የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
የኢትዮጵያ ምልክት ቋንቋ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • nwt ኢዮብ 1:1-42:17
  • ኢዮብ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ኢዮብ
  • አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ
አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ
ኢዮብ

ኢዮብ

1 በዑጽ ምድር የሚኖር ኢዮብ*+ የሚባል ሰው ነበር። እሱም በንጹሕ አቋም የሚመላለስ ቅን ሰው*+ እንዲሁም አምላክን የሚፈራና ከክፋት የራቀ ነበር።+ 2 ኢዮብ ሰባት ወንዶች ልጆችና ሦስት ሴቶች ልጆች ነበሩት። 3 የከብቶቹም ብዛት 7,000 በጎች፣ 3,000 ግመሎች፣ 1,000 ከብቶች፣* 500 አህዮች* ነበር፤ በተጨማሪም እጅግ ብዙ አገልጋዮች ስለነበሩት በምሥራቅ ካሉት ሰዎች ሁሉ ይበልጥ ታላቅ ሰው ሆነ።

4 ወንዶች ልጆቹ ሁሉ በተመደበላቸው ተራ መሠረት በየቤታቸው* ግብዣ ያደርጉ ነበር። እነሱም ሦስቱ እህቶቻቸው አብረዋቸው እንዲበሉና እንዲጠጡ ይጋብዟቸው ነበር። 5 ሁሉም ተራው ደርሷቸው የግብዣዎቹ ቀናት ከተጠናቀቁ በኋላ ኢዮብ ልጆቹ ይቀደሱ ዘንድ መልእክት ይልክባቸው ነበር። ከዚያም “ልጆቼ ኃጢአት ሠርተውና አምላክን በልባቸው ረግመው ይሆናል” ብሎ በማሰብ በማለዳ ተነስቶ ለእያንዳንዳቸው የሚቃጠል መሥዋዕት ያቀርብ ነበር።+ ኢዮብ ሁልጊዜ እንዲህ የማድረግ ልማድ ነበረው።+

6 የእውነተኛው አምላክ ልጆች*+ በይሖዋ ፊት ለመቆም+ የሚገቡበት ቀን በደረሰ ጊዜ ሰይጣንም+ መጥቶ በመካከላቸው ቆመ።+

7 ከዚያም ይሖዋ ሰይጣንን “ከየት መጣህ?” አለው። ሰይጣንም “በምድር ሁሉ ላይ ስዞርና በእሷ ላይ ስመላለስ ቆይቼ መጣሁ”+ ሲል ለይሖዋ መለሰ። 8 ይሖዋም ሰይጣንን እንዲህ አለው፦ “አገልጋዬን ኢዮብን ተመለከትከው?* በምድር ላይ እንደ እሱ ያለ ሰው የለም። በንጹሕ አቋም* የሚመላለስ ቅን ሰው+ እንዲሁም አምላክን የሚፈራና ከክፋት የራቀ ነው።” 9 ሰይጣንም ለይሖዋ እንዲህ ሲል መለሰ፦ “ኢዮብ አምላክን የሚፈራው እንዲያው በከንቱ ነው?+ 10 እሱን፣ ቤቱንና ያለውን ነገር ሁሉ በአጥር ከልለህ የለም?+ የእጁን ሥራ ባርከህለታል፤+ ከብቱም በምድሪቱ ላይ በዝቷል። 11 ሆኖም እስቲ እጅህን ዘርግተህ ያለውን ሁሉ አጥፋ፤ በእርግጥ ፊት ለፊት ይረግምሃል።” 12 ከዚያም ይሖዋ ሰይጣንን “እነሆ፣ ያለው ነገር ሁሉ በእጅህ* ነው። እሱን ራሱን ግን እንዳትነካው!” አለው። ሰይጣንም ከይሖዋ ፊት ወጥቶ ሄደ።+

13 የኢዮብ ወንዶችና ሴቶች ልጆች በታላቅ ወንድማቸው ቤት እየበሉና የወይን ጠጅ እየጠጡ በነበረበት ቀን፣+ 14 አንድ መልእክተኛ ወደ ኢዮብ መጥቶ እንዲህ አለው፦ “ከብቶቹ እያረሱ፣ አህዮቹም በአጠገባቸው እየጋጡ ሳለ 15 ሳባውያን ጥቃት ሰንዝረው ወሰዷቸው፤ አገልጋዮቹንም በሰይፍ ገደሉ። እኔም ብቻዬን አምልጬ ልነግርህ መጣሁ።”

16 እሱ ገና እየተናገረ ሳለ ሌላው መጥቶ እንዲህ አለ፦ “ከአምላክ ዘንድ ከሰማያት እሳት ወረደች፤* በበጎቹና በአገልጋዮቹ መካከልም ነድዳ በላቻቸው! እኔም ብቻዬን አምልጬ ልነግርህ መጣሁ።”

17 እሱ ገና እየተናገረ ሳለ ሌላው መጥቶ እንዲህ አለ፦ “ከለዳውያን+ በሦስት ቡድን መጥተው በድንገት ጥቃት በመሰንዘር ግመሎቹን ወሰዱ፤ አገልጋዮቹንም በሰይፍ ገደሉ። እኔም ብቻዬን አምልጬ ልነግርህ መጣሁ።”

18 እሱ ገና እየተናገረ ሳለ ሌላው ደግሞ መጥቶ እንዲህ አለ፦ “ወንዶችና ሴቶች ልጆችህ በታላቅ ወንድማቸው ቤት እየበሉና የወይን ጠጅ እየጠጡ ነበር። 19 በድንገት ከምድረ በዳው ኃይለኛ ነፋስ መጥቶ የቤቱን አራት ማዕዘናት መታ፤ ቤቱም በልጆችህ ላይ ወድቆ ገደላቸው። እኔም ብቻዬን አምልጬ ልነግርህ መጣሁ።”

20 በዚህ ጊዜ ኢዮብ ተነስቶ ልብሱን ቀደደ፤ ፀጉሩንም ተላጨ፤ ከዚያም መሬት ላይ ተደፍቶ ሰገደ፤ 21 እንዲህም አለ፦

“ከእናቴ ማህፀን ራቁቴን ወጣሁ፤

ራቁቴንም ወደዚያ እመለሳለሁ።+

ይሖዋ ሰጠ፤+ ይሖዋ ነሳ።

የይሖዋ ስም ምንጊዜም ይወደስ።”

22 ኢዮብ ይህ ሁሉ ቢደርስበትም ኃጢአት አልሠራም ወይም አምላክን በደል ሠርቷል ብሎ አልወነጀለም።*

2 የእውነተኛው አምላክ ልጆች፣*+ በይሖዋ ፊት ለመቆም+ የሚገቡበት ቀን በደረሰ ጊዜ ሰይጣንም በይሖዋ ፊት ለመቆም እነሱ መካከል ገባ።+

2 ከዚያም ይሖዋ ሰይጣንን “ከየት መጣህ?” አለው። ሰይጣንም “በምድር ሁሉ ላይ ስዞርና በእሷ ላይ ስመላለስ ቆይቼ መጣሁ”+ ሲል ለይሖዋ መለሰ። 3 ይሖዋም ሰይጣንን እንዲህ አለው፦ “አገልጋዬን ኢዮብን ተመለከትከው?* በምድር ላይ እንደ እሱ ያለ ሰው የለም። በንጹሕ አቋም የሚመላለስ ቅን ሰው*+ እንዲሁም አምላክን የሚፈራና ከክፋት የራቀ ነው። ያለምንም ምክንያት እንዳጠፋው* እኔን ለማነሳሳት ብትሞክርም+ እንኳ አሁንም በንጹሕ አቋሙ እንደጸና ነው።”+ 4 ሆኖም ሰይጣን እንዲህ ሲል ለይሖዋ መለሰ፦ “ቁርበት ስለ ቁርበት ነው። ሰውም ለሕይወቱ* ሲል ያለውን ነገር ሁሉ ይሰጣል። 5 ሆኖም እስቲ እጅህን ዘርግተህ በአጥንቱና በሥጋው ላይ ጉዳት አድርስበት፤ በእርግጥ ፊት ለፊት ይረግምሃል።”+

6 ከዚያም ይሖዋ ሰይጣንን “እነሆ፣ እሱ በእጅህ* ነው! ብቻ ሕይወቱን* እንዳታጠፋ!” አለው። 7 ሰይጣንም ከይሖዋ ፊት ወጥቶ በመሄድ ኢዮብን ከእግር ጥፍሩ እስከ ራስ ፀጉሩ ድረስ ክፉኛ በሚያሠቃይ እባጭ መታው።*+ 8 ኢዮብም ገላውን የሚያክበት ገል ወሰደ፤ በአመድም ላይ ተቀመጠ።+

9 በመጨረሻም ሚስቱ “አሁንም በንጹሕ አቋምህ* እንደጸናህ ነው? አምላክን እርገምና ሙት!” አለችው። 10 እሱ ግን እንዲህ አላት፦ “የምትናገሪው ማመዛዘን እንደጎደላት ሴት ነው። ከእውነተኛው አምላክ መቀበል ያለብን መልካም ነገር ብቻ ነው? ክፉውንስ መቀበል የለብንም?”+ ኢዮብ ይህ ሁሉ ቢደርስበትም በከንፈሩ አልበደለም።+

11 የኢዮብ ሦስት ጓደኞች* በእሱ ላይ የደረሰውን መከራ ሁሉ ሰምተው እያንዳንዳቸው ከሚኖሩበት ቦታ መጡ፤ ጓደኞቹም ቴማናዊው ኤሊፋዝ፣+ ሹሃዊው+ በልዳዶስ+ እና ናአማታዊው ሶፋር+ ነበሩ። እነሱም አንድ ላይ ተገናኝተው ወደ ኢዮብ በመሄድ እሱን ለማስተዛዘንና ለማጽናናት ተስማሙ። 12 ከሩቅ ሲመለከቱት እሱ መሆኑን መለየት አቃታቸው። እነሱም ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ማልቀስ ጀመሩ፤ ልብሳቸውንም ቀደዱ፤ እንዲሁም አቧራ ወደ ላይ በተኑ፤ ራሳቸውም ላይ ነሰነሱ።+ 13 ከዚያም ሰባት ቀንና ሰባት ሌሊት መሬት ላይ ከእሱ ጋር ተቀመጡ። ሥቃዩ በጣም ከባድ+ መሆኑን ስለተረዱ ከመካከላቸው አንድም ቃል የተናገረው አልነበረም።

3 ከዚህ በኋላ ኢዮብ መናገርና የተወለደበትን ቀን መርገም ጀመረ።+ 2 ኢዮብም እንዲህ አለ፦

 3 “የተወለድኩበት ቀን፣

‘ወንድ ልጅ ተፀነሰ!’ የተባለበትም ሌሊት ይጥፋ።+

 4 ያ ቀን ጨለማ ይሁን።

በላይ ያለው አምላክ አያስበው፤

ብርሃንም አይፈንጥቅበት።

 5 ድቅድቅ ጨለማ* ይውረሰው።

ጥቁር ደመና ይረፍበት።

ቀንን የሚያጨልም ነገር ያሸብረው።

 6 ያን ሌሊት ጨለማ ይውረሰው፤+

ከዓመቱ ቀኖች መካከል ያ ሌሊት ደስ አይበለው፤

ከወራቱም ቁጥር መካከል አይደመር።

 7 አዎ፣ ያ ሌሊት መሃን ይሁን!

እልልታም አይሰማበት።

 8 ቀንን የሚረግሙ፣

ሌዋታንንም*+ መቀስቀስ የሚችሉ ቀኑን ይርገሙት።

 9 አጥቢያ ኮከቦቹ ይጨልሙ፤

የቀን ብርሃንን ቢጠብቅም አያግኝ፤

የንጋትንም ጮራ አይመልከት።

10 የእናቴን ማህፀን በሮች አልዘጋምና፤+

ችግርንም ከዓይኔ አልሰወረም።

11 ምነው ስወለድ በሞትኩ!

ምነው ከማህፀን ስወጣ በተቀጨሁ!+

12 የሚቀበሉኝ ጉልበቶች፣

የሚያጠቡኝም ጡቶች ለምን ተገኙ?

13 ይህን ጊዜ ሳልረበሽ በተጋደምኩ ነበርና፤+

በተኛሁና እረፍት ባገኘሁ ነበር፤+

14 በአሁኑ ጊዜ ፈራርሰው ያሉ ቦታዎችን ለራሳቸው ከገነቡ*

የምድር ነገሥታትና አማካሪዎቻቸው ጋር፣

15 ወይም ቤታቸውን በብር ከሞሉ

ወርቅ ካላቸው መኳንንት ጋር ባረፍኩ ነበር።

16 እንደተሰወረ ጭንጋፍ፣

ፈጽሞ ብርሃን እንዳላዩ ልጆች ለምን አልሆንኩም?

17 በዚያ ክፉዎች እንኳ ከሚረብሽ ነገር ተገላግለዋል፤

የዛሉ ሰዎች በዚያ አርፈዋል።+

18 በዚያ እስረኞች በአንድነት ተረጋግተው ይኖራሉ፤

አስገድዶ የሚያሠራቸውን ሰው ድምፅ አይሰሙም።

19 በዚያ ትንሹም ሆነ ትልቁ አንድ ናቸው፤+

ባሪያውም ከጌታው ነፃ ወጥቷል።

20 እሱ መከራ ላይ ላለ ሰው ብርሃን፣

ለተመረሩ ሰዎችስ* ሕይወት ለምን ይሰጣል?+

21 ሞትን ቢመኙም የማያገኙት ለምንድን ነው?+

ከተሰወረ ሀብት ይበልጥ ይሹታል፤

22 መቃብር ሲያገኙ ሐሴት ያደርጋሉ፤

እጅግም ደስ ይላቸዋል።

23 መንገዱ ለጠፋበት፣

አምላክም ዙሪያውን ላጠረበት ሰው+ ለምን ብርሃን ይሰጣል?

24 በምግቤ ፋንታ ሲቃ ተናንቆኛልና፤+

የሥቃይ ጩኸቴ+ እንደ ውኃ ይፈስሳል።

25 የፈራሁት ነገር መጥቶብኛልና፤

ያሸበረኝም ነገር ደርሶብኛል።

26 ሰላምም ሆነ እርጋታ አላገኘሁም፤ እረፍትም አልነበረኝም፤

ይልቁንም መከራ አልተለየኝም።”

4 ከዚያም ቴማናዊው ኤሊፋዝ+ እንዲህ ሲል መለሰ፦

 2 “አንድ ሰው ሊያናግርህ ቢሞክር ትዕግሥት ታጣለህ?

ደግሞስ ማን ከመናገር ሊቆጠብ ይችላል?

 3 እርግጥ ነው፣ አንተ ብዙዎችን ታርም ነበር፤

የደከሙትንም እጆች ታበረታ ነበር።

 4 ቃልህ የተሰናከለውን ሁሉ ያነሳ ነበር፤

አንተም የሚብረከረኩትን ጉልበቶች ታጸና ነበር።

 5 አሁን ግን በአንተ ላይ ሲደርስ ዛልክ፤

በአንተ ላይ ሲመጣ ተደናገጥክ።

 6 ለአምላክ ያለህ አክብሮት* መተማመኛህ አይደለም?

ንጹሕ አቋምህን* ጠብቀህ መመላለስህ+ ተስፋ አልሰጠህም?

 7 እስቲ ለማስታወስ ሞክር፦ ንጹሕ ከሆኑ ሰዎች መካከል የጠፋ ማን አለ?

ቅኖችስ መቼ ተደምስሰው ያውቃሉ?

 8 እኔ እንዳየሁት ክፉ ነገርን የሚያርሱ፣*

መከራንም የሚዘሩ ያንኑ ያጭዳሉ።

 9 በአምላክ እስትንፋስ ይጠፋሉ፤

በቁጣውም ወላፈን ይደመሰሳሉ።

10 አንበሳ ሊያገሳ፣ የአንበሳም ግልገል ሊያጉረመርም ይችላል፤

ይሁን እንጂ የብርቱ አንበሶች* ጥርስም እንኳ ይሰበራል።

11 አንበሳ የሚታደን ሲያጣ ይጠፋል፤

የአንበሳም ግልገሎች ይበተናሉ።

12 ቃል በስውር መጣልኝ፤

ሹክሹክታውም ወደ ጆሮዬ ደረሰ።

13 ይህም የሆነው ሌሊት ያየሁት ራእይ ባስጨነቀኝ ወቅት፣

ሰዎችም ጭልጥ ያለ እንቅልፍ በወሰዳቸው ጊዜ ነበር፤

14 በጣም ተንቀጠቀጥኩ፤

አጥንቶቼም ሁሉ በፍርሃት ተዋጡ።

15 መንፈስም በፊቴ አለፈ፤

የገላዬም ፀጉር ቆመ።

16 እሱም ባለበት ቆመ፤

ሆኖም መልኩን መለየት አልቻልኩም።

አንድ ቅርጽ በዓይኔ ፊት ነበር፤

ጸጥታም ሰፍኖ ነበር፤ ከዚያም አንድ ድምፅ ሰማሁ፦

17 ‘ሟች የሆነ ሰው ከአምላክ ይልቅ ጻድቅ ሊሆን ይችላል?

ሰውስ ከገዛ ሠሪው ይበልጥ ንጹሕ ሊሆን ይችላል?’

18 እነሆ፣ በአገልጋዮቹ ላይ እምነት የለውም፤

በመላእክቱም* ላይ ስህተት ያገኛል።

19 በጭቃ ቤቶች የሚኖሩ፣

መሠረታቸው አፈር ውስጥ የሆነ፣+

እንደ ብል በቀላሉ የሚጨፈለቁማ ሁኔታቸው ምንኛ የከፋ ይሆን!

20 ከጠዋት እስከ ማታ ባለው ጊዜ ውስጥ ሙሉ በሙሉ ይደቅቃሉ፤

ለዘላለም ይጠፋሉ፤ ደግሞም ማንም ልብ አይላቸውም።

21 ገመዱ እንደተፈታበት ድንኳን አይደሉም?

ያለጥበብ ይሞታሉ።

5 “እስቲ ተጣራ! የሚመልስልህ ይኖራል?

ከቅዱሳንስ* መካከል ወደ የትኛው ዞር ትላለህ?

 2 ሞኝን ሰው ብስጭት ይገድለዋልና፤

ማስተዋል የጎደለውንም ቅናት ይገድለዋል።

 3 ሞኝ ሰው ሥር ሰዶ አየሁት፤

ይሁንና የመኖሪያ ስፍራው በድንገት ተረገመ።

 4 ወንዶች ልጆቹ ደህንነት ርቋቸዋል፤

በከተማው በር ተረግጠዋል፤+ የሚያድናቸውም የለም።

 5 እሱ የሰበሰበውን፣ የራበው ሰው ይበላዋል፤

ከእሾህም መካከል ይወስድበታል፤

ደግሞም ንብረታቸው በወጥመድ ተይዟል።

 6 ጎጂ የሆነ ነገር ከአፈር አይበቅልምና፤

ችግርም ከመሬት አይፈልቅም።

 7 የእሳት ፍንጣሪ ወደ ላይ እንደሚወረወር፣

ሰው የሚወለደው ለችግር ነው።

 8 እኔ ብሆን ኖሮ አምላክን እለምን ነበር፤

ጉዳዬንም ለአምላክ አቀርብ ነበር፤

 9 እሱ ታላላቅና የማይመረመሩ ነገሮችን ያደርጋል፤

ስፍር ቁጥር የሌላቸውን ድንቅ ነገሮች ይሠራል።

10 በምድር ላይ ዝናብ ያዘንባል፤

በሜዳዎችም ላይ ውኃ ይልካል።

11 ችግረኞችን ከፍ ያደርጋል፤

እንዲሁም ያዘነውን ሰው መዳን እንዲያገኝ ከፍ ከፍ ያደርገዋል።

12 የብልጣ ብልጦችን ዕቅድ ያከሽፋል፤

ስለዚህ የእጃቸው ሥራ አይሰምርም።

13 ጥበበኞችን በራሳቸው ተንኮል ይይዛቸዋል፤+

ስለሆነም የጮሌዎች ዕቅድ ይከሽፋል።

14 ቀኑ ጨለማ ይሆንባቸዋል፤

ሌሊት የሆነ ይመስል እኩለ ቀን ላይ በዳበሳ ይሄዳሉ።

15 ከአፋቸው ሰይፍ ያድናል፤

ድሃውንም ከብርቱው እጅ ይታደጋል፤

16 በመሆኑም ችግረኛው ተስፋ ይኖረዋል፤

የክፋት አፍ ግን ይዘጋል።

17 እነሆ፣ አምላክ የሚወቅሰው ሰው ደስተኛ ነው፤

ስለዚህ ሁሉን ቻይ የሆነውን አምላክ ተግሣጽ አትናቅ!

18 እሱ ሥቃይ ያመጣልና፤ ሆኖም ቁስሉን ይጠግናል፤

እሱ ይሰብራል፤ ይሁንና በገዛ እጆቹ ይፈውሳል።

19 ከስድስት መቅሰፍቶች ያድንሃል፤

ሰባተኛውም አይጎዳህም።

20 በረሃብ ወቅት ከሞት ይዋጅሃል፤

በጦርነትም ጊዜ ከሰይፍ ኃይል ይታደግሃል።

21 ከምላስ ጅራፍ ትጠበቃለህ፤+

ጥፋት ሲመጣም አትፈራም።

22 በጥፋትና በረሃብ ላይ ትስቃለህ፤

የምድርንም አራዊት አትፈራም።

23 በሜዳ ያሉ ድንጋዮች አይጎዱህም፤*

የዱር አራዊትም ከአንተ ጋር ሰላም ይኖራቸዋል።

24 በድንኳንህ ውስጥ አስተማማኝ ሁኔታ* እንደሚሰፍን ታውቃለህ፤

የግጦሽ መሬትህን ስትቃኝም አንዳች ነገር አይጎድልብህም።

25 ብዙ ልጆች ይኖሩሃል፤

ዘሮችህም በምድር ላይ እንደሚበቅል ሣር ይበዛሉ።

26 በወቅቱ እንደተሰበሰበ የእህል ነዶ፣

ብርቱ እንደሆንክ ወደ መቃብር ትወርዳለህ።

27 እነሆ፣ ይህን መርምረናል፤ እውነት መሆኑንም አረጋግጠናል።

ይህን ስማ፤ ደግሞም ተቀበል።”

6 ከዚያም ኢዮብ እንዲህ ሲል መለሰ፦

 2 “ምነው ሥቃዬ ሁሉ+ በተመዘነ ኖሮ!

ከመከራዬም ጋር ሚዛን ላይ በተቀመጠ ኖሮ!

 3 ከባሕር አሸዋ ይልቅ ከባድ ሆኖብኛልና።

ከዚህም የተነሳ እንዳመጣልኝ* እናገራለሁ።+

 4 ሁሉን የሚችለው አምላክ ፍላጻዎች ወግተውኛልና፤

መንፈሴም መርዛቸውን እየጠጣ ነው፤+

ከአምላክ የመጣ ሽብር በእኔ ላይ ተሰልፏል።

 5 የዱር አህያ+ ሣር እያለው ያናፋል?

በሬስ ገፈራ እያለው ይጮኻል?

 6 ጣዕም የሌለው ምግብ ያለጨው ይበላል?

ወይስ የልት* ፈሳሽ ጣዕም ይኖረዋል?

 7 እንዲህ ያሉ ነገሮችን መንካት ተጸይፌአለሁ።*

በምግቤ ውስጥ እንዳሉ የሚበክሉ ነገሮች ናቸው።*

 8 ምነው ጥያቄዬ መልስ ባገኘ!

አምላክም ፍላጎቴን በፈጸመልኝ!

 9 ምነው አምላክ እኔን ለማድቀቅ በፈቀደ!

እጁንም ዘርግቶ ባጠፋኝ!+

10 ይህም እንኳ ባጽናናኝ ነበርና፤

ፋታ የማይሰጥ ሥቃይ ቢኖርብኝም በደስታ እዘላለሁ፤

የቅዱሱን አምላክ ቃል አልካድኩምና።+

11 ከዚህ በላይ መታገሥ የምችልበት ምን አቅም አለኝ?+

በሕይወት መኖሬን ብቀጥልስ* ምን አገኛለሁ?

12 እኔ የዓለት ዓይነት ጥንካሬ አለኝ?

ወይስ ሥጋዬ ከመዳብ የተሠራ ነው?

13 ራሴን የምደግፍበት ነገር ሁሉ ከእኔ ርቆ ሳለ፣

ራሴን መርዳት የምችልበት መንገድ ይኖራል?

14 ለገዛ ወዳጁ ታማኝ ፍቅር የማያሳይ ሰው፣+

ሁሉን ቻይ የሆነውን አምላክ መፍራት ይተዋል።+

15 የገዛ ወንድሞቼ እንደ ክረምት ጅረት፣

እንደሚደርቅ የክረምት የጅረት ውኃ ከዳተኞች ሆኑብኝ።+

16 ከበረዶ የተነሳ ደፈረሱ፤

የሚቀልጥ አመዳይም በእነሱ ውስጥ ተሰውሯል።

17 ሆኖም ወቅቱ ሲደርስ ውኃ አልባ ይሆናሉ፤ ደግሞም ደብዛቸው ይጠፋል፤

በሙቀትም ጊዜ ይደርቃሉ።

18 የሚሄዱበት መንገድ ይቀየራል፤

ወደ በረሃ ፈስሰው ይጠፋሉ።

19 የቴማ+ ነጋዴዎች ይፈልጓቸዋል፤

የሳባም+ መንገደኞች* እነሱን ይጠባበቃሉ።

20 የተሳሳተ እምነት አድሮባቸው ስለነበር ለኀፍረት ተዳረጉ፤

ወደዚያ ቢሄዱም የጠበቁትን ባለማግኘታቸው አዘኑ።

21 እናንተም እንደዚሁ ሆናችሁብኛል፤+

መከራዬ ያስከተለውን ሽብር አይታችሁ በፍርሃት ተዋጣችሁ።+

22 ለመሆኑ እኔ ‘አንድ ነገር ስጡኝ’ ብያለሁ?

ወይስ ካፈራችሁት ሀብት ላይ ስጦታ እንድትሰጡኝ ጠይቄአለሁ?

23 ከጠላት እጅ እንድትታደጉኝ፣

ወይም ከጨቋኞች እንድታድኑኝ* ጠይቄአለሁ?

24 አስተምሩኝ፤ እኔም ዝም እላለሁ፤+

የሠራሁትን ስህተት እንዳስተውል እርዱኝ።

25 በሐቀኝነት የተነገረ ቃል አያቆስልም!+

የእናንተ ወቀሳ ግን ጥቅሙ ምንድን ነው?+

26 እኔ የምናገረውን ቃል፣

ነፋስ ጠራርጎ የሚወስደውን፣ ተስፋ የቆረጠ ሰው ንግግር+ ለማረም ታስባላችሁ?

27 ወላጅ አልባ በሆነውም ልጅ ላይ ዕጣ ትጣጣላላችሁ፤+

ወዳጃችሁንም ትሸጣላችሁ!*+

28 እስቲ አሁን ዞር ብላችሁ ተመልከቱኝ፤

በፊታችሁ አልዋሽም።

29 እባካችሁ፣ ቆም ብላችሁ አስቡበት፤ በተሳሳተ መንገድ አትረዱኝ፤

አዎ፣ ቆም ብላችሁ አስቡበት፤ ጽድቄ እንዳለ ነውና።

30 ምላሴ አግባብ ያልሆነ ነገር ይናገራል?

ላንቃዬስ የሆነ ችግር እንዳለ መለየት አይችልም?

7 “በምድር ላይ ያለ ሟች የሆነ ሰው ሕይወት፣ እንደ ግዳጅ አገልግሎት አይደለም?

የሕይወት ዘመኑስ እንደ ቅጥር ሠራተኛ ዘመን አይደለም?+

 2 እንደ ባሪያ፣ ጥላ ለማግኘት ይመኛል፤

እንደ ቅጥር ሠራተኛም ደሞዙን ለመቀበል በጉጉት ይጠባበቃል።+

 3 እኔም ከንቱ የሆኑ ወራት ተመድበውልኛል፤

በሥቃይ የተሞሉ ሌሊቶችም ተወስነውልኛል።+

 4 በተኛሁ ጊዜ ‘የምነሳው መቼ ነው?’ እላለሁ።+

ሌሊቱም ሲረዝም ጎህ እስኪቀድ* ድረስ ያለእረፍት እገላበጣለሁ።

 5 ሥጋዬ ትልና የአፈር ጓል ለብሷል፤+

ቆዳዬ በሙሉ አፈክፍኳል፤ ደግሞም መግል ይዟል።+

 6 ዘመኔ ከሸማኔ መወርወሪያ ይበልጥ በፍጥነት ያልፋል፤+

ያላንዳች ተስፋም ወደ ፍጻሜ ይደርሳል።+

 7 ሕይወቴ ነፋስ እንደሆነ፣+

ዓይኔም ዳግመኛ ደስታ* እንደማያይ አስታውስ።

 8 አሁን የሚያየኝ ዓይን ከእንግዲህ አያየኝም፤

ዓይኖችህ እኔን ይፈልጋሉ፤ እኔ ግን አልኖርም።+

 9 እንደሚበተንና እንደሚጠፋ ደመና፣

ወደ መቃብር* የሚወርድም ተመልሶ አይወጣም።+

10 ዳግመኛ ወደ ቤቱ አይመለስም፤

ስፍራውም ከእንግዲህ ወዲህ አያውቀውም።+

11 ስለዚህ እኔ ከመናገር ወደኋላ አልልም።

ከመንፈሴ ጭንቀት የተነሳ እናገራለሁ፤

በከባድ ምሬት* እሮሮ አሰማለሁ!+

12 በእኔ ላይ ጠባቂ የምታቆመው፣

እኔ ባሕር ነኝ ወይስ ግዙፍ የባሕር ፍጥረት?

13 ‘መኝታዬ ያጽናናኛል፣

አልጋዬ ሥቃዬን ያቀልልኛል’ ባልኩ ጊዜ፣

14 አንተ በሕልም ታሸብረኛለህ፤

በራእይም ታስፈራራኛለህ፤

15 ስለዚህ እኔ* መታፈንን፣

አዎ፣ ከሰውነቴም* ይልቅ ሞትን መረጥኩ።+

16 ሕይወቴን ተጸየፍኳት፤+ በሕይወት መቀጠል አልፈልግም።

ዘመኔ እንደ እስትንፋስ+ ስለሆነ ተወት አድርገኝ።

17 ታስበው ዘንድ፣

ትኩረት ትሰጠውም* ዘንድ ሟች የሆነ ሰው ምንድን ነው?+

18 በየማለዳው የምትመረምረው፣

በየጊዜውም የምትፈትነው ለምንድን ነው?+

19 ዓይንህን ከእኔ ላይ አታነሳም?

ምራቄን እስክውጥስ ድረስ ፋታ አትሰጠኝም?*+

20 የሰውን ልጅ የምትከታተል ሆይ፣+ ኃጢአት ብሠራ እንኳ አንተን እንዴት ልጎዳህ እችላለሁ?

ዒላማህ ያደረግከኝ ለምንድን ነው?

ሸክም ሆኜብሃለሁ?

21 መተላለፌን ይቅር የማትለው፣

በደሌንም በምሕረት የማታልፈው ለምንድን ነው?

ከጥቂት ጊዜ በኋላ አፈር ውስጥ እጋደማለሁና፤+

አንተም ትፈልገኛለህ፤ እኔ ግን አልገኝም።”

8 ከዚያም ሹሃዊው+ በልዳዶስ+ እንዲህ ሲል መለሰ፦

 2 “እንዲህ የምትናገረው እስከ መቼ ነው?+

ከአፍህ የሚወጣው ቃል ብርቱ ነፋስ ነው!

 3 አምላክ ፍትሕን ያዛባል?

ወይስ ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ጽድቅን ያጣምማል?

 4 ልጆችህ በእሱ ላይ ኃጢአት ሠርተው ከሆነ፣

ለፈጸሙት ዓመፅ እንዲቀጡ አድርጓል፤*

 5 አንተ ግን ወደ አምላክ ዞር ብትል፣+

ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ሞገስ እንዲያሳይህ ብትማጸን፣

 6 በእርግጥ ንጹሕና ቅን ብትሆን፣+

እሱ ትኩረት ይሰጥሃል፤*

ወደ ትክክለኛ ቦታህም ይመልስሃል።

 7 ጅማሬህ አነስተኛ ቢሆንም፣

የወደፊት ሕይወትህ ታላቅ ይሆናል።+

 8 እስቲ የቀድሞውን ትውልድ ጠይቅ፤

አባቶቻቸው ለተገነዘቧቸው ነገሮችም ትኩረት ስጥ።+

 9 እኛ የተወለድነው ገና ትናንት ስለሆነ የምናውቀው ነገር የለም፤

ምክንያቱም በምድር ላይ ዘመናችን እንደ ጥላ ነው።

10 እነሱ አያስተምሩህም?

ደግሞስ የሚያውቁትን ነገር* አይነግሩህም?

11 ደንገል ረግረጋማ ባልሆነ ስፍራ ያድጋል?

ሸምበቆስ ውኃ በሌለበት ቦታ ያድጋል?

12 ገና ሳያብብና ሳይቆረጥ፣

ከሌላው ተክል ሁሉ በፊት ይደርቃል።

13 አምላክን የሚረሱ ሰዎች ሁሉ መጨረሻቸው እንደዚህ ነው፤*

አምላክ የለሽ የሆነ* ሰው ተስፋ ይጨልማልና፤

14 የሚመካበት ነገር ከንቱ ነው፤

የሚታመንበትም ነገር ከሸረሪት ድር* የማይሻል ነው።

15 እሱ ቤቱን ይደገፈዋል፤ ሆኖም ቤቱ ጸንቶ አይቆምም፤

አጥብቆ ሊይዘው ይሞክራል፤ ሆኖም አይጸናም።

16 እሱ በፀሐይ ብርሃን እንደሚያድግ እርጥበት ያለው ተክል ነው፤

ቅርንጫፎቹም በአትክልት ስፍራው ውስጥ ይንሰራፋሉ።+

17 ሥሩም በድንጋይ ክምር ውስጥ ይጠላለፋል፤

በድንጋዮቹ መካከል ቤት ይፈልጋል።*

18 ሆኖም ከስፍራው በሚነቀልበት* ጊዜ፣

ያ ስፍራ ‘ፈጽሞ አይቼህ አላውቅም’ ብሎ ይክደዋል።+

19 አዎ፣ በዚህ ሁኔታ ይጠፋል፤*+

ከዚያም ሌሎች ከአፈሩ ውስጥ ይበቅላሉ።

20 በእርግጥም አምላክ ንጹሕ አቋማቸውን* የሚጠብቁትን አይጥልም፤

ክፉ ሰዎችንም አይረዳም፤*

21 በመጨረሻም አፍህን በሳቅ፣

ከንፈሮችህንም በእልልታ ይሞላል።

22 የሚጠሉህ ኀፍረት ይከናነባሉ፤

የክፉዎችም ድንኳን ይጠፋል።”

9 ኢዮብ እንዲህ ሲል መለሰ፦

 2 “እርግጥ ነገሩ እንዲህ መሆኑን አውቃለሁ።

ሆኖም ሟች የሆነ ሰው ከአምላክ ጋር ተሟግቶ እንዴት ትክክል ሊሆን ይችላል?+

 3 ሰው ከእሱ ጋር መሟገት ቢፈልግ፣*+

አምላክ ከሚያቀርብለት አንድ ሺህ ጥያቄዎች መካከል ለአንዱ እንኳ መልስ መስጠት አይችልም።

 4 እሱ ጥበበኛ ልብ አለው፤ ኃይሉም ታላቅ ነው።+

እሱን ተገዳድሮ ከጉዳት ማምለጥ የሚችል ማን ነው?+

 5 ማንም ሳያውቅ ተራሮችን ከስፍራቸው ይወስዳል፤*

በቁጣውም ይገለብጣቸዋል።

 6 ምድርን ከስፍራዋ ያናውጣታል፤

በመሆኑም ምሰሶዎቿ ይንቀጠቀጣሉ።+

 7 ብርሃን እንዳትፈነጥቅ ፀሐይን ያዛታል፤

የከዋክብትን ብርሃን ያሽጋል፤+

 8 ሰማያትንም ብቻውን ይዘረጋል፤+

ከፍ ባለው የባሕር ማዕበልም ላይ ይራመዳል።+

 9 የአሽ፣* የከሲልና* የኪማ ኅብረ ከዋክብትን*+

እንዲሁም የደቡቡን ሰማይ ኅብረ ከዋክብት* ሠርቷል፤

10 ታላላቅና የማይመረመሩ ነገሮችን፣

ስፍር ቁጥር የሌላቸውን ድንቅ ነገሮች ያደርጋል።+

11 በአጠገቤ ያልፋል፤ እኔ ግን ላየው አልችልም፤

አልፎኝ ይሄዳል፤ እኔ ግን አለየውም።

12 አንዳች ነገር ነጥቆ ሲወስድ ማን ሊከለክለው ይችላል?

‘ምን ማድረግህ ነው?’ ሊለው የሚችልስ ማን ነው?+

13 አምላክ ቁጣውን አይገታም፤+

የረዓብ*+ ረዳቶች እንኳ እግሩ ሥር ይወድቃሉ።

14 በመሆኑም ለእሱ መልስ ስሰጥ፣

ይልቁንም ከእሱ ጋር ስከራከር አስቤ መናገር ይጠበቅብኛል።

15 ትክክል ብሆን እንኳ መልስ አልሰጠውም።+

ዳኛዬን* ምሕረት ከመለመን ሌላ ምንም ማድረግ አልችልም።

16 ብጠራው ይመልስልኛል?

እኔ እንደሆነ፣ ስናገር ይሰማኛል የሚል እምነት የለኝም፤

17 በአውሎ ነፋስ ያደቀኛልና፤

ያለምክንያትም ቁስሌን ያበዛል።+

18 ለመተንፈስ እንኳ ፋታ አይሰጠኝም፤

መራራ ነገሮችን ያጠግበኛል።

19 የኃይል ጉዳይ ከሆነ እሱ ኃያል ነው።+

የፍትሕ ጉዳይ ከተነሳ ‘ማን ሊጠይቀኝ* ይችላል?’ ይላል።

20 ትክክል ብሆን እንኳ የገዛ አፌ ይፈርድብኛል፤

ንጹሕ አቋሜን ብጠብቅ እንኳ* እሱ ጥፋተኛ* ነህ ይለኛል።

21 ንጹሕ አቋሜን ብጠብቅ እንኳ* ስለ ራሴ እርግጠኛ አይደለሁም፤*

ይህን ሕይወቴን እጠላዋለሁ።*

22 ምንም ለውጥ የለውም። ‘እሱ ንጹሑንም* ሆነ ክፉውን ያጠፋል’

የምለው ለዚህ ነው።

23 ደራሽ ውኃ በድንገት ሰዎችን ቢያጠፋ፣

እሱ ንጹሐን ሰዎች በሚደርስባቸው ሥቃይ ያፌዛል።

24 ምድር ለክፉዎች ተሰጥታለች፤+

እሱ የዳኞቿን ዓይኖች* ይሸፍናል።

ይህን የሚያደርገው እሱ ካልሆነ ታዲያ ማን ነው?

25 ዘመኔ ከሚሮጥ ሰው ይልቅ ይፈጥናል፤+

መልካም ነገር ሳያይ ፈጥኖ ይነጉዳል።

26 ከደንገል እንደተሠሩ ጀልባዎች፣

የሚያድኑትንም ነገር ለመያዝ ወደ ታች እንደሚወረወሩ ንስሮች ይከንፋል።

27 ‘ብሶቴን እረሳለሁ፤

የፊቴን ገጽታ ቀይሬ ደስተኛ እሆናለሁ’ ብል እንኳ፣

28 ከሥቃዬ ሁሉ የተነሳ አሁንም ፍርሃት ይሰማኛል፤+

ንጹሕ ሆኜ እንደማታገኘኝ አውቃለሁ።

29 በደለኛ* ሆኜ መገኘቴ አይቀርም።

ታዲያ ለምን በከንቱ እደክማለሁ?+

30 ከቀለጠ በረዶ በተገኘ ውኃ ብታጠብ፣

እጆቼንም በእንዶድ* ባነጻ፣+

31 አንተ አዘቅት ውስጥ ትነክረኛለህ፤

ከዚህም የተነሳ የገዛ ልብሶቼ እንኳ ይጸየፉኛል።

32 መልስ እሰጠው ዘንድ፣

ችሎት ፊትም አብረን እንቀርብ ዘንድ እሱ እንደ እኔ ሰው አይደለምና።+

33 በመካከላችን የሚበይን፣*

ሊዳኘንም የሚችል* ሰው የለም።

34 እኔን መምታቱን ቢያቆም፣*

ሽብርም ባይለቅብኝ፣+

35 ያን ጊዜ ያለፍርሃት አናግረዋለሁ፤

በፍርሃት የምናገር ሰው አይደለሁምና።

10 “ሕይወቴን ተጸየፍኳት።*+

አንዳች ሳላስቀር ብሶቴን አሰማለሁ።

በታላቅ ምሬት* እናገራለሁ!

 2 አምላክን እንዲህ እለዋለሁ፦ ‘በደለኛ ነህ አትበለኝ።

ከእኔ ጋር የምትሟገተው ለምን እንደሆነ ንገረኝ።

 3 በክፉዎች ዕቅድ ደስ እየተሰኘህ፣

የእጆችህን ሥራ መጨቆንህና መናቅህ

ምን ይጠቅምሃል?+

 4 ዓይንህ የሥጋ ለባሽ ዓይን ነው?

ወይስ የምታየው ሟች የሆነ ሰው በሚያይበት መንገድ ነው?

 5 ዘመንህ እንደ ሟች ሰዎች ዘመን ነው?

ወይስ ዕድሜህ እንደ ሰው ዘመን ነው?+

 6 ታዲያ በደልን የምትፈላልግብኝ፣

ኃጢአቴንስ የምትከታተለው ለምንድን ነው?+

 7 በደለኛ እንዳልሆንኩ ታውቃለህ፤+

ደግሞም ማንም ከእጅህ ሊያስጥለኝ አይችልም።+

 8 የገዛ እጆችህ ቀረጹኝ፤ ደግሞም ሠሩኝ፤+

አሁን ግን ሙሉ በሙሉ ልታጠፋኝ ነው።

 9 ከሸክላ እንደሠራኸኝ እባክህ አስታውስ፤+

አሁን ግን ወደ አፈር ትመልሰኛለህ።+

10 እንደ ወተት አላፈሰስከኝም?

እንደ እርጎስ አላረጋኸኝም?

11 ቆዳና ሥጋ አለበስከኝ፤

በአጥንትና በጅማት አያይዘህ ሠራኸኝ።+

12 ሕይወት ሰጠኸኝ፤ ታማኝ ፍቅርም አሳየኸኝ፤

መንፈሴን* በእንክብካቤ ጠበቅክ።+

13 ሆኖም እነዚህን ነገሮች በስውር ለማድረግ አሰብክ።*

እነዚህ ነገሮች ከአንተ እንደመጡ አውቃለሁ።

14 ኃጢአት ብሠራ ትመለከተኛለህ፤+

ከበደሌም ነፃ አታደርገኝም።

15 በደለኛ ከሆንኩ ወዮልኝ!

ንጹሕ ብሆንም እንኳ ራሴን ቀና ማድረግ አልችልም፤+

ውርደትና ጉስቁልና በዝቶብኛልና።+

16 ራሴን ቀና ባደርግ እንደ አንበሳ ታድነኛለህ፤+

ዳግመኛም በእኔ ላይ ኃይልህን ታሳያለህ።

17 አዳዲስ ምሥክሮችን በእኔ ላይ ታቆማለህ፤

ቁጣህንም በእኔ ላይ ታበዛለህ፤

በመከራ ላይ መከራ ተደራርቦብኛል።

18 ታዲያ ከማህፀን ለምን አወጣኸኝ?+

ምነው የሰው ዓይን ሳያየኝ በሞትኩ ኖሮ!

19 እንዳልተፈጠርኩ በሆንኩ ነበር!

በቀጥታ ከማህፀን ወደ መቃብር በተወሰድኩ ነበር!’

20 የሕይወት ዘመኔ ጥቂት አይደለም?+ እስቲ ተወት ያድርገኝ፤

ትንሽ ፋታ እንዳገኝ* ዓይኑን ከእኔ ላይ ያንሳ፤+

21 ወደማልመለስበት ስፍራ፣+

ወደ ድቅድቅ ጨለማ* ምድር በቅርቡ እሄዳለሁ፤+

22 በጨለማ ወደተዋጠ፣ ፅልማሞት ወዳጠላበትና

ዝብርቅ ወደሰፈነበት፣

ብርሃኑ እንኳ እንደ ጨለማ ወደሆነበት ምድር እሄዳለሁ።”

11 ናአማታዊው ሶፋር+ እንዲህ ሲል መለሰ፦

 2 “ይህ ሁሉ ቃል መልስ ሳይሰጠው ሊታለፍ ይገባል?

ወይስ ብዙ ማውራት አንድን ሰው ትክክለኛ ያደርገዋል?*

 3 ከንቱ ንግግርህ ሰዎችን ዝም ያሰኛል?

ስታፌዝስ የሚገሥጽህ የለም?+

 4 ‘ትምህርቴ የጠራ ነው፤+

በፊትህም ንጹሕ ነኝ’ ትላለህና።+

 5 ምነው አምላክ በተናገረህ!

ከንፈሩንም በአንተ ላይ በከፈተ!+

 6 በዚያን ጊዜ የጥበብን ሚስጥር ይገልጥልሃል፤

ጥበብ* ፈርጀ ብዙ ናትና።

ያን ጊዜ፣ የሠራሃቸውን አንዳንድ በደሎች አምላክ እንደረሳልህ ትገነዘባለህ።

 7 የአምላክን ጥልቅ ነገሮች መርምረህ ልትደርስባቸው ትችላለህ?

ወይስ ሁሉን ቻይ ስለሆነው አምላክ ሁሉንም ነገር መርምረህ ልትደርስበት* ትችላለህ?

 8 ጥበብ ከሰማይ ይልቅ ከፍ ትላለች። አንተ ምን ልታደርግ ትችላለህ?

ከመቃብርም* ይልቅ ጥልቅ ነች። አንተ ምን ልታውቅ ትችላለህ?

 9 ከምድር ይልቅ ትረዝማለች፤

ከባሕርም ይልቅ ትሰፋለች።

10 እሱ በሚያልፍበት ጊዜ አንድን ሰው ይዞ ለፍርድ ካቀረበ፣

ማን ሊቃወመው ይችላል?

11 አታላይ ሰዎችን ያውቃልና።

እሱ ክፉ ነገር ሲያይ ትኩረት አይሰጥም?

12 የዱር አህያ ሰው መውለድ ቢችል፣*

ያን ጊዜ አእምሮ የሌለው ሰው ማስተዋል ያገኛል።

13 ምነው ልብህን ብታዘጋጅ፣

እጆችህንም ወደ እሱ ብትዘረጋ!

14 እጅህ መጥፎ ነገር የሚሠራ ከሆነ አርቀው፤

በድንኳኖችህም ውስጥ ክፋት አይኑር።

15 በዚያን ጊዜ ያለኀፍረት ፊትህን ቀና ታደርጋለህ፤

ምንም ሳትፈራ ጸንተህ ትቆማለህ።

16 ያን ጊዜ ችግርህን ትረሳለህና፤

አልፎህ እንደሄደ ውኃ አድርገህ ታስበዋለህ።

17 ሕይወትህ ከቀትር ይልቅ ብሩህ ይሆናል፤

ጨለማውም እንኳ እንደ ንጋት ይሆናል።

18 ተስፋ ስላለ ልበ ሙሉ ትሆናለህ፤

ዙሪያህንም ትመለከታለህ፤ ያለስጋትም ትተኛለህ።

19 የሚያስፈራህ ሳይኖር ትተኛለህ፤

ብዙ ሰዎችም የአንተን ሞገስ ለማግኘት ይሻሉ።

20 የክፉዎች ዓይን ግን ይደክማል፤

የሚሸሹበት ቦታም አያገኙም፤

ያላቸው ብቸኛ ተስፋ ሞት* ነው።”+

12 ከዚያም ኢዮብ እንዲህ ሲል መለሰ፦

 2 “በእርግጥ አዋቂዎች እናንተ ናችኋ!*

ጥበብም ከእናንተ ጋር ትሞታለቻ!

 3 እኔም እኮ ማስተዋል* አለኝ።

ከእናንተ አላንስም።

እነዚህን ነገሮች የማያውቅ ማን ነው?

 4 ወደ አምላክ ተጣርቼ መልስ የምጠብቅ፣+

የባልንጀሮቼ መሳለቂያ ሆኛለሁ።+

ጻድቅና ነቀፋ የሌለበት ሰው፣ የሰዎች መሳለቂያ ነው።

 5 የደላው ሰው ‘መከራ የሚደርሰው

እግራቸው በሚብረከረክ* ሰዎች ላይ ብቻ ነው’ ብሎ በማሰብ መከራን ይንቃል።

 6 የዘራፊዎች ድንኳን ሰላም አለው፤+

አምላክን የሚያስቆጡ ሰዎችም፣

አምላካቸውን* በእጃቸው እንደያዙ ሰዎች የደህንነት ስሜት ይሰማቸዋል።+

 7 ይሁን እንጂ እስቲ እንስሳትን ጠይቅ፤ እነሱም ያስተምሩሃል፤

በሰማያት የሚበርሩ ወፎችንም ጠይቅ፤ እነሱም ይነግሩሃል።

 8 ወይም በምድር ላይ ትኩረትህን አድርግ፤* እሷም ታስተምርሃለች፤

የባሕር ዓሣም ያሳውቅሃል።

 9 የይሖዋ እጅ ይህን ማድረጉን፣

ከእነዚህ ሁሉ መካከል የማያውቅ ማን ነው?

10 የሕያው ነገር ሁሉ ሕይወት፣*

የሰውም ሁሉ መንፈስ* በእሱ እጅ ነው።+

11 ምላስ* የምግብን ጣዕም እንደሚለይ ሁሉ፣

ጆሮስ ቃላትን አያመዛዝንም?+

12 በዕድሜ በገፉት መካከል ጥበብ፣

ከረጅም ዕድሜስ ጋር ማስተዋል አይገኝም?+

13 በእሱ ዘንድ ጥበብና ኃይል አለ፤+

ምክርና ማስተዋልም አለው።+

14 እሱ ያፈረሰውን ነገር መልሶ መገንባት አይቻልም፤+

እሱ የዘጋውን ማንም ሰው ሊከፍት አይችልም።

15 ውኃዎችን ሲከለክል ሁሉም ነገር ይደርቃል፤+

ሲልካቸውም ምድርን ያጥለቀልቃሉ።+

16 ብርታትና ጥበብ* በእሱ ዘንድ ናቸው፤+

መንገድ የሚስተውም ሆነ የሚያስተው የእሱ ናቸው፤

17 አማካሪዎችን ባዶ እግራቸውን ያስኬዳቸዋል፤*

ፈራጆችንም ያሞኛቸዋል።+

18 ነገሥታት ያሰሩትን ይፈታል፤+

በወገባቸውም ዙሪያ መታጠቂያ ያስራል።

19 ካህናትን ባዶ እግራቸውን ያስኬዳቸዋል፤+

በሥልጣን ላይ ተደላድለው የተቀመጡትንም ይገለብጣል፤+

20 የታመኑ አማካሪዎችን የሚሉትን ነገር ያሳጣቸዋል፤

ሽማግሌዎችንም ማስተዋል ይነሳል፤

21 በታላላቅ ሰዎች ላይ የውርደት መዓት ያዘንባል፤+

ብርቱዎችንም ደካማ ያደርጋል፤*

22 ጥልቅ የሆኑ ነገሮችን ከጨለማ ውስጥ ይገልጣል፤+

በድቅድቅ ጨለማ ላይ ብርሃን ይፈነጥቃል፤

23 ያጠፋቸው ዘንድ ብሔራትን ታላቅ ያደርጋል፤

ወደ ግዞት ይወስዳቸውም ዘንድ ብሔራትን እንዲስፋፉ ያደርጋቸዋል።

24 የሕዝቡን መሪዎች ማስተዋል* ይነሳል፤

መንገድ በሌለበት ጠፍ መሬትም እንዲቅበዘበዙ ያደርጋል።+

25 ብርሃን በሌለበት ጨለማ፣ በዳበሳ ይሄዳሉ፤+

እንደሰከሩ ሰዎች እንዲዳክሩ ያደርጋቸዋል።+

13 “አዎ፣ ዓይኔ ይህን ሁሉ አይታለች፤

ጆሮዬም ሰምታ አስተውላለች።

 2 እናንተ የምታውቁትን እኔም አውቃለሁ፤

ከእናንተ አላንስም።

 3 እኔ በበኩሌ ሁሉን ቻይ የሆነውን አምላክ ራሱን ባነጋግር እመርጣለሁ፤

ከአምላክ ጋር መሟገት እፈልጋለሁ።+

 4 እናንተ ግን በውሸት ስሜን እያጠፋችሁ ነው፤

ሁላችሁም የማትረቡ ሐኪሞች ናችሁ።+

 5 ምነው ዝም ብትሉ!

ጥበበኛ መሆናችሁ በዚህ ይታወቅ ነበር።+

 6 እስቲ የመከራከሪያ ሐሳቤን ስሙ፤

የከንፈሬንም አቤቱታ አዳምጡ።

 7 ከአምላክ ጎን ቆማችሁ አግባብ ያልሆነ ነገር ታወራላችሁ?

ለእሱ ብላችሁስ የማታለያ ቃል ትናገራላችሁ?

 8 ከእሱ ጎን ትቆማላችሁ?*

ወይስ ለእውነተኛው አምላክ ትሟገታላችሁ?

 9 እሱ ቢመረምራችሁ መልካም ይሆንላችኋል?+

ሟች የሆነውን ሰው እንደምታሞኙ እሱን ታሞኛላችሁ?

10 በስውር አድልዎ ለማድረግ ብትሞክሩ፣

እሱ በእርግጥ ይገሥጻችኋል።+

11 ክብሩ ሽብር አይለቅባችሁም?

የእሱ ፍርሃትስ አይወድቅባችሁም?

12 ጥበብ የተንጸባረቀባቸው* አባባሎቻችሁ ከንቱ ምሳሌዎች* ናቸው፤

መከላከያዎቻችሁ* ከሸክላ እንደተሠሩ ጋሻዎች ተሰባሪ ናቸው።

13 እኔ እንድናገር በፊቴ ዝም በሉ።

ከዚያ በኋላ የመጣው ይምጣብኝ!

14 ራሴን ለምን ለአደጋ አጋልጣለሁ?*

ሕይወቴንስ* ለምን በእጄ እይዛለሁ?

15 ቢገድለኝ እንኳ እሱን በተስፋ እጠባበቃለሁ፤+

በፊቱ ጉዳዬን አቅርቤ እከራከራለሁ።*

16 በዚህ ጊዜ እሱ አዳኜ ይሆናል፤+

አምላክ የለሽ* ሰው ፈጽሞ ፊቱ አይቀርብምና።+

17 ቃሌን በጥሞና ስሙ፤

የምናገረውንም ነገር ልብ ብላችሁ አድምጡ።

18 እንግዲህ ሙግቴን አዘጋጅቻለሁ፤

ትክክል እንደሆንኩ አውቃለሁ።

19 ከእኔ ጋር የሚሟገት ማን ነው?

ዝም ብል እሞታለሁ!*

20 አምላክ ሆይ፣ ከአንተ ሁለት ነገሮች ብቻ እሻለሁ፤*

በዚያን ጊዜ ራሴን ከፊትህ አልሰውርም፦

21 ከባዱን እጅህን ከእኔ አርቅ፤

አስፈሪነትህም አያስደንግጠኝ።+

22 ጥራኝና ልመልስልህ፤

አለዚያ እኔ ልናገር፤ አንተም መልስ ስጠኝ።

23 የሠራሁት በደልና ኃጢአት ምንድን ነው?

መተላለፌንና ኃጢአቴን አሳውቀኝ።

24 ፊትህን የምትሰውረውና+

እንደ ጠላትህ የምትቆጥረኝ ለምንድን ነው?+

25 ነፋስ የወሰደውን ቅጠል ለማስፈራራት ትሞክራለህ?

ወይስ የደረቀውን ገለባ ታሳድዳለህ?

26 ከባድ ክሶችን ትመዘግብብኛለህ፤

በወጣትነቴ ለሠራኋቸው ኃጢአቶች መልስ እንድሰጥ ታደርገኛለህ።

27 እግሮቼን በእግር ግንድ አስረሃል፤

መንገዴን ሁሉ ትመረምራለህ፤

ዱካዬንም ሁሉ በዓይነ ቁራኛ ትከታተላለህ።

28 በመሆኑም ሰው* እንደበሰበሰ ነገር፣

ብልም እንደበላው ልብስ እያለቀ ይሄዳል።

14 “ከሴት የተወለደ ሰው፣

የሕይወት ዘመኑ አጭርና+ በመከራ የተሞላ* ነው።+

 2 እንደ አበባ ይፈካል፤ ከዚያም ይጠወልጋል፤*+

እንደ ጥላም ወዲያው ያልፋል፤ ደብዛውም ይጠፋል።+

 3 አዎ፣ ዓይንህን በዚህ ሰው ላይ አሳርፈሃል፤

እሱንም ከአንተ ጋር ፍርድ ፊት ታቀርበዋለህ።*+

 4 ንጹሕ ካልሆነ ሰው፣ ንጹሕ የሆነ ሰው መውለድ የሚችል ማን ነው?+

ማንም የለም!

 5 የሰው የሕይወት ዘመን አጭር እንዲሆን የተወሰነ ከሆነ፣

የወራቱ ቁጥር በአንተ ቁጥጥር ሥር ነው፤

ከዚያ እንዳያልፍ ገደብ አበጅተህለታል።+

 6 እንደ ቅጥር ሠራተኛ ጊዜውን እስኪያጠናቅቅ ድረስ፣

እረፍት ያገኝ ዘንድ ዓይንህን ከእሱ ላይ መልስ።+

 7 ዛፍ እንኳ ተስፋ አለውና።

ቢቆረጥ መልሶ ያቆጠቁጣል፤

ቅርንጫፎቹም ማደጋቸውን ይቀጥላሉ።

 8 ሥሩ መሬት ውስጥ ቢያረጅ፣

ጉቶውም አፈር ውስጥ ቢበሰብስ፣

 9 የውኃ ሽታ ሲያገኝ ያቆጠቁጣል፤

እንደ አዲስ ተክልም ቅርንጫፎች ያወጣል።

10 ሰው ግን ይሞታል፤ አቅም አጥቶም ይጋደማል፤

ሰው ሲሞት የት ይገኛል?+

11 ውኃ ከባሕር ውስጥ ይጠፋል፤

ወንዝም ፈስሶ ይደርቃል።

12 ሰውም ያንቀላፋል፤ ደግሞም አይነሳም።+

ሰማይ እስከሚያልፍ ድረስ አይነቁም፤

ከእንቅልፋቸውም አይነሱም።+

13 ምነው በመቃብር* ውስጥ በሰወርከኝ!+

ቁጣህ እስኪያልፍ ድረስ በሸሸግከኝ!

ቀጠሮም ሰጥተህ ባስታወስከኝ!+

14 ሰው ከሞተ በኋላ ዳግመኛ በሕይወት ሊኖር ይችላል?+

እፎይታ የማገኝበት ጊዜ እስኪደርስ ድረስ፣

የግዳጅ አገልግሎት በምፈጽምበት ዘመን ሁሉ በትዕግሥት እጠብቃለሁ።+

15 አንተ ትጣራለህ፤ እኔም እመልስልሃለሁ።+

የእጅህን ሥራ ትናፍቃለህ።*

16 አሁን ግን እርምጃዬን ሁሉ ትቆጥራለህ፤

ኃጢአቴን ብቻ ትመለከታለህ።

17 መተላለፌ በከረጢት ውስጥ ታሽጓል፤

በደሌንም በሙጫ ታሽጋለህ።

18 ተራራ እንደሚወድቅና ተፈረካክሶ እንደሚጠፋ፣

ቋጥኝም ከስፍራው እንደሚወገድ፣

19 ውኃ ድንጋይን እንደሚቦረቡር፣

ጎርፍም የምድርን አፈር አጥቦ እንደሚወስድ፣

አንተም ሟች የሆነውን ሰው ተስፋ አጥፍተሃል።

20 እስኪጠፋ ድረስ በእሱ ላይ ታይልበታለህ፤+

ገጽታውን ለውጠህ ታሰናብተዋለህ።

21 ልጆቹ ክብር ቢያገኙም እሱ ይህን አያውቅም፤

ውርደት ሲደርስባቸውም ልብ አይልም።+

22 ሕመም የሚሰማው በሥጋ ሳለ ብቻ ነው፤

የሚያዝነው* በሕይወት ሳለ ብቻ ነው።”

15 ቴማናዊው ኤሊፋዝ+ እንዲህ ሲል መለሰ፦

 2 “ጥበበኛ ሰው ከንቱ በሆነ ንግግር* ይመልሳል?

ወይስ በምሥራቅ ነፋስ ሆዱን ይሞላል?

 3 በማይረባ ቃል መውቀስ ምንም ዋጋ የለውም፤

ደግሞም ወሬ ብቻውን ምንም ጥቅም የለውም።

 4 አንተ ፈሪሃ አምላክን ታጣጥላለህና፤

ስለ አምላክ ማሰብም ዋጋ የለውም ትላለህ።

 5 በደልህ በምትናገረው ነገር ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል፤*

ተንኮል ያዘለ ንግግር መናገርም ትመርጣለህ።

 6 እኔ ሳልሆን የገዛ አፍህ ይፈርድብሃል፤

የገዛ ከንፈሮችህ ይመሠክሩብሃል።+

 7 ለመሆኑ ከሰው ሁሉ በፊት የተወለድከው አንተ ነህ?

ወይስ የተወለድከው ከኮረብቶች በፊት ነው?

 8 የአምላክን ሚስጥር ትሰማለህ?

ወይስ ጥበብ ያለህ አንተ ብቻ ነህ?

 9 እኛ የማናውቀው አንተ ግን የምታውቀው ምን ነገር አለ?+

ደግሞስ እኛ የማናስተውለው አንተ ግን የምታስተውለው ምን ነገር አለ?

10 የሸበቱም ሆኑ በዕድሜ የገፉ፣

እንዲሁም ከአባትህ በዕድሜ እጅግ የሚበልጡ ከእኛ ጋር አሉ።+

11 የአምላክ ማጽናኛ፣

ወይም በለሰለሰ አንደበት የተነገረህ ቃል አነሰህ?

12 ልብህ ለምን ይታበያል?

ዓይኖችህስ ለምን በቁጣ ይጉረጠረጣሉ?

13 በአምላክ ላይ ተቆጥተሃልና፤

እንዲህ ያሉ ቃላትም ከገዛ አፍህ ወጥተዋል።

14 ንጹሕ ይሆን ዘንድ ሟች የሆነ ሰው ምንድን ነው?

ወይስ ጻድቅ ይሆን ዘንድ ከሴት የተወለደ ሰው ምንድን ነው?+

15 እነሆ፣ በቅዱሳኑ* ላይ እምነት የለውም፤

ሰማያትም እንኳ በፊቱ ንጹሐን አይደሉም።+

16 ታዲያ ክፋትን እንደ ውኃ የሚጠጣ፣

አስጸያፊና ብልሹ የሆነ ሰውማ እንዴት ሊታመን ይችላል?+

17 አዳምጠኝ! እኔ አሳውቅሃለሁ።

ያየሁትን እናገራለሁ፤

18 ጥበበኛ ሰዎች ከአባቶቻቸው ሰምተው የተናገሩትን፣+

ደግሞም ከሌሎች ያልሸሸጉትን ነገር እነግርሃለሁ።

19 ምድሪቱ የተሰጠችው ለእነሱ ብቻ ነበር፤

በመካከላቸውም ባዕድ ሰው አላለፈም።

20 ክፉ ሰው ዕድሜውን ሁሉ፣

ለጨቋኙ በተመደቡት ዓመታት በሙሉ ይሠቃያል።

21 አስፈሪ ድምፆችን ይሰማል፤+

በሰላም ጊዜ ወራሪዎች ጥቃት ይሰነዝሩበታል።

22 ከጨለማ እንደሚያመልጥ አያምንም፤+

ሰይፍም ይጠብቀዋል።

23 ‘ወዴት ነው?’ እያለ ምግብ* ፍለጋ ይቅበዘበዛል፤

የጨለማ ቀን እንደደረሰ በሚገባ ያውቃል።

24 ጭንቀትና ሥቃይ ያሸብሩታል፤

ጥቃት ለመሰንዘር እንደተዘጋጀ ንጉሥ ያይሉበታል።

25 በአምላክ ላይ እጁን ያነሳልና፤

ሁሉን ቻይ የሆነውን አምላክ ለመገዳደርም* ይሞክራል፤

26 ወፍራምና ጠንካራ ጋሻ* አንግቦ፣

በእልኸኝነት እየገሰገሰ ይመጣበታል፤

27 ፊቱ በስብ ተሸፍኗል፤

ወገቡም በስብ ተወጥሯል፤

28 በሚፈራርሱ ከተሞች፣

ደግሞም ማንም በማይኖርባቸውና

የድንጋይ ክምር በሚሆኑ ቤቶች ውስጥ ይኖራል።

29 ባለጸጋ አይሆንም፤ ሀብቱም አይከማችም፤

ንብረቱም በምድሪቱ ላይ አይበረክትም።

30 ከጨለማ አያመልጥም፤

ነበልባል ቅርንጫፉን ያደርቀዋል፤*

ከአምላክም* አፍ በሚወጣ እስትንፋስ ይጠፋል።+

31 መንገድ መሳትና ከንቱ በሆነ ነገር መታመን የለበትም፤

በአጸፋው የሚያገኘው ነገር ዋጋ አይኖረውምና፤

32 ቀኑ ከመድረሱ በፊት ይፈጸማል፤

ቅርንጫፎቹም አይለመልሙም።+

33 ያልበሰሉ ፍሬዎቹን እንደሚጥል የወይን ተክል፣

አበቦቹን እንደሚያረግፍ የወይራ ዛፍም ይሆናል።

34 አምላክ የለሽ የሆኑ ሰዎች* ጉባኤ ይመክናልና፤+

የጉቦ ድንኳኖችም እሳት ይበላቸዋል።

35 ችግር ይፀንሳሉ፤ ክፉ ነገርም ይወልዳሉ፤

ማህፀናቸውም ተንኮል ያፈራል።”

16 ኢዮብ እንዲህ ሲል መለሰ፦

 2 “ከዚህ በፊት እንዲህ ያሉ ብዙ ነገሮች ሰምቻለሁ።

ሁላችሁም የምታስጨንቁ አጽናኞች ናችሁ!+

 3 ከንቱ* ቃላት ማብቂያ የላቸውም?

እንዲህ ብለህ እንድትመልስ ያነሳሳህ ምንድን ነው?

 4 እኔም እንደ እናንተ መናገር እችል ነበር።

እናንተ በእኔ ቦታ ብትሆኑ ኖሮ፣*

አሳማኝ በሆነ መንገድ ልናገራችሁ እችል ነበር፤

በእናንተም ላይ ራሴን መነቅነቅ እችል ነበር።+

 5 እንዲህ ከማድረግ ይልቅ በአፌ ቃል አበረታችሁ ነበር፤

የከንፈሮቼም ማጽናኛ ባሳረፋችሁ ነበር።+

 6 ብናገር ከሥቃዬ አልገላገልም፤+

ዝም ብልስ ሥቃዬ ምን ያህል ይቀንስልኛል?

 7 አሁን ግን አምላክ እንድዝል አድርጎኛል፤+

መላ ቤተሰቤን* አጥፍቷል።

 8 ደግሞም ያዝከኝ፤ ይህም ምሥክር ሆኖብኛል፤

በመሆኑም ክሳቴ ተነስቶ በፊቴ ይመሠክራል።

 9 ቁጣው ቦጫጨቀኝ፤ በጥላቻ ተመለከተኝ።+

ጥርሱን አፋጨብኝ።

ባላጋራዬ በዓይኑ ወጋኝ።+

10 እነሱ አፋቸውን በሰፊው ከፈቱብኝ፤+

በንቀትም ጉንጬን አጮሉኝ፤

ብዙ ሆነው በእኔ ላይ ተሰበሰቡ።+

11 አምላክ ለልጆች አሳልፎ ሰጠኝ፤

በክፉዎችም እጅ ላይ ገፍትሮ ጣለኝ።+

12 ያለምንም ችግር እኖር ነበር፤ እሱ ግን ሰባበረኝ፤+

ማጅራቴን ይዞ አደቀቀኝ፤

ከዚያም ዒላማው አደረገኝ።

13 ቀስተኞቹ ከበቡኝ፤+

ኩላሊቴን ወጋ፤+ ምንም ርኅራኄ አላሳየኝም፤

ሐሞቴን መሬት ላይ አፈሰሰ።

14 እንደ ግንብ ሰንጥቆ ሰነጣጥቆ አፈራረሰኝ፤

እንደ ተዋጊ ተንደርድሮ መጣብኝ።

15 ቆዳዬን ለመሸፈን ማቅ ሰፍቻለሁ፤+

ክብሬንም* አፈር ውስጥ ቀብሬአለሁ።+

16 ከለቅሶ የተነሳ ፊቴ ቀልቷል፤+

ድቅድቅ ጨለማም* በዓይኖቼ ቆብ ላይ አጥልቷል፤

17 ይሁንና እጆቼ ምንም ዓመፅ አልሠሩም፤

ጸሎቴም ንጹሕ ነው።

18 ምድር ሆይ፣ ደሜን አትሸፍኚ!+

ጩኸቴም ማረፊያ ስፍራ አያግኝ!

19 አሁንም እንኳ ምሥክሬ በሰማያት አለ፤

ስለ እኔ መመሥከር የሚችል በከፍታ ቦታዎች ላይ ይገኛል።

20 ጓደኞቼ በእኔ ላይ ያፌዛሉ፤+

ዓይኔም ወደ አምላክ ያነባል።*+

21 በሰውና በባልንጀራው መካከል የሚዳኝ እንደሚኖር፣

በሰውና በአምላክ መካከልም የሚዳኝ ይኑር።+

22 የሚቀሩት ዓመታት ጥቂት ናቸውና፤

እኔም በማልመለስበት መንገድ እሄዳለሁ።+

17 “መንፈሴ ተሰብሯል፤ ዘመኔ አብቅቷል፤

መቃብር ይጠብቀኛል።+

 2 ፌዘኞች ከበውኛል፤+

ዓይኔም የዓመፅ ተግባራቸውን በትኩረት ትመለከታለች።*

 3 እባክህ፣ መያዣዬን ተቀብለህ አንተ ዘንድ አስቀምጥልኝ።

እጄን የሚመታና ተያዥ የሚሆነኝ ሌላ ማን ይኖራል?+

 4 ማስተዋልን ከልባቸው ሰውረሃልና፤+

ከዚህም የተነሳ ከፍ ከፍ አታደርጋቸውም።

 5 የልጆቹ ዓይን ደክሞ እያለ፣

ያለውን ለወዳጆቹ ሊያካፍል ይችላል።

 6 አምላክ የሰዎች መቀለጃ* አደረገኝ፤+

በመሆኑም ፊቱ ላይ እንደሚተፉበት ሰው ሆንኩ።+

 7 ከሐዘን የተነሳ ዓይኔ ፈዘዘ፤+

እጆቼና እግሮቼም እንደ ጥላ ሆኑ።

 8 ቅን የሆኑ ሰዎች በዚህ ነገር በመገረም ትኩር ብለው ይመለከታሉ፤

ንጹሕ የሆነውም፣ አምላክ የለሽ* በሆነው ሰው ይረበሻል።

 9 ጻድቅ መንገዱን በጥብቅ ይከተላል፤+

እጁ ንጹሕ የሆነ ሰውም እየበረታ ይሄዳል።+

10 ይሁን እንጂ ሁላችሁም ተመልሳችሁ መከራከራችሁን መቀጠል ትችላላችሁ፤

ከእናንተ መካከል አንድም ጥበበኛ አላገኘሁምና።+

11 የሕይወት ዘመኔ አበቃ፤+

ዕቅዴና የልቤ ምኞት ተንኮታኮተ።+

12 ሌሊቱን ወደ ቀን ይለውጣሉ፤

‘ጨለማ ስለሆነ ብርሃን የሚፈነጥቅበት ጊዜ ቀርቧል’ ይላሉ።

13 ዝም ብዬ ብጠብቅ ያን ጊዜ መቃብር፣* ቤቴ ይሆናል፤+

በጨለማ መኝታዬን እዘረጋለሁ።+

14 ጉድጓዱን*+ ‘አንተ አባቴ ነህ!’ እለዋለሁ፤

ትሏን ‘አንቺ እናቴና እህቴ ነሽ!’ እላታለሁ።

15 እንግዲህ የእኔ ተስፋ የት አለ?+

ተስፋ እንዳለኝ አድርጎ የሚያስብስ ማን ነው?

16 ሁላችንም ተያይዘን ወደ አፈር ስንገባ፣

ተስፋዬ ወደተቀረቀሩ የመቃብር* በሮች ይወርዳል።”+

18 ሹሃዊው በልዳዶስ+ እንዲህ ሲል መለሰ፦

 2 “እንዲህ ያለ ንግግር መናገራችሁን* የምትቀጥሉት እስከ መቼ ነው?

በተወሰነ መጠን ልታስተውሉ ይገባል፤ ያን ጊዜ እኛ እንናገራለን።

 3 ለምን እንደ እንስሳ እንቆጠራለን?+

በፊታችሁስ ለምን እንደ ደነዝ* እንታያለን?

 4 አንተ በቁጣ ራስህን* ብትቦጫጭቅ፣

ለአንተ ሲባል ምድር ባዶ ትቀራለች?

ወይስ ዓለት ከስፍራው ተነቅሎ ይወሰዳል?

 5 አዎ፣ የክፉዎች ብርሃን ይጠፋል፤

የእሳቱም ነበልባል አይበራም።+

 6 በድንኳኑ ውስጥ ያለው ብርሃን በእርግጥ ይጨልማል፤

በላዩ ያለው መብራትም ይጠፋል።

 7 ብርታት የተሞላበት እርምጃው ያጥራል፤

የገዛ ዕቅዱም ይጥለዋል።+

 8 እግሩ ወደ መረብ ይመራዋልና፤

በመረቡም ገመድ ይተበተባል።

 9 ወጥመድ ተረከዙን ይይዘዋል፤

ወስፈንጥርም ያጠምደዋል።+

10 በመሬት ላይ ሸምቀቆ በስውር ይቀመጥለታል፤

ወጥመድም በመንገዱ ላይ ይጠብቀዋል።

11 ሽብር ከሁሉም አቅጣጫ ፍርሃት ይለቅበታል፤+

እግር በእግርም ያሳድደዋል።

12 ጉልበቱ ይከዳዋል፤

አደጋም+ያንገዳግደዋል።*

13 ቆዳው ተበልቷል፤

እጅግ ቀሳፊ የሆነ በሽታ* እጆቹንና እግሮቹን ይበላል።

14 ተማምኖ ከሚኖርበት ድንኳኑ ይወገዳል፤+

ወደ ሽብር ንጉሥም* ይወሰዳል።

15 እንግዶች በድንኳኑ ውስጥ ይኖራሉ፤*

በቤቱም ላይ ድኝ ይበተናል።+

16 ሥሮቹ ከእሱ በታች ይደርቃሉ፤

ቅርንጫፎቹ ደግሞ ከእሱ በላይ ይጠወልጋሉ።

17 መታሰቢያው ከምድር ላይ ይጠፋል፤

በጎዳናም ላይ ስሙ አይታወቅም።*

18 ከብርሃን ወደ ጨለማ ይወሰዳል፤

ፍሬያማ ከሆነችውም ምድር ይባረራል።

19 በሕዝቡ መካከል ልጆችም ሆኑ ዘሮች አይኖሩትም፤

በሚኖርበት ስፍራም* የሚተርፍ ሰው አይኖረውም።

20 የሚጠፋበት ቀን ሲደርስ በምዕራብ ያሉ ሰዎች ይደነግጣሉ፤

በምሥራቅ ያሉ ሰዎችም በፍርሃት ይዋጣሉ።

21 የክፉ አድራጊ ድንኳኖች፣

አምላክን የማያውቁ ሰዎች ስፍራም እንዲህ ያለ ነገር ይደርስባቸዋል።”

19 ኢዮብ እንዲህ ሲል መለሰ፦

 2 “እናንተ ሰዎች ነፍሴን የምታበሳጯት፣*+

በቃላት የምትደቁሱኝስ+ እስከ መቼ ነው?

 3 ይኸው አሥር ጊዜ ገሠጻችሁኝ፤*

ከባድ በደል ስትፈጽሙብኝ አላፈራችሁም።+

 4 ስህተት ብፈጽምም እንኳ፣

የሠራሁት ስህተት ከእኔ ጋር ይኖራል።

 5 በእኔ ላይ የደረሰው ነቀፋ ተገቢ እንደሆነ አድርጋችሁ በመከራከር፣

በእኔ ላይ ራሳችሁን ከፍ ከፍ ብታደርጉ፣

 6 ያሳተኝ አምላክ እንደሆነ እወቁ፤

በማጥመጃ መረቡም ይዞኛል።

 7 እነሆ ‘ግፍ ተፈጸመብኝ!’ ብዬ ብጮኽም መልስ አላገኘሁም፤+

እርዳታ ለማግኘት ብጣራም ፍትሕ የለም።+

 8 መንገዴን በድንጋይ ግንብ ዘጋ፤ እኔም ማለፍ አልቻልኩም፤

ጎዳናዬንም በጨለማ ጋረደ።+

 9 ክብሬን ገፎኛል፤

አክሊሉንም ከራሴ ላይ አንስቷል።

10 እስክጠፋ ድረስ በሁሉም አቅጣጫ አፈራረሰኝ፤

ተስፋዬን እንደ ዛፍ ነቀለው።

11 ቁጣው በእኔ ላይ ነደደ፤

እንደ ጠላቱም ቆጠረኝ።+

12 ሠራዊቱ በአንድነት መጥተው ከበቡኝ፤

በድንኳኔም ዙሪያ ሰፈሩ።

13 የገዛ ወንድሞቼን ከእኔ አራቀ፤

የሚያውቁኝም ሰዎች ጥለውኝ ሄዱ።+

14 የቅርብ ወዳጆቼ ትተውኛል፤*

በደንብ የማውቃቸውም ሰዎች ረሱኝ።+

15 በቤቴ ያሉ እንግዶችና+ ሴቶች ባሪያዎቼ እንደ መጤ ቆጠሩኝ፤

እንደ ባዕድ አገር ሰው ተመለከቱኝ።

16 አገልጋዬን ጠራሁት፤ እሱ ግን አልመለሰልኝም፤

እንዲራራልኝ በአንደበቴ ለመንኩት።

17 ሚስቴ ትንፋሼን እንኳ ተጸየፈችው፤+

ለገዛ ወንድሞቼም* መጥፎ ጠረን ሆንኩባቸው።

18 ትናንሽ ልጆች እንኳ ናቁኝ፤

ስነሳ በእኔ ላይ ያላግጣሉ።

19 የቅርብ ወዳጆቼ ሁሉ ተጸየፉኝ፤+

የምወዳቸውም ሰዎች በእኔ ላይ ተነሱ።+

20 አጥንቶቼ ከቆዳዬና ከሥጋዬ ጋር ተጣበቁ፤+

ከሞት ለጥቂት* ተረፍኩ።

21 ወዳጆቼ ሆይ፣ ማሩኝ፤ እባካችሁ ማሩኝ፤

የአምላክ እጅ መታኛለችና።+

22 አምላክ እንዳሳደደኝ የምታሳድዱኝ ለምንድን ነው?+

ያለፋታ የምታጠቁኝስ* ለምንድን ነው?+

23 ምነው ቃሌ በተጻፈ!

ምነው በመጽሐፍ ላይ በሰፈረ!

24 ምነው በብረት ብዕርና በእርሳስ፣

በዓለቱ ላይ ለዘላለም በተቀረጸ!

25 የሚዋጀኝ*+ ሕያው እንደሆነ በሚገባ አውቃለሁና፤

ከጊዜ በኋላ መጥቶ በምድር ላይ ይቆማል።

26 ቆዳዬ በዚህ መንገድ ቢጠፋም፣

ገና በሥጋ እያለሁ አምላክን አየዋለሁ፤

27 እኔ ራሴ እሱን እመለከተዋለሁ፤

የሌላ ሰው ዓይን ሳይሆን የገዛ ዓይኖቼ ያዩታል።+

ይሁንና በውስጤ እንደዛልኩ ይሰማኛል!*

28 የችግሩ መንስኤ እኔ ጋ እያለ፣

‘የምናሳድደው እንዴት ነው?’ ትላላችሁና።+

29 እናንተ ራሳችሁ ሰይፉን ፍሩ፤+

ሰይፉ በበደል ላይ ቅጣት ያመጣልና፤

ፈራጅ መኖሩን ልታውቁ ይገባል።”+

20 ናአማታዊው ሶፋር+ እንዲህ ሲል መለሰ፦

 2 “ስሜቴ ስለታወከ፣

የሚረብሸኝ ሐሳብ መልስ እንድሰጥ ይገፋፋኛል።

 3 እኔን የሚዘልፍ ወቀሳ ሰምቻለሁ፤

ያለኝ ማስተዋል* መልስ እንድሰጥ ይገፋፋኛል።

 4 ከድሮ ጀምሮ ይህን ታውቅ ነበር ማለት ነው፤

ሰው* በምድር ላይ መኖር ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ እንዲህ ነበርና፤+

 5 የክፉዎች እልልታ ለአጭር ጊዜ፣

አምላክ የለሽ የሆነ* ሰው ደስታም ለቅጽበት ነው።+

 6 ታላቅነቱ ወደ ሰማይ ከፍ ቢል፣

ራሱም እስከ ደመናት ቢደርስ፣

 7 እንደ ራሱ እዳሪ ለዘላለም ይጠፋል፤

ያዩት የነበሩ ሰዎችም ‘የት ገባ?’ ይላሉ።

 8 እንደ ሕልም በሮ ይጠፋል፤ እነሱም አያገኙትም፤

እንደ ሌሊት ራእይ ይሰደዳል።

 9 ቀድሞ ያየው ዓይን ዳግመኛ አያየውም፤

የነበረበት ስፍራም ከእንግዲህ አይመለከተውም።+

10 የገዛ ልጆቹ የድሆችን ሞገስ ለማግኘት ይሻሉ፤

የገዛ እጆቹም ሀብቱን መልሰው ይሰጣሉ።+

11 አጥንቶቹ በወጣትነት ጉልበት የተሞሉ ነበሩ፤

ሆኖም ጉልበቱ ከእሱ ጋር አፈር ውስጥ ይተኛል።

12 መጥፎ የሆነ ነገር በአፉ ውስጥ ቢጣፍጥ፣

ከምላሱም በታች ቢደብቀው፣

13 እንዳያልቅበት ሳስቶ ቢያላምጠው፣

በአፉም ውስጥ ቢያቆየው፣

14 ምግቡ በውስጡ ይጎመዝዛል፤

በውስጡም እንደ ጉበና* መርዝ* ይሆናል።

15 የዋጠውን ሀብት መልሶ ይተፋዋል፤

አምላክ ከሆዱ ውስጥ ያወጣዋል።

16 የጉበናዎችን መርዝ ይጠባል፤

የእፉኝት ጥርስ* ይገድለዋል።

17 የውኃ ፈሳሾችን፣

የማርና የቅቤ ጅረቶችን ፈጽሞ አያይም።

18 ንብረቱን ሳይጠቀምበት ይመልሳል፤

ነግዶ ባገኘው ሀብት አይደሰትም።+

19 ድሆችን አድቅቋልና፤ ደግሞም ትቷቸዋል፤

ያልገነባውን ቤት ቀምቷል።

20 ሆኖም በውስጡ ሰላም አይኖረውም፤

ያካበተው ሀብት አያድነውም።

21 ሊበላው የሚችል የተረፈ ነገር አይኖርም፤

ከዚህም የተነሳ ብልጽግናው ዘላቂ አይሆንም።

22 ሀብቱ ሲትረፈረፍ በጭንቀት ይዋጣል፤

የመከራ ዓይነት ይፈራረቅበታል።

23 ሆዱ በሞላ ጊዜ፣

አምላክ* የሚነድ ቁጣውን በእሱ ላይ በመላክ፣

ወደ አንጀቱ እስኪገባ ያዘንብበታል።

24 ከብረት የጦር መሣሪያ ሲሸሽ፣

ከመዳብ የተሠራ ቀስት ይወጋዋል።

25 ቀስት ከጀርባው፣

የሚያብረቀርቅ መሣሪያ ከሐሞቱ መዝዞ ያወጣል፤

በሽብርም ይዋጣል።+

26 ውድ ሀብቱ ለድቅድቅ ጨለማ ይዳረጋል፤

ማንም ያላርገበገበው እሳት እሱን ይበላዋል፤

በድንኳኑ ውስጥ የቀረ ማንኛውም ሰው ጥፋት ይደርስበታል።

27 ሰማይ በደሉን ይገልጥበታል፤

ምድር በእሱ ላይ ትነሳለች።

28 ጎርፍ ቤቱን ጠርጎ ይወስደዋል፤

በአምላክ የቁጣ ቀን* የውኃ መጥለቅለቅ ይከሰታል።

29 ክፉ ሰው ከአምላክ የሚቀበለው ድርሻ፣

አምላክም የወሰነለት ርስት ይህ ነው።”

21 ኢዮብ እንዲህ ሲል መለሰ፦

 2 “የምናገረውን በጥሞና አዳምጡ፤

የምታጽናኑኝ በዚህ ይሁን።

 3 በምናገርበት ጊዜ በትዕግሥት አዳምጡኝ፤

ከተናገርኩ በኋላ ልትሳለቁብኝ ትችላላችሁ።+

 4 ቅሬታዬ በሰው ላይ ነው?

ቢሆንማ ኖሮ የእኔ* ትዕግሥት አያልቅም ነበር?

 5 እዩኝ፤ በመገረምም ተመልከቱኝ፤

እጃችሁን በአፋችሁ ላይ አድርጉ።

 6 ስለዚህ ነገር ሳስብ እረበሻለሁ፤

መላ ሰውነቴም ይንቀጠቀጣል።

 7 ክፉዎች በሕይወት የሚኖሩት፣+

ለእርጅና የሚበቁትና ባለጸጋ* የሚሆኑት ለምንድን ነው?+

 8 ልጆቻቸው ሁልጊዜ አብረዋቸው ይኖራሉ፤

ዘሮቻቸውንም ያያሉ።

 9 ቤታቸው ሰላም የሰፈነበት ነው፤ የሚያሰጋቸውም ነገር የለም፤+

አምላክም በበትሩ አይቀጣቸውም።

10 ኮርማዎቻቸው ዘር ያፈራሉ፤

ላሞቻቸው ይወልዳሉ፤ ደግሞም አይጨነግፉም።

11 ወንዶች ልጆቻቸው እንደ መንጋ በደጅ ይሯሯጣሉ፤

ልጆቻቸውም ይቦርቃሉ።

12 በአታሞና በበገና ታጅበው ይዘፍናሉ፤

በዋሽንትም ድምፅ* ደስ ይሰኛሉ።+

13 ዕድሜያቸውን በደስታ ያሳልፋሉ፤

በሰላምም* ወደ መቃብር* ይወርዳሉ።

14 ይሁንና እውነተኛውን አምላክ እንዲህ ይሉታል፦ ‘አትድረስብን!

መንገዶችህን ማወቅ አንፈልግም።+

15 እናገለግለው ዘንድ ሁሉን ቻይ አምላክ ማን ነው?+

ከእሱ ጋር መተዋወቃችን ምን ይጠቅመናል?’+

16 ሆኖም ብልጽግናቸው በእነሱ ቁጥጥር ሥር እንዳልሆነ አውቃለሁ።+

የክፉዎች ሐሳብ* ከእኔ የራቀች ናት።+

17 የክፉዎች መብራት የጠፋው ስንት ጊዜ ነው?+

መዓት የደረሰባቸውስ ስንት ጊዜ ነው?

አምላክ ተቆጥቶ ጥፋት የላከባቸው ስንት ጊዜ ነው?

18 ለመሆኑ በነፋስ ፊት እንዳለ ገለባ፣

አውሎ ነፋስም እንደሚወስደው እብቅ ሆነው ያውቃሉ?

19 አምላክ አንድ ሰው የሚደርስበትን ቅጣት ለገዛ ልጆቹ ያከማቻል።

ይሁንና ሰውየው ያውቀው ዘንድ አምላክ ብድራቱን ይክፈለው።+

20 የገዛ ዓይኖቹ የሚደርስበትን ጥፋት ይዩ፤

ደግሞም ሁሉን ቻይ የሆነውን አምላክ ቁጣ ይጠጣ።+

21 የወራቱ ቁጥር ቢያጥር፣*+

እሱ ከሄደ በኋላ በቤቱ ላይ ስለሚደርሰው ነገር ምን ግድ ይሰጠዋል?

22 ከፍ ባሉት ላይ እንኳ የሚፈርደው አምላክ ሆኖ ሳለ፣+

ለእሱ እውቀት ሊሰጠው* የሚችል ይኖራል?+

23 አንድ ሰው ሙሉ ብርታት እያለው፣

ተረጋግቶና ያላንዳች ጭንቀት እየኖረ ሳለ ይሞታል፤+

24 ጭኑ በስብ ተሞልቶ፣

አጥንቶቹም ጠንካራ ሆነው* እያለ በሞት ይለያል።

25 ሌላው ሰው ግን አንዳች ጥሩ ነገር ሳይቀምስ፣

በጭንቀት እንደተዋጠ* ይሞታል።

26 ሁለቱም በአንድነት አፈር ውስጥ ይጋደማሉ፤+

ትሎችም ይሸፍኗቸዋል።+

27 እነሆ፣ እናንተ የምታስቡትን፣

እኔንም ለመጉዳት* የጠነሰሳችሁትን ሴራ በሚገባ አውቃለሁ።+

28 እናንተ ‘የተከበረው ሰው ቤት የት አለ?

ክፉው ሰው የኖረበት ድንኳንስ የት አለ?’ ትላላችሁና።+

29 መንገደኞችን አልጠየቃችሁም?

እነሱ የሰጧቸውን አስተያየቶችስ* በሚገባ አልመረመራችሁም?

30 ክፉ ሰው በጥፋት ቀን ይተርፍ የለ?

በቁጣስ ቀን ይድን የለ?

31 ተግባሩን ፊት ለፊት የሚነግረው ማን ነው?

ለሠራውስ ነገር ብድራቱን የሚከፍለው ማን ነው?

32 እሱ ወደ መቃብር ቦታ ሲወሰድ፣

መቃብሩ ጥበቃ ይደረግለታል።

33 የሸለቆ* ጓል ይጣፍጠዋል፤+

ደግሞም ከእሱ በፊት እንደነበሩት ስፍር ቁጥር የሌላቸው ሰዎች ሁሉ፣

የሰው ዘር በሙሉ ይከተለዋል።*+

34 ታዲያ ትርጉም የለሽ ማጽናኛ የምትሰጡኝ ለምንድን ነው?+

የምትሰጡት መልስ ሁሉ ማታለያ ነው!”

22 ቴማናዊው ኤሊፋዝ+ እንዲህ ሲል መለሰ፦

 2 “ሰው አምላክን ሊጠቅመው ይችላል?

ማስተዋል ያለውስ ሰው ምን ይፈይድለታል?+

 3 ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ አንተ ጻድቅ መሆንህ ግድ ይሰጠዋል?*

ወይስ በንጹሕ አቋም* መመላለስህ እሱን ይጠቅመዋል?+

 4 አክብሮት* ስላሳየህ ይቀጣሃል?

ደግሞስ ፍርድ ቤት ያቀርብሃል?

 5 ይህን የሚያደርገው የሠራኸው ክፋት ታላቅ ስለሆነ፣

በደልህም ማብቂያ ስለሌለው አይደለም?+

 6 ያላንዳች ምክንያት ከወንድሞችህ ላይ መያዣ ትወስዳለህና፤

ሰዎችንም ልብሳቸውን ገፈህ ራቁታቸውን ታስቀራለህ።*+

 7 ለደከመው ሰው የሚጠጣ ውኃ አልሰጠህም፤

የራበውንም ሰው ምግብ ነፍገሃል።+

 8 ምድሪቱ የኃያል ሰው ንብረት ነች፤+

የታደለም ሰው ይኖርባታል።

 9 አንተ ግን መበለቶችን ባዶ እጃቸውን ሰደሃል፤

አባት የሌላቸውንም ልጆች* ክንድ ሰብረሃል።

10 ከዚህም የተነሳ በወጥመድ ተከበሃል፤+

ድንገተኛ ሽብርም ያስደነግጥሃል፤

11 በመሆኑም ማየት እንዳትችል ጨለማ ውጦሃል፤

ጎርፍም አጥለቅልቆሃል።

12 አምላክ የሚኖረው ከፍ ባለው ሰማይ አይደለም?

በሰማያት ያሉ ከዋክብትም ሁሉ ምን ያህል ከፍ ያሉ እንደሆኑ ተመልከት።

13 አንተ ግን እንዲህ ብለሃል፦ ‘አምላክ ምን ያውቃል?

በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ሊፈርድ ይችላል?

14 በሰማይ ክበብ ላይ ሲራመድ፣

ማየት እንዳይችል ደመናት ይጋርዱታል።’

15 ክፉ ሰዎች የሄዱበትን፣

የጥንቱን መንገድ ተከትለህ ትሄዳለህ?

16 እነሱ ጊዜያቸው ሳይደርስ ሞት ነጥቋቸዋል፤*

መሠረታቸው በጎርፍ* ተጠራርጎ ሄዷል።+

17 እውነተኛውን አምላክ ‘አትድረስብን!’

ደግሞም ‘ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ በእኛ ላይ ምን ሊያደርግ ይችላል?’ ይላሉ።

18 ሆኖም ቤቶቻቸውን በመልካም ነገሮች የሞላው እሱ ነው።

(እንዲህ ዓይነቱ ክፉ ሐሳብ ከእኔ የራቀ ነው።)

19 ጻድቅ ይህን አይቶ ይደሰታል፤

ንጹሕ የሆነውም ሰው ይሳለቅባቸዋል፤ እንዲህም ይላቸዋል፦

20 ‘ተቃዋሚዎቻችን ጠፍተዋል፤

ከእነሱ የቀረውንም እሳት ይበላዋል።’

21 እሱን እወቅ፤ ከእሱም ጋር ሰላም ይኖርሃል፤

እንዲህ ካደረግክ መልካም ነገሮች ታገኛለህ።

22 ሕጉን ከአፉ ተቀበል፤

ቃሉንም በልብህ አኑር።+

23 ሁሉን ቻይ ወደሆነው አምላክ ብትመለስ ትታደሳለህ፤+

ክፋትን ከድንኳንህ ብታርቅ፣

24 ወርቅህን* አፈር ውስጥ፣

የኦፊርንም ወርቅ+ ዓለታማ ሸለቆ* ውስጥ ብትጥል፣

25 ያን ጊዜ ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ወርቅና*

ጥራት ያለው ብር ይሆንልሃል።

26 በዚህ ጊዜ ሁሉን ቻይ በሆነው አምላክ ደስ ትሰኛለህና፤

ፊትህንም ወደ አምላክ ቀና ታደርጋለህ።

27 ትለምነዋለህ፤ እሱም ይሰማሃል፤

ስእለትህንም ትፈጽማለህ።

28 ለማድረግ ያሰብከው ነገር ሁሉ ይሳካልሃል፤

በመንገድህም ላይ ብርሃን ይበራል።

29 በእብሪት ስትናገር ትዋረዳለህና፤

ትሑት የሆነውን* ግን ያድነዋል።

30 እሱ ንጹሕ የሆኑትን ያድናል፤

ስለዚህ እጅህ ንጹሕ ከሆነ በእርግጥ ትድናለህ።”

23 ኢዮብ እንዲህ ሲል መለሰ፦

 2 “ዛሬም እንኳ ብሶት ማሰማቴን አላቆምም፤*+

ከመቃተቴ የተነሳ ኃይሌ ተሟጠጠ።

 3 አምላክን የት እንደማገኘው ባወቅኩ!+

ወደሚኖርበት ስፍራ እሄድ ነበር።+

 4 ጉዳዬን በፊቱ አቀርብ፣

አፌንም በሙግት እሞላ ነበር፤

 5 እሱ እንዴት እንደሚመልስልኝ ባወቅኩ፣

የሚለኝንም ባስተዋልኩ ነበር።

 6 ታላቅ ኃይሉን ተጠቅሞ ከእኔ ጋር ይሟገት ይሆን?

በፍጹም! ይልቁንም ያዳምጠኛል።+

 7 ያን ጊዜ ቅን የሆነው ሰው ከአምላክ ጋር ስምምነት መፍጠር ይችላል፤

ፈራጄም እኔን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በነፃ ይለቀኛል።

 8 ይሁንና ወደ ምሥራቅ ብሄድ እሱ በዚያ የለም፤

ተመልሼ ብመጣም ላገኘው አልችልም።

 9 በስተ ግራ ሆኖ ሲሠራ ላየው አልችልም፤

ከዚያም ወደ ቀኝ ይዞራል፤ በዚህ ጊዜም ቢሆን አላየውም።

10 እሱ ግን የሄድኩበትን መንገድ ያውቃል።+

ከፈተነኝ በኋላ እንደጠራ ወርቅ እሆናለሁ።+

11 እግሬ የእሱን ዱካ በጥብቅ ተከትሏል፤

ምንም ፈቀቅ ሳልል መንገዱን ጠብቄአለሁ።+

12 ከከንፈሩ ትእዛዝ አልራቅኩም።

የተናገረውን ቃል ከሚጠበቅብኝ* በላይ ከፍ አድርጌ ተመልክቻለሁ።+

13 ቆርጦ ከተነሳ ማን ሊቃወመው ይችላል?+

እሱ አንድ ነገር ማድረግ ከፈለገ* ከማድረግ ወደኋላ አይልም።+

14 በእኔ ላይ የተወሰነውን* ሙሉ በሙሉ ይፈጽማልና፤

እንደዚህ ያሉ ብዙ ነገሮችም በእሱ ዘንድ አሉ።

15 በእሱ የተነሳ የተጨነቅኩት ለዚህ ነው፤

ስለ እሱ ሳስብ ይበልጥ ፍርሃት ያድርብኛል።

16 አምላክ ራሱ ፈሪ አድርጎኛል፤

ሁሉን ቻይ የሆነውም አምላክ አስደንግጦኛል።

17 ይሁን እንጂ ጨለማውም ሆነ

ፊቴን የሸፈነው ድቅድቅ ጨለማ ዝም አላሰኘኝም።

24 “ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ለምን ጊዜ አልወሰነም?+

እሱን የሚያውቁትስ ቀኑን* ለምን አያዩም?

 2 ሰዎች የወሰን ምልክቶችን ይገፋሉ፤+

ነጥቀው የወሰዱትን መንጋ በራሳቸው መስክ ላይ ያሰማራሉ።

 3 አባት የሌላቸውን ልጆች አህያ እየነዱ ይወስዳሉ፤

የመበለቲቱንም በሬ መያዣ አድርገው ይወስዳሉ።+

 4 ድሃውን ከመንገድ ያስወጣሉ፤

በዚህ ጊዜ የምድሪቱ ምስኪኖች ከእነሱ ለመሸሸግ ይገደዳሉ።+

 5 ድሆች በምድረ በዳ እንዳሉ የዱር አህዮች፣+ ምግብ ፍለጋ ይራወጣሉ፤

በበረሃ ለልጆቻቸው ምግብ ይፈልጋሉ።

 6 ከሌላው ሰው እርሻ እህል* ለመሰብሰብ ይገደዳሉ፤

ከክፉውም ሰው የወይን እርሻ ይቃርማሉ።

 7 ያለልብስ ራቁታቸውን ያድራሉ፤+

ብርድ የሚከላከሉበት ልብስ የላቸውም።

 8 ከተራሮች በሚወርደው ዝናብ ይበሰብሳሉ፤

መጠለያ ስለማያገኙ ዓለት ያቅፋሉ።

 9 አባት የሌለው ልጅ ከእናቱ ጡት ላይ ተነጥቋል፤+

የድሃውም ልብስ በመያዣነት ተወስዷል፤+

10 ያለልብስ ራቁታቸውን ለመሄድ ይገደዳሉ፤

ተርበው እያሉም ነዶ ተሸክመው ይሄዳሉ።

11 በቀትር ሐሩር በእርከኖቹ መካከል ይለፋሉ፤*

የወይን መጭመቂያውን እየረገጡ እነሱ ግን ይጠማሉ።+

12 በሞት አፋፍ ላይ ያሉት በከተማዋ ውስጥ ያጣጥራሉ፤

ክፉኛም የቆሰሉት ሰዎች* እርዳታ ለማግኘት ይጮኻሉ፤+

አምላክ ግን ይህን በቸልታ ያልፋል።*

13 በብርሃን ላይ የሚያምፁ አሉ፤+

የብርሃኑን መንገድ አላወቁም፤

ጎዳናውንም አልተከተሉም።

14 ነፍሰ ገዳዩ ጎህ ሲቀድ ይነሳል፤

ምስኪኑንና ድሃውን ይገድላል፤+

በሌሊትም ይሰርቃል።

15 የአመንዝራ ዓይን ድንግዝግዝታን ይጠባበቃል፤+

‘ማንም አያየኝም!’ ይላል፤+

ፊቱንም ይሸፍናል።

16 በጨለማ ቤት ሰብረው* ይገባሉ፤

ቀን ላይ ተሸሽገው ይውላሉ።

ለብርሃን እንግዳ ናቸው።+

17 ለእነሱ ንጋት እንደ ድቅድቅ ጨለማ ነውና፤

ድቅድቅ ጨለማ የሚያስከትለውን ሽብር ያውቁታል።

18 ይሁንና ውኃ በፍጥነት ጠርጎ ይወስዳቸዋል።*

ርስታቸውም የተረገመ ይሆናል።+

ወደ ወይን እርሻቸው አይመለሱም።

19 ድርቁና ሐሩሩ የቀለጠውን በረዶ እንደሚያስወግደው፣

መቃብር* ኃጢአተኞችን ይነጥቃል!+

20 እናቱ* ትረሳዋለች፤ ትልም ትመጠምጠዋለች።

ዳግመኛ አይታወስም።+

ክፋትም እንደ ዛፍ ይሰበራል።

21 በመሃኒቱ ላይ ያደባል፤

መበለቲቱንም ይበድላል።

22 አምላክ* ኃይሉን ተጠቅሞ ብርቱ ሰዎችን ያጠፋል፤

ከፍ ከፍ ቢሉም ሕይወታቸው ዋስትና የለውም።

23 አምላክ* የመተማመን ስሜት እንዲያድርባቸውና ደህንነት እንዲሰማቸው ይፈቅዳል፤+

ይሁንና ዓይኑ በሚያደርጉት ነገር ሁሉ* ላይ ነው።+

24 ለጥቂት ጊዜ ከፍ ከፍ ይላሉ፤ ከዚያም ደብዛቸው ይጠፋል።+

ዝቅ ዝቅ ይደረጋሉ፤+ ደግሞም እንደ ማንኛውም ሰው ይሰበሰባሉ፤

እንደ እህል ዛላ ይቆረጣሉ።

25 እንግዲህ አሁን እኔን ውሸታም ሊያደርገኝ፣

ወይም ቃሌን ሊያስተባብል የሚችል ማን ነው?”

25 ሹሃዊው በልዳዶስ+ እንዲህ ሲል መለሰ፦

 2 “የመግዛት ሥልጣንና አስፈሪ ኃይል የእሱ ነው፤

በሰማይ* ሰላምን ያሰፍናል።

 3 የሠራዊቱ ብዛት ሊቆጠር ይችላል?

የእሱ ብርሃን የማያበራበት ማን አለ?

 4 ታዲያ ሟች የሆነ ሰው በአምላክ ፊት እንዴት ጻድቅ ሊሆን ይችላል?+

ወይስ ከሴት የተወለደ ሰው እንዴት ንጹሕ* ሊሆን ይችላል?+

 5 ጨረቃ እንኳ ብሩህ አይደለችም፤

ከዋክብትም በእሱ ፊት ንጹሕ አይደሉም፤

 6 እጭ የሆነው ሟች የሰው ልጅ፣

ትል የሆነው ሰውማ ምንኛ የባሰ ይሆን!”

26 ኢዮብ እንዲህ ሲል መለሰ፦

 2 “ኃይል የሌለውን ምንኛ ረዳኸው!

ብርታት የሌለውን ክንድ ምንኛ አዳንከው!+

 3 ጥበብ ለሌለው እንዴት ያለ ታላቅ ምክር ሰጠኸው!+

የጥበብህን* ብዛት* ምንኛ ገለጥክ!

 4 ለማን ለመናገር እየሞከርክ ነው?

እንዲህ ያለ ነገር እንድትናገር የገፋፋህስ ማን ነው?*

 5 በሞት የተረቱት ይንቀጠቀጣሉ፤

ከውኃዎችና በውስጣቸው ከሚኖሩት እንኳ በታች ናቸው።

 6 መቃብር* በአምላክ* ፊት የተራቆተ ነው፤+

የጥፋትም ስፍራ* አይሸፈንም።

 7 የሰሜኑን ሰማይ* በባዶ ስፍራ* ላይ ዘርግቷል፤+

ምድርንም ያለምንም ነገር አንጠልጥሏል፤

 8 ውኃዎችን በደመናቱ ውስጥ ይጠቀልላል፤+

ከክብደታቸውም የተነሳ ደመናቱ አይቀደዱም፤

 9 ደመናውን በላዩ ላይ በመዘርጋት፣

ዙፋኑን ይጋርዳል።+

10 በውኃዎቹ ገጽ ላይ አድማሱን* ያበጃል፤+

በብርሃንና በጨለማ መካከል ወሰን ያደርጋል።

11 የሰማይ ዓምዶች ተናጉ፤

ከተግሣጹም የተነሳ ደነገጡ።

12 ባሕሩን በኃይሉ ያናውጣል፤+

በማስተዋሉም ግዙፉን የባሕር ፍጥረት* ይቆራርጣል።+

13 በእስትንፋሱ* ሰማያትን ያጠራል፤

እጁ የማይጨበጠውን* እባብ ትወጋለች።

14 እነሆ፣ እነዚህ የመንገዱ ዳር ዳር ናቸው፤+

ስለ እሱ የሰማነው የሹክሹክታ ያህል ብቻ ነው!

ታዲያ ኃይለኛ የሆነውን ነጎድጓዱን ማን ሊያስተውል ይችላል?”+

27 ኢዮብ ንግግሩን* በመቀጠል እንዲህ አለ፦

 2 “ፍትሕ በነፈገኝ ሕያው በሆነው አምላክ፣+

እንድመረር ባደረገኝ*+ ሁሉን ቻይ በሆነው አምላክ እምላለሁ፤

 3 እስትንፋሴ በውስጤ፣

ከአምላክ ያገኘሁትም መንፈስ በአፍንጫዬ ውስጥ እስካለ ድረስ፣+

 4 ከንፈሮቼ ክፋት አይናገሩም፤

ምላሴም ፈጽሞ የማታለያ ቃል አይወጣውም!

 5 በእኔ በኩል እናንተን ጻድቅ አድርጎ መቁጠር የማይታሰብ ነገር ነው!

እስክሞት ድረስ ንጹሕ አቋሜን* አላጎድፍም!*+

 6 ጽድቄን አጥብቄ እይዛለሁ፤ ደግሞም ፈጽሞ አለቀውም፤+

በሕይወት ዘመኔም ሁሉ* ልቤ አይኮንነኝም።*

 7 ጠላቴ እንደ ክፉ ሰው ይሁን፤

እኔን የሚያጠቁኝ ሰዎች እንደ ዓመፀኛ ይሁኑ።

 8 አምላክ የለሽ የሆነ* ሰው ሲጠፋ፣

አምላክ ሕይወቱን* ሲቀጨው ምን ተስፋ ይኖረዋል?+

 9 መከራ ሲደርስበት

አምላክ ጩኸቱን ይሰማዋል?+

10 ወይስ ሁሉን ቻይ በሆነው አምላክ ደስ ይሰኛል?

ሁልጊዜስ ወደ አምላክ ይጣራል?

11 እኔ ስለ አምላክ ኃይል* አስተምራችኋለሁ፤

ሁሉን ቻይ ስለሆነው አምላክ ምንም የምደብቀው ነገር የለም።

12 ሁላችሁም ራእይ ካያችሁ፣

ንግግራችሁ ጨርሶ ባዶ የሆነው ለምንድን ነው?

13 ክፉ ሰው ከአምላክ የሚያገኘው ድርሻ፣+

ጨቋኞችም ሁሉን ቻይ ከሆነው አምላክ የሚወርሱት ውርሻ ይህ ነው።

14 ልጆቹ ቢበዙ በሰይፍ ይወድቃሉ፤+

ዘሮቹም በቂ ምግብ አያገኙም።

15 ከእሱ በኋላ የተረፉት ወገኖቹ በመቅሰፍት ይቀበራሉ፤

መበለቶቻቸውም አያለቅሱላቸውም።

16 ብርን እንደ አፈር ቢቆልል፣

ልብስንም እንደ ሸክላ ጭቃ ቢያከማች እንኳ፣

17 እሱ የሰበሰበውን

ጻድቁ ሰው ይለብሰዋል፤+

ብሩንም ንጹሐን ይከፋፈሉታል።

18 የሚሠራው ቤት ብል እንደሠራው ሽፋን፣

ጠባቂም እንደቀለሰው መጠለያ+ በቀላሉ የሚፈርስ ነው።

19 ባለጸጋ ሆኖ ይተኛል፤ ሆኖም ምንም የሚሰበስበው ነገር የለም፤

ዓይኑን ሲገልጥ በዚያ ምንም ነገር አይኖርም።

20 ሽብር እንደ ጎርፍ ድንገት ያጥለቀልቀዋል፤

አውሎ ነፋስ በሌሊት ይዞት ይሄዳል።+

21 የምሥራቅ ነፋስ ይወስደዋል፤ እሱም አይገኝም፤

ከቦታው ