ሁለተኛ ዜና መዋዕል
1 የዳዊት ልጅ ሰለሞን ንግሥናውን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያጠናከረ ሄደ፤ አምላኩ ይሖዋም ከእሱ ጋር ስለነበር እጅግ ገናና አደረገው።+
2 ሰለሞን ለእስራኤል ሁሉ፣ ለሺህ አለቆች፣ ለመቶ አለቆች፣ ለፈራጆችና የአባቶች ቤቶች መሪዎች ለሆኑት በመላው እስራኤል ለሚገኙት አለቆች ሁሉ መልእክት ላከ። 3 ከዚያም ሰለሞንና መላው ጉባኤ በገባኦን+ ወደሚገኘው ኮረብታ ሄዱ፤ ምክንያቱም የይሖዋ አገልጋይ ሙሴ በምድረ በዳ የሠራው የእውነተኛው አምላክ የመገናኛ ድንኳን የሚገኘው በዚያ ነበር። 4 ይሁን እንጂ ዳዊት የእውነተኛውን አምላክ ታቦት ከቂርያትየአሪም+ እሱ ወዳዘጋጀለት ስፍራ አምጥቶት ነበር፤ በኢየሩሳሌምም ድንኳን ተክሎለት ነበር።+ 5 የሁር ልጅ የዖሪ ልጅ ባስልኤል+ የሠራው የመዳብ መሠዊያ+ በይሖዋ የማደሪያ ድንኳን ፊት ይገኝ ነበር፤ ሰለሞንና ጉባኤውም በመሠዊያው ፊት ይጸልዩ ነበር።* 6 ሰለሞንም በዚያ በይሖዋ ፊት መባ አቀረበ፤ በመገናኛው ድንኳን በሚገኘው የመዳብ መሠዊያ ላይ 1,000 የሚቃጠሉ መባዎችን አቀረበ።+
7 በዚያ ሌሊት አምላክ ለሰለሞን ተገልጦ “እንድሰጥህ የምትፈልገውን ጠይቅ” አለው።+ 8 በዚህ ጊዜ ሰለሞን አምላክን እንዲህ አለው፦ “ለአባቴ ለዳዊት ጥልቅ የሆነ ታማኝ ፍቅር አሳይተኸዋል፤+ በእሱም ምትክ አንግሠኸኛል።+ 9 አሁንም ይሖዋ አምላክ ሆይ፣ ለአባቴ ለዳዊት የገባኸው ቃል ይፈጸም፤+ እንደ ምድር አፈር እጅግ ብዙ በሆነ ሕዝብ+ ላይ አንግሠኸኛልና። 10 ይህን ሕዝብ መምራት* እንድችል ጥበብና እውቀት ስጠኝ፤+ አለዚያማ ይህን ታላቅ ሕዝብህን ማን ሊዳኝ ይችላል?”+
11 ከዚያም አምላክ ሰለሞንን እንዲህ አለው፦ “የልብህ መሻት ይህ ስለሆነ ደግሞም ብልጽግና፣ ሀብትና ክብር ወይም የሚጠሉህን ሰዎች ሞት* አሊያም ረጅም ዕድሜ* ስላልተመኘህ፣ ይልቁንም አንተን ንጉሥ አድርጌ የሾምኩበትን ሕዝቤን ማስተዳደር እንድትችል ጥበብና እውቀት ስለጠየቅክ፣+ 12 ጥበብና እውቀት ይሰጥሃል፤ ከዚህም ሌላ ከአንተ በፊት የነበረ ማንኛውም ንጉሥ ያላገኘውን፣ ከአንተም በኋላ የሚነሳ የትኛውም ንጉሥ የማያገኘውን ብልጽግና፣ ሀብትና ክብር እሰጥሃለሁ።”+
13 ሰለሞንም በገባኦን+ ኮረብታ ከሚገኘው ከመገናኛው ድንኳን ፊት ወጥቶ ወደ ኢየሩሳሌም መጣ፤ በእስራኤልም ላይ ነገሠ። 14 ሰለሞን ሠረገሎችንና ፈረሶችን* መሰብሰቡን ቀጠለ፤ እሱም 1,400 ሠረገሎችና 12,000 ፈረሶች* ነበሩት፤+ እነሱንም በሠረገላ ከተሞችና+ በኢየሩሳሌም በንጉሡ አቅራቢያ አኖራቸው።+ 15 ንጉሡ ብርና ወርቅ በየቦታው እንደሚገኝ ድንጋይ እስኪሆን ድረስ በኢየሩሳሌም እንዲበዛ አደረገ፤+ አርዘ ሊባኖሱንም ከብዛቱ የተነሳ በሸፌላ እንደሚገኘው የሾላ ዛፍ አደረገው።+ 16 የሰለሞን ፈረሶች ከግብፅ ያስመጣቸው ነበሩ፤+ የንጉሡ ነጋዴዎችም የፈረሶቹን መንጋ አንዴ በተተመነው ዋጋ ይገዙ ነበር።*+ 17 ከግብፅ የሚመጣው እያንዳንዱ ሠረገላ 600 የብር ሰቅል ያወጣ ነበር፤ አንድ ፈረስ ደግሞ 150 ሰቅል ያወጣል፤ እነሱ ደግሞ በተራቸው ለሂታውያን ነገሥታትና ለሶርያ ነገሥታት ሁሉ ሠረገሎችንና ፈረሶችን ይሸጡ ነበር።
2 ሰለሞን ለይሖዋ ስም ቤት፣+ ለመንግሥቱም ቤት*+ እንዲሠራ አዘዘ። 2 ሰለሞን 70,000 ተራ የጉልበት ሠራተኞችና* በተራሮቹ ላይ ድንጋይ የሚጠርቡ 80,000 ሰዎች መረጠ፤+ በእነሱም ላይ 3,600 ሰዎችን የበላይ ተመልካቾች አድርጎ ሾመ።+ 3 ደግሞም ሰለሞን እንዲህ የሚል መልእክት ወደ ጢሮስ ንጉሥ ወደ ኪራም+ ላከ፦ “አባቴ ዳዊት የሚኖርበትን ቤት* ሲሠራ የአርዘ ሊባኖስ እንጨት እንደላክለት ሁሉ ለእኔም እንዲሁ አድርግልኝ።+ 4 እነሆ፣ በፊቱ ጥሩ መዓዛ ያለው ዕጣን+ ለማጠን፣ የሚነባበረውን ዳቦ*+ ዘወትር በዚያ ለማስቀመጥ እንዲሁም በየጠዋቱና በየማታው፣+ በየሰንበቱ፣+ በየወር መባቻውና+ በአምላካችን በይሖዋ የበዓላት ወቅቶች+ የሚቃጠል መባ ለማቅረብ ለአምላኬ ለይሖዋ ስም ቤት ልሠራና ለእሱ ልቀድሰው አስቤአለሁ። ይህም እስራኤላውያን ሁልጊዜ ሊፈጽሙት የሚገባ ግዴታ ነው። 5 አምላካችን ከሌሎች አማልክት ሁሉ ይበልጥ ታላቅ ስለሆነ የምሠራውም ቤት ታላቅ ይሆናል። 6 ለእሱ ቤት መሥራት የሚችል ማነው? ሰማያትና የሰማያት ሰማይ ሊይዙት አይችሉምና፤+ በፊቱ የሚጨስ መሥዋዕት የሚቀርብበት ስፍራ ካልሆነ በስተቀር ለእሱ ቤት እሠራለት ዘንድ እኔ ማን ነኝ? 7 አሁንም በወርቅ፣ በብር፣ በመዳብ፣+ በብረት፣ በሐምራዊ ሱፍ፣ በደማቅ ቀይ ክርና በሰማያዊ ክር ሥራ የተካነ እንዲሁም ቅርጻ ቅርጽ የመሥራት ችሎታ ያለው የእጅ ጥበብ ባለሙያ ላክልኝ። እሱም አባቴ ዳዊት ካዘጋጃቸው የተካኑ የእጅ ጥበብ ባለሙያዎቼ ጋር በይሁዳና በኢየሩሳሌም አብሮ ይሠራል።+ 8 የአርዘ ሊባኖስ፣ የጥድና+ የሰንደል ዛፍ+ ሳንቃ ከሊባኖስ ላክልኝ፤ አገልጋዮችህ የሊባኖስን+ ዛፎች በመቁረጥ ረገድ የተካኑ መሆናቸውን በሚገባ አውቃለሁ። አገልጋዮቼ ከአገልጋዮችህ ጋር አብረው በመሥራት+ 9 በርካታ ሳንቃዎችን ያዘጋጁልኛል፤ የምሠራው ቤት እጅግ ታላቅ ነውና። 10 እነሆ፣ ዛፍ ቆራጭና እንጨት ፈላጭ ለሆኑት አገልጋዮችህ ቀለብ እንዲሆናቸው 20,000 የቆሮስ መስፈሪያ* ስንዴ፣ 20,000 የቆሮስ መስፈሪያ* ገብስ፣ 20,000 የባዶስ መስፈሪያ* የወይን ጠጅና 20,000 የባዶስ መስፈሪያ ዘይት እሰጣቸዋለሁ።”+
11 በዚህ ጊዜ የጢሮስ ንጉሥ ኪራም የሚከተለውን መልእክት በጽሑፍ ለሰለሞን ላከለት፦ “ይሖዋ ሕዝቡን ስለሚወድ አንተን በእነሱ ላይ ንጉሥ አድርጎ ሾመህ።” 12 ከዚያም ኪራም እንዲህ አለ፦ “ሰማያትንና ምድርን የሠራው የእስራኤል አምላክ ይሖዋ ውዳሴ ይድረሰው፤ ምክንያቱም ለይሖዋ ቤት፣ ለመንግሥቱም ቤት የሚሠራ ልባምና አስተዋይ+ የሆነ ጥበበኛ ልጅ ለንጉሥ ዳዊት ሰጥቷል።+ 13 አሁንም አስተዋይ የሆነውን ኪራምአቢ+ የተባለውን የእጅ ጥበብ ባለሙያ ልኬልሃለሁ፤ 14 እናቱ ከዳን ወገን ስትሆን አባቱ ግን የጢሮስ ሰው ነው፤ እሱም በወርቅ፣ በብር፣ በመዳብ፣ በብረት፣ በድንጋይ፣ በሳንቃ፣ በሐምራዊ ሱፍ፣ በሰማያዊ ክር፣ ጥራት ባለው ጨርቅና በደማቅ ቀይ ክር ሥራ ልምድ ያካበተ ነው።+ ማንኛውንም ቅርጻ ቅርጽ መቅረጽ እንዲሁም የተሰጠውን ማንኛውንም ንድፍ መሥራት ይችላል።+ አንተ ጋ ካሉትም ሆነ ከጌታዬ ይኸውም ከአባትህ ከዳዊት የተካኑ የእጅ ጥበብ ባለሙያዎች ጋር ሆኖ ይሠራል። 15 አሁንም ጌታዬ ቃል በገባው መሠረት ስንዴውን፣ ገብሱን፣ ዘይቱንና የወይን ጠጁን ለአገልጋዮቹ ይላክ።+ 16 እኛም የምትፈልገውን ያህል ከሊባኖስ+ ዛፎች ቆርጠን አንድ ላይ በማሰር በባሕር ላይ እያንሳፈፍን ወደ ኢዮጴ+ እናመጣልሃለን፤ አንተም ወደ ኢየሩሳሌም ልትወስደው ትችላለህ።”+
17 በዚህ ጊዜ ሰለሞን አባቱ ዳዊት ካደረገው ቆጠራ+ በኋላ በእስራኤል ምድር የሚኖሩትን የባዕድ አገር ወንዶች ሁሉ ቆጠረ፤+ ቁጥራቸውም 153,600 ሆነ። 18 ከእነሱም መካከል 70,000ዎቹን ተራ የጉልበት ሠራተኞች፣* 80,000ዎቹን በተራሮቹ ላይ ድንጋይ ጠራቢዎች፣+ 3,600ዎቹን ደግሞ ሰዎቹን የሚያሠሩ የበላይ ተመልካቾች አድርጎ ሾማቸው።+
3 ከዚያም ሰለሞን በኢየሩሳሌም፣ ይሖዋ ለአባቱ ለዳዊት በተገለጠበት+ በሞሪያ ተራራ+ ይኸውም ዳዊት በኢያቡሳዊው በኦርናን+ አውድማ ላይ ባዘጋጀው ቦታ የይሖዋን ቤት መሥራት ጀመረ።+ 2 በነገሠ በአራተኛው ዓመት፣ በሁለተኛው ወር፣ በሁለተኛው ቀን የግንባታውን ሥራ ጀመረ። 3 ሰለሞን የእውነተኛውን አምላክ ቤት ለመሥራት የጣለው መሠረት በቀድሞው መለኪያ* ርዝመቱ 60 ክንድ፣ ወርዱም 20 ክንድ ነበር።+ 4 ከቤቱ ፊት ያለው በረንዳ ርዝመቱ 20 ክንድ ሲሆን ይህም ከቤቱ ወርድ ጋር እኩል ነው፤ ከፍታው ደግሞ 120* ነው፤ ውስጡንም በንጹሕ ወርቅ ለበጠው።+ 5 ዋናውን ክፍል* በጥድ እንጨት አልብሶ በጥሩ ወርቅ ለበጠው፤+ ከዚያም በዘንባባ ዛፍ ምስሎችና+ በሰንሰለቶች+ አስጌጠው። 6 በተጨማሪም ቤቱን ባማሩና በከበሩ ድንጋዮች ለበጠው፤+ የተጠቀመበትም ወርቅ+ ከፓርዋይም የመጣ ነበር። 7 እሱም ቤቱን፣ ወራጆቹን፣ ደፎቹን፣ ግድግዳዎቹንና በሮቹን በወርቅ ለበጣቸው፤+ በግድግዳዎቹም ላይ የኪሩቦችን ምስል ቀረጸ።+
8 ከዚያም የቅድስተ ቅዱሳኑን ክፍል* ሠራ፤+ ርዝመቱ ከቤቱ ወርድ ጋር እኩል የነበረ ሲሆን 20 ክንድ ነበር፤ ወርዱም 20 ክንድ ነበር። ከዚያም 600 ታላንት* በሚሆን ጥሩ ወርቅ ለበጠው።+ 9 ለምስማሮቹ የዋለው ወርቅ 50 ሰቅል* ይመዝን ነበር፤ ሰገነት ላይ ያሉትንም ክፍሎች በወርቅ ለበጣቸው።
10 ከዚያም በቅድስተ ቅዱሳኑ ክፍል* ውስጥ ሁለት የኪሩቦች ቅርጽ ሠርቶ በወርቅ ለበጣቸው።+ 11 የኪሩቦቹ ክንፎች+ አጠቃላይ ርዝመት 20 ክንድ ነበር፤ የመጀመሪያው ኪሩብ አንደኛው ክንፍ አምስት ክንድ ርዝመት ያለው ሲሆን የቤቱን ግድግዳ ይነካ ነበር፤ ሌላኛው ክንፉም አምስት ክንድ ርዝመት ያለው ሲሆን የሁለተኛውን ኪሩብ ክንፍ ይነካ ነበር። 12 የሁለተኛውም ኪሩብ አንደኛው ክንፍ አምስት ክንድ ርዝመት ያለው ሲሆን በአንጻሩ ያለውን የቤቱን ግድግዳ ይነካ ነበር፤ ሌላኛው ክንፉም አምስት ክንድ ርዝመት ያለው ሲሆን የመጀመሪያውን ኪሩብ ክንፍ ይነካ ነበር። 13 የተዘረጉት የእነዚህ ኪሩቦች ክንፎች 20 ክንድ ነበሩ፤ ኪሩቦቹም ፊታቸውን ወደ ውስጥ* አዙረው በእግራቸው ቆመው ነበር።
14 በተጨማሪም ከሰማያዊ ክር፣ ከሐምራዊ ሱፍ፣ ከደማቅ ቀይ ክርና ጥራት ካለው ጨርቅ መጋረጃ+ ሠርቶ የኪሩቦችን ምስል ጠለፈበት።+
15 ከቤቱ ፊት ለፊትም 35 ክንድ ርዝመት ያላቸው ሁለት ዓምዶችን+ ሠራ፤ በእያንዳንዱ ዓምድ ላይ ያለው የዓምድ ራስ አምስት ክንድ ነበር።+ 16 እንደ ሐብል ያሉ ሰንሰለቶች ሠርቶም በዓምዶቹ አናት ላይ አደረጋቸው፤ እንዲሁም 100 የሮማን ፍሬዎችን ሠርቶ ከሰንሰለቶቹ ጋር አያያዛቸው። 17 ዓምዶቹንም አንዱን በቀኝ* ሌላውን በግራ* አድርጎ በቤተ መቅደሱ ፊት ለፊት አቆማቸው፤ በስተ ቀኝ ያለውን ያኪን፣* በስተ ግራ ያለውን ደግሞ ቦዔዝ* ብሎ ሰየማቸው።
4 ከዚያም ርዝመቱ 20 ክንድ፣ ወርዱ 20 ክንድ፣ ከፍታውም 10 ክንድ የሆነ የመዳብ መሠዊያ ሠራ።+
2 ባሕሩን*+ በቀለጠ ብረት ሠራ። ባሕሩ ክብ ቅርጽ የነበረው ሲሆን ከአንዱ ጠርዝ እስከ ሌላኛው ጠርዝ 10 ክንድ፣ ከፍታው ደግሞ 5 ክንድ ነበር፤ መጠነ ዙሪያውም በመለኪያ ገመድ ሲለካ 30 ክንድ ሆነ።+ 3 በባሕሩም ዙሪያ ከሥሩ በእያንዳንዱ ክንድ ላይ በቅል+ ቅርጽ የተሠሩ አሥር ጌጦች ነበሩ። ቅሎቹም ከባሕሩ ጋር አንድ ወጥ ሆነው በሁለት ረድፍ ቀልጠው ተሠርተው ነበር። 4 ባሕሩ 3ቱ ወደ ሰሜን፣ 3ቱ ወደ ምዕራብ፣ 3ቱ ወደ ደቡብ እንዲሁም 3ቱ ወደ ምሥራቅ አቅጣጫ ፊታቸውን ባዞሩ 12 በሬዎች+ ላይ ተቀምጦ ነበር፤ ባሕሩም ላያቸው ላይ ነበር፤ የሁሉም ሽንጥ ወደ መሃል ገባ ያለ ነበር። 5 የውኃ ማጠራቀሚያው ውፍረት አንድ ጋት* ነበር፤ ጠርዙ የጽዋ ከንፈር ይመስል የነበረ ሲሆን በአበባ ቅርጽ የተሠራ ነበር። የውኃ ማጠራቀሚያው 3,000 የባዶስ መስፈሪያ* መያዝ ይችላል።
6 በተጨማሪም ለመታጠቢያ የሚሆኑ አሥር የውኃ ገንዳዎች ሠርቶ አምስቱን በስተ ቀኝ፣ አምስቱን ደግሞ በስተ ግራ አስቀመጣቸው።+ ገንዳዎቹን የሚቃጠለውን መባ+ ለማቅረብ የሚያገለግሉትን ነገሮች ለማጠብ ይጠቀሙባቸው ነበር። ባሕሩ ግን የካህናቱ መታጠቢያ ነበር።+
7 ከዚያም በተሰጠው መመሪያ መሠረት+ አሥር የወርቅ መቅረዞችን+ ሠርቶ በቤተ መቅደሱ ውስጥ አምስቱን በስተ ቀኝ፣ አምስቱን ደግሞ በስተ ግራ አስቀመጣቸው።+
8 በተጨማሪም አሥር ጠረጴዛዎችን ሠርቶ በቤተ መቅደሱ ውስጥ አምስቱን በስተ ቀኝ፣ አምስቱን በስተ ግራ አስቀመጣቸው፤+ ከዚያም 100 ጎድጓዳ የወርቅ ሳህኖችን ሠራ።
9 ከዚያም የካህናቱን+ ግቢ+ እንዲሁም ትልቁን ግቢና+ የግቢውን በሮች ሠራ፤ የግቢዎቹንም በሮች በመዳብ ለበጣቸው። 10 ባሕሩንም በስተ ቀኝ በኩል፣ በስተ ደቡብ ምሥራቅ አቅጣጫ አስቀመጠው።+
11 በተጨማሪም ኪራም አመድ ማጠራቀሚያዎቹን፣ አካፋዎቹንና ጎድጓዳ ሳህኖቹን ሠራ።+
ኪራምም በእውነተኛው አምላክ ቤት ለንጉሥ ሰለሞን ያከናውን የነበረውን ሥራ ጨረሰ፤+ 12 ሁለቱን ዓምዶች፣+ በሁለቱ ዓምዶች አናት ላይ የነበሩትን የጎድጓዳ ሳህን ቅርጽ ያላቸው የዓምድ ራሶች፣ በዓምዶቹ አናት ላይ የነበሩትን የጎድጓዳ ሳህን ቅርጽ ያላቸውን ሁለቱን ክብ የዓምድ ራሶች የሚያስጌጡትን ሁለት መረቦች፣+ 13 ለሁለቱ መረቦች የተሠሩትን 400 ሮማኖች+ ማለትም በዓምዶቹ አናት ላይ የነበሩትን የጎድጓዳ ሳህን ቅርጽ ያላቸውን ሁለት የዓምድ ራሶች ለማስጌጥ የተሠሩትን በእያንዳንዱ መረብ ላይ በሁለት ረድፍ የተደረደሩትን ሮማኖች፣+ 14 አሥሩን ጋሪዎችና* በጋሪዎቹ ላይ የነበሩትን አሥር የውኃ ገንዳዎች፣+ 15 ባሕሩንና ከሥሩ የነበሩትን 12 በሬዎች፣+ 16 አመድ ማጠራቀሚያዎቹን፣ አካፋዎቹን፣ ሹካዎቹንና+ ከዚህ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ዕቃዎች ሁሉ ኪራምአቢቭ+ ለይሖዋ ቤት መገልገያ እንዲሆኑ ለንጉሥ ሰለሞን ከተወለወለ መዳብ ሠራ። 17 ንጉሡ እነዚህ ነገሮች በዮርዳኖስ አውራጃ፣ በሱኮትና+ በጸሬዳህ መካከል በሚገኝ ስፍራ በሸክላ ጭቃ ውስጥ ቀልጠው እንዲሠሩ አደረገ። 18 ሰለሞን የሠራቸው ዕቃዎች እጅግ ብዙ ነበሩ፤ የመዳቡም ክብደት ምን ያህል እንደሆነ አልታወቀም።+
19 ሰለሞን ለእውነተኛው አምላክ ቤት መገልገያ የሚሆኑትን የሚከተሉትን ነገሮች+ ሠራ፦ የወርቅ መሠዊያውን፣+ ገጸ ኅብስቱ የሚቀመጥባቸውን+ ጠረጴዛዎች፣+ 20 በመመሪያው መሠረት በውስጠኛው ክፍል ፊት የሚበሩትን ከንጹሕ ወርቅ የተሠሩ መቅረዞችና መብራቶቻቸውን፣+ 21 ከወርቅ ይኸውም እጅግ ከጠራ ወርቅ የተሠሩትን የፈኩ አበቦች፣ መብራቶችና መቆንጠጫዎች፣ 22 ከንጹሕ ወርቅ የተሠሩትን የእሳት ማጥፊያዎች፣ ጎድጓዳ ሳህኖች፣ ጽዋዎችና መኮስተሪያዎች እንዲሁም ከወርቅ የተሠሩትን የቤቱን መግቢያ፣ የቅድስተ ቅዱሳኑን+ የውስጥ በሮችና የቤተ መቅደሱን ቤት በሮች።+
5 በዚህ ሁኔታ ሰለሞን ከይሖዋ ቤት ጋር በተያያዘ መሥራት የሚገባውን ሥራ በሙሉ ሠርቶ አጠናቀቀ።+ ከዚያም ሰለሞን አባቱ ዳዊት የቀደሳቸውን ነገሮች ወደዚያ አስገባ፤+ ብሩን፣ ወርቁንና ዕቃዎቹን በሙሉ በእውነተኛው አምላክ ቤት ግምጃ ቤቶች ውስጥ አስቀመጠ።+ 2 በዚህ ጊዜ ሰለሞን የእስራኤልን ሽማግሌዎች፣ የነገዶቹን መሪዎች ሁሉና የእስራኤልን የአባቶች ቤት አለቆች ሰበሰበ። እነሱም የይሖዋን የቃል ኪዳን ታቦት ከዳዊት ከተማ ማለትም ከጽዮን+ ለማምጣት ወደ ኢየሩሳሌም መጡ።+ 3 የእስራኤል ሰዎች በሙሉ በሰባተኛው ወር በሚከበረው በዓል* ላይ በንጉሡ ፊት ተሰበሰቡ።+
4 የእስራኤል ሽማግሌዎችም በሙሉ መጡ፤ ሌዋውያኑም ታቦቱን አነሱ።+ 5 ታቦቱን፣ የመገናኛ ድንኳኑንና+ በድንኳኑ ውስጥ የነበሩትን ቅዱስ ዕቃዎች በሙሉ አመጡ። እነዚህንም ያመጡት ካህናቱና ሌዋውያኑ* ናቸው። 6 ንጉሥ ሰለሞንና ወደ እሱ እንዲመጣ የተጠራው መላው የእስራኤል ማኅበረሰብ ታቦቱ ፊት ነበሩ። ከብዛታቸው የተነሳ ሊቆጠሩ የማይችሉ ብዙ በጎችና ከብቶች መሥዋዕት ሆነው ቀረቡ።+ 7 ከዚያም ካህናቱ የይሖዋን የቃል ኪዳን ታቦት አምጥተው ቦታው ላይ ማለትም በቤቱ ውስጠኛ ክፍል ይኸውም በቅድስተ ቅዱሳኑ ውስጥ ከኪሩቦቹ ክንፎች በታች አስቀመጡት።+ 8 የኪሩቦቹ ክንፎች ታቦቱ ባለበት ቦታ ላይ ተዘርግተው ስለነበር ኪሩቦቹ ታቦቱንና መሎጊያዎቹን+ ከላይ ሸፍነዋቸው ነበር። 9 መሎጊያዎቹ ረጅም ስለነበሩ የመሎጊያዎቹን ጫፎች ከውስጠኛው ክፍል ፊት ለፊት ባለው በቅድስቱ ውስጥ ሆኖ ማየት ይቻል ነበር፤ ከውጭ ግን አይታዩም ነበር። እስከ ዛሬም ድረስ እዚያው ይገኛሉ። 10 የእስራኤል ሰዎች ከግብፅ ምድር ሲወጡ+ ይሖዋ ከእነሱ ጋር ቃል ኪዳን+ በገባበት ጊዜ ሙሴ በኮሬብ ታቦቱ ውስጥ ካስቀመጣቸው ከሁለቱ የድንጋይ ጽላቶች+ በስተቀር በታቦቱ ውስጥ ምንም አልነበረም።
11 ካህናቱ ከቅዱሱ ስፍራ በወጡ ጊዜ (በዚያ የተገኙት ካህናት ሁሉ ከየትኛውም ምድብ+ ይሁኑ ራሳቸውን ቀድሰው ነበር)፣+ 12 ከአሳፍ፣+ ከሄማን፣+ ከየዱቱን+ እንዲሁም ከወንዶች ልጆቻቸውና ከወንድሞቻቸው ወገን የሆኑት ሌዋውያን ዘማሪዎች+ ሁሉ ጥራት ያለው ልብስ ለብሰውና ሲምባል፣* ባለ አውታር መሣሪያዎችና በገና ይዘው ነበር፤ ከመሠዊያው በስተ ምሥራቅ ቆመው የነበረ ሲሆን ከእነሱም ጋር መለከት የሚነፉ 120 ካህናት ነበሩ።+ 13 መለከት ነፊዎቹና ዘማሪዎቹ በኅብረት ይሖዋን ባወደሱና ባመሰገኑ ጊዜ እንዲሁም “እሱ ጥሩ ነውና፤ ታማኝ ፍቅሩ ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል”+ እያሉ ይሖዋን በማወደስ የመለከቱን፣ የሲምባሉንና የሌሎቹን የሙዚቃ መሣሪያዎች ድምፅ ባሰሙ ጊዜ ቤቱ ይኸውም የይሖዋ ቤት በደመና ተሞልቶ ነበር።+ 14 የይሖዋ ክብር የእውነተኛውን አምላክ ቤት ሞልቶት ስለነበር ካህናቱ ከደመናው የተነሳ በዚያ ቆመው ማገልገል አልቻሉም።+
6 በዚህ ጊዜ ሰለሞን እንዲህ አለ፦ “ይሖዋ በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ እንደሚኖር ተናግሯል።+ 2 አሁን እኔ እጅግ ከፍ ያለ ቤት፣ ለዘላለም የምትኖርበት ጸንቶ የተመሠረተ ቦታ ገንብቼልሃለሁ።”+
3 ከዚያም መላው የእስራኤል ጉባኤ ቆሞ ሳለ ንጉሡ ዞሮ የእስራኤልን ጉባኤ ሁሉ መባረክ ጀመረ።+ 4 እንዲህም አለ፦ “ለአባቴ ለዳዊት በገዛ አፉ እንዲህ ብሎ ቃል የገባውና ይህን በራሱ እጆች የፈጸመው የእስራኤል አምላክ ይሖዋ ይወደስ፦ 5 ‘ሕዝቤን እስራኤልን ከግብፅ ምድር ካወጣሁበት ዕለት አንስቶ ከእስራኤል ነገዶች ሁሉ መካከል ስሜ የሚጠራበት ቤት እንዲሠራበት አንድም ከተማ አልመረጥኩም፤+ ደግሞም የሕዝቤ የእስራኤል መሪ እንዲሆን ማንንም አልመረጥኩም። 6 ሆኖም ስሜ እንዲጠራባት ኢየሩሳሌምን፣+ በሕዝቤም በእስራኤል ላይ ገዢ እንዲሆን ዳዊትን መርጫለሁ።’+ 7 አባቴ ዳዊት ለእስራኤል አምላክ ለይሖዋ ስም ቤት ለመሥራት ከልቡ ተመኝቶ ነበር።+ 8 ሆኖም ይሖዋ አባቴን ዳዊትን እንዲህ አለው፦ ‘ለስሜ ቤት ለመሥራት ከልብህ ተመኝተህ ነበር፤ ይህን በልብህ መመኘትህም መልካም ነው። 9 ይሁንና ቤቱን የምትሠራው አንተ አይደለህም፤ ሆኖም ለስሜ ቤት የሚሠራልኝ የሚወለድልህ የገዛ ልጅህ* ይሆናል።’+ 10 ይሖዋ የገባውን ቃል ፈጽሟል፤ ልክ ይሖዋ ቃል በገባው መሠረት+ አባቴን ዳዊትን ተክቼ በእስራኤል ዙፋን ላይ ተቀምጫለሁና።+ በተጨማሪም ለእስራኤል አምላክ ለይሖዋ ስም ቤት ሠርቻለሁ፤ 11 በዚያም ይሖዋ ከእስራኤል ሕዝብ ጋር የገባው ቃል ኪዳን ያለበትን ታቦት+ አስቀምጫለሁ።”
12 ከዚያም ሰለሞን በይሖዋ መሠዊያ ፊት፣ በመላው የእስራኤል ጉባኤ ፊት ለፊት ቆመ፤ እጆቹንም ዘረጋ።+ 13 (ሰለሞን የመዳብ መድረክ ሠርቶ በግቢው መካከል አስቀምጦ ነበር።+ የመድረኩ ርዝመት አምስት ክንድ፣* ወርዱ አምስት ክንድ፣ ከፍታውም ሦስት ክንድ ነበር፤ እሱም በመድረኩ ላይ ቆሞ ነበር።) በመላው የእስራኤል ጉባኤ ፊት ተንበርክኮም እጆቹን ወደ ሰማያት ዘረጋ፤+ 14 እንዲህም አለ፦ “የእስራኤል አምላክ ይሖዋ ሆይ፣ በፊቱ በሙሉ ልባቸው ለሚመላለሱ አገልጋዮቹ ቃል ኪዳኑን የሚጠብቅና ታማኝ ፍቅር የሚያሳይ እንደ አንተ ያለ አምላክ በሰማያትም ሆነ በምድር የለም።+ 15 ለአገልጋይህ ለአባቴ ለዳዊት የገባኸውን ቃል ጠብቀሃል።+ በገዛ አፍህ ቃል ገባህ፤ ዛሬ ደግሞ በራስህ እጅ ፈጸምከው።+ 16 አሁንም የእስራኤል አምላክ ይሖዋ ሆይ ‘አንተ በፊቴ እንደተመላለስከው ሁሉ+ ልጆችህም በጥንቃቄ ሕጌን ጠብቀው ከተመላለሱ ከዘርህ በእስራኤል ዙፋን ላይ የሚቀመጥ ሰው ከፊቴ አይታጣም’+ በማለት ለአገልጋይህ ለአባቴ ለዳዊት የገባኸውን ቃል ጠብቅ። 17 አሁንም የእስራኤል አምላክ ይሖዋ ሆይ፣ ለአገልጋይህ ለዳዊት የገባኸው ቃል ይፈጸም።
18 “በእርግጥ አምላክ ከሰው ልጆች ጋር በምድር ላይ ይኖራል?+ እነሆ ሰማያት፣ አዎ ሰማየ ሰማያት እንኳ ሊይዙህ አይችሉም፤+ ታዲያ እኔ የሠራሁት ይህ ቤትማ ምንኛ ያንስ!+ 19 እንግዲህ አምላኬ ይሖዋ ሆይ፣ የአገልጋይህን ጸሎትና ሞገስ ለማግኘት የሚያቀርበውን ልመና በትኩረት ስማ፤ አገልጋይህ እርዳታ ለማግኘት የሚያሰማውን ጩኸትና በፊትህ የሚያቀርበውን ጸሎት አዳምጥ። 20 አገልጋይህ ወደዚህ ስፍራ የሚያቀርበውን ጸሎት ለመስማት ስምህ እንደሚጠራበት+ ወደተናገርከው ወደዚህ ቤት ዓይኖችህ ሌሊትና ቀን ይመልከቱ። 21 አገልጋይህ እርዳታ ለማግኘት የሚያቀርበውን ልመናና ሕዝብህ እስራኤል ወደዚህ ስፍራ በሚጸልይበት ጊዜ+ የሚያቀርበውን ልመና አዳምጥ፤ በማደሪያህም በሰማያት ሆነህ ስማ፤+ ሰምተህም ይቅር በል።+
