ዘፀአት
1 ቤተሰባቸውን ይዘው ከያዕቆብ ጋር ወደ ግብፅ የመጡት የእስራኤል ወንዶች ልጆች ስም የሚከተለው ነው፦+ 2 ሮቤል፣ ስምዖን፣ ሌዊ፣ ይሁዳ፣+ 3 ይሳኮር፣ ዛብሎን፣ ቢንያም፣ 4 ዳን፣ ንፍታሌም፣ ጋድና አሴር።+ 5 ከያዕቆብ አብራክ የወጡት* በጠቅላላ 70* ነበሩ፤ ዮሴፍ ግን ቀድሞውኑም እዚያው ግብፅ ነበር።+ 6 ከጊዜ በኋላ ዮሴፍ ሞተ፤+ ወንድሞቹም ሁሉ ሞቱ፤ ያም ትውልድ በሙሉ ሞተ። 7 እስራኤላውያንም* ተዋለዱ፤ በጣም ብዙ ሆኑ፤ ቁጥራቸውም በከፍተኛ ፍጥነት እየጨመረና ኃያል እየሆኑ ሄዱ፤ ከዚህም የተነሳ ምድሪቱን ሞሏት።+
8 ከጊዜ በኋላ ዮሴፍን የማያውቅ አዲስ ንጉሥ በግብፅ ተነሳ። 9 እሱም ሕዝቦቹን እንዲህ አላቸው፦ “ይኸው እንደምታዩት የእስራኤል ሕዝብ ከእኛ ይልቅ እጅግ ብዙና ኃያል ነው።+ 10 እንግዲህ እነሱን በተመለከተ አንድ መላ እንፍጠር። ካልሆነ ግን ቁጥራቸው እየበዛ ይሄዳል፤ ደግሞም ጦርነት ከተነሳ ከጠላቶቻችን ጋር ወግነው እኛን መውጋታቸውና አገሪቱን ጥለው መኮብለላቸው አይቀርም።”
11 በመሆኑም ከባድ ሥራ በማሠራት እንዲያስጨንቋቸው የግዳጅ ሥራ የሚያሠሩ አለቆችን ሾሙባቸው፤+ እነሱም ጲቶም እና ራምሴስ+ የተባሉ ለማከማቻ የሚሆኑ ከተሞችን ለፈርዖን ገነቡ። 12 ሆኖም ይበልጥ በጨቆኗቸው መጠን ይበልጥ እየበዙና በምድሩ ላይ ይበልጥ እየተስፋፉ ስለሄዱ ግብፃውያን በእስራኤላውያን የተነሳ ከፍተኛ ፍርሃት አደረባቸው።+ 13 በመሆኑም ግብፃውያን እስራኤላውያንን ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ በባርነት ይገዟቸው ጀመር።+ 14 የሸክላ ጭቃ በማስቦካት፣ ጡብ በማሠራትና በእርሻ ላይ ማንኛውንም ዓይነት የባርነት ሥራ እንዲሠሩ በማድረግ ሕይወታቸውን መራራ አደረጉባቸው። አዎ፣ ማንኛውንም ዓይነት የባርነት ሥራ በማሠራት በጭካኔ ያንገላቷቸው ነበር።+
15 በኋላም የግብፅ ንጉሥ፣ ሺፍራ እና ፑሃ የተባሉትን ዕብራውያን አዋላጆች አነጋገራቸው፤ 16 እንዲህም አላቸው፦ “ዕብራውያን ሴቶችን በምታዋልዱበት ጊዜ+ በማዋለጃው ዱካ ላይ ተቀምጠው ስታዩ የሚወለደው ልጅ ወንድ ከሆነ ግደሉት፤ ሴት ከሆነች ግን በሕይወት ትኑር።” 17 ይሁን እንጂ አዋላጆቹ እውነተኛውን አምላክ ስለፈሩ የግብፅ ንጉሥ ያላቸውን አላደረጉም። ከዚህ ይልቅ ወንዶቹን ልጆች በሕይወት እንዲኖሩ ይተዉአቸው ነበር።+ 18 ከጊዜ በኋላም የግብፅ ንጉሥ አዋላጆቹን ጠርቶ “ወንዶቹን ልጆች በሕይወት እንዲኖሩ የተዋችኋቸው ለምንድን ነው?” አላቸው። 19 አዋላጆቹም ፈርዖንን “ዕብራውያን ሴቶች እንደ ግብፃውያን ሴቶች አይደሉም። እነሱ ብርቱዎች ስለሆኑ አዋላጇ ከመድረሷ በፊት በራሳቸው ይወልዳሉ” አሉት።
20 ስለሆነም አምላክ ለአዋላጆቹ መልካም ነገር አደረገላቸው፤ ሕዝቡም እየበዛና እጅግ ኃያል እየሆነ ሄደ። 21 አዋላጆቹ እውነተኛውን አምላክ በመፍራታቸው፣ አምላክ ከጊዜ በኋላ ቤተሰብ ሰጣቸው። 22 በመጨረሻም ፈርዖን ሕዝቡን ሁሉ “አዲስ የሚወለዱትን የዕብራውያንን ወንዶች ልጆች ሁሉ አባይ ወንዝ ውስጥ ጣሏቸው፤ ሴቶቹን ልጆች ሁሉ ግን በሕይወት እንዲኖሩ ተዉአቸው” ሲል አዘዘ።+
2 በዚያን ጊዜ ከሌዊ ነገድ የሆነ አንድ ሰው የሌዊን ልጅ አገባ።+ 2 ሴቲቱም ፀንሳ ወንድ ልጅ ወለደች። ልጁም በጣም የሚያምር መሆኑን ስታይ ለሦስት ወር ደብቃ አቆየችው።+ 3 ከዚያ በላይ ደብቃ ልታቆየው እንደማትችል+ ስታውቅ ግን የደንገል ቅርጫት* ወስዳ ቅርጫቱን በቅጥራንና በዝፍት ለቀለቀችው፤ ከዚያም ልጁን በቅርጫቱ ውስጥ አድርጋ በአባይ ወንዝ ዳር በሚገኘው ቄጠማ መሃል አስቀመጠችው። 4 እህቱ+ ግን የሕፃኑ መጨረሻ ምን እንደሚሆን ለማወቅ ራቅ ብላ ቆማ ሁኔታውን ትከታተል ነበር።
5 በዚህ ጊዜ የፈርዖን ሴት ልጅ ገላዋን ልትታጠብ ወደ አባይ ወረደች፤ ደንገጡሮቿም በአባይ ወንዝ ዳር ዳር ይሄዱ ነበር። እሷም በቄጠማው መሃል ቅርጫቱን አየች። ወዲያውኑም ቅርጫቱን እንድታመጣላት ባሪያዋን ላከቻት።+ 6 ቅርጫቱንም ስትከፍት ሕፃኑን አየችው፤ ሕፃኑም እያለቀሰ ነበር። እሷም “ይህ ልጅ ከዕብራውያን ልጆች አንዱ ነው” አለች፤ ያም ሆኖ ለሕፃኑ አዘነችለት። 7 ከዚያም የሕፃኑ እህት የፈርዖንን ልጅ “ከዕብራውያን ሴቶች መካከል ልጁን እያጠባች የምታሳድግልሽ ሞግዚት ልጥራልሽ?” አለቻት። 8 የፈርዖንም ልጅ “አዎ፣ ሂጂ!” አለቻት። ልጅቷም ወዲያውኑ ሄዳ የሕፃኑን እናት+ ጠራቻት። 9 የፈርዖን ልጅም ሴትየዋን “ይህን ሕፃን ወስደሽ እያጠባሽ አሳድጊልኝ፤ እኔም እከፍልሻለሁ” አለቻት። በመሆኑም ሴትየዋ ልጁን ወስዳ እያጠባች ታሳድገው ጀመር። 10 ልጁም ባደገ ጊዜ አምጥታ ለፈርዖን ልጅ ሰጠቻት፤ እሱም ልጇ ሆነ።+ እሷም “ከውኃ ውስጥ አውጥቼዋለሁ” በማለት ስሙን ሙሴ* አለችው።+
11 ሙሴ በጎለመሰ ጊዜ* ወንድሞቹ የተጫነባቸውን ሸክም+ ለማየት ወደ እነሱ ወጣ፤ ከዚያም ከወንድሞቹ አንዱ የሆነውን ዕብራዊ አንድ ግብፃዊ ሲደበድበው አየ። 12 በመሆኑም ወዲያና ወዲህ ተመልክቶ ማንም አለመኖሩን ካረጋገጠ በኋላ ግብፃዊውን ገድሎ አሸዋ ውስጥ ደበቀው።+
13 ሆኖም በማግስቱ ሲወጣ ሁለት ዕብራውያን እርስ በርሳቸው ሲጣሉ ተመለከተ። እሱም ጥፋተኛውን “የገዛ ወገንህን የምትመታው ለምንድን ነው?” አለው።+ 14 በዚህ ጊዜ “አንተን በእኛ ላይ አለቃና ፈራጅ ማን አደረገህ? ግብፃዊውን እንደገደልከው እኔንም ልትገድለኝ ታስባለህ?” አለው።+ ሙሴም “ይህ ነገር ታውቋል ማለት ነው!” ብሎ በማሰብ ፈራ።
15 ከዚያም ፈርዖን ይህን ነገር ሰማ፤ ሙሴንም ሊገድለው ሞከረ፤ ይሁን እንጂ ሙሴ ከፈርዖን ሸሽቶ በምድያም+ ምድር ለመኖር ሄደ፤ እዚያም በአንድ የውኃ ጉድጓድ አጠገብ ተቀመጠ። 16 በምድያም የነበረው ካህን+ ሰባት ሴቶች ልጆች ነበሩት፤ እነሱም ውኃ ቀድተው ገንዳውን በመሙላት የአባታቸውን መንጋ ውኃ ለማጠጣት መጡ። 17 ሆኖም እንደወትሮው እረኞቹ መጥተው ሴቶቹን አባረሯቸው። በዚህ ጊዜ ሙሴ ተነስቶ ለሴቶቹ አገዘላቸው፤* መንጋቸውንም አጠጣላቸው። 18 ሴቶቹም ወደ ቤት፣ ወደ አባታቸው ወደ ረኡዔል*+ በተመለሱ ጊዜ አባታቸው “ዛሬ እንዴት ቶሎ መጣችሁ?” ሲል በመገረም ጠየቃቸው። 19 እነሱም “አንድ ግብፃዊ+ ከእረኞቹ እጅ አዳነን፤ እንዲያውም ውኃ ቀድቶ መንጋችንን አጠጣልን” አሉት። 20 እሱም ልጆቹን “ታዲያ ሰውየው የት አለ? ለምን ትታችሁት መጣችሁ? አብሮን ይበላ ዘንድ ጥሩት” አላቸው። 21 ከዚያ በኋላ ሙሴ ከሰውየው ጋር ለመኖር ተስማማ፤ ሰውየውም ልጁን ሲፓራን+ ለሙሴ ዳረለት። 22 እሷም ከጊዜ በኋላ ወንድ ልጅ ወለደች፤ ሙሴም “በባዕድ አገር የምኖር የባዕድ አገር ሰው ሆንኩ”+ በማለት ስሙን ጌርሳም*+ አለው።
23 ከረጅም ጊዜ* በኋላ የግብፁ ንጉሥ ሞተ፤+ እስራኤላውያን ግን ካሉበት የባርነት ሕይወት የተነሳ መቃተታቸውንና እሮሮ ማሰማታቸውን አላቆሙም ነበር፤ ከባርነት ሕይወታቸው የተነሳ እርዳታ ለማግኘት የሚያሰሙት ጩኸት ወደ እውነተኛው አምላክ ወጣ።+ 24 ከጊዜ በኋላም አምላክ በመቃተት የሚያሰሙትን ጩኸት አዳመጠ፤+ እንዲሁም ከአብርሃም፣ ከይስሐቅና ከያዕቆብ ጋር የገባውን ቃል ኪዳኑን አሰበ።+ 25 በመሆኑም አምላክ እስራኤላውያንን አየ፤ ያሉበትንም ሁኔታ ተመለከተ።
3 ሙሴ የምድያም ካህን የሆነው የአማቱ የዮቶር+ መንጋ እረኛ ሆነ። እሱም መንጋውን እየመራ ወደ ምድረ በዳው ምዕራባዊ ክፍል ከተጓዘ በኋላ በመጨረሻ ወደ እውነተኛው አምላክ ተራራ ወደ ኮሬብ+ ደረሰ። 2 ከዚያም የይሖዋ መልአክ በቁጥቋጦ መሃል በሚነድ የእሳት ነበልባል ውስጥ ተገለጠለት።+ እሱም ትኩር ብሎ ሲመለከት ቁጥቋጦው በእሳት ቢያያዝም አለመቃጠሉን አስተዋለ። 3 ስለዚህ ሙሴ “ይህ እንግዳ ነገር ምን እንደሆነ ለማወቅና ቁጥቋጦው የማይቃጠለው ለምን እንደሆነ ለማየት እስቲ ቀረብ ልበል” አለ። 4 ይሖዋም ሙሴ ሁኔታውን ለማየት ቀረብ ማለቱን ሲመለከት ከቁጥቋጦው መሃል “ሙሴ! ሙሴ!” ሲል ጠራው፤ እሱም “አቤት” አለ። 5 ከዚያም አምላክ “ከዚህ በላይ እንዳትቀርብ። የቆምክበት ስፍራ ቅዱስ መሬት ስለሆነ ጫማህን አውልቅ” አለው።
6 እሱም በመቀጠል “እኔ የአባትህ አምላክ፣ የአብርሃም አምላክ፣+ የይስሐቅ አምላክና+ የያዕቆብ አምላክ+ ነኝ” አለው። በዚህ ጊዜ ሙሴ እውነተኛውን አምላክ ለማየት ስለፈራ ፊቱን ከለለ። 7 ከዚያም ይሖዋ እንዲህ አለው፦ “በግብፅ የሚኖረውን የሕዝቤን መከራ በእርግጥ አይቻለሁ፤ አስገድደው በሚያሠሯቸው ሰዎች የተነሳ የሚያሰሙትን ጩኸት ሰምቻለሁ፤ እየደረሰባቸው ያለውንም ሥቃይ በሚገባ አውቃለሁ።+ 8 እኔም ከግብፃውያን እጅ ልታደጋቸው+ እንዲሁም ከዚያ ምድር አውጥቼ ወደ ከነአናውያን፣ ወደ ሂታውያን፣ ወደ አሞራውያን፣ ወደ ፈሪዛውያን፣ ወደ ሂዋውያንና ወደ ኢያቡሳውያን ግዛት ይኸውም ወተትና ማር ወደምታፈሰው መልካምና ሰፊ ምድር+ ላስገባቸው እወርዳለሁ።+ 9 እነሆ የእስራኤል ሕዝብ የሚያሰማው ጩኸት ወደ እኔ ደርሷል፤ ግብፃውያኑ እነሱን በመጨቆን እያደረሱባቸው ያለውን በደል ተመልክቻለሁ።+ 10 ስለዚህ አሁን ና፤ ወደ ፈርዖን እልክሃለሁ፤ አንተም ሕዝቤን እስራኤልን ከግብፅ ታወጣለህ።”+
11 ይሁን እንጂ ሙሴ እውነተኛውን አምላክ “ወደ ፈርዖን የምሄደውና እስራኤላውያንን ከግብፅ የማወጣው ለመሆኑ እኔ ማን ነኝ?” አለው። 12 እሱም በዚህ ጊዜ “እኔ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፤+ የላክሁህ እኔ ለመሆኔም ምልክቱ ይህ ነው፦ ሕዝቡን ከግብፅ ካወጣሃቸው በኋላ እውነተኛውን አምላክ በዚህ ተራራ ላይ ታገለግላላችሁ”*+ አለው።
13 ሆኖም ሙሴ እውነተኛውን አምላክ “ወደ እስራኤላውያን ሄጄ ‘የአባቶቻችሁ አምላክ ወደ እናንተ ልኮኛል’ ስላቸው እነሱ ደግሞ ‘ስሙ ማን ነው?’+ ብለው ቢጠይቁኝ ምን ልበላቸው?” አለው። 14 በዚህ ጊዜ አምላክ ሙሴን “መሆን የምፈልገውን እሆናለሁ”*+ አለው። በመቀጠልም “እስራኤላውያንን ‘“እሆናለሁ” ወደ እናንተ ልኮኛል’+ በላቸው” አለው። 15 ከዚያም አምላክ ሙሴን በድጋሚ እንዲህ አለው፦
“እስራኤላውያንን እንዲህ በላቸው፦ ‘የአባቶቻችሁ አምላክ፣ የአብርሃም አምላክ፣+ የይስሐቅ አምላክና+ የያዕቆብ አምላክ+ የሆነው ይሖዋ ወደ እናንተ ልኮኛል።’ ይህ ለዘላለም ስሜ ነው፤+ ከትውልድ እስከ ትውልድ የምታወሰውም በዚህ ነው። 16 አሁን ሄደህ የእስራኤልን ሽማግሌዎች ሰብስብ፤ እንዲህም በላቸው፦ ‘የአባቶቻችሁ አምላክ፣ የአብርሃም፣ የይስሐቅና የያዕቆብ አምላክ የሆነው ይሖዋ ተገልጦልኝ እንዲህ አለኝ፦ “እናንተንም ሆነ ግብፅ ውስጥ እየደረሰባችሁ ያለውን ነገር በእርግጥ ተመልክቻለሁ።+ 17 በመሆኑም እንዲህ አልኩ፦ ግብፃውያን ከሚያደርሱባችሁ መከራ አውጥቼ+ ከነአናውያን፣ ሂታውያን፣ አሞራውያን፣+ ፈሪዛውያን፣ ሂዋውያንና ኢያቡሳውያን+ ወደሚኖሩባት ወተትና ማር ወደምታፈሰው ምድር+ አስገባችኋለሁ።”’
18 “እነሱም በእርግጥ ቃልህን ይሰማሉ፤+ አንተና የእስራኤል ሽማግሌዎችም ወደ ግብፁ ንጉሥ ሄዳችሁ እንዲህ በሉት፦ ‘የዕብራውያን አምላክ ይሖዋ+ አነጋግሮን ነበር። በመሆኑም እባክህ ለአምላካችን ለይሖዋ መሥዋዕት ለማቅረብ የሦስት ቀን መንገድ ወደ ምድረ በዳ እንድንጓዝ ፍቀድልን።’+ 19 ይሁንና የግብፁ ንጉሥ ኃያል የሆነ ክንድ ካላስገደደው በስተቀር እንድትሄዱ እንደማይፈቅድላችሁ እኔ ራሴ በሚገባ አውቃለሁ።+ 20 በመሆኑም እጄን እዘረጋለሁ፤ ግብፅንም በመካከሏ በምፈጽማቸው ድንቅ ነገሮች ሁሉ እመታለሁ፤ ከዚያ በኋላ ይለቃችኋል።+ 21 እኔም ለዚህ ሕዝብ በግብፃውያን ፊት ሞገስ እሰጠዋለሁ፤ በምትወጡበትም ጊዜ በምንም ዓይነት ባዶ እጃችሁን አትሄዱም።+ 22 እያንዳንዷ ሴት ከጎረቤቷና ቤቷ ካረፈችው ሴት የብርና የወርቅ ዕቃዎችን እንዲሁም ልብሶችን ትጠይቅ፤ እነዚህንም ለወንዶችና ለሴቶች ልጆቻችሁ ታደርጉላቸዋላችሁ፤ ግብፃውያኑንም ትበዘብዛላችሁ።”+
4 ሆኖም ሙሴ “‘ይሖዋ አልተገለጠልህም’ ቢሉኝና ባያምኑኝስ? ቃሌንስ ባይሰሙ?”+ አለው። 2 ይሖዋም “በእጅህ የያዝከው ምንድን ነው?” ሲል ጠየቀው። እሱም መልሶ “በትር ነው” አለ። 3 እሱም “መሬት ላይ ጣለው” አለው። እሱም መሬት ላይ ጣለው፤ በትሩም እባብ ሆነ፤+ ሙሴም ከእባቡ ሸሸ። 4 በዚህ ጊዜ ይሖዋ ሙሴን “እጅህን ዘርግተህ ጅራቱን ያዘው” አለው። እሱም እጁን ዘርግቶ ያዘው፤ እባቡም በእጁ ላይ እንደገና በትር ሆነ። 5 ከዚያም አምላክ “ይህ የሆነው የአባቶቻቸው አምላክ፣ የአብርሃም አምላክ፣ የይስሐቅ አምላክና የያዕቆብ አምላክ ይሖዋ+ እንደተገለጠልህ እንዲያምኑ ነው” አለው።+
6 ይሖዋም በድጋሚ “እባክህ እጅህን ወዳጣፋኸው ልብስ ውስጥ አስገባ” አለው። እሱም እጁን ወዳጣፋው ልብስ ውስጥ አስገባ። ባወጣውም ጊዜ እጁ በሥጋ ደዌ ተመቶ ልክ እንደ በረዶ ነጭ ሆኖ ነበር!+ 7 ከዚያም “እጅህን ወዳጣፋኸው ልብስ ውስጥ መልሰህ አስገባው” አለው። እሱም እጁን መልሶ ልብሱ ውስጥ አስገባው። እጁንም ከልብሱ ውስጥ ባወጣው ጊዜ እጁ ተመልሶ እንደ ሌላው የሰውነቱ ክፍል ሆነ! 8 እሱም እንዲህ አለው፦ “ባያምኑህ ወይም የመጀመሪያውን ተአምራዊ ምልክት ችላ ቢሉ እንኳ የኋለኛውን ተአምራዊ ምልክት በእርግጥ አምነው ይቀበላሉ።+ 9 እንደዛም ሆኖ እነዚህን ሁለት ምልክቶች ባያምኑና ቃልህን ለመስማት ፈቃደኛ ባይሆኑ ከአባይ ወንዝ ውኃ ቀድተህ በደረቁ መሬት ላይ አፍስሰው፤ ከአባይ የቀዳኸው ውኃ በደረቁ መሬት ላይ ደም ይሆናል።”+
10 ሙሴም ይሖዋን “ይሖዋ ሆይ፣ ይቅርታ አድርግልኝ፤ እኔ ከዚህ በፊትም ሆነ አንተ አገልጋይህን ካነጋገርክበት ጊዜ ጀምሮ ፈጽሞ አንደበተ ርቱዕ አይደለሁም፤ ንግግር የማልችልና* ተብታባ ሰው ነኝ” አለው።+ 11 ይሖዋም እንዲህ አለው፦ “ለሰው አፍ የፈጠረለት ማን ነው? ሰዎችን ዱዳ፣ ደንቆሮ ወይም ዕውር የሚያደርግ አሊያም ለሰዎች የዓይን ብርሃን የሚሰጥ ማን ነው? እኔ ይሖዋ አይደለሁም? 12 በል አሁን ሂድ፤ በምትናገርበት ጊዜ እኔ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፤* የምትናገረውንም ነገር አስተምርሃለሁ።”+ 13 እሱ ግን “ይሖዋ ሆይ፣ ይቅርታ አድርግልኝ፤ እባክህ መላክ የፈለግከውን ሌላ ማንኛውንም ሰው ላክ” አለው። 14 በዚህ ጊዜ የይሖዋ ቁጣ በሙሴ ላይ ነደደ፤ እንዲህም አለው፦ “እሺ ሌዋዊው ወንድምህ አሮንስ?+ እሱ በደንብ መናገር እንደሚችል አውቃለሁ። ደግሞም አንተን ለማግኘት አሁን ወደዚህ እየመጣ ነው። በሚያይህም ጊዜ ልቡ በደስታ ይሞላል።+ 15 ስለሆነም እሱን አነጋግረው፤ ቃላቱንም በአንደበቱ አኑር፤+ በምትናገሩበትም ጊዜ ከአንተና ከእሱ ጋር እሆናለሁ፤+ ምን ማድረግ እንዳለባችሁም አስተምራችኋለሁ። 16 እሱም አንተን ወክሎ ለሕዝቡ ይናገራል፤ እንደ ቃል አቀባይም ይሆንልሃል፤ አንተም ለእሱ እንደ አምላክ ትሆናለህ።*+ 17 ይህን በትር በእጅህ ይዘህ ትሄዳለህ፤ በእሱም ተአምራዊ ምልክቶቹን ትፈጽማለህ።”+
18 ስለዚህ ሙሴ ወደ አማቱ ወደ ዮቶር+ ተመልሶ በመሄድ “እስካሁን በሕይወት መኖር አለመኖራቸውን አይ ዘንድ እባክህ በግብፅ ወዳሉት ወንድሞቼ ተመልሼ ልሂድ” አለው። ዮቶርም ሙሴን “በሰላም ሂድ” አለው። 19 ከዚያ በኋላ ይሖዋ ሙሴን በምድያም ሳለ “ሂድ፤ ወደ ግብፅ ተመለስ፤ ነፍስህን ለማጥፋት የሚፈልጉት ሰዎች በሙሉ ሞተዋል” አለው።+
20 ከዚያም ሙሴ ሚስቱንና ልጆቹን በአህያ ላይ አስቀምጦ ወደ ግብፅ ምድር ለመመለስ ጉዞ ጀመረ። የእውነተኛውን አምላክ በትርም በእጁ ይዞ ነበር። 21 ይሖዋም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ወደ ግብፅ ከተመለስክ በኋላ፣ በሰጠሁህ ኃይል የምታከናውናቸውን ተአምራት ሁሉ በፈርዖን ፊት መፈጸም እንዳለብህ አትዘንጋ።+ እኔ ግን ልቡ እንዲደነድን እፈቅዳለሁ፤+ እሱም ሕዝቡን አይለቅም።+ 22 ፈርዖንንም እንዲህ በለው፦ ‘ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “እስራኤል ልጄ ነው፤ አዎ፣ የበኩር ልጄ ነው።+ 23 እንግዲህ ‘እንዲያገለግለኝ ልጄን ልቀቅ’ ብዬሃለሁ። ለመልቀቅ ፈቃደኛ ካልሆንክ ግን ልጅህን፣ አዎ የበኩር ልጅህን እገድላለሁ።”’”+
24 ይሖዋም+ በመንገድ ላይ ባለው የእንግዳ ማረፊያ ስፍራ አገኘው፤ እሱንም ሊገድለው ፈልጎ ነበር።+ 25 በመጨረሻም ሲፓራ+ ባልጩት ወስዳ ልጇን ገረዘችው፤ ሸለፈቱን እግሩን ካስነካች በኋላም “ይህ የሆነው አንተ ለእኔ የደም ሙሽራ ስለሆንክ ነው” አለች። 26 ስለሆነም እንዲሄድ ፈቀደለት። እሷም በዚህ ጊዜ በግርዛቱ የተነሳ “የደም ሙሽራ” አለች።
27 ይሖዋም አሮንን “ሙሴን ለማግኘት ወደ ምድረ በዳ ሂድ” አለው።+ እሱም ሄደ፤ በእውነተኛውም አምላክ ተራራ+ ላይ አገኘው፤ ከዚያም ሳመው። 28 ሙሴም ይሖዋ እንዲናገር የላከውን ቃል ሁሉ+ እንዲሁም እንዲፈጽማቸው ያዘዘውን ተአምራዊ ምልክቶች ሁሉ+ ለአሮን ነገረው። 29 ከዚህ በኋላ ሙሴና አሮን ሄደው የእስራኤልን ሽማግሌዎች በሙሉ ሰበሰቡ።+ 30 አሮንም ይሖዋ ለሙሴ የነገረውን ቃል ሁሉ ነገራቸው፤ እሱም በሕዝቡ ፊት ተአምራዊ ምልክቶቹን አደረገ።+ 31 በዚህ ጊዜ ሕዝቡ አመነ።+ ይሖዋ ፊቱን ወደ እስራኤላውያን እንደመለሰና+ ሥቃያቸውንም እንዳየ+ ሲሰሙ ተደፍተው ሰገዱ።
5 ከዚያ በኋላ ሙሴና አሮን ወደ ፈርዖን ገብተው እንዲህ አሉት፦ “የእስራኤል አምላክ ይሖዋ ‘በምድረ በዳ በዓል እንዲያከብርልኝ ሕዝቤን ልቀቅ’ ይላል።” 2 ፈርዖን ግን እንዲህ አለ፦ “የእሱን ቃል ሰምቼ እስራኤልን የምለቀው ለመሆኑ ይሖዋ ማነው?+ እኔ ይሖዋ የምትሉትን ፈጽሞ አላውቅም፤ እስራኤልንም አለቅም።”+ 3 ሆኖም እነሱ እንዲህ አሉት፦ “የዕብራውያን አምላክ አነጋግሮን ነበር። በመሆኑም እባክህ የሦስት ቀን መንገድ ወደ ምድረ በዳ ተጉዘን ለአምላካችን ለይሖዋ መሥዋዕት ማቅረብ እንፈልጋለን፤+ ካልሆነ ግን በበሽታ ወይም በሰይፍ ይጨርሰናል።” 4 የግብፅም ንጉሥ “ሙሴና አሮን፣ ሕዝቡን ሥራ የምታስፈቱት ለምንድን ነው? አርፋችሁ ወደ ጉልበት ሥራችሁ ተመለሱ!” አላቸው።+ 5 ፈርዖንም በመቀጠል “የምድሩ ሕዝብ ምን ያህል ብዙ እንደሆነ ተመልከት፤ አንተ ደግሞ ሥራ ልታስፈታቸው ነው” አለ።
6 ፈርዖንም በዚያኑ ዕለት የሥራ ኃላፊዎቹንና አሠሪዎቹን እንዲህ ሲል አዘዛቸው፦ 7 “ከአሁን በኋላ ለጡብ መሥሪያ የሚሆን ጭድ ለሕዝቡ እንዳትሰጡ።+ ራሳቸው ሄደው ጭድ ይሰብስቡ። 8 ሆኖም በፊት ይሠሩት የነበረውን ያህል ጡብ ሠርተው እንዲያስረክቡ አድርጉ። ዘና እያሉ ስለሆነ* ማስረከብ ከሚጠበቅባቸው ጡብ ምንም እንዳትቀንሱላቸው። ‘መሄድ እንፈልጋለን፤ ሄደን ለአምላካችን መሥዋዕት ማቅረብ እንፈልጋለን!’ እያሉ የሚጮኹት ለዚህ ነው። 9 ለሐሰት ወሬ ጆሯቸውን እንዳይሰጡ ሥራውን አክብዱባቸው፤ እንዲሁም ፋታ አሳጧቸው።”
10 ስለዚህ የሥራ ኃላፊዎቹና+ አሠሪዎቹ ወጥተው ለሕዝቡ እንዲህ አሉ፦ “ፈርዖን እንዲህ ይላል፦ ‘ከእንግዲህ ጭድ አላቀርብላችሁም። 11 ራሳችሁ ሄዳችሁ ከየትም ፈልጋችሁ ጭድ አምጡ፤ ሥራችሁ ግን በምንም ዓይነት አይቀነስም።’” 12 ከዚያም ሕዝቡ እንደ ጭድ ሆኖ የሚያገለግለውን የእህል ቆረን* ለመሰብሰብ በመላው የግብፅ ምድር ተሰማራ። 13 የሥራ ኃላፊዎቹም “እያንዳንዳችሁ ጭድ ይቀርብላችሁ በነበረበት ጊዜ ታደርጉት እንደነበረው ሁሉ አሁንም በየዕለቱ የሚጠበቅባችሁን ሥራ ሠርታችሁ ማጠናቀቅ አለባችሁ” እያሉ ያስገድዷቸው ነበር። 14 በተጨማሪም የፈርዖን የሥራ ኃላፊዎች የሾሟቸው የእስራኤላውያን አሠሪዎች ተገረፉ።+ እነሱንም “ቀደም ሲል ሠርታችሁ ታስረክቡት የነበረውን ያህል ጡብ ሠርታችሁ ያላስረከባችሁት ለምንድን ነው? ትናንትም ሆነ ዛሬ እንዲህ አላደረጋችሁም” ብለው ጠየቋቸው።
15 በመሆኑም የእስራኤላውያን አሠሪዎች ወደ ፈርዖን ገብተው እንዲህ በማለት እሮሯቸውን አሰሙ፦ “በአገልጋዮችህ ላይ እንዲህ ያለ ድርጊት የምትፈጽመው ለምንድን ነው? 16 ለእኛ ለአገልጋዮችህ ምንም ጭድ አይሰጠንም፤ እነሱ ግን ‘ጡብ ሥሩ!’ ይሉናል። ጥፋቱ የገዛ ሰዎችህ ሆኖ ሳለ እኛ አገልጋዮችህ እንገረፋለን።” 17 እሱ ግን እንዲህ አላቸው፦ “እናንተ እኮ ተዝናንታችኋል፤* አዎ፣ ዘና እያላችሁ ነው!*+ ‘መሄድ እንፈልጋለን፤ ሄደን ለይሖዋ መሥዋዕት ማቅረብ እንፈልጋለን!’ የምትሉት ለዚህ ነው።+ 18 በሉ አሁን ወደ ሥራችሁ ተመለሱ! ምንም ጭድ አይቀርብላችሁም፤ ሆኖም የሚጠበቅባችሁን ያህል ጡብ መሥራት አለባችሁ።”
19 የእስራኤል አሠሪዎችም “በየዕለቱ ማስረከብ ከሚጠበቅባችሁ ጡብ ምንም ማጉደል የለባችሁም” የሚለውን ትእዛዝ ሲሰሙ ከባድ ችግር ውስጥ መውደቃቸውን ተረዱ። 20 እነሱም ፈርዖንን አነጋግረው ሲወጡ በዚያ ቆመው ይጠብቋቸው የነበሩትን ሙሴንና አሮንን አገኟቸው። 21 እነሱም እንዲህ አሏቸው፦ “በፈርዖንና በአገልጋዮቹ ፊት እንድንጠላ ስላደረጋችሁና* እንዲገድሉን በእጃቸው ሰይፍ ስለሰጣችኋቸው ይሖዋ ይይላችሁ፤ ደግሞም ይፍረድባችሁ።”+ 22 በዚህ ጊዜ ሙሴ ወደ ይሖዋ ተመልሶ እንዲህ አለው፦ “ይሖዋ ሆይ፣ ይህን ሕዝብ ለመከራ የዳረግከው ለምንድን ነው? እኔንስ የላክኸኝ ለምንድን ነው? 23 ፈርዖን በስምህ ለመናገር ወደ እሱ ከገባሁበት+ ጊዜ አንስቶ ይህን ሕዝብ ይበልጥ ማንገላታቱን ቀጥሏል፤+ አንተም ብትሆን ሕዝብህን አላዳንክም።”+
6 በመሆኑም ይሖዋ ሙሴን “አሁን በፈርዖን ላይ የማደርገውን ታያለህ።+ በኃያል ክንድ ተገዶ ይለቃቸዋል፤ በኃያል ክንድ ተገዶም ከምድሩ እንዲወጡ ያደርጋቸዋል” አለው።+
2 ከዚያም አምላክ ሙሴን እንዲህ አለው፦ “እኔ ይሖዋ ነኝ። 3 ለአብርሃም፣ ለይስሐቅና ለያዕቆብ ሁሉን ቻይ አምላክ+ ሆኜ እገለጥላቸው ነበር፤ ይሖዋ የሚለውን ስሜን+ በተመለከተ ግን ራሴን ሙሉ በሙሉ አልገለጥኩላቸውም።+ 4 በተጨማሪም የከነአንን ምድር ማለትም የባዕድ አገር ሰው ሆነው የኖሩባትን ምድር ልሰጣቸው ከእነሱ ጋር ቃል ኪዳን ገብቻለሁ።+ 5 እንግዲህ አሁን ግብፃውያን በባርነት እየገዟቸው ያሉት የእስራኤል ሰዎች እያሰሙት ያለውን የሥቃይ ጩኸት ሰምቻለሁ፤ ቃል ኪዳኔንም አስባለሁ።+
6 “ስለዚህ እስራኤላውያንን እንዲህ በላቸው፦ ‘እኔ ይሖዋ ነኝ፤ ከግብፃውያን ከባድ ሸክም ነፃ አወጣችኋለሁ፤ ከጫኑባችሁም የባርነት ቀንበር አላቅቃችኋለሁ፤+ በተዘረጋ* ክንድና በታላቅ ፍርድ እታደጋችኋለሁ።+ 7 የራሴ ሕዝብ አድርጌ እወስዳችኋለሁ፤ አምላካችሁም እሆናለሁ፤+ እናንተም ከግብፃውያን ከባድ ሸክም ነፃ የማወጣችሁ እኔ አምላካችሁ ይሖዋ መሆኔን በእርግጥ ታውቃላችሁ። 8 ለአብርሃም፣ ለይስሐቅና ለያዕቆብ ለመስጠት እጄን አንስቼ ወደማልኩላቸው ምድር አስገባችኋለሁ፤ ርስት አድርጌም እሰጣችኋለሁ።+ እኔ ይሖዋ ነኝ።’”+
9 ከዚያም ሙሴ ለእስራኤላውያን ይህን መልእክት ነገራቸው፤ እነሱ ግን ተስፋ ከመቁረጣቸውና አስከፊ ከሆነው የባርነት ሕይወታቸው የተነሳ ሊሰሙት ፈቃደኞች አልሆኑም።+
10 ይሖዋም ሙሴን እንዲህ አለው፦ 11 “ወደ ግብፁ ንጉሥ ወደ ፈርዖን ገብተህ እስራኤላውያንን ከምድሩ እንዲያሰናብታቸው ንገረው።” 12 ሆኖም ሙሴ “እንግዲህ እስራኤላውያን ሊሰሙኝ ፈቃደኛ አልሆኑም፤+ ታዲያ የመናገር ችግር ያለብኝን* እኔን፣ ፈርዖን እንዴት ብሎ ሊሰማኝ ይችላል?”+ በማለት ለይሖዋ መለሰ። 13 ይሖዋ ግን እስራኤላውያንን ከግብፅ ምድር ለማውጣት ለእነሱና ለግብፁ ንጉሥ ለፈርዖን ማስተላለፍ ያለባቸውን ትእዛዝ ለሙሴና ለአሮን በድጋሚ ነገራቸው።
14 የአባቶቻቸው ቤት መሪዎችም እነዚህ ናቸው፦ የእስራኤል የበኩር ልጅ የሮቤል+ ወንዶች ልጆች ሃኖክ፣ ፓሉ፣ ኤስሮን እና ካርሚ ነበሩ።+ እነዚህ የሮቤል ቤተሰቦች ናቸው።
15 የስምዖን ወንዶች ልጆች የሙኤል፣ ያሚን፣ ኦሃድ፣ ያኪን፣ ጾሃር እና ከአንዲት ከነአናዊት የወለደው ሻኡል ነበሩ።+ እነዚህ የስምዖን ቤተሰቦች ናቸው።
16 የሌዊ+ ወንዶች ልጆች በየቤተሰብ የዘር ሐረጋቸው ስማቸው ይህ ነው፦ ጌድሶን፣ ቀአት እና ሜራሪ።+ ሌዊ 137 ዓመት ኖረ።
17 የጌድሶን ወንዶች ልጆች በየቤተሰባቸው ሊብኒ እና ሺምአይ ነበሩ።+
18 የቀአት ወንዶች ልጆች አምራም፣ ይጽሃር፣ ኬብሮን እና ዑዚኤል ነበሩ።+ ቀአት 133 ዓመት ኖረ።
19 የሜራሪ ወንዶች ልጆች ማህሊ እና ሙሺ ነበሩ።
የሌዋውያን ቤተሰቦች በየቤተሰብ የዘር ሐረጋቸው እነዚህ ነበሩ።+
20 አምራም የአባቱን እህት ዮካቤድን አገባ።+ እሷም አሮንንና ሙሴን ወለደችለት።+ አምራም 137 ዓመት ኖረ።
21 የይጽሃር ወንዶች ልጆች ቆሬ፣+ ኔፌግ እና ዚክሪ ነበሩ።
22 የዑዚኤል ወንዶች ልጆች ሚሳኤል፣ ኤሊጻፋን+ እና ሲትሪ ነበሩ።
23 አሮን የነአሶን+ እህት የሆነችውን የአሚናዳብን ልጅ ኤሊሼባን አገባ። እሷም ናዳብን፣ አቢሁን፣ አልዓዛርን እና ኢታምርን ወለደችለት።+
24 የቆሬ ወንዶች ልጆች አሲር፣ ሕልቃና እና አቢያሳፍ ነበሩ።+ የቆሬያውያን ቤተሰቦች እነዚህ ናቸው።+
25 የአሮን ልጅ አልዓዛር+ ከፑቲኤል ልጆች መካከል አንዷን አገባ። እሷም ፊንሃስን+ ወለደችለት።
የሌዋውያን የአባቶች ቤት መሪዎች በየቤተሰባቸው እነዚህ ናቸው።+
26 ይሖዋ “የእስራኤልን ሕዝብ በቡድን በቡድን* በማድረግ ከግብፅ ምድር ይዛችሁ ውጡ”+ ብሎ የነገራቸው አሮንና ሙሴ እነዚህ ናቸው። 27 የእስራኤልን ሕዝብ ከግብፅ ለማውጣት የግብፁን ንጉሥ ፈርዖንን ያነጋገሩት ሙሴና አሮን ነበሩ።+
28 ይሖዋ በግብፅ ምድር ሙሴን ባነጋገረበት በዚያ ዕለት 29 ይሖዋ ሙሴን “እኔ ይሖዋ ነኝ። የምነግርህን ሁሉ ለግብፁ ንጉሥ ለፈርዖን ንገረው” አለው። 30 ከዚያም ሙሴ ይሖዋን “እኔ እንደሆነ የመናገር ችግር አለብኝ፤* ታዲያ ፈርዖን እንዴት ብሎ ይሰማኛል?” አለው።+
7 ይሖዋም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “እንግዲህ አንተን ለፈርዖን እንደ አምላክ አድርጌሃለሁ፤* የገዛ ወንድምህ አሮን ደግሞ የአንተ ነቢይ ይሆናል።+ 2 አንተም የማዝህን ሁሉ ደግመህ ትናገራለህ፤ ወንድምህ አሮንም ለፈርዖን ይነግረዋል፤ እሱም እስራኤላውያንን ከምድሩ እንዲወጡ ይለቃቸዋል። 3 እኔ ደግሞ የፈርዖን ልብ እንዲደነድን እፈቅዳለሁ፤+ በግብፅ ምድርም ምልክቶቼንና ተአምራቴን አበዛለሁ።+ 4 ፈርዖን ግን አይሰማችሁም፤ እኔም በግብፅ ምድር ላይ እጄን አሳርፋለሁ፤ ሠራዊቴን ይኸውም ሕዝቤ የሆኑትን እስራኤላውያንን በታላቅ ፍርድ ከግብፅ ምድር አወጣቸዋለሁ።+ 5 በግብፅ ላይ እጄን ስዘረጋና እስራኤላውያንን ከመካከላቸው ሳወጣ ግብፃውያን እኔ ይሖዋ መሆኔን በእርግጥ ያውቃሉ።”+ 6 ሙሴና አሮን ይሖዋ እንዳዘዛቸው አደረጉ፤ ልክ እንደተባሉት አደረጉ። 7 ከፈርዖን ጋር በተነጋገሩበት ጊዜ ሙሴ የ80 ዓመት ሰው፣ አሮን ደግሞ የ83 ዓመት ሰው ነበር።+
