የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
የኢትዮጵያ ምልክት ቋንቋ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • nwt ዘሌዋውያን 1:1-27:34
  • ዘሌዋውያን

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ዘሌዋውያን
  • አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ
አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ
ዘሌዋውያን

ዘሌዋውያን

1 ይሖዋም ሙሴን ጠርቶ ከመገናኛ ድንኳኑ+ እንዲህ ሲል አናገረው፦ 2 “እስራኤላውያንን* አናግራቸው፤ እንዲህም በላቸው፦ ‘ከእናንተ መካከል ማንኛችሁም ከቤት እንስሳት ለይሖዋ መባ ማቅረብ ከፈለጋችሁ መባችሁን ከከብቶች ወይም ከመንጎች መካከል ማቅረብ አለባችሁ።+

3 “‘የሰውየው መባ ከከብቶች መካከል ተወስዶ የሚቀርብ የሚቃጠል መባ ከሆነ እንከን የሌለበትን ተባዕት እንስሳ ማቅረብ ይኖርበታል።+ መባውን በራሱ ፈቃድ ተነሳስቶ+ በመገናኛ ድንኳኑ መግቢያ ላይ በይሖዋ ፊት ማቅረብ ይኖርበታል። 4 ለሚቃጠል መባ በሚቀርበው እንስሳ ራስ ላይ እጁን ይጫን፤ መባውም ለሰውየው ማስተሰረያ ይሆን ዘንድ ተቀባይነት ያገኛል።

5 “‘ከዚያም ወይፈኑ በይሖዋ ፊት ይታረድ፤ ካህናት+ የሆኑት የአሮን ወንዶች ልጆችም ደሙን ያቅርቡት፤ እንዲሁም ደሙን በመገናኛ ድንኳኑ መግቢያ ላይ በሚገኘው መሠዊያ ጎኖች ሁሉ ላይ ይርጩት።+ 6 የሚቃጠለውም መባ መገፈፍና መቆራረጥ ይኖርበታል።+ 7 ካህናት የሆኑት የአሮን ወንዶች ልጆችም በመሠዊያው ላይ እሳት ያንድዱ፤+ በእሳቱም ላይ እንጨት ይረብርቡበት። 8 እነሱም ተቆራርጦ የተዘጋጀውን መባ+ ከጭንቅላቱና ከሞራው* ጋር በመሠዊያው ላይ ባለው እሳት ላይ በሚገኘው እንጨት ላይ ይደርድሩት። 9 ሆድ ዕቃውና እግሮቹም በውኃ ይታጠቡ፤ ካህኑም የሚቃጠል መባ ይኸውም ይሖዋን ደስ የሚያሰኝ* መዓዛ ያለው በእሳት የሚቀርብ መባ አድርጎ ሙሉውን በመሠዊያው ላይ ያጭሰው።+

10 “‘ሰውየው የሚቃጠል መባ እንዲሆን የሚያቀርበው መባ ከመንጋው+ ማለትም ከበግ ጠቦቶቹ ወይም ከፍየሎቹ መካከል የተወሰደ ከሆነ እንከን የሌለበትን ተባዕት ያቅርብ።+ 11 በስተ ሰሜን በኩል ባለው የመሠዊያው ጎን በይሖዋ ፊት ይታረድ፤ ካህናት የሆኑት የአሮን ወንዶች ልጆችም ደሙን በመሠዊያው ጎኖች ሁሉ ላይ ይርጩት።+ 12 እሱም ጭንቅላቱንና ሞራውን* ጨምሮ እንስሳውን በየብልቱ ይቆራርጠዋል፤ ካህኑም በመሠዊያው ላይ ባለው እሳት ላይ በሚገኘው እንጨት ላይ ይደረድራቸዋል። 13 ሆድ ዕቃውንና እግሮቹንም በውኃ ያጥባቸዋል፤ ካህኑም ሙሉውን ያቀርበዋል፤ እንዲሁም በመሠዊያው ላይ እንዲጨስ ያደርገዋል። ይህም የሚቃጠል መባ ማለትም ይሖዋን ደስ የሚያሰኝ* መዓዛ ያለው በእሳት የሚቀርብ መባ ነው።

14 “‘ሆኖም ሰውየው አእዋፋትን ለይሖዋ የሚቃጠል መባ አድርጎ የሚያቀርብ ከሆነ መባውን ከዋኖሶች ወይም ከርግብ ጫጩቶች መካከል ያቀርባል።+ 15 ካህኑም በመሠዊያው ላይ ያቀርበዋል፤ እንዲሁም አንገቱ ላይ ቦጭቆ በመሠዊያው ላይ እንዲጨስ ያደርገዋል። ደሙ ግን በመሠዊያው ጎን ይንጠፍጠፍ። 16 ቋቱንና ላባዎቹንም ከለየ በኋላ ከመሠዊያው አጠገብ በስተ ምሥራቅ በኩል ወዳለው አመድ* ወደሚደፋበት ቦታ ይወርውራቸው።+ 17 ሙሉ በሙሉ ለሁለት ሳይለያየው ክንፎቹን ይዞ ይሰነጥቀዋል። ከዚያም ካህኑ በመሠዊያው ላይ ይኸውም በእሳቱ ላይ ባለው እንጨት ላይ እንዲጨስ ያደርገዋል። ይህም የሚቃጠል መባ ማለትም ይሖዋን ደስ የሚያሰኝ* መዓዛ ያለው በእሳት የሚቀርብ መባ ነው።

2 “‘አንድ ሰው* ለይሖዋ የእህል መባ+ የሚያቀርብ ከሆነ መባው የላመ ዱቄት መሆን አለበት፤ በላዩም ላይ ዘይት ያፍስበት፤ ነጭ ዕጣንም ያስቀምጥበት።+ 2 ከዚያም ካህናት ወደሆኑት የአሮን ወንዶች ልጆች ያመጣዋል፤ ካህኑም ከላዩ ላይ አንድ እፍኝ የላመ ዱቄትና ዘይት፣ ነጭ ዕጣኑንም በሙሉ ይወስዳል፤ ይህንም አምላክ መላውን መባ እንዲያስበው የሚያደርግ መባ+ ይኸውም ይሖዋን ደስ የሚያሰኝ* መዓዛ ያለው በእሳት የሚቀርብ መባ አድርጎ በመሠዊያው ላይ ያጨሰዋል። 3 ከእህል መባው የተረፈው ማንኛውም ነገር የአሮንና የወንዶች ልጆቹ ነው፤+ ይህም ለይሖዋ በእሳት ከሚቀርቡት መባዎች የተረፈ ስለሆነ እጅግ ቅዱስ ነው።+

4 “‘በመጋገሪያ ምድጃ የተጋገረ የእህል መባ የምታቀርብ ከሆነ ከላመ ዱቄት በዘይት ተለውሶ የተጋገረ እርሾ ያልገባበት የቀለበት ቅርጽ ያለው ዳቦ ወይም ዘይት የተቀባ ስስ ቂጣ* መሆን ይኖርበታል።+

5 “‘መባህ በምጣድ የተጋገረ የእህል መባ+ ከሆነ በዘይት ከተለወሰ እርሾ ያልገባበት የላመ ዱቄት የተጋገረ መሆን ይኖርበታል። 6 መቆራረስ አለበት፤ ዘይትም አፍስበት።+ ይህ የእህል መባ ነው።

7 “‘መባህ በድስት የተዘጋጀ የእህል መባ ከሆነ ከላመ ዱቄትና ከዘይት የተሠራ መሆን ይኖርበታል። 8 ከእነዚህ ነገሮች የተዘጋጀውን የእህል መባ ወደ ይሖዋ ማምጣት ይኖርብሃል፤ ወደ መሠዊያው ለሚያቀርበውም ካህን ይሰጠው። 9 ካህኑም አምላክ መላውን መባ እንዲያስበው የሚያደርግ መባ+ እንዲሆን ከእህል መባው ላይ የተወሰነውን በማንሳት ይሖዋን ደስ የሚያሰኝ* መዓዛ ያለው በእሳት የሚቀርብ መባ አድርጎ በመሠዊያው ላይ ያጨሰዋል።+ 10 ከእህል መባው የተረፈው የአሮንና የወንዶች ልጆቹ ነው፤ ይህም ለይሖዋ በእሳት ከሚቀርቡት መባዎች የተረፈ ስለሆነ እጅግ ቅዱስ ነው።+

11 “‘እርሾ ወይም ማር ለይሖዋ በእሳት የሚቀርብ መባ አድርጋችሁ ማጨስ ስለሌለባችሁ ለይሖዋ ከምታቀርቡት የእህል መባ ውስጥ እርሾ የገባበት ምንም ነገር አይኑር።+

12 “‘እነዚህንም የፍሬ በኩራት መባ+ አድርጋችሁ ለይሖዋ ልታቀርቧቸው ትችላላችሁ፤ ሆኖም ደስ እንደሚያሰኝ* መዓዛ ሆነው ወደ መሠዊያው መምጣት የለባቸውም።

13 “‘የምታቀርበው የእህል መባ በሙሉ በጨው መቀመም አለበት፤ የአምላክህ የቃል ኪዳን ጨውም ከእህል መባህ ላይ አይጥፋ። ከማንኛውም መባህ ጋር ጨው አብረህ ታቀርባለህ።+

14 “‘መጀመሪያ የደረሰውን ፍሬ የእህል መባ አድርገህ ለይሖዋ የምታቀርብ ከሆነ የደረሰውን ሆኖም ገና እሸት የሆነውን በእሳት የተጠበሰና የተከካ እህል መጀመሪያ ላይ እንደደረሰው ፍሬህ የእህል መባ አድርገህ አቅርብ።+ 15 በላዩም ላይ ዘይት ትጨምርበታለህ፤ ነጭ ዕጣንም ታስቀምጥበታለህ። ይህ የእህል መባ ነው። 16 ካህኑም ከተከካው እህልና ከዘይቱ የተወሰነውን፣ ነጭ ዕጣኑንም በሙሉ ወስዶ አምላክ መላውን መባ እንዲያስበው የሚያደርግ መባ+ ይኸውም ለይሖዋ በእሳት የሚቀርብ መባ አድርጎ ያጨሰዋል።

3 “‘አንድ ሰው የሚያቀርበው መባ የኅብረት መሥዋዕት*+ ቢሆንና ከከብቶች መካከል ወስዶ የሚያቀርብ ከሆነ እንስሳው ተባዕትም ሆነ እንስት እንከን የሌለበትን በይሖዋ ፊት ማቅረብ ይኖርበታል። 2 እሱም መባ አድርጎ በሚያቀርበው እንስሳ ራስ ላይ እጁን ይጭናል፤ እንስሳውም በመገናኛ ድንኳኑ መግቢያ ላይ ይታረዳል፤ ካህናት የሆኑት የአሮን ወንዶች ልጆችም ደሙን በመሠዊያው ጎኖች ሁሉ ላይ ይረጩታል። 3 እሱም ከኅብረት መሥዋዕቱ ላይ የተወሰነውን ለይሖዋ በእሳት የሚቃጠል መባ አድርጎ ያቀርበዋል፤+ ይኸውም አንጀቱን የሸፈነውን ስብ፣+ በአንጀቱ ዙሪያ ያለውን ስብ በሙሉ፣ 4 ሁለቱን ኩላሊቶችና በእነሱ ላይ ማለትም በሽንጡ አካባቢ ያለውን ስብ ያቀርባል። በጉበቱ ላይ ያለውንም ሞራ ከኩላሊቶቹ ጋር አብሮ ያነሳዋል።+ 5 የአሮን ወንዶች ልጆችም በመሠዊያው ላይ ይኸውም በእሳቱ ላይ ባለው እንጨት ላይ በሚገኘው የሚቃጠል መባ ላይ ያጨሱታል፤+ ይህም ይሖዋን ደስ የሚያሰኝ* መዓዛ ያለው በእሳት የሚቀርብ መባ ነው።+

6 “‘ለይሖዋ የኅብረት መሥዋዕት አድርጎ የሚያቀርበው መባ ከመንጋው መካከል የተወሰደ ከሆነ እንስሳው ተባዕትም ሆነ እንስት እንከን የሌለበትን ያቀርባል።+ 7 የበግ ጠቦት መባ አድርጎ የሚያቀርብ ከሆነ ይሖዋ ፊት ያቀርበዋል። 8 እሱም መባ አድርጎ በሚያቀርበው እንስሳ ራስ ላይ እጁን ይጭናል፤ እንስሳውም በመገናኛ ድንኳኑ ፊት ለፊት ይታረዳል። የአሮን ወንዶች ልጆችም ደሙን በመሠዊያው ጎኖች ሁሉ ላይ ይረጩታል። 9 ከኅብረት መሥዋዕቱ ላይም ስቡን ለይሖዋ በእሳት የሚቃጠል መባ አድርጎ ያቀርባል።+ ከጀርባ አጥንቱ አጠገብ ያለውን ላት በሙሉ፣ አንጀቱን የሸፈነውን ስብ፣ በአንጀቱ ዙሪያ ያለውን ስብ በሙሉ ያነሳዋል፤ 10 ደግሞም ሁለቱን ኩላሊቶችና በእነሱ ላይ ማለትም በሽንጡ አካባቢ ያለውን ስብ ያነሳዋል። በጉበቱ ላይ ያለውንም ሞራ ከኩላሊቶቹ ጋር አብሮ ያነሳል።+ 11 ካህኑም እንደ ምግብ* ይኸውም ለይሖዋ በእሳት እንደሚቀርብ መባ አድርጎ በመሠዊያው ላይ ያጨሰዋል።+

12 “‘ፍየል መባ አድርጎ የሚያቀርብ ከሆነ ይሖዋ ፊት ያቀርበዋል። 13 እጁንም በራሱ ላይ ይጭንበታል፤ በመገናኛ ድንኳኑም ፊት ይታረዳል፤ የአሮን ወንዶች ልጆችም ደሙን በመሠዊያው ጎኖች ሁሉ ላይ ይርጩት። 14 ለይሖዋ በእሳት የሚቃጠል መባ አድርጎ የሚያቀርበውም እነዚህን ነው፦ አንጀቱን የሸፈነውን ስብ፣ በአንጀቱ ዙሪያ ያለውን ስብ በሙሉ፣+ 15 ሁለቱን ኩላሊቶችና በእነሱ ላይ ማለትም በሽንጡ አካባቢ ያለውን ስብ ያቀርባል። በጉበቱ ላይ ያለውንም ሞራ ከኩላሊቶቹ ጋር አብሮ ያነሳል። 16 ካህኑም እንደ ምግብ ይኸውም ደስ የሚያሰኝ* መዓዛ እንዳለው በእሳት የሚቀርብ መባ አድርጎ በመሠዊያው ላይ ያጨሳቸዋል። ስቡ ሁሉ የይሖዋ ነው።+

17 “‘ስብም ሆነ ደም+ ፈጽሞ አትብሉ። ይህም በምትኖሩበት ስፍራ ሁሉ ለእናንተም ሆነ ለትውልዶቻችሁ ዘላቂ ደንብ ነው።’”

4 ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ 2 “እስራኤላውያንን እንዲህ በላቸው፦ ‘አንድ ሰው* ይሖዋ መደረግ የለባቸውም ብሎ ካዘዛቸው ነገሮች መካከል አንዱን በመፈጸም ባለማወቅ+ ኃጢአት ቢሠራ እንዲህ መደረግ ይኖርበታል፦

3 “‘የተቀባው ካህን+ ኃጢአት+ ቢሠራና ሕዝቡ በደለኛ እንዲሆን ቢያደርግ ለፈጸመው ኃጢአት እንከን የሌለበትን ወይፈን የኃጢአት መባ አድርጎ ለይሖዋ ያቅርብ።+ 4 ወይፈኑን ወደ መገናኛ ድንኳኑ መግቢያ+ ወደ ይሖዋ ፊት ያመጣዋል፤ እጁንም በወይፈኑ ራስ ላይ ይጭናል፤ ወይፈኑንም በይሖዋ ፊት ያርደዋል።+ 5 ከዚያም የተቀባው ካህን+ ከወይፈኑ ደም የተወሰነ ወስዶ ወደ መገናኛ ድንኳኑ ይዞ ይገባል፤ 6 ካህኑም ጣቱን ደሙ ውስጥ ነክሮ+ ደሙን በቅዱሱ ስፍራ መጋረጃ ፊት ለፊት በይሖዋ ፊት ሰባት ጊዜ ይረጨዋል።+ 7 በተጨማሪም ካህኑ ከደሙ የተወሰነውን ወስዶ በመገናኛ ድንኳኑ ውስጥ በይሖዋ ፊት የሚገኘውን ጥሩ መዓዛ ያለው ዕጣን የሚቀርብበትን መሠዊያ ቀንዶች ይቀባል፤+ ከዚያም የተረፈውን የወይፈኑን ደም በሙሉ በመገናኛ ድንኳኑ መግቢያ ላይ በሚገኘው የሚቃጠል መባ በሚቀርብበት መሠዊያ ሥር ያፈሰዋል።+

8 “‘ከዚያም አንጀቱን የሸፈነውን ስብና በአንጀቱ ዙሪያ ያለውን ስብ ጨምሮ ለኃጢአት መባ የቀረበውን ወይፈን ስብ በሙሉ ከላዩ ላይ ያነሳል፤ 9 እንዲሁም ሁለቱን ኩላሊቶችና በላያቸው ላይ ያለውን በሽንጡ አካባቢ የሚገኝ ስብ ያነሳል። በጉበቱ ላይ ያለውንም ሞራ ከኩላሊቶቹ ጋር አብሮ ያነሳል።+ 10 ይህም ለኅብረት መሥዋዕት+ ከሚቀርበው በሬ ላይ ከሚነሳው ጋር ተመሳሳይ ይሆናል። ካህኑም የሚቃጠል መባ በሚቀርብበት መሠዊያ ላይ እንዲጨሱ ያደርጋል።

11 “‘ሆኖም የወይፈኑን ቆዳ እንዲሁም ሥጋውን በሙሉ ከጭንቅላቱ፣ ከእግሮቹ፣ ከሆድ ዕቃውና ከፈርሱ ጋር+ 12 እንዲሁም ከወይፈኑ የቀረውን በሙሉ ከሰፈሩ ውጭ ወዳለው አመድ* ወደሚደፋበት ንጹሕ የሆነ ቦታ ይወስደዋል፤ በእሳቱ ላይ ባለው እንጨት ላይ አድርጎም ያቃጥለዋል።+ አመዱ በሚደፋበት ቦታ ላይ ይቃጠል።

13 “‘መላው የእስራኤል ማኅበረሰብ ባለማወቅ ኃጢአት በመሥራቱ በደለኛ ቢሆንና+ ጉባኤው ግን ይሖዋ አታድርጉ ብሎ ካዘዛቸው ነገሮች መካከል አንዱን መፈጸሙን ባይገነዘብ፣+ 14 በኋላም ኃጢአቱ ቢታወቅ ጉባኤው ለኃጢአት መባ የሚሆን ወይፈን ያቅርብ፤ ወደ መገናኛ ድንኳኑም ፊት ያምጣው። 15 የማኅበረሰቡ ሽማግሌዎች በይሖዋ ፊት እጃቸውን በወይፈኑ ራስ ላይ ይጭናሉ፤ ወይፈኑም በይሖዋ ፊት ይታረዳል።

16 “‘ከዚያም የተቀባው ካህን ከወይፈኑ ደም የተወሰነ ወስዶ ወደ መገናኛ ድንኳኑ ይዞ ይገባል። 17 ካህኑም ጣቱን ደሙ ውስጥ ነክሮ የተወሰነውን በመጋረጃው ፊት ለፊት በይሖዋ ፊት ሰባት ጊዜ ይረጨዋል።+ 18 የተወሰነውንም ደም ወስዶ በመገናኛ ድንኳኑ ውስጥ በይሖዋ ፊት የሚገኘውን መሠዊያ ቀንዶች ይቀባል፤+ ከዚያም የተረፈውን ደም በሙሉ በመገናኛ ድንኳኑ መግቢያ ላይ በሚገኘው የሚቃጠል መባ በሚቀርብበት መሠዊያ ሥር ያፈሰዋል።+ 19 ስቡንም በሙሉ አንስቶ በመሠዊያው ላይ እንዲጨስ ያደርገዋል።+ 20 በወይፈኑ ላይ ለኃጢአት መባ እንዲሆን በቀረበው በሌላኛው ወይፈን ላይ እንዳደረገው ሁሉ ያደርጋል። በዚህኛውም ላይ የሚያደርገው ይህንኑ ይሆናል፤ ካህኑም ለእነሱ ያስተሰርይላቸዋል፤+ እነሱም ይቅር ይባላሉ። 21 ወይፈኑንም ከሰፈሩ ውጭ እንዲወሰድ ካደረገ በኋላ ልክ የመጀመሪያውን ወይፈን እንዳቃጠለው ሁሉ ይሄኛውንም ያቃጥለዋል።+ ይህ ስለ ጉባኤው የሚቀርብ የኃጢአት መባ ነው።+

22 “‘አንድ አለቃ+ አምላኩ ይሖዋ መደረግ የለባቸውም ብሎ ካዘዛቸው ነገሮች መካከል አንዱን በመፈጸም ባለማወቅ ኃጢአት ሠርቶ በደለኛ ቢሆን 23 ወይም ትእዛዙን በመተላለፍ ኃጢአት እንደሠራ ቢያውቅ እንከን የሌለበትን ተባዕት የፍየል ጠቦት መባ አድርጎ ያምጣ። 24 እጁንም በፍየል ጠቦቱ ራስ ላይ ይጭናል፤ እንዲሁም የሚቃጠለው መባ በይሖዋ ፊት ዘወትር በሚታረድበት ስፍራ ያርደዋል።+ ይህ የኃጢአት መባ ነው። 25 ካህኑም ለኃጢአት መባ ከቀረበው እንስሳ ደም ላይ የተወሰነውን በጣቱ ወስዶ የሚቃጠል መባ የሚቀርብበትን መሠዊያ ቀንዶች ይቀባል፤+ ከዚያም የተረፈውን ደሙን የሚቃጠል መባ በሚቀርብበት መሠዊያ ሥር ያፈሳል።+ 26 ስቡንም በሙሉ ልክ እንደ ኅብረት መሥዋዕቱ ስብ በመሠዊያው ላይ እንዲጨስ ያደርጋል፤+ ካህኑም የእሱን ኃጢአት ያስተሰርይለታል፤ ኃጢአቱም ይቅር ይባልለታል።

27 “‘በምድሩ ከሚኖሩ ሕዝቦች መካከል ማንኛውም ሰው* ይሖዋ መደረግ የለባቸውም ብሎ ካዘዛቸው ነገሮች መካከል አንዱን በመፈጸም ባለማወቅ ኃጢአት ቢሠራና በደለኛ ቢሆን፣+ 28 በኋላም የሠራውን ኃጢአት ቢያውቅ ለፈጸመው ኃጢአት እንከን የሌለባትን እንስት የፍየል ጠቦት መባ አድርጎ ያምጣ። 29 እጁንም ለኃጢአት መባ በቀረበችው እንስሳ ራስ ላይ ይጭናል፤ እንዲሁም ለኃጢአት መባ የቀረበችውን እንስሳ የሚቃጠለው መባ በሚታረድበት ስፍራ ያርዳታል።+ 30 ካህኑም ከደሙ የተወሰነውን በጣቱ ወስዶ የሚቃጠል መባ የሚቀርብበትን መሠዊያ ቀንዶች ይቀባል፤ ከዚያም የተረፈውን ደሙን በሙሉ በመሠዊያው ሥር ያፈሰዋል።+ 31 ከኅብረት መሥዋዕቱ ላይ ስቡ+ እንደሚነሳ ሁሉ ከዚህ ላይም ስቡን በሙሉ ያነሳዋል፤+ ካህኑም ስቡ ይሖዋን ደስ የሚያሰኝ* መዓዛ እንዲሰጥ በመሠዊያው ላይ ያጨሰዋል፤ ካህኑም ያስተሰርይለታል፤ ኃጢአቱም ይቅር ይባልለታል።

32 “‘ሆኖም የኃጢአት መባ አድርጎ የሚያቀርበው የበግ ጠቦት ከሆነ እንከን የሌለባትን እንስት የበግ ጠቦት ማምጣት አለበት። 33 እጁንም ለኃጢአት መባ በቀረበችው እንስሳ ራስ ላይ ይጭናል፤ እንዲሁም እንስሳዋን የሚቃጠለው መባ በሚታረድበት ስፍራ የኃጢአት መባ አድርጎ ያርዳታል።+ 34 ካህኑም ለኃጢአት መባ ከቀረበችው እንስሳ ደም ላይ የተወሰነውን በጣቱ ወስዶ የሚቃጠል መባ የሚቀርብበትን መሠዊያ ቀንዶች ይቀባል፤+ ከዚያም የተረፈውን ደሙን በሙሉ በመሠዊያው ሥር ያፈሰዋል። 35 የኅብረት መሥዋዕት ሆኖ ከሚቀርበው የበግ ጠቦት ላይ ስቡ እንደሚነሳ ሁሉ ከዚህ ላይም ስቡን በሙሉ ያነሳዋል፤ እሱም በመሠዊያው ላይ ባሉት ለይሖዋ በእሳት በሚቀርቡት መባዎች ላይ እንዲጨሱ ያደርጋል።+ ካህኑም ሰውየው የሠራውን ኃጢአት ያስተሰርይለታል፤ ኃጢአቱም ይቅር ይባልለታል።+

5 “‘አንድ ሰው* ሰዎች የምሥክርነት ቃል እንዲሰጡ ጥሪ+ እየቀረበ መሆኑን ቢሰማና* እሱ መመሥከር እየቻለ ወይም ደግሞ ጉዳዩን አይቶ አሊያም አውቆ ሳለ ሳይናገር ቢቀር በሠራው ጥፋት ይጠየቅበታል።

2 “‘ወይም አንድ ሰው* ርኩስ የሆነን ማንኛውንም ነገር ይኸውም ርኩስ የሆነን የዱር አውሬ ወይም ርኩስ የሆነን የቤት እንስሳ አሊያም ርኩስ የሆነን የሚርመሰመስ ፍጥረት በድን ቢነካ፣+ ይህን ያደረገው ባለማወቅ ቢሆንም እንኳ ይህ ሰው ርኩስ ነው፤ በደለኛም ይሆናል። 3 ወይም አንድ ሰው ባለማወቅ የሰውን ርኩሰት+ ይኸውም እንዲረክስ ሊያደርገው የሚችለውን ማንኛውንም ርኩስ ነገር ቢነካና በኋላም ይህን ቢያውቅ በደለኛ ይሆናል።

4 “‘አሊያም ደግሞ አንድ ሰው* ነገሩ ምንም ሆነ ምን ክፉ ወይም መልካም ለማድረግ በችኮላ ቢምልና ይህን ያደረገው ባለማወቅ ቢሆን ሆኖም የማለው በችኮላ መሆኑን በኋላ ላይ ቢገነዘብ በደለኛ ይሆናል።*+

5 “‘ከእነዚህ ነገሮች በአንዱ በደለኛ ሆኖ ቢገኝ በምን መንገድ ኃጢአት እንደሠራ መናዘዝ+ አለበት። 6 ለሠራው ኃጢአት የበደል መባ+ ማለትም ከመንጋው መካከል እንስት የበግ ጠቦት ወይም እንስት የፍየል ግልገል የኃጢአት መባ አድርጎ ለይሖዋ ያመጣል። ከዚያም ካህኑ ኃጢአቱን ያስተሰርይለታል።

7 “‘በግ ለማምጣት አቅሙ የማይፈቅድለት ከሆነ ግን ለሠራው ኃጢአት የበደል መባ እንዲሆኑ ሁለት ዋኖሶችን ወይም ሁለት የርግብ ጫጩቶችን ለይሖዋ ያምጣ፤+ አንዱ ለኃጢአት መባ ሌላኛው ደግሞ ለሚቃጠል መባ ይሆናል።+ 8 ወደ ካህኑም ያመጣቸዋል፤ ካህኑም በቅድሚያ ለኃጢአት መባ የሚሆነውን ያቀርባል፤ አንገቱን ሙሉ በሙሉ ሳይቆርጥ ከፊት በኩል አንገቱን በመቦጨቅ ያቀርበዋል። 9 ከኃጢአት መባው ደም ላይ የተወሰነውን በመሠዊያው ጎን ላይ ይረጨዋል፤ የተረፈው ደም ግን በመሠዊያው ሥር ይንጠፈጠፋል።+ ይህ የኃጢአት መባ ነው። 10 ሌላኛውን ደግሞ በተለመደው አሠራር መሠረት የሚቃጠል መባ አድርጎ ያቀርበዋል፤+ ካህኑም ለሠራው ኃጢአት ማስተሰረያ ያቀርብለታል፤ ኃጢአቱም ይቅር ይባልለታል።+

11 “‘ሁለት ዋኖሶች ወይም ሁለት የርግብ ጫጩቶች ለማምጣት አቅሙ የማይፈቅድለት ከሆነ ደግሞ ለሠራው ኃጢአት፣ የኃጢአት መባ እንዲሆን አንድ አሥረኛ ኢፍ*+ የላመ ዱቄት መባ አድርጎ ያምጣ። የኃጢአት መባ ስለሆነ ዘይት አይጨምርበት ወይም ነጭ ዕጣን አያድርግበት። 12 ወደ ካህኑም ያመጣዋል፤ ካህኑም አምላክ መላውን መባ እንዲያስበው ለማድረግ ከላዩ ላይ አንድ እፍኝ አንስቶ በመሠዊያው ላይ ባሉት ለይሖዋ በእሳት በሚቀርቡት መባዎች ላይ እንዲጨስ ያደርጋል። ይህ የኃጢአት መባ ነው። 13 ካህኑም ሰውየው ከእነዚህ ኃጢአቶች ውስጥ ለሠራው ለየትኛውም ኃጢአት ማስተሰረያ ያቀርብለታል፤ ኃጢአቱም ይቅር ይባልለታል።+ እንደ እህል መባው+ ሁሉ ከመባው የተረፈውም የካህኑ ይሆናል።’”+

14 ይሖዋም ሙሴን እንዲህ አለው፦ 15 “አንድ ሰው* ለይሖዋ በተቀደሱት ነገሮች ላይ ባለማወቅ ኃጢአት በመሥራት ታማኝነቱን ቢያጎድል+ ከመንጋው መካከል እንከን የሌለበትን አውራ በግ የበደል መባ አድርጎ ለይሖዋ ያመጣል፤+ ዋጋው በብር ሰቅል* የሚተመነው እንደ ቋሚ መለኪያ ሆኖ በሚያገለግለው በቅዱሱ ስፍራ ሰቅል* መሠረት ነው።+ 16 በቅዱሱ ስፍራ ላይ ለፈጸመው ኃጢአት ካሳ ይከፍላል፤ የዋጋውንም አንድ አምስተኛ ይጨምርበታል።+ ካህኑ ለበደል መባ በቀረበው አውራ በግ አማካኝነት እንዲያስተሰርይለትም ለካህኑ ይሰጠዋል፤+ ኃጢአቱም ይቅር ይባልለታል።+

17 “አንድ ሰው* ይሖዋ እንዳይደረጉ ብሎ ካዘዛቸው ነገሮች መካከል አንዱን በመፈጸም ኃጢአት ቢሠራ፣ እንዲህ ያደረገው ባለማወቅ ቢሆንም እንኳ በደለኛ ይሆናል፤ በሠራውም ጥፋት ይጠየቅበታል።+ 18 የበደል መባ እንዲሆንም የተተመነለትን ዋጋ ያህል የሚያወጣ እንከን የሌለበት አውራ በግ ከመንጋው መካከል ወስዶ ለካህኑ ያምጣ።+ ከዚያም ካህኑ፣ ሰውየው ባለማወቅ ለፈጸመው ስህተት ያስተሰርይለታል፤ ኃጢአቱም ይቅር ይባልለታል። 19 ይህ የበደል መባ ነው። በይሖዋ ላይ ኃጢአት ስለፈጸመ በእርግጥ በደለኛ ይሆናል።”

6 ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ 2 “አንድ ሰው* በአደራ እንዲይዝ ወይም እንዲያስቀምጥ ከተሰጠው ነገር ጋር በተያያዘ+ ባልንጀራውን በማታለል ኃጢአት ቢሠራና በይሖዋ ላይ ታማኝነት የማጉደል ተግባር ቢፈጽም+ አሊያም ባልንጀራውን ቢሰርቅ ወይም ቢያጭበረብር 3 አሊያም ደግሞ የጠፋ ነገር አግኝቶ አላየሁም ብሎ ቢዋሽና ሰውየው ከእነዚህ ኃጢአቶች መካከል አንዱንም እንዳልሠራ አድርጎ በሐሰት ቢምል+ እንዲህ ማድረግ አለበት፦ 4 ኃጢአት ቢሠራና በደለኛ ሆኖ ቢገኝ የሰረቀውን፣ ቀምቶ ወይም አጭበርብሮ የወሰደውን አሊያም በአደራ ተሰጥቶት የነበረውን ወይም ደግሞ ጠፍቶ ያገኘውን ነገር ይመልስ፤ 5 አሊያም በሐሰት የማለበትን ማንኛውንም ነገር ይመልስ፤ ሙሉ ካሳ ይክፈል፤+ የዋጋውንም አንድ አምስተኛ ይጨምርበት። በደለኛ መሆኑ በተረጋገጠበትም ዕለት ለባለቤቱ ይሰጠዋል። 6 በተተመነውም ዋጋ መሠረት እንከን የሌለበትን አውራ በግ ከመንጋው መካከል በመውሰድ የበደል መባው አድርጎ ለይሖዋ ለማቅረብ ወደ ካህኑ ያመጣዋል።+ 7 ካህኑም በይሖዋ ፊት ያስተሰርይለታል፤ እሱም በደለኛ እንዲሆን ያደረገው ማንኛውም ነገር ይቅር ይባልለታል።”+

8 ይሖዋም ሙሴን እንዲህ አለው፦ 9 “አሮንንና ወንዶች ልጆቹን እንዲህ ብለህ እዘዛቸው፦ ‘የሚቃጠል መባ ሕግ ይህ ነው፦+ የሚቃጠለው መባ ሌሊቱን ሙሉ እስኪነጋ ድረስ በመሠዊያው ላይ ባለው ማንደጃ ላይ ይቀመጣል፤ እሳቱም በመሠዊያው ላይ ሲነድ ያድራል። 10 ካህኑ ከበፍታ የተሠራውን የክህነት ልብሱን+ ይለብሳል፤ እርቃኑንም ለመሸፈን ከበፍታ የተሠራውን ቁምጣ+ ያደርጋል። ከዚያም በመሠዊያው ላይ ከነበረው በእሳት ከነደደው የሚቃጠል መባ የወጣውን አመድ*+ ያነሳል፤ በመሠዊያውም ጎን ያደርገዋል። 11 ከዚያም ልብሱን አውልቆ+ ሌላ ልብስ ይለብሳል፤ አመዱንም ከሰፈሩ ውጭ ወደሚገኝ ንጹሕ የሆነ ቦታ ይወስደዋል።+ 12 እሳቱ በመሠዊያው ላይ ዘወትር ይነድዳል። መጥፋትም የለበትም። ካህኑም በየማለዳው እንጨት ይማግድበት፤+ በላዩም ላይ የሚቃጠለውን መባ ይረብርብበት፤ የኅብረት መሥዋዕቶቹንም ስብ በላዩ ላይ ያጨስበታል።+ 13 በመሠዊያውም ላይ ያለማቋረጥ እሳት ይነድዳል። መጥፋትም የለበትም።

14 “‘የእህል መባ ሕግ ደግሞ ይህ ነው፦+ እናንተ የአሮን ወንዶች ልጆች በመሠዊያው ፊት ለፊት በይሖዋ ፊት ታቀርቡታላችሁ። 15 ከመካከላቸው አንዱ ለእህል መባ ከቀረበው የላመ ዱቄት ላይ ከነዘይቱ አንድ እፍኝ ያነሳል፤ እንዲሁም በእህል መባው ላይ ያለውን ነጭ ዕጣን በሙሉ ይወስዳል። አምላክ መላውን መባ እንዲያስበውም ለይሖዋ ደስ የሚያሰኝ* መዓዛ አድርጎ በመሠዊያው ላይ ያጨሰዋል።+ 16 ከዚያ የተረፈውን አሮንና ወንዶች ልጆቹ ይበሉታል፤+ እንደ ቂጣ ተጋግሮ በቅዱስ ስፍራ ይበላል። በመገናኛ ድንኳኑ ግቢ ውስጥ ይበሉታል።+ 17 ያለእርሾ መጋገር አለበት።+ ለእኔ በእሳት ከሚቀርቡልኝ መባዎች ውስጥ ይህን ድርሻቸው አድርጌ ሰጥቻቸዋለሁ።+ እንደ ኃጢአት መባና እንደ በደል መባ ሁሉ ይህም እጅግ ቅዱስ ነገር ነው።+ 18 የአሮን ዘር የሆኑ ወንዶች ሁሉ ይበሉታል።+ ይህ ለይሖዋ በእሳት ከሚቀርቡ መባዎች ውስጥ በትውልዶቻችሁ ሁሉ ለእነሱ የሚሰጥ ዘላለማዊ ድርሻ ነው።+ የሚነካቸውም* ነገር ሁሉ ቅዱስ ይሆናል።’”

19 ይሖዋም በድጋሚ ሙሴን እንዲህ አለው፦ 20 “አሮን በሚቀባበት+ ቀን እሱና ወንዶች ልጆቹ ለይሖዋ የሚያቀርቡት መባ ይህ ነው፦ የኢፍ አንድ አሥረኛ*+ የላመ ዱቄት በቋሚነት የሚቀርብ የእህል መባ አድርገው ያቅርቡ፤+ ግማሹን ጠዋት፣ ግማሹን ደግሞ ምሽት ላይ ያቅርቡ። 21 በዘይት ከተለወሰ በኋላም በምጣድ ላይ ይጋገራል።+ ከዚያም በደንብ በዘይት ለውሰህ ታመጣዋለህ፤ የተጋገረውንም የእህል መባ ቆራርሰህ ደስ የሚያሰኝ* መዓዛ ይሆን ዘንድ ለይሖዋ ታቀርበዋለህ። 22 ከወንዶች ልጆቹ መካከል እሱን የሚተካው የተቀባው ካህንም ያቀርበዋል።+ ሙሉ በሙሉ የሚቀርብ መባም ሆኖ ለይሖዋ እንዲጨስ ይደረጋል፤ ይህም ዘላቂ ሥርዓት ነው። 23 አንድ ካህን የሚያቀርበው እያንዳንዱ የእህል መባ ሙሉ በሙሉ መቃጠል ይኖርበታል። መበላት የለበትም።”

24 ይሖዋ በድጋሚ ሙሴን እንዲህ አለው፦ 25 “አሮንንና ወንዶች ልጆቹን እንዲህ በላቸው፦ ‘የኃጢአት መባ ሕግ ይህ ነው፦+ ለኃጢአት መባ የሚሆነውም እንስሳ፣ ለሚቃጠል መባ የሚሆነው እንስሳ በሚታረድበት ቦታ+ በይሖዋ ፊት ይታረዳል። ይህ እጅግ ቅዱስ የሆነ ነገር ነው። 26 ይህን ለኃጢአት መሥዋዕት አድርጎ የሚያቀርበው ካህን ይበላዋል።+ በመገናኛ ድንኳኑ ግቢ ውስጥ ቅዱስ በሆነ ስፍራ ይበላል።+

27 “‘ሥጋውን የሚነካ ማንኛውም ነገር ቅዱስ ይሆናል፤ ማንም ሰው የእንስሳውን ደም በልብሱ ላይ ቢረጭ ደም የተረጨበትን ልብስ በቅዱስ ስፍራ እጠበው። 28 ሥጋው የተቀቀለበት የሸክላ ዕቃም መሰባበር አለበት። የተቀቀለው ከመዳብ በተሠራ ዕቃ ከሆነ ግን ዕቃው ፍትግ ተደርጎ በውኃ መታጠብ አለበት።

29 “‘ካህን የሆነ ወንድ ሁሉ ይበላዋል።+ እጅግ ቅዱስ የሆነ ነገር ነው።+ 30 ይሁን እንጂ በቅዱሱ ስፍራ ለማስተሰረያ እንዲሆን ደሙ ወደ መገናኛ ድንኳኑ የገባ የኃጢአት መባ መበላት የለበትም።+ በእሳት መቃጠል አለበት።

7 “‘የበደል መባ ሕግ ይህ ነው፦+ ይህ እጅግ የተቀደሰ ነገር ነው። 2 ለበደል መባ የሚሆነውን እንስሳ፣ ለሚቃጠል መባ የሚሆነውን እንስሳ በሚያርዱበት ቦታ ያርዱታል፤ ደሙም+ በመሠዊያው ጎኖች ሁሉ ላይ መረጨት ይኖርበታል።+ 3 ስቡን በሙሉ ይኸውም ላቱን፣ አንጀቱን የሸፈነውን ስብ፣+ 4 ሁለቱን ኩላሊቶች፣ በሽንጡ አካባቢ ካለው ስባቸው ጋር ያቅርብ። በጉበቱ ላይ ያለውንም ሞራ ከኩላሊቶቹ ጋር አብሮ ያነሳዋል።+ 5 ካህኑ ለይሖዋ በእሳት የሚቀርብ መባ አድርጎ በመሠዊያው ላይ ያጨሳቸዋል።+ ይህ የበደል መባ ነው። 6 ካህን የሆነ ወንድ ሁሉ ይበላዋል፤+ ቅዱስ በሆነ ስፍራም መበላት ይኖርበታል። ይህ እጅግ የተቀደሰ ነገር ነው።+ 7 ስለ ኃጢአት መባው የወጣው ሕግ ለበደል መባውም ይሠራል፤ መባውም በመባው ለሚያስተሰርየው ካህን ይሆናል።+

8 “‘ካህኑ ለአንድ ሰው የሚቃጠል መባ በሚያቀርብበት ጊዜ የሚቃጠል መባ ሆኖ ለካህኑ የቀረበው እንስሳ ቆዳ+ የእሱ ይሆናል።

9 “‘በመጋገሪያ ምድጃ የተጋገረ ወይም በድስት የተዘጋጀ አሊያም በምጣድ የተጋገረ የእህል መባ+ ሁሉ መባውን ለሚያቀርበው ካህን ይሆናል። መባው የእሱ ይሆናል።+ 10 በዘይት የተለወሰው+ ወይም ደረቅ የሆነው+ የእህል መባ ግን ለአሮን ወንዶች ልጆች በሙሉ ይከፋፈላል፤ እያንዳንዳቸውም እኩል ድርሻ ይኖራቸዋል።

11 “‘አንድ ሰው ለይሖዋ የሚያቀርበውን የኅብረት መሥዋዕት+ በተመለከተ ደግሞ ሕጉ ይህ ነው፦ 12 ሰውየው መሥዋዕቱን የሚያቀርበው አመስጋኝነቱን ለመግለጽ+ ከሆነ ከምስጋና መሥዋዕቱ ጋር በዘይት ተለውሶ የተጋገረ እርሾ ያልገባበት የቀለበት ቅርጽ ያለው ዳቦ፣ ዘይት የተቀባ ስስ ቂጣና በዘይት በደንብ ከራሰና ከተለወሰ የላመ ዱቄት የተጋገረ የቀለበት ቅርጽ ያለው ዳቦ አብሮ ያቀርባል። 13 መባውንም እርሾ ገብቶባቸው ከተጋገሩ የቀለበት ቅርጽ ያላቸው ዳቦዎችና የምስጋና መሥዋዕት አድርጎ ከሚያቀርባቸው የኅብረት መሥዋዕቶች ጋር አብሮ ያቀርባል። 14 ከዚያም ላይ ከእያንዳንዱ መባ አንድ አንድ በማንሳት ለይሖዋ የተቀደሰ ድርሻ አድርጎ ያቀርባል፤ ይህም የኅብረት መሥዋዕቶቹን ደም ለሚረጨው ካህን ይሆናል።+ 15 የምስጋና መሥዋዕት እንዲሆኑ ያቀረባቸው የኅብረት መሥዋዕቶች ሥጋ፣ መሥዋዕቱን ባቀረበበት ቀን መበላት ይኖርበታል። ከዚያ ላይ ምንም ማስቀረትና ማሳደር የለበትም።+

16 “‘መባ አድርጎ የሚያቀርበው መሥዋዕት ስእለት+ ወይም የፈቃደኝነት መባ+ ከሆነ መሥዋዕቱን ባቀረበበት ቀን መበላት አለበት፤ የተረፈውም በማግስቱ ሊበላ ይችላል። 17 ለመሥዋዕት ከቀረበው ሥጋ ተርፎ እስከ ሦስተኛው ቀን የቆየው ግን በእሳት መቃጠል አለበት።+ 18 ይሁን እንጂ የኅብረት መሥዋዕት እንዲሆን ያቀረበው ማንኛውም ሥጋ በሦስተኛው ቀን ቢበላ መሥዋዕቱን ያቀረበው ሰው ተቀባይነት አያገኝም። ያደረገውም ነገር አይታሰብለትም፤ ይህ አስጸያፊ ነገር ነው፤ ከዚያም ላይ የበላው ሰው* ለፈጸመው ስህተት ይጠየቅበታል።+ 19 ርኩስ የሆነን ማንኛውንም ነገር የነካ ሥጋ መበላት የለበትም። በእሳት መቃጠል አለበት። ንጹሕ የሆነ ማንኛውም ሰው ንጹሕ የሆነውን ሥጋ ሊበላ ይችላል።

20 “‘ሆኖም ማንኛውም ሰው* ርኩስ ሆኖ ሳለ ለይሖዋ ከቀረበው የኅብረት መሥዋዕት ሥጋ ቢበላ ያ ሰው* ከሕዝቡ መካከል ተለይቶ እንዲጠፋ ይደረግ።*+ 21 አንድ ሰው* ርኩስ የሆነ ነገር ይኸውም የሰውን ርኩሰት+ ወይም ርኩስ የሆነን እንስሳ+ ወይም ርኩስ የሆነን ማንኛውንም አስጸያፊ ነገር+ ቢነካና ለይሖዋ ከቀረበው የኅብረት መሥዋዕት ሥጋ ቢበላ ያ ሰው* ከሕዝቡ መካከል ተለይቶ እንዲጠፋ ይደረግ።’”

22 ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ 23 “እስራኤላውያንን እንዲህ በላቸው፦ ‘ማንኛውንም ዓይነት የበሬ፣ የበግ ጠቦት ወይም የፍየል ስብ አትብሉ።+ 24 ሞቶ የተገኘ እንስሳ ስብና አውሬ የገደለው እንስሳ ስብ ለሌላ ለማንኛውም አገልግሎት ሊውል ይችላል፤ እናንተ ግን ፈጽሞ እንዳትበሉት።+ 25 ማንኛውም ሰው ለይሖዋ በእሳት የሚቃጠል መባ አድርጎ ከሚያቀርበው እንስሳ ላይ ስብ ቢበላ ከሕዝቡ መካከል ተለይቶ እንዲጠፋ ይደረግ።

26 “‘በምትኖሩበት በየትኛውም ቦታ የወፍም ይሁን የእንስሳ፣ ማንኛውንም ደም አትብሉ።+ 27 ደም የሚበላ ማንኛውም ሰው* ከሕዝቡ መካከል ተለይቶ እንዲጠፋ ይደረግ።’”+

28 ከዚያም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ 29 “እስራኤላውያንን እንዲህ በላቸው፦ ‘የኅብረት መሥዋዕቱን ለይሖዋ የሚያቀርብ ማንኛውም ሰው ከኅብረት መሥዋዕቱ መባ ላይ የተወሰነውን ለይሖዋ ያቀርባል።+ 30 እሱም ስቡን+ ከፍርምባው ጋር ለይሖዋ በእሳት የሚቀርብ መባ እንዲሆን በራሱ እጆች ያመጣል፤ የሚወዘወዝ መባ+ አድርጎም በይሖዋ ፊት ወዲያና ወዲህ ይወዘውዘዋል። 31 ካህኑ ስቡን በመሠዊያው ላይ ያጨሰዋል፤+ ፍርምባው ግን የአሮንና የወንዶች ልጆቹ ይሆናል።+

32 “‘ከኅብረት መሥዋዕቶቻችሁም ላይ ቀኝ እግሩን ለካህኑ የተቀደሰ ድርሻ አድርጋችሁ ትሰጣላችሁ።+ 33 የኅብረት መሥዋዕቱን ደምና ስቡን የሚያቀርበው የአሮን ልጅ የእንስሳውን ቀኝ እግር እንደ ድርሻው አድርጎ ይወስዳል።+ 34 እስራኤላውያን ከሚያቀርቧቸው የኅብረት መሥዋዕቶች ላይ የሚወዘወዘውን መባ ፍርምባና የተቀደሰ ድርሻ ሆኖ የቀረበውን እግር እወስዳለሁ፤ ለእስራኤላውያንም ዘላቂ ሥርዓት እንዲሆን ለካህኑ ለአሮንና ለወንዶች ልጆቹ እሰጣቸዋለሁ።+

35 “‘ካህናት ሆነው ይሖዋን ለማገልገል በሚቀርቡበት ቀን፣ ለይሖዋ በእሳት ከቀረቡት መባዎች ላይ ለካህናቱ ይኸውም ለአሮንና ለወንዶች ልጆቹ የሚመደብላቸው ድርሻ ይህ ነው።+ 36 ይሖዋ በቀባቸው+ ቀን ይህ ድርሻ ከእስራኤላውያን ተወስዶ እንዲሰጣቸው አዟል። ይህ ለትውልዶቻቸው ዘላለማዊ ደንብ ነው።’”

37 የሚቃጠል መባን፣+ የእህል መባን፣+ የኃጢአት መባን፣+ የበደል መባን፣+ ለክህነት ሹመት ሥርዓት የሚቀርብ መሥዋዕትንና+ የኅብረት መሥዋዕትን+ በተመለከተ የተሰጠው ሕግ ይህ ነው፤ 38 ይህም እስራኤላውያን በሲና ምድረ በዳ መባዎቻቸውን ለይሖዋ እንዲያቀርቡ+ ባዘዛቸው ቀን ይሖዋ ሙሴን በሲና ተራራ ላይ ባዘዘው+ መሠረት የሚፈጸም ነው።

8 ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ 2 “አሮንን፣ ከእሱም ጋር ወንዶች ልጆቹን+ እንዲሁም ልብሶቹን፣+ የቅብዓት ዘይቱን፣+ ለኃጢአት መባ የሚሆነውን በሬ፣ ሁለቱን አውራ በጎችና ቂጣ ያለበትን ቅርጫት+ ውሰድ፤ 3 መላው ማኅበረሰብም በመገናኛ ድንኳኑ መግቢያ ላይ እንዲሰበሰብ አድርግ።”

4 ከዚያም ሙሴ ልክ ይሖዋ እንዳዘዘው አደረገ፤ ማኅበረሰቡም በመገናኛ ድንኳኑ መግቢያ ላይ ተሰበሰበ። 5 ሙሴም ለማኅበረሰቡ “ይሖዋ እንድናደርግ ያዘዘን ነገር ይህ ነው” አላቸው። 6 በመሆኑም ሙሴ አሮንንና ወንዶች ልጆቹን አቀረባቸው፤ በውኃም አጠባቸው።+ 7 ከዚያም ለአሮን ረጅሙን ቀሚስ+ አጠለቀለት፤ መቀነቱንም+ አሰረለት፤ እጅጌ የሌለውን ቀሚስም+ አለበሰው፤ ኤፉዱንም+ አደረገለት፤ ኤፉዱንም ተሸምኖ በተሠራው የኤፉዱ መቀነት+ ጠበቅ አድርጎ አሰረው። 8 በመቀጠልም የደረት ኪሱን+ አደረገለት፤ በደረት ኪሱም ውስጥ ኡሪሙንና ቱሚሙን+ አስቀመጠ። 9 ከዚያም ልክ ይሖዋ ሙሴን ባዘዘው መሠረት ጥምጥሙን+ በራሱ ላይ አደረገለት፤ በጥምጥሙም ከፊት በኩል፣ የሚያብረቀርቀውን ጠፍጣፋ ወርቅ ይኸውም ለአምላክ የተወሰኑ መሆንን የሚያሳየውን ቅዱስ ምልክት*+ አደረገለት።

10 ሙሴም የቅብዓት ዘይቱን ወስዶ የማደሪያ ድንኳኑንና በውስጡ ያሉትን ነገሮች በሙሉ ቀባቸው፤+ እንዲሁም ቀደሳቸው። 11 ከዚያም ይቀድሳቸው ዘንድ ከዘይቱ የተወሰነውን ወስዶ በመሠዊያው ላይ ሰባት ጊዜ በመርጨት መሠዊያውንና ዕቃዎቹን በሙሉ እንዲሁም የውኃ ገንዳውንና ማስቀመጫውን ቀባቸው። 12 በመጨረሻም ከቅብዓት ዘይቱ የተወሰነውን ወስዶ በአሮን ራስ ላይ አፈሰሰው፤ የተቀደሰም ይሆን ዘንድ ቀባው።+

13 ከዚያም ሙሴ ልክ ይሖዋ ባዘዘው መሠረት የአሮንን ወንዶች ልጆች አቀረባቸው፤ ረጅሞቹን ቀሚሶችም አለበሳቸው፤+ መቀነቶቹንም አሰረላቸው፤ የራስ ቆቡንም ደፋላቸው።

14 ከዚያም ለኃጢአት መባ የሚሆነውን በሬ አመጣ፤ አሮንና ወንዶች ልጆቹም እጆቻቸውን ለኃጢአት መባ በሚሆነው በሬ ራስ ላይ ጫኑ።+ 15 ሙሴም በሬውን አረደው፤ ደሙንም+ በጣቱ ወስዶ በሁሉም የመሠዊያው ጎኖች ላይ ያሉትን ቀንዶች ቀባ፤ መሠዊያውንም ከኃጢአት አነጻው፤ የቀረውንም ደም መሠዊያው ማስተሰረያ ይቀርብበት ዘንድ መሠዊያውን ለመቀደስ በሥሩ አፈሰሰው። 16 ከዚያም ሙሴ አንጀቱን የሸፈነውን ስብ ሁሉ፣ በጉበቱ ላይ ያለውን ሞራ፣ ሁለቱን ኩላሊቶችና በእነሱ ላይ ያለውን ስብ ወስዶ በመሠዊያው ላይ እንዲጨሱ አደረገ።+ 17 ሙሴም ልክ ይሖዋ ባዘዘው መሠረት ከበሬው የቀረውን፣ ቆዳውን፣ ሥጋውንና ፈርሱን ከሰፈሩ ውጭ በእሳት አቃጠለው።+

18 እሱም ለሚቃጠል መባ የሚሆነውን አውራ በግ አመጣ፤ አሮንና ወንዶች ልጆቹም እጆቻቸውን በአውራው በግ ራስ ላይ ጫኑ።+ 19 ከዚያም ሙሴ አውራውን በግ አረደው፤ ደሙንም በመሠዊያው ጎኖች ሁሉ ላይ ረጨው። 20 አውራውንም በግ በየብልቱ ቆራረጠው፤ ቀጥሎም ጭንቅላቱን፣ ብልቶቹንና ሞራውን* አጨሰው። 21 ሆድ ዕቃውንና እግሮቹንም በውኃ አጠባቸው፤ ሙሴም አውራው በግ በሙሉ በመሠዊያው ላይ እንዲጨስ አደረገ። ይህም ደስ የሚያሰኝ* መዓዛ ያለው የሚቃጠል መባ ነበር። ልክ ይሖዋ ሙሴን ባዘዘው መሠረት ለይሖዋ በእሳት የሚቀርብ መባ ነበር።

22 ከዚያም ሁለተኛውን አውራ በግ ይኸውም ለክህነት ሹመት ሥርዓት+ የሚቀርበውን አውራ በግ አመጣ፤ አሮንና ወንዶች ልጆቹም በአውራው በግ ራስ ላይ እጆቻቸውን ጫኑ።+ 23 ከዚያም ሙሴ አውራውን በግ አረደው፤ ከደሙም የተወሰነውን ወስዶ የአሮንን የቀኝ ጆሮ ጫፍ፣ የቀኝ እጁን አውራ ጣት እንዲሁም የቀኝ እግሩን አውራ ጣት ቀባ። 24 በመቀጠልም ሙሴ የአሮንን ወንዶች ልጆች ወደ ፊት አቀረባቸው፤ ከደሙም የተወሰነውን ወስዶ የቀኝ ጆሯቸውን ጫፍ፣ የቀኝ እጃቸውን አውራ ጣት እንዲሁም የቀኝ እግራቸውን አውራ ጣት ቀባ፤ የቀረውን ደም ግን በመሠዊያው ጎኖች ሁሉ ላይ ረጨው።+

25 ከዚያም ስቡን፣ ላቱን፣ አንጀቱን የሚሸፍነውን ስብ በሙሉ፣ የጉበቱን ሞራ፣ ሁለቱን ኩላሊቶችና በእነሱ ላይ ያለውን ስብ እንዲሁም ቀኝ እግሩን ወሰደ።+ 26 በይሖዋ ፊት ካለው ቂጣዎች ከተቀመጡበት ቅርጫት ውስጥም እርሾ ያልገባበት የቀለበት ቅርጽ ያለው አንድ ዳቦ፣+ ዘይት የተቀባ የቀለበት ቅርጽ ያለው አንድ ዳቦና+ አንድ ስስ ቂጣ ወሰደ። ከዚያም በስቦቹና በቀኝ እግሩ ላይ አደረጋቸው። 27 በመቀጠልም ሁሉንም በአሮን መዳፍና በወንዶች ልጆቹ መዳፍ ላይ አስቀመጣቸው፤ በይሖዋ ፊት እንደሚወዘወዝ መባም ወዲያና ወዲህ ወዘወዛቸው። 28 ከዚያም ሙሴ ከእጃቸው ላይ ወስዶ በመሠዊያው ላይ ባለው በሚቃጠለው መባ ላይ እንዲጨሱ አደረገ። እነዚህም ደስ የሚያሰኝ* መዓዛ የሚሰጡ የክህነት ሹመት መሥዋዕት ናቸው። ይህም ለይሖዋ በእሳት የሚቀርብ መባ ነበር።

29 ሙሴም ፍርምባውን ወስዶ በይሖዋ ፊት እንደሚወዘወዝ መባ ወዲያና ወዲህ ወዘወዘው።+ ልክ ይሖዋ ሙሴን ባዘዘው መሠረትም ለክህነት ሹመት ሥርዓት ከሚቀርበው አውራ በግ ላይ ይህ የእሱ ድርሻ ሆነ።+

30 ሙሴም ከቅብዓት ዘይቱና+ በመሠዊያው ላይ ካለው ደም የተወሰነውን ወስዶ በአሮንና በልብሶቹ እንዲሁም ከእሱ ጋር በነበሩት ወንዶች ልጆቹና በወንዶች ልጆቹ ልብሶች ላይ ረጨው። በዚህ መንገድ አሮንንና ልብሶቹን እንዲሁም ወንዶች ልጆቹንና+ ልብሶቻቸውን ቀደሰ።+

31 ከዚያም ሙሴ አሮንንና ወንዶች ልጆቹን እንዲህ አላቸው፦ “ሥጋውን በመገናኛ ድንኳኑ መግቢያ ላይ ቀቅሉት፤+ ‘አሮንና ወንዶች ልጆቹ ይበሉታል’ ተብዬ በታዘዝኩት መሠረት ሥጋውንም ሆነ በክህነት ሹመት ሥርዓቱ ቅርጫት ውስጥ ያለውን ቂጣ እዚያ ትበሉታላችሁ።+ 32 ከሥጋውም ሆነ ከቂጣው የተረፈውን በእሳት ታቃጥሉታላችሁ።+ 33 ለክህነት ሹመታችሁ ሥርዓት የተመደቡት ቀናት እስከሚያበቁ ድረስ ይኸውም ለሰባት ቀን ያህል በመገናኛ ድንኳኑ ደጃፍ ቆዩ፤ ምክንያቱም እናንተን ካህን አድርጎ መሾም* ሰባት ቀን ይፈጃል።+ 34 ለእናንተ ለማስተሰረይ+ ዛሬ ያደረግነውን ነገር እንድናደርግ ይሖዋ አዟል። 35 በመገናኛ ድንኳኑ መግቢያ ላይ ቀንና ሌሊት ለሰባት ቀን ያህል ትቆያላችሁ፤+ እንዳትሞቱም ለይሖዋ የገባችሁትን ግዴታ ፈጽሙ፤+ ምክንያቱም እንዲህ እንዳደርግ ታዝዣለሁ።”

36 አሮንና ወንዶች ልጆቹም ይሖዋ በሙሴ አማካኝነት ያዘዛቸውን ነገሮች በሙሉ አደረጉ።

9 በስምንተኛውም ቀን+ ሙሴ አሮንን፣ ወንዶች ልጆቹንና የእስራኤልን ሽማግሌዎች ጠራ። 2 አሮንንም እንዲህ አለው፦ “ለኃጢአት መባ+ አንድ ጥጃ፣ ለሚቃጠል መባ ደግሞ አንድ አውራ በግ ለራስህ ውሰድ፤ እንከን የሌለባቸው ይሁኑ፤ በይሖዋም ፊት አቅርባቸው። 3 እስራኤላውያንን ግን እንዲህ ትላቸዋለህ፦ ‘ለኃጢአት መባ አንድ ተባዕት ፍየል፣ ለሚቃጠል መባ ደግሞ እያንዳንዳቸው አንድ ዓመት የሆናቸውና እንከን የሌለባቸው አንድ ጥጃና አንድ የበግ ጠቦት ውሰዱ፤ 4 የኅብረት መሥዋዕት+ ሆነው በይሖዋ ፊት እንዲሠዉም አንድ በሬና አንድ አውራ በግ ውሰዱ፤ እንዲሁም በዘይት የተለወሰ የእህል መባ+ አቅርቡ፤ ምክንያቱም ይሖዋ ዛሬ ለእናንተ ይገለጣል።’”+

5 ስለዚህ ሙሴ ያዘዛቸውን ነገሮች በሙሉ ወደ መገናኛ ድንኳኑ ፊት አመጡ። ከዚያም መላው ማኅበረሰብ መጥቶ በይሖዋ ፊት ቆመ። 6 ሙሴም “የይሖዋ ክብር ይገለጥላችሁ+ ዘንድ ይሖዋ እንድታደርጉት ያዘዛችሁ ነገር ይህ ነው” አለ። 7 ከዚያም ሙሴ አሮንን እንዲህ አለው፦ “ወደ መሠዊያው ቀርበህ የኃጢአት መባህንና+ የሚቃጠል መባህን አቅርብ፤ ለራስህና ለቤትህም አስተሰርይ፤+ ይሖዋ ባዘዘውም መሠረት የሕዝቡን መባ አቅርብ፤+ እንዲሁም ለእነሱ አስተሰርይ።”+

8 አሮንም ወዲያው ወደ መሠዊያው ቀርቦ ስለ ራሱ የኃጢአት መባ ሆኖ የሚቀርበውን ጥጃ አረደ።+ 9 ከዚያም ወንዶች ልጆቹ ደሙን አቀረቡለት፤+ እሱም ጣቱን ደሙ ውስጥ በመንከር የመሠዊያውን ቀንዶች ቀባ፤ የቀረውንም ደም በመሠዊያው ሥር አፈሰሰው።+ 10 ይሖዋ ሙሴን ባዘዘውም መሠረት ከኃጢአት መባው ላይ ስቡን፣ ኩላሊቶቹንና በጉበቱ ላይ ያለውን ሞራ ወስዶ በመሠዊያው ላይ እንዲጨሱ አደረገ።+ 11 ሥጋውንና ቆዳውንም ከሰፈሩ ውጭ በእሳት አቃጠለው።+

12 ከዚያም የሚቃጠል መባ ሆኖ የሚቀርበውን እንስሳ አረደው፤ ወንዶች ልጆቹም ደሙን ሰጡት፤ እሱም ደሙን በመሠዊያው ጎኖች ሁሉ ላይ ረጨው።+ 13 እነሱም የሚቃጠለውን መባ ብልቶች ከነጭንቅላቱ ሰጡት፤ እሱም በመሠዊያው ላይ እንዲጨሱ አደረገ። 14 በተጨማሪም ሆድ ዕቃውንና እግሮቹን አጠባቸው፤ በመሠዊያው ላይ ባለው በሚቃጠለው መባ ላይም እንዲጨሱ አደረገ።

15 በመቀጠልም የሕዝቡን መባ አቀረበ፤ ለሕዝቡ የኃጢአት መባ ሆኖ የሚቀርበውን ፍየል ወስዶ አረደው፤ እንደ መጀመሪያው ሁሉ በዚህኛውም የኃጢአት መባ አቀረበ። 16 ከዚያም የሚቃጠለውን መባ አቀረበ፤ በተለመደውም አሠራር መሠረት አቀረበው።+

17 በመቀጠልም የእህል መባውን+ አቀረበ፤ ከላዩ ላይም እፍኝ ሙሉ አንስቶ ጠዋት ላይ ከሚቀርበው የሚቃጠል መባ በተጨማሪ በመሠዊያው ላይ እንዲጨስ አደረገ።+

18 በኋላም ለሕዝቡ የኅብረት መሥዋዕት የሚሆኑትን በሬውንና አውራውን በግ አረዳቸው። ወንዶች ልጆቹም ደሙን ሰጡት፤ እሱም ደሙን በመሠዊያው ጎኖች ሁሉ ላይ ረጨው።+ 19 ከዚያም የበሬውን ስቦች፣+ የአውራውን በግ ላት፣ ሆድ ዕቃውን የሸፈነውን ስብ፣ ኩላሊቶቹንና የጉበቱን ሞራ+ 20 ማለትም ስቡን ሁሉ በፍርምባዎቹ ላይ አደረጉ፤ ስቡም ሁሉ በመሠዊያው ላይ እንዲጨስ አደረገ።+ 21 ሆኖም አሮን ፍርምባዎቹንና ቀኝ እግሩን ልክ ሙሴ ባዘዘው መሠረት እንደሚወዘወዝ መባ በይሖዋ ፊት ወዲያና ወዲህ ወዘወዛቸው።+

22 ከዚያም አሮን እጆቹን ወደ ሕዝቡ በማንሳት ባረካቸው፤+ የኃጢአት መባውን፣ የሚቃጠል መባውንና የኅብረት መሥዋዕቶቹን ካቀረበ በኋላ ወረደ። 23 በመጨረሻም ሙሴና አሮን ወደ መገናኛ ድንኳኑ ገቡ፤ ከዚያም ወጥተው ሕዝቡን ባረኩ።+

በዚህ ጊዜ የይሖዋ ክብር ለሕዝቡ ሁሉ ተገለጠ፤+ 24 እሳትም ከይሖዋ ፊት ወጥቶ+ በመሠዊያው ላይ ያለውን የሚቃጠል መባና ስብ በላ። ሕዝቡም ሁሉ ይህን ሲያይ እልል አለ፤ በግንባሩም መሬት ላይ ተደፋ።+

10 በኋላም የአሮን ወንዶች ልጆች ናዳብና አቢሁ+ እያንዳንዳቸው የዕጣን ማጨሻቸውን አምጥተው በላዩ ላይ እሳት አደረጉበት፤ በእሳቱም ላይ ዕጣን ጨመሩበት።+ ከዚያም ይሖዋ እንዲያደርጉ ያላዘዛቸውን ያልተፈቀደ እሳት+ በፊቱ አቀረቡ። 2 በዚህ ጊዜ እሳት ከይሖዋ ፊት ወጥቶ በላቸው፤+ እነሱም በይሖዋ ፊት ሞቱ።+ 3 ከዚያም ሙሴ አሮንን እንዲህ አለው፦ “ይሖዋ ‘ወደ እኔ በሚቀርቡ ሰዎች መካከል እቀደሳለሁ፤+ በሕዝቡም ሁሉ ፊት እከበራለሁ’ ብሏል።” አሮንም ዝም አለ።

4 ሙሴም የአሮን አጎት የዑዚኤል+ ልጆች የሆኑትን ሚሳኤልንና ኤሊጻፋንን ጠርቶ “ኑ፣ ወንድሞቻችሁን ከቅዱሱ ስፍራ ፊት ለፊት አንስታችሁ ከሰፈሩ ውጭ ወዳለው ቦታ አውጧቸው” አላቸው። 5 ስለዚህ መጥተው ልክ ሙሴ በነገራቸው መሠረት ሟቾቹን ከነቀሚሳቸው ተሸክመው ከሰፈሩ ውጭ አወጧቸው።

6 ከዚያም ሙሴ አሮንን እንዲሁም ሌሎቹን የአሮን ልጆች አልዓዛርንና ኢታምርን እንዲህ አላቸው፦ “እንዳትሞቱ እንዲሁም አምላክ በመላው ማኅበረሰብ ላይ እንዳይቆጣ ፀጉራችሁን አታንጨብርሩ ወይም ልብሶቻችሁን አትቅደዱ።+ ሆኖም ወንድሞቻችሁ ይኸውም መላው የእስራኤል ቤት ይሖዋ በእሳት ለገደላቸው ያለቅሱላቸዋል። 7 የይሖዋ የቅብዓት ዘይት በላያችሁ ላይ ስላለ ከመገናኛ ድንኳኑ ደጃፍ መራቅ የለባችሁም፤+ አለዚያ ትሞታላችሁ።” እነሱም ሙሴ እንዳላቸው አደረጉ።

8 ከዚያም ይሖዋ አሮንን እንዲህ አለው፦ 9 “እንዳትሞቱ ወደ መገናኛ ድንኳኑ ስትገቡ አንተም ሆንክ ከአንተ ጋር ያሉት ወንዶች ልጆችህ የወይን ጠጅ ወይም ሌላ የሚያሰክር መጠጥ አትጠጡ።+ ይህ ትእዛዝ ለትውልዶቻችሁ ሁሉ ዘላለማዊ ደንብ ነው። 10 ይህም ቅዱስ የሆነውን ከረከሰው ነገር እንዲሁም ንጹሕ ያልሆነውን ንጹሕ ከሆነው ነገር ለመለየት+ 11 እንዲሁም ይሖዋ በሙሴ አማካኝነት የሰጣቸውን ሥርዓቶች በሙሉ ለእስራኤላውያን ለማስተማር ነው።”+

12 ከዚያም ሙሴ አሮንን እንዲሁም የተረፉትን የአሮን ልጆች አልዓዛርንና ኢታምርን እንዲህ አላቸው፦ “ለይሖዋ በእሳት ከሚቀርቡት መባዎች የተረፈውን የእህል መባ ወስዳችሁ ያለእርሾ በማዘጋጀት በመሠዊያው አጠገብ ብሉት፤+ ምክንያቱም ይህ እጅግ ቅዱስ ነገር ነው።+ 13 ለይሖዋ በእሳት ከሚቀርቡት መባዎች ላይ ይህ የአንተ ድርሻና የወንዶች ልጆችህ ድርሻ ስለሆነ ቅዱስ በሆነ ስፍራ ብሉት፤+ ምክንያቱም እንዲህ እንዳደርግ ታዝዣለሁ። 14 እንዲሁም የሚወዘወዘውን መባ ፍርምባና የቅዱሱን ድርሻ+ እግር አንተም ሆንክ ከአንተ ጋር ያሉት ወንዶችና ሴቶች ልጆችህ ንጹሕ በሆነ ስፍራ ትበሉታላችሁ፤+ ምክንያቱም እነዚህ ነገሮች እስራኤላውያን ከሚያቀርቧቸው የኅብረት መሥዋዕቶች ላይ የአንተ ድርሻና የወንዶች ልጆችህ ድርሻ ሆነው የተሰጡ ናቸው። 15 እነሱም የቅዱሱን ድርሻ እግርና የሚወዘወዘውን መባ ፍርምባ በእሳት ከሚቀርቡት የስብ መባዎች ጋር ያመጣሉ፤ ይህን የሚያደርጉት የሚወዘወዘውን መባ በይሖዋ ፊት ወዲያና ወዲህ ለመወዝወዝ ነው፤ ልክ ይሖዋ ባዘዘው መሠረትም ይህ ለአንተና ከአንተ ጋር ላሉት ወንዶች ልጆችህ ዘላለማዊ ድርሻ ሆኖ ያገለግላል።”+

16 ሙሴም ለኃጢአት መባ የሚሆነውን ፍየል በደንብ አፈላለገ፤+ በኋላም ፍየሉ መቃጠሉን ተረዳ። በመሆኑም የተረፉትን የአሮን ልጆች አልዓዛርንና ኢታምርን ተቆጣቸው፤ እንዲህም አላቸው፦ 17 “ይህ መባ እጅግ ቅዱስ ነገር ሆኖ ሳለና መባውንም የሰጣችሁ የማኅበረሰቡን ኃጢአት እንድትሸከሙ እንዲሁም በይሖዋ ፊት እንድታስተሰርዩላቸው ሆኖ ሳለ የኃጢአት መባውን በቅዱሱ ስፍራ ያልበላችሁት+ ለምንድን ነው? 18 ይኸው ደሙ ወደ ቅዱሱ ስፍራ አልገባም።+ ልክ እንደታዘዝኩት በቅዱሱ ስፍራ ልትበሉት ይገባችሁ ነበር።” 19 በዚህ ጊዜ አሮን ሙሴን እንዲህ አለው፦ “እንግዲህ እነሱ በዛሬው ዕለት የኃጢአት መባቸውንና የሚቃጠል መባቸውን በይሖዋ ፊት ያቀረቡት+ እኔ እንዲህ ያለ ነገር ደርሶብኝ እያለ ነው። ታዲያ ዛሬ የኃጢአት መባውን በልቼ ቢሆን ኖሮ ይሖዋ ይደሰት ነበር?” 20 ሙሴም ይህን ሲሰማ ነገሩን አጥጋቢ ሆኖ አገኘው።

11 ከዚያም ይሖዋ ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፦ 2 “እስራኤላውያንን እንዲህ በሏቸው፦ ‘በምድር ላይ ካሉ ሕያዋን ፍጥረታት* መካከል እነዚህን መብላት ትችላላችሁ፦+ 3 ሰኮናው የተሰነጠቀውንና ስንጥቁም ሙሉ በሙሉ የተከፈለውን እንዲሁም የሚያመሰኳውን ማንኛውንም እንስሳ መብላት ትችላላችሁ።

4 “‘ሆኖም የሚያመሰኩትን ወይም ሰኮናቸው የተሰነጠቀውን እነዚህን እንስሳት መብላት የለባችሁም፦ ግመል የሚያመሰኳ ቢሆንም ሰኮናው የተሰነጠቀ አይደለም። ለእናንተ ርኩስ ነው።+ 5 ሽኮኮም+ መብላት የለባችሁም፤ ምክንያቱም የሚያመሰኳ ቢሆንም ሰኮናው የተሰነጠቀ አይደለም። ለእናንተ ርኩስ ነው። 6 ጥንቸልም ብትሆን መብላት የለባችሁም፤ ምክንያቱም የምታመሰኳ ብትሆንም ሰኮናዋ የተሰነጠቀ አይደለም። ለእናንተ ርኩስ ነች። 7 አሳማም+ መብላት የለባችሁም፤ ሰኮናው የተሰነጠቀና ስንጥቁ ሙሉ በሙሉ የተከፈለ ቢሆንም እንኳ አያመሰኳም። ለእናንተ ርኩስ ነው። 8 የእነዚህን እንስሳት ሥጋ አትብሉ ወይም በድናቸውን አትንኩ። እነዚህ ለእናንተ ርኩስ ናቸው።+

9 “‘በውኃዎች ውስጥ ካሉት መካከል እነዚህን መብላት ትችላላችሁ፦ በባሕርም ሆነ በወንዞች፣ በውኃዎች ውስጥ ካሉት መካከል ክንፍና ቅርፊት ያላቸውን ሁሉ መብላት ትችላላችሁ።+ 10 በውኃዎች ውስጥ ካሉ የሚርመሰመሱ ፍጥረታትና ሌሎች ሕይወት ያላቸው ፍጥረታት* ሁሉ መካከል በባሕርና በወንዞች ውስጥ የሚገኙ ክንፍና ቅርፊት የሌላቸው ሁሉ ግን ለእናንተ አስጸያፊ ናቸው። 11 አዎ፣ እነዚህን ልትጸየፏቸው ይገባል፤ ሥጋቸውን ፈጽሞ አትብሉ፤+ በድናቸውንም ተጸየፉት። 12 በውኃዎች ውስጥ የሚኖሩ ክንፍና ቅርፊት የሌላቸው ሁሉ ለእናንተ አስጸያፊ ናቸው።

13 “‘ልትጸየፏቸው የሚገቡ በራሪ ፍጥረታት እነዚህ ናቸው፤ አስጸያፊ በመሆናቸው መበላት የለባቸውም፦ ንስር፣+ ዓሣ በል ጭላት፣ ጥቁር ጥምብ አንሳ፣+ 14 ቀይ ጭልፊት፣ ማንኛውም ዓይነት ጥቁር ጭልፊት፣ 15 ማንኛውም ዓይነት ቁራ፣ 16 ሰጎን፣ ጉጉት፣ ዓሣ አዳኝ፣ ማንኛውም ዓይነት ሲላ፣ 17 ትንሿ ጉጉት፣ ለማሚት፣ ባለ ረጅም ጆሮ ጉጉት፣ 18 ዝይ፣ ሻላ፣ ጥምብ አንሳ፣ 19 ራዛ፣ ማንኛውም ዓይነት ሽመላ፣ ጅንጅላቴና የሌሊት ወፍ። 20 በአራቱም እግሩ የሚሄድ ክንፍ ያለው የሚርመሰመስ ፍጡር* ሁሉ ለእናንተ አስጸያፊ ነው።

21 “‘በአራቱም እግራቸው ከሚሄዱ ክንፍ ካላቸው የሚርመሰመሱ ፍጥረታት መካከል መብላት የምትችሉት ከእግሮቻቸው በላይ በመሬት ላይ ለመፈናጠር የሚያገለግል የሚተጣጠፍ ቅልጥም ያላቸውን ብቻ ነው። 22 ከእነዚህም መካከል የሚከተሉትን መብላት ትችላላችሁ፦ የተለያየ ዓይነት የሚፈልስ አንበጣ፣ ሌሎች የሚበሉ አንበጦች፣+ እንጭራሪቶችና ፌንጣዎች። 23 አራት እግር ኖሯቸው ክንፍ ያላቸው ሌሎች የሚርመሰመሱ ፍጥረታት ሁሉ ለእናንተ አስጸያፊ ናቸው። 24 በእነዚህ ራሳችሁን ታረክሳላችሁ። በድናቸውን የሚነካ ማንኛውም ሰው እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል።+ 25 ከእነዚህ መካከል የማናቸውንም በድን የሚያነሳ ሁሉ ልብሶቹን ይጠብ፤+ እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ይሆናል።

26 “‘ሰኮናው የተሰነጠቀ፣ ስንጥቁ ግን ሙሉ በሙሉ ያልተከፈለ እንዲሁም የማያመሰኳ ማንኛውም እንስሳ ለእናንተ ርኩስ ነው። የሚነካቸውም ሁሉ ርኩስ ይሆናል።+ 27 በአራቱም እግራቸው ከሚሄዱ ፍጥረታት መካከል በመዳፋቸው የሚሄዱ ሕያዋን ፍጥረታት ሁሉ ለእናንተ ርኩስ ናቸው። በድናቸውን የሚነካ ማንኛውም ሰው እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል። 28 በድናቸውን የሚያነሳ ሰው ልብሶቹን ይጠብ፤+ እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ይሆናል።+ እነዚህ ለእናንተ ርኩስ ናቸው።

29 “‘ለእናንተ ርኩስ የሆኑት በምድር ላይ የሚርመሰመሱ ፍጥረታት እነዚህ ናቸው፦ ፍልፈል፣ አይጥ፣+ ማንኛውም ዓይነት እንሽላሊት፣ 30 ጌኮ፣ ገበሎ፣ የውኃ እንሽላሊት፣ የአሸዋ እንሽላሊትና እስስት። 31 እነዚህ የሚርመሰመሱ ፍጥረታት ለእናንተ ርኩስ ናቸው።+ በድናቸውን የሚነካ ሁሉ እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል።+

32 “‘በሚሞቱበት ጊዜ የወደቁበት ማንኛውም ነገር ይኸውም የእንጨት ዕቃም ሆነ ልብስ ወይም ቆዳ አሊያም ደግሞ በርኖስ ርኩስ ይሆናል። አገልግሎት ላይ የሚውል ማንኛውም ዕቃ ውኃ ውስጥ ይነከር፤ እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ይሆናል፤ ከዚያም ይነጻል። 33 በሸክላ ዕቃ ውስጥ ከወደቁ ዕቃውን ሰባብሩት፤ በውስጡ ያለውም ማንኛውም ነገር ርኩስ ይሆናል።+ 34 እንዲህ ባለ ዕቃ ውስጥ የነበረ ውኃ የነካው ማንኛውም ዓይነት ምግብ ርኩስ ይሆናል፤ በእንዲህ ዓይነቱ ዕቃ ውስጥ የነበረ የሚጠጣ ማንኛውም ዓይነት መጠጥም ርኩስ ይሆናል። 35 በድናቸው የወደቀበት ማንኛውም ነገር ርኩስ ይሆናል። መጋገሪያ ምድጃም ይሁን አነስተኛ ምድጃ ይሰበር። እነዚህ ነገሮች ርኩስ ናቸው፤ ለእናንተም ርኩስ ይሆናሉ። 36 ምንጭና የውኃ ማጠራቀሚያ ጉድጓድ ብቻ ንጹሕ ይሆናሉ፤ ይሁንና በድኑን የነካ ማንኛውም ሰው ርኩስ ይሆናል። 37 በድናቸው በሚዘራ ዘር ላይ ቢወድቅ ዘሩ ንጹሕ ነው። 38 ይሁንና በዘሩ ላይ ውኃ ተደርጎበት ሳለ የበድናቸው አንዱ ክፍል ዘሩ ላይ ቢወድቅ ዘሩ ለእናንተ ርኩስ ይሆናል።

39 “‘እንድትበሉ ከተፈቀደላችሁ እንስሳ አንዱ ቢሞት የእንስሳውን በድን የሚነካ ማንኛውም ሰው እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል።+ 40 ከበድኑ የበላ ማንኛውም ሰው ልብሶቹን ይጠብ፤ እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ይሆናል።+ በድኑን ያነሳ ማንኛውም ሰው ልብሶቹን ይጠብ፤ እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ይሆናል። 41 በምድር ላይ የሚርመሰመስ ማንኛውም ፍጥረት አስጸያፊ ነው።+ መበላት የለበትም። 42 በሆዱ የሚሳብን ማንኛውም ፍጥረት፣ በአራቱም እግሩ የሚሄድን ማንኛውም ፍጥረት ወይም ብዙ እግሮች ያሉትን በምድር ላይ የሚርመሰመስ ማንኛውም ፍጥረት መብላት የለባችሁም፤ ምክንያቱም አስጸያፊ ናቸው።+ 43 በምድር ላይ በሚርመሰመስ በማንኛውም ፍጥረት ራሳችሁን* አስጸያፊ አታድርጉ፤ በእነሱም ራሳችሁን በመበከል አትርከሱ።+ 44 እኔ አምላካችሁ ይሖዋ ነኝና፤+ እኔ ቅዱስ ስለሆንኩ+ እናንተም ራሳችሁን ልትቀድሱና ቅዱስ ልትሆኑ ይገባል።+ በምድር ላይ በሚንቀሳቀስ በማንኛውም የሚርመሰመስ ፍጥረት ራሳችሁን* አታርክሱ። 45 አምላካችሁ መሆኔን ለማስመሥከር ከግብፅ ምድር መርቼ ያወጣኋችሁ እኔ ይሖዋ ነኝና፤+ እኔ ቅዱስ ስለሆንኩ+ እናንተም ቅዱሳን መሆን አለባችሁ።+

46 “‘እንስሳትን፣ የሚበርሩ ፍጥረታትን፣ በውኃዎች ውስጥ የሚንቀሳቀስን ማንኛውም ዓይነት ሕያው ፍጡር* እንዲሁም በምድር ላይ የሚርመሰመስን ፍጡር* ሁሉ በተመለከተ ሕጉ ይህ ነው፤ 47 ርኩስ የሆነውንና ንጹሕ የሆነውን እንዲሁም ለመብል የሚሆነውንና ለመብል የማይሆነውን ሕያው ፍጡር ለመለየት ሕጉ ይህ ነው።’”+

12 ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ 2 “እስራኤላውያንን እንዲህ በላቸው፦ ‘አንዲት ሴት ብታረግዝና* ወንድ ልጅ ብትወልድ በወር አበባዋ ወቅት እንደምትረክሰው ሁሉ ለሰባት ቀን ትረክሳለች።+ 3 ሕፃኑም በስምንተኛው ቀን ይገረዛል።+ 4 እሷም ከደም ራሷን ለማንጻት ለቀጣዮቹ 33 ቀናት ትቆያለች። የምትነጻባቸው ቀናት እስኪያበቁ ድረስ ምንም ዓይነት ቅዱስ ነገር መንካትም ሆነ ወደ ቅዱሱ ስፍራ መግባት የለባትም።

5 “‘ሴት ልጅ ከወለደች ደግሞ በወር አበባዋ ወቅት እንደምትረክሰው ሁሉ ለ14 ቀን ትረክሳለች። ከደም ራሷን ለማንጻትም ለቀጣዮቹ 66 ቀናት ትቆያለች። 6 ሴትየዋ ወንድ ልጅ ወይም ሴት ልጅ ወልዳ የመንጻቷ ጊዜ ሲያበቃ ለሚቃጠል መባ እንዲሆን አንድ ዓመት ገደማ የሆነው የበግ ጠቦት፣+ ለኃጢአት መባ እንዲሆን ደግሞ አንድ የርግብ ጫጩት ወይም አንድ ዋኖስ ወደ መገናኛ ድንኳኑ መግቢያ ወደ ካህኑ ታመጣለች። 7 እሱም መባዎቹን በይሖዋ ፊት በማቅረብ ያስተሰርይላታል፤ እሷም ከሚፈሳት ደም ትነጻለች። ወንድ ልጅም ሆነ ሴት ልጅ ለወለደች ሴት የሚሠራው ሕግ ይህ ነው። 8 ሆኖም ሴትየዋ በግ ለማቅረብ አቅሟ የማይፈቅድላት ከሆነ ሁለት ዋኖሶች ወይም ሁለት የርግብ ጫጩቶች ታምጣ፤+ አንዱ ለሚቃጠል መባ ሌላው ደግሞ ለኃጢአት መባ ይሆናል። ካህኑም ያስተሰርይላታል፤ እሷም ንጹሕ ትሆናለች።’”

13 ይሖዋ ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፦ 2 “አንድ ሰው በቆዳው ላይ እብጠት፣ እከክ ወይም ቋቁቻ ቢወጣበትና ወደ ሥጋ ደዌነት*+ ቢለወጥበት ወደ ካህኑ አሮን ወይም ካህናት ከሆኑት ወንዶች ልጆቹ ወደ አንዱ ያምጡት።+ 3 ካህኑም በቆዳው ላይ ያለውን ቁስል ይመረምራል። ቁስሉ ባለበት ቦታ ላይ ያለው ፀጉር ወደ ነጭነት ከተለወጠና ቁስሉ ከቆዳው ዘልቆ የገባ ከሆነ ይህ የሥጋ ደዌ ነው። ካህኑ ቁስሉን ከመረመረ በኋላ ግለሰቡ ርኩስ መሆኑን ያስታውቃል። 4 ሆኖም በቆዳው ላይ ያለው ቋቁቻ ነጭ ከሆነና ከቆዳው ዘልቆ የገባ ካልሆነ እንዲሁም በዚያ ቦታ ላይ ያለው ፀጉር ወደ ነጭነት ካልተለወጠ ካህኑ ቁስል የወጣበትን ሰው ለሰባት ቀን ተገልሎ እንዲቆይ ያደርገዋል።+ 5 ከዚያም በሰባተኛው ቀን ካህኑ ሰውየውን ይመረምረዋል፤ ቁስሉ ባለበት ከቆመና በቆዳው ላይ ካልተስፋፋ ካህኑ ሰውየውን ለተጨማሪ ሰባት ቀን ተገልሎ እንዲቆይ ያደርገዋል።

6 “ካህኑም በሰባተኛው ቀን እንደገና ሰውየውን ይመርምረው፤ ቁስሉ ከከሰመና በቆዳው ላይ ካልተስፋፋ ካህኑ ሰውየው ንጹሕ መሆኑን ያስታውቃል፤+ ይህ እከክ ነው። ከዚያም ሰውየው ልብሶቹን ያጥባል፤ ንጹሕም ይሆናል። 7 ሆኖም ሰውየው መንጻቱን ለማረጋገጥ ካህኑ ፊት ከቀረበ በኋላ እከኩ* በቆዳው ላይ እየተስፋፋ ከሄደ እንደገና ካህኑ ፊት ይቀርባል። 8 ካህኑም ይመረምረዋል፤ እከኩ በቆዳው ላይ ተስፋፍቶ ከሆነ ካህኑ ሰውየው ርኩስ መሆኑን ያስታውቃል። ይህ የሥጋ ደዌ ነው።+

9 “አንድ ሰው የሥጋ ደዌ ቢይዘው ወደ ካህኑ እንዲቀርብ ይደረግ፤ 10 ካህኑም ይመረምረዋል።+ በቆዳው ላይ ነጭ እብጠት ካለና በዚያ ቦታ ላይ ያለውን ፀጉር ወደ ነጭነት ከለወጠው እንዲሁም በእብጠቱ ላይ አፉን የከፈተ ቁስል+ ካለ 11 ይህ በቆዳው ላይ የወጣ ሥር የሰደደ የሥጋ ደዌ ነው፤ ካህኑም ሰውየው ርኩስ መሆኑን ያስታውቃል። ሰውየው ርኩስ ስለሆነም ለተወሰነ ጊዜ ተገልሎ እንዲቆይ+ ማድረግ አያስፈልገውም። 12 የሥጋ ደዌው በቆዳው ሁሉ ላይ ቢወጣና የሥጋ ደዌው ካህኑ ሊያየው እስከሚችለው ድረስ ግለሰቡን ከራሱ አንስቶ እስከ እግሮቹ ድረስ ቢያለብሰው 13 እንዲሁም ካህኑ ሲመረምረው የሥጋ ደዌው ቆዳውን ሁሉ አልብሶት ቢያይ ቁስሉ የወጣበት ግለሰብ ንጹሕ* መሆኑን ያስታውቃል። ቆዳው ሙሉ በሙሉ ወደ ነጭነት ተለውጧል፤ ሰውየውም ንጹሕ ነው። 14 ሆኖም በቆዳው ላይ አፉን የከፈተ ቁስል በወጣበት በማንኛውም ጊዜ ሰውየው ርኩስ ይሆናል። 15 ካህኑ አፉን የከፈተ ቁስል ካየ ሰውየው ርኩስ መሆኑን ያስታውቃል።+ አፉን የከፈተው ቁስል ርኩስ ነው። ይህ የሥጋ ደዌ ነው።+ 16 ሆኖም አፉን የከፈተው ቁስል እንደገና ወደ ነጭነት ከተለወጠ ሰውየው ወደ ካህኑ ይመጣል። 17 ካህኑም ይመረምረዋል፤+ ቁስሉ ወደ ነጭነት ከተለወጠ ካህኑ ቁስሉ የወጣበት ግለሰብ ንጹሕ መሆኑን ያስታውቃል። ሰውየው ንጹሕ ነው።

18 “አንድ ሰው በቆዳው ላይ እባጭ ቢወጣበትና ቢድን 19 ሆኖም እባጩ በነበረበት ቦታ ላይ ነጭ እብጠት ወይም ነጣ ያለ ቀይ ቋቁቻ ቢወጣ ሰውየው ራሱን ለካህን ያሳይ። 20 ካህኑም ቁስሉን ይመረምረዋል፤+ ቁስሉ ከቆዳው ዘልቆ የገባ ከሆነና በዚያ ቦታ ላይ ያለው ፀጉር ወደ ነጭነት ከተለወጠ ካህኑ ሰውየው ርኩስ መሆኑን ያስታውቃል። ይህ በእባጩ ላይ የወጣ የሥጋ ደዌ ነው። 21 ይሁንና ካህኑ ቁስሉን ሲመረምረው በላዩ ላይ ነጭ ፀጉር ከሌለና ከቆዳው ዘልቆ የገባ ካልሆነ እንዲሁም እየከሰመ ከሆነ ካህኑ ሰውየውን ለሰባት ቀን ተገልሎ እንዲቆይ ያደርገዋል።+ 22 ቁስሉ በቆዳው ላይ እየተስፋፋ መሆኑ በግልጽ የሚታይ ከሆነ ካህኑ ሰውየው ርኩስ መሆኑን ያስታውቃል። ይህ ደዌ ነው። 23 ይሁን እንጂ ቋቁቻው ባለበት ከቆመና ካልተስፋፋ ይህ እባጩ ያስከተለው ቁስል ነው፤ ካህኑም ሰውየው ንጹሕ መሆኑን ያስታውቃል።+

24 “ወይም አንድ ሰው እሳት አቃጥሎት በሰውነቱ ቆዳ ላይ ጠባሳ ቢተውና ጠባሳው ላይ ያለው ያልሻረ ቁስል ነጣ ያለ ቀይ ወይም ነጭ ቋቁቻ ቢሆን 25 ካህኑ ቁስሉን ይመረምረዋል። በቋቁቻው ላይ ያለው ፀጉር ወደ ነጭነት ከተለወጠና ቁስሉ ከቆዳው ዘልቆ የገባ ከሆነ ይህ በጠባሳው ላይ የወጣ የሥጋ ደዌ ነው፤ ካህኑም ሰውየው ርኩስ መሆኑን ያስታውቃል። ይህ የሥጋ ደዌ ነው። 26 ይሁንና ካህኑ ሲመረምረው በቋቁቻው ላይ ነጭ ፀጉር ከሌለና ቁስሉ ከቆዳው ዘልቆ የገባ ካልሆነ እንዲሁም እየከሰመ ከሆነ ካህኑ ሰውየውን ለሰባት ቀን ተገልሎ እንዲቆይ ያደርገዋል።+ 27 ካህኑም በሰባተኛው ቀን ሰውየውን ይመረምረዋል፤ ቁስሉ በቆዳው ላይ እየተስፋፋ መሆኑ በግልጽ የሚታይ ከሆነ ካህኑ ሰውየው ርኩስ መሆኑን ያስታውቃል። ይህ የሥጋ ደዌ ነው። 28 ይሁንና ቋቁቻው ባለበት ከቆመና በቆዳው ላይ ካልተስፋፋ እንዲሁም ከከሰመ ይህ ጠባሳው ያስከተለው እብጠት ነው፤ ይህ የጠባሳው ቁስል ስለሆነ ካህኑ ሰውየው ንጹሕ መሆኑን ያስታውቃል።

