የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
የኢትዮጵያ ምልክት ቋንቋ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • nwt ዘፍጥረት 1:1-50:26
  • ዘፍጥረት

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ዘፍጥረት
  • አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ
አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ
ዘፍጥረት

ዘፍጥረት

1 በመጀመሪያ አምላክ ሰማያትንና ምድርን ፈጠረ።+

2 ምድርም ቅርጽ አልባና ባድማ ነበረች፤* ጥልቁም* ውኃ+ በጨለማ ተሸፍኖ ነበር፤ የአምላክም ኃይል*+ በውኃው ላይ ይንቀሳቀስ ነበር።+

3 አምላክም “ብርሃን ይሁን” አለ። ብርሃንም ሆነ።+ 4 ከዚህ በኋላ አምላክ ብርሃኑ መልካም እንደሆነ አየ፤ አምላክም ብርሃኑን ከጨለማው ለየ። 5 አምላክም ብርሃኑን ‘ቀን’ ብሎ ጠራው፤ ጨለማውን ግን ‘ሌሊት’ ብሎ ጠራው።+ መሸ፣ ነጋም፤ የመጀመሪያ ቀን።

6 ከዚያም አምላክ “በውኃዎቹ መካከል ጠፈር+ ይሁን፣ ውኃዎቹም ከውኃዎቹ ይከፈሉ” አለ።+ 7 ከዚያም አምላክ ጠፈርን ሠራ፤ ከጠፈሩ በታች ያሉትንም ውኃዎች ከጠፈሩ በላይ ካሉት ውኃዎች ለየ።+ እንዳለውም ሆነ። 8 አምላክ ጠፈሩን ‘ሰማይ’ ብሎ ጠራው። መሸ፣ ነጋም፤ ሁለተኛ ቀን።

9 በመቀጠልም አምላክ “ከሰማያት በታች ያሉት ውኃዎች አንድ ቦታ ላይ ይሰብሰቡና ደረቁ መሬት ይገለጥ” አለ።+ እንዳለውም ሆነ። 10 አምላክ ደረቁን መሬት ‘የብስ’+ ብሎ ጠራው፤ አንድ ላይ የተሰበሰቡትን ውኃዎች ግን ‘ባሕር’+ ብሎ ጠራቸው። አምላክም ይህ መልካም እንደሆነ አየ።+ 11 ቀጥሎም አምላክ “ምድር ሣርን፣ ዘር የሚሰጡ ተክሎችን እንዲሁም ዘር ያለው ፍሬ የሚያፈሩ ዛፎችን እንደየወገናቸው ታብቅል” አለ። እንዳለውም ሆነ። 12 ምድርም ሣርን፣ ዘር የሚሰጡ ተክሎችን+ እንዲሁም ዘር ያለው ፍሬ የሚያፈሩ ዛፎችን እንደየወገናቸው ማብቀል ጀመረች። ከዚያም አምላክ ይህ መልካም እንደሆነ አየ። 13 መሸ፣ ነጋም፤ ሦስተኛ ቀን።

14 አምላክም እንዲህ አለ፦ “ቀኑና ሌሊቱ እንዲለይ+ በሰማያት ጠፈር ላይ ብርሃን ሰጪ አካላት+ ይኑሩ፤ እነሱም ወቅቶችን፣ ቀናትንና ዓመታትን+ የሚጠቁሙ ምልክቶች ሆነው ያገለግላሉ። 15 በምድርም ላይ እንዲያበሩ በሰማያት ጠፈር ላይ ያሉ ብርሃን ሰጪ አካላት ሆነው ያገለግላሉ።” እንዳለውም ሆነ። 16 አምላክም ሁለቱን ታላላቅ ብርሃን ሰጪ አካላት ሠራ፤ ታላቁ ብርሃን ሰጪ አካል በቀን እንዲያይል፣+ ታናሹ ብርሃን ሰጪ አካል ደግሞ በሌሊት እንዲያይል አደረገ፤ ከዋክብትንም ሠራ።+ 17 በዚህ መንገድ አምላክ በምድር ላይ እንዲያበሩ በሰማያት ጠፈር ላይ አስቀመጣቸው፤ 18 በተጨማሪም በቀንና በሌሊት እንዲያይሉ እንዲሁም ብርሃኑን ከጨለማው እንዲለዩ አደረገ።+ አምላክም ይህ መልካም እንደሆነ አየ። 19 መሸ፣ ነጋም፤ አራተኛ ቀን።

20 ከዚያም አምላክ “ውኃዎቹ በሚርመሰመሱ ሕያዋን ፍጥረታት* ይሞሉ፤ እንዲሁም የሚበርሩ ፍጥረታት ከምድር በላይ በሰማያት ጠፈር ላይ ይብረሩ” አለ።+ 21 አምላክም ግዙፍ የባሕር ፍጥረታትን እንዲሁም በውኃዎቹ ውስጥ የሚንቀሳቀሱና የሚርመሰመሱ ሕያዋን ፍጥረታትን* ሁሉ እንደየወገናቸው ብሎም ክንፍ ያለውን እያንዳንዱን የሚበር ፍጥረት እንደየወገኑ ፈጠረ። አምላክም ይህ መልካም እንደሆነ አየ። 22 ከዚያም አምላክ “ብዙ ተባዙ፤ የባሕሩንም ውኃ ሙሉት፤+ የሚበርሩ ፍጥረታትም በምድር ላይ ይብዙ” ብሎ ባረካቸው። 23 መሸ፣ ነጋም፤ አምስተኛ ቀን።

24 ቀጥሎም አምላክ “ምድር ሕያዋን ፍጥረታትን* እንደየወገናቸው እንዲሁም የቤት እንስሳትን፣ መሬት ለመሬት የሚሄዱ እንስሳትንና* የዱር እንስሳትን እንደየወገናቸው ታውጣ” አለ።+ እንዳለውም ሆነ። 25 አምላክም በምድር ላይ ያሉ የዱር እንስሳትን እንደየወገናቸው፣ የቤት እንስሳትን እንደየወገናቸው እንዲሁም መሬት ለመሬት የሚሄዱ ፍጥረታትን ሁሉ እንደየወገናቸው ሠራ። አምላክም ይህ መልካም እንደሆነ አየ።

26 ከዚያም አምላክ “ሰውን በመልካችን እንደ አምሳላችን+ እንሥራ፤+ እሱም በባሕር ዓሣዎች፣ በሰማያት ላይ በሚበርሩ ፍጥረታት፣ በቤት እንስሳትና በምድር ሁሉ እንዲሁም በምድር ላይ በሚንቀሳቀሱ መሬት ለመሬት የሚሄዱ እንስሳት ሁሉ ላይ ሥልጣን ይኑረው”+ አለ። 27 አምላክም ሰውን በራሱ መልክ ፈጠረው፤ በአምላክ መልክ ፈጠረው፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው።+ 28 በተጨማሪም አምላክ ባረካቸው፤ እንዲህም አላቸው፦ “ብዙ ተባዙ፤ ምድርንም ሙሏት፤+ ግዟትም።+ እንዲሁም የባሕር ዓሣዎችን፣ በሰማያት ላይ የሚበርሩ ፍጥረታትንና በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱ ፍጥረታትን በሙሉ ግዟቸው።”+

29 ቀጥሎም አምላክ እንዲህ አለ፦ “በመላው ምድር ላይ ያሉ ዘር የሚሰጡ ተክሎችን በሙሉ እንዲሁም ዘር ያለው ፍሬ የሚያፈሩ ዛፎችን በሙሉ ይኸው ሰጥቻችኋለሁ። ምግብ ይሁኗችሁ።+ 30 በምድር ላይ ላለው የዱር እንስሳ ሁሉ፣ በሰማያት ላይ ለሚበር ፍጥረት ሁሉ እንዲሁም ሕይወት* ላለው በምድር ላይ ለሚንቀሳቀስ ነገር ሁሉ አረንጓዴ ተክሎችን በሙሉ ምግብ እንዲሆኗቸው ሰጥቻቸዋለሁ።”+ እንዳለውም ሆነ።

31 ከዚያ በኋላ አምላክ የሠራውን እያንዳንዱን ነገር ተመለከተ፤ እነሆ፣ እጅግ መልካም ነበር!+ መሸ፣ ነጋም፤ ስድስተኛ ቀን።

2 በዚህ መንገድ ሰማያትንና ምድርን እንዲሁም በውስጣቸው ያለውን ነገር ሁሉ* የመፍጠሩ ሥራ ተጠናቀቀ።+ 2 በሰባተኛውም ቀን አምላክ ይሠራው የነበረውን ሥራ አጠናቀቀ፤ በሰባተኛውም ቀን ይሠራው ከነበረው ሥራ ሁሉ ማረፍ ጀመረ።+ 3 አምላክም ሰባተኛውን ቀን ባረከው እንዲሁም ቀደሰው፤ ምክንያቱም አምላክ ከመፍጠር ሥራው ሁሉ፣ ሊሠራ ካሰበው ነገር ሁሉ ያረፈው ከዚያ ቀን አንስቶ ነው።

4 ሰማያትና ምድር በተፈጠሩበት ጊዜ፣ ይሖዋ* አምላክ ምድርንና ሰማይን በሠራበት+ ቀን የተከናወነው ነገር ይህ ነው።

5 በዚህ ጊዜ በምድር ላይ ምንም ዓይነት የሜዳ ቁጥቋጦ አልነበረም፤ እንዲሁም በሜዳ ላይ ምንም ዓይነት ተክል አልበቀለም፤ ምክንያቱም ይሖዋ አምላክ በምድር ላይ ዝናብ እንዲዘንብ አላደረገም ነበር፤ መሬቱን የሚያለማም ሰው አልነበረም። 6 ይሁንና ተን ከምድር እየተነሳ መላውን መሬት ያጠጣ ነበር።

7 ይሖዋ አምላክም ሰውን ከምድር አፈር ሠራው፤+ በአፍንጫውም የሕይወትን እስትንፋስ እፍ አለበት፤+ ሰውየውም ሕያው ሰው* ሆነ።+ 8 በተጨማሪም ይሖዋ አምላክ በስተ ምሥራቅ፣ በኤደን የአትክልት ስፍራ ተከለ፤+ የሠራውንም ሰው+ በዚያ አስቀመጠው። 9 ከዚያም ይሖዋ አምላክ ለማየት የሚያስደስተውንና ለምግብነት መልካም የሆነውን ዛፍ ሁሉ ከመሬት አበቀለ። በተጨማሪም በአትክልቱ ስፍራ መካከል የሕይወት ዛፍ+ እንዲሁም የመልካምና ክፉ እውቀት ዛፍ+ አበቀለ።

10 የአትክልቱን ስፍራ የሚያጠጣ ወንዝ ከኤደን ወጥቶ ይፈስ ነበር፤ ከዚያም ተከፋፍሎ አራት ወንዝ* ሆነ። 11 የመጀመሪያው ወንዝ ስም ፊሶን ነው፤ ይህ ወንዝ ወርቅ የሚገኝበትን መላውን የሃዊላ ምድር የሚከብ ነው። 12 የዚያ አገር ወርቅ ምርጥ ነው። በተጨማሪም በዚያ ጥሩ መዓዛ ያለው ሙጫና* የኦኒክስ ድንጋዮች ይገኛሉ። 13 የሁለተኛው ወንዝ ስም ግዮን ነው፤ ይህ ወንዝ መላውን የኢትዮጵያ* ምድር የሚከብ ነው። 14 የሦስተኛው ወንዝ ስም ጤግሮስ*+ ነው፤ ይህ ወንዝ ከአሦር+ በስተ ምሥራቅ የሚፈስ ነው። አራተኛው ወንዝ ደግሞ ኤፍራጥስ+ ነው።

15 ይሖዋ አምላክ ሰውየውን ወስዶ እንዲያለማውና እንዲንከባከበው በኤደን የአትክልት ስፍራ አስቀመጠው።+ 16 በተጨማሪም ይሖዋ አምላክ ለሰውየው ይህን ትእዛዝ ሰጠው፦ “በአትክልቱ ስፍራ ውስጥ ከሚገኘው ዛፍ ሁሉ እስክትረካ ድረስ መብላት ትችላለህ።+ 17 ከመልካምና ክፉ እውቀት ዛፍ ግን አትብላ፤ ምክንያቱም ከዚህ ዛፍ በበላህ ቀን በእርግጥ ትሞታለህ።”+

18 ከዚያም ይሖዋ አምላክ “ሰውየው ብቻውን መሆኑ መልካም አይደለም። ማሟያ የምትሆነውን ረዳት እሠራለታለሁ”+ አለ። 19 ይሖዋ አምላክም እያንዳንዱን የዱር እንስሳ እንዲሁም በሰማያት ላይ የሚበረውን እያንዳንዱን ፍጥረት ከአፈር ሠርቶ ነበር፤ ከዚያም ሰውየው እያንዳንዳቸውን ምን ብሎ እንደሚጠራቸው ለማየት ሁሉንም ወደ እሱ አመጣቸው፤ ሰውየው ለእያንዳንዱ ሕያው ፍጡር* የሰጠው መጠሪያም የዚያ ፍጡር ስም ሆነ።+ 20 በመሆኑም ሰውየው ለቤት እንስሳት በሙሉ፣ በሰማያት ላይ ለሚበርሩ ፍጥረታት እንዲሁም ለዱር እንስሳት ሁሉ ስም አወጣላቸው፤ ለሰው ግን ማሟያ የሚሆን ረዳት አልነበረውም። 21 ስለሆነም ይሖዋ አምላክ በሰውየው ላይ ከባድ እንቅልፍ ጣለበት፤ እንቅልፍ ወስዶት ሳለም ከጎድን አጥንቶቹ አንዷን ወሰደ፤ ቦታውንም በሥጋ ደፈነው። 22 ይሖዋ አምላክም ከሰውየው የወሰዳትን የጎድን አጥንት ሴት አድርጎ ሠራት፤ ሴቲቱንም ወደ ሰውየው አመጣት።+

23 በዚህ ጊዜ ሰውየው እንዲህ አለ፦

“እንግዲህ እሷ የአጥንቶቼ አጥንት፣

የሥጋዬም ሥጋ ናት።

እሷ ከወንድ ስለተገኘች+

‘ሴት’ ትባላለች።”

24 በዚህም ምክንያት ሰው ከአባቱና ከእናቱ ይለያል፤ ከሚስቱም ጋር ይጣበቃል።* ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ።+ 25 ሰውየውም ሆነ ሚስቱ ራቁታቸውን ነበሩ፤+ እንደዚያም ሆኖ ኀፍረት አይሰማቸውም ነበር።

3 እባብም+ ይሖዋ አምላክ ከሠራቸው የዱር እንስሳት ሁሉ እጅግ ጠንቃቃ* ነበር። በመሆኑም ሴቲቱን “በእርግጥ አምላክ ‘በአትክልቱ ስፍራ ካለው ከማንኛውም ዛፍ አትብሉ’ ብሏችኋል?”+ ሲል ጠየቃት። 2 በዚህ ጊዜ ሴቲቱ እባቡን እንዲህ አለችው፦ “በአትክልቱ ስፍራ ካሉት ዛፎች ፍሬ መብላት እንችላለን።+ 3 ይሁንና በአትክልቱ ስፍራ መካከል የሚገኘውን ዛፍ+ ፍሬ በተመለከተ አምላክ ‘ከእሱ አትብሉ፤ ፈጽሞም አትንኩት፤ አለዚያ ትሞታላችሁ’ ብሏል።” 4 በዚህ ጊዜ እባቡ ሴቲቱን እንዲህ አላት፦ “መሞት እንኳ ፈጽሞ አትሞቱም።+ 5 አምላክ ከዛፉ በበላችሁ ቀን ዓይኖቻችሁ እንደሚገለጡና መልካምና ክፉን በማወቅ ረገድ እንደ አምላክ እንደምትሆኑ+ ስለሚያውቅ ነው።”

6 በዚህም የተነሳ ሴቲቱ ዛፉ ለመብል መልካም፣ ሲያዩትም የሚያጓጓ እንደሆነ ተመለከተች፤ ዛፉ ለዓይን የሚማርክ ነበር። ስለሆነም ከዛፉ ፍሬ ወስዳ በላች።+ ባሏም አብሯት ሲሆን ለእሱም ሰጠችው፤ እሱም በላ።+ 7 ከዚያም የሁለቱም ዓይኖች ተገለጡ፤ ራቁታቸውን መሆናቸውንም አስተዋሉ። በመሆኑም የበለስ ቅጠል በመስፋት የሚያሸርጡት ነገር ለራሳቸው ሠሩ።+

8 በኋላም ሰውየውና ሚስቱ ቀኑ ነፋሻማ በሆነበት ጊዜ ላይ ይሖዋ አምላክ በአትክልቱ ስፍራ ውስጥ ሲሄድ ድምፁን ሰሙ፤ እነሱም በአትክልቱ ስፍራ ባሉት ዛፎች መካከል በመግባት ከይሖዋ አምላክ ፊት ተደበቁ። 9 ይሖዋ አምላክም ሰውየውን በተደጋጋሚ በመጣራት “የት ነህ?” አለው። 10 በመጨረሻም ሰውየው “በአትክልቱ ስፍራ ድምፅህን ሰማሁ፤ ሆኖም ራቁቴን ስለነበርኩ ፈራሁ፤ ስለሆነም ተደበቅኩ” አለ። 11 እሱም “ራቁትህን+ እንደሆንክ ማን ነገረህ? እንዳትበላ ብዬ ካዘዝኩህ ዛፍ+ በላህ?” አለው። 12 ሰውየውም “ከእኔ ጋር እንድትሆን የሰጠኸኝ ይህች ሴት ከዛፉ ፍሬ ሰጠችኝና በላሁ” አለ። 13 ከዚያም ይሖዋ አምላክ ሴቲቱን “ለመሆኑ ይህ ያደረግሽው ነገር ምንድን ነው?” አላት። ሴቲቱም “እባቡ አታለለኝና በላሁ”+ ስትል መለሰች።

14 ከዚያም ይሖዋ አምላክ እባቡን+ እንዲህ አለው፦ “ይህን ስላደረግክ ከቤት እንስሳት ሁሉ እንዲሁም ከዱር እንስሳት ሁሉ የተረገምክ ትሆናለህ። በሕይወትህ ዘመን ሁሉ በሆድህ እየተሳብክ ትሄዳለህ፤ እንዲሁም አፈር ትበላለህ። 15 በአንተና+ በሴቲቱ+ መካከል እንዲሁም በዘርህና+ በዘሯ+ መካከል ጠላትነት+ እንዲኖር አደርጋለሁ፤ እሱ ራስህን ይጨፈልቃል፤*+ አንተም ተረከዙን ታቆስላለህ።”*+

16 ሴቲቱንም እንዲህ አላት፦ “በእርግዝናሽ ወቅት የሚሰማሽን ሕመም በእጅጉ አበዛለሁ፤ ልጆች የምትወልጂውም በሥቃይ ይሆናል፤ ምኞትሽ ሁሉ ባልሽ ይሆናል፤ እሱ ደግሞ ይገዛሻል።”

17 አዳምንም* እንዲህ አለው፦ “የሚስትህን ቃል ስለሰማህና ‘ከእሱ አትብላ’ ብዬ ካዘዝኩህ ዛፍ+ ወስደህ ስለበላህ በአንተ የተነሳ ምድር የተረገመች ትሁን።+ በሕይወትህ ዘመን ሁሉ የምድርን ፍሬ በሥቃይ ትበላለህ።+ 18 ምድርም እሾህና አሜኬላ ታበቅልብሃለች፤ አንተም በሜዳ ላይ የሚበቅለውን ተክል ትበላለህ። 19 ከመሬት ስለተገኘህ+ ወደ መሬት እስክትመለስ ድረስ ላብህን እያንጠፈጠፍክ ምግብ ትበላለህ። አፈር ስለሆንክ ወደ አፈር ትመለሳለህ።”+

20 ከዚህ በኋላ አዳም ሚስቱን ሔዋን* ብሎ ጠራት፤ ምክንያቱም እሷ የሕያዋን ሁሉ እናት ትሆናለች።+ 21 ይሖዋ አምላክም ረጅም ልብስ ከቆዳ ሠርቶ አዳምንና ሚስቱን አለበሳቸው።+ 22 ከዚያም ይሖዋ አምላክ እንዲህ አለ፦ “እንግዲህ ሰውየው መልካምና ክፉን በማወቅ ረገድ ከእኛ እንደ አንዱ ሆኗል።+ አሁን ደግሞ እጁን በመዘርጋት ከሕይወት ዛፍ+ ፍሬ ወስዶ እንዳይበላና ለዘላለም እንዳይኖር . . .” 23 ይህን ካለ በኋላም የተገኘበትን መሬት እንዲያርስ፣+ ይሖዋ አምላክ አዳምን ከኤደን የአትክልት ስፍራ+ አባረረው። 24 ሰውየውንም አስወጣው፤ ወደ ሕይወት ዛፍ የሚወስደውንም መንገድ ለመጠበቅ በኤደን የአትክልት ስፍራ በስተ ምሥራቅ በኩል ኪሩቤልና+ ያለማቋረጥ የሚሽከረከር የነበልባል ሰይፍ አስቀመጠ።

4 አዳምም ከሚስቱ ከሔዋን ጋር የፆታ ግንኙነት ፈጸመ፤ እሷም ፀነሰች።+ ቃየንንም+ በወለደች ጊዜ “በይሖዋ እርዳታ ወንድ ልጅ አፈራሁ”* አለች። 2 በኋላም ወንድሙን አቤልን+ ወለደች።

አቤል የበግ እረኛ ሆነ፤ ቃየን ግን አራሽ ሆነ። 3 ከጊዜ በኋላም ቃየን የተወሰኑ የምድር ፍሬዎችን ለይሖዋ መባ አድርጎ አቀረበ። 4 አቤል ግን ከመንጋው በኩራት+ መካከል የተወሰኑትን ከነስባቸው አቀረበ። ይሖዋ አቤልንና ያቀረበውን መባ+ በጥሩ ፊት ሲመለከት 5 ቃየንንና ያቀረበውን መባ ግን በጥሩ ፊት አልተመለከተም። በመሆኑም ቃየን በጣም ተናደደ፤ እጅግ አዘነ። 6 ከዚያም ይሖዋ ቃየንን እንዲህ አለው፦ “ለምን ተናደድክ? ለምንስ አዘንክ? 7 መልካም ወደ ማድረግ ብታዘነብል ኖሮ ሞገስ አታገኝም ነበር?* መልካም ወደ ማድረግ ካላዘነበልክ ግን ኃጢአት በደጅህ እያደባ ነው፤ ሊቆጣጠርህም ይፈልጋል፤ ታዲያ አንተ ትቆጣጠረው ይሆን?”

8 ከዚያ በኋላ ቃየን ወንድሙን አቤልን “ና ወደ ሜዳ እንሂድ” አለው። በሜዳው ላይ ሳሉም ቃየን ወንድሙን አቤልን ደብድቦ ገደለው።+ 9 በኋላም ይሖዋ ቃየንን “ወንድምህ አቤል የት ነው?” አለው፤ እሱም “እኔ አላውቅም። እኔ የወንድሜ ጠባቂ ነኝ?” አለ። 10 በዚህ ጊዜ እንዲህ አለው፦ “ያደረግከው ነገር ምንድን ነው? ስማ! የወንድምህ ደም ከምድር ወደ እኔ እየጮኸ ነው።+ 11 እንግዲህ የወንድምህን ደም ከእጅህ ለመቀበል+ አፏን ከከፈተችው ምድር እንድትሰደድ ተረግመሃል። 12 ምድርን በምታርስበትም ጊዜ ምርቷን* አትሰጥህም። በምድር ላይ ተንከራታችና ስደተኛ ትሆናለህ።” 13 በዚህ ጊዜ ቃየን ይሖዋን እንዲህ አለው፦ “ለሠራሁት ጥፋት የምቀበለው ቅጣት ልሸከመው ከምችለው በላይ ነው። 14 ይኸው በዚህ ቀን ከምድሪቱ* ልታባርረኝ ነው፤ ከፊትህም እሰወራለሁ፤ እንዲሁም በምድር ላይ ተንከራታችና ስደተኛ እሆናለሁ፤ እንግዲህ በቃ፣ ያገኘኝ ሁሉ ይገድለኛል።” 15 ስለሆነም ይሖዋ “እንግዲያው ቃየንን የሚገድል ማንኛውም ሰው ሰባት እጥፍ የበቀል ቅጣት ይቀበላል” አለው።

በመሆኑም ያገኘው ማንም እንዳይገድለው ይሖዋ ለቃየን ምልክት አደረገለት።* 16 ከዚያም ቃየን ከይሖዋ ፊት ርቆ ሄደ፤ ከኤደን በስተ ምሥራቅ+ በሚገኘው በግዞት ምድር* መኖር ጀመረ።

17 ከዚህ በኋላ ቃየን ከሚስቱ+ ጋር የፆታ ግንኙነት ፈጸመ፤ እሷም ፀነሰች፤ ሄኖክንም ወለደች። ከዚያም ቃየን ከተማ መገንባት ጀመረ፤ ከተማዋንም በልጁ በሄኖክ ስም ሰየማት። 18 ከጊዜ በኋላም ሄኖክ ኢራድን ወለደ። ኢራድም መሁያኤልን ወለደ፤ መሁያኤልም መቱሻኤልን ወለደ፤ መቱሻኤል ደግሞ ላሜህን ወለደ።

19 ላሜህም ሁለት ሚስቶች አገባ፤ የመጀመሪያዋ ስም አዳ ሲሆን የሁለተኛዋ ስም ደግሞ ጺላ ነበር። 20 አዳ ያባልን ወለደች። ያባል በድንኳን የሚኖሩና ከብት የሚያረቡ ሰዎች አባት ነበር። 21 የወንድሙ ስም ዩባል ነበር። እሱም የበገና ደርዳሪዎችና የእምቢልታ* ነፊዎች አባት ነበር። 22 ጺላ ደግሞ ቱባልቃይንን ወለደች፤ እሱም መዳብና ብረት እየቀጠቀጠ የተለያዩ መሣሪያዎችን ይሠራ ነበር። የቱባልቃይን እህት ናዕማ ትባል ነበር። 23 ከዚያም ላሜህ ለሚስቶቹ ለአዳና ለጺላ የሚከተለውን ተቀኘ፦

“እናንተ የላሜህ ሚስቶች፣ ቃሌን ስሙ፤

የምላችሁንም አዳምጡ፦

አንድ ሰው ስላቆሰለኝ፣

አዎ፣ አንድ ወጣት ስለመታኝ ገደልኩት።

24 ቃየንን የሚገድል 7 እጥፍ የበቀል ቅጣት+ የሚደርስበት ከሆነ

ላሜህን የገደለማ 77 ጊዜ የበቀል ቅጣት ይደርስበታል።”

25 አዳም ከሚስቱ ጋር በድጋሚ የፆታ ግንኙነት ፈጸመ፤ እሷም ወንድ ልጅ ወለደች። ስሙንም “ቃየን አቤልን ስለገደለው+ በእሱ ፋንታ አምላክ ሌላ ዘር ተክቶልኛል” በማለት ሴት*+ አለችው። 26 ሴት ደግሞ ወንድ ልጅ ወለደ፤ ስሙንም ሄኖስ+ አለው። በዚያን ዘመን ሰዎች የይሖዋን ስም መጥራት ጀመሩ።*

5 የአዳምን ታሪክ የያዘው መጽሐፍ ይህ ነው። አምላክ አዳምን በፈጠረበት ቀን፣ በአምላክ አምሳል ሠራው።+ 2 ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው።+ በተፈጠሩበትም+ ቀን ባረካቸው፤ እንዲሁም ሰው* ብሎ ጠራቸው።

3 አዳም 130 ዓመት ኖረ፤ ከዚያም እሱን የሚመስል ወንድ ልጅ በራሱ አምሳያ ወለደ፤ ስሙንም ሴት+ አለው። 4 አዳም ሴትን ከወለደ በኋላ 800 ዓመት ኖረ። ወንዶችና ሴቶች ልጆችንም ወለደ። 5 ስለዚህ አዳም በአጠቃላይ 930 ዓመት ኖረ፤ ከዚያም ሞተ።+

6 ሴት 105 ዓመት ኖረ፤ ከዚያም ሄኖስን+ ወለደ። 7 ሴትም ሄኖስን ከወለደ በኋላ 807 ዓመት ኖረ። ወንዶችና ሴቶች ልጆችንም ወለደ። 8 ስለዚህ ሴት በአጠቃላይ 912 ዓመት ኖረ፤ ከዚያም ሞተ።

9 ሄኖስ 90 ዓመት ኖረ፤ ከዚያም ቃይናንን ወለደ። 10 ሄኖስም ቃይናንን ከወለደ በኋላ 815 ዓመት ኖረ። ወንዶችና ሴቶች ልጆችንም ወለደ። 11 ስለዚህ ሄኖስ በአጠቃላይ 905 ዓመት ኖረ፤ ከዚያም ሞተ።

12 ቃይናን 70 ዓመት ኖረ፤ ከዚያም መላልኤልን+ ወለደ። 13 ቃይናንም መላልኤልን ከወለደ በኋላ 840 ዓመት ኖረ። ወንዶችና ሴቶች ልጆችንም ወለደ። 14 ስለዚህ ቃይናን በአጠቃላይ 910 ዓመት ኖረ፤ ከዚያም ሞተ።

15 መላልኤል 65 ዓመት ኖረ፤ ከዚያም ያሬድን+ ወለደ። 16 መላልኤልም ያሬድን ከወለደ በኋላ 830 ዓመት ኖረ። ወንዶችና ሴቶች ልጆችንም ወለደ። 17 ስለዚህ መላልኤል በአጠቃላይ 895 ዓመት ኖረ፤ ከዚያም ሞተ።

18 ያሬድ 162 ዓመት ኖረ፤ ከዚያም ሄኖክን+ ወለደ። 19 ያሬድም ሄኖክን ከወለደ በኋላ 800 ዓመት ኖረ። ወንዶችና ሴቶች ልጆችንም ወለደ። 20 ስለዚህ ያሬድ በአጠቃላይ 962 ዓመት ኖረ፤ ከዚያም ሞተ።

21 ሄኖክ 65 ዓመት ኖረ፤ ከዚያም ማቱሳላን+ ወለደ። 22 ሄኖክ ማቱሳላን ከወለደ በኋላ ለ300 ዓመት ከእውነተኛው አምላክ* ጋር መሄዱን ቀጠለ። ወንዶችና ሴቶች ልጆችንም ወለደ። 23 ስለዚህ ሄኖክ በአጠቃላይ 365 ዓመት ኖረ። 24 ሄኖክ ከእውነተኛው አምላክ ጋር መሄዱን ቀጠለ።+ አምላክ ስለወሰደውም ከዚያ በኋላ አልተገኘም።+

25 ማቱሳላ 187 ዓመት ኖረ፤ ከዚያም ላሜህን+ ወለደ። 26 ማቱሳላም ላሜህን ከወለደ በኋላ 782 ዓመት ኖረ። ወንዶችና ሴቶች ልጆችንም ወለደ። 27 ስለዚህ ማቱሳላ በአጠቃላይ 969 ዓመት ኖረ፤ ከዚያም ሞተ።

28 ላሜህ 182 ዓመት ኖረ፤ ከዚያም ወንድ ልጅ ወለደ። 29 እሱም “ይህ ልጅ፣ ይሖዋ በረገማት ምድር+ የተነሳ ከምንለፋው ልፋትና ከምንደክመው ድካም በማሳረፍ ያጽናናናል”* በማለት ስሙን ኖኅ*+ ብሎ ጠራው። 30 ላሜህም ኖኅን ከወለደ በኋላ 595 ዓመት ኖረ። ወንዶችና ሴቶች ልጆችንም ወለደ። 31 ስለዚህ ላሜህ በአጠቃላይ 777 ዓመት ኖረ፤ ከዚያም ሞተ።

32 ኖኅ 500 ዓመት ከሆነው በኋላ ሴምን፣+ ካምንና+ ያፌትን+ ወለደ።

6 ሰዎች በምድር ላይ ቁጥራቸው እየጨመረ ሲሄድ ሴቶች ልጆችን ወለዱ፤ 2 የእውነተኛው አምላክ ልጆችም*+ የሰዎች ሴቶች ልጆች ውብ እንደሆኑ አስተዋሉ። በመሆኑም የመረጧቸውን ሁሉ ለራሳቸው ሚስቶች አድርገው ወሰዱ። 3 ከዚያም ይሖዋ “ሰው ሥጋ ስለሆነ* መንፈሴ ሰውን ለዘላለም አይታገሥም።+ በመሆኑም ዘመኑ 120 ዓመት ይሆናል”+ አለ።

4 በዚያ ዘመንም ሆነ ከዚያ በኋላ ኔፍሊም* በምድር ላይ ነበሩ። በዚያ ጊዜም የእውነተኛው አምላክ ልጆች ከሰዎች ሴቶች ልጆች ጋር ግንኙነት ፈጸሙ፤ ሴቶቹም ወንዶች ልጆችን ወለዱላቸው። እነሱም በጥንት ዘመን በኃያልነታቸው ዝና ያተረፉ ሰዎች ነበሩ።

5 በዚህም የተነሳ ይሖዋ የሰው ልጅ ክፋት በምድር ላይ እንደበዛና የልቡም ሐሳብ ሁሉ ምንጊዜም ወደ መጥፎ ብቻ ያዘነበለ+ እንደሆነ ተመለከተ። 6 ይሖዋም ሰዎችን በምድር ላይ በመፍጠሩ ተጸጸተ፤* ልቡም አዘነ።+ 7 በመሆኑም ይሖዋ እንዲህ አለ፦ “የፈጠርኳቸውን ሰዎች ከምድር ገጽ ጠራርጌ አጠፋለሁ፤ ሰውን ጨምሮ የቤት እንስሳትን እንዲሁም መሬት ለመሬት የሚሄዱ እንስሳትንና በሰማያት ላይ የሚበርሩ ፍጥረታትን አጠፋለሁ፤ ምክንያቱም እነሱን በመፍጠሬ ተጸጽቻለሁ።” 8 ኖኅ ግን በይሖዋ ፊት ሞገስ አገኘ።

9 የኖኅ ታሪክ ይህ ነው።

ኖኅ ጻድቅ ሰው ነበር።+ በዘመኑ* ከነበሩት ሰዎች መካከል እሱ እንከን* የሌለበት ሰው ነበር። ኖኅ ከእውነተኛው አምላክ ጋር ይሄድ ነበር።+ 10 ኖኅ ከጊዜ በኋላ ሴም፣ ካምና ያፌት+ የተባሉ ሦስት ወንዶች ልጆች ወለደ። 11 ይሁንና ምድር በእውነተኛው አምላክ ፊት ተበላሽታ ነበር፤ እንዲሁም በዓመፅ ተሞልታ ነበር። 12 አዎ፣ አምላክ ምድርን ተመለከተ፤ ምድርም ተበላሽታ ነበር፤+ ሰው* ሁሉ በምድር ላይ መንገዱን አበላሽቶ ነበር።+

13 ከዚህ በኋላ አምላክ ኖኅን እንዲህ አለው፦ “በእነሱ የተነሳ ምድር በዓመፅ ስለተሞላች ሥጋን ሁሉ ለማጥፋት ወስኛለሁ፤ ስለሆነም እነሱን ከምድር ጋር አጠፋቸዋለሁ።+ 14 አንተ ከጎፈር እንጨት ለራስህ መርከብ* ሥራ።+ በመርከቡም ውስጥ የተለያዩ ክፍሎችን ሥራ፤ እንዲሁም መርከቡን ከውስጥም ሆነ ከውጭ ቅጥራን*+ ለቅልቀው። 15 መርከቡንም የምትሠራው እንደሚከተለው ነው፦ የመርከቡ ርዝመት 300 ክንድ፣* ወርዱ 50 ክንድ እንዲሁም ከፍታው 30 ክንድ ይሁን። 16 በመርከቡም ላይ ከጣሪያው ሥር አንድ ክንድ ቁመት ያለው ብርሃን ማስገቢያ የሚሆን መስኮት* ሥራ፤ የመርከቡንም በር በጎኑ በኩል አድርግ፤+ መርከቡም ምድር ቤት እንዲሁም አንደኛና ሁለተኛ ፎቅ ይኑረው።

17 “እኔ ደግሞ ከሰማያት በታች የሕይወት እስትንፋስ* ያለውን ሥጋ ሁሉ ለማጥፋት በምድር ላይ የጥፋት ውኃ+ አመጣለሁ። በምድር ላይ ያለ ነገር ሁሉ ይጠፋል።+ 18 እኔም ከአንተ ጋር ቃል ኪዳኔን እመሠርታለሁ፤ አንተም ወደ መርከቡ መግባት አለብህ፤ አንተ፣ ከአንተም ጋር ወንዶች ልጆችህ፣ ሚስትህና የልጆችህ ሚስቶች ወደ መርከቡ መግባት ይኖርባችኋል።+ 19 ከአንተ ጋር በሕይወት እንዲተርፉ ከሁሉም ዓይነት ሕያው ፍጡር+ ተባዕትና እንስት እያደረግክ ሁለት ሁለት ወደ መርከቡ አስገባ፤+ 20 በሕይወት እንዲተርፉ የሚበርሩ ፍጥረታት እንደየወገናቸው፣ የቤት እንስሳት እንደየወገናቸው እንዲሁም በምድር ላይ ያሉ መሬት ለመሬት የሚሄዱ እንስሳት ሁሉ እንደየወገናቸው ሁለት ሁለት እየሆኑ ከአንተ ጋር ይግቡ።+ 21 ለአንተም ሆነ ለእንስሳቱ ምግብ እንዲሆን ማንኛውንም ዓይነት ምግብ+ ሰብስበህ ይዘህ ትገባለህ።”

22 ኖኅም አምላክ ያዘዘውን ሁሉ በተባለው መሠረት አከናወነ። ልክ እንደዚሁ አደረገ።+

7 ከዚህ በኋላ ይሖዋ ኖኅን እንዲህ አለው፦ “በዚህ ትውልድ መካከል በፊቴ ጻድቅ ሆነህ ያገኘሁህ አንተን ስለሆነ+ አንተም ሆንክ መላው ቤተሰብህ ወደ መርከቡ ግቡ። 2 ከአንተም ጋር ንጹሕ ከሆነው ከእያንዳንዱ እንስሳ ሰባት ሰባት* ትወስዳለህ፤+ ተባዕትና እንስት ይሁኑ፤ ንጹሕ ካልሆነው ከእያንዳንዱ እንስሳ ደግሞ ሁለት ሁለት ውሰድ፤ ተባዕትና እንስት ይሁኑ፤ 3 በተጨማሪም በመላው ምድር ላይ ዘራቸው እንዲተርፍ+ በሰማይ ላይ ከሚበርሩ ፍጥረታት ሰባት ሰባት* አስገባ፤ ተባዕትና እንስት ይሁኑ። 4 ከሰባት ቀን በኋላ በምድር ላይ 40 ቀንና 40 ሌሊት+ ዝናብ አዘንባለሁ፤+ የሠራሁትንም ሕይወት ያለው ነገር ሁሉ ከምድር ገጽ ጠራርጌ አጠፋለሁ።”+ 5 ኖኅም ይሖዋ ያዘዘውን ሁሉ አደረገ።

6 የጥፋት ውኃው በምድር ላይ በወረደበት ወቅት ኖኅ 600 ዓመቱ ነበር።+ 7 ኖኅም የጥፋት ውኃው ከመጀመሩ በፊት ከወንዶች ልጆቹ፣ ከሚስቱና ከልጆቹ ሚስቶች ጋር በመሆን ወደ መርከቡ ገባ።+ 8 እያንዳንዱ ንጹሕ እንስሳ፣ እያንዳንዱ ንጹሕ ያልሆነ እንስሳ እንዲሁም የሚበርሩ ፍጥረታትና በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱ ነገሮች ሁሉ+ 9 አምላክ ኖኅን ባዘዘው መሠረት ተባዕትና እንስት በመሆን ጥንድ ጥንድ እየሆኑ ኖኅ ወዳለበት ወደ መርከቡ ገቡ። 10 ከሰባት ቀን በኋላም የጥፋት ውኃው በምድር ላይ ወረደ።

11 ኖኅ በተወለደ በ600ኛው ዓመት፣ በሁለተኛው ወር ከወሩም በ17ኛው ቀን፣ በዚያ ቀን፣ ተንጣሎ የሚገኘው ጥልቅ ውኃ ምንጮች ሁሉ ተነደሉ፤ የሰማያት የውኃ በሮችም ተከፈቱ።+ 12 ዝናቡም ለ40 ቀንና ለ40 ሌሊት በምድር ላይ ወረደ። 13 በዚያው ቀን ኖኅ ከወንዶች ልጆቹ ከሴም፣ ከካምና ከያፌት+ እንዲሁም ከሚስቱና ከሦስቱ የልጆቹ ሚስቶች ጋር ወደ መርከቡ ገባ።+ 14 ከእነሱም ጋር እያንዳንዱ የዱር እንስሳ እንደየወገኑ፣ እያንዳንዱ የቤት እንስሳ እንደየወገኑ፣ በምድር ላይ ያለ መሬት ለመሬት የሚሄድ እያንዳንዱ እንስሳ እንደየወገኑ፣ እያንዳንዱ የሚበር ፍጥረት እንደየወገኑ እንዲሁም እያንዳንዱ ወፍና እያንዳንዱ ክንፍ ያለው ፍጡር ወደ መርከቡ ገባ። 15 የሕይወት እስትንፋስ* ያለው ሁሉም ዓይነት ሕያው ፍጡር ሁለት ሁለት ሆኖ ወደ ኖኅ በመምጣት መርከቡ ውስጥ ይገባ ጀመር። 16 በመሆኑም አምላክ ኖኅን ባዘዘው መሠረት ሁሉም ዓይነት ሕያው ፍጡር ተባዕትና እንስት እየሆነ ወደ መርከቡ ገባ። ከዚያም ይሖዋ ከኋላው በሩን ዘጋበት።

17 የጥፋት ውኃው ለ40 ቀን በምድር ላይ ያለማቋረጥ ወረደ። ውኃው እየጨመረ ሲሄድ መርከቡን ወደ ላይ አነሳው፤ መርከቡም መሬቱን ለቆ መንሳፈፍ ጀመረ። 18 ውኃው በምድር ላይ እያየለና በእጅጉ እየጨመረ ሄደ፤ መርከቡ ግን በውኃው ላይ መንሳፈፉን ቀጠለ። 19 ውኃው በምድር ላይ በጣም እያየለ ከመሄዱ የተነሳ ከሰማይ በታች ያሉ ረጃጅም ተራሮች በሙሉ ተሸፈኑ።+ 20 ውኃው ከተራሮቹ በላይ 15 ክንድ* ያህል ከፍ አለ።

21 በመሆኑም በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱ ሕያዋን ፍጥረታት በሙሉ* ይኸውም የሚበርሩ ፍጥረታት፣ የቤት እንስሳት፣ የዱር እንስሳት፣ የሚርመሰመሱ ፍጥረታትና ሰዎች በሙሉ+ ጠፉ።+ 22 በአፍንጫው የሕይወት እስትንፋስ*+ የነበረው በየብስ ላይ የሚኖር ፍጡር ሁሉ ሞተ። 23 እሱም ሰውን፣ እንስሳትን፣ መሬት ለመሬት የሚሄዱ እንስሳትንና በሰማይ ላይ የሚበርሩ ፍጥረታትን ጨምሮ ሕይወት ያለውን ነገር ሁሉ ከምድር ገጽ ጠራርጎ አጠፋ። ሁሉም ከምድር ላይ ተጠራርገው ጠፉ፤+ ከጥፋቱ የተረፉት ኖኅና ከእሱ ጋር በመርከቡ ውስጥ የነበሩት ብቻ ናቸው።+ 24 ውኃውም በምድር ላይ እንዳየለ ለ150 ቀናት ቆየ።+

8 ሆኖም አምላክ ኖኅን እንዲሁም ከእሱ ጋር በመርከቡ ውስጥ የነበሩትን የዱር እንስሳትና የቤት እንስሳት ሁሉ አሰበ።+ አምላክም ነፋስ በምድር ላይ እንዲነፍስ አደረገ፤ ውኃውም መጉደል ጀመረ። 2 የጥልቁ ውኃ ምንጮችና የሰማያት የውኃ በሮች ተደፈኑ፤ በመሆኑም ከሰማያት የሚወርደው ዝናብ መዝነቡን አቆመ።*+ 3 ከዚያም ውኃው ቀስ በቀስ ከምድር ላይ እየቀነሰ ሄደ። ከ150 ቀናት በኋላም ውኃው ጎደለ። 4 በሰባተኛው ወር፣ ከወሩም በ17ኛው ቀን መርከቡ በአራራት ተራሮች ላይ አረፈ። 5 ውኃውም እስከ አሥረኛው ወር ድረስ ቀስ በቀስ እየቀነሰ ሄደ። በአሥረኛው ወር፣ ከወሩም በመጀመሪያው ቀን የተራሮቹ አናት ታየ።+

6 ከ40 ቀንም በኋላ ኖኅ የሠራውን የመርከቡን መስኮት+ ከፍቶ 7 አንድ ቁራ ወደ ውጭ ላከ፤ ቁራው ከመርከቡ ውጭ ሲበር ይቆይና ተመልሶ ይመጣ ነበር፤ ውኃው ከምድር ላይ እስኪደርቅ ድረስ እንዲሁ ያደርግ ነበር።

8 በኋላም ውኃው ከምድር ላይ መጉደሉን ለማረጋገጥ አንዲት ርግብ ላከ። 9 ርግቧ ምንም የምታርፍበት* ቦታ ስላላገኘች እሱ ወደነበረበት መርከብ ተመልሳ መጣች፤ ምክንያቱም ውኃው ገና መላውን ምድር እንደሸፈነው ነበር።+ በመሆኑም እጁን ወደ ውጭ ዘርግቶ ተቀበላትና ወደ መርከቡ አስገባት። 10 ከዚያም ሌላ ሰባት ቀን ከጠበቀ በኋላ ርግቧን በድጋሚ ከመርከቡ አውጥቶ ለቀቃት። 11 ርግቧም አመሻሹ ላይ ወደ እሱ በመጣች ጊዜ አዲስ የተቀጠፈ ለምለም የወይራ ቅጠል በአፏ እንደያዘች አየ! ስለዚህ ኖኅ ውኃው ከምድር ላይ መጉደሉን+ አወቀ። 12 እንደገና ሌላ ሰባት ቀን ጠበቀ። ከዚያም ርግቧን አውጥቶ ለቀቃት፤ በዚህ ጊዜ ግን ርግቧ ወደ እሱ ተመልሳ አልመጣችም።

13 ኖኅ በተወለደ በ601ኛው ዓመት፣+ በመጀመሪያው ወር፣ ከወሩም በመጀመሪያው ቀን ውኃው ከመሬቱ ላይ ሸሸ፤ ኖኅም የመርከቡን ሽፋን አንስቶ ተመለከተ፤ በዚህ ጊዜ መሬቱ ደርቆ ነበር። 14 በሁለተኛው ወር፣ ከወሩም በ27ኛው ቀን ምድሪቱ ሙሉ በሙሉ ደረቀች።

15 ከዚያም አምላክ ኖኅን እንዲህ አለው፦ 16 “አንተ፣ ሚስትህ፣ ወንዶች ልጆችህና የልጆችህ ሚስቶች ከመርከቡ ውጡ።+ 17 በምድር ላይ እንዲዋለዱ፣ እንዲራቡና በምድር ላይ እንዲባዙ*+ አብሮህ ያለውን እያንዳንዱን ዓይነት ሕያው ፍጡር ሁሉ+ ይኸውም የሚበርሩ ፍጥረታትን፣ እንስሳትን እንዲሁም በምድር ላይ መሬት ለመሬት የሚሄዱ እንስሳትን ይዘህ ውጣ።”

18 ስለዚህ ኖኅ ከወንዶች ልጆቹ፣+ ከሚስቱና ከልጆቹ ሚስቶች ጋር አብሮ ወጣ። 19 እያንዳንዱ ሕያው ፍጡር፣ መሬት ለመሬት የሚሄድ እያንዳንዱ እንስሳና እያንዳንዱ የሚበር ፍጡር እንዲሁም በምድር ላይ የሚንቀሳቀስ ማንኛውም ነገር በወገን በወገኑ እየሆነ ከመርከቡ ወጣ።+ 20 ከዚያም ኖኅ ለይሖዋ መሠዊያ ሠራ፤+ ንጹሕ ከሆኑት እንስሳት ሁሉ እንዲሁም ንጹሕ ከሆኑት የሚበርሩ ፍጥረታት ሁሉ+ የተወሰኑትን ወስዶ በመሠዊያው ላይ የሚቃጠል መባ አቀረበ።+ 21 ይሖዋም ደስ የሚያሰኘውን* መዓዛ አሸተተ። ስለዚህ ይሖዋ በልቡ እንዲህ አለ፦ “በሰው የተነሳ ከእንግዲህ ወዲህ ፈጽሞ ምድርን አልረግምም፤+ ምክንያቱም የሰው የልብ ዝንባሌ ከልጅነቱ ጀምሮ መጥፎ ነው፤+ ደግሞም አሁን እንዳደረግኩት ሕያው ፍጡርን ሁሉ ፈጽሞ ዳግመኛ አላጠፋም።+ 22 ከአሁን ጀምሮ በምድር ላይ ዘር መዝራትና ማጨድ፣ ቅዝቃዜና ሙቀት፣ በጋና ክረምት እንዲሁም ቀንና ሌሊት ፈጽሞ አይቋረጡም።”+

9 አምላክም ኖኅንና ወንዶች ልጆቹን ባረካቸው፤ እንዲህም አላቸው፦ “ብዙ ተባዙ፤ ምድርንም ሙሏት።+ 2 አስፈሪነታችሁና አስደንጋጭነታችሁ በምድር ላይ ባለ በእያንዳንዱ ሕያው ፍጡር፣ በሰማያት ላይ በሚበር በእያንዳንዱ ፍጡር እንዲሁም በመሬት ላይ በሚንቀሳቀስ ማንኛውም ፍጡርና በባሕር ውስጥ ባለ ዓሣ ሁሉ ላይ ይሁን። ይኸው ሁሉም በእጃችሁ ውስጥ* እንዲሆኑ ተሰጥተዋል።+ 3 በሕይወት የሚንቀሳቀስ እያንዳንዱ እንስሳ ምግብ ይሁናችሁ።+ የለመለመውን ተክል እንደሰጠኋችሁ ሁሉ እነዚህን በሙሉ ሰጥቻችኋለሁ።+ 4 ብቻ ሕይወቱ* ማለትም ደሙ+ በውስጡ ያለበትን ሥጋ አትብሉ።+ 5 ከዚህም በተጨማሪ ሕይወታችሁ የሆነውን ደማችሁን* የሚያፈሰውን ሁሉ ተጠያቂ አደርገዋለሁ። እያንዳንዱን ሕያው ፍጡር ተጠያቂ አደርገዋለሁ፤ እያንዳንዱንም ሰው ለወንድሙ ሕይወት ተጠያቂ አደርገዋለሁ።+ 6 አምላክ ሰውን በአምሳሉ ስለሠራው+ የሰውን ደም የሚያፈስ ማንም ሰው የእሱም ደም በሰው እጅ ይፈስሳል።+ 7 እናንተ ግን ብዙ ተባዙ፤ ቁጥራችሁም በምድር ላይ እጅግ ይጨምር፤ ደግሞም ተባዙ።”+