22 “አንድ ሰው ባልንጀራውን በድሎ እንዲምል ቢደረግ፣* በመሐላውም* ተጠያቂ ቢሆን፣ በዳዩም በዚህ መሐላ* ሥር ሆኖ እዚህ ቤት ውስጥ ባለው መሠዊያህ ፊት ቢቀርብ፣+ 23 አንተ በሰማያት ሆነህ ስማ፤ ለክፉው እንደ ሥራው በመመለስና+ የእጁን እንዲያገኝ በማድረግ፣ ጻድቁንም ንጹሕ* መሆኑን በማሳወቅና እንደ ጽድቁ ወሮታውን በመክፈል+ እርምጃ ውሰድ፤ አገልጋዮችህንም ዳኝ።
24 “ሕዝብህ እስራኤላውያን አንተን ከመበደላቸው የተነሳ በጠላት ድል ቢነሱና+ ተመልሰው ስምህን ቢያወድሱ+ እንዲሁም በዚህ ቤት በፊትህ ቢጸልዩና+ ሞገስ ለማግኘት ልመና ቢያቀርቡ+ 25 ከሰማያት ሆነህ ስማ፤+ የሕዝብህንም የእስራኤልን ኃጢአት ይቅር በል፤ ለእነሱና ለአባቶቻቸው ወደሰጠኸው ምድርም መልሳቸው።+
26 “ሕዝቡ አንተን በመበደሉ የተነሳ+ ሰማያት ተዘግተው ዝናብ ቢጠፋ፣+ እነሱም አንተ ስላዋረድካቸው* ወደዚህ ስፍራ ቢጸልዩና ስምህን ቢያወድሱ እንዲሁም ከኃጢአታቸው ቢመለሱ+ 27 ከሰማያት ሆነህ ስማ፤ የአገልጋዮችህን፣ የሕዝብህን የእስራኤላውያንን ኃጢአት ይቅር በል፤ ስለሚሄዱበት ቀና መንገድ ታስተምራቸዋለህና፤+ ለሕዝብህ ርስት አድርገህ ባወረስከው ምድርህም ላይ ዝናብ አዝንብ።+
28 “በምድሪቱ ላይ ረሃብ+ ወይም ቸነፈር፣+ የሚለበልብና የሚያደርቅ ነፋስ ወይም ዋግ+ ቢከሰት፣ የአንበጣ መንጋ ወይም የማይጠግብ አንበጣ*+ ቢመጣ አሊያም ጠላቶቻቸው በምድሪቱ ላይ ባለ በየትኛውም ከተማ* ውስጥ ሳሉ ቢከቧቸው+ ወይም ደግሞ ማንኛውም ዓይነት መቅሰፍት አሊያም ማንኛውም ዓይነት በሽታ ቢከሰትና+ 29 ማንኛውም ሰው ወይም ሕዝብህ እስራኤል በሙሉ (እያንዳንዱ የገዛ ጭንቀቱንና ሥቃዩን ያውቃልና)+ ወደ አንተ ለመጸለይ+ ወይም ሞገስ እንድታሳየው ልመና ለማቅረብ+ እጁን ወደዚህ ቤት ቢዘረጋ+ 30 አንተ ከመኖሪያ ቦታህ ከሰማያት ሆነህ ስማ፤+ ደግሞም ይቅር በል፤+ ለእያንዳንዱም እንደ ሥራው ብድራቱን ክፈለው፤ ምክንያቱም አንተ ልቡን ታውቃለህ (የሰውን ልብ በሚገባ የምታውቀው አንተ ብቻ ነህ)፤+ 31 ይህም ለአባቶቻችን በሰጠኸው ምድር ላይ በሚኖሩበት ዘመን ሁሉ በመንገዶችህ በመመላለስ አንተን እንዲፈሩ ነው።
32 “በተጨማሪም ከሕዝብህ ከእስራኤል ወገን ያልሆነ የባዕድ አገር ሰው ከታላቁ ስምህ፣* ከኃያሉ እጅህና ከተዘረጋው ክንድህ የተነሳ ከሩቅ አገር ቢመጣ፣+ ወደዚህም ቤት መጥቶ ቢጸልይ፣+ 33 ከመኖሪያ ቦታህ ከሰማያት ሆነህ ስማ፤ የምድር ሕዝቦች ሁሉ እንደ ሕዝብህ እንደ እስራኤል ስምህን እንዲያውቁና+ እንዲፈሩህ እንዲሁም ስምህ እኔ በሠራሁት በዚህ ቤት እንደሚጠራ እንዲያውቁ ያ የባዕድ አገር ሰው የጠየቀህን ሁሉ ፈጽምለት።
34 “ሕዝብህ ጠላቶቻቸውን ለመውጋት አንተ በምትልካቸው መንገድ ለጦርነት ቢወጡና+ አንተ ወደመረጥከው ወደዚህ ከተማ እንዲሁም ለስምህ ወደሠራሁት ቤት አቅጣጫ+ ቢጸልዩ+ 35 ከሰማያት ሆነህ ጸሎታቸውንና ሞገስ ለማግኘት የሚያቀርቡትን ልመና ስማ፤ ፍረድላቸውም።+
36 “በአንተ ላይ ኃጢአት ቢሠሩ (መቼም ኃጢአት የማይሠራ ሰው የለም)፣+ አንተም በእነሱ እጅግ ተቆጥተህ ለጠላት አሳልፈህ ብትሰጣቸው፣ ጠላቶቻቸውም ራቅ ወዳለ ወይም ቅርብ ወደሆነ ምድር ምርኮኛ አድርገው ቢወስዷቸው፣+ 37 እነሱም በምርኮ በተወሰዱበት ምድር ወደ ልቦናቸው ቢመለሱና ወደ አንተ ዞር በማለት ‘ኃጢአት ሠርተናል፤ አጥፍተናል፤ ክፉ ድርጊትም ፈጽመናል’ በማለት በተማረኩበት ምድር ሆነው ሞገስ ለማግኘት ወደ አንተ ልመና ቢያቀርቡ፣+ 38 ደግሞም ተማርከው በተወሰዱበት፣ ምርኮኛ ሆነው በሚኖሩበት ምድር፣+ በሙሉ ልባቸውና+ በሙሉ ነፍሳቸው* ወደ አንተ ቢመለሱ እንዲሁም ለአባቶቻቸው በሰጠሃቸው ምድር፣ አንተ በመረጥካት ከተማና ለስምህ በሠራሁት ቤት አቅጣጫ ቢጸልዩ፣+ 39 ጸሎታቸውንና ሞገስ ለማግኘት ያቀረቡትን ልመና ከመኖሪያ ቦታህ ከሰማያት ሆነህ ስማ፤ ፍረድላቸውም፤+ በአንተ ላይ ኃጢአት የሠራውን ሕዝብህን ይቅር በል።
40 “አሁንም አምላኬ ሆይ፣ እባክህ በዚህ ቦታ* ወደቀረበው ጸሎት ዓይኖችህ ይመልከቱ፤ ጆሮዎችህም በትኩረት ያዳምጡ።+ 41 አሁንም ይሖዋ አምላክ ሆይ፣ ከብርታትህ ታቦት ጋር ወደ ማረፊያ ቦታህ+ ውጣ። ይሖዋ አምላክ ሆይ፣ ካህናትህ መዳንን ይልበሱ፤ ታማኞችህም በጥሩነትህ ሐሴት ያድርጉ።+ 42 ይሖዋ አምላክ ሆይ፣ የቀባኸውን ሰው ገሸሽ አታድርግ።*+ ለአገልጋይህ ለዳዊት ያሳየኸውን ታማኝ ፍቅር አስብ።”+
7 ሰለሞንም ጸሎቱን እንደጨረሰ+ እሳት ከሰማያት ወርዶ+ የሚቃጠለውን መባና መሥዋዕቶቹን በላ፤ የይሖዋም ክብር ቤቱን ሞላው።+ 2 የይሖዋ ክብር የይሖዋን ቤት ሞልቶት ስለነበር ካህናቱ ወደ ይሖዋ ቤት መግባት አልቻሉም።+ 3 የእስራኤልም ሕዝብ ሁሉ እሳቱ ሲወርድና የይሖዋ ክብር ከቤቱ በላይ ሲሆን ይመለከቱ ነበር፤ ወደ መሬት አጎንብሰው ድንጋይ በተነጠፈበት ወለል ላይ በግንባራቸው ተደፍተው ሰገዱ፤ ደግሞም “እሱ ጥሩ ነውና፤ ታማኝ ፍቅሩ ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል” እያሉ ይሖዋን አመሰገኑ።
4 ከዚያም ንጉሡና ሕዝቡ ሁሉ በይሖዋ ፊት መሥዋዕት አቀረቡ።+ 5 ንጉሥ ሰለሞን 22,000 ከብቶችና 120,000 በጎች መሥዋዕት አድርጎ አቀረበ። በዚህ መንገድ ንጉሡና ሕዝቡ ሁሉ የእውነተኛውን አምላክ ቤት መረቁ።+ 6 ካህናቱም ሆኑ የይሖዋን መዝሙር ለማጀብ የሚያገለግሉ የሙዚቃ መሣሪያዎችን የያዙት ሌዋውያን እንዲያገለግሉ በተመደቡበት ስፍራ ቆመው ነበር።+ (ንጉሥ ዳዊት እነዚህን መሣሪያዎች የሠራው ከእነሱ ጋር* ሆኖ ውዳሴ በሚያቀርብበት ጊዜ “ታማኝ ፍቅሩ ለዘላለም ጸንቶ ይኖራልና” በማለት ይሖዋን ለማመስገን ነው።) ካህናቱ በእነሱ ትይዩ ሆነው መለከቶቹን በኃይል ይነፉ ነበር፤+ በዚህ ጊዜ እስራኤላውያን ሁሉ በዚያ ቆመው ነበር።
7 ከዚያም ሰለሞን በይሖዋ ቤት ፊት የሚገኘውን የግቢውን መሃል ቀደሰው፤ ምክንያቱም ሰለሞን የሚቃጠለውን መባና+ የኅብረት መሥዋዕቱን ስብ በዚያ ማቅረብ ነበረበት፤ ይህም የሆነው ሰለሞን የሠራው የመዳብ መሠዊያ+ የሚቃጠለውን መሥዋዕት፣ የእህሉን መባና+ ስቡን+ መያዝ ስላልቻለ ነው። 8 በዚያን ጊዜ ሰለሞን ከመላው እስራኤል ጋር ይኸውም ከሌቦሃማት* አንስቶ እስከ ግብፅ ደረቅ ወንዝ* ድረስ+ ካለው ምድር ከመጣው ታላቅ ጉባኤ ጋር በመሆን ለሰባት ቀን በዓሉን* አከበረ።+ 9 ይሁንና የመሠዊያውን የምረቃ ሥነ ሥርዓት ለሰባት ቀን ስላከናወኑና በዓሉን ለሰባት ቀን ስላከበሩ በስምንተኛው ቀን* የተቀደሰ ጉባኤ አደረጉ።+ 10 ከዚያም በሰባተኛው ወር፣ በ23ኛው ቀን ሕዝቡን ወደየቤታቸው አሰናበተ፤ እነሱም ይሖዋ ለዳዊት፣ ለሰለሞንና ለሕዝቡ ለእስራኤል ባሳየው ጥሩነት እየተደሰቱና+ ከልባቸው እየፈነደቁ ሄዱ።+
11 ሰለሞንም የይሖዋን ቤትና የንጉሡን ቤት*+ ሠርቶ ጨረሰ፤ ከይሖዋ ቤትና ከራሱ ቤት ጋር በተያያዘ በልቡ ያሰበውን ሁሉ በተሳካ ሁኔታ አከናወነ።+ 12 ከዚያም ይሖዋ በሌሊት ለሰለሞን ተገልጦለት+ እንዲህ አለው፦ “ጸሎትህን ሰምቻለሁ፤ ይህን ቦታ መሥዋዕት የሚቀርብበት ቤት እንዲሆን ለራሴ መርጬዋለሁ።+ 13 ዝናብ እንዳይዘንብ ሰማያትን ብዘጋ፣ ምድሪቱን እንዲበሉ አንበጦችን ብልክ፣ በሕዝቤ መካከል ቸነፈር ብሰድ፣ 14 በስሜ የተጠሩትም ሕዝቤ+ ራሳቸውን ዝቅ ቢያደርጉ፣+ ቢጸልዩ፣ ፊቴን ቢሹና ከክፉ መንገዳቸው ቢመለሱ፣+ ከሰማያት ሆኜ እሰማለሁ፤ ኃጢአታቸውን ይቅር እላለሁ፤ ምድራቸውንም እፈውሳለሁ።+ 15 በዚህም ስፍራ ለሚቀርበው ጸሎት ዓይኖቼ ይገለጣሉ፤ ጆሮዎቼም ይከፈታሉ።+ 16 አሁንም ስሜ ለዘለቄታው በዚያ እንዲጠራ ይህን ቤት መርጬዋለሁ፤+ ደግሞም ቀድሼዋለሁ፤ ዓይኔም ሆነ ልቤ ሁልጊዜ በዚያ ይሆናል።+
17 “አንተም አባትህ ዳዊት እንዳደረገው ያዘዝኩህን ሁሉ በመፈጸም በፊቴ ብትሄድ እንዲሁም ሥርዓቶቼንና ድንጋጌዎቼን ብትጠብቅ፣+ 18 ለአባትህ ለዳዊት ‘ከዘር ሐረግህ በእስራኤል ላይ ገዢ የሚሆን አይታጣም’+ በማለት በገባሁለት ቃል ኪዳን መሠረት+ የንግሥና ዙፋንህን አጸናለሁ።+ 19 ሆኖም ጀርባችሁን ብትሰጡ፣ በፊታችሁ ያስቀመጥኳቸውን ደንቦቼንና ትእዛዛቴን ብትተዉ፣ ሄዳችሁም ሌሎች አማልክትን ብታገለግሉና ለእነሱ ብትሰግዱ፣+ 20 እስራኤልን ከሰጠሁት ምድሬ ላይ እነቅለዋለሁ፤+ ለስሜ የቀደስኩትንም ይህን ቤት ከፊቴ አስወግደዋለሁ፤ በሕዝቦች ሁሉ ዘንድ መቀለጃና* መሳለቂያ አደርገዋለሁ።+ 21 ይህም ቤት የፍርስራሽ ክምር ይሆናል። በዚያም የሚያልፉ ሰዎች ሁሉ በመገረም ትኩር ብለው እየተመለከቱ+ ‘ይሖዋ በዚህች ምድርና በዚህ ቤት ላይ እንዲህ ያለ ነገር ያደረገው ለምንድን ነው?’ በማለት ይጠይቃሉ።+ 22 ከዚያም እንዲህ ይላሉ፦ ‘ይህ የደረሰባቸው ከግብፅ ምድር ያወጣቸውን+ የአባቶቻቸውን አምላክ ይሖዋን ትተው+ ሌሎች አማልክትን ስለተከተሉና ለእነሱ ስለሰገዱ እንዲሁም እነሱን ስላገለገሉ ነው።+ ይህን ሁሉ መከራ ያመጣባቸው ለዚህ ነው።’”+
8 ሰለሞን የይሖዋን ቤትና የራሱን ቤት* ገንብቶ በጨረሰበት በ20ኛው ዓመት ማብቂያ ላይ+ 2 ኪራም+ የሰጠውን ከተሞች መልሶ ገነባቸው፤ እስራኤላውያንንም በዚያ አሰፈረ። 3 በተጨማሪም ሰለሞን በሃማትጾባ ላይ ዘምቶ ያዛት። 4 ከዚያም በምድረ በዳ የምትገኘውን ታድሞርንና በሃማት+ የሠራቸውን የማከማቻ ከተሞች ሁሉ ገነባ።*+ 5 ደግሞም ቅጥሮች፣ በሮችና መቀርቀሪያዎች ያሏቸውን የተመሸጉትን ከተሞች ይኸውም ላይኛውን ቤትሆሮንንና+ ታችኛውን ቤትሆሮንን+ ገነባ፤ 6 በተጨማሪም ባዓላትን፣+ የሰለሞንን የእህልና የዕቃ ማከማቻ ከተሞች በሙሉ፣ የሠረገላ ከተሞቹን በሙሉ፣+ የፈረሰኞቹን ከተሞች እንዲሁም ሰለሞን በኢየሩሳሌም፣ በሊባኖስና በእሱ ግዛት ውስጥ ባለው ምድር ሁሉ መገንባት የፈለጋቸውን ነገሮች በሙሉ ሠራ።
7 ከእስራኤል ወገን ያልሆኑትን+ ከሂታውያን፣ ከአሞራውያን፣ ከፈሪዛውያን፣ ከሂዋውያንና ከኢያቡሳውያን+ የተረፉትን ሕዝቦች በሙሉ፣ 8 ይኸውም እስራኤላውያን ፈጽመው ያላጠፏቸውን+ በምድሪቱ ላይ የቀሩትን ዘሮቻቸውን ሰለሞን የግዳጅ ሥራ እንዲሠሩ መለመላቸው፤+ እስከ ዛሬም ድረስ ይሠራሉ። 9 ሆኖም ሰለሞን ለሚያከናውነው ሥራ ከእስራኤላውያን መካከል አንዳቸውንም ባሪያ አላደረገም፤+ ምክንያቱም እነሱ ተዋጊዎቹ፣ የጦር መኮንኖቹ፣ የሠረገለኞቹና የፈረሰኞቹ አለቆች ነበሩ።+ 10 በሠራተኞቹ ላይ የተሾሙት ይኸውም የንጉሥ ሰለሞን የበታች ተቆጣጣሪዎቹ አለቆች+ 250 ነበሩ።
11 በተጨማሪም ሰለሞን የፈርዖንን ሴት ልጅ+ ከዳዊት ከተማ አውጥቶ ወደሠራላት ቤት አመጣት፤+ ይህን ያደረገው “እሷ ሚስቴ ብትሆንም የይሖዋ ታቦት የገባባቸው ቦታዎች ቅዱስ ስለሆኑ በእስራኤል ንጉሥ በዳዊት ቤት ልትኖር አይገባም” በማለት ነበር።+
12 ከዚያም ሰለሞን ከበረንዳው+ ፊት ለፊት በሠራው የይሖዋ መሠዊያ+ ላይ የሚቃጠል መሥዋዕት ለይሖዋ አቀረበ።+ 13 ለሙሴ ከተሰጠው ትእዛዝ ጋር በሚስማማ ሁኔታ በሥርዓቱ መሠረት በየዕለቱ ሊቀርቡ የሚገባቸውን መባዎች ማለትም የየሰንበቱን፣+ የየወሩን መባቻና+ በዓመት ሦስት ጊዜ የሚደረጉትን የተወሰኑትን በዓላት+ ይኸውም የቂጣን* በዓል፣+ የሳምንታትን በዓልና+ የዳስን* በዓል+ መባዎች አቀረበ። 14 በተጨማሪም አባቱ ዳዊት ባወጣው ደንብ መሠረት ካህናቱን በየአገልግሎት ምድባቸው፣+ ሌዋውያኑንም በየዕለቱ ሊከናወን በሚገባው ሥርዓት መሠረት ካህናቱ ባሉበት አምላክን እንዲያወድሱና+ እንዲያገለግሉ በተመደቡበት ስፍራ ላይ ሾማቸው፤ በር ጠባቂዎቹንም በተለያዩ በሮች ላይ በየቡድናቸው መደባቸው፤+ የእውነተኛው አምላክ ሰው ዳዊት ይህን ትእዛዝ አስተላልፎ ነበርና። 15 እነሱም ንጉሡ ማንኛውንም ጉዳይ ወይም ግምጃ ቤቶቹን በተመለከተ ለካህናቱና ለሌዋውያኑ ከሰጠው ትእዛዝ ፈቀቅ አላሉም። 16 በመሆኑም የይሖዋ ቤት መሠረቱ ከተጣለበት ጊዜ+ አንስቶ ሥራው እስካበቃበት ጊዜ ድረስ ሰለሞን የሠራው ሥራ ሁሉ በሚገባ የተደራጀ* ነበር። የይሖዋም ቤት ሥራ ሙሉ በሙሉ ተጠናቀቀ።+
17 ከዚያም ሰለሞን በኤዶም ምድር+ በባሕሩ ዳርቻ ወደሚገኙት ወደ ዔጽዮንጋብርና+ ወደ ኤሎት+ ሄደ። 18 ኪራም+ በአገልጋዮቹ አማካኝነት መርከቦችንና ልምድ ያላቸው ባሕረኞችን ላከለት። እነሱም ከሰለሞን አገልጋዮች ጋር ወደ ኦፊር+ በመሄድ 450 ታላንት* ወርቅ+ አምጥተው ለንጉሥ ሰለሞን ሰጡት።+
9 የሳባ ንግሥት+ ስለ ሰለሞን ዝና በሰማች ጊዜ አስቸጋሪ በሆኑ ጥያቄዎች* ልትፈትነው ወደ ኢየሩሳሌም መጣች። እሷም እጅግ ታላቅ አጀብ አስከትላ እንዲሁም የበለሳን ዘይት፣ በጣም ብዙ ወርቅና+ የከበሩ ድንጋዮች በግመል አስጭና ነበር። ወደ ሰለሞንም ገብታ በልቧ ያለውን ሁሉ ነገረችው።+ 2 ሰለሞንም ጥያቄዎቿን ሁሉ መለሰላት። ሰለሞን ሊያብራራላት ያልቻለው* ምንም ነገር አልነበረም።
3 የሳባ ንግሥት የሰለሞንን ጥበብና+ የሠራውን ቤት+ ስትመለከት፣ 4 በገበታው ላይ የሚቀርበውን ምግብ፣+ የአገልጋዮቹን አቀማመጥ፣ አስተናጋጆቹ በማዕድ ላይ የሚያስተናግዱበትን መንገድና አለባበሳቸውን፣ መጠጥ አሳላፊዎቹንና አለባበሳቸውን እንዲሁም በይሖዋ ቤት ዘወትር የሚያቀርባቸውን የሚቃጠሉ መሥዋዕቶች+ ስታይ በመገረም ፈዛ ቀረች።* 5 በመሆኑም ንጉሡን እንዲህ አለችው፦ “ስላከናወንካቸው ነገሮችና* ስለ ጥበብህ በአገሬ ሳለሁ የሰማሁት ነገር እውነት ነው። 6 ይሁንና እኔ ራሴ መጥቼ በገዛ ዓይኔ እስከማይ ድረስ የተነገረኝን ነገር አላመንኩም ነበር።+ እንደዚያም ሆኖ ታላቅ ከሆነው ጥበብህ ግማሹ እንኳ አልተነገረኝም!+ እኔ ስለ አንተ ከሰማሁት እጅግ የላቅክ ነህ።+ 7 አብረውህ ያሉ ሰዎች ደስተኞች ናቸው፤ ዘወትር በፊትህ ቆመው ጥበብህን የሚሰሙት አገልጋዮችህም እጅግ ደስተኞች ናቸው! 8 ለአምላክህ ለይሖዋ ንጉሥ ሆነህ እንድትገዛ አንተን በዙፋኑ ላይ በማስቀመጥ በአንተ ደስ የተሰኘው አምላክህ ይሖዋ ይወደስ። አምላክህ እስራኤልን ስለወደደውና+ ለዘላለም ያጸናው ዘንድ ስለፈለገ፣ ፍትሕንና ጽድቅን እንድታሰፍን በእስራኤል ላይ ንጉሥ አድርጎ ሾሞሃል።”
9 ከዚያም ለንጉሡ 120 ታላንት* ወርቅ+ እንዲሁም እጅግ ብዙ የበለሳን ዘይትና የከበሩ ድንጋዮችን ሰጠችው። የሳባ ንግሥት ለንጉሥ ሰለሞን የሰጠችውን ያህል የበለሳን ዘይት ከዚያ በኋላ መጥቶ አያውቅም።+
10 ከዚህ በተጨማሪ ከኦፊር ወርቅ+ ጭነው የመጡት የኪራም አገልጋዮችና የሰለሞን አገልጋዮች የሰንደል ዛፍ ሳንቃዎችና የከበሩ ድንጋዮች አመጡ።+ 11 ንጉሡም ከሰንደል ዛፍ ሳንቃዎቹ ለይሖዋ ቤትና ለንጉሡ ቤት*+ ደረጃዎችን+ እንዲሁም ለዘማሪዎቹ የሚሆኑ በገናዎችንና ሌሎች ባለ አውታር መሣሪያዎችን ሠራ።+ ከዚያ በፊት እንዲህ ያለ ነገር በይሁዳ ምድር ታይቶ አያውቅም።
12 ንጉሥ ሰለሞን ደግሞ የሳባ ንግሥት የፈለገችውንና የጠየቀችውን ነገር ሁሉ፣ ካመጣችለት ስጦታ የሚበልጥ ነገር ሰጣት።* ከዚያም ተነስታ አገልጋዮቿን በማስከተል ወደ አገሯ ተመለሰች።+
13 ሰለሞን በየዓመቱ 666 ታላንት ወርቅ ይመጣለት ነበር፤+ 14 ይህም ነጋዴዎችና ሻጮች የሚያስገቡትን ገቢ እንዲሁም የዓረብ ነገሥታት ሁሉና አገረ ገዢዎች ለሰለሞን የሚያመጡትን ወርቅና ብር ሳይጨምር ነው።+
15 ንጉሥ ሰለሞን ከቅይጥ ወርቅ 200 ትላልቅ ጋሻዎችን ሠራ፤+ (እያንዳንዱ ጋሻ በ600 ሰቅል* ቅይጥ ወርቅ ተለብጦ ነበር)፤+ 16 እንዲሁም ከቅይጥ ወርቅ 300 ትናንሽ ጋሻዎችን* ሠራ፤ (እያንዳንዱ ትንሽ ጋሻ በሦስት ምናን* ወርቅ ተለብጦ ነበር)። ከዚያም ንጉሡ የሊባኖስ ደን በተባለው ቤት አስቀመጣቸው።+
17 በተጨማሪም ንጉሡ ከዝሆን ጥርስ ትልቅ ዙፋን ሠርቶ በንጹሕ ወርቅ ለበጠው።+ 18 ወደ ዙፋኑ የሚያስወጡ ስድስት ደረጃዎች ነበሩ፤ ከዙፋኑም ጋር የተያያዘ ከወርቅ የተሠራ የእግር ማሳረፊያ ነበር፤ መቀመጫውም በጎንና በጎኑ የእጅ መደገፊያዎች ያሉት ሲሆን ከእጅ መደገፊያዎቹም አጠገብ ሁለት አንበሶች+ ቆመው ነበር። 19 በስድስቱ ደረጃዎች ዳርና ዳር አንድ አንድ አንበሳ፣ በአጠቃላይ 12 አንበሶች+ ቆመው ነበር። እንዲህ ያለ ዙፋን የሠራ አንድም ሌላ መንግሥት አልነበረም። 20 የንጉሥ ሰለሞን የመጠጫ ዕቃዎች በሙሉ ከወርቅ የተሠሩ ነበሩ፤ የሊባኖስ ደን በተባለው ቤት የነበሩት ዕቃዎችም በሙሉ ከንጹሕ ወርቅ የተሠሩ ነበሩ። ከብር የተሠራ ምንም ነገር አልነበረም፤ በሰለሞን ዘመን ብር እንደ ተራ ነገር ይቆጠር ነበር።+ 21 የኪራም+ አገልጋዮች የሰለሞንን መርከቦች እየነዱ ወደ ተርሴስ+ ይጓዙ ነበር። እነዚህ የተርሴስ መርከቦች በሦስት ዓመት አንድ ጊዜ ወርቅ፣ ብር፣ የዝሆን ጥርስ፣+ ጦጣና ጣዎስ* ጭነው ይመጡ ነበር።
22 በመሆኑም ንጉሥ ሰለሞን በብልጽግናና በጥበብ ምድር ላይ ካሉ ሌሎች ነገሥታት ሁሉ ይበልጥ ነበር።+ 23 የምድር ነገሥታትም ሁሉ እውነተኛው አምላክ በሰለሞን ልብ ውስጥ ያኖረውን ጥበብ ይሰሙ ዘንድ ከእሱ ጋር ለመገናኘት ይጓጉ ነበር።*+ 24 ወደ እሱ የሚመጡትም ሰዎች በየዓመቱ የብር ዕቃዎች፣ የወርቅ ዕቃዎች፣ ልብሶች፣+ የጦር ትጥቆች፣ የበለሳን ዘይት፣ ፈረሶችና በቅሎዎች ስጦታ አድርገው ያመጡ ነበር። 25 ሰለሞንም ለፈረሶቹ የሚሆኑ 4,000 ጋጣዎች፣ ሠረገሎችና 12,000 ፈረሶች* ነበሩት፤+ እነሱንም በሠረገላ ከተሞችና በኢየሩሳሌም በንጉሡ አቅራቢያ አኖራቸው።+ 26 እሱም ከወንዙ* አንስቶ እስከ ፍልስጤማውያን ምድርና እስከ ግብፅ ወሰን ድረስ ባሉት ነገሥታት ሁሉ ላይ ገዛ።+ 27 ንጉሡ በኢየሩሳሌም ያለውን ብር ከብዛቱ የተነሳ በየቦታው እንደሚገኝ ድንጋይ አደረገው፤ የአርዘ ሊባኖሱንም ብዛት በሸፌላ እንደሚገኘው የሾላ ዛፍ አደረገው።+ 28 ደግሞም ለሰለሞን ከግብፅና ከሌሎች አገሮች ሁሉ ፈረሶችን ያመጡለት ነበር።+
29 ከመጀመሪያ አንስቶ እስከ መጨረሻ ድረስ ያለው የቀረው የሰለሞን ታሪክ+ ነቢዩ ናታን+ ባዘጋጀው ጽሑፍ፣ የሴሎ ሰው የሆነው አኪያህ+ በተናገረው ትንቢትና ባለ ራእዩ ኢዶ+ ስለ ናባጥ ልጅ ስለ ኢዮርብዓም+ያየው ራእይ በሰፈረበት ዘገባ ላይ ተጽፎ የለም? 30 ሰለሞን በኢየሩሳሌም ሆኖ በመላው እስራኤል ላይ ለ40 ዓመት ገዛ። 31 በመጨረሻም ሰለሞን ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ። በአባቱም በዳዊት ከተማ+ ቀበሩት፤ በእሱም ምትክ ልጁ ሮብዓም ነገሠ።+
10 እስራኤላውያን በሙሉ ሮብዓምን ለማንገሥ ወደ ሴኬም+ መጥተው ስለነበር እሱም ወደ ሴኬም ሄደ።+ 2 የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም+ ይህን እንደሰማ (ምክንያቱም በወቅቱ ኢዮርብዓም ከንጉሥ ሰለሞን ሸሽቶ በግብፅ ይኖር ነበር)፣+ ከግብፅ ተመልሶ መጣ። 3 ከዚያም ሰዎች ልከው አስጠሩት፤ ኢዮርብዓምና መላው እስራኤልም መጥተው ሮብዓምን እንዲህ አሉት፦ 4 “አባትህ ቀንበራችንን አክብዶብን ነበር።+ አንተ ግን አባትህ የሰጠንን አስቸጋሪ ሥራና በላያችን የጫነብንን ከባድ* ቀንበር የምታቀልልን ከሆነ እናገለግልሃለን።”
5 በዚህ ጊዜ “ከሦስት ቀን በኋላ ተመልሳችሁ ኑ” አላቸው። በመሆኑም ሕዝቡ ሄደ።+ 6 ከዚያም ንጉሥ ሮብዓም አባቱ ሰለሞን በሕይወት በነበረበት ጊዜ ሲያገለግሉት የነበሩትን ሽማግሌዎች “ለዚህ ሕዝብ ምን ምላሽ እንድሰጥ ትመክሩኛላችሁ?” በማለት ምክር ጠየቀ። 7 እነሱም “ለዚህ ሕዝብ ጥሩ ብትሆንና ደስ ብታሰኛቸው እንዲሁም መልካም ምላሽ ብትሰጣቸው ምንጊዜም አገልጋዮችህ ይሆናሉ” በማለት መለሱለት።
8 ሆኖም ሮብዓም ሽማግሌዎቹ የሰጡትን ምክር ትቶ አብሮ አደጎቹ ከነበሩትና አሁን የእሱ አገልጋዮች ከሆኑት ወጣቶች ጋር ተማከረ።+ 9 እሱም እንዲህ ሲል ጠየቃቸው፦ “‘አባትህ የጫነብንን ቀንበር አቅልልልን’ ለሚለኝ ለዚህ ሕዝብ ምን ምላሽ እንድንሰጥ ትመክሩኛላችሁ?” 10 አብሮ አደጎቹ የሆኑት ወጣቶችም እንዲህ አሉት፦ “‘አባትህ ቀንበራችንን አክብዶብን ነበር፤ አንተ ግን ቀንበራችንን አቅልልልን’ ለሚልህ ሕዝብ እንዲህ በለው፦ ‘ትንሿ ጣቴ ከአባቴ ወገብ ትወፍራለች። 11 አባቴ ከባድ ቀንበር ጭኖባችሁ ነበር፤ እኔ ግን ቀንበራችሁን የባሰ አከብደዋለሁ። አባቴ በአለንጋ ገርፏችሁ ነበር፤ እኔ ግን በእሾህ አለንጋ እገርፋችኋለሁ።’”