8 በዚህ ጊዜ ይሖዋ ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፦ 9 “ምናልባት ፈርዖን ‘እስቲ ተአምር አሳዩ’ ቢላችሁ አሮንን ‘በትርህን ወስደህ በፈርዖን ፊት ጣለው’ በለው። በትሩም ትልቅ እባብ ይሆናል።”+ 10 ስለሆነም ሙሴና አሮን ወደ ፈርዖን ገብተው ልክ ይሖዋ እንዳዘዛቸው አደረጉ። አሮንም በትሩን በፈርዖንና በአገልጋዮቹ ፊት ጣለው፤ በትሩም ትልቅ እባብ ሆነ። 11 ይሁንና ፈርዖን ጠቢባኑንና መተተኞቹን ጠራ፤ አስማት የሚሠሩ የግብፅ ካህናትም+ በአስማታቸው* ተመሳሳይ ነገር አደረጉ።+ 12 እያንዳንዳቸውም በትራቸውን ጣሉ፤ በትሮቹም ትላልቅ እባቦች ሆኑ፤ ይሁን እንጂ የአሮን በትር የእነሱን በትሮች ዋጠ። 13 ያም ሆኖ የፈርዖን ልብ ደነደነ፤+ ልክ ይሖዋ እንዳለውም ያሉትን ነገር አልሰማቸውም።
14 ከዚያም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ “የፈርዖን ልብ ደንድኗል።+ እሱም ሕዝቡን ለመልቀቅ እንቢተኛ ሆኗል። 15 በማለዳ ወደ ፈርዖን ሂድ። እሱም ወደ ውኃው ይወርዳል! አንተም እሱን ለማግኘት በአባይ ወንዝ ዳር ቁም፤ ወደ እባብ ተለውጦ የነበረውንም በትር በእጅህ ያዝ።+ 16 እንዲህም በለው፦ ‘የዕብራውያን አምላክ ይሖዋ ወደ አንተ ልኮኛል፤+ እሱም “በምድረ በዳ እንዲያገለግለኝ ሕዝቤን ልቀቅ” ብሎሃል፤ ይኸው አንተ ግን እስካሁን ድረስ አልታዘዝክም። 17 እንግዲህ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “እኔ ይሖዋ እንደሆንኩ በዚህ ታውቃለህ።+ ይኸው በበትሬ በአባይ ወንዝ ውስጥ ያለውን ውኃ እመታለሁ፤ ውኃውም ወደ ደም ይለወጣል። 18 በአባይ ውስጥ ያሉት ዓሣዎች ይሞታሉ፤ አባይም ይከረፋል፤ ግብፃውያንም ከአባይ ወንዝ ውኃ መጠጣት አይችሉም።”’”
19 ከዚያም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ “አሮንን እንዲህ በለው፦ ‘የግብፅ ውኃዎች ይኸውም ወንዞቿ፣ የመስኖ ቦዮቿ፣* ረግረጋማ ቦታዎቿና+ የተጠራቀሙት ውኃዎቿ ሁሉ ወደ ደም እንዲለወጡ በትርህን ወስደህ በእነሱ ላይ እጅህን ዘርጋ።’+ በመላው የግብፅ ምድር ላይ ሌላው ቀርቶ ከእንጨትና ከድንጋይ በተሠሩ ዕቃዎች ውስጥ ደም ይሆናል።” 20 ሙሴና አሮን ወዲያውኑ ልክ ይሖዋ እንዳዘዛቸው አደረጉ። እሱም ፈርዖንና አገልጋዮቹ እያዩ በትሩን አንስቶ በአባይ ወንዝ ውስጥ ያለውን ውኃ መታ፤ በወንዙ ውስጥ የነበረውም ውኃ በሙሉ ወደ ደም ተለወጠ።+ 21 በወንዙ ውስጥ የነበሩት ዓሣዎች ሞቱ፤+ ወንዙም መከርፋት ጀመረ፤ ግብፃውያንም ከአባይ ወንዝ ውኃ መጠጣት አልቻሉም፤+ በመላው የግብፅ ምድር ላይም ደም ነበር።
22 ይሁንና አስማት የሚሠሩ የግብፅ ካህናትም በሚስጥራዊ ጥበባቸው ተመሳሳይ ነገር አደረጉ፤+ በመሆኑም የፈርዖን ልብ ደነደነ፤ ልክ ይሖዋ እንዳለውም እነሱን ለመስማት እንቢተኛ ሆነ።+ 23 ከዚያም ፈርዖን ተመልሶ ወደ ቤቱ ሄደ፤ ይህን ከቁም ነገር አልቆጠረውም። 24 ግብፃውያን ሁሉ ከአባይ ወንዝ ውኃ መጠጣት ስላልቻሉ የሚጠጣ ውኃ ለማግኘት የአባይን ዳርቻ ተከትለው ጉድጓዶችን ይቆፍሩ ነበር። 25 ይሖዋ አባይን ከመታ ሰባት ቀን አለፈ።
8 ከዚያም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ወደ ፈርዖን ገብተህ እንዲህ በለው፦ ‘ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “እንዲያገለግለኝ ሕዝቤን ልቀቅ።+ 2 እነሱን ለመልቀቅ አሁንም ፈቃደኛ የማትሆን ከሆነ ምድርህን በሙሉ በእንቁራሪት መቅሰፍት እመታለሁ።+ 3 የአባይም ወንዝ በእንቁራሪቶች ይሞላል፤ እነሱም ወጥተው ወደ ቤትህ፣ ወደ መኝታ ክፍልህ ይገባሉ፤ አልጋህም ላይ ይወጣሉ፤ እንዲሁም ወደ አገልጋዮችህ ቤቶች ይገባሉ፤ ሕዝብህም ላይ ይወጣሉ፤ መጋገሪያ ምድጃዎችህና ቡሃቃዎችህም ውስጥ ይገባሉ።+ 4 እንቁራሪቶቹ በአንተ፣ በሕዝብህና በአገልጋዮችህ ሁሉ ላይ ይወጡባችኋል።”’”
5 በኋላም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ “አሮንን እንዲህ በለው፦ ‘እጅህን ሰንዝረህ ወንዞቹን፣ የአባይ ወንዝ የመስኖ ቦዮቹንና ረግረጋማ ቦታዎቹን በበትርህ በመምታት እንቁራሪቶቹ በግብፅ ምድር ላይ እንዲወጡ አድርግ።’” 6 ስለዚህ አሮን በግብፅ ውኃዎች ላይ እጁን ሰነዘረ፤ እንቁራሪቶቹም እየወጡ የግብፅን ምድር መውረር ጀመሩ። 7 ይሁን እንጂ አስማተኞቹ ካህናትም በሚስጥራዊ ጥበባቸው ተመሳሳይ ነገር ፈጸሙ፤ እነሱም እንቁራሪቶች በግብፅ ምድር ላይ እንዲወጡ አደረጉ።+ 8 ከዚያም ፈርዖን ሙሴንና አሮንን ጠርቶ “ሕዝቡ ለይሖዋ መሥዋዕት እንዲያቀርብ መልቀቅ ስለምፈልግ እንቁራሪቶቹን ከእኔም ሆነ ከሕዝቤ ላይ እንዲያስወግድ ይሖዋን ለምኑልኝ”+ አላቸው። 9 ከዚያም ሙሴ ፈርዖንን እንዲህ አለው፦ “እንቁራሪቶቹ ከአንተ፣ ከአገልጋዮችህ፣ ከሕዝብህና ከቤቶችህ ይወገዱ ዘንድ አምላክን እንድለምንልህ የምትፈልገው መቼ እንደሆነ የመወሰኑን ጉዳይ ለአንተ ትቼዋለሁ። እንቁራሪቶቹ በአባይ ወንዝ ውስጥ ብቻ ተወስነው ይቀራሉ።” 10 እሱም “ነገ ይሁን” አለው። በመሆኑም ሙሴ እንዲህ አለው፦ “እንደ አምላካችን እንደ ይሖዋ ያለ ማንም እንደሌለ+ እንድታውቅ ልክ እንዳልከው ይሆናል። 11 እንቁራሪቶቹ ከአንተ፣ ከቤቶችህ፣ ከአገልጋዮችህና ከሕዝቦችህ ይወገዳሉ። በአባይ ወንዝ ውስጥ ብቻ ተወስነው ይቀራሉ።”+
12 ሙሴና አሮንም ከፈርዖን ፊት ወጥተው ሄዱ፤ ሙሴም ይሖዋ በፈርዖን ላይ ያመጣቸውን እንቁራሪቶች አስመልክቶ ወደ እሱ ጮኸ።+ 13 ይሖዋም ሙሴ እንደጠየቀው አደረገ፤ እንቁራሪቶቹም በየቤቱ፣ በየግቢውና በየሜዳው መሞት ጀመሩ። 14 እነሱም እንቁራሪቶቹን በየቦታው ከመሯቸው፤ ምድሪቱም መግማት ጀመረች። 15 ፈርዖንም ችግሩ ጋብ ማለቱን ባየ ጊዜ ልቡን አደነደነ፤ ልክ ይሖዋ እንደተናገረውም እነሱን ለመስማት ፈቃደኛ አልሆነም።+
16 በዚህ ጊዜ ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ “አሮንን እንዲህ በለው፦ ‘በትርህን ሰንዝረህ የምድርን አቧራ ምታ፤ አቧራውም በመላው የግብፅ ምድር ላይ ትንኝ ይሆናል።’” 17 እነሱም እንዲሁ አደረጉ። አሮን በእጁ የያዘውን በትር ሰንዝሮ የምድርን አቧራ መታ፤ ትንኞቹም ሰዉንም እንስሳውንም ወረሩ። በምድሪቱ ያለው አቧራ ሁሉ በመላው የግብፅ ምድር ላይ ትንኝ ሆነ።+ 18 አስማተኞቹ ካህናትም ተመሳሳይ ነገር ለመፈጸምና በሚስጥራዊ ጥበባቸው ትንኞች እንዲፈሉ ለማድረግ ሞከሩ፤+ ሆኖም አልቻሉም። ትንኞቹ ሰዉንም እንስሳውንም ወርረው ነበር። 19 በመሆኑም አስማተኞቹ ካህናት ፈርዖንን “ይህ የአምላክ ጣት ነው!”+ አሉት። የፈርዖን ልብ ግን ደነደነ፤ ልክ ይሖዋ እንዳለውም እነሱን አልሰማቸውም።
20 ከዚያም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ “በማለዳ ተነስተህ ፈርዖን ፊት ቁም። እሱም ወደ ውኃው ይወርዳል! አንተም እንዲህ በለው፦ ‘ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “እንዲያገለግለኝ ሕዝቤን ልቀቅ። 21 ሕዝቤን የማትለቅ ከሆነ ግን በአንተ፣ በአገልጋዮችህና በሕዝብህ ላይ እንዲሁም በቤቶችህ ውስጥ ተናካሽ ዝንብ እለቃለሁ፤ ዝንቦቹም በግብፅ ያሉትን ቤቶች ይሞላሉ፤ አልፎ ተርፎም የቆሙበትን* መሬት ይሸፍናሉ። 22 በዚያ ቀን ሕዝቤ የሚኖርበትን የጎሸንን ምድር እለያለሁ። በዚያ ምንም ተናካሽ ዝንብ አይኖርም፤+ ይህን በማድረጌም እኔ ይሖዋ በምድሪቱ መካከል እንዳለሁ ታውቃለህ።+ 23 እኔም በሕዝቤና በሕዝብህ መካከል ልዩነት እንዲኖር አደርጋለሁ። ይህ ምልክት ነገ ይፈጸማል።”’”
24 ይሖዋም እንዳለው አደረገ፤ የተናካሽ ዝንብ መንጋም የፈርዖንን ቤትና የአገልጋዮቹን ቤቶች እንዲሁም መላውን የግብፅ ምድር መውረር ጀመረ።+ በተናካሽ ዝንቦቹም የተነሳ ምድሪቱ ክፉኛ ተበላሸች።+ 25 በመጨረሻም ፈርዖን ሙሴንና አሮንን ጠርቶ “ሂዱ፤ በምድሪቱም ለአምላካችሁ መሥዋዕት ሠዉ” አላቸው። 26 ሙሴ ግን እንዲህ አለው፦ “ይሄማ ተገቢ አይደለም፤ ምክንያቱም እኛ ለአምላካችን ለይሖዋ መሥዋዕት የምናደርገው ነገር ለግብፃውያን አስጸያፊ ነው።+ ታዲያ ግብፃውያን የሚጸየፉትን መሥዋዕት እዚያው እነሱ እያዩን ብናቀርብ አይወግሩንም? 27 ስለዚህ ወደ ምድረ በዳው የሦስት ቀን መንገድ እንጓዛለን፤ በዚያም አምላካችን ይሖዋ ባለን መሠረት ለእሱ መሥዋዕት እናቀርባለን።”+
28 በዚህ ጊዜ ፈርዖን እንዲህ አለ፦ “በምድረ በዳ ለአምላካችሁ ለይሖዋ መሥዋዕት እንድታቀርቡ እለቃችኋለሁ። ብቻ ብዙ ርቃችሁ መሄድ የለባችሁም። ስለ እኔም ለምኑልኝ።”+ 29 ከዚያም ሙሴ እንዲህ አለው፦ “እንግዲህ አሁን ከአንተ ተለይቼ እወጣለሁ፤ ይሖዋንም እለምናለሁ፤ ተናካሽ ዝንቦቹም በነገው ዕለት ከፈርዖን፣ ከአገልጋዮቹና ከሕዝቡ ይወገዳሉ። ሆኖም ፈርዖን፣ ሕዝቡ ለይሖዋ መሥዋዕት ለማቅረብ እንዳይሄድ በመከልከል ሊያታልለን* መሞከሩን ይተው።”+ 30 ከዚያም ሙሴ ከፈርዖን ፊት ወጥቶ በመሄድ ይሖዋን ለመነ።+ 31 ይሖዋም ሙሴ እንዳለው አደረገ፤ ተናካሽ ዝንቦቹም ከፈርዖን፣ ከአገልጋዮቹና ከሕዝቡ ተወገዱ። አንድም ዝንብ አልቀረም። 32 ሆኖም ፈርዖን እንደገና ልቡን አደነደነ፤ ሕዝቡንም ለመልቀቅ ፈቃደኛ አልሆነም።
9 ስለሆነም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ወደ ፈርዖን ገብተህ እንዲህ በለው፦ ‘የዕብራውያን አምላክ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “እንዲያገለግለኝ ሕዝቤን ልቀቅ።+ 2 እነሱን ለመልቀቅ እንቢተኛ የምትሆንና እንዳይሄዱ የምትከለክላቸው ከሆነ 3 የይሖዋ እጅ+ በመስክ ያሉትን ከብቶችህን ይመታል። በፈረሶች፣ በአህዮች፣ በግመሎች፣ በበሬዎች፣ በላሞችና በመንጎች ላይ አጥፊ መቅሰፍት ይወርዳል።+ 4 ይሖዋም በእስራኤል ከብቶችና በግብፅ ከብቶች መካከል ልዩነት እንዲኖር ያደርጋል፤ ከእስራኤላውያን ከብቶች መካከል አንድ እንኳ አይሞትም።”’”+ 5 ከዚህም በላይ ይሖዋ “በነገው ዕለት እኔ ይሖዋ በምድሪቱ ላይ ይህን አደርጋለሁ” በማለት ቀን ቆርጧል።
6 ይሖዋም በማግስቱ ይህን አደረገ፤ የግብፅ ከብት ሁሉ ይሞት ጀመር፤+ ከእስራኤላውያን ከብቶች መካከል ግን አንድ እንኳ አልሞተም። 7 ፈርዖንም ሁኔታውን ሲያጣራ ከእስራኤላውያን ከብቶች መካከል አንድ እንኳ አለመሞቱን ተገነዘበ። ያም ሆኖ ግን የፈርዖን ልብ ደነደነ፤ ሕዝቡንም አለቀቀም።+
8 ከዚያም ይሖዋ ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፦ “ከሸክላ መተኮሻ ምድጃ እፍኝ ሙሉ ጥቀርሻ ውሰዱ፤ ሙሴም ጥቀርሻውን በፈርዖን ፊት ወደ ሰማይ ይበትነው። 9 ጥቀርሻውም በመላው የግብፅ ምድር ላይ አቧራ ይሆናል፤ ከዚያም በመላው የግብፅ ምድር ባለ ሰውና እንስሳ ላይ መግል የያዘ እባጭ ሆኖ ይወጣል።”
10 እነሱም ከሸክላ መተኮሻ ምድጃ ጥቀርሻ ወስደው ፈርዖን ፊት ቆሙ፤ ሙሴም ጥቀርሻውን ወደ ሰማይ በተነው፤ ጥቀርሻውም በሰውና በእንስሳ ላይ መግል የያዘ እባጭ ሆኖ ወጣ። 11 አስማተኞቹ ካህናት በእባጩ የተነሳ ሙሴ ፊት ሊቆሙ አልቻሉም፤ ምክንያቱም እባጩ በአስማተኞቹ ካህናትና በሁሉም ግብፃውያን ላይ ወጥቶ ነበር።+ 12 ሆኖም ይሖዋ የፈርዖን ልብ እንዲደነድን ፈቀደ፤ ፈርዖንም ልክ ይሖዋ ለሙሴ እንደነገረው እነሱን አልሰማቸውም።+
13 ከዚያም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ “በማለዳ ተነስተህ ፈርዖን ፊት ቁም፤ እንዲህም በለው፦ ‘የዕብራውያን አምላክ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “እንዲያገለግለኝ ሕዝቤን ልቀቅ። 14 ምክንያቱም በመላው ምድር ላይ እንደ እኔ ያለ ማንም እንደሌለ እንድታውቅ+ ልብህን፣ አገልጋዮችህንና ሕዝብህን ለመምታት መቅሰፍቴን በሙሉ አሁን አወርዳለሁ። 15 እስካሁን እጄን ዘርግቼ አንተንም ሆነ ሕዝብህን አጥፊ በሆነ መቅሰፍት በመታኋችሁ ነበር፤ አንተም ከምድር ገጽ ተጠራርገህ በጠፋህ ነበር። 16 ሆኖም ኃይሌን እንዳሳይህና ስሜ በመላው ምድር እንዲታወጅ ስል በሕይወት አቆይቼሃለሁ።+ 17 ሕዝቤን አለቅም በማለት አሁንም በእነሱ ላይ እንደታበይክ ነህ? 18 እንግዲህ በነገው ዕለት በዚህ ሰዓት ገደማ ግብፅ ከተመሠረተችበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ድረስ ሆኖ የማያውቅ እጅግ ታላቅ የበረዶ ውርጅብኝ አዘንባለሁ። 19 ስለዚህ አሁን መልእክት ልከህ በመስክ ላይ የተሰማሩትን ከብቶችህንና የአንተ የሆኑትን ሁሉ ወደ መጠለያ እንዲገቡ አድርግ። በመስክ የተገኘና ወደ ቤት ያልገባ ማንኛውም ሰውና እንስሳ በረዶው ይወርድበትና ይሞታል።”’”
20 ከፈርዖን አገልጋዮች መካከል የይሖዋን ቃል የፈሩ ሁሉ አገልጋዮቻቸውንና ከብቶቻቸውን በፍጥነት ወደ ቤት አስገቡ፤ 21 ሆኖም የይሖዋን ቃል ከቁም ነገር ያልቆጠሩት ሁሉ አገልጋዮቻቸውንና ከብቶቻቸውን እዚያው መስክ ላይ እንዳሉ ተዉአቸው።
22 በዚህ ጊዜ ይሖዋ ሙሴን “በመላው የግብፅ ምድር ላይ ይኸውም በሰው፣ በእንስሳና በግብፅ ምድር ላይ በበቀለው ተክል ሁሉ ላይ በረዶ እንዲወርድ+ እጅህን ወደ ሰማይ ዘርጋ” አለው።+ 23 በመሆኑም ሙሴ በትሩን ወደ ሰማይ አነሳ፤ ይሖዋም ነጎድጓድና በረዶ ላከ፤ እሳትም* በምድር ላይ ወረደ፤ ይሖዋ በግብፅ ምድር ላይ ያለማቋረጥ በረዶ እንዲወርድ አደረገ። 24 በረዶም ወረደ፤ በበረዶውም መካከል የእሳት ብልጭታ ነበር። በረዶውም እጅግ ከባድ ነበር፤ ግብፅ እንደ አገር ሆና ከተመሠረተችበት ጊዜ አንስቶ በዚያች ምድር ላይ እንዲህ ያለ በረዶ ተከስቶ አያውቅም።+ 25 በረዶው ከሰው አንስቶ እስከ እንስሳ ድረስ በግብፅ ምድር በመስክ ላይ የነበረውን ማንኛውንም ነገር መታ፤ ዕፀዋቱን ሁሉና በሜዳ ላይ ያለውን ዛፍ በሙሉ አወደመ።+ 26 በረዶ ያልወረደው እስራኤላውያን በሚኖሩበት በጎሸን ምድር ብቻ ነበር።+
27 ስለሆነም ፈርዖን ሙሴንና አሮንን አስጠርቶ እንዲህ አላቸው፦ “አሁንስ በድያለሁ። ይሖዋ ጻድቅ ነው፤ ጥፋተኞቹ እኔና ሕዝቤ ነን። 28 አምላክ ያመጣው ነጎድጓድና በረዶ እንዲቆም ይሖዋን ለምኑልኝ። እኔም እናንተን ለመልቀቅ ፈቃደኛ እሆናለሁ፤ ከአሁን በኋላ እዚህ አትቆዩም።” 29 በመሆኑም ሙሴ እንዲህ አለው፦ “ልክ ከከተማዋ እንደወጣሁ እጆቼን በይሖዋ ፊት እዘረጋለሁ። ምድር የይሖዋ እንደሆነች እንድታውቅም ነጎድጓዱ ይቆማል፤ በረዶውም ከዚያ በኋላ አይወርድም።+ 30 ሆኖም አንተም ሆንክ አገልጋዮችህ ይህ ከሆነ በኋላም እንኳ ይሖዋ አምላክን እንደማትፈሩ አውቃለሁ።”
31 በዚህ ጊዜ ገብሱ አሽቶ፣ ተልባውም አብቦ ስለነበር ተልባውና ገብሱ ከጥቅም ውጭ ሆኑ። 32 ስንዴውና አጃው ግን ወቅታቸው ገና ስለነበር ጉዳት አልደረሰባቸውም። 33 ሙሴም ከፈርዖን ተለይቶ ከከተማዋ ወጣ፤ እጆቹንም በይሖዋ ፊት ዘረጋ፤ ነጎድጓዱና በረዶውም ቆመ፤ ዝናቡም በምድር ላይ መዝነቡን አቆመ።+ 34 ፈርዖንም ዝናቡ፣ በረዶውና ነጎድጓዱ መቆሙን ባየ ጊዜ እንደገና ኃጢአት ሠራ፤ እሱም ሆነ አገልጋዮቹ ልባቸውን አደነደኑ።+ 35 የፈርዖን ልብ ደነደነ፤ ልክ ይሖዋ በሙሴ አማካኝነት እንደተናገረውም እስራኤላውያንን አለቀቀም።+
10 ከዚያም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ወደ ፈርዖን ግባ፤ ምክንያቱም የእሱም ሆነ የአገልጋዮቹ ልብ እንዲደነድን እፈቅዳለሁ፤+ ይህን የማደርገውም እነዚህን ተአምራዊ ምልክቶቼን በፊቱ እንዳሳይ+ 2 እንዲሁም ግብፅን እንዴት አድርጌ እንደቀጣሁና በመካከላቸው ተአምራዊ ምልክቶቼን እንዴት እንዳሳየሁ ለልጆችህና ለልጅ ልጆችህ እንድታውጅ ነው፤+ እናንተም እኔ ይሖዋ እንደሆንኩ በእርግጥ ታውቃላችሁ።”
3 በመሆኑም ሙሴና አሮን ወደ ፈርዖን ገብተው እንዲህ አሉት፦ “የዕብራውያን አምላክ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘ለመሆኑ ለእኔ ለመገዛት ፈቃደኛ የማትሆነው እስከ መቼ ነው?+ እንዲያገለግለኝ ሕዝቤን ልቀቅ። 4 አሁንም ሕዝቤን ለመልቀቅ ፈቃደኛ የማትሆን ከሆነ ግን በነገው ዕለት በግዛትህ ላይ አንበጦችን አመጣለሁ። 5 አንበጦቹም ምድሪቱን ይሸፍናሉ፤ መሬቱንም ማየት አይቻልም። እነሱም ከበረዶው ያመለጠውንና የቀረላችሁን ነገር ሁሉ ሙልጭ አድርገው ይበሉታል፤ በመስክ ላይ እየበቀሉ ያሉትን ዛፎቻችሁን በሙሉ ይበሏቸዋል።+ 6 አንበጦቹ አባቶችህና አያቶችህ በዚህች ምድር ላይ መኖር ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ድረስ አይተውት በማያውቁት ሁኔታ+ ቤቶችህን፣ የአገልጋዮችህን ቤቶች ሁሉና የግብፅን ቤቶች ሁሉ ይሞላሉ።’” እሱም ይህን ከተናገረ በኋላ ፊቱን አዙሮ ከፈርዖን ፊት ወጥቶ ሄደ።
7 ከዚያም የፈርዖን አገልጋዮች ፈርዖንን እንዲህ አሉት፦ “ይህ ሰው ወጥመድ የሚሆንብን እስከ መቼ ነው? አምላካቸውን ይሖዋን እንዲያገለግሉ ሰዎቹን ልቀቃቸው። ግብፅ እየጠፋች እንደሆነ እስካሁን አልተገነዘብክም?” 8 በመሆኑም ሙሴና አሮን ወደ ፈርዖን ተመልሰው እንዲመጡ ተደረገ፤ እሱም “ሂዱ፤ አምላካችሁን ይሖዋን አገልግሉ። ይሁንና የሚሄዱት እነማን ናቸው?” አላቸው። 9 በዚህ ጊዜ ሙሴ “ለይሖዋ የምናከብረው በዓል+ ስላለን ወጣቶቻችንን፣ አዛውንቶቻችንን፣ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችንን እንዲሁም በጎቻችንንና ከብቶቻችንን ይዘን እንሄዳለን” አለ።+ 10 እሱም እንዲህ አላቸው፦ “እናንተንና ልጆቻችሁን ከለቀኩማ በእርግጥም ይሖዋ ከእናንተ ጋር ነው!+ መቼም የሆነ ተንኮል እንዳሰባችሁ ግልጽ ነው። 11 ይሄማ አይሆንም! ወንዶቹ ብቻ ሄደው ይሖዋን ያገልግሉ፤ ምክንያቱም የጠየቃችሁት ይህንኑ ነው።” ከዚያም ከፈርዖን ፊት እንዲወጡ ተደረገ።
12 በዚህ ጊዜ ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ “አንበጦች መጥተው የግብፅን ምድር እንዲወሩና ከበረዶ የተረፈውን በምድሩ ላይ ያለውን ማንኛውንም ተክል ጠራርገው እንዲበሉ በግብፅ ምድር ላይ እጅህን ዘርጋ።” 13 ሙሴም ወዲያው በግብፅ ምድር ላይ በትሩን ሰነዘረ፤ ይሖዋም በዚያን ዕለት ቀኑንና ሌሊቱን ሙሉ በምድሩ ላይ የምሥራቅ ነፋስ እንዲነፍስ አደረገ። ሲነጋም የምሥራቁ ነፋስ አንበጦችን አመጣ። 14 አንበጦቹም በመላው የግብፅ ምድር ላይ መውጣትና በግብፅ ግዛት ሁሉ ላይ መስፈር ጀመሩ።+ ሁኔታው እጅግ አስከፊ ነበር፤+ ከዚህ በፊት ያን ያህል ብዛት ያለው አንበጣ ታይቶ አያውቅም፤ ዳግመኛም ያን ያህል ብዛት ያለው አንበጣ ፈጽሞ አይከሰትም። 15 አንበጦቹም መላውን ምድር ሸፈኑት፤ ምድሪቱም በእነሱ የተነሳ ጨለመች፤ እነሱም ከበረዶው የተረፈውን በምድሩ ላይ ያለውን ተክል ሁሉ እንዲሁም በዛፎች ላይ ያለውን ፍሬ ሁሉ ጠራርገው በሉት፤ በመላው የግብፅ ምድር በዛፎችም ሆነ በመስክ ባሉ ተክሎች ላይ አንድም ለምለም ቅጠል አልተረፈም።
16 በመሆኑም ፈርዖን ሙሴንና አሮንን በአስቸኳይ ጠርቶ እንዲህ አላቸው፦ “በአምላካችሁ በይሖዋም ሆነ በእናንተ ላይ ኃጢአት ሠርቻለሁ። 17 ስለሆነም አሁን እባካችሁ ይህን ኃጢአቴን ብቻ ይቅር በሉኝ፤ ይህን ገዳይ መቅሰፍት ከእኔ ላይ እንዲያስወግድልኝም አምላካችሁን ይሖዋን ለምኑልኝ።” 18 እሱም* ከፈርዖን ፊት ወጣ፤ ይሖዋንም ለመነ።+ 19 ከዚያም ይሖዋ ነፋሱ እንዲቀየር አደረገ፤ ነፋሱም ኃይለኛ የምዕራብ ነፋስ ሆነ፤ ነፋሱም አንበጦቹን ወስዶ ቀይ ባሕር ውስጥ ከተታቸው። በመላው የግብፅ ግዛት አንድም አንበጣ አልቀረም። 20 ሆኖም ይሖዋ የፈርዖን ልብ እንዲደነድን ፈቀደ፤+ እሱም እስራኤላውያንን አለቀቀም።
21 ከዚያም ይሖዋ ሙሴን “በግብፅ ምድር ላይ ጨለማ ይኸውም የሚዳሰስ የሚመስል ድቅድቅ ጨለማ እንዲከሰት እጅህን ወደ ሰማይ ዘርጋ” አለው። 22 ሙሴም ወዲያውኑ እጁን ወደ ሰማይ ዘረጋ፤ በመላው የግብፅ ምድር ላይም ለሦስት ቀን ያህል ድቅድቅ ጨለማ ተከሰተ።+ 23 እነሱም እርስ በርስ አይተያዩም ነበር፤ ለሦስት ቀን ማናቸውም ካሉበት ቦታ ንቅንቅ ማለት አልቻሉም፤ ሆኖም እስራኤላውያን ሁሉ በሚኖሩበት ስፍራ ብርሃን ነበር።+ 24 ከዚያም ፈርዖን ሙሴን ጠርቶ እንዲህ አለው፦ “ሂዱ፣ ይሖዋን አገልግሉ።+ በጎቻችሁና ከብቶቻችሁ ብቻ እዚሁ ይቀራሉ። ልጆቻችሁም አብረዋችሁ መሄድ ይችላሉ።” 25 ሙሴ ግን እንዲህ አለው፦ “እንግዲያውስ ለመሥዋዕቶችና ለሚቃጠሉ መባዎች የሚሆኑትን እንስሳት አንተው ራስህ ትሰጠንና ለአምላካችን ለይሖዋ መሥዋዕት አድርገን እናቀርባቸዋለን።+ 26 ከብቶቻችንም አብረውን መሄድ አለባቸው። አምላካችንን ይሖዋን ስናመልክ ከእነሱ መካከል አንዳንዶቹን መሥዋዕት አድርገን ስለምናቀርብ አንድም እንስሳ* እዚህ መቅረት የለበትም፤ ደግሞም እኛ ራሳችን ለይሖዋ አምልኮ ምን መሥዋዕት ማቅረብ እንዳለብን የምናውቀው እዚያ ስንደርስ ነው።” 27 ይሖዋም የፈርዖን ልብ እንዲደነድን ፈቀደ፤ እሱም ሊለቃቸው ፈቃደኛ አልሆነም።+ 28 ስለሆነም ፈርዖን “ከፊቴ ጥፋ! ዳግመኛ ፊቴን ለማየት እንዳትሞክር፤ ፊቴን የምታይበት ቀን መሞቻህ እንደሚሆን እወቅ” አለው። 29 በዚህ ጊዜ ሙሴ “እሺ፣ እንዳልከው ይሁን፤ ዳግመኛ ፊትህን አላይም” አለው።
11 ከዚያም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ “በፈርዖንና በግብፅ ላይ አንድ ተጨማሪ መቅሰፍት አመጣለሁ። ከዚያ በኋላ ከዚህ እንድትሄዱ ይለቃችኋል።+ ደግሞም በሚለቃችሁ ጊዜ አንዳችሁንም ሳያስቀር ከዚህ ያባርራችኋል።+ 2 እንግዲህ አሁን ወንዶቹም ሆኑ ሴቶቹ ሁሉ ከየጎረቤቶቻቸው የብርና የወርቅ ዕቃዎችን እንዲጠይቁ ለሕዝቡ ንገር።”+ 3 ይሖዋም ለሕዝቡ በግብፃውያን ፊት ሞገስ ሰጣቸው። ሙሴ ራሱም ቢሆን በፈርዖን አገልጋዮችና በሕዝቡ ፊት በግብፅ ምድር እጅግ የተከበረ ሰው ሆኖ ነበር።
4 ሙሴም እንዲህ አለ፦ “ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘እኩለ ሌሊት ገደማ በግብፅ መሃል እወጣለሁ፤+ 5 በዙፋኑ ላይ ከተቀመጠው ከፈርዖን የበኩር ልጅ አንስቶ የወፍጮ መጅ እስከምትገፋው ባሪያ የበኩር ልጅ ድረስ በግብፅ ምድር ያለ በኩር ሁሉ ይሞታል፤+ የእንስሳም በኩር ሁሉ ይሞታል።+ 6 በመላው የግብፅ ምድርም ከዚያ በፊት በጭራሽ ሆኖ የማያውቅ ከዚያ በኋላም ፈጽሞ ዳግመኛ የማይከሰት ታላቅ ዋይታ ይሆናል።+ 7 ሆኖም ይሖዋ በግብፃውያንና በእስራኤላውያን መካከል ልዩነት ማድረግ እንደሚችል እንድታውቁ በእስራኤላውያን ላይ፣ በሰዎቹም ሆነ በእንስሶቻቸው ላይ ውሻ እንኳ አይጮኽም።’*+ 8 አገልጋዮችህም ሁሉ ወደ እኔ ወርደው ‘አንተም ሆንክ አንተን የሚከተሉ ሰዎች ሁሉ ከዚህ ሂዱልን’ በማለት ይሰግዱልኛል።+ ከዚያ በኋላም እወጣለሁ።” ሙሴም ይህን ተናግሮ በታላቅ ቁጣ ከፈርዖን ፊት ወጣ።
9 ከዚያም ይሖዋ ሙሴን “ተአምራቶቼ በግብፅ ምድር ላይ እንዲበዙ+ ፈርዖን እናንተን አይሰማችሁም” አለው።+ 10 ሙሴና አሮንም እነዚህን ሁሉ ተአምራት በፈርዖን ፊት ፈጸሙ፤+ ሆኖም ይሖዋ የፈርዖን ልብ እንዲደነድን ስለፈቀደ ፈርዖን እስራኤላውያን ከምድሩ እንዲሄዱ ለመልቀቅ ፈቃደኛ አልሆነም።+
12 ይሖዋም ሙሴንና አሮንን በግብፅ ምድር እንዲህ አላቸው፦ 2 “ይህ ወር የወሮች መጀመሪያ ይሆንላችኋል። ከዓመቱም ወሮች የመጀመሪያው ይሆንላችኋል።+ 3 ለመላው የእስራኤል ማኅበረሰብ እንዲህ ብላችሁ ንገሩ፦ ‘ይህ ወር በገባ በአሥረኛው ቀን እያንዳንዱ ሰው ለአባቱ ቤት አንድ በግ ይኸውም ለአንድ ቤት አንድ በግ+ ይውሰድ። 4 ሆኖም ቤተሰቡ ለአንድ በግ የሚያንስ ከሆነ እነሱና የእነሱ* የቅርብ ጎረቤቶች በጉን በየቤታቸው ባሉት ሰዎች* ቁጥር ልክ ይከፋፈሉት። በምታሰሉበት ጊዜም እያንዳንዱ ሰው ከበጉ ምን ያህል እንደሚበላ ወስኑ። 5 የምትመርጡት በግ እንከን የሌለበት፣+ ተባዕትና አንድ ዓመት የሞላው መሆን ይኖርበታል። ከበግ ጠቦቶች ወይም ከፍየሎች መካከል መምረጥ ትችላላችሁ። 6 እስከዚህ ወር 14ኛ ቀን+ ድረስ እየተንከባከባችሁ አቆዩት፤ መላው የእስራኤል ማኅበረሰብ ጉባኤም አመሻሹ ላይ* ይረደው።+ 7 ከደሙም ወስደው በጉን በሚበሉበት ቤት በር በሁለቱ መቃኖችና በጉበኑ ላይ ይርጩት።+
8 “‘ሥጋውንም በዚያው ሌሊት ይብሉት።+ ሥጋውን በእሳት ጠብሰው ከቂጣና*+ ከመራራ ቅጠል+ ጋር ይብሉት። 9 የትኛውንም የሥጋውን ብልት ጥሬውን ወይም ቅቅሉን አትብሉ፤ ነገር ግን ጭንቅላቱን ከእግሩና ከሆድ ዕቃው ጋር በእሳት ጥበሱት። 10 እስከ ጠዋት ድረስ ምንም አታስተርፉ፤ ሳይበላ ያደረ ካለ ግን በእሳት አቃጥሉት።+ 11 የምትበሉትም ወገባችሁን ታጥቃችሁ፣ ጫማችሁን አድርጋችሁና በትራችሁን በእጃችሁ ይዛችሁ መሆን አለበት፤ በጥድፊያም ብሉት። ይህ የይሖዋ ፋሲካ* ነው። 12 ምክንያቱም በዚህ ሌሊት በግብፅ ምድር አልፋለሁ፤ ከሰው አንስቶ እስከ እንስሳ ድረስ በግብፅ ምድር ያለውን በኩር ሁሉ እመታለሁ፤+ በግብፅ አማልክት ሁሉ ላይም የፍርድ እርምጃ እወስዳለሁ።+ እኔ ይሖዋ ነኝ። 13 ደሙም እናንተ ያላችሁበትን ቤት የሚጠቁም ምልክት ሆኖ ያገለግላል፤ እኔም ደሙን ሳይ እናንተን አልፌ እሄዳለሁ፤ የግብፅን ምድር በምመታበት ጊዜ መቅሰፍቱ መጥቶ እናንተን አያጠፋም።+
14 “‘ይህ ቀን ለእናንተ መታሰቢያ ይሆናል፤ እናንተም በመጪዎቹ ትውልዶቻችሁ ሁሉ የይሖዋ በዓል አድርጋችሁ አክብሩት። ይህን ዘላቂ ደንብ አድርጋችሁ አክብሩት። 15 ለሰባት ቀን ቂጣ ትበላላችሁ።+ አዎ፣ በመጀመሪያው ቀን ከቤታችሁ እርሾ አስወግዱ፤ ምክንያቱም ከመጀመሪያው ቀን አንስቶ እስከ ሰባተኛው ቀን ድረስ እርሾ የገባበትን ነገር የሚበላ ማንኛውም ሰው* ከእስራኤል መካከል ተለይቶ እንዲጠፋ ይደረጋል። 16 በመጀመሪያው ቀን ቅዱስ ጉባኤ አድርጉ፤ በሰባተኛውም ቀን ሌላ ቅዱስ ጉባኤ አድርጉ። በእነዚህ ቀናት ምንም ዓይነት ሥራ መሠራት የለበትም።+ እያንዳንዱ ሰው* የሚበላውን ነገር ከማዘጋጀት ውጭ ሌላ ምንም ነገር አትሥሩ።
17 “‘የቂጣን በዓል አክብሩ፤+ ምክንያቱም በዚህ ቀን ሠራዊታችሁን ከግብፅ ምድር አወጣለሁ። እናንተም ይህን ዕለት በመጪዎቹ ትውልዶቻችሁ ሁሉ ዘላቂ ደንብ አድርጋችሁ አክብሩት። 18 በመጀመሪያው ወር፣ ከወሩም ከ14ኛው ቀን ምሽት አንስቶ እስከ ወሩ 21ኛ ቀን ምሽት ድረስ ቂጣ ትበላላችሁ።+ 19 ለሰባት ቀናት እርሾ የሚባል ነገር በቤታችሁ ውስጥ አይገኝ፤ ምክንያቱም እርሾ ያለበትን ነገር የሚበላ ማንኛውም ሰው የባዕድ አገር ሰውም ሆነ የአገሩ ተወላጅ፣+ ያ ሰው* ከእስራኤል ማኅበረሰብ መካከል ተለይቶ እንዲጠፋ ይደረጋል።+ 20 እርሾ ያለበት ምንም ነገር አትብሉ። በቤታችሁ ሁሉ ቂጣ ብሉ።’”