8 አምላክም ኖኅንና ከእሱ ጋር ያሉትን ወንዶች ልጆቹን እንዲህ አላቸው፦ 9 “እኔም አሁን፣ ከእናንተና ከእናንተ በኋላ ከሚመጡት ዘሮቻችሁ ጋር ቃል ኪዳኔን እመሠርታለሁ፤+ 10 እንዲሁም ከእናንተ ጋር ካለው ከእያንዳንዱ ሕያው ፍጡር* ማለትም ከወፎች፣ ከእንስሳት፣ አብረዋችሁ በምድር ላይ ከሚኖሩት ሕያዋን ፍጥረታት በሙሉ እንዲሁም ከመርከቡ ከወጡት ሁሉ ጋር ይኸውም በምድር ላይ ከሚገኝ ከእያንዳንዱ ሕያው ፍጡር ጋር ቃል ኪዳኔን እመሠርታለሁ።+ 11 አዎ፣ ከእንግዲህ ሥጋ* ሁሉ በጥፋት ውኃ እንደማይጠፋ እንዲሁም የጥፋት ውኃ ከእንግዲህ ወዲህ ምድርን ፈጽሞ እንደማያጠፋት ከእናንተ ጋር ቃል ኪዳኔን እመሠርታለሁ።”+

12 በተጨማሪም አምላክ እንዲህ አለ፦ “በእኔና በእናንተ እንዲሁም ከእናንተ ጋር ባለው በእያንዳንዱ ሕያው ፍጡር* መካከል ለመሠረትኩት ቃል ኪዳን ምልክቱ ይህ ነው፤ ይህም ቃል ኪዳን በመጪዎቹ ትውልዶች ሁሉ ጸንቶ ይኖራል። 13 ቀስተ ደመናዬን በደመናው ላይ አደርጋለሁ፤ ይህም በእኔና በምድር መካከል ላለው ቃል ኪዳን ምልክት ሆኖ ያገለግላል። 14 ምድርን በደመና በጋረድኩ ጊዜ ሁሉ ቀስተ ደመናው በደመናው ላይ ይታያል። 15 እኔም ከእናንተ እንዲሁም ከማንኛውም ዓይነት ሕያው ፍጡር* ሁሉ ጋር የገባሁትን ቃል ኪዳን አስታውሳለሁ፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሥጋን ሁሉ ለማጥፋት የጥፋት ውኃ ፈጽሞ አይወርድም።+ 16 ቀስተ ደመናው በደመናው ላይ ይታያል፤ እኔም እሱን በማይበት ጊዜ በአምላክና በምድር ላይ በሚኖር በማንኛውም ዓይነት ሕያው ፍጡር* መካከል ያለውን ዘላለማዊ ቃል ኪዳን አስታውሳለሁ።”

17 አምላክም “በእኔና በምድር ላይ በሚኖር ሥጋ ሁሉ መካከል ለመሠረትኩት ቃል ኪዳን ምልክቱ ይህ ነው”+ በማለት ለኖኅ በድጋሚ ነገረው።

18 ከመርከቡ የወጡት የኖኅ ወንዶች ልጆች ሴም፣ ካምና ያፌት ናቸው።+ ከጊዜ በኋላ ካም፣ ከነአንን ወለደ።+ 19 የኖኅ ወንዶች ልጆች እነዚህ ሦስቱ ነበሩ፤ የምድር ሕዝብ ሁሉ የተገኘው ከእነሱ ሲሆን በኋላም ወደተለያየ አካባቢ ተሰራጨ።+

20 ኖኅም ገበሬ ሆነ፤ የወይን እርሻም አለማ። 21 አንድ ቀን ኖኅ የወይን ጠጅ ጠጥቶ ሰከረ፤ በድንኳኑም ውስጥ ራቁቱን ሆነ። 22 የከነአን አባት ካምም የአባቱን እርቃን አየ፤ ውጭ ላሉት ሁለት ወንድሞቹም ነገራቸው። 23 ስለዚህ ሴምና ያፌት ልብስ ወስደው ትከሻቸው ላይ በማድረግ የኋሊት እየተራመዱ ገቡ። በዚህ መንገድም ፊታቸውን ወደ አባታቸው ሳያዞሩ እርቃኑን ሸፈኑ፤ በመሆኑም የአባታቸውን እርቃን አላዩም።

24 ኖኅ ከወይን ጠጅ ስካሩ ሲነቃ ታናሽ ልጁ ያደረገበትን አወቀ፤ 25 እንዲህም አለ፦

“ከነአን የተረገመ ይሁን።+

ለወንድሞቹም የባሪያ ባሪያ ይሁን።”+

26 በተጨማሪም እንዲህ አለ፦

“የሴም አምላክ ይሖዋ ይወደስ፤

ከነአንም የእሱ ባሪያ ይሁን።+

27 አምላክ ለያፌት ሰፊ መሬት ይስጠው፤

በሴም ድንኳኖች ውስጥም ይኑር።

ከነአን ለእሱም ጭምር ባሪያ ይሁን።”

28 ኖኅ ከጥፋት ውኃው በኋላ 350 ዓመት ኖረ።+ 29 በመሆኑም ኖኅ በአጠቃላይ 950 ዓመት ኖረ፤ ከዚያም ሞተ።

10 የኖኅ ወንዶች ልጆች የሆኑት የሴም፣ የካም እና የያፌት ታሪክ ይህ ነው።

ከጥፋት ውኃ በኋላ ወንዶች ልጆች ወለዱ።+ 2 የያፌት ወንዶች ልጆች ጎሜር፣+ ማጎግ፣+ ማዳይ፣ ያዋን፣ ቱባል፣+ መሼቅ+ እና ቲራስ+ ነበሩ።

3 የጎሜር ወንዶች ልጆች አሽከናዝ፣+ ሪፋት እና ቶጋርማ+ ነበሩ።

4 የያዋን ወንዶች ልጆች ኤሊሻ፣+ ተርሴስ፣+ ኪቲም+ እና ዶዳኒም ነበሩ።

5 በደሴቶች ላይ የሚኖሩ ሕዝቦች እንደየቋንቋቸውና እንደየቤተሰባቸው በየብሔራቸው በመሆን ወደየምድራቸው የተሰራጩት ከእነዚህ ነው።

6 የካም ወንዶች ልጆች ኩሽ፣ ሚጽራይም፣+ ፑጥ+ እና ከነአን+ ነበሩ።

7 የኩሽ ወንዶች ልጆች ሴባ፣+ ሃዊላ፣ ሳብታ፣ ራአማ+ እና ሳብተካ ነበሩ።

የራአማ ወንዶች ልጆች ሳባ እና ዴዳን ነበሩ።

8 ኩሽ ናምሩድን ወለደ። እሱም በምድር ላይ የመጀመሪያው ኃያል ሰው ነበር። 9 እሱም ይሖዋን የሚቃወም ኃያል አዳኝ ሆነ። በዚህም የተነሳ “እንደ ናምሩድ ያለ ይሖዋን የሚቃወም ኃያል አዳኝ” ይባል ነበር። 10 የግዛቱ መጀመሪያም* በሰናኦር+ ምድር የሚገኙት ባቤል፣+ ኤሬክ፣+ አካድ እና ካልኔ ነበሩ። 11 ከዚያ ምድር ተነስቶም ወደ አሦር+ በመሄድ ነነዌን፣+ ረሆቦትኢርን እና ካላህን ቆረቆረ፤ 12 እንዲሁም በነነዌና በካላህ መካከል የምትገኘውን ረሰንን ቆረቆረ፤ እሷም ታላቋ ከተማ ናት።*

13 ሚጽራይም ሉድን፣+ አናሚምን፣ ለሃቢምን፣ ናፊቱሂምን፣+ 14 ጳትሩሲምን፣+ ካስሉሂምን (ፍልስጤማውያን+ የተገኙት ከእሱ ነው) እንዲሁም ካፍቶሪምን+ ወለደ።

15 ከነአን የበኩር ልጁን ሲዶናን፣+ ሄትን+ 16 እንዲሁም ኢያቡሳዊውን፣+ አሞራዊውን፣+ ገርጌሻዊውን፣ 17 ሂዋዊውን፣+ አርቃዊውን፣ ሲናዊውን፣ 18 አርዋዳዊውን፣+ ጸማራዊውን እና ሃማታዊውን+ ወለደ። ከዚያ በኋላ የከነአናውያን ቤተሰቦች ተበተኑ። 19 በመሆኑም የከነአናውያን ወሰን ከሲዶና አንስቶ በጋዛ+ አቅራቢያ እስካለችው እስከ ጌራራ+ እንዲሁም እስከ ሰዶም፣ ገሞራ፣+ አድማህ እና በላሻ አቅራቢያ እስካለችው እስከ ጸቦይም+ ድረስ ያለው ነበር። 20 የካም ወንዶች ልጆች እንደየቤተሰባቸውና እንደየቋንቋቸው በየአገራቸውና በየብሔራቸው እነዚህ ነበሩ።

21 የኤቤር+ ወንዶች ልጆች ሁሉ ቅድመ አያትና የታላቅየው የያፌት ወንድም* የሆነው ሴምም ልጆች ወለደ። 22 የሴም ወንዶች ልጆች ኤላም፣+ አሹር፣+ አርፋክስድ፣+ ሉድ እና አራም+ ነበሩ።

23 የአራም ወንዶች ልጆች ዑጽ፣ ሁል፣ ጌተር እና ማሽ ነበሩ።

24 አርፋክስድ ሴሎምን+ ወለደ፤ ሴሎምም ኤቤርን ወለደ።

25 ኤቤር ሁለት ወንዶች ልጆችን ወለደ። የአንደኛው ስም ፋሌቅ*+ ነበር፤ ምክንያቱም በእሱ የሕይወት ዘመን ምድር ተከፋፍላ* ነበር። የወንድሙ ስም ደግሞ ዮቅጣን+ ነበር።

26 ዮቅጣን አልሞዳድን፣ ሸሌፍን፣ ሃጻርማዌትን፣ ያራህን፣+ 27 ሃዶራምን፣ ዑዛልን፣ ዲቅላን፣ 28 ኦባልን፣ አቢማዔልን፣ ሳባን፣ 29 ኦፊርን፣+ ሃዊላን እና ዮባብን ወለደ፤ እነዚህ ሁሉ የዮቅጣን ወንዶች ልጆች ነበሩ።

30 መኖሪያ ስፍራቸውም ከሜሻ አንስቶ እስከ ሰፋር ይኸውም እስከ ምሥራቅ ተራራማ አካባቢ ድረስ ይዘልቃል።

31 የሴም ወንዶች ልጆች እንደየቤተሰባቸውና እንደየቋንቋቸው በየአገራቸውና በየብሔራቸው እነዚህ ነበሩ።+

32 የኖኅ ወንዶች ልጆች ቤተሰቦች እንደየዘር ሐረጋቸው በየብሔራቸው እነዚህ ነበሩ። ከጥፋት ውኃው በኋላ ብሔራት ሁሉ በምድር ላይ የተሰራጩት ከእነዚህ ነበር።+

11 በዚህ ጊዜ፣ ምድር ሁሉ አንድ ቋንቋና ተመሳሳይ ቃላት ትጠቀም ነበር። 2 ወደ ምሥራቅ ሲጓዙም በሰናኦር+ ምድር ወደሚገኝ አንድ ሸለቋማ ሜዳ ደረሱ፤ በዚያም መኖር ጀመሩ። 3 እርስ በርሳቸውም “ኑ! ጡብ እንሥራ፤ በእሳትም እንተኩሰው” ይባባሉ ጀመር። በመሆኑም በድንጋይ ፋንታ ጡብ፣ ለማያያዣም ቅጥራን ተጠቀሙ። 4 ከዚያም “ኑ! በመላው ምድር ላይ እንዳንበተን+ ከተማና ጫፉ ሰማይ የሚደርስ ግንብ ለራሳችን እንገንባ፤ ስማችንንም እናስጠራ” ተባባሉ።

5 ከዚያም ይሖዋ ሰዎች የሠሩትን ከተማና ግንብ ለማየት ወረደ። 6 ይሖዋም እንዲህ አለ፦ “እነዚህ ሰዎች አንድ ቋንቋ የሚናገሩ አንድ ሕዝብ ናቸው፤+ ይኸው አሁን ደግሞ ይህን መሥራት ጀምረዋል። በዚህ ከቀጠሉ ያሰቡትን* ሁሉ ከማከናወን የሚያግዳቸው ምንም ነገር አይኖርም። 7 ና! እንውረድና*+ በቋንቋ እርስ በርስ እንዳይግባቡ ቋንቋቸውን እናዘበራርቅ።” 8 በመሆኑም ይሖዋ ከዚያ ቦታ ተነስተው በመላው ምድር ላይ እንዲበተኑ አደረገ፤+ እነሱም ቀስ በቀስ ከተማዋን መገንባታቸውን አቆሙ። 9 የከተማዋ ስም ባቤል*+ የተባለውም በዚህ የተነሳ ነው፤ ምክንያቱም ይሖዋ በዚያ የምድርን ሁሉ ቋንቋ አዘበራርቋል፤ እንዲሁም ይሖዋ ሰዎቹ ከዚያ ቦታ ተነስተው በመላው ምድር ላይ እንዲበተኑ አድርጓል።

10 የሴም+ ታሪክ ይህ ነው።

ሴም የጥፋት ውኃ ከተከሰተ ከሁለት ዓመት በኋላ አርፋክስድን+ ሲወልድ የ100 ዓመት ሰው ነበር። 11 ሴም አርፋክስድን ከወለደ በኋላ 500 ዓመት ኖረ። ወንዶችና ሴቶች ልጆችንም ወለደ።+

12 አርፋክስድ 35 ዓመት ኖረ፤ ከዚያም ሴሎምን+ ወለደ። 13 አርፋክስድ ሴሎምን ከወለደ በኋላ 403 ዓመት ኖረ። ወንዶችና ሴቶች ልጆችንም ወለደ።

14 ሴሎም 30 ዓመት ኖረ፤ ከዚያም ኤቤርን+ ወለደ። 15 ሴሎም ኤቤርን ከወለደ በኋላ 403 ዓመት ኖረ። ወንዶችና ሴቶች ልጆችንም ወለደ።

16 ኤቤር 34 ዓመት ኖረ፤ ከዚያም ፋሌቅን+ ወለደ። 17 ኤቤርም ፋሌቅን ከወለደ በኋላ 430 ዓመት ኖረ። ወንዶችና ሴቶች ልጆችንም ወለደ።

18 ፋሌቅ 30 ዓመት ኖረ፤ ከዚያም ረኡን+ ወለደ። 19 ፋሌቅ ረኡን ከወለደ በኋላ 209 ዓመት ኖረ። ወንዶችና ሴቶች ልጆችንም ወለደ።

20 ረኡ 32 ዓመት ኖረ፤ ከዚያም ሴሮህን ወለደ። 21 ረኡ ሴሮህን ከወለደ በኋላ 207 ዓመት ኖረ። ወንዶችና ሴቶች ልጆችንም ወለደ።

22 ሴሮህ 30 ዓመት ኖረ፤ ከዚያም ናኮርን ወለደ። 23 ሴሮህ ናኮርን ከወለደ በኋላ 200 ዓመት ኖረ። ወንዶችና ሴቶች ልጆችንም ወለደ።

24 ናኮር 29 ዓመት ኖረ፤ ከዚያም ታራን+ ወለደ። 25 ናኮር ታራን ከወለደ በኋላ 119 ዓመት ኖረ። ወንዶችና ሴቶች ልጆችንም ወለደ።

26 ታራ 70 ዓመት ከኖረ በኋላ አብራምን፣+ ናኮርን+ እና ካራንን ወለደ።

27 የታራ ታሪክ ይህ ነው።

ታራ አብራምን፣ ናኮርን እና ካራንን ወለደ፤ ካራን ደግሞ ሎጥን+ ወለደ። 28 ካራንም አባቱ ታራ ገና በሕይወት እያለ፣ በተወለደበት አገር በከለዳውያን+ ዑር+ ሞተ። 29 አብራምና ናኮር ሚስት አገቡ። የአብራም ሚስት ስሟ ሦራ+ ሲሆን የናኮር ሚስት ደግሞ ስሟ ሚልካ+ ነበር፤ እሷም የሚልካ እና የዪስካ አባት የሆነው የካራን ልጅ ናት። 30 በዚህ ጊዜ ሦራ መሃን ነበረች፤+ ልጅም አልነበራትም።

31 ከዚያም ታራ ልጁን አብራምንና የልጁ ልጅ የሆነውን የካራንን ልጅ ሎጥን+ እንዲሁም የልጁ የአብራም ሚስት የሆነችውን ምራቱን ሦራን ይዞ ወደ ከነአን ምድር+ ለመሄድ ከከለዳውያን ዑር ተነሳ። ከጊዜ በኋላም ወደ ካራን+ መጡ፤ በዚያም መኖር ጀመሩ። 32 ታራም 205 ዓመት ኖረ። ከዚያም በካራን ሞተ።

12 ይሖዋም አብራምን እንዲህ አለው፦ “ከአገርህ፣ ከዘመዶችህና ከአባትህ ቤት ወጥተህ እኔ ወደማሳይህ ምድር ሂድ።+ 2 አንተን ታላቅ ብሔር አደርግሃለሁ፤ እንዲሁም እባርክሃለሁ፤ ስምህንም ታላቅ አደርገዋለሁ፤ አንተም በረከት ትሆናለህ።+ 3 የሚባርኩህን እባርካለሁ፤ የሚረግምህንም እረግማለሁ፤+ የምድር ሕዝቦችም ሁሉ በአንተ አማካኝነት ይባረካሉ።”*+

4 ስለዚህ አብራም ልክ ይሖዋ በነገረው መሠረት ወጣ፤ ሎጥም አብሮት ሄደ። አብራም ከካራን በወጣበት ጊዜ ዕድሜው 75 ዓመት ነበር።+ 5 አብራም ሚስቱን ሦራን፣+ የወንድሙን ልጅ ሎጥን+ እንዲሁም ያፈሩትን ንብረት ሁሉና+ በካራን አብረዋቸው የነበሩትን ሰዎች* በሙሉ ይዞ ተነሳ፤ እነሱም ወደ ከነአን ምድር አቀኑ።+ ከነአን ምድር በደረሱም ጊዜ 6 አብራም በሞሬ ትላልቅ ዛፎች+ አቅራቢያ እስከሚገኘው ሴኬም+ እስከሚባለው አካባቢ ድረስ ወደ ምድሪቱ ዘልቆ ገባ። በዚያን ጊዜ ከነአናውያን በምድሪቱ ይኖሩ ነበር። 7 ይሖዋም ለአብራም ተገለጠለትና “ይህችን ምድር ለዘርህ+ እሰጣለሁ”+ አለው። ስለዚህ አብራም ተገልጦለት ለነበረው ለይሖዋ በዚያ መሠዊያ ሠራ። 8 በኋላም ከዚያ ተነስቶ ከቤቴል+ በስተ ምሥራቅ ወደሚገኘው ተራራማ አካባቢ ተጓዘ፤ እሱም ቤቴልን በስተ ምዕራብ፣ ጋይን+ ደግሞ በስተ ምሥራቅ አድርጎ ድንኳኑን ተከለ። በዚያም ለይሖዋ መሠዊያ ሠራ፤+ የይሖዋንም ስም ጠራ።+ 9 ከዚያ በኋላ አብራም ድንኳኑን ነቅሎ በየቦታው እየሰፈረ ወደ ኔጌብ+ ተጓዘ።

10 በምድሪቱም ላይ ረሃብ ተከሰተ፤ ረሃቡ በጣም አስከፊ ስለነበር+ አብራም ለተወሰነ ጊዜ* በግብፅ ለመኖር ወደዚያ ወረደ።+ 11 ወደ ግብፅ ለመግባት ሲቃረብም ሚስቱን ሦራን እንዲህ አላት፦ “እባክሽ ስሚኝ፤ አንቺ በጣም ውብ ሴት ነሽ።+ 12 ስለሆነም ግብፃውያን አንቺን ሲያዩ ‘ይህች ሚስቱ ናት’ ማለታቸው አይቀርም። ከዚያም እኔን ይገድሉኛል፤ አንቺን ግን ይተዉሻል። 13 በአንቺ የተነሳ መልካም እንዲሆንልኝ እባክሽ፣ እህቴ እንደሆንሽ አድርገሽ ተናገሪ፤ እንዲህ ካደረግሽ ሕይወቴ ይተርፋል።”*+

14 አብራምም ግብፅ እንደደረሰ ግብፃውያኑ ሴቲቱ እጅግ ውብ እንደሆነች ተመለከቱ። 15 የፈርዖንም መኳንንት ሴቲቱን አዩአት፤ ስለ እሷም ለፈርዖን በአድናቆት ነገሩት። በመሆኑም ሴቲቱ ወደ ፈርዖን ቤት ተወሰደች። 16 ፈርዖንም በእሷ ምክንያት አብራምን ተንከባከበው፤ በጎችን፣ ከብቶችን፣ ተባዕትና እንስት አህዮችን፣ ግመሎችን እንዲሁም ወንድና ሴት አገልጋዮችን ሰጠው።+ 17 ከዚያም ይሖዋ በአብራም ሚስት በሦራ+ የተነሳ ፈርዖንንና ቤተሰቡን በታላቅ መቅሰፍት መታ። 18 በመሆኑም ፈርዖን አብራምን ጠርቶ እንዲህ አለው፦ “ይህ ያደረግክብኝ ነገር ምንድን ነው? ሚስትህ እንደሆነች ያልነገርከኝ ለምንድን ነው? 19 ‘እህቴ ናት’+ ያልከውስ ለምንድን ነው? እኔ እኮ ወስጄ ሚስቴ ላደርጋት ነበር። በል፣ ሚስትህ ይችውልህ፤ ይዘሃት ሂድ!” 20 ስለዚህ ፈርዖን አብራምን በተመለከተ ለአገልጋዮቹ ትእዛዝ አስተላለፈ፤ እነሱም አብራምን ከሚስቱና ከንብረቱ ሁሉ ጋር አሰናበቱት።+

13 ከዚያም አብራም ሚስቱንና ያለውን ንብረት ሁሉ ይዞ ከሎጥ ጋር በመሆን ከግብፅ ወጥቶ ወደ ኔጌብ ሄደ።+ 2 አብራም በከብት፣ በብርና በወርቅ እጅግ በልጽጎ ነበር።+ 3 እሱም ከኔጌብ ተነስቶ ወደ ቤቴል በሚጓዝበት ጊዜ ድንኳኑን ተክሎበት ወደነበረው በቤቴልና በጋይ+ መካከል ወደሚገኘው ስፍራ እስኪደርስ ድረስ በየቦታው ይሰፍር ነበር፤ 4 ይህም ቀደም ሲል መሠዊያ ሠርቶበት የነበረው ስፍራ ነው። በዚያም አብራም የይሖዋን ስም ጠራ።

5 ከአብራም ጋር ይጓዝ የነበረው ሎጥም በጎች፣ ከብቶችና ድንኳኖች ነበሩት። 6 በመሆኑም ሁሉም አንድ ላይ ለመኖር ምድሪቱ አልበቃቻቸውም፤ ንብረታቸው በጣም እየበዛ ስለመጣ አብረው መኖር አልቻሉም። 7 በዚህም ምክንያት በአብራም እረኞችና በሎጥ እረኞች መካከል ጠብ ተነሳ። (በወቅቱ ከነአናውያንና ፈሪዛውያን በምድሪቱ ይኖሩ ነበር።)+ 8 ስለዚህ አብራም ሎጥን+ እንዲህ አለው፦ “እባክህ በእኔና በአንተ እንዲሁም በእኔ እረኞችና በአንተ እረኞች መካከል ምንም ዓይነት ጠብ አይኑር፤ እኛ እኮ ወንድማማቾች ነን። 9 ምድሪቱ ሁሉ በእጅህ አይደለችም? እባክህ ከእኔ ተለይ። አንተ ወደ ግራ ብትሄድ እኔ ወደ ቀኝ እሄዳለሁ፤ አንተ ወደ ቀኝ ብትሄድ ደግሞ እኔ ወደ ግራ እሄዳለሁ።” 10 ሎጥም ዓይኑን አቅንቶ መላውን የዮርዳኖስ አውራጃ እስከ ዞአር+ ድረስ ተመለከተ፤+ (ይሖዋ ሰዶምንና ገሞራን ከማጥፋቱ በፊት) አካባቢው ልክ እንደ ይሖዋ የአትክልት ስፍራ፣+ ልክ እንደ ግብፅ ምድር ውኃ የጠገበ ነበር። 11 ከዚያም ሎጥ መላውን የዮርዳኖስ አውራጃ ለራሱ መረጠ፤ ሎጥም ወደ ምሥራቅ ሄዶ ሰፈረ። በዚህ መንገድ አንዳቸው ከሌላው ተለዩ። 12 አብራም በከነአን ምድር ኖረ፤ ሎጥ ግን በአውራጃው በሚገኙ ከተሞች አቅራቢያ ኖረ።+ በመጨረሻም በሰዶም አቅራቢያ ድንኳን ተከለ። 13 የሰዶም ሰዎች በይሖዋ ፊት ከባድ ኃጢአት የሚፈጽሙ ክፉ ሰዎች ነበሩ።+

14 ሎጥ ከአብራም ከተለየ በኋላ ይሖዋ አብራምን እንዲህ አለው፦ “እባክህ ካለህበት ቦታ ሆነህ ዓይንህን አቅንተህ ወደ ሰሜን፣ ወደ ደቡብ፣ ወደ ምሥራቅና ወደ ምዕራብ ተመልከት፤ 15 ምክንያቱም የምታየውን ምድር ሁሉ ለአንተና ለዘርህ ለዘለቄታው ርስት አድርጌ እሰጣለሁ።+ 16 ዘርህን እንደ ምድር አፈር አበዛዋለሁ፤ ማንም ሰው የምድርን አፈር መቁጠር ከቻለ የአንተም ዘር ሊቆጠር ይችላል።+ 17 ተነሳ፣ ይህችን ምድር ልሰጥህ ስለሆነ በምድሪቱ ስፋትና ርዝመት ሂድ።” 18 በመሆኑም አብራም ሄደ፤ በድንኳን መኖሩንም ቀጠለ። ከጊዜ በኋላም በኬብሮን+ ወደሚገኙት የማምሬ+ ትላልቅ ዛፎች መጥቶ መኖር ጀመረ፤ በዚያም ለይሖዋ መሠዊያ ሠራ።+

14 በዚያን ጊዜ የሰናኦር+ ንጉሥ አምራፌል፣ የኤላሳር ንጉሥ አርዮክ፣ የኤላም+ ንጉሥ ኮሎዶጎምር+ እና የጎይም ንጉሥ ቲድአል 2 ከሰዶም+ ንጉሥ ከቤራ፣ ከገሞራ+ ንጉሥ ከቢርሻ፣ ከአድማህ ንጉሥ ከሺንአብ፣ ከጸቦይም+ ንጉሥ ከሸሜበር እና ከቤላ ማለትም ከዞአር ንጉሥ ጋር ጦርነት ገጠሙ። 3 እነዚህ* ሁሉ በሲዲም ሸለቆ*+ ማለትም በጨው ባሕር*+ ሠራዊታቸውን አሰባሰቡ።

4 እነሱም ኮሎዶጎምርን 12 ዓመት አገለገሉት፤ በ13ኛው ዓመት ግን ዓመፁ። 5 ስለሆነም በ14ኛው ዓመት ኮሎዶጎምርና አብረውት የነበሩት ነገሥታት መጥተው ረፋይምን በአስተሮትቃርናይም፣ ዙዚምን በሃም፣ ኤሚምን+ በሻዌቂሪያታይም፣ 6 ሆራውያንን+ ደግሞ ሴይር+ ከሚባለው ተራራቸው አንስቶ በምድረ በዳ እስከሚገኘው እስከ ኤልጳራን ድረስ በሚዘልቀው ስፍራ ድል አደረጓቸው። 7 ከዚያም ቃዴስ+ ወደምትባለው ወደ ኤንሚሽጳጥ ተመልሰው በመምጣት መላውን የአማሌቃውያን+ ግዛትና በሃጻጾንታማር+ ይኖሩ የነበሩትን አሞራውያንን+ ድል አደረጉ።

8 በዚህ ጊዜ የሰዶም ንጉሥ፣ የገሞራ ንጉሥ፣ የአድማህ ንጉሥ፣ የጸቦይም ንጉሥ እንዲሁም የቤላ ማለትም የዞአር ንጉሥ ከእነሱ ጋር ለመዋጋት ሠራዊታቸውን አስተባብረው በሲዲም ሸለቆ* ውስጥ ለጦርነት ተሰለፉ፤ 9 የኤላምን ንጉሥ ኮሎዶጎምርን፣ የጎይምን ንጉሥ ቲድአልን፣ የሰናኦርን ንጉሥ አምራፌልን እንዲሁም የኤላሳርን+ ንጉሥ አርዮክን ለመውጋት ተነሱ፤ አራቱ ነገሥታት ከአምስቱ ጋር ተዋጉ። 10 የሲዲም ሸለቆ* በቅጥራን ጉድጓዶች የተሞላ ነበር፤ የሰዶምና የገሞራ ነገሥታት ሸሽተው ለማምለጥ ሲሞክሩ እነዚህ ጉድጓዶች ውስጥ ወደቁ፤ የቀሩት ደግሞ ወደ ተራራማው አካባቢ ሸሹ። 11 ከዚያም ድል አድራጊዎቹ የሰዶምንና የገሞራን ንብረት በሙሉ እንዲሁም ምግባቸውን ሁሉ ይዘው ሄዱ።+ 12 በተጨማሪም በሰዶም ይኖር የነበረውን የአብራምን የወንድም ልጅ ሎጥን+ ከነንብረቱ ይዘውት ሄዱ።

13 ከዚያም አንድ ያመለጠ ሰው መጥቶ ለዕብራዊው ለአብራም ነገረው። በዚያን ጊዜ አብራም የኤሽኮል እና የአኔር ወንድም በሆነው በአሞራዊው በማምሬ+ ትላልቅ ዛፎች አጠገብ ይኖር* ነበር።+ እነዚህ ሰዎች የአብራም አጋሮች ነበሩ። 14 በዚህ መንገድ አብራም ዘመዱ*+ በምርኮ መወሰዱን ሰማ። ስለሆነም በቤቱ የተወለዱትን 318 የሠለጠኑ አገልጋዮች ሰብስቦ ተነሳ፤ ወራሪዎቹንም ተከትሎ እስከ ዳን+ ድረስ ሄደ። 15 በሌሊትም ሠራዊቱን ከፋፈለ፤ እሱና አገልጋዮቹም በወራሪዎቹ ላይ ጥቃት በመሰንዘር ድል አደረጓቸው። እሱም ከደማስቆ በስተ ሰሜን እስከምትገኘው እስከ ሆባ ድረስ አሳደዳቸው። 16 የወሰዷቸውን ንብረቶችም ሁሉ አስመለሰ፤ በተጨማሪም ዘመዱን ሎጥንና ንብረቶቹን እንዲሁም ሴቶቹንና ሌሎቹን ሰዎች አስመለሰ።

17 አብራም ኮሎዶጎምርንና ከእሱ ጋር የነበሩትን ነገሥታት ድል አድርጎ ከተመለሰ በኋላ የሰዶም ንጉሥ ከአብራም ጋር ለመገናኘት ወደ ሻዌ ሸለቆ* ማለትም ወደ ንጉሡ ሸለቆ+ ወጣ። 18 የሳሌም ንጉሥ+ መልከጼዴቅም+ ምግብና የወይን ጠጅ ይዞ ወጣ፤ እሱም የልዑሉ አምላክ ካህን+ ነበር።

19 አብራምንም ባረከው፤ እንዲህም አለው፦

“ሰማይንና ምድርን የሠራው

ልዑሉ አምላክ አብራምን ይባርክ፤

20 የሚጨቁኑህን በእጅህ አሳልፎ የሰጠህ፣

ልዑሉ አምላክ ይወደስ!”

አብራምም ከሁሉም ነገር ላይ አንድ አሥረኛውን ሰጠው።+

21 ከዚያም የሰዶም ንጉሥ አብራምን “ሰዎቹን* ስጠኝ፤ ንብረቶቹን ግን ለራስህ ውሰድ” አለው። 22 አብራም ግን የሰዶምን ንጉሥ እንዲህ አለው፦ “ሰማይንና ምድርን ወደሠራው ወደ ልዑሉ አምላክ ወደ ይሖዋ እጄን አንስቼ እምላለሁ፣ 23 ‘አብራምን አበለጸግኩት’ እንዳትል የአንተ ከሆነው ነገር ምንም አልወስድም፤ ሌላው ቀርቶ ብጣሽ ክርም ሆነ የጫማ ማሰሪያ አልወስድም። 24 ወጣቶቹ ከበሉት ምግብ በስተቀር ምንም ነገር አልወስድም። ከእኔ ጋር የዘመቱት አኔር፣ ኤሽኮልና ማምሬ+ ግን ድርሻቸውን ይውሰዱ።”

15 ከዚህ በኋላ የይሖዋ ቃል በራእይ ወደ አብራም መጥቶ “አብራም አትፍራ።+ እኔ ጋሻ እሆንሃለሁ።+ የምታገኘውም ሽልማት እጅግ ታላቅ ይሆናል”+ አለው። 2 አብራምም እንዲህ ሲል መለሰ፦ “ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ፣ ያለልጅ እንደቀረሁና ቤቴን የሚወርሰው የደማስቆ ሰው የሆነው ኤሊዔዘር+ እንደሆነ ታያለህ፤ ታዲያ ምን ትሰጠኛለህ?” 3 በተጨማሪም አብራም “እንግዲህ ዘር አልሰጠኸኝም፤+ ደግሞም ወራሼ የሚሆነው በቤቴ ያለው አገልጋይ* ነው” አለ። 4 ሆኖም እንዲህ የሚል የይሖዋ ቃል ወደ እሱ መጣ፦ “ይህ ሰው ወራሽህ አይሆንም፤ ከዚህ ይልቅ የገዛ ልጅህ* ወራሽህ ይሆናል።”+

5 ወደ ውጭም ካወጣው በኋላ “እባክህ ቀና ብለህ ወደ ሰማይ ተመልከት፤ እስቲ መቁጠር ከቻልክ ከዋክብቱን ቁጠራቸው” አለው። ከዚያም “የአንተም ዘር እንዲሁ ይሆናል”+ አለው። 6 አብራምም በይሖዋ አመነ፤+ አምላክም ይህን ጽድቅ አድርጎ ቆጠረለት።+ 7 ደግሞም እንዲህ አለው፦ “ይህችን ምድር ርስት አድርጌ ልሰጥህ ከከለዳውያን ዑር ያወጣሁህ እኔ ይሖዋ ነኝ።”+ 8 አብራምም “ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ፣ ይህችን ምድር ርስት አድርጌ እንደምወርስ እንዴት አውቃለሁ?” አለ። 9 እሱም መልሶ “አንዲት የሦስት ዓመት ጊደር፣ አንዲት የሦስት ዓመት ፍየል፣ አንድ የሦስት ዓመት አውራ በግ እንዲሁም አንድ ዋኖስና አንድ የርግብ ጫጩት ውሰድ” አለው። 10 እሱም እነዚህን እንስሳት ሁሉ ወስዶ ለሁለት ሰነጠቃቸው፤ ከዚያም አንዱን ግማሽ ከሌላኛው ግማሽ ትይዩ አድርጎ አስቀመጠ። ወፎቹን ግን አልሰነጠቃቸውም። 11 አሞሮችም በበድኖቹ ላይ መውረድ ጀመሩ፤ አብራም ግን ያባርራቸው ነበር።

12 ፀሐይ ልትጠልቅ ስትቃረብም አብራም ከባድ እንቅልፍ ወሰደው፤ ታላቅና የሚያስፈራ ጨለማም ወረደበት። 13 አምላክም አብራምን እንዲህ አለው፦ “ዘሮችህ በባዕድ አገር ባዕዳን ሆነው እንደሚኖሩ እንዲሁም በዚያ ያሉት ሰዎች ለ400 ዓመት በባርነት እንደሚገዟቸውና እንደሚያጎሳቁሏቸው በእርግጥ እወቅ።+ 14 ይሁንና በባርነት በሚገዛቸው ብሔር ላይ እፈርዳለሁ፤+ እነሱም ብዙ ንብረት ይዘው ይወጣሉ።+ 15 አንተ ግን ወደ አባቶችህ በሰላም ትሄዳለህ፤ ዕድሜ ጠግበህም ወደ መቃብር ትወርዳለህ።+ 16 ሆኖም በአራተኛው ትውልድ ወደዚህ ይመለሳሉ፤+ ምክንያቱም የአሞራውያን በደል ጽዋው ገና አልሞላም።”+

17 ፀሐይዋ ከጠለቀችና ድቅድቅ ጨለማ አካባቢውን ከዋጠው በኋላ የሚጨስ ምድጃ ታየ፤ ለሁለት በተከፈለውም ሥጋ መካከል የሚንቦገቦግ ችቦ አለፈ። 18 በዚያ ቀን ይሖዋ እንዲህ ሲል ከአብራም ጋር ቃል ኪዳን ገባ፦+ “ከግብፅ ወንዝ አንስቶ እስከ ታላቁ የኤፍራጥስ ወንዝ+ ድረስ ያለውን ይህን ምድር ለዘርህ እሰጣለሁ፤+ 19 የቄናውያንን፣+ የቀኒዛውያንን፣ የቃድሞናውያንን፣ 20 የሂታውያንን፣+ የፈሪዛውያንን፣+ የረፋይምን፣+ 21 የአሞራውያንን፣ የከነአናውያንን፣ የገርጌሻውያንንና የኢያቡሳውያንን+ ምድር ለዘርህ እሰጣለሁ።”

16 የአብራም ሚስት ሦራ ለአብራም ልጆች አልወለደችለትም ነበር፤+ ይሁንና አጋር+ የምትባል አንዲት ግብፃዊት አገልጋይ ነበረቻት። 2 በመሆኑም ሦራ አብራምን እንዲህ አለችው፦ “እንግዲህ እንደምታየው ይሖዋ ልጆች እንዳልወልድ አድርጎኛል። እባክህ ከአገልጋዬ ጋር ግንኙነት ፈጽም። ምናልባትም በእሷ አማካኝነት ልጆች ላገኝ እችላለሁ።”+ ስለሆነም አብራም የሦራን ቃል ሰማ። 3 አብራም በከነአን ምድር ለአሥር ዓመት ያህል ከኖረ በኋላ የአብራም ሚስት ሦራ ግብፃዊት አገልጋይዋን አጋርን ወስዳ ሚስት እንድትሆነው ለባሏ ለአብራም ሰጠችው። 4 በመሆኑም አብራም ከአጋር ጋር ግንኙነት ፈጸመ፤ እሷም ፀነሰች። መፀነሷን ባወቀች ጊዜም እመቤቷን መናቅ ጀመረች።

5 በዚህ ጊዜ ሦራ አብራምን እንዲህ አለችው፦ “ለደረሰብኝ በደል ተጠያቂው አንተ ነህ። አገልጋዬን በእቅፍህ ያደረግኩልህ እኔው ራሴ ነበርኩ፤ እሷ ግን መፀነሷን ባወቀች ጊዜ ትንቀኝ ጀመር። ይሖዋ በእኔና በአንተ መካከል ይፍረድ።” 6 በመሆኑም አብራም ሦራን “እንግዲህ አገልጋይሽ እንደሆነች በእጅሽ ናት። መልካም መስሎ የታየሽን ነገር አድርጊባት” አላት። ከዚያም ሦራ አገልጋይዋን አዋረደቻት፤ ስለዚህም ጥላት ኮበለለች።

7 በኋላም የይሖዋ መልአክ አጋርን በምድረ በዳ በሚገኝ አንድ የውኃ ምንጭ አጠገብ ማለትም ወደ ሹር+ በሚወስደው መንገድ ላይ ባለው ምንጭ አጠገብ አገኛት። 8 እሱም “የሦራ አገልጋይ አጋር፣ ለመሆኑ የመጣሽው ከየት ነው? ወዴትስ እየሄድሽ ነው?” አላት። እሷም መልሳ “ከእመቤቴ ከሦራ ኮብልዬ እየሄድኩ ነው” አለች። 9 የይሖዋም መልአክ “ወደ እመቤትሽ ተመለሽ፤ ለእሷም በትሕትና ተገዢላት” አላት። 10 ከዚያም የይሖዋ መልአክ “ከብዛቱ የተነሳ የማይቆጠር እስኪሆን ድረስ ዘርሽን እጅግ አበዛዋለሁ”+ አላት። 11 በተጨማሪም የይሖዋ መልአክ እንዲህ አላት፦ “እንግዲህ ይኸው ፀንሰሻል፤ ወንድ ልጅ ትወልጃለሽ። ስሙንም እስማኤል* ትይዋለሽ፤ ምክንያቱም ይሖዋ የሥቃይ ጩኸትሽን ሰምቷል። 12 እሱም እንደ ዱር አህያ* ይሆናል። ባገኘው ሰው ሁሉ ላይ እጁን ያነሳል፤ ያገኘውም ሰው ሁሉ እጁን ያነሳበታል፤ ከወንድሞቹም ሁሉ ፊት ለፊት ይኖራል።”*

13 ከዚያም አጋር “የሚያየኝን አሁን በእርግጥ አየሁት ማለት ነው?” ብላ ስላሰበች እያነጋገራት የነበረውን ይሖዋን ስሙን ጠርታ “አንተ የምታይ አምላክ ነህ”+ አለች። 14 የውኃ ጉድጓዱ ብኤርላሃይሮዒ* ተብሎ የተጠራው በዚህ የተነሳ ነው። (ጉድጓዱም በቃዴስና በቤሬድ መካከል ይገኛል።) 15 ስለዚህ አጋር ለአብራም ወንድ ልጅ ወለደችለት፤ አብራምም አጋር የወለደችለትን ልጅ እስማኤል+ ብሎ ስም አወጣለት። 16 አጋር ለአብራም እስማኤልን በወለደችለት ጊዜ አብራም የ86 ዓመት ሰው ነበር።

17 አብራም ዕድሜው 99 ዓመት ሲሆን ይሖዋ ተገለጠለትና እንዲህ አለው፦ “እኔ ሁሉን ቻይ አምላክ ነኝ። በፊቴ ተመላለስ፤ እንከን* የሌለብህ መሆንህንም አስመሥክር። 2 ከአንተ ጋር ቃል ኪዳኔን እመሠርታለሁ፤+ አንተንም እጅግ አበዛሃለሁ።”+

3 በዚህ ጊዜ አብራም በግንባሩ ተደፋ፤ አምላክም እንዲህ በማለት እሱን ማነጋገሩን ቀጠለ፦ 4 “በእኔ በኩል ከአንተ ጋር የገባሁት ቃል ኪዳኔ እንደጸና ነው፤+ አንተም በእርግጥ የብዙ ብሔር አባት ትሆናለህ።+ 5 ከእንግዲህ ስምህ አብራም* አይባልም፤ የብዙ ብሔር አባት ስለማደርግህ ስምህ አብርሃም* ይሆናል። 6 እጅግ አበዛሃለሁ፤ ብዙ ብሔርም አደርግሃለሁ፤ ነገሥታትም ከአንተ ይወጣሉ።+

7 “ለአንተም ሆነ ከአንተ በኋላ ለሚመጡት ዘሮችህ አምላክ እሆን ዘንድ በእኔና በአንተ እንዲሁም መጪዎቹን ትውልዶቻቸውን ሁሉ ጨምሮ ከአንተ በኋላ በሚመጡት ዘሮችህ መካከል ያለውን ቃል ኪዳኔን ዘላለማዊ ቃል ኪዳን አድርጌ እጠብቀዋለሁ።+ 8 ባዕድ ሆነህ የኖርክበትን አገር ይኸውም መላውን የከነአን ምድር ለአንተና ከአንተ በኋላ ለሚመጡት ዘሮችህ ዘላቂ ርስት አድርጌ እሰጣለሁ፤+ እኔም አምላካቸው እሆናለሁ።”+

9 በተጨማሪም አምላክ አብርሃምን እንዲህ አለው፦ “በአንተ በኩል፣ አንተም ሆንክ ከአንተ በኋላ የሚመጡት ዘሮችህ ከትውልድ እስከ ትውልድ ቃል ኪዳኔን መጠበቅ አለባችሁ። 10 እናንተም ሆናችሁ ከእናንተ በኋላ የሚመጡት ዘሮቻችሁ ልትጠብቁት የሚገባው በእኔና በእናንተ መካከል ያለው ቃል ኪዳኔ ይህ ነው፦ በእናንተ መካከል ያለ ወንድ ሁሉ መገረዝ አለበት።+ 11 ሸለፈታችሁን መገረዝ አለባችሁ፤ ይህም በእኔና በእናንተ መካከል ላለው ቃል ኪዳን እንደ ምልክት ሆኖ ያገለግላል።+ 12 በትውልዶቻችሁ ሁሉ በመካከላችሁ ያለ ስምንት ቀን የሞላው ማንኛውም ወንድ መገረዝ አለበት፤+ በቤት የተወለደም ሆነ ዘርህ ያልሆነ ወይም ደግሞ ከባዕድ ሰው ላይ በገንዘብ የተገዛ ማንኛውም ወንድ ሁሉ ይገረዝ። 13 በቤትህ የተወለደ ማንኛውም ወንድ እንዲሁም በገንዘብህ የተገዛ ማንኛውም ወንድ መገረዝ አለበት፤+ በሥጋችሁ ላይ ያለው ይህ ምልክት ከእናንተ ጋር ለገባሁት ዘላቂ ቃል ኪዳን ማስረጃ ሆኖ ያገለግላል። 14 ሸለፈቱ እንዲገረዝ የማያደርግ ያልተገረዘ ወንድ ካለ ያ ሰው* ከሕዝቡ መካከል ተለይቶ እንዲጠፋ ይደረግ።* ይህ ሰው ቃል ኪዳኔን አፍርሷል።”

15 ከዚያም አምላክ አብርሃምን እንዲህ አለው፦ “ሚስትህን ሦራን+ በተመለከተ ሦራ* ብለህ አትጥራት፤ ምክንያቱም ከእንግዲህ ስሟ ሣራ* ይሆናል። 16 እኔም እባርካታለሁ፤ ከእሷም ወንድ ልጅ እሰጥሃለሁ።+ እባርካታለሁ፤ እሷም ብዙ ብሔር ትሆናለች፤ የሕዝቦች ነገሥታትም ከእሷ ይወጣሉ።” 17 በዚህ ጊዜ አብርሃም በግንባሩ ተደፋ፤ እየሳቀም በልቡ እንዲህ አለ፦+ “እንዲያው ምንስ ቢሆን 100 ዓመት የሆነው ሰው የልጅ አባት ሊሆን ይችላል? ዘጠና ዓመት የሆናት ሣራስ ብትሆን ልጅ ልትወልድ ትችላለች?”+

18 ስለዚህ አብርሃም እውነተኛውን አምላክ “ምነው እስማኤልን ብቻ በባረክልኝ!”+ አለው። 19 አምላክም እንዲህ አለው፦ “ሚስትህ ሣራ በእርግጥ ወንድ ልጅ ትወልድልሃለች፤ ስሙንም ይስሐቅ*+ ትለዋለህ። እኔም ከእሱ በኋላ ለሚመጡት ዘሮቹ ጭምር ዘላለማዊ ቃል ኪዳን እንዲሆን ከእሱ ጋር ቃል ኪዳኔን እመሠርታለሁ።+ 20 እስማኤልን በተመለከተም ልመናህን ሰምቻለሁ። እሱንም ቢሆን እባርከዋለሁ፤ ፍሬያማ አደርገዋለሁ፤ እጅግም አበዛዋለሁ። ደግሞም 12 አለቆች ከእሱ ይወጣሉ፤ ታላቅ ብሔርም አደርገዋለሁ።+ 21 ሆኖም የዛሬ ዓመት በዚሁ ጊዜ ሣራ ከምትወልድልህ+ ከይስሐቅ ጋር ቃል ኪዳኔን እመሠርታለሁ።”+

22 አምላክ ከአብርሃም ጋር ተነጋግሮ ሲያበቃ ከእሱ ተለይቶ ወደ ላይ ወጣ። 23 ከዚያም አብርሃም ልጁን እስማኤልን፣ በቤቱ የተወለዱትንና በገንዘቡ የገዛቸውን ወንዶች ሁሉ እንዲሁም በአብርሃም ቤት የሚገኙትን ወንዶች ሁሉ ወስዶ ልክ አምላክ በነገረው መሠረት በዚያኑ ዕለት ሸለፈታቸውን ገረዘ።+ 24 አብርሃም ሸለፈቱን ሲገረዝ የ99 ዓመት ሰው ነበር።+ 25 ልጁ እስማኤል ሸለፈቱን በተገረዘበት ጊዜ ደግሞ 13 ዓመቱ ነበር።+ 26 በዚሁ ዕለት አብርሃም ተገረዘ፤ ልጁ እስማኤልም ተገረዘ። 27 በተጨማሪም በቤቱ የሚገኙ ወንዶች ሁሉ፣ በቤት የተወለዱ ሁሉ እንዲሁም ከባዕድ ሰው በገንዘብ የተገዙ ሁሉ ከእሱ ጋር ተገረዙ።

18 ከዚያም አብርሃም በጣም ሞቃታማ በሆነው የቀኑ ክፍለ ጊዜ ድንኳኑ ደጃፍ ላይ ተቀምጦ ሳለ ይሖዋ+ በማምሬ ትላልቅ ዛፎች+ አጠገብ ተገለጠለት። 2 ቀና ብሎም ሲመለከት እሱ ካለበት ትንሽ ራቅ ብሎ ሦስት ሰዎች ቆመው አየ።+ ሰዎቹን ባያቸው ጊዜም ከድንኳኑ ደጃፍ ተነስቶ ወደ እነሱ እየሮጠ ሄደ፤ ወደ መሬት ዝቅ ብሎም ሰገደ። 3 ከዚያም እንዲህ አለ፦ “ይሖዋ፣ እንግዲህ በፊትህ ሞገስ አግኝቼ ከሆነ እባክህ አገልጋይህን አልፈኸው አትሂድ። 4 እባካችሁ ጥቂት ውኃ ይምጣላችሁና እግራችሁን ታጠቡ፤+ ከዚያም ከዛፉ ሥር አረፍ በሉ። 5 ወደ አገልጋያችሁ ከመጣችሁ አይቀር፣ ብርታት እንድታገኙ* ትንሽ እህል ላምጣላችሁና ቅመሱ፤ ከዚያም ጉዟችሁን ትቀጥላላችሁ።” በዚህ ጊዜ እነሱ “እሺ፣ እንዳልከው አድርግ” አሉት።

6 በመሆኑም አብርሃም ሣራ ወዳለችበት ወደ ድንኳኑ በፍጥነት ሄዶ “ቶሎ በይ! ሦስት መስፈሪያ* የላመ ዱቄት ወስደሽ አቡኪና ቂጣ ጋግሪ” አላት። 7 በመቀጠልም አብርሃም ወደ መንጋው ሮጦ በመሄድ ሥጋው ገር የሆነ ፍርጥም ያለ ወይፈን መረጠ። ለአገልጋዩም ሰጠው፤ እሱም ለማዘጋጀት ተጣደፈ። 8 ከዚያም ቅቤና ወተት እንዲሁም ያዘጋጀውን ወይፈን ወስዶ ምግቡን አቀረበላቸው። እየበሉ ሳሉም ዛፉ ሥር አጠገባቸው ቆሞ ነበር።+

9 እነሱም “ሚስትህ ሣራ+ የት አለች?” አሉት። እሱም “እዚህ ድንኳኑ ውስጥ ናት” አላቸው። 10 ከመካከላቸውም አንዱ ንግግሩን በመቀጠል “የዛሬ ዓመት በዚሁ ጊዜ በእርግጥ ወደ አንተ እመለሳለሁ፤ ሚስትህ ሣራም ወንድ ልጅ ትወልዳለች”+ አለ። በዚህ ጊዜ ሣራ ከሰውየው በስተ ጀርባ ባለው በድንኳኑ ደጃፍ ላይ ሆና ታዳምጥ ነበር። 11 አብርሃምና ሣራ አርጅተው፣ ዕድሜያቸውም ገፍቶ ነበር።+ ሣራ ልጅ የመውለጃዋ ዕድሜ አልፎ ነበር።*+ 12 በመሆኑም ሣራ “አሁን እንዲህ አርጅቼ ጌታዬም ዕድሜው ገፍቶ እያለ በእርግጥ እንዲህ ዓይነት ደስታ ላገኝ እችላለሁ?”+ ብላ በማሰብ በልቧ ሳቀች። 13 ከዚያም ይሖዋ አብርሃምን እንዲህ አለው፦ “ሣራ ‘እንዲህ ካረጀሁ በኋላም እንኳ ልወልድ ነው ማለት ነው?’ በማለት የሳቀችው ለምንድን ነው? 14 ለይሖዋ የሚሳነው ነገር አለ?+ የዛሬ ዓመት በዚሁ በተወሰነው ጊዜ ወደ አንተ እመለሳለሁ፤ ሣራም ወንድ ልጅ ትወልዳለች።” 15 ሣራ ግን ስለፈራች “ኧረ አልሳቅኩም!” ስትል ካደች። በዚህ ጊዜ “እንዴ! ሳቅሽ እንጂ” አላት።

16 ሰዎቹም ለመሄድ በተነሱና ቁልቁል ወደ ሰዶም+ በተመለከቱ ጊዜ አብርሃም ሊሸኛቸው አብሯቸው ሄደ። 17 ይሖዋ እንዲህ አለ፦ “እኔ ላደርገው ያሰብኩትን ነገር ከአብርሃም ደብቄ አውቃለሁ?+ 18 አብርሃም በእርግጥ ታላቅና ኃያል ብሔር ይሆናል፤ የምድር ብሔራትም ሁሉ በእሱ አማካኝነት ይባረካሉ።*+ 19 እኔ ከአብርሃም ጋር የተዋወቅኩት ትክክለኛና ተገቢ የሆነውን ነገር በማድረግ የይሖዋን መንገድ ይጠብቁ ዘንድ ልጆቹንና ከእሱ በኋላ የሚመጣውን ቤተሰቡን እንዲያዝዝ ነው፤+ እንዲህ ካደረገ ይሖዋ አብርሃምን አስመልክቶ ቃል የገባውን ነገር ይፈጽምለታል።”

20 ከዚያም ይሖዋ እንዲህ አለ፦ “በሰዶምና በገሞራ ላይ የሚሰማው ጩኸት በእርግጥም ታላቅ ነው፤+ ኃጢአታቸውም እጅግ ከባድ ሆኗል።+ 21 ድርጊታቸው እኔ ዘንድ እንደደረሰው ጩኸት መሆን አለመሆኑን ለማየት ወደዚያ እወርዳለሁ። ነገሩ እንደዚያ ካልሆነም ማወቅ እችላለሁ።”+

22 ሰዎቹም ከዚያ ተነስተው ወደ ሰዶም አቀኑ፤ ይሖዋ+ ግን እዚያው ከአብርሃም ጋር ቀረ። 23 ከዚያም አብርሃም ቀረብ ብሎ እንዲህ አለ፦ “በእርግጥ ጻድቁን ከኃጢአተኛው ጋር አብረህ ታጠፋለህ?+ 24 እስቲ በከተማዋ ውስጥ 50 ጻድቅ ሰዎች አሉ እንበል። ታዲያ ሁሉንም ዝም ብለህ ታጠፋቸዋለህ? በውስጧ ስለሚኖሩት 50 ጻድቃን ስትል ስፍራውን አትምርም? 25 በጻድቁም ሆነ በኃጢአተኛው ላይ ተመሳሳይ ነገር እንዲደርስ የሚያደርግ እንዲህ ዓይነት እርምጃ በመውሰድ ጻድቁን ከኃጢአተኛው ጋር አንድ ላይ ትገድላለህ ብሎ ማሰብ ፈጽሞ የማይሆን ነገር ነው!+ ይህ በአንተ ዘንድ ፈጽሞ የማይታሰብ ነገር ነው።+ የምድር ሁሉ ዳኛ ትክክል የሆነውን ነገር አያደርግም?”+ 26 ከዚያም ይሖዋ “በሰዶም ከተማ ውስጥ 50 ጻድቅ ሰዎች ባገኝ ስለ እነሱ ስል ስፍራውን በሙሉ እምራለሁ” አለ። 27 አብርሃም ግን እንደገና እንዲህ ሲል መለሰ፦ “መቼም እኔ ትቢያና አመድ ሆኜ ሳለሁ አንዴ ደፍሬ ከይሖዋ ጋር መነጋገር ጀምሬያለሁ። 28 ከ50ዎቹ ጻድቃን መካከል አምስት ጎደሉ እንበል። ታዲያ በአምስቱ የተነሳ መላዋን ከተማ ታጠፋለህ?” እሱም “በዚያ 45 ባገኝ ከተማዋን አላጠፋም”+ አለ።

29 አብርሃም ግን በድጋሚ “በዚያ 40 ተገኙ እንበል” አለው። እሱም መልሶ “ስለ 40ዎቹ ስል አላደርገውም” አለ። 30 አብርሃም ግን በመቀጠል “ይሖዋ እባክህ፣ አትቆጣና+ አሁንም ልናገር፤ እንደው በዚያ 30 ብቻ ቢገኙስ?” አለ። እሱም “በዚያ 30 ካገኘሁ አላደርገውም” ሲል መለሰ። 31 አብርሃም ግን እንዲህ በማለት ቀጠለ፦ “መቼም አንዴ ደፍሬ ከይሖዋ ጋር መነጋገር ጀምሬያለሁ፤ እንደው በዚያ 20 ብቻ ቢገኙስ?” እሱም መልሶ “ስለ 20ዎቹ ስል አላጠፋትም” አለ። 32 በመጨረሻም አብርሃም እንዲህ አለ፦ “ይሖዋ እባክህ፣ አትቆጣና አንድ ጊዜ ብቻ ልናገር፤ በዚያ አሥር ብቻ ቢገኙስ?” እሱም መልሶ “ስለ አሥሩ ስል አላጠፋትም” አለ። 33 ይሖዋም ከአብርሃም ጋር ተነጋግሮ ሲጨርስ ጉዞውን ቀጠለ፤+ አብርሃም ደግሞ ወደ ስፍራው ተመለሰ።

19 ሁለቱ መላእክት ምሽት ላይ ሰዶም ደረሱ፤ ሎጥም በሰዶም በር ተቀምጦ ነበር። እሱም ባያቸው ጊዜ ተነስቶ ወደ እነሱ ሄደ፤ በግንባሩም መሬት ላይ ተደፋ።+ 2 እንዲህም አለ፦ “ጌቶቼ፣ እባካችሁ ወደ አገልጋያችሁ ቤት ጎራ በሉና እደሩ፤ እግራችሁንም ታጠቡ። ከዚያም በማለዳ ተነስታችሁ ጉዟችሁን ትቀጥላላችሁ።” እነሱም መልሰው “አይሆንም፣ አደባባዩ ላይ እናድራለን” አሉ። 3 እሱ ግን አጥብቆ ስለለመናቸው አብረውት ወደ ቤቱ ሄዱ። ከዚያም ግብዣ አደረገላቸው። ቂጣም ጋገረላቸው፤ እነሱም በሉ።

4 ከመተኛታቸውም በፊት የከተማዋ ሰዎች ማለትም በሰዶም ያሉ ወንዶች ሁሉ ከልጅ እስከ አዋቂ ድረስ ግልብጥ ብለው በመውጣት ቤቱን ከበቡት። 5 ሎጥንም ደጋግመው በመጥራት “በዚህ ምሽት ወደ አንተ የመጡት ሰዎች የት አሉ? ከእነሱ ጋር የፆታ ግንኙነት እንድንፈጽም ወደ ውጭ አውጣልን” ይሉት ጀመር።+

6 ከዚያም ሎጥ ወደ እነሱ ወደ ውጭ ወጣ፤ በሩንም ከኋላው ዘጋው። 7 እንዲህም አላቸው፦ “እባካችሁ ወንድሞቼ፣ እንዲህ ያለ ክፉ ድርጊት አትፈጽሙ። 8 እባካችሁ፣ ከወንድ ጋር የፆታ ግንኙነት ፈጽመው የማያውቁ ሁለት ሴቶች ልጆች አሉኝ። እባካችሁ፣ እነሱን ላውጣላችሁና መልካም መስሎ የታያችሁን አድርጉባቸው። እነዚህ ሰዎች ግን በጣሪያዬ ጥላ* ሥር ስለተጠለሉ በእነሱ ላይ ምንም ነገር አታድርጉ።”+ 9 በዚህ ጊዜ ሰዎቹ “ዞር በል!” አሉት። ከዚያም “ይህ ወገን የሌለው መጤ፣ ደግሞ በእኛ ላይ ዳኛ ልሁን ይላል እንዴ! በእነሱ ላይ ልናደርግ ካሰብነው የከፋ ነገር እንዳናደርግብህ” አሉት። ሎጥንም በኃይል ገፉት፤ በሩንም ሊሰብሩት ተቃረቡ። 10 ስለሆነም ውስጥ የነበሩት ሰዎች እጃቸውን ወደ ውጭ ዘርግተው ሎጥን እነሱ ወዳሉበት ወደ ቤት አስገቡት፤ በሩንም ዘጉት። 11 ሆኖም በቤቱ ደጃፍ ላይ የነበሩትን ሰዎች ከትንሹ አንስቶ እስከ ትልቁ ድረስ አሳወሯቸው፤ በዚህም የተነሳ ሰዎቹ በሩን ለማግኘት ሲዳክሩ ደከሙ።

12 ከዚያም ሰዎቹ ሎጥን እንዲህ አሉት፦ “እዚህ የሚኖሩ ሌሎች ዘመዶች አሉህ? አማቾችህን፣ ወንዶችና ሴቶች ልጆችህን እንዲሁም በከተማዋ ውስጥ የሚኖር ዘመድ አዝማድህን በሙሉ ከዚህ ስፍራ ይዘህ ውጣ! 13 ይህን ስፍራ ልናጠፋው ነው፤ ምክንያቱም ሕዝቦቿን በተመለከተ የሚሰማው ጩኸት በይሖዋ ፊት እየጨመረ ስለመጣ+ ይሖዋ ከተማዋን እንድናጠፋት ልኮናል።” 14 በመሆኑም ሎጥ ወጥቶ የሴት ልጆቹ እጮኛ የሆኑትን አማቾቹን “ተነሱ! ይሖዋ ከተማዋን ሊያጠፋት ስለሆነ ከዚህ ስፍራ ውጡ!” አላቸው። አማቾቹ ግን የሚያሾፍ መሰላቸው።+

15 ጎህ ሲቀድ መላእክቱ ሎጥን “ተነስ! በከተማዋ በደል የተነሳ እንዳትጠፋ ከአንተ ጋር ያሉትን ሚስትህንና ሁለቱን ሴቶች ልጆችህን ይዘህ ውጣ!” በማለት አቻኮሉት።+ 16 ሎጥ በዘገየ ጊዜ ይሖዋ ስለራራለት+ ሰዎቹ የእሱን እጅ፣ የሚስቱን እጅና የሁለቱን ሴቶች ልጆቹን እጅ ይዘው ከከተማዋ አስወጡት።+ 17 ልክ ከተማዋ ዳርቻ ላይ እንዳደረሷቸውም ከእነሱ አንዱ እንዲህ አለ፦ “ሕይወትህን* ለማትረፍ ሽሽ! ወደ ኋላህ እንዳትመለከት፤+ አውራጃውንም+ ለቀህ እስክትወጣ ድረስ የትኛውም ቦታ ላይ እንዳትቆም! እንዳትጠፋ ወደ ተራራማው አካባቢ ሽሽ!”

18 ከዚያም ሎጥ እንዲህ አላቸው፦ “እባክህ ይሖዋ፣ ወደዚያስ አልሂድ! 19 መቼም አገልጋይህ በፊትህ ሞገስ አግኝቷል፤ ሕይወቴን* በማትረፍ ታላቅ ደግነት* አሳይተኸኛል፤+ ሆኖም አደጋ እንዳይደርስብኝና እንዳልሞት ስለምፈራ+ ወደ ተራራማው አካባቢ ሸሽቼ ማምለጥ አልችልም። 20 እባክህ ይህች ከተማ ቅርብ ነች፤ ወደዚያ መሸሽ እችላለሁ፤ ትንሽ ስፍራ እኮ ናት። እባክህ፣ ወደዚያ መሸሽ እችላለሁ? ትንሽ ስፍራ እኮ ናት። እንደዚያ ከሆነ እተርፋለሁ።”* 21 እሱም እንዲህ አለው፦ “እሺ ይሁን፣ ያልካትን ከተማ ባለማጥፋት+ አሁንም አሳቢነት አሳይሃለሁ።+ 22 ፍጠን! አንተ እዚያ እስክትደርስ ድረስ ምንም ነገር ማድረግ ስለማልችል+ ወደዚያ ሽሽ!” ከተማዋን ዞአር*+ ብሎ የሰየማት ለዚህ ነው።

23 ሎጥ ዞአር ሲደርስ ፀሐይ በምድሩ ላይ ወጥታ ነበር። 24 ከዚያም ይሖዋ በሰዶምና በገሞራ ላይ እሳትና ድኝ አዘነበ፤ ይህም የመጣው ከሰማይ ከይሖዋ ዘንድ ነው።+ 25 እሱም እነዚህን ከተሞች ገለባበጠ፤ አዎ፣ የከተሞቹን ነዋሪዎችና የምድሪቱን ተክል+ ሁሉ ጨምሮ መላውን አውራጃ ገለባበጠ። 26 ሆኖም ከሎጥ በስተ ኋላ የነበረችው የሎጥ ሚስት ወደ ኋላ ዞራ መመልከት ጀመረች፤ እሷም የጨው ዓምድ ሆነች።+

27 አብርሃምም በማለዳ ተነሳ፤ ቀደም ሲል በይሖዋ ፊት ቆሞ ወደነበረበትም ስፍራ ሄደ።+ 28 ወደ ሰዶምና ወደ ገሞራ እንዲሁም በአውራጃው ውስጥ ወዳሉት ከተሞች በሙሉ ቁልቁል ሲያይም የሚያስገርም ነገር ተመለከተ። ከእቶን እንደሚወጣ ያለ የሚትጎለጎል ጭስ ከምድሩ እየተትጎለጎለ ይወጣ ነበር!+ 29 አምላክ የአውራጃውን ከተሞች ባጠፋበት ጊዜ ሎጥ ይኖርባቸው ከነበሩትና አምላክ ካጠፋቸው ከተሞች ውስጥ ሎጥን በማውጣት አብርሃምን አሰበው።+

30 በኋላም ሎጥ በዞአር+ መኖር ስለፈራ ከዞአር ወጥቶ ከሁለቱ ሴቶች ልጆቹ ጋር በተራራማው አካባቢ መኖር ጀመረ።+ ስለዚህ ከሁለቱ ሴቶች ልጆቹ ጋር በዋሻ ውስጥ መኖር ጀመረ። 31 የመጀመሪያዋ ልጅ ታናሿን እንዲህ አለቻት፦ “አባታችን አርጅቷል፤ በመላው ምድር ላይ ባለው ልማድ መሠረት ከእኛ ጋር ግንኙነት የሚፈጽም ወንድ በዚህ አካባቢ የለም። 32 ነይ፣ አባታችንን የወይን ጠጅ እናጠጣውና ከእሱ ጋር እንተኛ፤ እንዲህ በማድረግ ከአባታችን ዘር እናስቀር።”

33 በመሆኑም በዚያ ምሽት አባታቸውን ደጋግመው የወይን ጠጅ አጠጡት፤ ከዚያም የመጀመሪያዋ ልጅ ገብታ ከአባቷ ጋር ተኛች። እሱ ግን ስትተኛም ሆነ ስትነሣ አላወቀም። 34 በማግስቱም የመጀመሪያዋ ልጅ ታናሿን እንዲህ አለቻት፦ “ይኸው እኔ ትናንት ሌሊት ከአባቴ ጋር ተኝቻለሁ። ዛሬ ማታም የወይን ጠጅ እናጠጣው። ከዚያም አንቺ ገብተሽ ከእሱ ጋር ትተኚያለሽ። እንዲህ በማድረግ ከአባታችን ዘር እናስቀር።” 35 በመሆኑም በዚያ ምሽትም አባታቸውን ደጋግመው የወይን ጠጅ አጠጡት፤ ከዚያም ታናሽየዋ ልጅ ሄዳ ከአባቷ ጋር ተኛች። እሱ ግን ስትተኛም ሆነ ስትነሳ አላወቀም። 36 ስለሆነም ሁለቱም የሎጥ ሴቶች ልጆች ከአባታቸው ፀነሱ። 37 ታላቅየዋም ወንድ ልጅ ወለደች፤ ስሙንም ሞዓብ+ አለችው፤ እሱም ዛሬ ያሉት ሞዓባውያን አባት ነው።+ 38 ታናሽየዋም ወንድ ልጅ ወለደች፤ ስሙንም ቤንአሚ አለችው፤ እሱም ዛሬ ያሉት አሞናውያን አባት ነው።+

20 አብርሃም ድንኳኑን+ ከዚያ ነቅሎ ወደ ኔጌብ ምድር ሄደ፤ በቃዴስና+ በሹር+ መካከልም መኖር ጀመረ። በጌራራ+ እየኖረ* ሳለ 2 በድጋሚ ሚስቱን ሣራን “እህቴ ናት” አለ።+ በመሆኑም የጌራራ ንጉሥ አቢሜሌክ ሰዎችን ልኮ ሣራን አስመጣት፤ ከዚያም ወሰዳት።+ 3 ከዚያም አምላክ ለአቢሜሌክ ሌሊት በሕልም ተገልጦለት “በወሰድካት ሴት የተነሳ ትሞታለህ፤+ ምክንያቱም እሷ ያገባችና ባለቤት ያላት ሴት ናት”+ አለው። 4 ሆኖም አቢሜሌክ ወደ እሷ አልቀረበም ነበር።* በመሆኑም እንዲህ አለ፦ “ይሖዋ፣ ምንም በደል ያልፈጸመን* ብሔር ታጠፋለህ? 5 እሱ ‘እህቴ ናት’ አላለኝም? እሷስ ብትሆን ‘ወንድሜ ነው’ አላለችም? ይህን ያደረግኩት በቅን ልቦናና በንጹሕ እጅ ነው።” 6 ከዚያም እውነተኛው አምላክ በሕልም ተገልጦለት እንዲህ አለው፦ “ይህን ያደረግከው በቅን ልቦና ተነሳስተህ እንደሆነ አውቃለሁ፤ በእኔም ላይ ኃጢአት እንዳትሠራ ጠብቄሃለሁ። እንድትነካት ያልፈቀድኩልህም ለዚህ ነው። 7 በል አሁን የሰውየውን ሚስት መልስ፤ እሱ ነቢይ ነውና፤+ ስለ አንተም ልመና ያቀርባል፤+ አንተም በሕይወት ትኖራለህ። እሷን ባትመልስ ግን በእርግጥ እንደምትሞት እወቅ፤ አንተም ሆንክ የአንተ የሆነው ሁሉ ትሞታላችሁ።”

8 አቢሜሌክ በማለዳ ተነሳ፤ አገልጋዮቹንም በሙሉ ጠርቶ የሆነውን ሁሉ ነገራቸው፤ እነሱም በጣም ፈሩ። 9 ከዚያም አቢሜሌክ አብርሃምን ጠርቶ እንዲህ አለው፦ “ይህ ያደረግክብን ነገር ምንድን ነው? በእኔም ሆነ በግዛቴ ላይ እንዲህ ያለውን ታላቅ ኃጢአት ያመጣህብን ለመሆኑ ምን በድዬህ ነው? ያደረግክብኝ ነገር ትክክል አይደለም።” 10 በመቀጠልም አቢሜሌክ አብርሃምን “ለመሆኑ ይህን ያደረግከው ምን አስበህ ነው?” አለው።+ 11 አብርሃምም እንዲህ አለው፦ “ይህን ያደረግኩት ‘በዚህ ስፍራ እንደሆነ ፈሪሃ አምላክ የሚባል ነገር የለም፤ ሰዎቹ ለሚስቴ ሲሉ ሊገድሉኝ ይችላሉ’ ብዬ ስለሰጋሁ ነው።+ 12 ደግሞም እኮ በእርግጥ እህቴ ናት፤ የእናቴ ልጅ ባትሆንም የአባቴ ልጅ ናት፤ እሷም ሚስቴ ሆነች።+ 13 በመሆኑም አምላክ ከአባቴ ቤት ወጥቼ ከአገር አገር እየዞርኩ እንድኖር በነገረኝ ጊዜ+ ‘በምንሄድበት ስፍራ ሁሉ “ወንድሜ ነው” ብለሽ በመናገር ታማኝ ፍቅር አሳዪኝ’ ብያት ነበር።”+

14 ከዚያም አቢሜሌክ በጎችን፣ ከብቶችን እንዲሁም ወንድና ሴት አገልጋዮችን ለአብርሃም ሰጠው፤ ሚስቱን ሣራንም መለሰለት። 15 በተጨማሪም አቢሜሌክ “አገሬ አገርህ ናት፤ ደስ ባለህ ቦታ መኖር ትችላለህ” አለው። 16 ሣራንም እንዲህ አላት፦ “ይኸው ለወንድምሽ+ 1,000 የብር ሰቅል እሰጠዋለሁ። ይህም አንቺ ንጹሕ ሰው መሆንሽን ከአንቺ ጋር ባሉት ሰዎች ሁሉ ፊትም ሆነ በሌሎች ሰዎች ፊት የሚያሳውቅ ምልክት ነው፤* አንቺም ከማንኛውም ነቀፋ ነፃ ነሽ።” 17 አብርሃምም ወደ እውነተኛው አምላክ ልመና አቀረበ፤ አምላክም አቢሜሌክን፣ ሚስቱንና ሴት ባሪያዎቹን ፈወሳቸው፤ እነሱም ልጆች መውለድ ጀመሩ፤ 18 ምክንያቱም ይሖዋ በአብርሃም ሚስት በሣራ የተነሳ በአቢሜሌክ ቤት ያሉትን ሴቶች ሁሉ መሃን አድርጎ ነበር።*+

21 ይሖዋ ልክ በተናገረው መሠረት ሣራን አሰባት፤ ይሖዋም ለሣራ ቃል የገባላትን አደረገላት።+ 2 በመሆኑም ሣራ ፀነሰች፤+ ለአብርሃምም አምላክ ቃል በገባለት በተወሰነው ጊዜ ላይ በስተርጅናው ወንድ ልጅ ወለደችለት።+ 3 አብርሃም ሣራ የወለደችለትን ልጅ ይስሐቅ ብሎ ጠራው።+ 4 አብርሃምም ልክ አምላክ ባዘዘው መሠረት ልጁ ይስሐቅ ስምንት ቀን ሲሆነው ገረዘው።+ 5 አብርሃም ልጁ ይስሐቅ ሲወለድ ዕድሜው 100 ዓመት ነበር። 6 ከዚያም ሣራ “አምላክ በደስታ እንድስቅ አድርጎኛል፤ ይህን የሰማም ሁሉ ከእኔ ጋር አብሮ ይስቃል”* አለች። 7 አክላም “ለመሆኑ ለአብርሃም ‘ሣራ ልጆች ታጠባለች’ ማን ብሎት ያውቃል? እኔ ግን ይኸው በስተርጅናው ወንድ ልጅ ወለድኩለት” አለች።

8 ልጁም አደገ፤ ጡትም ጣለ፤ አብርሃምም ይስሐቅ ጡት በጣለበት ቀን ትልቅ ግብዣ አደረገ። 9 ሣራም ግብፃዊቷ አጋር ለአብርሃም የወለደችለት ልጅ+ በይስሐቅ ላይ እንደሚያፌዝበት+ በተደጋጋሚ አስተዋለች። 10 ስለዚህ አብርሃምን “ይህችን ባሪያና ልጇን ከዚህ አባር፤ ምክንያቱም የዚህች ባሪያ ልጅ ከልጄ ከይስሐቅ ጋር ወራሽ አይሆንም!”+ አለችው። 11 አብርሃም ግን ሣራ ስለ ልጁ የተናገረችው ነገር በጣም ቅር አሰኘው።+ 12 ከዚያም አምላክ አብርሃምን እንዲህ አለው፦ “ሣራ ስለ ልጁና ስለ ባሪያህ እየነገረችህ ያለው ነገር ምንም ቅር አያሰኝህ። ዘርህ የሚጠራልህ በይስሐቅ በኩል ስለሆነ የምትልህን* ስማ።+ 13 የባሪያይቱም ልጅ+ ቢሆን ልጅህ ስለሆነ ከእሱ አንድ ብሔር እንዲገኝ አደርጋለሁ።”+

14 ስለዚህ አብርሃም በማለዳ ተነሳ፤ ለአጋርም ምግብና የውኃ አቁማዳ ሰጣት። እነዚህንም በትከሻዋ አሸከማት፤ ከዚያም ከልጁ ጋር አሰናበታት።+ እሷም ሄደች፤ በቤርሳቤህ+ ምድረ በዳም ትንከራተት ጀመር። 15 በመጨረሻም በአቁማዳው ውስጥ የነበረው ውኃ አለቀ፤ እሷም ልጁን አንዱ ቁጥቋጦ ሥር ጣለችው። 16 ከዚያም “ልጁ ሲሞት ማየት አልፈልግም” ብላ የቀስት ውርወራ ያህል ርቃ ተቀመጠች። እሷም ትጮኽና ታለቅስ ጀመር።

17 በዚህ ጊዜ አምላክ የልጁን ድምፅ ሰማ፤+ የአምላክም መልአክ ከሰማይ አጋርን ጠርቶ እንዲህ አላት፦+ “አጋር፣ ምን ሆነሻል? ልጁ ካለበት ቦታ ሆኖ ሲያለቅስ አምላክ ስለሰማ አይዞሽ አትፍሪ። 18 ተነሽ፣ ልጁንም አንስተሽ በእጅሽ ያዢው፤ ምክንያቱም እኔ ታላቅ ብሔር አደርገዋለሁ።”+ 19 ከዚያም አምላክ ዓይኖቿን ከፈተላት፤ የውኃ ጉድጓድም ተመለከተች። ወደዚያም ሄዳ በአቁማዳው ውኃ ሞላች፤ ልጁንም አጠጣችው። 20 ልጁም እያደገ ሄደ፤ አምላክም ከልጁ+ ጋር ነበር። እሱም የሚኖረው በምድረ በዳ ነበር፤ ቀስተኛም ሆነ። 21 እሱም በፋራን ምድረ በዳ+ ኖረ፤ እናቱም ከግብፅ ምድር ሚስት አመጣችለት።

22 በዚያን ጊዜ አቢሜሌክ ከሠራዊቱ አዛዥ ከፊኮል ጋር ሆኖ አብርሃምን እንዲህ አለው፦ “በምታደርገው ነገር ሁሉ አምላክ ከአንተ ጋር ነው።+ 23 ስለዚህ እኔንም ሆነ ልጆቼንና ዘሮቼን እንደማትክድ እንዲሁም ለእኔም ሆነ ለምትኖርባት ምድር እኔ ያሳየሁህ ዓይነት ታማኝ ፍቅር እንደምታሳይ በአምላክ ስም ማልልኝ።”+ 24 አብርሃምም “እሺ፣ እምላለሁ” አለ።

25 ሆኖም አብርሃም የአቢሜሌክ አገልጋዮች በጉልበት ስለወሰዱት የውኃ ጉድጓድ ለአቢሜሌክ ቅሬታውን ገለጸለት።+ 26 አቢሜሌክም መልሶ “ይህን ያደረገው ማን እንደሆነ አላውቅም፤ አንተም ብትሆን ስለዚህ ጉዳይ አልነገርከኝም፤ ስለዚህ ነገር ያለዛሬ አልሰማሁም” አለው። 27 በዚህ ጊዜ አብርሃም በጎችንና ከብቶችን ወስዶ ለአቢሜሌክ ሰጠው፤ ሁለቱም ቃል ኪዳን ገቡ። 28 አብርሃም ሰባት እንስት በጎችን ከመንጋው ለይቶ ለብቻቸው እንዲሆኑ ባደረገ ጊዜ 29 አቢሜሌክ አብርሃምን “እነዚህን ሰባት እንስት በጎች ለብቻቸው የለየኸው ለምንድን ነው?” አለው። 30 እሱም “ይህን ጉድጓድ የቆፈርኩት እኔ ለመሆኔ ምሥክር እንዲሆን እነዚህን ሰባት እንስት በጎች ከእጄ ውሰድ” አለው። 31 የቦታውን ስም ቤርሳቤህ*+ ብሎ የጠራው በዚህ የተነሳ ነው፤ ምክንያቱም በዚያ ሁለቱ ተማምለዋል። 32 ስለዚህ በቤርሳቤህ ቃል ኪዳን ገቡ፤+ ከዚያም አቢሜሌክ ከሠራዊቱ አዛዥ ከፊኮል ጋር ሆኖ ወደ ፍልስጤማውያን+ ምድር ተመለሰ። 33 ከዚያም በኋላ አብርሃም በቤርሳቤህ የታማሪስክ ዛፍ ተከለ፤ በዚያም የዘላለማዊውን አምላክ+ የይሖዋን ስም ጠራ።+ 34 አብርሃምም በፍልስጤማውያን ምድር ረዘም ላለ ጊዜ* ኖረ።*+

22 ከዚህ በኋላ እውነተኛው አምላክ አብርሃምን ፈተነው፤+ “አብርሃም!” ሲል ጠራው፤ እሱም መልሶ “አቤት!” አለ። 2 ከዚያም አምላክ እንዲህ አለው፦ “እባክህ ልጅህን፣ በጣም የምትወደውን አንድ ልጅህን+ ይስሐቅን+ ይዘህ ወደ ሞሪያ+ ምድር ሂድ፤ በዚያም እኔ በማሳይህ በአንዱ ተራራ ላይ የሚቃጠል መባ አድርገህ አቅርበው።”

3 ስለዚህ አብርሃም በማለዳ ተነስቶ አህያውን ከጫነ በኋላ ከአገልጋዮቹ መካከል ሁለቱን ከልጁ ከይስሐቅ ጋር ይዞ ለመሄድ ተነሳ። ለሚቃጠል መባ የሚሆን እንጨትም ፈለጠ፤ ከዚያም ተነስቶ እውነተኛው አምላክ ወዳሳየው ስፍራ ተጓዘ። 4 በሦስተኛውም ቀን አብርሃም ቀና ብሎ ቦታውን ከሩቅ ተመለከተ። 5 በዚህ ጊዜ አብርሃም አገልጋዮቹን “እናንተ አህያውን ይዛችሁ እዚህ ቆዩ፤ እኔና ልጄ ግን ወደዚያ በመሄድ በአምላክ ፊት ሰግደን ወደ እናንተ እንመለሳለን” አላቸው።

6 ስለዚህ አብርሃም ለሚቃጠል መባ የሚሆነውን እንጨት ወስዶ ልጁን ይስሐቅን አሸከመው። እሱ ደግሞ እሳቱንና ቢላውን* ያዘ፤ ሁለቱም አብረው ሄዱ። 7 ይስሐቅም አባቱን አብርሃምን “አባዬ!” ሲል ጠራው። እሱም መልሶ “አቤት ልጄ!” አለው። ይስሐቅም “እሳቱና እንጨቱ ይኸውና፤ ለሚቃጠል መባ የሚሆነው በግ ግን የት አለ?” አለው። 8 በዚህ ጊዜ አብርሃም “ልጄ፣ ለሚቃጠል መባ የሚሆነውን በግ+ አምላክ ራሱ ያዘጋጃል” አለው። ሁለቱም አብረው ጉዟቸውን ቀጠሉ።

9 በመጨረሻም እውነተኛው አምላክ ወዳሳየው ስፍራ ደረሱ፤ አብርሃምም በዚያ መሠዊያ ሠርቶ እንጨቱን ረበረበበት። ልጁን ይስሐቅንም እጁንና እግሩን አስሮ በመሠዊያው ላይ በተረበረበው እንጨት ላይ አጋደመው።+ 10 ከዚያም አብርሃም ልጁን ለማረድ እጁን ዘርግቶ ቢላውን* አነሳ።+ 11 ሆኖም የይሖዋ መልአክ ከሰማይ ጠርቶት “አብርሃም፣ አብርሃም!” አለው፤ እሱም መልሶ “አቤት!” አለ። 12 መልአኩም እንዲህ አለው፦ “በልጁ ላይ እጅህን አታሳርፍበት፤ ምንም ነገር አታድርግበት፤ ምክንያቱም ልጅህን፣ አንድ ልጅህን ለእኔ ለመስጠት ስላልሳሳህ አምላክን የምትፈራ ሰው እንደሆንክ አሁን በእርግጥ አውቄአለሁ።”+ 13 በዚህ ጊዜ አብርሃም ቀና ብሎ ሲመለከት ከእሱ ትንሽ እልፍ ብሎ ቀንዶቹ በጥሻ የተያዙ አውራ በግ አየ። በመሆኑም አብርሃም አውራውን በግ ካመጣ በኋላ በልጁ ምትክ የሚቃጠል መባ አድርጎ አቀረበው። 14 አብርሃምም ያን ስፍራ ይሖዋ ይርኤ* ብሎ ጠራው። እስከ ዛሬም ድረስ “ይሖዋ በተራራው ላይ የሚያስፈልጉትን ነገሮች ያቀርባል”+ የሚባለው በዚህ የተነሳ ነው።

15 የይሖዋም መልአክ ከሰማይ ለሁለተኛ ጊዜ አብርሃምን ጠራው፤ 16 እንዲህም አለው፦ “ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘በራሴ እምላለሁ፤+ ይህን ስላደረግክ እንዲሁም ልጅህን፣ አንድ ልጅህን ለመስጠት ስላልሳሳህ+ 17 በእርግጥ እባርክሃለሁ፤ ዘርህንም በሰማያት ላይ እንዳሉ ከዋክብትና በባሕር ዳር እንዳለ አሸዋ በእርግጥ አበዛዋለሁ፤+ ዘርህም የጠላቶቹን በር* ይወርሳል።+ 18 ቃሌን ስለሰማህ የምድር ብሔራት ሁሉ በዘርህ+ አማካኝነት ለራሳቸው በረከት ያገኛሉ።’”+

19 ከዚያ በኋላ አብርሃም ወደ አገልጋዮቹ ተመለሰ፤ ተነስተውም አብረው ወደ ቤርሳቤህ+ ተመለሱ፤ አብርሃምም በቤርሳቤህ መኖሩን ቀጠለ።

20 ከዚህ በኋላ ለአብርሃም እንዲህ ተብሎ ተነገረው፦ “ሚልካም ለወንድምህ ለናኮር+ ወንዶች ልጆችን ወልዳለታለች፤ 21 እነሱም የበኩር ልጁ ዑጽ፣ ወንድሙ ቡዝ፣ የአራም አባት የሆነው ቀሙኤል፣ 22 ኬሰድ፣ ሃዞ፣ ፒልዳሽ፣ ይድላፍ እና ባቱኤል+ ናቸው።” 23 ባቱኤልም ርብቃን+ ወለደ። ሚልካ ለአብርሃም ወንድም ለናኮር እነዚህን ስምንቱን ወለደችለት። 24 ቁባቱ የሆነችው ረኡማም ተባህ፣ ጋሃም፣ ታሃሽ እና ማአካ የተባሉ ወንዶች ልጆችን ወለደች።

23 ሣራም 127 ዓመት ኖረች፤ ሣራ በሕይወት የኖረችው ይህን ያህል ዓመት ነበር።+ 2 ሣራም በቂርያትአርባ+ ይኸውም በከነአን ምድር+ በሚገኘው በኬብሮን+ ሞተች፤ አብርሃምም በሣራ ሞት ያዝንና ያለቅስ ጀመር። 3 ከዚያም አብርሃም ከሚስቱ አስከሬን አጠገብ ተነሳ፤ የሄትንም+ ወንዶች ልጆች እንዲህ አላቸው፦ 4 “እኔ በመካከላችሁ የምኖር የባዕድ አገር ሰውና ሰፋሪ ነኝ።+ አስከሬኔን ወስጄ እንድቀብር በመካከላችሁ የመቃብር ቦታ የሚሆን መሬት ስጡኝ።” 5 በዚህ ጊዜ የሄት ወንዶች ልጆች ለአብርሃም እንዲህ ሲሉ መለሱለት፦ 6 “ስማን ጌታዬ። አንተ እኮ በመካከላችን አምላክ የመረጠህ አለቃ* ነህ።+ ካሉን የመቃብር ስፍራዎች ምርጥ በሆነው ቦታ አስከሬንህን መቅበር ትችላለህ። ከእኛ መካከል አስከሬንህን እንዳትቀብር የመቃብር ቦታውን የሚከለክልህ ማንም የለም።”

7 በመሆኑም አብርሃም ተነሳ፤ ለዚያ አገር ሰዎች ይኸውም ለሄት+ ወንዶች ልጆች ሰገደ፤ 8 እንዲህም አላቸው፦ “አስከሬኔን ወስጄ እንድቀብር ከፈቀዳችሁልኝ* አንዴ ስሙኝ፤ የጾሃር ልጅ የሆነውን ኤፍሮንን 9 በእርሻ ቦታው ዳርቻ ላይ የሚገኘውን የእሱ ንብረት የሆነውን የማክፈላ ዋሻ እንዲሸጥልኝ ለምኑልኝ። የመቃብር ስፍራ የሚሆን ርስት+ እንዲኖረኝ ቦታው የሚያወጣውን ብር+ በሙሉ ልስጠውና በእናንተ ፊት ይሽጥልኝ።”

10 ኤፍሮን በሄት ወንዶች ልጆች መካከል ተቀምጦ ነበር። ስለሆነም ሂታዊው ኤፍሮን የሄት ወንዶች ልጆች እየሰሙ በከተማው በር+ በሚገቡት ሰዎች ሁሉ ፊት ለአብርሃም እንዲህ ሲል መለሰለት፦ 11 “የለም ጌታዬ! አዳምጠኝ። የእርሻ ቦታውንም ሆነ በውስጡ ያለውን ዋሻ ሰጥቼሃለሁ። የሕዝቤ ልጆች በተገኙበት ለአንተ ሰጥቼሃለሁ። አስከሬንህን በዚያ ቅበር።” 12 በዚህ ጊዜ አብርሃም በአገሩ ሰዎች ፊት ሰገደ፤ 13 የአገሩ ሰዎችም እየሰሙ ኤፍሮንን እንዲህ አለው፦ “ፈቃድህ ከሆነ ስማኝ! የእርሻ ቦታው የሚያወጣውን ብር በሙሉ እሰጥሃለሁ። አስከሬኔን በዚያ እንድቀብር ብሩን ተቀበለኝ።”

14 ከዚያም ኤፍሮን ለአብርሃም እንዲህ ሲል መለሰ፦ 15 “ጌታዬ እኔ የምልህን ስማኝ። የዚህ መሬት ዋጋ 400 የብር ሰቅል* ነው፤ ታዲያ ይህ በእኔና በአንተ መካከል ያን ያህል ትልቅ ነገር ሆኖ ነው? ይልቁንስ አስከሬንህን በዚያ ቅበር።” 16 አብርሃም፣ ኤፍሮን ያለውን ሰማ፤ አብርሃምም ኤፍሮን በሄት ወንዶች ልጆች ፊት የተናገረውን የብር መጠን ሰጠው፤ በነጋዴዎቹ ዘንድ ተቀባይነት ባለው ሚዛን መሠረት 400 ሰቅል* ብር ለኤፍሮን መዘነለት።+ 17 በዚህ መንገድ በማምሬ ፊት ለፊት የነበረው በማክፈላ የሚገኘው የኤፍሮን የእርሻ ቦታ ይኸውም የእርሻ ቦታው፣ በውስጡ ያለው ዋሻና በእርሻ ቦታው ክልል ውስጥ የሚገኙት ዛፎች በሙሉ 18 አብርሃም የገዛቸው ንብረቶች መሆናቸው የሄት ወንዶች ልጆች በተገኙበት በከተማው በር በሚገቡት ሰዎች ሁሉ ፊት ተረጋገጠ። 19 ከዚያ በኋላ አብርሃም ሚስቱን ሣራን በማምሬ ይኸውም በከነአን ምድር ባለው በኬብሮን ፊት ለፊት በሚገኘው በማክፈላ የእርሻ ቦታ ውስጥ ባለው ዋሻ ቀበራት። 20 በዚህ መንገድ የእርሻ ቦታውና በውስጡ የሚገኘው ዋሻ የመቃብር ቦታ እንዲሆን ከሄት ወንዶች ልጆች ለአብርሃም በርስትነት ተሰጠ።+

24 አብርሃምም አረጀ፤ ዕድሜውም ገፋ፤ ይሖዋም አብርሃምን በሁሉ ነገር ባረከው።+ 2 አብርሃም ንብረቱን በሙሉ የሚያስተዳድርለትንና በቤቱ ውስጥ ካሉት አገልጋዮች ሁሉ አንጋፋ የሆነውን አገልጋዩን+ እንዲህ አለው፦ “እባክህ እጅህን ከጭኔ ሥር አድርግ፤ 3 በመካከላቸው ከምኖረው ከከነአናውያን ሴቶች ልጆች ለልጄ ሚስት እንዳታመጣለት የሰማይና የምድር አምላክ በሆነው በይሖዋ አስምልሃለሁ።+ 4 ከዚህ ይልቅ ወደ አገሬና ወደ ዘመዶቼ+ ሄደህ ለልጄ ለይስሐቅ ሚስት አምጣለት።”

5 ይሁንና አገልጋዩ “ሴቲቱ ከእኔ ጋር ወደዚህ ምድር ለመምጣት ፈቃደኛ ባትሆንስ? ልጅህን አንተ ወደመጣህበት አገር+ መመለስ ይኖርብኛል?” አለው። 6 በዚህ ጊዜ አብርሃም እንዲህ አለው፦ “ልጄን ወደዚያ እንዳትወስደው ተጠንቀቅ።+ 7 ከአባቴ ቤትና ከዘመዶቼ አገር ያወጣኝ+ እንዲሁም ‘ይህን ምድር+ ለዘርህ+ እሰጣለሁ’ ብሎ የነገረኝና የማለልኝ+ የሰማይ አምላክ ይሖዋ መልአኩን ከፊትህ ይልካል፤+ አንተም ከዚያ አገር+ ለልጄ ሚስት ታመጣለታለህ። 8 ሆኖም ሴቲቱ ከአንተ ጋር ለመምጣት ፈቃደኛ ሳትሆን ብትቀር ከዚህ መሐላ ነፃ ትሆናለህ። ልጄን ግን በምንም ዓይነት ወደዚያ እንዳትወስደው።” 9 ከዚያም አገልጋዩ እጁን ከጌታው ከአብርሃም ጭን ሥር አደረገ፤ ስለዚህ ጉዳይም ማለለት።+

10 በመሆኑም አገልጋዩ ከጌታው ግመሎች መካከል አሥሩን ወሰደ፤ ከጌታውም ንብረት ምርጥ ምርጡን ሁሉ ይዞ ተነሳ። ከዚያም ወደ ሜሶጶጣሚያ፣ ወደ ናኮር ከተማ ጉዞ ጀመረ። 11 ከከተማዋ ውጭ ባለ አንድ የውኃ ጉድጓድ አጠገብም ግመሎቹን አንበረከከ። ጊዜውም ወደ ማምሻው አካባቢ ነበር፤ ይህ ጊዜ ደግሞ ሴቶች ውኃ ለመቅዳት የሚወጡበት ነው። 12 ከዚያም እንዲህ አለ፦ “የጌታዬ የአብርሃም አምላክ ይሖዋ፣ እባክህ በዚህ ዕለት ጉዳዬን አሳካልኝ፤ ለጌታዬ ለአብርሃምም ታማኝ ፍቅርህን አሳየው። 13 ይኸው እኔ እዚህ የውኃ ምንጭ አጠገብ ቆሜአለሁ፤ የከተማዋ ሴቶች ልጆች ውኃ ለመቅዳት እየመጡ ነው። 14 እንግዲህ ‘እባክሽ፣ ውኃ እንድጠጣ እንስራሽን አውርጂልኝ’ ስላት ‘እንካ ጠጣ፤ ግመሎችህንም አጠጣልሃለሁ’ የምትለኝ ወጣት ለአገልጋይህ ለይስሐቅ የመረጥካት ትሁን፤ እንዲህ ካደረግክልኝ ለጌታዬ ታማኝ ፍቅር እንዳሳየኸው አውቃለሁ።”

15 እሱም ገና ንግግሩን ሳይጨርስ የባቱኤል+ ልጅ ርብቃ እንስራዋን በትከሻዋ ተሸክማ ብቅ አለች፤ ባቱኤል የአብርሃም ወንድም የናኮር+ ሚስት ሚልካ+ የወለደችው ነው። 16 ወጣቷም በጣም ቆንጆና ከወንድ ጋር የፆታ ግንኙነት ፈጽማ የማታውቅ ድንግል ነበረች። እሷም ወደ ምንጩ ወርዳ በእንስራዋ ውኃ ሞልታ ተመለሰች። 17 አገልጋዩም ወዲያውኑ ወደ እሷ ሮጦ በመሄድ “እባክሽ ከእንስራሽ ውኃ ልጎንጭ” አላት። 18 እሷም መልሳ “ጌታዬ ጠጣ” አለችው። ከዚያም ፈጠን ብላ እንስራዋን ወደ እጇ በማውረድ የሚጠጣው ውኃ ሰጠችው። 19 ለእሱ ሰጥታው ከጠጣ በኋላ “ግመሎችህም ጠጥተው እስኪጠግቡ ድረስ ውኃ እቀዳላቸዋለሁ” አለችው። 20 በእንስራዋ ውስጥ የነበረውን ውኃም በፍጥነት ገንዳ ውስጥ ገለበጠች፤ ከዚያም በሩጫ እየተመላለሰች ከጉድጓዱ ውኃ ትቀዳ ጀመር፤ ለግመሎቹም ሁሉ ቀዳች። 21 ይህ ሁሉ ሲሆን ሰውየው ይሖዋ ጉዞውን አሳክቶለት እንደሆነና እንዳልሆነ በማሰብ ዝም ብሎ በመገረም ይመለከታት ነበር።

22 ግመሎቹም ጠጥተው ሲጨርሱ ሰውየው ግማሽ ሰቅል* የሚመዝን የወርቅ የአፍንጫ ቀለበት እንዲሁም አሥር ሰቅል* የሚመዝኑ ሁለት የወርቅ አምባሮች አውጥቶ ሰጣት፤ 23 እንዲህም አላት፦ “እስቲ ንገሪኝ፣ ለመሆኑ የማን ልጅ ነሽ? በአባትሽ ቤት የምናድርበት ቦታ ይኖር ይሆን?” 24 እሷም መልሳ “ሚልካ ለናኮር+ የወለደችለት የባቱኤል ልጅ ነኝ”+ አለችው። 25 አክላም “ገለባና ብዙ ገፈራ እንዲሁም ለማደሪያ የሚሆን ስፍራ አለን” አለችው። 26 በዚህ ጊዜ ሰውየው በይሖዋ ፊት ተደፍቶ ሰገደ፤ 27 እንዲህም አለ፦ “ለጌታዬ ታማኝ ፍቅሩንና ታማኝነቱን ያልነፈገው የጌታዬ የአብርሃም አምላክ ይወደስ። ይሖዋ ወደ ጌታዬ ወንድሞች ቤት መራኝ።”

28 ወጣቷም የሆነውን ሁሉ ለእናቷ ቤተሰቦች ለመንገር እየሮጠች ሄደች። 29 ርብቃ፣ ላባ+ የሚባል ወንድም ነበራት። ላባም ከከተማዋ ውጭ በምንጩ አጠገብ ወዳለው ሰው እየሮጠ ሄደ። 30 የአፍንጫ ቀለበቱንና አምባሮቹን በእህቱ እጆች ላይ ሲመለከት እንዲሁም እህቱ ርብቃ “ሰውየው እንዲህ እንዲህ አለኝ” ብላ ስትናገር ሲሰማ በምንጩ አጠገብ ከግመሎቹ ጋር ቆሞ የነበረውን ሰው ለማግኘት ወደ እሱ ሄደ። 31 እሱም ሰውየውን እንዳገኘው “አንተ ይሖዋ የባረከህ ሰው፣ ና እንጂ። ውጭ የቆምከው ለምንድን ነው? ቤቱን አዘጋጅቻለሁ፤ ለግመሎቹም ማደሪያ አለ” አለው። 32 ስለዚህ ሰውየው ወደ ቤት ገባ፤ እሱም* የግመሎቹን ጭነት አራገፈለት፤ ለግመሎቹም ገለባና ገፈራ ሰጣቸው። እንዲሁም ሰውየውና አብረውት የነበሩት ሰዎች እግራቸውን የሚታጠቡበት ውኃ አቀረበላቸው። 33 ሆኖም ሰውየው የሚበላ ነገር ሲቀርብለት “የመጣሁበትን ጉዳይ ሳልናገር እህል አልቀምስም” አለ። በመሆኑም ላባ “እሺ፣ ተናገር!” አለው።

34 እሱም እንዲህ አለ፦ “እኔ የአብርሃም አገልጋይ ነኝ።+ 35 ይሖዋ ጌታዬን እጅግ ባርኮታል፤ በጎች፣ ከብቶች፣ ብር፣ ወርቅ፣ ወንድና ሴት አገልጋዮች እንዲሁም ግመሎችና አህዮች በመስጠት በጣም አበልጽጎታል።+ 36 በተጨማሪም የጌታዬ ሚስት ሣራ በስተርጅናዋ ለጌታዬ ወንድ ልጅ ወልዳለታለች፤+ ጌታዬም ያለውን ሁሉ ለእሱ ይሰጠዋል።+ 37 በመሆኑም ጌታዬ እንዲህ በማለት አስማለኝ፦ ‘በአገራቸው ከምኖረው ከከነአናውያን ሴቶች ልጆች መካከል ለልጄ ሚስት እንዳታመጣለት።+ 38 ፈጽሞ እንዲህ እንዳታደርግ፤ ከዚህ ይልቅ ወደ አባቴ ቤትና ወደ ቤተሰቦቼ+ ሄደህ ለልጄ ሚስት አምጣለት።’+ 39 እኔ ግን ጌታዬን ‘ሴቲቱ ከእኔ ጋር ለመምጣት ፈቃደኛ ባትሆንስ?’ አልኩት።+ 40 እሱም እንዲህ አለኝ፦ ‘አካሄዴን በፊቱ ያደረግኩት+ ይሖዋ መልአኩን ከአንተ ጋር ይልካል፤+ ጉዞህን ያሳካልሃል፤ አንተም ከቤተሰቦቼና ከአባቴ ቤት+ ለልጄ ሚስት ታመጣለታለህ። 41 ወደ ቤተሰቦቼ ከሄድክና እነሱም ልጅቷን ለመስጠት ፈቃደኛ ካልሆኑ ከማልክልኝ መሐላ ነፃ ትሆናለህ። እንዲህ ካደረግክ ከመሐላህ ነፃ ትሆናለህ።’+