29 “በአንድ ወንድ ወይም በአንዲት ሴት ራስ ወይም አገጭ ላይ ቁስል ቢወጣ 30 ካህኑ ቁስሉን ይመረምረዋል።+ ቁስሉ ከቆዳው ዘልቆ የገባ ከሆነ እንዲሁም በዚያ ቦታ ላይ ያለው ፀጉር ቢጫ ከሆነና ከሳሳ ካህኑ ያ ሰው ርኩስ መሆኑን ያስታውቃል፤ ይህ በራስ ቆዳ ወይም በጢም ላይ የሚወጣ ቁስል ነው። ይህ የራስ ወይም የአገጭ የሥጋ ደዌ ነው። 31 ሆኖም ካህኑ ቁስሉ ከቆዳው ዘልቆ የገባ አለመሆኑንና በዚያ ቦታ ላይ ጥቁር ፀጉር አለመኖሩን ካየ ቁስሉ የወጣበትን ሰው ለሰባት ቀን ተገልሎ እንዲቆይ ያድርገው።+ 32 ካህኑም በሰባተኛው ቀን ቁስሉን ይመረምረዋል፤ ቁስሉ ካልተስፋፋና በዚያ ቦታ ላይ ቢጫ ፀጉር ካልወጣ እንዲሁም ቁስሉ ከቆዳው ዘልቆ የገባ ካልሆነ 33 ሰውየው ፀጉሩን ይላጭ፤ ቁስሉ ያለበትን ቦታ ግን አይላጨውም። ከዚያም ካህኑ ቁስሉ የወጣበትን ሰው ለሰባት ቀን ተገልሎ እንዲቆይ ያደርገዋል።

34 “ካህኑም በሰባተኛው ቀን ቁስሉ ያለበትን ቦታ እንደገና ይመረምረዋል፤ ቁስሉ በቆዳው ላይ ካልተስፋፋና ከቆዳው ዘልቆ የገባ ካልሆነ ካህኑ ሰውየው ንጹሕ መሆኑን ያስታውቅ፤ ሰውየውም ልብሶቹን ይጠብ፤ ንጹሕም ይሁን። 35 ሆኖም ሰውየው ከነጻ በኋላ ቁስሉ በቆዳው ላይ እየተስፋፋ መሆኑ በግልጽ ከታየ 36 ካህኑ ይመረምረዋል፤ ቁስሉ በቆዳው ላይ ከተስፋፋ ካህኑ ቢጫ ፀጉር መኖር አለመኖሩን ማየት አያስፈልገውም፤ ሰውየው ርኩስ ነው። 37 ሆኖም ካህኑ ሲመረምረው ቁስሉ ካልተስፋፋና በዚያ ቦታ ጥቁር ፀጉር ከበቀለ ቁስሉ ድኗል ማለት ነው። ሰውየው ንጹሕ ነው፤ ካህኑም ንጹሕ መሆኑን ያስታውቃል።+

38 “አንድ ወንድ ወይም አንዲት ሴት በቆዳቸው ላይ ቋቁቻ ቢወጣና ቋቁቻው ደግሞ ነጭ ቢሆን 39 ካህኑ ይመረምራቸዋል።+ በቆዳው ላይ የወጣው ቋቁቻ ደብዘዝ ያለ ነጭ ከሆነ ይህ ቆዳው ላይ የወጣ ጉዳት የሌለው ሽፍታ ነው። ሰውየው ንጹሕ ነው።

40 “አንድ ወንድ ራሱ ቢመለጥና ራሰ በራ ቢሆን ሰውየው ንጹሕ ነው። 41 ሰውየው ከፊት በኩል ቢመለጥና ራሰ በራ ቢሆን ንጹሕ ነው። 42 ሆኖም በራሱ ወይም በግንባሩ ላይ ባለው በራ ላይ ቀላ ያለ ነጭ ቁስል ቢወጣበት ይህ በራሱ ወይም በግንባሩ ላይ የወጣ ሥጋ ደዌ ነው። 43 ካህኑም ሰውየውን ይመረምረዋል፤ በአናቱ ወይም በግንባሩ ላይ ባለው በራ ላይ የወጣው ቁስል ያስከተለው እብጠት ቀላ ያለ ነጭ ከሆነና በቆዳው ላይ ሲታይ የሥጋ ደዌ የሚመስል ከሆነ 44 ሰውየው የሥጋ ደዌ በሽተኛ ነው። ርኩስ ነው፤ በራሱም ላይ ባለው ደዌ የተነሳ ካህኑ ሰውየው ርኩስ መሆኑን ያስታውቅ። 45 የሥጋ ደዌ ያለበት ሰው ልብሶቹ የተቀዳደዱ ይሁኑ፤ ፀጉሩም ይንጨብረር፤ አፍንጫው ሥር እስካለው ጢም ድረስ ተሸፋፍኖ ‘ርኩስ ነኝ፣ ርኩስ ነኝ!’ እያለ ይጩኽ። 46 ሰውየው ደዌው በላዩ ላይ ባለበት ጊዜ ሁሉ ርኩስ ይሆናል። ርኩስ ስለሆነም ከሰዎች ተገልሎ መኖር አለበት። መኖሪያውም ከሰፈሩ ውጭ ይሆናል።+

47 “ደዌው ከሱፍም ሆነ ከበፍታ የተሠራን ልብስ ቢበክል 48 ወይም የበፍታውንም ሆነ የሱፉን ድር ወይም ማግ አሊያም ቁርበትን ወይም ደግሞ ከቆዳ የተሠራን ማንኛውንም ነገር ቢበክል 49 እንዲሁም ደዌው ያስከተለው ወደ ቢጫነት ያደላ አረንጓዴ ወይም ቀላ ያለ ምልክት ልብሱን፣ ቆዳውን፣ ድሩን፣ ማጉን ወይም ደግሞ ከቆዳ የተሠራውን የትኛውንም ዕቃ ቢበክል ይህ በደዌ ምክንያት የተከሰተ ብክለት ነው፤ ካህኑ እንዲያየው መደረግ አለበት። 50 ካህኑም ደዌውን ይመረምረዋል፤ ደዌው ያለበትም ነገር ለሰባት ቀን ተገልሎ እንዲቀመጥ ያድርግ።+ 51 በሰባተኛው ቀን ደዌውን ሲመረምረው ደዌው በልብሱ፣ በድሩ፣ በማጉ ወይም በቆዳው ላይ (ቆዳው ለማንኛውም ዓይነት አገልግሎት የሚውል ይሁን) ተስፋፍቶ ቢገኝ ደዌው አደገኛ ደዌ ነው፤ ዕቃውም ርኩስ ነው።+ 52 እሱም ደዌው ያለበትን ልብስ ወይም የሱፍም ሆነ የበፍታ ድር ወይም ማግ አሊያም ደግሞ ከቆዳ የተሠራ ማንኛውም ዕቃ ያቃጥል፤ ምክንያቱም ይህ አደገኛ ደዌ ነው። በእሳት መቃጠል ይኖርበታል።

53  “ሆኖም ካህኑ ሲመረምረው ደዌው በልብሱ ወይም በድሩ አሊያም በማጉ ወይም ደግሞ ከቆዳ በተሠራው በማንኛውም ዕቃ ላይ ካልተስፋፋ 54 ካህኑ ደዌው ያለበትን ነገር እንዲያጥቡት ያዛል፤ ከዚያም እንደገና ለሰባት ቀን ተገልሎ እንዲቀመጥ ያደርጋል። 55 የተበከለው ዕቃ በደንብ ከታጠበ በኋላ ካህኑ ይመረምረዋል። ደዌው ባይስፋፋም እንኳ ብክለቱ መልኩን ካልቀየረ ዕቃው ርኩስ ነው። ዕቃው ከውስጡ ወይም ከውጭው ስለተበላ በእሳት አቃጥለው።

56 “ሆኖም ዕቃው በደንብ ከታጠበ በኋላ ካህኑ ሲመረምረው የተበከለው ክፍል ከደበዘዘ ያን ቦታ ከልብሱ ወይም ከቆዳው አሊያም ከድሩ ወይም ደግሞ ከማጉ ላይ ቀዶ ያወጣዋል። 57  ይሁንና ደዌው በልብሱ ወይም በድሩ አሊያም በማጉ ወይም ደግሞ ከቆዳ በተሠራው በማንኛውም ዕቃ ላይ በሌላ ቦታ አሁንም ከታየ ደዌው እየተስፋፋ ነው፤ ስለዚህ በደዌው የተበከለውን ማንኛውንም ዕቃ በእሳት አቃጥለው።+ 58 ሆኖም በልብሱ ወይም በድሩ አሊያም በማጉ ወይም ደግሞ ከቆዳ በተሠራው በማንኛውም ዕቃ ላይ የተከሰተው ብክለት ስታጥበው ከለቀቀ ዕቃው ለሁለተኛ ጊዜ ይታጠብ፤ ንጹሕም ይሆናል።

59 “ከሱፍ ወይም ከበፍታ በተሠራ ልብስ አሊያም በድር ወይም በማግ አሊያም ደግሞ ከቆዳ በተሠራ በማንኛውም ዕቃ ላይ የወጣን ደዌ በተመለከተ ዕቃው ንጹሕ ነው ብሎ ለማስታወቅም ሆነ ርኩስ ነው ለማለት ሕጉ ይህ ነው።”

14 ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ 2 “የሥጋ ደዌ ያለበት አንድ ሰው መንጻቱን ለማረጋገጥ ካህኑ ፊት እንዲቀርብ+ በሚደረግበት ዕለት የሚኖረው ሕግ ይህ ነው። 3 ካህኑ ከሰፈሩ ውጭ ወጥቶ ሰውየውን ይመረምረዋል። የሥጋ ደዌ ይዞት የነበረው ሰው ከሥጋ ደዌው ከዳነ 4 ካህኑ ሰውየው ራሱን ለማንጻት በሕይወት ያሉ ሁለት ንጹሕ ወፎችን፣ የአርዘ ሊባኖስ እንጨት፣ ደማቅ ቀይ ማግና ሂሶጵ እንዲያመጣ ያዘዋል።+ 5 እንዲሁም ካህኑ አንደኛዋ ወፍ ከወራጅ ውኃ የተቀዳ ውኃ ባለበት የሸክላ ዕቃ ውስጥ እንድትታረድ ትእዛዝ ይሰጣል። 6 በሕይወት ያለችውን ወፍ ደግሞ ከአርዘ ሊባኖስ እንጨቱ፣ ከደማቁ ቀይ ማግና ከሂሶጱ ጋር ወስዶ ከወራጅ ውኃ በተቀዳው ውኃ ላይ በታረደችው ወፍ ደም ውስጥ ይንከራቸው። 7 ከዚያም ራሱን ከሥጋ ደዌ በሚያነጻው ሰው ላይ ሰባት ጊዜ ይረጨዋል፤ ሰውየውም ንጹሕ መሆኑን ያስታውቃል፤ በሕይወት ያለችውንም ወፍ ሜዳ ላይ ይለቃታል።+

8 “ራሱን የሚያነጻውም ሰው ልብሶቹን ይጠብ፤ ፀጉሩንም በሙሉ ይላጭ፤ ገላውንም በውኃ ይታጠብ፤ ንጹሕም ይሆናል። ይህን ካደረገ በኋላ ወደ ሰፈሩ መግባት ይችላል፤ ሆኖም ለሰባት ቀን ከድንኳኑ ውጭ ይቀመጣል። 9 በሰባተኛው ቀን በራሱ ላይ ያለውን ፀጉር፣ ጺሙንና ቅንድቡን በሙሉ ይላጭ። ፀጉሩን በሙሉ ከተላጨ በኋላ ልብሶቹን ያጥባል እንዲሁም ገላውን በውኃ ይታጠባል፤ ከዚያም ንጹሕ ይሆናል።

10 “በስምንተኛው ቀን እንከን የሌለባቸውን ሁለት የበግ ጠቦቶች፣ አንድ ዓመት ገደማ የሆናትን እንከን የሌለባት አንዲት እንስት የበግ ጠቦት፣+ የእህል መባ እንዲሆን በዘይት የተለወሰ ሦስት አሥረኛ ኢፍ* የላመ ዱቄትና+ አንድ የሎግ መስፈሪያ* ዘይት ያመጣል፤+ 11 ሰውየው ንጹሕ መሆኑን የሚያስታውቀው ካህንም ራሱን የሚያነጻውን ሰው ከመባዎቹ ጋር በመገናኛ ድንኳኑ መግቢያ በይሖዋ ፊት ያቀርበዋል። 12 ካህኑም አንደኛውን የበግ ጠቦት ወስዶ ከአንዱ የሎግ መስፈሪያ ዘይት ጋር በማድረግ የበደል መባ እንዲሆን ያቀርበዋል፤+ እነዚህንም የሚወዘወዝ መባ አድርጎ በይሖዋ ፊት ወዲያና ወዲህ ይወዘውዛቸዋል።+ 13 ከዚያም የበግ ጠቦቱን የኃጢአት መባውና የሚቃጠል መባው ዘወትር በሚታረዱበት ቦታ+ ይኸውም ቅዱስ በሆነ ስፍራ ያርደዋል፤ ምክንያቱም እንደ ኃጢአት መባው ሁሉ የበደል መባውም የካህኑ ድርሻ ነው።+ ይህ እጅግ ቅዱስ የሆነ ነገር ነው።+

14 “ካህኑም ከበደል መባው ደም ላይ የተወሰነውን ይወስዳል፤ ከዚያም ራሱን የሚያነጻውን ሰው ቀኝ ጆሮ ጫፍ፣ የቀኝ እጁን አውራ ጣት እንዲሁም የቀኝ እግሩን አውራ ጣት ይቀባል። 15 ካህኑም ከአንዱ የሎግ መስፈሪያ ዘይት+ ላይ የተወሰነውን በራሱ የግራ እጅ መዳፍ ላይ ያንቆረቁረዋል። 16 ከዚያም የቀኝ እጁን ጣት በግራ እጁ መዳፍ ላይ ባለው ዘይት ውስጥ ይነክራል፤ ከዘይቱም የተወሰነውን በይሖዋ ፊት ሰባት ጊዜ በጣቱ ይረጨዋል። 17 በእጁም መዳፍ ላይ ከቀረው ዘይት ላይ የተወሰነውን ወስዶ ራሱን የሚያነጻውን ሰው ቀኝ ጆሮ ጫፍ፣ የቀኝ እጁን አውራ ጣት እንዲሁም የቀኝ እግሩን አውራ ጣት ይቀባል፤ በበደል መባው ደም ላይ ደርቦ ይቀባዋል። 18 ካህኑም በእጁ መዳፍ ላይ የቀረውን ዘይት ራሱን በሚያነጻው ሰው ራስ ላይ ያፈሰዋል፤ ለሰውየውም በይሖዋ ፊት ያስተሰርይለታል።+

19 “ካህኑ ለኃጢአት መባ የሚሆነውን እንስሳ ይሠዋል፤+ ራሱን ከርኩሰቱ ለሚያነጻውም ሰው ያስተሰርይለታል፤ ከዚያም ለሚቃጠል መባ የሚሆነውን እንስሳ ያርዳል። 20 ካህኑም የሚቃጠለውን መባና የእህሉን መባ+ በመሠዊያው ላይ ያቀርባል፤ ለሰውየውም ያስተሰርይለታል፤+ እሱም ንጹሕ ይሆናል።+

21 “ሆኖም ሰውየው ድሃ ከሆነና ይህን ለማቅረብ አቅሙ ካልፈቀደለት ለራሱ ማስተሰረያ እንዲሆንለት ለሚወዘወዝ መባ አንድ የበግ ጠቦት የበደል መባ አድርጎ ያመጣል፤ በተጨማሪም ለእህል መባ እንዲሆን በዘይት የተለወሰ አንድ አሥረኛ ኢፍ* የላመ ዱቄት፣ አንድ የሎግ መስፈሪያ ዘይት 22 እንዲሁም ከሁለት ዋኖሶች ወይም ከሁለት የርግብ ጫጩቶች አቅሙ የቻለውን ያቀርባል፤ አንደኛው ለኃጢአት መባ ሌላኛው ደግሞ ለሚቃጠል መባ ይሆናል።+ 23 መንጻቱን ለማረጋገጥም በስምንተኛው ቀን+ እነዚህን ይዞ በመገናኛ ድንኳኑ መግቢያ በይሖዋ ፊት ወዳለው ወደ ካህኑ ይመጣል።+

24 “ካህኑም ለበደል መባ እንዲሆን የቀረበውን የበግ ጠቦትና+ አንዱን የሎግ መስፈሪያ ዘይት ይወስዳል፤ እነዚህንም የሚወዘወዝ መባ አድርጎ በይሖዋ ፊት ወዲያና ወዲህ ይወዘውዛቸዋል።+ 25 ከዚያም ለበደል መባ እንዲሆን የቀረበውን የበግ ጠቦት ያርዳል፤ ከበደል መባው ደም ላይ የተወሰነውን ወስዶ ራሱን የሚያነጻውን ሰው ቀኝ ጆሮ ጫፍ፣ የቀኝ እጁን አውራ ጣት እንዲሁም የቀኝ እግሩን አውራ ጣት ይቀባል።+ 26 ካህኑም ከዘይቱ የተወሰነውን በራሱ የግራ እጅ መዳፍ ላይ ያንቆረቁረዋል።+ 27 በግራ እጁ መዳፍ ላይ ካለው ዘይት የተወሰነውን በቀኝ እጁ ጣት በይሖዋ ፊት ሰባት ጊዜ ይረጨዋል። 28 በእጁ መዳፍ ላይ ካለው ዘይት የተወሰነውን ወስዶ የበደል መባውን ደም በቀባበት ቦታ ላይ ማለትም ራሱን በሚያነጻው ሰው ቀኝ ጆሮ ጫፍ፣ በቀኝ እጁ አውራ ጣት እንዲሁም በቀኝ እግሩ አውራ ጣት ላይ ይቀባል። 29 ከዚያም በእጁ መዳፍ ላይ የቀረውን ዘይት ራሱን በሚያነጻው ሰው ራስ ላይ ያፈሰዋል፤ ይህን የሚያደርገው በይሖዋ ፊት እንዲያስተሰርይለት ነው።

30 “ካህኑም ሰውየው አቅሙ ፈቅዶ ካመጣቸው ዋኖሶች ወይም የርግብ ጫጩቶች መካከል አንዱን ያቀርባል፤+ 31 አቅሙ ፈቅዶ ካመጣቸውም መካከል አንዱን የኃጢአት መባ ሌላኛውን ደግሞ የሚቃጠል መባ+ አድርጎ ከእህል መባው ጋር ያቀርባል፤ ካህኑም ራሱን ለሚያነጻው ሰው በይሖዋ ፊት ያስተሰርይለታል።+

32 “የሥጋ ደዌ የነበረበትን ሆኖም መንጻቱን ለማረጋገጥ የሚያስፈልገውን ነገር ለማቅረብ አቅሙ የማይፈቅድለትን ሰው በተመለከተ ሕጉ ይህ ነው።”

33 ከዚያም ይሖዋ ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፦ 34 “ርስት አድርጌ ወደምሰጣችሁ+ ወደ ከነአን ምድር+ በምትገቡበት ጊዜ በምድራችሁ ውስጥ የሚገኝን አንድ ቤት በደዌ ብበክለው+ 35 የቤቱ ባለቤት ወደ ካህኑ መጥቶ ‘አንድ የሚበክል ነገር ቤቴ ውስጥ ታይቷል’ በማለት ይንገረው። 36 ካህኑም ቤቱ ውስጥ ያለውን ነገር ሁሉ ርኩስ ነው እንዳይል የሚበክለውን ነገር ለመመርመር ወደ ውስጥ ከመግባቱ በፊት ቤቱ ውስጥ ያለውን ዕቃ በሙሉ እንዲያወጡ ትእዛዝ ይሰጣል፤ ከዚያም ካህኑ ቤቱን ለመመርመር ወደ ውስጥ ይገባል። 37 እሱም ብክለቱ የታየበትን ቦታ ይመረምራል፤ በቤቱም ግድግዳ ላይ ወደ ቢጫነት ያደላ አረንጓዴ ወይም ቀላ ያለ የተቦረቦረ ምልክት ቢታይና ይህም ከላይ ወደ ውስጥ ዘልቆ የገባ ከሆነ 38 ካህኑ ከቤቱ ውስጥ ወደ ደጃፉ ወጥቶ ቤቱን ለሰባት ቀን ያሽገዋል።+

39 “ከዚያም ካህኑ በሰባተኛው ቀን ተመልሶ በመምጣት ቤቱን ይመረምረዋል። ቤቱን የበከለው ነገር በግድግዳው ላይ ተስፋፍቶ ከሆነ 40 ካህኑ ትእዛዝ ይሰጣል፤ የተበከሉትም ድንጋዮች ተሰርስረው መውጣትና ከከተማዋ ውጭ ወዳለ ርኩስ የሆነ ስፍራ መጣል አለባቸው። 41 ከዚያም ቤቱ ከውስጥ በኩል በደንብ እንዲፈቀፈቅ ያደርጋል፤ ተፈቅፍቆ የተነሳው ልስንና ምርጊትም ከከተማዋ ውጭ በሚገኝ ርኩስ የሆነ ስፍራ ይደፋ። 42 ባወጧቸውም ድንጋዮች ቦታ ሌሎች ድንጋዮችን ያስገቡ፤ ቤቱም በአዲስ ምርጊት እንዲለሰን ያድርግ።

43 “ድንጋዮቹ ተሰርስረው ከወጡና ቤቱ ተፈቅፍቆ ዳግመኛ ከተለሰነ በኋላ ብክለቱ እንደገና ተመልሶ በቤቱ ላይ ከታየ 44 ካህኑ ገብቶ ይመረምረዋል። ብክለቱ በቤቱ ውስጥ ተስፋፍቶ ከሆነ ይህ በቤቱ ላይ የወጣ አደገኛ ደዌ+ ነው። ቤቱ ርኩስ ነው። 45 ቤቱ ይኸውም ድንጋዮቹ፣ እንጨቶቹ፣ ልስኑና ምርጊቱ እንዲፈርስ ያደርጋል፤ ከከተማዋ ውጭ በሚገኝ ርኩስ የሆነ ስፍራም እንዲጣል ያደርጋል።+ 46 ሆኖም ቤቱ ታሽጎ+ በነበረበት በየትኛውም ቀን ወደዚያ ቤት የገባ ሰው እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል፤+ 47 እዚያ ቤት ውስጥ የተኛ ማንኛውም ሰው ልብሶቹን ማጠብ ይኖርበታል፤ እንዲሁም እዚያ ቤት ውስጥ የበላ ማንኛውም ሰው ልብሶቹን ማጠብ ይኖርበታል።

48 “ይሁንና ካህኑ መጥቶ ሲያየው ቤቱ ከተለሰነ በኋላ ብክለቱ በቤቱ ውስጥ ካልተስፋፋ ቤቱ ንጹሕ መሆኑን ያስታውቃል፤ ምክንያቱም ብክለቱ ጠፍቷል። 49 ቤቱንም ከርኩሰት* ለማንጻት ሁለት ወፎች፣ የአርዘ ሊባኖስ እንጨት፣ ደማቅ ቀይ ማግና ሂሶጵ ይወስዳል።+ 50 አንደኛዋንም ወፍ ከወራጅ ውኃ የተቀዳ ውኃ ባለበት የሸክላ ዕቃ ውስጥ ያርዳታል። 51 ከዚያም የአርዘ ሊባኖስ እንጨቱን፣ ሂሶጱን፣ ደማቁን ቀይ ማግና በሕይወት ያለችውን ወፍ ወስዶ በታረደችው ወፍ ደምና ከወራጅ ውኃ በተቀዳው ውኃ ውስጥ ይነክራቸዋል፤ ወደ ቤቱም ሰባት ጊዜ ይርጨው።+ 52 ቤቱንም በወፏ ደም፣ ከወራጅ ውኃ በተቀዳው ውኃ፣ በሕይወት ባለችው ወፍ፣ በአርዘ ሊባኖስ እንጨቱ፣ በሂሶጱና በደማቁ ቀይ ማግ ከርኩሰት* ያነጻዋል። 53  በሕይወት ያለችውንም ወፍ ከከተማዋ ውጭ ወደ ሜዳ ይለቃታል፤ ለቤቱም ያስተሰርይለታል፤ ቤቱም ንጹሕ ይሆናል።

54 “ከማንኛውም ዓይነት የሥጋ ደዌ፣ በራስ ቆዳ ወይም በጢም ላይ ከሚወጣ ቁስል፣+ 55 በልብስ+ ወይም በቤት+ ላይ ከሚወጣ ደዌ፣ 56 ከእባጭ፣ ከእከክና ከቋቁቻ+ ጋር በተያያዘ 57  አንድ ነገር ርኩስ ወይም ንጹሕ መሆኑን ለመወሰን የሚያገለግለው ሕግ ይህ ነው።+ የሥጋ ደዌን በተመለከተ ሕጉ ይህ ነው።”+

15 ይሖዋ ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፦ 2 “ለእስራኤላውያን እንዲህ ብላችሁ ንገሯቸው፦ ‘አንድ ወንድ ከብልቱ* ፈሳሽ የሚወጣ ከሆነ ይህ ፈሳሽ ርኩስ ያደርገዋል።+ 3 ሰውየው በፈሳሹ የተነሳ ርኩስ ነው፤ ፈሳሹ ከብልቱ እየፈሰሰ ቢሆንም ወይም ብልቱን ቢዘጋው ሰውየው ርኩስ ነው።

4 “‘ፈሳሽ የሚወጣው ሰው የተኛበት አልጋም ርኩስ ይሆናል፤ ይህ ሰው የተቀመጠበት ማንኛውም ነገርም ርኩስ ይሆናል። 5 የሰውየውን አልጋ የነካ ሰው ልብሶቹን ማጠብ ይኖርበታል፤ ገላውንም በውኃ መታጠብ አለበት፤ እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ይሆናል።+ 6 እንዲሁም ፈሳሽ የሚወጣው ሰው ተቀምጦበት በነበረ ነገር ላይ የተቀመጠ ማንኛውም ሰው ልብሶቹን ማጠብ ይኖርበታል፤ ገላውንም በውኃ መታጠብ አለበት፤ እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ይሆናል። 7 ፈሳሽ የሚወጣውን ሰው፣ ሰውነት የነካ ማንኛውም ሰው ልብሶቹን ማጠብ ይኖርበታል፤ ገላውንም በውኃ መታጠብ አለበት፤ እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ይሆናል። 8 ፈሳሽ የሚወጣው ሰው ንጹሕ በሆነ ሰው ላይ ቢተፋ የተተፋበት ሰው ልብሶቹን ማጠብ ይኖርበታል፤ ገላውንም በውኃ መታጠብ አለበት፤ እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ይሆናል። 9 ፈሳሽ የሚወጣው ሰው የተቀመጠበት ኮርቻ ርኩስ ይሆናል። 10 ይህ ሰው የተቀመጠበትን የትኛውንም ነገር የነካ ማንኛውም ሰው እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል፤ እነዚህን ነገሮች የያዘ ማንኛውም ሰው ልብሶቹን ማጠብ ይኖርበታል፤ ገላውንም በውኃ መታጠብ አለበት፤ እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ይሆናል። 11 ፈሳሽ የሚወጣው ሰው+ እጆቹን በውኃ ሳይታጠብ አንድን ሰው ቢነካ የተነካው ሰው ልብሶቹን ማጠብ ይኖርበታል፤ ገላውንም በውኃ መታጠብ አለበት፤ እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ይሆናል። 12 ፈሳሽ የሚወጣው ሰው የነካው የሸክላ ዕቃ ይሰበር፤ ማንኛውም የእንጨት ዕቃ ደግሞ በውኃ ይታጠብ።+

13 “‘እንግዲህ ፈሳሹ ቢቆምና ሰውየው ከፈሳሹ ቢነጻ ንጹሕ ለመሆን ሰባት ቀን ይቁጠር፤ ልብሶቹን ይጠብ፤ ገላውንም በምንጭ ውኃ ይታጠብ፤ ንጹሕም ይሆናል።+ 14 በስምንተኛውም ቀን ሁለት ዋኖሶችን ወይም ሁለት የርግብ ጫጩቶችን ይውሰድ፤+ እነዚህንም ይዞ በመገናኛ ድንኳኑ መግቢያ በይሖዋ ፊት በመቅረብ ለካህኑ ይስጥ። 15 ካህኑም አንዱን የኃጢአት መባ ሌላኛውን ደግሞ የሚቃጠል መባ አድርጎ ያቀርባቸዋል፤ ካህኑም ስለ ፈሳሹ ለሰውየው በይሖዋ ፊት ያስተሰርይለታል።

16 “‘አንድ ወንድ ዘር ቢፈሰው ገላውን በውኃ መታጠብ አለበት፤ እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ይሆናል።+ 17 የፈሰሰው ዘር የነካውን ማንኛውንም ዓይነት ልብስ ወይም ቁርበት በውኃ ማጠብ አለበት፤ እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ይሆናል።

18 “‘አንድ ወንድ ከአንዲት ሴት ጋር ቢተኛና ዘሩ ቢፈስ ገላቸውን በውኃ መታጠብ አለባቸው፤ እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ይሆናሉ።+

19 “‘አንዲት ሴት ከሰውነቷ ደም ቢፈሳት በወር አበባዋ የተነሳ ርኩስ እንደሆነች ለሰባት ቀን ትቀጥላለች፤+ እንዲሁም እሷን የሚነካ ማንኛውም ሰው እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል።+ 20 በወር አበባዋ የተነሳ ርኩስ በሆነችባቸው ጊዜያት የተኛችበት ማንኛውም ነገር ርኩስ ይሆናል፤ እንዲሁም የተቀመጠችበት ማንኛውም ነገር ርኩስ ይሆናል።+ 21 አልጋዋን የነካ ማንኛውም ሰው ልብሶቹን ማጠብ ይኖርበታል፤ ገላውንም በውኃ መታጠብ አለበት፤ እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ይሆናል። 22 እሷ ተቀምጣበት የነበረውን የትኛውንም ነገር የነካ ማንኛውም ሰው ልብሶቹን ማጠብ ይኖርበታል፤ ገላውንም በውኃ መታጠብ አለበት፤ እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ይሆናል። 23 የተቀመጠችው አልጋ ላይም ይሁን ሌላ ነገር ላይ ሰውየው ያን መንካቱ እስከ ማታ ድረስ እንዲረክስ ያደርገዋል።+ 24 አንድ ወንድ ከእሷ ጋር ቢተኛና በወር አበባዋ ቢረክስ+ ሰውየው ለሰባት ቀን ርኩስ ይሆናል፤ የተኛበት አልጋም ርኩስ ይሆናል።

