አስነሳለሁ።+ እሱም ከልቤ ፍላጎት* ጋር የሚስማማ ተግባር ይፈጽማል፤ እኔም ዘላቂ የሆነ ቤት እሠራለታለሁ፤ እሱም እኔ በቀባሁት ፊት ሁልጊዜ ይሄዳል። 36 ከቤትህ የሚተርፍ ሰው ቢኖር የሚከፈለው ገንዘብና ቁራሽ ዳቦ ለማግኘት ሲል መጥቶ ይሰግድለታል፤ ከዚያም “እባክህ፣ ቁራሽ ዳቦ እንዳገኝ በማንኛውም የክህነት ሥራ ላይ መድበኝ” ይላል።’”+

3 ይህ በእንዲህ እንዳለ ብላቴናው ሳሙኤል በኤሊ ፊት ይሖዋን ያገለግል ነበር፤+ ይሁን እንጂ በዚያ ዘመን ከይሖዋ የሚመጣ ቃል ብርቅ ነበር፤ ራእይ+ ማየትም ቢሆን ብዙ የተለመደ አልነበረም።

2 አንድ ቀን ኤሊ የተለመደው ቦታው ላይ ተኝቶ ነበር፤ ዓይኖቹ ስለደከሙ ማየት ተስኖታል።+ 3 የአምላክም መብራት+ ገና አልጠፋም፤ ሳሙኤልም የአምላክ ታቦት ባለበት የይሖዋ ቤተ መቅደስ*+ ውስጥ ተኝቶ ነበር። 4 ከዚያም ይሖዋ ሳሙኤልን ጠራው። እሱም “አቤት” አለ። 5 ወደ ኤሊም እየሮጠ ሄዶ “አቤት፣ ጠራኸኝ?” አለው። እሱ ግን “አይ፣ አልጠራሁህም። ተመልሰህ ተኛ” አለው። በመሆኑም ሄዶ ተኛ። 6 ይሖዋም እንደገና “ሳሙኤል!” ሲል ጠራው። በዚህ ጊዜ ሳሙኤል ተነስቶ ወደ ኤሊ በመሄድ “አቤት፣ ጠራኸኝ?” አለው። እሱ ግን “ኧረ አልጠራሁህም ልጄ። ተመልሰህ ተኛ” አለው። 7 (ሳሙኤል ይሖዋን ገና አላወቀውም ነበር፤ የይሖዋም ቃል ቢሆን ገና አልተገለጠለትም ነበር።)+ 8 በመሆኑም ይሖዋ ለሦስተኛ ጊዜ እንደገና “ሳሙኤል!” ሲል ጠራው። እሱም ተነስቶ ወደ ኤሊ በመሄድ “አቤት፣ ጠራኸኝ?” አለው።

ኤሊም ብላቴናውን እየጠራው ያለው ይሖዋ መሆኑን አስተዋለ። 9 በመሆኑም ኤሊ ሳሙኤልን እንዲህ አለው፦ “ሂድና ተኛ፤ እንደገና ከጠራህ ‘ይሖዋ ሆይ፣ አገልጋይህ እየሰማ ስለሆነ ተናገር’ በል።” ሳሙኤልም ወደ ስፍራው ተመልሶ ተኛ።

10 ይሖዋም መጥቶ በዚያ ቆመ፤ እንደ ሌላው ጊዜም “ሳሙኤል፣ ሳሙኤል!” ሲል ጠራው። ሳሙኤልም “አገልጋይህ እየሰማ ስለሆነ ተናገር” አለ። 11 ይሖዋ ሳሙኤልን እንዲህ አለው፦ “ለሰሚው ሁሉ ጆሮ የሚሰቀጥጥ ነገር በእስራኤል ውስጥ አደርጋለሁ።+ 12 በዚያ ቀን ስለ ኤሊ ቤት የተናገርኩትን ነገር ሁሉ ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ በእሱ ላይ እፈጽማለሁ።+ 13 እሱ በሚያውቀው ጥፋት የተነሳ በቤቱ ላይ ለዘለቄታው እንደምፈርድ ንገረው፤+ ምክንያቱም ልጆቹ አምላክን ረግመዋል፤+ እሱ ግን አልገሠጻቸውም።+ 14 በዚህም የተነሳ የኤሊ ቤት የፈጸመው ጥፋት መሥዋዕት ወይም መባ በማቅረብ ፈጽሞ እንደማይሰረይ ለኤሊ ቤት ምያለሁ።”+

15 ሳሙኤልም እስከ ንጋት ድረስ ተኛ፤ ከዚያም የይሖዋን ቤት በሮች ከፈተ። ሳሙኤል ራእዩን ለኤሊ መንገር ፈርቶ ነበር። 16 ኤሊ ግን ሳሙኤልን ጠርቶ “ልጄ፣ ሳሙኤል!” አለው። እሱም “አቤት” አለው። 17 ኤሊም እንዲህ ሲል ጠየቀው፦ “ለመሆኑ የነገረህ መልእክት ምንድን ነው? እባክህ አትደብቀኝ። እሱ ከነገረህ ነገር ውስጥ አንዲት ቃል እንኳ ብትደብቀኝ አምላክ እንዲህ ያድርግብህ፤ ከዚያም የከፋ ነገር ያምጣብህ።” 18 በመሆኑም ሳሙኤል እሱ የነገረውን በሙሉ ምንም ሳይደብቅ ነገረው። ኤሊም “ይህ ከይሖዋ ነው። እሱ መልካም መስሎ የታየውን ያድርግ” አለ።

19 ሳሙኤል እያደገ ሄደ፤ ይሖዋም ከእሱ ጋር ነበር፤+ የሚናገረውም ቃል ሁሉ እንዲፈጸም ያደርግ* ነበር። 20 ከዳን እስከ ቤርሳቤህ ያሉ እስራኤላውያን በሙሉ ሳሙኤል ተቀባይነት ያገኘ የይሖዋ ነቢይ እንደሆነ ተገነዘቡ። 21 ይሖዋም በሴሎ ይገለጥ ነበር፤ ምክንያቱም ይሖዋ በሴሎ በይሖዋ ቃል አማካኝነት ራሱን ለሳሙኤል ገልጦለት ነበር።+

4 የሳሙኤልም ቃል ለእስራኤላውያን ሁሉ ደረሰ።

ከዚያም እስራኤላውያን ከፍልስጤማውያን ጋር ለመዋጋት ወጡ፤ ኤቤንዔዘርም አጠገብ ሰፈሩ፤ ፍልስጤማውያን ደግሞ በአፌቅ ሰፍረው ነበር። 2 ፍልስጤማውያን እስራኤላውያንን ለመግጠም ተሰልፈው ወጡ፤ ውጊያውም እየተፋፋመ ሄደ፤ እስራኤላውያንም ውጊያው በተደረገበት ግንባር 4,000 ሰው በገደሉባቸው በፍልስጤማውያን ድል ተመቱ። 3 ሠራዊቱ ወደ ሰፈሩ በተመለሰ ጊዜ የእስራኤል ሽማግሌዎች እንዲህ አሉ፦ “ይሖዋ በዛሬው ዕለት በፍልስጤማውያን ፊት ድል እንድንመታ የፈቀደው ለምንድን ነው?*+ አብሮን እንዲሆንና ከጠላቶቻችን እጅ እንዲያድነን የይሖዋን የቃል ኪዳን ታቦት ከሴሎ ይዘነው እንሂድ።”+ 4 በመሆኑም ሕዝቡ ሰዎችን ወደ ሴሎ ላከ፤ እነሱም ከኪሩቤል በላይ* ዙፋን ላይ የተቀመጠውን+ የሠራዊት ጌታ የይሖዋን የቃል ኪዳን ታቦት ከዚያ ተሸክመው መጡ። ሁለቱ የኤሊ ልጆች ሆፍኒ እና ፊንሃስም+ ከእውነተኛው አምላክ የቃል ኪዳን ታቦት ጋር አብረው ነበሩ።

5 የይሖዋ የቃል ኪዳን ታቦት ወደ ሰፈሩ ሲገባ እስራኤላውያን ሁሉ ምድር እስክትናወጥ ድረስ ጮኹ። 6 ፍልስጤማውያንም ጩኸቱን ሲሰሙ “በዕብራውያን ሰፈር የሚሰማው ይህ ሁሉ ጩኸት ምንድን ነው?” አሉ። በመጨረሻም የይሖዋ ታቦት ወደ ሰፈሩ እንደገባ አወቁ። 7 ፍልስጤማውያንም “አምላክ ወደ ሰፈሩ ገብቷል!”+ በማለት በፍርሃት ተዋጡ። በመሆኑም እንዲህ አሉ፦ “ወየው ጉዳችን! እንዲህ ዓይነት ነገር ሆኖ አያውቅም! 8 ወየው ጉዳችን! ከዚህ ባለ ግርማ አምላክ እጅ ማን ያድነናል? ግብፃውያንን በምድረ በዳ በተለያዩ መቅሰፍቶች የመታቸው አምላክ እኮ ይህ ነው።+ 9 እናንተ ፍልስጤማውያን አይዟችሁ፣ ወንድነታችሁን አሳዩ፤ አለዚያ ዕብራውያን የእናንተ አገልጋዮች እንደነበሩ ሁሉ እናንተም የእነሱ አገልጋዮች ትሆናላችሁ።+ ወንድነታችሁን አሳዩ፤ ተዋጉ!” 10 በመሆኑም ፍልስጤማውያን ተዋጉ፤ እስራኤላውያንም ድል ተመቱ፤+ እያንዳንዱም ሰው ወደየድንኳኑ ሸሸ። በጣም ብዙ ሕዝብ አለቀ፤ ከእስራኤላውያንም ወገን 30,000 እግረኛ ወታደር ሞተ። 11 የአምላክም ታቦት ተማረከ፤ ሁለቱ የኤሊ ልጆች ሆፍኒ እና ፊንሃስም ሞቱ።+

12 አንድ ቢንያማዊ ልብሱን ቀዶና በራሱ ላይ አቧራ ነስንሶ+ ከጦር ግንባሩ እየሮጠ በዚያው ቀን ሴሎ ደረሰ። 13 ሰውየውም ሲደርስ ኤሊ በእውነተኛው አምላክ ታቦት+ የተነሳ ልቡ ስለተረበሸ መንገድ ዳር ወንበር ላይ ተቀምጦ ይጠባበቅ ነበር። ሰውየውም ወሬውን ለመንገር ወደ ከተማዋ ገባ፤ መላ ከተማዋም በጩኸት ትናወጥ ጀመር። 14 ኤሊም ጩኸቱን ሲሰማ “ይህ ሁሉ ጩኸት ምንድን ነው?” በማለት ጠየቀ። ሰውየውም በፍጥነት ወደ እሱ ሄዶ ወሬውን ነገረው። 15 (በዚህ ወቅት ኤሊ ዕድሜው 98 ዓመት ነበር፤ ኤሊ ማየት ተስኖት የነበረ ቢሆንም ዓይኖቹ ፊት ለፊት ትኩር ብለው ይመለከቱ ነበር።)+ 16 ከዚያም ሰውየው ኤሊን “ከጦር ግንባሩ የመጣሁት ሰው እኔ ነኝ! ከጦር ግንባሩ ሸሽቼ የመጣሁትም ዛሬ ነው” አለው። በዚህ ጊዜ ኤሊ “ልጄ፣ ለመሆኑ የተከሰተው ነገር ምንድን ነው?” ሲል ጠየቀው። 17 ወሬውን ያመጣውም ሰው እንዲህ አለው፦ “እስራኤላውያን ከፍልስጤማውያን ፊት ሸሽተዋል፤ ሕዝቡም ከፍተኛ ሽንፈት ደርሶበታል፤+ ሁለቱ ልጆችህ ሆፍኒ እና ፊንሃስም ሞተዋል፤+ የእውነተኛው አምላክ ታቦትም ተማርኳል።”+

18 ሰውየው ስለ እውነተኛው አምላክ ታቦት በተናገረበት ቅጽበት ኤሊ በሩ አጠገብ ከተቀመጠበት ወንበር ላይ ወደኋላው ወደቀ፤ በዕድሜ የገፋ ከመሆኑም ሌላ ሰውነቱ ከባድ ስለነበር አንገቱ ተሰብሮ ሞተ። እሱም ለ40 ዓመት በእስራኤል ላይ ፈራጅ ሆኖ አገልግሏል። 19 የኤሊ ምራት የፊንሃስ ሚስት ነፍሰ ጡር ነበረች፤ የምትወልድበትም ጊዜ ተቃርቦ ነበር። እሷም የእውነተኛው አምላክ ታቦት እንደተማረከ እንዲሁም አማቷና ባሏ እንደሞቱ ስትሰማ ሆዷን ይዛ ጎንበስ አለች፤ ድንገትም ምጥ ያዛትና ወለደች። 20 እሷም ልትሞት በምታጣጥርበት ጊዜ አጠገቧ ቆመው የነበሩት ሴቶች “አይዞሽ፣ ወንድ ልጅ ወልደሻል” አሏት። እሷ ግን መልስ አልሰጠችም፤ ልብም አላለችውም። 21 ሆኖም የእውነተኛው አምላክ ታቦት በመማረኩ እንዲሁም በአማቷና በባሏ ላይ በደረሰው ነገር+ የተነሳ “ክብር ከእስራኤል በግዞት ተወሰደ”+ ስትል ለልጁ ኢካቦድ*+ የሚል ስም አወጣችለት። 22 “የእውነተኛው አምላክ ታቦት ስለተማረከ ክብር ከእስራኤል በግዞት ተወሰደ”+ አለች።

5 ፍልስጤማውያኑ የእውነተኛውን አምላክ ታቦት ከማረኩ+ በኋላ ከኤቤንዔዘር ወደ አሽዶድ አመጡት። 2 እነሱም የእውነተኛውን አምላክ ታቦት ወስደው ወደ ዳጎን ቤት* አስገቡት፤ ከዳጎን+ አጠገብም አስቀመጡት። 3 በማግስቱም አሽዶዳውያን በማለዳ ሲነሱ ዳጎን በይሖዋ ታቦት ፊት መሬት ላይ በግንባሩ ተደፍቶ አገኙት።+ በመሆኑም ዳጎንን አንስተው ወደ ቦታው መለሱት።+ 4 በሚቀጥለውም ቀን ማለዳ ሲነሱ ዳጎን በይሖዋ ታቦት ፊት በግንባሩ ተደፍቶ አገኙት። የዳጎን ራስና መዳፎቹም ተቆርጠው ደፉ ላይ ወድቀው ነበር። ባለበት የቀረው የዓሣው ክፍል ብቻ* ነበር። 5 እስከ ዛሬም ድረስ የዳጎን ካህናትና ወደ ዳጎን ቤት የሚገቡ ሁሉ በአሽዶድ የሚገኘውን የዳጎንን ደፍ የማይረግጡት ለዚህ ነው።

6 የይሖዋም እጅ በአሽዶዳውያን ላይ ከበደባቸው፤ እሱም አሽዶድንና ግዛቶቿን በኪንታሮት*+ በመምታት አጠፋቸው። 7 የአሽዶድ ሰዎች የተከሰተውን ነገር ሲያዩ “የእስራኤል አምላክ ታቦት በመካከላችን እንዲቆይ አታድርጉ፤ ምክንያቱም እጁ በእኛና በአምላካችን በዳጎን ላይ ጨክኖብናል” አሉ። 8 በመሆኑም ሰዎችን ልከው የፍልስጤምን ገዢዎች በሙሉ በመሰብሰብ “የእስራኤልን አምላክ ታቦት ምን ብናደርገው ይሻላል?” ብለው ጠየቋቸው። እነሱም “የእስራኤል አምላክ ታቦት ወደ ጌት+ ይወሰድ” ሲሉ መለሱላቸው። ስለሆነም የእስራኤልን አምላክ ታቦት ወደዚያ ወሰዱት።

9 ታቦቱንም ወደዚያ ከወሰዱት በኋላ የይሖዋ እጅ በከተማዋ ላይ ሆነ፤ ታላቅ ሽብርም ለቀቀባቸው። እሱም የከተማዋን ሰዎች ከትንሽ እስከ ትልቅ መታቸው፤ ኪንታሮትም ወጣባቸው።+ 10 በመሆኑም የእውነተኛውን አምላክ ታቦት ወደ ኤቅሮን+ ላኩት፤ ሆኖም የእውነተኛው አምላክ ታቦት ኤቅሮን ሲደርስ ኤቅሮናውያን “እኛንም ሆነ ሕዝባችንን ለማስፈጀት የእስራኤልን አምላክ ታቦት ይኸው ወደ እኛ ደግሞ አመጡብን!” በማለት ይጮኹ ጀመር።+ 11 ከዚያም ሰዎችን ልከው የፍልስጤምን ገዢዎች በሙሉ በመሰብሰብ “የእስራኤልን አምላክ ታቦት ከዚህ አርቁልን፤ እኛም ሆንን ሕዝባችን እንዳናልቅ ወደ ቦታው እንዲመለስ አድርጉ” አሏቸው። ምክንያቱም መላ ከተማዋ በሞት ፍርሃት ተውጣ ነበር፤ የእውነተኛውም አምላክ እጅ በዚያ በጣም ከብዶ ነበር፤+ 12 ያልሞቱት ሰዎችም በኪንታሮት ተመቱ። ከተማዋ እርዳታ ለማግኘት የምታሰማው ጩኸትም ወደ ሰማይ ወጣ።

6 የይሖዋ ታቦት+ በፍልስጤማውያን ምድር ሰባት ወር ቆየ። 2 ፍልስጤማውያኑም ካህናትንና ሟርተኞችን+ ጠርተው “የይሖዋን ታቦት ምን ብናደርገው ይሻላል? ወደ ስፍራው እንዴት እንደምንመልሰው አሳውቁን” አሏቸው። 3 እነሱም እንዲህ ሲሉ መለሱላቸው፦ “የእስራኤልን አምላክ የይሖዋን የቃል ኪዳን ታቦት የምትመልሱ ከሆነ ያለመባ እንዳትመልሱት። ከበደል መባ ጋር አድርጋችሁ ወደ እሱ መመለስ ይኖርባችኋል።+ የምትፈወሱት እንዲህ ካደረጋችሁ ብቻ ነው፤ ደግሞም እጁ ከእናንተ ላይ ያልተመለሰው ለምን እንደሆነ ታውቃላችሁ።” 4 ስለዚህ “ወደ እሱ መላክ የሚኖርብን የበደል መባ ምንድን ነው?” ሲሉ ጠየቁ። እነሱም እንዲህ አሏቸው፦ “እናንተንም ሆነ ገዢዎቻችሁን ያሠቃየው መቅሰፍት ተመሳሳይ ስለሆነ በፍልስጤም ገዢዎች+ ቁጥር ልክ አምስት የወርቅ ኪንታሮቶችንና* አምስት የወርቅ አይጦችን ላኩ። 5 ምድሪቱን እያጠፉ ባሉት ኪንታሮቶቻችሁና አይጦቻችሁ+ አምሳያ ምስሎችን ሥሩ፤ የእስራኤልንም አምላክ አክብሩ። ምናልባትም በእናንተ፣ በአምላካችሁና በምድራችሁ ላይ የከበደውን እጁን ያቀልላችሁ ይሆናል።+ 6 ግብፅና ፈርዖን ልባቸውን እንዳደነደኑት እናንተም ለምን ልባችሁን ታደነድናላችሁ?+ እሱ ክፉኛ በቀጣቸው+ ጊዜ እስራኤላውያንን ለቀቋቸው፤ እነሱም ሄዱ።+ 7 ስለዚህ አሁን አዲስ ሠረገላ እንዲሁም እንቦሶች ያሏቸውና ቀንበር ያልተጫነባቸው ሁለት ላሞች አዘጋጁ። ከዚያም ሠረገላውን ጥመዱባቸው፤ እንቦሶቻቸውን ግን ከእነሱ ነጥላችሁ ወደ ቤት መልሷቸው። 8 የይሖዋን ታቦት ወስዳችሁ ሠረገላው ላይ አስቀምጡት፤ እንዲሁም ለእሱ የበደል መባ አድርጋችሁ የምትልኳቸውን የወርቅ ምስሎች በሣጥን አድርጋችሁ ታቦቱ አጠገብ አስቀምጡ።+ ከዚያም መንገዱን ይዞ እንዲሄድ ላኩት፤ 9 ልብ ብላችሁም ተመልከቱ፦ ታቦቱ ወደ አገሩ ወደ ቤትሼሜሽ+ የሚወስደውን መንገድ ተከትሎ ከሄደ ይህን ታላቅ መከራ ያመጣብን እሱ ነው ማለት ነው። ካልሆነ ግን የእሱ እጅ እንዳልመታን እናውቃለን፤ ይህ የደረሰብንም እንዲያው በአጋጣሚ ነው።”

10 ሰዎቹም እንዲሁ አደረጉ። እንቦሶች ያሏቸውን ሁለት ላሞች ወስደው ሠረገላውን ጠመዱባቸው፤ እንቦሶቹንም በረት ውስጥ ዘጉባቸው። 11 ከዚያም የይሖዋን ታቦት እንዲሁም የወርቅ አይጦቹንና የኪንታሮቶቻቸውን ምስል የያዘውን ሣጥን ሠረገላው ላይ ጫኑ። 12 ላሞቹም ወደ ቤትሼሜሽ በሚወስደው መንገድ ቀጥ ብለው ሄዱ።+ ወደ ቀኝም ወደ ግራም ሳይሉ አንዱን ጎዳና ተከትለው ‘እምቧ’ እያሉ ተጓዙ፤ በዚህ ጊዜ ሁሉ የፍልስጤም ገዢዎች እስከ ቤትሼሜሽ ድንበር ድረስ ከኋላ ከኋላቸው ይከተሏቸው ነበር። 13 የቤትሼሜሽ ሰዎች በሸለቋማው ሜዳ* ላይ ስንዴ እያጨዱ ነበር። እነሱም ቀና ብለው ታቦቱን ተመለከቱ፤ እሱን በማየታቸውም በጣም ተደሰቱ። 14 ሠረገላውም ወደ ቤትሼሜሻዊው ኢያሱ ማሳ ገብቶ እዚያ በሚገኝ አንድ ትልቅ ዓለት አጠገብ ቆመ። ሰዎቹም የሠረገላውን እንጨት ፈልጠው ላሞቹን+ ለይሖዋ የሚቃጠል መባ አድርገው አቀረቡ።

15 ሌዋውያኑም+ የይሖዋን ታቦትና አብሮት የነበረውን የወርቅ ምስሎቹን የያዘውን ሣጥን አውርደው በትልቁ ዓለት ላይ አስቀመጧቸው። በዚያም ቀን የቤትሼሜሽ+ ሰዎች ለይሖዋ የሚቃጠሉ መባዎችን አቀረቡ፤ መሥዋዕቶችንም ሠዉ።

16 አምስቱ የፍልስጤም ገዢዎችም ይህን ሲያዩ በዚያው ቀን ወደ ኤቅሮን ተመለሱ። 17 ፍልስጤማውያን ለይሖዋ የበደል መባ አድርገው የላኳቸው የወርቅ ኪንታሮቶች እነዚህ ናቸው፦+ ለአሽዶድ+ አንድ፣ ለጋዛ አንድ፣ ለአስቀሎን አንድ፣ ለጌት+ አንድ እንዲሁም ለኤቅሮን+ አንድ። 18 የወርቅ አይጦቹ ቁጥር አምስቱ የፍልስጤም ገዢዎች በሚያስተዳድሯቸው ከተሞች ሁሉ ይኸውም በተመሸጉት ከተሞችና በሥራቸው በሚገኙ አውላላ ሜዳ ላይ ባሉ መንደሮች ቁጥር ልክ ነበር።

የይሖዋን ታቦት ያስቀመጡበት በቤትሼሜሻዊው ኢያሱ ማሳ ውስጥ የሚገኘው ትልቅ ዓለት እስከ ዛሬ ድረስ ምሥክር ሆኖ ያገለግላል። 19 ይሁንና አምላክ የይሖዋን ታቦት ስለተመለከቱ የቤትሼሜሽን ሰዎች መታቸው። ከሕዝቡ መካከል 50,070 ሰዎችን* መታ፤ ሰዎቹም ይሖዋ ብዙ ሕዝብ ስለፈጀባቸው ያለቅሱ ጀመር።+ 20 በመሆኑም የቤትሼሜሽ ሰዎች “ታዲያ በዚህ ቅዱስ አምላክ+ በይሖዋ ፊት ማን ሊቆም ይችላል? ምናለ ከእኛ ላይ ዞር ቢልና ወደ ሌሎች ቢሄድ?” አሉ።+ 21 ስለዚህ ወደ ቂርያትየአሪም+ ነዋሪዎች መልእክተኞችን ልከው “ፍልስጤማውያን የይሖዋን ታቦት መልሰዋል። ወደዚህ ውረዱና ይዛችሁት ውጡ” አሏቸው።+

7 በመሆኑም የቂርያትየአሪም ሰዎች መጥተው የይሖዋን ታቦት በኮረብታው ላይ ወደሚገኘው ወደ አቢናዳብ ቤት+ ወሰዱት፤ የይሖዋን ታቦት እንዲጠብቅም ልጁን አልዓዛርን ቀደሱት።

2 ታቦቱም ወደ ቂርያትየአሪም ከመጣ ረጅም ጊዜ ይኸውም በአጠቃላይ 20 ዓመት አለፈው፤ የእስራኤልም ቤት ሁሉ ይሖዋን መፈለግ* ጀመረ።+ 3 ሳሙኤልም የእስራኤልን ቤት ሁሉ “በሙሉ ልባችሁ+ ወደ ይሖዋ የምትመለሱ ከሆነ ባዕዳን አማልክትንና+ የአስታሮትን ምስሎች+ ከመካከላችሁ አስወግዱ፤ ልባችሁንም ሙሉ በሙሉ ለይሖዋ ስጡ፤ እሱን ብቻ አገልግሉ፤+ እሱም ከፍልስጤማውያን እጅ ይታደጋችኋል”+ አላቸው። 4 በዚህ ጊዜ እስራኤላውያን የባአልንና የአስታሮትን ምስሎች አስወግደው ይሖዋን ብቻ አገለገሉ።+

5 ከዚያም ሳሙኤል “እስራኤልን ሁሉ በምጽጳ+ ሰብስቡ፤ እኔም ስለ እናንተ ወደ ይሖዋ እጸልያለሁ”+ አለ። 6 እነሱም በምጽጳ ተሰበሰቡ፤ ከዚያም ውኃ ቀድተው በይሖዋ ፊት አፈሰሱ፤ ያን ዕለትም ሲጾሙ ዋሉ።+ በዚያም “በይሖዋ ላይ ኃጢአት ሠርተናል” አሉ።+ ሳሙኤልም በምጽጳ በእስራኤላውያን ላይ ፈራጅ ሆኖ ማገልገል ጀመረ።+

7 ፍልስጤማውያንም እስራኤላውያን በምጽጳ አንድ ላይ መሰብሰባቸውን በሰሙ ጊዜ የፍልስጤም ገዢዎች+ እስራኤልን ለመውጋት ወጡ። እስራኤላውያንም ይህን ሲሰሙ ፍልስጤማውያንን ፈሩ። 8 ስለሆነም እስራኤላውያን ሳሙኤልን “አምላካችን ይሖዋ እንዲረዳንና ከፍልስጤማውያን እጅ እንዲያድነን ወደ እሱ መጮኽህን አታቁም” አሉት።+ 9 ከዚያም ሳሙኤል አንድ የሚጠባ ግልገል ወስዶ ለይሖዋ ሙሉ በሙሉ የሚቃጠል መባ+ አድርጎ አቀረበው፤ ሳሙኤልም ይሖዋ እስራኤላውያንን እንዲረዳቸው ተማጸነ፤ ይሖዋም መለሰለት።+ 10 ሳሙኤል የሚቃጠለውን መባ እያቀረበ ሳለ ፍልስጤማውያን እስራኤላውያንን ለመውጋት ቀረቡ። ይሖዋም በዚያን ዕለት በፍልስጤማውያን ላይ ኃይለኛ የነጎድጓድ ድምፅ ለቀቀባቸው፤+ ግራ እንዲጋቡም አደረጋቸው፤+ እነሱም በእስራኤላውያን ፊት ድል ተመቱ።+ 11 በዚህ ጊዜ የእስራኤል ሰዎች ከምጽጳ ወጥተው ፍልስጤማውያንን ማሳደዳቸውን ተያያዙት፤ ከቤትካር በስተ ደቡብ እስከሚገኘው አካባቢም ድረስ መቷቸው። 12 ከዚያም ሳሙኤል አንድ ድንጋይ+ ወስዶ በምጽጳ እና በየሻና መካከል አስቀመጠው፤ ስሙንም ኤቤንዔዘር* አለው፤ ይህን ያለው “ይሖዋ እስካሁን ድረስ ረድቶናል”+ ሲል ነው። 13 በዚህ ሁኔታ ፍልስጤማውያን ድል ተመቱ፤ ዳግመኛም ወደ እስራኤላውያን ክልል መጥተው አያውቁም፤+ በሳሙኤል ዘመን ሁሉ የይሖዋ እጅ በፍልስጤማውያን ላይ ነበር።+ 14 በተጨማሪም ፍልስጤማውያን ከእስራኤላውያን ላይ የወሰዷቸው ከኤቅሮን እስከ ጌት ያሉት ከተሞች ለእስራኤላውያን ተመለሱላቸው፤ እንዲሁም እስራኤላውያን በእነዚህ ከተሞች ሥር ያሉትን ክልሎች ከፍልስጤማውያን እጅ አስለቀቁ።

በእስራኤላውያንና በአሞራውያን መካከልም ሰላም ወረደ።+

15 ሳሙኤልም በሕይወት ዘመኑ ሁሉ ለእስራኤላውያን ፈራጅ ሆኖ አገለገለ።+ 16 በየዓመቱም በቤቴል፣+ በጊልጋል+ እና በምጽጳ+ በመዘዋወር በእነዚህ አካባቢዎች ሁሉ ለሚገኙ እስራኤላውያን ፈራጅ ሆኖ አገለገለ። 17 ሆኖም ቤቱ የሚገኘው በራማ+ ስለነበር ወደዚያ ይመለስ ነበር፤ በዚያም ለእስራኤላውያን ፈራጅ ሆኖ አገለገለ። በዚያም ለይሖዋ መሠዊያ ሠራ።+