42 “እኔም ዛሬ ምንጩ አጠገብ ስደርስ እንዲህ አልኩ፦ ‘የጌታዬ የአብርሃም አምላክ ይሖዋ፣ ጉዞዬን የምታሳካልኝ ከሆነ 43 ይኸው እዚህ የውኃ ምንጭ አጠገብ ቆሜአለሁ። አንዲት ወጣት ሴት+ ውኃ ለመቅዳት ስትመጣ “እባክሽ፣ ከእንስራሽ ትንሽ ውኃ አጠጪኝ” እላታለሁ፤ 44 እሷም “አንተም ጠጣ፤ ለግመሎችህም እቀዳላቸዋለሁ” ካለችኝ ይህች ሴት ይሖዋ ለጌታዬ ልጅ የመረጣት ትሁን።’+

45 “እኔም ገና በልቤ ተናግሬ ሳልጨርስ ርብቃ እንስራዋን በትከሻዋ ተሸክማ ብቅ አለች፤ እሷም ወደ ምንጩ ወርዳ ውኃ ቀዳች። ከዚያም እኔ ‘እባክሽ፣ ውኃ አጠጪኝ’ አልኳት።+ 46 እሷም ፈጠን ብላ እንስራዋን ከትከሻዋ በማውረድ ‘ጠጣ፤+ ግመሎችህንም አጠጣልሃለሁ’ አለችኝ። እኔም ጠጣሁ፤ ግመሎቹንም አጠጣች። 47 ከዚያም ‘ለመሆኑ የማን ልጅ ነሽ?’ ስል ጠየቅኳት፤ እሷም ‘ሚልካ ለናኮር የወለደችለት የባቱኤል ልጅ ነኝ’ አለችኝ። ስለዚህ ቀለበቱን በአፍንጫዋ ላይ፣ አምባሮቹን ደግሞ በእጆቿ ላይ አደረግኩላት።+ 48 እኔም በይሖዋ ፊት ተደፍቼ ሰገድኩ፤ የጌታዬን ወንድም ሴት ልጅ ለጌታዬ ልጅ እንድወስድለት በትክክለኛው መንገድ የመራኝን የጌታዬን የአብርሃምን አምላክ ይሖዋን አወደስኩ።+ 49 እንግዲህ አሁን ለጌታዬ ታማኝ ፍቅርና ታማኝነት ማሳየት የምትፈልጉ ከሆነ ንገሩኝ፤ ካልሆነ ግን ማድረግ ያለብኝን ነገር እንድወስን* ቁርጡን አሳውቁኝ።”+

50 ከዚያም ላባና ባቱኤል እንዲህ ሲሉ መለሱለት፦ “ይህ ነገር ከይሖዋ የመጣ ነው። እኛ እሺም ሆነ እንቢ ልንልህ አንችልም።* 51 ርብቃ ይቻትልህ። ይዘሃት ሂድ፤ ልክ ይሖዋ እንደተናገረውም ለጌታህ ልጅ ሚስት ትሁን።” 52 የአብርሃም አገልጋይም ያሉትን ሲሰማ ወዲያውኑ በይሖዋ ፊት መሬት ላይ ተደፍቶ ሰገደ። 53  ከዚያም አገልጋዩ የብርና የወርቅ ጌጣጌጦችን እንዲሁም ልብሶችን እያወጣ ለርብቃ ይሰጣት ጀመር፤ ለወንድሟና ለእናቷም ውድ የሆኑ ዕቃዎችን ሰጣቸው። 54 ከዚህ በኋላ እሱና ከእሱ ጋር ያሉት ሰዎች በሉ፣ ጠጡም፤ እዚያም አደሩ።

እሱም ጠዋት ሲነሳ “በሉ እንግዲህ ወደ ጌታዬ እንድንሄድ አሰናብቱን” አላቸው። 55 በዚህ ጊዜ ወንድሟና እናቷ “ልጅቷ ከእኛ ጋር ቢያንስ ለአሥር ቀን ትቆይ። ከዚያ በኋላ መሄድ ትችላለች” አሉት። 56 እሱ ግን “ይሖዋ ጉዞዬን እንዳሳካልኝ እያያችሁ አታዘግዩኝ። ወደ ጌታዬ እንድሄድ አሰናብቱኝ” አላቸው። 57  እነሱም “ልጅቷን እንጥራና እንጠይቃት” አሉት። 58 ርብቃን ጠርተውም “ከዚህ ሰው ጋር ትሄጃለሽ?” አሏት። እሷም “አዎ፣ እሄዳለሁ” አለች።

59 ስለዚህ እህታቸውን ርብቃንና+ ሞግዚቷን*+ እንዲሁም የአብርሃምን አገልጋይና አብረውት የነበሩትን ሰዎች አሰናበቷቸው። 60 ርብቃንም “እህታችን ሆይ፣ ሺዎች ጊዜ አሥር ሺህ ሁኚ፤* ዘርሽም የጠላቶቹን በር* ይውረስ”+ ብለው መረቋት። 61 ከዚያም ርብቃና ሴት አገልጋዮቿ ተነሱ፤ በግመሎች ላይ ተቀምጠው ሰውየውን ተከተሉት። አገልጋዩም ርብቃን ይዞ ጉዞውን ቀጠለ።

62 ይስሐቅም በኔጌብ+ ምድር ይኖር ስለነበር ከብኤርላሃይሮዒ+ አቅጣጫ መጣ። 63 ይስሐቅም አመሻሹ ላይ ለማሰላሰል+ ወደ ሜዳ ወጥቶ ነበር። ቀና ብሎ ሲመለከትም ግመሎች ሲመጡ አየ! 64 ርብቃም ቀና ብላ ስትመለከት ይስሐቅን አየችው፤ ከዚያም ከግመሉ ላይ በፍጥነት ወረደች። 65 አገልጋዩንም “ከእኛ ጋር ለመገናኘት ሜዳውን አቋርጦ የሚመጣው ያ ሰው ማን ነው?” ስትል ጠየቀችው። አገልጋዩም “ጌታዬ ነው” አላት። በመሆኑም ዓይነ ርግቧን ወስዳ ራሷን ሸፈነች። 66 አገልጋዩም ያደረገውን ሁሉ ለይስሐቅ ነገረው። 67 ከዚያም ይስሐቅ ርብቃን ወደ እናቱ ወደ ሣራ ድንኳን ይዟት ገባ።+ በዚህ መንገድ ሚስቱ አድርጎ ወሰዳት፤ እሱም ወደዳት፤+ ከእናቱም ሞት ተጽናና።+

25 አብርሃም ኬጡራ የምትባል ሌላ ሚስት አገባ። 2 እሷም ከጊዜ በኋላ ዚምራንን፣ ዮቅሻንን፣ ሚዳንን፣ ምድያምን፣+ ይሽባቅን እና ሹሃን+ ወለደችለት።

3 ዮቅሻንም ሳባን እና ዴዳንን ወለደ።

የዴዳን ወንዶች ልጆች ደግሞ አሹሪም፣ ለጡሺም እና ለኡሚም ነበሩ።

4 የምድያም ወንዶች ልጆች ኤፋ፣ ኤፌር፣ ሃኖክ፣ አቢዳዕ እና ኤልዳዓ ነበሩ።

እነዚህ ሁሉ የኬጡራ ወንዶች ልጆች ነበሩ።

5 በኋላም አብርሃም ያለውን ሁሉ ለይስሐቅ ሰጠው፤+ 6 ከቁባቶቹ ለወለዳቸው ወንዶች ልጆቹ ግን ስጦታ ሰጣቸው። ከዚያም ገና በሕይወት እያለ ከልጁ ከይስሐቅ እንዲርቁ በስተ ምሥራቅ አቅጣጫ ወደ ምሥራቅ ምድር ላካቸው።+ 7 አብርሃም በሕይወት የኖረበት ዘመን 175 ዓመት ነበር። 8 ከዚያም አብርሃም እስትንፋሱ ቀጥ አለ፤ ሸምግሎ፣ በሕይወቱ ረክቶና ዕድሜ ጠግቦ ሞተ፤ ወደ ወገኖቹም ተሰበሰበ።* 9 ልጆቹ ይስሐቅና እስማኤልም የሂታዊው የጾሃር ልጅ በሆነው በኤፍሮን የእርሻ ቦታ ውስጥ ባለው በማምሬ ፊት ለፊት በሚገኘው በማክፈላ ዋሻ ቀበሩት፤+ 10 ይህ የእርሻ ቦታ አብርሃም ከሄት ወንዶች ልጆች የገዛው ነው። አብርሃምም ከሚስቱ ከሣራ ጋር በዚያ ስፍራ ተቀበረ።+ 11 አብርሃም ከሞተ በኋላም አምላክ የአብርሃምን ልጅ ይስሐቅን መባረኩን ቀጠለ፤+ ይስሐቅ በብኤርላሃይሮዒ+ አቅራቢያ ይኖር ነበር።

12 የሣራ አገልጋይ የነበረችው ግብፃዊቷ አጋር+ ለአብርሃም የወለደችለት የአብርሃም ልጅ የእስማኤል+ ታሪክ ይህ ነው።

13 የእስማኤል ወንዶች ልጆች ስም በየስማቸውና በየቤተሰብ የዘር ሐረጋቸው ሲዘረዘር የሚከተለው ነው፦ የእስማኤል የበኩር ልጅ ነባዮት+ ከዚያም ቄዳር፣+ አድበዔል፣ ሚብሳም፣+ 14 ሚሽማ፣ ዱማ፣ ማሳ፣ 15 ሃዳድ፣ ቴማ፣ የጡር፣ ናፊሽ እና ቄድማ። 16 የእስማኤል ወንዶች ልጆች በየመንደራቸውና በየሰፈራቸው* ሲዘረዘሩ ስማቸው ይህ ነው፤ እነሱም በየነገዳቸው 12 የነገድ አለቆች ናቸው።+ 17 እስማኤል 137 ዓመት ኖረ። ከዚያም እስትንፋሱ ቀጥ አለና ሞተ፤ ወደ ወገኖቹም ተሰበሰበ።* 18 እነሱም ከግብፅ አጠገብ በሹር+ አቅራቢያ ከምትገኘው ከሃዊላ+ አንስቶ እስከ አሦር ድረስ ባለው አካባቢ ሰፍረው ነበር። በወንድሞቹም ሁሉ አቅራቢያ ሰፈረ።*+

19 የአብርሃም ልጅ+ የይስሐቅ ታሪክ ይህ ነው።

አብርሃም ይስሐቅን ወለደ። 20 ይስሐቅ በጳዳንአራም የሚኖረውን የአራማዊውን የባቱኤልን ሴት ልጅ+ ማለትም የአራማዊውን የላባን እህት ርብቃን ሲያገባ ዕድሜው 40 ዓመት ነበር። 21 ይስሐቅ ሚስቱ መሃን ስለነበረች ስለ እሷ አዘውትሮ ይሖዋን ይለምን ነበር፤ ይሖዋም ልመናውን ሰማው፤ ሚስቱ ርብቃም ፀነሰች። 22 በሆዷ ውስጥ ያሉት ልጆችም እርስ በርስ ይታገሉ ጀመር፤+ በመሆኑም “እንዲህ ከሆነስ ብሞት ይሻለኛል” አለች። ስለዚህ ይሖዋን ጠየቀች። 23 ይሖዋም እንዲህ አላት፦ “በማህፀንሽ ውስጥ ሁለት ብሔራት አሉ፤+ ከውስጥሽም ሁለት ሕዝቦች ተለያይተው ይወጣሉ።+ አንደኛው ብሔር ከሌላኛው ብሔር ይበረታል፤+ ታላቁም ታናሹን ያገለግላል።”+

24 የመውለጃዋም ጊዜ ሲደርስ በማህፀኗ ውስጥ መንታ ልጆች ነበሩ። 25 መጀመሪያ የወጣው መልኩ ቀይ ሲሆን ፀጉራም ካባ የለበሰ ይመስል ሰውነቱ በሙሉ በፀጉር የተሸፈነ ነበር፤+ በመሆኑም ስሙን ኤሳው*+ አሉት። 26 ከዚያም ወንድሙ ወጣ፤ በእጁም የኤሳውን ተረከዝ ይዞ ነበር፤+ በዚህም የተነሳ ስሙን ያዕቆብ* አለው።+ ርብቃ እነሱን ስትወልድ ይስሐቅ 60 ዓመቱ ነበር።

27 ልጆቹም እያደጉ ሲሄዱ ኤሳው ውጭ መዋል የሚወድ የተዋጣለት አዳኝ ሆነ፤+ ያዕቆብ ግን አብዛኛውን ጊዜውን በድንኳን የሚያሳልፍ+ ነቀፋ የሌለበት ሰው ነበር። 28 ይስሐቅ ኤሳውን ይወደው ነበር፤ ምክንያቱም እያደነ ያበላው ነበር፤ ርብቃ ግን ያዕቆብን ትወደው ነበር።+ 29 አንድ ቀን ኤሳው ውጭ ውሎ በጣም ደክሞት ሲመጣ ያዕቆብ ወጥ እየሠራ ነበር። 30 በመሆኑም ኤሳው ያዕቆብን “ቶሎ በል እባክህ፣ በጣም ስለደከመኝ* ከዚያ ከቀዩ ወጥ የተወሰነ* ስጠኝ!” አለው። ስሙ ኤዶም*+ የተባለውም በዚህ የተነሳ ነው። 31 በዚህ ጊዜ ያዕቆብ “በመጀመሪያ የብኩርና መብትህን+ ሽጥልኝ!” አለው። 32 ኤሳውም “እኔ ለራሴ ልሞት ደርሻለሁ! ታዲያ የብኩርና መብት ምን ይጠቅመኛል?” አለው። 33 ያዕቆብም “በመጀመሪያ ማልልኝ!” አለው። እሱም ማለለት፤ የብኩርና መብቱንም ለያዕቆብ ሸጠለት።+ 34 ከዚያም ያዕቆብ ለኤሳው ዳቦና ምስር ወጥ ሰጠው፤ እሱም በላ፣ ጠጣም፤ ተነሥቶም ሄደ። በዚህ መንገድ ኤሳው የብኩርና መብቱን አቃለለ።

26 በአብርሃም ዘመን ከተከሰተው ከመጀመሪያው ረሃብ+ ሌላ በምድሪቱ ላይ ረሃብ ተከሰተ፤ ስለዚህ ይስሐቅ በጌራራ ወደሚገኘው ወደ ፍልስጤማውያን ንጉሥ ወደ አቢሜሌክ ሄደ። 2 ከዚያም ይሖዋ ተገለጠለትና እንዲህ አለው፦ “ወደ ግብፅ አትውረድ። እኔ በማሳይህ ምድር ተቀመጥ። 3 በዚህ ምድር እንደ ባዕድ አገር ሰው ሆነህ ተቀመጥ፤+ እኔም ከአንተ ጋር መሆኔን እቀጥላለሁ፤ እንዲሁም እባርክሃለሁ። ምክንያቱም ይህችን ምድር በሙሉ ለአንተና ለዘሮችህ እሰጣለሁ፤+ ደግሞም ለአባትህ ለአብርሃም እንዲህ ስል የማልሁለትን መሐላ እፈጽማለሁ፦+ 4 ‘ዘርህን በሰማያት ላይ እንዳሉ ከዋክብት አበዛዋለሁ፤+ ይህችንም ምድር በሙሉ ለዘርህ እሰጣለሁ፤+ የምድርም ብሔራት ሁሉ በዘርህ አማካኝነት ለራሳቸው በረከት ያገኛሉ።’+ 5 ይህን የማደርገውም አብርሃም ቃሌን ስለሰማ እንዲሁም ሥርዓቶቼን፣ ትእዛዛቴን፣ ደንቦቼንና ሕጎቼን ጠብቆ ስለኖረ ነው።”+ 6 በመሆኑም ይስሐቅ በጌራራ መኖሩን ቀጠለ።+

7 የዚያ አገር ሰዎች ስለ ሚስቱ በተደጋጋሚ ሲጠይቁት “እህቴ ናት” ይላቸው ነበር።+ “የዚህ አገር ሰዎች በርብቃ የተነሳ ሊገድሉኝ ይችላሉ” ብሎ ስላሰበ “ሚስቴ ናት” ለማለት ፈርቶ ነበር፤ ምክንያቱም ርብቃ ቆንጆ ነበረች።+ 8 ከተወሰነ ጊዜ በኋላም የፍልስጤማውያን ንጉሥ አቢሜሌክ በመስኮት ወደ ውጭ ሲመለከት ይስሐቅ ለሚስቱ ለርብቃ ፍቅሩን ሲገልጽላት*+ አየ። 9 አቢሜሌክም ወዲያው ይስሐቅን ጠርቶ “መቼም እሷ ሚስትህ እንደሆነች ግልጽ ነው! ታዲያ ‘እህቴ ናት’ ያልከው ለምንድን ነው?” አለው። በዚህ ጊዜ ይስሐቅ “እንዲህ ያልኩት በእሷ የተነሳ ሕይወቴን እንዳላጣ ስለፈራሁ ነው” አለው።+ 10 አቢሜሌክ ግን “እንዴት እንዲህ ያለ ነገር ታደርግብናለህ?+ ከእኛ ሰዎች አንዱ ከሚስትህ ጋር ሊተኛ ይችል ነበር፤ እኛንም በደለኞች አድርገህ ታስቆጥረን ነበር!”+ አለው። 11 ከዚያም አቢሜሌክ “ይህን ሰውም ሆነ ሚስቱን የነካ ማንኛውም ሰው ያለምንም ጥርጥር ይገደላል!” በማለት ለሕዝቡ ሁሉ ትእዛዝ አስተላለፈ።

12 ይስሐቅም በዚያ ምድር ዘር መዝራት ጀመረ፤ ይሖዋም ስለባረከው በዚያ ዓመት፣ የዘራውን 100 እጥፍ አመረተ።+ 13 ሰውየውም ባለጸጋ ሆነ፤ እጅግ ባለጸጋ እስኪሆንም ድረስ በሀብት ላይ ሀብት እየጨመረ ሄደ። 14 የበግና የከብት መንጋው በዛለት፤ አገልጋዮቹም ብዙ ሆኑ፤+ ፍልስጤማውያንም ይቀኑበት ጀመር።

15 በመሆኑም ፍልስጤማውያን የአባቱ አገልጋዮች በአብርሃም ዘመን የቆፈሯቸውን የውኃ ጉድጓዶች+ በሙሉ አፈር በመሙላት ደፈኗቸው። 16 ከዚያም አቢሜሌክ ይስሐቅን “ከእኛ ይልቅ እየበረታህ ስለመጣህ አካባቢያችንን ለቅቀህ ሂድልን” አለው። 17 በመሆኑም ይስሐቅ ከዚያ ተነስቶ በመሄድ በጌራራ+ ሸለቆ* ሰፈረ፤ በዚያም መኖር ጀመረ። 18 ይስሐቅም በአባቱ በአብርሃም ዘመን ተቆፍረው የነበሩትንና አብርሃም ከሞተ በኋላ ፍልስጤማውያን የደፈኗቸውን የውኃ ጉድጓዶች እንደገና ቆፈረ፤+ ቀደም ሲል አባቱ ባወጣላቸው ስምም ጠራቸው።+

19 የይስሐቅ አገልጋዮችም በሸለቆው ውስጥ* ሲቆፍሩ ለመጠጥ የሚሆን ውኃ ያለበት አንድ ጉድጓድ አገኙ። 20 የጌራራ እረኞች “ውኃው የእኛ ነው!” በማለት ከይስሐቅ እረኞች ጋር ጠብ አነሱ። ከእሱ ጋር ስለተጣሉም የውኃ ጉድጓዱን ስም ኤሴቅ* አለው። 21 እነሱም ሌላ የውኃ ጉድጓድ ቆፈሩ፤ በዚህም ጉድጓድ ጠብ አነሱ። በመሆኑም የጉድጓዱን ስም ሲጥና* አለው። 22 ከዚያም ያን ቦታ ትቶ በመሄድ ሌላ የውኃ ጉድጓድ ቆፈረ፤ እነሱም በዚህ ጉድጓድ ጠብ አላነሱበትም። በመሆኑም “አሁን ይሖዋ ሰፊ ቦታ ሰጥቶናል፤ በምድርም ላይ እንድንበዛ አድርጎናል”+ በማለት የጉድጓዱን ስም ረሆቦት* አለው።

23 በኋላም ከዚያ ተነስቶ ወደ ቤርሳቤህ+ ወጣ። 24 ይሖዋም በዚያ ሌሊት ተገለጠለትና እንዲህ አለው፦ “እኔ የአባትህ የአብርሃም አምላክ ነኝ።+ እኔ ከአንተ ጋር ስለሆንኩ አትፍራ፤+ ስለ አገልጋዬ ስለ አብርሃም ስል እባርክሃለሁ እንዲሁም ዘርህን አበዛዋለሁ።”+ 25 በመሆኑም በዚያ መሠዊያ ሠራ፤ የይሖዋንም ስም ጠራ።+ እንዲሁም ይስሐቅ ድንኳኑን በዚያ ተከለ፤+ አገልጋዮቹም በዚያ የውኃ ጉድጓድ ቆፈሩ።

26 ከተወሰነ ጊዜ በኋላ አቢሜሌክ የግል አማካሪው ከሆነው ከአሁዛትና ከሠራዊቱ አዛዥ ከፊኮል+ ጋር በመሆን ከጌራራ ተነስቶ ወደ ይስሐቅ መጣ። 27 በዚህ ጊዜ ይስሐቅ “ጠልታችሁኝ ከአካባቢያችሁ ካባረራችሁኝ በኋላ አሁን ለምን ወደ እኔ መጣችሁ?” አላቸው። 28 እነሱም እንዲህ አሉት፦ “ይሖዋ ከአንተ ጋር እንደሆነ በግልጽ ማየት ችለናል።+ በመሆኑም እንዲህ አልን፦ ‘በእኛና በአንተ መካከል በመሐላ የጸና ስምምነት ይኑር፤ ከአንተም ጋር ቃል ኪዳን እንጋባ።+ 29 በአንተ ላይ ምንም ጉዳት እንዳላደረስንብህ ከዚህ ይልቅ በሰላም በማሰናበት መልካም እንዳደረግንልህ ሁሉ አንተም በእኛ ላይ ምንም መጥፎ ነገር እንደማታደርግብን ማልልን። አንተ አሁን ይሖዋ የባረከህ ሰው ነህ።’” 30 እሱም ግብዣ አዘጋጀላቸው፤ እነሱም በሉ፣ ጠጡም። 31 በማግስቱም በማለዳ ተነስተው እርስ በርሳቸው ተማማሉ።+ ከዚያም ይስሐቅ አሰናበታቸው፤ እነሱም ከእሱ ዘንድ በሰላም ሄዱ።

32 በዚያኑ ዕለት የይስሐቅ አገልጋዮች መጥተው ስለቆፈሩት+ የውኃ ጉድጓድ ነገሩት፤ እነሱም “ውኃ እኮ አገኘን!” አሉት። 33 በመሆኑም የጉድጓዱን ስም ሳቤህ አለው። የከተማዋ ስም እስከ ዛሬ ድረስ ቤርሳቤህ+ ተብሎ የሚጠራው በዚህ የተነሳ ነው።

34 ኤሳው 40 ዓመት ሲሆነው የሂታዊውን የቤኤሪን ልጅ ዮዲትን እንዲሁም የሂታዊውን የኤሎንን ልጅ ባሴማትን አገባ።+ 35 እነሱም ይስሐቅንና ርብቃን ለከፍተኛ ሐዘን ዳረጓቸው።*+

27 ይስሐቅ ባረጀና ዓይኖቹ ደክመው ማየት በተሳናቸው ጊዜ ታላቁን ልጁን ኤሳውን ወደ እሱ ጠርቶ+ “ልጄ ሆይ!” አለው። እሱም “አቤት!” አለው። 2 ይስሐቅም እንዲህ አለው፦ “እንግዲህ አሁን አርጅቻለሁ። የምሞትበትንም ቀን አላውቅም። 3 ስለሆነም አሁን መሣሪያዎችህን፣ የቀስት ኮሮጆህንና ደጋንህን ይዘህ ወደ ዱር ሂድ፤ አድነህም አምጣልኝ።+ 4 እኔ የምወደው ዓይነት ጣፋጭ ምግብ ሠርተህ አቅርብልኝ። ከመሞቴም በፊት እንድባርክህ* ልብላው።”

5 ይሁን እንጂ ይስሐቅ፣ ልጁን ኤሳውን ሲያነጋግረው ርብቃ ታዳምጥ ነበር። ኤሳው አደን አድኖ ለማምጣት ወደ ዱር ወጣ።+ 6 ርብቃም ልጇን ያዕቆብን እንዲህ አለችው፦+ “አባትህ ወንድምህን ኤሳውን እንዲህ ሲለው ሰምቻለሁ፦ 7 ‘እስቲ አደን አድነህ አምጣልኝና ጣፋጭ ምግብ ሥራልኝ። እኔም ሳልሞት በይሖዋ ፊት እንድባርክህ ልብላ።’+ 8 እንግዲህ ልጄ፣ አሁን የምልህን በጥሞና አዳምጥ፤ የማዝህንም አድርግ።+ 9 አባትህ የሚወደው ዓይነት ጣፋጭ ምግብ እንዳዘጋጅለት እባክህ ወደ መንጋው ሂድና ፍርጥም ያሉ ሁለት የፍየል ጠቦቶች አምጣልኝ። 10 ከዚያም ከመሞቱ በፊት እንዲባርክህ ምግቡን ለአባትህ ታቀርብለትና ይበላል።”

11 ያዕቆብ እናቱን ርብቃን እንዲህ አላት፦ “ወንድሜ ኤሳው ሰውነቱ ፀጉራም ነው፤+ የእኔ ሰውነት ግን ለስላሳ ነው። 12 አባቴ ቢዳብሰኝስ?+ በእሱ ላይ እያሾፍኩበት ያለሁ ሊመስል ይችላል፤ ይህ ከሆነ ደግሞ በረከት ሳይሆን እርግማን አተርፋለሁ።” 13 በዚህ ጊዜ እናቱ “ልጄ፣ ለአንተ የታሰበው እርግማን ለእኔ ይሁን። ብቻ እኔ የምልህን አድርግ፤ ሄደህ ጠቦቶቹን አምጣልኝ” አለችው።+ 14 ስለዚህ ሄዶ ጠቦቶቹን አመጣ፤ ለእናቱም ሰጣት፤ እናቱም አባቱ የሚወደው ዓይነት ጣፋጭ ምግብ ሠራች። 15 ከዚያም ርብቃ ቤት ውስጥ ያስቀመጠችውን የታላቁን ልጇን የኤሳውን ምርጥ ልብስ ወስዳ ታናሹን ልጇን ያዕቆብን አለበሰችው።+ 16 በተጨማሪም የፍየል ጠቦቶቹን ቆዳ በእጆቹና ፀጉር በሌለው የአንገቱ ክፍል ላይ አደረገች።+ 17 ከዚያም የሠራችውን ጣፋጭ ምግብና ዳቦ ለልጇ ለያዕቆብ ሰጠችው።+

18 እሱም ወደ አባቱ ገብቶ “አባቴ ሆይ!” አለው። እሱም መልሶ “አቤት! ለመሆኑ አንተ ማነህ ልጄ?” አለው። 19 ያዕቆብም አባቱን “እኔ የበኩር ልጅህ+ ኤሳው ነኝ። ልክ እንዳልከኝ አድርጌአለሁ። እንድትባርከኝ* እባክህ ቀና ብለህ ተቀመጥና አድኜ ካመጣሁት ብላ”+ አለው። 20 በዚህ ጊዜ ይስሐቅ ልጁን “እንዴት እንዲህ ቶሎ ቀናህ ልጄ?” አለው። እሱም መልሶ “አምላክህ ይሖዋ አምጥቶ እጄ ላይ ስለጣለልኝ ነው” አለው። 21 ከዚያም ይስሐቅ ያዕቆብን “ልጄ ሆይ፣ አንተ በእርግጥ ልጄ ኤሳው መሆንህን እንዳውቅ እስቲ ቀረብ በልና ልዳብስህ” አለው።+ 22 በመሆኑም ያዕቆብ ወደ አባቱ ወደ ይስሐቅ ቀረበ። እሱም ዳበሰውና “ድምፁ የያዕቆብ ድምፅ ነው፤ እጆቹ ግን የኤሳው እጆች ናቸው”+ አለ። 23 እጆቹ እንደ ወንድሙ እንደ ኤሳው እጆች ፀጉራም ስለነበሩ ማንነቱን አልለየውም። ስለዚህ ባረከው።+

24 ከዚያም “በእርግጥ አንተ ልጄ ኤሳው ነህ?” ሲል ጠየቀው። እሱም “አዎ፣ ነኝ” አለው። 25 በመቀጠልም “በል እንግዲህ ልጄ፣ አድነህ ያመጣህልኝን እንድበላ አቅርብልኝ፤ ከዚያም እባርክሃለሁ”* አለው። እሱም አቀረበለትና በላ፤ እንዲሁም የወይን ጠጅ አመጣለትና ጠጣ። 26 ከዚያም አባቱ ይስሐቅ “ልጄ፣ እስቲ ቀረብ በልና ሳመኝ”+ አለው። 27 ስለዚህ ወደ እሱ ቀረበና ሳመው፤ ይስሐቅም የልጁን ልብስ ጠረን አሸተተ።+ ከዚያም ባረከው፤ እንዲህም አለው፦

“አቤት፣ የልጄ ጠረን ይሖዋ እንደባረከው መስክ መዓዛ ነው። 28 እውነተኛው አምላክ የሰማያትን ጠል፣+ የምድርን ለም አፈር+ እንዲሁም የተትረፈረፈ እህልና አዲስ የወይን ጠጅ ይስጥህ።+ 29 ሕዝቦች ያገልግሉህ፤ ብሔራትም ይስገዱልህ። የወንድሞችህ ጌታ ሁን፤ የእናትህም ወንዶች ልጆች ይስገዱልህ።+ የሚረግሙህ ሁሉ የተረገሙ ይሁኑ፤ የሚባርኩህም ሁሉ የተባረኩ ይሁኑ።”+

30 ይስሐቅ ያዕቆብን ባርኮ እንዳበቃና ያዕቆብ ከአባቱ ከይስሐቅ ፊት እግሩ እንደወጣ ወንድሙ ኤሳው ከአደን ተመለሰ።+ 31 እሱም ደግሞ ጣፋጭ ምግብ አዘጋጅቶ ለአባቱ አቀረበለት፤ አባቱንም “እስቲ እንድትባርከኝ* አባቴ ይነሳና ልጁ አድኖ ካመጣለት ይብላ” አለው። 32 በዚህ ጊዜ አባቱ ይስሐቅ “አንተ ደግሞ ማን ነህ?” አለው። እሱም መልሶ “ልጅህ ነኛ! የበኩር ልጅህ ኤሳው”+ አለው። 33 ይስሐቅም በኃይል እየተንቀጠቀጠ “አደን አድኖ ያመጣልኝና ያቀረበልኝ ታዲያ ማን ነበር? እኔ እኮ አንተ ከመምጣትህ በፊት በላሁ፤ እንዲሁም ባረክሁት፤ ደግሞም የተባረከ ይሆናል!” አለው።

34 ኤሳው አባቱ የተናገረውን ሲሰማ ከፍ ባለ ድምፅ ምርር ብሎ እያለቀሰ አባቱን “አባቴ ባርከኝ፤ እኔንም ባርከኝ እንጂ!” አለው።+ 35 ይስሐቅ ግን “ወንድምህ ለአንተ የታሰበውን በረከት ለማግኘት አንድ ተንኮል ሠርቷል” አለው። 36 ኤሳውም እንዲህ አለ፦ “ስሙ ያዕቆብ* የተባለው መቼ ያለምክንያት ሆነ! የኔ የሆነውን ሲወስድብኝ ይህ ሁለተኛ ጊዜው ነው።+ የብኩርና መብቴን መውሰዱ+ ሳያንሰው አሁን ደግሞ በረከቴን ቀማኝ!”+ ከዚያም “ለእኔ ምንም በረከት አላስቀረህልኝም?” አለው። 37 ይስሐቅ ግን ኤሳውን እንዲህ አለው፦ “በአንተ ላይ ጌታ አድርጌ ሾሜዋለሁ፤+ እንዲሁም ወንድሞቹን ሁሉ አገልጋዮቹ እንዲሆኑ ሰጥቼዋለሁ። እህልና አዲስ የወይን ጠጅ እንዲበዛለት ባርኬዋለሁ፤+ ታዲያ ለአንተ ላደርግልህ የምችለው ምን የቀረ ነገር አለ ልጄ?”

38 ኤሳውም አባቱን “አባቴ ሆይ፣ ለእኔ የምትሆን አንዲት በረከት እንኳ የለችህም? አባቴ ባርከኝ። እኔንም ባርከኝ እንጂ!” አለው። ኤሳውም ከፍ ባለ ድምፅ ምርር ብሎ አለቀሰ።+ 39 ስለዚህ አባቱ ይስሐቅ እንዲህ አለው፦

“እንግዲህ መኖሪያህ ለም ከሆነው የምድር አፈር እንዲሁም በላይ ካሉት ሰማያት ጠል የራቀ ይሆናል።+ 40 በሰይፍህ ትኖራለህ፤+ ወንድምህንም ታገለግላለህ።+ ይሁንና እየተቅበጠበጥክ ባስቸገርክ ጊዜ ቀንበሩን ከጫንቃህ ላይ ሰብረህ ትጥላለህ።”+

41 ይሁን እንጂ ኤሳው አባቱ ያዕቆብን ስለባረከው ለያዕቆብ ከፍተኛ ጥላቻ አደረበት።+ ኤሳውም በልቡ “ለአባቴ ሐዘን የምንቀመጥበት ቀን ሩቅ አይደለም።+ ከዚያ በኋላ ወንድሜን ያዕቆብን እገድለዋለሁ” ይል ነበር። 42 ርብቃ ታላቁ ልጇ ኤሳው ያለው ነገር ሲነገራት ወዲያውኑ ለታናሹ ልጇ ለያዕቆብ እንዲህ የሚል መልእክት ላከችበት፦ “ወንድምህ ኤሳው አንተን በመግደል ሊበቀልህ እያሰበ ነው።* 43 እንግዲህ ልጄ እኔ የምልህን አድርግ። ተነስተህ በካራን ወደሚገኘው ወደ ወንድሜ ወደ ላባ ሽሽ።+ 44 የወንድምህ ቁጣ እስኪበርድ ድረስ ለተወሰነ ጊዜ እሱ ጋ ተቀመጥ፤ 45 ወንድምህ ንዴቱ እስኪበርድለትና ያደረግክበትን እስኪረሳ ድረስ እዚያ ቆይ። እኔም እልክብህና አስጠራሃለሁ። ሁለታችሁንም በአንድ ቀን ለምን ልጣ?”

46 ከዚያ በኋላ ርብቃ ይስሐቅን እንዲህ ትለው ጀመር፦ “በሄት ሴቶች ልጆች የተነሳ ሕይወቴን ጠልቻለሁ።+ ያዕቆብም በዚህ አገር የሚገኙትን እንደነዚህ ያሉትን የሄት ሴቶች ልጆች የሚያገባ ከሆነ በሕይወት መኖር ለእኔ ምን ያደርግልኛል?”+

28 በመሆኑም ይስሐቅ ያዕቆብን ጠርቶ ባረከውና እንዲህ ሲል አዘዘው፦ “ከከነአን ሴቶች ልጆች ሚስት እንዳታገባ።+ 2 በጳዳንአራም ወደሚገኘው ወደ እናትህ አባት ወደ ባቱኤል ቤት ሂድና ከእናትህ ወንድም ከላባ ሴቶች ልጆች+ መካከል አንዷን አግባ። 3 ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ይባርክሃል፤ ፍሬያማም ያደርግሃል፤ እንዲሁም ያበዛሃል፤ አንተም በእርግጥ ብዙ ሕዝብ ያቀፈ ጉባኤ ትሆናለህ።+ 4 አምላክ ለአብርሃም የሰጠውን፣+ አንተም እንደ ባዕድ አገር ሰው ሆነህ የምትኖርበትን ምድር እንድትወርስ የአብርሃምን በረከት+ ለአንተና ከአንተ ጋር ላለው ዘርህ ይሰጣል።”

5 ስለሆነም ይስሐቅ ያዕቆብን አሰናበተው፤ እሱም የያዕቆብና የኤሳው እናት የርብቃ ወንድም+ እንዲሁም የአራማዊው የባቱኤል ልጅ ወደሆነው ወደ ላባ+ ለመሄድ ወደ ጳዳንአራም ጉዞ ጀመረ።

6 ኤሳው፣ ይስሐቅ ያዕቆብን እንደባረከውና ሚስት እንዲያገባ ወደ ጳዳንአራም እንደላከው እንዲሁም በባረከው ጊዜ “ከከነአን ሴቶች ልጆች ሚስት እንዳታገባ”+ ብሎ እንዳዘዘውና 7 ያዕቆብም አባቱንና እናቱን በመታዘዝ ወደ ጳዳንአራም እንደሄደ አወቀ።+ 8 በዚህ ጊዜ ኤሳው የከነአን ሴቶች ልጆች በአባቱ በይስሐቅ ዘንድ የተጠሉ መሆናቸውን ተገነዘበ፤+ 9 ስለዚህ ኤሳው ወደ እስማኤል ሄደ፤ ካሉትም ሚስቶች በተጨማሪ የአብርሃም ልጅ እስማኤል የወለዳትን የነባዮትን እህት ማሃላትን አገባ።+

10 ያዕቆብ ከቤርሳቤህ ተነስቶ ወደ ካራን አቀና።+ 11 ከዚያም ወደ አንድ ስፍራ ደረሰ፤ ፀሐይ ጠልቃ ስለነበረም እዚያ ለማደር አሰበ። በመሆኑም በአካባቢው ካሉት ድንጋዮች አንዱን አንስቶ በመንተራስ እዚያው ተኛ።+ 12 እሱም ሕልም አለመ፤ በሕልሙም በምድር ላይ የተተከለ ደረጃ* አየ፤ የደረጃውም ጫፍ እስከ ሰማያት ይደርስ ነበር፤ በላዩም ላይ የአምላክ መላእክት ይወጡና ይወርዱ ነበር።+ 13 ከደረጃውም በላይ ይሖዋ ነበር፤ እሱም እንዲህ አለ፦

“እኔ የአባትህ የአብርሃም አምላክና የይስሐቅ አምላክ ይሖዋ ነኝ።+ የተኛህበትን ምድር ለአንተና ለዘርህ እሰጣለሁ።+ 14 ዘርህም በእርግጥ እንደ ምድር አፈር ብዙ ይሆናል፤+ ወደ ምዕራብ፣ ወደ ምሥራቅ፣ ወደ ሰሜንና ወደ ደቡብ ትስፋፋለህ። የምድር ቤተሰቦች ሁሉ በአንተና በዘርህ አማካኝነት በእርግጥ ይባረካሉ።*+ 15 እኔ ከአንተ ጋር ነኝ፤ በምትሄድበት ሁሉ እጠብቅሃለሁ፤ ወደዚህችም ምድር እመልስሃለሁ።+ የገባሁልህን ቃል እስክፈጽምልህ ድረስ አልተውህም።”+

16 ከዚያም ያዕቆብ ከእንቅልፉ ነቅቶ “በእርግጥም በዚህ ስፍራ ይሖዋ አለ፤ እኔ ግን ይህን አላወቅኩም ነበር” አለ። 17 እሱም በፍርሃት ተዋጠ፤ እንዲህም አለ፦ “ይህ ስፍራ እንዴት የሚያስፈራ ነው! ይህ የአምላክ ቤት እንጂ ሌላ ሊሆን አይችልም፤+ ይህ የሰማያት በር ነው።”+ 18 በመሆኑም ያዕቆብ በማለዳ ተነሳ፤ ተንተርሶት የነበረውን ድንጋይ ወስዶ እንደ ዓምድ አቆመው፤ በአናቱም ላይ ዘይት አፈሰሰበት።+ 19 ስለዚህ ያን ቦታ ቤቴል* አለው፤ የከተማዋ የቀድሞ ስም ግን ሎዛ+ ነበር።

20 ከዚያም ያዕቆብ እንዲህ ሲል ስእለት ተሳለ፦ “አምላክ ከእኔ ባይለይና በመንገዴ ቢጠብቀኝ እንዲሁም የምበላው ምግብና የምለብሰው ልብስ ቢሰጠኝ፣ 21 ወደ አባቴም ቤት በሰላም ብመለስ ይሖዋ አምላኬ መሆኑን አስመሠከረ ማለት ነው። 22 እንደ ዓምድ ያቆምኩት ይህ ድንጋይም የአምላክ ቤት ይሆናል፤+ አምላክ ሆይ፣ እኔም ከምትሰጠኝ ከማንኛውም ነገር አንድ አሥረኛውን ለአንተ እሰጣለሁ።”

29 ከዚያ በኋላ ያዕቆብ ጉዞውን ቀጠለ፤ ወደ ምሥራቅ ሰዎች ምድርም ሄደ። 2 እዚያም በሜዳ ላይ አንድ የውኃ ጉድጓድ ተመለከተ፤ እረኞች የበግ መንጎቻቸውን ሁልጊዜ የሚያጠጡት ከዚያ የውኃ ጉድጓድ ስለነበር በአቅራቢያው ሦስት የበግ መንጎች ተኝተው አየ። በጉድጓዱም አፍ ላይ ትልቅ ድንጋይ ነበር። 3 መንጎቹ በሙሉ እዚያ ከተሰበሰቡ በኋላ እረኞቹ በውኃ ጉድጓዱ አፍ ላይ ያለውን ድንጋይ ያንከባልሉና መንጎቹን ያጠጣሉ፤ ከዚያም ድንጋዩን ወደ ቦታው በመመለስ የጉድጓዱን አፍ ይገጥሙታል።

4 ያዕቆብም “ወንድሞቼ፣ ከየት ነው የመጣችሁት?” ብሎ ጠየቃቸው፤ እነሱም “ከካራን+ ነው የመጣነው” አሉት። 5 እሱም “የናኮርን+ የልጅ ልጅ ላባን+ ታውቁታላችሁ?” አላቸው፤ እነሱም “አዎ፣ እናውቀዋለን” አሉት። 6 እሱም “ለመሆኑ ደህና ነው?” አላቸው። እነሱም “አዎ፣ ደህና ነው። እንዲያውም ልጁ ራሔል+ ይኸው በጎች ይዛ እየመጣች ነው!” አሉት። 7 ከዚያም እሱ “እንደምታዩት ገና እኩለ ቀን ነው። አሁን እኮ መንጎች የሚገቡበት ሰዓት አይደለም፤ በጎቹን አጠጧቸውና ወደ ግጦሽ አሰማሯቸው” አላቸው። 8 እነሱም “መንጎቹ ሁሉ ካልተሰባሰቡና እረኞቹ ድንጋዩን ከጉድጓዱ አፍ ላይ ካላንከባለሉት እንዲህ ማድረግ አንችልም፤ በጎቹን ማጠጣት የምንችለው ከዚያ በኋላ ነው” አሉት።

9 እሱም ገና ከእነሱ ጋር እየተነጋገረ ሳለ ራሔል እረኛ ስለነበረች የአባቷን በጎች እየነዳች መጣች። 10 ያዕቆብ የእናቱን ወንድም የላባን ልጅ ራሔልንና የላባን በጎች ሲያይ ወዲያውኑ ወደ ጉድጓዱ ሄዶ ድንጋዩን ከጉድጓዱ አፍ ላይ አንከባለለ፤ የእናቱን ወንድም የላባን በጎችም አጠጣ። 11 ከዚያም ያዕቆብ ራሔልን ሳማት፤ ጮክ ብሎም አለቀሰ። 12 ያዕቆብም ለራሔል የአባቷ ዘመድና* የርብቃ ልጅ መሆኑን ነገራት። እሷም እየሮጠች ሄዳ ለአባቷ ነገረችው።

13 ላባም+ የእህቱ ልጅ ስለሆነው ስለ ያዕቆብ ሲሰማ ወደ እሱ እየሮጠ ሄዶ አቅፎ ሳመው፤ ወደ ቤቱም አስገባው። ያዕቆብም ሁኔታውን ሁሉ ለላባ ነገረው። 14 ላባም “በእርግጥም አንተ የአጥንቴ ፍላጭ የሥጋዬ ቁራጭ* ነህ” አለው። በመሆኑም ያዕቆብ ከእሱ ጋር አንድ ወር ሙሉ ተቀመጠ።

15 ከዚያም ላባ ያዕቆብን “ዘመዴ*+ ስለሆንክ ብቻ እኔን በነፃ ልታገለግለኝ ይገባል? ንገረኝ፣ ደሞዝህ ምንድን ነው?”+ አለው። 16 ላባ ሁለት ሴቶች ልጆች ነበሩት። የታላቋ ስም ሊያ ሲሆን የታናሿ ስም ደግሞ ራሔል ነበር።+ 17 ሊያ ዓይነ ልም* ነበረች፤ ራሔል ግን ዓይን የምትማርክ ውብ ሴት ነበረች። 18 ያዕቆብ ራሔልን ይወዳት ስለነበር “ለታናሿ ልጅህ ለራሔል ስል ሰባት ዓመት ላገለግልህ ፈቃደኛ ነኝ” አለው።+ 19 ላባም “ለሌላ ሰው ከምሰጣት ለአንተ ብሰጥህ ይሻለኛል፤ አብረኸኝ ተቀመጥ” አለው። 20 ያዕቆብም ለራሔል ሲል ሰባት ዓመት አገለገለ፤+ ይሁንና ራሔልን ይወዳት ስለነበር ሰባቱ ዓመታት ለእሱ እንደ ጥቂት ቀናት ነበሩ።

21 ከዚያም ያዕቆብ ላባን “እንግዲህ የተባባልነው ጊዜ ስላበቃ ሚስቴን ስጠኝ፤ ከእሷም ጋር ልተኛ” አለው። 22 ስለዚህ ላባ የአካባቢውን ሰዎች በሙሉ ጠራ፤ ግብዣም አደረገ። 23 ሆኖም ሲመሽ ላባ ልጁን ሊያን ወስዶ ከእሷ ጋር እንዲተኛ ለያዕቆብ ሰጠው። 24 በተጨማሪም ላባ የእሱ አገልጋይ የሆነችውን ዚልጳን አገልጋይዋ እንድትሆን ለልጁ ለሊያ ሰጣት።+ 25 በማግስቱ ጠዋት ያዕቆብ አብራው ያደረችው ሊያ መሆኗን አወቀ! በመሆኑም ያዕቆብ ላባን “ያደረግክብኝ ነገር ምንድን ነው? ያገለገልኩህ ለራሔል ስል አልነበረም? ታዲያ ለምን አታለልከኝ?”+ አለው። 26 ላባም እንዲህ አለው፦ “በአካባቢያችን በኩሯ እያለች ታናሺቱን መዳር የተለመደ አይደለም። 27 ሳምንቱን ከዚህችኛዋ ጋር ተሞሸር። ከዚያም ለምታገለግለኝ ተጨማሪ ሰባት ዓመታት ሌላኛዋን ደግሞ እሰጥሃለሁ።”+ 28 ያዕቆብም እንደተባለው አደረገ፤ ሳምንቱን ከዚህችኛዋ ጋር ተሞሸረ። ከዚያም ላባ ልጁን ራሔልን ሚስት እንድትሆነው ሰጠው። 29 በተጨማሪም ላባ አገልጋዩ የሆነችውን ባላን+ አገልጋይዋ እንድትሆን ለልጁ ለራሔል ሰጣት።+

30 ከዚያም ያዕቆብ ከራሔል ጋር ተኛ፤ ራሔልንም ከሊያ ይልቅ ወደዳት። ላባንም ሌላ ሰባት ዓመት አገለገለው።+ 31 ይሖዋም ሊያ እንዳልተወደደች* ሲመለከት መፀነስ እንድትችል አደረጋት፤*+ ራሔል ግን መሃን ነበረች።+ 32 ሊያም ፀነሰች፤ ወንድ ልጅም ወለደች። እሷም “ይህ የሆነው ይሖዋ መከራዬን ስላየልኝ ነው፤+ ከእንግዲህ ባሌ ይወደኛል” ስትል ስሙን ሮቤል*+ አለችው። 33 ዳግመኛም ፀነሰች፤ ወንድ ልጅም ወለደች። እሷም “ይሖዋ እንዳልተወደድኩ ስለሰማ ይሄኛውንም ልጅ ሰጠኝ” አለች። ስሙንም ስምዖን*+ አለችው። 34 አሁንም ደግሞ ፀነሰች፤ ወንድ ልጅም ወለደች። እሷም “ሦስት ወንዶች ልጆች ስለወለድኩለት አሁን ባሌ ይቀርበኛል” አለች። በዚህም የተነሳ ሌዊ*+ ተባለ። 35 አሁንም እንደገና ፀነሰች፤ ወንድ ልጅም ወለደች። እሷም “አሁን ይሖዋን አወድሰዋለሁ” አለች። ስለሆነም ይሁዳ*+ አለችው። ከዚያ በኋላ መውለድ አቆመች።

30 ራሔል ለያዕቆብ ምንም ልጅ እንዳልወለደችለት ባየች ጊዜ በእህቷ ቀናች፤ ያዕቆብንም “ልጆች ስጠኝ፤ አለዚያ እሞታለሁ” ትለው ጀመር። 2 በዚህ ጊዜ ያዕቆብ ራሔልን በጣም ተቆጥቶ “እኔ፣ እንዳትወልጂ ያደረገሽን* አምላክ መሰልኩሽ እንዴ?” አላት። 3 እሷም በዚህ ጊዜ “ባሪያዬ ባላ+ ይችውልህ፤ ልጆች እንድትወልድልኝና* እኔም በእሷ አማካኝነት ልጆች እንዳገኝ ከእሷ ጋር ግንኙነት ፈጽም” አለችው። 4 በዚህ መሠረት አገልጋይዋን ባላን ሚስት እንድትሆነው ሰጠችው፤ ያዕቆብም ከእሷ ጋር ግንኙነት ፈጸመ።+ 5 ባላም ፀነሰች፤ ከዚያም ለያዕቆብ ወንድ ልጅ ወለደችለት። 6 ራሔልም “አምላክ ዳኛ ሆነልኝ፤ ቃሌንም ሰማ። በመሆኑም ወንድ ልጅ ሰጠኝ” አለች። በዚህም የተነሳ ስሙን ዳን*+ አለችው። 7 የራሔል አገልጋይ ባላ በድጋሚ ፀነሰች፤ ከዚያም ለያዕቆብ ሁለተኛ ወንድ ልጅ ወለደችለት። 8 ራሔልም “ከእህቴ ጋር ብርቱ ትግል ገጠምኩ፤ አሸናፊም ሆንኩ!” አለች። በመሆኑም ስሙን ንፍታሌም*+ አለችው።

9 ሊያ ልጅ መውለድ እንዳቆመች ስትረዳ አገልጋይዋን ዚልጳን ለያዕቆብ ሚስት እንድትሆነው ሰጠችው።+ 10 የሊያም አገልጋይ ዚልጳ ለያዕቆብ ወንድ ልጅ ወለደችለት። 11 ከዚያም ሊያ “ምንኛ መታደል ነው!” አለች። በመሆኑም ስሙን ጋድ*+ አለችው። 12 ከዚያ በኋላ የሊያ አገልጋይ ዚልጳ ለያዕቆብ ሁለተኛ ወንድ ልጅ ወለደችለት። 13 ከዚያም ሊያ “ምንኛ ደስተኛ ነኝ! በእርግጥም ከእንግዲህ ሴቶች ደስተኛ ይሉኛል”+ አለች። በመሆኑም ስሙን አሴር*+ አለችው።