12 ኢዮርብዓምና መላው ሕዝብ ንጉሡ “በሦስተኛው ቀን ተመልሳችሁ ኑ” ባላቸው መሠረት በሦስተኛው ቀን ወደ ሮብዓም መጡ።+ 13 ይሁንና ንጉሡ መጥፎ ምላሽ ሰጣቸው። በዚህ መንገድ ንጉሥ ሮብዓም ሽማግሌዎቹ የሰጡትን ምክር ሳይቀበል ቀረ። 14 ወጣቶቹ በሰጡት ምክር መሠረት “ቀንበራችሁን አከብደዋለሁ፤ ከቀድሞውም የከፋ አደርገዋለሁ። አባቴ በአለንጋ ገርፏችሁ ነበር፤ እኔ ግን በእሾህ አለንጋ እገርፋችኋለሁ” አላቸው። 15 በመሆኑም ንጉሡ ሕዝቡን ሳይሰማ ቀረ፤ ይህም የሆነው ይሖዋ በሴሎናዊው በአኪያህ+ አማካኝነት ለናባጥ ልጅ ለኢዮርብዓም የተናገረው ቃል ይፈጸም ዘንድ እውነተኛው አምላክ እነዚህ ነገሮች በዚህ መንገድ እንዲከናወኑ ስላደረገ ነው።+
16 እስራኤላውያን ሁሉ ንጉሡ ሊሰማቸው ፈቃደኛ አለመሆኑን ሲያዩ ንጉሡን እንዲህ አሉት፦ “ከዳዊት ምን ድርሻ አለን? ከእሴይ ልጅ ምንም ርስት የለንም። እስራኤል ሆይ፣ እያንዳንድህ ወደ አማልክትህ ተመለስ! ዳዊት ሆይ፣ እንግዲህ የገዛ ቤትህን ጠብቅ!”+ ከዚያም እስራኤላውያን ሁሉ ወደየቤታቸው* ተመለሱ።+
17 ይሁንና ሮብዓም በይሁዳ ከተሞች በሚኖሩት እስራኤላውያን ላይ መግዛቱን ቀጠለ።+
18 ከዚያም ንጉሥ ሮብዓም የግዳጅ ሥራ እንዲሠሩ የተመለመሉት ሰዎች አለቃ የነበረውን ሃዶራምን+ ላከው፤ ሆኖም እስራኤላውያን በድንጋይ ወግረው ገደሉት። ንጉሥ ሮብዓም ግን እንደ ምንም ብሎ ሠረገላው ላይ በመውጣት ወደ ኢየሩሳሌም ሸሸ።+ 19 እስራኤላውያንም እስከዚህ ቀን ድረስ በዳዊት ቤት ላይ እንዳመፁ ናቸው።
11 ሮብዓም ኢየሩሳሌም በደረሰ ጊዜ ከእስራኤል ጋር ተዋግተው መንግሥቱን ለሮብዓም እንዲያስመልሱ ከይሁዳ ቤትና ከቢንያም ነገድ+ የተውጣጡ 180,000 የሠለጠኑ ተዋጊዎች* ወዲያውኑ ሰበሰበ።+ 2 ከዚያም የይሖዋ ቃል የእውነተኛው አምላክ ሰው ወደሆነው ወደ ሸማያህ+ እንዲህ ሲል መጣ፦ 3 “ለይሁዳ ንጉሥ ለሰለሞን ልጅ ለሮብዓም እንዲሁም በይሁዳና በቢንያም ላሉት እስራኤላውያን ሁሉ እንዲህ ብለህ ተናገር፦ 4 ‘ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “ከወንድሞቻችሁ ጋር ለመዋጋት አትውጡ። ይህ እንዲሆን ያደረግኩት እኔ ስለሆንኩ እያንዳንዳችሁ ወደ ቤታችሁ ተመለሱ።”’”+ ስለዚህ የይሖዋን ቃል ሰምተው ተመለሱ፤ በኢዮርብዓምም ላይ አልዘመቱም።
5 ሮብዓም መኖሪያውን በኢየሩሳሌም አድርጎ በይሁዳ የተመሸጉ ከተሞችን ገነባ። 6 ቤተልሔምን፣+ ኤጣምን፣ ተቆአን፣+ 7 ቤትጹርን፣ ሶኮን፣+ አዱላምን፣+ 8 ጌትን፣+ ማሬሻህን፣ ዚፍን፣+ 9 አዶራይምን፣ ለኪሶን፣+ አዜቃን፣+ 10 ጾራን፣ አይሎንንና+ ኬብሮንን+ ገነባ፤* እነዚህ በይሁዳና በቢንያም የነበሩ የተመሸጉ ከተሞች ናቸው። 11 በተጨማሪም የተመሸጉትን ከተሞች አጠናከረ፤ በከተሞቹም ላይ አዛዦችን ሾመ፤ በእነዚህ ከተሞች ምግብ፣ ዘይትና የወይን ጠጅ አከማቸ፤ 12 በከተሞቹም ሁሉ ትላልቅ ጋሻዎችና ጦር አስቀመጠ፤ ከተሞቹንም እጅግ አጠናከራቸው። ይሁዳንና ቢንያምንም መግዛቱን ቀጠለ።
13 በመላው እስራኤል ያሉት ካህናትና ሌዋውያንም የነበሩበትን ክልል በሙሉ ለቀው በመሄድ ከእሱ ጎን ቆሙ። 14 ሌዋውያኑ የይሖዋ ካህናት ሆነው እንዳያገለግሉ ኢዮርብዓምና ልጆቹ አባረዋቸው ስለነበር+ የግጦሽ መሬታቸውንና ርስታቸውን+ ትተው ወደ ይሁዳና ወደ ኢየሩሳሌም መጥተው ነበር። 15 በዚህ ጊዜ ኢዮርብዓም ከፍ ላሉት የማምለኪያ ቦታዎች፣ ፍየል ለሚመስሉት አጋንንትና*+ ለሠራቸው የጥጃ ምስሎች+ የራሱን ካህናት ሾመ።+ 16 የእስራኤልን አምላክ ይሖዋን ለመፈለግ ከልባቸው ቆርጠው የተነሱ ከሁሉም የእስራኤል ነገዶች የተውጣጡ ሰዎች ለአባቶቻቸው አምላክ ለይሖዋ መሥዋዕት ለማቅረብ ካህናቱንና ሌዋውያኑን ተከትለው ወደ ኢየሩሳሌም መጡ።+ 17 ለሦስት ዓመት በዳዊትና በሰለሞን መንገድ ይመላለሱ ስለነበር በእነዚህ ሦስት ዓመታት የይሁዳን መንግሥት አጠናከሩ፤ ደግሞም ለሰለሞን ልጅ ለሮብዓም ድጋፍ ሰጡ።
18 ከዚያም ሮብዓም የዳዊት ልጅ የሆነውን የየሪሞትን ሴት ልጅ ማሃላትን አገባ። ማሃላት የእሴይ ልጅ፣ የኤልያብ+ ሴት ልጅ የሆነችው የአቢሃይል ልጅ ነበረች። 19 ከጊዜ በኋላም የኡሽ፣ ሸማርያህ እና ዛሃም የተባሉ ወንዶች ልጆች ወለደችለት። 20 ከእሷ በኋላ የአቢሴሎም+ የልጅ ልጅ የሆነችውን ማአካን አገባ። እሷም አቢያህን፣+ አታይን፣ ዚዛን እና ሸሎሚትን ወለደችለት። 21 ሮብዓም የአቢሴሎም የልጅ ልጅ የሆነችውን ማአካን ከሌሎቹ ሚስቶቹና ቁባቶቹ ሁሉ+ አስበልጦ ይወዳት ነበር፤ እሱም 18 ሚስቶችና 60 ቁባቶች ነበሩት፤ ደግሞም 28 ወንዶች ልጆችና 60 ሴቶች ልጆች ወለደ። 22 ሮብዓምም የማአካን ልጅ አቢያህን ሊያነግሠው ስለፈለገ በወንድሞቹ ላይ ራስና መሪ አድርጎ ሾመው። 23 ይሁን እንጂ ማስተዋል የታከለበት እርምጃ በመውሰድ ከወንዶች ልጆቹ መካከል አንዳንዶቹን በይሁዳና በቢንያም ምድር ሁሉ ወደሚገኙት ወደተመሸጉት ከተሞች+ ሁሉ ላካቸው፤* የሚያስፈልጓቸውንም ነገሮች በብዛት ሰጣቸው፤ ብዙ ሚስቶችም አጋባቸው።
12 ሮብዓም በበረታና ንግሥናው በጸና ጊዜ+ እሱም ሆነ አብረውት ያሉት እስራኤላውያን ሁሉ የይሖዋን ሕግ ተዉ።+ 2 ለይሖዋ ታማኝ ሳይሆኑ በመቅረታቸው ንጉሥ ሮብዓም በነገሠ በአምስተኛው ዓመት የግብፅ ንጉሥ ሺሻቅ+ በኢየሩሳሌም ላይ ዘመተ። 3 እሱም 1,200 ሠረገሎችና 60,000 ፈረሰኞች አስከትሎ ነበር፤ ከእሱም ጋር ከግብፅ የመጡት ሊቢያውያን፣ ሱኪማውያንና ኢትዮጵያውያን+ ወታደሮች ስፍር ቁጥር አልነበራቸውም። 4 እሱም የይሁዳን የተመሸጉ ከተሞች ያዘ፤ በመጨረሻም ኢየሩሳሌም ደረሰ።
5 ነቢዩ ሸማያህ+ ወደ ሮብዓምና ሺሻቅን ፈርተው በኢየሩሳሌም ወደተሰበሰቡት የይሁዳ መኳንንት መጥቶ እንዲህ አላቸው፦ “ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘እናንተ ትታችሁኛል፤+ ስለዚህ እኔም በሺሻቅ እጅ ትቻችኋለሁ።’” 6 በዚህ ጊዜ የእስራኤል መኳንንትና ንጉሡ ራሳቸውን ዝቅ በማድረግ+ “ይሖዋ ጻድቅ ነው” አሉ። 7 ይሖዋ ራሳቸውን ዝቅ እንዳደረጉ ባየ ጊዜ፣ የይሖዋ ቃል እንዲህ ሲል ወደ ሸማያህ መጣ፦ “ራሳቸውን ዝቅ ስላደረጉ አላጠፋቸውም፤+ በቅርቡም እታደጋቸዋለሁ። ቁጣዬንም በሺሻቅ እጅ በኢየሩሳሌም ላይ አላፈስም። 8 ይሁን እንጂ እኔን በማገልገልና የሌሎች አገሮች ነገሥታትን* በማገልገል መካከል ያለውን ልዩነት እንዲያውቁ የእሱ አገልጋዮች ይሆናሉ።”
9 በመሆኑም የግብፁ ንጉሥ ሺሻቅ ኢየሩሳሌምን ለመውጋት መጣ። እሱም በይሖዋ ቤት የነበሩትን ውድ ንብረቶችና በንጉሡ ቤት* የነበሩትን ውድ ንብረቶች ወሰደ።+ ሰለሞን የሠራቸውን የወርቅ ጋሻዎች ጨምሮ ሁሉንም ነገር ወሰደ።+ 10 በመሆኑም ንጉሥ ሮብዓም በእነሱ ምትክ የመዳብ ጋሻዎችን ሠርቶ የንጉሡን ቤት በር ለሚጠብቁት የዘብ* አለቆች ሰጣቸው። 11 ዘቦቹም ንጉሡ ወደ ይሖዋ ቤት በመጣ ቁጥር ገብተው ጋሻዎቹን ያነግቡ ነበር፤ ከዚያም ወደ ዘቦቹ ክፍል ይመልሷቸው ነበር። 12 ንጉሡ ራሱን ስላዋረደ የይሖዋ ቁጣ ከእሱ ተመለሰ፤+ ሙሉ በሙሉም አላጠፋቸውም።+ በተጨማሪም በይሁዳ አንዳንድ መልካም ነገሮች ተገኝተው ነበር።+
13 ንጉሥ ሮብዓም በኢየሩሳሌም ሥልጣኑን አጠናክሮ መግዛቱን ቀጠለ፤ ሮብዓም በነገሠ ጊዜ ዕድሜው 41 ዓመት ነበር፤ እሱም ይሖዋ ስሙ እንዲኖርባት ከእስራኤል ነገዶች ሁሉ መካከል በመረጣት ከተማ በኢየሩሳሌም ሆኖ 17 ዓመት ገዛ። የንጉሡም እናት ናዕማ የተባለች አሞናዊት ነበረች።+ 14 ሆኖም ይሖዋን ለመፈለግ ከልቡ ቆርጦ ስላልተነሳ ክፉ ነገር አደረገ።+
15 ከመጀመሪያ አንስቶ እስከ መጨረሻ ድረስ ያለው የሮብዓም ታሪክ ነቢዩ ሸማያህና+ ባለ ራእዩ ኢዶ+ በትውልድ ሐረግ መዝገቡ ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ ውስጥ ይገኝ የለም? በሮብዓምና በኢዮርብዓም+ መካከል ምንጊዜም ጦርነት ይካሄድ ነበር። 16 በመጨረሻም ሮብዓም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በዳዊት ከተማም+ ተቀበረ፤ በእሱም ምትክ ልጁ አቢያህ+ ነገሠ።
13 ንጉሥ ኢዮርብዓም በነገሠ በ18ኛው ዓመት አቢያህ በይሁዳ ላይ ነገሠ።+ 2 እሱም በኢየሩሳሌም ለሦስት ዓመት ገዛ። የእናቱ ስም ሚካያህ*+ ነበር፤ እሷም የጊብዓዊው+ የዑሪኤል ልጅ ነበረች። በአቢያህና በኢዮርብዓም መካከልም ጦርነት ነበር።+
3 በመሆኑም አቢያህ 400,000 የሠለጠኑ* ኃያላን ተዋጊዎችን ያቀፈ ሠራዊት ይዞ ዘመተ።+ ኢዮርብዓምም 800,000 የሠለጠኑ* ኃያላን ተዋጊዎችን አስከትሎ እሱን ለመግጠም ተሰለፈ። 4 አቢያህ በኤፍሬም ተራራማ ክልል በሚገኘው በጸማራይም ተራራ ላይ ቆሞ እንዲህ አለ፦ “ኢዮርብዓምና እስራኤላውያን ሁሉ፣ ስሙኝ። 5 የእስራኤል አምላክ ይሖዋ፣ ዳዊትና ልጆቹ+ በእስራኤል ላይ ለዘላለም እንዲነግሡ በጨው ቃል ኪዳን*+ መንግሥት እንደሰጣቸው አታውቁም?+ 6 የዳዊት ልጅ የሰለሞን አገልጋይ የነበረው የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም+ ግን ተነስቶ በጌታው ላይ ዓመፀ።+ 7 ሥራ ፈት የሆኑ የማይረቡ ሰዎችም ወደ እሱ ተሰበሰቡ። የሰለሞን ልጅ ሮብዓም ለጋ ወጣት በነበረበትና ልቡ በቀላሉ ይሸበር በነበረበት ጊዜም በእሱ ላይ በረቱበት፤ ሊቋቋማቸውም አልቻለም።
8 “አሁንም እናንተ እጅግ ብዙ ስለሆናችሁና ኢዮርብዓም አማልክት አድርጎ የሠራላችሁን የወርቅ ጥጃዎች+ ስለያዛችሁ በዳዊት ልጆች እጅ ያለውን የይሖዋን መንግሥት መቋቋም እንደምትችሉ ተሰምቷችኋል። 9 የአሮን ዘሮች የሆኑትን የይሖዋን ካህናትና ሌዋውያንን አላባረራችሁም?+ ደግሞስ እንደ ሌሎቹ አገሮች ሕዝቦች የራሳችሁን ካህናት አልሾማችሁም?+ አንድ ወይፈንና ሰባት አውራ በጎች ይዞ የሚመጣ ማንኛውም ሰው አማልክት ላልሆኑት ጣዖቶች ካህን መሆን ይችላል። 10 እኛ ግን አምላካችን ይሖዋ ነው፤+ እሱንም አልተውነውም፤ የአሮን ዘሮች የሆኑት ካህናት ይሖዋን እያገለገሉ ሲሆን ሌዋውያንም በሥራው ይረዷቸዋል። 11 በየጠዋቱና በየማታው+ ለይሖዋ የሚቃጠል መባ እንዲሁም ጥሩ መዓዛ ያለው ዕጣን+ ያቀርባሉ፤ የሚነባበረውም ዳቦ*+ ከንጹሕ ወርቅ በተሠራው ጠረጴዛ ላይ ይቀመጣል፤ የወርቁን መቅረዝና+ መብራቶቹን በየማታው ያበራሉ፤+ ምክንያቱም እኛ በአምላካችን በይሖዋ ፊት ያለብንን ኃላፊነት እየተወጣን ነው፤ እናንተ ግን እሱን ትታችሁታል። 12 እነሆ፣ እውነተኛው አምላክ ከእኛ ጋር ነው፤ እሱም በእናንተ ላይ ጦርነት መታወጁን የሚያመለክት ድምፅ ለማሰማት መለከት ከያዙ ካህናቱ ጋር ሆኖ እየመራን ነው። የእስራኤል ሰዎች ሆይ፣ ስለማይሳካላችሁ ከአባቶቻችሁ አምላክ ከይሖዋ ጋር አትዋጉ።”+
13 ኢዮርብዓም ግን ከበስተ ጀርባቸው አድፍጠው ጥቃት የሚሰነዝሩ ተዋጊዎችን ላከ፤ ዋናው ሠራዊት ከፊት፣ ያደፈጡትም ተዋጊዎች ከበስተ ጀርባ ይሁዳን እንዲገጥሙ አደረገ። 14 የይሁዳ ሰዎች ዙሪያቸውን ሲመለከቱ ከፊትና ከኋላ መከበባቸውን አዩ። በዚህ ጊዜ ወደ ይሖዋ ጮኹ፤+ ካህናቱም መለከቶቹን በኃይል ነፉ። 15 የይሁዳ ሰዎች ቀረርቶ አሰሙ፤ የይሁዳ ሰዎች ቀረርቶ ባሰሙ ጊዜም እውነተኛው አምላክ ኢዮርብዓምንና እስራኤላውያንን ሁሉ በአቢያህና በይሁዳ ፊት ድል አደረጋቸው። 16 እስራኤላውያን ከይሁዳ ፊት ሸሹ፤ አምላክም በእጃቸው አሳልፎ ሰጣቸው። 17 አቢያህና ሕዝቡም ፈጇቸው፤ ከእስራኤላውያንም መካከል 500,000 የሠለጠኑ ተዋጊዎች* ተገደሉ። 18 በዚህ ጊዜ የእስራኤል ሰዎች ተዋረዱ፤ የይሁዳ ሰዎች ግን በአባቶቻቸው አምላክ በይሖዋ በመታመናቸው* ድል ነሱ።+ 19 አቢያህ ኢዮርብዓምን አሳደደው፤ ከተሞቹን ይኸውም ቤቴልንና+ በሥሯ* ያሉትን ከተሞች፣ የሻናንና በሥሯ ያሉትን ከተሞች እንዲሁም ኤፍራይንንና+ በሥሯ ያሉትን ከተሞች ወሰደበት። 20 ኢዮርብዓምም በአቢያህ ዘመን እንደገና ሊያንሰራራ አልቻለም፤ ከዚያም ይሖዋ ስለቀሰፈው ሞተ።+
21 አቢያህ ግን እየበረታ ሄደ። ከጊዜ በኋላም 14 ሚስቶችን+ አግብቶ 22 ወንዶች ልጆችና 16 ሴቶች ልጆች ወለደ። 22 የቀረው የአቢያህ ታሪክ፣ የሠራውና የተናገረው ነገር ሁሉ በነቢዩ ኢዶ ጽሑፎች* ላይ ሰፍሯል።+
14 በመጨረሻም አቢያህ ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በዳዊት ከተማም+ ቀበሩት፤ በምትኩም ልጁ አሳ ነገሠ። በእሱም ዘመን ምድሪቱ ለአሥር ዓመት አረፈች።
2 አሳ በአምላኩ በይሖዋ ፊት መልካምና ትክክል የሆነውን ነገር አደረገ። 3 የባዕድ አማልክቱን መሠዊያዎችና+ ከፍ ያሉትን የማምለኪያ ቦታዎች አስወገደ፤ የማምለኪያ ዓምዶቹንም ሰባበረ፤+ እንዲሁም የማምለኪያ ግንዶቹን* ቆራረጠ።+ 4 በተጨማሪም የይሁዳ ሰዎች የአባቶቻቸውን አምላክ ይሖዋን እንዲፈልጉ እንዲሁም ሕጉንና ትእዛዙን እንዲያከብሩ አዘዘ። 5 ከይሁዳም ከተሞች ሁሉ ከፍ ያሉትን የማምለኪያ ቦታዎችና የዕጣን ማጨሻዎቹን አስወገደ፤+ መንግሥቱም በእሱ አገዛዝ ሥር ሰላም አገኘ። 6 ምድሪቱ እረፍት አግኝታ ስለነበር በይሁዳ የተመሸጉ ከተሞችን ገነባ፤+ ይሖዋ እረፍት ሰጥቶት ስለነበር በእነዚያ ዓመታት በእሱ ላይ ጦርነት የከፈተ አልነበረም።+ 7 የይሁዳንም ሰዎች እንዲህ አላቸው፦ “እነዚህን ከተሞች እንገንባ፤ በዙሪያቸውም ቅጥርና ማማዎች+ እንዲሁም በሮችና* መቀርቀሪያዎች እንሥራ። አምላካችንን ይሖዋን ስለፈለግነው ምድሪቱ አሁንም በእጃችን ናት። እኛ ፈልገነዋል፤ እሱም በዙሪያችን ካሉት ጠላቶቻችን ሁሉ እረፍት ሰጥቶናል።” በመሆኑም የግንባታ ሥራቸው ስኬታማ ሆነ።+
8 አሳ ትልቅ ጋሻና ጦር የታጠቁ 300,000 የይሁዳ ሰዎችን ያቀፈ ሠራዊት ነበረው። ከቢንያምም ነገድ ትንሽ ጋሻ* የሚያነግቡና ደጋን የሚይዙ* 280,000 ኃያላን ተዋጊዎች ነበሩ።+
9 ከጊዜ በኋላ ኢትዮጵያዊው ዛራ 1,000,000 ሰዎችንና 300 ሠረገሎችን ያቀፈ ሠራዊት አስከትሎ ዘመተባቸው።+ ማሬሻህ+ በደረሰ ጊዜ 10 አሳ ሊገጥመው ወጣ፤ በማሬሻህ በሚገኘው በጸፋታ ሸለቆም ለውጊያ ተሰለፉ። 11 በዚህ ጊዜ አሳ ወደ አምላኩ ወደ ይሖዋ እንዲህ ሲል ጮኸ፦+ “ይሖዋ ሆይ፣ የምትረዳው ሕዝብ ብዛት ያለውም ይሁን ደካማ ለአንተ የሚያመጣው ለውጥ የለም።+ ይሖዋ አምላካችን ሆይ፣ እርዳን፤ በአንተ ታምነናልና፤*+ በስምህ ይህን ታላቅ ሠራዊት ለመግጠም ወጥተናል።+ ይሖዋ ሆይ፣ አንተ አምላካችን ነህ። ሟች የሆነ ሰው በአንተ ላይ አይበርታ።”+
12 በመሆኑም ይሖዋ ኢትዮጵያውያንን በአሳና በይሁዳ ፊት ድል አደረጋቸው፤ ኢትዮጵያውያኑም ሸሹ።+ 13 አሳና ከእሱ ጋር ያለው ሕዝብም እስከ ጌራራ+ ድረስ አሳደዷቸው፤ ኢትዮጵያውያኑም ፈጽመው እስኪጠፉ ድረስ ተመተው ወደቁ፤ በይሖዋና በሠራዊቱ ተደምስሰው ነበርና። በኋላም የይሁዳ ሰዎች እጅግ ብዙ ምርኮ ወሰዱ። 14 በተጨማሪም ይሖዋ በከተሞቹ ላይ ታላቅ ፍርሃት ለቆባቸው ስለነበር በጌራራ ዙሪያ ያሉትን ከተሞች ሁሉ መቱ፤ እነሱም በከተሞቹ ውስጥ ብዙ የሚበዘበዝ ነገር ስለነበር ከተሞቹን ሁሉ በዘበዙ። 15 በተጨማሪም የእረኞችን ድንኳኖች በመምታት እጅግ ብዙ በጎችንና ግመሎችን ማረኩ፤ ከዚያም ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ።
15 የአምላክ መንፈስ በኦዴድ ልጅ በአዛርያስ ላይ ወረደ። 2 እሱም ከአሳ ጋር ለመገናኘት ወጥቶ እንዲህ አለው፦ “አሳ ሆይ፣ ይሁዳና ቢንያም ሁሉ ስሙኝ! እናንተ ከእሱ ጋር እስከሆናችሁ ድረስ ይሖዋ ከእናንተ ጋር ይሆናል፤+ ብትፈልጉት ይገኝላችኋል፤+ ብትተዉት ግን ይተዋችኋል።+ 3 እስራኤል ያለእውነተኛው አምላክ፣ ያለአስተማሪ ካህንና ያለሕግ ብዙ ዘመን* አሳልፏል።+ 4 በተጨነቁ ጊዜ ግን ወደ እስራኤል አምላክ ወደ ይሖዋ ተመልሰው ፈለጉት፤ እሱም ተገኘላቸው።+ 5 በዚያ ዘመን በሰላም መጓዝ የሚችል ሰው አልነበረም፤* ምክንያቱም በየክልሉ በሚኖሩት ሰዎች ሁሉ መካከል ከፍተኛ ሁከት ነበር። 6 አምላክ በተለያየ ችግር ያውካቸው ስለነበር አንዱ ብሔር ሌላውን ብሔር፣ አንዱ ከተማም ሌላውን ከተማ ያደቅ ነበር።+ 7 እናንተ ግን የድካማችሁን ዋጋ ስለምታገኙ በርቱ፤ ተስፋም አትቁረጡ።”*+
8 አሳ ይህን ቃልና ነቢዩ ኦዴድ የተናገረውን ትንቢት ሲሰማ ተበረታታ፤ አስጸያፊ የሆኑትን ጣዖቶችም ከይሁዳና ከቢንያም ምድር ሁሉ እንዲሁም በተራራማው የኤፍሬም ክልል ከያዛቸው ከተሞች አስወገደ፤+ ከይሖዋ ቤት በረንዳ ፊት ለፊት የነበረውን የይሖዋን መሠዊያም አደሰ።+ 9 እሱም ይሁዳንና ቢንያምን ሁሉ እንዲሁም ከኤፍሬም፣ ከምናሴና ከስምዖን መጥተው ከእነሱ ጋር የተቀመጡትን የባዕድ አገር ሰዎች ሰበሰበ፤+ አምላኩ ይሖዋ ከእሱ ጋር እንደሆነ ባዩ ጊዜ በርካታ የባዕድ አገር ሰዎች እስራኤልን ትተው ወደ እሱ መጥተው ነበር። 10 በመሆኑም አሳ በነገሠ በ15ኛው ዓመት፣ በሦስተኛው ወር በኢየሩሳሌም ተሰበሰቡ። 11 በዚያም ቀን፣ ካመጡት ምርኮ ላይ 700 ከብቶችንና 7,000 በጎችን ለይሖዋ መሥዋዕት አድርገው አቀረቡ። 12 በተጨማሪም የአባቶቻቸውን አምላክ ይሖዋን በሙሉ ልባቸውና በሙሉ ነፍሳቸው* ለመፈለግ ቃል ኪዳን ገቡ።+ 13 የእስራኤልን አምላክ ይሖዋን የማይፈልግ ማንኛውም ሰው ትንሽም ሆነ ትልቅ፣ ወንድም ሆነ ሴት እንዲገደል ተስማሙ።+ 14 በታላቅ ድምፅ፣ በእልልታ፣ በመለከትና በቀንደ መለከት ለይሖዋ ማሉ። 15 የይሁዳ ሰዎች ሁሉ በሙሉ ልባቸው ስለማሉ በመሐላው ሐሴት አደረጉ፤ አምላክንም ከልባቸው ፈለጉት፤ እሱም ተገኘላቸው፤+ ይሖዋም በዙሪያቸው ካሉት ጠላቶቻቸው እረፍት ሰጣቸው።+
16 ሌላው ቀርቶ ንጉሥ አሳ አያቱ ማአካ+ ለማምለኪያ ግንዱ* አምልኮ ጸያፍ ጣዖት ሠርታ ስለነበር ከእመቤትነቷ* ሻራት።+ ከዚያም አሳ፣ አያቱ የሠራችውን ጸያፍ ጣዖት ቆርጦ በማድቀቅ በቄድሮን ሸለቆ አቃጠለው።+ 17 ከፍ ያሉት የማምለኪያ ቦታዎች ግን ከእስራኤል አልተወገዱም ነበር።+ ይሁንና አሳ በሕይወት ዘመኑ* ሁሉ በሙሉ ልቡ ተመላልሷል።*+ 18 እሱና አባቱ የቀደሷቸውን ነገሮች ይኸውም ብሩን፣ ወርቁንና ልዩ ልዩ ዕቃዎችን ወደ እውነተኛው አምላክ ቤት አስገባ።+ 19 እስከ 35ኛው የአሳ ዘመነ መንግሥት ድረስ ጦርነት አልነበረም።+
16 አሳ በነገሠ በ36ኛው ዓመት የእስራኤል ንጉሥ ባኦስ+ በይሁዳ ላይ ዘመተ፤ እሱም ማንም ወደ ይሁዳ ንጉሥ ወደ አሳ እንዳይገባና እንዳይወጣ*+ ለማድረግ ራማን+ መገንባት* ጀመረ። 2 በዚህ ጊዜ አሳ ከይሖዋ ቤትና ከንጉሡ ቤት* ግምጃ ቤቶች ብርና ወርቅ አውጥቶ+ በደማስቆ ወደሚገኘው የሶርያ ንጉሥ ወደ ቤንሃዳድ+ እንዲህ ሲል ላከ፦ 3 “በእኔና በአንተ እንዲሁም በአባቴና በአባትህ መካከል ውል* አለ። እኔ ብርና ወርቅ ልኬልሃለሁ። ስለዚህ ና፣ የእስራኤል ንጉሥ ባኦስ ከእኔ እንዲርቅ ከእሱ ጋር የገባኸውን ውል* አፍርስ።”
4 ቤንሃዳድ የንጉሥ አሳን ሐሳብ ተቀብሎ የጦር ሠራዊቱን አለቆች በእስራኤል ከተሞች ላይ አዘመተ፤ እነሱም ኢዮንን፣+ ዳንን፣+ አቤልማይምን እና በንፍታሌም+ ከተሞች ውስጥ ያሉትን የማከማቻ ስፍራዎች ሁሉ መቱ። 5 ባኦስም ይህን ሲሰማ ወዲያውኑ ራማን መገንባቱን* አቆመ፤ ሥራውንም አቋረጠ። 6 ከዚያም ንጉሡ አሳ የይሁዳን ሰዎች ሁሉ ይዞ ሄደ፤ እነሱም ባኦስ እየገነባባቸው የነበሩትን+ የራማን+ ድንጋዮችና ሳንቃዎች አጋዙ፤ እሱም በድንጋዮቹና በሳንቃዎቹ ጌባንና+ ምጽጳን+ ገነባ።*
7 በዚህ ጊዜ ባለ ራእዩ ሃናኒ+ ወደ ይሁዳ ንጉሥ ወደ አሳ መጥቶ እንዲህ አለው፦ “በአምላክህ በይሖዋ ከመታመን* ይልቅ በሶርያ ንጉሥ ስለታመንክ* የሶርያ ንጉሥ ሠራዊት ከእጅህ አምልጧል።+ 8 ኢትዮጵያውያንና ሊቢያውያን ብዙ ሠረገሎችና ፈረሰኞች ያሏቸው ታላቅ ሠራዊት አልነበሩም? ይሁንና በይሖዋ በመታመንህ በእጅህ አሳልፎ ሰጣቸው።+ 9 አዎ፣ በሙሉ ልባቸው ወደ እሱ ላዘነበሉት ሰዎች*+ ብርታቱን ያሳይ ዘንድ* የይሖዋ ዓይኖች በምድር ሁሉ ላይ ይመላለሳሉ።+ በዚህ ረገድ የሞኝነት ድርጊት ፈጽመሃል፤ ከእንግዲህ ወዲያ ጦርነት አይለይህም።”+
10 ሆኖም አሳ በባለ ራእዩ ተቆጣ፤ በዚህ ጉዳይ በጣም ስለተናደደበትም እስር ቤት* አስገባው። በዚያ ወቅት አሳ በሌሎች ሰዎችም ላይ በደል መፈጸም ጀመረ። 11 ከመጀመሪያ አንስቶ እስከ መጨረሻ ድረስ ያለው የአሳ ታሪክ በይሁዳና በእስራኤል ነገሥታት መጽሐፍ ተጽፏል።+