21 ሙሴም ወዲያው የእስራኤልን ሽማግሌዎች+ በሙሉ ጠርቶ እንዲህ አላቸው፦ “ሂዱ፣ ለየቤተሰባችሁ የሚሆን ጠቦት መርጣችሁ የፋሲካን መሥዋዕት እረዱ። 22 ከዚያም አንድ እስር ሂሶጵ ወስዳችሁ በሳህን ባለው ደም ውስጥ ከነከራችሁ በኋላ ደሙን በበራችሁ ጉበንና በሁለቱ መቃኖች ላይ እርጩት፤ ከእናንተም መካከል አንድም ሰው እስኪነጋ ድረስ ከቤቱ መውጣት የለበትም። 23 ይሖዋ ግብፃውያንን በመቅሰፍት ሊመታ በሚያልፍበት ጊዜ በበራችሁ ጉበንና በሁለቱ መቃኖች ላይ ያለውን ደም ሲያይ ይሖዋ በእርግጥ በሩን አልፎ ይሄዳል፤ የሞት መቅሰፍቱ* ወደ ቤታችሁ እንዲገባ አይፈቅድም።+
24 “እናንተም ይህን ነገር ለእናንተና ለልጆቻችሁ ዘላቂ ሥርዓት አድርጋችሁ አክብሩት።+ 25 ልክ ይሖዋ በተናገረው መሠረትም ወደሚሰጣችሁ ምድር በምትገቡበት ጊዜ ይህን በዓል አክብሩ።+ 26 ልጆቻችሁ ‘ይህን በዓል የምታከብሩት ለምንድን ነው?’ ብለው ሲጠይቋችሁ+ 27 እንዲህ በሏቸው፦ ‘ግብፃውያንን በመቅሰፍት በመታበት ጊዜ በግብፅ ያሉትን የእስራኤላውያንን ቤቶች አልፎ በመሄድ ቤቶቻችንን ላተረፈልን ለይሖዋ የሚቀርብ የፋሲካ መሥዋዕት ነው።’”
ከዚያም ሕዝቡ ተደፍቶ ሰገደ። 28 እስራኤላውያንም ሄደው ይሖዋ ሙሴንና አሮንን እንዳዘዛቸው አደረጉ።+ ልክ እንደተባሉት አደረጉ።
29 እኩለ ሌሊት ላይ ይሖዋ፣ በዙፋኑ ላይ ከተቀመጠው ከፈርዖን የበኩር ልጅ አንስቶ በእስር ቤት* እስከሚገኘው እስረኛ የበኩር ልጅ ድረስ በግብፅ ምድር ያለውን በኩር ሁሉ መታ፤ የእያንዳንዱን እንስሳ በኩርም መታ።+ 30 ከዚያም ፈርዖን በዚያ ሌሊት ተነሳ፤ እሱ ብቻ ሳይሆን አገልጋዮቹ ሁሉና ሌሎቹ ግብፃውያን በሙሉ ተነሱ፤ ሰው ያልሞተበት አንድም ቤት ስላልነበር በግብፃውያን መካከል ታላቅ ዋይታ ሆነ።+ 31 እሱም ወዲያውኑ ሙሴንና አሮንን በሌሊት ጠርቶ+ እንዲህ አላቸው፦ “ተነሱ፣ እናንተም ሆናችሁ ሌሎቹ እስራኤላውያን ከሕዝቤ መካከል ውጡ። ሂዱ፣ እንዳላችሁት ይሖዋን አገልግሉ።+ 32 ባላችሁትም መሠረት መንጎቻችሁንና ከብቶቻችሁን ይዛችሁ ሂዱ።+ እኔን ግን ባርኩኝ።”
33 ግብፃውያኑም “በዚህ ዓይነት እኮ ሁላችንም ማለቃችን ነው!”+ በማለት ሕዝቡ በአስቸኳይ ምድሪቱን ለቆ እንዲሄድላቸው ያጣድፉት ጀመር።+ 34 ስለዚህ ሕዝቡ ያልቦካውን ሊጥ በየቡሃቃው አድርጎ በልብሱ ከጠቀለለ በኋላ በትከሻው ተሸከመው። 35 እስራኤላውያንም ሙሴ የነገራቸውን አደረጉ፤ የብርና የወርቅ ዕቃዎችን እንዲሁም ልብሶችን እንዲሰጧቸውም ግብፃውያንን ጠየቁ።+ 36 ይሖዋም ለሕዝቡ በግብፃውያን ፊት ሞገስ ሰጣቸው፤ በመሆኑም የጠየቁትን ሁሉ ሰጧቸው፤ ግብፃውያኑንም በዘበዟቸው።+
37 ከዚያም እስራኤላውያን ከራምሴስ+ ተነስተው ወደ ሱኮት+ ሄዱ፤ ልጆችን ሳይጨምር እግረኛ የሆኑት ወንዶች ወደ 600,000 ገደማ ነበሩ።+ 38 ከእነሱም ጋር እጅግ ብዙ ድብልቅ ሕዝብ*+ እንዲሁም መንጎችና ከብቶች ይኸውም እጅግ ብዙ እንስሳ አብሮ ወጣ። 39 እነሱም ከግብፅ ይዘው በወጡት ሊጥ ቂጣ ጋገሩ። ይህም የሆነው ሊጡ ስላልቦካ ነበር፤ ምክንያቱም ከግብፅ እንዲወጡ የተደረገው በድንገት ስለነበር ለራሳቸው ስንቅ ማዘጋጀት አልቻሉም።+
40 በግብፅ የኖሩት እስራኤላውያን+ የኖሩበት ዘመን 430 ዓመት ነበር።+ 41 አራት መቶ ሠላሳው ዓመት በተፈጸመበት በዚያው ዕለት መላው የይሖዋ ሠራዊት ከግብፅ ምድር ወጣ። 42 ይህ ሌሊት ይሖዋ ከግብፅ ምድር ስላወጣቸው የሚያከብሩት ሌሊት ነው። ይህ ሌሊት መላው የእስራኤል ሕዝብ በመጪዎቹ ትውልዶች ሁሉ ለይሖዋ የሚያከብረው ሌሊት ነው።+
43 ከዚያም ይሖዋ ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፦ “የፋሲካው ደንብ ይህ ነው፦ ማንኛውም የባዕድ አገር ሰው ከፋሲካው አይብላ።+ 44 ሆኖም አንድ ሰው በገንዘብ የተገዛ ባሪያ ካለው ግረዘው።+ መብላት የሚችለው ይህ ከሆነ ብቻ ነው። 45 ሰፋሪና ቅጥር ሠራተኛ ከዚያ ላይ መብላት የለባቸውም። 46 በአንድ ቤት ውስጥ መበላት አለበት። ከሥጋውም ላይ የትኛውንም ቢሆን ከቤት ውጭ ይዘህ አትውጣ፤ ከአጥንቱም አንዱንም አትስበሩ።+ 47 መላው የእስራኤል ማኅበረሰብ ይህን በዓል ማክበር አለበት። 48 በመካከላችሁ የሚኖር የባዕድ አገር ሰው ካለና ለይሖዋ ፋሲካን ማክበር ከፈለገ የእሱ የሆኑት ወንዶች ሁሉ መገረዝ አለባቸው። ከዚያ በኋላ በዓሉን ለማክበር መቅረብ ይችላል፤ እሱም እንደ አገሩ ተወላጅ ይሆናል። ነገር ግን ማንኛውም ያልተገረዘ ሰው ከፋሲካው ምግብ መብላት አይችልም።+ 49 ለአገሩ ተወላጅም ሆነ በመካከላችሁ ለሚኖር የባዕድ አገር ሰው ሕጉ አንድ ዓይነት ነው።”+
50 በመሆኑም እስራኤላውያን በሙሉ ይሖዋ ሙሴን እና አሮንን እንዳዘዛቸው አደረጉ። ልክ እንደተባሉት አደረጉ። 51 በዚሁ ቀን ይሖዋ እስራኤላውያንን ከነሠራዊታቸው ከግብፅ ምድር አወጣቸው።
13 ይሖዋም ሙሴን እንዲህ አለው፦ 2 “ከእስራኤል ሕዝብ መካከል በኩር የሆነውን ወንድ ሁሉ ለእኔ ቀድስልኝ።* ከሰውም ሆነ ከእንስሳ መካከል በኩር የሆነው ወንድ ሁሉ* የእኔ ነው።”+
3 ከዚያም ሙሴ ሕዝቡን እንዲህ አለ፦ “ከግብፅ ከባርነት ቤት የወጣችሁበትን ይህን ቀን አስቡ፤+ ምክንያቱም ይሖዋ በኃያል ክንድ ከዚህ አውጥቷችኋል።+ በመሆኑም እርሾ የገባበት ምንም ነገር መበላት የለበትም። 4 ይኸው በዛሬው ዕለት በአቢብ* ወር ከዚህ ለቃችሁ እየወጣችሁ ነው።+ 5 ይሖዋ ለአንተ ይሰጥህ ዘንድ ለቀድሞ አባቶችህ ወደማለላቸው+ ወተትና ማር ወደምታፈሰው ምድር+ ይኸውም ወደ ከነአናውያን፣ ሂታውያን፣ አሞራውያን፣ ሂዋውያንና ኢያቡሳውያን ምድር+ ሲያስገባህ አንተ ደግሞ በዚህ ወር ይህን በዓል ማክበር አለብህ። 6 ለሰባት ቀን ቂጣ ትበላለህ፤+ በሰባተኛውም ቀን ለይሖዋ በዓል ይከበራል። 7 በእነዚህ ሰባት ቀናት መበላት ያለበት እርሾ ያልገባበት ቂጣ ነው፤+ በአንተ ዘንድ እርሾ የገባበት ምንም ነገር መገኘት የለበትም፤+ በወሰንህም ውስጥ ሁሉ ምንም እርሾ መገኘት የለበትም። 8 በዚያ ቀን ለልጅህ ‘ይህን የማደርገው ከግብፅ በወጣሁበት ጊዜ ይሖዋ ባደረገልኝ ነገር የተነሳ ነው’ ብለህ ንገረው።+ 9 የይሖዋ ሕግ በአፍህ ላይ እንዲሆን ይህ በዓል በእጅህ ላይ እንደታሰረ ምልክትና በግንባርህ* ላይ እንዳለ መታሰቢያ* ሆኖ ያገለግልሃል፤+ ምክንያቱም ይሖዋ በኃያል ክንድ ከግብፅ አውጥቶሃል። 10 አንተም ይህን ደንብ በየዓመቱ በተወሰነለት ጊዜ አክብረው።+
11 “ይሖዋ ለአንተ ለመስጠት ለአንተም ሆነ ለቀድሞ አባቶችህ ወደማለላችሁ+ ወደ ከነአናውያን ምድር ሲያስገባህ 12 በኩር የሆነውን ወንድ ሁሉ* እንዲሁም የአንተ ከሆነው እንስሳ መካከል በኩር የሆነውን ወንድ ሁሉ ለይሖዋ መስጠት አለብህ። ወንዶቹ ሁሉ የይሖዋ ናቸው።+ 13 የእያንዳንዱን አህያ በኩር በበግ ዋጀው፤ የማትዋጀው ከሆነ ግን አንገቱን ስበረው። ከወንዶች ልጆችህ መካከል በኩር የሆነውን ሁሉ ልትዋጀው ይገባል።+
14 “ምናልባት ወደፊት ልጅህ ‘ይህን የምታደርገው ለምንድን ነው?’ ብሎ ቢጠይቅህ እንዲህ በለው፦ ‘ይሖዋ በኃያል ክንድ ከግብፅ ከባርነት ቤት አወጣን።+ 15 ፈርዖን እኛን ለመልቀቅ ፈቃደኛ ባለመሆን ግትር አቋም በያዘ ጊዜ+ ይሖዋ ከሰው በኩር አንስቶ እስከ እንስሳ በኩር ድረስ በግብፅ ምድር ያለውን በኩር ሁሉ ገደለ።+ በኩር የሆነውን ወንድ ሁሉ* ለይሖዋ የምሠዋው እንዲሁም ከወንዶች ልጆቼ መካከል በኩር የሆነውን ሁሉ የምዋጀው ለዚህ ነው።’ 16 ይሖዋ በኃያል ክንድ ከግብፅ ስላወጣን ይህ በዓል በእጅህ ላይ እንዳለ ምልክትና በግንባርህ* ላይ እንደታሰረ ነገር ሆኖ ያገልግል።”+
17 ፈርዖን ሕዝቡን በለቀቀ ጊዜ አምላክ ምንም እንኳ አቋራጭ ቢሆንም ወደ ፍልስጤማውያን ምድር በሚወስደው መንገድ አልመራቸውም። ምክንያቱም “ሕዝቡ ጦርነት ቢያጋጥመው ሐሳቡን ለውጦ ወደ ግብፅ ሊመለስ ይችላል” በማለት አስቦ ነበር። 18 በመሆኑም አምላክ ሕዝቡ በቀይ ባሕር አቅራቢያ ባለው ምድረ በዳ በኩል ዞሮ እንዲሄድ አደረገ።+ እስራኤላውያንም ከግብፅ ምድር የወጡት የጦርነት አሰላለፍ ተከትለው ነበር። 19 በተጨማሪም ሙሴ የዮሴፍን አፅም ይዞ ነበር፤ ምክንያቱም ዮሴፍ እስራኤላውያንን “አምላክ ፊቱን ወደ እናንተ መመለሱ አይቀርም፤ በመሆኑም አፅሜን ከዚህ ይዛችሁ ውጡ” በማለት በጥብቅ አስምሏቸው ነበር።+ 20 እነሱም ከሱኮት ተነስተው በምድረ በዳው ዳርቻ ላይ በሚገኘው በኤታም ሰፈሩ።
21 ይሖዋ የሚሄዱበትን መንገድ ይመራቸው ዘንድ ቀን ቀን በደመና ዓምድ ውስጥ ሆኖ ከፊት ከፊታቸው ይሄድ ነበር፤+ ሌሊት ሌሊት ደግሞ ብርሃን እንዲያገኙ ለማድረግ በእሳት ዓምድ ውስጥ ሆኖ ይመራቸው ነበር፤+ በመሆኑም ቀንም ሆነ ሌሊት ይጓዙ ነበር። 22 ቀን ቀን የደመናው ዓምድ ሌሊት ሌሊት ደግሞ የእሳቱ ዓምድ ከሕዝቡ ፊት አይለይም ነበር።+
14 በዚህ ጊዜ ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ 2 “ወደ ኋላ ተመልሰው በሚግዶልና በባሕሩ መካከል ባለው በበዓልጸፎን ትይዩ በሚገኘው በፊሃሂሮት ፊት ለፊት እንዲሰፍሩ ለእስራኤላውያን ንገራቸው።+ በበዓልጸፎን ፊት ለፊት በባሕሩ አጠገብ ስፈሩ። 3 ፈርዖንም ስለ እስራኤላውያን ‘ግራ ተጋብተው በምድሪቱ ላይ እየተንከራተቱ ነው። ምድረ በዳው ጋሬጣ ሆኖባቸዋል’ ማለቱ አይቀርም። 4 እኔም የፈርዖን ልብ እንዲደነድን እፈቅዳለሁ፤+ እሱም ያሳድዳቸዋል፤ እኔም ፈርዖንንና ሠራዊቱን ድል በማድረግ ለራሴ ክብርን እጎናጸፋለሁ፤+ ግብፃውያንም እኔ ይሖዋ መሆኔን በእርግጥ ያውቃሉ።”+ እነሱም ልክ እንዲሁ አደረጉ።
5 በኋላም ለግብፁ ንጉሥ ሕዝቡ እንደኮበለለ ተነገረው። ፈርዖንና አገልጋዮቹም ስለ ሕዝቡ የነበራቸውን ሐሳብ ወዲያው በመቀየር+ “ምን ማድረጋችን ነው? እስራኤላውያን ባሪያ ሆነው እንዳያገለግሉን የለቀቅናቸው ምን ነክቶን ነው?” አሉ። 6 በመሆኑም ፈርዖን የጦር ሠረገሎቹ እንዲዘጋጁለት አደረገ፤ ሠራዊቱንም ከጎኑ አሰለፈ።+ 7 ከዚያም 600 የተመረጡ ሠረገሎችንና ሌሎች የግብፅ ሠረገሎችን ሁሉ ይዞ ተነሳ፤ በእያንዳንዱም ሠረገላ ላይ ተዋጊዎች ነበሩ። 8 በዚህ መንገድ ይሖዋ የግብፁ ንጉሥ የፈርዖን ልብ እንዲደነድን ፈቀደ፤ እስራኤላውያን ወጥተው በልበ ሙሉነት* እየሄዱ ሳሉ ፈርዖን እነሱን ማሳደዱን ተያያዘው።+ 9 ግብፃውያኑ ተከታተሏቸው፤+ እስራኤላውያን በበዓልጸፎን ፊት ለፊት በባሕሩ አጠገብ ባለው በፊሃሂሮት ሰፍረው ሳሉም የፈርዖን ሠረገሎች፣ ፈረሰኞቹና ሠራዊቱ በሙሉ ደረሱባቸው።
10 ፈርዖን ወደ እነሱ ሲቀርብ እስራኤላውያን ቀና ብለው ተመለከቱ፤ ግብፃውያኑ እነሱን እየተከታተሏቸው ነበር። እስራኤላውያንም ተሸበሩ፤ ወደ ይሖዋም ይጮኹ ጀመር።+ 11 እነሱም ሙሴን እንዲህ አሉት፦ “እዚህ ምድረ በዳ ውስጥ እንድንሞት ያመጣኸን በግብፅ የመቃብር ቦታ ጠፍቶ ነው?+ ከግብፅ መርተህ በማውጣት ምን ያደረግክልን ነገር አለ? 12 በግብፅ ሳለን ‘እባክህ ተወን፤ አርፈን ግብፃውያንን እናገልግል’ ብለንህ አልነበረም? እዚህ ምድረ በዳ ውስጥ ከመሞት ግብፃውያንን ብናገለግል ይሻለን ነበር።”+ 13 በዚህ ጊዜ ሙሴ ሕዝቡን እንዲህ አላቸው፦ “አትፍሩ።+ ጸንታችሁ ቁሙ፤ በዛሬው ዕለት ይሖዋ ለእናንተ ሲል የሚፈጽመውን የእሱን ማዳን እዩ።+ ዛሬ የምታዩአቸውን ግብፃውያን ዳግመኛ አታዩአቸውም፤ በጭራሽ አታዩአቸውም።+ 14 ይሖዋ ራሱ ስለ እናንተ ይዋጋል፤+ ብቻ እናንተ ዝም በሉ።”
15 በዚህ ጊዜ ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ለምን ወደ እኔ ትጮኻለህ? እስራኤላውያን ድንኳናቸውን ነቅለው እንዲጓዙ ንገራቸው። 16 አንተም እስራኤላውያን በባሕሩ መሃል በደረቅ መሬት እንዲሻገሩ በትርህን አንሳና እጅህን በባሕሩ ላይ ሰንዝር፤ ባሕሩንም ክፈለው። 17 እኔ ደግሞ የግብፃውያን ልብ እንዲደነድን ስለምፈቅድ እስራኤላውያንን ተከትለው ይገባሉ፤ እኔም ፈርዖንን፣ ሠራዊቱን ሁሉ፣ የጦር ሠረገሎቹንና ፈረሰኞቹን ድል በማድረግ ለራሴ ክብርን እጎናጸፋለሁ።+ 18 ፈርዖንን፣ የጦር ሠረገሎቹንና ፈረሰኞቹን ድል በማድረግ ለራሴ ክብርን በምጎናጸፍበት ጊዜ ግብፃውያን እኔ ይሖዋ መሆኔን በእርግጥ ያውቃሉ።”+
19 ከዚያም ከእስራኤል ሕዝብ ፊት ፊት ይሄድ የነበረው የእውነተኛው አምላክ መልአክ+ ከዚያ ተነስቶ ወደ ኋላቸው ሄደ፤ ከፊታቸው የነበረውም የደመና ዓምድ ወደ ኋላቸው ሄዶ በስተ ጀርባቸው ቆመ።+ 20 በመሆኑም የደመናው ዓምድ በግብፃውያንና በእስራኤላውያን መካከል ሆነ።+ ዓምዱ በአንደኛው በኩል ጭልም ያለ ደመና ነበር። በሌላኛው በኩል ደግሞ ለሌሊቱ ብርሃን ይሰጥ ነበር።+ ስለሆነም ሌሊቱን ሙሉ አንደኛው ወገን ወደ ሌላኛው ወገን መቅረብ አልቻለም።
21 ሙሴም እጁን በባሕሩ ላይ ሰነዘረ፤+ ይሖዋም ሌሊቱን ሙሉ ኃይለኛ የምሥራቅ ነፋስ በማምጣት ባሕሩ ወደ ኋላ እንዲመለስ አደረገ፤ የባሕሩንም ወለል ወደ ደረቅ መሬት ለወጠው፤+ ውኃውም ተከፈለ።+ 22 በመሆኑም እስራኤላውያን ውኃው በቀኛቸውና በግራቸው እንደ ግድግዳ ቆሞ+ በባሕሩ መሃል በደረቅ መሬት ተሻገሩ።+ 23 ግብፃውያኑም እነሱን ማሳደዳቸውን ተያያዙት፤ የፈርዖን ፈረሶች፣ የጦር ሠረገሎችና ፈረሰኞች ሁሉ ተከትለዋቸው ወደ ባሕሩ መሃል ገቡ።+ 24 በማለዳውም ክፍለ ሌሊት* ይሖዋ በእሳትና በደመና ዓምድ ውስጥ ሆኖ የግብፃውያንን ሠራዊት ተመለከተ፤+ የግብፃውያንም ሠራዊት ግራ እንዲጋባ አደረገ። 25 ሠረገሎቻቸውን መንዳት አስቸጋሪ እንዲሆንባቸው የሠረገሎቻቸውን መንኮራኩሮች* አወላለቀባቸው፤ ግብፃውያኑም “ይሖዋ እስራኤላውያንን በመደገፍ ግብፃውያንን እየተዋጋላቸው ስለሆነ ከእስራኤላውያን ፊት እንሽሽ” አሉ።+
26 ከዚያም ይሖዋ ሙሴን “ውኃው በግብፃውያን፣ በጦር ሠረገሎቻቸውና በፈረሰኞቻቸው ላይ ተመልሶ እንዲመጣባቸው እጅህን በባሕሩ ላይ ሰንዝር” አለው። 27 ሙሴም ወዲያውኑ እጁን በባሕሩ ላይ ሰነዘረ፤ ሊነጋጋ ሲልም ባሕሩ ወደ ቀድሞ ሁኔታው ተመለሰ። ግብፃውያንም ውኃው እንዳይደርስባቸው ለመሸሽ ሲሞክሩ ይሖዋ ግብፃውያኑን ባሕሩ መሃል ጣላቸው።+ 28 ውኃውም ተመልሶ እስራኤላውያንን ተከትለው የገቡትን የጦር ሠረገሎችና ፈረሰኞች እንዲሁም የፈርዖንን ሠራዊት በሙሉ አለበሳቸው።+ ከእነሱም መካከል አንድም የተረፈ የለም።+
29 እስራኤላውያን ግን ውኃው በቀኛቸውና በግራቸው እንደ ግድግዳ ቆሞ+ በባሕሩ መሃል በደረቅ መሬት ተጓዙ።+ 30 በዚህ መንገድ ይሖዋ በዚያ ቀን እስራኤላውያንን ከግብፃውያን እጅ አዳነ፤+ እስራኤላውያንም የግብፃውያን ሬሳ በባሕሩ ዳርቻ ላይ ወድቆ ተመለከቱ። 31 በተጨማሪም እስራኤላውያን ይሖዋ ግብፃውያንን የመታበትን ኃያል ክንድ ተመለከቱ፤ ሕዝቡም ይሖዋን መፍራት ጀመረ፤ በይሖዋና በአገልጋዩ በሙሴም አመነ።+
15 በዚያን ጊዜ ሙሴና እስራኤላውያን የሚከተለውን መዝሙር ለይሖዋ ዘመሩ፦+
“በክብር እጅግ ከፍ ከፍ ስላለ ለይሖዋ እዘምራለሁ።+
ፈረሱንና ፈረሰኛውን ባሕር ውስጥ ጣላቸው።+
2 አዳኜ ስለሆነልኝ ያህ* ብርታቴና ኃይሌ ነው።+
እሱ አምላኬ ነው፤ አወድሰዋለሁ፤+ የአባቴ አምላክ ነው፤+ እኔም ከፍ ከፍ አደርገዋለሁ።+
3 ይሖዋ ኃያል ተዋጊ ነው።+ ስሙ ይሖዋ ነው።+
4 የፈርዖንን ሠረገሎችና ሠራዊቱን ባሕር ውስጥ ወረወራቸው፣+
ምርጥ የሆኑ ተዋጊዎቹም ቀይ ባሕር ውስጥ ሰመጡ።+
5 ማዕበሉም ከደናቸው፤ እነሱም እንደ ድንጋይ ወደ ጥልቁ ሰመጡ።+
6 ይሖዋ ሆይ፣ ቀኝ እጅህ እጅግ ኃያል ነው፤+
ይሖዋ ሆይ፣ ቀኝ እጅህ ጠላትን ያደቃል።
7 እጅግ ታላቅ በሆነው ግርማህ በአንተ ላይ የሚነሱትን ሁሉ ቁልቁል ታሽቀነጥራቸዋለህ፤+
የሚነደውን ቁጣህን ትልካለህ፤ እነሱንም እንደ ገለባ* ይበላቸዋል።
8 በአፍንጫህ እስትንፋስ ውኃዎች ተቆለሉ፤
ወራጁንም ውኃ ገድበው ቀጥ ብለው ቆሙ፤
ማዕበሉም በባሕሩ ልብ ውስጥ ረጋ።
9 ጠላትም ‘አሳድዳቸዋለሁ! አሳድጄ እደርስባቸዋለሁ!
እስክጠግብም* ድረስ ምርኮን እከፋፈላለሁ!
ሰይፌን እመዛለሁ! እጄም ታንበረክካቸዋለች!’ አለ።+
10 አንተም እስትንፋስህን እፍ አልክ፤ ባሕሩም ከደናቸው፤+
እነሱም ኃያል በሆኑ ውኃዎች ውስጥ እንደ አረር ሰመጡ።
11 ይሖዋ ሆይ፣ ከአማልክት መካከል እንደ አንተ ያለ ማን ነው?+
በቅድስናው ኃያል መሆኑን የሚያሳይ እንደ አንተ ያለ ማን ነው?+
በመዝሙር ልትወደስ የሚገባህ የምትፈራ አምላክ ነህ፤ ድንቅ ነገሮችን ታደርጋለህ።+
12 ቀኝ እጅህን ዘረጋህ፤ ምድርም ዋጠቻቸው።+
13 የታደግካቸውን+ ሕዝቦች በታማኝ ፍቅርህ መራሃቸው፤
በብርታትህም ወደ ቅዱስ መኖሪያህ ትመራቸዋለህ።
14 ሕዝቦችም ይሰማሉ፤+ ይንቀጠቀጣሉ፤
የፍልስጤም ነዋሪዎችም ምጥ ይይዛቸዋል።
15 በዚያን ጊዜ የኤዶም አለቆች ይሸበራሉ፤
የሞዓብ ኃያላን ገዢዎች ብርክ ይይዛቸዋል።+
የከነአን ነዋሪዎችም ሁሉ ልባቸው ይከዳቸዋል።+
16 ፍርሃትና ድንጋጤ ይወድቅባቸዋል።+
ይሖዋ ሆይ፣ ሕዝቦችህ አልፈው እስኪሄዱ ድረስ፣
አንተ የፈጠርካቸው ሕዝቦች+ አልፈው እስኪሄዱ ድረስ፣+
ከክንድህ ታላቅነት የተነሳ እንደ ድንጋይ ደርቀው ይቀራሉ።
17 አምጥተህ በርስትህ ተራራ ላይ ትተክላቸዋለህ፤+
ይሖዋ ሆይ፣ አንተ ራስህ ልትኖርበት ባዘጋጀኸው ጸንቶ የተመሠረተ ቦታ፣
ይሖዋ ሆይ፣ እጆችህ በመሠረቱት መቅደስ ትተክላቸዋለህ።
18 ይሖዋ ለዘላለም ንጉሥ ሆኖ ይገዛል።+
19 የፈርዖን ፈረሶች፣ የጦር ሠረገሎቹና ፈረሰኞቹ ወደ ባሕሩ በገቡ ጊዜ፣+
ይሖዋ የባሕሩን ውኃ ላያቸው ላይ መለሰባቸው፤+
የእስራኤል ሕዝብ ግን በባሕሩ መሃል በደረቅ መሬት ተሻገረ።”+
20 ከዚያም የአሮን እህት ነቢዪቱ ሚርያም አታሞ አነሳች፤ ሴቶቹም ሁሉ አታሞ እየመቱና እየጨፈሩ ተከተሏት። 21 ሚርያምም ከወንዶቹ ጋር እየተቀባበለች እንዲህ ስትል ዘመረች፦
“በክብር እጅግ ከፍ ከፍ ስላለ ለይሖዋ ዘምሩ።+
ፈረሱንና ፈረሰኛውን ባሕር ውስጥ ጣላቸው።”+
22 ከዚያም ሙሴ እስራኤላውያንን ከቀይ ባሕር እየመራ ይዟቸው ወጣ፤ እነሱም ወደ ሹር ምድረ በዳ ሄዱ፤ በምድረ በዳውም ለሦስት ቀን ያህል ተጓዙ፤ ሆኖም ውኃ አላገኙም ነበር። 23 በኋላም ወደ ማራ*+ መጡ፤ ያም ሆኖ በማራ ያለው ውኃ መራራ ስለነበር ሊጠጡት አልቻሉም። የቦታውን ስም ማራ ያለውም በዚህ የተነሳ ነው። 24 በመሆኑም ሕዝቡ “እንግዲህ ምን ልንጠጣ ነው?” እያለ በሙሴ ላይ ማጉረምረም ጀመረ።+ 25 እሱም ወደ ይሖዋ ጮኸ፤+ ይሖዋም ወደ አንዲት ዛፍ መራው። ሙሴም ዛፏን ውኃው ውስጥ ሲጥላት ውኃው ጣፋጭ ሆነ።
እሱም በዚያ የሚመሩበት ሥርዓትና ለፍርድ መሠረት የሚሆን መመሪያ አወጣላቸው፤ በዚያም ፈተናቸው።+ 26 እንዲህም አላቸው፦ “የአምላካችሁን የይሖዋን ቃል በጥንቃቄ ብታዳምጡ፣ በእሱ ፊት ትክክል የሆነውን ነገር ብታደርጉ፣ ለትእዛዛቱ ጆሯችሁን ብትሰጡና ሥርዓቶቹን በሙሉ ብታከብሩ+ በግብፃውያን ላይ ካመጣሁባቸው በሽታዎች አንዱንም በእናንተ ላይ አላመጣም፤+ ምክንያቱም እኔ ይሖዋ እፈውሳችኋለሁ።”+
27 ከዚያም 12 የውኃ ምንጮችና 70 የዘንባባ ዛፎች ወዳሉበት ወደ ኤሊም መጡ። በዚያም በውኃው አጠገብ ሰፈሩ።
16 ከኤሊም ከተነሱ በኋላም መላው የእስራኤል ማኅበረሰብ ከግብፅ ምድር በወጣ በሁለተኛው ወር በ15ኛው ቀን በኤሊምና በሲና መካከል ወደሚገኘው ወደ ሲን ምድረ በዳ+ መጣ።
2 ከዚያም መላው የእስራኤል ማኅበረሰብ በምድረ በዳ ሳለ በሙሴና በአሮን ላይ ማጉረምረም ጀመረ።+ 3 እስራኤላውያንም እንዲህ ይሏቸው ነበር፦ “በግብፅ ምድር በሥጋው ድስት አጠገብ ተቀምጠን ሳለንና እስክንጠግብ ድረስ ዳቦ ስንበላ በነበረበት ጊዜ ምነው በይሖዋ እጅ ሞተን ባረፍነው ኖሮ።+ እናንተ ግን ይህን ጉባኤ በሙሉ በረሃብ ልትጨርሱት ወደዚህ ምድረ በዳ አመጣችሁን።”+
4 ከዚያም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ “እንግዲህ እኔ ከሰማይ ምግብ አዘንብላችኋለሁ፤+ ሕዝቡም ይውጣ፤ እያንዳንዱም ሰው ወጥቶ የሚበቃውን ያህል በየዕለቱ ይሰብስብ፤+ በዚህም ሕጌን አክብረው ይመላለሱ እንደሆነና እንዳልሆነ እፈትናቸዋለሁ።+ 5 በስድስተኛው ቀን+ የሰበሰቡትን በሚያዘጋጁበት ጊዜ ግን በሌሎቹ ቀናት ከሚሰበስቡት እጥፍ ይሁን።”+
6 በመሆኑም ሙሴና አሮን እስራኤላውያንን በሙሉ እንዲህ አሏቸው፦ “ከግብፅ ምድር ያወጣችሁ ይሖዋ መሆኑን በዚህ ምሽት በእርግጥ ታውቃላችሁ።+ 7 ጠዋት ላይ የይሖዋን ክብር ታያላችሁ፤ ምክንያቱም ይሖዋ በእሱ ላይ ማጉረምረማችሁን ሰምቷል። በእኛ ላይ የምታጉረመርሙት ለመሆኑ እኛ ማን ነን?” 8 ከዚያም ሙሴ እንዲህ አለ፦ “ይሖዋ ምሽት ላይ፣ የምትበሉት ሥጋ ጠዋት ላይ ደግሞ የምትፈልጉትን ያህል ዳቦ ሲሰጣችሁ ይሖዋ በእሱ ላይ ያጉረመረማችሁትን ማጉረምረም እንደሰማ ታያላችሁ። ታዲያ እኛ ማን ነን? ያጉረመረማችሁት በእኛ ላይ ሳይሆን በይሖዋ ላይ ነው።”+
9 ሙሴም አሮንን “ለመላው የእስራኤል ማኅበረሰብ ‘ማጉረምረማችሁን ስለሰማ ኑ በይሖዋ ፊት ቅረቡ’ በላቸው” አለው።+ 10 አሮን ለመላው የእስራኤል ማኅበረሰብ በተናገረ ጊዜ ሕዝቡ ወደ ምድረ በዳው ዞሮ ቆመ፤ በዚህ ጊዜ የይሖዋ ክብር በደመናው ውስጥ ተገለጠ።+
11 በተጨማሪም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ 12 “የእስራኤላውያንን ማጉረምረም ሰምቻለሁ።+ እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ ‘አመሻሹ ላይ* ሥጋ ትበላላችሁ፤ ጠዋት ላይ ደግሞ ዳቦ ትጠግባላችሁ፤+ እኔም አምላካችሁ ይሖዋ መሆኔን በእርግጥ ታውቃላችሁ።’”+
13 በዚህም መሠረት ምሽት ላይ ድርጭቶች መጥተው ሰፈሩን አለበሱት፤+ ጠዋት ላይም በሰፈሩ ውስጥ ሁሉ ጤዛ ወርዶ ነበር። 14 በኋላም ጤዛው ሲተን በምድረ በዳው ላይ እንደ አመዳይ ደቃቅ የሆነ ቅርፊት የሚመስል ስስ ነገር+ መሬቱ ላይ ታየ። 15 እስራኤላውያንም ባዩት ጊዜ ምን እንደሆነ ስላላወቁ እርስ በርሳቸው “ይህ ነገር ምንድን ነው?” ይባባሉ ጀመር። ስለሆነም ሙሴ እንዲህ አላቸው፦ “ይሖዋ እንድትበሉት የሰጣችሁ ምግብ ነው።+ 16 ይሖዋ እንዲህ ሲል አዟል፦ ‘እያንዳንዱ ሰው የሚበላውን ያህል ይሰብስብ። እያንዳንዳችሁ በድንኳናችሁ ውስጥ ባሉት ሰዎች ቁጥር* ልክ ለእያንዳንዱ ሰው አንድ ኦሜር*+ ሰፍራችሁ ውሰዱ።’” 17 እስራኤላውያንም እንደተባሉት አደረጉ፤ ይሰበስቡም ጀመር፤ አንዳንዶቹ ብዙ ሌሎቹ ደግሞ ትንሽ ሰበሰቡ። 18 የሰበሰቡትን በኦሜር ሲሰፍሩት ብዙ የሰበሰበው ምንም ትርፍ አላገኘም፤ ጥቂት የሰበሰበውም ምንም አልጎደለበትም።+ እያንዳንዳቸው የሰበሰቡት የሚበሉትን ያህል ነበር።
19 ከዚያም ሙሴ “ማንም ሰው እስከ ጠዋት ድረስ ምንም ማስተረፍ የለበትም”+ አላቸው። 20 እነሱ ግን ሙሴን አልሰሙትም። አንዳንዶቹ ከሰበሰቡት ውስጥ የተወሰነውን አሳደሩት፤ ሆኖም ተልቶ መሽተት ጀመረ፤ በመሆኑም ሙሴ በእነሱ ላይ እጅግ ተቆጣ። 21 በየማለዳው እያንዳንዱ ሰው የሚበላውን ያህል ይሰበስብ ነበር። ፀሐዩ እየበረታ በሚሄድበት ጊዜም ይቀልጥ ነበር።
22 በስድስተኛውም ቀን ሁለት እጥፍ ምግብ+ ይኸውም ለአንድ ሰው ሁለት ኦሜር ሰበሰቡ። በመሆኑም የማኅበረሰቡ አለቆች በሙሉ መጥተው ሁኔታውን ለሙሴ ነገሩት። 23 በዚህ ጊዜ እንዲህ አላቸው፦ “ይሄማ ይሖዋ የተናገረው ነገር ነው። ነገ ሙሉ በሙሉ የእረፍት ቀን* ይኸውም ለይሖዋ ቅዱስ ሰንበት ይሆናል።+ የምትጋግሩትን ጋግሩ፤ የምትቀቅሉትንም ቀቅሉ፤+ የተረፈውን ሁሉ አስቀምጡ፤ እስከ ጠዋትም ድረስ አቆዩት።” 24 እነሱም ልክ ሙሴ ባዘዛቸው መሠረት እስከ ጠዋት ድረስ አቆዩት፤ ምግቡም አልሸተተም ወይም አልተላም። 25 ከዚያም ሙሴ እንዲህ አላቸው፦ “ዛሬ ይህን ብሉ፤ ምክንያቱም ዛሬ የይሖዋ ሰንበት ነው። ዛሬ ሜዳው ላይ አታገኙትም። 26 ስድስት ቀን ትሰበስባላችሁ፤ በሰባተኛው ቀን ይኸውም በሰንበት ቀን+ ግን ምንም አይገኝም።” 27 ይሁንና ከሕዝቡ መካከል አንዳንዶቹ በሰባተኛው ቀን ሊሰበስቡ ወጡ፤ ሆኖም ምንም አላገኙም።
28 በመሆኑም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ “እናንተ ሰዎች ትእዛዛቴንና ሕጎቼን ለማክበር እንቢተኛ የምትሆኑት እስከ መቼ ነው?+ 29 ይሖዋ ሰንበትን እንደሰጣችሁ ልብ በሉ።+ በስድስተኛው ቀን ለሁለት ቀን የሚሆን ምግብ የሰጣችሁም ለዚህ ነው። እያንዳንዱ ሰው ባለበት ስፍራ መቆየት አለበት፤ በሰባተኛውም ቀን ማንም ሰው ካለበት ቦታ መውጣት የለበትም።” 30 ሕዝቡም በሰባተኛው ቀን ሰንበትን አከበረ።*+
31 የእስራኤልም ቤት ምግቡን “መና”* አሉት። እሱም እንደ ድንብላል ዘር ነጭ ሲሆን ጣዕሙም ማር እንደተቀባ ቂጣ ነበር።+ 32 ከዚያም ሙሴ እንዲህ አላቸው፦ “ይሖዋ እንዲህ ሲል አዟል፦ ‘ከግብፅ ምድር ባወጣኋችሁ ጊዜ በምድረ በዳ እንድትበሉት የሰጠኋችሁን ምግብ እንዲያዩ ከእሱ አንድ ኦሜር ሰፍራችሁ ለሚመጡት ትውልዶቻችሁ ሁሉ አስቀምጡ።’”+ 33 በመሆኑም ሙሴ አሮንን “ማሰሮ ወስደህ አንድ ኦሜር መና ጨምርበት፤ ለሚመጡት ትውልዶቻችሁ ሁሉ ተጠብቆ እንዲቆይ በይሖዋ ፊት አስቀምጠው” አለው።+ 34 አሮንም ይሖዋ ሙሴን ባዘዘው መሠረት ተጠብቆ እንዲቆይ መናውን በምሥክሩ*+ ፊት አስቀመጠው። 35 እስራኤላውያንም ወደሚኖሩበት ምድር እስከሚመጡ ድረስ+ ለ40 ዓመት+ መናውን በሉ። ወደ ከነአን ምድር ድንበር+ እስከሚደርሱ ድረስ መናውን በሉ። 36 አንድ ኦሜር፣ የኢፍ መስፈሪያ* አንድ አሥረኛ ነው።
17 መላው የእስራኤል ማኅበረሰብም ከሲን ምድረ በዳ+ ተነስቶ ይሖዋ ባዘዘው መሠረት+ ከቦታ ወደ ቦታ ሲጓዝ ከቆየ በኋላ በረፊዲም+ ሰፈረ። ሆኖም ሕዝቡ የሚጠጣው ውኃ አልነበረም።
2 በመሆኑም ሕዝቡ “የሚጠጣ ውኃ ስጠን” በማለት ከሙሴ ጋር ይጣላ ጀመር።+ ሙሴ ግን “ከእኔ ጋር የምትጣሉት ለምንድን ነው? ይሖዋንስ ለምን ትፈታተኑታላችሁ?”+ አላቸው። 3 ሆኖም ሕዝቡ ውኃ በጣም ተጠምቶ ስለነበር “እኛና ልጆቻችን እንዲሁም ከብቶቻችን በውኃ ጥም እንድናልቅ ከግብፅ ያወጣኸን ለምንድን ነው?” በማለት በሙሴ ላይ ማጉረምረሙን ቀጠለ።+ 4 በመጨረሻም ሙሴ “ይህን ሕዝብ ምን ባደርገው ይሻለኛል? ትንሽ ቆይተው እኮ ይወግሩኛል!” በማለት ወደ ይሖዋ ጮኸ።
5 ከዚያም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ከእስራኤል ሽማግሌዎች መካከል የተወሰኑትን ምረጥና የአባይን ወንዝ የመታህበትን በትር+ ይዘህ ከሕዝቡ ፊት ፊት ሂድ። በትሩን በእጅህ ይዘህ ሂድ። 6 እኔም በዚያ በኮሬብ በሚገኘው ዓለት ላይ ፊትህ እቆማለሁ። አንተም ዓለቱን ትመታዋለህ፤ ውኃም ከውስጡ ይፈልቃል፤ ሕዝቡም ይጠጣሉ።”+ ሙሴም የእስራኤል ሽማግሌዎች እያዩ እንደተባለው አደረገ። 7 እሱም እስራኤላውያን ስለተጣሉትና “ለመሆኑ ይሖዋ በመካከላችን አለ ወይስ የለም?” በማለት ይሖዋን ስለተፈታተኑት+ የቦታውን ስም ማሳህ*+ እና መሪባ*+ አለው።
8 ከዚያም አማሌቃውያን+ መጥተው በረፊዲም እስራኤላውያንን ወጉ።+ 9 በዚህ ጊዜ ሙሴ ኢያሱን+ እንዲህ አለው፦ “ሰዎች ምረጥልንና ከአማሌቃውያን ጋር ለመዋጋት ውጣ። እኔም በነገው ዕለት የእውነተኛውን አምላክ በትር በእጄ ይዤ በኮረብታው አናት ላይ እቆማለሁ።” 10 ከዚያም ኢያሱ ልክ ሙሴ እንዳለው አደረገ፤+ ከአማሌቃውያንም ጋር ተዋጋ። ሙሴ፣ አሮንና ሁርም+ ወደ ኮረብታው አናት ወጡ።
11 ሙሴ እጆቹን ወደ ላይ አንስቶ በሚቆይበት ጊዜ ሁሉ እስራኤላውያን ያይሉ፣ እጆቹን በሚያወርድበት ጊዜ ግን አማሌቃውያን ያይሉ ነበር። 12 የሙሴ እጆች በዛሉ ጊዜ ድንጋይ ወስደው ከሥሩ አስቀመጡለት፤ እሱም በድንጋዩ ላይ ተቀመጠ። ከዚያም አሮንና ሁር አንዱ በአንደኛው በኩል፣ ሌላው ደግሞ በሌላኛው በኩል ሆነው እጆቹን ደገፉለት፤ በመሆኑም ፀሐይ እስከምትጠልቅበት ጊዜ ድረስ እጆቹ ባሉበት ጸኑ። 13 በዚህ መንገድ ኢያሱ አማሌቅንና ሕዝቦቹን በሰይፍ ድል አደረገ።+
14 ይሖዋም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “መታሰቢያ* እንዲሆን ይህን በመጽሐፍ ጻፈው፤ ለኢያሱም ‘የአማሌቅን መታሰቢያ ከሰማይ በታች ሙሉ በሙሉ ጠራርጌ አጠፋለሁ’+ በማለት ይህን ደግመህ ንገረው።” 15 ከዚያም ሙሴ መሠዊያ ሠርቶ ስሙን ‘ይሖዋ ንሲ’* ብሎ ሰየመው፤ 16 እንዲህም ያለው “እጁ በያህ+ ዙፋን ላይ ስለተነሳ ይሖዋ ከአማሌቅ ጋር ከትውልድ እስከ ትውልድ ይዋጋል”+ በማለት ነው።
18 የምድያም ካህን የሆነው የሙሴ አማት ዮቶር+ አምላክ ለሙሴና ለሕዝቡ ለእስራኤል ያደረገውን ነገር ሁሉ ይኸውም ይሖዋ እስራኤልን ከግብፅ እንዴት እንዳወጣ ሰማ።+ 2 የሙሴ አማት ዮቶር የሙሴ ሚስት ሲፓራ ወደ እሱ ተመልሳ በተላከች ጊዜ እሷንና 3 ሁለቱን ወንዶች ልጆቿን+ ይዞ ተነሳ። ሙሴ “በባዕድ አገር የምኖር የባዕድ አገር ሰው ሆንኩ” ብሎ ስለነበር የአንደኛው ልጅ ስም ጌርሳም*+ ነበር፤ 4 እንዲሁም ሙሴ “ከፈርዖን ሰይፍ+ ያዳነኝ የአባቴ አምላክ ረዳቴ ነው” ብሎ ስለነበር የሌላኛው ልጁ ስም ኤሊዔዘር* ነበር።
5 በመሆኑም የሙሴ አማት ዮቶር ከሙሴ ሚስትና ወንዶች ልጆች ጋር በመሆን የእውነተኛው አምላክ ተራራ+ በሚገኝበት ምድረ በዳ ሰፍሮ ወደነበረው ወደ ሙሴ መጣ። 6 ከዚያም ዮቶር “እኔ አማትህ ዮቶር፣+ ከሚስትህና ከሁለቱ ወንዶች ልጆቿ ጋር ወደ አንተ እየመጣሁ ነው” የሚል መልእክት ወደ ሙሴ ላከ። 7 ሙሴም ወዲያውኑ አማቱን ሊቀበለው ወጣ፤ እሱም ሰገደለት፤ ከዚያም ሳመው። እርስ በርሳቸውም ስለ ደህንነታቸው ተጠያየቁ፤ በኋላም ወደ ድንኳኑ ገቡ።
8 ሙሴም ይሖዋ ለእስራኤል ሲል በፈርዖንና በግብፅ ላይ ያደረገውን ሁሉ+ እንዲሁም በጉዟቸው ያጋጠሟቸውን አስቸጋሪ ሁኔታዎችና+ ይሖዋ እንዴት እንዳዳናቸው ለአማቱ ተረከለት። 9 ዮቶርም ይሖዋ እስራኤልን ከግብፅ እጅ በማዳን ለእነሱ ሲል ባደረገላቸው መልካም ነገሮች ሁሉ ተደሰተ። 10 ከዚያም ዮቶር እንዲህ አለ፦ “ከግብፅና ከፈርዖን እጅ ያዳናችሁ እንዲሁም ሕዝቡን ከግብፅ እጅ ነፃ ያወጣው ይሖዋ ይወደስ። 11 ይሖዋ በሕዝቡ ላይ የእብሪት ድርጊት በፈጸሙ ሰዎች ላይ እንዲህ ያለ እርምጃ በመውሰዱ ከሌሎች አማልክት ሁሉ እንደሚበልጥ+ አሁን አውቄአለሁ።” 12 ከዚያም የሙሴ አማት ዮቶር የሚቃጠል መባና መሥዋዕቶችን ለአምላክ አመጣ፤ አሮንና የእስራኤል ሽማግሌዎች በሙሉ ከሙሴ አማት ጋር በእውነተኛው አምላክ ፊት ምግብ ለመብላት መጡ።
13 በማግስቱም ሙሴ እንደተለመደው ሕዝቡን በዳኝነት ለማገልገል ተቀመጠ፤ ሕዝቡም ከጠዋት አንስቶ እስከ ማታ ድረስ እየመጣ በሙሴ ፊት ይቆም ነበር። 14 የሙሴ አማትም ሙሴ ለሕዝቡ የሚያደርገውን ሁሉ ባየ ጊዜ “ይህ ለሕዝቡ እያደረግክ ያለኸው ነገር ምንድን ነው? አንተ ብቻህን ለመዳኘት የምትቀመጠውና ይህ ሁሉ ሕዝብ ከጠዋት እስከ ማታ ድረስ ፊትህ የሚቆመው ለምንድን ነው?” አለው። 15 ሙሴም አማቱን እንዲህ አለው፦ “ምክንያቱም ሕዝቡ አምላክን ለመጠየቅ ያለማቋረጥ ወደ እኔ ይመጣል። 16 አንድ ጉዳይ በሚነሳበት ጊዜ ጉዳዩ ወደ እኔ ይቀርባል፤ እኔ ደግሞ ባለጉዳዮቹን እዳኛለሁ፤ እንዲሁም የእውነተኛውን አምላክ ውሳኔዎችና ሕጎች አሳውቃለሁ።”+
17 በዚህ ጊዜ የሙሴ አማት እንዲህ አለው፦ “እያደረግክ ያለኸው ነገር መልካም አይደለም። 18 ይህ ሥራ ለአንተ ከባድ ሸክም ስለሚሆን አንተም ሆንክ ከአንተ ጋር ያለው ይህ ሕዝብ መድከማችሁ አይቀርም፤ ደግሞም ብቻህን ልትሸከመው አትችልም። 19 እንግዲህ አሁን የምልህን ስማ። አንድ ነገር ልምከርህ፤ አምላክም ከአንተ ጋር ይሆናል።+ አንተ በእውነተኛው አምላክ ፊት የሕዝቡ ተወካይ ሆነህ ታገለግላለህ፤+ ጉዳያቸውንም ወደ እውነተኛው አምላክ ታቀርባለህ።+ 20 ሥርዓቶቹና ሕጎቹ ምን እንደሆኑ በመንገር ማሳሰቢያ ትሰጣቸዋለህ፤+ እንዲሁም የሚሄዱበትን መንገድና የሚያከናውኑትን ነገር ታሳውቃቸዋለህ። 21 ሆኖም ከመላው ሕዝብ መካከል አምላክን የሚፈሩትንና ብቃት ያላቸውን+ እንዲሁም አግባብ ያልሆነ ጥቅም ለማግኘት የማይፈልጉትንና እምነት የሚጣልባቸውን ሰዎች+ ምረጥ፤ እነዚህንም የሺህ አለቆች፣ የመቶ አለቆች፣ የሃምሳ አለቆችና የአሥር አለቆች አድርገህ በሕዝቡ ላይ ሹማቸው።+ 22 እነሱም የተለያዩ ጉዳዮች በሚነሱበት ጊዜ* ሕዝቡን ይዳኙ፤ ከበድ ያሉ ጉዳዮች ሲያጋጥሟቸው ወደ አንተ ያምጡ፤+ ቀለል ያሉ ጉዳዮችን ግን ራሳቸው ይዳኙ። ሸክሙን እንዲጋሩህ በማድረግ በአንተ ላይ ያለውን ጫና አቅልል።+ 23 ይህን ነገር ከአምላክ እንደተቀበልከው ትእዛዝ አድርገህ ብትፈጽም ውጥረቱ ይቀንስልሃል፤ እያንዳንዱም ሰው ተደስቶ ወደ ቤቱ ይሄዳል።”
24 ሙሴም ወዲያውኑ አማቱን በመስማት ያለውን ሁሉ አደረገ። 25 ሙሴም ከመላው እስራኤል ብቃት ያላቸውን ወንዶች መርጦ የሺህ አለቆች፣ የመቶ አለቆች፣ የሃምሳ አለቆችና የአሥር አለቆች አድርጎ በሕዝቡ ላይ ሾማቸው። 26 በመሆኑም እነዚህ ሰዎች የተለያዩ ጉዳዮች በሚነሱበት ጊዜ ሕዝቡን ይዳኙ ነበር። ከበድ ያለ ጉዳይ ሲያጋጥማቸው ወደ ሙሴ ያመጡ+ የነበረ ሲሆን ቀለል ያሉ ጉዳዮችን ግን ራሳቸው ይዳኙ ነበር። 27 ከዚያም ሙሴ አማቱን ሸኘው፤+ እሱም ወደ አገሩ ሄደ።
19 እስራኤላውያን ከግብፅ በወጡ በሦስተኛው ወር በዚያው ቀን ወደ ሲና ምድረ በዳ መጡ። 2 ከረፊዲም+ ተነስተው ወደ ሲና ምድረ በዳ በመምጣት በምድረ በዳው ሰፈሩ። እስራኤላውያን በዚያ ከተራራው ፊት ለፊት ሰፈሩ።+
3 ከዚያም ሙሴ ወደ እውነተኛው አምላክ ወጣ፤ ይሖዋም ከተራራው ጠርቶት እንዲህ አለው፦+ “ለያዕቆብ ቤት የምትለው፣ ለእስራኤላውያንም የምትነግረው ይህ ነው፦ 4 ‘እናንተን በንስር ክንፎች ተሸክሜ+ ወደ እኔ ለማምጣት ስል በግብፃውያን ላይ ያደረግኩትን ሁሉ እናንተው ራሳችሁ አይታችኋል።+ 5 አሁንም ቃሌን በጥብቅ ብትታዘዙና ቃል ኪዳኔን ብትጠብቁ መላው ምድር የእኔ ስለሆነ+ እናንተ ከሌሎች ሕዝቦች ሁሉ የተመረጣችሁ ልዩ ንብረቶቼ* ትሆናላችሁ።+ 6 እናንተ ለእኔ የካህናት መንግሥትና ቅዱስ ብሔር ትሆናላችሁ።’+ ለእስራኤላውያን የምትነግራቸው ቃል ይህ ነው።”
7 በመሆኑም ሙሴ ሄዶ የሕዝቡን ሽማግሌዎች ጠራ፤ ይሖዋ ያዘዘውንም ይህን ቃል ነገራቸው።+ 8 ከዚያ በኋላ ሕዝቡ ሁሉ በአንድ ድምፅ “ይሖዋ የተናገረውን ሁሉ ለመፈጸም ፈቃደኞች ነን”+ ብለው መለሱ። ሙሴም ወዲያውኑ የሕዝቡን ምላሽ ይዞ ወደ ይሖዋ ሄደ። 9 ይሖዋም ሙሴን “ሕዝቡ ከአንተ ጋር ስነጋገር እንዲሰማና ምንጊዜም በአንተ ላይ እምነት እንዲጥል በጥቁር ደመና ወደ አንተ እመጣለሁ” አለው። ከዚያም ሙሴ የሕዝቡን ቃል ለይሖዋ ተናገረ።
10 ይሖዋም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ወደ ሕዝቡ ሄደህ ዛሬና ነገ ቀድሳቸው፤ እነሱም ልብሳቸውን ይጠቡ። 11 ለሦስተኛውም ቀን ይዘጋጁ፤ ምክንያቱም በሦስተኛው ቀን ይሖዋ ሕዝቡ ሁሉ እያዩ በሲና ተራራ ላይ ይወርዳል። 12 በተራራው ዙሪያ ለሕዝቡ ወሰን አብጅ፤ እንዲህም በላቸው፦ ‘ወደ ተራራው እንዳትወጡ፣ ድንበሩንም እንኳ እንዳትነኩ ተጠንቀቁ። ተራራውን የሚነካ ማንኛውም ሰው ይገደላል። 13 ይህን ሰው ማንም እንዳይነካው፤ ከዚህ ይልቅ በድንጋይ ይወገር ወይም ደግሞ ይወጋ።* እንስሳም ሆነ ሰው በሕይወት እንዲኖር አይተውም።’+ ሆኖም የቀንደ መለከቱ ድምፅ+ በሚሰማበት ጊዜ ወደ ተራራው ሊወጡ ይችላሉ።”
14 ከዚያም ሙሴ ከተራራው ወርዶ ወደ ሕዝቡ ሄደ፤ ሕዝቡንም ይቀድስ ጀመር፤ እነሱም ልብሳቸውን አጠቡ።+ 15 ሕዝቡንም “ለሦስተኛው ቀን ተዘጋጁ። የፆታ ግንኙነት ከመፈጸምም ተቆጠቡ”* አላቸው።
16 በሦስተኛውም ቀን ጠዋት ነጎድጓድ መሰማትና መብረቅ መታየት ጀመረ፤ በተራራውም ላይ ጥቅጥቅ ያለ ደመና ነበር፤+ ከፍተኛ የቀንደ መለከት ድምፅም ተሰማ፤ በሰፈሩም ውስጥ ያለው ሕዝብ በሙሉ በፍርሃት ተንቀጠቀጠ።+ 17 በዚህ ጊዜ ሙሴ ከእውነተኛው አምላክ ጋር እንዲገናኙ ሕዝቡን ከሰፈሩ ይዞ ወጣ፤ እነሱም በተራራው ግርጌ ቆሙ። 18 የሲና ተራራ ይሖዋ በእሳት ስለወረደበት ዙሪያውን ጨሰ፤+ ጭሱም እንደ እቶን ጭስ እየተትጎለጎለ ይወጣ ነበር፤ ተራራውም ሁሉ በኃይል ተናወጠ።+ 19 የቀንደ መለከቱም ድምፅ ይበልጥ እየጨመረ ሲመጣ ሙሴ ተናገረ፤ የእውነተኛውም አምላክ ድምፅ መለሰለት።
20 በመሆኑም ይሖዋ በሲና ተራራ አናት ላይ ወረደ። ከዚያም ይሖዋ ሙሴን ወደ ተራራው አናት ጠራው፤ ሙሴም ወጣ።+ 21 በዚህ ጊዜ ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ሂድ ውረድ፤ ሕዝቡ ይሖዋን ለማየት ሲሉ አልፈው ለመምጣት እንዳይሞክሩ አስጠንቅቃቸው፤ ካልሆነ ግን ብዙዎቹ ለጥፋት ይዳረጋሉ። 22 ዘወትር ወደ ይሖዋ የሚቀርቡት ካህናትም ይሖዋ እንዳይቀስፋቸው ራሳቸውን ይቀድሱ።”+ 23 ከዚያም ሙሴ ይሖዋን እንዲህ አለው፦ “አንተ ‘በተራራው ዙሪያ ወሰን አድርግ፤ እሱንም ቀድሰው’ በማለት ስላስጠነቀቅከን ሕዝቡ ወደ ሲና ተራራ መቅረብ አይችልም።”+ 24 ሆኖም ይሖዋ እንዲህ አለው፦ “ሂድ፣ ውረድና ከአሮን ጋር ተመልሰህ ወደዚህ ውጣ፤ ነገር ግን ካህናቱም ሆኑ ሕዝቡ አልፈው ወደ ይሖዋ ለመምጣት እንዳይሞክሩና እንዳይቀስፋቸው ከልክላቸው።”+ 25 ስለሆነም ሙሴ ወደ ሕዝቡ ወርዶ ነገራቸው።
20 ከዚያም አምላክ ይህን ቃል ሁሉ ተናገረ፦+
2 “ከግብፅ ምድር፣ ከባርነት ቤት ያወጣሁህ እኔ አምላክህ ይሖዋ ነኝ።+ 3 ከእኔ በቀር* ሌሎች አማልክት አይኑሩህ።+
4 “በላይ በሰማያት ወይም በታች በምድር አሊያም ከምድር በታች በውኃ ውስጥ ባለ በማንኛውም ነገር አምሳል የተቀረጸን ቅርጽ ወይም የተሠራን ምስል ለራስህ አታድርግ።+ 5 አትስገድላቸው፤ ተታለህም እነሱን አታገልግል፤+ ምክንያቱም እኔ አምላክህ ይሖዋ እኔ ብቻ እንድመለክ የምፈልግና+ በሚጠሉኝ ሁሉ ላይ በአባቶች ስህተት የተነሳ በልጆቻቸው እንዲሁም በሦስተኛና በአራተኛ ትውልዶቻቸው ላይ ቅጣት የማመጣ አምላክ ነኝ፤ 6 ሆኖም ለሚወዱኝና ትእዛዛቴን ለሚጠብቁ እስከ ሺህ ትውልድ ድረስ ታማኝ ፍቅር የማሳይ አምላክ ነኝ።+
7 “የአምላክህን የይሖዋን ስም በከንቱ አታንሳ፤+ ምክንያቱም ይሖዋ ስሙን በከንቱ የሚያነሳውን ሳይቀጣ አይተወውም።+
8 “የሰንበትን ቀን ቅዱስ አድርገህ መጠበቅ እንዳለብህ አትርሳ።+ 9 ሥራህንና የምታከናውናቸውን ነገሮች በሙሉ በስድስት ቀን ሠርተህ አጠናቅ፤+ 10 ሰባተኛው ቀን ግን ለአምላክህ ለይሖዋ ሰንበት ነው። በዚህ ቀን አንተም ሆንክ ወንድ ልጅህ ወይም ሴት ልጅህ፣ ወንድ ባሪያህም ሆነ ሴት ባሪያህ፣ የቤት እንስሳህም ሆነ በሰፈርህ* ውስጥ ያለ የባዕድ አገር ሰው ምንም ሥራ አትሥሩ።+ 11 ምክንያቱም ይሖዋ ሰማያትን፣ ምድርን፣ ባሕርንና በውስጣቸው ያሉትን ነገሮች ሁሉ በስድስት ቀናት ውስጥ ሠርቶ ካጠናቀቀ በኋላ በሰባተኛው ቀን ማረፍ ጀምሯል።+ ይሖዋ የሰንበትን ቀን የባረከውና የቀደሰው ለዚህ ነው።
12 “አምላክህ ይሖዋ በሚሰጥህ ምድር ላይ ዕድሜህ እንዲረዝም+ አባትህንና እናትህን አክብር።+
14 “አታመንዝር።+
15 “አትስረቅ።+
16 “በባልንጀራህ ላይ ምሥክር ሆነህ ስትቀርብ በሐሰት አትመሥክር።+
17 “የባልንጀራህን ቤት አትመኝ። የባልንጀራህን ሚስት፣+ ወንድ ባሪያውን፣ ሴት ባሪያውን፣ በሬውን ወይም አህያውን አሊያም የባልንጀራህ የሆነውን ማንኛውንም ነገር አትመኝ።”+
18 ሕዝቡም ሁሉ የነጎድጓዱንና የቀንደ መለከቱን ድምፅ ሰሙ፤ እንዲሁም የመብረቁን ብልጭታና የተራራውን ጭስ ተመለከቱ፤ ይህም በፍርሃት እንዲንቀጠቀጡና ርቀው እንዲቆሙ አደረጋቸው።+ 19 በመሆኑም ሙሴን “አንተ አነጋግረን፤ እኛም እናዳምጥሃለን፤ ሆኖም እንዳንሞት ስለምንፈራ አምላክ አያነጋግረን” አሉት።+ 20 ሙሴም ሕዝቡን “አትፍሩ፤ ምክንያቱም እውነተኛው አምላክ የመጣው እናንተን ለመፈተን+ ይኸውም ዘወትር እሱን በመፍራት ኃጢአት ከመሥራት እንድትቆጠቡ ለማድረግ ነው”+ አላቸው። 21 ሕዝቡም እዚያው ርቆ ባለበት ቆመ፤ ሙሴ ግን እውነተኛው አምላክ ወዳለበት ጥቁር ደመና ቀረበ።+
22 ከዚያም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ “እስራኤላውያንን እንዲህ በላቸው፦ ‘ከሰማይ ሆኜ እንዳነጋገርኳችሁ እናንተ ራሳችሁ አይታችኋል።+ 23 እኔን የሚቀናቀኑ ከብር የተሠሩ አማልክት አይኑሯችሁ፤ ከወርቅ የተሠሩ አማልክትም አይኑሯችሁ።+ 24 ከጭቃ መሠዊያ ሥራልኝ፤ በእሱም ላይ የሚቃጠሉ መባዎችህን፣ የኅብረት መሥዋዕቶችህን፣* መንጎችህንና ከብቶችህን ሠዋ። ስሜ እንዲታወስ በማደርግበት ቦታ ሁሉ+ ወደ አንተ እመጣለሁ፣ ደግሞም እባርክሃለሁ። 25 ከድንጋይ መሠዊያ የምትሠራልኝ ከሆነ በተጠረቡ ድንጋዮች አትሥራው።+ ምክንያቱም ድንጋዮቹን በመሮህ ከጠረብካቸው ታረክሳቸዋለህ። 26 ኀፍረተ ሥጋህ* በእሱ ላይ እንዳይጋለጥ ወደ መሠዊያዬ በደረጃ አትውጣ።’
21 “ለእነሱ የምትነግራቸው ድንጋጌዎች እነዚህ ናቸው፦+
2 “ዕብራዊ ባሪያ ከገዛህ+ ለስድስት ዓመት ባሪያ ሆኖ ያገለግልሃል፤ በሰባተኛው ዓመት ግን ያለምንም ክፍያ ነፃ ይወጣል።+ 3 የመጣው ብቻውን ከሆነ ብቻውን ነፃ ይወጣል። ሚስት ካለችው ግን ሚስቱም አብራው ነፃ ትውጣ። 4 ጌታው ሚስት ቢያጋባውና ሚስቱ ወንዶች ወይም ሴቶች ልጆችን ብትወልድለት ሚስቱና ልጆቿ የጌታዋ ይሆናሉ፤ እሱም ብቻውን ነፃ ይወጣል።+ 5 ሆኖም ባሪያው ‘ጌታዬን፣ ሚስቴንና ልጆቼን እወዳለሁ፤ ነፃ መውጣት አልፈልግም’+ በማለት በአቋሙ ከጸና 6 ጌታው በእውነተኛው አምላክ ፊት ያቅርበው። ከዚያም ጌታው ወደ በሩ ወይም ወደ መቃኑ አምጥቶ ጆሮውን በወስፌ ይበሳዋል፤ እሱም ዕድሜውን ሙሉ ባሪያው ይሆናል።
7 “አንድ ሰው ሴት ልጁን ባሪያ አድርጎ ቢሸጣት ነፃ የምትወጣው ወንድ ባሪያ ነፃ በሚወጣበት መንገድ አይደለም። 8 ጌታዋ ደስ ባይሰኝባትና ቁባቱ እንድትሆን ባይፈልግ ከዚህ ይልቅ ሌላ ሰው እንዲገዛት* ቢያደርግ እሷን ለባዕድ አገር ሰው የመሸጥ መብት አይኖረውም፤ ምክንያቱም ክህደት ፈጽሞባታል። 9 ለወንድ ልጁ እንድትሆን ከመረጣት ደግሞ አንዲት ልጅ ማግኘት የሚገባትን መብት እንድታገኝ ያድርግ። 10 ሌላ ሚስት ካገባም የመጀመሪያ ሚስቱ ምግቧ፣ ልብሷና የጋብቻ መብቷ ሊጓደልባት አይገባም።+ 11 እነዚህን ሦስት ነገሮች የማያሟላላት ከሆነ ግን ምንም ገንዘብ ሳትከፍል እንዲሁ ነፃ ትውጣ።
12 “አንድ ሰው ሌላውን ሰው መትቶ ቢገድል ገዳዩ ይገደል።+ 13 ሆኖም የገደለው ሆን ብሎ ባይሆንና እውነተኛው አምላክ ይህ ነገር እንዲሆን ቢፈቅድ ገዳዩ የሚሸሽበት ቦታ እኔ አዘጋጅልሃለሁ።+ 14 አንድ ሰው በባልንጀራው ላይ እጅግ ቢቆጣና ሆን ብሎ ቢገድለው+ ይህን ሰው ከመሠዊያዬ አጠገብም እንኳ ቢሆን ወስደህ ግደለው።+ 15 አባቱን ወይም እናቱን የሚመታ ይገደል።+
16 “ማንኛውም ግለሰብ አንድን ሰው አፍኖ ቢወስድና+ ቢሸጠው ወይም ይህን ሰው ይዞት ቢገኝ+ ይገደል።+
17 “አባቱን ወይም እናቱን የሚረግም ይገደል።+
18 “ሰዎች ተጣልተው አንደኛው ሌላውን በድንጋይ ወይም በቡጢ* ቢመታውና ተመቺው ባይሞት ከዚህ ይልቅ አልጋ ላይ ቢውል መደረግ ያለበት ነገር ይህ ነው፦ 19 ሰውየው ከአልጋው በመነሳት ከቤት ወጥቶ በምርኩዝ መንቀሳቀስ ከቻለ የመታው ሰው ከቅጣት ነፃ ይሆናል። ተጎጂው ሙሉ በሙሉ እስኪድን ድረስ ከሥራ በመስተጓጎሉ ለባከነበት ጊዜ ብቻ ካሳ ይከፍላል።
20 “አንድ ሰው ወንድ ባሪያውን ወይም ሴት ባሪያውን በበትር ቢመታና እጁ ላይ ቢሞትበት ወይም ብትሞትበት ይህ ሰው የበቀል ቅጣት መቀጣት አለበት።+ 21 ሆኖም ባሪያው ለአንድ ወይም ለሁለት ቀን በሕይወት ከቆየ የበቀል ቅጣት መቀጣት የለበትም፤ ምክንያቱም ይህ ሰው በጌታው ገንዘብ የተገዛ ነው።
22 “ሰዎች እርስ በርስ ሲታገሉ በአንዲት ነፍሰ ጡር ሴት ላይ ጉዳት ቢያደርሱባትና ያለጊዜዋ ብትወልድ*+ ሆኖም ለሞት* የተዳረገ ባይኖር ጉዳት ያደረሰው ሰው የሴትየዋ ባል የጠየቀውን ካሳ መክፈል አለበት፤ ፈራጆቹ የወሰኑበትን ካሳ መክፈል ይኖርበታል።+ 23 ሆኖም ለሞት የተዳረገ ካለ ሕይወት ስለ ሕይወት፣*+ 24 ዓይን ስለ ዓይን፣ ጥርስ ስለ ጥርስ፣ እጅ ስለ እጅ፣ እግር ስለ እግር፣+ 25 መቃጠል ስለ መቃጠል፣ ቁስል ስለ ቁስል እንዲሁም ምት ስለ ምት እንዲመለስ ማድረግ አለብህ።
26 “አንድ ሰው የወንድ ባሪያውን ወይም የሴት ባሪያውን ዓይን ቢመታና ዓይኑን ቢያጠፋው ለዓይኑ ካሳ እንዲሆን ባሪያውን ነፃ ሊያወጣው ይገባል።+ 27 የወንድ ባሪያውን ወይም የሴት ባሪያውን ጥርስ ቢያወልቅ ለጥርሱ ካሳ እንዲሆን ከባርነቱ ነፃ አድርጎ ሊያሰናብተው ይገባል።
28 “አንድ በሬ አንድን ወንድ ወይም አንዲትን ሴት ቢወጋና የተወጋው ሰው ቢሞት በሬው በድንጋይ ተወግሮ ይገደል፤+ ሥጋውም መበላት የለበትም። የበሬው ባለቤት ግን ከቅጣት ነፃ ነው። 29 በሬው የመዋጋት አመል እንዳለው የሚታወቅ ከሆነና ለባለቤቱም ስለ በሬው ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶት ከነበረ በሬውን ሳይጠብቀው ቀርቶ አንድን ወንድ ወይም አንዲትን ሴት ቢገድል፣ በሬው በድንጋይ ይወገር፤ ባለቤቱም ይገደል። 30 ቤዛ* እንዲከፍል ከተጠየቀ ለሕይወቱ* መዋጃ የሚሆነውን ዋጋ ይክፈል፤ የተጠየቀውንም ሁሉ ይስጥ። 31 በሬው ወንድ ወይም ሴት ልጅ ቢወጋ የበሬው ባለቤት በዚሁ ድንጋጌ መሠረት ሊፈረድበት ይገባል። 32 በሬው የወጋው አንድን ወንድ ባሪያ ወይም አንዲትን ሴት ባሪያ ከሆነ የበሬው ባለቤት ለባሪያው ጌታ 30 ሰቅል* ይሰጠዋል፤ በሬውም በድንጋይ ተወግሮ ይገደላል።
33 “አንድ ሰው ጉድጓድ ከፍቶ ወይም ቆፍሮ ጉድጓዱን ሳይከድነው ቢተወውና አንድ በሬ ወይም አንድ አህያ ጉድጓዱ ውስጥ ቢወድቅ 34 የጉድጓዱ ባለቤት ካሳ መክፈል አለበት።+ ዋጋውን ለእንስሳው ባለቤት መስጠት ይኖርበታል፤ የሞተውም እንስሳ የእሱ ይሆናል። 35 የአንድ ሰው በሬ በሌላው ሰው በሬ ላይ ጉዳት ቢያደርስና በሬው ቢሞት ሰዎቹ በሕይወት ያለውን በሬ ሸጠው ገንዘቡን ይካፈሉ፤ የሞተውንም በሬ ይካፈሉ። 36 ወይም በሬው የመዋጋት አመል እንዳለበት እየታወቀ ባለቤቱ ሳይጠብቀው ቀርቶ ከሆነ ባለቤቱ በበሬ ፋንታ በሬ ካሳ መክፈል አለበት፤ የሞተውም በሬ የእሱ ይሆናል።
22 “አንድ ሰው በሬ ወይም በግ ቢሰርቅና ቢያርደው ወይም ቢሸጠው ለበሬው አምስት በሬዎችን ለበጉ ደግሞ አራት በጎችን ካሳ መክፈል አለበት።+
2 (“አንድ ሌባ+ ሰብሮ ሲገባ ቢያዝና ተመቶ ቢሞት ማንም ስለ እሱ በደም ዕዳ ተጠያቂ አይሆንም። 3 ይህ የሆነው ግን ፀሐይ ከወጣች በኋላ ከሆነ ገዳዩ በደም ዕዳ ተጠያቂ ይሆናል።)
“ሌባው ካሳ መክፈል አለበት። ምንም የሚከፍለው ነገር ከሌለው ግን ለሰረቃቸው ነገሮች ካሳ እንዲከፍል እሱ ራሱ ይሸጥ። 4 የሰረቀው ነገር በሬም ሆነ አህያ ወይም በግ በሕይወት እንዳለ በእጁ ላይ ከተገኘ እጥፍ አድርጎ ካሳ መክፈል አለበት።
5 “አንድ ሰው ከብቶቹን በእርሻ ወይም በወይን ቦታ አሰማርቶ የሌላ ሰው እርሻ ውስጥ ገብተው ሲግጡ ዝም ቢላቸው ይህ ሰው ምርጥ ከሆነው ከራሱ እርሻ ወይም ምርጥ ከሆነው ከራሱ የወይን ቦታ ካሳ መክፈል አለበት።
6 “እሳት ተነስቶ ወደ ቁጥቋጦ ቢዛመትና ነዶዎችን ወይም ያልታጨደን እህል አሊያም አዝመራን ቢያወድም እሳቱን ያስነሳው ሰው ለተቃጠለው ነገር ካሳ መክፈል አለበት።
7 “አንድ ሰው ገንዘብ ወይም ንብረት እንዲያስቀምጥለት ለባልንጀራው ቢሰጠውና ገንዘቡ ወይም ንብረቱ ከባልንጀራው ቤት ቢሰረቅ፣ ሌባው ከተያዘ እጥፍ አድርጎ ካሳ መክፈል አለበት።+ 8 ሌባው ካልተያዘ ግን የቤቱ ባለቤት በባልንጀራው ንብረት ላይ እጁን አሳርፎ እንደሆነና እንዳልሆነ ለማረጋገጥ በእውነተኛው አምላክ ፊት እንዲቀርብ መደረግ አለበት።+ 9 አላግባብ በባለቤትነት የተያዘን ንብረት ይኸውም በሬን፣ አህያን፣ በግን፣ ልብስን ወይም ጠፍቶ የነበረን ማንኛውንም ነገር በተመለከተ ‘ይህ ንብረት የእኔ ነው!’ በሚል ክርክር ቢነሳ፣ ሁለቱም ሰዎች ጉዳያቸውን በእውነተኛው አምላክ ፊት ያቅርቡ።+ አምላክ ጥፋተኛ ነው ብሎ የሚፈርድበት ግለሰብ እጥፍ አድርጎ ለባልንጀራው ካሳ መክፈል አለበት።+
10 “አንድ ሰው አህያ ወይም በሬ ወይም በግ አሊያም ሌላ ማንኛውንም የቤት እንስሳ ለባልንጀራው በአደራ ቢሰጥና እንስሳው ቢሞት ወይም ከባድ ጉዳት ቢደርስበት አሊያም ማንም ሰው ሳያይ ተነድቶ ቢወሰድ 11 አደራ ተቀባዩ በባልንጀራው ንብረት ላይ እጁን እንዳላሳረፈ ለማረጋገጥ በይሖዋ ፊት ይማልለት፤ የንብረቱ ባለቤትም መሐላውን መቀበል አለበት። ያም ሰው ካሳ እንዲከፍል አይጠየቅም።+ 12 እንስሳው ተሰርቆበት ከሆነ ግን ለባለቤቱ ካሳ መክፈል አለበት። 13 በአውሬ ተበልቶ ከሆነ ደግሞ ከአውሬ የተረፈውን ማስረጃ አድርጎ ያቅርብ። አውሬ ለበላው ካሳ መክፈል አይጠበቅበትም።
14 “ሆኖም ማንኛውም ሰው ከባልንጀራው እንስሳ ቢዋስና እንስሳው ባለቤቱ በሌለበት ከባድ ጉዳት ቢደርስበት ወይም ቢሞት የተዋሰው ሰው ካሳ መክፈል አለበት። 15 ጉዳቱ የደረሰው ባለቤቱ አብሮ እያለ ከሆነ ግን ካሳ መክፈል የለበትም። እንስሳው በኪራይ መልክ የተወሰደ ከሆነ የደረሰው ጉዳት በኪራዩ ዋጋ ይሸፈናል።
16 “አንድ ወንድ አንዲትን ያልታጨች ድንግል አባብሎ አብሯት ቢተኛ የማጫዋን ዋጋ ከፍሎ ሚስቱ ሊያደርጋት ይገባል።+ 17 የልጅቷ አባት ልጁን ለእሱ ለመስጠት ፈጽሞ ፈቃደኛ ሳይሆን ቢቀር ይህ ሰው ለደናግል የሚከፈለውን የማጫ ዋጋ መክፈል አለበት።
18 “መተተኛ ሴት በሕይወት እንድትኖር አትፍቀድ።+
19 “ከእንስሳ ጋር የፆታ ግንኙነት የሚፈጽም ማንም ሰው ያለጥርጥር ይገደል።+
20 “ለይሖዋ ካልሆነ በቀር ለሌሎች አማልክት መሥዋዕት የሚያቀርብ ማንኛውም ሰው ይገደል።+
21 “የባዕድ አገር ሰውን አትበድል ወይም አትጨቁን፤+ ምክንያቱም እናንተ ራሳችሁ በግብፅ ምድር ሳላችሁ የባዕድ አገር ሰው ነበራችሁ።+
22 “መበለቲቱን ወይም አባት የሌለውን* ልጅ አታጎሳቁሉ።+ 23 ብታጎሳቁለውና ወደ እኔ ቢጮኽ እኔ በእርግጥ ጩኸቱን እሰማለሁ፤+ 24 ቁጣዬም ይነድዳል። እናንተንም በሰይፍ እገድላችኋለሁ፤ ሚስቶቻችሁ መበለቶች፣ ልጆቻችሁም አባት የሌላቸው ልጆች ይሆናሉ።
25 “ከሕዝቤ መካከል አብሮህ ላለ ችግረኛ ገንዘብ ብታበድር እንደ አራጣ አበዳሪ አትሁንበት። ወለድም አትጠይቁት።+
26 “የባልንጀራህን ልብስ መያዣ አድርገህ ብትይዝ ፀሐይ ከመጥለቋ በፊት ልትመልስለት ይገባል።+ 27 ምክንያቱም የሚለብሰው ልብስ ይኸውም ሰውነቱ ላይ የሚጥለው ልብስ እሱ ብቻ ነው፤ አለዚያ ምን ለብሶ ይተኛል?+ እሱም ወደ እኔ በሚጮኽበት ጊዜ በእርግጥ እሰማዋለሁ፤ ምክንያቱም እኔ ሩኅሩኅ* ነኝ።+
28 “አምላክን አትራገም፤+ በሕዝብህ መካከል ያለውን አለቃም* አትራገም።+
29 “ከተትረፈረፈው ምርትህና ሞልቶ ከሚፈሰው መጭመቂያህ* መባ ለማቅረብ አትሳሳ።+ የወንዶች ልጆችህን በኩር ለእኔ መስጠት አለብህ።+ 30 የበሬህንና የበግህን በኩር በተመለከተ ልታደርገው የሚገባህ ነገር ይህ ነው፦+ ለሰባት ቀን ከእናቱ ጋር ይቆይ። በስምንተኛው ቀን ለእኔ መስጠት አለብህ።+
31 “እናንተ ለእኔ ቅዱስ ሕዝብ ሆናችሁ መገኘት አለባችሁ፤+ አውሬ ዘንጥሎት ሜዳ ላይ የተገኘን የማንኛውንም እንስሳ ሥጋ አትብሉ።+ ለውሾች ጣሉት።
23 “የሐሰት ወሬ አትንዛ።*+ ተንኮል የሚሸርብ ምሥክር በመሆን ከክፉ ሰው ጋር አትተባበር።+ 2 ብዙኃኑን ተከትለህ ክፉ ነገር አታድርግ፤ ከብዙኃኑ ጋር ለመስማማት ስትል የተዛባ* ምሥክርነት በመስጠት ፍትሕን አታጣም። 3 ችግረኛው ሙግት ሲኖረው አታድላለት።+
4 “የጠላትህ በሬ ወይም አህያ ሲባዝን ብታገኘው ወደ እሱ ልትመልሰው ይገባል።+ 5 የሚጠላህ ሰው አህያ ጭነቱ ከብዶት ወድቆ ብታይ ዝም ብለህ አትለፈው። ከዚህ ይልቅ ጭነቱን ከእንስሳው ላይ ለማውረድ እርዳው።+
6 “በመካከልህ ያለ ድሃ ሙግት ሲኖረው ፍርድ አታጣምበት።+
7 “ከሐሰት ክስ* ራቅ፤ እኔ ክፉውን ሰው ጻድቅ እንደሆነ አድርጌ ስለማልቆጥር*+ ንጹሑንና ጻድቁን ሰው አትግደል።
8 “ጉቦ አትቀበል፤ ምክንያቱም ጉቦ አጥርተው የሚያዩ ሰዎችን ዓይን ያሳውራል፤ እንዲሁም የጻድቅ ሰዎችን ቃል ሊያዛባ ይችላል።+
9 “የባዕድ አገር ሰውን አትጨቁን። እናንተ ራሳችሁ በግብፅ ምድር ሳላችሁ የባዕድ አገር ሰው ስለነበራችሁ የባዕድ አገር ሰው መሆን ምን ስሜት እንደሚያሳድር* ታውቃላችሁ።+
10 “ለስድስት ዓመት መሬትህ ላይ ዘር ዝራ፤ አዝመራውንም ሰብስብ።+ 11 በሰባተኛው ዓመት ግን መሬትህን አትረሰው፤ እንዲሁ ተወው። በሕዝብህ መካከል ያሉ ድሆች ከዚያ ይበላሉ፤ ከእነሱ የተረፈውንም የዱር አራዊት ይበሉታል። በወይን እርሻህም ሆነ በወይራ ዛፍ እርሻህ እንደዚሁ ታደርጋለህ።
12 “ለስድስት ቀን ሥራህን ሥራ፤ ሆኖም በሬህና አህያህ እንዲያርፉ እንዲሁም የሴት ባሪያህ ልጅና የባዕድ አገሩ ሰው ጉልበታቸውን እንዲያድሱ በሰባተኛው ቀን ሥራ አትሥራ።+
13 “የነገርኳችሁን ነገሮች በሙሉ በጥንቃቄ ፈጽሙ፤+ እንዲሁም የሌሎች አማልክትን ስም አታንሱ፤ እንዲህ ዓይነቱ ነገር ከአፍህ ሲወጣ ሊሰማ አይገባም።+
14 “በዓመት ሦስት ጊዜ ለእኔ በዓል ታከብርልኛለህ።+ 15 የቂጣን በዓል ታከብራለህ።+ በአቢብ* ወር+ በተወሰነው ጊዜ፣ ባዘዝኩህ መሠረት ለሰባት ቀናት ቂጣ ትበላለህ፤ ምክንያቱም ከግብፅ የወጣኸው በዚህ ጊዜ ነው። ማንም ባዶ እጁን ፊቴ አይቅረብ።+ 16 በተጨማሪም በእርሻህ ላይ በዘራኸው መጀመሪያ በሚደርሰው የድካምህ ፍሬ የመከርን በዓል* አክብር፤+ ከእርሻህ ላይ የድካምህን ፍሬ በምትሰበስብበት በዓመቱ ማብቂያ ላይ የአዝመራ መክተቻን በዓል* አክብር።+ 17 የአንተ የሆኑ ሰዎች* ሁሉ በዓመት ሦስት ጊዜ በእውነተኛው ጌታ በይሖዋ ፊት ይቅረቡ።+
18 “የመሥዋዕቴን ደም እርሾ ከገባበት ከማንኛውም ነገር ጋር አብረህ አታቅርብ። በበዓሎቼም ላይ የሚቀርቡት የስብ መሥዋዕቶች እስከ ጠዋት ድረስ ማደር የለባቸውም።
19 “በምድርህ ላይ የሚገኘውን መጀመሪያ የደረሰውን ምርጥ ፍሬ ወደ አምላክህ ወደ ይሖዋ ቤት አምጣ።+
“የፍየል ጠቦትን በእናቱ ወተት አትቀቅል።+