8 ሳሙኤል በሸመገለ ጊዜ ልጆቹን በእስራኤል ውስጥ ፈራጆች ሆነው እንዲያገለግሉ ሾማቸው። 2 የበኩር ልጁ ስም ኢዩኤል ሲሆን የሁለተኛው ልጁ ስም ደግሞ አቢያህ+ ነበር፤ እነሱም በቤርሳቤህ ፈራጆች ነበሩ። 3 ይሁንና ልጆቹ የእሱን ፈለግ አልተከተሉም፤ ከዚህ ይልቅ ተገቢ ያልሆነ ጥቅም+ ለማግኘት ይጥሩ፣ ጉቦ ይቀበሉ+ እንዲሁም ፍርድ ያጣምሙ+ ነበር።

4 ከጊዜ በኋላ የእስራኤል ሽማግሌዎች በሙሉ አንድ ላይ ተሰብስበው በራማ ወደሚገኘው ወደ ሳሙኤል መጡ። 5 እንዲህም አሉት፦ “እንግዲህ አንተ አርጅተሃል፤ ልጆችህ ደግሞ የአንተን ፈለግ እየተከተሉ አይደለም። ስለዚህ እንደ ሌሎቹ ብሔራት ሁሉ በእኛ ላይ ፈራጅ የሚሆን ንጉሥ ሹምልን።”+ 6 ይሁንና “በእኛ ላይ ፈራጅ የሚሆን ንጉሥ ሹምልን” ማለታቸው ሳሙኤልን አላስደሰተውም።* ሳሙኤልም ወደ ይሖዋ ጸለየ፤ 7 ይሖዋም ሳሙኤልን እንዲህ አለው፦ “ሕዝቡ የሚልህን ሁሉ ስማ፤ አልቀበልም ያሉት አንተን አይደለም፤ ይልቁንም ንጉሣቸው አድርገው መቀበል ያልፈለጉት እኔን ነው።+ 8 እየፈጸሙ ያሉት ነገር ከግብፅ ካወጣኋቸው ቀን ጀምሮ እስከዚህች ዕለት ድረስ ሲያደርጉ የነበሩትን ነው፤ እኔን ትተው+ ሌሎች አማልክትን አገለገሉ፤+ በአንተም ላይ እያደረጉ ያሉት ይህንኑ ነው። 9 ስለዚህ የሚሉህን ስማ። ይሁን እንጂ በጥብቅ አስጠንቅቃቸው፤ በላያቸው የሚነግሠው ንጉሥ ምን እንዲደረግለት የመጠየቅ መብት እንዳለው ንገራቸው።”

10 በመሆኑም ሳሙኤል ንጉሥ እንዲያነግሥላቸው ለጠየቁት ሰዎች የይሖዋን ቃል ሁሉ ነገራቸው። 11 እንዲህ አላቸው፦ “በእናንተ ላይ የሚነግሠው ንጉሥ እንዲህ እንዲደረግለት የመጠየቅ መብት አለው፦+ ወንዶች ልጆቻችሁን ወስዶ+ ሠረገላው ውስጥ ያስቀምጣቸዋል፤+ ፈረሰኞችም+ ያደርጋቸዋል፤ የተወሰኑትንም ከሠረገሎቹ ፊት ፊት እንዲሮጡ ያደርጋል። 12 ለራሱም የሺህ አለቆችንና+ የሃምሳ አለቆችን+ ይሾማል፤ አንዳንዶቹም መሬቱን ያርሳሉ፣+ እህሉን ያጭዳሉ+ እንዲሁም የጦር መሣሪያዎቹንና ለሠረገሎቹ+ የሚሆኑትን ዕቃዎች ይሠራሉ። 13 ሴቶች ልጆቻችሁንም ወስዶ ቅባት ቀማሚዎች፣* ምግብ አብሳዮችና ዳቦ ጋጋሪዎች+ ያደርጋቸዋል። 14 እንዲሁም ከማሳችሁ፣ ከወይን እርሻችሁና ከወይራ ዛፎቻችሁ+ ምርጥ የሆነውን ይወስዳል፤ ለአገልጋዮቹም ይሰጣቸዋል። 15 ከእህል ማሳችሁና ከወይን እርሻችሁ ላይ አንድ አሥረኛውን ወስዶ ለቤተ መንግሥት ባለሥልጣናቱና ለአገልጋዮቹ ይሰጣል። 16 ወንድ አገልጋዮቻችሁንና ሴት አገልጋዮቻችሁን፣ ከከብቶቻችሁ መካከል ምርጥ የሆኑትን እንዲሁም አህዮቻችሁን ይወስዳል፤ ለራሱ ሥራም ይጠቀምባቸዋል።+ 17 ከመንጋችሁ መካከል አንድ አሥረኛውን ይወስዳል፤+ እናንተም የእሱ አገልጋዮች ትሆናላችሁ። 18 ለራሳችሁ ከመረጣችሁት ንጉሥ የተነሳ የምትጮኹበት ቀን ይመጣል፤+ ሆኖም በዚያ ቀን ይሖዋ አይመልስላችሁም።”

19 ሕዝቡ ግን ሳሙኤል የተናገረውን ለመስማት አሻፈረኝ አለ፤ እንዲህም አለ፦ “አይሆንም፣ ንጉሥ እንዲነግሥልን እንፈልጋለን። 20 ከዚያም እንደ ሌሎች ብሔራት እንሆናለን፤ ንጉሣችንም ፈራጅ ይሆንልናል፣ ይመራናል እንዲሁም ጦርነት ሲገጥመን ይዋጋልናል።” 21 ሳሙኤልም ሕዝቡ ያለውን ሁሉ ከሰማ በኋላ የተናገሩትን ነገር ይሖዋ እየሰማ በድጋሚ ተናገረ። 22 ይሖዋም ሳሙኤልን “የሚሉህን ስማ፤ በላያቸው የሚገዛ ንጉሥም አንግሥላቸው”+ አለው። ከዚያም ሳሙኤል የእስራኤልን ሰዎች “እያንዳንዳችሁ ወደ ከተማችሁ ተመለሱ” አላቸው።

9 የቢንያም ሰው የሆነ ቂስ+ የተባለ አንድ እጅግ ባለጸጋ ሰው ነበር፤ እሱም የቢንያማዊው+ የአፊያ ልጅ፣ የቤኮራት ልጅ፣ የጸሮር ልጅ፣ የአቢዔል ልጅ ነበር። 2 ይህ ሰው ሳኦል+ የተባለ መልከ መልካም ወጣት ልጅ ነበረው፤ ከእስራኤላውያንም መካከል እንደ እሱ ያለ መልከ መልካም ወንድ አልነበረም፤ እሱም ከትከሻው በላይ ዘለግ ያለ ሲሆን ቁመቱ ከሌሎቹ ሁሉ ይበልጥ ነበር።

3 የሳኦል አባት ቂስ አህዮቹ* በጠፉበት ጊዜ ልጁን ሳኦልን “እባክህ ከአገልጋዮቹ መካከል አንዱን ይዘህ ሂድና አህዮቹን ፈልጋቸው” አለው። 4 እነሱም የኤፍሬምን ተራራማ አካባቢና የሻሊሻን ምድር አቋርጠው ሄዱ፤ ሆኖም አህዮቹን አላገኟቸውም። ከዚያም የሻአሊምን ምድር አቋርጠው ተጓዙ፤ አህዮቹ ግን በዚያ አልነበሩም። እነሱም መላውን የቢንያማውያንን ምድር አቋርጠው ሄዱ፤ ይሁንና አህዮቹን አላገኟቸውም።

5 እነሱም ወደ ጹፍ ምድር መጡ፤ ሳኦልም አብሮት የነበረውን አገልጋዩን “አባቴ ስለ አህዮቹ ማሰቡን ትቶ ስለ እኛ መጨነቅ እንዳይጀምር፣ ና እንመለስ” አለው።+ 6 አገልጋዩ ግን እንዲህ አለው፦ “እነሆ፣ በዚህ ከተማ የሚኖር አንድ የተከበረ የአምላክ ሰው አለ። የሚናገረው ነገር በሙሉ መሬት ጠብ አይልም።+ ስለዚህ ወደዚያ እንሂድ። ምናልባት በየትኛው መንገድ መሄድ እንዳለብን ሊነግረን ይችላል።” 7 በዚህ ጊዜ ሳኦል አገልጋዩን እንዲህ አለው፦ “መሄዱንስ እንሂድ፤ ግን ለሰውየው ምን ይዘንለት እንሄዳለን? በከረጢታችን ውስጥ የያዝነው ዳቦ እንደሆነ አልቋል፤ ለእውነተኛው አምላክ ሰው ስጦታ አድርገን የምንሰጠው ምንም ነገር የለንም። ታዲያ ምን ብናደርግ ይሻላል?” 8 አገልጋዩም መልሶ ሳኦልን “እንግዲህ ሩብ ሰቅል* ብር በእጄ አለ። ይህን ለእውነተኛው አምላክ ሰው እሰጠዋለሁ፤ እሱም በየትኛው መንገድ መሄድ እንዳለብን ይነግረናል” አለው። 9 (ቀደም ባሉት ጊዜያት በእስራኤል ውስጥ አንድ ሰው አምላክን ለመፈለግ ሲሄድ “ኑ፣ ወደ ባለ ራእዩ+ እንሂድ” ይል ነበር። ምክንያቱም በዛሬው ጊዜ ነቢይ የሚባለው ቀደም ባሉት ጊዜያት ባለ ራእይ ይባል ነበር።) 10 ከዚያም ሳኦል አገልጋዩን “የተናገርከው ነገር መልካም ነው። በል ና፣ እንሂድ” አለው። በመሆኑም የእውነተኛው አምላክ ሰው ወደሚገኝበት ከተማ ሄዱ።

11 እነሱም ወደ ከተማዋ የሚወስደውን አቀበት እየወጡ ሳለ ውኃ ለመቅዳት የወጡ ልጃገረዶችን አገኙ። በመሆኑም “ባለ ራእዩ+ እዚህ ነው ያለው?” አሏቸው። 12 እነሱም እንዲህ ሲሉ መለሱላቸው፦ “አዎ እዚህ ነው። እነሆ፣ ከፊታችሁ ነው ያለው! ፈጠን ብላችሁ ሂዱ፣ በዛሬው ዕለት ሕዝቡ ከፍ ባለው ቦታ+ ላይ መሥዋዕት ስለሚያቀርብ+ ወደ ከተማዋ መጥቷል። 13 ልክ ወደ ከተማዋ እንደገባችሁ ለመብላት ወደ ኮረብታው ከመውጣቱ በፊት ታገኙታላችሁ። መሥዋዕቱን የሚባርከው እሱ ስለሆነ ሕዝቡ እሱ ካልመጣ መብላት አይጀምርም። ከዚያ በኋላ የተጋበዙት ይበላሉ። በሉ አሁኑኑ ውጡ፤ ታገኙታላችሁ።” 14 ስለዚህ ወደ ከተማዋ ወጡ። ከተማዋ መሃል ሲደርሱም ሳሙኤል ከእነሱ ጋር ተገናኝቶ ወደ ኮረብታው ለመውጣት ወደ እነሱ እየመጣ ነበር።

15 ይሖዋ፣ ሳኦል ከመምጣቱ ከአንድ ቀን በፊት ለሳሙኤል እንዲህ ብሎት* ነበር፦ 16 “ነገ በዚህ ጊዜ ገደማ ከቢንያም ምድር+ የመጣ አንድ ሰው ወደ አንተ እልካለሁ። አንተም በሕዝቤ በእስራኤል ላይ መሪ አድርገህ ቀባው፤+ እሱም ሕዝቤን ከፍልስጤማውያን እጅ ያድናቸዋል። ምክንያቱም የሕዝቤን መከራ አይቻለሁ፤ ጩኸታቸውም ወደ እኔ ደርሷል።”+ 17 ሳሙኤል፣ ሳኦልን ባየው ጊዜ ይሖዋ “‘ሕዝቤን የሚገዛው* እሱ ነው’ ብዬ የነገርኩህ ሰው ይህ ነው” አለው።+

18 ከዚያም ሳኦል በሩ መሃል ላይ ወደነበረው ወደ ሳሙኤል ቀርቦ “እባክህ፣ የባለ ራእዩ ቤት የት እንደሆነ ትነግረኛለህ?” አለው። 19 ሳሙኤልም ለሳኦል እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “ባለ ራእዩ እኔ ነኝ። ከእኔ ቀድመህ ወደ ኮረብታው ውጣ፤ ዛሬ አብራችሁኝ ትበላላችሁ።+ በማለዳም አሰናብትሃለሁ፤ ማወቅ የምትፈልገውንም ነገር ሁሉ* እነግርሃለሁ። 20 ከሦስት ቀን በፊት ስለጠፉብህ አህዮች አትጨነቅ፤+ ምክንያቱም ተገኝተዋል። በእስራኤል ውስጥ ያለው ምርጥ ነገር ሁሉ የማን ነው? የአንተና የመላው የአባትህ ቤት አይደለም?”+ 21 በዚህ ጊዜ ሳኦል እንዲህ አለው፦ “እኔ ከእስራኤል ነገዶች ሁሉ አነስተኛ ከሆነው ከቢንያም ነገድ የተገኘሁ ቢንያማዊ አይደለሁም?+ ቤተሰቤስ ቢሆን ከቢንያም ነገድ ቤተሰቦች መካከል እዚህ ግባ የሚባል ሆኖ ነው? ታዲያ እንዲህ የምትለኝ ለምንድን ነው?”

22 ከዚያም ሳሙኤል ሳኦልንና አገልጋዩን ወደ መመገቢያ አዳራሹ ይዟቸው ሄደ፤ እነሱንም በተጋበዙት ሰዎች ፊት በክብር ቦታ አስቀመጣቸው፤ ተጋባዦቹም 30 ገደማ ነበሩ። 23 ሳሙኤልም ምግብ የሚያበስለውን ሰው “‘ለይተህ አስቀምጠው’ ብዬ የሰጠሁህን ድርሻ አምጣው” አለው። 24 በዚህ ጊዜ ምግብ የሚያበስለው ሰው ጭኑንና ላዩ ላይ የነበረውን አንስቶ ሳኦል ፊት አስቀመጠው። ሳሙኤልም እንዲህ አለው፦ “ተለይቶ ተቀምጦ የነበረው ፊትህ ቀርቦልሃል። ይህ ለዚህ ጊዜ ብለው ለይተው ያስቀመጡልህ ስለሆነ ብላ። ምክንያቱም ‘እንግዶች ጋብዣለሁ’ ብዬ ነግሬያቸዋለሁ።” በመሆኑም ሳኦል በዚያ ቀን ከሳሙኤል ጋር በላ። 25 ከዚያም ከኮረብታው+ ወደ ከተማው ወረዱ፤ ሳሙኤልም ከሳኦል ጋር በቤቱ ሰገነት ላይ ሲነጋገር ቆየ። 26 እነሱም በማለዳ ተነሱ፤ ጎህ እንደቀደደም ሳሙኤል ሳኦልን ወደ ቤቱ ሰገነት ጠርቶ “በል ተዘጋጅና ላሰናብትህ” አለው። ስለዚህ ሳኦል ተዘጋጀ፤ ከዚያም እሱና ሳሙኤል ወደ ውጭ ወጡ። 27 እነሱም በከተማዋ ዳርቻ ቁልቁል እየወረዱ ሳሉ ሳሙኤል ሳኦልን “አገልጋይህ+ ቀድሞን እንዲሄድ ንገረው” አለው፤ እሱም ቀድሞ ሄደ። ሳሙኤልም “አንተ ግን የአምላክን ቃል እንዳሰማህ እዚሁ ቁም” አለው።

10 ሳሙኤልም የዘይት ዕቃውን አንስቶ ዘይቱን በሳኦል ራስ ላይ አፈሰሰው።+ ከዚያም ሳመውና እንዲህ አለው፦ “በርስቱ+ ላይ መሪ እንድትሆን ይሖዋ ቀብቶህ የለም?+ 2 ዛሬ ከእኔ ተለይተህ ስትሄድ በቢንያም ግዛት ውስጥ በምትገኘው በጸልጻህ ባለው የራሔል መቃብር+ አጠገብ ሁለት ሰዎች ታገኛለህ፤ እነሱም እንዲህ ይሉሃል፦ ‘ስትፈልጋቸው የነበሩት አህዮች ተገኝተዋል፤ አባትህ ግን ስለ አህዮቹ ማሰቡን ትቶ+ ስለ እናንተ እየተጨነቀ ነው። ደግሞም “የልጄን ነገር ምን ባደርግ ይሻላል?” እያለ ነው።’ 3 አንተም ከዚያ ተነስተህ ታቦር የሚገኘው ትልቅ ዛፍ አጠገብ እስክትደርስ ድረስ ጉዞህን ቀጥል፤ እዚያም ሦስት ሰዎች በቤቴል+ ወደሚገኘው ወደ እውነተኛው አምላክ ሲወጡ ታገኛለህ፤ እነሱም አንደኛው ሦስት የፍየል ግልገል፣ ሌላኛው ሦስት ዳቦ፣ ሌላኛው ደግሞ በእንስራ የወይን ጠጅ ይዘዋል። 4 እነዚህ ሰዎች ስለ ደህንነትህ ከጠየቁህ በኋላ ሁለት ዳቦ ይሰጡሃል፤ አንተም ዳቦዎቹን ተቀበላቸው። 5 ከዚህ በኋላ የፍልስጤማውያን የጦር ሰፈር ወዳለበት ወደ እውነተኛው አምላክ ኮረብታ ትመጣለህ። ወደ ከተማዋም በምትደርስበት ጊዜ ትንቢት እየተናገረ ከኮረብታው የሚወርድ አንድ የነቢያት ቡድን ታገኛለህ፤ ከፊት ከፊቱም ባለ አውታር መሣሪያ፣ አታሞ፣ ዋሽንትና በገና የሚጫወቱ ሰዎች ይሄዳሉ። 6 የይሖዋ መንፈስ ኃይል ይሰጥሃል፤+ አንተም ከእነሱ ጋር ትንቢት ትናገራለህ፤ ተለውጠህም እንደ ሌላ ሰው ትሆናለህ።+ 7 እነዚህ ምልክቶች ሲፈጸሙ ስታይ ማድረግ የምትችለውን ሁሉ አድርግ፤ ምክንያቱም እውነተኛው አምላክ ከአንተ ጋር ነው። 8 ከዚያም ከእኔ ቀድመህ ወደ ጊልጋል+ ውረድ፤ እኔም የሚቃጠሉ መሥዋዕቶችንና የኅብረት መሥዋዕቶችን ለማቅረብ አንተ ወዳለህበት እወርዳለሁ። እኔ ወደ አንተ እስክመጣ ድረስ ሰባት ቀን መጠበቅ አለብህ። ከዚያም ምን ማድረግ እንዳለብህ አሳውቅሃለሁ።”

9 ሳኦልም ከሳሙኤል ተለይቶ ለመሄድ ፊቱን ሲያዞር አምላክ የሳኦል ልብ ወደ ሌላ ሰው ልብ እንዲለወጥ አደረገ፤ እነዚህም ሁሉ ምልክቶች በዚያው ቀን ተፈጸሙ። 10 በመሆኑም ከዚያ ተነስተው ወደ ኮረብታው ሄዱ፤ አንድ የነቢያት ቡድንም አገኘው። ወዲያውም የአምላክ መንፈስ ኃይል ሰጠው፤+ እሱም አብሯቸው ትንቢት መናገር ጀመረ።+ 11 ቀደም ሲል ያውቁት የነበሩት ሁሉ ከነቢያቱ ጋር ሆኖ ትንቢት ሲናገር ሲያዩት እርስ በርሳቸው “የቂስ ልጅ ምን ሆኗል? ሳኦልም ከነቢያት አንዱ ሆነ እንዴ?” ተባባሉ። 12 ከዚያም የአካባቢው ነዋሪ የሆነ አንድ ሰው “ለመሆኑ የእነሱስ አባት ማን ነው?” አለ። “ሳኦልም ከነቢያት አንዱ ሆነ እንዴ?” የሚል ምሳሌያዊ አባባል የኖረው በዚህ የተነሳ ነው።+

13 እሱም ትንቢት ተናግሮ ሲጨርስ ወደ ኮረብታው መጣ። 14 በኋላም የሳኦል አባት ወንድም ሳኦልንና አገልጋዩን “የት ነበራችሁ?” ሲል ጠየቃቸው። ሳኦልም “አህዮቹን ፍለጋ ሄደን ነበር፤+ ሆኖም በዚያ ልናገኛቸው ስላልቻልን ወደ ሳሙኤል ሄድን” አለው። 15 የሳኦልም አጎት “እስቲ ንገረኝ፣ ሳሙኤል ምን አላችሁ?” አለው። 16 ሳኦልም መልሶ አጎቱን “አህዮቹ መገኘታቸውን በትክክል ነገረን” አለው። ይሁን እንጂ ሳሙኤል ስለ ንግሥና የነገረውን ነገር አልነገረውም።

17 ከዚያም ሳሙኤል ሕዝቡን በምጽጳ+ በይሖዋ ፊት እንዲሰበሰብ ከጠራ በኋላ 18 እስራኤላውያንን እንዲህ አላቸው፦ “የእስራኤል አምላክ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘እስራኤልን ከግብፅ ያወጣሁት እንዲሁም ከግብፅ እጅና+ ይጨቁኗችሁ ከነበሩት መንግሥታት ሁሉ እጅ የታደግኳችሁ እኔ ነኝ። 19 ዛሬ ግን እናንተ ከመከራችሁና ከጭንቀታችሁ ሁሉ ያዳናችሁን አምላካችሁን አንቀበልም በማለት+ “አይሆንም፣ ንጉሥ እንዲነግሥልን እንፈልጋለን” አላችሁ። ስለዚህ አሁን በየነገዳችሁና በየሺህ ምድባችሁ* ሆናችሁ በይሖዋ ፊት ቁሙ።’”

20 ስለዚህ ሳሙኤል የእስራኤል ነገዶች በሙሉ እንዲቀርቡ አደረገ፤+ ከእነሱም መካከል የቢንያም ነገድ ተመረጠ።+ 21 ከዚያም የቢንያም ነገድ በየቤተሰቡ ሆኖ እንዲቀርብ አደረገ፤ የማጥራውያን ቤተሰብም ተመረጠ። በመጨረሻም የቂስ ልጅ ሳኦል ተመረጠ።+ ሆኖም ፈልገው ሊያገኙት አልቻሉም። 22 ስለዚህ “ለመሆኑ ሰውየው እዚህ መጥቷል?” በማለት ይሖዋን ጠየቁ።+ ይሖዋም “ያውላችሁ፣ ጓዙ መካከል ተደብቋል” አላቸው። 23 በመሆኑም ሮጠው ከዚያ አመጡት። እሱም በሕዝቡ መካከል በቆመ ጊዜ ከትከሻው በላይ ዘለግ ብሎ በቁመት ከሌሎቹ ሰዎች ሁሉ በልጦ ይታይ ነበር።+ 24 ሳሙኤልም ሕዝቡን ሁሉ “ይሖዋ የመረጠውን ሰው አያችሁት?+ ከሕዝቡ ሁሉ መካከል እንደ እሱ ያለ የለም” አላቸው። ሕዝቡም ሁሉ “ንጉሡ ለዘላለም ይኑር!” በማለት መጮኽ ጀመረ።

25 ሳሙኤልም ለነገሥታት ምን ሊደረግላቸው እንደሚገባ ለሕዝቡ ተናገረ፤+ እንዲሁም በመጽሐፍ ጽፎ በይሖዋ ፊት አስቀመጠው። ከዚያም ሳሙኤል ሕዝቡን ሁሉ ወደየቤቱ አሰናበተ። 26 ሳኦልም ይሖዋ ልባቸውን ባነሳሳው ተዋጊዎች ታጅቦ በጊብዓ ወዳለው ቤቱ ሄደ። 27 አንዳንድ የማይረቡ ሰዎች ግን “ይህ ሰው እንዴት ሊያድነን ይችላል?” አሉ።+ በመሆኑም ናቁት፤ ምንም ዓይነት ስጦታም አላመጡለትም።+ እሱ ግን ዝም አለ።*

11 ከዚያም አሞናዊው+ ናሃሽ ወጥቶ በጊልያድ የምትገኘውን ኢያቢስን ከበባት። የኢያቢስ+ ሰዎች በሙሉ ናሃሽን “ከእኛ ጋር ቃል ኪዳን ግባ፤* እኛም እናገለግልሃለን” አሉት። 2 አሞናዊው ናሃሽም “ከእናንተ ጋር ቃል ኪዳን የምገባው የእያንዳንዳችሁ ቀኝ ዓይን ከወጣ ነው። ይህን የማደርገውም መላውን እስራኤል ለማዋረድ ስል ነው” አላቸው። 3 የኢያቢስ ሽማግሌዎችም “ወደ መላው የእስራኤል ግዛት መልእክተኞችን እንድንልክ የሰባት ቀን ጊዜ ስጠን። ከዚያም የሚያድነን ሰው ከሌለ ለአንተ እጃችንን እንሰጣለን” ሲሉ መለሱለት። 4 መልእክተኞቹም ሳኦል ወደሚገኝበት ወደ ጊብዓ+ መጥተው ይህን መልእክት ለሕዝቡ ተናገሩ፤ ሕዝቡም ሁሉ ድምፁን ከፍ አድርጎ አለቀሰ።

5 ሳኦል ግን መንጋውን እየነዳ ከመስክ በመምጣት ላይ ነበር፤ ሳኦልም “ሕዝቡ የሚያለቅሰው ምን ሆኖ ነው?” አለ። እነሱም የኢያቢስ ሰዎች ያሏቸውን ነገሩት። 6 ሳኦልም ይህን ሲሰማ የአምላክ መንፈስ ኃይል ሰጠው፤+ ቁጣውም ነደደ። 7 እሱም ጥንድ በሬዎችን ወስዶ ቆራረጣቸው፤ እነዚህንም በመልእክተኞቹ እጅ አስይዞ “ሳኦልንና ሳሙኤልን የማይከተል ማንኛውም ሰው ከብቱ እንዲህ ይቆራረጣል!” በማለት እንዲናገሩ ወደ መላው የእስራኤል ግዛት ላካቸው። በሕዝቡም ላይ የይሖዋ ፍርሃት ስለወደቀ ሕዝቡ እንደ አንድ ሰው ሆኖ ወጣ። 8 ከዚያም ሳኦል ሰዎቹን ቤዜቅ ላይ ቆጠራቸው፤ እነሱም 300,000 እስራኤላውያንና 30,000 የይሁዳ ሰዎች ነበሩ። 9 የመጡትንም መልእክተኞች እንዲህ አሏቸው፦ “በጊልያድ ባለችው በኢያቢስ የሚኖሩትን ሰዎች ‘በነገው ዕለት ፀሐይዋ በምትከርበት ጊዜ መዳን ታገኛላችሁ’ በሏቸው።” ከዚያም መልእክተኞቹ መጥተው ለኢያቢስ ሰዎች ነገሯቸው፤ እነሱም በደስታ ፈነደቁ። 10 ስለሆነም የኢያቢስ ሰዎች “ነገ እጃችንን ለእናንተ እንሰጣለን፤ እናንተም መልካም መስሎ የታያችሁን ሁሉ ልታደርጉብን ትችላላችሁ” አሏቸው።+

11 በማግስቱ ሳኦል ሕዝቡን በሦስት ቡድን ከፈለው፤ እነሱም በማለዳው ክፍለ ሌሊት* ወደ አሞናውያን+ ሰፈር ገብተው ፀሐይዋ እስክትከር ድረስ መቷቸው። የተረፉትም ቢሆኑ ሁለቱ እንኳ አንድ ላይ መሆን እስከማይችሉ ድረስ ተበታተኑ። 12 ከዚያም ሕዝቡ ሳሙኤልን “‘አሁን ሳኦል በእኛ ላይ ንጉሥ ሊሆን ነው?’ ሲሉ የነበሩት እነማን ናቸው?+ እነዚህን ሰዎች ስጡንና እንግደላቸው” አለው። 13 ሳኦል ግን “ይህ ዕለት ይሖዋ እስራኤልን ያዳነበት ስለሆነ በዚህ ቀን ማንም ሰው መገደል የለበትም” አለ።+

14 በኋላም ሳሙኤል ሕዝቡን “ኑ፣ ወደ ጊልጋል+ እንውጣና ንግሥናውን እንደገና እናጽና” አለ።+ 15 በመሆኑም ሕዝቡ ሁሉ ወደ ጊልጋል ሄደ፤ በጊልጋልም ሳኦልን በይሖዋ ፊት አነገሡት። በዚያም በይሖዋ ፊት የኅብረት መሥዋዕቶችን አቀረቡ፤+ ሳኦልና የእስራኤል ሰዎች ሁሉ እጅግ ተደሰቱ።+

12 በመጨረሻም ሳሙኤል እስራኤላውያንን ሁሉ እንዲህ አላቸው፦ “እንግዲህ እኔ ያላችሁኝን ሁሉ አድርጌአለሁ፤* የሚገዛችሁም ንጉሥ አንግሼላችኋለሁ።+ 2 የሚመራችሁ* ንጉሥ ይኸው!+ እኔ ዕድሜዬ ገፍቷል፤ ፀጉሬም ሸብቷል፤ እነሆ፣ ልጆቼ አብረዋችሁ ናቸው፤+ እኔ እንደሆንኩ ከልጅነቴ ጀምሮ እስከዚህ ቀን ድረስ ስመራችሁ ቆይቻለሁ።+ 3 አሁንም ያለሁት በፊታችሁ ነው። እስቲ የምከሰስበት ነገር ካለ በይሖዋና እሱ በቀባው+ ፊት ንገሩኝ፦ የማንን በሬ ወይም የማንን አህያ ወስጃለሁ?+ ወይስ ማንን አታልያለሁ? ደግሞስ በማን ላይ ግፍ ፈጽሜአለሁ? አይቼ እንዳላየሁ ለመሆንስ ከማን እጅ ጉቦ ተቀብያለሁ?+ እንዲህ አድርጌ ከሆነ እመልስላችኋለሁ።”+ 4 በዚህ ጊዜ እነሱ “አታለኸንም ሆነ ግፍ ፈጽመህብን ወይም ደግሞ ከማንም ሰው እጅ ምንም ነገር ተቀብለህ አታውቅም” አሉት። 5 በመሆኑም ሳሙኤል “እኔን የምትከሱበት ምንም ነገር እንዳላገኛችሁ* ይሖዋም ሆነ እሱ የቀባው ዛሬ በእናንተ ላይ ምሥክሮች ናቸው” አላቸው። እነሱም “እሱ ምሥክር ነው” አሉ።

6 ሳሙኤልም ለሕዝቡ እንዲህ አለ፦ “ሙሴንና አሮንን የመረጠው እንዲሁም አባቶቻችሁን ከግብፅ ምድር ያወጣው+ ይሖዋ ምሥክር ነው። 7 እንግዲህ እናንተ ባላችሁበት ቁሙ፤ እኔም ይሖዋ ለእናንተና ለአባቶቻችሁ ባደረጋቸው የጽድቅ ሥራዎች መሠረት በይሖዋ ፊት እፋረዳችኋለሁ።

8 “ያዕቆብ ወደ ግብፅ በገባና+ አባቶቻችሁም ይሖዋ እንዲረዳቸው በጮኹ ጊዜ+ ይሖዋ አባቶቻችሁን ከግብፅ መርተው እንዲያወጧቸውና በዚህ ስፍራ እንዲያኖሯቸው+ ሙሴንና አሮንን ላከ።+ 9 እነሱ ግን አምላካቸውን ይሖዋን ረሱ፤ እሱም የሃጾር ሠራዊት አለቃ ለነበረው ለሲሳራ፣+ ለፍልስጤማውያንና ለሞዓብ+ ንጉሥ እጅ+ አሳልፎ ሸጣቸው፤+ እነሱም ወጓቸው። 10 በዚህ ጊዜ ይሖዋ እንዲረዳቸው ጮኹ፤+ እንዲህም አሉ፦ ‘ባአልንና+ የአስታሮትን+ ምስሎች ለማገልገል ስንል ይሖዋን ስለተውን ኃጢአት ሠርተናል፤+ ስለሆነም እንድናገለግልህ አሁን ከጠላቶቻችን እጅ ታደገን።’ 11 ከዚያም ይሖዋ ያለስጋት መኖር እንድትችሉ የሩባአልን፣+ ቤዳንን፣ ዮፍታሔንና+ ሳሙኤልን+ ልኮ በዙሪያችሁ ካሉት ጠላቶቻችሁ ሁሉ እጅ ታደጋችሁ።+ 12 የአሞናውያን ንጉሥ የሆነው ናሃሽ+ በእናንተ ላይ ጥቃት ለመሰንዘር እንደመጣ ስታዩ ምንም እንኳ አምላካችሁ ይሖዋ ንጉሣችሁ ቢሆንም+ ‘አይሆንም፣ ንጉሥ እንዲነግሥልን እንፈልጋለን!’ አላችሁኝ።+ 13 እንግዲህ የመረጣችሁትና የጠየቃችሁት ንጉሥ ይኸውላችሁ። እነሆ፣ ይሖዋ በላያችሁ ንጉሥ አንግሦአል።+ 14 ይሖዋን ብትፈሩና+ ብታገለግሉ፣+ ቃሉን ብትታዘዙና+ በይሖዋ ትእዛዝ ላይ ባታምፁ እንዲሁም እናንተም ሆናችሁ በላያችሁ የሚገዛው ንጉሥ አምላካችሁን ይሖዋን ብትከተሉ መልካም ይሆንላችኋል። 15 ሆኖም የይሖዋን ቃል ባትታዘዙና በይሖዋ ትእዛዝ ላይ ብታምፁ የይሖዋ እጅ በእናንተና በአባቶቻችሁ ላይ ይሆናል።+ 16 ስለሆነም አሁን ባላችሁበት ቆማችሁ ይሖዋ ዓይናችሁ እያየ የሚፈጽመውን ይህን ታላቅ ነገር ተመልከቱ። 17 ዛሬ የስንዴ መከር የሚታጨድበት ጊዜ አይደለም? ይሖዋን ነጎድጓድና ዝናብ እንዲልክ እጠይቀዋለሁ፤ እናንተም ንጉሥ እንዲነግሥላችሁ በመጠየቅ በይሖዋ ፊት ምን ያህል ታላቅ በደል እንደፈጸማችሁ ታውቃላችሁ፤ ደግሞም ታስተውላላችሁ።”+

18 ከዚያም ሳሙኤል ይሖዋን ጠየቀ፤ ይሖዋም በዚያ ቀን ነጎድጓድና ዝናብ ላከ፤ በመሆኑም ሕዝቡ ሁሉ ይሖዋንና ሳሙኤልን እጅግ ፈራ። 19 ሕዝቡም ሳሙኤልን “ሌላው ኃጢአታችን ሳያንሰን ንጉሥ እንዲነግሥልን በመለመን ተጨማሪ በደል ስለፈጸምን እንዳንሞት ስለ አገልጋዮችህ ወደ አምላክህ ወደ ይሖዋ ጸልይልን”+ አለው።

20 በመሆኑም ሳሙኤል ሕዝቡን እንዲህ አለ፦ “አትፍሩ። እርግጥ ይህን ሁሉ ክፋት ፈጽማችኋል። ብቻ ይሖዋን ከመከተል ዞር አትበሉ፤+ ይሖዋንም በሙሉ ልባችሁ አገልግሉት።+ 21 ምንም ዋጋ የሌላቸውንና+ ማዳን የማይችሉ ከንቱ+ ነገሮችን* ወደ መከተል ዞር አትበሉ፤ ምክንያቱም እነሱ ከንቱ* ነገሮች ናቸው። 22 ይሖዋ ስለ ታላቁ ስሙ ሲል+ ሕዝቡን አይተውም፤+ ምክንያቱም ይሖዋ እናንተን የራሱ ሕዝብ ሊያደርጋችሁ ፈልጓል።+ 23 እኔም ብሆን ስለ እናንተ መጸለዬን በመተው በይሖዋ ላይ ኃጢአት መሥራት ፈጽሞ የማላስበው ነገር ነው፤ እንዲሁም መልካምና ትክክለኛ የሆነውን መንገድ እናንተን ማስተማሬን እቀጥላለሁ። 24 ብቻ እናንተ ይሖዋን ፍሩ፤+ በሙሉ ልባችሁም በታማኝነት* አገልግሉት፤ ለእናንተ ያደረጋቸውን ታላላቅ ነገሮች አስታውሱ።+ 25 ሆኖም በግትርነት መጥፎ ነገር ማድረጋችሁን ብትቀጥሉ እናንተም ሆናችሁ ንጉሣችሁ+ ተጠራርጋችሁ ትጠፋላችሁ።”+

13 ሳኦል በነገሠ ጊዜ ዕድሜው . . .* ነበር፤+ እሱም በእስራኤል ላይ ሁለት ዓመት ገዛ። 2 ሳኦል ከእስራኤላውያን መካከል 3,000 ሰዎችን መረጠ፤ ከእነዚህም መካከል 2,000ዎቹ በሚክማሽና በቤቴል ተራራማ አካባቢ ከሳኦል ጋር ሆኑ፤ ሌሎቹ 1,000 ሰዎች ደግሞ በቢንያም ግዛት በጊብዓ+ ከዮናታን+ ጋር ሆኑ። የቀሩትን ሰዎች እያንዳንዳቸውን ወደየድንኳናቸው አሰናበታቸው። 3 ዮናታንም በጌባ+ የነበረውን የፍልስጤማውያንን+ የጦር ሰፈር መታ፤ ፍልስጤማውያንም ይህን ሰሙ። ሳኦልም “ዕብራውያን ይስሙ!” በማለት በምድሩ ሁሉ ቀንደ መለከት አስነፋ።+ 4 እስራኤላውያን በሙሉ “ሳኦል የፍልስጤማውያንን የጦር ሰፈር መታ፤ እስራኤላውያንም በፍልስጤማውያን ዘንድ እንደ ግም ተቆጠሩ” ሲባል ሰሙ። በመሆኑም ሕዝቡ ሳኦልን ለመከተል በጊልጋል ተሰበሰበ።+

5 ፍልስጤማውያንም 30,000 የጦር ሠረገሎች፣ 6,000 ፈረሰኞችና በባሕር ዳር እንዳለ አሸዋ እጅግ ብዙ የሆነ ሠራዊት ይዘው ከእስራኤላውያን ጋር ለመዋጋት ተሰባሰቡ፤+ እነሱም ወጥተው ከቤትአዌን+ በስተ ምሥራቅ በሚክማሽ ሰፈሩ። 6 የእስራኤል ሰዎችም አደጋ እንደተጋረጠባቸው ስላዩ ከፍተኛ ውጥረት ውስጥ ገብተው ነበር፤ በመሆኑም ሕዝቡ በየዋሻው፣ በየጉድጓዱ፣ በየዓለቱ፣ በየጎሬውና በየውኃ ማጠራቀሚያ ጉድጓዱ ውስጥ ተደበቀ።+ 7 እንዲያውም አንዳንድ ዕብራውያን ዮርዳኖስን ተሻግረው ወደ ጋድና ወደ ጊልያድ+ ምድር ሄዱ። ሳኦል ግን እዚያው ጊልጋል ነበር፤ የተከተሉት ሰዎችም ሁሉ በፍርሃት ይንቀጠቀጡ ነበር። 8 እሱም ሳሙኤል የቀጠረው ጊዜ እስኪደርስ ድረስ ለሰባት ቀን ጠበቀ፤ ሳሙኤል ግን ወደ ጊልጋል አልመጣም፤ ሕዝቡም ሳኦልን ትቶ መበታተን ጀመረ። 9 በመጨረሻም ሳኦል “የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የኅብረት መሥዋዕቶቹን አምጡልኝ” አለ። ከዚያም የሚቃጠለውን መሥዋዕት አቀረበ።+

10 ሆኖም ሳኦል የሚቃጠለውን መሥዋዕት አቅርቦ እንደጨረሰ ሳሙኤል መጣ። በመሆኑም ሳኦል ሊቀበለውና ሊባርከው ወጣ። 11 ከዚያም ሳሙኤል “ያደረግከው ነገር ምንድን ነው?” አለው። ሳኦልም እንዲህ ሲል መለሰ፦ “ሕዝቡ ትቶኝ መበታተን እንደጀመረና+ አንተም በተቀጠረው ጊዜ እንዳልመጣህ እንዲሁም ፍልስጤማውያኑ በሚክማሽ+ እየተሰባሰቡ መሆናቸውን አየሁ። 12 በመሆኑም ‘እንግዲህ ፍልስጤማውያን ወደ ጊልጋል ወርደው ሊወጉኝ ነው፤ እኔ ደግሞ ይሖዋ ሞገስ እንዲያሳየኝ አለመንኩም’ ብዬ አሰብኩ። ስለሆነም የሚቃጠለውን መሥዋዕት ማቅረብ ግድ ሆነብኝ።”

13 በዚህ ጊዜ ሳሙኤል ሳኦልን እንዲህ አለው፦ “የፈጸምከው የሞኝነት ድርጊት ነው። አምላክህ ይሖዋ የሰጠህን ትእዛዝ አልጠበቅክም።+ ጠብቀህ ቢሆን ኖሮ ይሖዋ መንግሥትህን በእስራኤል ላይ ለዘላለም ባጸናልህ ነበር። 14 አሁን ግን መንግሥትህ አይዘልቅም።+ ይሖዋ እንደ ልቡ የሚሆንለት ሰው ያገኛል፤+ ይሖዋም በሕዝቡ ላይ መሪ አድርጎ ይሾመዋል፤+ ምክንያቱም አንተ የይሖዋን ትእዛዝ አልጠበቅክም።”+

15 ከዚያም ሳሙኤል ተነስቶ ከጊልጋል በቢንያም ግዛት ወደምትገኘው ወደ ጊብዓ ወጣ፤ ሳኦልም ሕዝቡን ቆጠረ፤ አብረውት ያሉት ሰዎች ብዛታቸው 600 ገደማ ነበር።+ 16 ሳኦልና ልጁ ዮናታን እንዲሁም አብረዋቸው የቀሩት ሰዎች በቢንያም ግዛት በምትገኘው በጌባ+ ሰፍረው የነበረ ሲሆን ፍልስጤማውያን ደግሞ በሚክማሽ+ ሰፍረው ነበር። 17 በሦስት ምድብ የተከፈለው የወራሪዎች ቡድን ከፍልስጤማውያን ሰፈር ይወጣል። አንደኛው ቡድን ወደ ሹአል ምድር ወደ ኦፍራ ወደሚወስደው መንገድ ያቀናል፤ 18 ሌላኛው ቡድን ወደ ቤትሆሮን+ ወደሚወስደው መንገድ ይሄዳል፤ ሦስተኛው ቡድን ደግሞ የጸቦይምን ሸለቆ ቁልቁል ወደሚያሳየው ወሰን ይኸውም ወደ ምድረ በዳው ወደሚወስደው መንገድ ያቀናል።

19 በመላው የእስራኤል ምድር አንድም ብረት ቀጥቃጭ አልነበረም፤ ምክንያቱም ፍልስጤማውያን “ዕብራውያን ሰይፍ ወይም ጦር እንዳይሠሩ” ብለው ነበር። 20 ስለዚህ እስራኤላውያን በሙሉ ማረሻቸውን ወይም ዶማቸውን አሊያም መጥረቢያቸውን ወይም ማጭዳቸውን ለማሳል ወደ ፍልስጤማውያን ይወርዱ ነበር። 21 ማረሻ፣ ዶማ፣ መንሽና መጥረቢያ ለማሳል እንዲሁም የበሬ መውጊያ ለማሳሰር ዋጋው አንድ ፊም* ነበር። 22 ውጊያው በተደረገበት ቀን ከሳኦልና ከዮናታን ጋር ባሉት ሰዎች እጅ አንድም ሰይፍ ወይም ጦር አልተገኘም፤ መሣሪያ የነበራቸው ሳኦልና ልጁ ዮናታን ብቻ ነበሩ።+

23 በዚህ ጊዜ አንደኛው የፍልስጤማውያን ጦር በሚክማሽ+ ወደሚገኝ ጠባብ ሸለቆ ወጥቶ ነበር።

14 አንድ ቀን የሳኦል ልጅ ዮናታን+ ጋሻ ጃግሬውን “ና፣ በዚያ በኩል ወዳለው የፍልስጤማውያን የጦር ሰፈር እንሻገር” አለው። ይህን ግን ለአባቱ አልነገረውም። 2 ሳኦልም በጊብዓ+ ዳርቻ በሚግሮን በሚገኘው የሮማን ዛፍ ሥር ሰፍሮ ነበር፤ ከእሱም ጋር 600 ሰዎች ነበሩ።+ 3 (በሴሎ+ የይሖዋ ካህን የሆነው የኤሊ+ ልጅ፣ የፊንሃስ+ ልጅ፣ የኢካቦድ+ ወንድም የአኪጡብ+ ልጅ አኪያህ ኤፉድ ለብሶ ነበር።)+ ሕዝቡም ዮናታን መሄዱን አላወቀም። 4 ዮናታን ወደ ፍልስጤማውያን የጦር ሰፈር ለመሻገር ባሰበባቸው መተላለፊያዎች መካከል በአንደኛው በኩል እንደ ጥርስ የሾለ ዓለት፣ በሌላኛውም በኩል እንደ ጥርስ የሾለ ዓለት ነበር፤ የአንደኛው ስም ቦጼጽ ሲሆን የሌላኛው ስም ደግሞ ሴኔ ነበር። 5 አንደኛው ዓለት በሚክማሽ ትይዩ በስተ ሰሜን እንደ ዓምድ ቆሞ ነበር፤ ሌላኛው ደግሞ በጊብዓ+ ትይዩ በስተ ደቡብ ቆሞ ነበር።

6 በመሆኑም ዮናታን ጋሻ ጃግሬውን “ና፣ ወደ እነዚህ ያልተገረዙ ሰዎች የጦር ሰፈር እንሻገር።+ ይሖዋ በብዙም ሆነ በጥቂት ሰዎች ተጠቅሞ ከማዳን የሚያግደው ነገር ስለሌለ ምናልባት ይሖዋ ስለ እኛ ሲል እርምጃ ይወስድ ይሆናል” አለው።+ 7 በዚህ ጊዜ ጋሻ ጃግሬው “ልብህ ያነሳሳህን ማንኛውንም ነገር አድርግ። ወደፈለግክበት ሂድ፤ እኔም ልብህ ወዳነሳሳህ ወደየትኛውም ቦታ ተከትዬህ እሄዳለሁ” አለው። 8 ከዚያም ዮናታን እንዲህ አለው፦ “እንግዲያውስ ወደ እነዚያ ሰዎች እንሻገርና እንታያቸው። 9 እነሱም ‘ወደ እናንተ እስክንመጣ ድረስ ባላችሁበት ጠብቁን’ ካሉን ባለንበት ሆነን እንጠብቃቸዋለን፤ ወደ እነሱም አንወጣም። 10 ይሁንና ‘ውጡና ግጠሙን!’ ካሉን ወደዚያ እንወጣለን፤ ምክንያቱም ይሖዋ እነሱን በእጃችን አሳልፎ ይሰጠናል። እንግዲህ ይህ ምልክት ይሆነናል።”+

11 ከዚያም ሁለቱ ወጥተው ለፍልስጤማውያን የጦር ሰፈር ታዩ። ፍልስጤማውያኑም “አያችሁ፣ ዕብራውያኑ ከተደበቁባቸው ጉድጓዶች እየወጡ ነው” አሉ።+ 12 በመሆኑም በጦር ሰፈሩ የነበሩት ሰዎች ዮናታንንና ጋሻ ጃግሬውን “ኑ፣ ወደ እኛ ውጡ፤ እናሳያችኋለን!” አሏቸው።+ ዮናታንም ወዲያውኑ ጋሻ ጃግሬውን “ይሖዋ እስራኤላውያን እጅ ላይ ስለሚጥላቸው ተከተለኝ” አለው።+ 13 ዮናታንም በእጁና በእግሩ እየቧጠጠ ወጣ፤ ጋሻ ጃግሬውም ይከተለው ነበር፤ ዮናታንም በፍልስጤማውያን ላይ ጥቃት ሰነዘረ፤ ጋሻ ጃግሬውም ከኋላው እየተከተለ ገደላቸው። 14 ዮናታንና ጋሻ ጃግሬው መጀመሪያ ላይ በሰነዘሩት ጥቃት አንድ ጥማድ በሚያውል የእርሻ መሬት ላይ ግማሽ ትልም በሚያህል ቦታ 20 ሰው ገደሉ።

15 ከዚያም በእርሻው ውስጥ በሰፈረው ሠራዊትና በጦር ሰፈሩ ውስጥ በነበረው ሕዝብ ሁሉ መካከል ሽብር ተነዛ፤ ሌላው ቀርቶ ወራሪ ቡድኖቹ+ እንኳ ተሸበሩ። ምድሪቱም መንቀጥቀጥ ጀመረች፤ ከአምላክ የመጣ ሽብርም ወረደባቸው። 16 በቢንያም ግዛት በምትገኘው በጊብዓ+ የነበሩት የሳኦል ጠባቂዎችም በየአቅጣጫው ሁከት መሰራጨቱን አዩ።+

17 ሳኦልም አብረውት የነበሩትን ሰዎች “እስቲ ሕዝቡን ቁጠሩና ትቶን የሄደው ማን እንደሆነ እወቁ” አላቸው። እነሱም ሲቆጥሩ ዮናታንና ጋሻ ጃግሬው እዚያ እንዳልነበሩ ተረዱ። 18 ሳኦልም አኪያህን+ “የእውነተኛውን አምላክ ታቦት ወደዚህ አምጣ!” አለው። (በዚያ ጊዜ* የእውነተኛው አምላክ ታቦት በእስራኤላውያን ዘንድ ነበር።) 19 ሳኦል ካህኑን እያነጋገረ ሳለ በፍልስጤማውያን ሰፈር የነበረው ትርምስ ይበልጥ እየጨመረ ሄደ። ከዚያም ሳኦል ካህኑን “እያደረግክ ያለኸውን ነገር ተው”* አለው። 20 በመሆኑም ሳኦልና አብረውት የነበሩት ሰዎች በሙሉ ተሰባስበው ውጊያው ወደሚደረግበት ቦታ ሄዱ፤ እዚያ ሲደርሱም ፍልስጤማውያኑ እርስ በርሳቸው በሰይፍ ሲጨፋጨፉ አገኟቸው፤ ከፍተኛ ትርምስ ተፈጥሮ ነበር። 21 ቀደም ሲል ከፍልስጤማውያን ጋር ወግነው የነበሩትና አብረዋቸው ወደ ሰፈሩ የመጡት ዕብራውያንም በሳኦልና በዮናታን ሥር ከነበሩት እስራኤላውያን ጋር ተቀላቀሉ። 22 በተጨማሪም በኤፍሬም ተራራማ አካባቢ ተደብቀው+ የነበሩት የእስራኤል ሰዎች በሙሉ ፍልስጤማውያን እየሸሹ መሆኑን ሰሙ፤ እነሱም ከሌሎቹ ጋር በመተባበር ፍልስጤማውያንን ማሳደዱን ተያያዙት። 23 በዚህ መንገድ ይሖዋ በዚያ ቀን እስራኤልን አዳነ፤+ ውጊያውም እስከ ቤትአዌን+ ድረስ ዘለቀ።

24 ሆኖም ሳኦል “ጠላቶቼን ከመበቀሌ በፊት እስከ ማታ ድረስ እህል የሚቀምስ ሰው የተረገመ ይሁን!” በማለት ሕዝቡን አስምሎ ስለነበር በዚያ ዕለት የእስራኤል ሰዎች ተጨንቀው ዋሉ። በመሆኑም ከሕዝቡ መካከል አንድም ሰው እህል አልቀመሰም።+

25 ሕዝቡም* ሁሉ ወደ ጫካው ገባ፤ መሬቱም ላይ ማር ነበር። 26 ሕዝቡም ወደ ጫካው ሲገባ ማሩ ሲንጠባጠብ አየ፤ ሆኖም ሁሉም መሐላውን ስለፈሩ እጁን ወደ አፉ ያነሳ አንድም ሰው አልነበረም። 27 ዮናታን ግን አባቱ ሕዝቡን ሲያስምል አልሰማም ነበር፤+ በመሆኑም በእጁ የነበረውን በትር ዘርግቶ ጫፉን የማር እንጀራው ውስጥ አጠቀሰ። ከዚያም እጁን ወደ አፉ ሲመልስ ዓይኑ በራ። 28 በዚህ ጊዜ ከሕዝቡ መካከል አንዱ “አባትህ እኮ ‘በዛሬው ዕለት እህል የሚቀምስ ሰው የተረገመ ይሁን!’+ በማለት ሕዝቡን በጥብቅ አስምሏል። ሕዝቡ በጣም የተዳከመው ለዚህ ነው” አለው። 29 ዮናታን ግን እንዲህ አለ፦ “አባቴ በምድሪቱ ላይ ከባድ ችግር አምጥቷል። እኔ ይህችን ማር በመቅመሴ ዓይኖቼ እንዴት እንደበሩ እስቲ ተመልከቱ። 30 ሕዝቡ ከጠላቶቻቸው ከወሰዱት ምርኮ ዛሬ በነፃነት በልተው ቢሆን ኖሮ ምንኛ የተሻለ ይሆን ነበር!+ የተገደሉት ፍልስጤማውያንም ቁጥር ከዚህ እጅግ በበለጠ ነበር።”

31 በዚያም ዕለት ፍልስጤማውያንን ከሚክማሽ አንስተው እስከ አይሎን+ ድረስ መቷቸው፤ ሕዝቡም በጣም ተዳከመ። 32 ስለሆነም ሕዝቡ ምርኮውን በመስገብገብ ተሻምቶ ወሰደ፤ በጎችን፣ ከብቶችንና ጥጆችን ወስደው መሬት ላይ አረዷቸው፤ ሥጋውንም ከነደሙ በሉት።+ 33 በመሆኑም ሳኦል “ይኸው ሕዝቡ ሥጋውን ከነደሙ በመብላት+ በይሖዋ ላይ ኃጢአት እየሠራ ነው” ተብሎ ተነገረው። እሱም በዚህ ጊዜ “እምነት እንደሌላችሁ የሚያሳይ ድርጊት ፈጽማችኋል። በሉ አሁኑኑ አንድ ትልቅ ድንጋይ አንከባላችሁ አምጡልኝ” አለ። 34 አክሎም እንዲህ አለ፦ “በሕዝቡ መሃል ተበታትናችሁ እንዲህ በሏቸው፦ ‘እያንዳንዳችሁ በሬያችሁንና በጋችሁን አምጡ፤ በዚህም ስፍራ አርዳችሁ ብሉ። ሥጋውን ከነደሙ በመብላት በይሖዋ ላይ ኃጢአት አትሥሩ።’”+ በመሆኑም በዚያ ምሽት እያንዳንዱ ሰው በሬውን አምጥቶ በዚያ ስፍራ አረደው። 35 ሳኦልም ለይሖዋ መሠዊያ ሠራ።+ ይህ መሠዊያ ሳኦል ለይሖዋ የሠራው የመጀመሪያ መሠዊያ ነው።

36 በኋላም ሳኦል “በሌሊት ፍልስጤማውያንን ተከታትለን በመውረድ እስኪነጋ ድረስ እንበዝብዛቸው። አንድም ሰው በሕይወት አናስተርፍም” አለ። በዚህ ጊዜ ሕዝቡ “መልካም መስሎ የታየህን ማንኛውንም ነገር አድርግ” አሉት። ከዚያም ካህኑ “እዚሁ ወደ እውነተኛው አምላክ እንቅረብ” አለ።+ 37 ሳኦልም “ፍልስጤማውያንን ተከትዬ ልውረድ?+ በእስራኤላውያን እጅ እንዲወድቁ ታደርጋለህ?” በማለት አምላክን ጠየቀ። አምላክ ግን በዚያ ዕለት አልመለሰለትም። 38 በመሆኑም ሳኦል እንዲህ አለ፦ “እናንተ የሕዝቡ አለቆች ሁሉ ወደዚህ ቅረቡ፤ በዛሬው ዕለት ምን ኃጢአት እንደተፈጸመ አጣሩ። 39 እስራኤልን ባዳነው ሕያው በሆነው በይሖዋ እምላለሁ ይህን ኃጢአት የሠራው ልጄ ዮናታን ሆኖ ቢገኝ እንኳ መሞት አለበት።” ሆኖም ከሕዝቡ መካከል መልስ የሰጠው አንድም ሰው አልነበረም። 40 ከዚያም እስራኤላውያንን በሙሉ “እናንተ በአንድ በኩል ትሆናላችሁ፤ እኔና ልጄ ዮናታን ደግሞ በሌላኛው በኩል እንሆናለን” አላቸው። በዚህ ጊዜ ሕዝቡ ሳኦልን “መልካም መስሎ የታየህን ማንኛውንም ነገር አድርግ” አለው።

41 ሳኦልም ይሖዋን “የእስራኤል አምላክ ሆይ፣ በቱሚም+ አማካኝነት መልስ ስጠን!” አለው። ከዚያም ዮናታንና ሳኦል ተመረጡ፤ ሕዝቡም ነፃ ሆነ። 42 በዚህ ጊዜ ሳኦል “ከእኔና ከልጄ ከዮናታን ማን እንደሆነ ለመለየት ዕጣ ጣሉ”+ አለ። ዕጣውም በዮናታን ላይ ወጣ። 43 ሳኦልም ዮናታንን “ንገረኝ፣ ያደረግከው ነገር ምንድን ነው?” አለው። በመሆኑም ዮናታን “በእጄ ይዤው በነበረው በትር ጫፍ ትንሽ ማር ቀምሻለሁ።+ እንግዲህ ይኸው ለመሞት ዝግጁ ነኝ!” በማለት መለሰለት።

44 በዚህ ጊዜ ሳኦል “ዮናታን፣ እንደው አንተ ካልሞትክ አምላክ ይፍረድብኝ፤ የከፋም ነገር ያድርግብኝ” አለ።+ 45 ሕዝቡ ግን ሳኦልን እንዲህ አለው፦ “ለእስራኤል ይህን ታላቅ ድል*+ ያስገኘው ዮናታን መሞት ይገባዋል? ይሄማ ፈጽሞ የማይሆን ነገር ነው! ሕያው በሆነው በይሖዋ እንምላለን፣ ከራስ ፀጉሩ አንዷ እንኳ መሬት ላይ አትወድቅም፤ ምክንያቱም በዚህ ዕለት ይህን ያደረገው ከአምላክ ጋር ሆኖ ነው።”+ በዚህ መንገድ ሕዝቡ ዮናታንን ታደገው፤* እሱም ከሞት ዳነ።

46 ሳኦልም ፍልስጤማውያንን ማሳደዱን ተወ፤ ፍልስጤማውያንም ወደ ክልላቸው ሄዱ።

47 ሳኦልም በእስራኤል ላይ ንግሥናውን አጸና፤ በዙሪያው ከነበሩት ጠላቶቹ ማለትም ከሞዓባውያን፣+ ከአሞናውያን፣+ ከኤዶማውያን፣+ ከጾባህ+ ነገሥታትና ከፍልስጤማውያን+ ጋር ተዋጋ፤ በሄደበትም ሁሉ ድል ያደርጋቸው ነበር። 48 እንዲሁም በጀግንነት በመዋጋት አማሌቃውያንን+ ድል አደረገ፤ እስራኤላውያንንም ከዘራፊዎቻቸው እጅ አዳነ።

49 የሳኦል ወንዶች ልጆች ዮናታን፣ ይሽዊ እና ሜልኪሳ+ ነበሩ። እሱም ሁለት ሴቶች ልጆች የነበሩት ሲሆን የትልቋ ስም ሜሮብ፣+ የትንሿ ደግሞ ሜልኮል+ ነበር። 50 የሳኦል ሚስት የአኪማዓስ ልጅ አኪኖዓም ነበረች። የሠራዊቱ አዛዥ ደግሞ አበኔር+ ሲሆን እሱም የሳኦል አጎት የኔር ልጅ ነበር። 51 የሳኦል አባት ቂስ+ ነበር፤ የአበኔር አባት ኔር+ ደግሞ የአቢዔል ልጅ ነበር።

52 በሳኦል ዘመን ሁሉ ከፍልስጤማውያን ጋር ከባድ ውጊያ ይደረግ ነበር።+ ሳኦልም ብርቱ ወይም ደፋር ሰው ሲያገኝ ወደ ሠራዊቱ እንዲቀላቀል ይመለምለው ነበር።+

15 ከዚያም ሳሙኤል ሳኦልን እንዲህ አለው፦ “ይሖዋ በሕዝቡ በእስራኤል ላይ ንጉሥ አድርጌ እንድቀባህ የላከው እኔን ነበር፤+ እንግዲህ አሁን ይሖዋ ምን እንደሚል ስማ።+ 2 የሠራዊት ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘እስራኤላውያን ከግብፅ በወጡ ጊዜ በመንገድ ላይ እነሱን በመቃወም ለፈጸሙት ድርጊት አማሌቃውያንን እቀጣቸዋለሁ።+ 3 በል አሁን ሂድ፤ አማሌቃውያንን+ ምታቸው፤ እነሱንም ካላቸው ነገር ሁሉ ጋር ፈጽመህ አጥፋቸው።+ አንዳቸውንም አታስቀር፤* ወንድም ሆነ ሴት፣ ልጅም ሆነ ሕፃን፣ በሬም ሆነ በግ፣ ግመልም ሆነ አህያ ሁሉንም ግደል።’”+ 4 ሳኦልም ሕዝቡን በጤላይም ሰብስቦ ቆጠረ፤ በዚያም 200,000 እግረኛ ወታደሮችና 10,000 የይሁዳ ሰዎች ነበሩ።+

5 ከዚያም ሳኦል እስከ አማሌቃውያን ከተማ ድረስ በመጠጋት በሸለቆው* ውስጥ አደፈጠ። 6 ሳኦልም ቄናውያንን+ “ከአማሌቃውያን ጋር አብሬ እንዳላጠፋችሁ+ ሂዱ፣ ከእነሱ መካከል ውጡ። ምክንያቱም እናንተ እስራኤላውያን ከግብፅ በወጡበት ጊዜ ለሕዝቡ በሙሉ ታማኝ ፍቅር አሳይታችኋል”+ አላቸው። በመሆኑም ቄናውያን ከአማሌቃውያን መካከል ወጡ። 7 ከዚያም ሳኦል አማሌቃውያንን+ ከሃዊላ+ አንስቶ በግብፅ አጠገብ እስከምትገኘው እስከ ሹር+ ድረስ መታቸው። 8 እሱም የአማሌቅን ንጉሥ አጋግን+ ከነሕይወቱ ማረከው፤ የቀረውን ሕዝብ ሁሉ ግን በሰይፍ ፈጽሞ አጠፋ።+ 9 ሆኖም ሳኦልና ሕዝቡ አጋግን እንዲሁም ከመንጋው፣ ከከብቱ፣ ከደለቡት እንስሳትና ከአውራ በጎቹ መካከል ምርጥ የሆኑትንና ጥሩ ጥሩ የሆነውን ነገር ሁሉ ሳያጠፉ ተዉ።+ እነዚህን ሊያጠፏቸው አልፈለጉም። የማይረባውንና የማይፈለገውን ነገር ሁሉ ግን ፈጽመው አጠፉ።

10 ከዚያም የይሖዋ ቃል እንዲህ ሲል ወደ ሳሙኤል መጣ፦ 11 “ሳኦልን ንጉሥ በማድረጌ ተጸጽቻለሁ፤* ምክንያቱም እሱ እኔን ከመከተል ዞር ብሏል፤ ቃሌንም አልፈጸመም።”+ ሳሙኤልም በጣም ስለተረበሸ ሌሊቱን ሙሉ ወደ ይሖዋ ሲጮኽ አደረ።+ 12 ሳሙኤል ሳኦልን ለማግኘት በማለዳ ተነስቶ ሲሄድ “ሳኦል ወደ ቀርሜሎስ+ ሄዶ በዚያ ለራሱ የመታሰቢያ ሐውልት አቁሟል።+ ከዚያም ተመልሶ ወደ ጊልጋል ወርዷል” ተብሎ ተነገረው። 13 በመጨረሻም ሳሙኤል ወደ ሳኦል ሲመጣ ሳኦል “ይሖዋ ይባርክህ። የይሖዋን ቃል ፈጽሜአለሁ” አለው። 14 ሳሙኤል ግን “ታዲያ ይህ በጆሮዬ የምሰማው የበጎችና የከብቶች ድምፅ ምንድን ነው?” አለው።+ 15 በዚህ ጊዜ ሳኦል “ሕዝቡ ከአማሌቃውያን ላይ ወስዶ ያመጣቸው ናቸው፤ ከመንጋውና ከከብቶቹ መካከል ምርጥ የሆኑትን ለአምላክህ ለይሖዋ መሥዋዕት እንዲሆኑ ሳያጠፉ ተዉአቸው፤* የቀረውን ግን ሙሉ በሙሉ አጥፍተናል” አለው። 16 ሳሙኤልም ሳኦልን “ተው በቃ! ትናንት ማታ ይሖዋ ምን እንዳለኝ ልንገርህ” አለው።+ እሱም “እሺ ንገረኝ!” አለው።

17 ሳሙኤልም እንዲህ አለው፦ “በእስራኤል ነገዶች ላይ መሪ ሆነህ በተሾምክበትና ይሖዋ በእስራኤል ላይ ንጉሥ አድርጎ በቀባህ+ ጊዜ አንተ ራስህ እዚህ ግባ የማትባል ሰው እንደሆንክ ተሰምቶህ አልነበረም?+ 18 በኋላም ይሖዋ ‘ሄደህ ኃጢአተኞቹን አማሌቃውያንን ፈጽመህ አጥፋቸው።+ ጨርሰህ እስክታጠፋቸውም ድረስ ከእነሱ ጋር ተዋጋ’ በማለት ላከህ።+ 19 ታዲያ የይሖዋን ቃል ያልታዘዝከው ለምንድን ነው? ከዚህ ይልቅ ለምርኮው በመስገብገብ+ በይሖዋ ፊት መጥፎ የሆነውን ነገር አድርገሃል!”

20 ሳኦል ግን ሳሙኤልን እንዲህ አለው፦ “እኔ እኮ የይሖዋን ቃል ታዝዣለሁ! ይሖዋ የሰጠኝን ተልእኮ ለመፈጸም ሄጃለሁ፤ የአማሌቃውያንን ንጉሥ አጋግን ይዤ አምጥቻለሁ፤ አማሌቃውያንንም ፈጽሜ አጥፍቻለሁ።+ 21 ሕዝቡ ግን በጊልጋል ለአምላክህ ለይሖዋ ለመሠዋት ከምርኮው ላይ በጎችንና ከብቶችን ይኸውም ለጥፋት ከተለየው ነገር ላይ ምርጥ የሆነውን ወሰደ።”+

22 ከዚያም ሳሙኤል እንዲህ አለ፦ “ይሖዋን ይበልጥ የሚያስደስተው የትኛው ነው? የሚቃጠሉ መባዎችንና መሥዋዕቶችን+ ማቅረብ ወይስ የይሖዋን ቃል መታዘዝ? እነሆ፣ መታዘዝ ከመሥዋዕት፣+ መስማትም ከአውራ በግ ስብ+ ይበልጣል፤ 23 ምክንያቱም ዓመፀኝነት+ ሟርት+ ከመፈጸም አይተናነስም፤ እብሪተኝነትም ቢሆን ከጥንቆላና ከጣዖት አምልኮ* ተለይቶ አይታይም። አንተ የይሖዋን ቃል ስላልተቀበልክ+ እሱም የአንተን ንግሥና አልተቀበለውም።”+

24 ከዚያም ሳኦል ሳሙኤልን እንዲህ አለው፦ “ኃጢአት ሠርቻለሁ፤ ሕዝቡን በመፍራትና ቃላቸውን በመስማት የይሖዋን ትእዛዝም ሆነ የአንተን ቃል ጥሻለሁ። 25 አሁንም እባክህ ኃጢአቴን ይቅር በል፤ ለይሖዋም እንድሰግድ አብረኸኝ ተመለስ።”+ 26 ሳሙኤል ግን ሳኦልን “አንተ የይሖዋን ቃል ስላልተቀበልክና ይሖዋም በእስራኤል ላይ ንጉሥ ሆነህ እንድትቀጥል ስላልፈቀደ ከአንተ ጋር አልመለስም” አለው።+ 27 ሳሙኤል ለመሄድ ዞር ሲል ሳኦል የሳሙኤልን ልብስ ጫፍ አፈፍ አድርጎ ያዘ፤ ልብሱም ተቀደደ። 28 በዚህ ጊዜ ሳሙኤል እንዲህ አለው፦ “ይሖዋ የእስራኤልን ንጉሣዊ አገዛዝ በዛሬው ዕለት ከአንተ ቀዶታል፤ ከአንተ ለሚሻል ባልንጀራህም አሳልፎ ይሰጠዋል።+ 29 ደግሞም የእስራኤል ክቡር+ አይዋሽም+ ወይም ሐሳቡን አይቀይርም፤* ምክንያቱም እሱ ሐሳቡን ይቀይር* ዘንድ+ የሰው ልጅ አይደለም።”

30 እሱም “ኃጢአት ሠርቻለሁ። ሆኖም እባክህ በሕዝቤ ሽማግሌዎችና በእስራኤል ፊት አክብረኝ። አብረኸኝ ተመለስ፤ እኔም ለአምላክህ ለይሖዋ እሰግዳለሁ”+ አለው። 31 በመሆኑም ሳሙኤል ሳኦልን ተከትሎት ተመለሰ፤ ሳኦልም በይሖዋ ፊት ሰገደ። 32 ሳሙኤልም “የአማሌቅን ንጉሥ አጋግን አምጡልኝ” አለ። አጋግም “መቼም የሞትን መራራ ጽዋ የምቀምስበት ጊዜ አልፏል” ብሎ ስላሰበ ፈራ ተባ እያለ* ወደ እሱ ሄደ። 33 ሆኖም ሳሙኤል “በአንተ ሰይፍ የተነሳ ልጆቻቸውን ያጡ ሴቶች እንዳዘኑ ሁሉ የአንተም እናት ከሴቶች ሁሉ ይበልጥ ታዝናለች” አለው። ከዚያም ሳሙኤል በጊልጋል በይሖዋ ፊት አጋግን ቆራረጠው።+

34 ሳሙኤል ወደ ራማ ሄደ፤ ሳኦልም በጊብዓ ወደሚገኘው ቤቱ አቀና። 35 ሳሙኤልም ለሳኦል እጅግ አዘነ፤+ እስከ ዕለተ ሞቱም ድረስ ሳኦልን ዳግመኛ አላየውም። ይሖዋም ሳኦልን በእስራኤል ላይ ንጉሥ በማድረጉ ተጸጸተ።+

16 ከጊዜ በኋላ ይሖዋ ሳሙኤልን እንዲህ አለው፦ “ሳኦል በእስራኤል ላይ ንጉሥ እንዲሆን አልፈለግኩም፤+ ታዲያ አንተ ለእሱ የምታዝነው እስከ መቼ ነው?+ በል ቀንድህን ዘይት ሙላና+ ሂድ። የቤተልሔም ሰው ወደሆነው ወደ እሴይ+ እልክሃለሁ፤ ምክንያቱም ከወንዶች ልጆቹ መካከል ንጉሥ የሚሆንልኝ ሰው መርጫለሁ።”+ 2 ሳሙኤል ግን “እንዴት መሄድ እችላለሁ? ሳኦል ይህን ከሰማ ይገድለኛል”+ አለ። ይሖዋም እንዲህ አለው፦ “አንዲት ጊደር ይዘህ ሂድ፤ ከዚያም ‘የመጣሁት ለይሖዋ መሥዋዕት ለማቅረብ ነው’ በል። 3 እሴይንም ወደ መሥዋዕቱ ጥራው፤ እኔም ምን ማድረግ እንዳለብህ አሳውቅሃለሁ። አንተም እኔ የምመርጥልህን ሰው ትቀባልኛለህ።”+

4 ሳሙኤልም ይሖዋ የነገረውን አደረገ። ቤተልሔም+ እንደደረሰም የከተማዋ ሽማግሌዎች ባገኙት ጊዜ እየተንቀጠቀጡ “የመጣኸው በሰላም ነው?” አሉት። 5 እሱም “አዎ በሰላም ነው። የመጣሁት ለይሖዋ መሥዋዕት ለማቅረብ ነው። ራሳችሁን ቀድሱ፤ ወደ መሥዋዕቱም አብራችሁኝ ሂዱ” አላቸው። ከዚያም እሴይንና ልጆቹን ቀደሳቸው፤ ወደ መሥዋዕቱ እንዲመጡም ጠራቸው። 6 እነሱም እዚያ በደረሱ ጊዜ ሳሙኤል ኤልያብን+ ሲያየው “መቼም ይሖዋ የሚቀባው ሰው ይህ መሆን አለበት” አለ። 7 ሆኖም ይሖዋ ሳሙኤልን እንዲህ አለው፦ “እኔ ስላልተቀበልኩት መልኩንና የቁመቱን ርዝማኔ አትይ።+ አምላክ የሚያየው ሰው በሚያይበት መንገድ አይደለም፤ ምክንያቱም ሰው የሚያየው ውጫዊ ገጽታን ነው፤ ይሖዋ ግን የሚያየው ልብን ነው።”+ 8 ከዚያም እሴይ አቢናዳብን+ ጠርቶ በሳሙኤል ፊት እንዲያልፍ አደረገ፤ እሱ ግን “ይሄኛውንም ይሖዋ አልመረጠውም” አለ። 9 ቀጥሎም እሴይ ሻማህ+ እንዲቀርብ አደረገ፤ እሱ ግን “ይሄኛውንም ይሖዋ አልመረጠውም” አለ። 10 በመሆኑም እሴይ ሰባቱም ወንዶች ልጆቹ በሳሙኤል ፊት እንዲያልፉ አደረገ፤ ሳሙኤል ግን እሴይን “ይሖዋ ከእነዚህ መካከል ማናቸውንም አልመረጠም” አለው።

11 በመጨረሻም ሳሙኤል እሴይን “ወንዶች ልጆችህ እነዚሁ ብቻ ናቸው?” አለው። እሱም “ታናሽየው+ ገና ይቀራል፤ በጎች እየጠበቀ ነው” አለ።+ ከዚያም ሳሙኤል እሴይን “በል ልከህ አስመጣው፤ ምክንያቱም እሱ ሳይመጣ ምግብ ለመብላት መቀመጥ አንችልም” አለው። 12 በመሆኑም ልኮ አስመጣው። እሱም የቀይ ዳማ፣ ዓይኑ የሚያምርና መልከ መልካም ነበር።+ ከዚያም ይሖዋ “ተነስ፣ ቀባው፤ የመረጥኩት እሱን ነው!” አለው።+ 13 ስለዚህ ሳሙኤል የዘይቱን ቀንድ+ ወስዶ በወንድሞቹ ፊት ቀባው። ከዚያም ቀን አንስቶ የይሖዋ መንፈስ ለዳዊት ኃይል ሰጠው።+ በኋላም ሳሙኤል ተነስቶ ወደ ራማ+ ሄደ።

14 በዚህ ጊዜ የይሖዋ መንፈስ ከሳኦል ራቀ፤+ ከይሖዋ የመጣ መጥፎ መንፈስም ይረብሸው ጀመር።+ 15 የሳኦል አገልጋዮችም እንዲህ አሉት፦ “እንግዲህ ከአምላክ የመጣ መጥፎ መንፈስ እየረበሸህ ነው። 16 ጌታችን በፊቱ የቆሙትን አገልጋዮቹን በገና የሚደረድር ጥሩ ችሎታ ያለው ሰው እንዲፈልጉ ይዘዝ።+ ከአምላክ የመጣው መጥፎ መንፈስ በአንተ ላይ ሲወርድ ይህ ሰው በገና ይጫወትልሃል፤ አንተም ደህና ትሆናለህ።” 17 ስለዚህ ሳኦል አገልጋዮቹን “እንግዲያው እባካችሁ ጥሩ አድርጎ በገና የሚደረድር ሰው ፈልጋችሁ አምጡልኝ” አላቸው።

18 ከአገልጋዮቹም አንዱ እንዲህ አለ፦ “የቤተልሔሙ ሰው የእሴይ ልጅ በገና የመደርደር ጥሩ ችሎታ እንዳለው አይቻለሁ፤ እሱም ደፋርና ኃያል ተዋጊ ነው።+ ደግሞም አንደበተ ርቱዕና መልከ መልካም+ ሲሆን ይሖዋም ከእሱ ጋር ነው።”+ 19 ከዚያም ሳኦል ወደ እሴይ መልእክተኞችን ልኮ “በጎች የሚጠብቀውን ልጅህን ዳዊትን ላክልኝ” አለው።+ 20 በመሆኑም እሴይ ዳቦና በወይን ጠጅ የተሞላ አቁማዳ በአህያ አስጭኖ እንዲሁም የፍየል ግልገል አስይዞ ልጁን ዳዊትን ወደ ሳኦል ላከው። 21 በዚህ መንገድ ዳዊት ወደ ሳኦል መጣ፤ እሱንም ያገለግለው ጀመር።+ ሳኦልም እጅግ እየወደደው ሄደ፤ ጋሻ ጃግሬውም ሆነ። 22 ሳኦልም “ዳዊት በፊቴ ሞገስ ስላገኘ እባክህ እዚሁ እኔ ጋ ሆኖ እንዲያገለግለኝ ፍቀድልኝ” በማለት ወደ እሴይ መልእክት ላከ። 23 ከአምላክ የሚመጣ መጥፎ መንፈስ በሳኦል ላይ በሚወርድበት ጊዜ ሁሉ ዳዊት በገናውን አንስቶ ይደረድር ነበር፤ ሳኦልም ቀለል ይለውና ደህና ይሆን ነበር፤ መጥፎው መንፈስም ከእሱ ይርቅ ነበር።+

17 ፍልስጤማውያን+ ሠራዊታቸውን ለውጊያ አሰባሰቡ። እነሱም በይሁዳ በምትገኘው በሶኮህ+ ከተሰባሰቡ በኋላ በሶኮህ እና በአዜቃ+ መካከል በምትገኘው በኤፌስዳሚም+ ሰፈሩ። 2 ሳኦልና የእስራኤል ሰዎች ደግሞ ተሰባስበው በኤላህ ሸለቆ*+ ውስጥ ሰፈሩ፤ እነሱም ለጦርነት ተሰልፈው ፍልስጤማውያንን ለመግጠም ወጡ። 3 ፍልስጤማውያን በአንድ በኩል ያለውን ተራራ ያዙ፣ እስራኤላውያን ደግሞ በሌላ በኩል ያለውን ተራራ ያዙ፤ በመካከላቸውም ሸለቆ ነበር።

4 በዚህ ጊዜ አንድ ኃያል ተዋጊ ከፍልስጤማውያን ሰፈር ብቅ አለ፤ እሱም የጌት+ ሰው ሲሆን ስሙ ጎልያድ+ ይባላል፤ ቁመቱም ስድስት ክንድ ከአንድ ስንዝር* ነበር። 5 እሱም ከመዳብ የተሠራ የራስ ቁር ደፍቶ ነበር፤ እንዲሁም ከተነባበሩ ጠፍጣፋ መዳቦች የተሠራ ጥሩር ለብሶ ነበር። የጥሩሩም+ ክብደት 5,000 ሰቅል* ነበር። 6 ቅልጥሙ ላይ ከመዳብ የተሠራ ገምባሌ አድርጎ ነበር፤ በትከሻውና በትከሻውም መካከል ከመዳብ የተሠራ ጦር+ አንግቶ ነበር። 7 የጭሬውም ዘንግ የሸማኔ መጠቅለያ ያህል ነበር፤+ ከብረት የተሠራው የጭሬው ጫፍ 600 ሰቅል* ነበር፤ ጋሻ ጃግሬውም ከፊት ከፊቱ ይሄድ ነበር። 8 ከዚያም ጎልያድ ከቆመበት ቦታ ሆኖ የተሰለፈውን የእስራኤል ሠራዊት+ በመጣራት እንዲህ አላቸው፦ “ለውጊያ ተሰልፋችሁ የወጣችሁት ለምንድን ነው? እኔ ፍልስጤማዊ፣ እናንተ ደግሞ የሳኦል አገልጋዮች አይደላችሁም? እንግዲህ አንድ ሰው ምረጡና ወደ እኔ ይውረድ። 9 ከእኔ ጋር ተዋግቶ እኔን መግደል ከቻለ እኛ የእናንተ አገልጋዮች እንሆናለን። እኔ ባሸንፈውና ብገድለው ግን እናንተ የእኛ አገልጋዮች ትሆናላችሁ፤ እኛንም ታገለግላላችሁ።” 10 በመቀጠልም ፍልስጤማዊው “ዛሬ፣ ለውጊያ የተሰለፈውን የእስራኤል ሠራዊት እሳለቅበታለሁ።*+ በሉ አሁን አንድ ሰው ምረጡና እንጋጠም!” አለ።

11 ሳኦልና እስራኤላውያን በሙሉ ፍልስጤማዊው የተናገረውን ይህን ቃል ሲሰሙ ተሸበሩ፤ እንዲሁም በጣም ፈሩ።

12 ዳዊት በይሁዳ በምትገኘው በቤተልሔም+ የሚኖረው የኤፍራታዊው+ የእሴይ ልጅ ነበር፤ እሴይ+ ስምንት ወንዶች ልጆች+ የነበሩት ሲሆን በሳኦል የንግሥና ዘመን ዕድሜው ገፍቶ ነበር። 13 ሦስቱ የእሴይ ትላልቅ ልጆች ሳኦልን ተከትለው ወደ ውጊያው ሄደው ነበር።+ ወደ ውጊያው የሄዱት ሦስቱ ወንዶች ልጆቹ የበኩር ልጁ ኤልያብ፣+ ሁለተኛ ልጁ አቢናዳብና+ ሦስተኛ ልጁ ሻማህ+ ነበሩ። 14 ዳዊት የሁሉም ታናሽ ነበር፤+ ትላልቆቹ ሦስቱ ሳኦልን ተከትለው ሄደው ነበር።

15 ዳዊት ሳኦልን ያገለግል እንዲሁም ከዚያ እየተመላለሰ በቤተልሔም የአባቱን በጎች ይጠብቅ ነበር።+ 16 ይህ በእንዲህ እንዳለ ፍልስጤማዊው 40 ቀን ሙሉ ጠዋትና ማታ ወደ እነሱ በመቅረብ ፊታቸው ቆሞ ይገዳደራቸው ነበር።

17 ከዚያም እሴይ ልጁን ዳዊትን እንዲህ አለው፦ “እስቲ እባክህ ይህን አንድ የኢፍ* መስፈሪያ ቆሎና እነዚህን አሥር ዳቦዎች ይዘህ በጦር ሰፈሩ ውስጥ ላሉት ወንድሞችህ ቶሎ አድርስላቸው። 18 እንዲሁም ይህን አሥር የአይብ ጥፍጥፍ ለሺህ አለቃው ውሰድለት፤ በተጨማሪም ወንድሞችህ እንዴት እንደሆኑ አይተህ ደህንነታቸውን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ይዘህ ና።” 19 የዳዊት ወንድሞች ከሳኦልና ከሌሎቹ የእስራኤል ሰዎች ጋር ሆነው በኤላህ ሸለቆ*+ ከፍልስጤማውያን ጋር እየተዋጉ ነበር።+

20 በመሆኑም ዳዊት በማለዳ ተነስቶ በጎቹን ለጠባቂ ሰጠ፤ ከዚያም ዕቃዎቹን ይዞ እሴይ ባዘዘው መሠረት ሄደ። እሱም ወደ ጦር ሰፈሩ ሲደርስ የጦር ሠራዊቱ እየፎከረ ወደ ጦር ግንባሩ እየወጣ ነበር። 21 ለጦርነት የተሰለፉት እስራኤላውያንና ፍልስጤማውያንም ፊት ለፊት ተፋጠው ነበር። 22 ዳዊትም ወዲያውኑ ዕቃውን ስንቅ ጠባቂው ጋ አስቀምጦ ወደ ጦር ግንባሩ እየሮጠ ሄደ። እዚያም ሲደርስ የወንድሞቹን ደህንነት መጠየቅ ጀመረ።+

23 እሱም ከእነሱ ጋር እየተነጋገረ ሳለ የጌት ሰው የሆነው ጎልያድ+ የተባለው ኃያል ፍልስጤማዊ ተዋጊ መጣ። እሱም ለውጊያ ከተሰለፉት ፍልስጤማውያን መካከል ብቅ ብሎ እንደ በፊቱ መደንፋት ጀመረ፤+ ዳዊትም ሰማው። 24 የእስራኤልም ሰዎች በሙሉ ሰውየውን ሲመለከቱት እጅግ ተሸብረው ከፊቱ ሸሹ።+ 25 እነሱም እንዲህ ይሉ ነበር፦ “እየመጣ ያለውን ይህን ሰው አያችሁት? የሚመጣው እኮ በእስራኤል ላይ ለመሳለቅ ነው።+ እሱን ለሚገድል ሰው ንጉሡ ብዙ ሀብት ይሰጠዋል፤ ሴት ልጁንም ይድርለታል፤+ የአባቱንም ቤት በእስራኤል ውስጥ ከማንኛውም ዓይነት ግዴታ ነፃ እንዲሆን ያደርጋል።”

26 ዳዊትም አጠገቡ ቆመው የነበሩትን ሰዎች እንዲህ አላቸው፦ “ለመሆኑ ያን ፍልስጤማዊ ገድሎ እንዲህ ያለውን ውርደት ከእስራኤል ላይ ለሚያስወግድ ሰው ምን ይደረግለታል? ደግሞስ ይህ ያልተገረዘ ፍልስጤማዊ ሕያው በሆነው አምላክ ሠራዊት ላይ የሚሳለቀው ማን ስለሆነ ነው?”+ 27 ሰዎቹም “ለሚገድለው ሰውማ እንዲህ እንዲህ ይደረግለታል” በማለት ቀደም ሲል የተናገሩትን ነገር ደገሙለት። 28 ታላቅ ወንድሙ ኤልያብም+ ዳዊት ከሰዎቹ ጋር ሲነጋገር ሲሰማ በእሱ ላይ እጅግ ተቆጥቶ እንዲህ አለው፦ “ወደዚህ የወረድከው ለምንድን ነው? ለመሆኑ እነዚያን ጥቂት በጎች ምድረ በዳ ላይ ለማን ተውካቸው?+ እኔ ትዕቢትህንና የልብህን ክፉ ሐሳብ መች አጣሁት፤ ወደዚህ የመጣኸው ለሌላ ሳይሆን ውጊያውን ለማየት ነው።” 29 ዳዊትም መልሶ “ቆይ አሁን ምን አጠፋሁ? ጥያቄ እኮ ነው የጠየቅኩት!” አለ። 30 ከዚያም ከእሱ ዞር ብሎ ያንኑ ጥያቄ ሌላ ሰው ጠየቀ፤+ ሰዎቹም እንደቀድሞው ያንኑ መልስ ሰጡት።+

31 ዳዊት የተናገረው ነገር ተሰማ፤ ለሳኦልም ተነገረው። ስለዚህ ሳኦል ልኮ አስጠራው። 32 ዳዊትም ሳኦልን “በዚህ ሰው የተነሳ የማንም ሰው ልብ አይቅለጥ።* አገልጋይህ ሄዶ ከዚህ ፍልስጤማዊ ጋር ይዋጋል” አለው።+ 33 ሳኦል ግን ዳዊትን “አንተ ገና አንድ ፍሬ ልጅ ነህ፤+ እሱ ግን ከልጅነቱ ጀምሮ ጦረኛ ነው፤ ስለዚህ ይህን ፍልስጤማዊ ልትገጥመው አትችልም” አለው። 34 ዳዊትም ሳኦልን እንዲህ አለው፦ “አገልጋይህ የአባቱን መንጋ በሚጠብቅበት ጊዜ አንበሳ+ እንዲሁም ድብ ይመጣና ከመንጋው መካከል አንድ በግ ነጥቆ ይወስድ ነበር። 35 እኔም ተከትዬው በመሄድ እመታውና በጉን ከአፉ አስጥለው ነበር። ሊያጠቃኝ በተነሳ ጊዜም ጉሮሮውን አንቄ* በመምታት እገድለው ነበር። 36 አገልጋይህ አንበሳውንም ሆነ ድቡን ገድሏል፤ ይህ ያልተገረዘ ፍልስጤማዊም ሕያው በሆነው አምላክ ሠራዊት ላይ ስለተሳለቀ መጨረሻው ከእነሱ እንደ አንዱ ይሆናል።”+ 37 ዳዊትም በመቀጠል “ከአንበሳና ከድብ ጥፍር የታደገኝ ይሖዋ አሁንም ከዚህ ፍልስጤማዊ እጅ ይታደገኛል” አለ።+ በዚህ ጊዜ ሳኦል ዳዊትን “እሺ ሂድ፤ ይሖዋ ከአንተ ጋር ይሁን” አለው።

38 ከዚያም ሳኦል ለዳዊት የራሱን ልብሶች አለበሰው። በራሱም ላይ ከመዳብ የተሠራ ቁር ደፋለት፤ ጥሩርም አለበሰው። 39 በኋላም ዳዊት ሰይፉን በልብሱ ላይ ታጥቆ ለመራመድ ሞከረ፤ ሆኖም ከዚህ በፊት እንደዚህ ዓይነት ትጥቅ ታጥቆ ስለማያውቅ መራመድ አልቻለም። ዳዊትም ሳኦልን “እንዲህ ያሉ ትጥቆችን ታጥቄ ስለማላውቅ እነሱን አድርጌ መራመድ አልቻልኩም” አለው። በመሆኑም ዳዊት ከላዩ ላይ አወለቃቸው። 40 ከዚያም በትሩን በእጁ ያዘ፤ አምስት ድቡልቡል ድንጋዮችንም ከወንዝ* ከመረጠ በኋላ በእረኛ ኮሮጆው ውስጥ ጨመራቸው፤ በእጁም ወንጭፉን+ ይዞ ነበር። ከዚያም ወደ ፍልስጤማዊው ቀረበ።

41 ፍልስጤማዊውም ወደ ዳዊት እየቀረበ መጣ፤ ጋሻ ጃግሬውም ከፊት ከፊቱ ይሄድ ነበር። 42 ፍልስጤማዊውም ዳዊትን ትኩር ብሎ ሲያየው ዳዊት የቀይ ዳማና መልከ መልካም የሆነ አንድ ፍሬ ልጅ+ ስለነበር ናቀው። 43 በመሆኑም ፍልስጤማዊው ዳዊትን “በትር ይዘህ ወደ እኔ የምትመጣው እኔ ውሻ ነኝ?”+ አለው። በአማልክቱም ስም ረገመው። 44 ከዚያም “እስቲ ወደ እኔ ና፤ ሥጋህን ለሰማይ አሞሮችና ለምድር አራዊት እሰጣለሁ” አለው።

45 ዳዊትም መልሶ ፍልስጤማዊውን እንዲህ አለው፦ “አንተ ሰይፍ፣ ጭሬና ጦር+ ይዘህ ትመጣብኛለህ፤ እኔ ግን አንተ በተሳለቅክበት፣+ የእስራኤል ተዋጊዎች አምላክ በሆነው በሠራዊት ጌታ በይሖዋ ስም+ እመጣብሃለሁ። 46 ዛሬ ይሖዋ አንተን በእጄ አሳልፎ ይሰጥሃል፤+ እኔም አንተን ገድዬ ራስህን እቆርጠዋለሁ፤ በዚህ ቀን የፍልስጤማውያንን ሠራዊት ሬሳ ለሰማይ አሞሮችና ለምድር አራዊት እሰጣለሁ፤ በመላው ምድር የሚኖሩ ሰዎችም በእስራኤል አምላክ እንዳለ ያውቃሉ።+ 47 እዚህ የተሰበሰቡትም ሁሉ ይሖዋ የሚያድነው በሰይፍ ወይም በጦር እንዳልሆነ ያውቃሉ፤+ ምክንያቱም ውጊያው የይሖዋ ነው፤+ እሱም ሁላችሁንም በእጃችን አሳልፎ ይሰጣችኋል።”+

48 ፍልስጤማዊውም ተነስቶ ዳዊትን ለመግጠም ወደ እሱ እየተራመደ መጣ፤ ዳዊትም ፍልስጤማዊውን ለመግጠም ወደ ጦር ግንባሩ እየተንደረደረ ሄደ። 49 ከዚያም ዳዊት እጁን ወደ ኮሮጆው በመስደድ አንድ ድንጋይ አውጥቶ ወነጨፈው። ፍልስጤማዊውንም ግንባሩ ላይ መታው፤ ድንጋዩም ግንባሩ ውስጥ ገብቶ ተቀረቀረ፤ ሰውየውም በአፍጢሙ መሬት ላይ ተደፋ።+ 50 በዚህ ሁኔታ ዳዊት ፍልስጤማዊውን በወንጭፍና በድንጋይ አሸነፈው፤ ዳዊት በእጁ ሰይፍ ባይዝም ፍልስጤማዊውን መትቶ ገደለው።+ 51 ከዚያም ዳዊት እየሮጠ ሄዶ ላዩ ላይ ቆመ። የፍልስጤማዊውንም ሰይፍ+ ከሰገባው ውስጥ በመምዘዝ አንገቱን ቆርጦ ገደለው። ፍልስጤማውያንም ጀግናቸው መሞቱን ሲያዩ ሸሹ።+

52 በዚህ ጊዜ የእስራኤልና የይሁዳ ሰዎች ተነስተው እየጮኹ ፍልስጤማውያኑን ከሸለቆው+ አንስቶ እስከ ኤቅሮን+ በሮች ድረስ አሳደዷቸው፤ የፍልስጤማውያኑም ሬሳ ከሻአራይም+ አንስቶ እስከ ጌት እና እስከ ኤቅሮን ድረስ በየመንገዱ ወድቆ ነበር። 53  እስራኤላውያን ፍልስጤማውያኑን ከማሳደድ ከተመለሱ በኋላ ሰፈሮቻቸውን በዘበዙ።

54 ዳዊትም የፍልስጤማዊውን ራስ ወደ ኢየሩሳሌም አመጣው፤ የፍልስጤማዊውን የጦር መሣሪያዎች ግን በራሱ ድንኳን ውስጥ አስቀመጣቸው።+

55 ዳዊት፣ ፍልስጤማዊውን ለመግጠም በሚሄድበት ጊዜ ሳኦል ዳዊትን ተመልክቶ የሠራዊቱን አዛዥ አበኔርን+ “አበኔር፣ ለመሆኑ ይህ የማን ልጅ ነው?”+ አለው። አበኔርም መልሶ “ንጉሥ ሆይ፣ በሕያውነትህ እምላለሁ፣* አላውቅም!” አለው። 56 ንጉሡም “ይህ ወጣት የማን ልጅ እንደሆነ አጣራ” አለው። 57  ስለዚህ ዳዊት ፍልስጤማዊውን ገድሎ ሲመለስ አበኔር ዳዊትን ወስዶ የፍልስጤማዊውን ራስ+ በእጁ እንደያዘ ንጉሡ ፊት አቀረበው። 58 ሳኦልም “አንተ ወጣት፣ የማን ልጅ ነህ?” ሲል ጠየቀው፤ ዳዊትም መልሶ “የቤተልሔም+ ሰው የሆነው የአገልጋይህ የእሴይ+ ልጅ ነኝ” አለው።

18 ዳዊት ከሳኦል ጋር ተነጋግሮ እንደጨረሰ ዮናታንና+ ዳዊት የጠበቀ ወዳጅነት መሠረቱ፤* ዮናታንም እንደ ራሱ* ወደደው።+ 2 ከዚያን ቀን ጀምሮ ሳኦል ዳዊት ከእሱ ጋር እንዲኖር አደረገ፤ ወደ አባቱም ቤት እንዲመለስ አልፈቀደለትም።+ 3 ዮናታንም ዳዊትን እንደ ራሱ* ስለወደደው+ ከዳዊት ጋር ቃል ኪዳን ተጋቡ።+ 4 ከዚያም ዮናታን ለብሶት የነበረውን መደረቢያ አውልቆ ለዳዊት ሰጠው፤ እንዲሁም ልብሶቹን ሌላው ቀርቶ ሰይፉን፣ ቀስቱንና ቀበቶውን ሰጠው። 5 ዳዊትም ለውጊያ ይወጣ ጀመር፤ ሳኦል በሚልከው በማንኛውም ቦታ ተልእኮውን በተሳካ ሁኔታ* ይፈጽም ነበር።+ በመሆኑም ሳኦል በሠራዊቱ ላይ ሾመው፤+ ይህም ሕዝቡንና የሳኦልን አገልጋዮች በሙሉ አስደሰታቸው።

6 ዳዊትና አብረውት ያሉት ሰዎች ፍልስጤማውያንን መትተው በተመለሱ ጊዜ በመላው የእስራኤል ከተሞች የሚገኙ ሴቶች አታሞና+ ባለ ሦስት አውታር መሣሪያ ይዘው በደስታ እየዘፈኑና+ እየጨፈሩ ንጉሥ ሳኦልን ለመቀበል ወጡ። 7 እየጨፈሩ የነበሩት ሴቶችም እንዲህ እያሉ ዘፈኑ፦

“ሳኦል ሺዎችን ገደለ፤

ዳዊት ደግሞ አሥር ሺዎችን ገደለ።”+

8 ሳኦልም እጅግ ተቆጣ፤+ ዘፈኑም አላስደሰተውም፤ በመሆኑም “ለዳዊት አሥር ሺህ አሉለት፤ ለእኔ ግን ሺህ ብቻ፤ ያልተሰጠው ነገር እኮ መንግሥት ብቻ ነው!” አለ።+ 9 ከዚያች ዕለት አንስቶ ሳኦል ዳዊትን በጥርጣሬ ዓይን ይመለከተው ጀመር።

10 በማግስቱም ከአምላክ የመጣ መጥፎ መንፈስ ሳኦልን ያዘው፤+ ዳዊት በፊት እንደሚያደርገው ሁሉ በገና እየደረደረ+ ሳለ ሳኦል ቤቱ ውስጥ እንግዳ ባሕርይ ያሳይ* ጀመር። ሳኦልም በእጁ ጦር ይዞ ነበር፤+ 11 እሱም ‘ዳዊትን ከግድግዳው ጋር አጣብቀዋለሁ!’ ብሎ በማሰብ ጦሩን በኃይል ወረወረው።+ ዳዊት ግን ሁለት ጊዜ ከእሱ አመለጠ። 12 ይሖዋ ከሳኦል ተለይቶ+ ከዳዊት ጋር ስለነበር+ ሳኦል ዳዊትን ፈራው። 13 በመሆኑም ሳኦል ከፊቱ እንዲርቅ አደረገው፤ የሺህ አለቃ አድርጎም ሾመው፤ ዳዊትም ሠራዊቱን እየመራ ወደ ጦርነት ይሄድ ነበር።*+ 14 ዳዊት የሚያከናውነው ነገር ሁሉ ይሳካለት ነበር፤*+ ይሖዋም ከእሱ ጋር ነበር።+ 15 ሳኦልም ዳዊት ስኬታማ እንደሆነ ሲያይ ፈራው። 16 መላው እስራኤልና ይሁዳ ግን ዳዊትን ወደዱት፤ ምክንያቱም ወደ ጦርነት ሲወጡ የሚመራቸው እሱ ነበር።

17 በኋላም ሳኦል ዳዊትን እንዲህ አለው፦ “እንግዲህ ትልቋ ልጄ ሜሮብ+ አለች። እሷን እድርልሃለሁ።+ ሆኖም ጀግንነትህን ለእኔ ከማሳየት ወደኋላ ማለት የለብህም፤ የይሖዋንም ጦርነቶች መዋጋት ይኖርብሃል።”+ ሳኦል ይህን ያለው ‘እጄን በዚህ ሰው ላይ አላሳርፍም። ከዚህ ይልቅ በፍልስጤማውያን እጅ ይሙት’ ብሎ ስላሰበ ነው።+ 18 በዚህ ጊዜ ዳዊት ሳኦልን “ለንጉሡ አማች እሆን ዘንድ እኔም ሆንኩ የአባቴ ቤተሰቦች የሆኑት ዘመዶቼ በእስራኤል ውስጥ ከቶ ማን ሆነን ነው?” አለው።+ 19 ሆኖም የሳኦል ልጅ ሜሮብ ለዳዊት ልትሰጥ የነበረበት ጊዜ ሲደርስ እሷ ቀድሞውኑ ለመሆላታዊው ለአድሪዔል+ ተድራ ነበር።

20 የሳኦል ልጅ ሜልኮል+ ዳዊትን ትወደው ነበር፤ ይህን ለሳኦል ነገሩት፤ እሱም ነገሩ ደስ አሰኘው። 21 በመሆኑም ሳኦል “ወጥመድ እንድትሆነውና የፍልስጤማውያን እጅ በእሱ ላይ እንዲሆን እሷን እሰጠዋለሁ” አለ።+ ከዚያም ሳኦል ለሁለተኛ ጊዜ ዳዊትን “በዛሬዋ ዕለት በዚህች በሁለተኛዋ ሴት አማካኝነት ከእኔ ጋር በጋብቻ ትዛመዳለህ”* አለው። 22 በተጨማሪም ሳኦል አገልጋዮቹን እንዲህ ሲል አዘዛቸው፦ “ለዳዊት እንዲህ ብላችሁ በሚስጥር ንገሩት፦ ‘ንጉሡ በአንተ ደስ ብሎታል፤ አገልጋዮቹም በሙሉ ይወዱሃል። ስለሆነም አሁን ከንጉሡ ጋር በጋብቻ ተዛመድ።’” 23 የሳኦልም አገልጋዮች ይህን በነገሩት ጊዜ ዳዊት “እዚህ ግባ ለማልባል ለእንደኔ ዓይነቱ ድሃ ከንጉሡ ጋር በጋብቻ መዛመድ እንዲህ ቀላል ነገር ይመስላችኋል?” አላቸው።+ 24 ከዚያም የሳኦል አገልጋዮች “ዳዊት እኮ እንዲህ እንዲህ አለ” ብለው ነገሩት።

25 በዚህ ጊዜ ሳኦል እንዲህ አለ፦ “ዳዊትን እንዲህ በሉት፦ ‘ንጉሡ ከአንተ የሚፈልገው ጥሎሽ+ ሳይሆን ጠላቶቹን መበቀል እንዲችል የ100 ፍልስጤማውያንን ሸለፈት+ ብቻ ነው።’” ሳኦል ይህን ያለው ዳዊት በፍልስጤማውያን እጅ እንዲወድቅ ተንኮል አስቦ ስለነበር ነው። 26 በመሆኑም አገልጋዮቹ ይህንኑ ለዳዊት ነገሩት፤ ዳዊትም ከንጉሡ ጋር በጋብቻ የመዛመዱ ጉዳይ አስደሰተው።+ ስለሆነም የተሰጠው ጊዜ ከማብቃቱ በፊት 27 ዳዊት አብረውት ከነበሩት ሰዎች ጋር በመሄድ 200 ፍልስጤማውያንን መታ፤ ዳዊት ከንጉሡ ጋር በጋብቻ ለመዛመድ የገደላቸውን ሰዎች ሸለፈት በሙሉ አምጥቶ ለንጉሡ ሰጠው። በመሆኑም ሳኦል ልጁን ሜልኮልን ዳረለት።+ 28 ሳኦል ይሖዋ ከዳዊት ጋር እንደነበርና+ ልጁ ሜልኮልም ዳዊትን እንደወደደችው+ ተረዳ። 29 በዚህም ምክንያት ሳኦል ዳዊትን ከበፊቱ ይልቅ ፈራው፤ በመሆኑም ዕድሜውን ሙሉ የዳዊት ጠላት ሆነ።+

30 የፍልስጤም መኳንንትም ለውጊያ ይወጡ ነበር፤ ሆኖም ለውጊያ በወጡ ቁጥር ዳዊት ከሳኦል አገልጋዮች ሁሉ ይበልጥ ይሳካለት ነበር፤*+ ስሙም እየገነነ መጣ።+

19 በኋላም ሳኦል፣ ዳዊት እንዲገደል ማሰቡን ለልጁ ለዮናታንና ለአገልጋዮቹ በሙሉ ነገራቸው።+ 2 የሳኦል ልጅ ዮናታን ዳዊትን በጣም ይወደው+ ስለነበር ዳዊትን እንዲህ አለው፦ “አባቴ ሳኦል ሊገድልህ ይፈልጋል። ስለዚህ እባክህ ጠዋት ላይ ተጠንቀቅ፤ ወደ አንድ ሰዋራ ቦታም ሄደህ ተሸሽገህ ቆይ። 3 እኔም እወጣና አንተ ባለህበት ሜዳ ከአባቴ አጠገብ እቆማለሁ። ከእሱም ጋር ስለ አንተ እነጋገራለሁ፤ የሆነ ነገር እንዳለ ከተረዳሁ እነግርሃለሁ።”+

4 በመሆኑም ዮናታን ለአባቱ ለሳኦል ስለ ዳዊት መልካም ነገር ነገረው።+ እንዲህም አለው፦ “ንጉሡ በአገልጋዩ በዳዊት ላይ ኃጢአት አይሥራ፤ ምክንያቱም እሱ በአንተ ላይ የሠራው ኃጢአት የለም፤ ያደረገልህም ነገር ቢሆን ለአንተ የሚበጅ ነው። 5 ሕይወቱን አደጋ ላይ ጥሎ* ፍልስጤማዊውን መታ፤+ ይሖዋም ለመላው እስራኤል ታላቅ ድል አጎናጸፈ።* አንተም ይህን አይተህ በጣም ተደስተህ ነበር። ታዲያ ያለምንም ምክንያት ዳዊትን በመግደል በንጹሕ ሰው ደም ላይ ለምን ኃጢአት ትሠራለህ?”+ 6 ሳኦልም የዮናታንን ቃል ሰማ፤ እሱም “ሕያው በሆነው በይሖዋ እምላለሁ፣ ዳዊት አይገደልም” ሲል ማለ። 7 ከዚያም ዮናታን ዳዊትን ጠርቶ ሁሉንም ነገር ነገረው። ስለዚህ ዮናታን ዳዊትን ወደ ሳኦል አመጣው፤ እሱም እንደቀድሞው ሳኦልን ማገልገሉን ቀጠለ።+

8 ከጊዜ በኋላ ሌላ ጦርነት ተነሳ፤ ዳዊትም ወጥቶ ከፍልስጤማውያን ጋር ተዋጋ፤ ክፉኛም ጨፈጨፋቸው፤ እነሱም ከፊቱ ሸሹ።

9 ሳኦል ጦሩን ይዞ ቤቱ ውስጥ ተቀምጦ ሳለ ከይሖዋ የመጣ መጥፎ መንፈስ ወረደበት፤+ በዚህ ጊዜ ዳዊት በገና እየደረደረ ነበር።+ 10 ሳኦልም ዳዊትን በጦሩ ከግድግዳው ጋር ሊያጣብቀው ሞከረ፤ ዳዊት ግን ከሳኦል ፊት ዞር በማለቱ ጦሩ ግድግዳው ላይ ተሰካ። ዳዊትም በዚያ ሌሊት ሸሽቶ አመለጠ። 11 በኋላም ሳኦል የዳዊትን ቤት ከበው በንቃት በመጠባበቅ ጠዋት ላይ እንዲገድሉት መልእክተኞችን ላከ፤+ ሆኖም የዳዊት ሚስት ሜልኮል “ዛሬ ሌሊት ካላመለጥክ* ነገ ትገደላለህ” አለችው። 12 ሜልኮልም ዳዊት ሸሽቶ እንዲያመልጥ ወዲያውኑ በመስኮት አሾልካ አወረደችው። 13 ከዚያም የተራፊም ቅርጹን* ወስዳ አልጋው ላይ አጋደመች፤ በራስጌውም ከፍየል ፀጉር የተሠራ እንደ መረብ ያለ ጨርቅ አደረገች፤ በልብስም ሸፈነችው።

14 ሳኦልም ዳዊትን እንዲይዙት መልእክተኞችን ላከ፤ እሷ ግን “አሞታል” አለቻቸው። 15 በመሆኑም ሳኦል ዳዊትን እንዲያዩት መልእክተኞቹን ላከ፤ እነሱንም “ዳዊትን እንድገድለው በአልጋው ላይ እንዳለ አምጡልኝ” አላቸው።+ 16 መልእክተኞቹም ሲገቡ አልጋው ላይ ያገኙት የተራፊም ቅርጹን* ነበር፤ በራስጌውም ከፍየል ፀጉር የተሠራ እንደ መረብ ያለ ጨርቅ ነበር። 17 ሳኦልም ሜልኮልን “እንዲህ ያታለልሽኝና ጠላቴ+ ሸሽቶ እንዲያመልጥ ያደረግሽው ለምንድን ነው?” አላት። ሜልኮልም “‘እንዳመልጥ እርጂኝ፣ አለዚያ እገድልሻለሁ!’ አለኝ” አለችው።

18 ዳዊትም ሸሽቶ አመለጠ፤ በራማ+ ወደሚገኘው ወደ ሳሙኤልም መጣ። ሳኦል ያደረገበትንም ነገር ሁሉ ነገረው። ከዚያም እሱና ሳሙኤል ሄደው በናዮት+ መኖር ጀመሩ። 19 ከጊዜ በኋላም ሳኦል “ዳዊት እኮ ያለው በራማ በምትገኘው በናዮት ነው!” የሚል ወሬ ደረሰው። 20 ሳኦልም ዳዊትን እንዲይዙት ወዲያውኑ መልእክተኞችን ላከ። የሳኦል መልእክተኞችም አረጋውያን የሆኑት ነቢያት ትንቢት ሲናገሩ፣ ሳሙኤል ደግሞ እንደ መሪያቸው ሆኖ ቆሞ ሲያዩ የአምላክ መንፈስ ወረደባቸው፤ እነሱም እንደ ነቢያት ያደርጋቸው ጀመር።

21 ይህን ለሳኦል በነገሩት ጊዜ ወዲያውኑ ሌሎች መልእክተኞችን ላከ፤ እነሱም እንደ ነቢያት ያደርጋቸው ጀመር። በመሆኑም ሳኦል ለሦስተኛ ጊዜ መልእክተኞችን ላከ፤ እነሱም እንደ ነቢያት ያደርጋቸው ጀመር። 22 በመጨረሻም እሱ ራሱ ወደ ራማ ሄደ። በሰኩ ወደሚገኘው ትልቅ የውኃ ማጠራቀሚያ ጉድጓድ እንደደረሰም “ለመሆኑ ሳሙኤልና ዳዊት የት ናቸው?” ሲል ጠየቀ። እነሱም “በራማ ባለችው በናዮት+ ይገኛሉ” ብለው መለሱለት። 23 ሳኦልም በራማ ወደምትገኘው ወደ ናዮት እየሄደ ሳለ የአምላክ መንፈስ በእሱም ላይ ወረደበት፤ እሱም በራማ ወደምትገኘው ወደ ናዮት እስኪደርስ ድረስ እንደ ነቢይ አደረገው። 24 ልብሱንም አወለቀ፤ በሳሙኤልም ፊት እንደ ነቢይ አደረገው፤ ቀኑንና ሌሊቱን ሙሉ ራቁቱን* ሆኖ በዚያ ተጋደመ። እነሱም “ሳኦልም ከነቢያቱ አንዱ ነው እንዴ?”+ ያሉት በዚህ የተነሳ ነው።

20 ከዚያም ዳዊት በራማ ከምትገኘው ከናዮት ሸሸ። ሆኖም ወደ ዮናታን መጥቶ “ምን አደረግኩ?+ የፈጸምኩትስ በደል ምንድን ነው? አባትህ ሕይወቴን* ለማጥፋት የሚፈልገው በእሱ ላይ ምን ኃጢአት ሠርቼ ነው?” አለው። 2 ዮናታንም እንዲህ አለው፦ “ይሄማ የማይታሰብ ነው!+ ፈጽሞ አትሞትም! አባቴ እንደሆነ ትልቅም ሆነ ትንሽ፣ ለእኔ ሳይነግረኝ ምንም ነገር አያደርግም። ታዲያ አባቴ ይህን ነገር ከእኔ የሚደብቅበት ምን ምክንያት አለው? እንዲህማ አይሆንም።” 3 ዳዊት ግን እንደገና ማለለት፤ እንዲህም አለው፦ “አባትህ በፊትህ ሞገስ ማግኘቴን+ በሚገባ ስለሚያውቅ ‘ዮናታን ሊያዝን ስለሚችል ይህን ነገር ማወቅ የለበትም’ ብሎ ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ ሕያው በሆነው በይሖዋና በሕያውነትህ* እምላለሁ፣ በእኔና በሞት መካከል ያለው አንድ እርምጃ ብቻ ነው!”+

4 ከዚያም ዮናታን ዳዊትን “የምትለውን* ማንኛውንም ነገር አደርግልሃለሁ” አለው። 5 በዚህ ጊዜ ዳዊት ዮናታንን እንዲህ አለው፦ “እነሆ፣ ነገ አዲስ ጨረቃ+ የምትወጣበት ቀን ነው፤ እኔም ከንጉሡ ጋር ለመመገብ በማዕድ መቀመጥ ይጠበቅብኛል፤ አንተ ካሰናበትከኝ ግን እስከ ሦስተኛው ቀን ምሽት ድረስ ወደ ሜዳ ሄጄ እደበቃለሁ። 6 ምናልባት አባትህ አለመኖሬን አስተውሎ ከጠየቀ ‘ዳዊት በከተማው በቤተልሔም+ ለመላ ቤተሰቡ የሚቀርብ ዓመታዊ መሥዋዕት ስላለ ቶሎ ወደዚያ ይሄድ ዘንድ እንድፈቅድለት ለመነኝ’ በለው።+ 7 እሱም ‘ጥሩ ነው!’ ካለ አገልጋይህን የሚያሰጋው ነገር የለም ማለት ነው። ከተቆጣ ግን በእኔ ላይ ጉዳት ለማድረስ እንደቆረጠ እወቅ። 8 አገልጋይህ ከአንተ ጋር በይሖዋ ፊት ቃል ኪዳን እንዲገባ ያደረግከው+ አንተ ስለሆንክ ለአገልጋይህ ታማኝ ፍቅር አሳየው።+ በእኔ ላይ ጥፋት ከተገኘ+ ግን አንተው ራስህ ግደለኝ። ለምን ለአባትህ አሳልፈህ ትሰጠኛለህ?”

9 በዚህ ጊዜ ዮናታን “እንዲህ ብለህ ማሰብማ የለብህም! አባቴ በአንተ ላይ ጉዳት ለማድረስ መቁረጡን ባውቅ እንዴት ሳልነግርህ ዝም እላለሁ?” አለው።+ 10 ከዚያም ዳዊት ዮናታንን “ታዲያ አባትህ ክፉ ቃል ቢመልስልህ ማን ይነግረኛል?” አለው። 11 ዮናታንም ዳዊትን “ና፣ ወደ ሜዳ እንውጣ” አለው። በመሆኑም ተያይዘው ወደ ሜዳ ወጡ። 12 ከዚያም ዮናታን ዳዊትን እንዲህ አለው፦ “ነገ በዚህ ጊዜ ወይም ከነገ ወዲያ አባቴ ያለውን አመለካከት ባላጣራ የእስራኤል አምላክ ይሖዋ ምሥክር ይሁንብኝ። እሱ ለዳዊት ጥሩ አመለካከት ካለው ወደ አንተ ልኬ የማላሳውቅህ ይመስልሃል? 13 አባቴ በአንተ ላይ ጉዳት ለማድረስ አስቦ ቢሆንና እኔ ግን ይህን ሳላሳውቅህ ብቀር እንዲሁም በሰላም እንድትሄድ ባላደርግ ይሖዋ በዮናታን ላይ ይህን ያድርግበት፤ ከዚህ የከፋም ነገር ያምጣበት። ይሖዋ ከአባቴ ጋር እንደነበር+ ሁሉ ከአንተም ጋር ይሁን።+ 14 አንተስ ብትሆን በሕይወት ሳለሁም ሆነ ስሞት የይሖዋን ታማኝ ፍቅር አታሳየኝም?+ 15 ይሖዋ የዳዊትን ጠላቶች በሙሉ ከምድር ገጽ ጠራርጎ በሚያጠፋበት ጊዜም ለቤተሰቤ+ ታማኝ ፍቅርህን ከማሳየት ፈጽሞ ወደኋላ አትበል።” 16 ስለዚህ ዮናታን “ይሖዋ የዳዊትን ጠላቶች ይፋረዳቸዋል” በማለት ከዳዊት ቤት ጋር ቃል ኪዳን ገባ። 17 በመሆኑም ዮናታን ዳዊት ለእሱ ባለው ፍቅር እንደገና እንዲምልለት አደረገ፤ ምክንያቱም ዳዊትን እንደ ራሱ* ይወደው ነበር።+

18 ዮናታንም ዳዊትን እንዲህ አለው፦ “ነገ አዲስ ጨረቃ+ የምትወጣበት ቀን ነው፤ የምትቀመጥበት ቦታ ባዶ ስለሚሆን አለመኖርህ ይታወቃል። 19 በሦስተኛውም ቀን፣ አለመኖርህ ይበልጥ ግልጽ ይሆናል፤ አንተም ያን ቀን* ተደብቀህበት ወደነበረው ቦታ ሂድ፤ እዚህ ድንጋይ አጠገብም ቆይ። 20 እኔም ዒላማ የምመታ አስመስዬ በድንጋዩ አጠገብ ሦስት ቀስቶችን አስፈነጥራለሁ። 21 አገልጋዩንም ‘ሂድ፣ ፍላጻዎቹን አምጣቸው’ ብዬ እልከዋለሁ። አገልጋዩን ‘ፍላጻዎቹ ከአንተ በዚህኛው በኩል ናቸው፤ አምጣቸው’ ካልኩት ሕያው በሆነው በይሖዋ እምላለሁ ሁሉ ነገር ሰላም ስለሆነና ምንም የሚያሰጋህ ነገር ስለሌለ ተመልሰህ መምጣት ትችላለህ። 22 ሆኖም ልጁን ‘ፍላጻዎቹ ከአንተ ወዲያ ናቸው’ ካልኩት ይሖዋ አሰናብቶሃልና ሂድ። 23 እኔና አንተ የተጋባነውን ቃል+ በተመለከተም ይሖዋ በእኔና በአንተ መካከል ለዘላለም ምሥክር ይሁን።”+

24 በመሆኑም ዳዊት ወደ ሜዳ ሄዶ ተደበቀ። አዲስ ጨረቃ ስትወጣም ንጉሡ ለመብላት በማዕድ ተቀመጠ።+ 25 ንጉሡ እንደተለመደው በግድግዳው በኩል ባለው መቀመጫው ላይ ተቀምጦ ነበር። ዮናታን ከፊት ለፊቱ፣ አበኔር+ ደግሞ ከሳኦል ጎን ተቀምጠው ነበር፤ የዳዊት ቦታ ግን ባዶ ነበር። 26 ሳኦል ‘መቼም ዳዊት እንዳይነጻ+ የሚያደርገው የሆነ ነገር ገጥሞት መሆን ይኖርበታል። አዎ፣ ረክሶ መሆን አለበት’ ብሎ ስላሰበ በዚያን ቀን ምንም አልተናገረም። 27 አዲስ ጨረቃ በወጣችበት ቀን ማግስት ይኸውም በሁለተኛው ቀን የዳዊት ቦታ ክፍት እንደሆነ ነበር። ከዚያም ሳኦል ልጁን ዮናታንን “የእሴይ+ ልጅ ትናንትም፣ ዛሬም ማዕድ ላይ ያልተገኘው ለምንድን ነው?” አለው። 28 ዮናታንም ለሳኦል እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “ዳዊት ወደ ቤተልሔም ይሄድ ዘንድ እንድፈቅድለት ለመነኝ።+ 29 እንዲህም አለኝ፦ ‘ቤተሰባችን በከተማዋ ውስጥ መሥዋዕት ስለሚያቀርብና ወንድሜም በዚያ እንድገኝ ስለጠራኝ እባክህ እንድሄድ ፍቀድልኝ። እንግዲህ በፊትህ ሞገስ ካገኘሁ እባክህ ወንድሞቼን አይ ዘንድ ሹልክ ብዬ ልሂድ።’ ዳዊት በንጉሡ ማዕድ ላይ ያልተገኘው ለዚህ ነው።” 30 በዚህ ጊዜ ሳኦል በዮናታን ላይ እጅግ ተቆጣ፤ እንዲህም አለው፦ “አንተ የዚያች ዓመፀኛ ሴት ልጅ፣ በራስህም ሆነ በእናትህ* ላይ ውርደት ለማምጣት ከእሴይ ልጅ ጋር መወገንህን የማላውቅ መሰለህ? 31 የእሴይ ልጅ በምድር ላይ በሕይወት እስካለ ድረስ አንተም ሆንክ መንግሥትህ አትጸኑም።+ እሱ መሞት ስላለበት* በል አሁኑኑ ልከህ አስመጣልኝ።”+