12 አሳ በ39ኛው የግዛት ዘመኑ እግሩን ታመመ፤ ሕመሙም ጠናበት፤ ታሞ ሳለም እንኳ የባለ መድኃኒቶችን እንጂ የይሖዋን እርዳታ አልፈለገም። 13 በመጨረሻም አሳ ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤+ በ41ኛው የግዛት ዘመኑም ሞተ። 14 እነሱም በዳዊት ከተማ+ ለራሱ ባስቆፈረው ታላቅ የመቃብር ቦታ ቀበሩት፤ የበለሳን ዘይት እንዲሁም ከተለያዩ ቅመሞች የተዘጋጀ ልዩ ቅባት በሞላበት ቃሬዛ ላይ አኖሩት።+ በተጨማሪም ለክብሩ ታላቅ እሳት አነደዱለት።*
17 ልጁ ኢዮሳፍጥም+ በምትኩ ነገሠ፤ በእስራኤልም ላይ ሥልጣኑን አጠናከረ። 2 በይሁዳ ባሉት የተመሸጉ ከተሞች ሁሉ የጦር ሠራዊት አሰፈረ፤ በይሁዳ ምድርና አባቱ አሳ በያዛቸው በኤፍሬም ከተሞችም የጦር ሰፈሮች አቋቋመ።+ 3 ኢዮሳፍጥ፣ በቀድሞዎቹ ዘመናት አባቱ ዳዊት የሄደበትን መንገድ በመከተሉና+ ባአልን ባለመፈለጉ ይሖዋ ከእሱ ጋር ነበር። 4 የእስራኤልን ልማድ ከመከተል ይልቅ+ የአባቱን አምላክ ፈልጓል፤+ ትእዛዙንም ተከትሏል።* 5 ይሖዋ መንግሥቱን በእጁ አጸናለት፤+ የይሁዳም ሰዎች ሁሉ ለኢዮሳፍጥ ስጦታ ያመጡለት ነበር፤ እሱም ብዙ ሀብትና ታላቅ ክብር አገኘ።+ 6 ልቡም የይሖዋን መንገዶች በድፍረት ተከተለ፤ ደግሞም ከፍ ያሉትን የማምለኪያ ቦታዎችና የማምለኪያ ግንዶቹን* ከይሁዳ አስወገደ።+
7 በነገሠ በሦስተኛው ዓመት በይሁዳ ከተሞች እንዲያስተምሩ መኳንንቱን ይኸውም ቤንሃይልን፣ አብድዩን፣ ዘካርያስን፣ ናትናኤልንና ሚካያህን አስጠራቸው። 8 ከእነሱ ጋር ሌዋውያኑ ሸማያህ፣ ነታንያህ፣ ዘባድያህ፣ አሳሄል፣ ሸሚራሞት፣ የሆናታን፣ አዶንያስ፣ ጦቢያህ እና ቶብአዶኒያህ ይገኙ ነበር፤ ካህናቱ ኤሊሻማ እና ኢዮራምም አብረዋቸው ነበሩ።+ 9 እነሱም በይሁዳ ማስተማር ጀመሩ፤ የይሖዋን ሕግ መጽሐፍም ይዘው ነበር፤+ በይሁዳ ከተሞች ሁሉ እየተዘዋወሩ ሕዝቡን ያስተምሩ ነበር።
10 ይሖዋም በይሁዳ ዙሪያ በሚገኙ አገሮች ባሉት መንግሥታት ሁሉ ላይ ፍርሃት ለቆባቸው ስለነበር ከኢዮሳፍጥ ጋር አልተዋጉም። 11 ፍልስጤማውያንም ለኢዮሳፍጥ ስጦታ አመጡለት፤ ገንዘብም ገበሩለት። ዓረቦች ከመንጎቻቸው መካከል 7,700 አውራ በጎችንና 7,700 አውራ ፍየሎችን አመጡለት።
12 ኢዮሳፍጥ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያየለ ሄደ፤+ በይሁዳም ምሽጎችንና+ የማከማቻ ከተሞችን+ መገንባቱን ተያያዘው። 13 በይሁዳ ከተሞች መጠነ ሰፊ የሆነ ሥራ አከናወነ፤ በኢየሩሳሌምም ኃያላን ተዋጊዎች የሆኑ ወታደሮች ነበሩት። 14 እነዚህ ሰዎች በየአባቶቻቸው ቤት ተመድበው ነበር፦ ከይሁዳ የሺህ አለቆች መካከል አለቃው አድናህ የነበረ ሲሆን ከእሱ ጋር 300,000 ኃያላን ተዋጊዎች ነበሩ።+ 15 ከእሱ ሥር ደግሞ የሆሃናን የተባለ አለቃ የነበረ ሲሆን ከእሱም ጋር 280,000 ሰዎች ነበሩ። 16 ደግሞም ከእሱ ሥር ለይሖዋ አገልግሎት ራሱን በፈቃደኝነት ያቀረበው የዚክሪ ልጅ አማስያህ የነበረ ሲሆን ከእሱም ጋር 200,000 ኃያላን ተዋጊዎች ነበሩ። 17 ከቢንያምም+ ወገን ኃያል ተዋጊ የሆነው ኤሊያዳ የነበረ ሲሆን ከእሱም ጋር ቀስትና ጋሻ የታጠቁ 200,000 ሰዎች ነበሩ።+ 18 ከእሱም ሥር የሆዛባድ የነበረ ሲሆን ከእሱም ጋር ለውጊያ የታጠቁ 180,000 ሰዎች ነበሩ። 19 እነዚህ ንጉሡ በመላው ይሁዳ በተመሸጉ ከተሞች+ ውስጥ ካስቀመጣቸው ሌላ ንጉሡን ያገለግሉ የነበሩ ሰዎች ናቸው።
18 ኢዮሳፍጥ ብዙ ሀብትና ታላቅ ክብር አገኘ፤+ ይሁንና ከአክዓብ+ ጋር በጋብቻ ተዛመደ። 2 ከተወሰኑ ዓመታት በኋላም በሰማርያ ወደሚገኘው ወደ አክዓብ ወረደ፤+ አክዓብም ለኢዮሳፍጥና አብረውት ለነበሩት ሰዎች እጅግ ብዙ በግና ከብት መሥዋዕት አደረገ። ደግሞም በራሞትጊልያድ+ ላይ እንዲዘምት ገፋፋው።* 3 ከዚያም የእስራኤል ንጉሥ አክዓብ የይሁዳን ንጉሥ ኢዮሳፍጥን “ወደ ራሞትጊልያድ ከእኔ ጋር አብረህ ትሄዳለህ?” አለው። እሱም “እኔ ማለት እኮ አንተ ማለት ነህ፤ ሕዝቤም ሕዝብህ ነው፤ በጦርነቱም አብረንህ እንሰለፋለን” አለው።
4 ሆኖም ኢዮሳፍጥ የእስራኤልን ንጉሥ “እባክህ፣ በመጀመሪያ ይሖዋ ምን እንደሚል ጠይቅ” አለው።+ 5 በመሆኑም የእስራኤል ንጉሥ 400 የሚሆኑ ነቢያትን አንድ ላይ ሰብስቦ “ራሞትጊልያድን ለመውጋት ልዝመት ወይስ ይቅርብኝ?” አላቸው። እነሱም “ዝመት፤ እውነተኛው አምላክ በንጉሡ እጅ አሳልፎ ይሰጣታል” አሉት።
6 ከዚያም ኢዮሳፍጥ “በዚህ ቦታ የይሖዋ ነቢይ የለም?+ ካለ በእሱም አማካኝነት እንጠይቅ” አለ።+ 7 በዚህ ጊዜ የእስራኤል ንጉሥ ኢዮሳፍጥን “በእሱ አማካኝነት ይሖዋን ልንጠይቅ የምንችልበት አንድ ሰው ይቀራል፤+ ሆኖም ሁልጊዜ ስለ እኔ መጥፎ ነገር እንጂ መልካም ነገር ፈጽሞ ስለማይተነብይ በጣም እጠላዋለሁ።+ እሱም የይምላ ልጅ ሚካያህ ነው” አለው። ኢዮሳፍጥ ግን “ንጉሡ እንዲህ ሊል አይገባም” አለ።
8 ስለሆነም የእስራኤል ንጉሥ አንድ የቤተ መንግሥት ባለሥልጣን ጠርቶ “የይምላን ልጅ ሚካያህን በአስቸኳይ ይዘኸው ና” አለው።+ 9 በዚህ ጊዜ የእስራኤል ንጉሥና የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሳፍጥ የንግሥና ልብሳቸውን ለብሰው በየዙፋናቸው ተቀምጠው ነበር፤ የተቀመጡትም በሰማርያ መግቢያ በር በሚገኘው አውድማ ላይ ሲሆን ነቢያቱ ሁሉ በፊታቸው ትንቢት ይናገሩ ነበር። 10 ከዚያም የኬናአና ልጅ ሴዴቅያስ የብረት ቀንዶች ሠርቶ “ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘ሶርያውያንን እስክታጠፋቸው ድረስ በእነዚህ ትወጋቸዋለህ’”* አለ። 11 ሌሎቹ ነቢያትም ሁሉ “ወደ ራሞትጊልያድ ውጣ፤ ይሳካልሃል፤+ ይሖዋም እሷን በንጉሡ እጅ አሳልፎ ይሰጣታል” በማለት ተመሳሳይ ትንቢት ይናገሩ ነበር።
12 ሚካያህን ለመጥራት የሄደው መልእክተኛም “እነሆ፣ ነቢያቱ ሁሉ በአንድ ድምፅ ለንጉሡ የተናገሩት ነገር ጥሩ ነው። እባክህ፣ የአንተም ቃል እንደ እነሱ ይሁን፤+ አንተም ጥሩ ነገር ተናገር” አለው።+ 13 ሚካያህ ግን “ሕያው በሆነው በይሖዋ እምላለሁ፤ የምናገረው አምላኬ የሚለውን ብቻ ነው” አለ።+ 14 ከዚያም ወደ ንጉሡ ገባ፤ ንጉሡም “ሚካያህ፣ ራሞትጊልያድን ለመውጋት እንዝመት ወይስ ይቅርብኝ?” ሲል ጠየቀው። እሱም ወዲያውኑ “ውጡ፤ ይቀናችኋል፤ በእጃችሁም አልፈው ይሰጣሉ” በማለት መለሰለት። 15 በዚህ ጊዜ ንጉሡ “በይሖዋ ስም ከእውነት በስተቀር ሌላ አንዳች ነገር እንዳትነግረኝ የማስምልህ ስንት ጊዜ ነው?” አለው። 16 በመሆኑም ሚካያህ እንዲህ በማለት ተናገረ፦ “እስራኤላውያን ሁሉ እረኛ እንደሌላቸው በጎች በተራሮች ላይ ተበታትነው አያለሁ።+ ይሖዋም ‘እነዚህ ጌታ የላቸውም። እያንዳንዳቸው በሰላም ወደየቤታቸው ይመለሱ’ ብሏል።”
17 ከዚያም የእስራኤል ንጉሥ ኢዮሳፍጥን “‘ስለ እኔ መጥፎ ነገር ብቻ እንጂ ጥሩ ነገር አይተነብይም’ ብዬህ አልነበረም?” አለው።+
18 በዚህ ጊዜ ሚካያህ እንዲህ አለ፦ “እንግዲህ የይሖዋን ቃል ስሙ፦ ይሖዋ በዙፋኑ ላይ ተቀምጦ፣+ የሰማያት ሠራዊትም+ ሁሉ በቀኙና በግራው ቆመው አየሁ።+ 19 ከዚያም ይሖዋ ‘በራሞትጊልያድ ላይ ዘምቶ እዚያው እንዲሞት የእስራኤልን ንጉሥ አክዓብን ማን ያሞኘዋል?’ አለ። በዚህ ጊዜ አንዱ አንድ ነገር፣ ሌላው ደግሞ ሌላ ነገር ተናገረ። 20 ከዚያም አንድ መንፈስ*+ ወደ ፊት ወጥቶ ይሖዋ ፊት በመቆም ‘እኔ አሞኘዋለሁ’ አለ። ይሖዋም ‘እንዴት አድርገህ?’ አለው። 21 ‘እኔ እወጣና በነቢያቱ ሁሉ አፍ ላይ አሳሳች መንፈስ እሆናለሁ’ አለ። እሱም ‘እንግዲያው ታሞኘዋለህ፤ ደግሞም ይሳካልሃል። ውጣና እንዳልከው አድርግ’ አለው። 22 ይሖዋም በእነዚህ ነቢያትህ አፍ ላይ አሳሳች መንፈስ አኑሯል፤+ ሆኖም ይሖዋ ጥፋት እንደሚመጣብህ ተናግሯል።”
23 የኬናአና ልጅ ሴዴቅያስም+ ወደ ሚካያህ+ ቀርቦ በጥፊ መታውና+ “ለመሆኑ የይሖዋ መንፈስ እኔን በየት በኩል አልፎ ነው አንተን ያናገረህ?” አለው።+ 24 ሚካያህም “በየት በኩል እንዳለፈማ፣ ለመደበቅ ወደ ውስጠኛው ክፍል በምትገባበት ቀን ታውቀዋለህ” አለው። 25 ከዚያም የእስራኤል ንጉሥ እንዲህ አለ፦ “ሚካያህን ወስዳችሁ ለከተማው አለቃ ለአምዖን እና የንጉሡ ልጅ ለሆነው ለዮአስ አስረክቡት። 26 እንዲህም በሏቸው፦ ‘ንጉሡ “በሰላም ተመልሼ እስክመጣ ድረስ ይህን ሰው እስር ቤት አቆዩት፤+ ጥቂት ምግብና ውኃ ብቻ ስጡት” ብሏል።’” 27 ሚካያህ ግን “እውነት አንተ በሰላም ከተመለስክ ይሖዋ በእኔ አልተናገረም ማለት ነው!” አለ።+ ከዚያም “እናንተ ሰዎች፣ ሁላችሁም ልብ በሉ” አለ።
28 በመሆኑም የእስራኤል ንጉሥና የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሳፍጥ ወደ ራሞትጊልያድ+ ወጡ። 29 የእስራኤልም ንጉሥ ኢዮሳፍጥን “እኔ ማንነቴ እንዳይታወቅ ራሴን ለውጬ ወደ ውጊያው እገባለሁ፤ አንተ ግን ንጉሣዊ ልብስህን ልበስ” አለው። ስለዚህ የእስራኤል ንጉሥ ማንነቱ እንዳይታወቅ ራሱን ለወጠ፤ ከዚያም ወደ ውጊያው ገቡ። 30 በዚህ ጊዜ የሶርያ ንጉሥ የሠረገሎቹን አዛዦች “ከእስራኤል ንጉሥ በስተቀር ከትንሹም ሆነ ከትልቁ፣ ከማንም ጋር እንዳትዋጉ” በማለት አዟቸው ነበር። 31 የሠረገሎቹ አዛዦችም ኢዮሳፍጥን ባዩት ጊዜ “ይህ የእስራኤል ንጉሥ ነው” ብለው አሰቡ። በመሆኑም ሊወጉት ወደ እሱ ዞሩ፤ በዚህ ጊዜ ኢዮሳፍጥ እርዳታ ለማግኘት ጮኸ፤+ ይሖዋም ረዳው፤ አምላክም ወዲያውኑ ከእሱ እንዲርቁ አደረገ። 32 የሠረገሎቹ አዛዦችም የእስራኤል ንጉሥ አለመሆኑን ሲያዩ ወዲያውኑ እሱን ማሳደዳቸውን ትተው ተመለሱ።
33 ይሁንና አንድ ሰው በነሲብ* ቀስቱን ሲያስወነጭፍ የእስራኤልን ንጉሥ የጥሩሩ መጋጠሚያ ላይ ወጋው። ስለሆነም ንጉሡ ሠረገላ ነጂውን “ክፉኛ ስለቆሰልኩ ሠረገላውን አዙረህ ከጦርነቱ* ይዘኸኝ ውጣ” አለው።+ 34 ያን ቀን ሙሉ የተፋፋመ ውጊያ ተካሄደ፤ የእስራኤልንም ንጉሥ ሠረገላው ውስጥ እንዳለ ፊቱን ወደ ሶርያውያን አዙረው እስከ ምሽት ድረስ ደግፈው አቆሙት፤ ፀሐይ ስትጠልቅም ሞተ።+
19 ከዚያም የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሳፍጥ በኢየሩሳሌም ወደሚገኘው ቤቱ* በደህና ተመለሰ።+ 2 ባለ ራእዩ የሃናኒ+ ልጅ ኢዩ+ ከንጉሥ ኢዮሳፍጥ ጋር ለመገናኘት ሄደ፤ እንዲህም አለው፦ “ለክፉ ሰው እርዳታ መስጠት ይገባሃል?+ ይሖዋን የሚጠሉትንስ መውደድ ይገባሃል?+ በዚህ ምክንያት ይሖዋ በአንተ ላይ ተቆጥቷል። 3 ይሁንና የማምለኪያ ግንዶቹን* ከምድሪቱ ስላስወገድክና እውነተኛውን አምላክ ለመፈለግ ልብህን ስላዘጋጀህ*+ መልካም ነገር ተገኝቶብሃል።”+
4 ኢዮሳፍጥ በኢየሩሳሌም መኖሩን ቀጠለ፤ ወደ አባቶቻቸው አምላክ ወደ ይሖዋ ይመልሳቸውም ዘንድ ከቤርሳቤህ አንስቶ እስከ ተራራማው የኤፍሬም ምድር+ ድረስ ወዳለው ሕዝብ ዳግመኛ ወጣ።+ 5 በተጨማሪም በመላ ምድሪቱ ይኸውም በተመሸጉት የይሁዳ ከተሞች ሁሉ ላይ፣ በእያንዳንዱ ከተማ ፈራጆችን መደበ።+ 6 ፈራጆቹንም እንዲህ አላቸው፦ “የምትፈርዱት ለሰው ሳይሆን ለይሖዋ ስለሆነ የምታደርጉትን ነገር በጥንቃቄ አከናውኑ፤ እሱም በምትፈርዱበት ጊዜ ከእናንተ ጋር ነው።+ 7 አሁንም ይሖዋን መፍራት በእናንተ ላይ ይሁን።+ በአምላካችን በይሖዋ ዘንድ ፍትሕ ማዛባት፣+ አድልዎ+ ወይም ጉቦ መቀበል+ ስለሌለ የምታደርጉትን ነገር በጥንቃቄ አከናውኑ።”
8 ኢዮሳፍጥ በኢየሩሳሌምም የተወሰኑ ሌዋውያንንና ካህናትን እንዲሁም ከእስራኤል የአባቶች ቤት መሪዎች መካከል አንዳንዶቹን ፈራጆች ሆነው ይሖዋን እንዲያገለግሉና የኢየሩሳሌምን ነዋሪዎች ሙግት እንዲቋጩ መደበ።+ 9 እንዲህም ሲል አዘዛቸው፦ “ይሖዋን በመፍራት በታማኝነትና በሙሉ ልብ* ይህን ልታደርጉ ይገባል፦ 10 በየከተሞቻቸው የሚኖሩት ወንድሞቻችሁ ከደም መፋሰስ ጋር የተያያዘ ክስ+ አሊያም ከሕግ፣ ከትእዛዝ፣ ከሥርዓት ወይም ከድንጋጌዎች ጋር የተያያዘ ጥያቄ ይዘው በሚመጡበት ጊዜ ሁሉ በይሖዋ ፊት በደለኛ እንዳይሆኑ ልታስጠነቅቋቸው ይገባል፤ ይህ ካልሆነ ግን በእናንተም ሆነ በወንድሞቻችሁ ላይ ቁጣው ይመጣል። በደለኛ እንዳትሆኑ ይህን ልታደርጉ ይገባል። 11 እነሆ፣ የይሖዋ በሆነው ነገር ሁሉ ላይ በእናንተ ላይ የተሾመው የካህናቱ አለቃ አማርያህ አለ።+ የእስማኤል ልጅ ዘባድያህ ከንጉሡ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ሁሉ የይሁዳ ቤት መሪ ነው። ሌዋውያኑ ደግሞ አለቆች ሆነው ያገለግሏችኋል። በርቱ፤ ሥራችሁንም በትጋት አከናውኑ፤ ይሖዋም መልካም የሆነውን ነገር ከሚያደርጉት* ጋር ይሁን።”+
20 ከጊዜ በኋላ ሞዓባውያንና+ አሞናውያን+ ከተወሰኑ የአሞኒም ሰዎች* ጋር ሆነው ከኢዮሳፍጥ ጋር ለመዋጋት መጡ። 2 በመሆኑም ኢዮሳፍጥ እንዲህ የሚል ወሬ ሰማ፦ “በባሕሩ* አካባቢ ካለው ክልል፣ ከኤዶም+ ታላቅ ሠራዊት አንተን ሊወጋ መጥቷል፤ ሠራዊቱም በሃጻጾንታማር ማለትም በኤንገዲ+ ይገኛል።” 3 ኢዮሳፍጥ ይህን ሲሰማ ፈራ፤ ይሖዋንም ለመፈለግ ቆርጦ ተነሳ።*+ በመሆኑም በመላው ይሁዳ ጾም አወጀ። 4 ከዚያም የይሁዳ ሰዎች ይሖዋን ለመጠየቅ ተሰበሰቡ፤+ የይሖዋን መመሪያ ለማግኘት ከይሁዳ ከተሞች ሁሉ መጡ።
5 ከዚያም ኢዮሳፍጥ በይሖዋ ቤት ከአዲሱ ግቢ ፊት ለፊት በይሁዳና በኢየሩሳሌም ጉባኤ መካከል ቆመ፤ 6 እንዲህም አለ፦
“የአባቶቻችን አምላክ ይሖዋ ሆይ፣ አንተ በሰማያት ያለህ አምላክ አይደለህም?+ የብሔራትን መንግሥታት ሁሉ የምትገዛ አንተ አይደለህም?+ ኃይልና ብርታት በእጅህ ነው፤ አንተን ሊቋቋም የሚችል ማንም የለም።+ 7 አምላካችን ሆይ፣ የዚህችን ምድር ነዋሪዎች ከሕዝብህ ከእስራኤል ፊት አሳደህ ምድሪቱን ለወዳጅህ ለአብርሃም ዘሮች ለዘለቄታው ርስት አድርገህ የሰጠኸው አንተ አይደለህም?+ 8 እነሱም በምድሪቱ መኖር ጀመሩ፤ በዚያም ለስምህ መቅደስ ሠሩ፤+ እንዲህም አሉ፦ 9 ‘ሰይፍ፣ የቅጣት ፍርድ፣ ቸነፈር ወይም ረሃብ በእኛ ላይ ጥፋት ቢያደርስብን በዚህ ቤትና በአንተ ፊት እንቆማለን (ይህን ቤት ለስምህ መርጠኸዋልና)፤+ ከጭንቀታችንም እንድትገላግለን ወደ አንተ እንጮኻለን፤ አንተም ሰምተህ አድነን።’+ 10 አሁንም የአሞንና የሞዓብ ሰዎች እንዲሁም በሴይር ተራራማ ክልል+ የሚኖሩ ሰዎች የሚያደርጉትን ተመልከት። እስራኤላውያን ከግብፅ ምድር በወጡበት ጊዜ እነሱን እንዲወሩ አልፈቀድክም ነበር። እነሱም አልነኳቸውም፤ ደግሞም አላጠፏቸውም።+ 11 እነሱ ግን ርስት አድርገህ ካወረስከን ምድር እኛን በማባረር ብድራት ሊመልሱልን መጥተዋል።+ 12 አምላካችን ሆይ፣ በእነሱ ላይ አትፈርድባቸውም?+ እኛ የመጣብንን ይህን ታላቅ ሠራዊት ለመቋቋም የሚያስችል ኃይል የለንም፤ ምን ማድረግ እንዳለብንም አናውቅም፤+ ነገር ግን ዓይኖቻችን ወደ አንተ ይመለከታሉ።”+
13 በዚህ ጊዜ የይሁዳ ሰዎች በሙሉ ከሕፃኖቻቸው፣ ከሚስቶቻቸውና ከልጆቻቸው* ጋር በይሖዋ ፊት ቆመው ነበር።
14 ከዚያም በጉባኤው መካከል የይሖዋ መንፈስ ከአሳፍ ልጆች ወገን በሆነው በሌዋዊው በማታንያህ ልጅ፣ በየኢዔል ልጅ፣ በበናያህ ልጅ፣ በዘካርያስ ልጅ በያሃዚኤል ላይ መጣ። 15 እሱም እንዲህ አለ፦ “የይሁዳ ሰዎች ሁሉ፣ እናንተም የኢየሩሳሌም ነዋሪዎችና ንጉሥ ኢዮሳፍጥ፣ አዳምጡ! ይሖዋ እንዲህ ይላችኋል፦ ‘ከዚህ ታላቅ ሠራዊት የተነሳ አትፍሩ፤ አትሸበሩ፤ ውጊያው የአምላክ እንጂ የእናንተ አይደለምና።+ 16 ነገ በእነሱ ላይ ውረዱ። እነሱ በጺጽ መተላለፊያ ሽቅብ ይወጣሉ፤ እናንተም የሩኤል ምድረ በዳ ከመድረሳችሁ በፊት በሸለቆው መጨረሻ* ላይ ታገኟቸዋላችሁ። 17 እናንተ ይህን ጦርነት መዋጋት አያስፈልጋችሁም። ቦታ ቦታችሁን ይዛችሁ ዝም ብላችሁ ቁሙ፤+ ይሖዋ ለእናንተ ሲል የሚወስደውን የማዳን እርምጃ ተመልከቱ።*+ ይሁዳና ኢየሩሳሌም ሆይ፣ አትፍሩ ወይም አትሸበሩ።+ ነገ በእነሱ ላይ ውጡ፤ ይሖዋም ከእናንተ ጋር ይሆናል።’”+
18 ኢዮሳፍጥ ወዲያውኑ በግንባሩ ወደ መሬት ተደፋ፤ የይሁዳ ሰዎች ሁሉና የኢየሩሳሌም ነዋሪዎችም በይሖዋ ፊት ተደፍተው ይሖዋን አመለኩ። 19 ከዚያም የቀአታውያንና+ የቆሬያውያን ዘሮች የሆኑት ሌዋውያን የእስራኤልን አምላክ ይሖዋን እጅግ ከፍ ባለ ድምፅ ለማወደስ ተነሱ።+
20 በማግስቱም በማለዳ ተነስተው በተቆአ+ ወደሚገኘው ምድረ በዳ ሄዱ። እየሄዱ ሳሉ ኢዮሳፍጥ ቆሞ እንዲህ አለ፦ “ይሁዳና የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ሆይ፣ ስሙኝ! ጸንታችሁ መቆም እንድትችሉ በአምላካችሁ በይሖዋ እመኑ። በነቢያቱም እመኑ፤+ እንዲህ ካደረጋችሁ ይሳካላችኋል።”
21 ከሕዝቡ ጋር ከተማከረ በኋላም ከታጠቁት ሰዎች ፊት ፊት እየሄዱ “ለይሖዋ ምስጋና አቅርቡ፤ ታማኝ ፍቅሩ ለዘላለም ጸንቶ ይኖራልና”+ እያሉ ለይሖዋ የሚዘምሩ እንዲሁም ያጌጠ የቅድስና ልብስ ለብሰው ውዳሴ የሚያቀርቡ ሰዎችን መደበ።+
22 በደስታ የውዳሴ መዝሙር መዘመር በጀመሩ ጊዜ ይሖዋ ይሁዳን በወረሩት በአሞን፣ በሞዓብና በሴይር ተራራማ ክልል በሚኖሩት ሰዎች ላይ ድንገተኛ ጥቃት ሰነዘረባቸው፤ እነሱም እርስ በርስ ተፋጁ።+ 23 አሞናውያኑና ሞዓባውያኑ በሴይር ተራራማ ክልል+ በሚኖሩት ሰዎች ላይ ተነስተው አጠፏቸው፤ ደመሰሷቸውም፤ የሴይርን ነዋሪዎች ካጠፉም በኋላ እርስ በርስ ተላለቁ።+
24 የይሁዳ ሰዎች በምድረ በዳ+ ወዳለው መጠበቂያ ግንብ መጥተው ሠራዊቱን ሲመለከቱ መሬቱ ሬሳ በሬሳ ሆኖ አዩ፤+ በሕይወት የተረፈ አንድም ሰው አልነበረም። 25 በመሆኑም ኢዮሳፍጥና ሕዝቡ ከእነሱ ላይ ምርኮ ለመውሰድ መጡ፤ በእነሱም መካከል እጅግ ብዙ ዕቃ፣ ልብስና ውድ ነገሮች አገኙ፤ መሸከም እስኪያቅታቸው ድረስ ብዙ ነገር ገፈፏቸው።+ ከብዛቱ የተነሳ ለሦስት ቀን ያህል ምርኮ ሲሰበስቡ ቆዩ። 26 በአራተኛውም ቀን በቤራካ ሸለቆ* ተሰበሰቡ፤ በዚያም ይሖዋን አወደሱ።* ይህን ስፍራ እስከ ዛሬ ድረስ የቤራካ* ሸለቆ ብለው የሚጠሩት ከዚህ የተነሳ ነው።+
27 ከዚያም የይሁዳና የኢየሩሳሌም ሰዎች ሁሉ ይሖዋ በጠላቶቻቸው ላይ ድል ስላቀዳጃቸው በኢዮሳፍጥ እየተመሩ በታላቅ ደስታ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ።+ 28 በባለ አውታር መሣሪያዎች፣ በበገናና+ በመለከት+ ድምፅ ታጅበው ወደ ኢየሩሳሌም መጡ፤ ከዚያም ወደ ይሖዋ ቤት ሄዱ።+ 29 ይሖዋ የእስራኤልን ጠላቶች እንደተዋጋ በሰሙ ጊዜ በምድሪቱ ያሉ መንግሥታት ሁሉ አምላክን ፈሩ።+ 30 በመሆኑም የኢዮሳፍጥ መንግሥት ከሁከት ነፃ ሆነ፤ አምላኩም በዙሪያው ካሉት ጠላቶቹ ሁሉ እረፍት ሰጠው።+
31 ኢዮሳፍጥም በይሁዳ መግዛቱን ቀጠለ። በነገሠ ጊዜ ዕድሜው 35 ዓመት የነበረ ሲሆን በኢየሩሳሌም 25 ዓመት ገዛ። እናቱ የሺልሂ ልጅ አዙባ ነበረች።+ 32 እሱም በአባቱ በአሳ መንገድ ሄደ።+ ከዚያ ፈቀቅ አላለም፤ በይሖዋም ፊት ትክክል የሆነውን ነገር አደረገ።+ 33 ይሁን እንጂ ከፍ ያሉት የማምለኪያ ቦታዎች አልተወገዱም ነበር፤+ ሕዝቡም ልቡን ለአባቶቹ አምላክ ገና አላዘጋጀም ነበር።+
34 ከመጀመሪያ አንስቶ እስከ መጨረሻ ድረስ ያለው የቀረው የኢዮሳፍጥ ታሪክ የሃናኒ+ ልጅ ኢዩ+ በጻፈው ዘገባ ላይ ሰፍሯል፤ ይህም በእስራኤል ነገሥታት መጽሐፍ ውስጥ ተካቷል። 35 ከዚህ በኋላ የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሳፍጥ፣ ክፉ ድርጊት ከፈጸመው ከእስራኤል ንጉሥ ከአካዝያስ ጋር ግንባር ፈጠረ።+ 36 ወደ ተርሴስ+ የሚሄዱ መርከቦችን ለመሥራትም ተሻረኩ፤ መርከቦቹንም በዔጽዮንጋብር+ ሠሩ። 37 ይሁን እንጂ የማሬሻ ሰው የሆነው የዶዳዋ ልጅ ኤሊዔዘር “ከአካዝያስ ጋር ግንባር በመፍጠርህ ይሖዋ ሥራህን ያፈርሰዋል” ሲል በኢዮሳፍጥ ላይ ትንቢት ተናገረ።+ በመሆኑም መርከቦቹ ተሰባበሩ፤+ ወደ ተርሴስም መሄድ ሳይችሉ ቀሩ።
21 በመጨረሻም ኢዮሳፍጥ ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በዳዊት ከተማም ከአባቶቹ ጋር ተቀበረ፤ በእሱም ምትክ ልጁ ኢዮራም ነገሠ።+ 2 የኢዮሳፍጥ ልጆች የሆኑት ወንድሞቹ አዛርያስ፣ የሂኤል፣ ዘካርያስ፣ አዛርያስ፣ ሚካኤል እና ሰፋጥያህ ነበሩ፤ እነዚህ ሁሉ የእስራኤል ንጉሥ የኢዮሳፍጥ ወንዶች ልጆች ናቸው። 3 አባታቸውም ብዙ ብር፣ ወርቅና ውድ የሆኑ ነገሮች ስጦታ አድርጎ የሰጣቸው ከመሆኑም በላይ በይሁዳ የተመሸጉ ከተሞችን ሰጣቸው፤+ መንግሥቱን ግን የበኩር ልጁ ለነበረው ለኢዮራም+ ሰጠው።