14 የስንዴ መከር በሚሰበሰብበት ወቅት ሮቤል+ ወደ ሜዳ ወጣ፤ ከሜዳውም ላይ ፍሬ* ለቀመ። ለእናቱ ለሊያም አመጣላት። ከዚያም ራሔል ሊያን “እባክሽ፣ ልጅሽ ካመጣው ፍሬ የተወሰነ ስጪኝ” አለቻት። 15 በዚህ ጊዜ ሊያ “ባሌን የወሰድሽብኝ አነሰሽና+ አሁን ደግሞ ልጄ ያመጣውን ፍሬ መውሰድ ትፈልጊያለሽ?” አለቻት። በመሆኑም ራሔል “እሺ፣ ልጅሽ ባመጣው ፍሬ ፋንታ ዛሬ ማታ ከአንቺ ጋር ይደር” አለቻት።

16 ያዕቆብ የዚያን ቀን ምሽት ከእርሻ ሲመለስ ሊያ ወጥታ ተቀበለችውና “ልጄ ባመጣው ፍሬ ስለተከራየሁህ ዛሬ የምትተኛው ከእኔ ጋር ነው” አለችው። ስለሆነም በዚያ ሌሊት ከእሷ ጋር አደረ። 17 አምላክም ሊያን ሰማት፤ መልስም ሰጣት፤ እሷም ፀነሰች፤ ከዚያም ለያዕቆብ አምስተኛ ወንድ ልጅ ወለደችለት። 18 ሊያም “አገልጋዬን ለባሌ ስለሰጠሁ አምላክ ደሞዜን* ከፈለኝ” አለች። በመሆኑም ስሙን ይሳኮር*+ አለችው። 19 ሊያም በድጋሚ ፀነሰች፤ ከዚያም ለያዕቆብ ስድስተኛ ወንድ ልጅ ወለደችለት።+ 20 ሊያም “አምላክ አድሎኛል፤ አዎ፣ መልካም ስጦታ ሰጥቶኛል። ለባሌ ስድስት ወንዶች ልጆች ስለወለድኩለት+ ከእንግዲህ ይታገሠኛል”+ አለች። በመሆኑም ስሙን ዛብሎን*+ አለችው። 21 ከዚያ በኋላ ሴት ልጅ ወለደች፤ ስሟንም ዲና+ አለቻት።

22 በመጨረሻም አምላክ ራሔልን አሰባት፤ ልመናዋንም ሰምቶ መፀነስ እንድትችል በማድረግ* ጸሎቷን መለሰላት።+ 23 እሷም ፀነሰች፤ ወንድ ልጅም ወለደች። ከዚያም “አምላክ ነቀፋዬን አስወገደልኝ!”+ አለች። 24 በመሆኑም “ይሖዋ ሌላ ወንድ ልጅ ጨመረልኝ” በማለት ስሙን ዮሴፍ*+ አለችው።

25 ራሔል ዮሴፍን ከወለደች በኋላ ብዙም ሳይቆይ ያዕቆብ ላባን እንዲህ አለው፦ “ወደ ስፍራዬና ወደ ምድሬ እንድመለስ አሰናብተኝ።+ 26 ለእነሱ ስል ያገለገልኩህን ሚስቶቼንና ልጆቼን ስጠኝና ልሂድ፤ ምን ያህል እንዳገለገልኩህ በሚገባ ታውቃለህ።”+ 27 ከዚያም ላባ “በፊትህ ሞገስ አግኝቼ ከሆነ እባክህ ከእኔ ጋር ተቀመጥ፤ ይሖዋ እየባረከኝ ያለው በአንተ የተነሳ መሆኑን በንግርት* ተረድቻለሁ” አለው። 28 ከዚያም “ደሞዝህን አሳውቀኝና እሰጥሃለሁ”+ አለው። 29 በመሆኑም ያዕቆብ እንዲህ አለው፦ “እንዴት እንዳገለገልኩህና መንጋህም ምን ያህል እየበዛልህ እንዳለ ታውቃለህ፤+ 30 እኔ ከመምጣቴ በፊት የነበረህ ነገር ጥቂት እንደሆነና እኔ ከመጣሁ በኋላ ግን ከብቶችህ በጣም እየበዙ እንደሄዱ፣ ይሖዋም እንደባረከህ ታውቃለህ። ታዲያ ለራሴ ቤት አንድ ነገር የማደርገው መቼ ነው?”+

31 ከዚያም ላባ “ምን እንድሰጥህ ትፈልጋለህ?” አለው። ያዕቆብም እንዲህ አለ፦ “እኔ ምንም ነገር እንድትሰጠኝ አልፈልግም! የምጠይቅህን አንድ ነገር ብቻ የምታደርግልኝ ከሆነ መንጋህን መጠበቄንና መንከባከቤን እቀጥላለሁ።+ 32 ዛሬ በመንጎችህ ሁሉ መካከል እዘዋወራለሁ። አንተም ከመንጋው መካከል ጠቃጠቆ ያለባቸውንና ዥጉርጉር የሆኑትን በጎች ሁሉ፣ ከጠቦቶቹም መካከል ጥቁር ቡናማ የሆኑትን በጎች ሁሉ እንዲሁም ዥጉርጉር የሆኑትንና ጠቃጠቆ ያለባቸውን እንስት ፍየሎች ሁሉ ለይ። ከዚህ በኋላ እንዲህ ዓይነቶቹ የእኔ ደሞዝ ይሆናሉ።+ 33 ወደፊት ደሞዜን ለመመልከት በምትመጣበት ጊዜ ጽድቄ* ስለ እኔ ይናገራል፤ ከእንስት ፍየሎቹ መካከል ጠቃጠቆ የሌለበትና ዥጉርጉር ያልሆነ እንዲሁም ከጠቦቶቹ መካከል ጥቁር ቡናማ ያልሆነ በእኔ ዘንድ ከተገኘ ያ የተሰረቀ እንደሆነ ይቆጠራል።”

34 በዚህ ጊዜ ላባ “ይሄማ ጥሩ ነው! እንዳልከው ይሁን” አለው።+ 35 ከዚያም በዚያኑ ቀን ሽንትር ያለባቸውንና ዥጉርጉር የሆኑትን ተባዕት ፍየሎች ሁሉ፣ ጠቃጠቆ ያለባቸውንና ዥጉርጉር የሆኑትን እንስት ፍየሎች ሁሉ፣ ነጭ የሚባል ነገር ያለበትን ሁሉ እንዲሁም ከጠቦቶቹ መካከል ጥቁር ቡናማ የሆኑትን ሁሉ ለየ፤ እነዚህንም ወንዶች ልጆቹ እንዲጠብቋቸው ሰጣቸው። 36 ከዚህ በኋላ በእሱና በያዕቆብ መካከል የሦስት ቀን መንገድ ያህል ርቀት እንዲኖር አደረገ፤ ያዕቆብም የቀሩትን የላባን መንጎች ይጠብቅ ጀመር።

37 ከዚያም ያዕቆብ ከሊብነህ፣* ከአልሞንድና ከአርሞን* ዛፎች ላይ የተቆረጡ እርጥብ በትሮችን ወሰደ፤ በመቀጠልም በትሮቹን አለፍ አለፍ ብሎ በመላጥና ነጩ እንዲታይ በማድረግ ዥጉርጉር እንዲሆኑ አደረገ። 38 ከዚያም የላጣቸውን በትሮች ወስዶ መንጎቹ ውኃ ለመጠጣት ሲመጡ እንዲያዩአቸው በመንጎቹ ፊት ለፊት በቦዮቹ ማለትም ውኃ በሚጠጡባቸው ገንዳዎች ውስጥ አስቀመጣቸው፤ ይህን ያደረገውም መንጎቹ ውኃ ለመጠጣት ሲመጡ በበትሮቹ ፊት ለስሪያ እንዲነሳሱ ለማድረግ ነው።

39 ስለዚህ መንጎቹ በበትሮቹ ፊት ለስሪያ ይነሳሱ ነበር፤ መንጎቹም ሽንትርና ጠቃጠቆ ያለባቸውን እንዲሁም ዥጉርጉር የሆኑ ግልገሎችን ይወልዱ ነበር። 40 ከዚያም ያዕቆብ ጠቦቶቹን ለየ፤ ከዚያም መንጎቹ በላባ መንጎች መካከል ወዳሉት ሽንትር ወዳለባቸውና ጥቁር ቡናማ ወደሆኑት ሁሉ እንዲመለከቱ አደረገ። ከዚያም የራሱን መንጎች ለየ፤ ከላባ መንጎች ጋር አልቀላቀላቸውም። 41 ያዕቆብም ብርቱ የሆኑት እንስሳት ለስሪያ በተነሳሱ ቁጥር በትሮቹን በመንጎቹ ፊት ለፊት ገንዳዎቹ ውስጥ ያስቀምጣቸው ነበር፤ እንዲህ የሚያደርገው መንጎቹ በበትሮቹ አማካኝነት ለስሪያ እንዲነሳሱ ለማድረግ ነበር። 42 እንስሶቹ ደካማ ሲሆኑ ግን በትሮቹን ገንዳዎቹ ውስጥ አያስቀምጥም ነበር። ስለሆነም ደካማ ደካማዎቹ ለላባ ሲሆኑ ብርቱ ብርቱዎቹ ግን ለያዕቆብ ሆኑ።+

43 በዚህ መንገድ ይህ ሰው እጅግ ባለጸጋ እየሆነ ሄደ፤ የብዙ መንጎች፣ የወንድና የሴት አገልጋዮች፣ የግመሎች እንዲሁም የአህዮች ባለቤት ሆነ።+

31 ከጊዜ በኋላ ያዕቆብ፣ የላባ ልጆች “ያዕቆብ የአባታችንን ንብረት እንዳለ ወስዷል፤ ይህን ሁሉ ሀብት ያካበተው እኮ ከአባታችን ንብረት ነው”+ ሲሉ ሰማ። 2 ያዕቆብ የላባን ፊት ሲመለከት ፊቱ እንደተለወጠበት አስተዋለ።+ 3 በመጨረሻም ይሖዋ ያዕቆብን “ወደ አባቶችህና ወደ ዘመዶችህ አገር ተመለስ፤+ እኔም ከአንተ ጋር እሆናለሁ” አለው። 4 ከዚያም ያዕቆብ ራሔልና ሊያ መንጎቹን ወዳሰማራበት መስክ እንዲመጡ መልእክት ላከባቸው፤ 5 እንዲህም አላቸው፦

“አባታችሁን ሳየው ፊቱ ተለውጦብኛል፤+ የአባቴ አምላክ ግን ከእኔ አልተለየም።+ 6 መቼም አባታችሁን ባለኝ አቅም ሁሉ እንዳገለገልኩት እናንተ ራሳችሁ በሚገባ ታውቃላችሁ።+ 7 አባታችሁ ሊያጭበረብረኝ ሞክሯል፤ ደሞዜንም አሥር ጊዜ ቀያይሮብኛል፤ አምላክ ግን ጉዳት እንዲያደርስብኝ አልፈቀደለትም። 8 ‘ደሞዝህ ዥጉርጉር የሆኑት ይሆናሉ’ ሲለኝ መንጎቹ ሁሉ ዥጉርጉር ወለዱ፤ ‘ደሞዝህ ሽንትር ያለባቸው ይሆናሉ’ ሲለኝ ደግሞ መንጎቹ ሁሉ ሽንትር ያለባቸው ወለዱ።+ 9 ስለዚህ አምላክ የአባታችሁን ከብቶች ከእሱ እየወሰደ ለእኔ ይሰጠኝ ነበር። 10 በአንድ ወቅት፣ መንጎቹ ለስሪያ በሚነሳሱበት ጊዜ እንስቶቹን የሚያጠቁት አውራ ፍየሎች ሽንትር ያለባቸው፣ ዥጉርጉር የሆኑና ጠቃጠቆ ያለባቸው መሆናቸውን በሕልሜ አየሁ።+ 11 ከዚያም የእውነተኛው አምላክ መልአክ በሕልሜ ‘ያዕቆብ!’ ሲል ጠራኝ፤ እኔም ‘አቤት’ አልኩት። 12 እሱም እንዲህ አለኝ፦ ‘እንስቶቹን የሚያጠቁት አውራ ፍየሎች ሁሉ ሽንትር ያለባቸው፣ ዥጉርጉር የሆኑና ጠቃጠቆ ያለባቸው መሆናቸውን እባክህ ቀና ብለህ ተመልከት፤ ምክንያቱም ላባ እየፈጸመብህ ያለውን ነገር ሁሉ ተመልክቻለሁ።+ 13 ዓምድ አቁመህ የቀባህበትና በዚያም ለእኔ ስእለት የተሳልክበት የቤቴል+ እውነተኛው አምላክ እኔ ነኝ።+ በል አሁን ተነስተህ ከዚህ ምድር ውጣ፤ ወደተወለድክበትም ምድር ተመለስ።’”+

14 በዚህ ጊዜ ራሔልና ሊያ እንዲህ ሲሉ መለሱለት፦ “እንደው ለመሆኑ በአባታችን ቤት ልንወርሰው የምንችለው የቀረ ነገር ይኖራል? 15 እሱ እኛን የሸጠንና ለእኛ የተሰጠውን ገንዘብ የበላው እንደ ባዕድ ስለሚያየን አይደለም?+ 16 አምላክ ከአባታችን ላይ የወሰደበት ሀብት ሁሉ የእኛና የልጆቻችን ነው።+ ስለሆነም አምላክ አድርግ ያለህን ነገር ሁሉ አድርግ።”+

17 ከዚያም ያዕቆብ ተነሳ፤ ልጆቹንና ሚስቶቹን ግመል ላይ አስቀመጣቸው፤+ 18 እንዲሁም መንጎቹን ሁሉና ያከማቸውን ንብረት ሁሉ፣+ በጳዳንአራም ሳለ ያገኛቸውንም ከብቶች ሁሉ እየነዳ በከነአን ምድር ወደሚገኘው ወደ አባቱ ወደ ይስሐቅ ለመሄድ ጉዞ ጀመረ።+

19 በዚህ ጊዜ ላባ በጎቹን ለመሸለት ሄዶ ነበር፤ ራሔልም የአባቷን+ የተራፊም ቅርጻ ቅርጾች*+ ሰረቀች። 20 ያዕቆብም ቢሆን ለአራማዊው ለላባ ሳይነግረው ሊኮበልል በመነሳቱ አታሎታል። 21 ያዕቆብም ያለውን ሁሉ ይዞ ኮበለለ፤ ወንዙንም*+ ተሻግሮ ሄደ። ከዚያም ጊልያድ+ ወደተባለው ተራራማ አካባቢ አቀና። 22 በሦስተኛውም ቀን የያዕቆብ መኮብለል ለላባ ተነገረው። 23 በመሆኑም ላባ ያዕቆብ ላይ ለመድረስ ወንድሞቹን* አስከትሎ የሰባት ቀን መንገድ ተጓዘ፤ ከዚያም ጊልያድ በተባለው ተራራማ አካባቢ ደረሰበት። 24 ከዚያም አምላክ ለአራማዊው+ ለላባ ሌሊት በሕልም ተገልጦለት+ “ክፉም ሆነ ደግ ያዕቆብን ስለምትናገረው ነገር ተጠንቀቅ”* አለው።+

25 ያዕቆብ በተራራው ላይ ድንኳኑን ተክሎ ሳለ ላባ ወደ ያዕቆብ ቀረበ፤ ላባም ከወንድሞቹ ጋር ጊልያድ በተባለው ተራራማ አካባቢ ሰፈረ። 26 ከዚያም ላባ ያዕቆብን እንዲህ አለው፦ “ይህ ያደረግከው ነገር ምንድን ነው? እኔን ለማታለል የተነሳሳኸውና ሴት ልጆቼን በሰይፍ እንደተማረከ ምርኮኛ አስገድደህ የወሰድካቸው ለምንድን ነው? 27 ምንም ሳትነግረኝ ተደብቀህ የሸሸኸውና ያታለልከኝስ ለምንድን ነው? ነግረኸኝ ቢሆን ኖሮ በደስታና በዘፈን፣ በአታሞና በበገና እሸኝህ ነበር። 28 አንተ ግን የልጅ ልጆቼንና* ሴቶች ልጆቼን ስሜ እንድሰናበት እንኳ ዕድል አልሰጠኸኝም። የሠራኸው የሞኝነት ሥራ ነው። 29 እናንተን መጉዳት እችል ነበር፤ ሆኖም ትናንት ሌሊት የአባታችሁ አምላክ ‘ክፉም ሆነ ደግ ያዕቆብን ስለምትናገረው ነገር ተጠንቀቅ’ አለኝ።+ 30 እሺ፣ አንተ ለመሄድ የተነሳኸው ወደ አባትህ ቤት ለመመለስ ስለናፈቅክ ነው፤ ሆኖም አማልክቴን+ የሰረቅከው ለምንድን ነው?”

31 ያዕቆብ ለላባ እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “እንዲህ ያደረግኩት ‘ሴቶች ልጆችህን በኃይል ነጥቀህ ታስቀርብኛለህ’ ብዬ ስለፈራሁ ነው። 32 አማልክትህን ያገኘህበት ማንኛውም ሰው ይገደል። በወንድሞቻችን ፊት ንብረቴን ፈትሽና የእኔ ነው የምትለውን ውሰድ።” ይሁንና ያዕቆብ ራሔል ጣዖቶቹን እንደሰረቀች አላወቀም ነበር። 33 በመሆኑም ላባ ወደ ያዕቆብ ድንኳን ገባ፤ ከዚያም ወደ ሊያ ድንኳን እንዲሁም ወደ ሁለቱ ሴት ባሪያዎች+ ድንኳን ገባ፤ ሆኖም ምንም አላገኘም። ከዚያም ከሊያ ድንኳን ወጥቶ ወደ ራሔል ድንኳን ገባ። 34 በዚህ ጊዜ ራሔል የተራፊም ቅርጻ ቅርጾቹን በግመል ኮርቻ ላይ በሚገኘው የሴቶች ዕቃ ማስቀመጫ ውስጥ ከትታ በላያቸው ላይ ተቀምጣ ነበር። በመሆኑም ላባ ድንኳኑን በሙሉ በረበረ፤ ሆኖም ምንም አላገኘም። 35 ከዚያም ራሔል አባቷን “ጌታዬ፣ ስላልተነሳሁልህ አትቆጣ፤ የሴቶች ልማድ+ ደርሶብኝ ነው” አለችው። ስለዚህ ላባ በጥንቃቄ ፈተሸ፤ ይሁንና የተራፊም ቅርጻ ቅርጾቹን+ አላገኘም።

36 በዚህ ጊዜ ያዕቆብ ተቆጣ፤ ላባንም ወቀሰው። ከዚያም ላባን እንዲህ አለው፦ “እስቲ የፈጸምኩት በደል ምንድን ነው? እንደዚህ በቁጣ ገንፍለህ የምታሳድደኝ ምን ኃጢአት ሠርቼ ነው? 37 ይኸው ዕቃዬን ሁሉ ፈትሸሃል፤ ታዲያ የቤትህ ንብረት የሆነ ምን ነገር አገኘህ? እስቲ በወንድሞቼና በወንድሞችህ ፊት አስቀምጠውና እነሱ በሁለታችን መካከል ይፍረዱ። 38 ከአንተ ጋር አብሬ በኖርኩባቸው በእነዚህ 20 ዓመታት ውስጥ በጎችህና ፍየሎችህ ጨንግፈው አያውቁም፤+ እኔም ከመንጋህ መካከል አንዲት በግ እንኳ አልበላሁም። 39 አውሬ የቦጫጨቀውን እንስሳ+ አምጥቼልህ አላውቅም። ኪሳራውን በራሴ ላይ ቆጥሬ እከፍልህ ነበር። በቀንም ይሁን በሌሊት አንድ እንስሳ ቢሰረቅ ታስከፍለኝ ነበር። 40 ቀን በሐሩር፣ ሌሊት ደግሞ በቁር ስሠቃይ ኖሬአለሁ፤ እንቅልፍም በዓይኔ አይዞርም ነበር።+ 41 እንግዲህ 20 ዓመት ሙሉ በቤትህ የኖርኩት በዚህ ሁኔታ ነበር። ለሁለት ሴቶች ልጆችህ ስል 14 ዓመት፣ ለመንጋህ ስል ደግሞ 6 ዓመት አገለገልኩህ። አንተ ግን ደሞዜን አሥር ጊዜ ትቀያይርብኝ ነበር።+ 42 የአባቴ አምላክ፣+ የአብርሃም አምላክና ይስሐቅ የሚፈራው አምላክ*+ ከእኔ ጋር ባይሆን ኖሮ ባዶ እጄን ታሰናብተኝ ነበር። አምላክ ጉስቁልናዬንና ልፋቴን አየ፤ ትናንት ሌሊት የገሠጸህም ለዚህ ነው።”+

43 ከዚያም ላባ ለያዕቆብ እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “ሴቶቹ የገዛ ልጆቼ ናቸው፤ ልጆቹም ቢሆኑ ልጆቼ ናቸው፤ መንጋውም ቢሆን የእኔው መንጋ ነው፤ የምታየው ነገር ሁሉ የእኔና የሴት ልጆቼ ነው። ታዲያ ዛሬ በእነዚህም ሆነ በወለዷቸው ልጆቻቸው ላይ ምን ማድረግ እችላለሁ? 44 በል አሁን ና፣ እኔና አንተ ቃል ኪዳን እንጋባ፤ ይህም በእኔና በአንተ መካከል ምሥክር ሆኖ ያገለግላል።” 45 ስለዚህ ያዕቆብ ድንጋይ ወስዶ እንደ ዓምድ አቆመው።+ 46 ከዚያም ያዕቆብ ወንድሞቹን “ድንጋይ ሰብስቡ!” አላቸው። እነሱም ድንጋይ እያመጡ ከመሩ። በኋላም እዚያው ድንጋዩ ክምር ላይ በሉ። 47 ላባም የድንጋዩን ክምር ያጋርሳሃዱታ* አለው፤ ያዕቆብ ግን ጋልኢድ* ሲል ጠራው።

48 ከዚያም ላባ “ይህ የድንጋይ ክምር ዛሬ በእኔና በአንተ መካከል ምሥክር ነው” አለ። ከዚህም የተነሳ ያዕቆብ ጋልኢድ+ 49 እና መጠበቂያ ግንብ የሚል ስም አወጣለት፤ ምክንያቱም ላባ እንዲህ ብሎ ነበር፦ “እርስ በርስ በማንተያይበት ጊዜ ይሖዋ በእኔና በአንተ መካከል ጠባቂ ይሁን። 50 ልጆቼን ብትበድላቸውና በእነሱ ላይ ሌሎች ሚስቶችን ብታገባ ማንም ሰው ባያይም እንኳ አምላክ በእኔና በአንተ መካከል ምሥክር እንደሆነ አትርሳ።” 51 ላባም ያዕቆብን እንዲህ አለው፦ “የድንጋይ ክምሩ ይኸው፤ በእኔና በአንተ መካከል ያቆምኩት ዓምድም ይኸው። 52 እኔ አንተን ለመጉዳት ይህን የድንጋይ ክምር አልፌ ላልመጣ፣ አንተም እኔን ለመጉዳት ይህን የድንጋይ ክምርና ይህን ዓምድ አልፈህ ላትመጣ ይህ የድንጋይ ክምር ምሥክር ነው፤+ ዓምዱም ቢሆን ምሥክር ይሆናል። 53  የአብርሃም አምላክና*+ የናኮር አምላክ የሆነው የአባታቸው አምላክ በእኛ መካከል ይፍረድ።” ያዕቆብም አባቱ ይስሐቅ በሚፈራው አምላክ*+ ማለ።

54 ከዚያ በኋላ ያዕቆብ በተራራው ላይ መሥዋዕት አቀረበ። ወንድሞቹንም ምግብ እንዲበሉ ጋበዛቸው። እነሱም ምግብ በሉ፤ በተራራውም ላይ አደሩ። 55 ላባም በማግስቱ ጠዋት ተነስቶ የልጅ ልጆቹንና*+ ሴቶች ልጆቹን ስሞ መረቃቸው።+ ተነስቶም ወደ ቤቱ ተመለሰ።+

32 ከዚያም ያዕቆብ ጉዞውን ቀጠለ፤ የአምላክ መላእክትም አገኙት። 2 ያዕቆብም ልክ እንዳያቸው “ይህ የአምላክ ሰፈር ነው!” አለ። በመሆኑም የቦታውን ስም ማሃናይም* አለው።

3 ከዚያም ያዕቆብ በኤዶም+ ክልል* ሴይር+ በተባለው ምድር ወደሚኖረው ወንድሙ ወደ ኤሳው መልእክተኞችን አስቀድሞ ላከ፤ 4 እንዲህም ብሎ አዘዛቸው፦ “ጌታዬን ኤሳውን እንዲህ በሉት፦ ‘አገልጋይህ ያዕቆብ እንዲህ ይላል፦ “ከላባ ጋር እስካሁን ድረስ ለረጅም ጊዜ ኖሬአለሁ።*+ 5 አሁን በሬዎች፣ አህዮች፣ በጎች እንዲሁም ወንድና ሴት አገልጋዮች+ አሉኝ፤ ይህን መልእክት ለጌታዬ የላክሁት በፊትህ ሞገስ እንዳገኝ ለመጠየቅ ነው።”’”

6 ከተወሰነ ጊዜ በኋላም መልእክተኞቹ ወደ ያዕቆብ ተመልሰው በመምጣት እንዲህ አሉት፦ “ወንድምህን ኤሳውን አግኝተነው ነበር፤ እሱም ከአንተ ጋር ለመገናኘት ወደዚህ እየመጣ ነው፤ ከእሱም ጋር 400 ሰዎች አሉ።”+ 7 ያዕቆብም እጅግ ፈራ፤ በጭንቀትም ተዋጠ።+ በመሆኑም አብረውት ያሉትን ሰዎች፣ መንጎቹን፣ ከብቶቹንና ግመሎቹን በሁለት ቡድን ከፈላቸው። 8 እሱም “ምናልባት ኤሳው በአንደኛው ቡድን ላይ ጥቃት ቢሰነዝር፣ ሌላኛው ቡድን ሊያመልጥ ይችላል” አለ።

9 ከዚህ በኋላ ያዕቆብ እንዲህ አለ፦ “‘ወደ አገርህና ወደ ዘመዶችህ ተመለስ፤ እኔም መልካም ነገር አደርግልሃለሁ’ ያልከኝ የአባቴ የአብርሃም አምላክና የአባቴ የይስሐቅ አምላክ የሆንከው ይሖዋ ሆይ፣+ 10 እኔ ባሪያህ ይህን ያህል ታማኝ ፍቅርና ታማኝነት ልታሳየኝ+ የሚገባኝ ሰው አልነበርኩም፤ ዮርዳኖስን ስሻገር ከበትር ሌላ ምንም አልነበረኝም፤ አሁን ግን ይኸው ሁለት ቡድን ሆኛለሁ።+ 11 ከወንድሜ ከኤሳው እጅ እንድታድነኝ እለምንሃለሁ፤+ ምክንያቱም መጥቶ በእኔም ሆነ በእነዚህ እናቶችና በልጆቻቸው ላይ ጥቃት እንዳይሰነዝር ፈርቻለሁ።+ 12 አንተው ራስህ ‘በእርግጥ መልካም አደርግልሃለሁ፤ ዘርህንም ከብዛቱ የተነሳ ሊቆጠር እንደማይችል የባሕር አሸዋ አደርገዋለሁ’ ብለኸኛል።”+

13 እሱም በዚያ ሌሊት እዚያው አደረ። ከንብረቱም መካከል የተወሰነውን ወስዶ ለወንድሙ ለኤሳው ስጦታ አዘጋጀ፤+ 14 ስጦታውም የሚከተለው ነበር፦ 200 እንስት ፍየሎች፣ 20 ተባዕት ፍየሎች፣ 200 እንስት በጎች፣ 20 አውራ በጎች 15 እንዲሁም 30 የሚያጠቡ ግመሎች፣ 40 ላሞች፣ 10 በሬዎች፣ 20 እንስት አህዮችና 10 ተባዕት አህዮች።+

16 እሱም በመንጋ በመንጋ ለይቶ ለአገልጋዮቹ ሰጣቸው። አገልጋዮቹንም “ቀድማችሁኝ ተሻገሩ፤ አንዱን መንጋ ከሌላው መንጋ አራርቁት” አላቸው። 17 በተጨማሪም የመጀመሪያውን እንዲህ ሲል አዘዘው፦ “ወንድሜ ኤሳው ቢያገኝህና ‘ለመሆኑ አንተ የማን ነህ? የምትሄደው ወዴት ነው? እነዚህ የምትነዳቸው እንስሳትስ የማን ናቸው?’ ብሎ ቢጠይቅህ፣ 18 ‘የአገልጋይህ የያዕቆብ ናቸው። ይህ ለጌታዬ ለኤሳው የተላከ ስጦታ ነው፤+ እንዲያውም እሱ ራሱ ከኋላችን እየመጣ ነው’ በለው።” 19 እንዲሁም ሁለተኛውን፣ ሦስተኛውንና መንጎቹን የሚነዱትን በሙሉ እንዲህ ሲል አዘዛቸው፦ “ኤሳውን ስታገኙት ይህንኑ ንገሩት። 20 ‘አገልጋይህ ያዕቆብ ከኋላችን እየመጣ ነው’ ማለት እንዳለባችሁም አትዘንጉ።” ይህን ያላቸው ‘ስጦታውን አስቀድሜ በመላክ ቁጣው እንዲበርድለት ካደረግኩ ከእሱ ጋር ስገናኝ በጥሩ ሁኔታ ይቀበለኝ ይሆናል’ ብሎ ስላሰበ ነው።+ 21 በመሆኑም ስጦታው ከእሱ ቀድሞ ተሻገረ፤ እሱ ግን እዚያው የሰፈረበት ቦታ አደረ።

22 በኋላም በዚያው ሌሊት ተነሳ፤ ሁለቱን ሚስቶቹን፣+ ሁለቱን ሴት አገልጋዮቹንና+ 11ዱን ወንዶች ልጆቹን ይዞ በያቦቅ+ መልካ* ተሻገረ። 23 እነሱንም ወስዶ ወንዙን* አሻገራቸው፤ ያለውንም ነገር ሁሉ አሻገረ።

24 በመጨረሻም ያዕቆብ ብቻውን ቀረ። ከዚያም አንድ ሰው ጎህ እስኪቀድ ድረስ ሲታገለው ቆየ።+ 25 ሰውየውም ሊያሸንፈው እንዳልቻለ ሲያይ የጭኑን መጋጠሚያ ነካው፤ ያዕቆብም ከእሱ ጋር በሚታገልበት ጊዜ የጭኑ መጋጠሚያ ከቦታው ተናጋ።+ 26 በኋላም ሰውየው “ጎህ እየቀደደ ስለሆነ ልቀቀኝና ልሂድ” አለው። እሱም “ካልባረክኸኝ አለቅህም” አለው።+ 27 በመሆኑም ሰውየው “ስምህ ማን ነው?” አለው፤ እሱም “ያዕቆብ” ሲል መለሰለት። 28 ሰውየውም “ከእንግዲህ ወዲህ ስምህ እስራኤል* እንጂ ያዕቆብ አይባልም፤+ ምክንያቱም ከአምላክም ሆነ ከሰዎች ጋር ታግለህ+ በመጨረሻ አሸንፈሃል” አለው። 29 ያዕቆብም መልሶ “እባክህ ስምህን ንገረኝ” አለው። እሱ ግን “ስሜን የምትጠይቀኝ ለምንድን ነው?” አለው።+ እንዲህ ካለው በኋላም በዚያ ስፍራ ባረከው። 30 በመሆኑም ያዕቆብ “አምላክን ፊት ለፊት አይቼ እንኳ ሕይወቴ ተርፏል”*+ በማለት የቦታውን ስም ጰኒኤል*+ አለው።

31 ያዕቆብ ጰኑኤልን* እንዳለፈ ፀሐይ ወጣችበት፤ እሱም ጭኑ በመጎዳቱ ምክንያት ያነክስ ነበር።+ 32 የእስራኤል ልጆች እስከ ዛሬ ድረስ በጭን መጋጠሚያ ላይ ያለውን ጅማት የማይበሉት ለዚህ ነው፤ ምክንያቱም ሰውየው በያዕቆብ ጭን መጋጠሚያ ላይ ያለውን ጅማት ነክቶ ነበር።

33 ያዕቆብም ቀና ብሎ ሲመለከት ኤሳው ሲመጣ አየ፤ ከእሱም ጋር 400 ሰዎች ነበሩ።+ በመሆኑም ልጆቹን ለሊያ፣ ለራሔልና ለሁለቱ ሴት አገልጋዮች+ አከፋፈላቸው። 2 እሱም ሴት አገልጋዮቹንና ልጆቻቸውን ከፊት፣+ ሊያንና ልጆቿን ከእነሱ ቀጥሎ፣+ ራሔልንና ዮሴፍን+ ደግሞ ከእነሱ በኋላ እንዲሆኑ አደረገ። 3 ከዚያም እሱ ቀድሟቸው ሄደ፤ ወደ ወንድሙ ሲቀርብም ሰባት ጊዜ ወደ መሬት ዝቅ ብሎ ሰገደ።

4 ሆኖም ኤሳው ወደ እሱ እየሮጠ በመሄድ አንገቱ ላይ ተጠምጥሞ ሳመው፤ ሁለቱም ተላቀሱ። 5 ኤሳውም ቀና ብሎ ሴቶቹንና ልጆቹን ሲያይ እንዲህ አለ፦ “እነዚህ አብረውህ ያሉት እነማን ናቸው?” እሱም “አምላክ በቸርነቱ ለአገልጋይህ የሰጣቸው ልጆች ናቸው”+ አለው። 6 በዚህ ጊዜ ሴት አገልጋዮቹ ከልጆቻቸው ጋር ወደ ፊት ቀርበው ሰገዱ፤ 7 ሊያና ልጆቿም ወደ ፊት ቀርበው ሰገዱ። ከዚያም ዮሴፍና ራሔል ወደ ፊት ቀርበው ሰገዱ።+

8 ኤሳውም “ቀደም ሲል ያገኘኋቸውን ሰዎችና እንስሳት የላክሃቸው ለምንድን ነው?” አለው።+ እሱም “በጌታዬ ፊት ሞገስ ባገኝ ብዬ ነው” አለው።+ 9 ከዚያም ኤሳው “ወንድሜ ሆይ፣ እኔ ከበቂ በላይ አለኝ።+ የአንተ የሆነው ለራስህ ይሁን” አለው። 10 ያዕቆብ ግን እንዲህ አለው፦ “የለም፣ እንዲህማ አይሆንም። በፊትህ ሞገስ አግኝቼ ከሆነ ስጦታዬን ከእጄ መውሰድ አለብህ፤ ምክንያቱም ስጦታውን የላክሁት ፊትህን እንዳይ ብዬ ነው። እንዲህ በደስታ ተቀብለኸኝ የአንተን ፊት ማየቴ ራሱ ለእኔ የአምላክን ፊት የማየት ያህል ነው።+ 11 አምላክ ሞገስ ስላሳየኝና የሚያስፈልገኝ ነገር ሁሉ ስላለኝ+ የመልካም ምኞት መግለጫ እንዲሆን ያመጣሁልህን ይህን ስጦታ እባክህ ተቀበለኝ።”+ ያዕቆብም አጥብቆ ለመነው፤ ስለዚህ ስጦታውን ወሰደ።

12 በኋላም ኤሳው “በል እንነሳና ጉዟችንን እንቀጥል፤ እኔም ከፊት ከፊትህ እሄዳለሁ” አለው። 13 እሱ ግን እንዲህ አለው፦ “ልጆቹ አቅም እንደሌላቸው+ እንዲሁም የሚያጠቡ በጎችና ከብቶች እንዳሉኝ ጌታዬ ያውቃል። እንስሳቱ ለአንድ ቀን እንኳ በጥድፊያ ቢነዱ መንጋው በሙሉ ያልቃል። 14 ስለዚህ ጌታዬ ከአገልጋዩ ቀድሞ ይሂድ፤ እኔ ግን ከጌታዬ ጋር እዚያው ሴይር እስከምንገናኝ+ ድረስ በምነዳቸው ከብቶች ፍጥነትና እንደ ልጆቹ እርምጃ ቀስ እያልኩ ላዝግም።” 15 ኤሳውም “እባክህ ከእኔ ጋር ካሉት ሰዎች መካከል ጥቂቶቹን ልተውልህ” አለው። እሱም “ለምን ብለህ? በጌታዬ ፊት ሞገስ ማግኘቴ ብቻ ይበቃኛል” አለው። 16 በመሆኑም በዚያ ቀን ኤሳው ወደ ሴይር ለመመለስ ጉዞ ጀመረ።

17 ያዕቆብም ወደ ሱኮት+ ሄደ፤ በዚያም ለራሱ ቤት፣ ለመንጎቹም ዳስ ሠራ። የቦታውንም ስም ሱኮት* ያለው ለዚህ ነበር።

18 ያዕቆብ ከጳዳንአራም+ ተነስቶ በመጓዝ በከነአን+ ምድር ወደምትገኘው ወደ ሴኬም+ ከተማ በሰላም ደረሰ፤ በከተማዋም አቅራቢያ ሰፈረ። 19 ከዚያም ድንኳኑን የተከለበትን ቦታ ከሴኬም አባት ከኤሞር ወንዶች ልጆች እጅ በ100 ጥሬ ገንዘብ ገዛ።+ 20 በዚያም መሠዊያ አቆመ፤ መሠዊያውንም አምላክ፣ የእስራኤል አምላክ ብሎ ጠራው።+

34 ያዕቆብ ከሊያ የወለዳት ዲና+ የተባለችው ልጅ እዚያ አገር ካሉ ወጣት ሴቶች ጋር ጊዜ ለማሳለፍ* ትወጣ ነበር።+ 2 የአገሩ አለቃ የሆነው የሂዋዊው+ የኤሞር ልጅ ሴኬም ዲናን አያት፤ ከዚያም ወሰዳትና አብሯት ተኛ፤ አስገድዶም ደፈራት። 3 እሱም ልቡ* በያዕቆብ ልጅ በዲና ተማረከ፤ ወጣቷንም አፈቀራት፤ በሚያባብሉ ቃላትም አነጋገራት።* 4 በመጨረሻም ሴኬም አባቱን ኤሞርን+ “ከዚህች ልጅ ጋር አጋባኝ” አለው።

5 ያዕቆብ፣ ሴኬም ልጁን ዲናን እንዳስነወራት በሰማ ጊዜ ወንዶች ልጆቹ በመስክ መንጎቹን እየጠበቁ ነበር። በመሆኑም ያዕቆብ ልጆቹ እስኪመለሱ ድረስ ዝም አለ። 6 በኋላም የሴኬም አባት ኤሞር ከያዕቆብ ጋር ለመነጋገር ወጣ። 7 ሆኖም የያዕቆብ ወንዶች ልጆች ስለ ሁኔታው ሰሙ፤ ወዲያውኑም ከመስክ መጡ። ሴኬም የያዕቆብን ሴት ልጅ በመድፈር ፈጽሞ መደረግ የማይገባውን ድርጊት ስለፈጸመና+ በዚህም እስራኤልን ስላዋረደ በጣም ተበሳጩ፤ እጅግም ተቆጡ።+

8 ኤሞርም እንዲህ አላቸው፦ “ልጄ ሴኬም ልጃችሁን በጣም ወዷታል።* እባካችሁ ሚስት እንድትሆነው ስጡት፤ 9 በጋብቻም እንዛመድ። ሴቶች ልጆቻችሁን ዳሩልን፤ የእኛንም ሴቶች ልጆች አግቡ።+ 10 አብራችሁንም መኖር ትችላላችሁ፤ አገራችን አገራችሁ ናት። ኑሩባት፤ ነግዱባት፤ ሀብትም አፍሩባት።” 11 ከዚያም ሴኬም አባቷንና ወንድሞቿን እንዲህ አላቸው፦ “በፊታችሁ ሞገስ ላግኝ እንጂ የምትጠይቁኝን ሁሉ እሰጣለሁ። 12 ብዙ ጥሎሽና ስጦታ ልትጠይቁኝ ትችላላችሁ።+ እኔ የጠየቃችሁኝን ሁሉ ለመስጠት ፈቃደኛ ነኝ። ብቻ ይህችን ወጣት ሚስቴ እንድትሆን ስጡኝ።”

13 የያዕቆብ ወንዶች ልጆችም ሴኬም እህታቸውን ዲናን ስላስነወረ ለእሱና ለአባቱ ለኤሞር ተንኮል ያዘለ መልስ ሰጧቸው። 14 እንዲህም አሏቸው፦ “እንዲህ ያለ ነገር ፈጽሞ አናደርግም፤ እህታችንን ላልተገረዘ ሰው አንሰጥም፤+ ምክንያቱም ይህ ለእኛ ውርደት ነው። 15 በሐሳባችሁ የምንስማማው እኛን ከመሰላችሁና የእናንተ የሆነው ወንድ ሁሉ እንዲገረዝ ካደረጋችሁ ብቻ ነው።+ 16 ከዚያም ሴቶች ልጆቻችንን እንድርላችኋለን፤ እኛም ሴቶች ልጆቻችሁን እናገባለን፤ አብረናችሁም እንኖራለን፤ አንድ ሕዝብም እንሆናለን። 17 የምንላችሁን የማትሰሙና ለመገረዝ ፈቃደኛ የማትሆኑ ከሆነ ግን ልጃችንን ይዘን እንሄዳለን።”

18 የተናገሩትም ነገር ኤሞርንና+ ልጁን ሴኬምን+ ደስ አሰኛቸው። 19 ወጣቱም ያሉትን ነገር ለማድረግ ጊዜ አልወሰደበትም፤+ ምክንያቱም የያዕቆብን ልጅ ወዷት ነበር፤ ደግሞም በአባቱ ቤት ካሉት ሰዎች ሁሉ እጅግ የተከበረ ነበር።

20 በመሆኑም ኤሞርና ልጁ ሴኬም ወደ ከተማዋ በር በመሄድ በከተማቸው የሚኖሩትን ወንዶች+ እንዲህ አሏቸው፦ 21 “እነዚህ ሰዎች ከእኛ ጋር በሰላም መኖር ይፈልጋሉ። ምድሪቱ ለእነሱም ስለምትበቃ በምድሪቱ ይኑሩ፤ እንዲሁም ይነግዱ። ሴቶች ልጆቻቸውን ማግባት፣ የእኛንም ሴቶች ልጆች ለእነሱ መዳር እንችላለን።+ 22 ሆኖም ሰዎቹ ከእኛ ጋር አንድ ሕዝብ በመሆን አብረውን ለመኖር የሚስማሙት፣ ልክ እነሱ እንደተገረዙት የእኛ የሆኑ ወንዶች ሁሉ የሚገረዙ ከሆነ ብቻ ነው።+ 23 እንዲህ ብናደርግ ንብረታቸው፣ ሀብታቸውና ከብቶቻቸው ሁሉ የእኛ ሆኑ ማለት አይደለም? በመሆኑም ከእኛ ጋር ለመኖር ባቀረቡት ሐሳብ እንስማማ።” 24 በከተማው በር የሚወጡ ሁሉ ኤሞርና ልጁ ሴኬም ያሏቸውን ሰሙ፤ በከተማዋም በር የሚወጡ ወንዶች በሙሉ ተገረዙ።

25 ሆኖም በሦስተኛው ቀን፣ ሰዎቹ ገና ቆስለው እያሉ የዲና ወንድሞች+ የሆኑት ሁለቱ የያዕቆብ ልጆች ማለትም ስምዖንና ሌዊ ማንም ሳይጠረጥራቸው ሰይፋቸውን ይዘው ወደ ከተማዋ በመግባት ወንዶቹን ሁሉ ገደሉ።+ 26 ኤሞርንና ልጁን ሴኬምን በሰይፍ ገደሏቸው፤ ከዚያም ዲናን ከሴኬም ቤት ይዘው ሄዱ። 27 ሌሎቹ የያዕቆብ ወንዶች ልጆችም በሬሳ ላይ እየተረማመዱ ከተማዋን ዘረፉ፤ ይህን ያደረጉትም እህታቸው ስለተነወረች ነው።+ 28 እነሱም መንጎቻቸውን፣ ከብቶቻቸውን፣ አህዮቻቸውን እንዲሁም በከተማዋ ውስጥና በመስክ ያገኙትን ሁሉ ወሰዱ። 29 በተጨማሪም ንብረቶቻቸውን በሙሉ ወሰዱ፤ እንዲሁም ትናንሽ ልጆቻቸውንና ሚስቶቻቸውን ማረኩ፤ በየቤቱ ያገኙትን ሁሉ ዘረፉ።

30 በዚህ ጊዜ ያዕቆብ፣ ስምዖንንና ሌዊን+ እንዲህ አላቸው፦ “በዚህች አገር በሚኖሩት በከነአናውያንና በፈሪዛውያን ዘንድ እንደ ጥምብ እንድቆጠር በማድረግ ከፍተኛ ችግር ውስጥ ከተታችሁኝ።* እኔ እንግዲህ በቁጥር አነስተኛ ነኝ፤ እነሱም በእኔ ላይ ጥቃት ለመሰንዘር ግንባር ፈጥረው መምጣታቸው አይቀርም፤ በዚህም የተነሳ እኔም ሆንኩ ቤቴ እንጠፋለን።” 31 እነሱ ግን “ታዲያ ማንም እህታችንን እንደ ዝሙት አዳሪ ቆጥሮ እንዲህ ያለ ድርጊት ይፈጽምባት?” አሉ።

35 ከዚያ በኋላ አምላክ ያዕቆብን እንዲህ አለው፦ “ተነስተህ ወደ ቤቴል+ ውጣ፤ በዚያም ኑር፤ ከወንድምህ ከኤሳው እየሸሸህ+ ሳለህ ለተገለጠልህ ለእውነተኛው አምላክ በዚያ መሠዊያ ሥራ።”

2 ከዚያም ያዕቆብ ቤተሰቡንና አብረውት የነበሩትን ሰዎች ሁሉ እንዲህ አላቸው፦ “በመካከላችሁ ያሉትን ባዕዳን አማልክት አስወግዱ፤+ ራሳችሁን አንጹ፤ ልብሳችሁንም ቀይሩ፤ 3 ተነስተንም ወደ ቤቴል እንውጣ። በዚያም በጭንቀቴ ጊዜ ለሰማኝና በሄድኩበት ሁሉ* ከእኔ ላልተለየው+ ለእውነተኛው አምላክ መሠዊያ እሠራለሁ።” 4 በመሆኑም ባዕዳን አማልክታቸውን በሙሉ እንዲሁም በጆሯቸው ላይ ያደረጓቸውን ጉትቻዎች ለያዕቆብ ሰጡት፤ ያዕቆብም በሴኬም አቅራቢያ ባለው ትልቅ ዛፍ ሥር ቀበራቸው።*

5 በሚጓዙበት ጊዜም አምላክ በዙሪያቸው ባሉት ከተሞች ላይ ሽብር ይለቅባቸው ስለነበር የያዕቆብን ልጆች አላሳደዷቸውም። 6 በመጨረሻም ያዕቆብና አብረውት ያሉት ሰዎች በሙሉ በከነአን ምድር ወደምትገኘው ወደ ሎዛ+ ማለትም ወደ ቤቴል መጡ። 7 እሱም በዚያ መሠዊያ ሠራ፤ የቦታውንም ስም ኤልቤቴል* አለው፤ ምክንያቱም ከወንድሙ በሸሸበት ጊዜ እውነተኛው አምላክ በዚያ ራሱን ገልጦለት ነበር።+ 8 በኋላም የርብቃ ሞግዚት ዲቦራ+ ሞተች፤ በቤቴል አቅራቢያ በሚገኝ የባሉጥ ዛፍ ሥርም ተቀበረች። በመሆኑም ስሙን አሎንባኩት* አለው።

9 ያዕቆብ ከጳዳንአራም እየተመለሰ ሳለ አምላክ ዳግመኛ ተገለጠለትና ባረከው። 10 አምላክም “ስምህ ያዕቆብ ነው።+ ከእንግዲህ ያዕቆብ ተብለህ አትጠራም፤ ከዚህ ይልቅ ስምህ እስራኤል ይባላል” አለው። ስለዚህ እስራኤል ብሎ ጠራው።+ 11 በተጨማሪም አምላክ እንዲህ አለው፦ “እኔ ሁሉን ቻይ አምላክ ነኝ።+ ብዛ፣ ተባዛ። ብሔራትና ብዙ ብሔራትን ያቀፈ ጉባኤ ከአንተ ይገኛሉ፤+ ነገሥታትም ከአንተ ይወጣሉ።*+ 12 ለአብርሃምና ለይስሐቅ የሰጠኋትን ምድር ለአንተ እሰጥሃለሁ፤ ከአንተ በኋላ ለሚመጡት ዘሮችህም ይህችን ምድር እሰጣለሁ።”+ 13 ከዚያም አምላክ ከእሱ ጋር ሲነጋገርበት ከነበረው ስፍራ ወደ ላይ ወጣ።

14 ስለዚህ ያዕቆብ ከአምላክ ጋር ሲነጋገር በነበረበት ስፍራ ላይ የድንጋይ ዓምድ አቆመ፤ ባቆመውም ዓምድ ላይ የመጠጥ መባና ዘይት አፈሰሰበት።+ 15 ያዕቆብም ከአምላክ ጋር የተነጋገረበትን ስፍራ ቤቴል+ በሚለው በዚያው ስም ጠራው።

16 ከዚያም ከቤቴል ተነስተው ሄዱ። ኤፍራታ ለመድረስ የተወሰነ ርቀት ሲቀራቸው ራሔል ምጥ ያዛት፤ ምጡም እጅግ ጠናባት። 17 ምጡ እጅግ አስጨንቋት ሳለም አዋላጇ “አይዞሽ አትፍሪ፤ ሌላ ወንድ ልጅ ልትገላገዪ ነው” አለቻት።+ 18 እሷ ግን ሕይወቷ ሊያልፍ በማጣጣር ላይ ሳለች* (ሞት አፋፍ ላይ ስለነበረች) የልጁን ስም ቤንኦኒ* አለችው፤ አባቱ ግን ስሙን ቢንያም*+ አለው። 19 ራሔልም ሞተች፤ ወደ ኤፍራታ ይኸውም ወደ ቤተልሔም+ በሚወስደው መንገድ ላይ ተቀበረች። 20 ያዕቆብም በመቃብሯ ላይ ዓምድ አቆመ፤ ይህ የራሔል መቃብር ዓምድ እስከ ዛሬ ድረስ አለ።

21 ከዚያ በኋላ እስራኤል ከዚያ ተነስቶ በመሄድ ከኤዴር ማማ አለፍ ብሎ ድንኳኑን ተከለ። 22 አንድ ቀን፣ እስራኤል በዚያ ምድር ሰፍሮ ሳለ ሮቤል ከአባቱ ቁባት ከባላ ጋር ተኛ፤ እስራኤልም ይህን ሰማ።+