32 ዮናታን ግን አባቱን ሳኦልን “ለምን ይገደላል?+ ጥፋቱስ ምንድን ነው?” አለው። 33 በዚህ ጊዜ ሳኦል እሱን ለመግደል ጦሩን ወረወረበት፤+ ስለሆነም ዮናታን አባቱ፣ ዳዊትን ለመግደል ቆርጦ መነሳቱን አወቀ።+ 34 ዮናታንም ወዲያውኑ በታላቅ ቁጣ ከማዕዱ ላይ ተነሳ፤ በዳዊት ምክንያት በጣም ስላዘነና+ የገዛ አባቱም ስላዋረደው አዲስ ጨረቃ በወጣች በሁለተኛው ቀን ምንም ምግብ አልቀመሰም።

35 ዮናታንም በማለዳ ተነስቶ ከዳዊት ጋር ወደተቀጣጠሩበት ቦታ ሄደ፤ አንድ ወጣት አገልጋይም አብሮት ነበር።+ 36 እሱም አገልጋዩን “ሂድ፣ ሩጥ፤ የምወነጭፋቸውንም ፍላጻዎች ፈልግ” አለው። ከዚያም አገልጋዩ ሮጠ፤ ዮናታንም ፍላጻውን ከእሱ አሳልፎ ወነጨፈው። 37 አገልጋዩም ዮናታን የወነጨፈው ፍላጻ ያረፈበት ቦታ ሲደርስ ዮናታን አገልጋዩን ጠርቶ “ፍላጻው ያለው ከአንተ ወዲያ አይደለም?” አለው። 38 ዮናታንም በድጋሚ አገልጋዩን ጠርቶ “ፍጠን እንጂ! ቶሎ በል! አትዘግይ!” አለው። የዮናታን አገልጋይም ፍላጻዎቹን አንስቶ ወደ ጌታው ተመለሰ። 39 አገልጋዩ ስለ ጉዳዩ የሚያውቀው ነገር አልነበረም፤ የዚህ ትርጉም ምን እንደሆነ የሚያውቁት ዮናታንና ዳዊት ብቻ ነበሩ። 40 ከዚያም ዮናታን የጦር መሣሪያዎቹን ለአገልጋዩ ሰጥቶ “ሂድ፣ ወደ ከተማ ይዘሃቸው ተመለስ” አለው።

41 አገልጋዩም ሲሄድ ዳዊት በስተ ደቡብ በኩል ከሚገኝ በአቅራቢያው ካለ ስፍራ ተነስቶ መጣ። ሦስት ጊዜም በግንባሩ መሬት ላይ ተደፍቶ እጅ ነሳ፤ ከዚያም ተሳሳሙ፤ ተላቀሱ፤ ይበልጥ ያለቀሰው ግን ዳዊት ነበር። 42 ዮናታንም ዳዊትን “ሁለታችንም ‘ይሖዋ በእኔና በአንተ፣ በዘሮቼና በዘሮችህ መካከል ለዘላለም ይሁን’+ ብለን በይሖዋ ስም ስለተማማልን+ በሰላም ሂድ” አለው።

ከዚያም ዳዊት ተነስቶ ሄደ፤ ዮናታንም ወደ ከተማዋ ተመለሰ።

21 በኋላም ዳዊት ካህኑ አሂሜሌክ ወደሚገኝበት ወደ ኖብ+ መጣ። አሂሜሌክም ዳዊትን ሲያገኘው ተንቀጠቀጠ፤ እሱም “ምነው ብቻህን? ሰው አብሮህ የለም?” አለው።+ 2 ዳዊትም ለካህኑ ለአሂሜሌክ እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “ንጉሡ አንድ ጉዳይ እንዳስፈጽም አዞኝ ነበር፤ ሆኖም ‘ስለሰጠሁህ ተልእኮና ስላዘዝኩህ ነገር ማንም ሰው ምንም ነገር እንዳያውቅ’ ብሎኛል። ከሰዎቼም ጋር የሆነ ቦታ ላይ ለመገናኘት ተቀጣጥረናል። 3 ስለዚህ አሁን እጅህ ላይ አምስት ዳቦ ካለ ወይም የተገኘውን ማንኛውንም ነገር ስጠኝ።” 4 ካህኑ ግን ዳዊትን እንዲህ አለው፦ “ማንኛውም ሰው የሚበላው ዓይነት ዳቦ የለኝም፤ ሰሞኑን ሰዎቹ ራሳቸውን ከሴት ጠብቀው*+ ከሆነ ግን የተቀደሰው ኅብስት አለ።”+ 5 ስለዚህ ዳዊት ካህኑን እንዲህ አለው፦ “ከዚህ በፊት ለውጊያ እንደወጣሁባቸው ጊዜያት ሁሉ አሁንም ፈጽሞ ሴቶች ወደ እኛ አልቀረቡም።+ ተራ በሆነ ተልእኮም እንኳ የሰዎቹ አካል ቅዱስ ከነበረ ታዲያ ዛሬማ እንዴት ይበልጥ ቅዱስ አይሆን!” 6 በመሆኑም ካህኑ የተቀደሰውን ኅብስት ሰጠው፤+ ምክንያቱም ትኩስ ኅብስት በሚተካበት ቀን ከይሖዋ ፊት ከተነሳው ገጸ ኅብስት በስተቀር ሌላ ዳቦ አልነበረም።

7 ከሳኦል አገልጋዮች አንዱ በይሖዋ ፊት እንዲቆይ በመገደዱ ያን ቀን እዚያ ነበር። ዶይቅ+ የተባለው ይህ ኤዶማዊ+ የሳኦል እረኞች አለቃ ነበር።

8 ከዚያም ዳዊት አሂሜሌክን “ንጉሡ የሰጠኝ ተልእኮ አስቸኳይ ስለነበር ሰይፌንም ሆነ የጦር መሣሪያዎቼን አልያዝኩም፤ እዚህ አንተ ጋ ጦር ወይም ሰይፍ ይኖራል?” አለው። 9 ካህኑም “በኤላህ ሸለቆ*+ አንተ የገደልከው የፍልስጤማዊው የጎልያድ ሰይፍ+ አለ፤ ያውልህ ከኤፉዱ+ ኋላ በጨርቅ ተጠቅልሎ ተቀምጧል። ከእሱ ሌላ እዚህ ምንም ስለሌለ ከፈለግክ እሱን ውሰደው” አለው። ዳዊትም “ከእሱ የተሻለማ የትም አይገኝም። እሱኑ ስጠኝ” አለው።

10 በዚያም ቀን ዳዊት ተነስቶ ከሳኦል ሸሸ፤+ ከጊዜ በኋላም ወደ ጌት+ ንጉሥ ወደ አንኩስ መጣ። 11 የአንኩስ አገልጋዮችም እንዲህ አሉት፦ “ይህ የምድሪቱ ንጉሥ፣ ዳዊት አይደለም?

‘ሳኦል ሺዎችን ገደለ፤

ዳዊት ደግሞ አሥር ሺዎችን ገደለ’+

በማለት እየዘፈኑ የጨፈሩለትስ ለዚህ ሰው አይደለም?” 12 ዳዊትም ይህን ቃል በቁም ነገር ተመለከተው፤ የጌትን ንጉሥ አንኩስንም እጅግ ፈራው።+ 13 በመሆኑም በፊታቸው አእምሮውን እንደሳተ ሰው ሆነ፤+ በመካከላቸውም* እንደአበደ ሰው አደረገው። የከተማዋን በሮች ይቦጫጭር እንዲሁም ለሃጩን በጢሙ ላይ ያዝረበርብ ጀመር። 14 አንኩስም አገልጋዮቹን እንዲህ አላቸው፦ “እስቲ ተመልከቱ፣ ሰውየው እኮ እብድ ነው! ታዲያ ወደ እኔ ያመጣችሁት ለምንድን ነው? 15 ይህን ሰው ፊቴ እንዲህ እንዲያብድ ያመጣችሁት እኔ እብድ አጥቼ ነው? ይህስ ሰው ቤቴ መግባት ይገባዋል?”

22 ዳዊትም ከዚያ ተነስቶ+ ወደ አዱላም+ ዋሻ ሸሸ። ወንድሞቹና መላው የአባቱ ቤት ይህን ሲሰሙ እሱ ወዳለበት ወደዚያ ወረዱ። 2 ችግር ያጋጠማቸው፣ ዕዳ ያለባቸውና የተከፉ* ሰዎች ሁሉ ወደ እሱ ተሰበሰቡ፤ እሱም አለቃቸው ሆነ። ከእሱም ጋር 400 ገደማ የሚሆኑ ሰዎች ነበሩ።

3 በኋላም ዳዊት ከዚያ ተነስቶ በሞዓብ ወዳለችው ወደ ምጽጳ ሄደ፤ የሞዓብንም+ ንጉሥ “አምላክ የሚያደርግልኝን ነገር እስካውቅ ድረስ እባክህ አባቴና እናቴ አንተ ጋ ይሁኑ” አለው። 4 በመሆኑም የሞዓብ ንጉሥ ጋ አስቀመጣቸው፤ እነሱም ዳዊት በተራራው ላይ ምሽግ ውስጥ በነበረበት ጊዜ ሁሉ እዚያ ተቀመጡ።+

5 ከጊዜ በኋላም ነቢዩ ጋድ+ ዳዊትን “እዚህ ምሽግ ውስጥ መቆየት የለብህም። ሄደህ ወደ ይሁዳ ምድር ግባ” አለው።+ በመሆኑም ዳዊት ሄዶ ወደ ሄሬት ጫካ ገባ።

6 ሳኦልም ዳዊትና ከእሱ ጋር የነበሩት ሰዎች መገኘታቸውን ሰማ። በዚህ ጊዜ ሳኦል በጊብዓ+ በኮረብታው ላይ ባለው የታማሪስክ ዛፍ ሥር ጦሩን ይዞ ተቀምጦ ነበር፤ አገልጋዮቹም ሁሉ በዙሪያው ቆመው ነበር። 7 ከዚያም ሳኦል በዙሪያው የቆሙትን አገልጋዮቹን እንዲህ አላቸው፦ “እናንተ ቢንያማውያን፣ እስቲ ስሙኝ፤ ለመሆኑ የእሴይ+ ልጅ እንደ እኔ፣ እርሻና የወይን ቦታ ለሁላችሁም ይሰጣችኋል? ሁላችሁንስ የሺህ አለቆችና የመቶ አለቆች አድርጎ ይሾማችኋል?+ 8 እናንተ ሁላችሁ በእኔ ላይ ደባ ፈጽማችሁብኛል! የገዛ ልጄ ከእሴይ ልጅ ጋር ቃል ኪዳን ሲጋባ+ አንድም ሰው አልነገረኝም! ይኸው አሁን እንደምታዩት የገዛ ልጄ፣ አገልጋዬን በእኔ ላይ እንዲያደባብኝ ማነሳሳቱን አንዳችሁም ብትሆኑ ስለ እኔ ተቆርቁራችሁ አልነገራችሁኝም።”

9 ከዚያም በሳኦል አገልጋዮች ላይ ተሹሞ የነበረው ኤዶማዊው ዶይቅ+ እንዲህ ሲል መለሰ፦+ “የእሴይ ልጅ በኖብ ወደሚገኘው ወደ አኪጡብ+ ልጅ ወደ አሂሜሌክ ሲመጣ አይቻለሁ። 10 አሂሜሌክም ይሖዋን ጠየቀለት፤ ስንቅም ሰጠው። ሌላው ቀርቶ የፍልስጤማዊውን የጎልያድን ሰይፍ ሰጠው።”+ 11 ንጉሡም ወዲያውኑ ሰዎች ልኮ የካህኑን የአኪጡብን ልጅ አሂሜሌክንና በኖብ በአባቱ ቤት የነበሩትን ካህናት በሙሉ አስጠራ። በመሆኑም ሁሉም ወደ ንጉሡ መጡ።

12 ሳኦልም “አንተ የአኪጡብ ልጅ፣ እስቲ ስማኝ!” አለው፤ እሱም መልሶ “እሺ ጌታዬ፣ እየሰማሁ ነው” አለ። 13 ከዚያም ሳኦል “ለእሴይ ልጅ ምግብና ሰይፍ በመስጠት እንዲሁም ስለ እሱ አምላክን በመጠየቅ አንተም ሆንክ እሱ ደባ የፈጸማችሁብኝ ለምንድን ነው? ይኸው አሁን እንደሚታየው እየተቃወመኝና እያደባብኝ ነው” አለው። 14 በዚህ ጊዜ አሂሜሌክ ንጉሡን እንዲህ አለው፦ “እንደው ለመሆኑ ከአገልጋዮችህ ሁሉ መካከል እንደ ዳዊት ያለ እምነት የሚጣልበት* ማን አለ?+ እሱ የንጉሡ አማች፣+ የክብር ዘቦችህ አለቃና በቤትህ የተከበረ ሰው ነው።+ 15 ስለ እሱ አምላክን ስጠይቅ+ ዛሬ የመጀመሪያዬ ነው? የምትናገረው ነገር ፈጽሞ ያላሰብኩትን ነው! ንጉሡ አገልጋዩንም ሆነ የአባቴን ቤት በሙሉ ጥፋተኛ አያድርግ፤ ምክንያቱም አገልጋይህ ስለዚህ ጉዳይ ምንም የሚያውቀው ነገር የለም።”+

16 ንጉሡ ግን “አሂሜሌክ፣ አንተም ሆንክ የአባትህ ቤት+ በሙሉ በእርግጥ ትሞታላችሁ”+ አለው። 17 ከዚያም ንጉሡ በዙሪያው ቆመው የነበሩትን ጠባቂዎች* “ከዳዊት ጋር ስላበሩ ዙሩና የይሖዋን ካህናት ግደሉ! ዳዊት መኮብለሉን እያወቁ አልነገሩኝም!” አላቸው። የንጉሡ አገልጋዮች ግን የይሖዋን ካህናት ለመግደል እጃቸውን ማንሳት አልፈለጉም። 18 ንጉሡም ዶይቅን+ “እንግዲያውስ አንተ ዙርና ካህናቱን ግደላቸው!” አለው። ኤዶማዊው+ ዶይቅም ወዲያውኑ ሄዶ ካህናቱን ገደላቸው። በዚያን ቀን፣ ከበፍታ የተሠራ ኤፉድ የለበሱ 85 ሰዎችን ገደለ።+ 19 እንዲሁም የካህናቱን ከተማ ኖብን+ በሰይፍ መታ፤ ወንድም ሆነ ሴት፣ ልጅም ሆነ ጨቅላ ሕፃን፣ በሬም ሆነ አህያ ወይም በግ አንድም ሳያስቀር ሁሉንም በሰይፍ ገደለ።

20 ሆኖም ከአኪጡብ ልጅ ከአሂሜሌክ ልጆች አንዱ የሆነው አብያታር+ አምልጦ ዳዊትን ለመከተል እሱ ወዳለበት እየሮጠ ሄደ። 21 አብያታር ለዳዊት “ሳኦል እኮ የይሖዋን ካህናት ገደላቸው” ሲል ነገረው። 22 በዚህ ጊዜ ዳዊት አብያታርን እንዲህ አለው፦ “ያን ቀን ኤዶማዊው ዶይቅ እዚያ ስለነበር ይህን ለሳኦል እንደሚነግረው አውቄአለሁ።+ በአባትህ ቤት ላሉት ሰዎች* ሁሉ ሞት ተጠያቂው እኔ ራሴ ነኝ። 23 አሁን እኔ ጋ ቆይ። የአንተን ሕይወት* የሚፈልግ የእኔን ሕይወት* የሚፈልግ ስለሆነ አትፍራ፤ እኔ ከለላ እሆንሃለሁ።”+

23 ከጊዜ በኋላም ዳዊት “ፍልስጤማውያን በቀኢላ+ ላይ ውጊያ ከፍተው በየአውድማው ያለውን እህል እየዘረፉ ነው” ተብሎ ተነገረው። 2 ስለሆነም ዳዊት “ሄጄ እነዚህን ፍልስጤማውያን ልምታ?” በማለት ይሖዋን ጠየቀ።+ ይሖዋም ዳዊትን “ሂድ፣ ፍልስጤማውያንን ምታ፤ ቀኢላንም አድናት” አለው። 3 የዳዊት ሰዎች ግን “እዚህ በይሁዳ እያለን እንኳ ፈርተናል፤+ የፍልስጤማውያንን ሠራዊት ለመውጋት ወደ ቀኢላ ከሄድንማ ምን ያህል እንፈራ!”+ አሉት። 4 በመሆኑም ዳዊት እንደገና ይሖዋን ጠየቀ።+ ይሖዋም “ፍልስጤማውያንን በእጅህ አሳልፌ ስለምሰጥህ+ ተነስተህ ወደ ቀኢላ ውረድ” ሲል መለሰለት። 5 ስለዚህ ዳዊት ከሰዎቹ ጋር በመሆን ወደ ቀኢላ ሄዶ ከፍልስጤማውያን ጋር ተዋጋ፤ ከብቶቻቸውን እየነዳ ወሰደ፤ ብዙ ሰውም ገደለባቸው፤ በዚህ መንገድ ዳዊት የቀኢላን ነዋሪዎች ታደጋቸው።+

6 የአሂሜሌክ ልጅ አብያታር+ በቀኢላ ወደነበረው ወደ ዳዊት በሸሸ ጊዜ ኤፉድ ይዞ ነበር። 7 ሳኦል “ዳዊት ወደ ቀኢላ መጥቷል” የሚል ወሬ ደረሰው። ሳኦልም “ዳዊት በሮችና መቀርቀሪያዎች ወዳሏት ከተማ በመግባት ራሱን ወጥመድ ውስጥ ከቷል፤ ስለሆነም አምላክ እሱን በእጄ አሳልፎ ሰጥቶታል”*+ አለ። 8 በመሆኑም ሳኦል ወደ ቀኢላ በመውረድ ዳዊትንና ሰዎቹን ከቦ ለመያዝ ሕዝቡን ሁሉ ለጦርነት አሰባሰበ። 9 ዳዊትም ሳኦል ሴራ እየጠነሰሰበት መሆኑን ሲያውቅ ካህኑን አብያታርን “ኤፉዱን ወደዚህ አምጣው” አለው።+ 10 ከዚያም ዳዊት እንዲህ አለ፦ “የእስራኤል አምላክ ይሖዋ ሆይ፣ ሳኦል ወደ ቀኢላ መጥቶ በእኔ የተነሳ ከተማዋን ለማጥፋት+ ማሰቡን አገልጋይህ በእርግጥ ሰምቷል። 11 ታዲያ የቀኢላ መሪዎች* ለእሱ አሳልፈው ይሰጡኝ ይሆን? አገልጋይህ እንደሰማውስ ሳኦል ወደዚህ ይወርድ ይሆን? የእስራኤል አምላክ ይሖዋ ሆይ፣ እባክህ ለአገልጋይህ አሳውቀው።” በዚህ ጊዜ ይሖዋ “አዎ፣ ይወርዳል” አለው። 12 ዳዊትም “የቀኢላ መሪዎች እኔንና ሰዎቼን ለሳኦል አሳልፈው ይሰጡን ይሆን?” በማለት ጠየቀ። ይሖዋም “አዎ፣ አሳልፈው ይሰጧችኋል” ሲል መለሰለት።

13 ዳዊትም 600 ገደማ+ ከሚሆኑት የራሱ ሰዎች ጋር ወዲያውኑ ተነሳ፤ ከቀኢላም ወጥተው መሄድ ወደሚችሉበት ቦታ ሁሉ ሄዱ። ሳኦልም ዳዊት ከቀኢላ መሸሹ ሲነገረው እሱን ለማሳደድ መውጣቱን ተወው። 14 ዳዊትም በምድረ በዳው ውስጥ በሚገኙ በቀላሉ በማይደረስባቸው ቦታዎች፣ በዚፍ+ ምድረ በዳ ባለው ተራራማ አካባቢ ተቀመጠ። ሳኦል ሁልጊዜ ይፈልገው ነበር፤+ ይሖዋ ግን በእጁ አሳልፎ አልሰጠውም። 15 ዳዊት በሆሬሽ በሚገኘው በዚፍ ምድረ በዳ ሳለ ሳኦል የእሱን ሕይወት* ለመፈለግ መውጣቱን አውቆ* ነበር።

16 የሳኦል ልጅ ዮናታንም በሆሬሽ ወደሚገኘው ወደ ዳዊት ሄደ፤ እሱም በይሖዋ ላይ ያለው ትምክህት እንዲጠናከር ረዳው።*+ 17 እንዲህም አለው፦ “አባቴ ሳኦል ስለማያገኝህ አትፍራ፤ አንተ በእስራኤል ላይ ንጉሥ ትሆናለህ፤+ እኔ ደግሞ ከአንተ ቀጥዬ ሁለተኛ ሰው እሆናለሁ፤ አባቴ ሳኦልም ቢሆን ይህን ያውቃል።”+ 18 ከዚያም ሁለቱም በይሖዋ ፊት ቃል ኪዳን ተጋቡ፤+ ዳዊትም በሆሬሽ ተቀመጠ፤ ዮናታን ደግሞ ወደ ቤቱ ተመለሰ።

19 በኋላም የዚፍ ሰዎች በጊብዓ+ ወደነበረው ወደ ሳኦል ወጥተው እንዲህ አሉት፦ “ዳዊት እዚሁ አጠገባችን ከየሺሞን*+ በስተ ደቡብ፣* በሃኪላ ኮረብታ+ ላይ በሆሬሽ+ በሚገኙት በቀላሉ የማይደረስባቸው ስፍራዎች ተደብቆ የለም?+ 20 አሁንም ንጉሥ ሆይ፣ ወደዚህ ለመውረድ* በምትፈልግበት በማንኛውም ጊዜ ወደዚህ ና፤ እኛም እሱን ለንጉሡ አሳልፈን እንሰጣለን።”+ 21 በዚህ ጊዜ ሳኦል እንዲህ አላቸው፦ “ለእኔ ስለተቆረቆራችሁ ይሖዋ ይባርካችሁ። 22 አሁንም እባካችሁ ሂዱና ያለበትን ትክክለኛ ቦታም ሆነ በዚያ ያየውን ሰው ማንነት ለይታችሁ ለማወቅ ጥረት አድርጉ፤ ምክንያቱም እሱ በጣም ተንኮለኛ ሰው እንደሆነ ሰምቻለሁ። 23 የሚደበቅባቸውን ቦታዎች በሙሉ በደንብ አጣሩ፤ ከዚያም ተጨባጭ ማስረጃ ይዛችሁልኝ ኑ። እኔም አብሬያችሁ እሄዳለሁ፤ በዚያ አገር የሚገኝ ከሆነ ከይሁዳ ሺዎች* ሁሉ መካከል የገባበት ገብቼ አወጣዋለሁ።”

24 በመሆኑም ሰዎቹ ተነሱ፤ ከሳኦልም ቀድመው ወደ ዚፍ+ ሄዱ፤ በዚህ ጊዜ ዳዊትና ሰዎቹ ከየሺሞን በስተ ደቡብ በሚገኘው በአረባ፣+ በማኦን+ ምድረ በዳ ነበሩ። 25 ሳኦልም ዳዊትን ለመፈለግ ከሰዎቹ ጋር መጣ።+ ዳዊትም ይህ በተነገረው ጊዜ ወዲያውኑ ወደ ዓለቱ+ ወርዶ በማኦን ምድረ በዳ ተቀመጠ። ሳኦል ይህን ሲሰማ ዳዊትን እያሳደደ ወደ ማኦን ምድረ በዳ ሄደ። 26 ከዚያም ሳኦል ከተራራው በአንደኛው በኩል ሲሆን ዳዊትና ሰዎቹ ደግሞ ከተራራው በሌላኛው በኩል ሆኑ። ዳዊት ከሳኦል ለማምለጥ እየተጣደፈ ነበር፤+ ይሁን እንጂ ሳኦልና አብረውት የነበሩት ሰዎች ዳዊትንና ሰዎቹን ለመያዝ ተቃርበው ነበር።+ 27 ሆኖም አንድ መልእክተኛ ወደ ሳኦል መጥቶ “ፍልስጤማውያን ምድሪቱን ስለወረሯት ቶሎ ድረስ!” አለው። 28 በዚህ ጊዜ ሳኦል ዳዊትን ማሳደዱን ትቶ+ ፍልስጤማውያንን ለመግጠም ሄደ። ያ ቦታ ‘የመለያያ ዓለት’ የተባለው በዚህ የተነሳ ነው።

29 ዳዊትም ከዚያ ወጥቶ በኤንገዲ+ በሚገኙ በቀላሉ በማይደረስባቸው ስፍራዎች ተቀመጠ።

24 ሳኦል ፍልስጤማውያንን አሳዶ እንደተመለሰ “ዳዊት በኤንገዲ+ ምድረ በዳ ይገኛል” ብለው ነገሩት።

2 ስለዚህ ሳኦል ከመላው እስራኤል የተመረጡ 3,000 ሰዎችን ይዞ ዳዊትንና ሰዎቹን ለመፈለግ የተራራ ፍየሎች ወደሚገኙበት ዓለታማ ገደላ ገደል ሄደ። 3 ሳኦልም በመንገዱ ዳር ወዳለ ከድንጋይ የተሠራ የበጎች ጉረኖ ደረሰ፤ በዚያም አንድ ዋሻ ነበር፤ በመሆኑም ሳኦል ለመጸዳዳት* ወደ ዋሻው ገባ፤ በዚህ ጊዜ ዳዊትና ሰዎቹ በዋሻው+ ውስጠኛ ክፍል ተቀምጠው ነበር። 4 ከዚያም የዳዊት ሰዎች “ይሖዋ ‘ጠላትህን በእጅህ አሳልፌ እሰጥሃለሁ፤+ አንተም ደስ ያለህን ታደርግበታለህ’ ያለህ ቀን ይህ ነው” አሉት። ስለሆነም ዳዊት ተነሳ፤ የሳኦልንም ልብስ ጫፍ በቀስታ ቆርጦ ወሰደ። 5 በኋላ ላይ ግን ዳዊት የሳኦልን ልብስ ጫፍ በመቁረጡ ልቡ* ወቀሰው።+ 6 አብረውት የነበሩትንም ሰዎች “ይሖዋ በቀባው በጌታዬ ላይ እጄን በማንሳት እንዲህ ያለውን ድርጊት መፈጸም በይሖዋ ዓይን ፈጽሞ የማይታሰብ ነገር ነው፤ ምክንያቱም እሱ ይሖዋ የቀባው ነው”+ አላቸው። 7 ስለዚህ ዳዊት ይህን በማለት ሰዎቹን ከለከላቸው፤* በሳኦል ላይ ጉዳት እንዲያደርሱበትም አልፈቀደላቸውም። ሳኦልም ተነስቶ ከዋሻው ወጥቶ ሄደ።

8 ከዚያም ዳዊት ከዋሻው በመውጣት “ጌታዬ ንጉሥ ሆይ!”+ በማለት ሳኦልን ጠራው። ሳኦልም ወደኋላው ዞር ብሎ ሲመለከት ዳዊት በግንባሩ መሬት ላይ ተደፍቶ ሰገደ። 9 ዳዊትም ሳኦልን እንዲህ አለው፦ “‘ዳዊት የአንተን ክፉ ማየት ይፈልጋል’ የሚሉትን ሰዎች ወሬ ለምን ትሰማለህ?+ 10 በዛሬዋ ዕለት በዋሻው ውስጥ ይሖዋ አንተን እንዴት አድርጎ በእጄ ሰጥቶኝ እንደነበር በገዛ ዓይንህ አይተሃል። አንድ ሰው እንድገድልህ ገፋፍቶኝ+ የነበረ ቢሆንም እኔ ግን ለአንተ በማዘን ‘ይሖዋ የቀባው+ ስለሆነ በጌታዬ ላይ እጄን አላነሳም’ አልኩ። 11 አሁንም አባቴ ሆይ፣ ተመልከት፣ በእጄ የያዝኩትን የልብስህን ቁራጭ እይ፤ የልብስህን ጫፍ በቆረጥኩ ጊዜ ልገድልህ እችል ነበር፤ ግን አልገደልኩህም። እንግዲህ አንተን ለመጉዳትም ሆነ በአንተ ላይ ለማመፅ ፈጽሞ እንዳላሰብኩ ከዚህ ማየትና መረዳት ትችላለህ፤ ምንም እንኳ ሕይወቴን* ለማጥፋት እያሳደድከኝ+ ቢሆንም እኔ በአንተ ላይ ምንም የፈጸምኩት በደል የለም።+ 12 ይሖዋ በእኔና በአንተ መካከል ይፍረድ፤+ ይሖዋ አንተን ይበቀልልኝ+ እንጂ እኔ በምንም ዓይነት እጄን በአንተ ላይ አላነሳም።+ 13 ‘ከክፉ ሰው ክፉ ነገር ይወጣል’ የሚል የጥንት አባባል አለ፤ እኔ ግን በምንም ዓይነት እጄን በአንተ ላይ አላነሳም። 14 ለመሆኑ የእስራኤል ንጉሥ የወጣው ማንን ፍለጋ ነው? የምታሳድደውስ ማንን ነው? አንድን የሞተ ውሻ? ወይስ አንዲትን ቁንጫ?+ 15 አሁንም ይሖዋ ዳኛ ሆኖ በእኔና በአንተ መካከል ይፍረድ፤ ጉዳዩንም ተመልክቶ ስለ እኔ ይሟገትልኝ፤+ እሱ ይፍረድልኝ፣ ከእጅህም ያድነኝ።”

16 ዳዊት ይህን ተናግሮ ሲጨርስ ሳኦል “ልጄ ዳዊት፣ ይህ የአንተ ድምፅ ነው?”+ አለው። ከዚያም ሳኦል ድምፁን ከፍ አድርጎ አለቀሰ። 17 ዳዊትንም እንዲህ አለው፦ “አንተ መልካም ስታደርግልኝ እኔ ግን ክፉ መለስኩልህ፤ ስለሆነም አንተ ከእኔ ይልቅ ጻድቅ ነህ።+ 18 አዎ፣ ይሖዋ እኔን በእጅህ አሳልፎ ቢሰጥህም ሳትገድለኝ በመቅረት ለእኔ ያደረግከውን መልካም ነገር ይኸው ዛሬ ነገርከኝ።+ 19 ለመሆኑ ጠላቱን አግኝቶ ጉዳት ሳያደርስበት የሚለቀው ሰው ይኖራል? ዛሬ አንተ ለእኔ መልካም ስላደረግክልኝ ይሖዋም ለአንተ መልካም በማድረግ ወሮታህን ይመልስልህ።+ 20 ደግሞም አንተ በእርግጥ ንጉሥ ሆነህ እንደምትገዛ አውቃለሁ፤+ የእስራኤልም መንግሥት በእጅህ ይጸናል። 21 በመሆኑም አሁን ከእኔ በኋላ የሚመጡትን ዘሮቼን እንደማታጠፋና ስሜንም ከአባቴ ቤት+ እንደማትደመስስ በይሖዋ ማልልኝ።”+ 22 ስለዚህ ዳዊት ለሳኦል ማለለት፤ ከዚያም ሳኦል ወደ ቤቱ ሄደ።+ ዳዊትና ሰዎቹ ግን ወደ ምሽጉ ወጡ።+

25 ከጊዜ በኋላም ሳሙኤል+ ሞተ፤ እስራኤላውያንም በሙሉ ሊያለቅሱለትና በራማ+ በሚገኘው ቤቱ ሊቀብሩት ተሰበሰቡ። ከዚያም ዳዊት ተነስቶ ወደ ፋራን ምድረ በዳ ወረደ።

2 በማኦን+ የሚኖር እጅግ ባለጸጋ የሆነ አንድ ሰው ነበር። ይህ ሰው የሚሠራው በቀርሜሎስ*+ ሲሆን 3,000 በጎችና 1,000 ፍየሎች ነበሩት፤ በዚያን ወቅት በቀርሜሎስ በጎቹን እየሸለተ ነበር። 3 የሰውየው ስም ናባል፣+ የሚስቱ ስም ደግሞ አቢጋኤል+ ነበር። እሷም በጣም አስተዋይና ውብ ሴት ነበረች፤ ከካሌብ+ ወገን የሆነው ባሏ ግን ኃይለኛና ምግባረ ብልሹ ሰው ነበር።+ 4 ዳዊት በምድረ በዳ ሳለ ናባል በጎቹን እየሸለተ መሆኑን ሰማ። 5 ስለዚህ ዳዊት አሥር ወጣቶችን ወደ እሱ ላከ፤ ዳዊትም ወጣቶቹን እንዲህ አላቸው፦ “ወደ ቀርሜሎስ ወጥታችሁ ናባልን ስታገኙት በስሜ ስለ ደህንነቱ ጠይቁት። 6 ከዚያም ናባልን እንዲህ በሉት፦ ‘ረጅም ዕድሜና ጤና* እመኝልሃለሁ፤ ለመላ ቤተሰብህና የአንተ ለሆነው ሁሉ ሰላም ይሁን። 7 በጎችህን እየሸለትክ እንዳለህ ሰምቻለሁ። እረኞችህም ከእኛ ጋር በነበሩበት ጊዜ ምንም ዓይነት ጉዳት አላደረስንባቸውም፤+ በቀርሜሎስ በነበሩበት ጊዜ ሁሉ ምንም ነገር አልጠፋባቸውም። 8 ወጣቶችህን ጠይቅ፤ ይነግሩሃል። እንግዲህ የመጣነው በደስታ* ቀን ስለሆነ ወጣቶቼ በፊትህ ሞገስ ያግኙ። እባክህ ለአገልጋዮችህና ለልጅህ ለዳዊት የቻልከውን ያህል ስጥ።’”+

9 በመሆኑም ዳዊት የላካቸው ወጣቶች ሄደው ይህን ሁሉ በዳዊት ስም ለናባል ነገሩት። ተናግረው እንዳበቁም 10 ናባል የዳዊትን አገልጋዮች እንዲህ አላቸው፦ “ለመሆኑ ዳዊት ማን ነው? ደግሞስ የእሴይ ልጅ ማን ነው? በአሁኑ ጊዜ እንደሆነ ከጌቶቻቸው የሚኮበልሉ+ አገልጋዮች ብዙ ናቸው። 11 ታዲያ ዳቦዬን፣ ውኃዬንና ለሚሸልቱልኝ ሰዎች ያረድኩትን ሥጋ ከየት እንደመጡ እንኳ ለማላውቃቸው ሰዎች መስጠት ይኖርብኛል?”