4 ኢዮራም በአባቱ መንግሥት ላይ ተደላድሎ በተቀመጠ ጊዜ ወንድሞቹን በሙሉ እንዲሁም ከእስራኤል መኳንንት መካከል የተወሰኑትን በሰይፍ በመግደል ሥልጣኑን አጠናከረ።+ 5 ኢዮራም በነገሠ ጊዜ ዕድሜው 32 ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌምም ሆኖ ስምንት ዓመት ገዛ።+ 6 የአክዓብን ልጅ አግብቶ+ ስለነበር ከአክዓብ ቤት የሆኑት እንዳደረጉት ሁሉ እሱም በእስራኤል ነገሥታት መንገድ ሄደ፤+ በይሖዋም ፊት መጥፎ የሆነውን ነገር አደረገ። 7 ሆኖም ይሖዋ ከዳዊት ጋር ለገባው ቃል ኪዳን ሲል የዳዊትን ቤት ማጥፋት አልፈለገም፤+ ምክንያቱም ለእሱና ለልጆቹ ለሁልጊዜ የሚኖር መብራት* እንደሚሰጥ ቃል ገብቶ ነበር።+
8 በእሱ ዘመን ኤዶም በይሁዳ ላይ ዓምፆ+ የራሱን ንጉሥ አነገሠ።+ 9 በመሆኑም ኢዮራም ከአዛዦቹ ጋር ሠረገሎቹን ሁሉ ይዞ ተሻገረ፤ በሌሊትም ተነስቶ እሱንና የሠረገሎቹን አዛዦች ከበው የነበሩትን ኤዶማውያን ድል አደረገ። 10 ሆኖም ኤዶም እስከ ዛሬ ድረስ በይሁዳ ላይ እንዳመፀ ነው። ሊብናም+ በዚሁ ጊዜ በእሱ ላይ ዓመፀ፤ ምክንያቱም ኢዮራም የአባቶቹን አምላክ ይሖዋን ትቶ ነበር።+ 11 ደግሞም በይሁዳ ተራሮች ላይ ከፍ ያሉ የማምለኪያ ቦታዎችን ሠርቶ+ የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች መንፈሳዊ ምንዝር እንዲፈጽሙ አደረገ፤ ይሁዳንም አሳተ።
12 በመጨረሻም ነቢዩ ኤልያስ እንዲህ የሚል መልእክት በጽሑፍ ላከለት፦+ “የአባትህ የዳዊት አምላክ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘በአባትህ በኢዮሳፍጥ+ ወይም በይሁዳ ንጉሥ በአሳ+ መንገድ አልሄድክም። 13 ይልቁንም በእስራኤል ነገሥታት መንገድ በመሄድ፣+ ይሁዳና የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች የአክዓብ ቤት የፈጸመውን ምንዝር+ የሚመስል መንፈሳዊ ምንዝር እንዲፈጽሙ አድርገሃል፤+ ከዚህም በላይ ከአንተ ይሻሉ የነበሩትን የአባትህ ቤት ልጆች የሆኑትን የገዛ ወንድሞችህን ገድለሃል።+ 14 ስለዚህ ይሖዋ ሕዝብህን፣ ልጆችህን፣ ሚስቶችህንና ንብረትህን ሁሉ በታላቅ መቅሰፍት ይመታል። 15 አንተም የአንጀት በሽታን ጨምሮ በብዙ ሕመም ትሠቃያለህ፤ ከበሽታው የተነሳ አንጀትህ እስኪወጣ ድረስ ሕመሙ ዕለት ተዕለት እየጠናብህ ይሄዳል።’”
16 ከዚያም ይሖዋ ፍልስጤማውያንና+ በኢትዮጵያውያን አቅራቢያ የሚኖሩት ዓረቦች+ በኢዮራም ላይ እንዲነሱ አደረገ።*+ 17 እነሱም ይሁዳን ወረሩ፤ በኃይል ጥሰው በመግባትም በንጉሡ ቤት* ያገኙትን ንብረት ሁሉ+ እንዲሁም ልጆቹንና ሚስቶቹን ማርከው ወሰዱ፤ ከመጨረሻው ልጁ ከኢዮዓካዝ*+ በቀር አንድም ልጅ አልቀረለትም። 18 ከዚህ ሁሉ በኋላ ይሖዋ በማይድን የአንጀት በሽታ ቀሰፈው።+ 19 ድፍን ሁለት ዓመት ከታመመ በኋላም ሕመሙ ጠንቶበት አንጀቱ ወጣ፤ በበሽታውም እጅግ ሲሠቃይ ቆይቶ በመጨረሻ ሞተ፤ ሕዝቡም ለአባቶቹ ያደርጉት እንደነበረው ለእሱ ክብር እሳት አላነደዱም።+ 20 በነገሠ ጊዜ ዕድሜው 32 ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌምም ለስምንት ዓመት ገዛ። ሲሞት ማንም አላዘነለትም። በመሆኑም በነገሥታቱ የመቃብር ስፍራ ሳይሆን+ በዳዊት ከተማ+ ቀበሩት።
22 ከዚያም የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች የመጨረሻ ልጁን አካዝያስን* በእሱ ምትክ አነገሡት፤ ከዓረቦቹ ጋር ወደ ሰፈሩ የመጡት ወራሪዎች ታላላቆቹን በሙሉ ገድለዋቸው ነበር።+ በመሆኑም የኢዮራም ልጅ አካዝያስ የይሁዳ ንጉሥ ሆኖ መግዛት ጀመረ።+ 2 አካዝያስ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው 22 ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌምም ሆኖ አንድ ዓመት ገዛ። እናቱም ጎቶልያ+ የተባለች የኦምሪ+ የልጅ ልጅ* ነበረች።
3 እናቱ ክፉ ነገር እንዲያደርግ ትመክረው ስለነበር እሱም የአክዓብን+ ቤት መንገድ ተከተለ። 4 ከአባቱ ሞት በኋላ የአክዓብ ቤት ሰዎች አማካሪዎቹ በመሆን ወደ ጥፋት ስለመሩት ልክ እንደ አክዓብ ቤት እሱም በይሖዋ ፊት መጥፎ የሆነውን ነገር ማድረጉን ቀጠለ። 5 እሱም የእነሱን ምክር ተከትሎ ከሶርያ ንጉሥ ከሃዛኤል+ ጋር በራሞትጊልያድ+ ለመዋጋት ከእስራኤል ንጉሥ ከአክዓብ ልጅ ከኢዮራም ጋር ሄደ፤ በዚያም ቀስተኞች ኢዮራምን አቆሰሉት። 6 እሱም ከሶርያ ንጉሥ ከሃዛኤል ጋር በተዋጋበት ጊዜ+ በራማ ካቆሰሉት ቁስል ለማገገም ወደ ኢይዝራኤል+ ተመለሰ።
የይሁዳ ንጉሥ የኢዮራም+ ልጅ አካዝያስ* የአክዓብ ልጅ ኢዮራም+ ቆስሎ*+ ስለነበር እሱን ለማየት ወደ ኢይዝራኤል ወረደ። 7 ይሁንና አካዝያስ ወደ ኢዮራም በመምጣቱ አምላክ ለውድቀት ዳረገው፤ እዚያ ከደረሰ በኋላም ከኢዮራም ጋር የኒምሺን የልጅ ልጅ* ኢዩን+ ለማግኘት ሄዱ፤ ኢዩ የአክዓብን ቤት እንዲያጠፋ ይሖዋ የቀባው ሰው ነበር።+ 8 ኢዩም በአክዓብ ቤት ላይ የተላለፈውን ፍርድ ማስፈጸም ሲጀምር የአካዝያስ አገልጋዮች የነበሩትን የይሁዳን መኳንንትና የአካዝያስን ወንድሞች ልጆች አግኝቶ ገደላቸው።+ 9 ከዚያም አካዝያስን ለመፈለግ ሄደ፤ እነሱም በሰማርያ ተደብቆ ሳለ ያዙት፤ ወደ ኢዩም አመጡት። ከዚያም ገደሉት፤ ይሁንና “ይሖዋን በሙሉ ልቡ የፈለገው የኢዮሳፍጥ የልጅ ልጅ ነው” በማለት ቀበሩት።+ ከአካዝያስ ቤት የመንግሥቱን ሥልጣን የመያዝ ብቃት ያለው ሰው አልነበረም።
10 የአካዝያስ እናት ጎቶልያ+ ልጇ መሞቱን ባየች ጊዜ ተነስታ የይሁዳን ንጉሣውያን ቤተሰብ* በሙሉ አጠፋች።+ 11 ይሁንና የንጉሡ ልጅ የሆነችው ዮሳቤት ሊገደሉ ከነበሩት የንጉሡ ልጆች መካከል የአካዝያስን ልጅ ኢዮዓስን+ ሰርቃ በመውሰድ እሱንና ሞግዚቱን በውስጠኛው መኝታ ክፍል አስቀመጠቻቸው። የንጉሥ ኢዮራም+ ልጅ የሆነችው ዮሳቤት (የካህኑ ዮዳሄ+ ሚስትና የአካዝያስ እህት ነበረች) ከጎቶልያ ደብቃ አቆየችው፤ በመሆኑም ጎቶልያ ሳትገድለው ቀረች።+ 12 እሱም ከእነሱ ጋር ለስድስት ዓመት በእውነተኛው አምላክ ቤት ተደብቆ ቆየ፤ በዚህ ጊዜ ጎቶልያ በምድሪቱ ላይ ትገዛ ነበር።
23 በሰባተኛው ዓመት ካህኑ ዮዳሄ ድፍረት የተሞላበት እርምጃ በመውሰድ ከመቶ አለቆቹ+ ይኸውም ከየሮሃም ልጅ ከአዛርያስ፣ ከየሆሃናን ልጅ ከእስማኤል፣ ከኢዮቤድ ልጅ ከአዛርያስ፣ ከአዳያህ ልጅ ከማአሴያህ እና ከዚክሪ ልጅ ከኤሊሻፋጥ ጋር ስምምነት* አደረገ። 2 ከዚያም በይሁዳ ሁሉ በመዘዋወር ከመላው የይሁዳ ከተሞች ሌዋውያንንና+ የእስራኤልን የአባቶች ቤት መሪዎች ሰበሰቡ። ወደ ኢየሩሳሌም ሲመጡ 3 መላው ጉባኤ በእውነተኛው አምላክ ቤት ከንጉሡ ጋር ቃል ኪዳን ገባ፤+ ከዚያም ዮዳሄ እንዲህ አላቸው፦
“እነሆ፣ ይሖዋ የዳዊትን ወንዶች ልጆች አስመልክቶ ቃል በገባው መሠረት የንጉሡ ልጅ ይገዛል።+ 4 እናንተም እንዲህ ታደርጋላችሁ፦ በሰንበት ቀን ተረኛ ከሚሆኑት ካህናትና ሌዋውያን+ መካከል አንድ ሦስተኛዎቹ በር ጠባቂዎች ይሆናሉ፤+ 5 አንድ ሦስተኛዎቹ ደግሞ በንጉሡ ቤት*+ ይሆናሉ፤ ሌላው አንድ ሦስተኛ በመሠረት በር ላይ ይሆናል፤ ሕዝቡ ሁሉ ደግሞ በይሖዋ ቤት ግቢዎች+ ውስጥ ይሆናል። 6 ከሚያገለግሉት ካህናትና ሌዋውያን በስተቀር ማንንም ወደ ይሖዋ ቤት እንዳታስገቡ።+ እነሱ የተቀደሱ ስለሆኑ ይግቡ፤ የቀረውም ሕዝብ ሁሉ ለይሖዋ ያለበትን ግዴታ ይፈጽማል። 7 ሌዋውያኑም እያንዳንዳቸው የጦር መሣሪያቸውን በእጃቸው ይዘው ንጉሡን ዙሪያውን ይክበቡት። ወደ ቤቱም ውስጥ የሚገባ ማንኛውም ሰው ይገደላል። ንጉሡ በሚሄድበት ሁሉ* አብራችሁት ሁኑ።”
8 ሌዋውያኑና የይሁዳ ሰዎች በሙሉ ልክ ካህኑ ዮዳሄ እንዳዘዛቸው አደረጉ። እያንዳንዳቸውም በሰንበት ቀን ተረኛ የሚሆኑትንና በሰንበት ቀን ከሥራ ነፃ የሚሆኑትን የራሳቸውን ሰዎች ወሰዱ፤+ ካህኑ ዮዳሄ ተራቸው ባይሆንም እንኳ በየምድቡ+ ያሉትን ከሥራ አላሰናበተም ነበርና። 9 ካህኑ ዮዳሄም በእውነተኛው አምላክ ቤት+ የነበሩትን የንጉሥ ዳዊት ጦሮች፣ ትናንሽ ጋሻዎችና* ክብ ጋሻዎች+ ለመቶ አለቆቹ+ ሰጣቸው። 10 ከዚያም ሕዝቡ ሁሉ እያንዳንዳቸው የጦር መሣሪያቸውን* ይዘው በስተ ቀኝ በኩል ካለው የቤቱ ጎን አንስቶ በስተ ግራ በኩል እስካለው የቤቱ ጎን ድረስ በመሠዊያውና በቤቱ አጠገብ በንጉሡ ዙሪያ እንዲቆሙ አደረገ። 11 የንጉሡንም ልጅ+ አውጥተው አክሊሉን* ጫኑበት፤ ምሥክሩንም*+ ሰጡት፤ በዚህም መንገድ አነገሡት፤ ዮዳሄና ወንዶች ልጆቹም ቀቡት። ከዚያም “ንጉሡ ለዘላለም ይኑር!” አሉ።+
12 ጎቶልያ ሕዝቡ ሲሯሯጥና ንጉሡን ሲያወድስ ስትሰማ ወዲያውኑ በይሖዋ ቤት ወዳለው ሕዝብ መጣች።+ 13 ከዚያም ንጉሡ በመግቢያው ላይ ባለው በዓምዱ አጠገብ ቆሞ አየች። መኳንንቱና+ መለከት ነፊዎቹ ከንጉሡ ጋር ነበሩ፤ የምድሪቱም ሕዝብ ሁሉ እጅግ እየተደሰተና+ መለከት እየነፋ ነበር፤ የሙዚቃ መሣሪያ የያዙት ዘማሪዎችም ውዳሴውን ይመሩ* ነበር። በዚህ ጊዜ ጎቶልያ ልብሷን ቀዳ “ይህ ሴራ ነው! ሴራ ነው!” በማለት ጮኸች። 14 ካህኑ ዮዳሄ ግን በሠራዊቱ ላይ የተሾሙትን መቶ አለቆች ይዟቸው በመውጣት “ከረድፉ መካከል አውጧት፤ እሷን ተከትሎ የሚመጣ ሰው ካለ በሰይፍ ግደሉት!” አላቸው። ካህኑ “በይሖዋ ቤት ውስጥ እንዳትገድሏት” ብሎ ነበር። 15 በመሆኑም ያዟት፤ በንጉሡም ቤት* ወዳለው የፈረስ በር መግቢያ እንደደረሰች ገደሏት።
16 ከዚያም ዮዳሄ የይሖዋ ሕዝብ ሆነው እንዲቀጥሉ እሱ፣ ሕዝቡ ሁሉና ንጉሡ ቃል ኪዳን እንዲጋቡ አደረገ።+ 17 የምድሪቱም ሕዝብ ሁሉ ወደ ባአል ቤት* መጥቶ አፈራረሰው፤+ መሠዊያዎቹንና ምስሎቹንም ሰባበረ፤+ የባአል ካህን የነበረውን ማታንንም በመሠዊያዎቹ ፊት ገደሉት።+ 18 ከዚያም ዮዳሄ በይሖዋ ቤት የሚከናወኑትን ሥራዎች እንዲቆጣጠሩ ካህናቱንና ሌዋውያኑን ሾመ፤ እነሱም በሙሴ ሕግ ላይ በተጻፈው+ እንዲሁም ዳዊት ባዘዘው መሠረት* በደስታና በመዝሙር ለይሖዋ የሚቃጠል መሥዋዕት እንዲያቀርቡ ዳዊት በይሖዋ ቤት በየምድቡ የመደባቸው ናቸው።+ 19 በተጨማሪም በማንኛውም ነገር የረከሰ ሰው እንዳይገባ በር ጠባቂዎቹን+ በይሖዋ ቤት በሮች ላይ አቆመ። 20 ከዚያም መቶ አለቆቹን፣+ መኳንንቱን፣ የሕዝቡን ገዢዎችና የምድሪቱን ሕዝብ ሁሉ ሰበሰበ፤ ንጉሡንም አጅበው ከይሖዋ ቤት ወደ ታች አመጡት። በላይኛውም በር በኩል ወደ ንጉሡ ቤት* ገቡ፤ ንጉሡንም በመንግሥቱ+ ዙፋን+ ላይ አስቀመጡት። 21 በመሆኑም የምድሪቱ ሕዝብ ሁሉ እጅግ ተደሰተ፤ ጎቶልያንም በሰይፍ ስለገደሏት ከተማዋ ጸጥታ ሰፈነባት።
24 ኢዮዓስ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ሰባት ዓመት ነበር፤+ በኢየሩሳሌም ሆኖ 40 ዓመት ገዛ። እናቱ ጺብያ የተባለች የቤርሳቤህ+ ተወላጅ ነበረች። 2 ኢዮዓስ ካህኑ ዮዳሄ በነበረበት ዘመን ሁሉ በይሖዋ ፊት መልካም የሆነውን ነገር አደረገ።+ 3 ዮዳሄ ሁለት ሚስቶች መረጠለት፤ እሱም ወንዶችና ሴቶች ልጆች ወለደ።
4 ከጊዜ በኋላ ኢዮዓስ የይሖዋን ቤት ለማደስ ልባዊ ፍላጎት አደረበት።+ 5 በመሆኑም ካህናቱንና ሌዋውያኑን ሰብስቦ እንዲህ አላቸው፦ “ወደ ይሁዳ ከተሞች ሄዳችሁ የአምላካችሁን ቤት በየዓመቱ ለማደስ ከእስራኤል ሁሉ ገንዘብ ሰብስቡ፤+ እናንተም በአስቸኳይ ይህንኑ አድርጉ።” ሌዋውያኑ ግን አፋጣኝ እርምጃ አልወሰዱም።+ 6 ስለዚህ ንጉሡ የካህናቱን አለቃ ዮዳሄን ጠርቶ እንዲህ አለው፦+ “የይሖዋ አገልጋይ የሆነው ሙሴ ያዘዘውንና+ ለምሥክሩ ድንኳን+ የሚውለውን የተቀደሰ ግብር ይኸውም የእስራኤልን ጉባኤ የተቀደሰ ግብር ከይሁዳና ከኢየሩሳሌም እንዲያመጡ ሌዋውያኑን ያላዘዝካቸው ለምንድን ነው? 7 የዚያች ክፉ ሴት የጎቶልያ+ ወንዶች ልጆች ወደ እውነተኛው አምላክ ቤት ሰብረው በመግባት+ በይሖዋ ቤት የነበሩትን የተቀደሱ ዕቃዎች በሙሉ ለባአል አገልግሎት እንዳዋሉ ታውቃለህ።” 8 ከዚያም በንጉሡ ትእዛዝ መሠረት ሣጥን+ ተሠርቶ በይሖዋ ቤት በር አጠገብ በውጭ በኩል ተቀመጠ።+ 9 ከዚህ በኋላ የእውነተኛው አምላክ አገልጋይ ሙሴ በምድረ በዳ ሳሉ በእስራኤል ላይ የጣለው የተቀደሰ ግብር+ ለይሖዋ እንዲሰጥ በመላው ይሁዳና ኢየሩሳሌም አዋጅ ተነገረ። 10 መኳንንቱ ሁሉና ሕዝቡ ሁሉ ሐሴት አደረጉ፤+ ሣጥኑ እስኪሞላም* ድረስ መዋጮ እያመጡ ይጨምሩ ነበር።
11 ሌዋውያኑ ሣጥኑን ወደ ንጉሡ በሚያመጡበትና በውስጡ ብዙ ገንዘብ መኖሩን በሚያዩበት ጊዜ ሁሉ የንጉሡ ጸሐፊና የካህናቱ አለቃ ሹም መጥተው ሣጥኑን ካጋቡ+ በኋላ ወደ ቦታው ይመልሱት ነበር። በየዕለቱ እንዲህ ያደርጉ ነበር፤ እጅግ ብዙ ገንዘብም ሰበሰቡ። 12 ከዚያም ንጉሡና ዮዳሄ ገንዘቡን በይሖዋ ቤት አገልግሎት የሚከናወነውን ሥራ ለሚቆጣጠሩት ሰዎች ይሰጧቸው ነበር፤ እነሱ ደግሞ የይሖዋን ቤት ለማደስ+ ድንጋይ ጠራቢዎችንና የእጅ ጥበብ ባለሙያዎችን እንዲሁም የይሖዋን ቤት ለመጠገን የብረትና የመዳብ ሠራተኞችን ይቀጥሩ ነበር። 13 ሥራውን የሚቆጣጠሩት ሰዎችም ሥራው እንዲጀመር አደረጉ፤ የጥገናውም ሥራ በእነሱ አመራር ሥር ተፋጠነ፤ የእውነተኛውን አምላክ ቤት በማደስ ወደ ቀድሞው ሁኔታ መለሱት፤ ቤቱንም አጠናከሩት። 14 ሥራውን እንደጨረሱም የተረፈውን ገንዘብ ወደ ንጉሡና ወደ ዮዳሄ አመጡ፤ እነሱም ለይሖዋ ቤት የሚያስፈልጉ ዕቃዎችን፣ ለአገልግሎትና መባ ለማቅረብ የሚያስፈልጉ ዕቃዎችን፣ ጽዋዎችን እንዲሁም የወርቅና የብር ዕቃዎችን ለመሥራት ተጠቀሙበት።+ ዮዳሄ በነበረበት ዘመን ሁሉ በይሖዋ ቤት የሚቃጠሉ መሥዋዕቶችን+ ዘወትር ያቀርቡ ነበር።
15 ዮዳሄ ሸምግሎና ዕድሜ ጠግቦ ሞተ፤ በሞተ ጊዜ ዕድሜው 130 ዓመት ነበር። 16 ከእውነተኛው አምላክና ከአምላክ ቤት ጋር በተያያዘ በእስራኤል መልካም ነገር ስላደረገ+ በዳዊት ከተማ ከነገሥታት ጋር ቀበሩት።+
17 ከዮዳሄ ሞት በኋላ የይሁዳ መኳንንት መጥተው ንጉሡን እጅ ነሱ፤ ንጉሡም እነሱ ያሉትን ሰማ። 18 እነሱም የአባቶቻቸውን አምላክ የይሖዋን ቤት ትተው የማምለኪያ ግንዶችንና* ጣዖቶችን ማገልገል ጀመሩ፤ ከፈጸሙት በደል የተነሳ በይሁዳና በኢየሩሳሌም ላይ የአምላክ ቁጣ መጣ።* 19 ይሖዋ ወደ እሱ እንዲመልሷቸው ነቢያትን ይልክላቸው ነበር፤ እነሱም ያስጠነቅቋቸው* ነበር፤ ሕዝቡ ግን ለመስማት ፈቃደኛ አልነበረም።+
20 የአምላክ መንፈስ በካህኑ በዮዳሄ+ ልጅ በዘካርያስ ላይ ወረደ፤ እሱም በሕዝቡ ፊት ከፍ ያለ ቦታ ላይ ቆሞ እንዲህ አላቸው፦ “እውነተኛው አምላክ እንዲህ ይላል፦ ‘የይሖዋን ትእዛዛት የምትተላለፉት ለምንድን ነው? አይሳካላችሁም! ይሖዋን ስለተዋችሁ እሱም ይተዋችኋል።’”+ 21 እነሱ ግን በእሱ ላይ አሴሩ፤+ ንጉሡም በሰጠው ትእዛዝ መሠረት በይሖዋ ቤት ግቢ ውስጥ በድንጋይ ወገሩት።+ 22 ንጉሥ ኢዮዓስ፣ አባቱ* ዮዳሄ ያሳየውን ታማኝ ፍቅር አላሰበም፤ ልጁንም ገደለው፤ እሱም ሊሞት ሲል “ይሖዋ ይየው፤ የእጅህንም ይስጥህ” አለ።+
23 በዓመቱ መጀመሪያ ላይ የሶርያ ሠራዊት በኢዮዓስ ላይ ዘመተ፤ እነሱም ይሁዳንና ኢየሩሳሌምን ወረሩ።+ ከዚያም የሕዝቡን መኳንንት ሁሉ አጠፉ፤+ የማረኩትንም ሁሉ ወደ ደማስቆ ንጉሥ ላኩ። 24 ወራሪው የሶርያ ሠራዊት አነስተኛ ቁጥር የነበረው ቢሆንም ይሖዋ እጅግ ብዙ የሆነውን ሠራዊት በእጁ አሳልፎ ሰጠው፤+ ይህም የሆነው የአባቶቻቸውን አምላክ ይሖዋን በመተዋቸው ነው፤ እነሱም* በኢዮዓስ ላይ የተላለፈውን ፍርድ ፈጸሙ። 25 እነሱም ጥለውት በሄዱ ጊዜ (ክፉኛ አቁስለውት* ነበርና) የገዛ አገልጋዮቹ የካህኑን የዮዳሄን ልጆች* ደም በማፍሰሱ አሴሩበት።+ አልጋው ላይ እንዳለ ገደሉት።+ ከሞተም በኋላ በዳዊት ከተማ ቀበሩት፤+ በነገሥታቱ የመቃብር ስፍራ ግን አልቀበሩትም።+
26 በእሱ ላይ ያሴሩት+ የአሞናዊቷ የሺምዓት ልጅ ዛባድና የሞዓባዊቷ የሺምሪት ልጅ የሆዛባድ ነበሩ። 27 ስለ ወንዶች ልጆቹ፣ በእሱ ላይ ስለተላለፉት በርካታ የፍርድ መልእክቶችና+ የእውነተኛውን አምላክ ቤት ስለማደሱ*+ የሚገልጸው ታሪክ ሁሉ በነገሥታቱ መጽሐፍ ዘገባዎች* ላይ ሰፍሯል። በእሱም ምትክ ልጁ አሜስያስ ነገሠ።
25 አሜስያስ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው 25 ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌምም ሆኖ ለ29 ዓመት ገዛ። እናቱ ዮዓዳን የተባለች የኢየሩሳሌም ተወላጅ ነበረች።+ 2 እሱም በይሖዋ ፊት ትክክል የሆነውን ነገር አደረገ፤ ሆኖም በሙሉ ልቡ አልነበረም። 3 መንግሥቱ በእጁ እንደጸናለትም ንጉሥ የነበረውን አባቱን የገደሉትን አገልጋዮቹን ገደላቸው።+ 4 ይሁንና “አባቶች በልጆቻቸው ኃጢአት መገደል የለባቸውም፤ ልጆችም በአባቶቻቸው ኃጢአት መገደል የለባቸውም፤ ይልቁንም እያንዳንዱ ሰው በገዛ ኃጢአቱ ይገደል” በሚለው በሙሴ የሕግ መጽሐፍ ላይ በተጻፈው የይሖዋ ትእዛዝ መሠረት የገዳዮቹን ልጆች አልገደላቸውም።+
5 አሜስያስም የይሁዳን ሰዎች ሰብስቦ በየአባቶቻቸው ቤት፣ በሺህ አለቆችና በመቶ አለቆች በመደልደል መላውን ይሁዳና ቢንያም ወክለው እንዲቆሙ አደረገ።+ ዕድሜያቸው 20 ዓመትና ከዚያ በላይ የሆናቸውን መዘገበ፤+ በጦርና በትልቅ ጋሻ መጠቀምና በሠራዊቱ ውስጥ ማገልገል የሚችሉ 300,000 የሠለጠኑ* ተዋጊዎችን አገኘ። 6 በተጨማሪም በ100 የብር ታላንት፣* 100,000 ኃያላን ተዋጊዎችን ከእስራኤል ቀጠረ። 7 ይሁንና አንድ የእውነተኛው አምላክ ሰው ወደ እሱ መጥቶ እንዲህ አለው፦ “ንጉሥ ሆይ፣ ይሖዋ ከእስራኤል፣ ከኤፍሬማውያን ሁሉ ጋር ስላልሆነ+ የእስራኤል ሠራዊት ከአንተ ጋር እንዲዘምት አታድርግ። 8 ይልቁንም ብቻህን ዝመት፤ ወደኋላ አትበል፤ በቆራጥነትም ተዋጋ። እንዲህ ባታደርግ ግን እውነተኛው አምላክ በጠላቶችህ ፊት ሊጥልህ ይችላል፤ አምላክ ለመርዳትም ሆነ ለመጣል ኃይል አለውና።”+ 9 በዚህ ጊዜ አሜስያስ የእውነተኛውን አምላክ ሰው “ታዲያ ለእስራኤል ወታደሮች የሰጠሁት 100 ታላንት ምን ይሁን?” አለው። የእውነተኛውም አምላክ ሰው “ይሖዋ ከዚህ እጅግ የሚበልጥ ሊሰጥህ ይችላል” ሲል መለሰለት።+ 10 በመሆኑም አሜስያስ ከኤፍሬም ወደ እሱ የመጡትን ወታደሮች ወደ ስፍራቸው እንዲመለሱ አሰናበታቸው። እነሱ ግን በይሁዳ እጅግ ተበሳጭተው በታላቅ ቁጣ ወደ ገዛ አገራቸው ተመለሱ።
11 ከዚያም አሜስያስ ተበረታታ፤ የራሱንም ወታደሮች እየመራ ወደ ጨው ሸለቆ+ ሄደ፤ ደግሞም 10,000 የሚሆኑ የሴይር ሰዎችን ገደለ።+ 12 የይሁዳም ሰዎች 10,000 የሚሆኑ ሰዎችን ማረኩ። ከዚያም ወደ ገደል አፋፍ ወስደው፣ ከአፋፉ ላይ ቁልቁል ወረወሯቸው፤ ሁሉም ተፈጥፍጠው ብትንትናቸው ወጣ። 13 ይሁንና አሜስያስ ከእሱ ጋር ወደ ጦርነት እንዳይሄዱ ያሰናበታቸው ወታደሮች+ ከሰማርያ+ አንስቶ እስከ ቤትሆሮን+ ድረስ ያሉትን የይሁዳ ከተሞች ወረሩ፤ 3,000 ሰዎችም ገደሉ፤ ብዙ ምርኮም ወሰዱ።
14 አሜስያስ ኤዶማውያንን መትቶ ከተመለሰ በኋላ የሴይርን ሰዎች አማልክት ይዞ በመምጣት ለራሱ አማልክት አድርጎ አቆማቸው፤+ በእነሱም ፊት ይሰግድ እንዲሁም የሚጨስ መሥዋዕት ያቀርብላቸው ጀመር። 15 ስለሆነም የይሖዋ ቁጣ በአሜስያስ ላይ ነደደ፤ ነቢይም ልኮ “የገዛ ሕዝባቸውን ከእጅህ መታደግ ያልቻሉትን የሕዝቡን አማልክት የምትከተለው ለምንድን ነው?” አለው።+ 16 በዚህ ጊዜ ንጉሡ ነቢዩን “የንጉሡ አማካሪ አድርገን ሾመንሃል?+ ዝም በል!+ መሞት ትፈልጋለህ?” አለው። ነቢዩም ዝም አለ፤ ሆኖም “ይህን በማድረግህና ምክሬን ባለመስማትህ አምላክ ሊያጠፋህ እንደወሰነ ተረዳሁ” አለ።+
17 የይሁዳ ንጉሥ አሜስያስ ከአማካሪዎቹ ጋር ከተማከረ በኋላ የእስራኤል ንጉሥ ወደሆነው ወደ ኢዩ ልጅ ወደ ኢዮዓካዝ ልጅ ወደ ኢዮዓስ “ና፣ ውጊያ እንግጠም”* የሚል መልእክት ላከበት።+ 18 የእስራኤል ንጉሥ ኢዮዓስ ደግሞ ወደ ይሁዳ ንጉሥ ወደ አሜስያስ ይህን መልእክት ላከ፦ “በሊባኖስ የሚገኘው ኩርንችት በሊባኖስ ወደሚገኘው አርዘ ሊባኖስ ‘ሴት ልጅህን ለወንድ ልጄ ዳርለት’ የሚል መልእክት ላከ። ይሁን እንጂ በሊባኖስ የነበረ አንድ የዱር አውሬ በዚያ ሲያልፍ ያን ኩርንችት ረገጠው። 19 አንተ ‘እኔ ኤዶምን መትቻለሁ’ ብለሃል።+ በመሆኑም ልብህ ክብር በመሻት ታብዮአል። አሁን ግን አርፈህ ቤትህ* ተቀመጥ። በራስህ ላይ ለምን ጥፋት ትጋብዛለህ? ደግሞስ ራስህንም ሆነ ይሁዳን ለምን ለውድቀት ትዳርጋለህ?”