25 “‘አንዲት ሴት የወር አበባዋ ከሚመጣበት ከተለመደው ጊዜ ውጭ ለብዙ ቀናት ደም ቢፈሳት+ ወይም በወር አበባዋ ወቅት ከወትሮው ረዘም ላለ ጊዜ ደም ቢፈሳት+ የወር አበባዋ በሚመጣባቸው ቀናት እንደሚሆነው ፈሳሽ በሚፈሳት ጊዜ ሁሉ ርኩስ ትሆናለች። 26 ፈሳሽ በሚፈሳት ቀናት ሁሉ የተኛችበት አልጋ በወር አበባዋ የተነሳ ርኩስ በሆነችባቸው ጊዜያት እንደተኛችበት አልጋ ይሆናል፤+ እንዲሁም የተቀመጠችበት ማንኛውም ነገር በወር አበባዋ ወቅት ርኩስ እንደሚሆን ሁሉ በዚህ ጊዜም ርኩስ ይሆናል። 27 እነዚህን ነገሮች የነካ ማንኛውም ሰው ርኩስ ይሆናል፤ ልብሶቹንም ማጠብ ይኖርበታል፤ ገላውንም በውኃ መታጠብ አለበት፤ እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ይሆናል።+

28 “‘ይሁን እንጂ ይፈሳት ከነበረው ፈሳሽ በምትነጻበት ጊዜ ለራሷ ሰባት ቀን ትቆጥራለች፤ ከዚያ በኋላ ንጹሕ ትሆናለች።+ 29 በስምንተኛውም ቀን ሁለት ዋኖሶችን ወይም ሁለት የርግብ ጫጩቶችን ትውሰድ፤+ እነዚህንም በመገናኛ ድንኳኑ መግቢያ ወዳለው ወደ ካህኑ ታመጣቸዋለች።+ 30 ካህኑም አንዱን ለኃጢአት መባ ሌላኛውን ደግሞ ለሚቃጠል መባ ያደርገዋል፤ ካህኑም የሚፈሳትን ርኩስ ፈሳሽ አስመልክቶ ለሴትየዋ በይሖዋ ፊት ያስተሰርይላታል።+

31 “‘በመካከላቸው ያለውን የማደሪያ ድንኳኔን በማርከስ በርኩሰታቸው እንዳይሞቱ በዚህ መንገድ እስራኤላውያንን ከርኩሰታቸው ለዩአቸው።+

32 “‘ፈሳሽ የሚወጣውን ወንድ፣ ዘሩ በመፍሰሱ የተነሳ ርኩስ የሆነውን ወንድ፣+ 33 በወር አበባዋ ላይ በመሆኗ ርኩስ የሆነችን ሴት፣+ ወንድም ሆነ ሴት ከሰውነቱ ፈሳሽ የሚወጣውን ማንኛውንም ሰው+ እንዲሁም ርኩስ ከሆነች ሴት ጋር የተኛን ወንድ በተመለከተ ሕጉ ይህ ነው።’”

16 ሁለቱ የአሮን ወንዶች ልጆች ይሖዋ ፊት በመቅረባቸው የተነሳ ከሞቱ+ በኋላ ይሖዋ ሙሴን አነጋገረው። 2 ይሖዋም እንዲህ አለው፦ “እኔ ከመክደኛው በላይ+ በደመና ውስጥ+ ስለምገለጥ በመጋረጃው ውስጥ+ ወዳለው ቅዱስ ስፍራ+ ይኸውም በታቦቱ ላይ ወዳለው መክደኛ ፊት በፈለገው ጊዜ እንዳይገባና በዚህም የተነሳ እንዳይሞት+ ለወንድምህ ለአሮን ንገረው።

3 “አሮን ወደተቀደሰው ስፍራ በሚገባበት ጊዜ ለኃጢአት መባ የሚሆን አንድ ወይፈንና+ ለሚቃጠል መባ የሚሆን አንድ አውራ በግ+ ይዞ ይምጣ። 4 ቅዱሱን የበፍታ ቀሚስ+ ይልበስ፤ በበፍታ ቁምጣዎቹም+ ሰውነቱን ይሸፍን፤ የበፍታ መቀነቱንም+ ይታጠቅ፤ ራሱም ላይ የበፍታ ጥምጥሙን+ ይጠምጥም። እነዚህ ቅዱስ ልብሶች+ ናቸው። እሱም ገላውን በውኃ ታጥቦ+ ይለብሳቸዋል።

5 “ከእስራኤል ማኅበረሰብም ሁለት ተባዕት የፍየል ጠቦቶችን ለኃጢአት መባ፣ አንድ አውራ በግ ደግሞ ለሚቃጠል መባ ይውሰድ።+

6 “ከዚያም አሮን ለራሱ የኃጢአት መባ የሚሆነውን ወይፈን ያቅርብ፤ ለራሱም+ ሆነ ለቤቱ ያስተሰርያል።

7 “ሁለቱን ፍየሎች ወስዶ በመገናኛ ድንኳኑ መግቢያ በይሖዋ ፊት እንዲቆሙ ያደርጋል። 8 አሮንም በሁለቱ ፍየሎች ላይ ዕጣ ይጥላል፤ አንደኛው ዕጣ ለይሖዋ ሌላኛው ዕጣ ደግሞ ለአዛዜል* ይሆናል። 9 አሮንም ለይሖዋ እንዲሆን ዕጣ+ የወጣበትን ፍየል ያቀርባል፤ የኃጢአትም መባ ያደርገዋል። 10 ለአዛዜል እንዲሆን ዕጣ የወጣበት ፍየል ግን በእሱ አማካኝነት ስርየት እንዲፈጸምበት ከነሕይወቱ መጥቶ በይሖዋ ፊት እንዲቆም ይደረግ፤ ከዚያም ለአዛዜል እንዲሆን ወደ ምድረ በዳ ይለቀቃል።+

11 “አሮንም ለራሱ የኃጢአት መባ የሚሆነውን ወይፈን ያቀርባል፤ ለራሱም ሆነ ለቤቱ ያስተሰርያል፤ ከዚያም ለራሱ የኃጢአት መባ የሚሆነውን ወይፈን ያርዳል።+

12 “በይሖዋ ፊት ካለው መሠዊያ ላይ የተወሰደ ፍም+ የሞላበትን ዕጣን ማጨሻና+ ሁለት እፍኝ ሙሉ ጥሩ መዓዛ ያለው ዕጣን+ ይወስዳል፤ እነዚህንም ይዞ ወደ መጋረጃው ውስጥ ይገባል።+ 13 እንዳይሞትም ዕጣኑን በይሖዋ ፊት+ ባለው እሳት ላይ ይጨምረዋል፤ የዕጣኑም ጭስ ከምሥክሩ+ በላይ ያለውን የታቦቱን መክደኛ+ ይሸፍነዋል።

14 “ከወይፈኑም ደም+ የተወሰነውን ወስዶ ከመክደኛው ፊት ለፊት በስተ ምሥራቅ በኩል በጣቱ ይረጨዋል፤ የተወሰነውን ደም ደግሞ ከመክደኛው ፊት በጣቱ ሰባት ጊዜ ይረጨዋል።+

15 “ከዚያም ለሕዝቡ የኃጢአት መባ+ የሚሆነውን ፍየል ያርደዋል፤ ደሙንም ወደ መጋረጃው ውስጥ ይዞ በመግባት+ ልክ በወይፈኑ ደም+ እንዳደረገው በዚህኛውም ደም ያደርጋል፤ ደሙንም ወደ መክደኛውና በመክደኛው ፊት ይረጨዋል።

16 “እስራኤላውያን ስለፈጸሙት ርኩሰት፣ ስለ መተላለፋቸውና ስለ ኃጢአታቸው+ ለቅዱሱ ስፍራ ያስተሰርይ፤ በእነሱ ዘንድ በርኩሰታቸው መካከል ለሚገኘው ለመገናኛ ድንኳኑም ይህንኑ ያድርግ።

17 “ለማስተሰረይ ወደ ቅዱሱ ስፍራ ገብቶ እስኪወጣ ድረስ ሌላ ማንም ሰው በመገናኛ ድንኳኑ ውስጥ መገኘት የለበትም። እሱም ለራሱ፣ ለቤቱና+ ለመላው የእስራኤል ጉባኤ+ ያስተሰርያል።

18 “ከዚያም በይሖዋ ፊት ወዳለው መሠዊያ ይወጣል፤+ ለመሠዊያውም ያስተሰርይለታል፤ ከወይፈኑ ደም የተወሰነውን እንዲሁም ከፍየሉ ደም የተወሰነውን ወስዶ በመሠዊያው ጎኖች ሁሉ ላይ ያሉትን ቀንዶች ይቀባል። 19 በተጨማሪም ከደሙ የተወሰነውን ወስዶ በመሠዊያው ላይ በጣቱ ሰባት ጊዜ በመርጨት እስራኤላውያን ከፈጸሙት ርኩሰት ያነጻዋል እንዲሁም ይቀድሰዋል።

20 “ለቅዱሱ ስፍራ፣ ለመገናኛ ድንኳኑና ለመሠዊያው+ ካስተሰረየ+ በኋላ በሕይወት ያለውንም ፍየል ያቀርባል።+ 21 ከዚያም አሮን ሁለቱንም እጆቹን በሕይወት ባለው ፍየል ራስ ላይ በመጫን እስራኤላውያን የሠሩትን ስህተት ሁሉ፣ መተላለፋቸውን ሁሉና ኃጢአታቸውን ሁሉ ይናዘዝበታል፤ እነዚህንም በፍየሉ ራስ ላይ ያደርጋል፤+ ፍየሉንም ለዚህ በተመደበው* ሰው እጅ ወደ ምድረ በዳ ይሰደዋል። 22 ፍየሉም ስህተቶቻቸውን በሙሉ ተሸክሞ+ ወደ በረሃ ይሄዳል፤+ እሱም ፍየሉን ወደ ምድረ በዳ ይሰደዋል።+

23 “ከዚያም አሮን ወደ መገናኛ ድንኳኑ ይገባል፤ ወደ ቅዱሱ ስፍራ ሲገባ ለብሷቸው የነበሩትንም የበፍታ ልብሶች ያወልቃል፤ ልብሶቹንም እዚያው ይተዋቸዋል። 24 ገላውንም በቅዱስ ስፍራ በውኃ ይታጠብ፤+ ልብሶቹንም ይልበስ፤+ ከዚያም ወጥቶ የራሱን የሚቃጠል መባ+ እንዲሁም የሕዝቡን የሚቃጠል መባ+ ያቀርባል፤ ለራሱና ለሕዝቡም ያስተሰርያል።+ 25 የኃጢአት መባው ስብም በመሠዊያው ላይ እንዲጨስ ያደርጋል።

26 “ለአዛዜል+ ሲል ፍየሉን የለቀቀውም ሰው ልብሶቹን ይጠብ፤ ገላውንም በውኃ ይታጠብ፤ ከዚያም ወደ ሰፈሩ መግባት ይችላል።

27 “ደማቸው ለማስተሰረያ እንዲሆን ወደ ቅዱሱ ስፍራ የገባው የኃጢአት መባው ወይፈንና የኃጢአት መባው ፍየል ከሰፈሩ ውጭ ይወሰዳሉ፤ ቆዳቸው፣ ሥጋቸውና ፈርሳቸውም በእሳት ይቃጠላል።+ 28 እነዚህን ያቃጠለው ሰው ልብሶቹን ይጠብ፤ ገላውንም በውኃ ይታጠብ፤ ከዚያም ወደ ሰፈሩ መግባት ይችላል።

29 “ይህም ለእናንተ ዘላቂ ደንብ ሆኖ ያገለግላል፦ በሰባተኛው ወር ከወሩም በአሥረኛው ቀን ራሳችሁን አጎሳቁሉ፤* ምንም ዓይነት ሥራም አትሥሩ፤+ የአገራችሁ ሰውም ሆነ በመካከላችሁ የሚኖር የባዕድ አገር ሰው ምንም ዓይነት ሥራ አይሥራ። 30 በዚህ ቀን፣ ንጹሕ መሆናችሁን ለማሳወቅ ለእናንተ ማስተሰረያ+ ይቀርባል። በይሖዋም ፊት ከኃጢአታችሁ ሁሉ ንጹሕ ትሆናላችሁ።+ 31 ይህ ሙሉ በሙሉ የምታርፉበት ሰንበት ነው፤ እናንተም ራሳችሁን* አጎሳቁሉ።+ ይህም ዘላቂ ደንብ ነው።

32 “አባቱን ተክቶ+ በክህነት እንዲያገለግል የሚቀባውና የሚሾመው*+ ካህን ያስተሰርያል፤ እንዲሁም ቅዱስ የሆኑትን የበፍታ ልብሶች+ ይለብሳል። 33 ለቅዱሱ መቅደስ፣+ ለመገናኛ ድንኳኑና+ ለመሠዊያው+ ያስተሰርያል፤ እንዲሁም ለካህናቱና ለጉባኤው ሕዝብ በሙሉ ያስተሰርያል።+ 34 ይህም የእስራኤላውያንን ኃጢአት በሙሉ በዓመት አንድ ጊዜ+ ለማስተሰረይ የሚያገለግል ዘላቂ ደንብ ይሆናል።”+

እሱም ልክ ይሖዋ ሙሴን ባዘዘው መሠረት አደረገ።

17 ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ 2 “አሮንንና ወንዶች ልጆቹን እንዲሁም እስራኤላውያንን በሙሉ እንዲህ በላቸው፦ ‘ይሖዋ ያዘዘው ይህ ነው፦

3 “‘“ከእስራኤል ቤት የሆነ ማንኛውም ሰው በሬ ወይም የበግ ጠቦት አሊያም ፍየል በሰፈሩ ውስጥ ወይም ከሰፈሩ ውጭ ቢያርድና 4 በይሖዋ የማደሪያ ድንኳን ፊት ለይሖዋ መባ አድርጎ ለማቅረብ ወደ መገናኛ ድንኳኑ መግቢያ ባያመጣ ያ ሰው በደም ዕዳ ይጠየቃል። ሰውየው ደም አፍስሷል፤ በመሆኑም ይህ ሰው ከሕዝቡ መካከል ተለይቶ እንዲጠፋ መደረግ አለበት። 5 ይህም እስራኤላውያን በሜዳ ላይ እየሠዉ ያሉትን መሥዋዕት ወደ ይሖዋ፣ ወደ መገናኛ ድንኳኑ መግቢያና ወደ ካህኑ እንዲያመጡ ነው። እነዚህንም ለይሖዋ የኅብረት መሥዋዕቶች አድርገው መሠዋት አለባቸው።+ 6 ካህኑም ደሙን በመገናኛ ድንኳኑ መግቢያ ላይ ባለው የይሖዋ መሠዊያ ላይ ይረጨዋል፤ ስቡንም ለይሖዋ ደስ የሚያሰኝ* መዓዛ አድርጎ ያጨሰዋል።+ 7 ከእንግዲህ ወዲህ፣ አብረዋቸው ምንዝር ለሚፈጽሙት+ ፍየል የሚመስሉ አጋንንት*+ አይሠዉም። ይህም በመጪዎቹ ትውልዶቻችሁ ሁሉ ለእናንተ ዘላቂ ደንብ ሆኖ ያገለግላል።”’

8 “እንዲህም በላቸው፦ ‘የሚቃጠል መባ ወይም መሥዋዕት የሚያቀርብ ከእስራኤል ቤት የሆነ ማንኛውም ሰው ወይም በመካከላችሁ የሚኖር ማንኛውም የባዕድ አገር ሰው 9 ይህን ለይሖዋ ለማቅረብ ወደ መገናኛ ድንኳኑ መግቢያ ባያመጣ ከሕዝቡ መካከል ተለይቶ እንዲጠፋ መደረግ አለበት።+

10 “‘ከእስራኤል ቤት የሆነ ማንኛውም ሰው ወይም በመካከላችሁ የሚኖር የትኛውም የባዕድ አገር ሰው ምንም ዓይነት ደም ቢበላ፣+ ደም በሚበላው ሰው* ላይ በእርግጥ ፊቴን አጠቁርበታለሁ፤ ከሕዝቡም መካከል ለይቼ አጠፋዋለሁ። 11 ምክንያቱም የሥጋ ሕይወት* ያለው በደሙ ውስጥ ነው፤+ ለራሳችሁም* ማስተሰረያ እንዲሆን እኔ ራሴ ደሙን ለእናንተ ስል ለመሠዊያው ሰጥቼዋለሁ፤+ ምክንያቱም በውስጡ ባለው ሕይወት* አማካኝነት የሚያስተሰርየው ደሙ ነው።+ 12 እስራኤላውያንን “ማንኛችሁም ደም መብላት የለባችሁም፤* እንዲሁም በመካከላችሁ የሚኖር ማንኛውም የባዕድ አገር ሰው+ ደም አይብላ”+ ያልኳቸው ለዚህ ነው።

13 “‘አንድ እስራኤላዊ ወይም በመካከላችሁ የሚኖር አንድ የባዕድ አገር ሰው ለመብልነት የተፈቀደ እንስሳ ወይም ወፍ አድኖ ቢይዝ ደሙን ያፍሰው፤+ አፈርም ያልብሰው። 14 የሥጋ ሁሉ ሕይወት* ደሙ ነውና፤ ምክንያቱም በውስጡ ሕይወት* አለ። በዚህም የተነሳ እስራኤላውያንን እንዲህ አልኳቸው፦ “የሥጋ ሁሉ ሕይወት* ደሙ ስለሆነ የማንኛውንም ሥጋ ደም አትብሉ። ደም የሚበላ ማንኛውም ሰው ተለይቶ እንዲጠፋ ይደረጋል።”+ 15 የአገሬው ተወላጅም ይሁን የባዕድ አገር ሰው፣ ማንኛውም ሰው* ሞቶ የተገኘን ወይም አውሬ የቦጫጨቀውን እንስሳ+ ሥጋ ቢበላ ልብሶቹን ይጠብ፤ በውኃም ይታጠብ፤ እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ይሁን፤+ ከዚያም ንጹሕ ይሆናል። 16 ሆኖም ልብሶቹን ካላጠበና ሰውነቱን ካልታጠበ በሠራው ጥፋት ይጠየቅበታል።’”+

18 ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ 2 “እስራኤላውያንን እንዲህ በላቸው፦ ‘እኔ አምላካችሁ ይሖዋ ነኝ።+ 3 ትኖሩበት በነበረው በግብፅ ምድር ያሉ ሰዎች እንደሚያደርጉት አታድርጉ፤ እኔ በማስገባችሁ በከነአን ምድር ያሉ ሰዎች እንደሚያደርጉትም አታድርጉ።+ እንዲሁም እነሱ የሚከተሏቸውን ደንቦች አትከተሉ። 4 ድንጋጌዎቼን ተግባር ላይ አውሉ፤ ደንቦቼንም በመጠበቅ በእነሱ ሂዱ።+ እኔ አምላካችሁ ይሖዋ ነኝ። 5 ደንቦቼንና ድንጋጌዎቼን ጠብቁ፤ እንዲህ የሚያደርግ ማንኛውም ሰው በእነሱ አማካኝነት በሕይወት ይኖራል።+ እኔ ይሖዋ ነኝ።

6 “‘ከመካከላችሁ ማንም ሰው የፆታ ግንኙነት ለመፈጸም ወደ ማንኛውም የቅርብ ዘመዱ አይቅረብ።+ እኔ ይሖዋ ነኝ። 7 ከአባትህ ጋር የፆታ ግንኙነት አትፈጽም፤ ከእናትህም ጋር የፆታ ግንኙነት አትፈጽም። እሷ እናትህ ናት፤ ከእሷ ጋር የፆታ ግንኙነት አትፈጽም።

8 “‘ከአባትህ ሚስት ጋር የፆታ ግንኙነት አትፈጽም።+ ይህ አባትህን ለኀፍረት መዳረግ ነው።*

9 “‘የአባትህ ልጅም ሆነች የእናትህ ልጅ ወይም በቤት የተወለደችም ሆነች በውጭ፣ ከእህትህ ጋር የፆታ ግንኙነት አትፈጽም።+

10 “‘ከወንድ ልጅህ ሴት ልጅ ወይም ከሴት ልጅህ ሴት ልጅ ጋር የፆታ ግንኙነት አትፈጽም፤ ምክንያቱም እነሱ የአንተው እርቃን ናቸው።

11 “‘የአባትህ ልጅ ከሆነችው ከአባትህ ሚስት ሴት ልጅ ጋር የፆታ ግንኙነት አትፈጽም፤ ምክንያቱም እሷ እህትህ ናት።

12 “‘ከአባትህ እህት ጋር የፆታ ግንኙነት አትፈጽም። እሷ የአባትህ የሥጋ ዘመድ ናት።+

13 “‘ከእናትህ እህት ጋር የፆታ ግንኙነት አትፈጽም፤ ምክንያቱም እሷ የእናትህ የሥጋ ዘመድ ናት።

14 “‘ከአባትህ ወንድም ሚስት ጋር የፆታ ግንኙነት በመፈጸም እሱን ለኀፍረት አትዳርገው።* እሷ ዘመድህ ናት።+

15 “‘ከልጅህ ሚስት ጋር የፆታ ግንኙነት አትፈጽም።+ እሷ የልጅህ ሚስት ናት፤ ከእሷ ጋር ግንኙነት መፈጸም የለብህም።

16 “‘ከወንድምህ ሚስት ጋር የፆታ ግንኙነት አትፈጽም፤+ ምክንያቱም ይህ ወንድምህን ለኀፍረት መዳረግ ነው።*

17 “‘ከአንዲት ሴትና ከሴት ልጇ ጋር የፆታ ግንኙነት አትፈጽም።+ ከወንድ ልጇ ሴት ልጅም ሆነ ከሴት ልጇ ሴት ልጅ ጋር የፆታ ግንኙነት ለመፈጸም እነሱን አትውሰድ። እነሱ የእሷ የቅርብ ዘመዶች ናቸው፤ ይህ ጸያፍ ድርጊት* ነው።

18 “‘እህቷ ጣውንቷ እንዳትሆን+ ሚስትህ በሕይወት እያለች ከእህቷ ጋር የፆታ ግንኙነት አትፈጽም።

19 “‘አንዲት ሴት በወር አበባዋ ረክሳ እያለች ከእሷ ጋር የፆታ ግንኙነት ለመፈጸም ወደ እሷ አትቅረብ።+

20 “‘ከጓደኛህ* ሚስት ጋር የፆታ ግንኙነት በመፈጸም ራስህን አታርክስ።+

21 “‘ከልጆችህ መካከል የትኛውንም ለሞሎክ እንዲሰጥ* አታድርግ።+ በዚህ መንገድ የአምላክህን ስም አታርክስ።+ እኔ ይሖዋ ነኝ።

22 “‘ከሴት ጋር እንደምትተኛ ከወንድ ጋር አትተኛ።+ ይህ አስጸያፊ ድርጊት ነው።

23 “‘አንድ ወንድ ከእንስሳ ጋር የፆታ ግንኙነት በመፈጸም ራሱን አያርክስ፤ ሴትም ብትሆን ከእንስሳ ጋር የፆታ ግንኙነት ለመፈጸም ራሷን ለእንስሳ አታቅርብ።+ ይህ ከተፈጥሮ ውጭ የሆነ ነገር ነው።

24 “‘ከእነዚህ ነገሮች በየትኛውም ራሳችሁን አታርክሱ፤ ምክንያቱም ከእናንተ ፊት አባርሬ የማስወጣቸው ብሔራት ራሳቸውን በእነዚህ ነገሮች አርክሰዋል።+ 25 ስለሆነም ምድሪቱ ረክሳለች፤ እኔም ለሠራችው ስህተት ቅጣት አመጣባታለሁ፤ ምድሪቱም ነዋሪዎቿን ትተፋቸዋለች።+ 26 እናንተ ግን ደንቦቼንና ድንጋጌዎቼን ጠብቁ፤+ ከእነዚህ አስጸያፊ ነገሮች መካከል የትኛውንም ማድረግ የለባችሁም፤ የአገራችሁ ሰውም ሆነ በመካከላችሁ የሚኖር የባዕድ አገር ሰው እንዲህ ማድረግ የለበትም።+ 27 ምክንያቱም ከእናንተ በፊት በምድሪቱ ላይ ይኖሩ የነበሩት ሰዎች እነዚህን አስጸያፊ ነገሮች ሁሉ ፈጽመዋል፤+ በዚህም የተነሳ አሁን ምድሪቱ ረክሳለች። 28 እናንተ ግን ምድሪቱን ስለማታረክሷት ከእናንተ በፊት የነበሩትን ብሔራት እንደተፋቻቸው እናንተን አትተፋችሁም። 29 ማንኛውም ሰው ከእነዚህ አስጸያፊ ነገሮች መካከል የትኛውንም ቢፈጽም ይህን የፈጸመው ሰው* ከሕዝቡ መካከል ተለይቶ እንዲጠፋ ይደረግ። 30 ከእናንተ በፊት የነበሩ ሰዎች ይከተሏቸው ከነበሩት አስጸያፊ ልማዶች በመራቅ ለእኔ የገባችሁትን ግዴታ ፈጽሙ፤+ አለዚያ በእነሱ ምክንያት ራሳችሁን ታረክሳላችሁ። እኔ አምላካችሁ ይሖዋ ነኝ።’”

19 በተጨማሪም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ 2 “ለመላው የእስራኤል ማኅበረሰብ እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ ‘እኔ አምላካችሁ ይሖዋ ቅዱስ ስለሆንኩ እናንተም ቅዱስ ልትሆኑ ይገባል።+

3 “‘ከእናንተ እያንዳንዱ እናቱንና አባቱን ያክብር፤*+ ሰንበቶቼንም ይጠብቅ።+ እኔ አምላካችሁ ይሖዋ ነኝ። 4 ከንቱ ወደሆኑ አማልክት ዞር አትበሉ፤+ ወይም ከቀለጠ ብረት ለራሳችሁ አማልክትን አትሥሩ።+ እኔ አምላካችሁ ይሖዋ ነኝ።

5 “‘ለይሖዋ የኅብረት መሥዋዕት የምታቀርቡ+ ከሆነ ተቀባይነት በሚያስገኝላችሁ መንገድ አቅርቡት።+ 6 መሥዋዕቱም በዚያው ባቀረባችሁበት ዕለትና በቀጣዩ ቀን መበላት ይኖርበታል፤ ተርፎ እስከ ሦስተኛው ቀን የቆየ ካለ ግን በእሳት መቃጠል አለበት።+ 7 ይሁንና ከተረፈው ላይ በሦስተኛው ቀን ከተበላ ተቀባይነት የሌለው አስጸያፊ ነገር ይሆናል። 8 የበላውም ሰው የይሖዋን ቅዱስ ነገር ስላረከሰ በጥፋቱ ይጠየቃል፤ ያም ሰው* ከሕዝቡ መካከል ተለይቶ እንዲጠፋ መደረግ አለበት።

9 “‘የምድራችሁን አዝመራ በምትሰበስቡበት ጊዜ በእርሻችሁ ዳር ዳር ያለውን ሙልጭ አድርጋችሁ አትጨዱት፤ የእርሻችሁን ቃርሚያም አትልቀሙ።+ 10 በተጨማሪም በወይን እርሻህ ላይ የተረፈውን አትሰብስብ፤ በወይን እርሻህ ላይ የወዳደቀውን የወይን ፍሬ አትልቀም። እነዚህን ለድሃውና* ለባዕድ አገሩ ሰው ተውለት።+ እኔ አምላካችሁ ይሖዋ ነኝ።

11 “‘አትስረቁ፤+ አታታሉ፤+ አንዳችሁ በሌላው ላይ ሐቀኝነት የጎደለው ድርጊት አትፈጽሙ። 12 በስሜ በሐሰት አትማሉ፤+ በዚህም የአምላካችሁን ስም አታርክሱ። እኔ ይሖዋ ነኝ። 13 ባልንጀራህን አታጭበርብር፤+ አትዝረፈውም።+ የቅጥር ሠራተኛውን ደሞዝ ሳትከፍል አታሳድር።+

14 “‘መስማት የተሳነውን አትርገም ወይም በዓይነ ስውሩ ፊት እንቅፋት አታስቀምጥ፤+ አምላክህን ፍራ።+ እኔ ይሖዋ ነኝ።

15 “‘ፍርድ አታዛቡ። ለድሃው አታዳላ ወይም ባለጸጋውን ከሌሎች አስበልጠህ አትመልከት።+ ለባልንጀራህ ፍትሐዊ ፍርድ ፍረድ።

16 “‘በሕዝብህ መካከል እየዞርክ ስም አታጥፋ።+ በባልንጀራህ ሕይወት* ላይ አትነሳ።*+ እኔ ይሖዋ ነኝ።

17 “‘ወንድምህን በልብህ አትጥላው።+ የባልንጀራህ ኃጢአት ተባባሪ እንዳትሆን ተግሣጽ በሚያስፈልገው ጊዜ ሁሉ ገሥጸው።+

18 “‘የሕዝብህን ልጆች አትበቀል፤+ በእነሱም ላይ ቂም አትያዝ፤ ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ።+ እኔ ይሖዋ ነኝ።

19 “‘የሚከተሉትን ደንቦቼን ጠብቁ፦ ሁለት ዓይነት እንስሳትን አታዳቅል። በእርሻህ ላይ ሁለት ዓይነት ዘር አትዝራ፤+ ከሁለት የተለያዩ የክር ዓይነቶች የተሠራ ልብስ አትልበስ።+

20 “‘አንድ ወንድ ከአንዲት ሴት ጋር ቢተኛና ከእሷ ጋር የፆታ ግንኙነት ቢፈጽም፣ ሴቲቱ ደግሞ ለሌላ ወንድ የታጨች ሆኖም ገና ያልተዋጀች ወይም ነፃ ያልወጣች ባሪያ ብትሆን የቅጣት እርምጃ መወሰድ አለበት። ይሁንና ይህች ሴት ገና ነፃ ስላልወጣች መገደል የለባቸውም። 21 ሰውየው የበደል መባውን ይኸውም ለበደል መባ የሚሆነውን አውራ በግ ወደ ይሖዋ ወደ መገናኛ ድንኳኑ መግቢያ ያምጣ።+ 22 ካህኑም ሰውየው ለሠራው ኃጢአት የበደል መባ እንዲሆን በቀረበው አውራ በግ በይሖዋ ፊት ያስተሰርይለታል፤ የሠራውም ኃጢአት ይቅር ይባልለታል።

23 “‘እናንተም ወደ ምድሪቱ ብትገቡና ለምግብ የሚሆን ዛፍ ብትተክሉ ፍሬውን ርኩስና የተከለከለ* አድርጋችሁ ቁጠሩት። ለሦስት ዓመት ከእሱ መብላት የለባችሁም።* ፍሬው መበላት የለበትም። 24 በአራተኛው ዓመት ግን ፍሬው በሙሉ በይሖዋ ፊት የምትደሰቱበት ቅዱስ ነገር ይሆናል።+ 25 ከዚያም በአምስተኛው ዓመት ፍሬውን መብላት ትችላላችሁ፤ ይህን ካደረጋችሁ ምርታችሁ ይበዛላችኋል። እኔ አምላካችሁ ይሖዋ ነኝ።