12 ዳዊት የላካቸው ወጣቶችም ወደመጡበት ተመልሰው በመሄድ የተባሉትን ሁሉ ነገሩት። 13 ዳዊትም ወዲያውኑ አብረውት ላሉት ሰዎች “በሉ ሁላችሁም ሰይፋችሁን ታጠቁ!”+ አላቸው። በመሆኑም ሁሉም ሰይፋቸውን ታጠቁ፤ ዳዊትም ሰይፉን ታጠቀ፤ ወደ 400 ገደማ የሚሆኑ ሰዎች ከዳዊት ጋር ሲወጡ 200ዎቹ ግን ጓዙን ለመጠበቅ እዚያው ቀሩ።

14 ይህ በእንዲህ እንዳለ ከአገልጋዮቹ አንዱ ለናባል ሚስት ለአቢጋኤል እንዲህ አላት፦ “እነሆ፣ ዳዊት ለጌታችን መልካም ምኞቱን ለመግለጽ መልእክተኞችን ከምድረ በዳ ልኮ ነበር፤ እሱ ግን የስድብ ናዳ አወረደባቸው።+ 15 ሰዎቹ ለእኛ እጅግ ጥሩ ነበሩ። ምንም ዓይነት ጉዳት አድርሰውብን አያውቁም፤ በመስክ ከእነሱ ጋር አብረን በነበርንባቸው ጊዜያት ሁሉ አንድም ነገር ጠፍቶብን አያውቅም።+ 16 መንጋውን እየጠበቅን ከእነሱ ጋር በቆየንባቸው ጊዜያት ሁሉ ሌሊትም ሆነ ቀን በዙሪያችን እንደ መከላከያ ቅጥር ሆነውልን ነበር። 17 እንግዲህ አሁን በጌታችንና በቤቱ ሁሉ ላይ ጥፋት+ መምጣቱ ስለማይቀር ምን ማድረግ እንዳለብሽ ወስኚ፤ እሱ እንደሆነ የማይረባ*+ ሰው ስለሆነ ማንም ሊያናግረው አይችልም።”

18 ስለሆነም አቢጋኤል+ ወዲያውኑ 200 ዳቦ፣ ሁለት እንስራ የወይን ጠጅ፣ ታርደው የተሰናዱ አምስት በጎች፣ አምስት የሲህ መስፈሪያ* ቆሎ፣ 100 የዘቢብ ቂጣ እንዲሁም 200 የበለስ ጥፍጥፍ ወስዳ ሁሉንም በአህዮች ላይ ጫነች።+ 19 ከዚያም አገልጋዮቿን “ቀድማችሁኝ ሂዱ፤ እኔም እከተላችኋለሁ” አለቻቸው። ለባሏ ለናባል ግን ምንም አልነገረችውም።

20 አቢጋኤልም አህያ ላይ እንደተቀመጠች በተራራው ተከልላ እየወረደች ሳለ ዳዊትና ሰዎቹም ወደ እሷ እየወረዱ ነበር፤ እሷም አገኘቻቸው። 21 ዳዊትም እንዲህ ብሎ ነበር፦ “በምድረ በዳ የዚህን ሰው ንብረት የጠበቅኩለት ለካስ እንዲያው በከንቱ ነበር። ደግሞም ከንብረቱ መካከል አንድም ነገር አልጠፋበትም፤+ እሱ ግን ደግ በሠራሁለት ክፉ መለሰልኝ።+ 22 የእሱ ከሆኑት ወንዶች* መካከል እስከ ነገ ጠዋት ድረስ አንድ ሰው እንኳ ባስቀር አምላክ በዳዊት ጠላቶች ላይ* ይህን ያድርግ፤ ከዚህ የከፋም ነገር ያምጣ።”

23 አቢጋኤልም ዳዊትን ባየችው ጊዜ፣ ከተቀመጠችበት አህያ ላይ በፍጥነት በመውረድ በዳዊት ፊት በግንባሯ ተደፍታ ሰገደች። 24 ከዚያም እግሩ ላይ ወድቃ እንዲህ አለችው፦ “ጌታዬ ሆይ፣ ጥፋቱ በእኔ ላይ ይሁን፤ እባክህ አገልጋይህ እንድታናግርህ ፍቀድላት፤ የአገልጋይህንም ቃል ስማ። 25 እባክህ ጌታዬ፣ ናባል የተባለውን ይህን የማይረባ+ ሰው ከቁብ አትቁጠረው፤ እሱ ልክ እንደ ስሙ ነውና። ስሙ ናባል* ነው፤ ደግሞም ማስተዋል የጎደለው ሰው ነው። እኔ አገልጋይህ ግን ጌታዬ የላካቸውን ወጣቶች አላየሁም። 26 እናም አሁን ጌታዬ፣ ሕያው በሆነው በይሖዋና በሕያውነትህ* እምላለሁ፣ በደም ዕዳ ተጠያቂ+ ከመሆንና በራስህ እጅ ከመበቀል* የጠበቀህ+ ይሖዋ ነው። አሁንም ጠላቶችህና ጌታዬን ሊጎዱ የሚፈልጉ ሁሉ እንደ ናባል ይሁኑ። 27 ስለዚህ አገልጋይህ ለጌታዬ ያመጣችው ይህ ስጦታ*+ ጌታዬን ለሚከተሉት ወጣቶች+ ይሰጥ። 28 ጌታዬ እየተዋጋ ያለው የይሖዋን ጦርነት+ ስለሆነ ይሖዋ የጌታዬን ቤት ለዘለቄታው ያጸናለታል፤+ ስለሆነም እባክህ የአገልጋይህን መተላለፍ ይቅር በል፤ በሕይወት ዘመንህም ሁሉ ክፋት አይገኝብህ።+ 29 ማንም ሰው አንተን ለማሳደድ ቢነሳና ሕይወትህን* ለማጥፋት ቢፈልግ የጌታዬ ሕይወት* በአምላክህ በይሖዋ ዘንድ በደንብ በታሰረ የሕይወት ከረጢት ውስጥ ትቀመጣለች፤ የጠላቶችህን ሕይወት* ግን ከወንጭፍ እንደሚወረወር ድንጋይ ይወነጭፈዋል። 30 ይሖዋ ቃል የገባለትን መልካም ነገር ሁሉ ለጌታዬ በሚፈጽምለትና በእስራኤል ላይ መሪ አድርጎ በሚሾመው+ ጊዜ 31 ጌታዬ ያለምክንያት ደም በማፍሰሱና እጁን ለበቀል በማንሳቱ* ልቡን የሚቆጨው ወይም የሚጸጽተው* ነገር አይኖርም።+ ይሖዋ ለጌታዬ መልካም ነገር በሚያደርግለት ጊዜ አገልጋይህን አስባት።”

32 በዚህ ጊዜ ዳዊት አቢጋኤልን እንዲህ አላት፦ “ዛሬ እኔን እንድታገኚኝ የላከሽ የእስራኤል አምላክ ይሖዋ ይወደስ! 33 ማስተዋልሽም የተባረከ ይሁን! በዚህ ዕለት በራሴ ላይ የደም ዕዳ እንዳላመጣና+ በገዛ እጄ እንዳልበቀል* ስለጠበቅሽኝ አንቺም የተባረክሽ ሁኚ። 34 በአንቺ ላይ ጉዳት ከማድረስ በጠበቀኝ+ ሕያው በሆነው በእስራኤል አምላክ በይሖዋ እምላለሁ፣ እኔን ለማግኘት ፈጥነሽ ባትመጪ ኖሮ+ እስከ ነገ ጠዋት ድረስ የናባል የሆነ አንድም ወንድ* ባልተረፈ ነበር።”+ 35 ከዚያም ዳዊት ያመጣችለትን ነገር ከእጇ ተቀብሎ “ወደ ቤትሽ በሰላም ሂጂ። ይኸው ቃልሽን ሰምቻለሁ፤ የጠየቅሽኝንም እፈጽምልሻለሁ” አላት።

36 በኋላም አቢጋኤል በቤቱ እንደ ንጉሥ ግብዣ ያለ ታላቅ ግብዣ አዘጋጅቶ ወደነበረው ወደ ናባል ተመለሰች፤ ናባልም ልቡ በሐሴት ተሞልቶ በጣም ሰክሮ ነበር። እሷም እስኪነጋ ድረስ ምንም ነገር አልነገረችውም። 37 ጠዋት ላይ ናባል ስካሩ ሲበርድለት ሚስቱ የሆነውን ሁሉ ነገረችው። ልቡም እንደ ሞተ ሰው ልብ ሆነ፤ ሰውነቱም እንደ ድንጋይ በድን ሆነ። 38 ከአሥር ቀን ገደማ በኋላም ይሖዋ ናባልን ስለቀሰፈው ሞተ።

39 ዳዊት፣ ናባል መሞቱን ሲሰማ እንዲህ አለ፦ “ከናባል የደረሰብኝን ነቀፋ+ የተሟገተልኝና+ አገልጋዩን መጥፎ ድርጊት ከመፈጸም የጠበቀው+ ይሖዋ ይወደስ፤ ይሖዋ የናባልን ክፋት በራሱ ላይ መለሰው!” ከዚያም ዳዊት አቢጋኤል ሚስት እንድትሆነው ጥያቄ ለማቅረብ መልእክት ላከ። 40 በመሆኑም የዳዊት አገልጋዮች በቀርሜሎስ ወዳለችው ወደ አቢጋኤል መጥተው “ዳዊት ሊያገባሽ ስለፈለገ ወደ አንቺ ልኮናል” አሏት። 41 እሷም ወዲያውኑ ተነሳች፤ በግንባሯም ተደፍታ በመስገድ “ባሪያህ እንደ አገልጋይ በመሆን የጌታዬን አገልጋዮች እግር ለማጠብ+ ዝግጁ ነች” አለች። 42 ከዚያም አቢጋኤል+ ፈጥና ተነሳች፤ አምስት ሴት አገልጋዮቿንም በማስከተል በአህያ ላይ ተቀምጣ ጉዞ ጀመረች፤ ከዳዊት መልእክተኞችም ጋር አብራ ሄደች፤ የዳዊትም ሚስት ሆነች።

43 በተጨማሪም ዳዊት ከኢይዝራኤል+ አኪኖዓምን+ አግብቶ ነበር፤ ሁለቱም ሴቶች ሚስቶቹ ሆኑ።+

44 ሳኦል ግን የዳዊት ሚስት የነበረችውን ልጁን ሜልኮልን+ የጋሊም ሰው ለሆነው ለላይሽ ልጅ ለፓልጢ+ ድሯት ነበር።

26 ከጊዜ በኋላ የዚፍ+ ሰዎች በጊብዓ+ ወደሚገኘው ወደ ሳኦል መጥተው “ዳዊት በየሺሞን*+ ፊት ለፊት በሚገኘው በሃኪላ ኮረብታ ተደብቆ የለም?” አሉት። 2 ስለሆነም ሳኦል ከእስራኤል የተመረጡ 3,000 ሰዎችን በማስከተል ዳዊትን በዚፍ ምድረ በዳ ለመፈለግ ወደዚያ ወረደ።+ 3 ሳኦልም ከየሺሞን ፊት ለፊት በሚገኘው በሃኪላ ኮረብታ ላይ መንገድ ዳር ሰፈረ። በዚህ ጊዜ ዳዊት በምድረ በዳ ይኖር ነበር፤ ዳዊትም ሳኦል እሱን ለመፈለግ ወደ ምድረ በዳ እንደመጣ ሰማ። 4 በመሆኑም ሳኦል በእርግጥ መጥቶ እንደሆነ ለማወቅ ሰላዮችን ላከ። 5 በኋላም ዳዊት ሳኦል ወደሰፈረበት ቦታ ሄደ፤ ሳኦልና የሠራዊቱ አዛዥ የሆነው የኔር ልጅ አበኔር+ የተኙበትንም ቦታ አየ፤ ሳኦል በሰፈሩ መሃል ተኝቶ ነበር፤ ሠራዊቱም ዙሪያውን ሰፍሮ ነበር። 6 ከዚያም ዳዊት ሂታዊውን+ አሂሜሌክንና የኢዮዓብ ወንድም የሆነውን የጽሩያን+ ልጅ አቢሳን+ “ሳኦል ወደሰፈረበት ቦታ አብሮኝ የሚወርድ ማን ነው?” አላቸው። አቢሳም “እኔ አብሬህ እወርዳለሁ” አለ። 7 ስለዚህ ዳዊትና አቢሳ በሌሊት ሠራዊቱ ወዳለበት ሄዱ፤ ሳኦልም ጦሩን ራስጌው አጠገብ መሬት ላይ ሰክቶ በሰፈሩ መሃል ተኝቶ አገኙት፤ አበኔርና ሠራዊቱም በዙሪያው ተኝተው ነበር።

8 አቢሳም ዳዊትን “አምላክ ዛሬ ጠላትህን እጅህ ላይ ጥሎታል።+ እባክህ አሁን አንድ ጊዜ ብቻ በጦር ወግቼ ከመሬት ጋር ላጣብቀው፤ መድገም አያስፈልገኝም” አለው። 9 ሆኖም ዳዊት አቢሳን “ጉዳት እንዳታደርስበት፤ ለመሆኑ ይሖዋ በቀባው+ ላይ እጁን አንስቶ ከበደል ነፃ የሚሆን ማን ነው?”+ አለው። 10 ከዚያም ዳዊት እንዲህ አለው፦ “ሕያው በሆነው በይሖዋ እምላለሁ፣ ይሖዋ ራሱ ይቀስፈዋል፤+ ወይም ደግሞ እንደ ማንኛውም ሰው አንድ ቀን ይሞታል፤+ አሊያም ወደ ጦርነት ወርዶ እዚያ ይገደላል።+ 11 በእኔ በኩል ይሖዋ በቀባው ላይ እጄን ማንሳት በይሖዋ ዓይን ፈጽሞ የማይታሰብ ነገር ነው!+ በል አሁን ራስጌው አጠገብ ያለውን ጦርና የውኃ መያዣውን አንሳና እንሂድ።” 12 በመሆኑም ዳዊት ጦሩንና የውኃ መያዣውን ከሳኦል ራስጌ ወሰደ፤ ከዚያም ሄዱ። ሁሉም ተኝተው ስለነበር ያያቸውም ሆነ ልብ ያላቸው ወይም ከእንቅልፉ የነቃ አንድም ሰው አልነበረም፤+ ምክንያቱም ይሖዋ ከባድ እንቅልፍ ጥሎባቸው ነበር። 13 ከዚያም ዳዊት ወደ ማዶ ተሻግሮ በተራራው ጫፍ ላይ ራቅ ብሎ ቆመ፤ በመካከላቸውም ያለው ርቀት ሰፊ ነበር።

14 ዳዊትም ወደ ሠራዊቱና ወደ ኔር ልጅ ወደ አበኔር+ ተጣርቶ “አበኔር፣ የማትመልስልኝ ለምንድን ነው?” አለ። አበኔርም “ንጉሡን የምትጣራው አንተ ማን ነህ?” ሲል መለሰለት። 15 ዳዊትም አበኔርን እንዲህ አለው፦ “አንተ ወንድ አይደለህም? ደግሞስ በእስራኤል ውስጥ እንደ አንተ ያለ ማን አለ? ታዲያ ጌታህን ንጉሡን በንቃት ያልጠበቅከው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ከወታደሮቹ አንዱ ንጉሡን ጌታህን ለመግደል መጥቶ ነበር።+ 16 ይህ ያደረግከው ነገር ጥሩ አይደለም። ሕያው በሆነው በይሖዋ እምላለሁ፣ ይሖዋ የቀባውን+ ጌታችሁን በንቃት ስላልጠበቃችሁ ሞት ይገባችኋል። እስቲ ዙሪያህን ተመልከት! በንጉሡ ራስጌ አጠገብ የነበረው የንጉሡ ጦርና የውኃ መያዣ+ የት አለ?”

17 ሳኦልም የዳዊት ድምፅ መሆኑን ስለለየ “ልጄ ዳዊት ሆይ፣ ይህ የአንተ ድምፅ ነው?” አለው።+ ዳዊትም መልሶ “ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፣ አዎ የእኔ ድምፅ ነው” አለ። 18 አክሎም እንዲህ አለ፦ “ጌታዬ አገልጋዩን የሚያሳድደው ለምንድን ነው?+ ምን አድርጌ ነው? የተገኘብኝስ በደል ምንድን ነው?+ 19 ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፣ እባክህ የአገልጋይህን ቃል ስማ፦ በእኔ ላይ እንድትነሳ ያደረገህ ይሖዋ ከሆነ የማቀርበውን የእህል መባ ይቀበል።* ሆኖም እንዲህ እንድታደርግ ያነሳሱህ ሰዎች ከሆኑ+ በይሖዋ ፊት የተረገሙ ይሁኑ፤ ምክንያቱም ‘ሂድ፣ ሌሎች አማልክትን አገልግል!’ ብለው በይሖዋ ርስት+ ውስጥ ድርሻ እንዳይኖረኝ ዛሬ አባረውኛል። 20 አሁንም ደሜ ከይሖዋ ፊት ርቆ መሬት ላይ እንዲፈስ አታድርግ፤ ምክንያቱም የእስራኤል ንጉሥ በተራራ ላይ ቆቅ የሚያሳድድ ይመስል አንዲት ቁንጫ+ ለመፈለግ ወጥቷል።”

21 ሳኦልም መልሶ እንዲህ አለው፦ “በእርግጥ ኃጢአት ሠርቻለሁ።+ ልጄ ዳዊት ሆይ፣ ከእንግዲህ ምንም ጉዳት ስለማላደርስብህ ተመለስ፤ ምክንያቱም በዛሬው ዕለት ሕይወቴን* ውድ አድርገህ+ ተመልክተሃታል። በእርግጥም የሞኝነት ድርጊት ፈጽሜአለሁ፤ ትልቅ ስህተት ሠርቻለሁ።” 22 ዳዊትም እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “የንጉሡ ጦር ይኸውና። ከወጣቶቹ መካከል አንዱ ይምጣና ይውሰደው። 23 ለእያንዳንዱ ሰው እንደ ጽድቁና+ እንደ ታማኝነቱ የሚከፍለው ይሖዋ ነው፤ ይኸው ዛሬ ይሖዋ እጄ ላይ ጥሎህ ነበር፤ እኔ ግን ይሖዋ በቀባው ላይ እጄን ለማንሳት ፈቃደኛ አልሆንኩም።+ 24 እነሆ፣ ዛሬ የአንተ ሕይወት* በፊቴ ውድ እንደሆነች ሁሉ የእኔም ሕይወት* በይሖዋ ፊት ውድ ትሁን፤ ከመከራም ሁሉ ያድነኝ።”+ 25 ሳኦልም ዳዊትን “ልጄ ዳዊት ሆይ፣ የተባረክ ሁን። አንተ ታላላቅ ሥራዎችን ታከናውናለህ፤ ድል አድራጊም ትሆናለህ” አለው።+ ከዚያም ዳዊት መንገዱን ቀጠለ፤ ሳኦልም ወደ ስፍራው ተመለሰ።+

27 ሆኖም ዳዊት በልቡ እንዲህ አለ፦ “አንድ ቀን በሳኦል እጅ መጥፋቴ አይቀርም። የሚያዋጣኝ ወደ ፍልስጤማውያን ምድር መሸሽ ነው፤+ ሳኦልም ተስፋ ቆርጦ በእስራኤል ግዛት ሁሉ እኔን መፈለጉን ያቆማል፤+ እኔም ከእጁ አመልጣለሁ።” 2 በመሆኑም ዳዊት አብረውት ከነበሩት 600 ሰዎች+ ጋር ተነስቶ የጌት ንጉሥ ወደሆነው ወደ ማኦክ ልጅ ወደ አንኩስ+ ተሻገረ። 3 ዳዊትና ሰዎቹም እያንዳንዳቸው ከነቤተሰባቸው ጌት ውስጥ አንኩስ ዘንድ ተቀመጡ። ዳዊትም ከሁለቱ ሚስቶቹ ማለትም ከኢይዝራኤላዊቷ ከአኪኖዓም+ እና የናባል ሚስት ከነበረችው ከቀርሜሎሳዊቷ ከአቢጋኤል+ ጋር ነበር። 4 ሳኦልም ዳዊት ወደ ጌት መሸሹ ሲነገረው እሱን መፈለጉን ተወ።+

5 ከዚያም ዳዊት አንኩስን “በፊትህ ሞገስ አግኝቼ ከሆነ በገጠር ካሉ ከተሞች በአንዱ እንድኖር ቦታ እንዲሰጡኝ አድርግ። አገልጋይህ ለምን በንጉሥ ከተማ ከአንተ ጋር ይኖራል?” አለው። 6 በመሆኑም አንኩስ በዚያ ቀን ጺቅላግን+ ሰጠው። ጺቅላግ እስካሁንም ድረስ የይሁዳ ነገሥታት ይዞታ የሆነችው በዚህ ምክንያት ነው።

7 ዳዊት በፍልስጤማውያን ገጠራማ አካባቢ የኖረበት ጊዜ* አንድ ዓመት ከአራት ወር ነበር።+ 8 ዳዊትም ከሰዎቹ ጋር በመሆን ገሹራውያንን፣+ ጊዝራውያንን እና አማሌቃውያንን+ ለመውረር ይወጣ ነበር፤ ምክንያቱም እነዚህ ሕዝቦች ከቴላም አንስቶ እስከ ሹር+ እና እስከ ግብፅ ምድር ድረስ ባለው አካባቢ ይኖሩ ነበር። 9 ዳዊት በምድሪቱ ላይ ጥቃት በሚሰነዝርበት ጊዜ ወንድም ሆነ ሴት በሕይወት አያስቀርም ነበር፤+ ሆኖም መንጎችን፣ ከብቶችን፣ አህዮችን፣ ግመሎችንና ልብሶችን ወስዶ ወደ አንኩስ ይመለስ ነበር። 10 አንኩስም “ዛሬ በማን ላይ ዘመታችሁ?” ይለው ነበር። ዳዊትም “በይሁዳ ደቡባዊ ክፍል*+ ላይ ዘምተን ነበር” ወይም “በየራህምኤላውያን+ ምድር ደቡባዊ ክፍል ላይ ዘምተን ነበር” አሊያም “በቄናውያን+ ምድር ደቡባዊ ክፍል ላይ ዘምተን ነበር” በማለት ይመልስለት ነበር። 11 ዳዊት “‘እሱ እንዲህ አደረገ’ በማለት ስለ እኛ ሊነግሯቸው ይችላሉ” ብሎ ስላሰበ ወንድም ሆነ ሴት በሕይወት አስተርፎ ወደ ጌት አያመጣም ነበር። (ዳዊት በፍልስጤም ገጠራማ አካባቢ በኖረበት ዘመን ሁሉ እንዲህ የማድረግ ልማድ ነበረው።) 12 ስለዚህ አንኩስ ‘በእርግጥም ይህ ሰው በገዛ ሕዝቦቹ በእስራኤላውያን ዘንድ እንደ ጥንብ ተቆጥሯል፤ ስለሆነም ዕድሜ ልኩን አገልጋዬ ይሆናል’ ብሎ ስላሰበ ዳዊትን አመነው።

28 በዚያም ዘመን ፍልስጤማውያን ከእስራኤል ጋር ለመዋጋት ሠራዊታቸውን አሰባሰቡ።+ በመሆኑም አንኩስ ዳዊትን “መቼም አንተና ሰዎችህ አብራችሁኝ ወደ ጦርነት እንደምትወጡ ታውቃለህ” አለው።+ 2 ዳዊትም አንኩስን “አገልጋይህ ምን እንደሚያደርግ አንተ በእርግጥ ታውቃለህ” አለው። ከዚያም አንኩስ ዳዊትን “እኔም በቋሚነት የግል ጠባቂዬ* እንድትሆን የምሾምህ ለዚህ ነው” አለው።+

3 በዚህ ጊዜ ሳሙኤል ሞቶ ነበር፤ እስራኤላውያንም ሁሉ አልቅሰውለት በገዛ ከተማው በራማ+ ቀብረውት ነበር። ሳኦልም መናፍስት ጠሪዎችንና ጠንቋዮችን ከምድሪቱ አስወግዶ ነበር።+

4 ፍልስጤማውያንም ተሰብስበው በመምጣት በሹነም+ ሰፈሩ። ሳኦል ደግሞ እስራኤላውያንን በሙሉ አሰባሰበ፤ እነሱም በጊልቦአ+ ሰፈሩ። 5 ሳኦል የፍልስጤማውያንን ሠራዊት ባየ ጊዜ ፈራ፤ ልቡም እጅግ ተሸበረ።+ 6 ሳኦል ይሖዋን ቢጠይቅም+ ይሖዋ በሕልምም ሆነ በኡሪም+ አሊያም በነቢያት በኩል መልስ አልሰጠውም። 7 በመጨረሻም ሳኦል አገልጋዮቹን “መናፍስት ጠሪ+ ፈልጉልኝ፤ እኔም ሄጄ ምክር እጠይቃታለሁ” አላቸው። አገልጋዮቹም “በኤንዶር+ አንዲት መናፍስት ጠሪ አለች” በማለት መለሱለት።

8 በመሆኑም ሳኦል ማንነቱን ሰውሮና ሌላ ልብስ ለብሶ ከሁለት ሰዎች ጋር በመሆን በሌሊት ወደ ሴትየዋ ሄደ። እሱም “እባክሽ፣ መናፍስትን ጠርተሽ+ ጠንቁይልኝ፤ የምነግርሽንም ሰው አስነሺልኝ” አላት። 9 ሆኖም ሴትየዋ እንዲህ አለችው፦ “ሳኦል መናፍስት ጠሪዎችንና ጠንቋዮችን ከምድሪቱ በማስወገድ ምን እንዳደረገ አንተ ራስህ በሚገባ ታውቃለህ።+ ታዲያ እኔ እንድገደል ልታጠምደኝ* የምትሞክረው ለምንድን ነው?”+ 10 ከዚያም ሳኦል “ሕያው በሆነው በይሖዋ እምላለሁ፣ በዚህ ጉዳይ በጥፋተኝነት አትጠየቂም!” በማለት በይሖዋ ማለላት። 11 በዚህ ጊዜ ሴትየዋ “እሺ ማንን ላስነሳልህ?” አለችው። እሱም “ሳሙኤልን አስነሺልኝ” አላት። 12 ሴትየዋም “ሳሙኤልን”*+ ስታየው በኃይል ጮኸች፤ ከዚያም ሳኦልን “ያታለልከኝ ለምንድን ነው? አንተ ሳኦል አይደለህ!” አለችው። 13 ንጉሡም “አትፍሪ፤ ለመሆኑ ምን እያየሽ ነው?” አላት። ሴትየዋም ለሳኦል “አማልክትን የሚመስል ከምድር ሲወጣ አያለሁ” ስትል መለሰችለት። 14 እሱም ወዲያውኑ “ምን ይመስላል?” አላት፤ እሷም “የወጣው አንድ አረጋዊ ሰው ነው፤ እጅጌ የሌለው ቀሚስ ለብሷል”+ አለችው። በዚህ ጊዜ ሳኦል የወጣው “ሳሙኤል” እንደሆነ ተገነዘበ፤ በግንባሩም መሬት ላይ ተደፍቶ ሰገደ።