20 አሜስያስ ግን አልሰማም፤+ የኤዶምን አማልክት በመከተላቸው+ እውነተኛው አምላክ በጠላቶቻቸው እጅ አሳልፎ ሊሰጣቸው ወስኗልና።+ 21 በመሆኑም የእስራኤል ንጉሥ ኢዮዓስ ወጣ፤ እሱና የይሁዳ ንጉሥ አሜስያስም በይሁዳ በምትገኘው በቤትሼሜሽ+ ተጋጠሙ። 22 ይሁዳ በእስራኤል ድል ተመታ፤ እያንዳንዳቸውም ወደየቤታቸው* ሸሹ። 23 የእስራኤል ንጉሥ ኢዮዓስ የኢዮአካዝ* ልጅ፣ የኢዮዓስ ልጅ የሆነውን የይሁዳን ንጉሥ አሜስያስን ቤትሼሜሽ ላይ ያዘው። ከዚያም ወደ ኢየሩሳሌም አመጣው፤ የኢየሩሳሌምን ቅጥር፣ ከኤፍሬም በር+ አንስቶ እስከ ማዕዘን በር+ ድረስ አፈረሰ፤ ርዝመቱም 400 ክንድ* ያህል ነበር። 24 በእውነተኛው አምላክ ቤት በኦቤድዔዶም እጅና* በንጉሡ ቤት* ግምጃ ቤቶች+ የተገኘውን ወርቅ፣ ብርና ዕቃ ሁሉ እንዲሁም የታገቱትን ሰዎች ወሰደ። ከዚያም ወደ ሰማርያ ተመለሰ።
25 የእስራኤል ንጉሥ የኢዮዓካዝ ልጅ ኢዮዓስ+ ከሞተ በኋላ፣ የይሁዳ ንጉሥ የኢዮዓስ ልጅ አሜስያስ+ 15 ዓመት ኖረ።+ 26 ከመጀመሪያ አንስቶ እስከ መጨረሻ ድረስ ያለው የቀረው የአሜስያስ ታሪክ በይሁዳና በእስራኤል ነገሥታት መጽሐፍ ውስጥ ተጽፎ የለም? 27 አሜስያስ ይሖዋን መከተል ከተወበት ጊዜ ጀምሮ በኢየሩሳሌም በእሱ ላይ ሲያሴሩ ቆዩ፤+ እሱም ወደ ለኪሶ ሸሸ፤ እነሱ ግን ተከታትለው እንዲይዙት ሰዎችን ወደ ለኪሶ ላኩ፤ በዚያም ገደሉት። 28 ከዚያም በፈረሶች ላይ ጭነው አመጡት፤ ከአባቶቹም ጋር በይሁዳ ከተማ ቀበሩት።
26 ከዚያም የይሁዳ ሕዝብ ሁሉ የ16 ዓመት ልጅ የነበረውን ዖዝያን*+ ወስደው በአባቱ በአሜስያስ ምትክ አነገሡት።+ 2 እሱም፣ ንጉሡ* ከአባቶቹ ጋር ካንቀላፋ በኋላ ኤሎትን+ መልሶ በመገንባት ወደ ይሁዳ መለሳት።+ 3 ዖዝያ+ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው 16 ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌምም ሆኖ ለ52 ዓመት ገዛ። እናቱ ይኮልያ የተባለች የኢየሩሳሌም ተወላጅ ነበረች።+ 4 እሱም አባቱ አሜስያስ እንዳደረገው ሁሉ በይሖዋ ፊት ትክክል የሆነውን ነገር አደረገ።+ 5 እውነተኛውን አምላክ መፍራት ባስተማረው በዘካርያስ ዘመን አምላክን ይፈልግ ነበር። ይሖዋን ይፈልግ በነበረበት ዘመን እውነተኛው አምላክ አበለጸገው።+
6 እሱም ወጥቶ ከፍልስጤማውያን+ ጋር በመዋጋት የጌትን+ ቅጥር፣ የያብነህን+ ቅጥርና የአሽዶድን ቅጥር አፈረሰ። ከዚያም በአሽዶድና+ በፍልስጤማውያን ክልል ከተሞችን ገነባ። 7 እውነተኛው አምላክ በፍልስጤማውያን ላይ፣ በጉርባዓል በሚኖሩት ዓረቦች+ ላይ እንዲሁም በመኡኒም ላይ ድል እንዲቀዳጅ ረዳው። 8 አሞናውያን+ ለዖዝያ ግብር ይገብሩለት ጀመር። እጅግ እየበረታ ስለሄደም ዝናው እስከ ግብፅ ድረስ ናኘ። 9 በተጨማሪም ዖዝያ በኢየሩሳሌም በማዕዘን በር፣+ በሸለቆ በርና+ የቅጥሩ ማጠናከሪያ በሚገኝበት ስፍራ ጠንካራ ማማዎችን+ ሠራ። 10 ከዚህም ሌላ በምድረ በዳው ማማዎችን ገነባ፤+ ብዙ የውኃ ማጠራቀሚያ ጉድጓዶችንም ቆፈረ* (ብዙ ከብቶች ነበሩትና)፤ በሸፌላና በሜዳውም* ላይ እንዲሁ አደረገ። ግብርና ይወድ ስለነበር በተራሮቹ ላይና በቀርሜሎስ፣ ገበሬዎችና የወይን አትክልት ሠራተኞች ነበሩት።
11 በተጨማሪም ዖዝያ ለውጊያ ዝግጁ የሆነ ሠራዊት ነበረው። በቡድን በቡድን ተደራጅተው ለጦርነት ይወጡ ነበር። እነዚህ ሰዎች ከንጉሡ መኳንንት አንዱ በሆነው በሃናንያህ አመራር ሥር ሆነው በሚያገለግሉት በጸሐፊው የኢዔል+ እና በአለቃው ማአሴያህ አማካኝነት ተቆጥረው ተመዘገቡ።+ 12 በእነዚህ ኃያላን ተዋጊዎች ላይ የተሾሙት የአባቶች ቤት መሪዎች አጠቃላይ ቁጥር 2,600 ነበር። 13 በእነሱ አመራር ሥር 307,500 ወታደሮችን ያቀፈ ሠራዊት ነበር፤ ይህም ንጉሡ በጠላት ላይ በሚያደርገው ዘመቻ ድጋፍ የሚሰጡ ለጦርነት ዝግጁ የሆኑ ሰዎችን የያዘ ጠንካራ ወታደራዊ ኃይል ነው።+ 14 ዖዝያ መላው ሠራዊት ጋሻ፣ ጦር፣+ የራስ ቁር፣ ጥሩር፣+ ቀስትና የወንጭፍ ድንጋይ+ እንዲታጠቅ አደረገ። 15 በተጨማሪም ባለሙያዎች ባወጡት ንድፍ የተሠሩ የጦር መሣሪያዎችን በኢየሩሳሌም አዘጋጀ፤ መሣሪያዎቹ በየማማውና+ በቅጥሩ ማዕዘናት ላይ የተተከሉ ሲሆን ቀስትና ትላልቅ ድንጋዮች ለማስወንጨፍ ያገለግሉ ነበር። ዖዝያ ከፍተኛ እርዳታ በማግኘቱና እየበረታ በመሄዱ ዝናው በሩቅ ቦታ ሁሉ ተሰማ።
16 ይሁን እንጂ ዖዝያ በበረታ ጊዜ ለጥፋት እስኪዳረግ ድረስ ልቡ ታበየ፤ በዕጣን መሠዊያው ላይ ዕጣን ለማጠን ወደ ይሖዋ ቤተ መቅደስ በመግባት በአምላኩ በይሖዋ ላይ ታማኝነት የጎደለው ድርጊት ፈጸመ።+ 17 ወዲያውኑም ካህኑ አዛርያስና ደፋር የሆኑ ሌሎች 80 የይሖዋ ካህናት ተከትለውት ገቡ። 18 ከዚያም ንጉሥ ዖዝያን ፊት ለፊት በመጋፈጥ እንዲህ አሉት፦ “ዖዝያ ሆይ፣ አንተ ለይሖዋ ዕጣን ማጠንህ ተገቢ አይደለም!+ ዕጣን ማጠን ያለባቸው ካህናቱ ብቻ ናቸው፤ እነሱ የተቀደሱ የአሮን ዘሮች ናቸውና።+ ታማኝነት የጎደለው ድርጊት ስለፈጸምክ ከመቅደሱ ውጣ፤ እንዲህ ማድረግህ በይሖዋ አምላክ ዘንድ ምንም ዓይነት ክብር አያስገኝልህም።”
19 ዕጣን ለማጠን በእጁ ጥና ይዞ የነበረው ዖዝያ ግን እጅግ ተቆጣ፤+ ካህናቱን እየተቆጣ ሳለም በይሖዋ ቤት በዕጣን መሠዊያው አጠገብ ካህናቱ ባሉበት ግንባሩ ላይ የሥጋ ደዌ+ ወጣበት። 20 የካህናቱ አለቃ አዛርያስና ካህናቱ ሁሉ ባዩት ጊዜ ግንባሩ በሥጋ ደዌ ተመቶ ነበር! በመሆኑም ከዚያ አጣድፈው አስወጡት፤ እሱ ራሱም ይሖዋ ስለመታው ለመውጣት ቸኩሎ ነበር።
21 ንጉሥ ዖዝያ እስከ ዕለተ ሞቱ ድረስ የሥጋ ደዌ በሽተኛ ሆኖ ኖረ፤ የሥጋ ደዌ በሽተኛ በመሆኑ በአንድ የተለየ ቤት ውስጥ ተገልሎ ተቀመጠ፤+ ወደ ይሖዋ ቤት እንዳይገባ ታግዶ ነበር። ልጁ ኢዮዓታም በንጉሡ ቤት* ላይ ተሹሞ በምድሪቱ በሚኖረው ሕዝብ ላይ ይፈርድ ነበር።+
22 ከመጀመሪያ አንስቶ እስከ መጨረሻ ድረስ ያለውን የቀረውን የዖዝያ ታሪክ የአሞጽ ልጅ ነቢዩ ኢሳይያስ+ ጽፎታል። 23 በመጨረሻም ዖዝያ ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ ከአባቶቹም ጋር ቀበሩት፤ ሆኖም “የሥጋ ደዌ አለበት” ብለው ስላሰቡ የቀበሩት ከነገሥታቱ የመቃብር ቦታ ውጭ ባለ መሬት ላይ ነበር። በእሱም ምትክ ልጁ ኢዮዓታም+ ነገሠ።
27 ኢዮዓታም+ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው 25 ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌምም ሆኖ ለ16 ዓመት ገዛ። እናቱም የሩሻህ ትባል ነበር፤ እሷም የሳዶቅ ልጅ ነበረች።+ 2 ኢዮዓታም አባቱ ዖዝያ እንዳደረገው ሁሉ በይሖዋ ፊት ትክክል የሆነውን ነገር አደረገ፤+ ይሁንና ሥርዓቱን ጥሶ ወደ ይሖዋ ቤተ መቅደስ አልገባም።+ ሕዝቡ ግን ክፉ ድርጊት መፈጸሙን አልተወም ነበር። 3 እሱም የይሖዋን ቤት+ የላይኛውን በር ሠራ፤ በኦፌልም+ ቅጥር ላይ መጠነ ሰፊ የግንባታ ሥራ አከናወነ። 4 በተጨማሪም በተራራማው የይሁዳ ክልል+ ከተሞችን ሠራ፤+ በደን በተሸፈኑት ስፍራዎችም ምሽጎችንና+ ማማዎችን+ ገነባ። 5 ከአሞናውያንም ንጉሥ ጋር ተዋጋ፤+ በመጨረሻም አሸነፋቸው፤ በመሆኑም አሞናውያን በዚያ ዓመት 100 የብር ታላንት፣* 10,000 የቆሮስ መስፈሪያ* ስንዴና 10,000 የቆሮስ መስፈሪያ ገብስ ሰጡት። በተጨማሪም አሞናውያን በሁለተኛውና በሦስተኛው ዓመት ይህንኑ ግብር አመጡለት።+ 6 ኢዮዓታም በአምላኩ በይሖዋ ፊት መንገዱን ስላጸና* ከጊዜ ወደ ጊዜ እየበረታ ሄደ።
7 የቀረው የኢዮዓታም ታሪክ፣ ያካሄዳቸው ጦርነቶችና የተከተለው መንገድ ሁሉ በእስራኤልና በይሁዳ ነገሥታት መጽሐፍ ውስጥ ተጽፈዋል።+ 8 እሱ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው 25 ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌምም ሆኖ ለ16 ዓመት ገዛ።+ 9 በመጨረሻም ኢዮዓታም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በዳዊት ከተማም+ ቀበሩት። በእሱም ምትክ ልጁ አካዝ ነገሠ።+
28 አካዝ+ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው 20 ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌምም ሆኖ ለ16 ዓመት ገዛ። አባቱ ዳዊት እንዳደረገው በይሖዋ ፊት ትክክል የሆነውን ነገር አላደረገም።+ 2 ከዚህ ይልቅ የእስራኤልን ነገሥታት መንገድ ተከተለ፤+ አልፎ ተርፎም ከብረት የተሠሩ የባአል ሐውልቶችን* ሠራ።+ 3 በተጨማሪም በሂኖም ልጅ ሸለቆ* የሚጨስ መሥዋዕት ያቀረበ ከመሆኑም ሌላ ይሖዋ ከእስራኤላውያን ፊት ያባረራቸው ብሔራት ይፈጽሙ የነበረውን አስጸያፊ ድርጊት በመከተል+ ወንዶች ልጆቹን በእሳት አቃጠለ።+ 4 ደግሞም ከፍ ባሉት የማምለኪያ ቦታዎች፣ በኮረብቶቹና በእያንዳንዱ የለመለመ ዛፍ ሥር+ ይሠዋ እንዲሁም የሚጨስ መሥዋዕት ያቀርብ ነበር።+
5 ስለዚህ አምላኩ ይሖዋ በሶርያ ንጉሥ+ እጅ አሳልፎ ሰጠው፤ እነሱም ድል አደረጉት፤ ከሕዝቡም መካከል ብዙዎቹን ማርከው ወደ ደማስቆ+ ወሰዱ። ደግሞም አምላክ በእስራኤል ንጉሥ እጅ አሳልፎ ሰጠው፤ እሱም ከባድ እልቂት አደረሰበት። 6 የረማልያህ ልጅ ፋቁሄ+ በይሁዳ 120,000 ሰዎችን በአንድ ቀን የገደለ ሲሆን ሁሉም ደፋር ተዋጊዎች ነበሩ፤ ይህም የሆነው የአባቶቻቸውን አምላክ ይሖዋን በመተዋቸው ነው።+ 7 ዚክሪ የተባለው ኤፍሬማዊ ተዋጊም የንጉሡን ልጅ ማአሴያህን፣ የቤተ መንግሥቱን* አዛዥ አዝሪቃምንና የንጉሡ ምክትል የሆነውን ሕልቃናን ገደለ። 8 በተጨማሪም እስራኤላውያን ከአይሁዳውያን ወገኖቻቸው መካከል 200,000 ሴቶችን፣ ወንዶች ልጆችንና ሴቶች ልጆችን ማረኩ፤ እጅግ ብዙ ምርኮም ወሰዱ፤ የበዘበዙትንም ወደ ሰማርያ+ ይዘው ሄዱ።
9 ይሁንና በዚያ ኦዴድ የተባለ የይሖዋ ነቢይ ነበር። እሱም ወደ ሰማርያ እየመጣ የነበረውን ሠራዊት ለመገናኘት ወጥቶ እንዲህ አላቸው፦ “እነሆ፣ የአባቶቻችሁ አምላክ ይሖዋ የይሁዳ ሰዎችን በእጃችሁ አሳልፎ የሰጣችሁ በእነሱ ላይ ስለተቆጣ ነው፤+ እናንተም እስከ ሰማይ በሚደርስ ታላቅ ቁጣ ፈጃችኋቸው። 10 አሁንም የይሁዳንና የኢየሩሳሌምን ሕዝብ ለራሳችሁ ወንድ አገልጋዮችና ሴት አገልጋዮች ልታደርጓቸው ታስባላችሁ።+ እናንተስ ብትሆኑ በአምላካችሁ በይሖዋ ፊት ተጠያቂ አይደላችሁም? 11 እንግዲህ ስሙኝ፤ የይሖዋ ቁጣ በእናንተ ላይ ስለነደደ ከወንድሞቻችሁ መካከል የማረካችኋቸውን ሰዎች መልሱ።”
12 በዚህ ጊዜ ከኤፍሬማውያን አለቆች መካከል አንዳንድ ሰዎች ይኸውም የየሆሃናን ልጅ አዛርያስ፣ የመሺሌሞት ልጅ ቤራክያህ፣ የሻሉም ልጅ የሂዝቂያ እና የሃድላይ ልጅ አሜሳይ ከጦርነቱ የተመለሱትን ሰዎች በመቃወም 13 እንዲህ አሏቸው፦ “ምርኮኞቹን ወደዚህ አታምጧቸው፤ በይሖዋ ፊት በደለኞች ታደርጉናላችሁ። በደላችን ብዙ ሆኖ ሳለ፣ በኃጢአታችንና በበደላችን ላይ ልትጨምሩብን ታስባላችሁ? በእስራኤል ላይ ቁጣ ነዷልና።” 14 ስለዚህ የታጠቁት ወታደሮች ምርኮኞቹንና የበዘበዙትን ነገር+ ለመኳንንቱና ለመላው ጉባኤ አስረከቡ። 15 ከዚያም በስም ተጠቅሰው ኃላፊነት የተሰጣቸው ሰዎች ተነስተው ምርኮኞቹን ተረከቡ፤ ራቁታቸውን ለነበሩት ሁሉ ከምርኮው ልብስ ሰጧቸው። ልብስ አለበሷቸው፤ እንዲሁም ጫማ ሰጧቸው፤ የሚበሉትና የሚጠጡት ነገር አቀረቡላቸው፤ ለገላቸውም ዘይት ሰጧቸው። ከዚህም ሌላ የደከሙትን በአህያ ላይ አስቀምጠው ወንድሞቻቸው ወደሚገኙባት የዘንባባ ዛፎች ከተማ ወደሆነችው ወደ ኢያሪኮ ወሰዷቸው። ከዚያም ወደ ሰማርያ ተመለሱ።
16 በዚህ ጊዜ ንጉሥ አካዝ፣ የአሦር ነገሥታት እንዲረዱት ጠየቀ።+ 17 ኤዶማውያንም በድጋሚ መጥተው ይሁዳን በመውረር ጥቃት ሰነዘሩ፤ ምርኮኞችንም ወሰዱ። 18 ፍልስጤማውያን+ ደግሞ በይሁዳ የሚገኙትን የሸፌላንና+ የኔጌብን ከተሞች ወረሩ፤ ቤትሼሜሽን፣+ አይሎንን፣+ ገዴሮትን፣ ሶኮንና በሥሯ* ያሉትን ከተሞች፣ ቲምናንና+ በሥሯ ያሉትን ከተሞች እንዲሁም ጊምዞንና በሥሯ ያሉትን ከተሞች ያዙ፤ በዚያም ተቀመጡ። 19 ይሖዋ በእስራኤል ንጉሥ በአካዝ የተነሳ ይሁዳን አዋረደ፤ ምክንያቱም አካዝ የይሁዳን ሰዎች መረን ለቆ ነበር፤ ይህም ንጉሡ ለይሖዋ የነበረውን ታማኝነት በከፍተኛ ሁኔታ እንዲያጓድል አደረገው።
20 በመጨረሻም የአሦር ንጉሥ ቴልጌልቴልፌልሶር+ እሱን ከመርዳት ይልቅ በእሱ ላይ ዘምቶ አስጨነቀው።+ 21 አካዝ የይሖዋን ቤት እንዲሁም የንጉሡን ቤትና*+ የመኳንንቱን ቤቶች አራቁቶ ለአሦር ንጉሥ ስጦታ አበረከተ፤ ይህ ግን ምንም የፈየደለት ነገር የለም። 22 ንጉሥ አካዝ በተጨነቀ ጊዜ በይሖዋ ላይ ታማኝነት የጎደለው ድርጊት መፈጸሙን ይበልጥ ገፋበት። 23 እሱም “የሶርያ ነገሥታት አማልክት እነሱን ስለሚረዷቸው፣ እኔንም እንዲረዱኝ መሥዋዕት አቀርብላቸዋለሁ”+ በማለት ላሸነፉት+ የደማስቆ አማልክት+ መሥዋዕት ያቀርብ ጀመር። ይሁንና እነሱ፣ ለእሱም ሆነ ለመላው እስራኤል እንቅፋት ሆኑ። 24 በተጨማሪም አካዝ የእውነተኛውን አምላክ ቤት ዕቃዎች ሰበሰበ፤ ከዚያም የእውነተኛውን አምላክ ቤት ዕቃዎች ሰባበረ፤+ የይሖዋን ቤት በሮች ዘጋ፤+ በኢየሩሳሌምም በየመንገዱ ማዕዘን ላይ መሠዊያዎችን ለራሱ ሠራ። 25 በይሁዳ ከተሞች ሁሉ ለሌሎች አማልክት የሚጨስ መሥዋዕት የሚቀርቡባቸው ከፍ ያሉ የማምለኪያ ቦታዎችን ሠራ፤+ በዚህም የአባቶቹን አምላክ ይሖዋን አስቆጣ።
26 የቀረው ታሪክ፣ ከመጀመሪያ አንስቶ እስከ መጨረሻ ድረስ ያከናወነው ነገር ሁሉ በይሁዳና በእስራኤል ነገሥታት መጽሐፍ ውስጥ ተጽፏል።+ 27 በመጨረሻም አካዝ ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ እነሱም በኢየሩሳሌም ከተማ ቀበሩት፤ ሆኖም የቀበሩት በእስራኤል ነገሥታት የመቃብር ስፍራ አልነበረም።+ በእሱም ምትክ ልጁ ሕዝቅያስ ነገሠ።
29 ሕዝቅያስ+ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው 25 ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌምም ሆኖ ለ29 ዓመት ገዛ። እናቱ አቢያህ ትባል ነበር፤ እሷም የዘካርያስ ልጅ ነበረች።+ 2 አባቱ ዳዊት እንዳደረገው ሁሉ+ እሱም በይሖዋ ፊት ትክክል የሆነውን ነገር አደረገ።+ 3 መግዛት በጀመረ በመጀመሪያው ዓመት፣ በመጀመሪያው ወር የይሖዋን ቤት በሮች ከፈተ፤ አደሳቸውም።+ 4 ከዚያም ካህናቱንና ሌዋውያኑን አስጠርቶ በምሥራቅ በኩል በሚገኘው አደባባይ ሰበሰባቸው። 5 እንዲህም አላቸው፦ “እናንተ ሌዋውያን፣ ስሙኝ። ራሳችሁንም ሆነ የአባቶቻችሁን አምላክ የይሖዋን ቤት ቀድሱ፤+ ርኩስ የሆነውንም ነገር ከቅዱሱ ስፍራ አስወግዱ።+ 6 አባቶቻችን ታማኞች አልነበሩም፤ በአምላካችን በይሖዋም ፊት ክፉ ነገር አድርገዋል።+ እሱን የተዉት ከመሆኑም ሌላ ከይሖዋ የማደሪያ ድንኳን ፊታቸውን መልሰዋል፤ ጀርባቸውንም ሰጥተውታል።+ 7 በተጨማሪም የበረንዳውን በሮች ዘጉ፤+ መብራቶቹንም አጠፉ።+ ዕጣን ማጠንና+ በተቀደሰው ስፍራ ለእስራኤል አምላክ የሚቃጠል መሥዋዕት ማቅረብ+ አቆሙ። 8 ስለዚህ የይሖዋ ቁጣ በይሁዳና በኢየሩሳሌም ላይ ነደደ፤+ በመሆኑም በገዛ ዓይናችሁ እንደምታዩት መቀጣጫ፣ የሰዎች መደነቂያና ማፏጫ* አደረጋቸው።+ 9 በዚህም የተነሳ አባቶቻችን በሰይፍ ወደቁ፤+ እንዲሁም ወንዶች ልጆቻችን፣ ሴቶች ልጆቻችንና ሚስቶቻችን ተማርከው ተወሰዱ።+ 10 አሁንም የሚነድ ቁጣው ከእኛ እንዲመለስ ከእስራኤል አምላክ ከይሖዋ ጋር ቃል ኪዳን ለመግባት ከልቤ ተመኝቻለሁ።+ 11 እንግዲህ ልጆቼ በፊቱ እንድትቆሙ፣ እንድታገለግሉትና+ የሚጨስ መሥዋዕቱን እንድታቀርቡ+ ይሖዋ የመረጠው እናንተን ስለሆነ አሁን ቸልተኛ የምትሆኑበት* ጊዜ አይደለም።”
12 በዚህ ጊዜ ሌዋውያኑ ለሥራ ተነሱ፤ እነሱም የሚከተሉት ናቸው፦ ከቀአታውያን+ መካከል የአማሳይ ልጅ ማሃት እና የአዛርያስ ልጅ ኢዩኤል፤ ከሜራራውያን+ መካከል የአብዲ ልጅ ቂስ እና የይሃሌልዔል ልጅ አዛርያስ፤ ከጌድሶናውያን+ መካከል የዚማ ልጅ ዮአህ እና የዮአህ ልጅ ኤደን፤ 13 ከኤሊጻፋን ልጆች መካከል ሺምሪ እና የኡዔል፤ ከአሳፍ+ ልጆች መካከል ዘካርያስ እና ማታንያህ፤ 14 ከሄማን+ ልጆች መካከል የሂኤል እና ሺምአይ እንዲሁም ከየዱቱን+ ልጆች መካከል ሸማያህ እና ዑዚኤል። 15 እነሱም ወንድሞቻቸውን ከሰበሰቡና ራሳቸውን ከቀደሱ በኋላ ንጉሡ በይሖዋ ቃል ባዘዛቸው መሠረት የይሖዋን ቤት ለማንጻት መጡ።+ 16 ከዚያም ካህናቱ የይሖዋን ቤት ለማንጻት ወደ ውስጥ ገቡ፤ በይሖዋ ቤተ መቅደስ ውስጥ ያገኙትን ርኩስ የሆነ ነገር ሁሉ አውጥተው ወደ ይሖዋ ቤት ግቢ+ ወሰዱት። ሌዋውያኑ ደግሞ ከዚያ አውጥተው በቄድሮን ሸለቆ+ ውስጥ ጣሉት። 17 እነሱም በዚህ መንገድ በመጀመሪያው ወር፣ በመጀመሪያው ቀን የማንጻት ሥራውን ጀመሩ፤ በወሩም በስምንተኛ ቀን ወደ ይሖዋ ቤት በረንዳ+ ደረሱ። የይሖዋንም ቤት ለስምንት ቀን ቀደሱ፤ በመጀመሪያውም ወር በ16ኛው ቀን ሥራውን አጠናቀቁ።
18 ከዚያም ወደ ንጉሥ ሕዝቅያስ ገብተው እንዲህ አሉት፦ “የይሖዋን ቤት በሙሉ፣ የሚቃጠለው መባ የሚቀርብበትን መሠዊያና+ ዕቃዎቹን በሙሉ+ እንዲሁም የሚነባበረው ዳቦ*+ የሚቀመጥበትን ጠረጴዛና ዕቃዎቹን በሙሉ አንጽተናል። 19 ንጉሥ አካዝ በንግሥና ዘመኑ ታማኝነቱን ባጎደለ ጊዜ+ ከቦታቸው ያስወገዳቸውን ዕቃዎች ሁሉ አዘጋጅተን ቀድሰናቸዋል፤+ ዕቃዎቹም በይሖዋ መሠዊያ ፊት ይገኛሉ።”
20 ንጉሥ ሕዝቅያስም በማለዳ ተነስቶ የከተማዋን መኳንንት ሰበሰበ፤ ከዚያም ወደ ይሖዋ ቤት ወጡ። 21 እነሱም ለመንግሥቱ፣ ለመቅደሱና ለይሁዳ የኃጢአት መባ ሆነው የሚቀርቡ ሰባት በሬዎች፣ ሰባት አውራ በጎች፣ ሰባት ተባዕት የበግ ጠቦቶችና ሰባት ተባዕት ፍየሎች አመጡ።+ እሱም በይሖዋ መሠዊያ ላይ እንዲያቀርቧቸው የአሮን ዘሮች ለሆኑት ካህናት ነገራቸው። 22 ከዚያም ከብቶቹን አረዱ፤+ ካህናቱም ደሙን ወስደው በመሠዊያው ላይ ረጩት፤+ ቀጥሎም አውራ በጎቹን አርደው ደሙን መሠዊያው ላይ ረጩ፤ ተባዕት የበግ ጠቦቶቹንም አርደው ደሙን በመሠዊያው ላይ ረጩ። 23 ከዚያ በኋላ ለኃጢአት መባ የሚሆኑትን ተባዕት ፍየሎች በንጉሡና በጉባኤው ፊት አቀረቧቸው፤ እጆቻቸውንም ጫኑባቸው። 24 ካህናቱም ፍየሎቹን አርደው ለእስራኤል ሁሉ ማስተሰረያ እንዲሆን ደማቸውን በመሠዊያው ላይ የኃጢአት መባ አድርገው አቀረቡ፤ ምክንያቱም ንጉሡ የሚቃጠለው መባና ለኃጢአት የሚሆነው መባ ለመላው እስራኤል እንዲቀርብ አዝዞ ነበር።
25 እሱም በዳዊት፣+ የንጉሡ ባለ ራእይ በሆነው በጋድና+ በነቢዩ ናታን+ በተሰጠው ትእዛዝ መሠረት ሌዋውያኑን ሲምባል፣ ባለ አውታር መሣሪያዎችና በገና+ አስይዞ በይሖዋ ቤት እንዲቆሙ አደረገ፤ ይህም ይሖዋ በነቢያቱ አማካኝነት የሰጠው ትእዛዝ ነበር። 26 በመሆኑም ሌዋውያኑ የዳዊትን የሙዚቃ መሣሪያዎች፣ ካህናቱ ደግሞ መለከቶችን+ ይዘው ቆሙ።
27 ከዚያም ሕዝቅያስ የሚቃጠለው መሥዋዕት በመሠዊያው ላይ እንዲቀርብ አዘዘ።+ የሚቃጠለው መባ መቅረብ በጀመረበት ጊዜ የይሖዋ መዝሙር ተሰማ፤ ደግሞም የእስራኤልን ንጉሥ የዳዊትን የሙዚቃ መሣሪያዎች ተከትለው መለከቶቹ ተነፉ። 28 መዝሙሩ በሚዘመርበትና መለከቶቹ በሚነፉበት ጊዜም መላው ጉባኤ ተደፍቶ ሰገደ፤ የሚቃጠለው መባ እስኪጠናቀቅ ድረስ ይህ ሁሉ መከናወኑን ቀጠለ። 29 መባውን አቅርበው እንደጨረሱም ንጉሡና አብረውት ያሉት ሁሉ በግንባራቸው ተደፍተው ሰገዱ። 30 ንጉሥ ሕዝቅያስና መኳንንቱ በዳዊትና+ በባለ ራእዩ በአሳፍ+ መዝሙራት ይሖዋን እንዲያወድሱ ሌዋውያኑን አዘዙ። እነሱም በታላቅ ደስታ ውዳሴ አቀረቡ፤ ተደፍተውም ሰገዱ።
31 ከዚያም ሕዝቅያስ እንዲህ አለ፦ “አሁን እናንተ ለይሖዋ ስለተለያችሁ* ቅረቡ፤ ለይሖዋም ቤት መሥዋዕቶችና የምስጋና መባዎች አምጡ።” በመሆኑም ጉባኤው መሥዋዕቶችንና የምስጋና መባዎችን ማምጣት ጀመረ፤ ልቡ ያነሳሳውም ሁሉ የሚቃጠል መባ አመጣ።+ 32 ጉባኤው ያመጣቸው የሚቃጠሉ መባዎች ብዛት 70 ከብቶች፣ 100 አውራ በጎችና 200 ተባዕት የበግ ጠቦቶች ነበሩ፤ እነዚህ ሁሉ ለይሖዋ የሚቃጠል መባ+ ሆነው የሚቀርቡ ነበሩ፤ 33 ሌሎቹ ቅዱስ መባዎች ደግሞ 600 ከብቶችና 3,000 በጎች ነበሩ። 34 ይሁንና የሚቃጠል መባ ሆነው የሚቀርቡትን እንስሳት ሁሉ ለመግፈፍ በቂ ካህናት ስላልነበሩ ሥራው እስኪጠናቀቅና ካህናቱ ራሳቸውን እስኪቀድሱ+ ድረስ ወንድሞቻቸው የሆኑት ሌዋውያን ረዷቸው፤+ ሌዋውያኑ ራሳቸውን በመቀደስ ረገድ ከካህናቱ ይበልጥ ጠንቃቆች* ነበሩና። 35 በተጨማሪም የሚቃጠሉት መባዎችና+ የኅብረት መሥዋዕቶቹ+ ስብ እንዲሁም ከሚቃጠሉት መባዎች ጋር የሚቀርቡት የመጠጥ መባዎች+ ብዙ ነበሩ። በዚህ መንገድ የይሖዋ ቤት አገልግሎት እንደገና ተደራጀ።* 36 ሕዝቅያስና ሕዝቡ ሁሉ እውነተኛው አምላክ ለሕዝቡ ይህን በማቋቋሙና ይህ ሁሉ ነገር በአጭር ጊዜ ውስጥ በመከናወኑ እጅግ ተደሰቱ።+
30 ሕዝቅያስ ለእስራኤል አምላክ ለይሖዋ ፋሲካን*+ ለማክበር በኢየሩሳሌም ወደሚገኘው ወደ ይሖዋ ቤት እንዲመጡ ለእስራኤልና ለይሁዳ ሁሉ መልእክት ላከ፤+ ለኤፍሬምና ለምናሴም እንኳ ሳይቀር ደብዳቤ ጻፈ።+ 2 ይሁን እንጂ ንጉሡና መኳንንቱ እንዲሁም በኢየሩሳሌም ያለው መላው ጉባኤ ፋሲካን በሁለተኛው ወር ለማክበር ወሰኑ፤+ 3 በቂ ካህናት ራሳቸውን ስላልቀደሱና+ ሕዝቡ ገና በኢየሩሳሌም ስላልተሰበሰበ ፋሲካውን በመደበኛው ጊዜ ማክበር አልቻሉም ነበር።+ 4 ይህ ዝግጅት በንጉሡና በመላው ጉባኤ ፊት ተቀባይነት አገኘ። 5 ስለዚህ ሕዝቡ ወደ ኢየሩሳሌም መጥቶ ለእስራኤል አምላክ ለይሖዋ ፋሲካን እንዲያከብር በመላው እስራኤል፣ ከቤርሳቤህ አንስቶ እስከ ዳን+ ድረስ አዋጅ እንዲነገር ወሰኑ፤ በተጻፈው መሠረት በዓሉን በጋራ አክብረው አያውቁም ነበር።+
6 ከዚያም መልእክተኞቹ* የንጉሡንና የመኳንንቱን ደብዳቤዎች ይዘው ወደ እስራኤልና ወደ ይሁዳ ሁሉ ሄዱ፤ ንጉሡም እንዲህ የሚል ትእዛዝ አስተላልፎ ነበር፦ “የእስራኤል ሕዝብ ሆይ፣ የአብርሃም፣ የይስሐቅና የእስራኤል አምላክ ወደሆነው ወደ ይሖዋ ተመለሱ፤ እሱም ከአሦር ነገሥታት እጅ ወዳመለጡት ቀሪዎች ይመለሳል።+ 7 አሁን እንደምታዩት፣ መቀጣጫ እስኪያደርጋቸው ድረስ በአባቶቻቸው አምላክ በይሖዋ ላይ ታማኝነት የጎደለው ድርጊት እንደፈጸሙት እንደ አባቶቻችሁና እንደ ወንድሞቻችሁ አትሁኑ።+ 8 አሁንም እንደ አባቶቻችሁ አንገታችሁን አታደንድኑ።+ የሚነድ ቁጣው ከእናንተ እንዲመለስ ለይሖዋ ተገዙ፤+ ለዘላለም ወደቀደሰው መቅደሱ ኑ፤+ አምላካችሁን ይሖዋን አገልግሉ። 9 ወደ ይሖዋ ስትመለሱ ወንድሞቻችሁና ልጆቻችሁ በማረኳቸው ዘንድ ምሕረት ያገኛሉ፤+ ወደዚህች ምድር እንዲመለሱም ይለቋቸዋል፤+ አምላካችሁ ይሖዋ ሩኅሩኅና* መሐሪ ነውና፤+ ወደ እሱም ከተመለሳችሁ ፊቱን አያዞርባችሁም።”+
10 ስለዚህ መልእክተኞቹ* ከከተማ ወደ ከተማ እየተዘዋወሩ የኤፍሬምንና የምናሴን+ እንዲሁም የዛብሎንን አገር ሁሉ አዳረሱ፤ ሕዝቡ ግን ያፌዝባቸውና ይሳለቅባቸው ነበር።+ 11 ይሁን እንጂ ከአሴር፣ ከምናሴና ከዛብሎን ምድር የተወሰኑ ሰዎች ራሳቸውን ዝቅ አድርገው ወደ ኢየሩሳሌም መጡ።+ 12 በተጨማሪም የእውነተኛው አምላክ እጅ ከይሁዳ ሰዎች ጋር ስለነበር ንጉሡና መኳንንቱ በይሖዋ ቃል መሠረት ያስተላለፉትን ትእዛዝ እንዲፈጽሙ አንድ ልብ ሰጣቸው።
13 በሁለተኛው ወር+ የቂጣን በዓል+ ለማክበር እጅግ ብዙ ሕዝብ በኢየሩሳሌም ተሰበሰበ፤ ጉባኤው እጅግ ታላቅ ነበር። 14 እነሱም ተነስተው በኢየሩሳሌም የነበሩትን መሠዊያዎችና የዕጣን መሠዊያዎች ከነቃቀሉ+ በኋላ በቄድሮን ሸለቆ ውስጥ ጣሏቸው። 15 ከዚያም በሁለተኛው ወር በ14ኛው ቀን የፋሲካን መሥዋዕት አረዱ። ካህናቱና ሌዋውያኑ አፍረው ስለነበር ራሳቸውን ቀደሱ፤ ወደ ይሖዋም ቤት የሚቃጠል መባ አመጡ። 16 በእውነተኛው አምላክ ሰው በሙሴ ሕግ መሠረት የተሰጣቸውን መመሪያ ተከትለው መደበኛ ቦታቸውን ያዙ፤ ከዚያም ካህናቱ ከሌዋውያኑ እጅ የተቀበሉትን ደም ረጩ።+ 17 በጉባኤው መካከል ራሳቸውን ያልቀደሱ ብዙ ሰዎች ስለነበሩ ሌዋውያኑ ያልነጹትን ሰዎች+ ለይሖዋ ለመቀደስ የፋሲካን መሥዋዕት የማረድ ኃላፊነት ተጥሎባቸው ነበር። 18 እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ በተለይም ከኤፍሬም፣ ከምናሴ፣+ ከይሳኮርና ከዛብሎን የመጡ ሰዎች ራሳቸውን ያላነጹ ቢሆንም የተጻፈውን መመሪያ ተላልፈው ፋሲካውን በሉ። ይሁንና ሕዝቅያስ እንዲህ ሲል ጸለየላቸው፦ “ጥሩ የሆነው+ ይሖዋ ይቅር ይበል፤ 19 የቅድስናውን መሥፈርት አሟልተው ራሳቸውን ባያነጹም+ እንኳ እውነተኛ አምላክ የሆነውን የአባቶቻቸውን አምላክ ይሖዋን ለመፈለግ ልባቸውን ያዘጋጁትን+ ሁሉ ይቅር ይበላቸው።” 20 ይሖዋም ሕዝቅያስን ሰምቶ ሕዝቡን ይቅር አለ።*