ያዕቆብ 12 ወንዶች ልጆች ነበሩት። 23 ከሊያ የወለዳቸው ወንዶች ልጆቹ የበኩር ልጁ ሮቤል+ ከዚያም ስምዖን፣ ሌዊ፣ ይሁዳ፣ ይሳኮር እና ዛብሎን ነበሩ። 24 ከራሔል የወለዳቸው ወንዶች ልጆቹ ዮሴፍና ቢንያም ነበሩ። 25 ከራሔል አገልጋይ ከባላ የወለዳቸው ወንዶች ልጆቹ ዳንና ንፍታሌም ነበሩ። 26 ከሊያ አገልጋይ ከዚልጳ የወለዳቸው ወንዶች ልጆቹ ደግሞ ጋድና አሴር ነበሩ። እነዚህ ያዕቆብ በጳዳንአራም ሳለ የወለዳቸው ወንዶች ልጆቹ ናቸው።

27 ከጊዜ በኋላ ያዕቆብ አባቱ ይስሐቅ ወደነበረበት፣ አብርሃምና ይስሐቅ የባዕድ አገር ሰው ሆነው ወደኖሩበት+ በቂርያትአርባ ይኸውም በኬብሮን አካባቢ ወደሚገኘው ወደ ማምሬ መጣ።+ 28 ይስሐቅ 180 ዓመት ኖረ።+ 29 ከዚያም ይስሐቅ የመጨረሻ እስትንፋሱን ተነፈሰ፤ ዕድሜ ጠግቦና በሕይወቱ ረክቶ ሞተ፤ ወደ ወገኖቹም ተሰበሰበ፤* ልጆቹ ኤሳውና ያዕቆብም ቀበሩት።+

36 የኤሳው ማለትም የኤዶም + ታሪክ ይህ ነው።

2 ኤሳው ከከነአን ሴቶች ልጆች ሚስቶችን አገባ፤ እነሱም የሂታዊው+ የኤሎን ልጅ አዳ+ እንዲሁም የአና ልጅና የሂዋዊው የጺብኦን የልጅ ልጅ የሆነችው ኦሆሊባማ+ ናቸው፤ 3 በተጨማሪም የእስማኤል ልጅ የሆነችውን የነባዮትን+ እህት ባሴማትን+ አገባ።

4 አዳ ለኤሳው ኤሊፋዝን ወለደችለት፤ ባሴማት ደግሞ ረኡዔልን ወለደች፤

5 ኦሆሊባማ የኡሽን፣ ያላምን እና ቆሬን ወለደች።+

እነዚህ ኤሳው በከነአን ምድር ሳለ የተወለዱለት ልጆች ናቸው። 6 ከዚያም ኤሳው ሚስቶቹን፣ ወንዶችና ሴቶች ልጆቹን፣ የቤተሰቡን አባላት* ሁሉ፣ መንጋውን፣ ሌሎቹን እንስሳት ሁሉና በከነአን ምድር ያፈራውን ሀብት ሁሉ+ ይዞ ከወንድሙ ከያዕቆብ ርቆ ወደ ሌላ ምድር ሄደ።+ 7 ምክንያቱም ንብረታቸው በጣም ስለበዛ አብረው መኖር አልቻሉም፤ እንዲሁም ከመንጋቸው ብዛት የተነሳ ይኖሩበት* የነበረው ምድር ሊበቃቸው አልቻለም። 8 በመሆኑም ኤሳው በሴይር ተራራማ አካባቢ መኖር ጀመረ።+ ኤሳው ኤዶም ተብሎም ይጠራል።+

9 በሴይር ተራራማ አካባቢ የሚኖረው የኤዶማውያን አባት የኤሳው ታሪክ ይህ ነው።+

10 የኤሳው ወንዶች ልጆች ስም የሚከተለው ነው፦ የኤሳው ሚስት የአዳ ልጅ ኤሊፋዝና የኤሳው ሚስት የባሴማት ልጅ ረኡዔል ናቸው።+

11 የኤሊፋዝ ወንዶች ልጆች ደግሞ ቴማን፣+ ኦማር፣ ጸፎ፣ ጋታም እና ቀናዝ+ ናቸው። 12 ቲምና የኤሳው ልጅ የኤሊፋዝ ቁባት ሆነች። ከጊዜ በኋላም ለኤሊፋዝ አማሌቅን+ ወለደችለት። የኤሳው ሚስት የአዳ ወንዶች ልጆች እነዚህ ናቸው።

13 የረኡዔል ወንዶች ልጆች ናሃት፣ ዛራ፣ ሻማህ እና ሚዛህ ናቸው። እነዚህም የኤሳው ሚስት የባሴማት+ ልጆች ነበሩ።

14 የአና ልጅና የጺብኦን የልጅ ልጅ የሆነችው የኤሳው ሚስት ኦሆሊባማ ለኤሳው የወለደቻቸው ወንዶች ልጆች የኡሽ፣ ያላም እና ቆሬ ናቸው።

15 የነገድ አለቆች* የሆኑት የኤሳው ወንዶች ልጆች+ የሚከተሉት ናቸው፦ የኤሳው የበኩር ልጅ የኤሊፋዝ ወንዶች ልጆችም አለቃ ቴማን፣ አለቃ ኦማር፣ አለቃ ጸፎ፣ አለቃ ቀናዝ፣+ 16 አለቃ ቆሬ፣ አለቃ ጋታም እና አለቃ አማሌቅ ናቸው። እነዚህ በኤዶም ምድር የነገድ አለቆች የሆኑት የኤሊፋዝ ልጆች+ ነበሩ። እነዚህ የአዳ ወንዶች ልጆች ናቸው።

17 የኤሳው ልጅ የረኡዔል ወንዶች ልጆች፣ አለቃ ናሃት፣ አለቃ ዛራ፣ አለቃ ሻማህ እና አለቃ ሚዛህ ናቸው። እነዚህ በኤዶም ምድር የነገድ አለቆች የሆኑት የረኡዔል ልጆች+ ናቸው። እነዚህ የኤሳው ሚስት የባሴማት ወንዶች ልጆች ናቸው።

18 በመጨረሻም የኤሳው ሚስት የኦሆሊባማ ወንዶች ልጆች፣ አለቃ የኡሽ፣ አለቃ ያላም እና አለቃ ቆሬ ናቸው። እነዚህ የነገድ አለቆች የአና ልጅ የሆነችው የኤሳው ሚስት የኦሆሊባማ ልጆች ናቸው።

19 የኤሳው ማለትም የኤዶም+ ወንዶች ልጆችና አለቆቻቸው እነዚህ ናቸው።

20 በዚያ ምድር የሚኖሩት የሆራዊው የሴይር ወንዶች ልጆች እነዚህ ናቸው፦+ ሎጣን፣ ሾባል፣ ጺብኦን፣ አና፣+ 21 ዲሾን፣ ኤጼር እና ዲሻን።+ እነዚህ በኤዶም ምድር የሆራውያን የነገድ አለቆች የሆኑት የሴይር ወንዶች ልጆች ናቸው።

22 የሎጣን ወንዶች ልጆች ሆሪ እና ሄማም ናቸው፤ የሎጣን እህት ቲምና ትባላለች።+

23 የሾባል ወንዶች ልጆች አልዋን፣ ማናሃት፣ ኤባል፣ ሼፎ እና ኦናም ናቸው።

24 የጺብኦን+ ወንዶች ልጆች አያ እና አና ናቸው። ይህ አና የአባቱን የጺብኦንን አህዮች ሲጠብቅ በምድረ በዳ የፍል ውኃ ምንጮችን ያገኘው ነው።

25 የአና ልጆች ዲሾን እና የአና ሴት ልጅ ኦሆሊባማ ናቸው።

26 የዲሾን ወንዶች ልጆች ሄምዳን፣ ኤሽባን፣ ይትራን እና ኬራን ናቸው።+

27 የኤጼር ወንዶች ልጆች ቢልሃን፣ ዛአዋን እና አቃን ናቸው።

28 የዲሻን ወንዶች ልጆች ዑጽ እና አራን ናቸው።+

29 የሆራውያን የነገድ አለቆች እነዚህ ናቸው፦ አለቃ ሎጣን፣ አለቃ ሾባል፣ አለቃ ጺብኦን፣ አለቃ አና፣ 30 አለቃ ዲሾን፣ አለቃ ኤጼር እና አለቃ ዲሻን።+ በሴይር ምድር የሆራውያን የነገድ አለቆች በየአለቆቻቸው ሲዘረዘሩ እነዚህ ናቸው።

31 እነዚህ በእስራኤላውያን* ላይ የትኛውም ንጉሥ መግዛት ከመጀመሩ በፊት+ በኤዶም ምድር ይገዙ የነበሩ ነገሥታት ናቸው።+ 32 የቢዖር ልጅ ቤላ በኤዶም ይገዛ ነበር፤ የከተማውም ስም ዲንሃባ ይባል ነበር። 33 ቤላ ሲሞት የቦስራው የዛራ ልጅ ዮባብ በእሱ ምትክ መግዛት ጀመረ። 34 ዮባብ ሲሞት ከቴማናውያን ምድር የመጣው ሁሻም በእሱ ምትክ መግዛት ጀመረ። 35 ሁሻም ሲሞት ምድያማውያንን+ በሞዓብ ክልል* ድል ያደረጋቸው የቤዳድ ልጅ ሃዳድ በእሱ ምትክ መግዛት ጀመረ፤ የከተማውም ስም አዊት ይባል ነበር። 36 ሃዳድ ሲሞት የማስረቃው ሳምላ በእሱ ምትክ መግዛት ጀመረ። 37 ሳምላ ሲሞት በወንዙ አጠገብ ያለው የረሆቦቱ ሻኡል በእሱ ምትክ መግዛት ጀመረ። 38 ሻኡል ሲሞት የአክቦር ልጅ ባአልሀናን በእሱ ምትክ መግዛት ጀመረ። 39 የአክቦር ልጅ ባአልሀናን ሲሞት ሃዳር በእሱ ምትክ መግዛት ጀመረ። የከተማው ስም ጳኡ ነበር፤ የሚስቱም ስም መሄጣቤል ሲሆን እሷም የመዛሃብ ሴት ልጅ የማጥሬድ ልጅ ናት።

40 እንግዲህ የኤሳው ልጆች የሆኑ የነገድ አለቆች በየቤተሰባቸው፣ በየስፍራቸውና በየስማቸው ሲዘረዘሩ ስማቸው ይህ ነው፦ አለቃ ቲምና፣ አለቃ አልዋህ፣ አለቃ የቴት፣+ 41 አለቃ ኦሆሊባማ፣ አለቃ ኤላህ፣ አለቃ ፒኖን፣ 42 አለቃ ቀናዝ፣ አለቃ ቴማን፣ አለቃ ሚብጻር፣ 43 አለቃ ማግዲኤል እና አለቃ ኢራም። ከኤዶም የተገኙት የነገድ አለቆች ርስት አድርገው በያዙት ምድር እንደየመኖሪያቸው ሲዘረዘሩ እነዚህ ናቸው።+ የኤዶማውያን አባት ኤሳው ይህ ነው።+

37 ያዕቆብ አባቱ የባዕድ አገር ሰው ሆኖ ይኖርበት በነበረው በከነአን ምድር ኖረ።+

2 የያዕቆብ ታሪክ ይህ ነው።

ዮሴፍ+ የ17 ዓመት ወጣት ሳለ ከአባቱ ሚስቶች ከባላና ከዚልጳ ወንዶች ልጆች+ ጋር በጎች ይጠብቅ+ ነበር። እሱም ስለ ወንድሞቹ መጥፎ ድርጊት የሚገልጽ ወሬ ለአባታቸው ይዞለት መጣ። 3 እስራኤል ዮሴፍን የወለደው በስተርጅናው ስለነበር ከሌሎቹ ወንዶች ልጆቹ ሁሉ+ ይበልጥ ይወደው ነበር፤ ለእሱም ልዩ የሆነ ቀሚስ* አሠራለት። 4 ወንድሞቹም አባታቸው ከእነሱ አስበልጦ እንደሚወደው ሲያዩ ይጠሉት ጀመር፤ በሰላምም ሊያናግሩት አልቻሉም።

5 በኋላም ዮሴፍ ሕልም አለመ፤ ሕልሙንም ለወንድሞቹ ነገራቸው፤+ እነሱም እሱን የሚጠሉበት ተጨማሪ ምክንያት አገኙ። 6 እሱም እንዲህ አላቸው፦ “እባካችሁ ያየሁትን ሕልም ልንገራችሁ፣ ስሙኝ። 7 በእርሻ መካከል ነዶ እያሰርን ነበር፤ ከዚያም የእኔ ነዶ ተነስታ ቀጥ ብላ ስትቆም የእናንተ ነዶዎች ደግሞ የእኔን ነዶ ከበው ሰገዱላት።”+ 8 ወንድሞቹም “በእኛ ላይ ንጉሥ ልትሆንና ልትገዛን ታስባለህ ማለት ነው?” አሉት።+ በመሆኑም ያየው ሕልምና የተናገረው ነገር እሱን ይበልጥ እንዲጠሉት አደረጋቸው።

9 ከዚያም ሌላ ሕልም አለመ፤ ሕልሙንም ለወንድሞቹ እንዲህ ሲል ነገራቸው፦ “ሌላም ሕልም አለምኩ። አሁን ደግሞ ፀሐይ፣ ጨረቃና 11 ከዋክብት ሲሰግዱልኝ አየሁ።”+ 10 ሕልሙንም ለአባቱና ለወንድሞቹ ነገራቸው፤ አባቱም ገሠጸው፤ እንዲህም አለው፦ “ይህ ያለምከው ሕልም ፍቺ ምንድን ነው? እኔም ሆንኩ እናትህና ወንድሞችህ መጥተን መሬት ላይ ተደፍተን እንድንሰግድልህ ታስባለህ?” 11 ወንድሞቹም ይበልጥ ቀኑበት፤+ አባቱ ግን ነገሩን በልቡ ያዘው።

12 ወንድሞቹ የአባታቸውን መንጋ ለማሰማራት ሴኬም+ አቅራቢያ ወደሚገኝ ቦታ ሄደው ነበር። 13 በኋላም እስራኤል ዮሴፍን “ወንድሞችህ በሴኬም አቅራቢያ መንጎቹን እየጠበቁ እንዳሉ አውቀሃል አይደል? በል ና፣ ወደ እነሱ ልላክህ” አለው። እሱም “እሺ፣ እሄዳለሁ!” አለ። 14 በመሆኑም “እባክህ ሂድና ወንድሞችህ ደህና መሆናቸውን እይ። መንጋውም ደህና መሆኑን እይና መጥተህ ትነግረኛለህ” አለው። በዚህም መሠረት ከኬብሮን+ ሸለቆ* ወደዚያ ላከው፤ ዮሴፍም ወደ ሴኬም ሄደ። 15 በኋላም ዮሴፍ በሜዳ ላይ ሲባዝን አንድ ሰው አገኘው። ሰውየውም “ምን ፈልገህ ነው?” ሲል ጠየቀው። 16 እሱም “ወንድሞቼን እየፈለግኩ ነው። መንጎቹን እየጠበቁ ያሉት የት እንደሆነ እባክህ ንገረኝ” አለው። 17 ሰውየውም “ከዚህ ሄደዋል፤ ምክንያቱም ‘ወደ ዶታን እንሂድ’ ሲባባሉ ሰምቻቸዋለሁ” አለው። ስለዚህ ዮሴፍ ወንድሞቹን ፍለጋ ሄደ፤ ዶታን ላይም አገኛቸው።

18 እነሱም ከሩቅ ሲመጣ ተመለከቱት፤ አጠገባቸውም ከመድረሱ በፊት እሱን እንዴት እንደሚገድሉት ይመካከሩ ጀመር። 19 እነሱም እንዲህ ተባባሉ፦ “ያውና! ያ ሕልም አላሚ መጣ።+ 20 ኑ፣ እንግደለውና ከውኃ ጉድጓዶቹ በአንዱ ውስጥ እንጣለው፤ ከዚያም ኃይለኛ አውሬ በልቶታል እንላለን። እስቲ የሕልሞቹን መጨረሻ እናያለን።” 21 ሮቤል+ ይህን ሲሰማ ከእነሱ ሊያስጥለው አሰበ፤ በመሆኑም “ሕይወቱን* እንኳ አናጥፋ”+ አለ። 22 ከዚያም እንዲህ አላቸው፦ “ደም አታፍስሱ።+ በምድረ በዳ በሚገኘው በዚህ የውኃ ጉድጓድ ውስጥ ጣሉት እንጂ ጉዳት አታድርሱበት።”*+ ይህን ያላቸው ከእነሱ ሊያስጥለውና ወደ አባቱ ሊመልሰው አስቦ ነበር።

23 ዮሴፍ ወደ ወንድሞቹ እንደደረሰም የለበሰውን ያን ልዩ ቀሚስ+ ገፈፉት፤ 24 ወስደውም የውኃ ጉድጓዱ ውስጥ ጣሉት። ጉድጓዱም ባዶ ነበር፤ ውኃም አልነበረበትም።

25 ከዚያም ሊበሉ ተቀመጡ። ቀና ብለው ሲመለከቱም እስማኤላውያን+ ነጋዴዎች ግመሎቻቸውን አግተልትለው ከጊልያድ ሲመጡ አዩ። እነሱም በግመሎቻቸው ላይ ጥሩ መዓዛ ያለው ሙጫ፣ በለሳንና ከርቤ+ ጭነው ወደ ግብፅ እየወረዱ ነበር። 26 በዚህ ጊዜ ይሁዳ ወንድሞቹን እንዲህ አላቸው፦ “ወንድማችንን ብንገድለውና ደሙን ብንሸሽግ ምን እንጠቀማለን?+ 27 ኑ፣ ለእስማኤላውያን እንሽጠው፤+ እጃችንን አንሰንዝርበት። ደግሞም እኮ እሱ ወንድማችን፣ የገዛ ሥጋችን ነው።” እነሱም በወንድማቸው ሐሳብ ተስማሙ። 28 ምድያማውያን+ ነጋዴዎች በአጠገባቸው ሲያልፉም ዮሴፍን ከውኃ ጉድጓዱ አውጥተው በ20 የብር ሰቅል ለእስማኤላውያን ሸጡት።+ እነሱም ዮሴፍን ወደ ግብፅ ወሰዱት።

29 በኋላም ሮቤል ወደ ውኃ ጉድጓዱ ተመልሶ ዮሴፍ በዚያ አለመኖሩን ሲመለከት ልብሱን ቀደደ። 30 ወደ ወንድሞቹም ተመልሶ “ልጁ የለም! እንግዲህ ምንድን ነው የማደርገው?” አላቸው።

31 ስለዚህ የዮሴፍን ቀሚስ ወሰዱ፤ አንድ ፍየል ካረዱ በኋላም ቀሚሱን ደሙ ውስጥ ነከሩት። 32 ከዚያም ያን ልዩ ቀሚስ እንዲህ ከሚል መልእክት ጋር ወደ አባታቸው ላኩት፦ “ይህን አገኘን፤ እባክህ ይህ የልጅህ ቀሚስ መሆን አለመሆኑን እስቲ እየው።”+ 33 እሱም ልብሱን አገላብጦ ካየው በኋላ “ይሄማ የልጄ ቀሚስ ነው! ኃይለኛ አውሬ በልቶት መሆን አለበት! በቃ ዮሴፍን አውሬ ቦጫጭቆታል ማለት ነው!” አለ። 34 ከዚያም ያዕቆብ ልብሱን ቀደደ፤ በወገቡም ላይ ማቅ ታጥቆ ለብዙ ቀናት ለልጁ አለቀሰ። 35 ወንዶችና ሴቶች ልጆቹ ሁሉ ሊያጽናኑት ሞከሩ፤ እሱ ግን ፈጽሞ ሊጽናና አልቻለም፤ “በልጄ ሐዘን እንደተቆራመድኩ ወደ መቃብር* እወርዳለሁ!”+ ይል ነበር። አባቱም ለልጁ ማልቀሱን አላቋረጠም።

36 በዚህ ጊዜ ምድያማውያን ዮሴፍን ግብፅ ውስጥ ጶጢፋር ለተባለ ሰው ሸጡት፤ ይህ ሰው የፈርዖን የቤተ መንግሥት ባለሥልጣንና+ የዘቦች አለቃ+ ነበር።

38 በዚሁ ጊዜ አካባቢ ይሁዳ ከወንድሞቹ ተለይቶ በመውረድ ሂራ በሚባል አዱላማዊ ሰው አቅራቢያ ድንኳኑን ተከለ። 2 በዚያም ሹአ የሚባል የአንድ ከነአናዊ ሰው ሴት ልጅ+ አየ። እሷንም አገባትና ከእሷ ጋር ግንኙነት ፈጸመ፤ 3 እሷም ፀነሰች። ወንድ ልጅም ወለደች፤ ስሙንም ኤር+ አለው። 4 ዳግመኛም ፀነሰች፤ ወንድ ልጅም ወለደች፤ ስሙንም ኦናን አለችው። 5 በድጋሚም ሌላ ወንድ ልጅ ወለደች፤ ስሙንም ሴሎም አለችው። እሱም* ልጅ በወለደችለት ጊዜ አክዚብ+ በሚባል ቦታ ነበር።

6 ከጊዜ በኋላ ይሁዳ ለበኩር ልጁ ለኤር ሚስት አመጣለት፤ ስሟም ትዕማር+ ይባል ነበር። 7 ይሁንና የይሁዳ የበኩር ልጅ ኤር ይሖዋ ያዘነበት ሰው ነበር፤ በመሆኑም ይሖዋ በሞት ቀሰፈው። 8 በዚህ የተነሳ ይሁዳ ኦናንን “ከወንድምህ ሚስት ጋር ግንኙነት በመፈጸም የዋርሳነት ግዴታህን ተወጣ፤ ለወንድምህም ዘር ተካለት” አለው።+ 9 ኦናን ግን የሚወለደው ልጅ የእሱ ልጅ እንደሆነ ተደርጎ እንደማይቆጠር ያውቅ ነበር።+ በመሆኑም ለወንድሙ ዘር ላለመተካት ሲል ከወንድሙ ሚስት ጋር ግንኙነት በሚፈጽምበት ጊዜ ዘሩን መሬት ላይ ያፈስ ነበር።+ 10 እሱም ያደረገው ነገር በይሖዋ ፊት መጥፎ ስለነበር አምላክ በሞት ቀሰፈው።+ 11 ይሁዳ ምራቱን ትዕማርን “ልጄ ሴሎም እስኪያድግ ድረስ በአባትሽ ቤት መበለት ሆነሽ ተቀመጪ” አላት፤ ይህን ያላት ‘እሱም እንደ ወንድሞቹ ሊሞትብኝ ይችላል’ ብሎ ስላሰበ ነው።+ ስለዚህ ትዕማር ሄዳ በአባቷ ቤት መኖር ጀመረች።

12 የተወሰነ ጊዜ ካለፈ በኋላም የሹአ+ ልጅ የሆነችው የይሁዳ ሚስት ሞተች። ይሁዳም ሐዘን ተቀምጦ ተነሳ፤ ከዚያም ከአዱላማዊው ወዳጁ ከሂራ+ ጋር በመሆን በጎቹን የሚሸልቱለት ሰዎች ወዳሉበት ወደ ቲምና+ ሄደ። 13 ትዕማርም “አማትሽ በጎቹን ለመሸለት ወደ ቲምና እየወጣ ነው” ተብሎ ተነገራት። 14 በዚህ ጊዜ የመበለትነት ልብሷን በማውለቅ የአንገት ልብስ ተከናንባና ፊቷን ተሸፍና ወደ ቲምና በሚወስደው መንገድ ላይ በምትገኘው በኤናይም መግቢያ ላይ ተቀመጠች፤ ይህን ያደረገችው ሴሎም ቢያድግም ለእሱ እንዳልተዳረች ስላየች ነው።+

15 ይሁዳም ባያት ጊዜ ዝሙት አዳሪ መሰለችው፤ ምክንያቱም ፊቷን ሸፍና ነበር። 16 ስለሆነም ከመንገዱ ወጣ በማለት ወደ እሷ ጠጋ ብሎ “እባክሽ አብሬሽ እንድተኛ ፍቀጂልኝ” አላት፤ ይህን ያደረገውም ምራቱ መሆኗን ስላላወቀ ነው።+ ሆኖም እሷ “አብሬህ ብተኛ ምን ትሰጠኛለህ?” አለችው። 17 እሱም “ከመንጋዬ መካከል አንድ የፍየል ጠቦት እልክልሻለሁ” አላት። እሷ ግን “ጠቦቱን እስክትልክልኝ ድረስ መያዣ ትሰጠኛለህ?” አለችው። 18 እሱም “ምን መያዣ ልስጥሽ?” አላት። እሷም “የማኅተም ቀለበትህን+ ከነማንጠልጠያ ክሩ እንዲሁም በእጅህ የያዝከውን በትርህን ስጠኝ” አለችው። ከዚያም እነዚህን ነገሮች ሰጣት፤ ከእሷም ጋር ተኛ፤ ከእሱም ፀነሰች። 19 ከዚያ በኋላ ተነስታ ሄደች፤ የአንገት ልብሷንም አውልቃ የመበለትነት ልብሷን ለበሰች።

20 ይሁዳም መያዣውን ከሴቲቱ እጅ ለማስመለስ አዱላማዊ+ ወዳጁን የፍየል ጠቦት አስይዞ ወደ እሷ ላከው፤ እሱ ግን ፈጽሞ ሊያገኛት አልቻለም። 21 እሱም የአካባቢውን ሰዎች “ያቺ መንገድ ዳር የምትቀመጠው በኤናይም ያለች የቤተ መቅደስ ዝሙት አዳሪ የት አለች?” በማለት ጠየቀ። እነሱ ግን “ኧረ በዚህ አካባቢ የቤተ መቅደስ ዝሙት አዳሪ ታይታ አትታወቅም” አሉት። 22 በመጨረሻም ወደ ይሁዳ ተመልሶ እንዲህ አለው፦ “ሴቲቱን በፍጹም ላገኛት አልቻልኩም፤ ደግሞም የአካባቢው ሰዎች ‘በዚህ አካባቢ የቤተ መቅደስ ዝሙት አዳሪ ታይታ አትታወቅም’ አሉኝ።” 23 በመሆኑም ይሁዳ “በኋላ እኛ መሳለቂያ እንዳንሆን መያዣውን ትውሰደው። እኔ እንደሆነ ይህን ጠቦት ልኬላት ነበር፤ አንተ ግን ፈጽሞ ልታገኛት አልቻልክም” አለው።

24 ይሁን እንጂ ከሦስት ወር በኋላ ለይሁዳ “ምራትህ ትዕማር ዝሙት አዳሪ ሆናለች፤ ዝሙት በመፈጸሟም ፀንሳለች” ተብሎ ተነገረው። በዚህ ጊዜ ይሁዳ “አውጧትና በእሳት ትቃጠል” አለ።+ 25 እሷም ይዘዋት እየሄዱ ሳሉ ለአማቷ “የፀነስኩት የእነዚህ ዕቃዎች ባለቤት ከሆነ ሰው ነው” የሚል መልእክት ላከችበት። በተጨማሪም “ይህ የማኅተም ቀለበትና ማንጠልጠያ ክሩ እንዲሁም ይህ በትር የማን እንደሆነ እስቲ አጣራ” አለችው።+ 26 ይሁዳም ዕቃዎቹን ከተመለከተ በኋላ “እሷ ከእኔ ይልቅ ጻድቅ ናት፤ ምክንያቱም ለልጄ ለሴሎም ልድራት ይገባኝ ነበር” አለ።+ ከእሷም ጋር ዳግመኛ የፆታ ግንኙነት አልፈጸመም።

27 የመውለጃዋም ጊዜ ሲደርስ በሆዷ ውስጥ መንታ ልጆች እንዳሉ ታወቀ። 28 በምትወልድበት ጊዜም አንደኛው ልጅ እጁን አወጣ፤ አዋላጇም “መጀመሪያ የወጣው ይህ ነው” በማለት ወዲያውኑ በእጁ ላይ ቀይ ክር አሰረችለት። 29 ይሁን እንጂ ልጁ እጁን በመለሰ ጊዜ ወንድሙ ቀድሞት ወጣ፤ በመሆኑም አዋላጇ “አንተ እንዴት ጥሰህ ወጣህ?” አለች። በመሆኑም ስሙ ፋሬስ*+ ተባለ። 30 በኋላም እጁ ላይ ቀይ ክር የታሰረለት ወንድሙ ወጣ፤ ስሙም ዛራ+ ተባለ።

39 ዮሴፍም ወደ ግብፅ ተወሰደ፤+ የፈርዖን የቤተ መንግሥት ባለሥልጣንና የዘቦች አለቃ የሆነ ጶጢፋር+ የሚባል አንድ ግብፃዊ ወደዚያ ይዘውት ከወረዱት እስማኤላውያን+ እጅ ዮሴፍን ገዛው። 2 ሆኖም ይሖዋ ከዮሴፍ ጋር ነበር።+ በዚህም የተነሳ ስኬታማ ሆነ፤ በግብፃዊው ጌታው ቤትም ላይ ኃላፊ ሆኖ ተሾመ። 3 ጌታውም ይሖዋ ከዮሴፍ ጋር እንደሆነና የሚሠራውንም ነገር ሁሉ ይሖዋ እንደሚያሳካለት አየ።

4 ዮሴፍም በፊቱ ሞገስ እያገኘ ሄደ፤ የቅርብ አገልጋዩም ሆነ። በመሆኑም በቤቱ ላይ ሾመው፤ የእሱ የሆነውንም ነገር ሁሉ በኃላፊነት ሰጠው። 5 በቤቱና ባለው ነገር ሁሉ ላይ ከሾመው ጊዜ አንስቶ ይሖዋ በዮሴፍ ምክንያት የግብፃዊውን ቤት ባረከ፤ ይሖዋም በቤትና በመስክ ያለውን ነገር ሁሉ ባረከለት።+ 6 ከጊዜ በኋላም ያለውን ነገር ሁሉ ለዮሴፍ በኃላፊነት ሰጠው፤ እሱም ከሚመገበው ምግብ በስተቀር ስለ ሌላው ነገር ምንም አይጨነቅም ነበር። ደግሞም ዮሴፍ ሰውነቱ እየዳበረና መልኩ እያማረ ሄደ።

7 በኋላም የጌታው ሚስት በዮሴፍ ላይ ዓይኗን ጣለችበት፤ እሷም “ከእኔ ጋር ተኛ” ትለው ጀመር። 8 እሱ ግን ፈቃደኛ አለመሆኑን በመግለጽ የጌታውን ሚስት እንዲህ አላት፦ “ጌታዬ በዚህ ቤት በእኔ እጅ ስላለው ነገር ምንም የሚያውቀው ነገር የለም፤ ያለውንም ነገር ሁሉ በአደራ ሰጥቶኛል። 9 በዚህ ቤት ውስጥ ከእኔ የሚበልጥ ሰው የለም፤ ጌታዬ ከአንቺ በስተቀር ምንም ያልሰጠኝ ነገር የለም፤ ይህን ያደረገውም ሚስቱ ስለሆንሽ ነው። ታዲያ እንዲህ ያለውን እጅግ መጥፎ ድርጊት በመፈጸም በአምላክ ላይ እንዴት ኃጢአት እሠራለሁ?”+

10 እሷም ዮሴፍን በየቀኑ ትወተውተው ነበር፤ እሱ ግን ከእሷ ጋር ለመተኛትም ሆነ አብሯት ለመሆን ፈጽሞ ፈቃደኛ አልሆነም። 11 ይሁንና አንድ ቀን ዮሴፍ ሥራውን ለማከናወን ወደ ቤት ሲገባ ከቤቱ አገልጋዮች መካከል አንዳቸውም በዚያ አልነበሩም። 12 እሷም ልብሱን አፈፍ አድርጋ ይዛ “አብረኸኝ ተኛ!” አለችው። እሱ ግን ልብሱን እጇ ላይ ጥሎ ወደ ውጭ ሸሽቶ ወጣ። 13 እሷም ልብሱን እጇ ላይ ጥሎ ወደ ውጭ እንደሸሸ ባየች ጊዜ 14 የቤቷን ሰዎች ጮኻ በመጣራት እንዲህ አለቻቸው፦ “አያችሁ! ባለቤቴ ያመጣው ይህ ዕብራዊ መሳለቂያ ሊያደርገን ነው። መጥቶ አብሬሽ ካልተኛሁ አለኝ፤ እኔ ግን ጩኸቴን አቀለጥኩት። 15 ድምፄን ከፍ አድርጌ ስጮኽ ልብሱን አጠገቤ ጥሎ ወደ ውጭ ሸሽቶ ወጣ።” 16 ከዚያም ጌታው ወደ ቤቱ እስኪመለስ ድረስ ልብሱን አጠገቧ አቆየችው።

17 ከዚያም እንዲህ ስትል ያንኑ ነገር ነገረችው፦ “ይህ ያመጣህብን ዕብራዊ አገልጋይ እኔ ወዳለሁበት ገብቶ መሳለቂያ ሊያደርገኝ ነበር። 18 ሆኖም ድምፄን ከፍ አድርጌ ስጮኽ ልብሱን አጠገቤ ጥሎ ወደ ውጭ ሸሽቶ ወጣ።” 19 ጌታውም “ይኸውልህ፣ አገልጋይህ እንዲህ አደረገኝ” ብላ ሚስቱ የነገረችውን ሲሰማ ቁጣው ነደደ። 20 በመሆኑም የዮሴፍ ጌታ ዮሴፍን ወስዶ የንጉሡ እስረኞች የታሰሩበት እስር ቤት አስገባው፤ ዮሴፍም እዚያው እስር ቤት ውስጥ ቆየ።+

21 ይሁን እንጂ ይሖዋ ከዮሴፍ አልተለየም፤ እንደወትሮው ሁሉ ለእሱ ታማኝ ፍቅር ከማሳየት ወደኋላ አላለም፤ በእስር ቤቱ አለቃም ፊት ሞገስ ሰጠው።+ 22 በመሆኑም የእስር ቤቱ አለቃ ዮሴፍን በእስር ቤቱ ውስጥ ባሉት እስረኞች ሁሉ ላይ ኃላፊ አደረገው፤ በእስር ቤቱ ውስጥ እስረኞቹ የሚያከናውኑትን ማንኛውንም ሥራ የሚቆጣጠረው እሱ ነበር።+ 23 ይሖዋ ከዮሴፍ ጋር ስለነበርና የሚያደርገውን ነገር ሁሉ ይሖዋ ስለሚያሳካለት የእስር ቤቱ አለቃ በዮሴፍ ኃላፊነት ሥር ስላለው ስለ ማንኛውም ነገር ምንም አይጨነቅም ነበር።+

40 ይህ ከሆነ በኋላ የግብፁ ንጉሥ የመጠጥ አሳላፊዎች አለቃና+ የዳቦ ጋጋሪዎች አለቃ ጌታቸውን የግብፁን ንጉሥ በደሉ። 2 በመሆኑም ፈርዖን በሁለቱ ሹማምንቱ ማለትም በመጠጥ አሳላፊዎቹ አለቃና በዳቦ ጋጋሪዎቹ አለቃ ላይ እጅግ ተቆጣ፤+ 3 እሱም በዘቦች አለቃ+ ቤት በሚገኘው ወህኒ ቤት ይኸውም ዮሴፍ በታሰረበት እስር ቤት+ ውስጥ እንዲታሰሩ አደረገ። 4 ከዚያም የዘቦቹ አለቃ፣ ዮሴፍ ከእነሱ ጋር እንዲሆንና እንዲረዳቸው መደበው፤+ እነሱም ለተወሰነ ጊዜ* ወህኒ ቤት ውስጥ ቆዩ።

5 እስር ቤት ውስጥ ታስረው የነበሩት የግብፁ ንጉሥ መጠጥ አሳላፊና ዳቦ ጋጋሪ በአንድ ሌሊት ሕልም አለሙ፤ የእያንዳንዳቸውም ሕልም የተለያየ ፍቺ ነበረው። 6 በማግስቱ ጠዋት ዮሴፍ ገብቶ ሲያያቸው ተክዘው አገኛቸው። 7 በመሆኑም በጌታው ቤት ከእሱ ጋር የታሰሩትን የፈርዖንን ሹማምንት “ምነው ዛሬ ፊታችሁ በሐዘን ጠቆረ?” ሲል ጠየቃቸው። 8 እነሱም “ሁለታችንም ሕልም አልመን ነበር፤ ሕልማችንን የሚፈታልን ሰው ግን አላገኘንም” አሉት። ዮሴፍም “ሕልምን የሚፈታው አምላክ አይደለም?+ እስቲ ያያችሁትን ሕልም ንገሩኝ” አላቸው።

9 በመሆኑም የመጠጥ አሳላፊዎቹ አለቃ እንዲህ ሲል ሕልሙን ለዮሴፍ ነገረው፦ “በሕልሜ ከፊት ለፊቴ አንድ የወይን ተክል አየሁ። 10 በወይኑም ተክል ላይ ሦስት ቀንበጦች ነበሩ፤ ተክሉም በማቆጥቆጥ ላይ እያለ አበባ አወጣ፤ በዘለላዎቹም ላይ ያሉት ፍሬዎች በሰሉ። 11 እኔም የፈርዖንን ጽዋ በእጄ ይዤ ነበር፤ የወይን ፍሬዎቹንም ወስጄ በፈርዖን ጽዋ ውስጥ ጨመቅኳቸው። ከዚያም ጽዋውን ለፈርዖን በእጁ ሰጠሁት።” 12 በዚህ ጊዜ ዮሴፍ እንዲህ አለው፦ “የሕልሙ ፍቺ ይህ ነው፦ ሦስቱ ቀንበጦች ሦስት ቀናት ናቸው። 13 ከሦስት ቀን በኋላ ፈርዖን ከእስር ቤት ያስወጣሃል፤* ወደ ቀድሞ ሹመትህም ይመልስሃል።+ አንተም የመጠጥ አሳላፊው በነበርክበት ጊዜ ታደርግ እንደነበረው ሁሉ የፈርዖንን ጽዋ በእጁ ትሰጠዋለህ።+ 14 ይሁንና ሁኔታዎች ሲስተካከሉልህ እኔን እንዳትረሳኝ። እባክህ ታማኝ ፍቅር አሳየኝ፤ ከዚህ እስር ቤት እንዲያስፈታኝም ስለ እኔ ለፈርዖን ንገረው። 15 በመሠረቱ እኔ ከዕብራውያን ምድር ወደዚህ የመጣሁት ተገድጄ ነው፤+ አሁንም ቢሆን እዚህ እስር ቤት* ውስጥ የጣሉኝ ያለምንም ጥፋት ነው።”+

16 የዳቦ ጋጋሪዎቹ አለቃም ዮሴፍ የተናገረው የሕልሙ ፍቺ መልካም መሆኑን ሲያይ እሱም እንዲህ አለው፦ “እኔም ሕልም አይቼ ነበር፤ በሕልሜም ነጭ ዳቦዎች የያዙ ሦስት ቅርጫቶች በራሴ ላይ ተሸክሜ ነበር፤ 17 ከላይ ባለው ቅርጫት ውስጥ ለፈርዖን የሚቀርቡ የተለያዩ የተጋገሩ ምግቦች ነበሩ፤ ወፎችም በራሴ ላይ ከተሸከምኩት ቅርጫት ውስጥ ይበሉ ነበር።” 18 ከዚያም ዮሴፍ እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “የሕልሙ ፍቺ ይህ ነው፦ ሦስቱ ቅርጫቶች ሦስት ቀናት ናቸው። 19 ከሦስት ቀን በኋላ ፈርዖን ራስህን ይቆርጣል፤* በእንጨትም ላይ ይሰቅልሃል፤ ወፎችም ሥጋህን ይበላሉ።”+

20 ሦስተኛው ቀን ደግሞ ፈርዖን የልደት በዓሉን የሚያከብርበት ዕለት ነበር፤+ እሱም ለአገልጋዮቹ በሙሉ ግብዣ አዘጋጀ። አገልጋዮቹ ባሉበትም የመጠጥ አሳላፊዎቹን አለቃና የዳቦ ጋጋሪዎቹን አለቃ ከእስር ቤት አስወጣቸው።* 21 የመጠጥ አሳላፊዎቹንም አለቃ ወደ መጠጥ አሳላፊነት ሹመቱ መለሰው፤ እሱም እንደቀድሞው ለፈርዖን ጽዋውን ይሰጠው ጀመር። 22 የዳቦ ጋጋሪዎቹን አለቃ ግን ዮሴፍ ሕልማቸውን በፈታላቸው መሠረት ሰቀለው።+ 23 ይሁንና የመጠጥ አሳላፊዎቹ አለቃ ዮሴፍን አላስታወሰውም፤ ጨርሶም ረሳው።+

41 ሁለት ድፍን ዓመታት ካለፉ በኋላ ፈርዖን በሕልሙ አባይ ወንዝ ዳር ቆሞ አየ።+ 2 ከዚያም ቁመናቸው ያማረ ሰባት የሰቡ ላሞች ከአባይ ወንዝ ሲወጡ አየ፤ እነሱም አባይ ወንዝ ዳር ያለውን ሣር ይበሉ ነበር።+ 3 ከእነሱም ቀጥሎ አስቀያሚ መልክ ያላቸውና ከሲታ የሆኑ ሌሎች ሰባት ላሞች ከአባይ ወንዝ ወጡ፤ እነሱም አባይ ወንዝ ዳር ከነበሩት የሰቡ ላሞች አጠገብ ቆሙ። 4 ከዚያም አስቀያሚ መልክ ያላቸው ከሲታ የሆኑት ላሞች ያማረ ቁመና ያላቸውን የሰቡትን ሰባት ላሞች በሏቸው። በዚህ ጊዜ ፈርዖን ከእንቅልፉ ባነነ።

5 ከዚያም ፈርዖን በድጋሚ እንቅልፍ ወሰደው፤ ለሁለተኛ ጊዜም ሕልም አለመ። በሕልሙም በአንድ አገዳ ላይ የተንዠረገጉና ያማሩ ሰባት የእህል ዛላዎች ሲወጡ አየ።+ 6 ከእነሱም በኋላ የቀጨጩና በምሥራቅ ነፋስ የተመቱ ሰባት የእህል ዛላዎች በቀሉ። 7 የቀጨጩት የእህል ዛላዎች የተንዠረገጉትንና የፋፉትን ሰባት የእህል ዛላዎች ዋጧቸው። በዚህ ጊዜ ፈርዖን ከእንቅልፉ ባነነ፤ ሕልም እንደሆነም ተገነዘበ።

8 በነጋም ጊዜ መንፈሱ ተረበሸ። በመሆኑም በግብፅ የሚገኙ አስማተኛ ካህናትን በሙሉ እንዲሁም ጥበበኞቿን በሙሉ አስጠራ። ፈርዖንም ያያቸውን ሕልሞች ነገራቸው፤ ሆኖም ለፈርዖን ሕልሞቹን ሊፈታለት የቻለ አንድም ሰው አልነበረም።

9 በዚህ ጊዜ የመጠጥ አሳላፊዎቹ አለቃ ፈርዖንን እንዲህ አለው፦ “ኃጢአቴን ዛሬ ልናዘዝ። 10 ፈርዖን በአገልጋዮቹ ተቆጥቶ ነበር። በመሆኑም እኔንና የዳቦ ጋጋሪዎቹን አለቃ በዘቦቹ አለቃ ቤት በሚገኘው ወህኒ ቤት ውስጥ አስሮን ነበር።+ 11 ከዚያም ሁለታችንም በአንድ ሌሊት ሕልም አለምን። እኔም ሆንኩ እሱ ያለምነው ሕልም የተለያየ ፍቺ ነበረው።+ 12 ከእኛም ጋር የዘቦቹ አለቃ አገልጋይ+ የሆነ አንድ ወጣት ዕብራዊ ነበር። ያየናቸውንም ሕልሞች በነገርነው ጊዜ+ የእያንዳንዳችንን ሕልም ፈታልን። 13 ነገሩ ሁሉ ልክ እሱ እንደፈታልን ሆነ። እኔ ወደ ሹመቴ ተመለስኩ፤ ሌላኛው ሰው ግን ተሰቀለ።”+

14 ስለሆነም ፈርዖን ዮሴፍን እንዲያመጡት ሰዎች ላከ፤+ እነሱም ከእስር ቤቱ* በፍጥነት ይዘውት መጡ።+ እሱም ተላጭቶና ልብሱን ለውጦ ወደ ፈርዖን ገባ። 15 ከዚያም ፈርዖን ዮሴፍን እንዲህ አለው፦ “ሕልም አይቼ ነበር፤ የሚፈታልኝ ሰው ግን አልተገኘም። አንተ ሕልም ሰምተህ መፍታት እንደምትችል ሰማሁ።”+ 16 በዚህ ጊዜ ዮሴፍ ለፈርዖን “ኧረ እኔ እዚህ ግባ የምባል ሰው አይደለሁም! ለፈርዖን መልካም የሆነውን ነገር የሚያሳውቀው አምላክ ነው”+ ሲል መለሰለት።

17 ፈርዖንም ለዮሴፍ እንዲህ ሲል ነገረው፦ “በሕልሜ አባይ ወንዝ ዳር ቆሜ ነበር። 18 ከዚያም ቁመናቸው ያማረ የሰቡ ሰባት ላሞች ከአባይ ወንዝ ሲወጡ አየሁ፤ እነሱም አባይ ወንዝ ዳር ያለውን ሣር ይበሉ ጀመር።+ 19 ከእነሱ ቀጥሎም የተጎሳቆሉ እንዲሁም አስቀያሚ ቁመና ያላቸውና ከሲታ የሆኑ ሌሎች ሰባት ላሞች ወጡ፤ በመላው የግብፅ ምድር እንደ እነሱ ያሉ አስቀያሚ ላሞች ፈጽሞ አይቼ አላውቅም። 20 ከዚያም ከሲታ የሆኑት አስቀያሚ ላሞች የመጀመሪያዎቹን ሰባት የሰቡ ላሞች በሏቸው። 21 ከበሏቸው በኋላም ግን ቁመናቸው ልክ እንደቀድሞው አስቀያሚ ስለነበር ማንም ሰው እንደበሏቸው እንኳ ሊያውቅ አይችልም ነበር። በዚህ ጊዜ ከእንቅልፌ ባነንኩ።

22 “ከዚያ በኋላ የፋፉና ያማሩ ሰባት የእህል ዛላዎች በአንድ አገዳ ላይ ሲወጡ በሕልሜ አየሁ።+ 23 ከእነሱም በኋላ የቀጨጩና በምሥራቅ ነፋስ የተመቱ ሰባት የጠወለጉ የእህል ዛላዎች በቀሉ። 24 ከዚያም የቀጨጩት የእህል ዛላዎች ያማሩትን ሰባት የእህል ዛላዎች ዋጧቸው። እኔም ሕልሜን አስማተኛ ለሆኑት ካህናት ነገርኳቸው፤+ ሆኖም ሊያብራራልኝ የቻለ አንድም ሰው አልተገኘም።”+

25 ከዚያም ዮሴፍ ፈርዖንን እንዲህ አለው፦ “ሁለቱም የፈርዖን ሕልሞች አንድ ዓይነትና ተመሳሳይ ናቸው። እውነተኛው አምላክ ወደፊት የሚያደርገውን ነገር ለፈርዖን አሳውቆታል።+ 26 ሰባቱ ያማሩ ላሞች ሰባት ዓመታት ናቸው። በተመሳሳይም ሰባቱ ያማሩ የእህል ዛላዎች ሰባት ዓመታት ናቸው። ሕልሞቹ አንድ ዓይነትና ተመሳሳይ ናቸው። 27 ከእነሱ በኋላ የመጡት ሰባቱ ከሲታና አስቀያሚ ላሞች ሰባት ዓመታት ናቸው፤ በምሥራቅ ነፋስ የተመቱት ሰባቱ ፍሬ አልባ የእህል ዛላዎች ረሃብ የሚከሰትባቸው ሰባት ዓመታት ይሆናሉ። 28 ቀደም ብዬ ለፈርዖን እንደተናገርኩት እውነተኛው አምላክ ወደፊት የሚያደርገውን ነገር ለፈርዖን አሳይቶታል።

29 “በመላው የግብፅ ምድር እህል እጅግ የሚትረፈረፍባቸው ሰባት ዓመታት ይመጣሉ። 30 ከዚያ በኋላ ግን ረሃብ የሚከሰትባቸው ሰባት ዓመታት ይመጣሉ። በግብፅ ምድር እህል የተትረፈረፈበት ዘመን ፈጽሞ ይረሳል፤ ረሃቡም ምድሪቱን በእጅጉ ይጎዳል።+ 31 ከዚያ በኋላ በሚከሰተው ረሃብ የተነሳ በምድሪቱ እህል የተትረፈረፈበት ጊዜ ፈጽሞ አይታወስም፤ ምክንያቱም ረሃቡ በጣም አስከፊ ይሆናል። 32 ሕልሙ ለፈርዖን ሁለት ጊዜ መታየቱ ነገሩ በእውነተኛው አምላክ ዘንድ የተቆረጠ መሆኑን ያሳያል፤ እውነተኛውም አምላክ ይህን በቅርቡ ይፈጽመዋል።

33 “ስለሆነም አሁን ፈርዖን ልባምና ጠቢብ የሆነ ሰው ይፈልግና በግብፅ ምድር ላይ ይሹም። 34 ፈርዖን በምድሪቱ ላይ የበላይ ተመልካቾችን በመሾም እርምጃ ይውሰድ፤ እህል በሚትረፈረፍባቸው ሰባት ዓመታትም በግብፅ ምድር ከሚገኘው ምርት አንድ አምስተኛውን ያከማች።+ 35 እነሱም በመጪዎቹ መልካም ዓመታት የሚገኘውን እህል በሙሉ ይሰብስቡ፤ ለምግብነት የሚሆነውንም እህል በፈርዖን ሥልጣን ሥር በየከተማው ያከማቹ፤ የተከማቸውንም እህል ይጠብቁት።+ 36 በግብፅ ምድር ረሃብ በሚከሰትባቸው ሰባት ዓመታት ምድሪቱ በረሃቡ እንዳትጠፋ የተከማቸው እህል ለአገሪቱ ነዋሪዎች ይሰጣል።”+

37 ፈርዖንና አገልጋዮቹ በሙሉ ይህን ሐሳብ መልካም ሆኖ አገኙት። 38 በመሆኑም ፈርዖን አገልጋዮቹን “ታዲያ የአምላክ መንፈስ ያለበት እንዲህ ያለ ሌላ ሰው ሊገኝ ይችላል?” አላቸው። 39 ከዚያም ፈርዖን ዮሴፍን እንዲህ አለው፦ “አምላክ ይህን ሁሉ እንድታውቅ ስላደረገህ እንደ አንተ ያለ ልባምና ጠቢብ ሰው የለም። 40 አንተው ራስህ በቤቴ ላይ ትሾማለህ፤ ሕዝቤም ሁሉ ያላንዳች ማንገራገር ይታዘዝልሃል።+ እኔ ከአንተ የምበልጠው ንጉሥ በመሆኔ* ብቻ ይሆናል።” 41 በመቀጠልም ፈርዖን ዮሴፍን “ይኸው በግብፅ ምድር ሁሉ ላይ ሾሜሃለሁ” አለው።+ 42 ከዚያም ፈርዖን የማኅተም ቀለበቱን ከእጁ ላይ አውልቆ በዮሴፍ እጅ ላይ አደረገለት፤ ከጥሩ የተልባ እግር የተሠራ ልብስም አለበሰው፤ በአንገቱም ላይ የወርቅ ሐብል አጠለቀለት። 43 ከዚህም በላይ ከእሱ ቀጥሎ ባለው የክብር ሠረገላው ላይ አስቀመጠው፤ ሰዎችም ከፊት ከፊቱ እየሄዱ “አቭሬክ!”* እያሉ ይጮኹ ነበር። በዚህ መንገድ በመላው የግብፅ ምድር ላይ ሾመው።