26 “‘ደም ያለበትን ማንኛውንም ነገር አትብሉ።+

“‘አታስጠንቁሉ ወይም አስማት አትሥሩ።+

27 “‘ጆሮ ግንዳችሁ አካባቢ ያለውን ፀጉር አትላጩ* ወይም የጢማችሁን ዳር ዳር አትላጩ።+

28 “‘ለሞተ ሰው* ብላችሁ አካላችሁን አትተልትሉ+ ወይም ሰውነታችሁን አትነቀሱ። እኔ ይሖዋ ነኝ።

29 “‘ምድሪቱ ዝሙት እንዳትፈጽምና ልቅ በሆነ ምግባር እንዳትሞላ+ ሴት ልጅህን ዝሙት አዳሪ በማድረግ አታዋርዳት።+

30 “‘ሰንበቶቼን ጠብቁ፤+ ለመቅደሴ አክብሮት* ይኑራችሁ። እኔ ይሖዋ ነኝ።

31 “‘ወደ መናፍስት ጠሪዎች አትሂዱ፤+ ጠንቋዮችንም አትጠይቁ፤+ እንዲህ ካደረጋችሁ በእነሱ ትረክሳላችሁ። እኔ አምላካችሁ ይሖዋ ነኝ።

32 “‘በሸበተው ሰው ፊት ተነስ፤+ አረጋዊውንም አክብር፤+ አምላክህን ፍራ።+ እኔ ይሖዋ ነኝ።

33 “‘በምድራችሁ አብሯችሁ የሚኖር የባዕድ አገር ሰው ካለ አትበድሉት።+ 34 አብሯችሁ የሚኖረውን የባዕድ አገር ሰው እንደ አገራችሁ ተወላጅ አድርጋችሁ ተመልከቱት፤+ እንደ ራሳችሁ አድርጋችሁም ውደዱት፤ ምክንያቱም እናንተም በግብፅ ምድር ሳላችሁ የባዕድ አገር ሰው ነበራችሁ።+ እኔ አምላካችሁ ይሖዋ ነኝ።

35 “‘ርዝመትን፣ ክብደትን ወይም መጠንን ስትለኩ በተጭበረበረ መለኪያ አትጠቀሙ።+ 36 ትክክለኛ ሚዛን፣ ትክክለኛ የሚዛን ድንጋዮች፣ ትክክለኛ የደረቅ ነገር መስፈሪያና* ትክክለኛ የፈሳሽ ነገር መለኪያ* ሊኖራችሁ ይገባል።+ ከግብፅ ምድር ያወጣኋችሁ እኔ አምላካችሁ ይሖዋ ነኝ። 37 ስለሆነም ደንቦቼን ሁሉና ድንጋጌዎቼን በሙሉ ጠብቁ፤ እንዲሁም ፈጽሟቸው።+ እኔ ይሖዋ ነኝ።’”

20 ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ 2 “እስራኤላውያንን እንዲህ በላቸው፦ ‘ልጁን ለሞሎክ የሚሰጥ ማንኛውም እስራኤላዊ ወይም እስራኤል ውስጥ የሚኖር ማንኛውም የባዕድ አገር ሰው ይገደል።+ የአገሩ ሰዎች በድንጋይ ወግረው ይግደሉት። 3 ልጆቹን ለሞሎክ ስለሰጠ እንዲሁም ቅዱሱን ስፍራዬን ስላረከሰና+ ቅዱሱን ስሜን ስላቃለለ እኔ ራሴ በዚያ ሰው ላይ ፊቴን አጠቁርበታለሁ፤ ከሕዝቡም መካከል ለይቼ አጠፋዋለሁ። 4 የአገሩ ሰዎች ሰውየው ልጁን ለሞሎክ በመስጠት የፈጸመውን ድርጊት አይተው እንዳላዩ ቢሆኑና ሳይገድሉት ቢቀሩ+ 5 እኔ ራሴ በዚህ ሰውና በቤተሰቡ ላይ እነሳባቸዋለሁ።+ ያንን ሰውም ሆነ ከሞሎክ ጋር ምንዝር በመፈጸም የእሱን ፈለግ የተከተሉትን ሁሉ ከሕዝቡ መካከል ለይቼ አጠፋቸዋለሁ።

6 “‘አንድ ሰው* ከመናፍስት ጠሪዎችና+ ከጠንቋዮች+ ጋር መንፈሳዊ ምንዝር ለመፈጸም ወደ እነሱ ቢሄድ እኔ በዚያ ሰው* ላይ በእርግጥ እነሳበታለሁ፤ ከሕዝቡም መካከል ለይቼ አጠፋዋለሁ።+

7 “‘እኔ አምላካችሁ ይሖዋ ስለሆንኩ ራሳችሁን ቀድሱ፤ ቅዱሳንም ሁኑ።+ 8 ደንቦቼን ጠብቁ፤ እንዲሁም ፈጽሟቸው።+ የምቀድሳችሁ እኔ ይሖዋ ነኝ።+

9 “‘አባቱን ወይም እናቱን የሚረግም ማንኛውም ሰው ይገደል።+ አባቱን ወይም እናቱን ስለረገመ ደሙ በራሱ ላይ ነው።

10 “‘ከሌላ ሰው ሚስት ጋር ምንዝር የሚፈጽምን ሰው በተመለከተ እንዲህ ይደረግ፦ ከባልንጀራው ሚስት ጋር ምንዝር የሚፈጽም ሰው ይገደል፤ አመንዝራውም ሆነ አመንዝራይቱ ይገደሉ።+ 11 ከአባቱ ሚስት ጋር የተኛ ሰው አባቱን ለኀፍረት ዳርጎታል።*+ ሁለቱም ይገደሉ። ደማቸው በራሳቸው ላይ ነው። 12 አንድ ሰው ከልጁ ሚስት ጋር ቢተኛ ሁለቱም ይገደሉ። ከተፈጥሮ ውጭ የሆነ ድርጊት ፈጽመዋል። ደማቸው በራሳቸው ላይ ነው።+

13 “‘አንድ ሰው ከሴት ጋር እንደሚተኛ ከወንድ ጋር ቢተኛ ሁለቱም አስጸያፊ ድርጊት ፈጽመዋል።+ ስለዚህ ይገደሉ። ደማቸው በራሳቸው ላይ ነው።

14 “‘አንድ ሰው አንዲትን ሴትና እናቷን ቢያገባ፣ ይህ ጸያፍ ድርጊት* ነው።+ ይህ ጸያፍ ምግባር በመካከላችሁ እንዳይቀጥል እሱንም ሆነ እነሱን በእሳት ያቃጥሏቸው።+

15 “‘አንድ ሰው ከእንስሳ ጋር የፆታ ግንኙነት ቢፈጽም ይገደል፤ እንስሳውንም ግደሉት።+ 16 አንዲት ሴት የፆታ ግንኙነት ለመፈጸም ወደ ማንኛውም እንስሳ ብትቀርብ+ ሴትየዋንም ሆነ እንስሳውን ግደል፤ ሁለቱም ይገደሉ። ደማቸው በራሳቸው ላይ ነው።

17 “‘አንድ ሰው ከእህቱ ማለትም ከአባቱ ሴት ልጅ ወይም ከእናቱ ሴት ልጅ ጋር የፆታ ግንኙነት ቢፈጽምና እርቃኗን ቢያይ፣ እሷም የእሱን እርቃን ብታይ ይህ አሳፋሪ ድርጊት ነው።+ በሕዝቦቻቸው ልጆች ፊት እንዲጠፉ ይደረጉ። እህቱን ለኀፍረት ዳርጓል።* ለፈጸመው ጥፋት ይጠየቅበታል።

18 “‘አንድ ሰው በወር አበባዋ ወቅት ከአንዲት ሴት ጋር ቢተኛና ከእሷ ጋር የፆታ ግንኙነት ቢፈጽም እሱም ሆነ እሷ የሚፈሰውን ደሟን ገልጠዋል።+ ስለሆነም ሁለቱም ከሕዝቦቻቸው መካከል ተለይተው እንዲጠፉ ይደረጉ።

19 “‘ከእናትህ እህት ወይም ከአባትህ እህት ጋር የፆታ ግንኙነት አትፈጽም፤ ምክንያቱም ይህ የሥጋ ዘመድን ለኀፍረት መዳረግ ነው።+ ለፈጸሙት ጥፋት ይጠየቁበታል። 20 ከአጎቱ ሚስት ጋር የተኛ ሰው አጎቱን ለኀፍረት ዳርጓል።*+ ለፈጸሙት ኃጢአት ይጠየቁበታል። ልጅ ሳይኖራቸው ይሙቱ። 21 አንድ ሰው የወንድሙን ሚስት ቢወስድ ይህ አስጸያፊ ድርጊት ነው።+ ወንድሙን ለኀፍረት ዳርጓል።* ያለልጅም ይቅሩ።

22 “‘ትኖሩባት ዘንድ እናንተን የማስገባባት ምድር እንዳትተፋችሁ+ ደንቦቼንና ድንጋጌዎቼን ሁሉ ጠብቁ፤+ እንዲሁም ፈጽሟቸው።+ 23 ከፊታችሁ አባርሬ የማስወጣቸው ብሔራት በሚመሩባቸው ደንቦች አትሂዱ፤+ ምክንያቱም እነሱ እነዚህን ነገሮች ሁሉ አድርገዋል፤ እኔም እጸየፋቸዋለሁ።+ 24 በመሆኑም እንዲህ አልኳችሁ፦ “ምድራቸውን ትወርሳላችሁ፤ እኔ ደግሞ ወተትና ማር የምታፈሰውን ምድር+ እንድትወርሷት እሰጣችኋለሁ። ከሕዝቦች የለየኋችሁ አምላካችሁ ይሖዋ እኔ ነኝ።”+ 25 ንጹሕ በሆነውና ርኩስ በሆነው እንስሳ እንዲሁም ርኩስ በሆነውና ንጹሕ በሆነው ወፍ መካከል ልዩነት አድርጉ፤+ እኔ ርኩስ ነው ብዬ በለየሁላችሁ እንስሳ ወይም ወፍ አሊያም መሬት ለመሬት በሚሄድ ማንኛውም ነገር ራሳችሁን* አታርክሱ።+ 26 እኔ ይሖዋ ቅዱስ ስለሆንኩ እናንተም ለእኔ ቅዱስ ልትሆኑ ይገባል፤+ የእኔ ትሆኑ ዘንድ ከሌሎች ሕዝቦች ለየኋችሁ።+

27 “‘መናፍስት ጠሪ ወይም ጠንቋይ የሆነ ወንድ ወይም የሆነች ሴት ካሉ ይገደሉ።+ ሕዝቡ በድንጋይ ወግሮ ይግደላቸው። ደማቸው በራሳቸው ላይ ነው።’”

21 ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ለካህናቱ ማለትም ለአሮን ወንዶች ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ ‘ማንም ሰው ከሕዝቦቹ መካከል ለሞተ ሰው* ራሱን አያርክስ።*+ 2 ይሁንና ለቅርብ የሥጋ ዘመዱ ይኸውም ለእናቱ፣ ለአባቱ፣ ለወንድ ልጁ፣ ለሴት ልጁ፣ ለወንድሙ እንዲህ ማድረግ ይችላል፤ 3 እንዲሁም ድንግል ለሆነች፣ ለምትቀርበውና ላላገባች እህቱ ሲል ራሱን ማርከስ ይችላል። 4 ከሕዝቡ መካከል ባል ላገባች ሴት ሲል ራሱን ማርከስና ማዋረድ የለበትም። 5 ራሳቸውን መላጨት+ ወይም የጢማቸውን ዳር ዳር መላጨት አሊያም ሰውነታቸውን መተልተል የለባቸውም።+ 6 የአምላካቸው ምግብ* የሆኑትን ለይሖዋ በእሳት የሚቀርቡትን መባዎች የሚያቀርቡት እነሱ ስለሆኑ ለአምላካቸው ቅዱሳን መሆንና+ የአምላካቸውን ስም ከማርከስ መራቅ አለባቸው፤+ ቅዱሳን መሆን ይኖርባቸዋል።+ 7 ዝሙት አዳሪ የሆነችን ይኸውም የረከሰችን ሴት ወይም ከባሏ የተፋታችን ሴት አያግቡ፤+ ምክንያቱም ካህኑ ለአምላኩ ቅዱስ ነው። 8 የአምላክህን ምግብ የሚያቀርበው እሱ ስለሆነ ቀድሰው።+ እናንተን የምቀድሳችሁ እኔ ይሖዋ ቅዱስ ስለሆንኩ እሱም በአንተ ፊት ቅዱስ ሆኖ መገኘት አለበት።+

9 “‘የአንድ ካህን ሴት ልጅ ዝሙት አዳሪ በመሆን ራሷን ብታረክስ አባቷን ታረክሳለች። ስለዚህ በእሳት መቃጠል አለባት።+

10 “‘ከወንድሞቹ መካከል ሊቀ ካህናት በመሆን በራሱ ላይ የቅብዓት ዘይት የሚፈስበትና+ የክህነት ልብሶቹን እንዲለብስ+ የተሾመው* ካህን ፀጉሩን ማንጨብረር ወይም ልብሶቹን መቅደድ የለበትም።+ 11 ወደ ሞተ ሰው* አይጠጋ።+ ሌላው ቀርቶ ለአባቱ ወይም ለእናቱ ሲል ራሱን አያርክስ። 12 ለአምላክ የተወሰኑ መሆንን የሚያሳየው ምልክት ይኸውም የአምላኩ የቅብዓት ዘይት+ በላዩ ላይ ስላለ ከመቅደሱ መውጣትም ሆነ የአምላኩን መቅደስ ማርከስ የለበትም።+ እኔ ይሖዋ ነኝ።

13 “‘የሚያገባው ድንግል የሆነችን ሴት መሆን ይኖርበታል።+ 14 ባል የሞተባትን፣ ከባሏ የተፋታችን፣ የረከሰችን ወይም ዝሙት አዳሪ የሆነችን ሴት አያግባ፤ ሆኖም ከሕዝቡ መካከል ድንግል የሆነችውን ያግባ። 15 እሱን የምቀድሰው እኔ ይሖዋ ስለሆንኩ በሕዝቡ መካከል ዘሩን ማርከስ የለበትም።’”+

16 ይሖዋም ሙሴን እንዲህ አለው፦ 17 “አሮንን እንዲህ በለው፦ ‘ከዘርህ መካከል በትውልዶቹ ሁሉ በሰውነቱ ላይ እንከን ያለበት ማንም ሰው የአምላኩን ምግብ ለማቅረብ አይምጣ። 18 እንደሚከተሉት ያሉ እንከኖች ያሉበት ማንም ሰው መቅረብ የለበትም፦ ዓይነ ስውር ወይም አንካሳ አሊያም የፊቱ ገጽታ የተበላሸ* ወይም አንዱ እግሩ ወይም አንዱ እጁ የረዘመ 19 አሊያም እግሩ የተሰበረ ወይም እጁ የተሰበረ ሰው 20 አሊያም ጀርባው ላይ ጉብር ያለበት ወይም ድንክ የሆነ* አሊያም የዓይን ችግር ያለበት ወይም ችፌ የያዘው አሊያም ጭርት ያለበት ወይም የዘር ፍሬው የተጎዳ አይቅረብ።+ 21 ከካህኑ ከአሮን ዘር እንከን ያለበት ማንኛውም ሰው በእሳት የሚቀርቡትን የይሖዋን መባዎች ለማቅረብ አይምጣ። ይህ ሰው እንከን ስላለበት የአምላኩን ምግብ ለማቅረብ መምጣት አይችልም። 22 እጅግ ቅዱስ ከሆኑት ነገሮችና+ ቅዱስ ከሆኑት ነገሮች+ የአምላኩን ምግብ መብላት ይችላል። 23 ሆኖም እንከን ስላለበት ወደ መጋረጃው+ አይቅረብ፤ ወደ መሠዊያውም+ አይጠጋ፤ የምቀድሳቸው+ እኔ ይሖዋ ስለሆንኩ መቅደሴን+ አያርክስ።’”

24 ስለዚህ ሙሴ ይህን ለአሮን፣ ለወንዶች ልጆቹና ለእስራኤላውያን በሙሉ ነገራቸው።

22 በተጨማሪም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ 2 “ለአሮንና ለወንዶች ልጆቹ፣ እስራኤላውያን የሚያመጧቸውን ቅዱስ ነገሮች የሚይዙበትን መንገድ በተመለከተ ጥንቃቄ እንዲያደርጉና* ለእኔ የተቀደሱ አድርገው በለዩአቸው ነገሮች+ ቅዱስ ስሜን እንዳያረክሱ+ ንገራቸው። እኔ ይሖዋ ነኝ። 3 እንዲህ በላቸው፦ ‘በትውልዶቻችሁ ሁሉ ከልጆቻችሁ መካከል ረክሶ እያለ እስራኤላውያን ለይሖዋ የተቀደሱ አድርገው ወደለዩአቸው ቅዱስ ነገሮች የሚቀርብ ሰው ካለ ያ ሰው* ከፊቴ እንዲጠፋ ይደረግ።+ እኔ ይሖዋ ነኝ። 4 ከአሮን ልጆች መካከል የሥጋ ደዌ+ ያለበት ወይም ፈሳሽ የሚወጣው+ ማንኛውም ሰው ንጹሕ እስኪሆን ድረስ+ ቅዱስ ከሆኑት ነገሮች መብላት የለበትም፤ የሞተን ሰው* በመንካት የረከሰን ሰው+ የነካ ወይም ከሰውነቱ የዘር ፈሳሽ የሚወጣው+ 5 አሊያም ርኩስ የሆነን የሚርመሰመስ ፍጡር የነካ+ ወይም ደግሞ ሊያረክሰው በሚችል በማንኛውም ዓይነት ነገር የረከሰን ሰው የነካ+ ሰው ከእነዚህ ነገሮች አይብላ። 6 እንደነዚህ ያሉ ነገሮችን የነካ ማንኛውም ሰው* እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል፤ ገላውንም በውኃ እስካልታጠበ+ ድረስ ቅዱስ ከሆኑት ነገሮች መብላት አይችልም። 7 ፀሐይ በምትጠልቅበት ጊዜ ንጹሕ ይሆናል፤ ከዚያ በኋላ ቅዱስ ከሆኑት ነገሮች መብላት ይችላል፤ ምክንያቱም ይህ ምግቡ ነው።+ 8 በተጨማሪም እንዳይረክስ ሞቶ የተገኘን ወይም አውሬ የቦጫጨቀውን የማንኛውንም እንስሳ ሥጋ መብላት የለበትም።+ እኔ ይሖዋ ነኝ።

9 “‘ለእኔ የገቡትን ግዴታ ባለመጠበቅ በራሳቸው ላይ ኃጢአት እንዳያመጡና በዚህም የተነሳ ቅዱስ የሆነውን ነገር በማርከስ እንዳይሞቱ የገቡትን ግዴታ መጠበቅ አለባቸው። የምቀድሳቸው እኔ ይሖዋ ነኝ።

10 “‘ያልተፈቀደለት ማንኛውም ሰው* ቅዱስ የሆነውን የትኛውንም ነገር መብላት የለበትም።+ ካህኑ ቤት በእንግድነት ያረፈ ሰው ወይም ቅጥር ሠራተኛ ቅዱስ ከሆነው ነገር መብላት የለበትም። 11 ሆኖም አንድ ካህን በገዛ ገንዘቡ አንድ ሰው* ቢገዛ ያ ሰው ከምግቡ መካፈል ይችላል። በቤቱ የተወለዱ ባሪያዎችም ከእሱ ምግብ መካፈል ይችላሉ።+ 12 የአንድ ካህን ሴት ልጅ፣ ካህን ያልሆነን ሰው ብታገባ* በመዋጮ ከተሰጡት ቅዱስ የሆኑ ነገሮች መብላት አትችልም። 13 ይሁንና የአንድ ካህን ሴት ልጅ፣ ባሏ ቢሞት ወይም ብትፋታና ልጅ ባይኖራት እንደ ወጣትነቷም ጊዜ ወደ አባቷ ቤት ብትመለስ ከአባቷ ምግብ መብላት ትችላለች፤+ ያልተፈቀደለት ማንኛውም ሰው* ግን ከዚያ መብላት የለበትም።

14 “‘አንድ ሰው ቅዱስ ከሆነው ነገር ባለማወቅ ቢበላ የቅዱሱን ነገር ዋጋ አንድ አምስተኛ በመጨመር ቅዱስ የሆነውን መባ ለካህኑ ይስጥ።+ 15 ካህናቱ፣ እስራኤላውያን ለይሖዋ መዋጮ አድርገው የሰጧቸውን ቅዱስ ነገሮች ማርከስ+ 16 እንዲሁም ሕዝቡ ያመጣቸውን ቅዱስ ነገሮች እንዲበላና ቅጣት የሚያስከትል በደል እንዲፈጽም ማድረግ የለባቸውም፤ ምክንያቱም የምቀድሳቸው እኔ ይሖዋ ነኝ።’”

17 ይሖዋም ሙሴን እንዲህ አለው፦ 18 “ለአሮን፣ ለወንዶች ልጆቹና ለእስራኤላውያን በሙሉ እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ ‘ስእለቱን ለመፈጸም ወይም የፈቃደኝነት መባ ለማቅረብ+ ሲል የሚቃጠል መባውን ለይሖዋ የሚያቀርብ አንድ እስራኤላዊ ወይም በእስራኤል ውስጥ የሚኖር አንድ የባዕድ አገር ሰው+ 19 ተቀባይነት እንዲያገኝ ከፈለገ መሥዋዕቱ ከመንጋው፣ ከጠቦቶቹ ወይም ከፍየሎቹ መካከል የተወሰደ እንከን የሌለበት ተባዕት+ መሆን ይኖርበታል። 20 ተቀባይነት ስለማያስገኝላችሁ እንከን ያለበትን ማንኛውንም ነገር አታቅርቡ።+

21 “‘አንድ ሰው ስእለቱን ለመፈጸም ወይም የፈቃደኝነት መባ ለመስጠት ሲል ለይሖዋ የኅብረት መሥዋዕት+ ቢያቀርብ መሥዋዕቱ ተቀባይነት እንዲያገኝ ከከብቶቹ ወይም ከመንጋው መካከል እንከን የሌለበትን ማቅረብ ይኖርበታል። ምንም ዓይነት እንከን ሊኖርበት አይገባም። 22 መባ ሆኖ የሚቀርበው እንስሳ ዕውር ወይም ሰባራ አሊያም ቆራጣ ወይም ደግሞ ኪንታሮት አሊያም እከክ ወይም ጭርት ያለበት መሆን የለበትም፤ እንዲህ ያለውን እንስሳ ለይሖዋ ማቅረብ የለባችሁም ወይም እንዲህ ያለውን መባ ለይሖዋ በመሠዊያው ላይ ማቅረብ የለባችሁም። 23 አንዱ እግሩ የረዘመን ወይም ያጠረን በሬ ወይም በግ የፈቃደኝነት መባ አድርጋችሁ ማቅረብ ትችላላችሁ፤ የስእለት መባ አድርጋችሁ ብታቀርቡት ግን ተቀባይነት አይኖረውም። 24 የዘር ፍሬው ጉዳት የደረሰበትን ወይም የተቀጠቀጠን አሊያም ተሰንጥቆ የወጣን ወይም የተቆረጠን እንስሳ ለይሖዋ ማቅረብ የለባችሁም፤ በምድራችሁ እነዚህን የመሰሉ እንስሳትን ማቅረብ አይኖርባችሁም። 25 እነዚህ ጉድለትና እንከን ስላለባቸው ከመካከላቸው የትኛውንም ከባዕድ ሰው እጅ በመቀበል የአምላካችሁ ምግብ አድርጋችሁ ማቅረብ የለባችሁም። ተቀባይነት አያገኙላችሁም።’”

26 በተጨማሪም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ 27 “ጥጃ ወይም የበግ ግልገል አሊያም የፍየል ግልገል በሚወለድበት ጊዜ ለሰባት ቀን ከእናቱ ጋር ይቆይ፤+ ከስምንተኛው ቀን አንስቶ ግን መባ ይኸውም ለይሖዋ በእሳት የሚቀርብ መባ ሆኖ ቢቀርብ ተቀባይነት ይኖረዋል። 28 ላምን ከጥጃዋ ወይም በግን ከግልገሏ ጋር በአንድ ቀን አትረዱ።+

29 “ለይሖዋ የምሥጋና መሥዋዕት+ የምትሠዉ ከሆነ ተቀባይነት በሚያስገኝላችሁ መንገድ ልትሠዉት ይገባል። 30 መሥዋዕቱ በዚያው ዕለት መበላት ይኖርበታል። ከእሱም ላይ ምንም አስተርፋችሁ አታሳድሩ።+ እኔ ይሖዋ ነኝ።

31 “እናንተም ትእዛዛቴን ጠብቁ፤ እንዲሁም ፈጽሟቸው።+ እኔ ይሖዋ ነኝ። 32 ቅዱሱን ስሜን አታርክሱ፤+ እኔ በእስራኤላውያን መካከል ልቀደስ ይገባኛል።+ የምቀድሳችሁ እኔ ይሖዋ ነኝ፤+ 33 አምላክ መሆኔን ለእናንተ ለማሳየት ከግብፅ ምድር ያወጣኋችሁ እኔ ነኝ።+ እኔ ይሖዋ ነኝ።”

23 ይሖዋም ሙሴን እንዲህ አለው፦ 2 “ለእስራኤላውያን እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ ‘ልታውጇቸው የሚገቡት+ በየወቅቱ የሚከበሩ የይሖዋ በዓላት+ ቅዱስ ጉባኤዎች ናቸው። በየወቅቱ የሚከበሩት የእኔ በዓላት የሚከተሉት ናቸው፦

3 “‘ለስድስት ቀን ሥራ መሥራት ይቻላል፤ ሰባተኛው ቀን ግን ሙሉ በሙሉ የሚታረፍበት ሰንበት+ ይኸውም ቅዱስ ጉባኤ ነው። ምንም ዓይነት ሥራ መሥራት የለባችሁም። በምትኖሩባቸው ቦታዎች ሁሉ ይህ የይሖዋ ሰንበት ነው።+

4 “‘በተወሰነላቸው ጊዜ ላይ ልታውጇቸው የሚገቡት በየወቅቱ የሚከበሩ የይሖዋ በዓላት ማለትም ቅዱስ ጉባኤዎች የሚከተሉት ናቸው፦ 5 በመጀመሪያው ወር ከወሩም በ14ኛው ቀን+ አመሻሹ ላይ* ለይሖዋ ፋሲካ* ይከበራል።+

6 “‘በዚህ ወር 15ኛ ቀን ላይ የቂጣ በዓል ለይሖዋ ይከበራል።+ ለሰባት ቀንም ቂጣ መብላት ይኖርባችኋል።+ 7 በመጀመሪያው ቀን ቅዱስ ጉባኤ ታከብራላችሁ።+ ምንም ዓይነት ከባድ ሥራ መሥራት የለባችሁም። 8 ሆኖም ለሰባት ቀን ያህል ለይሖዋ በእሳት የሚቀርብ መባ ታቀርባላችሁ። በሰባተኛው ቀን ቅዱስ ጉባኤ ይሆናል። ምንም ዓይነት ከባድ ሥራ መሥራት የለባችሁም።’”

9 በመቀጠልም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ 10 “ለእስራኤላውያን እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ ‘እኔ ወደምሰጣችሁ ምድር ገብታችሁ የምድሪቱን አዝመራ በምታጭዱበት ጊዜ ከአዝመራችሁ መጀመሪያ የደረሰውን+ እህል ነዶ ለካህኑ ማምጣት አለባችሁ።+ 11 እሱም ተቀባይነት እንድታገኙ ነዶውን በይሖዋ ፊት ወዲያና ወዲህ ይወዝውዘው። ካህኑ በሰንበት ማግስት ነዶውን ወዲያና ወዲህ ሊወዘውዘው ይገባል። 12 ነዶው ወዲያና ወዲህ እንዲወዘወዝ በምታደርጉበት ቀን አንድ ዓመት ገደማ የሆነው እንከን የሌለበት ጠቦት ለይሖዋ የሚቃጠል መባ አድርጋችሁ ማቅረብ አለባችሁ። 13 ከዚህም ጋር ሁለት አሥረኛ ኢፍ* በዘይት የተለወሰ የላመ ዱቄት የእህል መባ ይኸውም ለይሖዋ በእሳት የሚቀርብ ደስ የሚያሰኝ* መዓዛ ያለው መባ አድርጋችሁ አቅርቡ። በተጨማሪም አንድ አራተኛ ሂን* የወይን ጠጅ ከዚያ ጋር የመጠጥ መባ አድርጋችሁ አቅርቡ። 14 የአምላካችሁን መባ እስከምታቀርቡበት እስከዚህ ቀን ድረስ ምንም ዓይነት ዳቦም ሆነ ቆሎ ወይም እሸት መብላት የለባችሁም። በምትኖሩበት በየትኛውም ቦታ በትውልዶቻችሁ ሁሉ ይህ ዘላቂ ደንብ ነው።

15 “‘ከሰንበት ማግስት ይኸውም ለሚወዘወዝ መባ የሚሆነውን ነዶ ካመጣችሁበት ቀን ጀምሮ ሰባት ሰንበቶችን ቁጠሩ።+ እነሱም ሙሉ ሳምንታት መሆን አለባቸው። 16 እስከ ሰባተኛው ሰንበት ማግስት ድረስ 50 ቀን+ ቁጠሩ፤ ከዚያም ለይሖዋ አዲስ የእህል መባ አቅርቡ።+ 17 ከምትኖሩባቸው ቦታዎች ሁለት ዳቦዎችን ለሚወዘወዝ መባ ማምጣት ይኖርባችኋል። እነሱም ከሁለት አሥረኛ ኢፍ* የላመ ዱቄት የተዘጋጁ መሆን አለባቸው። ለይሖዋ የሚቀርቡ መጀመሪያ የደረሱ ፍሬዎች+ እንደመሆናቸው መጠን እርሾ ገብቶባቸው+ መጋገር ይኖርባቸዋል። 18 ከዳቦዎቹም ጋር እያንዳንዳቸው አንድ ዓመት የሆናቸውና እንከን የሌለባቸው ሰባት ተባዕት የበግ ጠቦቶች፣ አንድ ወይፈንና ሁለት አውራ በጎች አቅርቡ።+ እነዚህም ከእህል መባቸውና ከመጠጥ መባዎቻቸው ጋር ለይሖዋ የሚቃጠል መባ ማለትም ይሖዋን ደስ የሚያሰኝ* መዓዛ ያለው በእሳት የሚቀርብ መባ ሆነው ይቀርባሉ። 19 እንዲሁም ለኃጢአት መባ እንዲሆን ከፍየሎች መካከል አንድ ግልገል፣+ ለኅብረት መሥዋዕት+ እንዲሆኑ ደግሞ እያንዳንዳቸው አንድ ዓመት የሆናቸው ሁለት ተባዕት የበግ ጠቦቶችን አቅርቡ። 20 ካህኑም መጀመሪያ ከደረሱ ፍሬዎች ከተዘጋጁት ዳቦዎችና ከሁለቱ ተባዕት ጠቦቶች ጋር በይሖዋ ፊት የሚወዘወዝ መባ አድርጎ ወዲያና ወዲህ ይወዝውዛቸው። እነዚህም ለይሖዋ የተቀደሱ ነገሮች ናቸው፤ የካህኑም ድርሻ ይሆናሉ።+ 21 በዚህ ቀን ለእናንተ ቅዱስ ጉባኤ ታውጃላችሁ።+ ምንም ዓይነት ከባድ ሥራ አትሥሩ። በምትኖሩበት በየትኛውም ቦታ በትውልዶቻችሁ ሁሉ ይህ ዘላቂ ደንብ ነው።

22 “‘የምድራችሁን አዝመራ በምታጭዱበት ጊዜ የእርሻችሁን ዳርና ዳር ሙልጭ አድርጋችሁ አትጨዱት፤ የእርሻችሁን ቃርሚያም አትልቀሙ።+ እነዚህን ለድሃውና*+ ለባዕድ አገሩ ሰው+ ተዉለት። እኔ አምላካችሁ ይሖዋ ነኝ።’”