20 “በመንገድ ላይ እንዲጠብቅህና ወዳዘጋጀሁት ስፍራ እንዲያመጣህ በፊትህ መልአክ እልካለሁ።+ 21 የሚልህን ስማ፤ ቃሉንም ታዘዝ። መተላለፋችሁን ይቅር ስለማይል+ በእሱ ላይ አታምፁ፤ ምክንያቱም እሱ ስሜን ተሸክሟል። 22 ይሁን እንጂ ቃሉን በጥንቃቄ ብትታዘዝና የምልህን ሁሉ ብታደርግ ለጠላቶችህ ጠላት እሆናለሁ፤ የሚቃወሙህንም እቃወማለሁ። 23 ምክንያቱም መልአኬ በፊትህ ይሄዳል፤ እንዲሁም ወደ አሞራውያን፣ ሂታውያን፣ ፈሪዛውያን፣ ከነአናውያን፣ ሂዋውያንና ኢያቡሳውያን ያመጣሃል፤ እኔም ጠራርጌ አጠፋቸዋለሁ።+ 24 ለአማልክታቸው አትስገድ፤ ወይም ተታለህ እነሱን አታገልግል፤ የሚያደርጉትን ነገር አታድርግ።+ ከዚህ ይልቅ አውድማቸው፤ የማምለኪያ ዓምዶቻቸውንም ሰባብር።+ 25 አምላካችሁን ይሖዋን አገልግሉ፤+ እሱም ምግብህንና ውኃህን ይባርክልሃል።+ እኔም ከመካከልህ በሽታን አስወግዳለሁ።+ 26 በምድርህ ላይ የሚኖሩ ሴቶች አያስወርዳቸውም ወይም መሃን አይሆኑም፤+ ረጅም ዕድሜ እሰጥሃለሁ።
27 “አንተ ከመድረስህ በፊት ስለ እኔ ሰምተው ይፈራሉ፤+ የምታገኛቸውም ሕዝቦች ሁሉ ግራ እንዲጋቡ አደርጋለሁ። ጠላቶችህም ሁሉ ድል ተመተው ከፊትህ እንዲሸሹ* አደርጋለሁ።+ 28 ከአንተ አስቀድሜ ጭንቀት* እልካለሁ፤+ ሂዋውያንን፣ ከነአናውያንንና ሂታውያንን ከፊትህ አባሮ ያስወጣቸዋል።+ 29 ምድሩ ባድማ እንዳይሆንና የዱር አራዊት በዝተው እንዳያስቸግሩህ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ከፊትህ አባርሬ አላስወጣቸውም።+ 30 ቁጥርህ እስኪበዛና ምድሩን እስክትቆጣጠር ድረስ ጥቂት በጥቂት ከፊትህ አባርሬ አስወጣቸዋለሁ።+
31 “ወሰንህንም ከቀይ ባሕር አንስቶ እስከ ፍልስጤማውያን ባሕር እንዲሁም ከምድረ በዳው አንስቶ እስከ ወንዙ* ድረስ አደርገዋለሁ።+ ምክንያቱም የምድሩን ነዋሪዎች በእጃችሁ አሳልፌ እሰጣችኋለሁ፤ አንተም ከፊትህ አባረህ ታስወጣቸዋለህ።+ 32 ከእነሱም ሆነ ከአማልክታቸው ጋር ቃል ኪዳን መግባት የለብህም።+ 33 በእኔ ላይ ኃጢአት እንድትሠራ እንዳያደርጉህ በምድርህ ላይ መኖር የለባቸውም። አማልክታቸውን ብታገለግል ወጥመድ ይሆንብሃል።”+
24 ሙሴንም እንዲህ አለው፦ “አንተ፣ አሮን፣ ናዳብ፣ አቢሁና+ 70ዎቹ የእስራኤል ሽማግሌዎች ወደ ይሖዋ ውጡ፤ ከሩቅ ሆናችሁም ስገዱ። 2 ሙሴ ብቻውን ወደ ይሖዋ ይቅረብ፤ ሌሎቹ ግን መቅረብ የለባቸውም፤ ሕዝቡም ከእሱ ጋር መውጣት የለበትም።”+
3 ከዚያም ሙሴ መጥቶ የይሖዋን ቃል ሁሉ እንዲሁም ድንጋጌዎቹን በሙሉ ለሕዝቡ ነገራቸው፤+ ሕዝቡም ሁሉ “ይሖዋ የተናገረውን ቃል በሙሉ ለመፈጸም ፈቃደኞች ነን”+ ሲሉ በአንድ ድምፅ መለሱ። 4 ስለሆነም ሙሴ የይሖዋን ቃል ሁሉ በጽሑፍ አሰፈረ።+ በማለዳም ተነስቶ በተራራው ግርጌ መሠዊያና 12ቱን የእስራኤል ነገዶች የሚወክሉ 12 ዓምዶች ሠራ። 5 ከዚያም ወጣት እስራኤላውያን ወንዶችን ላከ፤ እነሱም የሚቃጠሉ መባዎችን አቀረቡ፤ እንዲሁም በሬዎችን የኅብረት መሥዋዕቶች+ አድርገው ለይሖዋ ሠዉ። 6 ሙሴም ከደሙ ግማሹን ወስዶ በሳህኖች ውስጥ አስቀመጠው፤ ግማሹን ደም ደግሞ በመሠዊያው ላይ ረጨው። 7 ከዚያም የቃል ኪዳኑን መጽሐፍ ወስዶ ድምፁን ከፍ በማድረግ ለሕዝቡ አነበበ።+ ሕዝቡም “ይሖዋ የተናገረውን ሁሉ ለመፈጸምና ለመታዘዝ ፈቃደኞች ነን” አሉ።+ 8 በመሆኑም ሙሴ ደሙን ወስዶ በሕዝቡ ላይ ረጨው፤+ እንዲህም አለ፦ “በእነዚህ ቃላት መሠረት ይሖዋ ከእናንተ ጋር የገባው ቃል ኪዳን ደም ይህ ነው።”+
9 ሙሴ፣ አሮን፣ ናዳብ፣ አቢሁና 70ዎቹ የእስራኤል ሽማግሌዎች ወደ ላይ ወጡ፤ 10 የእስራኤልንም አምላክ አዩ።+ ከእግሩም ሥር እንደ ሰማይ የጠራ የሰንፔር ንጣፍ የሚመስል ነገር ነበር።+ 11 እሱም በእስራኤል አለቆች+ ላይ ጉዳት አላደረሰባቸውም፤ እነሱም እውነተኛውን አምላክ በራእይ ተመለከቱ፤ በሉ፣ ጠጡም።
12 በዚህ ጊዜ ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ወደ እኔ ወደ ተራራው ውጣና በዚያ ቆይ። ለሕዝቡ መመሪያ እንዲሆን እኔ የጻፍኩትን ሕግና ትእዛዝ የያዙትን የድንጋይ ጽላቶች እሰጥሃለሁ።”+ 13 በመሆኑም ሙሴ ከአገልጋዩ ከኢያሱ+ ጋር ተነስቶ ወደ እውነተኛው አምላክ ተራራ ወጣ።+ 14 ሽማግሌዎቹን ግን እንዲህ አላቸው፦ “ወደ እናንተ እስክንመለስ ድረስ እዚሁ ጠብቁን።+ አሮንና ሁር+ አብረዋችሁ ናቸው። ሙግት ያለው ሰው ቢኖር እነሱ ፊት መቅረብ ይችላል።”+ 15 ሙሴም ወደ ተራራው ሲወጣ ደመናው ተራራውን ሸፍኖት ነበር።+
16 የይሖዋም ክብር+ በሲና ተራራ ላይ እንዳረፈ ነበር፤+ ደመናውም ለስድስት ቀናት ተራራውን ሸፍኖት ነበር። በሰባተኛውም ቀን ከደመናው መሃል ሙሴን ጠራው። 17 ሁኔታውን ይከታተሉ ለነበሩት እስራኤላውያን የይሖዋ ክብር በተራራው አናት ላይ እንዳለ የሚባላ እሳት ሆኖ ታያቸው። 18 ከዚያም ሙሴ ወደ ደመናው ገባ፤ ወደ ተራራውም ወጣ።+ ሙሴም በተራራው ላይ 40 ቀንና 40 ሌሊት ቆየ።+
25 ከዚያም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ 2 “ለእስራኤላውያን መዋጮ እንዲያመጡልኝ ንገራቸው፤ ለመስጠት ልቡ ካነሳሳው ከእያንዳንዱ ሰው መዋጮዬን ትቀበላላችሁ።+ 3 ከእነሱ የምትቀበሉት መዋጮም ይህ ነው፦ ወርቅ፣+ ብር፣+ መዳብ፣+ 4 ሰማያዊ ክር፣ ሐምራዊ ሱፍ፣* ደማቅ ቀይ ማግ፣ ጥሩ በፍታ፣ የፍየል ፀጉር፣ 5 ቀይ ቀለም የተነከረ የአውራ በግ ቆዳ፣ የአቆስጣ ቆዳ፣ የግራር እንጨት፣+ 6 ለመብራት የሚሆን ዘይት፣+ ለቅብዓት ዘይትና+ ጥሩ መዓዛ ላለው ዕጣን+ የሚሆን በለሳን፣ 7 ለኤፉዱ+ እንዲሁም ለደረት ኪሱ+ የሚሆኑ የኦኒክስ ድንጋዮችና ሌሎች ድንጋዮች። 8 ለእኔም መቅደስ ይሠሩልኛል፤ እኔም በመካከላቸው እኖራለሁ።*+ 9 የማደሪያ ድንኳኑንም ሆነ በውስጡ የሚቀመጡትን ቁሳቁሶች ሁሉ እኔ በማሳይህ ንድፍ መሠረት ትሠሯቸዋላችሁ።+
10 “ርዝመቱ ሁለት ክንድ* ተኩል፣ ወርዱ አንድ ክንድ ተኩል እንዲሁም ከፍታው አንድ ክንድ ተኩል የሆነ ታቦት* ከግራር እንጨት ይሠራሉ።+ 11 ከዚያም በንጹሕ ወርቅ ትለብጠዋለህ።+ ውስጡንና ውጭውን ትለብጠዋለህ፤ በዙሪያውም የወርቅ ክፈፍ ትሠራለታለህ።+ 12 አራት የወርቅ ቀለበቶች ትሠራለታለህ፤ ከዚያም ሁለቱን ቀለበቶች በአንዱ በኩል ሁለቱን ቀለበቶች ደግሞ በሌላው በኩል በማድረግ ከአራቱ እግሮቹ በላይ ታያይዛቸዋለህ። 13 ከግራር እንጨት መሎጊያዎችን ትሠራለህ፤ በወርቅም ትለብጣቸዋለህ።+ 14 ታቦቱን ለመሸከም እንዲያገለግሉ መሎጊያዎቹን በታቦቱ ጎንና ጎን ባሉት ቀለበቶች ውስጥ ታስገባቸዋለህ። 15 መሎጊያዎቹ በታቦቱ ቀለበቶች ውስጥ እንዳሉ ይቀመጣሉ፤ ከዚያ መውጣት የለባቸውም።+ 16 የምሰጥህንም ምሥክር በታቦቱ ውስጥ ታስቀምጠዋለህ።+
17 “እንዲሁም ርዝመቱ ሁለት ክንድ ተኩል፣ ወርዱ ደግሞ አንድ ክንድ ተኩል የሆነ መክደኛ ከንጹሕ ወርቅ ትሠራለህ።+ 18 ሁለት የወርቅ ኪሩቦችን ትሠራለህ፤ ወርቁን በመጠፍጠፍም በመክደኛው ጫፍና ጫፍ ላይ ወጥ አድርገህ ትሠራቸዋለህ።+ 19 በሁለቱ የመክደኛው ጫፎች ላይ ኪሩቦቹን ሥራ፤ አንዱን ኪሩብ በዚህኛው ጫፍ፣ ሌላኛውን ኪሩብ ደግሞ በዚያኛው ጫፍ ላይ ሥራ። 20 ኪሩቦቹ ሁለቱን ክንፎቻቸውን ወደ ላይ በመዘርጋት መክደኛውን በክንፎቻቸው ይከልሉታል፤+ እነሱም ትይዩ ይሆናሉ። የኪሩቦቹ ፊት ወደ መክደኛው ያጎነበሰ ይሆናል። 21 መክደኛውንም+ በታቦቱ ላይ ትገጥመዋለህ፤ የምሰጥህንም ምሥክር በታቦቱ ውስጥ ታስቀምጠዋለህ። 22 እኔም በዚያ እገለጥልሃለሁ፤ ከመክደኛውም በላይ ሆኜ አነጋግርሃለሁ።+ በምሥክሩ ታቦት ላይ በሚገኙት በሁለቱ ኪሩቦች መካከል ሆኜ እስራኤላውያንን በተመለከተ የማዝህንም ሁሉ አሳውቅሃለሁ።
23 “በተጨማሪም ርዝመቱ ሁለት ክንድ፣ ወርዱ አንድ ክንድ፣ ከፍታው ደግሞ አንድ ክንድ ተኩል የሆነ ጠረጴዛ ከግራር እንጨት ትሠራለህ።+ 24 በንጹሕ ወርቅ ትለብጠዋለህ፤ በዙሪያውም የወርቅ ክፈፍ ትሠራለታለህ። 25 ዙሪያውንም አንድ ጋት* ስፋት ያለው ጠርዝ ታበጅለታለህ፤ በጠርዙም ዙሪያ የወርቅ ክፈፍ ታደርግለታለህ። 26 አራት የወርቅ ቀለበቶች ትሠራለታለህ፤ ከዚያም ቀለበቶቹን አራቱ እግሮቹ በሚገኙባቸው አራት ማዕዘኖች ላይ ታደርጋቸዋለህ። 27 ጠረጴዛውን ለመሸከም የሚያገለግሉትን መሎጊያዎች እንዲይዙ ቀለበቶቹ በጠርዙ አጠገብ ይሆናሉ። 28 መሎጊያዎቹንም ከግራር እንጨት ሠርተህ በወርቅ ትለብጣቸዋለህ፤ ጠረጴዛውንም በእነሱ አማካኝነት ትሸከማለህ።
29 “ለመጠጥ መባ ማፍሰሻ የሚያገለግሉትን ሳህኖቹን፣ ጽዋዎቹን፣ ማንቆርቆሪያዎቹንና ጎድጓዳ ሳህኖቹን ትሠራለህ። ከንጹሕ ወርቅ ትሠራቸዋለህ።+ 30 ገጸ ኅብስቱን በጠረጴዛው ላይ ሁልጊዜ በፊቴ ታስቀምጣለህ።+
31 “ከንጹሕ ወርቅ መቅረዝ+ ትሠራለህ። መቅረዙም ወጥ ከሆነ ወርቅ ተጠፍጥፎ የተሠራ ይሁን። የመቅረዙ መቆሚያ፣ ግንድ፣ ቅርንጫፎች፣ አበባ አቃፊዎች፣ እንቡጦችና የፈኩት አበቦች ወጥ ሆነው የተሠሩ ይሆናሉ።+ 32 በመቅረዙ ጎንና ጎን ስድስት ቅርንጫፎች ይኖራሉ፤ ሦስቱ የመቅረዙ ቅርንጫፎች ከአንዱ ጎን፣ ሦስቱ የመቅረዙ ቅርንጫፎች ደግሞ ከሌላው ጎን የወጡ ይሆናሉ። 33 በአንዱ በኩል ባሉት ቅርንጫፎች በእያንዳንዳቸው ላይ የአልሞንድ አበባ የሚመስሉ ሦስት የአበባ አቃፊዎችን ከእንቡጦቹና ከፈኩት አበቦች ጋር እያፈራረቅክ ትሠራለህ፤ በሌላኛው በኩል ባሉት ቅርንጫፎችም በእያንዳንዳቸው ላይ የአልሞንድ አበባ የሚመስሉ ሦስት የአበባ አቃፊዎችን ከእንቡጦቹና ከፈኩት አበቦች ጋር እያፈራረቅክ ትሠራለህ። ስድስቱ ቅርንጫፎች ከመቅረዙ ግንድ የሚወጡት በዚህ መንገድ ይሆናል። 34 በግንዱ ላይም የአልሞንድ አበባ የሚመስሉ አራት የአበባ አቃፊዎችን ከእንቡጦቹና ከፈኩት አበቦች ጋር እያፈራረቅክ ትሠራለህ። 35 ከግንዱ በሚወጡት በመጀመሪያዎቹ ሁለት ቅርንጫፎች ሥር አንድ እንቡጥ ይኖራል፤ በቀጣዮቹ ሁለት ቅርንጫፎች ሥርም አንድ እንቡጥ ይኖራል፤ በቀጣዮቹ ሁለት ቅርንጫፎች ሥርም እንዲሁ አንድ እንቡጥ ይኖራል፤ ከግንዱ የሚወጡት ስድስቱም ቅርንጫፎች በዚሁ መንገድ ይሠራሉ። 36 እንቡጦቹና ቅርንጫፎቻቸው እንዲሁም የመቅረዙ ሁለመና ንጹሕ ከሆነ አንድ ወጥ ወርቅ ተጠፍጥፈው የተሠሩ ይሆናሉ።+ 37 ሰባት መብራቶች ትሠራለታለህ፤ መብራቶቹ በሚለኮሱበት ጊዜ ከፊት ለፊቱ ላለው አካባቢ ብርሃን ይሰጣሉ።+ 38 መቆንጠጫዎቹና መኮስተሪያዎቹ ከንጹሕ ወርቅ የተሠሩ ይሁኑ።+ 39 ቁሳቁሶቹ ሁሉ ከአንድ ታላንት* ንጹሕ ወርቅ ይሠሩ። 40 በተራራው ላይ ተገልጦልህ ባየኸው ንድፍ መሠረት ተጠንቅቀህ ሥራቸው።+
26 “በቀጭኑ ከተፈተለ ጥሩ በፍታ፣ ከሰማያዊ ክር፣ ከሐምራዊ ሱፍ እንዲሁም ከደማቅ ቀይ ማግ ከተዘጋጁ አሥር የድንኳን ጨርቆች የማደሪያ ድንኳኑን+ ትሠራለህ። በጨርቆቹ ላይ ኪሩቦችን+ ትጠልፍባቸዋለህ።+ 2 የእያንዳንዱ የድንኳን ጨርቅ ርዝመት 28 ክንድ* ወርዱ ደግሞ 4 ክንድ ይሆናል። ሁሉም የድንኳን ጨርቆች መጠናቸው እኩል ይሆናል።+ 3 አምስቱ የድንኳን ጨርቆች አንድ ላይ ይቀጣጠላሉ፤ የቀሩት አምስቱ የድንኳን ጨርቆችም እንዲሁ አንድ ላይ ይቀጣጠላሉ። 4 እርስ በርስ ከተቀጣጠሉት የድንኳን ጨርቆች በመጨረሻው ጨርቅ ጠርዝ ላይ ከሰማያዊ ክር የተሠሩ ማቆላለፊያዎችን ታደርጋለህ፤ እርስ በርስ የተቀጣጠለው ሌላኛው የድንኳን ጨርቅ ከዚህኛው ጋር በሚጋጠምበት የመጨረሻው የድንኳን ጨርቅ ጠርዝ ላይም እንዲሁ ታደርጋለህ። 5 በአንደኛው የድንኳን ጨርቅ ላይ 50 ማቆላለፊያዎችን ትሠራለህ፤ በሌላኛው የድንኳን ጨርቅ ጠርዝ ላይም 50 ማቆላለፊያዎችን ታደርጋለህ፤ ማቆላለፊያዎቹም የሚጋጠሙበት ቦታ ላይ እርስ በርሳቸው ትይዩ ይሆናሉ። 6 ከዚያም 50 የወርቅ ማያያዣዎችን ሠርተህ የድንኳን ጨርቆቹን በማያያዣዎቹ አማካኝነት እርስ በርስ ታጋጥማቸዋለህ፤ በዚህ መንገድ ማደሪያ ድንኳኑ አንድ ወጥ ይሆናል።+
7 “በተጨማሪም ለማደሪያ ድንኳኑ ልባስ የሚሆኑ ጨርቆችን ከፍየል ፀጉር+ ትሠራለህ። አሥራ አንድ የድንኳን ጨርቆችን ትሠራለህ።+ 8 የእያንዳንዱ የድንኳን ጨርቅ ርዝመት 30 ክንድ ወርዱ ደግሞ 4 ክንድ ይሆናል። የአሥራ አንዱም የድንኳን ጨርቆች መጠን እኩል ይሆናል። 9 አምስቱን የድንኳን ጨርቆች አንድ ላይ ትቀጣጥላቸዋለህ፤ የቀሩትን ስድስቱን የድንኳን ጨርቆች ደግሞ አንድ ላይ ትቀጣጥላቸዋለህ፤ ስድስተኛውን የድንኳን ጨርቅ በድንኳኑ ፊት በኩል ታጥፈዋለህ። 10 እርስ በርስ ከተቀጣጠሉት የድንኳን ጨርቆች በመጨረሻው ጠርዝ ላይ 50 ማቆላለፊያዎችን ትሠራለህ፤ እርስ በርስ የተቀጣጠለው ሌላኛው የድንኳን ጨርቅ ከዚህኛው ጋር በሚጋጠምበት ጨርቅ ጠርዝ ላይም 50 ማቆላለፊያዎችን ታደርጋለህ። 11 ከዚያም 50 የመዳብ ማያያዣዎችን ትሠራለህ፤ ማያያዣዎቹንም ማቆላለፊያዎቹ ውስጥ በማስገባት ድንኳኑን ታጋጥመዋለህ፤ በዚህ መንገድ የድንኳኑ ጨርቅ አንድ ወጥ ይሆናል። 12 ከድንኳኑ ጨርቆች ትርፍ ሆኖ የወጣው እንደተንጠለጠለ ይተዋል። ትርፍ ሆኖ የወጣው ግማሹ የድንኳን ጨርቅ በማደሪያ ድንኳኑ ጀርባ ላይ ይንጠለጠላል። 13 ትርፍ ሆኖ የወጣው አንድ አንድ ክንድ ጨርቅ ድንኳኑን እንዲሸፍን በማደሪያ ድንኳኑ ጎንና ጎን ይንጠለጠላል።
14 “በተጨማሪም ቀይ ቀለም ከተነከረ የአውራ በግ ቆዳ ለድንኳኑ መደረቢያ ትሠራለህ፤ በዚያ ላይ የሚደረግ መደረቢያም ከአቆስጣ ቆዳ ትሠራለህ።+
15 “የግራር እንጨት ጣውላዎችን በማገጣጠም ለማደሪያ ድንኳኑ የሚሆኑ አራት ማዕዘን ቋሚዎችን ትሠራለህ።+ 16 የእያንዳንዱ ቋሚ ቁመት አሥር ክንድ ወርዱ ደግሞ አንድ ክንድ ተኩል ይሆናል። 17 እያንዳንዱ ቋሚም እርስ በርስ የተያያዙ ሁለት ጉጦች ይኑሩት። ለማደሪያ ድንኳኑ የሚያገለግሉትን ቋሚዎች በሙሉ በዚህ መንገድ ሥራቸው። 18 በስተ ደቡብ በኩል ለሚገኘው ፊቱ በደቡብ አቅጣጫ ላለው የማደሪያ ድንኳኑ ጎን 20 ቋሚዎችን ትሠራለህ።
19 “ከ20ዎቹ ቋሚዎች ሥር የሚሆኑ 40 የብር መሰኪያዎችን+ ትሠራለህ፤ በአንዱ ቋሚ ሥር ያሉት ሁለት ጉጦች ሁለት መሰኪያዎች፣ ቀጥሎ ባለው በእያንዳንዱ ቋሚ ሥር ያሉት ሁለት ጉጦችም+ ሁለት መሰኪያዎች ይኖሯቸዋል። 20 በስተ ሰሜን በኩል ላለው ለሌላኛውም የማደሪያ ድንኳኑ ጎን 20 ቋሚዎችን ሥራ፤ 21 እንዲሁም 40 የብር መሰኪያዎቻቸውን ሥራ፤ በአንዱ ቋሚ ሥር ሁለት መሰኪያዎች፣ ቀጥሎ ባለው በእያንዳንዱም ቋሚ ሥር ሁለት መሰኪያዎች ይኑሩ። 22 በስተ ምዕራብ በኩል ለሚገኘው ለኋለኛው የማደሪያ ድንኳኑ ጎን ስድስት ቋሚዎችን ትሠራለህ።+ 23 በማደሪያ ድንኳኑ በስተ ኋላ በኩል የማዕዘን ቋሚዎች እንዲሆኑ ሁለት ቋሚዎችን ትሠራለህ። 24 ቋሚዎቹም ከታች አንስቶ የመጀመሪያው ቀለበት እስከሚገኝበት እስከ ላይ ድረስ ድርብ መሆን አለባቸው። ሁለቱም በዚህ መንገድ መሠራት አለባቸው፤ እነሱም ሁለት የማዕዘን ቋሚዎች ሆነው ያገለግላሉ። 25 ስምንት ቋሚዎችና ከብር የተሠሩ 16 መሰኪያዎች ይኸውም በአንዱ ቋሚ ሥር ሁለት መሰኪያዎች፣ ቀጥሎ ባለው በእያንዳንዱም ቋሚ ሥር ሁለት መሰኪያዎች ይኖራሉ።
26 “ከግራር እንጨት አግዳሚ እንጨቶችን ታዘጋጃለህ፤ በአንዱ ጎን ላሉት የማደሪያ ድንኳኑ ቋሚዎች አምስት አግዳሚ እንጨቶችን፣+ 27 በሌላኛው ጎን ላሉት የማደሪያ ድንኳኑ ቋሚዎች አምስት አግዳሚ እንጨቶችን እንዲሁም በስተ ምዕራብ በኩል ባለው በኋለኛው የማደሪያ ድንኳኑ ጎን ላሉት ቋሚዎች አምስት አግዳሚ እንጨቶችን ታዘጋጃለህ። 28 በቋሚዎቹ መሃል ላይ የሚያርፈው መካከለኛው አግዳሚ እንጨት ከጫፍ እስከ ጫፍ የሚዘልቅ መሆን ይኖርበታል።
29 “ቋሚዎቹን በወርቅ ትለብጣቸዋለህ፤+ አግዳሚ እንጨቶቹን የሚሸከሙትን የቋሚዎቹን ቀለበቶች ከወርቅ ትሠራቸዋለህ፤ አግዳሚ እንጨቶቹንም በወርቅ ትለብጣቸዋለህ። 30 የማደሪያ ድንኳኑን በተራራው ላይ ተገልጦልህ ባየኸው ንድፍ መሠረት ትከለው።+
31 “ከሰማያዊ ክር፣ ከሐምራዊ ሱፍ፣ ከደማቅ ቀይ ማግ እንዲሁም በቀጭኑ ከተፈተለ ጥሩ የበፍታ ድር መጋረጃ+ ትሠራለህ። በላዩም ላይ ኪሩቦች ይጠለፉበታል። 32 መጋረጃውንም በወርቅ በተለበጡ አራት የግራር እንጨት ዓምዶች ላይ ታንጠለጥለዋለህ። ማንጠልጠያዎቻቸውም ከወርቅ የተሠሩ ይሁኑ። ዓምዶቹም ከብር በተሠሩ አራት መሰኪያዎች ላይ ይቆማሉ። 33 መጋረጃውን ከማያያዣዎቹ በታች ታንጠለጥለዋለህ፤ የምሥክሩንም ታቦት+ በመጋረጃው ውስጥ ታስቀምጠዋለህ። መጋረጃውም ቅድስቱንና+ ቅድስተ ቅዱሳኑን+ ለመለየት ያገለግላችኋል። 34 መክደኛውንም በቅድስተ ቅዱሳኑ ውስጥ በሚገኘው በምሥክሩ ታቦት ላይ ግጠመው።
35 “ጠረጴዛውንም ከመጋረጃው ውጭ ታስቀምጠዋለህ፤ መቅረዙን+ በስተ ደቡብ በኩል ባለው የማደሪያ ድንኳኑ ጎን ከጠረጴዛው ትይዩ ታስቀምጠዋለህ፤ ጠረጴዛውን ደግሞ በስተ ሰሜን በኩል ታስቀምጠዋለህ። 36 ለድንኳኑ መግቢያ ከሰማያዊ ክር፣ ከሐምራዊ ሱፍ፣ ከደማቅ ቀይ ማግ እንዲሁም በቀጭኑ ከተፈተለ ጥሩ የበፍታ ድር የተሸመነ መከለያ* ትሠራለህ።+ 37 ለመከለያውም* አምስት ዓምዶችን ከግራር እንጨት ትሠራለህ፤ በወርቅም ትለብጣቸዋለህ። ማንጠልጠያዎቹም ከወርቅ የተሠሩ ይሆናሉ፤ ለዓምዶቹም አምስት የመዳብ መሰኪያዎችን ትሠራለህ።
27 “ርዝመቱ አምስት ክንድ፣* ወርዱም አምስት ክንድ የሆነ መሠዊያ ከግራር እንጨት ትሠራለህ።+ መሠዊያው አራቱም ጎኖቹ እኩል፣ ከፍታው ደግሞ ሦስት ክንድ መሆን አለበት።+ 2 በአራቱ ማዕዘኖቹ ላይ ቀንዶች+ ትሠራለታለህ፤ ቀንዶቹም የመሠዊያው ክፍል ይሆናሉ፤ መሠዊያውንም በመዳብ ትለብጠዋለህ።+ 3 አመዱን* ማስወገጃ ባልዲዎችን፣ አካፋዎችን፣ ሳህኖችን፣ ሹካዎችንና መኮስተሪያዎችን ትሠራለህ፤ ዕቃዎቹንም ሁሉ ከመዳብ ትሠራቸዋለህ።+ 4 ለመሠዊያው እንደ መረብ አድርገህ የመዳብ ፍርግርግ ትሠራለታለህ፤ በፍርግርጉ በአራቱም ማዕዘኖቹ ላይ አራት የመዳብ ቀለበቶችን ትሠራለታለህ። 5 ፍርግርጉንም ከመሠዊያው ጠርዝ ወደ ታች ወረድ አድርገህ ታስቀምጠዋለህ፤ ፍርግርጉም መሠዊያው መሃል አካባቢ ይሆናል። 6 ለመሠዊያው የሚሆኑ መሎጊያዎችን ከግራር እንጨት ትሠራለህ፤ በመዳብም ትለብጣቸዋለህ። 7 መሎጊያዎቹም ቀለበቶቹ ውስጥ ይገባሉ፤ መሠዊያውን በምትሸከሙበትም ጊዜ መሎጊያዎቹ በሁለቱ ጎኖቹ በኩል ይሆናሉ።+ 8 መሠዊያውንም ባዶ ሣጥን አስመስለህ ከሳንቃ ትሠራዋለህ። ልክ ተራራው ላይ ባሳየህ መሠረት ይሠራ።+
9 “የማደሪያ ድንኳኑን ግቢ ትሠራለህ።+ በስተ ደቡብ በኩል የሚገኘው፣ ፊቱ በደቡብ አቅጣጫ ያለው የግቢው ጎን በቀጭኑ ከተፈተለ ጥሩ በፍታ የተሠሩ መጋረጃዎች ይኖሩታል፤ የአንዱ ጎን ርዝመት 100 ክንድ ይሆናል።+ 10 ግቢው 20 ቋሚዎችና ከመዳብ የተሠሩ 20 መሰኪያዎች ይኖሩታል። በቋሚዎቹ ላይ ያሉት ማንጠልጠያዎችና ማያያዣዎቻቸው* ደግሞ ከብር የተሠሩ ይሆናሉ። 11 በስተ ሰሜን በኩል በሚገኘው ጎን ያሉት መጋረጃዎችም ርዝመታቸው 100 ክንድ ይሆናል፤ እንዲሁም 20 ቋሚዎችና ለቋሚዎቹ የሚሆኑ ከመዳብ የተሠሩ 20 መሰኪያዎች ይኖራሉ፤ በቋሚዎቹም ላይ ማንጠልጠያዎችና ማያያዣዎች* ይኖራሉ። 12 በስተ ምዕራብ አቅጣጫ በግቢው ወርድ ልክ 50 ክንድ ርዝመት ያላቸው መጋረጃዎች ይኖራሉ፤ አሥር ቋሚዎችና አሥር መሰኪያዎችም ይኖሯቸዋል። 13 በስተ ምሥራቅ አቅጣጫ በፀሐይ መውጫ በኩል ያለው የግቢው ወርድ 50 ክንድ ነው። 14 በአንዱ በኩል 15 ክንድ ርዝመት ያላቸው መጋረጃዎች ይኖራሉ፤ ሦስት ቋሚዎችና ሦስት መሰኪያዎችም ይኖሯቸዋል።+ 15 በሌላኛውም በኩል 15 ክንድ ርዝመት ያላቸው መጋረጃዎች ይኖራሉ፤ ሦስት ቋሚዎችና ሦስት መሰኪያዎችም ይኖሯቸዋል።
16 “የግቢው መግቢያ ከሰማያዊ ክር፣ ከሐምራዊ ሱፍ፣ ከደማቅ ቀይ ማግ እንዲሁም በቀጭኑ ከተፈተለ ጥሩ የበፍታ ድር+ ተሸምኖ የተሠራ 20 ክንድ ርዝመት ያለው መከለያ* ይኑረው፤ አራት ቋሚዎችና ለቋሚዎቹ የሚሆኑ አራት መሰኪያዎችም ይኑሩት።+ 17 በግቢው ዙሪያ ያሉት ቋሚዎች በሙሉ ከብር የተሠሩ መቆንጠጫዎችና ከብር የተሠሩ ማንጠልጠያዎች ይኖሯቸዋል፤ መሰኪያዎቻቸው ግን ከመዳብ የተሠሩ ይሆናሉ።+ 18 ግቢው ርዝመቱ 100 ክንድ፣+ ወርዱ 50 ክንድ ሆኖ በቀጭኑ ከተፈተለ ጥሩ በፍታ የተሠሩ 5 ክንድ ከፍታ ያላቸው መጋረጃዎች ይኖሩታል፤ ከመዳብ የተሠሩ መሰኪያዎችም ይኑሩት። 19 በማደሪያ ድንኳኑ ውስጥ ለሚቀርበው አገልግሎት የሚውሉት ቁሳቁሶችና ዕቃዎች በሙሉ እንዲሁም የድንኳኑ ካስማዎችና የግቢው ካስማዎች በሙሉ ከመዳብ የተሠሩ ይሆናሉ።+
20 “አንተም መብራቶቹ ያለማቋረጥ እንዲበሩ ለመብራት የሚሆን ተጨቅጭቆ የተጠለለ የወይራ ዘይት እንዲያመጡልህ እስራኤላውያንን ታዛቸዋለህ።+ 21 አሮንና ወንዶች ልጆቹ መብራቶቹ በመገናኛ ድንኳኑ ውስጥ በምሥክሩ+ አጠገብ ካለው መጋረጃ ውጭ ከምሽት አንስቶ እስከ ጠዋት ድረስ በይሖዋ ፊት+ እንዲበሩ ያደርጋሉ። ይህ እስራኤላውያን በትውልዶቻቸው ሁሉ የሚፈጽሙት ዘላቂ ደንብ ነው።+
28 “አንተም ለእኔ ካህን ሆኖ እንዲያገለግለኝ+ ወንድምህን አሮንን ከወንዶች ልጆቹ ጋር ከእስራኤላውያን መካከል ለይተህ ትጠራዋለህ፤ አሮንን+ እንዲሁም የአሮንን ወንዶች ልጆች+ ናዳብን፣ አቢሁን፣+ አልዓዛርንና ኢታምርን+ ትጠራቸዋለህ። 2 ለወንድምህ ለአሮንም ክብርና ውበት የሚያጎናጽፉትን ቅዱስ ልብሶች ትሠራለታለህ።+ 3 የጥበብ መንፈስ የሞላሁባቸውን ጥሩ ችሎታ* ያላቸውን ሰዎች+ ሁሉ አንተ ራስህ ታናግራቸዋለህ፤ እነሱም አሮን ለእኔ ካህን ሆኖ እንዲያገለግለኝ እሱን ለመቀደስ ልብሶቹን ይሠሩለታል።
4 “የሚሠሯቸው ልብሶችም እነዚህ ናቸው፦ የደረት ኪስ፣+ ኤፉድ፣+ እጅጌ የሌለው ቀሚስ፣+ በካሬ ንድፍ የተሸመነ ረጅም ቀሚስ፣ ጥምጥምና+ መቀነት፤+ ወንድምህ አሮንና ወንዶች ልጆቹ ካህን ሆነው እንዲያገለግሉኝ እነዚህን ቅዱስ ልብሶች ይሠሩላቸዋል። 5 እነዚህ የእጅ ጥበብ ባለሙያዎች ወርቁን፣ ሰማያዊውን ክር፣ ሐምራዊውን ሱፍ፣ ደማቁን ቀይ ማግና ጥሩውን በፍታ ተጠቅመው ይሠሯቸዋል።
6 “ከወርቅ፣ ከሰማያዊ ክር፣ ከሐምራዊ ሱፍ፣ ከደማቅ ቀይ ማግና በቀጭኑ ከተፈተለ ጥሩ በፍታ ኤፉዱን ያዘጋጃሉ፤ ኤፉዱም ጥልፍ የተጠለፈበት ይሁን።+ 7 ኤፉዱ በሁለቱ የላይኛው ጫፎቹ ላይ የተያያዙ ሁለት የትከሻ ጥብጣቦች ይኖሩታል። 8 ኤፉዱ ወዲያ ወዲህ እንዳይንቀሳቀስ ለማሰር የሚያገለግለው ከኤፉዱ ጋር የተያያዘው በሽመና የተሠራው መቀነት+ ልክ እንደ ኤፉዱ ከወርቅ፣ ከሰማያዊ ክር፣ ከሐምራዊ ሱፍ፣ ከደማቅ ቀይ ማግና በቀጭኑ ከተፈተለ ጥሩ በፍታ የተሠራ መሆን ይኖርበታል።
9 “ሁለት የኦኒክስ ድንጋዮችን+ ወስደህ የእስራኤልን ወንዶች ልጆች ስሞች+ ትቀርጽባቸዋለህ፤ 10 በትውልዳቸው ቅደም ተከተል መሠረት የስድስቱን ስሞች በአንዱ ድንጋይ ላይ፣ የቀሩትን የስድስቱን ስሞች ደግሞ በሌላኛው ድንጋይ ላይ ትቀርጻለህ። 11 አንድ ቅርጽ አውጪ በድንጋይ ላይ ማኅተም እንደሚቀርጽ ሁሉ የእስራኤልን ወንዶች ልጆች ስሞች በሁለቱ ድንጋዮች ላይ ይቀርጽባቸዋል።+ ከዚያም በወርቅ አቃፊዎች ውስጥ እንዲቀመጡ ታደርጋለህ። 12 ለእስራኤል ልጆች እንደ መታሰቢያ ድንጋዮች ሆነው እንዲያገለግሉ ሁለቱን ድንጋዮች በኤፉዱ የትከሻ ጥብጣቦች ላይ ታስቀምጣቸዋለህ፤+ አሮንም እንደ መታሰቢያ ሆነው እንዲያገለግሉ ስሞቻቸውን በሁለቱ የትከሻ ጥብጣቦች ላይ በይሖዋ ፊት ይሸከማል። 13 አንተም የወርቅ አቃፊዎችን 14 እንዲሁም እንደ ገመድ የተገመዱ ሁለት ሰንሰለቶችን ከንጹሕ ወርቅ ትሠራለህ፤+ የተገመዱትንም ሰንሰለቶች ከአቃፊዎቹ ጋር አያይዛቸው።+
15 “የፍርዱን የደረት ኪስ የጥልፍ ባለሙያ እንዲሠራው ታደርጋለህ።+ የደረት ኪሱ ልክ እንደ ኤፉዱ ከወርቅ፣ ከሰማያዊ ክር፣ ከሐምራዊ ሱፍ፣ ከደማቅ ቀይ ማግና በቀጭኑ ከተፈተለ ጥሩ በፍታ መሠራት ይኖርበታል።+ 16 ለሁለት በሚታጠፍበትም ጊዜ ቁመቱ አንድ ስንዝር፣* ወርዱ ደግሞ አንድ ስንዝር የሆነ ካሬ ይሁን። 17 የከበሩ ድንጋዮችን* በአራት ረድፍ በማቀፊያ ውስጥ ታደርግበታለህ። በመጀመሪያው ረድፍ ሩቢ፣ ቶጳዝዮንና መረግድ ይደርደር። 18 በሁለተኛው ረድፍ በሉር፣ ሰንፔርና ኢያስጲድ ይደርደር። 19 በሦስተኛው ረድፍ ለሼም፣ አካትምና አሜቴስጢኖስ ይደርደር። 20 በአራተኛውም ረድፍ ክርስቲሎቤ፣ ኦኒክስና ጄድ ይደርደር። በወርቅ አቃፊዎችም ውስጥ ይቀመጡ። 21 ድንጋዮቹም የእስራኤልን ወንዶች ልጆች ስሞች ማለትም 12ቱን በየስማቸው የሚወክሉ ይሆናሉ። ለ12ቱም ነገዶች ልክ ማኅተም በሚቀረጽበት መንገድ ለእያንዳንዳቸው በየስማቸው ይቀረጽላቸው።
22 “በደረት ኪሱም ላይ ከንጹሕ ወርቅ እንደተሠሩ ገመዶች የተጎነጎኑ ሰንሰለቶችን ትሠራለህ።+ 23 ለደረት ኪሱም ሁለት የወርቅ ቀለበቶችን ሠርተህ ሁለቱን ቀለበቶች ከሁለቱ የደረት ኪሱ ጫፎች ጋር ታያይዛቸዋለህ። 24 ሁለቱን የወርቅ ገመዶችም በደረት ኪሱ ዳርና ዳር ባሉት ጫፎች ላይ በሚገኙት በሁለቱ ቀለበቶች ውስጥ ታስገባቸዋለህ። 25 የሁለቱን ገመዶች ሁለት ጫፎች በሁለቱ አቃፊዎች ውስጥ ታስገባለህ፤ እነሱንም ከኤፉዱ የትከሻ ጥብጣቦች ጋር በፊት በኩል ታያይዛቸዋለህ። 26 ሁለት የወርቅ ቀለበቶችንም ሠርተህ በኤፉዱ በኩል በሚውለው በደረት ኪሱ ውስጠኛ ጠርዝ ላይ ባሉት ሁለት ጫፎች ላይ ታደርጋቸዋለህ።+ 27 ሁለት ተጨማሪ የወርቅ ቀለበቶችንም ሠርተህ በኤፉዱ በፊት በኩል ከሁለቱ የትከሻ ጥብጣቦች በታች ኤፉዱ በተጋጠመበት ቦታ አካባቢ፣ በሽመና ከተሠራው የኤፉዱ መቀነት በላይ አድርጋቸው።+ 28 የደረት ኪሱ ከቦታው እንዳይንቀሳቀስ የደረት ኪሱ ቀለበቶች ከኤፉዱ ቀለበቶች ጋር በሰማያዊ ገመድ መያያዝ ይኖርባቸዋል። ይህም የደረት ኪሱ ከመቀነቱ በላይ ከኤፉዱ ላይ ሳይንቀሳቀስ እንዲቀመጥ ያደርገዋል።
29 “አሮን ወደ ቅድስቱ በሚገባበት ጊዜ በይሖዋ ፊት ቋሚ መታሰቢያ እንዲሆን በልቡ ላይ በሚገኘው የፍርድ የደረት ኪስ የእስራኤልን ልጆች ስሞች ይሸከም። 30 ኡሪሙንና ቱሚሙን*+ በፍርድ የደረት ኪሱ ውስጥ ታስቀምጣቸዋለህ፤ አሮን በይሖዋ ፊት ለመቅረብ በሚገባበት ጊዜ በልቡ ላይ መሆን አለባቸው፤ አሮን በይሖዋ ፊት በሚቀርብበት ጊዜ ለእስራኤላውያን ፍርድ መስጫውን ዘወትር በልቡ ላይ ይሸከም።
31 “እጅጌ የሌለውን የኤፉዱን ቀሚስ ሙሉ በሙሉ ከሰማያዊ ክር ትሠራዋለህ።+ 32 ከላይ በኩል መሃል ላይ የአንገት ማስገቢያ ይኖረዋል። የአንገት ማስገቢያውም ዙሪያውን በሽመና ባለሙያ የተሠራ ቅምቅማት ይኑረው። የአንገት ማስገቢያውም እንዳይቀደድ እንደ ጥሩር አንገትጌ ሆኖ ይሠራ። 33 በታችኛው ጠርዝ ዙሪያ ከሰማያዊ ክር፣ ከሐምራዊ ሱፍና ከደማቅ ቀይ ማግ የተሠሩ ሮማኖችን አድርግ፤ በመሃል በመሃላቸውም የወርቅ ቃጭሎች አድርግ። 34 እጅጌ በሌለው ቀሚስ በታችኛው ጠርዝ ዙሪያ የወርቅ ቃጭል ከዚያም ሮማን፣ የወርቅ ቃጭል ከዚያም ሮማን እያፈራረቅክ አንጠልጥልበት። 35 አሮን በሚያገለግልበት ጊዜ ይህን ልብስ መልበስ አለበት፤ በይሖዋ ፊት ለመቅረብ ወደ መቅደሱ በሚገባበትና ከዚያ በሚወጣበት ጊዜ እንዳይሞት የቃጭሎቹ ድምፅ መሰማት አለበት።+
36 “ከንጹሕ ወርቅም የሚያብረቀርቅ ጠፍጣፋ ወርቅ ሠርተህ ልክ ማኅተም በሚቀረጽበት መንገድ ‘ቅድስና የይሖዋ ነው’+ ብለህ ትቀርጽበታለህ። 37 እሱንም በሰማያዊ ገመድ በጥምጥሙ ላይ እሰረው፤+ በጥምጥሙ ላይ ከፊት በኩል ይሆናል። 38 በአሮን ግንባር ላይ ይሆናል፤ አሮንም አንድ ሰው ቅዱስ ከሆኑ ነገሮች ይኸውም እስራኤላውያን ቅዱስ ስጦታ አድርገው በሚያቀርቧቸው ጊዜ ከሚቀድሷቸው ነገሮች ጋር በተያያዘ ለሚፈጽመው ስህተት ተጠያቂ ይሆናል።+ በይሖዋም ፊት ተቀባይነት እንዲያገኙ ዘወትር በግንባሩ ላይ መሆን ይኖርበታል።