21 በመሆኑም በኢየሩሳሌም የተገኙት እስራኤላውያን የቂጣን በዓል+ ለሰባት ቀናት በታላቅ ደስታ አከበሩ፤+ ሌዋውያኑና ካህናቱም ከፍ ባለ ድምፅ ለይሖዋ የሙዚቃ መሣሪያዎቻቸውን በመጫወት በየዕለቱ ይሖዋን ያወድሱ ነበር።+ 22 በተጨማሪም ሕዝቅያስ ይሖዋን በማስተዋል ያገለግሉ የነበሩትን ሌዋውያን ሁሉ በማነጋገር አበረታታቸው።* እነሱም የኅብረት መሥዋዕቶች+ በማቅረብና ለአባቶቻቸው አምላክ ለይሖዋ ምስጋና በማቅረብ በዓሉ ተጀምሮ እስኪያበቃ ድረስ ለሰባት ቀናት በሉ።+
23 ከዚያም መላው ጉባኤ ለተጨማሪ ሰባት ቀናት በዓሉን ለማክበር ወሰነ፤ በመሆኑም እንደገና ለሰባት ቀናት በዓሉን በታላቅ ደስታ አከበሩ።+ 24 የይሁዳ ንጉሥ ሕዝቅያስም 1,000 በሬዎችና 7,000 በጎች ለጉባኤው ሰጥቶ ነበር፤ መኳንንቱ ደግሞ 1,000 በሬዎችና 10,000 በጎች ለጉባኤው አበረከቱ፤+ እጅግ ብዙ ካህናትም ራሳቸውን ቀደሱ።+ 25 መላው የይሁዳ ጉባኤ፣ ካህናቱ፣ ሌዋውያኑ፣ ከእስራኤል የመጣው መላው ጉባኤ+ እንዲሁም ከእስራኤል ምድር የመጡትና በይሁዳ የሚኖሩት የባዕድ አገር ሰዎች+ እጅግ ተደሰቱ። 26 ከእስራኤል ንጉሥ ከዳዊት ልጅ ከሰለሞን ዘመን አንስቶ በኢየሩሳሌም እንዲህ ያለ ነገር ሆኖ ስለማያውቅ በኢየሩሳሌም ታላቅ ደስታ ሆነ።+ 27 በመጨረሻም ሌዋውያኑ ካህናት ተነስተው ሕዝቡን ባረኩ፤+ አምላክም ድምፃቸውን ሰማ፤ ጸሎታቸውም ወደ ቅዱሱ መኖሪያው ወደ ሰማያት ደረሰ።
31 ከዚህ በኋላ በዚያ የተገኙት እስራኤላውያን በሙሉ ወደ ይሁዳ ከተሞች ወጥተው በመላው ይሁዳና ቢንያም እንዲሁም በኤፍሬምና በምናሴ+ የነበሩትን የማምለኪያ ዓምዶች+ ሰባበሩ፤ የማምለኪያ ግንዶቹን*+ ቆረጡ፤ ከፍ ያሉትንም የማምለኪያ ቦታዎችና+ መሠዊያዎቹን+ አፈራረሱ፤ ምንም ያስቀሩት ነገር አልነበረም፤ ከዚህ በኋላ እስራኤላውያን በሙሉ ወደየከተሞቻቸው፣ እያንዳንዳቸውም ወደየርስታቸው ተመለሱ።
2 ከዚያም ሕዝቅያስ ካህናቱን በየምድባቸው፣+ ሌዋውያኑንም በየምድባቸው+ ሾማቸው፤ እያንዳንዱን ካህንና ሌዋዊ በተሰጠው ሥራ መሠረት ደለደለ።+ እነሱም የሚቃጠለውን መባና የኅብረት መሥዋዕቶቹን ያቀርባሉ፣ ያገለግላሉ እንዲሁም በይሖዋ ቤተ መቅደስ ዙሪያ ባሉት የግቢዎቹ* በሮች ለእሱ ምስጋናና ውዳሴ ያቀርባሉ።+ 3 በይሖዋ ሕግ ላይ በተጻፈው መሠረት ጠዋትና ማታ የሚቀርበውን መባ+ እንዲሁም በየሰንበቱ፣+ በየወር መባቻውና+ በበዓላት ወቅት+ የሚቀርቡትን የሚቃጠሉ መባዎች ጨምሮ ለሚቃጠሉት መባዎች+ እንዲውል ከንጉሡ ንብረት ላይ የተወሰነ ድርሻ ይሰጥ ነበር።
4 በተጨማሪም ሕዝቅያስ የይሖዋን ሕግ በጥብቅ መከተል* እንዲችሉ በኢየሩሳሌም የሚኖረው ሕዝብ ለካህናቱና ለሌዋውያኑ ተገቢውን ድርሻ እንዲሰጥ አዘዘ።+ 5 ትእዛዙ እንደወጣ እስራኤላውያን የእህሉን፣ የአዲሱን የወይን ጠጅ፣ የዘይቱን፣+ የማሩንና የእርሻውን ፍሬ+ ሁሉ በኩራት በብዛት ሰጡ፤ ከእያንዳንዱም ነገር ላይ አንድ አሥረኛውን አትረፍርፈው አመጡ።+ 6 በይሁዳ ከተሞች ይኖሩ የነበሩት የእስራኤልና የይሁዳ ሕዝብም ከከብቶቻቸውና ከበጎቻቸው አንድ አሥረኛውን እንዲሁም ለአምላካቸው ለይሖዋ ከተለዩት ቅዱስ የሆኑ ነገሮች ላይ አንድ አሥረኛውን አመጡ።+ ያመጡትንም ብዙ ቦታ ላይ ቆለሉት። 7 በሦስተኛው ወር+ ያመጡትን መዋጮ መከመር የጀመሩ ሲሆን በሰባተኛው ወር+ አጠናቀቁ። 8 ሕዝቅያስና መኳንንቱ መጥተው ክምሩን ባዩ ጊዜ ይሖዋን አወደሱ፤ ሕዝቡን እስራኤልንም ባረኩ።
9 ሕዝቅያስ ካህናቱንና ሌዋውያኑን ስለ ክምሩ ሲጠይቃቸው 10 ከሳዶቅ ቤት የሆነው የካህናት አለቃው አዛርያስ እንዲህ አለው፦ “መዋጮውን ወደ ይሖዋ ቤት ማምጣት+ ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ ሕዝቡ እስኪጠግብ ድረስ ሲበላ ቆይቷል፤ ገና ያልተነካ ብዙ ነገር አለ፤ ይሖዋ ሕዝቡን ስለባረከ ይህን ያህል ብዛት ያለው ነገር ሊተርፍ ችሏል።”+
11 በዚህ ጊዜ ሕዝቅያስ በይሖዋ ቤት ማከማቻ ክፍሎች*+ እንዲያዘጋጁ አዘዘ፤ እነሱም አዘጋጁ። 12 ከዚያም መዋጮውን፣ አንድ አሥረኛውንና*+ ቅዱስ የሆኑትን ነገሮች በታማኝነት ማምጣታቸውን ቀጠሉ፤ ሌዋዊው ኮናንያ የእነዚህ ሁሉ ነገሮች ተቆጣጣሪ ሆኖ ተሹሞ የነበረ ሲሆን ወንድሙ ሺምአይ ደግሞ የእሱ ምክትል ነበር። 13 የሂኤል፣ አዛዝያ፣ ናሃት፣ አሳሄል፣ የሪሞት፣ ዮዛባድ፣ ኤሊዔል፣ ይስማክያ፣ ማሃት እና በናያህ በንጉሥ ሕዝቅያስ ትእዛዝ ኮናንያን እና ወንድሙን ሺምአይን የሚረዱ ሹሞች ነበሩ፤ አዛርያስም የእውነተኛው አምላክ ቤት ተቆጣጣሪ ነበር። 14 የምሥራቁ በር ጠባቂ የሆነው ሌዋዊው+ የይምናህ ልጅ ቆረ ለእውነተኛው አምላክ በበጎ ፈቃድ የሚቀርቡትን መባዎች+ ይቆጣጠር ነበር፤ ደግሞም ለይሖዋ የተሰጠውን መዋጮና+ እጅግ ቅዱስ የሆኑትን ነገሮች+ ያከፋፍል ነበር። 15 በእሱም አመራር ሥር ኤደን፣ ሚንያሚን፣ የሹዋ፣ ሸማያህ፣ አማርያህ እና ሸካንያህ የነበሩ ሲሆን በየምድቦቹ ውስጥ ላሉት ወንድሞቻቸው፣+ ለትልቁም ሆነ ለትንሹ ድርሻቸውን እኩል ለማከፋፈል በካህናቱ ከተሞች+ ታማኝነት በሚጠይቅ ቦታ ላይ ተሹመው ነበር። 16 ይህም ስማቸው በትውልድ ሐረግ መዝገቡ ላይ ለሰፈሩት ሦስት ዓመትና ከዚያ በላይ ለሆናቸው ወንዶች የሚከፋፈለውን ሳይጨምር ነው፤ እነሱም በይሖዋ ቤት ለማገልገል በየዕለቱ ይመጡና እንደየምድባቸው ያሉባቸውን ኃላፊነቶች ይፈጽሙ ነበር።
17 ካህናቱ፣ 20 ዓመትና ከዚያ በላይ+ እንደሆናቸው ሌዋውያን ሁሉ በትውልድ ሐረግ መዝገቡ ላይ የሰፈሩት በየአባቶቻቸው ቤት+ እንደየምድብ ሥራቸው ነበር።+ 18 የትውልድ ሐረግ መዝገቡ ልጆቻቸውን፣ ሚስቶቻቸውን፣ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን በሙሉ፣ መላውን የሌዋውያን ማኅበረሰብ ይጨምራል፤ እነሱ በተሾሙበት ታማኝነት የሚጠይቅ ቦታ የተነሳ ቅዱስ ለሆነው ነገር ራሳቸውን ቀድሰዋል፤ 19 በተጨማሪም መዝገቡ ላይ በከተሞቻቸው ዙሪያ ባሉ የግጦሽ መሬቶች ላይ የሚኖሩት የአሮን ዘሮች የሆኑት ካህናትም ይገኛሉ።+ በሁሉም ከተሞች ውስጥ በካህናት ቤተሰብ ውስጥ ላሉት ወንዶች ሁሉና በሌዋውያን የትውልድ ሐረግ መዝገብ ላይ ለተጻፉት በሙሉ እንዲያከፋፍሉ በስም ተጠቅሰው ኃላፊነት የተሰጣቸው ወንዶች ነበሩ።
20 ሕዝቅያስ በመላው ይሁዳ ይህን አደረገ፤ በአምላኩ በይሖዋም ፊት ጥሩና ትክክል የሆነውን አደረገ፤ ለእሱም ታማኝ ነበር። 21 ከእውነተኛው አምላክ ቤት+ አገልግሎት ጋርም ሆነ ከሕጉና ከትእዛዙ ጋር በተያያዘ አምላኩን ይፈልግ ዘንድ የጀመረውን ሥራ ሁሉ፣ በሙሉ ልቡ አከናወነ፤ ደግሞም ተሳካለት።
32 እነዚህ ነገሮች ከተከናወኑና ሕዝቅያስ በታማኝነት ሲመላለስ+ ከቆየ በኋላ የአሦር ንጉሥ ሰናክሬም መጥቶ ይሁዳን ወረረ። ቅጥራቸውን አፍርሶ ለመያዝ ስላሰበ የተመሸጉትን ከተሞች ከበበ።+
2 ሕዝቅያስ ሰናክሬም ኢየሩሳሌምን ለመውጋት አስቦ እንደመጣ ባየ ጊዜ፣ 3 ከመኳንንቱና ከተዋጊዎቹ ጋር ተማክሮ ከከተማዋ ውጭ ያሉትን የውኃ ምንጮች ለመድፈን ወሰነ፤+ እነሱም ረዱት። 4 ብዙ ሰዎች ተሰብስበው “የአሦር ነገሥታት መጥተው ለምን ብዙ ውኃ ያግኙ?” በማለት ምንጮቹንና በምድሪቱ መካከል የሚፈሰውን ጅረት በሙሉ ደፈኑ።
5 በተጨማሪም ሕዝቅያስ በትጋት በመሥራት የፈረሰውን ቅጥር በሙሉ ገነባ፤ በላዩም ላይ ማማዎችን ሠራ፤ ከውጭ በኩልም ሌላ ቅጥር ገነባ። ደግሞም የዳዊትን ከተማ ጉብታ*+ ጠገነ፤ እንዲሁም ብዙ የጦር መሣሪያዎችና* ጋሻዎች ሠራ። 6 ከዚያም በሕዝቡ ላይ የጦር አለቆችን ሾሞ በከተማዋ በር በሚገኘው አደባባይ ሰበሰባቸው፤ እንዲህም በማለት አበረታታቸው፦* 7 “ደፋርና ብርቱዎች ሁኑ። ከአሦር ንጉሥና ከእሱ ጋር ካለው ብዙ ሠራዊት የተነሳ አትፍሩ ወይም አትሸበሩ፤+ ከእሱ ጋር ካሉት ይልቅ ከእኛ ጋር ያሉት ይበልጣሉ።+ 8 ከእሱ ጋር ያለው የሥጋ ክንድ* ሲሆን ከእኛ ጋር ያለው ግን አምላካችን ይሖዋ ነው፤ እሱ ይረዳናል፤ ደግሞም ይዋጋልናል።”+ ሕዝቡም የይሁዳ ንጉሥ ሕዝቅያስ በተናገረው ቃል ተበረታታ።+
9 ከዚህ በኋላ የአሦር ንጉሥ ሰናክሬም ከሠራዊቱ ሁሉ* ጋር በለኪሶ+ ሳለ አገልጋዮቹን ወደ ኢየሩሳሌም ይኸውም ወደ ይሁዳ ንጉሥ ወደ ሕዝቅያስና በኢየሩሳሌም ወደሚኖሩት አይሁዳውያን+ ሁሉ እንዲህ ሲል ላከ፦
10 “የአሦር ንጉሥ ሰናክሬም እንዲህ ይላል፦ ‘ኢየሩሳሌም ተከባ ሳለ ከከተማዋ ሳትወጡ የቀራችሁት በምን ተማምናችሁ ነው?+ 11 ሕዝቅያስ “አምላካችን ይሖዋ ከአሦር ንጉሥ እጅ ይታደገናል” እያለ እናንተን በማታለል በረሃብና በጥም እንድትሞቱ አሳልፎ ሊሰጣችሁ አይደለም?+ 12 የአምላካችሁን* ከፍ ያሉ የማምለኪያ ቦታዎችና+ መሠዊያዎች+ ካስወገደ በኋላ ይሁዳንና ኢየሩሳሌምን “በአንድ መሠዊያ ፊት ስገዱ፤ በዚያም ላይ የሚጨስ መሥዋዕት አቅርቡ” ያለው ሕዝቅያስ ራሱ አይደለም?+ 13 እኔም ሆንኩ አባቶቼ በተለያዩ አገሮች ሕዝቦች ሁሉ ላይ ያደረግነውን አታውቁም?+ የእነዚህ አገሮች ሕዝቦች አማልክት ምድራቸውን ከእጄ መታደግ ችለዋል?+ 14 አባቶቼ ፈጽመው ካጠፏቸው ከእነዚህ ብሔራት አማልክት ሁሉ መካከል ሕዝቡን ከእጄ መታደግ የቻለ የትኛው ነው? ታዲያ የእናንተስ አምላክ ቢሆን ከእጄ ሊታደጋችሁ ይችላል?+ 15 አሁንም ሕዝቅያስ በዚህ መንገድ አያታላችሁ ወይም አያሳስታችሁ!+ አትመኑት፤ የየትኛውም ብሔርም ሆነ መንግሥት አምላክ ከእኔና ከአባቶቼ እጅ ሕዝቡን መታደግ አልቻለም። የእናንተ አምላክማ ከእጄ ይታደጋችሁ ዘንድ ምንኛ ያንስ!’”+
16 የሰናክሬም አገልጋዮች በእውነተኛው አምላክ በይሖዋና በአገልጋዩ በሕዝቅያስ ላይ ሌላ ብዙ ነገር ተናገሩ። 17 በተጨማሪም ንጉሡ የእስራኤልን አምላክ ይሖዋን ለመስደብና+ እሱን ለማቃለል እንዲህ ሲል ደብዳቤ ጻፈ፦+ “የሌሎች ብሔራት አማልክት ሕዝባቸውን ከእጄ መታደግ እንዳልቻሉ ሁሉ+ የሕዝቅያስም አምላክ ሕዝቡን ከእጄ ሊታደግ አይችልም።” 18 በቅጥሩ ላይ ያሉትን የኢየሩሳሌም ሰዎች በማስፈራራትና በማሸበር ከተማዋን ለመያዝ ሲሉ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው በአይሁዳውያን ቋንቋ ለሰዎቹ መናገራቸውን ቀጠሉ።+ 19 የሰው እጅ ሥራ በሆኑት በሌሎች የምድር ሕዝቦች አማልክት ላይ እንደተናገሩ ሁሉ፣ በኢየሩሳሌም አምላክ ላይም ተናገሩ። 20 ንጉሥ ሕዝቅያስና የአሞጽ ልጅ ነቢዩ ኢሳይያስ+ ግን ይህን ጉዳይ በተመለከተ አጥብቀው ጸለዩ፤ እርዳታ ለማግኘትም ወደ ሰማይ ጮኹ።+
21 ከዚያም ይሖዋ አንድ መልአክ ልኮ በአሦር ንጉሥ ሰፈር የነበሩትን ኃያላን ተዋጊዎች+ እንዲሁም መሪዎችና አለቆች ሁሉ ጠራርጎ አጠፋ፤ ንጉሡም ኀፍረት ተከናንቦ ወደ ገዛ አገሩ ተመለሰ። በኋላም ወደ አምላኩ ቤት ገባ፤* በዚያም ሳለ የገዛ ወንዶች ልጆቹ በሰይፍ ገደሉት።+ 22 በዚህ መንገድ ይሖዋ ሕዝቅያስንና የኢየሩሳሌምን ነዋሪዎች ከአሦር ንጉሥ ከሰናክሬም እጅና ከሌሎች ሁሉ እጅ አዳናቸው፤ በዙሪያቸውም ካሉ ጠላቶቻቸው ሁሉ እረፍት ሰጣቸው። 23 ብዙዎችም ለይሖዋ ስጦታ፣ ለይሁዳ ንጉሥ ለሕዝቅያስም ምርጥ የሆኑ ነገሮች ይዘው ወደ ኢየሩሳሌም መጡ፤+ እሱም ከዚያ በኋላ በብሔራት ሁሉ ዘንድ ታላቅ አክብሮት አተረፈ።
24 በዚያን ጊዜ ሕዝቅያስ በጠና ታሞ ሞት አፋፍ ደርሶ ነበር፤ ወደ ይሖዋም ጸለየ፤+ እሱም መለሰለት፤ ምልክትም* ሰጠው።+ 25 ይሁንና ሕዝቅያስ ልቡ ታብዮ ስለነበር ለተደረገለት መልካም ነገር አድናቆት ሳያሳይ ቀረ፤ የአምላክም ቁጣ በእሱ፣ በይሁዳና በኢየሩሳሌም ላይ መጣ። 26 ይሁን እንጂ ሕዝቅያስ ስለ ልቡ ትዕቢት ራሱን ዝቅ አደረገ፤+ እሱና የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ትሕትና አሳዩ፤ የይሖዋም ቁጣ በሕዝቅያስ ዘመን አልመጣባቸውም።+
27 ሕዝቅያስም እጅግ ብዙ ሀብት አገኘ፤ ታላቅ ክብርም ተጎናጸፈ፤+ ብሩን፣ ወርቁን፣ የከበሩ ድንጋዮቹን፣ የበለሳን ዘይቱን፣ ጋሻዎቹንና ውድ የሆኑትን ዕቃዎች ሁሉ የሚያስቀምጥባቸው ግምጃ ቤቶች ሠራ።+ 28 በተጨማሪም ለእህሉ፣ ለአዲሱ የወይን ጠጅና ለዘይቱ የማከማቻ ቦታዎች አዘጋጀ፤ እንዲሁም ለተለያዩ እንስሳት በረት፣ ለበጎችና ለፍየሎች ደግሞ ጉረኖ ሠራ። 29 ለራሱም ከተሞችን ገነባ፤ እጅግ ብዙ ከብቶች፣ መንጎችና እንስሳት ነበሩት፤ አምላክ ብዙ ንብረት ሰጥቶት ነበር። 30 የግዮንን+ ውኃ የላይኛውን መውጫ ደፍኖ+ ውኃው በምዕራብ በኩል በቀጥታ ወደ ዳዊት ከተማ+ እንዲወርድ ያደረገው ሕዝቅያስ ነበር፤ ሥራውም ሁሉ ተሳካለት። 31 ይሁንና የባቢሎን መኳንንት ቃል አቀባዮች በምድሪቱ ላይ ስለተከሰተው+ ምልክት* እንዲጠይቁት+ ወደ እሱ በተላኩ ጊዜ እውነተኛው አምላክ እሱን ለመፈተንና+ በልቡ ያለውን ሁሉ ለማወቅ+ ሲል ተወው።
32 የቀረው የሕዝቅያስ ታሪክና ያሳየው ታማኝ ፍቅር+ የአሞጽ ልጅ ነቢዩ ኢሳይያስ ባየው ራእይ ላይ፣+ በይሁዳና በእስራኤል ነገሥታት መጽሐፍ ተጽፏል።+ 33 በመጨረሻም ሕዝቅያስ ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ ወደ ዳዊት ልጆች የመቃብር ስፍራ በሚወስድ ከፍ ያለ ቦታ ላይ ቀበሩት፤+ በሞተበት ጊዜም መላው ይሁዳና የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች አከበሩት። በእሱም ምትክ ልጁ ምናሴ ነገሠ።
33 ምናሴ+ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው 12 ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌምም ሆኖ 55 ዓመት ገዛ።+
2 እሱም ይሖዋ ከእስራኤል ሕዝብ ፊት ያባረራቸው ብሔራት ይፈጽሟቸው የነበሩትን አስጸያፊ ልማዶች በመከተል በይሖዋ ፊት መጥፎ የሆነውን ነገር አደረገ።+ 3 አባቱ ሕዝቅያስ አፍርሷቸው የነበሩትን ከፍ ያሉ የማምለኪያ ቦታዎች መልሶ ገነባ፣+ ለባአል አማልክት መሠዊያዎችን አቆመ፣ የማምለኪያ ግንዶች* ሠራ እንዲሁም ለሰማይ ሠራዊት ሁሉ ሰገደ፤ እነሱንም አገለገለ።+ 4 በተጨማሪም ይሖዋ “ኢየሩሳሌም ለዘላለም በስሜ ትጠራለች”+ ብሎ በተናገረለት በይሖዋ ቤት ውስጥ መሠዊያዎችን ሠራ።+ 5 ደግሞም በይሖዋ ቤት በሚገኙት በሁለቱ ግቢዎች ውስጥ ለሰማይ ሠራዊት ሁሉ መሠዊያዎችን ሠራ።+ 6 በሂኖም ልጅ ሸለቆም+ የገዛ ልጆቹን ለእሳት አሳልፎ ሰጠ፤+ አስማተኛ፣+ ሟርተኛና መተተኛ ሆነ፤ መናፍስት ጠሪዎችንና ጠንቋዮችን ቀጠረ።+ ይሖዋን ያስቆጣው ዘንድ በእሱ ፊት በጣም ብዙ መጥፎ ነገሮችን ሠራ።
7 ምናሴም የሠራውን የተቀረጸ ምስል አምላክ ለዳዊትና ለልጁ ለሰለሞን እንዲህ ብሎ በተናገረለት በእውነተኛው አምላክ ቤት ውስጥ አስቀመጠው፦+ “በዚህ ቤትና ከእስራኤል ነገዶች ሁሉ በመረጥኳት በኢየሩሳሌም ስሜን ለዘለቄታው አኖራለሁ።+ 8 እነሱ በሙሴ በኩል የሰጠኋቸውን ሕግ ሁሉ እንዲሁም ሥርዓቶቹንና ድንጋጌዎቹን በጥንቃቄ ይጠብቁ እንጂ የእስራኤላውያን እግር ለአባቶቻቸው ከሰጠሁት ምድር ዳግመኛ እንዲወጣ አላደርግም።” 9 ምናሴም ይሖዋ ከእስራኤላውያን ፊት ካጠፋቸው ብሔራት የባሰ ክፉ ነገር እንዲሠሩ የይሁዳንና የኢየሩሳሌምን ነዋሪዎች አሳተ።+
10 ይሖዋ ለምናሴና ለሕዝቡ በተደጋጋሚ ቢናገርም እነሱ ለመስማት ፈቃደኛ አልሆኑም።+ 11 ስለዚህ ይሖዋ የአሦርን ንጉሥ ሠራዊት አለቆች አመጣባቸው፤ እነሱም ምናሴን በመንጠቆ ያዙት፤* ከመዳብ በተሠሩ ሁለት የእግር ብረቶች አስረው ወደ ባቢሎን ወሰዱት። 12 በተጨነቀም ጊዜ ሞገስ እንዲያሳየው አምላኩን ይሖዋን ለመነ፤ በአባቶቹም አምላክ ፊት ራሱን እጅግ አዋረደ። 13 ወደ እሱ አጥብቆ ጸለየ፤ እሱም ተለመነው፤ በእሱ ዘንድ ሞገስ ለማግኘት ያቀረበውንም ልመና ሰማው፤ ወደ ኢየሩሳሌም፣ ወደ ንግሥናው መለሰው።+ ከዚያም ምናሴ፣ ይሖዋ እውነተኛ አምላክ እንደሆነ አወቀ።+
14 ከዚህ በኋላ በሸለቆው ውስጥ ከሚገኘው* ከግዮን+ በስተ ምዕራብ አንስቶ እስከ ዓሣ በር+ ድረስ ለዳዊት ከተማ+ በውጭ በኩል ቅጥር ሠራ። ቅጥሩ ከዚያ ተነስቶ ከተማዋን በመዞር እስከ ኦፌል+ የሚደርስ ሲሆን እጅግ ከፍ አድርጎ ሠራው። በተጨማሪም በተመሸጉ የይሁዳ ከተሞች ሁሉ ላይ የጦር አለቆች ሾመ። 15 ከዚያም ባዕዳን አማልክቱንና የጣዖቱን ምስል ከይሖዋ ቤት አስወገደ፤+ ደግሞም በይሖዋ ቤት ተራራ ላይና በኢየሩሳሌም የሠራቸውን መሠዊያዎች ሁሉ አፍርሶ ከከተማዋ ውጭ እንዲጣሉ አደረገ።+ 16 በተጨማሪም የይሖዋን መሠዊያ አድሶ+ በላዩ ላይ የኅብረት መሥዋዕቶችና+ የምስጋና መሥዋዕቶች+ ያቀርብ ጀመር፤ የይሁዳም ሰዎች የእስራኤልን አምላክ ይሖዋን እንዲያገለግሉ አዘዘ። 17 ያም ሆኖ ሕዝቡ ከፍ ባሉት የማምለኪያ ቦታዎቹ ላይ መሠዋታቸውን አልተዉም፤ የሚሠዉት ግን ለአምላካቸው ለይሖዋ ነበር።
18 የቀረው የምናሴ ታሪክ፣ ለአምላኩ ያቀረበው ጸሎትና በእስራኤል አምላክ በይሖዋ ስም ያናገሩት ባለ ራእዮች ቃል ስለ እስራኤል ነገሥታት በተጻፈው ታሪክ ውስጥ ተመዝግበዋል። 19 በተጨማሪም ያቀረበው ጸሎት፣+ ልመናው እንዴት እንደተሰማለት፣ የሠራው ኃጢአት ሁሉና ታማኝነት በማጉደል የፈጸመው ድርጊት+ በባለ ራእዮቹ ዘገባዎች ውስጥ ተካተዋል፤ ደግሞም ራሱን ከማዋረዱ በፊት ከፍ ያሉ የማምለኪያ ቦታዎች የሠራባቸው እንዲሁም የማምለኪያ ግንዶችና*+ የተቀረጹ ምስሎች ያቆመባቸው ስፍራዎች በእነዚህ ዘገባዎች ላይ ተጽፈዋል። 20 በመጨረሻም ምናሴ ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ እነሱም በቤቱ ቀበሩት፤ ልጁም አምዖን በእሱ ምትክ ነገሠ።+
21 አምዖን+ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው 22 ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌምም ሆኖ ለሁለት ዓመት ገዛ።+ 22 እሱም አባቱ ምናሴ እንዳደረገው በይሖዋ ፊት መጥፎ ነገር አደረገ፤+ አምዖን አባቱ ምናሴ ለሠራቸው የተቀረጹ ምስሎች ሁሉ ሠዋ፤+ ያገለግላቸውም ነበር። 23 ይሁንና አባቱ ምናሴ ራሱን እንዳዋረደ፣+ በይሖዋ ፊት ራሱን አላዋረደም፤+ ይልቁንም በበደል ላይ በደል እየጨመረ ሄደ። 24 ከጊዜ በኋላም አገልጋዮቹ በእሱ ላይ አሲረው+ በገዛ ቤቱ ውስጥ ገደሉት። 25 ሆኖም የምድሪቱ ሕዝብ በንጉሥ አምዖን ላይ ያሴሩትን ሁሉ ገደላቸው፤+ በእሱም ምትክ ልጁን ኢዮስያስን አነገሠው።+
34 ኢዮስያስ+ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ስምንት ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌምም ሆኖ ለ31 ዓመት ገዛ።+ 2 ኢዮስያስም በይሖዋ ፊት ትክክል የሆነውን ነገር አደረገ፤ በአባቱም በዳዊት መንገድ ሄደ፤ ወደ ቀኝም ወደ ግራም ፈቀቅ አላለም።
3 በነገሠ በ8ኛው ዓመት፣ ገና ልጅ ሳለ የአባቱን የዳዊትን አምላክ መፈለግ ጀመረ፤+ በ12ኛውም ዓመት ይሁዳንና ኢየሩሳሌምን ከፍ ካሉ የማምለኪያ ቦታዎች፣+ ከማምለኪያ ግንዶች፣* ከተቀረጹ ምስሎችና+ ከብረት ከተሠሩ ሐውልቶች* አነጻ።+ 4 በተጨማሪም እሱ በተገኘበት የባአልን መሠዊያዎች አፈራረሱ፤ በላያቸው ላይ የነበሩትንም የዕጣን ማጨሻዎች ሰባበራቸው። ደግሞም የማምለኪያ ግንዶቹን፣* የተቀረጹትን ምስሎችና ከብረት የተሠሩትን ሐውልቶች* ሰባብሮ አደቀቃቸው፤ ከዚያም ለእነሱ ይሠዉ በነበሩት ሰዎች መቃብር ላይ በተነው።+ 5 የካህናቱንም አጥንቶች በመሠዊያዎቻቸው ላይ አቃጠለ።+ በዚህ መንገድ ይሁዳንና ኢየሩሳሌምን አነጻ።
6 በተጨማሪም ከምናሴ፣ ከኤፍሬምና+ ከስምዖን አንስቶ እስከ ንፍታሌም ባሉት ከተሞች እንዲሁም በዙሪያቸው ባሉ የወደሙ ስፍራዎች ሁሉ፣ 7 መሠዊያዎችን አፈራረሰ፤ የማምለኪያ ግንዶችንና* የተቀረጹትን ምስሎች+ ሰባብሮ አደቀቃቸው፤ በመላው የእስራኤል ምድር የሚገኙትንም የዕጣን ማጨሻዎች ሰባበረ፤+ ከዚያም ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ።
8 እሱም በነገሠ በ18ኛው ዓመት ምድሪቱንና ቤተ መቅደሱን* ካነጻ በኋላ የአዜልያን ልጅ ሳፋንን፣+ የከተማዋን አለቃ ማአሴያህንና ታሪክ ጸሐፊውን የዮአሃዝን ልጅ ዮአህን የአምላኩን የይሖዋን ቤት እንዲጠግኑ ላካቸው።+ 9 እነሱም ወደ ሊቀ ካህናቱ ወደ ኬልቅያስ መጥተው ወደ አምላክ ቤት የመጣውን ገንዘብ አስረከቡት፤ ገንዘቡም በር ጠባቂዎች ሆነው የሚያገለግሉት ሌዋውያን ከምናሴ፣ ከኤፍሬም፣ ከቀረው የእስራኤል ሕዝብ ሁሉ+ እንዲሁም ከይሁዳ፣ ከቢንያምና ከኢየሩሳሌም ነዋሪዎች የሰበሰቡት ነበር። 10 ከዚያም በይሖዋ ቤት የሚከናወነውን ሥራ እንዲቆጣጠሩ ለተሾሙት ሠራተኞች ገንዘቡን ሰጧቸው። በይሖዋ ቤት የሚሠሩት ሠራተኞች ደግሞ ቤቱን ለመጠገንና ለማደስ አዋሉት። 11 በመሆኑም ጥርብ ድንጋዮችንና ለማጠናከሪያ የሚያገለግሉ ሳንቃዎችን እንዲሁም የይሁዳ ነገሥታት ትተዋቸው የፈራረሱትን ቤቶች ለመጠገን የሚያስፈልጉ ወራጆችን እንዲገዙ ገንዘቡን ለእጅ ጥበብ ባለሙያዎቹና ለግንበኞቹ ሰጧቸው።+
12 ሰዎቹም ሥራውን በታማኝነት አከናወኑ።+ በእነሱም ላይ ከሜራራውያን+ ሌዋውያኑ ያሃት እና አብድዩ፣ ከቀአታውያን+ ደግሞ ዘካርያስ እና መሹላም የበላይ ተመልካቾች ሆነው እንዲያገለግሉ ተሹመው ነበር። የሙዚቃ መሣሪያዎችን በመጫወት የተካኑት ሌዋውያንም ሁሉ፣+ 13 በጉልበት ሠራተኞቹ* ላይ ተሹመው ነበር፤ እንዲሁም በሁሉም ዓይነት አገልግሎት ላይ ተመድበው በሚሠሩት ሠራተኞች ላይ የበላይ ተመልካቾች ሆነው ያገለግሉ ነበር፤ ከሌዋውያኑም መካከል አንዳንዶቹ ጸሐፊዎች፣ አለቆችና በር ጠባቂዎች ነበሩ።+
14 ወደ ይሖዋ ቤት የመጣውን ገንዘብ በሚያወጡበት+ ጊዜ ካህኑ ኬልቅያስ በሙሴ በኩል* የተሰጠውን+ የይሖዋን ሕግ መጽሐፍ+ አገኘ። 15 በመሆኑም ኬልቅያስ ጸሐፊውን ሳፋንን “የሕጉን መጽሐፍ በይሖዋ ቤት ውስጥ አገኘሁት” አለው። ከዚያም ኬልቅያስ መጽሐፉን ለሳፋን ሰጠው። 16 ሳፋንም መጽሐፉን ወደ ንጉሡ ወስዶ እንዲህ አለው፦ “አገልጋዮችህ የተመደበላቸውን ሥራ ሁሉ እያከናወኑ ነው። 17 በይሖዋ ቤት የተገኘውን ገንዘብ አውጥተው ለተሾሙት ሰዎችና ለሠራተኞቹ አስረክበዋል።” 18 በተጨማሪም ጸሐፊው ሳፋን ንጉሡን “ካህኑ ኬልቅያስ የሰጠኝ አንድ መጽሐፍ አለ” አለው።+ ከዚያም ሳፋን መጽሐፉን በንጉሡ ፊት ማንበብ ጀመረ።+
19 ንጉሡ የሕጉን ቃል ሲሰማ ልብሱን ቀደደ።+ 20 ከዚያም ንጉሡ ኬልቅያስን፣ የሳፋንን ልጅ አኪቃምን፣+ የሚክያስን ልጅ አብዶንን፣ ጸሐፊውን ሳፋንን እና የንጉሡን አገልጋይ አሳያህን እንዲህ ሲል አዘዛቸው፦ 21 “ሄዳችሁ በተገኘው መጽሐፍ ላይ የሰፈረውን ቃል በተመለከተ እኔን እንዲሁም በእስራኤልና በይሁዳ የቀረውን ሕዝብ ወክላችሁ ይሖዋን ጠይቁ፤ አባቶቻችን በዚህ መጽሐፍ የተጻፉትን ነገሮች ሁሉ ስላልፈጸሙና የይሖዋን ቃል ስላልጠበቁ በእኛ ላይ የሚወርደው የይሖዋ ቁጣ ታላቅ ነው።”+
22 በመሆኑም ኬልቅያስና ንጉሡ የላካቸው ሰዎች ወደ ነቢዪቱ+ ሕልዳና ሄዱ። ሕልዳና የሃርሐስ ልጅ፣ የቲቅዋ ልጅ፣ የአልባሳት ጠባቂው የሻሉም ሚስት ስትሆን ኢየሩሳሌም ውስጥ በሁለተኛው ክፍል ትኖር ነበር፤ እነሱም በዚያ አነጋገሯት።+ 23 እሷም እንዲህ አለቻቸው፦ “የእስራኤል አምላክ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘ወደ እኔ የላካችሁን ሰው እንዲህ በሉት፦ 24 “ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘በዚህ ቦታና በነዋሪዎቹ ላይ መከራ አመጣለሁ፤+ በይሁዳ ንጉሥ ፊት ባነበቡት መጽሐፍ ላይ የሰፈረውን እርግማን ሁሉ አመጣለሁ።+ 25 እኔን በመተው+ በእጆቻቸው ሥራ ሁሉ ያስቆጡኝ ዘንድ ለሌሎች አማልክት የሚጨስ መሥዋዕት ስለሚያቀርቡ+ በዚህ ቦታ ላይ ቁጣዬ ይፈስሳል፤ ደግሞም አይጠፋም።’”+ 26 ይሖዋን እንድትጠይቁ ለላካችሁ ለይሁዳ ንጉሥ ግን እንዲህ በሉት፦ “የእስራኤል አምላክ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘የሰማኸውን ቃል በተመለከተ፣+ 27 ስለዚህ ቦታና ስለ ነዋሪዎቹ የተናገረውን ቃል ስትሰማ ልብህ ስለተነካና* በአምላክ ፊት ራስህን ስላዋረድክ እንዲሁም ራስህን በፊቴ ዝቅ ስላደረግክ፣ ልብስህን ስለቀደድክና በፊቴ ስላለቀስክ እኔም ሰምቼሃለሁ ይላል ይሖዋ።+ 28 ወደ አባቶችህ የምሰበስብህ* በዚህ የተነሳ ነው፤ አንተም በሰላም በመቃብርህ ታርፋለህ፤ በዚህ ቦታና በነዋሪዎቹ ላይ የማመጣውን መከራ ሁሉ ዓይኖችህ አያዩም።’”’”+