23 ይሖዋም ሙሴን እንዲህ አለው፦ 24 “እስራኤላውያንን እንዲህ በላቸው፦ ‘በሰባተኛው ወር ከወሩም በመጀመሪያው ቀን መለከት በመንፋት የሚታሰብ+ ሙሉ በሙሉ የሚታረፍበት ቅዱስ ጉባኤ ታከብራላችሁ። 25 ምንም ዓይነት ከባድ ሥራ አትሥሩ፤ ለይሖዋ በእሳት የሚቀርብ መባ ታቀርባላችሁ።’”

26 በተጨማሪም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ 27 “ሆኖም የዚህ የሰባተኛው ወር አሥረኛ ቀን የስርየት ቀን ነው።+ ቅዱስ ጉባኤ አክብሩ፣ ራሳችሁን አጎሳቁሉ*+ እንዲሁም ለይሖዋ በእሳት የሚቀርብ መባ አቅርቡ። 28 ይህ ቀን በአምላካችሁ በይሖዋ ፊት ለእናንተ ማስተሰረያ+ የሚቀርብበት የስርየት ቀን ስለሆነ በዚህ ቀን ምንም ዓይነት ሥራ መሥራት የለባችሁም። 29 በዚህ ቀን ራሱን የማያጎሳቁል* ማንኛውም ሰው* ከሕዝቡ መካከል ተለይቶ እንዲጠፋ ይደረጋል።+ 30 በዚህ ቀን ምንም ዓይነት ሥራ የሚሠራን ሰው* ሁሉ ከሕዝቡ መካከል ለይቼ አጠፋዋለሁ። 31 ምንም ዓይነት ሥራ መሥራት የለባችሁም። በምትኖሩበት በየትኛውም ቦታ በትውልዶቻችሁ ሁሉ ይህ ዘላቂ ደንብ ነው። 32 ይህ እናንተ ሙሉ በሙሉ የምታርፉበት ሰንበት ነው፤ በወሩም ዘጠነኛ ቀን ምሽት ላይ ራሳችሁን* ታጎሳቁላላችሁ።+ ሰንበታችሁንም ከዚያ ዕለት ምሽት አንስቶ እስከ ቀጣዩ ቀን ምሽት ድረስ አክብሩ።”

33 ከዚያም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ 34 “እስራኤላውያንን እንዲህ በላቸው፦ ‘በዚህ በሰባተኛው ወር ከ15ኛው ቀን ጀምሮ ለሰባት ቀን ያህል ለይሖዋ የዳስ* በዓል ይከበራል።+ 35 በመጀመሪያው ቀን ላይ ቅዱስ ጉባኤ ይሆናል፤ እናንተም ምንም ዓይነት ከባድ ሥራ መሥራት የለባችሁም። 36 ለሰባት ቀን ለይሖዋ በእሳት የሚቀርብ መባ ማቅረብ ይኖርባችኋል። በስምንተኛው ቀን ቅዱስ ጉባኤ ታከብራላችሁ፤+ ለይሖዋም በእሳት የሚቀርብ መባ ማቅረብ አለባችሁ። ይህ የተቀደሰ ጉባኤ ነው። ምንም ዓይነት ከባድ ሥራ አትሥሩ።

37 “‘ለይሖዋ በእሳት የሚቀርበውን መባ ማለትም የሚቃጠለውን መባ፣+ ከመሥዋዕቱ ጋር የሚቀርበውን የእህል መባና+ በየዕለቱ እንዲቀርቡ የተመደቡትን የመጠጥ መባዎች+ ለማቅረብ ቅዱስ ጉባኤዎች+ እንደሆኑ አድርጋችሁ የምታውጇቸው በየወቅቱ የሚከበሩት የይሖዋ በዓላት+ እነዚህ ናቸው። 38 እነዚህ ለይሖዋ ልትሰጧቸው ከሚገቡት በይሖዋ ሰንበቶች+ ላይ ከሚቀርቡት፣ ከስጦታዎቻችሁ፣+ ስእለት ለመፈጸም ከምታቀርቧቸው መባዎችና+ ከፈቃደኝነት መባዎቻችሁ+ በተጨማሪ የምታቀርቧቸው ናቸው። 39 ይሁን እንጂ የምድራችሁን ፍሬ በምትሰበስቡበት ጊዜ በሰባተኛው ወር ላይ ከ15ኛው ቀን ጀምሮ የይሖዋን በዓል ለሰባት ቀን ታከብራላችሁ።+ የመጀመሪያው ቀን ሙሉ በሙሉ የሚታረፍበት ሰንበት ይሆናል፤ ስምንተኛውም ቀን ሙሉ በሙሉ የሚታረፍበት ሰንበት ይሆናል።+ 40 በመጀመሪያውም ቀን የተንዠረገጉ ዛፎችን ፍሬ፣ የዘንባባ ዝንጣፊዎችን፣+ የለመለሙ ዛፎችን ቅርንጫፎችና በሸለቆ* የሚበቅሉ የአኻያ ዛፎችን ውሰዱ፤ በአምላካችሁም በይሖዋ ፊት ለሰባት ቀን+ ተደሰቱ።+ 41 ይህን በዓል በየዓመቱ ለሰባት ቀን ለይሖዋ የሚከበር በዓል አድርጋችሁ ታከብሩታላችሁ።+ በትውልዶቻችሁም ሁሉ ዘላቂ ደንብ አድርጋችሁ በሰባተኛው ወር አክብሩት። 42 ለሰባት ቀን በዳስ ውስጥ ተቀመጡ።+ በእስራኤል የሚኖሩ የአገሩ ተወላጆች በሙሉ በዳስ ውስጥ ይቀመጡ፤ 43 ይህን የሚያደርጉት እስራኤላውያንን ከግብፅ ምድር ባወጣኋቸው ጊዜ በዳስ ውስጥ እንዲቀመጡ እንዳደረግኩ መጪዎቹ ትውልዶቻችሁ እንዲያውቁ+ ነው።+ እኔ አምላካችሁ ይሖዋ ነኝ።’”

44 ስለዚህ ሙሴ በየወቅቱ የሚከበሩትን የይሖዋን በዓላት ለእስራኤላውያን አስታወቀ።

24 ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ 2 “መብራቱ ያለማቋረጥ እንዲበራ ለማድረግ ለመብራቱ የሚሆን ተጨቅጭቆ የተጠለለ ንጹሕ የወይራ ዘይት እንዲያመጡልህ እስራኤላውያንን እዘዛቸው።+ 3 ከምሽት አንስቶ እስከ ጠዋት ድረስ መብራቱ በይሖዋ ፊት ያለማቋረጥ እንዲበራ አሮን በመገናኛ ድንኳኑ ውስጥ ካለው ከምሥክሩ መጋረጃ ውጭ ያስቀምጠው። በትውልዶቻችሁ ሁሉ ይህ ዘላለማዊ ደንብ ነው። 4 ዘወትር በይሖዋ ፊት እንዲሆኑ መብራቶቹን ከንጹሕ ወርቅ በተሠራው መቅረዝ+ ላይ በቦታ በቦታቸው ያስቀምጣቸው።

5 “አንተም የላመ ዱቄት ወስደህ የቀለበት ቅርጽ ያላቸው 12 ዳቦዎችን ጋግር። እያንዳንዱ ዳቦ ከሁለት አሥረኛ ኢፍ* ዱቄት የተዘጋጀ መሆን ይኖርበታል። 6 እነዚህንም በይሖዋ ፊት ባለው ከንጹሕ ወርቅ በተሠራው ጠረጴዛ+ ላይ ስድስት ስድስት አድርገህ በማነባበር በሁለት ረድፍ ታስቀምጣቸዋለህ።+ 7 ተነባብሮ በተቀመጠው በእያንዳንዱ ረድፍ ላይም ንጹሕ ነጭ ዕጣን አድርግ፤ ይህም ለምግቡ መታሰቢያ እንዲሆን+ ለይሖዋ በእሳት የሚቀርብ መባ ይሆናል። 8 እሱም በየሰንበቱ ዘወትር በይሖዋ ፊት ይደርድረው።+ ይህ በእኔና በእስራኤላውያን መካከል ያለ ዘላቂ ቃል ኪዳን ነው። 9 ይህም የአሮንና የወንዶች ልጆቹ ይሆናል፤+ ለይሖዋ በእሳት ከሚቀርቡት መባዎች መካከል ለእሱ እጅግ ቅዱስ ነገር ስለሆነ ቅዱስ በሆነ ቦታ ይበሉታል፤+ ይህ ዘላቂ ሥርዓት ነው።”

10 በእስራኤላውያን መካከል በእናቱ እስራኤላዊ በአባቱ ግን ግብፃዊ የሆነ አንድ ሰው ነበር፤+ በሰፈሩም ውስጥ በእሱና በአንድ እስራኤላዊ መካከል ጠብ ተነሳ። 11 የእስራኤላዊቷም ልጅ የአምላክን ስም* መሳደብና መራገም ጀመረ።+ በመሆኑም ወደ ሙሴ አመጡት።+ የእናትየውም ስም ሸሎሚት ነበር፤ እሷም ከዳን ነገድ የሆነው የዲብራይ ልጅ ነበረች። 12 እነሱም የይሖዋ ውሳኔ ግልጽ እስኪሆንላቸው ድረስ በጥበቃ ሥር እንዲቆይ አደረጉት።+

13 ከዚያም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ 14 “የተራገመውን ሰው ከሰፈሩ ውጭ አውጣው፤ የሰሙትም ሰዎች ሁሉ እጃቸውን በራሱ ላይ ይጫኑበት፤ መላው ጉባኤም በድንጋይ ይውገረው።+ 15 ለእስራኤላውያንም እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ ‘ማንኛውም ሰው አምላኩን ቢራገም ለሠራው ኃጢአት ይጠየቅበታል። 16 ስለሆነም የይሖዋን ስም የተሳደበው ሰው ይገደል።+ መላው ጉባኤም በድንጋይ ይውገረው። የባዕድ አገሩም ሰው የአምላክን ስም ከተሳደበ ልክ እንደ አገሩ ተወላጅ ይገደል።

17 “‘አንድ ሰው የሰው ሕይወት ካጠፋ* ይገደል።+ 18 የቤት እንስሳን የገደለ* ሰው፣ ሕይወት ስለ ሕይወት* ካሳ አድርጎ መክፈል ይኖርበታል። 19 አንድ ሰው በባልንጀራው ላይ ጉዳት ቢያደርስ ልክ እሱ ያደረሰው ዓይነት ጉዳት በራሱ ላይ እንዲደርስ ይደረግ።+ 20 ስብራት ስለ ስብራት፣ ዓይን ስለ ዓይን፣ ጥርስ ስለ ጥርስ ይሁን፤ በሰውየው ላይ ያደረሰው ዓይነት ጉዳት በእሱ ላይ እንዲደርስ ይደረግ።+ 21 እንስሳን መትቶ የገደለ ስለ እንስሳው ካሳ መክፈል ይኖርበታል፤+ ሰውን መትቶ የገደለ ግን መገደል አለበት።+

22 “‘ለባዕድ አገሩም ሰው ሆነ ለአገሬው ተወላጅ፣ ለሁላችሁም የሚሠራው አንድ ዓይነት ድንጋጌ ነው፤+ ምክንያቱም እኔ አምላካችሁ ይሖዋ ነኝ።’”

23 ከዚያም ሙሴ ለእስራኤላውያን ነገራቸው፤ እነሱም የተራገመውን ሰው ከሰፈሩ ውጭ አውጥተው በድንጋይ ወገሩት።+ በዚህ መንገድ እስራኤላውያን ልክ ይሖዋ ሙሴን እንዳዘዘው አደረጉ።

25 በተጨማሪም ይሖዋ ሙሴን በሲና ተራራ ላይ እንዲህ አለው፦ 2 “ለእስራኤላውያን እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ ‘እኔ ወደምሰጣችሁ ምድር በምትገቡበት ጊዜ+ ምድሪቱ ለይሖዋ ሰንበትን ማክበር ይኖርባታል።+ 3 ስድስት ዓመት በእርሻህ ላይ ዘር ዝራ፤ ስድስት ዓመት ወይንህን ግረዝ፤ እንዲሁም የምድሪቱን ምርት ሰብስብ።+ 4 ሰባተኛው ዓመት ግን ምድሪቱ ሙሉ በሙሉ የምታርፍበት ሰንበት ይኸውም የይሖዋ ሰንበት ይሁን። በእርሻህ ላይ ዘር አትዝራ ወይም ወይንህን አትግረዝ። 5 በማሳህ ላይ የበቀለውን ገቦ* አትጨድ፤ ያልተገረዘውን ወይንህን ፍሬ አትልቀም። ምድሪቱ ለአንድ ዓመት ሙሉ በሙሉ ማረፍ ይኖርባታል። 6 ሆኖም ምድሪቱ በሰንበት እረፍቷ ጊዜ የምታበቅለውን እህል መብላት ትችላለህ፤ አንተ፣ ወንድ ባሪያህ፣ ሴት ባሪያህ፣ ቅጥር ሠራተኛህና አብረውህ የሚኖሩ ባዕዳን ሰፋሪዎች ልትበሉት ትችላላችሁ፤ 7 እንዲሁም በምድርህ ለሚኖሩ የቤትና የዱር እንስሳት ምግብ ይሁን። ምድሪቱ የምትሰጠው ምርት ሁሉ ለምግብነት ሊውል ይችላል።

8 “‘ሰባት የሰንበት ዓመታትን ማለትም ሰባት ጊዜ ሰባት ዓመታትን ትቆጥራለህ፤ ሰባቱ የሰንበት ዓመታትም 49 ዓመታት ይሆናሉ። 9 ከዚያም በሰባተኛው ወር ከወሩም በአሥረኛው ቀን ቀንደ መለከቱን ድምፁን ከፍ አድርገህ ትነፋዋለህ፤ በስርየት ቀን+ የቀንደ መለከቱ ድምፅ በምድራችሁ ሁሉ እንዲሰማ ማድረግ አለባችሁ። 10 ሃምሳኛውን ዓመት ቀድሱ፤ በምድሪቱም ለሚኖሩ ሁሉ ነፃነት አውጁ።+ ለእናንተ ኢዮቤልዩ ይሆንላችኋል፤ ከእናንተ እያንዳንዱ ወደየርስቱ ይመለሳል፤ ከእናንተም እያንዳንዱ ወደየቤተሰቡ ይመለስ።+ 11 ሃምሳኛው ዓመት ለእናንተ ኢዮቤልዩ ይሆንላችኋል። ዘር አትዘሩም ወይም ማሳ ላይ የበቀለውን ገቦ አታጭዱም አሊያም ያልተገረዘውን የወይን ፍሬ አትሰበስቡም።+ 12 ምክንያቱም ይህ ኢዮቤልዩ ነው። ለእናንተም ቅዱስ መሆን ይኖርበታል። ምድሪቱ በራሷ የምታበቅለውን ብቻ መብላት ትችላላችሁ።+

13 “‘በዚህ የኢዮቤልዩ ዓመት ከእናንተ እያንዳንዱ ወደየርስቱ ይመለስ።+ 14 ለባልንጀራችሁ አንድ ነገር ብትሸጡ ወይም ከባልንጀራችሁ እጅ አንድ ነገር ብትገዙ አንዳችሁ ሌላውን መጠቀሚያ አታድርጉ።+ 15 ከባልንጀራህ ላይ መሬት ስትገዛ ከኢዮቤልዩ በኋላ ያሉትን ዓመታት ግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርብሃል፤ እሱም ሲሸጥልህ እህል የሚሰበሰብባቸውን የቀሩትን ዓመታት ማስላት ይኖርበታል።+ 16 ብዙ ዓመታት የሚቀሩ ከሆነ ዋጋውን መጨመር ይችላል፤ የሚቀሩት ዓመታት ጥቂት ከሆኑ ደግሞ ዋጋውን መቀነስ ይኖርበታል፤ ምክንያቱም የሚሸጥልህ አዝመራ የሚሰበሰብበትን ጊዜ አስልቶ ነው። 17 ከእናንተ መካከል ማንም ባልንጀራውን መጠቀሚያ ማድረግ የለበትም፤+ አምላክህን ፍራ፤+ ምክንያቱም እኔ አምላካችሁ ይሖዋ ነኝ።+ 18 ደንቦቼን ብትፈጽሙና ድንጋጌዎቼን ብትጠብቁ በምድሪቱ ላይ ያለስጋት ትኖራላችሁ።+ 19 ምድሪቱ ፍሬዋን ትሰጣለች፤+ እናንተም እስክትጠግቡ ድረስ ትበላላችሁ፤ በዚያም ያለስጋት ትኖራላችሁ።+

20 “‘ሆኖም ‘ዘር ካልዘራን ወይም እህል ካልሰበሰብን በሰባተኛው ዓመት ምን እንበላለን?’ ብትሉ+ 21 እኔ በስድስተኛው ዓመት በረከቴን እልክላችኋለሁ፤ ምድሪቱም ለሦስት ዓመት የሚበቃ እህል ታፈራለች።+ 22 ከዚያም በስምንተኛው ዓመት ዘር ትዘራላችሁ፤ እስከ ዘጠነኛውም ዓመት ድረስ ቀድሞ ከሰበሰባችሁት ትበላላችሁ። እህሉ እስኪደርስ ድረስ ቀድሞ የሰበሰባችሁትን ትበላላችሁ።

23 “‘ምድሪቱ የእኔ ስለሆነች+ መሬት ለዘለቄታው መሸጥ አይኖርበትም።+ ምክንያቱም እናንተ በእኔ አመለካከት የባዕድ አገር ሰዎችና ሰፋሪዎች ናችሁ።+ 24 በርስትነት በያዛችሁት ምድር ሁሉ መሬትን መልሶ መግዛት የሚያስችል መብት እንዲኖር አድርጉ።

25 “‘ወንድምህ ቢደኸይና ከርስቱ የተወሰነውን ለመሸጥ ቢገደድ የሚዋጅ የቅርብ ዘመዱ መጥቶ ወንድሙ የሸጠውን መልሶ ይግዛ።+ 26 አንድ ሰው የሚዋጅለት ቢያጣ ሆኖም እሱ ራሱ ሀብት ቢያገኝና መሬቱን ለመዋጀት የሚያስችል አቅም ቢኖረው 27 መሬቱን ከሸጠበት ጊዜ አንስቶ ያሉትን ዓመታት በመቁጠር ዋጋውን ያስላ፤ የዋጋውንም ልዩነት ለሸጠለት ሰው ይመልስ። ከዚያም ወደ ርስቱ መመለስ ይችላል።+

28 “‘ሆኖም መሬቱን ከሰውየው ላይ ለማስመለስ የሚያስችል አቅም ባይኖረው የሸጠው መሬት እስከ ኢዮቤልዩ ዓመት ድረስ በገዢው እጅ ይቆያል፤+ መሬቱም በኢዮቤልዩ ይመለስለታል፤ እሱም ወደ ርስቱ ይመለሳል።+

29 “‘አንድ ሰው በቅጥር በታጠረ ከተማ ውስጥ የሚገኝን መኖሪያ ቤት ቢሸጥ ከሸጠበት ጊዜ አንስቶ እስከ አንድ ዓመት ድረስ የመዋጀት መብቱ እንደተጠበቀ ይቆያል፤ የመዋጀት መብቱ+ ለአንድ ዓመት ሙሉ እንደተጠበቀ ይቆያል። 30 ይሁንና ዓመቱ ከመጠናቀቁ በፊት መልሶ ሊገዛው ካልቻለ በቅጥር በታጠረው ከተማ ውስጥ የሚገኘው ቤት ለዘለቄታው የገዢው ንብረት ሆኖ በትውልዶቹ ሁሉ ይቀጥላል። በኢዮቤልዩ ነፃ አይለቀቅም። 31 ቅጥር በሌላቸው መንደሮች ውስጥ የሚገኙ ቤቶች ግን በገጠራማ አካባቢ የሚገኝ የእርሻ መሬት ክፍል እንደሆኑ ይቆጠራሉ። የመዋጀት መብታቸው እንደተጠበቀ ይቆይ፤ በኢዮቤልዩም ነፃ ይለቀቁ።

32 “‘በሌዋውያን ከተሞች+ ውስጥ ያሉትን የሌዋውያን ቤቶች በተመለከተ ግን ሌዋውያኑ እነዚህን ቤቶች የመዋጀት መብታቸው ምንጊዜም የተጠበቀ ነው። 33 የሌዋውያን ንብረት ተመልሶ ካልተገዛ የእነሱ በሆነው ከተማ ውስጥ የሚገኘው የተሸጠው ቤት በኢዮቤልዩ ነፃ ይለቀቃል፤+ ምክንያቱም በሌዋውያኑ ከተሞች ውስጥ የሚገኙት ቤቶች በእስራኤላውያን መካከል ያሉ የሌዋውያኑ ንብረቶች ናቸው።+ 34 ከዚህም በላይ በከተሞቻቸው ዙሪያ ያለው የግጦሽ መሬት+ ዘላለማዊ ርስታቸው ስለሆነ መሸጥ አይኖርበትም።

35 “‘በአቅራቢያህ ያለ ወንድምህ ቢደኸይና ራሱን ማስተዳደር ቢያቅተው አብሮህ በሕይወት ይኖር ዘንድ አንድን የባዕድ አገር ሰውና ሰፋሪ+ እንደምትረዳ ሁሉ ልትረዳው ይገባል።+ 36 ከእሱ ወለድ ወይም ትርፍ* አትቀበል።+ ከዚህ ይልቅ አምላክህን ፍራ፤+ ወንድምህም አብሮህ በሕይወት ይኖራል። 37 ገንዘብህን በወለድ አታበድረው+ ወይም እህል ስታበድረው ትርፍ አትጠይቀው። 38 የከነአንን ምድር በመስጠት አምላካችሁ መሆኔን አስመሠክር ዘንድ ከግብፅ ምድር ያወጣኋችሁ እኔ አምላካችሁ ይሖዋ ነኝ።+

39 “‘በአቅራቢያህ የሚኖር ወንድምህ ቢደኸይና ራሱን ለአንተ ለመሸጥ ቢገደድ+ እንደ ባሪያ እንዲሠራ አታስገድደው።+ 40 እንደ ቅጥር ሠራተኛና እንደ ሰፋሪ ሊታይ ይገባዋል።+ እስከ ኢዮቤልዩ ዓመት ድረስ ያገልግልህ። 41 ከዚያም እሱም ሆነ አብረውት ያሉት ልጆቹ* ትተውህ ይሄዳሉ፤ ወደ ዘመዶቹም ይመለሳሉ። እሱም ወደ ቀድሞ አባቶቹ ርስት ይመለስ።+ 42 ምክንያቱም እነሱ ከግብፅ ምድር ያወጣኋቸው ባሪያዎቼ ናቸው።+ እንደ ባሪያ ራሳቸውን መሸጥ የለባቸውም። 43 የጭካኔ ድርጊት ልትፈጽምበት አይገባም፤+ አምላክህን መፍራት ይኖርብሃል።+ 44 ወንድ ባሪያዎቻችሁና ሴት ባሪያዎቻችሁ በዙሪያችሁ ካሉት ብሔራት የመጡ ይሁኑ፤ ከእነሱ መካከል ወንድ ባሪያ ወይም ሴት ባሪያ መግዛት ትችላላችሁ። 45 በተጨማሪም ከእናንተ ጋር ከሚኖሩት ባዕዳን ሰፋሪዎች+ እንዲሁም እነሱ በምድራችሁ ከወለዷቸው ቤተሰቦቻቸው መካከል ባሪያዎችን መግዛት ትችላላችሁ፤ እነሱም የእናንተ ንብረት ይሆናሉ። 46 እነሱንም እንደ ቋሚ ንብረት አድርጋችሁ ከእናንተ በኋላ ለሚመጡት ልጆቻችሁ ማውረስ ትችላላችሁ። ባሪያ አድርጋችሁ ልታሠሯቸው ትችላላችሁ፤ ወንድሞቻችሁ የሆኑትን እስራኤላውያንን ግን በጭካኔ አትግዟቸው።+

47 “‘በመካከልህ ያለ የባዕድ አገር ሰው ወይም ሰፋሪ ሀብታም ቢሆንና ከእሱ ጋር ያለው ወንድምህ ደግሞ ደህይቶ ለባዕድ አገሩ ሰው ወይም ሰፋሪ አሊያም ከባዕድ አገሩ ሰው ቤተሰብ መካከል ለአንዱ ራሱን ለመሸጥ ቢገደድ 48 ይህ ሰው ራሱን ከሸጠም በኋላ የመዋጀት መብቱ የተጠበቀ ይሆናል። ከወንድሞቹ አንዱ መልሶ ሊገዛው ይችላል፤+ 49 ወይም ደግሞ አጎቱ አሊያም የአጎቱ ልጅ መልሶ ሊገዛው ይችላል፤ አሊያም ደግሞ ማንኛውም የቅርብ ዘመዱ* ማለትም ከቤተሰቦቹ አንዱ መልሶ ሊገዛው ይችላል።

“‘ወይም ደግሞ ሰውየው ራሱ ሀብት ካገኘ ራሱን መልሶ ሊገዛ ይችላል።+ 50 እሱም ራሱን ከሸጠበት ዓመት አንስቶ እስከ ኢዮቤልዩ ዓመት ድረስ ያለውን+ ጊዜ ከገዛው ሰው ጋር በመሆን ያስላ፤ የተሸጠበትም ገንዘብ ከዓመታቱ ብዛት ጋር የሚመጣጠን ይሁን።+ በዚህ ጊዜ ውስጥ ያሉት የሥራ ቀናት የሚሰሉት የአንድ ቅጥር ሠራተኛ የሥራ ቀናት በሚሰሉበት መንገድ ይሆናል።+ 51 ገና ብዙ ዓመታት የሚቀሩ ከሆነ እሱን ለመግዛት ከተከፈለው ገንዘብ ላይ የቀሪዎቹን ዓመታት ብዛት ግምት ውስጥ በማስገባት ራሱን የሚዋጅበትን ዋጋ ይክፈል። 52 እስከ ኢዮቤልዩ ዓመት ድረስ የሚቀሩት ዓመታት ጥቂት ከሆኑ ደግሞ ይህን ለራሱ ያስላ፤ በቀሩት ዓመታት ብዛት ልክም የሚዋጅበትን ዋጋ ይክፈል። 53  ከእሱም ጋር በሚቆይበት ጊዜ ከዓመት እስከ ዓመት እንደ ቅጥር ሠራተኛ ሆኖ ያገልግለው፤ አንተም የጭካኔ ድርጊት እንዳይፈጽምበት ተከታተል።+ 54 ሆኖም ከእነዚህ መንገዶች በአንዱ ራሱን መልሶ መግዛት ካልቻለ በኢዮቤልዩ ዓመት ነፃ ይለቀቃል፤+ እሱም ሆነ ልጆቹ* አብረውት ነፃ ይለቀቁ።

55 “‘እስራኤላውያን የእኔ ባሪያዎች ናቸው። እነሱ ከግብፅ ምድር ያወጣኋቸው ባሪያዎቼ ናቸው።+ እኔ አምላካችሁ ይሖዋ ነኝ።

26 “‘ትሰግዱላቸው ዘንድ+ ለራሳችሁ ከንቱ አማልክትን አትሥሩ፤+ እንዲሁም ለራሳችሁ የተቀረጸ ምስል+ ወይም የማምለኪያ ዓምድ አታቁሙ፤ በምድራችሁም ከድንጋይ የተቀረጸ ምስል አታኑሩ፤+ ምክንያቱም እኔ አምላካችሁ ይሖዋ ነኝ። 2 ሰንበቶቼን ጠብቁ፤ ለመቅደሴም አክብሮት* ይኑራችሁ። እኔ ይሖዋ ነኝ።

3 “‘ባወጣኋቸው ደንቦች መሠረት ብትሄዱና ትእዛዛቴን ብትጠብቁ እንዲሁም ብትፈጽሙ+ 4 ዝናብን በወቅቱ አዘንብላችኋለሁ፤+ ምድሪቱም ምርቷን ትሰጣለች፤+ የሜዳ ዛፎችም ፍሬያቸውን ይሰጣሉ። 5 ገና እህላችሁን ወቅታችሁ ሳትጨርሱ ወይናችሁን የምትሰበስቡበት ጊዜ ይደርሳል፤ ገና ወይኑን ሰብስባችሁ ሳትጨርሱ ደግሞ ዘር የምትዘሩበት ጊዜ ይመጣል፤ ምግባችሁን እስክትጠግቡ ድረስ ትበላላችሁ፤ በምድራችሁም ያለስጋት ትቀመጣላችሁ።+ 6 በምድሪቱ ሰላም አሰፍናለሁ፤+ እናንተም ማንም ሳያስፈራችሁ ትተኛላችሁ፤+ እኔም አደገኛ አውሬዎች በምድሪቱ እንዳይኖሩ አደርጋለሁ፤ በምድራችሁም የጦርነት ሰይፍ አያልፍም። 7 እናንተም በእርግጥ ጠላቶቻችሁን ታሳድዳላችሁ፤ እነሱም በፊታችሁ በሰይፍ ይወድቃሉ። 8 አምስታችሁ 100 ሰዎችን ታሳድዳላችሁ፤ መቶዎቻችሁ ደግሞ 10,000 ሰዎችን ታሳድዳላችሁ፤ ጠላቶቻችሁም በፊታችሁ በሰይፍ ይወድቃሉ።+

9 “‘እኔም ሞገስ አሳያችኋለሁ፤* ፍሬያማ እንድትሆኑና እንድትበዙ አደርጋችኋለሁ፤+ ከእናንተ ጋር የገባሁትንም ቃል ኪዳኔን እጠብቃለሁ።+ 10 እናንተም ያለፈውን ዓመት እህል ገና በልታችሁ ሳትጨርሱ ለዘንድሮው እህል ቦታ ለማግኘት ያለፈውን ዓመት እህል ታስለቅቃላችሁ። 11 የማደሪያ ድንኳኔን በመካከላችሁ እተክላለሁ፤+ እኔም አልተዋችሁም።* 12 በመካከላችሁ እሄዳለሁ፤ አምላካችሁም እሆናለሁ፤+ እናንተ ደግሞ ሕዝቦቼ ትሆናላችሁ።+ 13 የግብፃውያን ባሪያዎች ሆናችሁ እንዳትቀሩ ከዚያ ምድር ያወጣኋችሁና ቀንበራችሁን ሰብሬ ራሳችሁን ቀና አድርጋችሁ* እንድትሄዱ ያደረግኳችሁ እኔ አምላካችሁ ይሖዋ ነኝ።

14 “‘ይሁን እንጂ የማትሰሙኝ ወይም እነዚህን ትእዛዛት በሙሉ የማትፈጽሙ ከሆነ+ 15 እንዲሁም ደንቦቼን ችላ የምትሉና+ ትእዛዛቴን በሙሉ ላለመፈጸም ድንጋጌዎቼን የምትጸየፉ፣* ቃል ኪዳኔንም የምታፈርሱ ከሆነ+ 16 እኔ ደግሞ እንዲህ አደርግባችኋለሁ፦ ዓይናችሁ እንዲጠፋና ሕይወታችሁ* እንዲመነምን የሚያደርግ የሳንባ ነቀርሳና ኃይለኛ ትኩሳት በእናንተ ላይ በማምጣት በጭንቀት እቀጣችኋለሁ። ዘራችሁን የምትዘሩት እንዲሁ በከንቱ ይሆናል፤ ምክንያቱም የሚበሉት ጠላቶቻችሁ ናቸው።+ 17 እኔም በእርግጥ ፊቴን አጠቁርባችኋለሁ፤ ጠላቶቻችሁም ድል ያደርጓችኋል፤+ የሚጠሏችሁም ሰዎች ይረግጧችኋል፤+ እንዲሁም ማንም ሳያሳድዳችሁ ትሸሻላችሁ።+