44 በተጨማሪም ፈርዖን ዮሴፍን “እኔ ፈርዖን ነኝ፤ ሆኖም ያለአንተ ፈቃድ ማንም ሰው በመላው የግብፅ ምድር ላይ ምንም ነገር ማድረግ* አይችልም” አለው።+ 45 ከዚያም ፈርዖን ለዮሴፍ ጸፍናትፓነህ የሚል ስም አወጣለት፤ የኦን* ካህን የሆነውን የጶጥፌራን ልጅ አስናትንም+ አጋባው። ዮሴፍም መላውን የግብፅ ምድር መቃኘት* ጀመረ።+ 46 ዮሴፍ በግብፁ ንጉሥ በፈርዖን ፊት በቆመ* ጊዜ ዕድሜው 30 ዓመት+ ነበር።

ከዚያም ዮሴፍ ከፈርዖን ፊት ወጣ፤ መላውን የግብፅ ምድርም ተዘዋውሮ ተመለከተ። 47 እህል ይትረፈረፍባቸዋል በተባሉት ሰባት ዓመታት ምድሪቱ የተትረፈረፈ* ምርት ሰጠች። 48 በእነዚያ ሰባት ዓመታት በግብፅ ምድር የተገኘውንም እህል በሙሉ እየሰበሰበ በየከተሞቹ ያከማች ነበር። በእያንዳንዱ ከተማ ዙሪያ ከሚገኘው እርሻ የተሰበሰበውን እህል በየከተማው ያከማች ነበር። 49 በመጨረሻም ሰዎቹ እህሉን መስፈር አቅቷቸው መስፈራቸውን እስኪተዉ ድረስ ዮሴፍ እንደ ባሕር አሸዋ በጣም ብዙ የሆነ እህል አከማቸ።

50 ዮሴፍ የረሃቡ ዓመት ከመጀመሩ በፊት የኦን* ካህን ከሆነው ከጶጥፌራ ልጅ ከአስናት ሁለት ወንዶች ልጆች ወለደ።+ 51 ዮሴፍም “አምላክ የደረሰብኝን ችግር ሁሉና የአባቴን ቤት በሙሉ እንድረሳ አደረገኝ” በማለት ለበኩር ልጁ ምናሴ*+ የሚል ስም አወጣለት። 52 ሁለተኛውን ልጁን ደግሞ “መከራዬን ባየሁበት ምድር አምላክ ፍሬያማ አደረገኝ”+ በማለት ኤፍሬም*+ የሚል ስም አወጣለት።

53  ከዚያም በግብፅ ምድር እህል የተትረፈረፈባቸው ሰባት ዓመታት አበቁ፤+ 54 ልክ ዮሴፍ እንደተናገረውም ሰባቱ የረሃብ ዓመታት ጀመሩ።+ ረሃቡም በምድር ሁሉ ላይ እየሰፋ ሄደ፤ በመላው የግብፅ ምድር ግን ምግብ ነበር።+ 55 በመጨረሻም መላው የግብፅ ምድር በረሃቡ ተጠቃ፤ ሕዝቡም ምግብ ለማግኘት ወደ ፈርዖን ይጮኽ ጀመር።+ ፈርዖንም ግብፃውያንን ሁሉ “ወደ ዮሴፍ ሂዱ፤ የሚላችሁንም ሁሉ አድርጉ” ይላቸው ነበር።+ 56 ረሃቡም በመላው ምድር ላይ እየተስፋፋ ሄደ።+ ረሃቡ በግብፅ ምድር ላይ እየጸና ስለሄደ ዮሴፍ በመካከላቸው ያሉትን የእህል ጎተራዎች በሙሉ በመክፈት ለግብፃውያን እህል ይሸጥላቸው ጀመር።+ 57  በተጨማሪም ረሃቡ በመላው ምድር ላይ ክፉኛ ጸንቶ ስለነበር በመላው ምድር የሚኖሩ ሰዎች ከዮሴፍ እህል ለመግዛት ወደ ግብፅ ይመጡ ነበር።+

42 ያዕቆብ በግብፅ እህል መኖሩን+ ባወቀ ጊዜ ወንዶች ልጆቹን “ለምን ዝም ብላችሁ እርስ በርስ ትተያያላችሁ?” አላቸው። 2 ከዚያም “በግብፅ እህል እንዳለ ሰምቻለሁ። በሕይወት እንድንኖር ወደዚያ ወርዳችሁ እህል ግዙልን፤ አለዚያ ማለቃችን ነው” አላቸው።+ 3 ስለሆነም አሥሩ የዮሴፍ ወንድሞች+ እህል ለመግዛት ወደ ግብፅ ወረዱ። 4 ሆኖም ያዕቆብ የዮሴፍን ወንድም ቢንያምን+ “ምናልባት አደጋ ሊደርስበትና ሊሞትብኝ ይችላል” ብሎ ስላሰበ ከሌሎቹ ወንድሞቹ ጋር አላከውም።+

5 ረሃቡ እስከ ከነአን ምድር ድረስ ተስፋፍቶ ስለነበር የእስራኤል ወንዶች ልጆች እህል ለመግዛት ወደ ግብፅ ከሚመጡት ሰዎች ጋር አብረው መጡ።+ 6 በዚያን ጊዜ በምድሩ ላይ አስተዳዳሪ የነበረውና+ ለምድር ሕዝቦች ሁሉ እህል የሚሸጠው ዮሴፍ ነበር።+ በመሆኑም የዮሴፍ ወንድሞች መጥተው መሬት ላይ በመደፋት ሰገዱለት።+ 7 ዮሴፍም ወንድሞቹን ሲያያቸው ወዲያውኑ አወቃቸው፤ እሱ ግን ማንነቱን ከእነሱ ደበቀ።+ በመሆኑም “የመጣችሁት ከየት ነው?” በማለት በቁጣ ተናገራቸው፤ እነሱም “እህል ለመግዛት ከከነአን ምድር ነው የመጣነው” አሉት።+

8 ዮሴፍ ወንድሞቹን ያወቃቸው ቢሆንም እነሱ ግን አላወቁትም። 9 ዮሴፍም ስለ እነሱ ያያቸው ሕልሞች ወዲያው ትዝ አሉት፤+ እሱም “እናንተ ሰላዮች ናችሁ! የመጣችሁት ምድሪቱ በየት በኩል ለጥቃት እንደተጋለጠች* ለማየት ነው!” አላቸው። 10 እነሱም እንዲህ አሉት፦ “ኧረ እንደዚያ አይደለም ጌታዬ፤ እኛ አገልጋዮችህ የመጣነው እህል ለመግዛት ነው። 11 ሁላችንም የአንድ ሰው ልጆች ነን። እኛ ንጹሐን ሰዎች ነን። አገልጋዮችህ ሰላዮች አይደለንም።” 12 እሱ ግን “በፍጹም አይደለም! የመጣችሁት ምድሪቱ በየት በኩል ለጥቃት እንደተጋለጠች ለማየት ነው!” አላቸው። 13 በዚህ ጊዜ እንዲህ አሉት፦ “እኛ አገልጋዮችህ 12 ወንድማማቾች ነን።+ በከነአን ምድር የሚኖር የአንድ ሰው ልጆች ነን፤+ ትንሹ ወንድማችን አሁን ከአባታችን ጋር ነው፤+ አንደኛው ግን የለም።”+

14 ይሁን እንጂ ዮሴፍ እንዲህ አላቸው፦ “‘እናንተ ሰላዮች ናችሁ!’ አልኳችሁ እኮ፤ 15 እንግዲህ ሰላዮች መሆን አለመሆናችሁ በዚህ ይረጋገጣል፤ በፈርዖን ሕይወት እምላለሁ፣ ትንሹ ወንድማችሁ ወደዚህ ካልመጣ በስተቀር ከዚህች ንቅንቅ አትሉም።+ 16 እናንተ እዚሁ ታስራችሁ እያላችሁ ከመካከላችሁ አንዱን ላኩትና ወንድማችሁን ይዞት ይምጣ። በዚህ መንገድ የተናገራችሁት ነገር እውነት መሆን አለመሆኑ ይረጋገጣል። አለዚያ ግን በፈርዖን ሕይወት እምላለሁ፣ እናንተ ሰላዮች ናችሁ።” 17 ከዚያም ለሦስት ቀን አንድ ላይ እስር ቤት አቆያቸው።

18 በሦስተኛውም ቀን ዮሴፍ እንዲህ አላቸው፦ “እንግዲህ እኔ አምላክን ስለምፈራ እንዲህ በማድረግ ሕይወታችሁን አትርፉ። 19 እንዳላችሁት ንጹሐን ሰዎች ከሆናችሁ ከመካከላችሁ አንዱ ወንድማችሁ እዚሁ እስር ቤት ውስጥ ይቆይ፤ የቀራችሁት ግን ለተራቡት ቤተሰቦቻችሁ እህል ይዛችሁ መሄድ ትችላላችሁ።+ 20 የተናገራችሁት ቃል እውነት መሆኑ እንዲረጋገጥና ከሞት እንድትተርፉ ትንሹን ወንድማችሁን ወደ እኔ ይዛችሁት ኑ።” እነሱም እንደተባሉት አደረጉ።

21 ከዚያም እርስ በርሳቸው እንዲህ ተባባሉ፦ “ይህ ሁሉ እየደረሰብን ያለው በወንድማችን ላይ በፈጸምነው ግፍ የተነሳ እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለውም፤+ ምክንያቱም ተጨንቆ* እንድንራራለት ሲማጸነን እኛ ግን አልሰማነውም። ይህ ሁሉ መከራ እየደረሰብን ያለው በዚህ ምክንያት ነው።” 22 በዚህ ጊዜ ሮቤል እንዲህ አላቸው፦ “‘በዚህ ልጅ ላይ ክፉ ነገር አታድርጉ’ ብያችሁ አልነበረም? እናንተ ግን አልሰማችሁኝም።+ ይኸው አሁን ደሙ ከእጃችን እየተፈለገ ነው።”+ 23 ይሁንና ዮሴፍ ያነጋገራቸው በአስተርጓሚ ስለነበር ምን እየተባባሉ እንዳለ እንደሚሰማ አላወቁም ነበር። 24 በመሆኑም ከፊታቸው ዞር ብሎ አለቀሰ።+ ከዚያም ወደ እነሱ ተመልሶ በመምጣት በድጋሚ ካነጋገራቸው በኋላ ስምዖንን+ ከእነሱ ለይቶ በመውሰድ ዓይናቸው እያየ አሰረው።+ 25 በኋላም ዮሴፍ በየከረጢቶቻቸው እህል እንዲሞሉላቸው አዘዘ፤ በተጨማሪም የእያንዳንዳቸውን ገንዘብ በየከረጢቶቻቸው መልሰው እንዲያስቀምጡና ለጉዟቸው የሚሆን ስንቅ እንዲሰጧቸው ትእዛዝ አስተላለፈ። ልክ እንዳለውም ተደረገላቸው።

26 እነሱም እህላቸውን በአህዮቻቸው ላይ ጭነው ጉዞ ጀመሩ። 27 ከእነሱ መካከል አንዱ ባረፉበት ቦታ ለአህያው መኖ ለመስጠት ከረጢቱን ሲፈታ ገንዘቡን ከረጢቱ አፍ ላይ አገኘው። 28 እሱም በዚህ ጊዜ ወንድሞቹን “ኧረ ገንዘቤ ተመልሶልኛል፤ ይኸው እዚህ ከረጢቴ ውስጥ አገኘሁት!” አላቸው። እነሱም ልባቸው በፍርሃት ራደ፤ እየተንቀጠቀጡም እርስ በርሳቸው “አምላክ ያደረገብን ይህ ነገር ምንድን ነው?” ተባባሉ።

29 በከነአን ምድር ወዳለው ወደ አባታቸው ወደ ያዕቆብ በደረሱም ጊዜ ያጋጠማቸውን ሁሉ እንዲህ በማለት ነገሩት፦ 30 “የአገሩ ጌታ የሆነው ሰው በቁጣ ተናገረን፤+ አገሪቱን ለመሰለል እንደሄድን አድርጎም ቆጠረን። 31 እኛ ግን እንዲህ አልነው፦ ‘እኛ ንጹሐን ሰዎች ነን። ሰላዮች አይደለንም።+ 32 እኛ የአንድ አባት ልጆች የሆን 12 ወንድማማቾች ነን።+ አንዱ የለም፤+ ትንሹ ወንድማችን ደግሞ አሁን ከአባታችን ጋር በከነአን ምድር ይገኛል’፤+ 33 ሆኖም የአገሩ ጌታ የሆነው ሰው እንዲህ አለን፦ ‘እንግዲህ ንጹሐን ሰዎች መሆን አለመሆናችሁን በዚህ አውቃለሁ፤ አንዱ ወንድማችሁ እዚህ እኔ ጋ እንዲቆይ አድርጉ።+ የቀራችሁት ግን ለተራቡት ቤተሰቦቻችሁ የሆነ ነገር ይዛችሁ ሂዱ።+ 34 ንጹሐን ሰዎች እንጂ ሰላዮች አለመሆናችሁንም እንዳውቅ ትንሹን ወንድማችሁን ወደ እኔ ይዛችሁት ኑ። ወንድማችሁንም መልሼ እሰጣችኋለሁ፤ እናንተም በምድሪቱ መነገድ ትችላላችሁ።’”

35 እያንዳንዳቸውም ከረጢታቸውን ሲያራግፉ ገንዘባቸውን እንደተቋጠረ በከረጢታቸው ውስጥ አገኙት። እነሱም ሆኑ አባታቸው የተቋጠረውን ገንዘብ ሲያዩ ደነገጡ። 36 አባታቸው ያዕቆብም “ለሐዘን የዳረጋችሁት እኔን ነው!+ ዮሴፍ የለም፤+ ስምዖንም የለም፤+ አሁን ደግሞ ቢንያምን ልትወስዱት ነው! ኧረ ምን ጉድ ነው የመጣብኝ!” አላቸው። 37 ሮቤል ግን አባቱን “ልጁን መልሼ ባላመጣልህ ሁለቱን ወንዶች ልጆቼን ግደላቸው።+ ለእኔ በኃላፊነት ስጠኝ፤ እኔ ራሴ መልሼ አስረክብሃለሁ” አለው።+ 38 እሱ ግን እንዲህ አለ፦ “ልጄ ከእናንተ ጋር ወደዚያ አይወርድም። ምክንያቱም ወንድሙ ሞቷል፤ አሁን የቀረው እሱ ብቻ ነው።+ ከእናንተ ጋር አብሮ ሲሄድ መንገድ ላይ አደጋ ቢደርስበትና ቢሞት ሽበቴን በሐዘን+ ወደ መቃብር*+ ታወርዱታላችሁ።”

43 ረሃቡ በምድሪቱ ላይ በርትቶ ነበር።+ 2 ስለሆነም ከግብፅ ያመጡትን እህል በልተው ሲጨርሱ+ አባታቸው “ተመልሳችሁ ሂዱና ጥቂት እህል ግዙልን” አላቸው። 3 በዚህ ጊዜ ይሁዳ እንዲህ አለው፦ “ሰውየው ‘ወንድማችሁን ይዛችሁት ካልመጣችሁ በምንም ዓይነት ዳግመኛ ፊቴን አታዩም’ በማለት በግልጽ አስጠንቅቆናል።+ 4 ወንድማችንን ከእኛ ጋር የምትልከው ከሆነ ወደዚያ ወርደን እህል እንገዛልሃለን። 5 እሱን የማትልከው ከሆነ ግን ወደዚያ አንወርድም፤ ምክንያቱም ሰውየው ‘ወንድማችሁን ይዛችሁት ካልመጣችሁ በምንም ዓይነት ዳግመኛ ፊቴን አታዩም’ ብሎናል።”+ 6 እስራኤልም+ “ምነው እንዲህ ላለ ችግር ዳረጋችሁኝ? ሌላ ወንድም እንዳላችሁ ለምን ለሰውየው ነገራችሁት?” አላቸው። 7 እነሱም እንዲህ አሉት፦ “ሰውየው ‘አባታችሁ አሁንም በሕይወት አለ? ሌላስ ወንድም አላችሁ?’ በማለት በቀጥታ ስለ እኛና ስለ ዘመዶቻችን ጠየቀን፤ እኛም ለጥያቄው መልስ ሰጠነው።+ ታዲያ ‘ወንድማችሁን ይዛችሁ ኑ’ ይለናል ብለን እንዴት ልንጠረጥር እንችላለን?”+

8 ከዚያም ይሁዳ አባቱን እስራኤልን እንዲህ በማለት ለመነው፦ “እኛም ሆን አንተ እንዲሁም ትናንሽ ልጆቻችን+ በረሃብ ከምናልቅ፣ በሕይወት እንድንተርፍ+ ልጁ ከእኔ ጋር እንዲሄድ ፍቀድና+ ተነስተን ወደዚያ እንሂድ። 9 የልጁን ደህንነት በተመለከተ ኃላፊነቱን እኔ እወስዳለሁ።*+ አንድ ነገር ቢሆን እኔን ተጠያቂ ልታደርገኝ ትችላለህ። ልጁን ወደ አንተ መልሼ ባላመጣውና ባላስረክብህ በሕይወቴ ሙሉ በፊትህ በደለኛ ልሁን። 10 ዝም ብለን ጊዜ ባናጠፋ ኖሮ እስካሁን ሁለት ጊዜ እዚያ ደርሰን በተመለስን ነበር።”

11 በመሆኑም አባታቸው እስራኤል እንዲህ አላቸው፦ “እንግዲህ ሌላ አማራጭ ከጠፋ እንዲህ አድርጉ፦ ምድሪቱ ከምታፈራቸው ምርጥ ነገሮች መካከል ጥቂት በለሳን፣+ ጥቂት ማር፣ ጥሩ መዓዛ ያለው ሙጫ፣ ከርቤ፣+ ለውዝና አልሞንድ ለሰውየው ስጦታ+ እንዲሆን በከረጢቶቻችሁ ይዛችሁ ውረዱ። 12 በተጨማሪም እጥፍ ገንዘብ ያዙ፤ በከረጢቶቻችሁ አፍ ላይ ተደርጎ የተመለሰላችሁንም ገንዘብ ይዛችሁ ሂዱ።+ ምናልባት በስህተት የመጣ ሊሆን ይችላል። 13 በሉ ተነሱና ወንድማችሁን ይዛችሁ ወደ ሰውየው ሂዱ። 14 ሌላውን ወንድማችሁንና ቢንያምን እንዲለቅላችሁ ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ የሰውየውን ልብ ያራራላችሁ። እንግዲህ ልጆቼን አጥቼ ለሐዘን ከተዳረግኩም ምን አደርጋለሁ፤ የመጣውን እቀበላለሁ!”+

15 ስለዚህ ሰዎቹ ይህን ስጦታና እጥፍ ገንዘብ እንዲሁም ቢንያምን ይዘው ተነሱ። ወደ ግብፅም ወረዱ፤ እንደገናም ዮሴፍ ፊት ቀረቡ።+ 16 ዮሴፍ ቢንያምን ከእነሱ ጋር ሲያየው የቤቱ ኃላፊ የሆነውን ሰው ወዲያውኑ እንዲህ አለው፦ “ሰዎቹን ወደ ቤት ውሰዳቸው፤ አብረውኝ ምሳ ስለሚበሉ እንስሳ አርደህ ምግብ አዘጋጅ።” 17 ሰውየውም ወዲያውኑ ልክ ዮሴፍ እንዳለው አደረገ፤+ ሰዎቹንም ወደ ዮሴፍ ቤት ወሰዳቸው። 18 ሰዎቹ ግን ወደ ዮሴፍ ቤት ሲወሰዱ ፈሩ፤ እንዲህም ይሉ ጀመር፦ “ወደዚህ ያመጡን ባለፈው ጊዜ በከረጢቶቻችን ውስጥ በተመለሰው ገንዘብ የተነሳ ነው። በቃ አሁን ያሠቃዩናል፤ ባሪያ ያደርጉናል፤ አህዮቻችንንም ይቀሙናል!”+

19 በመሆኑም የዮሴፍ ቤት ኃላፊ ወደሆነው ሰው ቀርበው በቤቱ በራፍ ላይ አነጋገሩት። 20 እነሱም እንዲህ አሉት፦ “ይቅርታ ጌታዬ! እኛ ባለፈው ጊዜ ወደዚህ የመጣነው እህል ለመግዛት ነበር።+ 21 ሆኖም የምናርፍበት ቦታ ደርሰን ከረጢቶቻችንን ስንከፍት የእያንዳንዳችንን ገንዘብ ምንም ሳይጎድል በየከረጢታችን አፍ ላይ አገኘነው።+ ስለዚህ ራሳችን ገንዘቡን መመለስ እንፈልጋለን። 22 እህል ለመግዛት ተጨማሪ ገንዘብ ይዘናል። ገንዘባችንን በከረጢታችን ውስጥ መልሶ ያስቀመጠው ማን እንደሆነ አናውቅም።”+ 23 እሱም “አይዟችሁ፣ አትፍሩ። ይህን ገንዘብ በከረጢቶቻችሁ ውስጥ ያስቀመጠላችሁ የእናንተ አምላክና የአባታችሁ አምላክ ነው። እኔ እንደሆነ ገንዘባችሁ ደርሶኛል” አላቸው። ከዚያም ስምዖንን አውጥቶ ወደ እነሱ አመጣው።+

24 ከዚያም ሰውየው ሰዎቹን ወደ ዮሴፍ ቤት አስገባቸው፤ እግራቸውን እንዲታጠቡም ውኃ አቀረበላቸው፤ እንዲሁም ለአህዮቻቸው ገፈራ ሰጣቸው። 25 እነሱም እዚያው ምሳ እንደሚበሉ+ ስለሰሙ ዮሴፍ ቀትር ላይ ሲመጣ የሚሰጡትን ስጦታ+ ማዘገጃጀት ጀመሩ። 26 ዮሴፍ ወደ ቤት ሲገባ፣ ያዘጋጁትን ስጦታ ይዘው ወደ እሱ በመግባት አበረከቱለት፤ መሬት ላይም ተደፍተው ሰገዱለት።+ 27 ከዚያም ስለ ደህንነታቸው ጠየቃቸው፤ እንዲህም አላቸው፦ “ባለፈው ጊዜ የነገራችሁኝ አረጋዊ አባታችሁ ደህና ነው? አሁንም በሕይወት አለ?”+ 28 እነሱም “አገልጋይህ አባታችን ደህና ነው። አሁንም በሕይወት አለ” አሉት። ከዚያም መሬት ላይ ተደፍተው ሰገዱ።+

29 ዮሴፍም ቀና ብሎ ሲመለከት የእናቱን ልጅ ወንድሙን+ ቢንያምን አየ፤ እሱም “ባለፈው ጊዜ ስለ እሱ የነገራችሁኝ ትንሹ ወንድማችሁ ይሄ ነው?” አላቸው።+ ቢንያምንም “የእኔ ልጅ፣ አምላክ ሞገሱን ያሳይህ” አለው። 30 ዮሴፍ ወንድሙን ሲያይ ስሜቱን መቆጣጠር ስላቃተው በፍጥነት ወጣ፤ የሚያለቅስበትንም ቦታ ፈለገ። ብቻውን ወደ አንድ ክፍል ገብቶም አለቀሰ።+ 31 ከዚያም ፊቱን ተጣጥቦ ወጣ፤ እንደ ምንም ስሜቱን ተቆጣጥሮም “ምግብ ይቅረብ” አለ። 32 እነሱም ለዮሴፍ ለብቻው አቀረቡለት፤ ለእነሱም ለብቻቸው አቀረቡላቸው። እንዲሁም በቤቱ ለሚበሉት ግብፃውያን ለብቻቸው አቀረቡላቸው። ይህን ያደረጉት ግብፃውያን ከዕብራውያን ጋር አብረው ምግብ ስለማይበሉ ነው፤ ምክንያቱም ይህ ለግብፃውያን አስጸያፊ ነገር ነው።+

33 ወንድማማቾቹም* የበኩሩ እንደ ብኩርና መብቱ፣+ ታናሹም እንደ ታናሽነቱ በፊቱ ተቀመጡ፤ እርስ በርሳቸውም በመገረም ይተያዩ ነበር። 34 እሱም ፊቱ ከቀረበው ምግብ እየተነሳ ለእነሱ እንዲሰጣቸው ያደርግ ነበር፤ የቢንያም ድርሻ ግን ከሌሎቹ አምስት እጥፍ እንዲበልጥ ያደርግ ነበር።+ እነሱም እስኪጠግቡ ድረስ አብረውት በሉ፣ ጠጡም።

44 ከዚህ በኋላ ዮሴፍ የቤቱ ኃላፊ የሆነውን ሰው እንዲህ ሲል አዘዘው፦ “የቻሉትን ያህል እህል በየከረጢቶቻቸው ሙላላቸው፤ የእያንዳንዳቸውንም ገንዘብ በየከረጢቶቻቸው አፍ ላይ አድርገው።+ 2 ሆኖም የእኔን ጽዋ ይኸውም የብር ጽዋዬን ውሰድና እህል ለመግዛት ካመጣው ገንዘብ ጋር አድርገህ በትንሹ ወንድማቸው ከረጢት አፍ ላይ አድርገው።” እሱም ልክ ዮሴፍ እንዳዘዘው አደረገ።

3 ሰዎቹም ማለዳ ላይ ጎህ ሲቀድ ከነአህዮቻቸው ተሸኙ። 4 እነሱም ከከተማዋ ብዙም ርቀው ሳይሄዱ ዮሴፍ የቤቱ ኃላፊ የሆነውን ሰው እንዲህ አለው፦ “ተነስ! ሰዎቹን ተከታተላቸው! ስትደርስባቸውም እንዲህ በላቸው፦ ‘ለተደረገላችሁ መልካም ነገር ክፉ የመለሳችሁት ለምንድን ነው? 5 ይህ ጌታዬ የሚጠጣበትና የሚጠነቁልበት ጽዋ አይደለም? የፈጸማችሁት ድርጊት በጣም አሳፋሪ ነው።’”

6 እሱም ተከታትሎ ደረሰባቸውና ልክ እንደተባለው አላቸው። 7 እነሱ ግን እንዲህ አሉት፦ “ጌታዬ እንዲህ ያለ ነገር የሚናገረው ለምንድን ነው? አገልጋዮችህ እንዲህ ያለ ነገር ያደርጋሉ ማለት ፈጽሞ የማይታሰብ ነው። 8 በከረጢቶቻችን አፍ ላይ ያገኘነውን ገንዘብ እንኳ ከከነአን ምድር ድረስ ይዘን ወደ አንተ መጥተን የለም?+ ታዲያ ከጌታህ ቤት ብር ወይም ወርቅ እንዴት እንሰርቃለን? 9 ከእኛ ከባሪያዎችህ መካከል የተገኘበት ቢኖር ያ ሰው ይገደል፤ የቀረነውም ለጌታዬ ባሪያዎች እንሆናለን።” 10 እሱም “እሺ፣ እንዳላችሁት ይሁን፤ ጽዋው የተገኘበት ሰው ባሪያዬ ይሆናል፤ የቀራችሁት ግን ነፃ ትሆናላችሁ” አላቸው። 11 ከዚያም እያንዳንዳቸው ወዲያውኑ ከረጢታቸውን መሬት አውርደው መፍታት ጀመሩ። 12 እሱም ከታላቁ ጀምሮ እስከ ታናሹ ድረስ በጥንቃቄ ፈተሸ። በመጨረሻም ጽዋው በቢንያም ከረጢት ውስጥ ተገኘ።+

13 በዚህ ጊዜ ልብሳቸውን ቀደዱ፤ እያንዳንዳቸውም ጓዛቸውን መልሰው በአህዮቻቸው ላይ በመጫን ወደ ከተማዋ ተመለሱ። 14 ይሁዳና+ ወንድሞቹ ወደ ዮሴፍ ቤት ሲገቡ ዮሴፍ ገና ከቤት አልወጣም ነበር፤ እነሱም በፊቱ መሬት ላይ ተደፉ።+ 15 ዮሴፍም “ይህ ያደረጋችሁት ነገር ምንድን ነው? እንደ እኔ ያለ ሰው ማንኛውንም ነገር በጥንቆላ የማወቅ ችሎታ እንዳለው አታውቁም?” አላቸው።+ 16 በዚህ ጊዜ ይሁዳ እንዲህ አለ፦ “እንግዲህ ለጌታዬ ምን ማለት እንችላለን? ምንስ አፍ አለን? ጻድቅ መሆናችንን እንዴት ማረጋገጥ እንችላለን? እውነተኛው አምላክ ባሪያዎችህ የፈጸሙትን ስህተት አጋልጧል።+ እንግዲህ እኛም ሆን ጽዋው የተገኘበት ሰው ለጌታዬ ባሪያዎች እንሆናለን!” 17 እሱ ግን እንዲህ አላቸው፦ “ይህንማ ፈጽሞ አላደርገውም! ባሪያዬ የሚሆነው ጽዋው የተገኘበት ሰው ነው።+ የቀራችሁት ግን ወደ አባታችሁ በሰላም ሂዱ።”

18 ይሁዳም ወደ እሱ ቀርቦ እንዲህ አለው፦ “እባክህ ጌታዬ እማጸንሃለሁ፤ ባሪያህ አንዲት ቃል ብቻ ይናገር፤ ጌታዬም ይስማው፤ እባክህ በባሪያህ ላይ አትቆጣ፤ ምክንያቱም አንተ ልክ እንደ ፈርዖን ነህ።+ 19 ጌታዬ እኛን ባሪያዎቹን ‘አባት ወይም ወንድም አላችሁ?’ በማለት ጠይቆን ነበር። 20 እኛም ለጌታዬ እንዲህ ስንል መለስንለት፦ ‘አረጋዊ አባት አለን፤ እንዲሁም በስተርጅናው የወለደው የሁላችንም ታናሽ የሆነ ወንድም አለን።+ ወንድሙ ግን ሞቷል፤+ በመሆኑም ከአንድ እናት ከተወለዱት መካከል የቀረው እሱ ብቻ ነው፤+ አባቱም በጣም ይወደዋል።’ 21 ከዚያም አንተ እኛን ባሪያዎችህን ‘እንዳየው ወደ እኔ አምጡት’ አልከን።+ 22 እኛ ግን ጌታዬን ‘ልጁ ከአባቱ ሊለይ አይችልም። ከተለየው ደግሞ አባቱ ያለጥርጥር ይሞታል’+ አልነው። 23 አንተም እኛን ባሪያዎችህን ‘ትንሹን ወንድማችሁን ይዛችሁት ካልመጣችሁ ከእንግዲህ ፊቴን አታዩም’ አልከን።+

24 “በመሆኑም ወደ ባሪያህ ወደ አባታችን ሄደን የጌታዬን ቃል ነገርነው። 25 ከጊዜ በኋላም አባታችን ‘ተመልሳችሁ ሂዱና ጥቂት እህል ግዙልን’ አለን።+ 26 እኛ ግን እንዲህ አልነው፦ ‘ወደዚያ መሄድ አንችልም። ትንሹ ወንድማችን ከእኛ ጋር ካልሄደ የሰውየውን ፊት ማየት ስለማንችል ትንሹ ወንድማችን አብሮን የሚሄድ ከሆነ ወደዚያ እንወርዳለን።’+ 27 በዚህ ጊዜ ባሪያህ አባታችን እንዲህ አለን፦ ‘ሚስቴ ከሁለት ወንዶች ልጆች ሌላ ምንም እንዳልወለደችልኝ እናንተ ራሳችሁ በሚገባ ታውቃላችሁ።+ 28 ሆኖም አንዱ እንደወጣ በመቅረቱ “መቼም አውሬ ቦጫጭቆት መሆን አለበት!” አልኩ፤+ ይኸው ከዚያን ጊዜ ወዲህ አይቼው አላውቅም። 29 ይሄኛውንም ልጅ ከእኔ ለይታችሁ ብትወስዱትና አደጋ ደርሶበት ቢሞት ሽበቴን በሥቃይ+ ወደ መቃብር*+ ታወርዱታላችሁ።’

30 “እንግዲህ ወደ ባሪያህ ወደ አባቴ ስመለስ ልጁ ከእኛ ጋር ከሌለ፣ የአባታችን ሕይወት* ከልጁ ሕይወት* ጋር በጥብቅ የተቆራኘ ስለሆነ 31 አባታችን ልጁ አብሮን አለመኖሩን ሲያይ ይሞታል፤ ባሪያዎችህም የባሪያህን የአባታችንን ሽበት በሐዘን ወደ መቃብር* ያወርዱታል። 32 እኔ ባሪያህ ‘ልጁን ወደ አንተ መልሼ ባላመጣው በአባቴ ፊት ለዘላለም በደለኛ ልሁን’ ብዬ ለአባቴ ቃል ገብቻለሁ።+ 33 ስለዚህ እባክህ ልጁ ከወንድሞቹ ጋር እንዲሄድ እኔ ባሪያህ በልጁ ፋንታ እዚሁ ቀርቼ ለጌታዬ ባሪያ ልሁን። 34 ልጁን ሳልይዝ እንዴት ወደ አባቴ እመለሳለሁ? በአባቴ ላይ እንዲህ ያለ መከራ ሲደርስ ማየት አልችልም!”

45 በዚህ ጊዜ ዮሴፍ አጠገቡ በነበሩት አገልጋዮቹ ፊት ስሜቱን መቆጣጠር አልቻለም።+ በመሆኑም “ሁሉንም ሰው አስወጡልኝ!” በማለት ጮኸ። ዮሴፍ ራሱን ለወንድሞቹ በገለጠበት+ ወቅት ከእሱ ጋር ማንም ሰው አልነበረም።

2 ከዚያም ጮክ ብሎ ማልቀስ ጀመረ፤ ግብፃውያንም ሰሙት፤ በፈርዖንም ቤት ተሰማ። 3 በመጨረሻም ዮሴፍ ወንድሞቹን “እኔ ዮሴፍ ነኝ። አባቴ እስካሁን በሕይወት አለ?” አላቸው። ወንድሞቹ ግን በሁኔታው በጣም ስለደነገጡ ምንም ሊመልሱለት አልቻሉም። 4 ስለሆነም ዮሴፍ ወንድሞቹን “እባካችሁ ወደ እኔ ቅረቡ” አላቸው። እነሱም ወደ እሱ ቀረቡ።

ከዚያም እንዲህ አላቸው፦ “እኔ ወደ ግብፅ የሸጣችሁኝ ወንድማችሁ ዮሴፍ ነኝ።+ 5 አሁን ግን እኔን ወደዚህ በመሸጣችሁ አትዘኑ፤ እርስ በርሳችሁም አትወቃቀሱ፤ ምክንያቱም አምላክ ከእናንተ አስቀድሞ የላከኝ ሕይወት ለማዳን ሲል ነው።+ 6 ረሃቡ በምድር ላይ ከጀመረ ይህ ሁለተኛ ዓመቱ ነው፤+ ምንም የማይታረስባቸውና አዝመራ የማይሰበሰብባቸው አምስት ዓመታት ገና ይቀራሉ። 7 አምላክ ግን በምድር ላይ ዘራችሁን ሊያስቀርና+ በታላቅ ማዳን ሕይወታችሁን ሊታደግ ከእናንተ አስቀድሞ ላከኝ። 8 ስለዚህ ለፈርዖን ዋና አማካሪ፣* በቤቱም ሁሉ ላይ ጌታ እንዲሁም በመላው የግብፅ ምድር ላይ ገዢ ሊያደርገኝ+ ወደዚህ የላከኝ እውነተኛው አምላክ እንጂ እናንተ አይደላችሁም።

9 “ቶሎ ብላችሁ ወደ አባቴ ሂዱና እንዲህ በሉት፦ ‘ልጅህ ዮሴፍ እንዲህ ይላል፦ “አምላክ በመላው ግብፅ ላይ ጌታ አድርጎኛል።+ ሳትዘገይ ወደ እኔ ና።+ 10 ወንዶች ልጆችህን፣ የልጅ ልጆችህን፣ መንጎችህን፣ ከብቶችህንና ያለህን ነገር በሙሉ ይዘህ በመምጣት በአቅራቢያዬ በጎሸን ምድር ትኖራለህ።+ 11 ረሃቡ ገና ለአምስት ዓመታት ስለሚቀጥል እኔ የሚያስፈልግህን ምግብ እሰጥሃለሁ።+ አለዚያ አንተም ሆንክ ቤትህ እንዲሁም የአንተ የሆነው ሁሉ ችግር ላይ ትወድቃላችሁ።”’ 12 እንግዲህ አሁን እያናገርኳችሁ ያለሁት እኔው ራሴ መሆኔን እናንተም ሆናችሁ ወንድሜ ቢንያም በገዛ ዓይናችሁ አይታችኋል።+ 13 በመሆኑም በግብፅ ስላለኝ ክብር ሁሉ እንዲሁም ስላያችሁት ስለ ማንኛውም ነገር ለአባቴ ንገሩት። አሁንም በፍጥነት ሄዳችሁ አባቴን ወደዚህ ይዛችሁት ኑ።”

14 ከዚያም በወንድሙ በቢንያም አንገት ላይ ተጠምጥሞ አለቀሰ፤ ቢንያምም አንገቱን አቅፎት አለቀሰ።+ 15 የቀሩትን ወንድሞቹንም አንድ በአንድ እየሳመ አለቀሰ፤ ከዚህ በኋላም ወንድሞቹ ከእሱ ጋር ማውራት ጀመሩ።

16 “የዮሴፍ ወንድሞች መጥተዋል!” የሚለው ወሬ በፈርዖን ቤት ተሰማ። ፈርዖንና አገልጋዮቹም ደስ አላቸው። 17 ስለዚህ ፈርዖን ዮሴፍን እንዲህ አለው፦ “ወንድሞችህን እንዲህ በላቸው፦ ‘እንዲህ አድርጉ፦ የጋማ ከብቶቻችሁን ጫኑና ወደ ከነአን ምድር ሂዱ። 18 የግብፅን ምድር መልካም ነገሮች እንድሰጣችሁ አባታችሁንና ቤተሰባችሁን ይዛችሁ ወደ እኔ ኑ፤ ከዚያም ለም* ከሆነው የምድሪቱ ክፍል ትበላላችሁ።’+ 19 አንተንም እንዲህ ብለህ እንድትነግራቸው አዝዤሃለሁ፦+ ‘እንዲህ አድርጉ፦ ልጆቻችሁንና ሚስቶቻችሁን የምታጓጉዙባቸውን ሠረገሎች ከግብፅ ምድር ውሰዱ፤+ አባታችሁንም በአንዱ ሠረገላ ላይ ጭናችሁ ወደዚህ ኑ።+ 20 ስለ ንብረታችሁ+ ምንም አትጨነቁ፤ ምክንያቱም በግብፅ ምድር ያለ ምርጥ ነገር ሁሉ የእናንተው ነው።’”

21 የእስራኤልም ወንዶች ልጆች እንደተባሉት አደረጉ፤ ዮሴፍ በፈርዖን ትእዛዝ መሠረት ሠረገሎችን ሰጣቸው፤ ለጉዟቸው የሚሆን ስንቅም አስያዛቸው። 22 ለእያንዳንዳቸው ቅያሪ ልብስ ሰጣቸው፤ ለቢንያም ግን 300 የብር ሰቅልና አምስት ቅያሪ ልብስ ሰጠው።+ 23 ለአባቱም የግብፅን ምድር መልካም ነገሮች የጫኑ አሥር አህዮችን እንዲሁም ለጉዞ ስንቅ እንዲሆነው እህል፣ ዳቦና ሌሎች ምግቦችን የጫኑ አሥር እንስት አህዮችን ላከ። 24 በዚህ መንገድ ወንድሞቹን ሸኛቸው፤ እነሱም ጉዞ ሲጀምሩ “ደግሞ በመንገድ ላይ እርስ በርስ እንዳትጣሉ” አላቸው።+

25 እነሱም ከግብፅ ወጥተው ሄዱ፤ በከነአን ምድር ወዳለው ወደ አባታቸው ወደ ያዕቆብም መጡ። 26 ከዚያም “ዮሴፍ በሕይወት አለ፤ ደግሞም በመላው የግብፅ ምድር ላይ ገዢ ሆኗል!”+ ሲሉ ነገሩት። እሱ ግን ክው ብሎ ቀረ፤ ሊያምናቸውም አልቻለም።+ 27 ዮሴፍ የነገራቸውን ነገር በሙሉ ሲነግሩትና ዮሴፍ እሱን ለመውሰድ የላካቸውን ሠረገሎች ሲያይ የአባታቸው የያዕቆብ መንፈስ ታደሰ። 28 እስራኤልም “በቃ አምኛችኋለሁ! ልጄ ዮሴፍ በሕይወት አለ! እንግዲህ ከመሞቴ በፊት ሄጄ ዓይኑን ማየት አለብኝ!” አላቸው።+

46 በመሆኑም እስራኤል ያለውን* ሁሉ ይዞ ተነሳ። ቤርሳቤህ+ በደረሰ ጊዜም ለአባቱ ለይስሐቅ አምላክ+ መሥዋዕቶችን አቀረበ። 2 ከዚያም አምላክ ለእስራኤል ሌሊት በራእይ ተገልጦለት “ያዕቆብ፣ ያዕቆብ!” ሲል ጠራው፤ እሱም “አቤት!” አለ። 3 አምላክም እንዲህ አለው፦ “እኔ የአባትህ አምላክ የሆንኩት እውነተኛው አምላክ ነኝ።+ ወደ ግብፅ ለመውረድ አትፍራ፤ ምክንያቱም በዚያ ታላቅ ብሔር አደርግሃለሁ።+ 4 እኔ ራሴ ከአንተ ጋር ወደ ግብፅ እወርዳለሁ፤ ደግሞም እኔ ራሴ ከዚያ አወጣሃለሁ፤+ ዮሴፍም ዓይኖችህን በእጁ ይከድናል።”*+

5 ከዚያ በኋላ ያዕቆብ ከቤርሳቤህ ተነሳ፤ የእስራኤል ወንዶች ልጆችም አባታቸውን ያዕቆብን፣ ልጆቻቸውንና ሚስቶቻቸውን ፈርዖን በላከለት ሠረገሎች ላይ አሳፍረው ጉዞ ጀመሩ። 6 እነሱም በከነአን ምድር ያፈሩትን ንብረትና መንጎቻቸውን ይዘው ሄዱ። ከዚያም ያዕቆብና ከእሱ ጋር የነበሩት ልጆቹ በሙሉ ወደ ግብፅ መጡ። 7 እሱም ወንዶች ልጆቹንና ወንዶች የልጅ ልጆቹን እንዲሁም ሴቶች ልጆቹንና ሴቶች የልጅ ልጆቹን ይኸውም ዘሮቹን ሁሉ ይዞ ወደ ግብፅ መጣ።

8 ወደ ግብፅ የመጡት የእስራኤል ማለትም የያዕቆብ ወንዶች ልጆች ስም ይህ ነው፦+ የያዕቆብ የበኩር ልጅ ሮቤል።+

9 የሮቤል ወንዶች ልጆች ሃኖክ፣ ፓሉ፣ ኤስሮን እና ካርሚ ነበሩ።+

10 የስምዖን+ ወንዶች ልጆች የሙኤል፣ ያሚን፣ ኦሃድ፣ ያኪን፣ ጾሃር እንዲሁም ከአንዲት ከነአናዊት የወለደው ሻኡል ነበሩ።+

11 የሌዊ+ ወንዶች ልጆች ጌድሶን፣ ቀአት እና ሜራሪ ነበሩ።+

12 የይሁዳ+ ወንዶች ልጆች ኤር፣ ኦናን፣ ሴሎም፣+ ፋሬስ+ እና ዛራ+ ነበሩ፤ ይሁንና ኤር እና ኦናን በከነአን ምድር ሞቱ።+

የፋሬስ ወንዶች ልጆች ኤስሮን እና ሃሙል ነበሩ።+

13 የይሳኮር ወንዶች ልጆች ቶላ፣ ፑዋ፣ ዮብ እና ሺምሮን ነበሩ።+

14 የዛብሎን+ ወንዶች ልጆች ሰሬድ፣ ኤሎን እና ያህልኤል ነበሩ።+

15 ሴት ልጁን ዲናን+ ጨምሮ እነዚህ ሊያ በጳዳንአራም ለያዕቆብ የወለደችለት ልጆች ናቸው። በአጠቃላይ ወንዶች ልጆቹና ሴቶች ልጆቹ 33 ነበሩ።*

16 የጋድ+ ወንዶች ልጆች ጺፍዮን፣ ሃጊ፣ ሹኒ፣ ኤጽቦን፣ ኤሪ፣ አሮድ እና አርዔላይ ነበሩ።+

17 የአሴር+ ወንዶች ልጆች ይምናህ፣ ይሽዋ፣ ይሽዊ እና በሪአ ሲሆኑ እህታቸውም ሴራህ ትባላለች።

የበሪአ ወንዶች ልጆች ሄቤር እና ማልኪኤል ነበሩ።+

18 ላባ ለልጁ ለሊያ የሰጣት ዚልጳ+ የተባለችው አገልጋይ የወለደቻቸው ወንዶች ልጆች እነዚህ ናቸው። እሷም ለያዕቆብ እነዚህን ወለደችለት፤ እነሱም በአጠቃላይ 16* ነበሩ።

19 የያዕቆብ ሚስት የራሔል ወንዶች ልጆች ዮሴፍና+ ቢንያም+ ነበሩ።

20 ዮሴፍ በግብፅ ምድር ሳለ ምናሴንና+ ኤፍሬምን*+ ወለደ፤ እነዚህም የኦን* ካህን የሆነው የጶጥፌራ ልጅ አስናት+ የወለደችለት ናቸው።

21 የቢንያም+ ወንዶች ልጆች ቤላ፣ ቤኬር፣ አሽቤል፣ ጌራ፣+ ንዕማን፣ ኤሂ፣ ሮሽ፣ ሙጲም፣ ሁፒም+ እና አርድ+ ነበሩ።

22 እነዚህ ራሔል ለያዕቆብ የወለደችለት ወንዶች ልጆች ናቸው፤ እነሱም በአጠቃላይ 14* ነበሩ።

23 የዳን+ ልጅ* ሁሺም+ ነበር።

24 የንፍታሌም+ ወንዶች ልጆች ያህጽኤል፣ ጉኒ፣ የጼር እና ሺሌም ነበሩ።+

25 ላባ ለልጁ ለራሔል የሰጣት ባላ የተባለችው አገልጋይ የወለደቻቸው ወንዶች ልጆች እነዚህ ናቸው። እሷም ለያዕቆብ እነዚህን ወለደችለት፤ እነሱም በአጠቃላይ ሰባት* ነበሩ።

26 የያዕቆብ ዝርያዎች የሆኑትና ከእሱ ጋር ወደ ግብፅ የገቡት ሰዎች፣* የልጆቹን ሚስቶች ሳይጨምር በአጠቃላይ 66 ነበሩ።+ 27 ዮሴፍ በግብፅ የወለዳቸው ወንዶች ልጆች ሁለት* ነበሩ። ወደ ግብፅ የገቡት የያዕቆብ ቤተሰቦች በአጠቃላይ 70* ነበሩ።+

28 ያዕቆብ ወደ ጎሸን እየሄደ መሆኑን ለዮሴፍ እንዲነግረው ይሁዳን+ ከእሱ አስቀድሞ ላከው። ወደ ጎሸን ምድር+ በደረሱም ጊዜ 29 ዮሴፍ ሠረገላው እንዲዘጋጅለት ካደረገ በኋላ አባቱን እስራኤልን ለመቀበል ወደ ጎሸን ሄደ። ባገኘውም ጊዜ አንገቱ ላይ ተጠምጥሞ ረዘም ላለ ጊዜ አለቀሰ። 30 ከዚያም እስራኤል ዮሴፍን “ከእንግዲህ ብሞት አይቆጨኝም፤ ዓይንህን ለማየት በቅቻለሁ፤ በሕይወት መኖርህንም አረጋግጫለሁ” አለው።

31 ከዚያም ዮሴፍ ወንድሞቹንና የአባቱን ቤተሰቦች እንዲህ አላቸው፦ “ወደ ፈርዖን ወጥቼ ሁኔታውን ልንገረው፤+ እንዲህም ልበለው፦ ‘በከነአን ምድር ይኖሩ የነበሩት ወንድሞቼና የአባቴ ቤተሰቦች ወደ እኔ መጥተዋል።+ 32 እነሱ እረኞችና+ ከብት አርቢዎች+ ናቸው፤ መንጎቻቸውን፣ ከብቶቻቸውንና ያላቸውን ሁሉ ይዘው መጥተዋል።’+ 33 እንግዲህ ፈርዖን ጠርቶ ‘ሥራችሁ ምንድን ነው?’ ብሎ ሲጠይቃችሁ 34 ‘እኛ አገልጋዮችህም ሆን የቀድሞ አባቶቻችን ከልጅነታችን ጀምሮ ከብት አርቢዎች ነን’ በሉት።+ ግብፃውያን በግ ጠባቂዎችን ስለሚጸየፉ+ በጎሸን ምድር እንድትኖሩ+ ይፈቅድላችኋል።”

47 ስለዚህ ዮሴፍ ወደ ፈርዖን ሄዶ “አባቴና ወንድሞቼ እንዲሁም መንጎቻቸው፣ ከብቶቻቸውና የእነሱ የሆነው ሁሉ ከከነአን ምድር መጥተዋል፤ በጎሸን ምድር ይገኛሉ”+ አለው።+ 2 እሱም ከወንድሞቹ መካከል አምስቱን ወስዶ ፈርዖን ፊት አቀረባቸው።+

3 ፈርዖንም የዮሴፍን ወንድሞች “ሥራችሁ ምንድን ነው?” ሲል ጠየቃቸው። እነሱም “እኛ አገልጋዮችህም ሆን የቀድሞ አባቶቻችን በግ አርቢዎች ነን” በማለት መለሱለት።+ 4 ከዚያም ፈርዖንን እንዲህ አሉት፦ “ወደዚህ የመጣነው በምድሪቱ ላይ እንደ ባዕድ አገር ሰው ሆነን ለመኖር ነው፤+ ምክንያቱም በከነአን ምድር ረሃቡ በጣም ስለበረታ ለአገልጋዮችህ መንጋ የሚሆን የግጦሽ ቦታ የለም።+ ስለሆነም እባክህ አገልጋዮችህ በጎሸን ምድር እንዲኖሩ ፍቀድላቸው።”+ 5 በዚህ ጊዜ ፈርዖን ዮሴፍን እንዲህ አለው፦ “አባትህና ወንድሞችህ ወደ አንተ መጥተዋል። 6 የግብፅ ምድር እንደሆነ በእጅህ ነው። አባትህና ወንድሞችህ ምርጥ በሆነው የምድሪቱ ክፍል እንዲኖሩ አድርግ።+ በጎሸን ምድር ይኑሩ፤ ከእነሱ መካከል ጥሩ ችሎታ እንዳላቸው የምታውቃቸው ሰዎች ካሉ በከብቶቼ ላይ ኃላፊ አድርገህ ሹማቸው።”