ከዚያም ሰዎቹ መልሱን ለንጉሡ አመጡለት። 29 ንጉሡም መልእክት ልኮ የይሁዳንና የኢየሩሳሌምን ሽማግሌዎች ሁሉ ጠራ።+ 30 ከዚያ በኋላ ንጉሡ ከይሁዳ ሰዎች፣ ከኢየሩሳሌም ነዋሪዎች፣ ከካህናቱ፣ ከሌዋውያኑ እንዲሁም ትልቅ ትንሽ ሳይባል ከሕዝቡ ሁሉ ጋር ወደ ይሖዋ ቤት ወጣ። እሱም በይሖዋ ቤት የተገኘውን የቃል ኪዳኑን መጽሐፍ ቃል ሁሉ የተሰበሰቡት ሰዎች እየሰሙ አነበበላቸው።+ 31 ንጉሡ ባለበት ስፍራ ቆሞ፣ በዚህ መጽሐፍ ላይ የሰፈሩትን የቃል ኪዳኑን ቃላት በመፈጸም+ በሙሉ ልቡና በሙሉ ነፍሱ*+ ይሖዋን ለመከተል እንዲሁም ትእዛዛቱን፣ ማሳሰቢያዎቹንና ሥርዓቶቹን ለመጠበቅ በይሖዋ ፊት ቃል ኪዳን ገባ።*+ 32 በተጨማሪም በኢየሩሳሌምና በቢንያም ያሉት ሁሉ በቃል ኪዳኑ እንዲስማሙ አደረገ። የኢየሩሳሌምም ነዋሪዎች በአምላክ ይኸውም በአባቶቻቸው አምላክ ቃል ኪዳን መሠረት እርምጃ ወሰዱ።+ 33 ከዚያም ኢዮስያስ ከመላው የእስራኤላውያን ምድር አስጸያፊዎቹን ነገሮች* በሙሉ አስወገደ፤+ እንዲሁም በእስራኤል ያሉ ሁሉ አምላካቸውን ይሖዋን እንዲያገለግሉ አደረገ። በሕይወት ዘመኑ* ሁሉ የአባቶቻቸውን አምላክ ይሖዋን ከመከተል ፈቀቅ አላሉም።
35 ኢዮስያስ በኢየሩሳሌም ለይሖዋ ፋሲካ አደረገ፤+ በመጀመሪያው ወር በ14ኛው ቀን+ የፋሲካን መሥዋዕት አረዱ።+ 2 ካህናቱን በየሥራቸው ላይ መደባቸው፤ የይሖዋንም ቤት አገልግሎት እንዲያከናውኑ አበረታታቸው።+ 3 ከዚያም የመላው እስራኤል አስተማሪዎች+ የሆኑትንና ለይሖዋ የተቀደሱትን ሌዋውያን እንዲህ አላቸው፦ “ቅዱሱን ታቦት የእስራኤል ንጉሥ የዳዊት ልጅ ሰለሞን በሠራው ቤት ውስጥ አስቀምጡት፤+ ከዚህ በኋላ ታቦቱን በትከሻችሁ መሸከም አያስፈልጋችሁም።+ አሁን አምላካችሁን ይሖዋንና ሕዝቡን እስራኤልን አገልግሉ። 4 የእስራኤል ንጉሥ ዳዊትና+ ልጁ ሰለሞን+ በጻፉት ትእዛዝ መሠረት በየአባቶቻችሁ ቤት እንደየምድባችሁ ራሳችሁን አዘጋጁ። 5 ወንድሞቻችሁ የሆኑትን የቀሩትን ሰዎች* ለማገልገል በየአባቶች ቤት ምድብ በተቀደሰው ስፍራ ቁሙ፤ እያንዳንዱም የሌዋውያን ቡድን ከሕዝቡ መካከል የሚደርሰውን የአባቶች ቤት ምድብ ያገልግል። 6 የፋሲካውን መሥዋዕት እረዱ፤+ ራሳችሁንም ቀድሱ፤ ይሖዋ በሙሴ በኩል የሰጠውን ትእዛዝ መፈጸም እንድትችሉ ለወንድሞቻችሁ አስፈላጊውን ዝግጅት አድርጉ።”
7 ኢዮስያስም ለሕዝቡ ይኸውም በዚያ ለተገኙት ሁሉ ለፋሲካ መሥዋዕት እንዲሆኑ ከመንጋው መካከል በድምሩ 30,000 ተባዕት የበግና የፍየል ጠቦቶች እንዲሁም 3,000 ከብቶች ሰጠ። እነዚህ የተሰጡት ከንጉሡ ሀብት ላይ ነበር።+ 8 መኳንንቱም ለሕዝቡ፣ ለካህናቱና ለሌዋውያኑ በፈቃደኝነት የሚቀርብ መባ ሰጡ። የእውነተኛው አምላክ ቤት መሪዎች የሆኑት ኬልቅያስ፣+ ዘካርያስና የሂኤል ለፋሲካ መሥዋዕት የሚሆኑ 2,600 በጎችና ፍየሎች እንዲሁም 300 ከብቶች ለካህናቱ ሰጡ። 9 ኮናንያ፣ ወንድሞቹ ሸማያህ እና ናትናኤል እንዲሁም የሌዋውያኑ አለቆች ሃሻብያህ፣ የኢዔል እና ዮዛባድ ለፋሲካ መሥዋዕት የሚሆኑ 5,000 በጎችና ፍየሎች እንዲሁም 500 ከብቶች ለሌዋውያኑ ሰጡ።
10 የአገልግሎቱ ዝግጅት ከተጠናቀቀ በኋላ ንጉሡ ባዘዘው መሠረት ካህናቱ በየቦታቸው፣ ሌዋውያኑም በየምድባቸው+ ቆሙ። 11 የፋሲካውንም መሥዋዕት አረዱ፤+ ሌዋውያኑ ቆዳውን ሲገፉ+ ካህናቱ ደግሞ ከእነሱ የተቀበሉትን ደም መሠዊያው ላይ ረጩ።+ 12 ከዚያም በየአባቶች ቤት ለተመደቡት ለቀሩት ሰዎች ለማከፋፈል የሚቃጠለውን መባ አዘጋጁ፤ ይህም የሆነው በሙሴ መጽሐፍ ላይ በተጻፈው መሠረት መባው ለይሖዋ እንዲቀርብ ነው፤ ከብቶቹንም በዚሁ መንገድ አዘጋጁ። 13 በልማዱም መሠረት የፋሲካን መባ በእሳት አበሰሉ፤*+ የተቀደሱትንም መባዎች በድስት፣ በሰታቴና በመጥበሻ አብስለው ወዲያውኑ ለቀሩት ሰዎች ሁሉ አቀረቡ። 14 ከዚያም ለራሳቸውና ለካህናቱ አዘጋጁ፤ ምክንያቱም የአሮን ዘሮች የሆኑት ካህናቱ እስኪመሽ ድረስ፣ የሚቃጠሉትን መሥዋዕቶችና ስቡን ያቀርቡ ነበር፤ በመሆኑም ሌዋውያኑ ለራሳቸውና የአሮን ዘሮች ለሆኑት ለካህናቱ አዘጋጁ።
15 ዳዊት፣+ አሳፍ፣+ ሄማንና የንጉሡ ባለ ራእይ የሆነው የዱቱን+ በሰጡት ትእዛዝ መሠረት የአሳፍ+ ልጆች የሆኑት ዘማሪዎቹ በየቦታቸው ላይ ነበሩ፤ በር ጠባቂዎቹም በየበሩ ላይ ነበሩ።+ ወንድሞቻቸው የሆኑት ሌዋውያን አዘጋጅተውላቸው ስለነበር ሥራቸውን ትተው መሄድ አላስፈለጋቸውም። 16 በመሆኑም ንጉሥ ኢዮስያስ ባዘዘው መሠረት+ ፋሲካን ለማክበርና+ በይሖዋ መሠዊያ ላይ የሚቃጠለውን መባ ለማቅረብ፣ ለይሖዋ አገልግሎት የሚያስፈልገው ነገር ሁሉ በዚያን ቀን ተዘጋጅቶ ነበር።
17 በስፍራው የተገኙት እስራኤላውያን በዚያ ጊዜ ፋሲካን አከበሩ፤ የቂጣንም በዓል ለሰባት ቀን አከበሩ።+ 18 ከነቢዩ ሳሙኤል ዘመን ወዲህ እንደዚህ ያለ የፋሲካ በዓል በእስራኤል ተከብሮ አያውቅም፤ ኢዮስያስ፣ ካህናቱ፣ ሌዋውያኑ፣ በዚያ የተገኙት የይሁዳና የእስራኤል ሰዎች ሁሉ እንዲሁም የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ያከበሩት ዓይነት ፋሲካ ያከበረ አንድም የእስራኤል ንጉሥ የለም።+ 19 ይህ ፋሲካ የተከበረው ኢዮስያስ በነገሠ በ18ኛው ዓመት ነበር።
20 ከዚህ ሁሉ በኋላ ኢዮስያስ ቤተ መቅደሱን* አዘጋጅቶ ባጠናቀቀ ጊዜ የግብፁ ንጉሥ ኒካዑ+ በኤፍራጥስ አጠገብ ባለው በካርከሚሽ ለመዋጋት መጣ። በዚህ ጊዜ ኢዮስያስ ሊገጥመው ወጣ።+ 21 ኒካዑም እንዲህ ሲል መልእክተኞችን ላከበት፦ “የይሁዳ ንጉሥ ሆይ፣ እኔን ልትወጋ የመጣኸው ለምንድን ነው? አሁን የመጣሁት ከሌላ ብሔር ጋር ልዋጋ እንጂ አንተን ልወጋ አይደለም፤ አምላክም እንድፈጥን አዞኛል። ከእኔ ጋር የሆነውን አምላክ መቃወም ቢቀርብህ ይሻላል፤ አለዚያ ያጠፋሃል።” 22 ኢዮስያስ ግን ለመመለስ ፈቃደኛ አልሆነም፤ ይልቁንም ማንነቱ እንዳይታወቅ ራሱን ለውጦ+ ከእሱ ጋር ለመዋጋት ወጣ፤ በኒካዑ በኩል የተነገረውን የአምላክ ቃል አልሰማም። በመሆኑም ለመዋጋት ወደ መጊዶ+ ሜዳ መጣ።
23 ቀስተኞችም ንጉሥ ኢዮስያስን ወጉት፤ ንጉሡም አገልጋዮቹን “ክፉኛ ስለቆሰልኩ ከዚህ አውጡኝ” አላቸው። 24 በመሆኑም አገልጋዮቹ ከሠረገላው አውርደው በሁለተኛው የጦር ሠረገላው ላይ ካስቀመጡት በኋላ ወደ ኢየሩሳሌም ወሰዱት። እሱም በዚህ ሁኔታ ሞተ፤ በአባቶቹም መቃብር ተቀበረ፤+ የይሁዳና የኢየሩሳሌም ሰዎች ሁሉ ለኢዮስያስ አለቀሱ። 25 ኤርምያስም+ ለኢዮስያስ የሐዘን እንጉርጉሮ ተቀኘ፤ ወንዶችና ሴቶች ዘማሪዎችም+ ሁሉ እስከ ዛሬ ድረስ በሙሿቸው* ላይ ስለ ኢዮስያስ ይዘምራሉ፤ ደግሞም በእስራኤል እንዲዘመርና ሌሎች ሙሾዎች በተጻፉበት መጽሐፍ ላይ እንዲሰፍር ተወሰነ።
26 የቀረው የኢዮስያስ ታሪክና በይሖዋ ሕግ ላይ በተጻፈው መሠረት ያከናወናቸው ታማኝ ፍቅር የተንጸባረቀባቸው ተግባራት 27 እንዲሁም ከመጀመሪያ አንስቶ እስከ መጨረሻ ድረስ ያደረጋቸው ነገሮች በእስራኤልና በይሁዳ ነገሥታት መጽሐፍ ተጽፈዋል።+
36 ከዚያም የምድሪቱ ሕዝብ የኢዮስያስን ልጅ ኢዮዓካዝን+ በአባቱ ምትክ በኢየሩሳሌም አነገሡት።+ 2 ኢዮዓካዝ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው 23 ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌምም ሆኖ ለሦስት ወር ገዛ። 3 ይሁን እንጂ የግብፅ ንጉሥ በኢየሩሳሌም ካለው ዙፋኑ አወረደው፤ በምድሪቱም ላይ 100 የብር ታላንትና* አንድ የወርቅ ታላንት ቅጣት ጣለ።+ 4 በተጨማሪም የግብፁ ንጉሥ ኒካዑ+ የኢዮዓካዝን ወንድም ኤልያቄምን በይሁዳና በኢየሩሳሌም ላይ አነገሠው፤ ስሙንም ቀይሮ ኢዮዓቄም አለው፤ ወንድሙን ኢዮዓካዝን ግን ወደ ግብፅ ወሰደው።+
5 ኢዮዓቄም+ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው 25 ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌምም ሆኖ ለ11 ዓመት ገዛ። እሱም በአምላኩ በይሖዋ ፊት መጥፎ የሆነውን ነገር አደረገ።+ 6 የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነጾር+ ከመዳብ በተሠሩ ሁለት የእግር ብረቶች አስሮ ወደ ባቢሎን ለመውሰድ በእሱ ላይ ዘመተ።+ 7 ናቡከደነጾርም በይሖዋ ቤት ያሉ የተወሰኑ ዕቃዎችን ወደ ባቢሎን ወስዶ በባቢሎን በሚገኘው ቤተ መንግሥቱ አስቀመጣቸው።+ 8 የቀረው የኢዮአቄም ታሪክ፣ የፈጸማቸው አስጸያፊ ነገሮችና በእሱ ላይ የተገኘበት መጥፎ ነገር በእስራኤልና በይሁዳ ነገሥታት መጽሐፍ ተጽፈዋል፤ በእሱም ምትክ ልጁ ዮአኪን ነገሠ።+
9 ዮአኪን+ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው 18 ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌምም ሆኖ ለሦስት ወር ከአሥር ቀን ገዛ፤ እሱም በይሖዋ ፊት መጥፎ የሆነውን ነገር አደረገ።+ 10 በዓመቱ መጀመሪያ* ላይ ንጉሥ ናቡከደነጾር አገልጋዮቹን ልኮ በይሖዋ ቤት ካሉት ውድ ዕቃዎች+ ጋር ወደ ባቢሎን አመጣው።+ የአባቱን ወንድም ሴዴቅያስንም በይሁዳና በኢየሩሳሌም ላይ አነገሠው።+
11 ሴዴቅያስ+ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው 21 ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌምም ሆኖ ለ11 ዓመት ገዛ።+ 12 በአምላኩ በይሖዋ ፊት መጥፎ የሆነውን ነገር አደረገ። በይሖዋ ትእዛዝ በተናገረው በነቢዩ ኤርምያስ ፊት ራሱን ዝቅ አላደረገም።+ 13 ደግሞም በአምላክ ስም ባስማለው በንጉሥ ናቡከደነጾር ላይ ዓመፀ፤+ ግትር ሆነ፤* ልቡንም አጠነከረ፤ ወደ እስራኤል አምላክ ወደ ይሖዋ ለመመለስ አሻፈረኝ አለ። 14 ዋነኞቹ ካህናት ሁሉና ሕዝቡ፣ ብሔራት የሚፈጽሟቸውን አስጸያፊ ነገሮች በማድረግ እጅግ ከፍተኛ ክህደት ፈጸሙ፤ ይሖዋ በኢየሩሳሌም የቀደሰውንም ቤት አረከሱ።+
15 የአባቶቻቸው አምላክ ይሖዋ ለሕዝቡና ለማደሪያው ስፍራ ስለራራ መልእክተኞቹን እየላከ በተደጋጋሚ ያስጠነቅቃቸው ነበር። 16 እነሱ ግን የይሖዋ ቁጣ በሕዝቡ ላይ እስኪነድና+ ፈውስ እስከማይገኝላቸው ድረስ በእውነተኛው አምላክ መልእክተኞች ላይ ያላግጡ፣+ ቃሉን ይንቁና+ በነቢያቱ ላይ ያፌዙ+ ነበር።
17 ስለዚህ የከለዳውያንን+ ንጉሥ አመጣባቸው፤ እሱም ወጣቶቻቸውን በቤተ መቅደሳቸው+ ውስጥ በሰይፍ ገደለ፤+ ለወጣቱም ሆነ ለድንግሊቱ፣ ለሽማግሌውም ሆነ ለአቅመ ደካማው አልራራም።+ አምላክ ሁሉንም በእጁ አሳልፎ ሰጠው።+ 18 በእውነተኛው አምላክ ቤት የነበሩትን ትላልቅም ሆኑ ትናንሽ ዕቃዎች በሙሉ፣ የይሖዋን ቤት ውድ ሀብት እንዲሁም የንጉሡንና የመኳንንቱን ውድ ሀብት ሁሉ ወደ ባቢሎን አጋዘ።+ 19 የእውነተኛውን አምላክ ቤት አቃጠለ፤+ የኢየሩሳሌምን ቅጥር አፈረሰ፤+ የማይደፈሩ ማማዎቿን ሁሉ በእሳት አቃጠለ፤ እንዲሁም ውድ የሆኑትን ዕቃዎች በሙሉ አወደመ።+ 20 ከሰይፍ የተረፉትንም ሁሉ ማርኮ ወደ ባቢሎን ወሰዳቸው፤+ እነሱም የፋርስ መንግሥት* መግዛት እስከጀመረበት ጊዜ ድረስ+ የእሱና የወንዶች ልጆቹ አገልጋዮች ሆኑ፤+ 21 ይህም የሆነው ይሖዋ በኤርምያስ በኩል የተናገረው ቃል ይፈጸም ዘንድ፣+ ምድሪቱ የሰንበት ዕዳዋን እስክትከፍል ድረስ ነው።+ ፈራርሳ በቆየችባቸው ጊዜያት ሁሉ፣ 70 ዓመት እስኪፈጸም ድረስ ሰንበትን አከበረች።+
22 በኤርምያስ በኩል የተነገረው የይሖዋ ቃል ይፈጸም ዘንድ+ የፋርስ ንጉሥ ቂሮስ+ በነገሠ በመጀመሪያው ዓመት የሚከተለውን አዋጅ በመላ ግዛቱ እንዲያውጅ ይሖዋ የፋርሱን ንጉሥ የቂሮስን መንፈስ አነሳሳ፤ እሱም ይህ በጽሑፍ እንዲሰፍር አደረገ፦+ 23 “የፋርስ ንጉሥ ቂሮስ እንዲህ ይላል፦ ‘የሰማይ አምላክ ይሖዋ የምድርን መንግሥታት ሁሉ ሰጥቶኛል፤+ በይሁዳ በምትገኘው በኢየሩሳሌምም ቤት እንድሠራለት አዞኛል።+ ከእሱ ሕዝብ መካከል የሆነ አብሯችሁ የሚኖር ማንኛውም ሰው አምላኩ ይሖዋ ከእሱ ጋር ይሁን፤ እሱም ወደዚያ ይውጣ።’”+
ወይም “በዚያ አምላክን ይጠይቁ ነበር።”
ቃል በቃል “በዚህ ሕዝብ ፊት መውጣትና መግባት።”
ወይም “ነፍስ።”
ቃል በቃል “ብዙ ቀናት።”
ወይም “ፈረሰኞችን።”
ወይም “ፈረሰኞች።”
“ከግብፅና ከቀዌ ያስመጣቸው ነበሩ፤ የንጉሡ ነጋዴዎች ከቀዌ አንዴ በተተመነው ዋጋ ይገዟቸው ነበር” ማለትም ሊሆን ይችላል። ቀዌ ኪልቅያን ልታመለክት ትችላለች።
ወይም “ቤተ መንግሥት።”
ወይም “ተሸካሚዎችና።”
ወይም “ቤተ መንግሥት።”
ገጸ ኅብስቱን ያመለክታል።
አንድ የቆሮስ መስፈሪያ 220 ሊትር (170 ኪሎ ግራም ገደማ) ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
አንድ የቆሮስ መስፈሪያ ገብስ 130 ኪሎ ግራም ገደማ ነው።
አንድ የባዶስ መስፈሪያ 22 ሊትር ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
ወይም “ተሸካሚዎች።”
በመደበኛው መለኪያ መሠረት አንድ ክንድ 44.5 ሴንቲ ሜትር ነው፤ አንዳንዶች ግን “የቀድሞው መለኪያ” 51.8 ሴንቲ ሜትር የሚሆነውን ረጅሙን ክንድ እንደሚያመለክት ይሰማቸዋል። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
የመለኪያው ምንነት በእርግጠኝነት አይታወቅም።
ቃል በቃል “ታላቁን ቤት።” ቅድስቱን የሚያመለክት ሳይሆን አይቀርም።
ቃል በቃል “ቤት።”
አንድ ታላንት 34.2 ኪሎ ግራም ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
አንድ ሰቅል 11.4 ግራም ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
ቃል በቃል “ቤት።”
ወደ ቅድስቱ ማለት ነው።
ወይም “በደቡብ።”
ወይም “በሰሜን።”
“እሱ [ማለትም ይሖዋ] አጽንቶ ይመሥርት” የሚል ትርጉም አለው።
“በብርታት” ማለት ሳይሆን አይቀርም።
ወይም “ውኃ ማጠራቀሚያውን።”
አንድ ጋት 7.4 ሴንቲ ሜትር ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
አንድ ባዶስ 22 ሊትር ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
ወይም “የውኃ መጫኛ ጋሪዎችና።”
የዳስ በዓልን ያመለክታል።
ወይም “ሌዋውያኑ ካህናት።”
እዚህ ላይ የገባው የዕብራይስጥ ቃል፣ እርስ በርሱ ሲጋጭ ኃይለኛ ድምፅ የሚያወጣን ክብ ቅርጽ ያለው ከብረት የተሠራ የሙዚቃ መሣሪያ ያመለክታል።
ቃል በቃል “ከወገብህ የሚወጣው ወንድ ልጅህ።”
አንድ ክንድ 44.5 ሴንቲ ሜትር ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
ወይም “ባልንጀራው በእርግማን ሥር ቢያደርገው።” ግለሰቡ የማለው በውሸት ከሆነ ወይም መሐላውን ከጣሰ እርግማኑ እንደ ቅጣት እንደሚደርስበት ያመለክታል።
ቃል በቃል “በእርግማኑም።”
ቃል በቃል “እርግማን።”
ቃል በቃል “ጻድቅ።”
ወይም “ስላጎሳቆልካቸው።”
ወይም “ፌንጣ።”
ቃል በቃል “በበሮቹ ምድር።”
ወይም “ዝናህ።”
የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ወይም “ከዚህ ቦታ ጋር በተያያዘ።”
ቃል በቃል “ፊት አትመልስ።”
ሌዋውያኑን የሚያመለክት ሳይሆን አይቀርም።
ወይም “ከሃማት መግቢያ።”
የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
የዳስ በዓልን ያመለክታል።
ከበዓሉ በኋላ ያለው ቀን ወይም 15ኛው ቀን።
ወይም “ቤተ መንግሥት።”
ቃል በቃል “መተረቻና።”
ወይም “ቤተ መንግሥት።”
ወይም “መልሶ ገነባ።”
የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ወይም “የጊዜያዊ መጠለያን።”
ወይም “ሥርዓታማ፤ የተሟላ።”
አንድ ታላንት 34.2 ኪሎ ግራም ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
ወይም “በእንቆቅልሽ።”
ቃል በቃል “ከሰለሞን የተሰወረ።”
ቃል በቃል “በውስጧ መንፈስ አልቀረም።”
ወይም “ስለ ቃሎችህና።”
አንድ ታላንት 34.2 ኪሎ ግራም ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
ወይም “ቤተ መንግሥት።”
“ያመጣችለትን ነገር በዋጋ የሚተካከል ስጦታ የሰጣት ሲሆን ተጨማሪ ገጸ በረከትም አበረከተላት” ማለትም ሊሆን ይችላል።
አንድ ሰቅል 11.4 ግራም ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
አብዛኛውን ጊዜ ቀስተኞች የሚይዙት ትንሽ ጋሻ።
በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ አንድ ምናን 570 ግራም ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
ዥጉርጉር ቀለም ያለው ትልቅ የወፍ ዝርያ። እንግሊዝኛ፣ ፒኮክ።
ቃል በቃል “የእሱን ፊት ይሹ ነበር።”
ወይም “ፈረሰኞች።”
ኤፍራጥስን ያመለክታል።
ወይም “ጨቋኝ።”
ቃል በቃል “ወደየድንኳናቸው።”
ቃል በቃል “የተመረጡ ተዋጊዎች።”
ወይም “አጠናከረ።”
ቃል በቃል “ለፍየሎችና።”
ወይም “ወደተመሸጉት ከተሞች ሁሉ በተናቸው።”
ቃል በቃል “መንግሥታትን።”
ወይም “ቤተ መንግሥት።”
ቃል በቃል “የሯጮቹ።”
1ነገ 15:2 እና 2ዜና 11:20-22 ላይ ማአካ ተብላም ተጠርታለች።
ቃል በቃል “የተመረጡ።”
ቃል በቃል “የተመረጡ።”
ዘላቂና የማይለወጥ ቃል ኪዳንን ያመለክታል።
ገጸ ኅብስቱን ያመለክታል።
ቃል በቃል “የተመረጡ ተዋጊዎች።”
ቃል በቃል “በመደገፋቸው።”
ወይም “በዙሪያዋ።”
ወይም “ዘገባ፤ ሐተታ።”
የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ቃል በቃል “ሁለት ሳንቃዎች ያሏቸው በሮችና።”
አብዛኛውን ጊዜ ቀስተኞች የሚይዙት ትንሽ ጋሻ።
ቃል በቃል “ደጋን የሚረግጡ።”
ቃል በቃል “ተደግፈናልና።”
ቃል በቃል “ብዙ ቀናት።”
ቃል በቃል “የሚወጣውም ሆነ የሚገባው ሰላም አልነበረውም።”
ቃል በቃል “እጆቻችሁ አይዛሉ።”
የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ወይም “እንደ ንጉሡ እናት ተቆጥራ ከተሰጣት ቦታ።”
ቃል በቃል “በቀናቱ።”
ወይም “ሙሉ በሙሉ ለአምላክ ያደረ ነበር።”
ወይም “ከይሁዳ ንጉሥ ከአሳ ግዛት ማንም እንዳይወጣ ወይም ማንም ወደዚያ እንዳይገባ።”
ወይም “ማጠናከር፤ መልሶ መገንባት።”
ወይም “ቤተ መንግሥት።”
ወይም “ቃል ኪዳን።”
ወይም “ቃል ኪዳን።”
ወይም “ማጠናከሩን፤ መልሶ መገንባቱን።”
ወይም “አጠናከረ፤ መልሶ ገነባ።”
ቃል በቃል “ከመደገፍ።”
ቃል በቃል “ስለተደገፍክ።”
ወይም “ሙሉ በሙሉ ለእሱ ላደሩ ሰዎች።”
ወይም “ያዘነበሉትን ሰዎች ይረዳ ዘንድ።”
ቃል በቃል “የእግር ግንድ ቤት ውስጥ።”
ያነደዱት የአሳን አስከሬን ሳይሆን የተለያዩ ቅመማ ቅመሞችን እንደሆነ ግልጽ ነው።
ቃል በቃል “በትእዛዙም ተመላልሷል።”
የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ወይም “አግባባው።”
ወይም “ትገፋቸዋለህ።”
ወይም “አንድ መልአክ።”
ወይም “ሳያስብ።”
ቃል በቃል “ከሰፈሩ።”
ወይም “ቤተ መንግሥቱ።”
የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ወይም “ልብህ ስለቆረጠ።”
ወይም “ሙሉ በሙሉ ለአምላክ ባደረ ልብ።”
ወይም “መልካም ከሆነው ነገር።”
“መኡኒማውያን” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ሙት ባሕርን ሊያመለክት ይችላል።
ቃል በቃል “ፊቱን አቀና።”
ቃል በቃል “ከወንዶች ልጆቻቸው።”
ወይም “በደረቁ ወንዝ መጨረሻ።”
ወይም “ይሖዋ እንዴት እንደሚታደጋችሁ ተመልከቱ።”
ወይም “ረባዳማ ሜዳ።”
ቃል በቃል “ባረኩ።”
“በረከት” የሚል ትርጉም አለው።
“መብራት” የሚለው ቃል ከዳዊት ቤት የሆነን ንጉሥ ወይም የእሱን ሥርወ መንግሥት ያመለክታል።
ቃል በቃል “የፍልስጤማውያንንና በኢትዮጵያውያን አቅራቢያ የሚኖሩትን ዓረቦች መንፈስ በኢዮራም ላይ አነሳሳ።”
ወይም “ቤተ መንግሥት።”
አካዝያስ ተብሎም ይጠራል።
በ2ዜና 21:17 ላይ ኢዮዓካዝ ተብሎም ተጠርቷል።
ቃል በቃል “ሴት ልጅ።”
በአንዳንድ የዕብራይስጥ ጥንታዊ ቅጂዎች ላይ አዛርያስ ተብሎም ተጠርቷል።
ወይም “ታሞ።”
ቃል በቃል “ወንድ ልጅ።”
ቃል በቃል “የመንግሥት ዘር።”
ወይም “ቃል ኪዳን።”
ወይም “ቤተ መንግሥት።”
ቃል በቃል “በሚወጣበትም ሆነ በሚገባበት ጊዜ።”
አብዛኛውን ጊዜ ቀስተኞች የሚይዙት ትንሽ ጋሻ።
ወይም “ተወንጫፊ መሣሪያቸውን።”
ወይም “ዘውዱን።”
የአምላክ ሕግ የሰፈረበት ጥቅልል ሊሆን ይችላል።
ወይም “ውዳሴ እንዲቀርብ ምልክት ይሰጡ።”
ወይም “ቤተ መንግሥት።”
ወይም “ቤተ መቅደስ።”
ቃል በቃል “በዳዊት እጅ።”
ወይም “ቤተ መንግሥት።”
“ሁሉም እስኪሰጡ” ማለትም ሊሆን ይችላል።
የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ቃል በቃል “ቁጣ ሆነ።”
ወይም “ይመሠክሩባቸው።”
የዘካርያስን አባት ያመለክታል።
የሶርያን ሰዎች ያመለክታል።
ወይም “በጠና ታሞ።”
ወይም “ወንድ ልጅ።” በብዙ ቁጥር የተገለጸው ልጁ ትልቅ ቦታ እንደሚሰጠው ለማሳየት ሊሆን ይችላል።
ቃል በቃል “ስለመመሥረቱ።”
ወይም “ሐተታ፤ ማብራሪያ።”
ቃል በቃል “የተመረጡ።”
አንድ ታላንት 34.2 ኪሎ ግራም ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
ወይም “ፊት ለፊት እንገናኝ።”
ወይም “በቤተ መንግሥትህ።”
ቃል በቃል “ወደየድንኳናቸው።”
አካዝያስ ተብሎም ይጠራል።
ርዝመቱም ወደ 178 ሜትር ገደማ ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
ወይም “በኦቤድዔዶም ኃላፊነት ሥርና።”
ወይም “ቤተ መንግሥት።”
በ2ነገ 14:21 ላይ አዛርያስ ተብሎም ተጠርቷል።
አባቱን አሜስያስን ያመለክታል።
ወይም “ፈልፍሎ ሠራ።” ከዓለት ሳይሆን አይቀርም።
ወይም “በአምባውም።”
ወይም “በንጉሡ ቤተ መንግሥት።”
አንድ ታላንት 34.2 ኪሎ ግራም ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
አንድ ቆሮስ 220 ሊትር ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
ወይም “ስላዘጋጀ።”
ወይም “ቀልጠው የተሠሩ የባአል ሐውልቶችን።”
የቃላት መፍቻው ላይ “ገሃነም” የሚለውን ተመልከት።
ቃል በቃል “የቤቱን።”
ወይም “በዙሪያዋ።”
ወይም “ቤተ መንግሥቱንና።”
ወይም “ማላገጫ።”
ወይም “የምታርፉበት።”
ገጸ ኅብስቱን ያመለክታል።
ቃል በቃል “እጃችሁን ስለሞላችሁ።”
ቃል በቃል “ይበልጥ ልበ ቀና።”
ወይም “ተዘጋጀ።”
ወይም “የማለፍን በዓል።” የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ቃል በቃል “ሯጮቹ።”
ወይም “ቸርና።”
ቃል በቃል “ሯጮቹ።”
ቃል በቃል “ፈወሰ።”
ቃል በቃል “ለልባቸው ተናገረ።”
የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ቃል በቃል “የሰፈሮቹ።”
ወይም “ሙሉ በሙሉ ለይሖዋ ሕግ ማደር።”
ወይም “መመገቢያ ክፍሎች።”
ወይም “አሥራቱንና።”
ወይም “ሚሎ።” “መሙላት” የሚል ትርጉም ያለው የዕብራይስጥ ቃል ነው።
ወይም “ተወንጫፊ መሣሪያዎችና።”
ቃል በቃል “ለልባቸው ተናገረ።”
ወይም “ሰብዓዊ ኃይል።”
ወይም “ከወታደራዊ ኃይሉና ግርማው ሁሉ።”
ቃል በቃል “የእሱን።”
ወይም “ቤተ መቅደስ ገባ።”
ወይም “ድንቅ ነገርም።”
ወይም “ድንቅ ነገር።”
የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
“ጉድጓድ ውስጥ አግኝተው ያዙት” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “በደረቁ ወንዝ አካባቢ ከሚገኘው።”
የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ወይም “ቀልጠው ከተሠሩ ሐውልቶች።”
የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ወይም “ቀልጠው የተሠሩትን ሐውልቶች።”
የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ቃል በቃል “ቤቱን።”
ወይም “በተሸካሚዎቹ።”
ቃል በቃል “እጅ።”
ቃል በቃል “ልብህ ስለለሰለሰና።”
ይህ ሞትን የሚያመለክት ቅኔያዊ አነጋገር ነው።
የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ወይም “ቃል ኪዳኑን አደሰ።”
ወይም “ጣዖታቱን።”
ቃል በቃል “በቀኖቹ።”
ቃል በቃል “የሕዝቡን ወንዶች ልጆች።”
“ጠበሱ” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ቃል በቃል “ቤቱን።”
ወይም “በሐዘን እንጉርጉሯቸው።”
አንድ ታላንት 34.2 ኪሎ ግራም ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
በበልግ ወቅት ሊሆን ይችላል።
ቃል በቃል “አንገቱን አደነደነ።”
ወይም “ንጉሣዊ አገዛዝ።”