15 ከዚያም “ሳሙኤል” ሳኦልን “እንድነሳ በማድረግ ለምን ትረብሸኛለህ?” አለው። ሳኦልም እንዲህ አለው፦ “ከባድ ጭንቅ ውስጥ ገብቻለሁ። ፍልስጤማውያን እየወጉኝ ነው፤ አምላክም ከእኔ ርቋል፤ በነቢያትም ሆነ በሕልም አማካኝነት መልስ አይሰጠኝም፤+ ስለሆነም ምን ማድረግ እንዳለብኝ እንድትነግረኝ ጠራሁህ።”+

16 “ሳሙኤልም” እንዲህ አለው፦ “ታዲያ ይሖዋ ከራቀህና+ ጠላት ከሆነብህ እኔን ለምን ትጠይቀኛለህ? 17 ይሖዋ በእኔ በኩል አስቀድሞ የተናገረውን ይፈጽማል፦ ይሖዋ መንግሥትን ከእጅህ ነጥቆ ከባልንጀሮችህ አንዱ ለሆነው ለዳዊት ይሰጠዋል።+ 18 የይሖዋን ቃል ስላልሰማህና በአማሌቃውያን ላይ የነደደውን ቁጣውን ስላላስፈጸምክ+ ይሖዋ በዚህ ቀን ይህን ያደርግብሃል። 19 ይሖዋ አንተንም ሆነ እስራኤላውያንን ለፍልስጤማውያን+ አሳልፎ ይሰጣችኋል፤ ነገ አንተና+ ልጆችህ+ ከእኔ ጋር ትሆናላችሁ። በተጨማሪም ይሖዋ የእስራኤልን ሠራዊት ለፍልስጤማውያን አሳልፎ ይሰጣል።”+

20 በዚህ ጊዜ ሳኦል በቁመቱ መሬት ላይ ተዘረረ፤ “ሳሙኤል” በተናገረውም ቃል የተነሳ በከፍተኛ ፍርሃት ተዋጠ። ደግሞም ሙሉ ቀንና ሙሉ ሌሊት እህል ስላልቀመሰ አቅሙ ተሟጠጠ። 21 ሴትየዋም ወደ ሳኦል መጥታ በጣም እንደተረበሸ ስታይ እንዲህ አለችው፦ “እንግዲህ እኔ አገልጋይህ ቃልህን ሰምቻለሁ፤ ሕይወቴን አደጋ ላይ ጥዬም*+ እንዳደርገው የነገርከኝን ፈጽሜአለሁ። 22 አሁንም እባክህ፣ የአገልጋይህን ቃል ስማ። ትንሽ ምግብ ላቅርብልህና ብላ፤ ከዚያም ለመሄድ የሚያስችል ብርታት ታገኛለህ።” 23 እሱ ግን “አልበላም” በማለት እንቢ አለ። ሆኖም አገልጋዮቹና ሴትየዋ አጥብቀው ለመኑት። በመጨረሻም ቃላቸውን በመስማት ከመሬት ተነስቶ አልጋ ላይ ተቀመጠ። 24 ሴትየዋም ቤት ውስጥ አንድ የሰባ ጥጃ ነበራት፤ ስለዚህ ፈጠን ብላ ጥጃውን አረደችው፤* ከዚያም ዱቄት ወስዳ ካቦካች በኋላ ቂጣ ጋገረች። 25 ለሳኦልና ለአገልጋዮቹም አቀረበችላቸው፤ እነሱም በሉ። ከዚያም ተነስተው በሌሊት ሄዱ።+

29 ፍልስጤማውያን+ ሠራዊታቸውን በሙሉ በአፌቅ አሰባሰቡ፤ እስራኤላውያን ደግሞ በኢይዝራኤል+ በሚገኘው ምንጭ አጠገብ ሰፍረው ነበር። 2 የፍልስጤም ገዢዎችም በመቶዎችና በሺዎች እየሆኑ አለፉ፤ ዳዊትና ሰዎቹም ከአንኩስ+ ጋር ሆነው ከኋላ ተሰልፈው ይሄዱ ነበር። 3 የፍልስጤም መኳንንት ግን “እነዚህ ዕብራውያን እዚህ ምን ያደርጋሉ?” አሉ። በዚህ ጊዜ አንኩስ የፍልስጤምን መኳንንት “ይህ ሰው ከእኔ ጋር ለአንድ ዓመት ወይም ከዚያ በላይ አብሮኝ የኖረው የእስራኤል ንጉሥ የሳኦል አገልጋይ የሆነው ዳዊት ነው።+ ወደ እኔ ከተጠጋበት ቀን አንስቶ እስከዚህች ዕለት ድረስ ምንም ስህተት አላገኘሁበትም” አላቸው። 4 የፍልስጤም መኳንንት ግን በእሱ ላይ ተቆጥተው እንዲህ አሉት፦ “ይህ ሰው እንዲመለስ አድርግ።+ ወደሰጠኸውም ስፍራ ይመለስ። በውጊያው ወቅት እኛኑ ዞሮ እንዳይወጋን+ አብሮን ወደ ጦርነቱ እንዲሄድ ማድረግ የለብህም። ደግሞስ ከጌታው ጋር ለመታረቅ የእኛን ሰዎች ራስ ቆርጦ ከመውሰድ በስተቀር ምን የተሻለ ነገር ሊያደርግ ይችላል? 5 ይህ ሰው

‘ሳኦል ሺዎችን ገደለ፤

ዳዊት ደግሞ አሥር ሺዎችን ገደለ’ በማለት እየዘፈኑ የጨፈሩለት ዳዊት አይደለም?”+

6 በመሆኑም አንኩስ+ ዳዊትን ጠርቶ እንዲህ አለው፦ “ሕያው በሆነው በይሖዋ እምላለሁ፣ አንተ ቅን ሰው ነህ፤ በእኔ በኩል ከሠራዊቴ ጋር አብረህ ብትዘምት ደስ ባለኝ፤+ ምክንያቱም ወደ እኔ ከመጣህበት ቀን አንስቶ እስከዚህች ዕለት ድረስ ምንም ስህተት አላገኘሁብህም።+ ሆኖም ገዢዎቹ አላመኑህም።+ 7 ስለዚህ በሰላም ተመለስ፤ የፍልስጤም ገዢዎችን ቅር የሚያሰኝ ምንም ነገር አታድርግ።” 8 ዳዊት ግን አንኩስን “ምን አደረግኩ? ወደ አንተ ከመጣሁበት ጊዜ አንስቶ እስከዚህች ዕለት ድረስ በአገልጋይህ ላይ ምን ጥፋት አግኝተህበታል? ከአንተ ጋር የማልሄደውና ከንጉሡ ከጌታዬ ጠላቶች ጋር የማልዋጋው ለምንድን ነው?” አለው። 9 አንኩስም ዳዊትን እንዲህ አለው፦ “በእኔ በኩል አንተ እንደ አምላክ መልአክ ጥሩ ሰው ነህ።+ የፍልስጤም መኳንንት ግን ‘ከእኛ ጋር ለጦርነት እንዲወጣ አታድርግ’ አሉኝ። 10 አሁንም አብረውህ ከመጡት የጌታህ አገልጋዮች ጋር በማለዳ ተነሱ፤ ልክ ጎህ ሲቀድ ጉዞ ጀምሩ።”

11 በመሆኑም ዳዊትና ሰዎቹ ወደ ፍልስጤማውያን ምድር ለመመለስ በጠዋት ተነሱ፤ ፍልስጤማውያንም ወደ ኢይዝራኤል+ ወጡ።

30 በሦስተኛው ቀን ዳዊትና ሰዎቹ ወደ ጺቅላግ+ ሲመጡ አማሌቃውያን+ በስተ ደቡብ* ያለውን አካባቢና ጺቅላግን ወረው ነበር፤ እነሱም በጺቅላግ ላይ ጥቃት ሰነዘሩ፤ በእሳትም አቃጠሏት። 2 ሴቶችንና+ በዚያ የነበሩትንም ሁሉ ትንሽ ትልቅ ሳይሉ ማርከው ወሰዱ። አንድም ሰው አልገደሉም፤ ከዚህ ይልቅ ሁሉንም ይዘው ሄዱ። 3 ዳዊትና ሰዎቹ ወደ ጺቅላግ ሲመጡ ከተማዋ በእሳት ተቃጥላ አገኟት፤ ሚስቶቻቸውም ሆኑ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸው በምርኮ ተወስደው ነበር። 4 በመሆኑም ዳዊትና አብረውት የነበሩት ሰዎች ለማልቀስ አቅም እስኪያጡ ድረስ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው አለቀሱ። 5 ሁለቱ የዳዊት ሚስቶችም ማለትም ኢይዝራኤላዊቷ አኪኖዓም እና የቀርሜሎሳዊው የናባል ሚስት የነበረችው አቢጋኤል በምርኮ ተወስደው ነበር።+ 6 ዳዊት ሰዎቹ ሊወግሩት እየተማከሩ ስለነበር እጅግ ተጨነቀ፤ ምክንያቱም ሰዎቹ* ሁሉ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸው በመወሰዳቸው ተመርረው ነበር። ይሁንና ዳዊት በአምላኩ በይሖዋ ራሱን አበረታ።+

7 ከዚያም ዳዊት የአሂሜሌክን ልጅ ካህኑን አብያታርን+ “እባክህ፣ ኤፉዱን አምጣልኝ”+ አለው። አብያታርም ኤፉዱን ለዳዊት አመጣለት። 8 ዳዊትም “ይህን ወራሪ ቡድን ላሳደው? እደርስበት ይሆን?” ሲል ይሖዋን ጠየቀ።+ እሱም “በእርግጥ ስለምትደርስባቸውና የወሰዱትን ሁሉ ከእጃቸው ስለምታስጥል ሂድ አሳዳቸው” አለው።+

9 ዳዊትም ወዲያውኑ አብረውት ከነበሩት 600 ሰዎች+ ጋር ወጣ፤ እነሱም እስከ በሶር ሸለቆ* ድረስ ሄዱ፤ በዚያም የተወሰኑ ሰዎች ወደ ኋላ ቀሩ። 10 ዳዊትም ከ400 ሰዎች ጋር ሆኖ ማሳደዱን ቀጠለ፤ በጣም ከመድከማቸው የተነሳ የበሶርን ሸለቆ መሻገር ያልቻሉት 200 ሰዎች ግን እዚያው ቀሩ።+

11 ከዚያም ሜዳ ላይ አንድ ግብፃዊ አግኝተው ወደ ዳዊት አመጡት። የሚበላው ምግብና የሚጠጣው ውኃ ሰጡት። 12 በተጨማሪም ቁራሽ የበለስ ጥፍጥፍና ሁለት የዘቢብ ቂጣ ሰጡት። እሱም ከበላ በኋላ ብርታት አገኘ፤* ምክንያቱም ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ሙሉ እህልም ሆነ ውኃ አልቀመሰም ነበር። 13 ዳዊትም “ለመሆኑ አንተ የማን ነህ? የመጣኸውስ ከየት ነው?” አለው፤ እሱም መልሶ እንዲህ አለው፦ “እኔ ለአንድ አማሌቃዊ ባሪያ የሆንኩ ግብፃዊ ነኝ፤ ሆኖም ከሦስት ቀን በፊት ታምሜ ስለነበር ጌታዬ ጥሎኝ ሄደ። 14 የከሪታውያንን+ ምድር ደቡባዊ ክፍል፣* የይሁዳን ግዛትና የካሌብን+ ደቡባዊ ክፍል* ወረርን፤ ጺቅላግንም በእሳት አጋየናት።” 15 በዚህ ጊዜ ዳዊት “ይህ ወራሪ ቡድን ወዳለበት መርተህ ትወስደኛለህ?” አለው። እሱም “ብቻ እንደማትገድለኝና ለጌታዬ አሳልፈህ እንደማትሰጠኝ በአምላክ ማልልኝ እንጂ ወራሪው ቡድን ወዳለበት መርቼ አደርስሃለሁ” አለው።

16 በመሆኑም ሰዎቹ ከፍልስጤማውያን ምድርና ከይሁዳ ምድር በወሰዱት ታላቅ ምርኮ የተነሳ በየቦታው ተበታትነው ይበሉና ይጠጡ እንዲሁም ይደሰቱ ወደነበረበት ቦታ መርቶ ወሰደው። 17 ከዚያም ዳዊት ጎህ ሳይቀድ ጀምሮ እስከ ማግስቱ ምሽት ድረስ መታቸው፤ ፈጽሞም አጠፋቸው፤ በግመል ተቀምጠው ከሸሹት 400 ሰዎች በስተቀር አንድም ሰው አላመለጠም።+ 18 ዳዊትም አማሌቃውያን የወሰዱትን ሁሉ አስጣለ፤+ ሁለቱን ሚስቶቹንም አስመለሰ። 19 ከትንሽ እስከ ትልቅ ምንም የጎደለ ነገር አልነበረም። ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውንም ሆነ ዘርፈው የወሰዱባቸውን ንብረት ሁሉ አስመለሱ፤+ ዳዊት የወሰዱትን ሁሉ አስመለሰ። 20 በመሆኑም ዳዊት መንጎቹንና ከብቶቹን በሙሉ ወሰደ፤ እነሱም ከራሳቸው ከብቶች ፊት ፊት ነዷቸው። እነሱም “ይህ የዳዊት ምርኮ ነው” አሉ።

21 ከዚያም ዳዊት በጣም ከመድከማቸው የተነሳ አብረውት ሊሄዱ ወዳልቻሉትና በበሶር ሸለቆ+ ቀርተው ወደነበሩት 200 ሰዎች መጣ፤ እነሱም ዳዊትንና አብረውት የነበሩትን ሰዎች ለመቀበል ወጡ። ዳዊትም ወደ ሰዎቹ በቀረበ ጊዜ ስለ ደህንነታቸው ጠየቃቸው። 22 ሆኖም ከዳዊት ጋር አብረው ከሄዱት መካከል ክፉ የሆኑትና የማይረቡት ሰዎች “እነዚህ ሰዎች አብረውን ስላልሄዱ እያንዳንዳቸው ሚስቶቻቸውንና ልጆቻቸውን ይዘው ይሂዱ እንጂ ካመጣነው ምርኮ ላይ ምንም ነገር አንሰጣቸውም” አሉ። 23 ዳዊት ግን እንዲህ አለ፦ “ወንድሞቼ ይሖዋ በሰጠን ነገርማ እንዲህ ማድረግ የለባችሁም። የጠበቀንና የመጣብንን ወራሪ ቡድን በእጃችን አሳልፎ የሰጠን እሱ ነው።+ 24 ታዲያ አሁን ይህን የምትሉትን ማን ይሰማችኋል? ወደ ውጊያ የዘመተው ሰው የሚያገኘው ድርሻና ጓዝ የጠበቀው ሰው የሚያገኘው ድርሻ እኩል ነው።+ ሁሉም ድርሻ ይኖረዋል።”+ 25 ዳዊትም ከዚያ ቀን ጀምሮ እስከዚህ ዕለት ድረስ ይህን ለእስራኤል ሥርዓትና ደንብ አድርጎ አጸደቀው።

26 ዳዊትም ወደ ጺቅላግ በተመለሰ ጊዜ “ከይሖዋ ጠላቶች ከተገኘው ምርኮ የተሰጠ ስጦታ* ይኸውላችሁ” በማለት ወዳጆቹ ለሆኑት የይሁዳ ሽማግሌዎች ከምርኮው ላይ የተወሰነውን ላከ። 27 ስጦታውንም በቤቴል፣+ በኔጌብ* ራሞት፣ በያቲር፣+ 28 በአሮዔር፣ በሲፍሞት፣ በኤሽተሞዓ፣+ 29 በራካል፣ በየራህምኤል+ ከተሞች፣ በቄናውያን+ ከተሞች፣ 30 በሆርማ፣+ በቦርአሻን፣ በአታክ፣ 31 በኬብሮን+ እንዲሁም ዳዊትና ሰዎቹ በሚያዘወትሩባቸው ስፍራዎች ሁሉ ለነበሩት ላከ።

31 ፍልስጤማውያን ከእስራኤል ጋር እየተዋጉ ነበር።+ የእስራኤልም ሰዎች ከፍልስጤማውያን ፊት ሸሹ፤ ብዙዎቹም በጊልቦአ+ ተራራ ላይ ተገደሉ። 2 ፍልስጤማውያንም ሳኦልንና ወንዶች ልጆቹን እግር በእግር ተከታተሏቸው፤ ፍልስጤማውያንም የሳኦልን ልጆች ዮናታንን፣+ አቢናዳብንና ሜልኪሳን መትተው ገደሏቸው።+ 3 ውጊያው በሳኦል ላይ በረታ፤ ቀስተኞቹም አገኙት፤ እነሱም ክፉኛ አቆሰሉት።+ 4 ከዚያም ሳኦል ጋሻ ጃግሬውን “እነዚህ ያልተገረዙ+ ሰዎች መጥተው እንዳይወጉኝና በጭካኔ እንዳያሠቃዩኝ* ሰይፍህን መዘህ ውጋኝ” አለው። ጋሻ ጃግሬው ግን እጅግ ፈርቶ ስለነበር ፈቃደኛ አልሆነም። በመሆኑም ሳኦል ሰይፉን ወስዶ በላዩ ላይ ወድቆ ሞተ።+ 5 ጋሻ ጃግሬውም ሳኦል መሞቱን ሲያይ+ እሱም በራሱ ሰይፍ ላይ ወድቆ ከእሱ ጋር ሞተ። 6 ስለዚህ ሳኦል፣ ሦስቱ ወንዶች ልጆቹ፣ ጋሻ ጃግሬውና የእሱ ሰዎች በሙሉ በዚያ ቀን አብረው ሞቱ።+ 7 በሸለቆውና* በዮርዳኖስ አካባቢ የነበሩት እስራኤላውያን፣ የእስራኤል ሠራዊት መሸሹን እንዲሁም ሳኦልና ልጆቹ መሞታቸውን ባዩ ጊዜ ከተሞቹን ጥለው ሸሹ፤+ ከዚያም ፍልስጤማውያን መጥተው ከተሞቹን ያዙ።

8 በማግስቱ ፍልስጤማውያን የሞቱትን ሰዎች ልብስና ትጥቅ ለመግፈፍ ሲመጡ ሳኦልንና ሦስቱን ወንዶች ልጆቹን በጊልቦአ+ ተራራ ላይ ወድቀው አገኟቸው። 9 ስለሆነም የሳኦልን ራስ ከቆረጡና የጦር ትጥቁን ከገፈፉ በኋላ ወሬው በጣዖቶቻቸው+ ቤቶችና* በሕዝቡ ሁሉ መካከል እንዲሰራጭ+ ለማድረግ በመላው የፍልስጤም ምድር መልእክት ላኩ። 10 ከዚያም የጦር ትጥቁን በአስታሮት ምስሎች ቤት አስቀመጡት፣ አስከሬኑን ደግሞ በቤትሻን+ ግንብ ላይ ቸነከሩት። 11 የኢያቢስጊልያድ+ ነዋሪዎችም ፍልስጤማውያን በሳኦል ላይ ያደረጉትን ሲሰሙ 12 ተዋጊዎቹ ሁሉ ተነስተው ሌሊቱን ሙሉ ሲጓዙ አደሩ፤ ከዚያም የሳኦልንና የልጆቹን አስከሬን ከቤትሻን ግንብ ላይ አወረዱ። ወደ ኢያቢስ ተመልሰውም በዚያ አቃጠሏቸው። 13 ከዚያም አፅማቸውን+ ወስደው በኢያቢስ+ በሚገኝ የታማሪስክ ዛፍ ሥር ቀበሩት፤ ለሰባት ቀንም ጾሙ።

ወይም “ለመስገድና።”

ቃል በቃል “ማህፀኗን ዘግቶት ነበር።”

የመገናኛ ድንኳኑን ያመለክታል።

ወይም “በነፍሷ ተመርራ።”

ወይም “መንፈሷ ክፉኛ የተደቆሰባት ሴት።”

የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

“ጊዜው ሲደርስ” ማለትም ሊሆን ይችላል።

“የአምላክ ስም” የሚል ትርጉም አለው።

አንድ ኢፍ 22 ሊትር ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።

ወይም “በሕያው ነፍስህ።”

በዕብራይስጥ “አውሰዋለሁ።”

ሕልቃናን እንደሚያመለክት ከሁኔታው መረዳት ይቻላል።

ወይም “ብርታቴም።” የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

ቃል በቃል “መነመነች።”

ወይም “ሕያው ያደርጋል።”

ወይም “ሲኦል።” የሰው ልጆችን ሁሉ መቃብር ያመለክታል። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

“ከቆሻሻ መጣያ” ማለትም ሊሆን ይችላል።

“ከይሖዋ ጋር የሚፎካከሩ ይሸበራሉ” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ወይም “ብርታቱን።” የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

ወይም “ይሖዋን ያገለግል ነበር።”

ትልቅ ድስት።

ወይም “ነፍስህ የጓጓችለትን።”

ቃል በቃል “ታጥቆ።”

በዕብራይስጥ “በውሰት በተሰጠው።”

“አምላክ ይፈርድለታል” ማለትም ሊሆን ይችላል።

“የመሥዋዕት ጭስ እንዲያጨስና” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ቃል በቃል “የእስራኤል ወንዶች ልጆች።”

ቃል በቃል “በርግጫ ያላችሁት።”

ቃል በቃል “ክንድ።”

ወይም “ነፍስህ እንድትመነምን።”

ወይም “በልቤ ውስጥና በነፍሴ ውስጥ ካለው።”

የመገናኛ ድንኳኑን ያመለክታል።

ቃል በቃል “መሬት ጠብ እንዲል አያደርግም።”

ቃል በቃል “ይሖዋ ድል ያደረገን ለምንድን ነው?”

“መካከል” ማለትም ሊሆን ይችላል።

“ክብሩ የት አለ?” የሚል ትርጉም አለው።

ወይም “ቤተ መቅደስ።”

ቃል በቃል “ዳጎን ብቻ።”

ወይም “በፊንጢጣ ኪንታሮት።”

ወይም “የፊንጢጣ ኪንታሮቶችንና።”

ወይም “በረባዳማው ሜዳ።”

ቃል በቃል “70 ሰዎችን፣ 50,000 ሰዎችን።”

ወይም “ወደ ይሖዋ ማልቀስ።”

“የእርዳታ ድንጋይ” የሚል ትርጉም አለው።

ቃል በቃል “ለሳሙኤል መጥፎ ሆኖ ታየው።”

ወይም “ሽቶ ቀማሚዎች።”

ቃል በቃል “እንስት አህዮቹ።”

አንድ ሰቅል 11.4 ግራም ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።

ቃል በቃል “ጆሮውን ከፍቶለት።”

ወይም “ሕዝቤን የሚቆጣጠረው።”

ቃል በቃል “በልብህ ያለውንም ነገር ሁሉ።”

ወይም “በየጎሳችሁ።”

ቃል በቃል “እንደ ዱዳ ሆነ።”

ወይም “ስምምነት አድርግ።”

ከሌሊቱ 8 ሰዓት እስከ ጠዋት 12 ሰዓት ገደማ ያለውን ጊዜ ያመለክታል።

ቃል በቃል “ቃላችሁን ሁሉ ሰምቻለሁ።”

ቃል በቃል “ፊት ፊታችሁ የሚሄደው።”

ቃል በቃል “በእጄ ምንም ነገር እንዳላገኛችሁ።”

ወይም “የማይጨበጡ ነገሮችን።”

ወይም “የማይጨበጡ።”

ወይም “በእውነት።”

በዕብራይስጡ ጽሑፍ ላይ ቁጥሩ አይገኝም።

ይህ ጥንታዊ መለኪያ ሲሆን የሰቅል ሁለት ሦስተኛ ገደማ ይሆናል።

ቃል በቃል “በዚያን ቀን።”

ቃል በቃል “እጅህን ሰብስብ።”

ቃል በቃል “ምድሩም።”

ወይም “መዳን።”

ቃል በቃል “ተቤዠው።”

ወይም “አትራራላቸው።”

ወይም “በደረቁ ወንዝ።”

ወይም “አዝኛለሁ።”

ወይም “ራሩላቸው።”

ቃል በቃል “ከተራፊም ሐውልቶች።” የቤት ውስጥ አማልክትን ወይም ጣዖታትን ያመለክታሉ።

ወይም “አይጸጸትም።”

ወይም “ይጸጸት።”

“እየተጀነነ” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ወይም “ረባዳማ ሜዳ።”

ቁመቱ 2.9 ሜትር ገደማ ነበር። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።

ወደ 57 ኪሎ ግራም ገደማ ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።

ወደ 6.84 ኪሎ ግራም ገደማ ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።

ወይም “እገዳደራለሁ።”

አንድ ኢፍ 22 ሊትር ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።

ወይም “ረባዳማ ሜዳ።”

ወይም “ማንም ሰው ወኔ አይክዳው።”

ወይም “መንጋጋውን ይዤ።” ቃል በቃል “ጺሙን ጨምድጄ።”

ወይም “ከደረቁ ወንዝ።”

ወይም “በሕያው ነፍስህ እምላለሁ።”

ወይም “የዮናታን ነፍስ ከዳዊት ነፍስ ጋር ተቆራኘች።”

ወይም “እንደ ገዛ ነፍሱ።”

ወይም “እንደ ገዛ ነፍሱ።”

ወይም “ተልእኮውን በጥበብ።”

ወይም “እንደ ነቢይ ያደርገው።”

ቃል በቃል “በሕዝቡ ፊት ይወጣና ይገባ ነበር።”

ወይም “የሚያከናውነውን ነገር ሁሉ በጥበብ ያደርግ ነበር።”

ወይም “አማቼ ትሆናለህ።”

ወይም “በጥበብ ይመላለስ ነበር።”

ወይም “ነፍሱን በእጁ ይዞ።”

ወይም “መዳን አስገኘ።”

ወይም “ነፍስህ እንድታመልጥ ካላደረግክ።”

ወይም “የቤት ውስጥ አምላኩን፤ ጣዖቱን።”

ወይም “የቤት ውስጥ አምላኩን፤ ጣዖቱን።”

ወይም “ከውስጥ በለበሰው ልብስ ብቻ።”

ወይም “ነፍሴን።”

ወይም “በሕያው ነፍስህ።”

ወይም “ነፍስህ የምትለውን።”

ወይም “እንደ ገዛ ነፍሱ።”

ቃል በቃል “በአዘቦቱ ቀን።”

ቃል በቃል “በእናትህ እርቃን።”

ቃል በቃል “የሞት ልጅ ስለሆነ።”

ወይም “የፆታ ግንኙነት ከመፈጸም ተቆጥበው።”

ወይም “ረባዳማ ሜዳ።”

ቃል በቃል “እጃቸውም ላይ።”

ወይም “በነፍሳቸው የተመረሩ።”

ወይም “ታማኝ።”

ቃል በቃል “ሯጮች።”

ወይም “ላለው ነፍስ።”

ወይም “ነፍስ።”

ወይም “ነፍስ።”

ቃል በቃል “ለእጄ አሳልፎ ሸጦታል።”

“ባለርስቶች” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ወይም “ነፍስ።”

“በመውጣቱ ፈርቶ” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ቃል በቃል “በይሖዋ እጁን አበረታለት።”

“ከበረሃው፤ ከምድረ በዳው” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ቃል በቃል “በስተ ቀኝ በኩል።”

ወይም “ነፍስህ ወደዚህ ለመውረድ።”

ወይም “ጎሳዎች።”

ቃል በቃል “እግሩን ለመሸፈን።”

ወይም “ሕሊናው።”

“በተናቸው” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ወይም “ነፍሴን።”

በይሁዳ የምትገኝ ከተማ ናት፤ የቀርሜሎስን ተራራ የሚያመለክት አይደለም።

ወይም “ሰላም።”

ቃል በቃል “በጥሩ።”

ወይም “ምናምንቴ።”

አንድ ሲህ 7.33 ሊትር ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።

ቃል በቃል “ግንብ ላይ ከሚሸኑ።” ወንዶችን የሚያናንቅ የዕብራይስጥ አገላለጽ ነው።

“በዳዊት ላይ” ማለትም ሊሆን ይችላል።

“የማያመዛዝን፤ ጅል” የሚል ትርጉም አለው።

ወይም “በሕያው ነፍስህ።”

ወይም “መዳን ለማምጣት ከመሞከር።”

ቃል በቃል “በረከት።”

ወይም “ነፍስህን።”

ወይም “ነፍስ።”

ወይም “ነፍስ።”

ወይም “በእጁ መዳን ለማምጣት በመሞከሩ።”

ቃል በቃል “የሚያንገዳግደው ወይም የሚያደናቅፈው።”

ወይም “መዳን ለማምጣት እንዳልሞክር።”

ቃል በቃል “ግንብ ላይ የሚሸና።” ወንዶችን የሚያናንቅ የዕብራይስጥ አገላለጽ ነው።

“በበረሃው፤ በምድረ በዳው” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ቃል በቃል “ያሽትት።”

ወይም “ነፍሴን።”

ወይም “ነፍስ።”

ወይም “ነፍስ።”

ቃል በቃል “የቀናት ቁጥር።”

ወይም “ኔጌብ።”

ቃል በቃል “በዘመኑ ሁሉ የራሴ ጠባቂ።”

ወይም “ነፍሴን ልታጠምድ።”

ወይም “ሳሙኤልን መስሎ የቀረበውን።”

ወይም “ነፍሴን በእጄ ይዤም።”

ወይም “ሠዋችው።”

ወይም “በኔጌብ።”

ወይም “የሰዎቹ ነፍስ።”

የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

ቃል በቃል “መንፈሱ ተመለሰለት።”

ወይም “ኔጌብ።”

ወይም “ኔጌብ።”

ቃል በቃል “በረከት።”

ወይም “በደቡብ።”

ወይም “እንዳይጫወቱብኝ።”

ወይም “በረባዳማው ሜዳና።”

ወይም “ቤተ መቅደሶችና።”

    የኢትዮጵያ ምልክት ቋንቋ ጽሑፎች (2011-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • የኢትዮጵያ ምልክት ቋንቋ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