39 “ከጥሩ በፍታ ረጅም ቀሚስ በካሬ ንድፍ ትሸምንለታለህ፤ እንዲሁም ከጥሩ በፍታ ጥምጥም ትሠራለህ፤ በተጨማሪም በሽመና የተሠራ መቀነት ትሠራለህ።+
40 “ለአሮን ወንዶች ልጆችም ክብርና ውበት የሚያጎናጽፏቸውን+ ረጃጅም ቀሚሶች፣ መቀነቶችና የራስ ቆቦች ትሠራላቸዋለህ።+ 41 ወንድምህን አሮንንና ወንዶች ልጆቹን ታለብሳቸዋለህ፤ እንዲሁም ትቀባቸዋለህ፣+ ትሾማቸዋለህ*+ ደግሞም ትቀድሳቸዋለህ፤ እነሱም ካህናት ሆነው ያገለግሉኛል። 42 እርቃናቸውን የሚሸፍኑበት የበፍታ ቁምጣም ትሠራላቸዋለህ።+ ቁምጣውም ከወገባቸው እስከ ጭናቸው የሚደርስ ይሆናል። 43 በደል እንዳይሆንባቸውና እንዳይሞቱ አሮንና ወንዶች ልጆቹ ወደ መገናኛ ድንኳኑ በሚገቡበት ጊዜ ወይም ቅዱስ በሆነው ስፍራ ለማገልገል ወደ መሠዊያው በሚቀርቡበት ጊዜ እነዚህን ልብሶች መልበስ አለባቸው። ይህ ለእሱም ሆነ ከእሱ በኋላ ለሚመጡት ዘሮቹ ዘላለማዊ ደንብ ነው።
29 “ለእኔ ካህናት ሆነው እንዲያገለግሉኝ እነሱን ለመቀደስ የምታደርገው ነገር ይህ ነው፦ እንከን የሌለበትን አንድ ወይፈንና እንከን የሌለባቸውን ሁለት አውራ በጎች ውሰድ፤+ 2 እንዲሁም ቂጣ፣* በዘይት ከተለወሰ ሊጥ የተጋገረ የቀለበት ቅርጽ ያለው እርሾ ያልገባበት ዳቦና ዘይት የተቀባ ስስ ቂጣ ውሰድ።+ እነዚህንም ከላመ የስንዴ ዱቄት ጋግረህ 3 በቅርጫት ውስጥ ታደርጋቸዋለህ፤ በቅርጫት ውስጥ አድርገህም+ ከወይፈኑና ከሁለቱ አውራ በጎች ጋር ታቀርባቸዋለህ።
4 “አሮንንና ወንዶች ልጆቹን ወደ መገናኛ ድንኳኑ መግቢያ+ ታቀርባቸዋለህ፤ በውኃም ታጥባቸዋለህ።+ 5 ከዚያም ልብሶቹን+ ወስደህ ረጅሙን ቀሚስ፣ እጅጌ የሌለውን የኤፉዱን ቀሚስ፣ ኤፉዱንና የደረት ኪሱን አሮንን አልብሰው፤ በሽመና የተሠራውን የኤፉዱን መቀነትም ወገቡ ላይ ጠበቅ አድርገህ ታስርለታለህ።+ 6 ጥምጥሙንም በራሱ ላይ ታደርግለታለህ፤ በጥምጥሙም ላይ ለአምላክ የተወሰኑ መሆንን የሚያሳየውን ቅዱስ ምልክት* ታደርጋለህ፤+ 7 የቅብዓት ዘይቱንም+ ወስደህ በራሱ ላይ በማፍሰስ ትቀባዋለህ።+
8 “ከዚያም ወንዶች ልጆቹን አምጥተህ ረጃጅሞቹን ቀሚሶች አልብሳቸው፤+ 9 አሮንንና ወንዶች ልጆቹን መቀነቱን አስታጥቃቸው፤ የራስ ቆባቸውንም አድርግላቸው፤ ክህነቱም ዘላለማዊ ደንብ ሆኖ የእነሱ ይሆናል።+ በዚህም መንገድ አሮንና ወንዶች ልጆቹ ካህናት ሆነው እንዲያገለግሉ ትሾማቸዋለህ።*+
10 “ከዚያም ወይፈኑን በመገናኛ ድንኳኑ ፊት ታቀርበዋለህ፤ አሮንና ወንዶች ልጆቹም በወይፈኑ ራስ ላይ እጆቻቸውን ይጭናሉ።+ 11 ወይፈኑንም በመገናኛ ድንኳኑ መግቢያ ላይ በይሖዋ ፊት እረደው።+ 12 ከወይፈኑም ደም ላይ የተወሰነውን ወስደህ በጣትህ በመሠዊያው ቀንዶች+ ላይ አድርግ፤ የቀረውንም ደም በሙሉ መሠዊያው ሥር አፍስሰው።+ 13 ከዚያም አንጀቱን የሸፈነውን ስብ+ ሁሉ፣ በጉበቱ ላይ ያለውን ሞራ፣ ሁለቱን ኩላሊቶችና በእነሱ ላይ ያለውን ስብ ውሰድ፤ በመሠዊያውም ላይ እንዲጨሱ አቃጥላቸው።+ 14 የወይፈኑን ሥጋ፣ ቆዳውንና ፈርሱን ግን ከሰፈሩ ውጭ አውጥተህ በእሳት ታቃጥለዋለህ። ይህ የኃጢአት መባ ነው።
15 “ከዚያም አንዱን አውራ በግ ውሰድ፤ አሮንና ወንዶች ልጆቹም በአውራው በግ ራስ ላይ እጆቻቸውን ይጫኑ።+ 16 አንተም አውራውን በግ እረደው፤ ደሙንም ወስደህ በመሠዊያው ጎኖች ሁሉ ላይ እርጨው።+ 17 አውራውንም በግ በየብልቱ ቆራርጠው፤ ሆድ ዕቃውንና እግሮቹንም እጠባቸው፤+ ከዚያም የተቆራረጡትን ብልቶች ከጭንቅላቱ ጋር አሰናድተህ አስቀምጣቸው። 18 አውራውንም በግ ሙሉ በሙሉ በማቃጠል በመሠዊያው ላይ እንዲጨስ አድርገው። ይህም ለይሖዋ የሚቀርብ የሚቃጠል መባ ይኸውም ደስ የሚያሰኝ* መዓዛ+ ነው። ለይሖዋ በእሳት የሚቀርብ መባ ነው።
19 “ከዚያም ሌላኛውን አውራ በግ ትወስዳለህ፤ አሮንና ወንዶች ልጆቹም በአውራው በግ ራስ ላይ እጆቻቸውን ይጭኑበታል።+ 20 አንተም አውራውን በግ እረደው፤ ከደሙም ወስደህ የአሮንን የቀኝ ጆሮ ጫፍና የወንዶች ልጆቹን የቀኝ ጆሮ ጫፍ፣ የቀኝ እጃቸውን አውራ ጣት እንዲሁም የቀኝ እግራቸውን አውራ ጣት ቀባ፤ ደሙንም በመሠዊያው ጎኖች ሁሉ ላይ እርጨው። 21 በመሠዊያው ላይ ካለው ደምና ከቅብዓት ዘይቱ+ ውሰድ፤ ከዚያም አሮንና ልብሶቹ እንዲሁም ወንዶች ልጆቹና ልብሶቻቸው ቅዱስ እንዲሆኑ በአሮንና በልብሶቹ እንዲሁም በወንዶች ልጆቹና በልብሶቻቸው ላይ እርጨው።+
22 “አውራው በግ የክህነት ሹመት ሥርዓት በሚካሄድበት ጊዜ የሚቀርብ+ ስለሆነ ከአውራው በግ ላይ ስቡን፣ ላቱን፣ አንጀቱን የሚሸፍነውን ስብ፣ የጉበቱን ሞራ፣ ሁለቱን ኩላሊቶችና በእነሱ ላይ ያለውን ስብ+ እንዲሁም ቀኝ እግሩን ውሰድ። 23 በተጨማሪም በይሖዋ ፊት ካለው ቂጣ ከተቀመጠበት ቅርጫት ውስጥ ቂጣውን፣ በዘይት ከተለወሰ ሊጥ የተጋገረውን የቀለበት ቅርጽ ያለው ዳቦና ስሱን ቂጣ ውሰድ። 24 ሁሉንም በአሮን እጅና በወንዶች ልጆቹ እጅ ላይ አስቀምጣቸው፤ ከዚያም በይሖዋ ፊት እንደሚወዘወዝ መባ ወዲያና ወዲህ ወዝውዛቸው። 25 በይሖዋም ፊት ደስ የሚያሰኝ* መዓዛ እንዲሆን ከእጃቸው ላይ ወስደህ በመሠዊያው ላይ ባለው በሚቃጠለው መባ ላይ ታቃጥላቸዋለህ። ይህ ለይሖዋ በእሳት የሚቀርብ መባ ነው።
26 “ከዚያም ለአሮን የክህነት ሹመት ሥርዓት የሚቀርበውን አውራ በግ+ ፍርምባ ወስደህ በይሖዋ ፊት እንደሚወዘወዝ መባ ወዲያና ወዲህ ወዝውዘው፤ እሱም የአንተ ድርሻ ይሆናል። 27 ለአሮንና ለወንዶች ልጆቹ የክህነት ሹመት ሥርዓት ከቀረበው አውራ በግ+ ተወስዶ ለሚወዘወዝ መባ የቀረበውን ፍርምባና የተቀደሰ ድርሻ እንዲሆን የተወዘወዘውን እግር ትቀድሳቸዋለህ። 28 ይህም የተቀደሰ ድርሻ ስለሆነ የአሮንና የወንዶች ልጆቹ ይሆናል፤ ይህም እስራኤላውያን የሚፈጽሙት ዘላለማዊ ሥርዓት ነው፤ ይህ ድርሻ እስራኤላውያን የሚያቀርቡት የተቀደሰ ድርሻ ይሆናል።+ ከሚያቀርቧቸው የኅብረት መሥዋዕቶች ላይ ለይሖዋ የሚሰጥ የተቀደሰ ድርሻቸው ነው።+
29 “የአሮን ቅዱስ ልብሶችም+ ከእሱ በኋላ የሚመጡት ወንዶች ልጆቹ በሚቀቡበትና ካህናት ሆነው በሚሾሙበት ጊዜ ይገለገሉባቸዋል።+ 30 ከወንዶች ልጆቹ መካከል እሱን የሚተካውና በቅዱሱ ስፍራ ለማገልገል ወደ መገናኛ ድንኳኑ የሚገባው ካህን ለሰባት ቀን ይለብሳቸዋል።+
31 “ለክህነት ሹመት ሥርዓት የሚቀርበውን አውራ በግ ወስደህ ሥጋውን በተቀደሰ ስፍራ ትቀቅለዋለህ።+ 32 አሮንና ወንዶች ልጆቹ የአውራውን በግ ሥጋና በቅርጫቱ ውስጥ ያለውን ቂጣ በመገናኛ ድንኳኑ መግቢያ ላይ ይበሉታል።+ 33 እነሱን ካህናት አድርጎ ለመሾምና* ለመቀደስ ማስተሰረያ ሆነው የቀረቡትን ነገሮች ይበላሉ። ሆኖም እነዚህ ነገሮች የተቀደሱ ስለሆኑ ያልተፈቀደለት ሰው* ሊበላቸው አይችልም።+ 34 ለክህነት ሹመት ሥርዓቱ መሥዋዕት ሆኖ ከቀረበው ሥጋና ቂጣ ተርፎ ያደረ ካለ የተረፈውን በእሳት አቃጥለው።+ የተቀደሰ ስለሆነ መበላት የለበትም።
35 “እኔ ባዘዝኩህ ሁሉ መሠረት ለአሮንና ለወንዶች ልጆቹ በዚሁ መንገድ ታደርግላቸዋለህ። እነሱን ካህናት አድርገህ ለመሾም* ሰባት ቀን ይፈጅብሃል።+ 36 ለማስተሰረያ እንዲሆን የኃጢአት መባ የሚሆነውን በሬ በየዕለቱ ታቀርባለህ፤ ለመሠዊያውም ማስተሰረያ በማቅረብ መሠዊያውን ከኃጢአት ታነጻዋለህ፤ መሠዊያውን ለመቀደስም ቀባው።+ 37 መሠዊያውን ለማስተሰረይ ሰባት ቀን ይፈጅብሃል፤ እጅግ ቅዱስ መሠዊያ እንዲሆንም ቀድሰው።+ መሠዊያውን የሚነካ ማንኛውም ሰው ቅዱስ መሆን አለበት።
38 “በመሠዊያውም ላይ የምታቀርበው እነዚህን ይሆናል፦ አንድ ዓመት የሆናቸው ሁለት የበግ ጠቦቶችን በየቀኑ ሳታቋርጥ ታቀርባለህ።+ 39 አንደኛውን የበግ ጠቦት ጠዋት ላይ ታቀርበዋለህ፤ ሌላኛውን የበግ ጠቦት ደግሞ አመሻሹ ላይ* ታቀርበዋለህ።+ 40 ተጨቅጭቆ በተጠለለ አንድ አራተኛ ሂን* ዘይት የተለወሰ የኢፍ መስፈሪያ* አንድ አሥረኛ የላመ ዱቄትና ለመጠጥ መባ የሚሆን አንድ አራተኛ ሂን የወይን ጠጅ ከመጀመሪያው የበግ ጠቦት ጋር ይቅረብ። 41 ሁለተኛውንም የበግ ጠቦት ልክ ማለዳ ላይ ከምታቀርባቸው ጋር ተመሳሳይ ከሆኑ የእህልና የመጠጥ መባዎች ጋር አመሻሹ ላይ* ታቀርበዋለህ። ይህን ደስ የሚያሰኝ* መዓዛ ይኸውም ለይሖዋ በእሳት የሚቀርብ መባ አድርገህ ታቀርበዋለህ። 42 ይህም እኔ እናንተን ለማነጋገር ራሴን በምገልጥበት በመገናኛ ድንኳኑ+ መግቢያ ላይ በመጪዎቹ ትውልዶቻችሁ ሁሉ በይሖዋ ፊት ዘወትር የሚቀርብ የሚቃጠል መባ ይሆናል።
43 “እኔም በዚያ ራሴን ለእስራኤላውያን እገልጣለሁ፤ ያም ስፍራ በክብሬ+ የተቀደሰ ይሆናል። 44 የመገናኛ ድንኳኑንና መሠዊያውን እቀድሰዋለሁ፤ ካህናት ሆነው እንዲያገለግሉኝ አሮንንና ወንዶች ልጆቹን እቀድሳቸዋለሁ።+ 45 እኔም በእስራኤል ሕዝብ መካከል እኖራለሁ፤* አምላካቸውም እሆናለሁ።+ 46 እነሱም በመካከላቸው እኖር ዘንድ ከግብፅ ምድር ያወጣኋቸው እኔ አምላካቸው ይሖዋ መሆኔን በእርግጥ ያውቃሉ።+ እኔ አምላካቸው ይሖዋ ነኝ።
30 “ዕጣን የሚጨስበት መሠዊያ ትሠራለህ፤+ ከግራር እንጨትም ትሠራዋለህ።+ 2 ርዝመቱ አንድ ክንድ፣* ወርዱ አንድ ክንድ ሆኖ አራቱም ጎኖቹ እኩል ይሁኑ፤ ቁመቱ ደግሞ ሁለት ክንድ ይሁን። ቀንዶቹም ከዚያው ወጥ ሆነው የተሠሩ ይሆናሉ።+ 3 ላዩን፣ ሁሉንም ጎኖቹን እንዲሁም ቀንዶቹን በንጹሕ ወርቅ ትለብጠዋለህ፤ ዙሪያውንም የወርቅ ክፈፍ ትሠራለታለህ። 4 በተጨማሪም በሁለቱ ተቃራኒ ጎኖቹ ላይ ከክፈፉ በታች ሁለት የወርቅ ቀለበቶችን ትሠራለታለህ፤ ቀለበቶቹም መሠዊያውን ለመሸከም የሚያገለግሉት መሎጊያዎች የሚገቡባቸው ይሆናሉ። 5 መሎጊያዎቹን ከግራር እንጨት ሠርተህ በወርቅ ለብጣቸው። 6 ራሴን ለአንተ ከምገልጥበት+ ከምሥክሩ ታቦት+ አጠገብ ካለው መጋረጃ በፊት ይኸውም ምሥክሩን ከሚጋርደው መከለያ በፊት ታስቀምጠዋለህ።
7 “አሮንም+ ጥሩ መዓዛ ያለው ዕጣን+ ያጨስበታል፤+ በየማለዳው መብራቶቹን+ በሚያዘገጃጅበት ጊዜም ዕጣኑ በመሠዊያው ላይ እንዲጨስ ያደርጋል። 8 በተጨማሪም አሮን አመሻሹ ላይ* መብራቶቹን በሚያበራበት ጊዜ ዕጣኑን ያጨሰዋል። ይህም በትውልዶቻችሁ ሁሉ ዘወትር በይሖዋ ፊት የሚቀርብ የዕጣን መባ ነው። 9 በዚህ መሠዊያ ላይ ያልተፈቀደ ዕጣን+ ወይም የሚቃጠል መባ አሊያም የእህል መባ አታቅርቡ፤ እንዲሁም በላዩ ላይ የመጠጥ መባ አታፍስሱ። 10 አሮንም በዓመት አንድ ጊዜ በቀንዶቹ ላይ ማስተሰረያ ያድርግ።+ ለማስተሰረያ ከቀረበው የኃጢአት መባ ላይ የተወሰነ ደም ወስዶ+ በዓመት አንድ ጊዜ ለመሠዊያው ማስተሰረያ ያደርጋል፤ ይህም በትውልዶቻችሁ ሁሉ ይደረጋል። ይህ ለይሖዋ እጅግ የተቀደሰ ነው።”
11 ከዚያም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ 12 “የሕዝብ ቆጠራ በማካሄድ የእስራኤልን ልጆች በምትቆጥርበት+ ጊዜ ሁሉ እያንዳንዱ ሰው በቆጠራው ወቅት ለይሖዋ ስለ ሕይወቱ* ቤዛ መስጠት አለበት። ይህን የሚያደርጉት በሚመዘገቡበት ጊዜ መቅሰፍት እንዳይመጣባቸው ነው። 13 የተመዘገቡት ሁሉ የሚሰጡት ይህን ነው፦ እንደ ቋሚ መለኪያ ሆኖ በሚያገለግለው በቅዱሱ ስፍራ ሰቅል* መሠረት+ ግማሽ ሰቅል* ይሰጣሉ። አንድ ሰቅል ሃያ ጌራ* ነው። ለይሖዋ የሚሰጠው መዋጮ ግማሽ ሰቅል ነው።+ 14 ሃያ ዓመትና ከዚያ በላይ ሆኗቸው የተመዘገቡት ሁሉ ለይሖዋ መዋጮ ይሰጣሉ።+ 15 ለሕይወታችሁ* ማስተሰረያ እንዲሆን ለይሖዋ መዋጮ በምትሰጡበት ጊዜ ባለጸጋው ከግማሽ ሰቅል* አብልጦ፣ ችግረኛውም ከግማሽ ሰቅል አሳንሶ አይስጥ። 16 ለሕይወታችሁ* ማስተሰረያ በመሆን በይሖዋ ፊት ለእስራኤላውያን እንደ መታሰቢያ ሆኖ እንዲያገለግል ለማስተሰረያ የቀረበውን የብር ገንዘብ ከእስራኤላውያን ወስደህ በመገናኛ ድንኳኑ ውስጥ ለሚቀርበው አገልግሎት ትሰጠዋለህ።”
17 በተጨማሪም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ 18 “ለመታጠቢያ እንዲሆን ከመዳብ ገንዳና ማስቀመጫውን ሥራ፤+ በመገናኛ ድንኳኑና በመሠዊያው መካከል አስቀምጠው፤ ውኃም ጨምርበት።+ 19 አሮንና ወንዶች ልጆቹም እጃቸውንና እግራቸውን ይታጠቡበታል።+ 20 ወደ መገናኛ ድንኳኑ በሚገቡበት ወይም ለማገልገልና በእሳት የሚቀርብ መባ ለይሖዋ ለማቅረብ ወደ መሠዊያው በሚቀርቡበት ጊዜ እንዳይሞቱ በውኃ ይታጠባሉ። 21 እንዳይሞቱ እጃቸውንና እግራቸውን ይታጠቡ፤ ይህም ለእሱና ለዘሮቹ በትውልዶቻቸው ሁሉ ዘላለማዊ ሥርዓት ሆኖ ያገልግል።”+
22 ይሖዋም እንዲህ በማለት ሙሴን ማነጋገሩን ቀጠለ፦ 23 “አንተም ጥሩ መዓዛ ያላቸውን የሚከተሉትን ምርጥ ቅመሞች ውሰድ፦ 500 ሰቅል የረጋ ከርቤ፣ የዚህን ግማሽ ይኸውም 250 ሰቅል ጣፋጭ ቀረፋ፣ 250 ሰቅል ጥሩ መዓዛ ያለው ጠጅ ሣር፣ 24 እንደ ቋሚ መለኪያ ሆኖ በሚያገለግለው በቅዱሱ ስፍራ ሰቅል* መሠረት+ 500 ሰቅል ብርጉድ* እንዲሁም አንድ ሂን* የወይራ ዘይት። 25 ከእነዚህም ቅዱስ የቅብዓት ዘይት አዘጋጅ፤ በብልሃት የተቀመመ መሆን ይኖርበታል።+ ይህም ቅዱስ የቅብዓት ዘይት ይሆናል።
26 “አንተም የመገናኛ ድንኳኑንና+ የምሥክሩን ታቦት 27 እንዲሁም ጠረጴዛውንና ዕቃዎቹን በሙሉ፣ መቅረዙንና ዕቃዎቹን፣ የዕጣን መሠዊያውን፣ 28 የሚቃጠል መባ የሚቀርብበትን መሠዊያና ዕቃዎቹን በሙሉ እንዲሁም የውኃ ገንዳውንና ማስቀመጫውን በዘይቱ ትቀባለህ። 29 እጅግ ቅዱስ እንዲሆኑም ቀድሳቸው።+ የሚነካቸው ማንኛውም ሰው ቅዱስ መሆን አለበት።+ 30 አንተም አሮንንና ወንዶች ልጆቹን ትቀባቸዋለህ፤+ ካህናት ሆነው እንዲያገለግሉኝም+ ትቀድሳቸዋለህ።
31 “አንተም ለእስራኤላውያን እንዲህ ብለህ ትነግራቸዋለህ፦ ‘በትውልዶቻችሁ ሁሉ ይህ ምንጊዜም ለእኔ ቅዱስ የቅብዓት ዘይት ይሆናል።+ 32 ይህ ማንም ሰው ሰውነቱን የሚቀባው አይደለም፤ እንዲሁም በተመሳሳይ መንገድ በመቀመም እንዲህ ያለ ቅባት ማዘጋጀት የለባችሁም። ይህ የተቀደሰ ነገር ነው። ለእናንተም ምንጊዜም የተቀደሰ ይሆናል። 33 ይህን የመሰለ ቅባት የሚሠራና ያልተፈቀደለትን ሰው* የሚቀባ ማንኛውም ሰው ከሕዝቡ መካከል ተለይቶ እንዲጠፋ ይደረግ።’”+
34 ከዚያም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ “አንተም ጥሩ መዓዛ ካላቸው ቅመሞች+ ይኸውም ከሚንጠባጠብ ሙጫ፣ ከኦኒካ፣* ከሚሸት ሙጫ እንዲሁም ከንጹሕ ነጭ ዕጣን እኩል መጠን ውሰድ። 35 ከዚያም ዕጣን አድርገህ አዘጋጀው፤+ ይህም ዕጣን በብልሃት የተቀመመ፣ ጨው የተጨመረበት፣+ ንጹሕና ቅዱስ መሆን ይኖርበታል። 36 ከእሱም የተወሰነውን ወቅጠህ በማላም ራሴን ለአንተ በምገልጥበት በመገናኛ ድንኳኑ ውስጥ ባለው ምሥክር ፊት ታስቀምጠዋለህ። ይህም ለእናንተ እጅግ ቅዱስ መሆን ይኖርበታል። 37 በተመሳሳይ መንገድ የተቀመመ ዕጣን ለራስህ ማዘጋጀት የለብህም።+ ለይሖዋ የተቀደሰ እንደሆነ አድርገህ ልትመለከተው ይገባል። 38 በመዓዛው ለመደሰት ሲል ይህን የመሰለ ዕጣን የሚያዘጋጅ ማንኛውም ሰው ከሕዝቡ መካከል ተለይቶ እንዲጠፋ ይደረግ።”
31 ይሖዋ እንዲህ በማለት ሙሴን ማነጋገሩን ቀጠለ፦ 2 “እንግዲህ እኔ ከይሁዳ ነገድ የሆነው የሁር ልጅ ዖሪ+ የወለደውን ባስልኤልን+ መርጬዋለሁ።* 3 ደግሞም ጥበብ፣ ማስተዋልና እውቀት በመስጠት በማንኛውም ዓይነት የእጅ ሙያ የተካነ እንዲሆን በአምላክ መንፈስ እሞላዋለሁ፤ 4 ይህን የማደርገው የተለያዩ ንድፎችን እንዲያወጣ፣ በወርቅ፣ በብርና በመዳብ የተለያዩ ነገሮችን እንዲሠራ፣ 5 ፈርጥ የሚሆኑትን ድንጋዮች እንዲቀርጽና በቦታቸው እንዲያስቀምጥ+ እንዲሁም ከእንጨት ልዩ ልዩ ቁሳቁሶችን እንዲሠራ ነው።+ 6 በተጨማሪም ከዳን ነገድ የሆነውን የአሂሳማክን ልጅ ኤልያብን+ ረዳት እንዲሆነው መርጬዋለሁ፤ እኔ ያዘዝኩህን የሚከተሉትን ነገሮች በሙሉ እንዲሠሩ ጥሩ ችሎታ* ባላቸው ሰዎች ሁሉ ልብ ውስጥ ጥበብን አኖራለሁ፦+ 7 የመገናኛ ድንኳኑን፣+ የምሥክሩን ታቦትና+ በላዩ ላይ ያለውን መክደኛ፣+ የድንኳኑን ዕቃዎች በሙሉ፣ 8 ጠረጴዛውንና+ ዕቃዎቹን፣ ከንጹሕ ወርቅ የሚሠራውን መቅረዝና ዕቃዎቹን በሙሉ፣+ የዕጣን መሠዊያውን፣+ 9 የሚቃጠል መባ የሚቀርብበትን መሠዊያና+ ዕቃዎቹን በሙሉ፣ መታጠቢያ ገንዳውንና መቆሚያውን፣+ 10 ጥሩ ሆነው የተሸመኑትን ልብሶች፣ የካህኑን የአሮንን ቅዱስ ልብሶች፣ ወንዶች ልጆቹ ካህናት ሆነው ሲያገለግሉ የሚለብሷቸውን ልብሶች፣+ 11 የቅብዓት ዘይቱንና ለመቅደሱ የሚሆነውን ጥሩ መዓዛ ያለው ዕጣን።+ ማንኛውንም ነገር ልክ እኔ ባዘዝኩህ መሠረት ይሠሩታል።”
12 በተጨማሪም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ 13 “ለእስራኤላውያን እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ ‘እናንተን የምቀድሳችሁ እኔ ይሖዋ መሆኔን እንድታውቁ የሚያደርግ፣ በትውልዶቻችሁ ሁሉ በእኔና በእናንተ መካከል ያለ ምልክት ስለሆነ በተለይ ሰንበቴን ማክበር አለባችሁ።+ 14 ለእናንተ የተቀደሰ ስለሆነ ሰንበትን አክብሩ።+ ሰንበትን የሚያረክስ ሰው ይገደል። ማንም ሰው በዚያ ቀን ሥራ ቢሠራ ያ ሰው* ከሕዝቡ መካከል ተለይቶ እንዲጠፋ መደረግ አለበት።+ 15 ስድስት ቀን ሥራ መሥራት ይቻላል፤ ሰባተኛው ቀን ግን ሙሉ በሙሉ የሚታረፍበት ሰንበት ነው።+ ለይሖዋ የተቀደሰ ነው። በሰንበት ቀን ሥራ የሚሠራ ማንም ሰው ይገደል። 16 እስራኤላውያን ሰንበትን መጠበቅ አለባቸው፤ በትውልዶቻቸው ሁሉ ሰንበትን ማክበር አለባቸው። ይህ ዘላቂ ቃል ኪዳን ነው። 17 በእኔና በእስራኤል ሕዝብ መካከል ያለ ዘላለማዊ ምልክት ነው፤+ ምክንያቱም ይሖዋ ሰማያትንና ምድርን በስድስት ቀናት ውስጥ ሠርቶ በማጠናቀቅ ሥራውን ያቆመውና ያረፈው በሰባተኛው ቀን ነው።’”+
18 በሲና ተራራ ላይ ከእሱ ጋር ተነጋግሮ እንደጨረሰ የምሥክሩን ሁለት ጽላቶች+ ይኸውም በአምላክ ጣት+ የተጻፈባቸውን የድንጋይ ጽላቶች ለሙሴ ሰጠው።
32 በዚህ ጊዜ ሕዝቡ ሙሴ ከተራራው ላይ ሳይወርድ እንደቆየ አየ።+ በመሆኑም አሮንን ከበው እንዲህ አሉት፦ “እንግዲህ ከግብፅ ምድር መርቶ ያወጣን ያ ሙሴ ምን እንደደረሰበት ስለማናውቅ በል ተነስተህ ከፊት ከፊታችን የሚሄድ አምላክ ሥራልን።”+ 2 አሮንም “በሚስቶቻችሁ እንዲሁም በወንዶችና በሴቶች ልጆቻችሁ ጆሮዎች ላይ ያሉትን የወርቅ ጉትቻዎች+ አውልቃችሁ አምጡልኝ” አላቸው። 3 በመሆኑም ሕዝቡ ሁሉ በጆሮዎቻቸው ላይ የነበሩትን የወርቅ ጉትቻዎች እያወለቁ ወደ አሮን ያመጡ ጀመር። 4 እሱም ወርቁን ከእነሱ ወስዶ በቅርጽ ማውጫ ቅርጽ አወጣለት፤ የጥጃ ሐውልትም* አድርጎ ሠራው።+ እነሱም “እስራኤል ሆይ፣ ከግብፅ ምድር መርቶ ያወጣህ አምላክህ ይህ ነው” ይሉ ጀመር።+
5 አሮንም ይህን ሲያይ በምስሉ ፊት መሠዊያ ሠራ። ከዚያም ድምፁን ከፍ አድርጎ “ነገ ለይሖዋ የሚከበር በዓል አለ” ሲል ተናገረ። 6 በመሆኑም በማግስቱ በማለዳ ተነስተው የሚቃጠል መባና የኅብረት መሥዋዕት ያቀርቡ ጀመር። ሊበሉና ሊጠጡ ተቀመጡ። ከዚያም ሊጨፍሩ ተነሱ።+
7 በዚህ ጊዜ ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ከግብፅ ምድር መርተህ ያወጣኸው ሕዝብህ ምግባረ ብልሹ+ ስለሆነ ሂድ፣ ውረድ። 8 እንዲሄዱበት ካዘዝኳቸው መንገድ+ ፈጥነው ዞር ብለዋል። ለራሳቸውም የጥጃ ሐውልት* ሠርተዋል፤ ለእሱም እየሰገዱና መሥዋዕት እያቀረቡ ‘እስራኤል ሆይ፣ ከግብፅ ምድር መርቶ ያወጣህ አምላክህ ይህ ነው’ እያሉ ነው።” 9 ይሖዋም በመቀጠል ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ይህ ሕዝብ ግትር* መሆኑን ተመልክቻለሁ።+ 10 እንግዲህ አሁን ቁጣዬ እንዲነድባቸውና እንዳጠፋቸው ተወኝ፤ አንተን በእነሱ ምትክ ታላቅ ብሔር አደርግሃለሁ።”+
11 ሙሴም አምላኩን ይሖዋን ተማጸነ፤+ እንዲህም አለ፦ “ይሖዋ ሆይ፣ በታላቅ ኃይልና በብርቱ እጅ ከግብፅ ምድር ካወጣሃቸው በኋላ በሕዝብህ ላይ ቁጣህ የሚነደው ለምንድን ነው?+ 12 ግብፃውያንስ ‘ቀድሞውንም ቢሆን መርቶ ያወጣቸው ተንኮል አስቦ ነው። በተራሮች ላይ ሊገድላቸውና ከምድር ገጽ ሊያጠፋቸው ፈልጎ ነው’ ለምን ይበሉ?+ ከሚነደው ቁጣህ ተመለስ፤ በሕዝብህ ላይ ይህን ጥፋት ለማምጣት ያደረግከውን ውሳኔ እስቲ እንደገና አስበው።* 13 ‘ዘራችሁን በሰማያት ላይ እንዳሉት ከዋክብት አበዛዋለሁ፤+ ለዘላለም ርስት አድርጎ እንዲወርሰውም ለዘራችሁ ለመስጠት ያሰብኩትን ይህን ምድር በሙሉ እሰጠዋለሁ’+ በማለት በራስህ የማልክላቸውን አገልጋዮችህን አብርሃምን፣ ይስሐቅንና እስራኤልን አስታውስ።”
14 በመሆኑም ይሖዋ በሕዝቡ ላይ እንደሚያመጣ የተናገረውን ጥፋት እንደገና አሰበበት።*+
15 ከዚያም ሙሴ ሁለቱን የምሥክር ጽላቶች+ በእጁ እንደያዘ+ ተመልሶ ከተራራው ወረደ። ጽላቶቹም በሁለቱም በኩል ተቀርጾባቸው ነበር፤ በፊትም ሆነ በጀርባ ተጽፎባቸው ነበር። 16 ጽላቶቹ የአምላክ ሥራ ነበሩ፤ በጽላቶቹ ላይ የተቀረጸው ጽሑፍም የአምላክ ጽሑፍ ነበር።+ 17 ኢያሱም ሕዝቡ ይጮኽ ስለነበር ጫጫታውን ሲሰማ ሙሴን “በሰፈሩ ውስጥ የጦርነት ሁካታ ይሰማል” አለው። 18 ሙሴ ግን እንዲህ አለው፦
“ይህ ድምፅ የድል መዝሙር አይደለም፤
ይህ ድምፅ በሽንፈት ምክንያት የሚሰማ የለቅሶ ድምፅም አይደለም፤
ይህ የምሰማው ድምፅ የተለየ መዝሙር ድምፅ ነው።”
19 ሙሴም ወደ ሰፈሩ ሲቃረብ ጥጃውንና+ ጭፈራውን አየ፤ በዚህ ጊዜ ቁጣው ነደደ። ጽላቶቹንም ከእጁ ወርውሮ በተራራው ግርጌ ሰባበራቸው።+ 20 የሠሩትንም ጥጃ ወስዶ በእሳት አቃጠለው፤ ሰባብሮም ዱቄት አደረገው፤+ ከዚያም በውኃው ላይ በመበተን እስራኤላውያን እንዲጠጡት አደረገ።+ 21 ሙሴም አሮንን “ይህን ከባድ ኃጢአት ያመጣህበት ይህ ሕዝብ ምን ቢያደርግህ ነው?” አለው። 22 በዚህ ጊዜ አሮን እንዲህ አለ፦ “ጌታዬ አትቆጣ። መቼም ይህ ሕዝብ ወደ ክፋት ያዘነበለ እንደሆነ አንተ ራስህ በሚገባ ታውቃለህ።+ 23 ስለዚህ ‘ከግብፅ ምድር መርቶ ያወጣን ያ ሙሴ ምን እንደደረሰበት ስለማናውቅ ከፊት ከፊታችን የሚሄድ አምላክ ሥራልን’ አሉኝ።+ 24 በመሆኑም ‘ወርቅ ያለው ሁሉ አውልቆ ይስጠኝ’ አልኳቸው። ከዚያም ወርቁን እሳቱ ውስጥ ጣልኩት፤ ይህም ጥጃ ወጣ።”
25 በተቃዋሚዎቻቸው ፊት መሳለቂያ እንዲሆኑ አሮን ሕዝቡን መረን ስለለቀቃቸው ሙሴ ሕዝቡ መረን እንደተለቀቀ አስተዋለ። 26 ከዚያም ሙሴ በሰፈሩ መግቢያ ላይ ቆሞ “ከይሖዋ ጎን የሚቆም ማን ነው? ወደ እኔ ይምጣ!”+ አለ። በዚህ ጊዜ ሌዋውያን በሙሉ በዙሪያው ተሰበሰቡ። 27 እሱም እንዲህ አላቸው፦ “የእስራኤል አምላክ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘እያንዳንዳችሁ ሰይፋችሁን ታጠቁ፤ ከአንዱ በር ወደ ሌላው በር በመሄድና በሰፈሩ ውስጥ በማለፍ እያንዳንዱ ሰው ወንድሙን፣ ጎረቤቱንና የቅርብ ጓደኛውን ይግደል።’”+ 28 ሌዋውያኑም ሙሴ እንዳላቸው አደረጉ። በመሆኑም በዚያ ዕለት 3,000 ገደማ የሚሆኑ ወንዶች ተገደሉ። 29 ከዚያም ሙሴ እንዲህ አለ፦ “እያንዳንዳችሁ በገዛ ልጃችሁና በገዛ ወንድማችሁ ላይ ስለተነሳችሁ+ ዛሬ ራሳችሁን ለይሖዋ ለዩ፤* እሱም ዛሬ በረከትን ያፈስላችኋል።”+
30 በማግስቱም ሙሴ ሕዝቡን እንዲህ አላቸው፦ “ከባድ ኃጢአት ሠርታችኋል፤ እንግዲህ አሁን ኃጢአታችሁን ይቅር እንዲላችሁ አንድ ነገር ማድረግ እችል እንደሆነ ለማየት ወደ ይሖዋ እወጣለሁ።”+ 31 በመሆኑም ሙሴ ወደ ይሖዋ ተመልሶ እንዲህ አለ፦ “ይህ ሕዝብ የፈጸመው ኃጢአት ምንኛ ከባድ ነው! የወርቅ አምላክ ሠርተዋል።+ 32 ሆኖም አሁን ፈቃድህ ከሆነ ኃጢአታቸውን ይቅር በል፤+ ካልሆነ ግን እባክህ እኔን ከጻፍከው መጽሐፍህ ላይ ደምስሰኝ።”+ 33 ይሁንና ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ “በእኔ ላይ ኃጢአት የሠራውን ሁሉ ከመጽሐፌ ላይ እደመስሰዋለሁ። 34 በል አሁን ሄደህ ሕዝቡን ወደነገርኩህ ስፍራ እየመራህ ውሰዳቸው። እነሆ መልአኬ ከፊት ከፊትህ ይሄዳል፤+ ሕዝቡን በምመረምርበትም ቀን ስለሠሩት ኃጢአት ቅጣት አመጣባቸዋለሁ።” 35 ከዚያም ይሖዋ፣ በሠሩት ጥጃ ይኸውም አሮን በሠራላቸው ጥጃ ምክንያት ሕዝቡን በመቅሰፍት መታ።
33 በተጨማሪም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ከግብፅ መርተህ ካወጣኸው ሕዝብ ጋር ከዚህ ተነስተህ ሂድ። ‘ለዘርህ እሰጠዋለሁ’ በማለት ለአብርሃም፣ ለይስሐቅና ለያዕቆብ ወደማልኩላቸውም ምድር ተጓዝ።+ 2 እኔም ከአንተ አስቀድሜ መልአክ በመላክ+ ከነአናውያንን፣ አሞራውያንን፣ ሂታውያንን፣ ፈሪዛውያንን፣ ሂዋውያንንና ኢያቡሳውያንን አስወጣለሁ።+ 3 ወተትና ማር ወደምታፈሰው ምድር+ ሂዱ። ሆኖም እናንተ ግትር* ሕዝብ ስለሆናችሁ+ በመንገድ ላይ እንዳላጠፋችሁ+ በመካከላችሁ ሆኜ አብሬያችሁ አልሄድም።”
4 ሕዝቡም ይህን ኃይለኛ ንግግር ሲሰሙ በሐዘን ተዋጡ፤ ከመካከላቸውም ማንም ጌጡን አላደረገም። 5 ይሖዋም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “እስራኤላውያንን እንዲህ በላቸው፦ ‘እናንተ ግትር* ሕዝብ ናችሁ።+ ለአንድ አፍታ በመካከላችሁ አልፌ ላጠፋችሁ እችል ነበር።+ በእናንተ ላይ ምን ማድረግ እንዳለብኝ እስክወስን ድረስ ጌጣጌጣችሁን አውልቁ።’” 6 ስለዚህ እስራኤላውያን ከኮሬብ ተራራ አንስቶ ጌጣጌጣቸውን ማድረግ ተዉ።
7 ሙሴም የራሱን ድንኳን ወስዶ ከሰፈሩ ውጭ ማለትም ከሰፈሩ ትንሽ ራቅ አድርጎ ተከለው፤ ድንኳኑንም የመገናኛ ድንኳን ብሎ ጠራው። ይሖዋን የሚጠይቅ+ ማንኛውም ሰው ከሰፈሩ ውጭ ወዳለው የመገናኛ ድንኳን ይሄድ ነበር። 8 ሙሴ ወደ ድንኳኑ ሲሄድ ሕዝቡ በሙሉ ተነስተው በየድንኳናቸው መግቢያ ላይ በመቆም ሙሴ ወደ ድንኳኑ እስኪገባ ድረስ ትክ ብለው ይመለከቱት ነበር። 9 ሙሴ ወደ ድንኳኑ ገብቶ አምላክ ከሙሴ ጋር በሚነጋገርበት+ ጊዜ የደመናው ዓምድ+ ወርዶ በድንኳኑ መግቢያ ላይ ይቆማል። 10 ሕዝቡም ሁሉ የደመናው ዓምድ በድንኳኑ መግቢያ ላይ ቆሞ ሲመለከት እያንዳንዳቸው ተነስተው በየድንኳናቸው መግቢያ ላይ ይሰግዱ ነበር። 11 አንድ ሰው ከሌላ ሰው ጋር እንደሚነጋገር ይሖዋ ከሙሴ ጋር ፊት ለፊት ይነጋገር ነበር።+ ሙሴ ወደ ሰፈሩ በሚመለስበት ጊዜ አገልጋዩና ረዳቱ+ የነበረው የነዌ ልጅ ኢያሱ+ ከድንኳኑ አይለይም ነበር።
12 ሙሴም ይሖዋን እንዲህ አለው፦ “እንግዲህ ‘ይህን ሕዝብ ምራ’ እያልከኝ ነው፤ ሆኖም ከእኔ ጋር ማንን እንደምትልክ አላሳወቅከኝም። ከዚህም በላይ ‘በስም አውቄሃለሁ፤* ደግሞም በፊቴ ሞገስ አግኝተሃል’ ብለኸኝ ነበር። 13 እባክህ በፊትህ ሞገስ አግኝቼ ከሆነ እንዳውቅህና በፊትህ ሞገስ አግኝቼ እንድኖር መንገድህን አሳውቀኝ።+ እንዲሁም ይህ ብሔር ሕዝብህ እንደሆነ አስብ።”+ 14 በመሆኑም እሱ “እኔ ራሴ ከአንተ ጋር እሄዳለሁ፤*+ እረፍትም እሰጥሃለሁ” አለው።+ 15 ከዚያም ሙሴ እንዲህ አለው፦ “አንተ ራስህ ከእኛ ጋር የማትሄድ* ከሆነ ይህን ቦታ ለቅቀን እንድንሄድ አታድርገን። 16 ታዲያ እኔም ሆንኩ ሕዝብህ በፊትህ ሞገስ እንዳገኘን የሚታወቀው እንዴት ነው? እኔም ሆንኩ ሕዝብህ በምድር ላይ ካሉ ሌሎች ሕዝቦች ሁሉ የተለየን እንድንሆን+ ስትል አብረኸን በመሄድህ አይደለም?”+
17 ይሖዋም ሙሴን “በፊቴ ሞገስ ስላገኘህና በስም ስላወቅኩህ የጠየቅከውን ይህን ነገር እፈጽማለሁ” አለው። 18 እሱም በዚህ ጊዜ “እባክህ ክብርህን አሳየኝ” አለው። 19 ሆኖም እሱ እንዲህ አለው፦ “እኔ ራሴ ጥሩነቴ ሁሉ በፊትህ እንዲያልፍ አደርጋለሁ፤ ይሖዋ የተባለውንም ስሜን በፊትህ አውጃለሁ።+ ሞገስ ላሳየው የምፈልገውን ሞገስ አሳየዋለሁ፤ ልምረው የምፈልገውን ደግሞ እምረዋለሁ።”+ 20 ሆኖም “ማንም ሰው አይቶኝ በሕይወት መኖር ስለማይችል ፊቴን ማየት አትችልም” አለው።
21 በተጨማሪም ይሖዋ እንዲህ አለው፦ “ይኸው አጠገቤ ቦታ አለ። አንተም በዓለቱ ላይ ቁም። 22 ክብሬ በዚያ በሚያልፍበትም ጊዜ በዓለቱ ዋሻ ውስጥ አስቀምጥሃለሁ፤ እስከማልፍም ድረስ በእጄ እጋርድሃለሁ። 23 ከዚያም እጄን አነሳለሁ፤ አንተም ጀርባዬን ታያለህ። ፊቴ ግን አይታይም።”+
34 ከዚያም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ “እንደ መጀመሪያዎቹ ያሉ ሁለት የድንጋይ ጽላቶችን ጥረብ፤+ እኔም በጽላቶቹ ላይ አንተ በሰበርካቸው+ በመጀመሪያዎቹ ጽላቶች ላይ የነበሩትን ቃላት እጽፍባቸዋለሁ።+ 2 አንተም በጠዋት ወደ ሲና ተራራ ወጥተህ በዚያ በተራራው አናት ላይ በፊቴ ስለምትቆም በጠዋት ለመሄድ ተዘጋጅ።+ 3 ሆኖም ከአንተ ጋር ማንም ሰው አይውጣ፤ ደግሞም በተራራው ላይ በየትኛውም ቦታ ሌላ ማንም ሰው አይታይ። ሌላው ቀርቶ በጎችም ሆኑ ከብቶች እንኳ በተራራው ፊት ለፊት አይሰማሩ።”+
4 በመሆኑም ሙሴ ልክ ይሖዋ ባዘዘው መሠረት የመጀመሪያዎቹን የሚመስሉ ሁለት የድንጋይ ጽላቶችን ከጠረበ በኋላ በጠዋት ተነስቶ ወደ ሲና ተራራ ወጣ፤ ሁለቱንም የድንጋይ ጽላቶች በእጁ ይዞ ነበር። 5 ከዚያም ይሖዋ በደመና ውስጥ ወርዶ+ በዚያ ከእሱ ጋር ሆነ፤ ይሖዋ የተባለውንም ስሙን አወጀ።+ 6 ይሖዋም በፊቱ እያለፈ እንዲህ ሲል አወጀ፦ “ይሖዋ፣ ይሖዋ፣ መሐሪና+ ሩኅሩኅ*+ የሆነ አምላክ፣ ለቁጣ የዘገየ፣+ ታማኝ ፍቅሩና*+ እውነቱ*+ እጅግ ብዙ የሆነ፣ 7 ታማኝ ፍቅርን ለሺዎች የሚያሳይ፣+ ስህተትን፣ መተላለፍንና ኃጢአትን ይቅር የሚል፣+ ጥፋተኛውን ግን በምንም ዓይነት ሳይቀጣ የማያልፍ+ እንዲሁም አባቶች ለሠሩት ስህተት በልጆች፣ በልጅ ልጆች፣ በሦስተኛና በአራተኛ ትውልድ ላይ ቅጣትን የሚያመጣ።”+
8 ሙሴም ወዲያውኑ መሬት ላይ ተደፍቶ ሰገደ። 9 ከዚያም እንዲህ አለ፦ “ይሖዋ ሆይ፣ በፊትህ ሞገስ አግኝቼ ከሆነ እባክህ ይሖዋ፣ እኛ ግትር* ሕዝብ ብንሆንም+ በመካከላችን ሆነህ አብረኸን ሂድ፤+ ደግሞም ስህተታችንንና ኃጢአታችንን ይቅር በል፤+ እንደ ርስትህም አድርገህ ውሰደን።” 10 እሱም መልሶ እንዲህ አለው፦ “እንግዲህ እኔ ከእናንተ ጋር ቃል ኪዳን እገባለሁ፦ በመላው ምድርም ሆነ በብሔራት ሁሉ መካከል ፈጽሞ ተደርገው* የማያውቁ ድንቅ ነገሮችን በሕዝብህ ሁሉ ፊት አደርጋለሁ፤+ ለአንተ ስል የማደርገው ነገር የሚያስፈራ ስለሆነ በመካከላቸው የምትኖረው ሕዝቦች ሁሉ የይሖዋን ሥራ ያያሉ።+
11 “እኔ ዛሬ የማዝህን ነገር ልብ በል።+ እኔም አሞራውያንን፣ ከነአናውያንን፣ ሂታውያንን፣ ፈሪዛውያንን፣ ሂዋውያንንና ኢያቡሳውያንን ከፊትህ አስወጣቸዋለሁ።+ 12 በምትሄድበት ምድር ከሚኖሩ ሰዎች ጋር ቃል ኪዳን እንዳትጋባ ተጠንቀቅ፤+ አለዚያ ወጥመድ ይሆንብሃል።+ 13 ከዚህ ይልቅ መሠዊያዎቻቸውን ታፈራርሳላችሁ፤ የማምለኪያ ዓምዶቻቸውን ትሰባብራላችሁ፤ እንዲሁም የማምለኪያ ግንዶቻቸውን* ትቆራርጣላችሁ።+ 14 ይሖዋ፣ እሱ ብቻ እንዲመለክ የሚፈልግ* አምላክ በመሆኑ የሚታወቅ ስለሆነ ለሌላ አምላክ አትስገድ።+ አዎ፣ እሱ ብቻ እንዲመለክ የሚፈልግ አምላክ ነው።+ 15 ከምድሪቱ ነዋሪዎች ጋር ቃል ኪዳን እንዳትጋባ ተጠንቀቅ፤ ምክንያቱም እነሱ አማልክታቸውን በማምለክ ምንዝር በሚፈጽሙበትና ለአማልክታቸው በሚሠዉበት+ ጊዜ ከመካከላቸው አንዱ አንተን መጋበዙ አይቀርም፣ አንተም ካቀረበው መሥዋዕት ትበላለህ።+ 16 ከዚያም ሴቶች ልጆቻቸውን ከወንዶች ልጆችህ ጋር ታጋባለህ፤+ ሴቶች ልጆቻቸውም አማልክታቸውን በማምለክ ምንዝር መፈጸማቸው እንዲሁም ወንዶች ልጆችህ የእነሱን አማልክት በማምለክ ምንዝር እንዲፈጽሙ ማድረጋቸው አይቀርም።+
17 “ከቀለጠ ብረት አማልክት አትሥራ።+
18 “የቂጣን በዓል ታከብራለህ።+ ልክ ባዘዝኩህ መሠረት ቂጣ ትበላለህ፤ ከግብፅ የወጣኸው በአቢብ* ወር+ ስለሆነ በአቢብ ወር በተወሰነው ጊዜ ላይ ለሰባት ቀን ይህን ታደርጋለህ።
19 “በኩር የሆነ ወንድ ሁሉ* የእኔ ነው፤+ ደግሞም የመንጋህ በኩር ሁሉ፣ በኩር የሆነ በሬም ሆነ ተባዕት በግ የእኔ ነው።+ 20 የአህያን በኩር በበግ ዋጀው። የማትዋጀው ከሆነ ግን አንገቱን ስበረው። ከወንዶች ልጆችህ መካከል በኩር የሆነውን ሁሉ ትዋጀዋለህ።+ ማንም ባዶ እጁን ፊቴ አይቅረብ።
21 “ስድስት ቀን ትሠራለህ፤ በሰባተኛው ቀን ግን ታርፋለህ።*+ በሚታረስበትም ሆነ አዝመራ በሚሰበሰብበት ወቅትም እንኳ ታርፋለህ።
22 “የሳምንታት በዓልህን መጀመሪያ በደረሰው የስንዴ በኩር አክብር፤ የአዝመራ መክተቻን በዓልም* በዓመቱ ማብቂያ ላይ አክብር።+
23 “የአንተ የሆነ ሰው* ሁሉ በዓመት ሦስት ጊዜ የእስራኤል አምላክ በሆነው በእውነተኛው ጌታ በይሖዋ ፊት ይቅረብ።+ 24 ብሔራትን ከፊትህ አስወጣለሁና፤+ ክልልህንም ሰፊ አደርገዋለሁ፤ የአምላክህን የይሖዋን ፊት ለማየት በዓመት ሦስቴ በምትወጣበት ጊዜ ማንም ምድርህን አይመኝም።
25 “የመሥዋዕቴን ደም እርሾ ከገባበት ከማንኛውም ነገር ጋር አድርገህ አታቅርብ።+ የፋሲካ በዓል መሥዋዕት እስከ ጠዋት ድረስ መቆየት የለበትም።+
26 “መጀመሪያ የደረሰውን የአፈርህን ምርጥ ፍሬ ወደ አምላክህ ወደ ይሖዋ ቤት አምጣ።+
“የፍየልን ጠቦት በእናቱ ወተት አትቀቅል።”+
27 ከዚያም ይሖዋ ሙሴን “ከአንተም ሆነ ከእስራኤል ጋር ቃል ኪዳን የምገባው+ በእነዚህ ቃላት መሠረት ስለሆነ እነዚህን ቃላት ጻፍ”+ አለው። 28 እሱም በዚያ ከይሖዋ ጋር 40 ቀንና 40 ሌሊት ቆየ። እህል አልቀመሰም፤ ውኃም አልጠጣም።+ እሱም* በጽላቶቹ ላይ የቃል ኪዳኑን ቃላት ይኸውም አሥርቱን ትእዛዛት* ጻፈ።+
29 ከዚያም ሙሴ ከሲና ተራራ ወረደ፤ ሁለቱንም የምሥክር ጽላቶች በእጁ ይዞ ነበር።+ ከአምላክ ጋር ሲነጋገር ስለቆየ ከተራራው በወረደበት ጊዜ ፊቱ እንደሚያንጸባርቅ አላወቀም ነበር። 30 አሮንና እስራኤላውያን ሁሉ ሙሴን ሲያዩት ፊቱ እንደሚያንጸባርቅ አስተዋሉ፤ ወደ እሱ ለመቅረብም ፈሩ።+
31 ሙሴ ግን ጠራቸው፤ በመሆኑም አሮንና የማኅበረሰቡ አለቆች በሙሉ ወደ እሱ መጡ፤ ሙሴም አነጋገራቸው። 32 ከዚያም እስራኤላውያን በሙሉ ወደ እሱ ቀረቡ፤ እሱም ይሖዋ በሲና ተራራ ላይ የሰጠውን ትእዛዝ ሁሉ ሰጣቸው።+ 33 ሙሴም ከእነሱ ጋር ተነጋግሮ ሲጨርስ ፊቱን በመሸፈኛ ይሸፍን ነበር።+ 34 ሙሴ፣ ይሖዋ ፊት ቀርቦ ከእሱ ጋር ለመነጋገር ወደ ውስጥ በሚገባበት ጊዜ ግን ከዚያ እስከሚወጣበት ጊዜ ድረስ መሸፈኛውን ያነሳ ነበር።+ ከዚያም ወጥቶ የተቀበለውን ትእዛዝ ለእስራኤላውያን ይነግራቸው ነበር።+ 35 እስራኤላውያንም የሙሴ ፊት እንደሚያንጸባርቅ ተመለከቱ፤ ከዚያም ሙሴ አምላክን* ለማነጋገር ወደ ውስጥ እስከሚገባበት ጊዜ ድረስ መሸፈኛውን መልሶ ፊቱ ላይ አደረገው።+
35 በኋላም ሙሴ የእስራኤልን ማኅበረሰብ ሁሉ አንድ ላይ ሰብስቦ እንዲህ አላቸው፦ “ይሖዋ እንድትፈጽሟቸው ያዘዛችሁ ነገሮች እነዚህ ናቸው፦+ 2 ስድስት ቀን ሥራ ይሠራል፤ ሰባተኛው ቀን ግን ለእናንተ የተቀደሰ ይሆናል፤ ለይሖዋም ሙሉ በሙሉ የሚታረፍበት ሰንበት ይሆናል።+ በዚህ ቀን ሥራ የሚሠራ ማንም ሰው ይገደላል።+ 3 በምትኖሩበት በየትኛውም ቦታ በሰንበት ቀን እሳት አታቀጣጥሉ።”
4 ከዚያም ሙሴ ለእስራኤል ማኅበረሰብ ሁሉ እንዲህ አለ፦ “ይሖዋ እንዲህ ሲል አዟል፦ 5 ‘ካላችሁ ነገር ለይሖዋ መዋጮ አምጡ።+ ልቡ ያነሳሳው+ ማንኛውም ሰው የሚከተሉትን ነገሮች ለይሖዋ መዋጮ አድርጎ ያምጣ፦ ወርቅ፣ ብር፣ መዳብ፣ 6 ሰማያዊ ክር፣ ሐምራዊ ሱፍ፣ ደማቅ ቀይ ማግ፣ ጥሩ በፍታ፣ የፍየል ፀጉር፣+ 7 ቀይ ቀለም የተነከረ የአውራ በግ ቆዳ፣ የአቆስጣ ቆዳ፣ የግራር እንጨት፣ 8 ለመብራት የሚሆን ዘይት፣ ለቅብዓት ዘይትና ጥሩ መዓዛ ላለው ዕጣን የሚሆን የበለሳን ዘይት፣+ 9 በኤፉዱና በደረት ኪሱ+ ላይ የሚቀመጡ የኦኒክስ ድንጋዮችና+ ሌሎች ድንጋዮች።
10 “‘በመካከላችሁ ያሉ ጥሩ ችሎታ* ያላቸው+ ሰዎች ሁሉ መጥተው ይሖዋ ያዘዘውን ነገር ሁሉ ይሥሩ፤ 11 እነዚህም የማደሪያ ድንኳኑ ከተለያየ ቁሳቁሱና ከመደረቢያው ጋር፣ ማያያዣዎቹ፣ አራት ማዕዘን ቋሚዎቹ፣ አግዳሚ እንጨቶቹ፣ ዓምዶቹ፣ መሰኪያዎቹ፣ 12 ታቦቱና+ መሎጊያዎቹ፣+ መክደኛው፣+ ለመከለያ የሚሆነው መጋረጃ፣+ 13 ጠረጴዛው+ እንዲሁም መሎጊያዎቹና ዕቃዎቹ በሙሉ፣ ገጸ ኅብስቱ፣+ 14 የመብራት መቅረዙና+ ዕቃዎቹ፣ መብራቶቹ፣ ለመብራቱ የሚሆነው ዘይት፣+ 15 የዕጣን መሠዊያውና+ መሎጊያዎቹ፣ የቅብዓት ዘይቱና ጥሩ መዓዛ ያለው ዕጣን፣+ ለማደሪያ ድንኳኑ መግቢያ የሚሆነው መከለያ፣* 16 የሚቃጠል መባ የሚቀርብበት መሠዊያ+ እንዲሁም የመዳብ ፍርግርጉ፣ መሎጊያዎቹና ዕቃዎቹ በሙሉ፣ ገንዳውና ማስቀመጫው፣+ 17 የግቢው መጋረጃ+ እንዲሁም ቋሚዎቹና መሰኪያዎቹ፣ ለግቢው መግቢያ የሚሆነው መከለያ፣* 18 የማደሪያ ድንኳኑ ካስማዎችና የግቢው ካስማዎች እንዲሁም ገመዶቻቸው፣+ 19 በመቅደሱ ለማገልገል የሚለበሱት በጥሩ ሁኔታ የተሸመኑት ልብሶች፣+ የካህኑ የአሮን ቅዱስ ልብሶች+ እንዲሁም ወንዶች ልጆቹ ካህናት ሆነው ሲያገለግሉ የሚለብሷቸው ልብሶች ናቸው።’”
20 ከዚያም የእስራኤል ማኅበረሰብ በሙሉ ከሙሴ ፊት ሄደ። 21 ከዚያም ልባቸው የገፋፋቸውና+ መንፈሳቸው ያነሳሳቸው ሁሉ መጥተው ለመገናኛ ድንኳኑ ሥራና በዚያ ለሚከናወነው ማንኛውም አገልግሎት እንዲሁም ለቅዱሶቹ ልብሶች እንዲሆን መዋጮአቸውን ለይሖዋ አመጡ። 22 ፈቃደኛ ልብ ያላቸው ሁሉ፣ ወንዶችም ሆኑ ሴቶች የደረት ጌጥ፣ የጆሮ ጌጥ፣ ቀለበትና ሌላ ጌጣጌጥ እንዲሁም ሁሉንም ዓይነት ከወርቅ የተሠራ ጌጣጌጥ ይዘው ይመጡ ነበር። ሁሉም የወርቅ መባዎቻቸውን* ለይሖዋ አቀረቡ።+ 23 ደግሞም ሰማያዊ ክር፣ ሐምራዊ ሱፍ፣ ደማቅ ቀይ ማግ፣ ጥሩ በፍታ፣ የፍየል ፀጉር፣ ቀይ ቀለም የተነከረ የአውራ በግ ቆዳ እንዲሁም የአቆስጣ ቆዳ ያላቸው ሁሉ እነዚህን አመጡ። 24 ብርና መዳብ የሚያዋጡ ሁሉ ለይሖዋ የሚሆነውን መዋጮ አመጡ፤ ለመገናኛው ድንኳን ሥራ የሚውል የግራር እንጨት ያላቸውም ሁሉ ይህን አመጡ።
25 ጥሩ ችሎታ ያላቸው ሴቶችም+ ሁሉ በእጃቸው ይፈትሉ ነበር፤ እነሱም የሚከተሉትን ነገሮች ፈትለው አመጡ፦ ሰማያዊ ክር፣ ሐምራዊ ሱፍ፣ ደማቅ ቀይ ማግ እንዲሁም ጥሩ በፍታ። 26 ጥሩ ችሎታ ያላቸው ልባቸው ያነሳሳቸው ሴቶች ሁሉ የፍየል ፀጉሩን ይፈትሉ ነበር።
27 አለቆቹም በኤፉዱና በደረት ኪሱ+ ላይ የሚቀመጡ የኦኒክስ ድንጋዮችንና ሌሎች ድንጋዮችን፣ 28 የበለሳን ዘይቱን እንዲሁም ለመብራት፣ ለቅብዓት ዘይቱና+ ጥሩ መዓዛ ላለው ዕጣን+ የሚሆነውን ዘይት አመጡ። 29 ልባቸው ያነሳሳቸው ወንዶችና ሴቶች በሙሉ ይሖዋ በሙሴ አማካኝነት እንዲከናወን ላዘዘው ሥራ የሚውሉ ነገሮችን አመጡ፤ እስራኤላውያኑ ይህን በፈቃደኝነት የሚቀርብ መባ አድርገው ለይሖዋ አመጡ።+
30 ከዚያም ሙሴ እስራኤላውያንን እንዲህ አላቸው፦ “እንደምታዩት ይሖዋ ከይሁዳ ነገድ የሆነው የሁር ልጅ ዖሪ+ የወለደውን ባስልኤልን መርጦታል። 31 ደግሞም በማንኛውም ዓይነት የእጅ ሙያ ማስተዋል፣ ጥበብና እውቀት በመስጠት በአምላክ መንፈስ ሞልቶታል። 32 ይኸውም የተለያዩ ንድፎችን እንዲያወጣ እንዲሁም በወርቅ፣ በብርና በመዳብ የተለያዩ ነገሮችን እንዲሠራ፣ 33 ፈርጥ የሚሆኑትን ድንጋዮች እንዲቀርጽና በቦታቸው እንዲያስቀምጥ እንዲሁም ድንቅ የሆኑ ልዩ ልዩ የእንጨት ቁሳቁሶችን እንዲሠራ ነው። 34 አምላክም ለእሱና ከዳን ነገድ ለሆነው ለአሂሳማክ ልጅ ለኤልያብ+ ሌሎችን የማስተማር ችሎታ ሰጥቷቸዋል። 35 የእጅ ጥበብ ባለሙያ፣ የጥልፍ ባለሙያ እንዲሁም በሰማያዊ ክር፣ በሐምራዊ ሱፍ፣ በደማቅ ቀይ ማግና በጥሩ በፍታ የሚሸምን የጥበብ ባለሙያ ብሎም የሽመና ባለሙያ የሚያከናውኗቸውን ሥራዎች በሙሉ እንዲሠሩ ጥሩ ችሎታ* ሰጥቷቸዋል።+ እነዚህ ሰዎች ሁሉንም ዓይነት ሥራዎች የሚሠሩና ሁሉንም ዓይነት ንድፎች የሚያወጡ ነበሩ።
36 “ባስልኤል ከኤልያብና ጥሩ ችሎታ* ካላቸው ወንዶች ሁሉ ጋር ይሠራል፤ እነዚህ ወንዶች ቅዱስ ከሆነው አገልግሎት ጋር የተያያዘው ሥራ በሙሉ ልክ ይሖዋ ባዘዘው መሠረት እንዴት እንደሚከናወን ማወቅ ይችሉ ዘንድ ይሖዋ ጥበብና ማስተዋል የሰጣቸው ናቸው።”+
2 ከዚያም ሙሴ ባስልኤልንና ኤልያብን እንዲሁም ይሖዋ በልባቸው ጥበብን ያኖረላቸውን ጥሩ ችሎታ ያላቸውን ወንዶች+ ሁሉ ይኸውም ሥራውን ለመሥራት በፈቃደኝነት ራሳቸውን እንዲያቀርቡ ልባቸው ያነሳሳቸውን+ ሁሉ ጠራ። 3 እነሱም እስራኤላውያን ለቅዱሱ አገልግሎት ሥራ ያመጡትን መዋጮ+ በሙሉ ከሙሴ ወሰዱ። ሕዝቡ ግን በየማለዳው የፈቃደኝነት መባ ወደ እሱ ያመጣ ነበር።
4 ቅዱሱን ሥራ ከጀመሩም በኋላ ጥሩ ችሎታ ያላቸው ሠራተኞች ሁሉ አንድ በአንድ ይመጡ ነበር፤ 5 ሙሴንም “ሕዝቡ፣ ይሖዋ እንዲሠራ ላዘዘው ሥራ ከሚፈለገው በላይ እያመጣ ነው” አሉት። 6 ስለዚህ ሙሴ በሰፈሩ ሁሉ እንዲህ የሚል ማስታወቂያ እንዲነገር አዘዘ፦ “ወንዶችም ሆናችሁ ሴቶች፣ ከእንግዲህ ለቅዱሱ መዋጮ የሚሆን ተጨማሪ ነገር አታምጡ።” በመሆኑም ሕዝቡ ምንም ነገር ከማምጣት ተገታ። 7 የመጣውም ነገር ሥራውን ሁሉ ለማከናወን በቂ፣ እንዲያውም ከበቂ በላይ ነበር።
8 ጥሩ ችሎታ ያላቸውም ሰዎች+ ሁሉ በቀጭኑ ከተፈተለ ጥሩ የበፍታ ድር፣ ከሰማያዊ ክር፣ ከሐምራዊ ሱፍና ከደማቅ ቀይ ማግ ከተሠሩ አሥር የድንኳን ጨርቆች የማደሪያ ድንኳኑን ሠሩ፤+ እሱም* በጨርቆቹ ላይ ኪሩቦችን ጠለፈባቸው።+ 9 የእያንዳንዱ የድንኳን ጨርቅ ርዝመት 28 ክንድ* ወርዱ ደግሞ 4 ክንድ ነበር። ሁሉም የድንኳን ጨርቆች መጠናቸው እኩል ነበር። 10 ከዚያም አምስቱን የድንኳን ጨርቆች አንድ ላይ ቀጣጠላቸው፤ ሌሎቹን አምስት የድንኳን ጨርቆችም እንዲሁ አንድ ላይ ቀጣጠላቸው። 11 ከዚህ በኋላ አንደኛው የድንኳን ጨርቅ ከሌላኛው ጋር በሚጋጠምበት ጠርዝ ላይ ከሰማያዊ ክር ማቆላለፊያዎችን ሠራ። ሌላኛው የድንኳን ጨርቅ ከዚህኛው ጋር በሚጋጠምበት በመጨረሻው የድንኳን ጨርቅ ጠርዝ ላይም እንዲሁ አደረገ። 12 በአንደኛው የድንኳን ጨርቅ ላይ 50 ማቆላለፊያዎችን ሠራ፤ ማቆላለፊያዎቹም ትይዩ እንዲሆኑ ሌላኛው የድንኳን ጨርቅ ከዚህኛው ጋር በሚጋጠምበት የድንኳኑ ጨርቅ ጠርዝ ላይ 50 ማቆላለፊያዎችን ሠራ። 13 በመጨረሻም 50 የወርቅ ማያያዣዎችን ሠርቶ የድንኳኑን ጨርቆች በማያያዣዎቹ አማካኝነት እርስ በርስ አጋጠማቸው፤ በዚህም መንገድ የማደሪያ ድንኳኑ አንድ ወጥ ሆነ።
14 ከዚያም ለማደሪያ ድንኳኑ ልባስ የሚሆኑ የድንኳን ጨርቆችን ከፍየል ፀጉር ሠራ። አሥራ አንድ የድንኳን ጨርቆችን ሠራ።+ 15 የእያንዳንዱ የድንኳን ጨርቅ ርዝመት 30 ክንድ ወርዱ ደግሞ 4 ክንድ ነበር። አሥራ አንዱም የድንኳን ጨርቆች መጠናቸው እኩል ነበር። 16 ከዚያም አምስቱን የድንኳን ጨርቆች አንድ ላይ፣ ሌሎቹን ስድስት የድንኳን ጨርቆች ደግሞ አንድ ላይ ቀጣጠላቸው። 17 በመቀጠልም አንደኛው የድንኳን ጨርቅ ከሌላኛው ጋር በሚጋጠምበት በመጨረሻው የድንኳን ጨርቅ ጠርዝ ላይ 50 ማቆላለፊያዎችን ሠራ፤ እንዲሁም ከዚህኛው ጋር በሚጋጠመው በሌላኛው የድንኳን ጨርቅ ጠርዝ ላይ 50 ማቆላለፊያዎችን ሠራ። 18 ከዚያም ድንኳኑን በማያያዝ አንድ ወጥ እንዲሆን ለማድረግ 50 የመዳብ ማያያዣዎችን ሠራ።
19 እሱም ቀይ ቀለም ከተነከረ የአውራ በግ ቆዳ ለድንኳኑ መደረቢያ ሠራ፤ እንዲሁም ከአቆስጣ ቆዳ በላዩ ላይ የሚደረብ መደረቢያ ሠራ።+
20 ከዚያም የግራር እንጨት+ ጣውላዎችን በማገጣጠም የማደሪያ ድንኳኑን ቋሚዎች ሠራ።+ 21 እያንዳንዱ ቋሚ ቁመቱ አሥር ክንድ ወርዱ ደግሞ አንድ ክንድ ተኩል ነበር። 22 እያንዳንዱ ቋሚም እርስ በርስ የተያያዙ ሁለት ጉጦች ነበሩት። ሁሉንም የማደሪያ ድንኳኑን ቋሚዎች የሠራው በዚህ መንገድ ነበር። 23 በመሆኑም በስተ ደቡብ በኩል ለሚገኘው፣ ፊቱ በደቡብ አቅጣጫ ላለው የማደሪያ ድንኳኑ ጎን ቋሚዎችን ይኸውም 20 ቋሚዎችን ሠራ። 24 ከዚያም በ20ዎቹ ቋሚዎች ሥር የሚሆኑ 40 የብር መሰኪያዎችን ሠራ፤ በአንዱ ቋሚ ሥር ላሉት ሁለት ጉጦች የሚሆኑ ሁለት መሰኪያዎችን፣ ቀጥሎ ባለው በእያንዳንዱም ቋሚ ሥር ላሉት ሁለት ጉጦች የሚሆኑ ሁለት መሰኪያዎችን አደረገ።+ 25 በስተ ሰሜን በኩል ላለው ለሌላኛውም የማደሪያ ድንኳኑ ጎን 20 ቋሚዎችን ሠራ፤ 26 እንዲሁም 40 የብር መሰኪያዎቻቸውን ሠራ፤ በአንዱ ቋሚ ሥር ሁለት መሰኪያዎችን፣ በተቀረው በእያንዳንዱም ቋሚ ሥር ሁለት መሰኪያዎችን አደረገ።
27 በስተ ምዕራብ በኩል ለሚገኘው ለኋለኛው የማደሪያ ድንኳኑ ጎን ስድስት ቋሚዎችን ሠራ።+ 28 በማደሪያ ድንኳኑ በስተ ኋላ በኩል ባሉት ሁለት ማዕዘኖች ላይ የማዕዘን ቋሚዎች የሚሆኑ ሁለት ቋሚዎችን ሠራ። 29 ቋሚዎቹም ከታች አንስቶ የመጀመሪያው ቀለበት እስከሚገኝበት እስከ ላይ ድረስ ድርብ ነበሩ። ሁለቱን የማዕዘን ቋሚዎች የሠራቸው በዚህ መንገድ ነበር። 30 በመሆኑም ስምንት ቋሚዎች የነበሩ ሲሆን እነሱም ከብር የተሠሩ 16 መሰኪያዎች ነበሯቸው፤ ይህም በእያንዳንዱ ቋሚ ሥር ሁለት መሰኪያ ማለት ነው።
31 ከዚያም ከግራር እንጨት አግዳሚ እንጨቶችን ሠራ፤ በአንዱ ጎን ላሉት የማደሪያ ድንኳኑ ቋሚዎች አምስት አግዳሚ እንጨቶችን፣+ 32 በሌላኛው ጎን ላሉት የማደሪያ ድንኳኑ ቋሚዎች ደግሞ አምስት አግዳሚ እንጨቶችን እንዲሁም በስተ ምዕራብ በሚገኘው በኋለኛው የማደሪያ ድንኳኑ ጎን ላሉት ቋሚዎች አምስት አግዳሚ እንጨቶችን ሠራ። 33 በቋሚዎቹ መሃል ላይ ከጫፍ እስከ ጫፍ እንዲዘልቅ መካከለኛውን አግዳሚ እንጨት ሠራ። 34 ቋሚዎቹንም በወርቅ ለበጣቸው፤ አግዳሚ እንጨቶቹን የሚሸከሙትን ቀለበቶችም ከወርቅ ሠራቸው። አግዳሚ እንጨቶቹንም በወርቅ ለበጣቸው።+
35 ከዚያም ከሰማያዊ ክር፣ ከሐምራዊ ሱፍ፣ ከደማቅ ቀይ ማግ እንዲሁም በቀጭኑ ከተፈተለ ጥሩ የበፍታ ድር መጋረጃ ሠራ።+ በላዩም ላይ ኪሩቦች+ እንዲጠለፉበት አደረገ።+ 36 ከዚያም ለመጋረጃው ከግራር እንጨት አራት ዓምዶችን ሠርቶ በወርቅ ለበጣቸው፤ ማንጠልጠያዎቻቸውም ከወርቅ የተሠሩ ነበሩ፤ ለዓምዶቹም ከብር የተሠሩ አራት መሰኪያዎችን አዘጋጀ። 37 በመቀጠልም ለድንኳኑ መግቢያ ከሰማያዊ ክር፣ ከሐምራዊ ሱፍ፣ ከደማቅ ቀይ ማግ እንዲሁም በቀጭኑ ከተፈተለ ጥሩ የበፍታ ድር የተሸመነ መከለያ* ሠራ፤+ 38 እንዲሁም አምስቱን ዓምዶችና ማንጠልጠያዎቹን ሠራ። አናታቸውንና ማያያዣዎቻቸውንም* በወርቅ ለበጣቸው፤ አምስቱ መሰኪያዎቻቸው ግን ከመዳብ የተሠሩ ነበሩ።
37 ከዚያም ባስልኤል+ ከግራር እንጨት ታቦቱን+ ሠራ። ርዝመቱ ሁለት ክንድ* ተኩል፣ ወርዱ አንድ ክንድ ተኩል፣ ከፍታው ደግሞ አንድ ክንድ ተኩል ነበር።+ 2 ውስጡንና ውጭውንም በንጹሕ ወርቅ ለበጠው፤ በዙሪያውም የወርቅ ክፈፍ ሠራለት።+ 3 ከአራቱ እግሮቹ በላይ የሚሆኑ አራት የወርቅ ቀለበቶችን ሠራለት፤ ሁለቱን ቀለበቶች በአንድ ጎኑ፣ ሁለቱን ቀለበቶች ደግሞ በሌላኛው ጎኑ በኩል አደረጋቸው። 4 ከዚያም ከግራር እንጨት መሎጊያዎችን ሠራ፤ በወርቅም ለበጣቸው።+ 5 ታቦቱንም ለመሸከም እንዲያገለግሉ መሎጊያዎቹን በታቦቱ ጎንና ጎን ባሉት ቀለበቶች ውስጥ አስገባቸው።+
6 እሱም ከንጹሕ ወርቅ መክደኛውን ሠራ።+ ርዝመቱ ሁለት ክንድ ተኩል ወርዱ ደግሞ አንድ ክንድ ተኩል ነበር።+ 7 በተጨማሪም በመክደኛው+ ጫፍና ጫፍ ላይ ከተጠፈጠፈ ወርቅ ሁለት ኪሩቦችን+ ሠራ። 8 አንዱ ኪሩብ በአንዱ ጫፍ ሌላኛው ኪሩብ ደግሞ በሌላኛው ጫፍ ላይ ነበር። ኪሩቦቹን በሁለቱም የመክደኛው ጫፎች ላይ ሠራቸው። 9 ሁለቱ ኪሩቦችም ክንፎቻቸውን ወደ ላይ በመዘርጋት መክደኛውን በክንፎቻቸው ከልለውት ነበር።+ እርስ በርስ ትይዩ ነበሩ፤ ፊታቸውንም ወደ መክደኛው አጎንብሰው ነበር።+
10 ከዚያም ከግራር እንጨት ጠረጴዛውን ሠራ።+ ርዝመቱ ሁለት ክንድ፣ ወርዱ አንድ ክንድ ከፍታው ደግሞ አንድ ክንድ ተኩል ነበር።+ 11 በንጹሕ ወርቅም ለበጠው፤ ዙሪያውንም የወርቅ ክፈፍ ሠራለት። 12 ከዚያም በዙሪያው አንድ ጋት* ስፋት ያለው ጠርዝ ሠራለት፤ ለጠርዙም ዙሪያውን የወርቅ ክፈፍ ሠራለት። 13 በተጨማሪም አራት የወርቅ ቀለበቶች ሠራለት፤ ቀለበቶቹንም አራቱ እግሮቹ በሚገኙባቸው አራት ማዕዘኖች ላይ አደረጋቸው። 14 ጠረጴዛውን ለመሸከም የሚያገለግሉትን መሎጊያዎች የሚይዙት ቀለበቶች በጠርዙ አጠገብ ነበሩ። 15 ከዚያም ጠረጴዛውን ለመሸከም የሚያገለግሉትን መሎጊያዎች ከግራር እንጨት ሠርቶ በወርቅ ለበጣቸው። 16 በኋላም በጠረጴዛው ላይ የሚሆኑትን ዕቃዎች ይኸውም ሳህኖቹንና ጽዋዎቹን እንዲሁም ለመጠጥ መባ ማፍሰሻ የሚያገለግሉትን ጎድጓዳ ሳህኖቹንና ማንቆርቆሪያዎቹን ከንጹሕ ወርቅ ሠራ።+
17 ከዚያም መቅረዙን ከንጹሕ ወርቅ ሠራ።+ መቅረዙን ጠፍጥፎ ሠራው። የመቅረዙ መቆሚያ፣ ግንዱ፣ አበባ አቃፊዎቹ፣ እንቡጦቹና የፈኩት አበቦች ወጥ ሆነው የተሠሩ ነበሩ።+ 18 መቅረዙ ከግንዱ ላይ የወጡ ስድስት ቅርንጫፎች ነበሩት፤ ሦስቱ ቅርንጫፎቹ ከአንዱ ጎን ሦስቱ ቅርንጫፎቹ ደግሞ ከሌላው ጎን የወጡ ነበሩ። 19 በአንዱ በኩል ባሉት ቅርንጫፎች በእያንዳንዳቸው ላይ የአልሞንድ አበባ የሚመስሉ ሦስት የአበባ አቃፊዎች ከእንቡጦችና ከፈኩ አበቦች ጋር በማፈራረቅ ተሠርተው ነበር፤ በሌላኛው በኩል ባሉት ቅርንጫፎችም በእያንዳንዳቸው ላይ የአልሞንድ አበባ የሚመስሉ ሦስት የአበባ አቃፊዎች ከእንቡጦችና ከፈኩ አበቦች ጋር በማፈራረቅ ተሠርተው ነበር። ከመቅረዙ ግንድ በሚወጡት ስድስት ቅርንጫፎች ላይ የተደረገው ይህ ነበር። 20 በመቅረዙም ግንድ ላይ የአልሞንድ አበባ የሚመስሉ አራት የአበባ አቃፊዎች ከእንቡጦችና ከፈኩ አበቦች ጋር በማፈራረቅ ተሠርተው ነበር። 21 ከግንዱ በሚወጡት በመጀመሪያዎቹ ጥንድ ቅርንጫፎች ሥር አንድ እንቡጥ፣ ቀጥሎ ባሉት ጥንድ ቅርንጫፎች ሥር አንድ እንቡጥ እንዲሁም ቀጥሎ ባሉት ጥንድ ቅርንጫፎች ሥር አንድ እንቡጥ ነበር፤ ከመቅረዙ ግንድ ለሚወጡት ስድስት ቅርንጫፎች እንዲሁ ተደርጎላቸው ነበር። 22 እንቡጦቹም ሆኑ ቅርንጫፎቹ፣ መላው መቅረዙ ከንጹሕ ወርቅ ተጠፍጥፎ ወጥ ሆኖ የተሠራ ነበር። 23 ከዚያም ሰባቱን መብራቶች+ እንዲሁም መቆንጠጫዎቹንና መኮስተሪያዎቹን ከንጹሕ ወርቅ ሠራ። 24 መቅረዙን ከዕቃዎቹ ሁሉ ጋር የሠራው ከአንድ ታላንት* ንጹሕ ወርቅ ነበር።
25 ከዚያም ከግራር እንጨት የዕጣን መሠዊያውን+ ሠራ። ርዝመቱ አንድ ክንድ፣ ወርዱ አንድ ክንድ ሆኖ አራቱም ጎኖቹ እኩል ሲሆኑ ከፍታው ደግሞ ሁለት ክንድ ነበር። ቀንዶቹ ከዚያው ወጥ ሆነው የተሠሩ ነበሩ።+ 26 እሱም ላዩን፣ ሁሉንም ጎኖቹን እንዲሁም ቀንዶቹን በንጹሕ ወርቅ ለበጠው፤ በዙሪያውም የወርቅ ክፈፍ ሠራለት። 27 መሠዊያውን ለመሸከም የሚያገለግሉትን መሎጊያዎች እንዲይዙም በሁለቱ ተቃራኒ ጎኖቹ ላይ ከክፈፉ በታች ሁለት የወርቅ ቀለበቶችን ሠራለት። 28 ከዚያ በኋላ መሎጊያዎቹን ከግራር እንጨት ሠርቶ በወርቅ ለበጣቸው። 29 በተጨማሪም ቅዱሱን የቅብዓት ዘይትና+ በብልሃት የተቀመመውን ጥሩ መዓዛ ያለውን ንጹሕ ዕጣን+ አዘጋጀ።
38 እሱም የሚቃጠል መባ የሚቀርብበትን መሠዊያ ከግራር እንጨት ሠራ። ርዝመቱ አምስት ክንድ፣* ወርዱም አምስት ክንድ ሲሆን አራቱም ጎኖቹ እኩል ነበሩ፤ ከፍታው ደግሞ ሦስት ክንድ ነበር።+ 2 ከዚያም በአራቱ ማዕዘኖች ላይ ቀንዶቹን ሠራለት። ቀንዶቹም ከዚያው ወጥ ሆነው የተሠሩ ነበሩ። በመቀጠልም በመዳብ ለበጠው።+ 3 ከዚህ በኋላ የመሠዊያውን ዕቃዎች በሙሉ ይኸውም ባልዲዎቹን፣ አካፋዎቹን፣ ሳህኖቹን፣ ሹካዎቹንና መኮስተሪያዎቹን ሠራ። ዕቃዎቹን በሙሉ ከመዳብ ሠራቸው። 4 በተጨማሪም ለመሠዊያው ከጠርዙ ወደ ታች ወረድ ብሎ ወደ መሃል አካባቢ እንደ መረብ ያለ የመዳብ ፍርግርግ ሠራለት። 5 መሎጊያዎቹን ለመያዝ የሚያገለግሉትንም አራት ቀለበቶች ከመዳብ ፍርግርጉ አጠገብ በአራቱ ማዕዘኖች ላይ ሠራ። 6 በኋላም መሎጊያዎቹን ከግራር እንጨት ሠርቶ በመዳብ ለበጣቸው። 7 ከዚያም መሠዊያውን ለመሸከም እንዲያገለግሉ መሎጊያዎቹን በመሠዊያው ጎኖች ላይ ባሉት ቀለበቶች ውስጥ አስገባቸው። መሠዊያውንም ባዶ ሣጥን አስመስሎ ከሳንቃዎች ሠራው።
8 ከዚያም የመዳቡን ገንዳና+ ከመዳብ የተሠራውን ማስቀመጫውን ሠራ፤ ለዚህም በመገናኛው ድንኳን መግቢያ ላይ በተደራጀ መልክ ያገለግሉ የነበሩትን ሴት አገልጋዮች መስተዋቶች* ተጠቀመ።
9 ከዚያም ግቢውን ሠራ።+ በስተ ደቡብ በኩል ለሚገኘው፣ ፊቱ በደቡብ አቅጣጫ ላለው የግቢው ጎን በቀጭኑ ከተፈተለ ጥሩ በፍታ ርዝመታቸው 100 ክንድ የሆነ መጋረጃዎች ሠራ።+ 10 ከመዳብ የተሠሩ 20 ቋሚዎችና 20 መሰኪያዎች ነበሩ፤ በቋሚዎቹ ላይ ያሉት ማንጠልጠያዎችና ማያያዣዎቻቸው* ደግሞ ከብር የተሠሩ ነበሩ። 11 በተጨማሪም በስተ ሰሜን በኩል ባለው ጎን ያሉት መጋረጃዎች ርዝመታቸው 100 ክንድ ነበር። ሃያዎቹ ቋሚዎቻቸውና 20ዎቹ መሰኪያዎቻቸው ከመዳብ የተሠሩ ነበሩ። በቋሚዎቹ ላይ ያሉት ማንጠልጠያዎችና ማያያዣዎቻቸው* ደግሞ ከብር የተሠሩ ነበሩ። 12 በስተ ምዕራብ በኩል ባለው ጎን ያሉት መጋረጃዎች ግን ርዝመታቸው 50 ክንድ ነበር። አሥር ቋሚዎችና አሥር መሰኪያዎች ነበሩ፤ በቋሚዎቹ ላይ ያሉት ማንጠልጠያዎችና ማያያዣዎቻቸው* ከብር የተሠሩ ነበሩ። 13 በስተ ምሥራቅ አቅጣጫ ይኸውም በፀሐይ መውጫ በኩል ያለው ጎን ርዝመቱ 50 ክንድ ነበር። 14 በአንደኛው በኩል ያሉት የመግቢያው መጋረጃዎች ርዝመታቸው 15 ክንድ ሲሆን ሦስት ቋሚዎችና ሦስት መሰኪያዎች ነበሯቸው። 15 በሌላኛው በኩል ያሉት የግቢው መግቢያ መጋረጃዎችም ርዝመታቸው 15 ክንድ ሲሆን ሦስት ቋሚዎችና ሦስት መሰኪያዎች ነበሯቸው። 16 በግቢው ዙሪያ ያሉት መጋረጃዎች በሙሉ በቀጭኑ ከተፈተለ ጥሩ በፍታ የተሠሩ ነበሩ። 17 የቋሚዎቹ መሰኪያዎች ከመዳብ የተሠሩ ነበሩ፤ በቋሚዎቹ ላይ ያሉት ማንጠልጠያዎችና ማያያዣዎቻቸው* ከብር የተሠሩ ሲሆኑ አናታቸውም በብር የተለበጠ ነበር። የግቢው ቋሚዎች በሙሉ ከብር የተሠሩ ማያያዣዎች ነበሯቸው።+
18 የግቢው መግቢያ መከለያ* ከሰማያዊ ክር፣ ከሐምራዊ ሱፍ፣ ከደማቅ ቀይ ማግ እንዲሁም በቀጭኑ ከተፈተለ ጥሩ የበፍታ ድር ተሸምኖ የተሠራ ነበር። ርዝመቱ 20 ክንድ ሲሆን ከፍታው ደግሞ ልክ እንደ ግቢው መጋረጃዎች 5 ክንድ ነበር።+ 19 አራቱ ቋሚዎቻቸውና አራቱ መሰኪያዎቻቸው ከመዳብ የተሠሩ ነበሩ። ማንጠልጠያዎቻቸውና ማያያዣዎቻቸው* ከብር የተሠሩ ሲሆኑ አናታቸው ደግሞ በብር የተለበጠ ነበር። 20 የማደሪያ ድንኳኑና በግቢው ዙሪያ የሚገኙት ካስማዎች በሙሉ ከመዳብ የተሠሩ ነበሩ።+
21 በሙሴ ትእዛዝ መሠረት ተቆጥረው የተመዘገቡት የማደሪያ ድንኳኑ ይኸውም የምሥክሩ የማደሪያ ድንኳን+ ዕቃዎች የሚከተሉት ናቸው፤ ይህን ያከናወኑት ሌዋውያኑ+ ሲሆኑ መሪያቸውም የካህኑ የአሮን ልጅ ኢታምር+ ነበር። 22 ከይሁዳ ነገድ የሆነው የሁር ልጅ የዖሪ ልጅ ባስልኤል+ ይሖዋ ሙሴን ያዘዘውን ሁሉ አደረገ። 23 ከእሱም ጋር ከዳን ነገድ የሆነው የአሂሳማክ ልጅ ኤልያብ+ ነበር፤ እሱም የእጅ ባለሙያና የጥልፍ ባለሙያ እንዲሁም በሰማያዊ ክር፣ በሐምራዊ ሱፍ፣ በደማቅ ቀይ ማግ እንዲሁም በጥሩ በፍታ የሚሸምን የሽመና ባለሙያ ነበር።
24 በአጠቃላይ በቅዱሱ ስፍራ ለተከናወነው ሥራ የዋለው ወርቅ በሙሉ መባ*+ ሆኖ ከቀረበው ወርቅ ጋር ተመጣጣኝ ነበር፤ ይህም እንደ ቋሚ መለኪያ ሆኖ በሚያገለግለው በቅዱሱ ስፍራ ሰቅል* 29 ታላንት* ከ730 ሰቅል* ነበር። 25 ከማኅበረሰቡ መካከል ከተመዘገቡት ሰዎች የተገኘው ብር ደግሞ እንደ ቋሚ መለኪያ ሆኖ በሚያገለግለው በቅዱሱ ስፍራ ሰቅል 100 ታላንት ከ1,775 ሰቅል ነበር። 26 ሃያ ዓመትና ከዚያ በላይ ሆኗቸው ከተመዘገቡት 603,550+ ሰዎች መካከል የሆነ እያንዳንዱ ግለሰብ የሰጠው ግማሽ ሰቅል፣ እንደ ቋሚ መለኪያ ሆኖ በሚያገለግለው በቅዱሱ ስፍራ ሰቅል* ግማሽ ሰቅል ነበር።+
27 የቅዱሱን ስፍራ መሰኪያዎችና ለመጋረጃው ቋሚዎች የሚሆኑትን መሰኪያዎች ለመሥራት የዋለው 100 ታላንት ብር ነበር፤ 100 መሰኪያዎች 100 ታላንት ነበሩ፤ ይህም ለእያንዳንዱ መሰኪያ አንድ ታላንት ማለት ነው።+ 28 ለቋሚዎቹ ከ1,775 ሰቅል ብር ማንጠልጠያዎችን ሠራ፤ አናታቸውንም ከለበጠ በኋላ እርስ በርስ አያያዛቸው።
29 መባ* ሆኖ የቀረበው መዳብ ደግሞ 70 ታላንት ከ2,400 ሰቅል ነበር። 30 በዚህም የመገናኛ ድንኳኑን መግቢያ መሰኪያዎች፣ የመዳብ መሠዊያውንና የመዳብ ፍርግርጉን እንዲሁም የመሠዊያውን ዕቃዎች በሙሉ ሠራ፤ 31 እንዲሁም በግቢው ዙሪያ ያሉትን መሰኪያዎች፣ ለግቢው መግቢያ የሚሆኑትን መሰኪያዎች እንዲሁም የማደሪያ ድንኳኑን ካስማዎች በሙሉና በግቢው ዙሪያ ያሉትን የድንኳን ካስማዎች+ በሙሉ ሠራ።
39 በቅዱሱ ስፍራ ለማገልገል የሚለበሱትን በጥሩ ሁኔታ የተሸመኑትን ልብሶች ከሰማያዊ ክር፣ ከሐምራዊ ሱፍና ከደማቅ ቀይ ማግ ሠሩ።+ ልክ ይሖዋ ሙሴን ባዘዘው መሠረትም የአሮንን ቅዱስ ልብሶች ሠሩ።+
2 እሱም ኤፉዱን+ ከወርቅ፣ ከሰማያዊ ክር፣ ከሐምራዊ ሱፍ፣ ከደማቅ ቀይ ማግና በቀጭኑ ከተፈተለ ጥሩ በፍታ ሠራው። 3 እነሱም ወርቁን በመቀጥቀጥ በስሱ ጠፈጠፉት፤ እሱም ከሰማያዊው ክር፣ ከሐምራዊው ሱፍ፣ ከደማቁ ቀይ ማግና ከጥሩው በፍታ ጋር አብሮ እንዲሠራው ወርቁን እንደ ክር በቀጫጭኑ ሰነጣጠቀው፤ ከዚያም በወርቁ ጥልፍ ጠለፈበት። 4 ለኤፉዱ በሁለቱ የላይኛው ጫፎቹ ላይ የተያያዙ ሁለት የትከሻ ጥብጣቦች ሠሩለት። 5 ኤፉዱ ወዲያ ወዲህ እንዳይንቀሳቀስ ለማሰር የሚያገለግለው ከኤፉዱ ጋር የተያያዘው በሽመና የተሠራው መቀነትም + ልክ ይሖዋ ሙሴን ባዘዘው መሠረት እንደ ኤፉዱ ሁሉ ከወርቅ፣ ከሰማያዊ ክር፣ ከሐምራዊ ሱፍ፣ ከደማቅ ቀይ ማግና በቀጭኑ ከተፈተለ ጥሩ በፍታ ተሠራ።
6 ከዚያም የኦኒክስ ድንጋዮቹን በወርቅ አቃፊዎቹ ውስጥ አስቀመጧቸው፤ የእስራኤልን ወንዶች ልጆች ስሞችም ልክ ማኅተም በሚቀረጽበት መንገድ ቀረጹባቸው።+ 7 እሱም ይሖዋ ሙሴን ባዘዘው መሠረት ለእስራኤል ልጆች እንደ መታሰቢያ ድንጋዮች ሆነው እንዲያገለግሉ+ በኤፉዱ የትከሻ ጥብጣቦች ላይ አስቀመጣቸው። 8 ከዚያም የደረት ኪሱን+ የጥልፍ ባለሙያ እንደሚሠራው አድርጎ ልክ ኤፉዱ በተሠራበት መንገድ ከወርቅ፣ ከሰማያዊ ክር፣ ከሐምራዊ ሱፍ፣ ከደማቅ ቀይ ማግና በቀጭኑ ከተፈተለ ጥሩ በፍታ ሠራው።+ 9 ለሁለት በሚታጠፍበት ጊዜም አራቱም ጎኖቹ እኩል ነበሩ። ለሁለት በሚታጠፍበት ጊዜ ቁመቱም ሆነ ወርዱ አንድ ስንዝር* የሆነውን የደረት ኪስ ሠሩ። 10 በላዩም ላይ አራት ረድፍ ድንጋዮችን አደረጉበት። በመጀመሪያው ረድፍ ሩቢ፣ ቶጳዝዮንና መረግድ ተደረደረ። 11 በሁለተኛው ረድፍ ደግሞ በሉር፣ ሰንፔርና ኢያስጲድ ተደረደረ። 12 በሦስተኛው ረድፍ ለሼም፣ አካትምና አሜቴስጢኖስ ተደረደረ። 13 በአራተኛውም ረድፍ ክርስቲሎቤ፣ ኦኒክስና ጄድ ተደረደረ። በወርቅ አቃፊዎችም ውስጥ ተቀመጡ። 14 ድንጋዮቹም 12ቱን የእስራኤል ወንዶች ልጆች ስሞች የሚወክሉ ነበሩ፤ ስሞቹም ልክ ማኅተም በሚቀረጽበት መንገድ ተቀረጹ፤ እያንዳንዱ ስም ከ12ቱ ነገዶች አንዱን የሚወክል ነበር።
15 ከዚያም በደረት ኪሱ ላይ እንደ ገመድ የተጎነጎነ ሰንሰለት ከንጹሕ ወርቅ ሠሩ።+ 16 በመቀጠልም ሁለት የወርቅ አቃፊዎችንና ሁለት ቀለበቶችን ሠሩ፤ ሁለቱን ቀለበቶችም በደረት ኪሱ ሁለት ማዕዘኖች ላይ አያያዟቸው። 17 በኋላም ሁለቱን የወርቅ ገመዶች በደረት ኪሱ ማዕዘኖች ላይ በሚገኙት ሁለት ቀለበቶች ውስጥ አስገቧቸው። 18 ከዚያም የሁለቱን ገመዶች ሁለት ጫፎች በሁለቱ አቃፊዎች ውስጥ አስገቧቸው፤ በኤፉዱ በፊት በኩል በትከሻ ጥብጣቦቹ ላይ አያያዟቸው። 19 በመቀጠልም ሁለት የወርቅ ቀለበቶችን ሠርተው በኤፉዱ በኩል በሚውለው በደረት ኪሱ ውስጠኛ ጠርዝ ሁለት ጫፎች ላይ አደረጓቸው።+ 20 ከዚያም ሁለት ተጨማሪ የወርቅ ቀለበቶችን ሠርተው በኤፉዱ ላይ ከፊት በኩል ከሁለቱ የትከሻ ጥብጣቦች በታች፣ መጋጠሚያው አጠገብ፣ በሽመና ከተሠራው የኤፉዱ መቀነት በላይ አደረጓቸው። 21 በመጨረሻም ይሖዋ ሙሴን ባዘዘው መሠረት የደረት ኪሱ ከኤፉዱ ላይ ሳይንቀሳቀስ፣ ተሸምኖ ከተሠራው መቀነት በላይ እንዲውል የደረት ኪሱን ቀለበቶች ከኤፉዱ ቀለበቶች ጋር በሰማያዊ ገመድ አያያዟቸው።
22 ከዚያም እጅጌ የሌለውን የኤፉዱን ቀሚስ የሽመና ባለሙያ ሙሉ በሙሉ በሰማያዊ ክር ሸምኖ እንዲሠራው አደረገ።+ 23 የቀሚሱ አንገት ማስገቢያ ልክ እንደ ጥሩር አንገት ማስገቢያ መሃል ላይ ነበር። የአንገት ማስገቢያውም እንዳይቀደድ ዙሪያውን ተቀምቅሞ ነበር። 24 ከዚያም ሰማያዊ ክር፣ ሐምራዊ ሱፍና ደማቅ ቀይ ማግ አንድ ላይ በመግመድ በታችኛው የቀሚሱ ጠርዝ ዙሪያ ዘርፍ የሚሆኑ ሮማኖችን ሠሩ። 25 በተጨማሪም ከንጹሕ ወርቅ ቃጭሎችን ሠሩ፤ ቃጭሎቹንም በቀሚሱ ጠርዝ ዙሪያ በሮማኖቹ መሃል መሃል አደረጓቸው። 26 ልክ ይሖዋ ሙሴን ባዘዘው መሠረትም ለአገልግሎት በሚውለው ቀሚስ የታችኛው ጠርዝ ዙሪያ ቃጭል ከዚያም ሮማን፣ ቃጭል ከዚያም ሮማን እያፈራረቁ አደረጉበት።
27 ከዚያም ለአሮንና ለወንዶች ልጆቹ ከጥሩ በፍታ ረጅም ቀሚስ በሽመና ባለሙያ አሠሩላቸው፤+ 28 በተጨማሪም ጥምጥሙን+ ከጥሩ በፍታ፣ ጌጠኛ የራስ ቆቦቹንም+ ከጥሩ በፍታ፣ የበፍታ ቁምጣውን+ በቀጭኑ ከተፈተለ በፍታ 29 እንዲሁም ልክ ይሖዋ ሙሴን ባዘዘው መሠረት መቀነቱን በቀጭኑ ከተፈተለ ጥሩ በፍታ፣ ከሰማያዊ ክር፣ ከሐምራዊ ሱፍና ከደማቅ ቀይ ማግ ሸምነው ሠሩት።
30 በመጨረሻም የሚያብረቀርቀውን ጠፍጣፋ ወርቅ ይኸውም ለአምላክ የተወሰኑ መሆንን የሚያሳየውን ቅዱስ ምልክት* ከንጹሕ ወርቅ ሠሩ፤ አንድ ሰው ማኅተም በሚቀርጽበት መንገድ “ቅድስና የይሖዋ ነው” የሚል ጽሑፍ በላዩ ላይ ቀረጹበት።+ 31 ከዚያም ልክ ይሖዋ ሙሴን ባዘዘው መሠረት በጥምጥሙ ላይ እንዲውል ለማድረግ ሰማያዊ ገመድ አሰሩበት።
32 የማደሪያ ድንኳኑ ይኸውም የመገናኛ ድንኳኑ ሥራ በሙሉ ተጠናቀቀ፤ እስራኤላውያን ይሖዋ ሙሴን ያዘዘውን ነገር ሁሉ ሠሩ።+ ልክ እንደታዘዙትም አደረጉ።
33 እነሱም የማደሪያ ድንኳኑን+ ወደ ሙሴ አመጡ፤ ድንኳኑንና+ ዕቃዎቹን በሙሉ ማለትም ማያያዣዎቹን፣+ አራት ማዕዘን ቋሚዎቹን፣+ አግዳሚ እንጨቶቹን፣+ ዓምዶቹን፣ መሰኪያዎቹን፣+ 34 ለመደረቢያ የሚሆነውን ቀይ ቀለም የተነከረ የአውራ በግ ቆዳና+ ለመደረቢያ የሚሆነውን የአቆስጣ ቆዳ፣ ለመግቢያው መከለያ የሚሆነውን መጋረጃ፣+ 35 የምሥክሩን ታቦት እንዲሁም መሎጊያዎቹንና+ መክደኛውን፣+ 36 ጠረጴዛውን እንዲሁም ዕቃዎቹን+ በሙሉና ገጸ ኅብስቱን፣ 37 ከንጹሕ ወርቅ የተሠራውን መቅረዝ+ እንዲሁም በመደዳ የተደረደሩትን መብራቶቹንና ዕቃዎቹን+ በሙሉ፣ የመብራቱን ዘይት፣+ 38 የወርቅ መሠዊያውን፣+ የቅብዓት ዘይቱን፣+ ጥሩ መዓዛ ያለውን ዕጣን፣+ ለድንኳኑ መግቢያ የሚሆነውን መከለያ፣*+ 39 የመዳብ መሠዊያውንና+ የመዳብ ፍርግርጉን እንዲሁም መሎጊያዎቹንና+ ዕቃዎቹን+ በሙሉ፣ ገንዳውንና ማስቀመጫውን፣+ 40 የግቢውን መጋረጃዎች እንዲሁም ቋሚዎቹን፣ መሰኪያዎቹን፣+ ለግቢው መግቢያ የሚሆነውን መከለያ፣*+ የድንኳኑን ገመዶች፣ የድንኳኑን ካስማዎችና+ በማደሪያ ድንኳኑ ይኸውም በመገናኛ ድንኳኑ ለሚከናወነው አገልግሎት የሚውሉትን ዕቃዎች በሙሉ፣ 41 በመቅደሱ ለማገልገል የሚለበሱትን በጥሩ ሁኔታ ተሸምነው የተሠሩትን ልብሶች፣ የካህኑን የአሮንን ቅዱስ ልብሶች+ እንዲሁም ወንዶች ልጆቹ ካህናት ሆነው ሲያገለግሉ የሚለብሷቸውን ልብሶች አመጡ።
42 እስራኤላውያን ሥራውን በሙሉ ያከናወኑት ይሖዋ ለሙሴ በሰጠው ትእዛዝ መሠረት ነበር።+ 43 ሙሴም ሥራቸውን በሙሉ ሲመለከት ልክ ይሖዋ ባዘዘው መሠረት እንደሠሩ አየ፤ ከዚያም ባረካቸው።
40 ይሖዋም ሙሴን እንዲህ አለው፦ 2 “በመጀመሪያው ወር፣ ከወሩም በመጀመሪያው ቀን የማደሪያ ድንኳኑን ይኸውም የመገናኛ ድንኳኑን ትከል።+ 3 የምሥክሩን ታቦት በውስጡ ካስቀመጥክ+ በኋላ ታቦቱን በመጋረጃው ከልለው።+ 4 ጠረጴዛውንም+ ካስገባህ በኋላ በላዩ ላይ የሚቀመጡትን ነገሮች አስተካክለህ አስቀምጥ፤ መቅረዙንም+ አስገብተህ መብራቶቹን+ አብራቸው። 5 ከዚያም ለዕጣን የሚሆነውን የወርቅ መሠዊያ+ ከምሥክሩ ታቦት በፊት አስቀምጠው፤ ለማደሪያ ድንኳኑ መግቢያ የሚሆነውን መከለያም* በቦታው አድርገው።+
6 “የሚቃጠል መባ የሚቀርብበትን መሠዊያም+ በማደሪያ ድንኳኑ ይኸውም በመገናኛ ድንኳኑ መግቢያ ፊት አድርገው፤ 7 ገንዳውንም በመገናኛ ድንኳኑና በመሠዊያው መካከል አድርገህ ውኃ ጨምርበት።+ 8 በመገናኛ ድንኳኑም ዙሪያ ግቢ ከልልለት፤+ ለግቢውም መግቢያ መከለያ*+ አድርግለት። 9 የማደሪያ ድንኳኑም የተቀደሰ እንዲሆን የቅብዓት ዘይቱን+ ወስደህ ድንኳኑንና በውስጡ ያሉትን ነገሮች በሙሉ ትቀባቸዋለህ፤+ ድንኳኑንም ሆነ ዕቃዎቹን በሙሉ ትቀድሳለህ። 10 የሚቃጠል መባ የሚቀርብበትም መሠዊያ እጅግ ቅዱስ እንዲሆን መሠዊያውንና ዕቃዎቹን በሙሉ ትቀባቸዋለህ፤ መሠዊያውንም ትቀድሳለህ።+ 11 ገንዳውንና ማስቀመጫውንም ቀባ፤ ቀድሰውም።
12 “ከዚያም አሮንንና ወንዶች ልጆቹን ወደ መገናኛ ድንኳኑ መግቢያ አቅርባቸው፤ በውኃም እጠባቸው።+ 13 አሮንንም ቅዱስ የሆኑትን ልብሶች ካለበስከው+ በኋላ ቀባው፤+ እንዲሁም ቀድሰው፤ እሱም ካህን ሆኖ ያገለግለኛል። 14 ከዚያም ወንዶች ልጆቹን አቅርበህ ረጃጅሞቹን ቀሚሶች አልብሳቸው።+ 15 ካህናት ሆነውም እንዲያገለግሉኝ አባታቸውን እንደቀባኸው ሁሉ እነሱንም ቀባቸው፤+ መቀባታቸውም ክህነታቸው ለትውልዶቻቸው ሁሉ በዘላቂነት እንዲቀጥል ያስችላል።”+
16 ሙሴም ይሖዋ ባዘዘው መሠረት አደረገ።+ ልክ እንደዚሁ አደረገ።
17 በሁለተኛው ዓመት፣ በመጀመሪያው ወር፣ ከወሩም በመጀመሪያው ቀን የማደሪያ ድንኳኑ ተተከለ።+ 18 ሙሴም የማደሪያ ድንኳኑን ሲተክል መሰኪያዎቹን+ ከሥር በማስቀመጥ አራት ማዕዘን ቋሚዎቹን+ አደረገባቸው፤ አግዳሚ እንጨቶቹንም+ አስገባቸው፤ ዓምዶቹንም አቆማቸው። 19 ከዚያም ልክ ይሖዋ ሙሴን ባዘዘው መሠረት የማደሪያ ድንኳኑን በድንኳኑ ጨርቅ አለበሰው፤+ በላዩም ላይ የድንኳኑን መደረቢያ ደረበበት።+
20 ቀጥሎም የምሥክሩን ጽላቶች+ ወስዶ በታቦቱ+ ውስጥ አስቀመጣቸው፤ የታቦቱንም መሎጊያዎች+ አስገባቸው፤ መክደኛውንም+ በታቦቱ ላይ አደረገው።+ 21 ከዚያም ልክ ይሖዋ ሙሴን ባዘዘው መሠረት ታቦቱን ወደ ማደሪያ ድንኳኑ አስገባው፤ የመግቢያው መከለያ የሆነውን መጋረጃ+ በቦታው በማድረግ የምሥክሩን ታቦት ከለለው።+
22 በመቀጠልም ጠረጴዛውን+ በመገናኛ ድንኳኑ ውስጥ በስተ ሰሜን በኩል ባለው የማደሪያ ድንኳኑ ጎን ከመጋረጃው ውጭ አደረገው፤ 23 በላዩም ላይ ልክ ይሖዋ ሙሴን ባዘዘው መሠረት የተነባበረውን ኅብስት በይሖዋ ፊት አስቀመጠ።+
24 መቅረዙንም+ በመገናኛ ድንኳኑ ውስጥ ከጠረጴዛው ትይዩ፣ በስተ ደቡብ በኩል ባለው የማደሪያ ድንኳኑ ጎን አስቀመጠው። 25 ከዚያም ልክ ይሖዋ ሙሴን ባዘዘው መሠረት መብራቶቹን+ በይሖዋ ፊት አበራቸው።
26 የወርቅ መሠዊያውንም+ በመገናኛ ድንኳኑ ውስጥ ከመጋረጃው በፊት አስቀመጠው፤ 27 ይህን ያደረገውም ልክ ይሖዋ ሙሴን ባዘዘው መሠረት ጥሩ መዓዛ ያለው ዕጣን+ እንዲጨስበት+ ነው።
28 ቀጥሎም የማደሪያ ድንኳኑን መግቢያ መከለያ*+ በቦታው አደረገው።
29 ከዚያም ልክ ይሖዋ ሙሴን ባዘዘው መሠረት የሚቃጠለውን መባና የእህሉን መባ በላዩ ላይ እንዲያቀርብበት የሚቃጠል መባ የሚቀርብበትን መሠዊያ+ በማደሪያ ድንኳኑ ይኸውም በመገናኛ ድንኳኑ መግቢያ ላይ አደረገው።
30 በመቀጠልም ገንዳውን በመገናኛ ድንኳኑና በመሠዊያው መካከል አደረገው፤ ለመታጠቢያ የሚሆን ውኃም ጨመረበት።+ 31 ሙሴ እንዲሁም አሮንና ወንዶች ልጆቹ እጃቸውንና እግራቸውን ታጠቡበት። 32 ልክ ይሖዋ ሙሴን ባዘዘው መሠረት ወደ መገናኛ ድንኳኑ በሚገቡበትና ወደ መሠዊያው በሚቀርቡበት ጊዜ ሁሉ ይታጠቡ ነበር።+
33 በመጨረሻም በማደሪያ ድንኳኑና በመሠዊያው ዙሪያ ግቢውን ከለለ፤+ ለግቢውም መግቢያ መከለያ* አደረገለት።+
በዚህ መንገድ ሙሴ ሥራውን አጠናቀቀ። 34 ደመናውም የመገናኛ ድንኳኑን ሸፈነው፤ የይሖዋም ክብር የማደሪያ ድንኳኑን ሞላው።+ 35 ደመናው በመገናኛ ድንኳኑ ላይ አርፎ ስለነበርና የይሖዋም ክብር የማደሪያ ድንኳኑን ስለሞላው ሙሴ ወደ መገናኛ ድንኳኑ መግባት አልቻለም ነበር።+
36 እስራኤላውያንም በጉዟቸው ወቅት ሁሉ ደመናው ከማደሪያ ድንኳኑ ላይ በሚነሳበት ጊዜ ድንኳናቸውን ነቅለው ይንቀሳቀሱ ነበር።+ 37 ሆኖም ደመናው ካልተነሳ፣ ደመናው እስከሚነሳበት ቀን ድረስ ድንኳናቸውን ነቅለው አይንቀሳቀሱም ነበር።+ 38 መላው የእስራኤል ቤት በሚጓዝበት ወቅት ሁሉ ቀን ቀን የይሖዋ ደመና፣ ሌሊት ሌሊት ደግሞ እሳት በማደሪያ ድንኳኑ ላይ ሆኖ ያይ ነበር።+
ወይም “የወጡት ነፍሳት።”
ወይም “70 ነፍስ።”
ቃል በቃል “የእስራኤል ወንዶች ልጆችም።”
ወይም “ሣጥን።”
“ከውኃ የወጣ” የሚል ትርጉም አለው፤ ይህም ከውኃ መዳንን ያመለክታል።
ወይም “ሙሴ በበረታ ጊዜ።”
ወይም “ተከላከለላቸው።”
ዮቶርን ያመለክታል።
“በዚያ የሚኖር የባዕድ አገር ሰው” የሚል ትርጉም አለው።
ቃል በቃል “ከብዙ ቀናት።”
ወይም “ታመልካላችሁ።”
ወይም “የምሆነውን እሆናለሁ።” ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ4ን ተመልከት።
ቃል በቃል “አፈ ከባድና።”
ቃል በቃል “ከአፍህ ጋር እሆናለሁ።”
ወይም “ለእሱ የአምላክ ተወካይ ትሆንለታለህ።”
ወይም “ሰነፎች ስለሆኑ።”
ጤፍ ወይም ስንዴ ከታጨደ በኋላ ማሳው ላይ የሚቀር አገዳ።
ወይም “ሰነፎች ናችሁ።”
ወይም “ሰነፎች ናችሁ።”
ወይም “በፈርዖንና በአገልጋዮቹ ፊት እንደ ግም ስላስቆጠራችሁንና።”
ወይም “በኃያል።”
ቃል በቃል “ከንፈሮቼ ያልተገረዙትን።”
ቃል በቃል “በየሠራዊታቸው።”
ቃል በቃል “ከንፈሮቼ አልተገረዙም።”
ቃል በቃል “አምላክ አድርጌሃለሁ።”
ወይም “በአስማታዊ ጥበባቸው።”
ከአባይ ወንዝ የሚወጡ ቦዮችን ያመለክታል።
ግብፃውያንን ያመለክታል።
ወይም “ሊጫወትብን።”
ኃይለኛ መብረቅን የሚያመለክት ሊሆን ይችላል።
ሙሴን የሚያመለክት ይመስላል።
ቃል በቃል “ሰኮና።”
ቃል በቃል “ምላሱን አያሾልም።”
ቃል በቃል “እሱና የእሱ።”
ወይም “ነፍሳት።”
ቃል በቃል “በሁለቱ ምሽቶች መካከል።”
የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ቃል በቃል “ዘሎ መሄድ፤ ማለፍ።” የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ወይም “ነፍስ።”
ወይም “ነፍስ።”
ወይም “ነፍስ።”
ቃል በቃል “ጥፋቱ።”
ቃል በቃል “በውኃ ማጠራቀሚያ ጉድጓድ ቤት።”
ግብፃውያንን ጨምሮ እስራኤላውያን ያልሆኑ ድብልቅ ሕዝቦችን ያመለክታል።
ወይም “ለይልኝ።”
ቃል በቃል “እያንዳንዱን ማህፀን የሚከፍተው በኩር ሁሉ።”
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ15ን ተመልከት።
ቃል በቃል “በዓይኖችህ መካከል።”
ወይም “ማስታወሻ።”
ቃል በቃል “ማህፀን የሚከፍተውን ሁሉ።”
ቃል በቃል “ማህፀን የሚከፍተውን ሁሉ።”
ቃል በቃል “በዓይኖችህ መካከል።”
ቃል በቃል “ወደ ላይ በተዘረጋ እጅ።”
ከሌሊቱ 8 ሰዓት እስከ ጠዋት 12 ሰዓት ገደማ ያለውን ጊዜ ያመለክታል።
ተሽከርካሪ እግር።
“ያህ” የይሖዋ ስም አጭር መጠሪያ ነው።
ቃል በቃል “ቆረን።” ጤፍ ወይም ስንዴ ከታጨደ በኋላ ማሳው ላይ የሚቀረውን አገዳ ያመለክታል።
ወይም “ነፍሴ እስክትጠግብም።”
“መራራ” የሚል ትርጉም አለው።
ቃል በቃል “በሁለቱ ምሽቶች መካከል።”
ወይም “ነፍሳት ቁጥር።”
አንድ ኦሜር 2.2 ሊትር ገደማ ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
ወይም “የሰንበት በዓል።”
ወይም “አረፈ።”
“ምንድን ነው?” የሚል ትርጉም ካለው የዕብራይስጥ አባባል የመጣ ሳይሆን አይቀርም።
“ምሥክሩ” የሚለው ቃል አስፈላጊ የሆኑ ሰነዶች ተጠብቀው እንዲቆዩ የሚቀመጡበትን ሣጥን የሚያመለክት ሊሆን ይችላል።
አንድ ኢፍ 22 ሊትር ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
“ፈተና፤ ፈታኝ ሁኔታ” የሚል ትርጉም አለው።
“ጠብ” የሚል ትርጉም አለው።
ወይም “ማስታወሻ።”
“ይሖዋ አርማዬ ነው” የሚል ትርጉም አለው።
“በዚያ የሚኖር የባዕድ አገር ሰው” የሚል ትርጉም አለው።
“አምላኬ ረዳት ነው” የሚል ትርጉም አለው።
ቃል በቃል “እነሱም በማንኛውም ጊዜ።”
ወይም “ውድ ሀብቴ።”
በቀስት መወጋትን የሚያመለክት ሊሆን ይችላል።
ቃል በቃል “ወደ ሴት አትቅረቡ።”
ወይም “እኔን የሚቀናቀኑ።”
ቃል በቃል “በደጆችህ።”
እዚህ ላይ የሚገኘው “አትግደል” የሚለው ቃል ሆን ብሎ መግደልን ወይም ሕገ ወጥ ግድያን ያመለክታል።
ወይም “የሰላም መባዎችህን።”
ቃል በቃል “እርቃንህ።”
ቃል በቃል “እንዲዋጃት።”
“በሥራ መሣሪያ” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ቃል በቃል “ልጆቿ ቢወጡ።”
ወይም “ለከባድ ጉዳት።”
ወይም “ነፍስ ስለ ነፍስ።”
ወይም “ካሳ።”
ወይም “ለነፍሱ።”
አንድ ሰቅል 11.4 ግራም ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
ወይም “ወላጅ አልባ የሆነውን።”
ወይም “ቸር።”
ወይም “ገዢም።”
የዘይትና የወይን መጭመቂያን ያመለክታል።
ቃል በቃል “አታንሳ።”
ወይም “በብዙኃኑ ዘንድ ተቀባይነት ያለው።”
ቃል በቃል “ቃል።”
ወይም “ክፉውን ሰው በነፃ ስለማልለቅ።”
ወይም “የባዕድ አገር ሰውን ሕይወት (ነፍስ)።”
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ15ን ተመልከት።
የሳምንታት በዓል ወይም ጴንጤቆስጤ በመባልም ይታወቃል።
የዳስ (የማደሪያ ድንኳን) በዓል በመባልም ይታወቃል።
ወይም “ወንዶች።”
ወይም “ጠላቶችህ ሁሉ ጀርባቸውን ወደ አንተ እንዲያዞሩ።”
“ድንጋጤ፤ ሽብር” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ኤፍራጥስን ያመለክታል።
ወይም “ቀይ ሐምራዊ ቀለም የተነከረ ሱፍ።”
ወይም “በመካከላቸው አድራለሁ።”
አንድ ክንድ 44.5 ሴንቲ ሜትር ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
ወይም “ሣጥን።”
አንድ ጋት 7.4 ሴንቲ ሜትር ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
አንድ ታላንት 34.2 ኪሎ ግራም ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
አንድ ክንድ 44.5 ሴንቲ ሜትር ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
ወይም “መጋረጃ።”
ወይም “ለመጋረጃውም።”
አንድ ክንድ 44.5 ሴንቲ ሜትር ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
ወይም “በስብ የራሰውን አመድ።” መሥዋዕት ሆነው በሚቀርቡት እንስሳት ስብ የራሰውን አመድ ያመለክታል።
ወይም ለማያያዣነት የሚያገለግሉት “ቀለበቶቻቸው።”
ወይም ለማያያዣነት የሚያገለግሉ “ቀለበቶች።”
ወይም “መጋረጃ።”
ቃል በቃል “ጥበበኛ ልብ።”
አንድ ስንዝር 22.2 ሴንቲ ሜትር ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ቃል በቃል “እጃቸውን ትሞላለህ።”
የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ወይም “ቅዱሱን ዘውድ።”
ቃል በቃል “የአሮንን እጅና የወንዶች ልጆቹን እጅ ትሞላለህ።”
ወይም “የሚያረጋጋ፤ የሚያበርድ።” ቃል በቃል “እረፍት የሚሰጥ።”
ወይም “የሚያረጋጋ፤ የሚያበርድ።” ቃል በቃል “እረፍት የሚሰጥ።”
ቃል በቃል “እጃቸውን ለመሙላትና።”
ቃል በቃል “ባዕድ ሰው።” ከአሮን ወገን ያልሆነን ሰው ያመለክታል።
ቃል በቃል “እጃቸውን ለመሙላት።”
ቃል በቃል “በሁለቱ ምሽቶች መካከል።”
አንድ ሂን 3.67 ሊትር ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
አንድ ኢፍ 22 ሊትር ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
ቃል በቃል “በሁለቱ ምሽቶች መካከል።”
ወይም “የሚያረጋጋ፤ የሚያበርድ።” ቃል በቃል “እረፍት የሚሰጥ።”
ወይም “አድራለሁ።”
አንድ ክንድ 44.5 ሴንቲ ሜትር ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
ቃል በቃል “በሁለቱ ምሽቶች መካከል።”
ወይም “ነፍሱ።”
ወይም “በቅዱሱ ሰቅል።”
አንድ ሰቅል 11.4 ግራም ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
አንድ ጌራ 0.57 ግራም ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
ወይም “ለነፍሳችሁ።”
አንድ ሰቅል 11.4 ግራም ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
ወይም “ለነፍሳችሁ።”
ወይም “በቅዱሱ ሰቅል።”
ከቀረፋ ዛፍ ጋር የሚዛመድ ዛፍ ነው።
አንድ ሂን 3.67 ሊትር ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
ቃል በቃል “ባዕዱን ሰው።” ከአሮን ወገን ያልሆነን ሰው ያመለክታል።
የዚህ ቅመም ምንነት በውል አይታወቅም። ከሚሸት ተክል ወይም ከዛጎል ውስጥ የሚገኝ ሊሆን ይችላል።
ቃል በቃል “በስም ጠርቼዋለሁ።”
ቃል በቃል “ጥበበኛ ልብ።”
ወይም “ነፍስ።”
ወይም “ቀልጦ የተሠራ የጥጃ ሐውልት።”
ወይም “ቀልጦ የተሠራ የጥጃ ሐውልት።”
ቃል በቃል “አንገተ ደንዳና።”
ወይም “ተጸጸት።”
ወይም “በተናገረው ጥፋት ተጸጸተ።”
ቃል በቃል “እጃችሁን ሙሉ።”
ቃል በቃል “አንገተ ደንዳና።”
ቃል በቃል “አንገተ ደንዳና።”
ወይም “መርጬሃለሁ።”
ቃል በቃል “ፊቴ ከአንተ ጋር ይሄዳል።”
ቃል በቃል “ፊትህ ከእኛ ጋር የማይሄድ።”
ወይም “ቸር።”
ወይም “ፍቅራዊ ደግነቱና።”
ወይም “ታማኝነቱ።”
ቃል በቃል “አንገተ ደንዳና።”
ወይም “ተፈጥረው።”
የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ወይም “ተቀናቃኞቹን የማይታገሥ።”
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ15ን ተመልከት።
ቃል በቃል “ማህፀን የሚከፍተው ሁሉ።”
ወይም “ሰንበትን ታከብራለህ።”
የዳስ (የማደሪያ ድንኳን) በዓል በመባልም ይታወቃል።
ወይም “ወንድ።”
እዚህ ላይ “እሱ” የሚለው ቃል ይሖዋን እንደሚያመለክት መረዳት ይቻላል። ዘፀ 34:1ን ተመልከት።
ቃል በቃል “አሥርቱን ቃላት።”
ቃል በቃል “እሱን።”
ቃል በቃል “ጥበበኛ ልብ።”
ወይም “መጋረጃ።”
ወይም “መጋረጃ።”
ወይም “የሚወዘወዙ መባዎቻቸውን።”
ቃል በቃል “ጥበበኛ ልብ።”
ቃል በቃል “ጥበበኛ ልብ።”
ባስልኤልን የሚያመለክት ሳይሆን አይቀርም።
አንድ ክንድ 44.5 ሴንቲ ሜትር ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
ወይም “መጋረጃ።”
ወይም ለማያያዣነት የሚያገለግሉ “ቀለበቶቻቸውንም።”
አንድ ክንድ 44.5 ሴንቲ ሜትር ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
አንድ ጋት 7.4 ሴንቲ ሜትር ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
አንድ ታላንት 34.2 ኪሎ ግራም ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
አንድ ክንድ 44.5 ሴንቲ ሜትር ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
በደንብ የተወለወሉ የብረት መስተዋቶችን ያመለክታል።
ወይም ለማያያዣነት የሚያገለግሉት “ቀለበቶቻቸው።”
ወይም ለማያያዣነት የሚያገለግሉት “ቀለበቶቻቸው።”
ወይም ለማያያዣነት የሚያገለግሉት “ቀለበቶቻቸው።”
ወይም ለማያያዣነት የሚያገለግሉት “ቀለበቶቻቸው።”
ወይም “መጋረጃ።”
ወይም ለማያያዣነት የሚያገለግሉት “ቀለበቶቻቸው።”
ወይም “የሚወዘወዝ መባ።”
ወይም “በቅዱሱ ሰቅል።”
አንድ ታላንት 34.2 ኪሎ ግራም ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
አንድ ሰቅል 11.4 ግራም ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
ወይም “በቅዱሱ ሰቅል።”
ወይም “የሚወዘወዝ መባ።”
አንድ ስንዝር 22.2 ሴንቲ ሜትር ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
ወይም “ቅዱሱን ዘውድ።”
ወይም “መጋረጃ።”
ወይም “መጋረጃ።”
ወይም “መጋረጃም።”
ወይም “መጋረጃ።”
ወይም “መጋረጃ።”
ወይም “መጋረጃ።”