7 ከዚያም ዮሴፍ አባቱን ያዕቆብን አስገብቶ ፈርዖን ፊት አቀረበው፤ ያዕቆብም ፈርዖንን ባረከው። 8 ፈርዖንም ያዕቆብን “ለመሆኑ ዕድሜህ ስንት ነው?” ሲል ጠየቀው። 9 ያዕቆብም ፈርዖንን እንዲህ አለው፦ “ከቦታ ወደ ቦታ በመንከራተት* ያሳለፍኩት ዘመን 130 ዓመት ነው። የሕይወት ዘመኔ አጭርና ጭንቀት የበዛበት ነበር፤+ ደግሞም አባቶቼ ከቦታ ወደ ቦታ በመንከራተት* ያሳለፉትን ዘመን አያክልም።”+ 10 ከዚህ በኋላ ያዕቆብ ፈርዖንን መረቀው፤ ከፊቱም ወጥቶ ሄደ።

11 በመሆኑም ዮሴፍ፣ አባቱና ወንድሞቹ እንዲሰፍሩ አደረገ፤ ፈርዖንም ባዘዘው መሠረት ምርጥ ከሆነው የግብፅ ምድር፣ የራምሴስን ምድር ርስት አድርጎ ሰጣቸው።+ 12 ዮሴፍም ለአባቱ፣ ለወንድሞቹና ለመላው የአባቱ ቤተሰብ በትናንሽ ልጆቻቸው ቁጥር ልክ ቀለብ ይሰፍርላቸው ነበር።

13 በዚህ ወቅት ረሃቡ እጅግ በርትቶ ስለነበር በመላው ምድር እህል አልነበረም፤ የግብፅም ምድር ሆነ የከነአን ምድር በረሃቡ የተነሳ በጣም ተጎድተው ነበር።+ 14 ዮሴፍም ሰዎች እህል ሲገዙ የከፈሉትን በግብፅ ምድርና በከነአን ምድር የሚገኘውን ገንዘብ በሙሉ እየሰበሰበ ወደ ፈርዖን ቤት ያስገባ ነበር።+ 15 ከጊዜ በኋላ በግብፅ ምድርና በከነአን ምድር ያለው ገንዘብ አለቀ፤ ግብፃውያንም በሙሉ ወደ ዮሴፍ በመምጣት “እህል ስጠን! ገንዘብ ስለጨረስን ብቻ እንዴት ዓይንህ እያየ እንለቅ?” ይሉት ጀመር። 16 ዮሴፍም “ገንዘባችሁ ካለቀ ከብቶቻችሁን አምጡ፤ እኔም በከብቶቻችሁ ምትክ እህል እሰጣችኋለሁ” አላቸው። 17 በመሆኑም ከብቶቻቸውን ወደ ዮሴፍ ያመጡ ጀመር፤ ዮሴፍም በፈረሶቻቸው፣ በመንጎቻቸው፣ በከብቶቻቸውና በአህዮቻቸው ምትክ እህል ይሰጣቸው ነበር፤ በዚያም ዓመት በከብቶቻቸው ሁሉ ምትክ እህል ሲሰጣቸው ከረመ።

18 ያም ዓመት ካለቀ በኋላ በቀጣዩ ዓመት ሕዝቡ ወደ እሱ በመምጣት እንዲህ ይለው ጀመር፦ “ከጌታዬ የምንደብቀው ምንም ነገር የለም፤ ገንዘባችንንም ሆነ ከብቶቻችንን ለጌታዬ አስረክበናል። ከእኛ ከራሳችንና ከመሬታችን በስተቀር በጌታዬ ፊት ምንም የቀረን ነገር የለም። 19 ዓይንህ እያየ ለምን እንለቅ? መሬታችንስ ለምን ጠፍ ሆኖ ይቅር? እኛንም ሆነ መሬታችንን በእህል ግዛን፤ እኛ ለፈርዖን ባሪያዎች እንሁን፤ መሬታችንም የእሱ ይሁን። በሕይወት እንድንኖርና እንዳንሞት እንዲሁም መሬታችን ጠፍ ሆኖ እንዳይቀር የምንዘራው እህል ስጠን።” 20 በመሆኑም ዮሴፍ የግብፃውያንን መሬት በሙሉ ለፈርዖን ገዛለት፤ ምክንያቱም ረሃቡ እጅግ ስለበረታባቸው ሁሉም ግብፃውያን መሬታቸውን ሸጠው ነበር፤ ስለዚህ ምድሪቱ የፈርዖን ሆነች።

21 ዮሴፍም በግብፅ ምድር ከዳር እስከ ዳር ያለው ሕዝብ ወደ ከተሞች እንዲገባ አደረገ።+ 22 ዮሴፍ ያልገዛው የካህናቱን መሬት ብቻ ነበር፤ ምክንያቱም ፈርዖን ለካህናቱ ቀለብ ይሰፍርላቸው ነበር፤+ እነሱም የሚኖሩት ፈርዖን በሚሰፍርላቸው ቀለብ ነበር። መሬታቸውን ያልሸጡትም ለዚህ ነው። 23 ከዚያም ዮሴፍ ሕዝቡን እንዲህ አላቸው፦ “ይኸው ዛሬ እናንተንም ሆነ መሬታችሁን ለፈርዖን ገዝቻለሁ። ዘር ይኸውላችሁ፤ እናንተም በመሬቱ ላይ ዝሩ። 24 ባፈራም ጊዜ አንድ አምስተኛውን ለፈርዖን ስጡ፤+ አራቱ እጅ ግን ለመሬታችሁ ዘር እንዲሁም ለራሳችሁ፣ በቤታችሁ ላሉትና ለልጆቻችሁ ምግብ እንዲሆናችሁ የእናንተ ይሆናል።” 25 እነሱም “አንተ ሕይወታችንን አትርፈህልናል፤+ በጌታዬ ፊት ሞገስ እናግኝ እንጂ እኛ ለፈርዖን ባሪያዎች እንሆናለን” አሉት።+ 26 ከዚያም ዮሴፍ አንድ አምስተኛው ለፈርዖን እንዲሰጥ የሚያዝ ሕግ አወጣ፤ ይህም ሕግ እስከ ዛሬ ድረስ በግብፅ ምድር ይሠራበታል። የፈርዖን ያልሆነው የካህናቱ መሬት ብቻ ነበር።+

27 እስራኤላውያንም በግብፅ አገር፣ በጎሸን ምድር መኖራቸውን ቀጠሉ።+ በዚያም ተደላድለው ይኖሩ ጀመር፤ ፍሬያማም ሆኑ፤ ቁጥራቸውም እጅግ እየበዛ ሄደ።+ 28 ያዕቆብም በግብፅ ምድር ለ17 ዓመት ኖረ፤ በመሆኑም ያዕቆብ በሕይወት የኖረበት ዘመን 147 ዓመት ሆነ።+

29 እስራኤልም የሚሞትበት ቀን ሲቃረብ+ ልጁን ዮሴፍን ጠርቶ እንዲህ አለው፦ “እንግዲህ በፊትህ ሞገስ አግኝቼ ከሆነ እባክህ እጅህን ከጭኔ በታች አድርግ፤ ለእኔም ታማኝ ፍቅርና ታማኝነት አሳየኝ። እባክህ በግብፅ አትቅበረኝ።+ 30 በምሞትበት* ጊዜ ከግብፅ አውጥተህ በአባቶቼ መቃብር ቅበረኝ።”+ እሱም “እሺ፣ እንዳልከኝ አደርጋለሁ” አለው። 31 ያዕቆብም “በል ማልልኝ” አለው፤ እሱም ማለለት።+ በዚህ ጊዜ እስራኤል በአልጋው ራስጌ ላይ ሰገደ።+

48 ይህ ከሆነ በኋላ ዮሴፍ “አባትህ ደክሟል” ተብሎ ተነገረው። ዮሴፍም ሁለቱን ወንዶች ልጆቹን ምናሴንና ኤፍሬምን ይዞ ሄደ።+ 2 ከዚያም ያዕቆብ “ልጅህ ዮሴፍ ወደ አንተ መጥቷል” ተብሎ ተነገረው። በመሆኑም እስራኤል እንደ ምንም ቀና ብሎ አልጋው ላይ ተቀመጠ። 3 ያዕቆብም ዮሴፍን እንዲህ አለው፦

“ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ በከነአን ምድር በምትገኘው በሎዛ ተገልጦልኝ ባረከኝ።+ 4 እሱም እንዲህ አለኝ፦ ‘ፍሬያማ እያደረግኩህ ነው፤ ደግሞም አበዛሃለሁ፤ ብዙ ሕዝብ ያቀፈ ጉባኤም አደርግሃለሁ፤+ ይህችን ምድር ከአንተ በኋላ ለሚመጡት ዘሮችህ ዘላቂ ርስት አድርጌ እሰጣቸዋለሁ።’+ 5 አንተ ወዳለህበት ወደ ግብፅ ከመምጣቴ በፊት በግብፅ ምድር የወለድካቸው ሁለት ወንዶች ልጆች የእኔ ናቸው።+ ሮቤልና ስምዖን የእኔ እንደሆኑ ሁሉ ኤፍሬምና ምናሴም የእኔ ይሆናሉ።+ 6 ከእነሱ በኋላ የምትወልዳቸው ልጆች ግን የአንተ ይሆናሉ። እነሱም ርስት+ በሚሰጣቸው ጊዜ በወንድሞቻቸው ስም ይጠራሉ። 7 እኔም ከጳዳን ስመጣ ኤፍራታ ለመድረስ ረዘም ያለ መንገድ ሲቀረኝ ራሔል በከነአን ምድር ሞተችብኝ።+ በመሆኑም ወደ ኤፍራታ+ ማለትም ወደ ቤተልሔም+ በሚወስደው መንገድ ላይ ቀበርኳት።”

8 ከዚያም እስራኤል የዮሴፍን ወንዶች ልጆች ሲያይ “እነዚህ እነማን ናቸው?” ሲል ጠየቀው። 9 ዮሴፍም አባቱን “እነዚህ አምላክ በዚህ ስፍራ የሰጠኝ ወንዶች ልጆቼ ናቸው”+ አለው። በዚህ ጊዜ “እባክህ እንድባርካቸው ወደ እኔ አቅርባቸው” አለው።+ 10 የእስራኤል ዓይኖች በእርጅና የተነሳ ደክመው ነበር፤ እሱም ማየት ተስኖት ነበር። ስለዚህ ዮሴፍ ልጆቹን ወደ እሱ አቀረባቸው። እሱም ሳማቸው፤ እንዲሁም አቀፋቸው። 11 እስራኤልም ዮሴፍን “ዓይንህን አያለሁ ብዬ አላሰብኩም ነበር፤+ አምላክ ግን ልጆችህንም ጭምር ለማየት አበቃኝ” አለው። 12 ከዚያም ዮሴፍ ልጆቹን ከእስራኤል ጉልበቶች መካከል አውጥቶ ፈቀቅ ካደረጋቸው በኋላ በግንባሩ መሬት ላይ ተደፍቶ ሰገደ።

13 ዮሴፍም ሁለቱን ልጆች ወስዶ ኤፍሬምን+ ከራሱ በስተ ቀኝ ከእስራኤል በስተ ግራ፣ ምናሴን+ ደግሞ ከራሱ በስተ ግራ ከእስራኤል በስተ ቀኝ አድርጎ ወደ እሱ አቀረባቸው። 14 ይሁን እንጂ እስራኤል ታናሽየው ኤፍሬም ቢሆንም ቀኝ እጁን በእሱ ራስ ላይ አደረገ፤ ግራ እጁን ደግሞ በምናሴ ራስ ላይ አደረገ። እንዲህ ያደረገው ሆን ብሎ ነው፤ ምክንያቱም ምናሴ የበኩር ልጅ ነበር።+ 15 ከዚያም ዮሴፍን ባረከው፤+ እንዲህም አለው፦

“አባቶቼ አብርሃምና ይስሐቅ በፊቱ የተመላለሱት+ እውነተኛው አምላክ፣

እስከ ዛሬዋ ዕለት ድረስ በሕይወቴ ዘመን ሁሉ እረኛ የሆነልኝ እውነተኛው አምላክ፣+

16 ከአደጋ ሁሉ ያዳነኝ መልአክ+ እነዚህን ልጆች ይባርክ።+

የእኔም ሆነ የአባቶቼ የአብርሃምና የይስሐቅ ስም በእነሱ ይጠራ።

በምድርም ላይ ቁጥራቸው እየበዛ ይሂድ።”+

17 ዮሴፍም አባቱ ቀኝ እጁን በኤፍሬም ራስ ላይ እንዳደረገ ሲያይ ቅር ተሰኘ፤ ስለዚህ የአባቱን እጅ ከኤፍሬም ራስ ላይ አንስቶ በምናሴ ራስ ላይ ሊያደርገው ሞከረ። 18 ዮሴፍም አባቱን “አባቴ፣ እንዲህ አይደለም፤ በኩሩ+ እኮ ይሄኛው ነው። ቀኝ እጅህን በእሱ ራስ ላይ አድርግ” አለው። 19 አባቱ ግን “አውቄአለሁ ልጄ፣ አውቄአለሁ። እሱም ቢሆን ሕዝብ ይሆናል፤ ታላቅም ይሆናል። ይሁን እንጂ ታናሽ ወንድሙ ከእሱ የበለጠ ይሆናል፤+ ዘሩም በዝቶ ብዙ ብሔር ለመሆን ይበቃል”+ በማለት እንቢ አለው። 20 በመሆኑም በዚያው ቀን እንዲህ ሲል እነሱን መባረኩን ቀጠለ፦+

“እስራኤል በአንተ ስም እንዲህ በማለት ይባርክ፦

‘አምላክ እንደ ኤፍሬምና እንደ ምናሴ ያድርግህ።’”

በዚህ ሁኔታ ኤፍሬምን ከምናሴ አስቀደመው።

21 ከዚያም እስራኤል ዮሴፍን እንዲህ አለው፦ “እንግዲህ እኔ የምሞትበት ጊዜ ቀርቧል።+ አምላክ ግን ከእናንተ እንደማይለይ እንዲሁም ወደ አባቶቻችሁ ምድር እንደሚመልሳችሁ የተረጋገጠ ነው።+ 22 በእኔ በኩል ከአሞራውያን እጅ በሰይፌና በቀስቴ የወሰድኩትን መሬት ከወንድሞችህ አንድ ድርሻ መሬት* አስበልጬ ለአንተ ሰጥቼሃለሁ።”

49 ያዕቆብም ወንዶች ልጆቹን ጠርቶ እንዲህ አላቸው፦ “በኋለኞቹ ቀናት ምን እንደሚያጋጥማችሁ እንድነግራችሁ ተሰብሰቡ። 2 እናንተ የያዕቆብ ወንዶች ልጆች ተሰብሰቡና ስሙ፤ አዎ፣ አባታችሁን እስራኤልን አዳምጡ።

3 “ሮቤል፣+ አንተ የበኩር ልጄ ነህ፤+ ኃይሌና የብርታቴ የመጀመሪያ ፍሬ ነህ፤ የላቀ ክብርና የላቀ ኃይል ነበረህ። 4 እንደሚናወጥ ውኃ ስለምትዋልል የበላይ አትሆንም፤ ምክንያቱም አባትህ አልጋ ላይ ወጥተሃል።+ በዚያን ወቅት መኝታዬን አርክሰሃል። በእርግጥም አልጋዬ ላይ ወጥቷል!

5 “ስምዖንና ሌዊ ወንድማማቾች ናቸው።+ ሰይፎቻቸው የዓመፅ መሣሪያዎች ናቸው።+ 6 ነፍሴ* ሆይ፣ ከእነሱ ጋር አትወዳጂ። ክብሬ ሆይ፣ ከእነሱ ማኅበር ጋር አትተባበር፤ ምክንያቱም በቁጣ ተነሳስተው ሰዎችን ገድለዋል፤+ ደስ ስላላቸውም ብቻ የበሬዎችን ቋንጃ ቆርጠዋል። 7 ቁጣቸው ጨካኝ፣ ንዴታቸውም ምሕረት የለሽ ስለሆነ የተረገመ ይሁን።+ በያዕቆብ ልበትናቸው፤ በእስራኤልም ላሰራጫቸው።+

8 “ይሁዳ+ ሆይ፣ ወንድሞችህ ያወድሱሃል።+ እጅህ የጠላቶችህን አንገት ያንቃል።+ የአባትህ ወንዶች ልጆች በፊትህ ይሰግዳሉ።+ 9 ይሁዳ የአንበሳ ደቦል ነው።+ ልጄ፣ በእርግጥም ያደንከውን በልተህ ትነሳለህ። እንደ አንበሳ ያደፍጣል፤ እንደ አንበሳ ይንጠራራል፤ ማንስ ሊያስነሳው ይደፍራል? 10 ሴሎ* እስኪመጣ ድረስ በትረ መንግሥት ከይሁዳ፣+ የአዛዥም በትር ከእግሮቹ መካከል አይወጣም፤+ ለእሱም ሕዝቦች ይታዘዙለታል።+ 11 አህያውን በወይን ተክል ላይ፣ ውርንጭላውንም ምርጥ በሆነ የወይን ተክል ላይ ያስራል፤ ልብሱን በወይን ጠጅ፣ መጎናጸፊያውንም በወይን ፍሬ ጭማቂ ያጥባል። 12 ዓይኖቹ ከወይን ጠጅ የተነሳ የቀሉ፣ ጥርሶቹም ከወተት የተነሳ የነጡ ናቸው።

13 “የዛብሎን+ መኖሪያ በባሕር ዳርቻ፣ መርከቦች መልሕቅ ጥለው በሚቆሙበት ዳርቻ ይሆናል፤+ የወሰኑም ጫፍ በሲዶና አቅጣጫ ይሆናል።+

14 “ይሳኮር+ በመንታ ጭነት መካከል የሚተኛ አጥንተ ብርቱ አህያ ነው። 15 ማረፊያ ቦታው መልካም፣ ምድሩም አስደሳች መሆኑን ያያል። ሸክሙን ለመሸከም ትከሻውን ዝቅ ያደርጋል፤ ለግዳጅ ሥራ ይንበረከካል።

16 “ከእስራኤል ነገዶች አንዱ የሆነው ዳን+ በሕዝቡ ላይ ይፈርዳል።+ 17 ዳን፣ ጋላቢው ወደ ኋላ እንዲወድቅ የፈረሱን ሰኮና የሚነክስ በመንገድ ዳር ያለ እባብ፣ በመተላለፊያ ላይ ያለ ቀንዳም እባብ ይሁን።+ 18 ይሖዋ ሆይ፣ የአንተን ማዳን እጠባበቃለሁ።

19 “ጋድ+ ደግሞ የወራሪዎች ቡድን አደጋ ይጥልበታል፤ እሱ ግን ዱካውን ተከታትሎ ይመታዋል።+

20 “የአሴር+ ምግብ የተትረፈረፈ* ይሆናል፤ በንጉሥ ፊት የሚቀርብ ምግብ ያዘጋጃል።+

21 “ንፍታሌም+ ሸንቃጣ የሜዳ ፍየል ነው። ከአፉም ያማሩ ቃላት ይወጣሉ።+

22 “ዮሴፍ+ ፍሬያማ የሆነ ዛፍ ቀንበጥ ነው፤ ቅርንጫፎቹን በግንብ ላይ የሚሰድ በምንጭ ዳር ያለ ፍሬያማ የሆነ ዛፍ ቀንበጥ ነው። 23 ቀስተኞች ግን እረፍት ነሱት፤ ቀስታቸውንም ወረወሩበት፤ ለእሱም ጥላቻ አደረባቸው።+ 24 ሆኖም ቀስቱ ከቦታው ንቅንቅ አላለም፤+ እጆቹም ብርቱና ቀልጣፋ ናቸው።+ ይህም ከያዕቆብ ኃያል አምላክ እጆች፣ ከእረኛው፣ ከእስራኤል ዓለት የተገኘ ነው። 25 እሱ* ከአባትህ አምላክ የተገኘ ነው፤ አምላክም ይረዳሃል፤ እሱም ሁሉን ቻይ ከሆነው አምላክ ጋር ይሆናል። አምላክም ከላይ ከሰማያት በሚገኙ በረከቶች፣ ከታች ከጥልቁ በሚገኙ በረከቶች+ እንዲሁም ከጡትና ከማህፀን በሚገኙ በረከቶች ይባርክሃል። 26 የአባትህ በረከቶች ከዘላለማዊ ተራሮች ከሚመጡት በረከቶችና ጸንተው ከሚኖሩት ኮረብቶች ከሚገኙት መልካም ነገሮች የላቁ ይሆናሉ።+ በረከቶቹም በዮሴፍ ራስ ላይ፣ ከወንድሞቹ መካከል ተነጥሎ በወጣው በእሱ አናት ላይ ይሆናሉ።+

27 “ቢንያም+ እንደ ተኩላ ይቦጫጭቃል።+ ያደነውን ጠዋት ላይ ይበላል፤ ምሽት ላይ ደግሞ ምርኮ ያከፋፍላል።”+

28 እነዚህ ሁሉ 12ቱ የእስራኤል ነገዶች ናቸው፤ አባታቸው በባረካቸው ጊዜ የነገራቸው ነገር ይህ ነው። ለእያንዳንዳቸውም የሚገባቸውን በረከት ሰጣቸው።+

29 ከዚህ በኋላ የሚከተሉትን ትእዛዛት ሰጣቸው፦ “እንግዲህ እኔ ወደ ወገኖቼ ልሰበሰብ* ነው።+ በሂታዊው በኤፍሮን እርሻ ውስጥ በሚገኘው ዋሻ+ ከአባቶቼ ጋር ቅበሩኝ፤ 30 አብርሃም ለመቃብር ስፍራ ብሎ ከሂታዊው ከኤፍሮን በገዛው እርሻ ይኸውም በከነአን ምድር በማምሬ ፊት ለፊት በሚገኘው በማክፈላ እርሻ ውስጥ ባለው ዋሻ ቅበሩኝ። 31 አብርሃምንና ሚስቱን ሣራን የቀበሯቸው እዚያ ነው።+ ይስሐቅንና ሚስቱን ርብቃንም የቀበሯቸው እዚያ ነው፤+ እኔም ብሆን ሊያን የቀበርኳት እዚያው ነው። 32 እርሻውም ሆነ በውስጡ ያለው ዋሻ የተገዛው ከሄት ወንዶች ልጆች ነው።”+

33 በዚህ መንገድ ያዕቆብ ለወንዶች ልጆቹ እነዚህን መመሪያዎች ሰጥቶ ጨረሰ። ከዚያም እግሮቹን ወደ አልጋው አውጥቶ የመጨረሻ እስትንፋሱን ተነፈሰ፤ ወደ ወገኖቹም ተሰበሰበ።*+

50 ከዚያም ዮሴፍ አባቱ ላይ ተደፍቶ አለቀሰ፤+ አባቱንም ሳመው። 2 በኋላም ዮሴፍ መድኃኒት ቀማሚ የሆኑ አገልጋዮቹን የአባቱን አስከሬን መድኃኒት እንዲቀቡ+ አዘዛቸው። መድኃኒት ቀማሚዎቹም እስራኤልን መድኃኒት ቀቡት፤ 3 ይህም 40 ቀን ሙሉ ፈጀባቸው፤ ምክንያቱም አስከሬን መድኃኒት መቀባት ይህን ያህል ጊዜ ይወስድ ነበር፤ ግብፃውያንም 70 ቀን አለቀሱለት።

4 የሐዘኑም ጊዜ ሲያበቃ ዮሴፍ የፈርዖንን ቤተ መንግሥት ባለሥልጣናት* እንዲህ አላቸው፦ “በፊታችሁ ሞገስ አግኝቼ ከሆነ እባካችሁ ለፈርዖን ይህን መልእክት ንገሩልኝ፦ 5 ‘አባቴ “እንግዲህ እኔ የምሞትበት ጊዜ ቀርቧል።+ በመሆኑም በከነአን ምድር ባዘጋጀሁት+ የመቃብር ስፍራ ቅበረኝ”+ ሲል አስምሎኛል።+ ስለዚህ እባክህ ልውጣና አባቴን ልቅበር፤ ከዚያም እመለሳለሁ።’” 6 ፈርዖንም “እንግዲህ ባስማለህ መሠረት+ ሄደህ አባትህን ቅበር” አለው።

7 በመሆኑም ዮሴፍ አባቱን ለመቅበር ወጣ፤ ከእሱም ጋር የፈርዖን አገልጋዮች በሙሉ ሄዱ፤ በቤተ መንግሥቱም ያሉ ሽማግሌዎች፣+ በግብፅ ምድር የሚገኙ ሽማግሌዎች በሙሉ፣ 8 በዮሴፍ ቤት ያሉ ሁሉ፣ ወንድሞቹና የአባቱ ቤተሰቦች ሄዱ።+ በጎሸን ምድር የቀሩት ትናንሽ ልጆቻቸው፣ መንጎቻቸውና ከብቶቻቸው ብቻ ነበሩ። 9 ሠረገሎችና+ ፈረሰኞችም አብረውት ወጡ፤ ያጀበውም ሰው እጅግ ብዙ ነበር። 10 ከዚያም በዮርዳኖስ ክልል ወደሚገኘው አጣድ የተባለ አውድማ ደረሱ፤ በዚያም እየጮኹ ምርር ብለው አለቀሱ፤ እሱም ለአባቱ ሰባት ቀን ለቅሶ ተቀመጠ። 11 በዚያ የሚኖሩ ከነአናውያንም ሰዎቹ በአጣድ አውድማ ሲያለቅሱ ሲመለከቱ “መቼም ይህ ለግብፃውያን ከባድ ሐዘን መሆን አለበት!” አሉ። በዮርዳኖስ ክልል የሚገኘው የዚህ ስፍራ ስም አቤልምጽራይም* የተባለው በዚህ የተነሳ ነው።

12 በመሆኑም ልጆቹ ልክ በሰጣቸው መመሪያ መሠረት አደረጉለት።+ 13 ወንዶች ልጆቹም ወደ ከነአን ምድር ወስደው አብርሃም ለመቃብር ቦታ ብሎ ከሂታዊው ከኤፍሮን በገዛው ከማምሬ ፊት ለፊት በሚገኘው እርሻ ማለትም በማክፈላ እርሻ ውስጥ ባለው ዋሻ ቀበሩት።+ 14 ዮሴፍም አባቱን ከቀበረ በኋላ ከወንድሞቹና ለአባቱ ቀብር አብረውት ከሄዱት ሁሉ ጋር ወደ ግብፅ ተመለሰ።

15 የዮሴፍ ወንድሞች አባታቸው መሞቱን ባዩ ጊዜ “ምናልባት እኮ ዮሴፍ በፈጸምንበት በደል የተነሳ ቂም ይዞ ይበቀለን ይሆናል” አሉ።+ 16 ስለዚህ ለዮሴፍ እንዲህ የሚል መልእክት ላኩበት፦ “አባትህ ከመሞቱ በፊት እንዲህ የሚል ትእዛዝ አስተላልፎ ነበር፦ 17 ‘ዮሴፍን እንዲህ በሉት፦ “የወንድሞችህን በደል እንዲሁም በአንተ ላይ እንዲህ ያለ ጉዳት በማድረስ የሠሩትን ኃጢአት ይቅር እንድትል እማጸንሃለሁ።”’ እናም እባክህ የአባትህን አምላክ አገልጋዮች በደል ይቅር በል።” ዮሴፍም እንዲህ ሲሉት አለቀሰ። 18 ከዚያም ወንድሞቹ መጡ፤ በፊቱም ተደፍተው በመስገድ “እኛ የአንተ ባሪያዎች ነን!” አሉት።+ 19 ዮሴፍም እንዲህ አላቸው፦ “አይዟችሁ አትፍሩ። ለመሆኑ እኔን በአምላክ ቦታ ያስቀመጠኝ ማን ነው? 20 ምንም እንኳ እኔን ለመጉዳት አስባችሁ የነበረ ቢሆንም+ አምላክ ግን ይኸው ዛሬ እንደምታዩት ነገሩን ለመልካም አደረገው፤ የብዙ ሰዎችንም ሕይወት ለማዳን ተጠቀመበት።+ 21 ስለሆነም አትፍሩ። ለእናንተም ሆነ ለትናንሽ ልጆቻችሁ የሚያስፈልገውን እህል እሰጣችኋለሁ።”+ እሱም በዚህ መንገድ አጽናናቸው፤ እንዲሁም አረጋጋቸው።

22 ዮሴፍ ከአባቱ ቤተሰቦች ጋር በግብፅ መኖሩን ቀጠለ፤ ዮሴፍም 110 ዓመት ኖረ። 23 እሱም የኤፍሬምን ወንዶች ልጆች እስከ ሦስት ትውልድ ድረስ አየ፤+ እንዲሁም የምናሴን ልጅ የማኪርን ወንዶች ልጆች አየ።+ እነዚህ የተወለዱት በዮሴፍ ጭን ላይ ነበር።* 24 ከጊዜ በኋላ ዮሴፍ ወንድሞቹን እንዲህ አላቸው፦ “እንግዲህ እኔ የምሞትበት ጊዜ ቀርቧል፤ ይሁንና አምላክ ፊቱን ወደ እናንተ እንደሚመልስ የተረጋገጠ ነው፤+ ደግሞም ያለጥርጥር ከዚህ ምድር አውጥቶ ለአብርሃም፣ ለይስሐቅና ለያዕቆብ ወደማለላቸው ምድር ያስገባችኋል።”+ 25 በመሆኑም ዮሴፍ የእስራኤልን ወንዶች ልጆች “አምላክ ፊቱን ወደ እናንተ እንደሚመልስ ጥርጥር የለውም። አደራ፣ በዚያን ጊዜ አፅሜን ከዚህ ይዛችሁ እንድትወጡ” በማለት አስማላቸው።+ 26 ዮሴፍም በ110 ዓመቱ ሞተ፤ እነሱም አስከሬኑን መድኃኒት ቀቡት፤+ ከዚያም በሬሳ ሣጥን ውስጥ አድርገው በግብፅ አስቀመጡት።

ወይም “ባዶ ነበረች።”

ወይም “የሚነዋወጠውም።”

ወይም “የአምላክም መንፈስ።”

ወይም “ነፍሳት።”

ወይም “ነፍሳትን።”

ወይም “ነፍሳትን።”

ይህ አገላለጽ በምድር ላይ የሚሳቡ እንስሳትን ጨምሮ ከሌሎች የእንስሳት ምድብ የማይመደቡትን እንስሳት ሊያመለክት ይችላል።

ወይም “ሕያው ነፍስ።”

ቃል በቃል “ሠራዊታቸውን ሁሉ።”

አምላክ ብቻ የሚጠራበት የግል ስሙ ይኸውም יהוה (የሐወሐ) ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀሰው እዚህ ላይ ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ4ን ተመልከት።

ወይም “ነፍስ።” በዕብራይስጥ ነፈሽ ሲሆን ቃል በቃል ሲተረጎም “የሚተነፍስ ፍጥረት” ማለት ነው። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

ቃል በቃል “አራት ራስ።”

ይህ ሙጫ በሞቃታማ አካባቢዎች ከሚበቅሉ ትናንሽ ዛፎች የሚገኝ ከርቤ የሚመስል ጥሩ መዓዛ ያለው ሙጫ ነው።

ወይም “የኩሽ።” ይህ ቦታ ከየት እስከ የት ያለውን አካባቢ እንደሚያመለክት በትክክል አይታወቅም።

ወይም “ሂዲኬል።”

ወይም “ነፍስ።”

ወይም “አብሮ ይኖራል።”

ወይም “በጣም መሠሪ፤ እጅግ ተንኮለኛ።”

ወይም “ያቆስላል፤ ይመታል።”

ወይም “ትመታለህ፤ ትጨፈልቃለህ።”

“ምድራዊ ሰው፤ ሰው፤ የሰው ዘር” የሚል ትርጉም አለው።

“ሕያው” የሚል ትርጉም አለው።

ወይም “ወለድኩ።”

ወይም “ሐሴት ታደርግ አልነበረም?”

ቃል በቃል “ኃይሏን።”

ቃል በቃል “ከምድር ገጽ።”

ወይም “አበጀለት።”

ወይም “በኖድ ምድር።”

ወይም “የዋሽንት።”

“የተሾመ፤ የተቀመጠ፤ የተመደበ” የሚል ትርጉም አለው።

ወይም “ሰዎች የይሖዋን ስም ማቃለል ጀመሩ።”

ወይም “አዳም፤ የሰው ዘር።”

ቃል በቃል “ከአምላክ።” የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

ወይም “እፎይታ ያስገኝልናል።”

“እረፍት፤ ማጽናኛ” የሚል ትርጉም ሳይኖረው አይቀርም።

የአምላክ ልጆች የሆኑትን መላእክት የሚያመለክት የዕብራይስጥ ዘይቤያዊ አነጋገር ነው።

ወይም “የሥጋውን ፈቃድ ስለሚፈጽም።”

“የሚያፈርጡ” ይኸውም ሌሎችን እያነሱ የሚያፈርጡ ማለት ሳይሆን አይቀርም። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

ወይም “ተከፋ።”

ቃል በቃል “በእሱ ትውልድ።”

ወይም “ነቀፋ።”

ቃል በቃል “ሥጋ።”

ቃል በቃል “ትልቅ ሣጥን።” ትልቅ ጀልባ።

ወይም “ሬንጅ።”

አንድ ክንድ 44.5 ሴንቲ ሜትር ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።

የዕብራይስጡ ቃል “ጾሃር” ነው። ይህ ቃል ከብርሃን ማስገቢያ ቀዳዳ ወይም መስኮት ይልቅ አንድ ክንድ ተዳፋት የሆነን ጣሪያ የሚያመለክት ሊሆን ይችላል።

ወይም “የሕይወት መንፈስ።”

“ንጹሕ ከሆነው ከእያንዳንዱ እንስሳ ሰባት ጥንድ” ማለትም ሊሆን ይችላል።

“በሰማይ ላይ ከሚበርሩ ፍጥረታት ሰባት ጥንድ” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ወይም “የሕይወት መንፈስ።”

አንድ ክንድ 44.5 ሴንቲ ሜትር ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።

ቃል በቃል “(የሚንቀሳቀስ) ሥጋ ሁሉ።”

ወይም “የሕይወት መንፈስ እስትንፋስ።”

ወይም “ዝናብ ተገታ።”

ወይም “እግሯን የምታሳርፍበት።”

ወይም “እንዲርመሰመሱ።”

ወይም “የሚያረጋጋውን፤ የሚያበርደውን።” ቃል በቃል “እረፍት የሚሰጠውን።”

ወይም “በሥልጣናችሁ ሥር።”

ወይም “ነፍሱ።”

ወይም “የነፍሳችሁን ደም።”

ወይም “ነፍስ።”

ወይም “ሕይወት ያለው ነገር።”

ወይም “ነፍስ።”

ወይም “ከእያንዳንዱ ሥጋ ሕያው ነፍስ።”

ወይም “በእያንዳንዱ ሥጋ ሕያው ነፍስ ሁሉ።”

ወይም “የግዛቱ የመጀመሪያ ከተሞችም።”

“እነሱም ታላቋን ከተማ መሠረቱ” ማለትም ሊሆን ይችላል።

“የያፌት ታላቅ ወንድም” ማለትም ሊሆን ይችላል።

“ክፍፍል” የሚል ትርጉም አለው።

ወይም “የምድር ሕዝቦች ተከፋፍለው።”

ወይም “የወጠኑትን።”

የዕብራይስጡ ቃል ሁለት ወይም ከዚያ በላይ የሆኑ አካላትን ሊያመለክት ይችላል።

“ዝብርቅ” የሚል ትርጉም አለው።

ወይም “ለራሳቸው በረከት ያገኛሉ።”

ወይም “ነፍሳት።”

ወይም “እንደ ባዕድ አገር ሰው ሆኖ።”

ወይም “ነፍሴ በሕይወት ትኖራለች።”

“እነዚህ” የሚለው ቃል የሚያመለክተው በዘፍጥረት 14:1 ላይ የተጠቀሱትን ነገሥታት ነው።

ወይም “ረባዳማ ሜዳ።”

ሙት ባሕርን ያመለክታል።

ወይም “ረባዳማ ሜዳ።”

ወይም “ረባዳማ ሜዳ።”

ወይም “በድንኳኖች ውስጥ ይኖር።”

ቃል በቃል “ወንድሙ።”

ወይም “ረባዳማ ሜዳ።”

ወይም “ነፍሳቱን።”

ቃል በቃል “ወንድ ልጅ።”

ቃል በቃል “የአብራክህ ክፋይ።”

“አምላክ ይሰማል” የሚል ትርጉም አለው።

እዚህ ላይ የተጠቀሰው እንስሳ አንዳንዶች የሜዳ አህያ እንደሆነ አድርገው ቢያስቡም የዱር አህያ ዝርያ ነው። ይህም በራስ የመመራት ባሕርይን ለማመልከት የገባ ሳይሆን አይቀርም።

“ከወንድሞቹ ሁሉ ጋር በጠላትነት ይኖራል” ማለትም ሊሆን ይችላል።

“የሚያየኝ ሕያው አምላክ የውኃ ጉድጓድ” የሚል ትርጉም አለው።

ወይም “ነቀፋ።”

“አብ ከፍ ከፍ ያለ ነው” የሚል ትርጉም አለው።

“የብዙ ሕዝብ አባት፤ የብዙዎች አባት” የሚል ትርጉም አለው።

ወይም “ነፍስ።”

ወይም “ይገደል።”

“ተጨቃጫቂ” ማለት ሳይሆን አይቀርም።

“ልዕልት” የሚል ትርጉም አለው።

“ሳቅ” የሚል ትርጉም አለው።

ቃል በቃል “ልባችሁን እንድታበረቱ።”

ቃል በቃል “የሲህ መስፈሪያ።” አንድ ሲህ 7.33 ሊትር ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።

ቃል በቃል “በሴቶች ላይ የሚታየው ልማድ ከሣራ ተቋርጦ ነበር።”

ወይም “ለራሳቸው በረከት ያገኛሉ።”

ወይም “ከለላ።”

ወይም “ነፍስህን።”

ወይም “ነፍሴን።”

ወይም “ታማኝ ፍቅር።”

ወይም “ነፍሴ በሕይወት ትኖራለች።”

“ትንሽነት” የሚል ትርጉም አለው።

ወይም “እንደ ባዕድ አገር ሰው ሆኖ።”

ከእሷ ጋር የፆታ ግንኙነት አለመፈጸሙን ያመለክታል።

ወይም “ጻድቅ የሆነን።”

ቃል በቃል “እነሆ፣ ይህ ለአንቺ የዓይን መሸፈኛ ነው።”

ወይም “በአቢሜሌክ ቤት ያለውን ማህፀን ሁሉ ፈጽሞ ዘግቶ ነበር።”

“ይስቅብኛል” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ቃል በቃል “ድምፅዋን።”

“የመሐላው የውኃ ጉድጓድ” ወይም “የሰባት የውኃ ጉድጓድ” ማለት ሳይሆን አይቀርም።

ቃል በቃል “ለብዙ ቀናት።”

ወይም “እንደ ባዕድ አገር ሰው ሆኖ ኖረ።”

ወይም “ማረጃ ቢላውን።”

ወይም “ማረጃ ቢላውን።”

“ይሖዋ ያቀርባል፤ ይሖዋ ይፈጽመዋል” የሚል ትርጉም አለው።

ወይም “ከተሞች።”

“ታላቅ አለቃ” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ወይም “ነፍሳችሁ ከፈቀደልኝ።”

አንድ ሰቅል 11.4 ግራም ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።

አንድ ሰቅል 11.4 ግራም ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።

አንድ ሰቅል 11.4 ግራም ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።

አንድ ሰቅል 11.4 ግራም ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።

ላባን የሚያመለክት ሳይሆን አይቀርም።

ቃል በቃል “ወደ ቀኝ ወይም ወደ ግራ ዞር እንድል።”

ወይም “ክፉም ሆነ መልካም ልንመልስልህ አንችልም።”

በወቅቱ ደንገጡር ሆና የምታገለግላትን ሞግዚት ያመለክታል።

ወይም “የእልፍ አእላፋት እናት ሁኚ።”

ወይም “ከተሞች።”

ይህ ሞትን የሚያመለክት ቅኔያዊ አነጋገር ነው።

ወይም “በግንብ በታጠሩት ሰፈሮቻቸው።”

ይህ ሞትን የሚያመለክት ቅኔያዊ አነጋገር ነው።

“ከወንድሞቹም ሁሉ ጋር በጠላትነት ኖረ” ማለትም ሊሆን ይችላል።

“ፀጉራም” የሚል ትርጉም አለው።

“ተረከዝ የሚይዝ፤ የሚተካ” የሚል ትርጉም አለው።

ወይም “በጣም ስለራበኝ።”

ወይም “አንድ ጉርሻ።”

“ቀይ” የሚል ትርጉም አለው።

ወይም “ርብቃን ሲያቅፋት።”

ወይም “ደረቅ ወንዝ።”

ወይም “በደረቁ ወንዝ ውስጥ።”

“ጠብ” የሚል ትርጉም አለው።

“ክስ” የሚል ትርጉም አለው።

“ሰፋፊ ቦታዎች” የሚል ትርጉም አለው።

ቃል በቃል “የይስሐቅንና የርብቃን መንፈስ አስመረሩ።”

ወይም “ነፍሴ እንድትባርክህ።”

ወይም “ነፍስህ እንድትባርከኝ።”

ወይም “ነፍሴ ትባርክሃለች።”

ወይም “ነፍስህ እንድትባርከኝ።”

“ተረከዝ የሚይዝ፤ የሚተካ” የሚል ትርጉም አለው።

ወይም “አንተን እንደሚገድልህ በማሰብ ራሱን እያጽናና ነው።”

ወይም “መሰላል።”

ወይም “ለራሳቸው በረከት ያገኛሉ።”

“የአምላክ ቤት” የሚል ትርጉም አለው።

ቃል በቃል “ወንድምና።”

ወይም “የሥጋ ዘመዴ።”

ቃል በቃል “ወንድሜ።”

ወይም “ፈዛዛ።”

ቃል በቃል “እንደተጠላች።”

ቃል በቃል “ማህፀኗን ከፈተላት።”

“እነሆ፣ ወንድ ልጅ!” የሚል ትርጉም አለው።

“መስማት” የሚል ትርጉም አለው።

“አጥብቆ ደገፈ፤ ተባበረ” የሚል ትርጉም አለው።

“የተመሰገነ፤ ምስጉን” የሚል ትርጉም አለው።

ወይም “የማህፀን ፍሬ የነፈገሽን።”

ቃል በቃል “በጉልበቶቼ ላይ እንድትወልድልኝና።”

“ዳኛ” የሚል ትርጉም አለው።

“የገጠምኩት ትግል” የሚል ትርጉም አለው።

“መልካም ዕድል” የሚል ትርጉም አለው።

“ደስተኛ፤ ደስታ” የሚል ትርጉም አለው።

እንግሊዝኛ፣ ማንድሬክ። ከድንች ዝርያ የሚመደብ ተክል ሲሆን ብርቱካንማ ቀለም ያለው ፍሬ ያፈራል፤ ከፕሪም ጋር የሚመሳሰል ቅርጽ አለው።

ወይም “የቅጥር ደሞዝ።”

“እሱ ደሞዝ ነው” የሚል ትርጉም አለው።

“መቻል” የሚል ትርጉም አለው።

ቃል በቃል “አምላክ ልመናዋን ሰምቶ ማህፀኗን በመክፈት።”

ዮሴፍያህ የተባለው ስም አጭር አጠራር ሲሆን “ያህ ይጨምር” የሚል ትርጉም አለው።

ወይም “ከማስረጃው።”

ወይም “ሐቀኝነቴ።”

ጥሩ መዓዛ ያላቸው ነጫጭ አበቦች የሚያወጣ ዛፍ።

የተንዠረገጉ ቅርንጫፎችና እየተቀረፈ የሚወድቅ ቅርፊት ያለው ዛፍ።

ወይም “የቤት ውስጥ አማልክት፤ ጣዖታት።”

ኤፍራጥስ ወንዝን ያመለክታል።

ወይም “ዘመዶቹን።”

ቃል በቃል “ከያዕቆብ ጋር ከደግ እስከ ክፉ እንዳትነጋገር ተጠንቀቅ።”

ቃል በቃል “ወንዶች ልጆቼንና።”

ቃል በቃል “የይስሐቅ ፍርሃት።”

“የምሥክር ክምር” የሚል ትርጉም ያለው የአራማውያን አባባል ነው።

“የምሥክር ክምር” የሚል ትርጉም ያለው የዕብራይስጥ አባባል ነው።

ሶርያዊው ላባ በተራፊሞች ያምን ስለነበር እዚህ ላይ የተጠቀሰው ቃል ‘አማልክትን’ የሚያመለክት ሊሆን ይችላል።

ቃል በቃል “በአባቱ በይስሐቅ ፍርሃት።”

ቃል በቃል “ወንዶች ልጆቹንና።”

“ሁለት ሰፈር” የሚል ትርጉም አለው።

ቃል በቃል “ሜዳ።”

ወይም “እንደ ባዕድ አገር ሰው ሆኜ ኖሬአለሁ።”

ወንዝ ማቋረጥ የሚቻልበት ጥልቀት የሌለው የወንዝ ክፍል።

ወይም “ደረቁን ወንዝ።”

“ከአምላክ ጋር የታገለ (በጽናት የተጣበቀ)” ወይም “አምላክ ይታገላል” የሚል ትርጉም አለው።

ወይም “ነፍሴ ተርፋለች።”

“የአምላክ ፊት” የሚል ትርጉም አለው።

ወይም “ጰኒኤልን።”

“ዳሶች፤ መጠለያዎች” የሚል ትርጉም አለው።

ወይም “በዚያ አገር ያሉ ወጣት ሴቶችን ለማየት።”

ወይም “ነፍሱ።”

ቃል በቃል “ለወጣቷ ልብ ተናገረ።”

ወይም “የልጄ የሴኬም ነፍስ ከልጃችሁ ጋር ተጣብቋል።”

ወይም “እንድገለል አደረጋችሁኝ።”

ወይም “በሄድኩበት መንገድ።”

ወይም “ደበቃቸው።”

“የቤቴል አምላክ” የሚል ትርጉም አለው።

“የለቅሶ የባሉጥ ዛፍ” የሚል ትርጉም አለው።

ቃል በቃል “ከወገብህ ይወጣሉ።”

ወይም “ነፍሷ በምትወጣበት ጊዜ።”

“የሐዘኔ ልጅ” የሚል ትርጉም አለው።

“የቀኝ እጅ ልጅ” የሚል ትርጉም አለው።

ይህ ሞትን የሚያመለክት ቅኔያዊ አነጋገር ነው።

ወይም “በቤቱ ውስጥ ያለውን ነፍስ።”

ወይም “እንደ ባዕድ አገር ሰው ሆነው ይኖሩበት።”

ቃል በቃል “ሺኮች።” የነገድ አለቃ የሆነ ሰው “ሺክ” ተብሎ ይጠራ ነበር።

ቃል በቃል “በእስራኤል ወንዶች ልጆች።”

ቃል በቃል “ሜዳ።”

ወይም “የሚያምር ረጅም ልብስ።”

ወይም “ረባዳማ ሜዳ።”

ወይም “ነፍሱን።”

ወይም “እጃችሁን አታሳርፉበት።”

ወይም “ሲኦል።” የሰው ልጆችን ሁሉ መቃብር ያመለክታል። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

ይሁዳን ያመለክታል።

“መጣስ” የሚል ትርጉም አለው፤ ማህፀኗን ጥሶ መውጣቱን የሚያመለክት ሳይሆን አይቀርም።

ቃል በቃል “ለተወሰኑ ቀናት።”

ቃል በቃል “ራስህን ያነሳል።”

ቃል በቃል “የውኃ ማጠራቀሚያ ጉድጓድ፤ ጉድጓድ።”

ቃል በቃል “ራስህን ከላይህ ላይ ያነሳል።”

ቃል በቃል “ራስ ከፍ አደረገ።”

ቃል በቃል “ከውኃ ማጠራቀሚያው ጉድጓድ፤ ከጉድጓዱ።”

ወይም “በዙፋኔ።”

ይህ አነጋገር ሰዎች አክብሮት ማሳየት እንዳለባቸው የሚጠቁም መግለጫ ሊሆን ይችላል።

ቃል በቃል “እጁንም ሆነ እግሩን ማንሳት።”

ሂልያፖሊስን ያመለክታል።

ወይም “በመላው የግብፅ ምድር መዘዋወር።”

ወይም “ፈርዖንን ማገልገል በጀመረ።”

ቃል በቃል “እፍኝ ሙሉ።”

ሂልያፖሊስን ያመለክታል።

“ማስረሻ፤ የሚያስረሳ” የሚል ትርጉም አለው።

“እጥፍ ፍሬያማ” የሚል ትርጉም አለው።

ወይም “የምድሪቱን ደካማ ጎን።”

ወይም “ነፍሱ ተጨንቃ።”

ወይም “ሲኦል።” የሰው ልጆችን ሁሉ መቃብር ያመለክታል። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

ወይም “ለእሱ ዋስ እሆናለሁ።”

ቃል በቃል “እነሱም።”

ወይም “ሲኦል።” የሰው ልጆችን ሁሉ መቃብር ያመለክታል። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

ወይም “ነፍስ።”

ወይም “ነፍስ።”

ወይም “ሲኦል።” የሰው ልጆችን ሁሉ መቃብር ያመለክታል። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

ቃል በቃል “ለፈርዖን እንደ አባት።”

ወይም “ስብ።”

ወይም “የእሱ የሆኑትን።”

ያዕቆብ በሚሞትበት ጊዜ ዓይኖቹን መክደንን ያመለክታል።

ወይም “የወንዶችና የሴቶች ልጆቹ ነፍስ ሁሉ 33 ነበር።”

ወይም “16 ነፍስ።”

የሰብዓ ሊቃናት ትርጉም አምስት ተጨማሪ ስሞችን ይጠቅሳል። እስጢፋኖስ በሥራ 7:14 ላይ 70 ነፍስ በማለት ፋንታ 75 ነፍስ ያለው ከዚህ ትርጉም ስለጠቀሰ ሊሆን ይችላል።

ሂልያፖሊስን ያመለክታል።

ወይም “14 ነፍስ።”

ቃል በቃል “ወንዶች ልጆች።”

ወይም “ሰባት ነፍስ።”

ወይም “ነፍሳት።”

ወይም “ሁለት ነፍስ።”

ወይም “70 ነፍስ።” የሰብዓ ሊቃናት ትርጉም “ሰባ አምስት” ነፍስ ይላል። ዘፍ 46:20 ላይ የሚገኘውን የግርጌ ማስታወሻ ተመልከት።

ወይም “በጊዜያዊ ነዋሪነት፤ እንደ ባዕድ አገር ሰው ሆኜ።”

ወይም “በጊዜያዊ ነዋሪነት፤ እንደ ባዕድ አገር ሰው ሆነው።”

ቃል በቃል “ከአባቶቼ ጋር በማንቀላፋበት።”

ወይም “አንድ ተዳፋት መሬት።” ቃል በቃል “አንድ ትከሻ።”

የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

“የእሱ የሆነው፤ ባለቤት የሆነው” የሚል ትርጉም አለው።

ቃል በቃል “ስብ።”

ዮሴፍን ያመለክታል።

ይህ አባባል ሞትን የሚያመለክት ቅኔያዊ አነጋገር ነው።

ይህ አባባል ሞትን የሚያመለክት ቅኔያዊ አነጋገር ነው።

ወይም “ቤተሰቦች።”

“የግብፃውያን ሐዘን” የሚል ትርጉም አለው።

እንደ ልጆቹ ይመለከታቸውና በጣም ይወዳቸው እንደነበር ያመለክታል።

    የኢትዮጵያ ምልክት ቋንቋ ጽሑፎች (2011-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • የኢትዮጵያ ምልክት ቋንቋ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