18 “‘እነዚህ ሁሉ ነገሮች ደርሰውባችሁም የማትሰሙኝ ከሆነ ለሠራችሁት ኃጢአት ሰባት እጥፍ እቀጣችኋለሁ። 19 ኃይለኛ የሆነውን ትዕቢታችሁን እሰብረዋለሁ፤ ሰማያችሁን እንደ ብረት፣+ ምድራችሁን ደግሞ እንደ መዳብ አደርገዋለሁ። 20 ምድራችሁ ምርቷን ስለማትሰጥና የምድርም ዛፍ ፍሬ ስለማያፈራ ኃይላችሁን እንዲሁ በከንቱ ታባክናላችሁ።+

21 “‘ሆኖም እኔን መቃወማችሁን ከቀጠላችሁና እኔን ለመስማት ፈቃደኞች ሳትሆኑ ከቀራችሁ እንደ ኃጢአታችሁ መጠን ሰባት እጥፍ እመታችኋለሁ። 22 የዱር አራዊትን እሰድባችኋለሁ፤+ እነሱም ልጆቻችሁን ይነጥቋችኋል፤+ የቤት እንስሶቻችሁንም ይበሉባችኋል፤ ቁጥራችሁም እንዲመናመን ያደርጋሉ፤ መንገዶቻችሁም ጭር ይላሉ።+

23 “‘እነዚህ ሁሉ ነገሮች ደርሰውባችሁም እርማቴን ባትቀበሉና+ እኔን መቃወማችሁን ብትገፉበት 24 እኔም እናንተን በመቃወም እመጣባችኋለሁ፤ ለኃጢአታችሁም ሰባት እጥፍ እመታችኋለሁ። 25 ከእኔ ጋር የገባችሁትን ቃል ኪዳን ስላፈረሳችሁ+ በላያችሁ ላይ የበቀል ሰይፍ አመጣባችኋለሁ። በከተሞቻችሁ ውስጥ ከተሰበሰባችሁ በመካከላችሁ በሽታ እልክባችኋለሁ፤+ እናንተም ለጠላት እጅ ትሰጣላችሁ።+ 26 የዳቦ እጥረት እንዲከሰትባችሁ+ በማደርግበት ጊዜ* አሥር ሴቶች በአንድ ምድጃ ብቻ ዳቦ ይጋግሩላችኋል፤ ዳቦውንም እየመዘኑ ያከፋፍሏችኋል፤+ እናንተም ትበላላችሁ፤ ነገር ግን አትጠግቡም።+

27 “‘ይሁን እንጂ በዚህም እኔን ለመስማት ፈቃደኛ ካልሆናችሁና እኔን መቃወማችሁን ከገፋችሁበት 28 በኃይል እቃወማችኋለሁ፤+ እኔ ራሴም ለኃጢአታችሁ ሰባት እጥፍ እቀጣችኋለሁ። 29 በመሆኑም የወንድ ልጆቻችሁን ሥጋ ትበላላችሁ፤ የሴት ልጆቻችሁንም ሥጋ ትበላላችሁ።+ 30 በከፍታ ቦታዎች ላይ ያሉትን ቅዱስ ስፍራዎቻችሁን+ አጠፋለሁ፤ የዕጣን ማጨሻዎቻችሁንም አስወግዳለሁ፤ በድናችሁንም አስጸያፊ በሆኑት ጣዖቶቻችሁ* በድን ላይ እከምረዋለሁ፤+ እኔም ተጸይፌያችሁ ከእናንተ ዞር እላለሁ።*+ 31 ከተሞቻችሁን ለሰይፍ አሳልፌ እሰጣለሁ፤+ መቅደሶቻችሁንም ባዶ አደርጋቸዋለሁ፤ የመሥዋዕቶቻችሁን ደስ የሚያሰኝ* መዓዛ አላሸትም። 32 እኔ ራሴ ምድሪቱን ባድማ አደርጋታለሁ፤+ በዚያ የሚኖሩ ጠላቶቻችሁም በመደነቅ ይመለከቷታል።+ 33 እናንተንም በብሔራት መካከል እበትናችኋለሁ፤+ ሰይፍም መዝዤ አሳድዳችኋለሁ፤+ ምድራችሁ ባድማ ትሆናለች፤+ ከተሞቻችሁም ይፈራርሳሉ።

34 “‘በጠላቶቻችሁ ምድር ሆናችሁ ምድሪቱ ባድማ ሆና በምትቆይባቸው ጊዜያት ሁሉ የሰንበት ዕዳዋን ትከፍላለች። በዚያን ጊዜ ምድሪቱ የሰንበት ዕዳዋን መክፈል ስላለባት ታርፋለች።*+ 35 ምድሪቱ ትኖሩባት በነበረው ጊዜ በሰንበታችሁ ወቅት ስላላረፈች ባድማ ሆና በምትቆይባቸው ጊዜያት ሁሉ ታርፋለች።

36 “‘ከእናንተ መካከል በሕይወት የሚተርፉትም+ በጠላቶቻቸው ምድር ልባቸው ተስፋ እንዲቆርጥ አደርጋለሁ፤ የቅጠል ኮሽታ እንኳ ያስበረግጋቸዋል፤ ከሰይፍ እንደሚሸሽ ሰው ይፈረጥጣሉ፤ ማንም ሳያሳድዳቸው ይወድቃሉ።+ 37 ከሰይፍ እንደሚሸሹ ሰዎች እነሱም ማንም ሳያሳድዳቸው እርስ በርሳቸው እየተደነቃቀፉ ይወድቃሉ። እናንተም ጠላቶቻችሁን መቋቋም ይሳናችኋል።+ 38 በብሔራት መካከል ትጠፋላችሁ፤+ የጠላቶቻችሁም ምድር ትበላችኋለች። 39 ከእናንተ መካከል የሚተርፉትም በሠሩት ስህተት የተነሳ በጠላቶቻችሁ ምድር ይበሰብሳሉ።+ አዎ፣ በአባቶቻቸው ስህተት የተነሳ ይበሰብሳሉ።+ 40 ከዚያም የገዛ ራሳቸውን ስህተት እንዲሁም አባቶቻቸው የፈጸሙትን ስህተትና ታማኝነት የጎደለው ድርጊት ይናዘዛሉ፤+ እንዲሁም እኔን በመቃወም ታማኝ ሳይሆኑ መቅረታቸውን አምነው ይቀበላሉ።+ 41 እኔም እነሱን ወደ ጠላቶቻቸው ምድር በማምጣት+ እቃወማቸዋለሁ።+

“‘ምናልባትም ያልተገረዘው* ልባቸው በዚያ ጊዜ ትሑት ይሆናል፤+ የስህተታቸውንም ዋጋ ይከፍላሉ። 42 እኔም ከያዕቆብ ጋር የገባሁትን ቃል ኪዳንና ከይስሐቅ ጋር የገባሁትን ቃል ኪዳን አስባለሁ፤+ እንዲሁም ከአብርሃም ጋር የገባሁትን ቃል ኪዳን አስታውሳለሁ፤+ ምድሪቱንም አስባለሁ። 43 እነሱም ምድሪቱን ትተዋት በሄዱበት ጊዜ ምድሪቱ የሰንበት ዕዳዋን ትከፍላለች፤+ ያለእነሱም ባድማ ሆና ትቆያለች፤ እነሱም ድንጋጌዎቼን ችላ ስላሉና ደንቦቼን ስለተጸየፉ*+ የስህተታቸውን ዋጋ ይከፍላሉ። 44 ይህ ሁሉ ቢሆንም ግን በጠላቶቻቸው ምድር በሚቆዩበት ጊዜ ሁሉ እርግፍ አድርጌ አልተዋቸውም፤+ ፈጽሜ እስካጠፋቸውም ድረስ አልጥላቸውም፤ እንዲህ ባደርግ ከእነሱ ጋር የገባሁትን ቃል ኪዳን ማፍረስ ይሆንብኛል፤+ ምክንያቱም እኔ አምላካቸው ይሖዋ ነኝ። 45 አምላካቸው መሆኔን አስመሠክር ዘንድ ብሔራት በዓይናቸው እያዩ ከግብፅ ምድር ካወጣኋቸው አባቶቻቸው+ ጋር የገባሁትን ቃል ኪዳን ስለ እነሱ ስል አስባለሁ።+ እኔ ይሖዋ ነኝ።’”

46 ይሖዋ በሲና ተራራ ላይ በሙሴ አማካኝነት በራሱና በእስራኤላውያን መካከል ያስቀመጣቸው ሥርዓቶች፣ ድንጋጌዎችና ሕጎች እነዚህ ናቸው።+

27 ይሖዋም ሙሴን እንዲህ አለው፦ 2 “ለእስራኤላውያን እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ ‘አንድ ሰው የአንድን ግለሰብ* የተተመነ ዋጋ ለይሖዋ ለማቅረብ ልዩ ስእለት ቢሳል+ 3 ከ20 ዓመት እስከ 60 ዓመት ድረስ ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ ለሚገኝ ወንድ የሚተመነው ዋጋ እንደ ቋሚ መለኪያ ሆኖ በሚያገለግለው በቅዱሱ ስፍራ ሰቅል* 50 የብር ሰቅል* ይሆናል። 4 ሴት ከሆነች ግን የሚተመንላት ዋጋ 30 ሰቅል ይሆናል። 5 ከ5 ዓመት እስከ 20 ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኝ ወንድ ከሆነ የሚተመንለት ዋጋ 20 ሰቅል ይሆናል፤ ሴት ከሆነች ደግሞ 10 ሰቅል ይሆናል። 6 ከአንድ ወር እስከ አምስት ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኝ ወንድ ከሆነ የሚተመንለት ዋጋ አምስት የብር ሰቅል ይሆናል፤ ሴት ከሆነች ደግሞ ሦስት የብር ሰቅል ይሆናል።

7 “‘ዕድሜው ከ60 ዓመት በላይ ለሆነ ወንድ ደግሞ የሚተመንለት ዋጋ 15 ሰቅል ይሆናል፤ ሴት ከሆነች 10 ሰቅል ይሆናል። 8 ሆኖም ሰውየው በጣም ድሃ ቢሆንና የተተመነውን ዋጋ መስጠት ባይችል+ ግለሰቡ ካህኑ ፊት ይቆማል፤ ካህኑም ለሰውየው ዋጋ ይተምንለታል። ካህኑ ስእለት የተሳለውን ሰው አቅም ግምት ውስጥ በማስገባት ለሰውየው ዋጋ ይተምንለታል።+

9 “‘ስእለቱ ለይሖዋ መባ ሆኖ መቅረብ የሚችል እንስሳ ከሆነ ለይሖዋ የሚሰጠው ማንኛውም ነገር የተቀደሰ ይሆናል። 10 እንስሳውን በሌላ መተካትም ሆነ መጥፎውን በጥሩ፣ ጥሩውን በመጥፎ መለወጥ አይችልም። እንስሳውን በሌላ እንስሳ መለወጥ ካለበት ግን የመጀመሪያው እንስሳም ሆነ ተለዋጭ ሆኖ የቀረበው እንስሳ የተቀደሱ ይሆናሉ። 11 ሰውየው ያቀረበው እንስሳ ለይሖዋ መባ ሆኖ ሊቀርብ የማይችል ርኩስ እንስሳ+ ከሆነ እንስሳውን ካህኑ ፊት ያቁመው። 12 ካህኑ እንስሳው ጥሩ ወይም መጥፎ መሆኑን ግምት ውስጥ በማስገባት ዋጋ ይተምንለት። ካህኑ የተመነውም ዋጋ ይጸናል። 13 ሆኖም ሰውየው እንስሳውን መልሶ መግዛት ከፈለገ በተተመነው ዋጋ ላይ አንድ አምስተኛውን ጨምሮ መስጠት አለበት።+

14 “‘አንድ ሰው ቤቱን ቅዱስ አድርጎ ለይሖዋ ቢሰጥ ካህኑ ቤቱ ጥሩ ወይም መጥፎ መሆኑን ግምት ውስጥ በማስገባት ዋጋ ይተምንለት። የቤቱ ዋጋ ካህኑ የተመነው ዋጋ ይሆናል።+ 15 ሆኖም ቤቱን ቅዱስ አድርጎ የሰጠው ሰው ቤቱን መልሶ መግዛት ከፈለገ በተተመነው ዋጋ ላይ የገንዘቡን አንድ አምስተኛ ጨምሮ መስጠት አለበት፤ ቤቱም የእሱ ይሆናል።

16 “‘አንድ ሰው ርስት አድርጎ ከያዘው እርሻ ላይ የተወሰነውን ለይሖዋ ቅዱስ አድርጎ ቢሰጥ ዋጋው መተመን ያለበት የሚዘራበትን ዘር መጠን ግምት ውስጥ በማስገባት ይሆናል፤ ለአንድ ሆሜር* የገብስ ዘር 50 የብር ሰቅል ይሆናል። 17 ሰውየው እርሻውን ከኢዮቤልዩ ዓመት+ አንስቶ ቅዱስ አድርጎ ከሰጠ የተተመነለት ዋጋ ይጸናል። 18 ሰውየው እርሻውን ቅዱስ አድርጎ የሰጠው ኢዮቤልዩ ካለፈ በኋላ ከሆነ ካህኑ እስከ ቀጣዩ የኢዮቤልዩ ዓመት ድረስ የቀሩትን ዓመታት ግምት ውስጥ በማስገባት ዋጋውን ያስላለት፤ ከተተመነውም ዋጋ ላይ መቀነስ አለበት።+ 19 ሆኖም እርሻውን ቅዱስ አድርጎ የሰጠው ሰው እርሻውን መልሶ መግዛት ከፈለገ በተተመነው ዋጋ ላይ የገንዘቡን አንድ አምስተኛ ጨምሮ መስጠት አለበት፤ ከዚያም እርሻው የእሱ ንብረት እንደሆነ ይጸናል። 20 ሰውየው እርሻውን መልሶ ባይገዛውና እርሻው ለሌላ ሰው ቢሸጥ ሰውየው መልሶ ሊገዛው አይችልም። 21 እርሻው በኢዮቤልዩ ነፃ በሚለቀቅበት ጊዜ ለይሖዋ እንደተሰጠ እርሻ ተቆጥሮ ለእሱ የተቀደሰ ይሆናል። የካህናቱም ንብረት ይሆናል።+

22 “‘አንድ ሰው በውርስ ያገኘው ንብረት ክፍል ያልሆነውን በገንዘቡ የገዛውን እርሻ+ ለይሖዋ ቅዱስ አድርጎ ቢሰጥ 23 ካህኑ እስከ ኢዮቤልዩ ዓመት ድረስ የሚያወጣውን ዋጋ ይተምንለት፤ እሱም የተተመነውን ዋጋ በዚያው ቀን ይስጥ።+ ይህ ለይሖዋ የተቀደሰ ነው። 24 በኢዮቤልዩ ዓመት እርሻው ለሻጩ ይኸውም ለመሬቱ ባለቤት ይመለሳል።+

25 “‘እያንዳንዱ ዋጋ እንደ ቋሚ መለኪያ ሆኖ በሚያገለግለው በቅዱሱ ስፍራ ሰቅል መሠረት መተመን አለበት። አንዱ ሰቅል 20 ጌራ* መሆን ይኖርበታል።

26 “‘ይሁንና ማንም ሰው ከእንስሳት መካከል በኩር የሆነውን ቅዱስ አድርጎ መስጠት የለበትም፤ ምክንያቱም በኩሩ የይሖዋ ነው።+ በሬም ሆነ በግ ቀድሞውንም የይሖዋ ነው።+ 27 በኩሩ ርኩስ ከሆኑት እንስሳት መካከል ከሆነና በተተመነለት ዋጋ መሠረት ከዋጀው በዋጋው ላይ አንድ አምስተኛውን ጨምሮ መስጠት አለበት።+ ሰውየው መልሶ የማይገዛው ከሆነ ግን በተተመነው ዋጋ መሠረት ይሸጥ።

28 “‘አንድ ሰው የራሱ ከሆኑት ነገሮች ውስጥ ያለምንም ገደብ ለይሖዋ የሰጠው ማንኛውም ተለይቶ የተሰጠ ነገር ይኸውም የእሱ ንብረት የሆነ ሰውም ሆነ እንስሳ አሊያም እርሻ ሊሸጥም ሆነ ተመልሶ ሊገዛ አይችልም። ተለይቶ የተሰጠ ማንኛውም ነገር ለይሖዋ እጅግ የተቀደሰ ነው።+ 29 በተጨማሪም እንዲጠፋ የተበየነበት ማንኛውም ለጥፋት የተለየ ሰው አይዋጅም፤+ ከዚህ ይልቅ መገደል አለበት።+

30 “‘እርሻው ከሚሰጠው ምርትም ሆነ ዛፉ ከሚያፈራው ፍሬ ውስጥ የምድሩ አንድ አሥረኛ*+ ሁሉ የይሖዋ ነው። ይህ ለይሖዋ የተቀደሰ ነው። 31 አንድ ሰው አንድ አሥረኛ አድርጎ የሰጠውን ማንኛውንም ነገር መልሶ መግዛት ቢፈልግ በዋጋው ላይ አንድ አምስተኛውን ጨምሮ መስጠት አለበት። 32 ከከብቶቹና ከመንጋው መካከል አንድ አሥረኛው ማለትም በበትሩ ሥር ከሚያልፉት መካከል አሥረኛው እንስሳ* ለይሖዋ የተቀደሰ መሆን አለበት። 33 ከዚህ በኋላ እንስሳው ጥሩ ይሁን መጥፎ መመርመር የለበትም፤ በሌላ ሊለውጠውም አይገባም። እንስሳውን በሌላ መለወጥ ካሰበ ግን የመጀመሪያው እንስሳም ሆነ ተለዋጭ ሆኖ የቀረበው እንስሳ የተቀደሱ ይሆናሉ።+ ተመልሶ ሊገዛ አይችልም።’”

34 ይሖዋ በሲና ተራራ+ ላይ በሙሴ አማካኝነት ለእስራኤላውያን የሰጣቸው ትእዛዛት እነዚህ ናቸው።

ቃል በቃል “የእስራኤልን ወንዶች ልጆች።”

ወይም “ኩላሊቱን ከሸፈነው ስብ።”

ወይም “የሚያረጋጋ፤ የሚያበርድ።” ቃል በቃል “እረፍት የሚሰጥ።”

ወይም “ኩላሊቱን የሸፈነውን ስብ።”

ወይም “የሚያረጋጋ፤ የሚያበርድ።” ቃል በቃል “እረፍት የሚሰጥ።”

ወይም “በስብ የራሰው አመድ።” መሥዋዕት ሆነው በሚቀርቡት እንስሳት ስብ የራሰውን አመድ ያመለክታል።

ወይም “የሚያረጋጋ፤ የሚያበርድ።” ቃል በቃል “እረፍት የሚሰጥ።”

ወይም “ነፍስ።”

ወይም “የሚያረጋጋ፤ የሚያበርድ።” ቃል በቃል “እረፍት የሚሰጥ።”

የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

ወይም “የሚያረጋጋ፤ የሚያበርድ።” ቃል በቃል “እረፍት የሚሰጥ።”

ወይም “እንደሚያረጋጋ፣ እንደሚያበርድ።” ቃል በቃል “እረፍት እንደሚሰጥ።”

ወይም “የሰላም መባ መሥዋዕት።”

ወይም “የሚያረጋጋ፤ የሚያበርድ።” ቃል በቃል “እረፍት የሚሰጥ።”

ቃል በቃል “ዳቦ።” እንደ አምላክ ድርሻ የሚቆጠረውን የኅብረት መሥዋዕት ያመለክታል።

ወይም “የሚያረጋጋ፤ የሚያበርድ።” ቃል በቃል “እረፍት የሚሰጥ።”

ወይም “ማንኛውም ነፍስ።”

ወይም “በስብ የራሰው አመድ።” መሥዋዕት ሆነው በሚቀርቡት እንስሳት ስብ የራሰውን አመድ ያመለክታል።

ወይም “ነፍስ።”

ወይም “የሚያረጋጋ፤ የሚያበርድ።” ቃል በቃል “እረፍት የሚሰጥ።”

ወይም “ነፍስ።”

ቃል በቃል “የእርግማን (የመሐላ) ድምፅ ቢሰማና።” መጥፎ ድርጊት በፈጸመ ሰው ወይም የምሥክርነት ቃሉን ለመስጠት ፈቃደኛ በማይሆን ምሥክር ላይ የሚነገረውን እርግማን ጨምሮ አንድን መጥፎ ድርጊት በተመለከተ የሚታወጅን አዋጅ የሚያመለክት ሳይሆን አይቀርም።

ወይም “ነፍስ።”

ወይም “ነፍስ።”

አንድ ሰው የገባውን ቃል ሳይፈጽም መቅረቱን የሚያመለክት ሊሆን ይችላል።

አንድ አሥረኛ ኢፍ 2.2 ሊትር ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።

ወይም “ነፍስ።”

አንድ ሰቅል 11.4 ግራም ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።

ወይም “በቅዱሱ ሰቅል።”

ወይም “ነፍስ።”

ወይም “ነፍስ።”

ወይም “በስብ የራሰ አመድ።” መሥዋዕት ሆነው በሚቀርቡት እንስሳት ስብ የራሰውን አመድ ያመለክታል።

ወይም “የሚያረጋጋ፤ የሚያበርድ።” ቃል በቃል “እረፍት የሚሰጥ።”

ወይም “መባዎቹን የሚነካቸውም።”

አንድ አሥረኛ ኢፍ 2.2 ሊትር ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።

ወይም “የሚያረጋጋ፤ የሚያበርድ።” ቃል በቃል “እረፍት የሚሰጥ።”

ወይም “ነፍስ።”

ወይም “ነፍስ።”

ወይም “ነፍስ።”

ወይም “ይገደል።”

ወይም “ነፍስ።”

ወይም “ነፍስ።”

ወይም “ነፍስ።”

ወይም “ቅዱሱን ዘውድ።”

ወይም “ኩላሊቱን የሸፈነውን ስብ።”

ወይም “የሚያረጋጋ፤ የሚያበርድ።” ቃል በቃል “እረፍት የሚሰጥ።”

ወይም “የሚያረጋጋ፤ የሚያበርድ።” ቃል በቃል “እረፍት የሚሰጥ።”

ቃል በቃል “እጃችሁን መሙላት።”

ወይም “ከየብስ እንስሳት።”

ወይም “ነፍሳት።”

ወይም “ነፍስ።”

ወይም “ነፍሳችሁን።”

ወይም “ነፍሳችሁን።”

ወይም “ነፍስ።”

ወይም “ነፍስ።”

ወይም “ዘር ብትፀንስና።”

“የሥጋ ደዌ” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል ሰፊ ትርጉም ያለው ሲሆን የተለያዩ ተላላፊ የቆዳ በሽታዎችን ሊያመለክት ይችላል። ልብስንና ቤትን የሚበክሉ አንዳንድ በሽታዎችንም ሊጨምር ይችላል።

ወይም “ቁስሉ።”

ወይም “በሽታው የማይተላለፍ።”

ሦስት አሥረኛ ኢፍ 6.6 ሊትር ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።

አንድ ሎግ 0.31 ሊትር ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።

አንድ አሥረኛ ኢፍ 2.2 ሊትር ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።

ቃል በቃል “ከኃጢአት።”

ቃል በቃል “ከኃጢአት።”

ቃል በቃል “ከሥጋው።”

“የሚጠፋ ፍየል” የሚል ትርጉም ሊኖረው ይችላል።

ወይም “ዝግጁ ሆኖ በቆመው።”

ወይም “ነፍሳችሁን አጎሳቁሉ።” “ራስን ማጎሳቆል” በአብዛኛው መጾምን ጨምሮ የራስን ፍላጎት ከመፈጸም መቆጠብን የሚያሳዩ የተለያዩ ድርጊቶችን ሊያመለክት ይችላል።

ወይም “ነፍሳችሁን።”

ቃል በቃል “እጁ የሚሞላው።”

ወይም “የሚያረጋጋ፤ የሚያበርድ።” ቃል በቃል “እረፍት የሚሰጥ።”

ቃል በቃል “ፍየሎች።”

ወይም “ነፍስ።”

ወይም “ነፍስ።”

ወይም “ለነፍሳችሁም።”

ወይም “ነፍስ።”

ወይም “ማንኛውም ነፍስ ደም መብላት የለበትም።”

ወይም “ነፍስ።”

ወይም “ነፍስ።”

ወይም “ነፍስ።”

ወይም “ነፍስ።”

ቃል በቃል “ይህ የአባትህ እርቃን ነው።”

ቃል በቃል “የአባትህን ወንድም እርቃን አትግለጥ።”

ቃል በቃል “ይህ የወንድምህ እርቃን ነው።”

ወይም “አሳፋሪ ምግባር፤ ሴሰኝነት።”

ወይም “ከጎረቤትህ።”

ወይም “መሥዋዕት እንዲሆን።”

ወይም “ነፍስ።”

ቃል በቃል “ይፍራ።”

ወይም “ነፍስ።”

ወይም “ለጎስቋላውና።”

ቃል በቃል “ደም።”

“የባልንጀራህ ሕይወት ለአደጋ ሲጋለጥ ዝም ብለህ አትመልከት” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ቃል በቃል “እንደ ፍሬው ሸለፈት።”

ቃል በቃል “ለእናንተ እንዳልተገረዘ ይሆናል።”

ወይም “አትከርክሙ፤ አትቁረጡ።”

ወይም “ነፍስ።” እዚህ ቦታ ላይ የገባው ነፈሽ የሚለው የዕብራይስጥ ቃል የሞተን ሰው የሚያመለክት ነው።

ወይም “አድናቆት።” ቃል በቃል “ፍርሃት።”

ቃል በቃል “ትክክለኛ ኢፍና።” ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።

ቃል በቃል “ትክክለኛ ሂን።” ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።

ወይም “ነፍስ።”

ወይም “ነፍስ።”

ቃል በቃል “የአባቱን እርቃን ገልጧል።”

ወይም “አሳፋሪ ምግባር፤ ሴሰኝነት።”

ቃል በቃል “የእህቱን እርቃን ገልጧል።”

ቃል በቃል “የአጎቱን እርቃን ገልጧል።”

ቃል በቃል “የወንድሙን እርቃን ገልጧል።”

ወይም “ነፍሳችሁን።”

ወይም “ነፍስ።”

ካህናት ሬሳ ከነኩ ወይም በሞተው ሰው የሐዘን ሥርዓት ላይ ከተካፈሉ ራሳቸውን ያረክሳሉ።

መሥዋዕቶችን ያመለክታል።

ቃል በቃል “እጁ የተሞላው።”

ወይም “ወደ ሞተ ነፍስ።” እዚህ ቦታ ላይ የገባው ነፈሽ የሚለው የዕብራይስጥ ቃል “ሙት” የሚል ትርጉም ካለው የዕብራይስጥ ቃል ጋር ተያያዥነት አለው።

ቃል በቃል “አፍንጫው የተሰነጠቀ።”

“የመነመነ” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ቃል በቃል “እስራኤላውያን ከሚያመጧቸው ቅዱስ ነገሮች ራሳቸውን እንዲለዩና።”

ወይም “ነፍስ።”

ወይም “ነፍስ።”

ወይም “ነፍስ።”

ቃል በቃል “ባዕድ ሰው።” ከአሮን ወገን ያልሆነን ሰው ያመለክታል።

ወይም “ነፍስ።”

ወይም “ባዕድ ሰው ብታገባ።”

ቃል በቃል “ባዕድ ሰው።” ከአሮን ወገን ያልሆነን ሰው ያመለክታል።

ቃል በቃል “በሁለቱ ምሽቶች መካከል።”

ወይም “የማለፍ በዓል።” የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

ሁለት አሥረኛ ኢፍ 4.4 ሊትር ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።

ወይም “የሚያረጋጋ፤ የሚያበርድ።” ቃል በቃል “እረፍት የሚሰጥ።”

አንድ ሂን 3.67 ሊትር ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።

ሁለት አሥረኛ ኢፍ 4.4 ሊትር ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።

ወይም “የሚያረጋጋ፤ የሚያበርድ።” ቃል በቃል “እረፍት የሚሰጥ።”

ወይም “ለተጎሳቆለውና።”

ወይም “ነፍሳችሁን አጎሳቁሉ።” “ራስን ማጎሳቆል” በአብዛኛው መጾምን ጨምሮ የራስን ፍላጎት ከመፈጸም መቆጠብን የሚያሳዩ የተለያዩ ድርጊቶችን ሊያመለክት ይችላል።

“የማይጾም” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ወይም “ነፍስ።”

ወይም “ነፍስ።”

ወይም “ነፍሳችሁን።”

ወይም “የጊዜያዊ መጠለያ።”

ወይም “በደረቅ ወንዝ።”

ሁለት አሥረኛ ኢፍ 4.4 ሊትር ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።

ዘሌ 24:15 እና 16 እንደሚጠቁሙት ይሖዋ የሚለውን ስም ያመለክታል።

ወይም “የማንኛውንም ሰው ነፍስ መትቶ ከገደለ።”

ወይም “የቤት እንስሳን ነፍስ መትቶ የገደለ።”

ወይም “ነፍስ ስለ ነፍስ።”

ሰብል በሚሰበሰብበት ጊዜ ማሳው ላይ ረግፎ እንደገና የሚበቅለውን እህል ያመለክታል።

ወይም “አራጣ።”

ቃል በቃል “ወንዶች ልጆቹ።”

ወይም “የሥጋ ዘመዱ።”

ቃል በቃል “ወንዶች ልጆቹ።”

ወይም “አድናቆት።” ቃል በቃል “ፍርሃት።”

ቃል በቃል “ወደ እናንተ ዞር እላለሁ።”

ወይም “ነፍሴም አትተዋችሁም።”

ቃል በቃል “ቀጥ ብላችሁ።”

ወይም “ነፍሳችሁ ትእዛዛቴን በሙሉ ላለመፈጸም ድንጋጌዎቼን የምትጸየፍ።”

ወይም “ነፍሳችሁ።”

ቃል በቃል “የዳቦ በትሮቻችሁን በምሰብርበት ጊዜ።” ዳቦ ለማስቀመጥ የሚያገለግሉ በትሮችን የሚያመለክት ሳይሆን አይቀርም።

እዚህ ላይ የገባው የዕብራይስጥ ቃል “ፋንድያ” ከሚለው ቃል ጋር ዝምድና ሊኖረው የሚችል ሲሆን ንቀትን ለማመልከት ተሠርቶበታል።

ወይም “ነፍሴ ተጸይፋችሁ ከእናንተ ዞር ትላለች።”

ወይም “የሚያረጋጋ፤ የሚያበርድ።” ቃል በቃል “እረፍት የሚሰጥ።”

ወይም “ሰንበትን ታከብራለች።”

ወይም “ግትር የሆነው።”

ወይም “ነፍሳቸው ደንቦቼን ስለተጸየፈች።”

ወይም “ነፍስ።”

ወይም “በቅዱሱ ሰቅል።”

አንድ ሰቅል 11.4 ግራም ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።

አንድ ሆሜር 220 ሊትር ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።

አንድ ጌራ 0.57 ግራም ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።

ወይም “አሥራት።”

ወይም “ራስ።”

    የኢትዮጵያ ምልክት ቋንቋ ጽሑፎች (2011-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • የኢትዮጵያ ምልክት ቋንቋ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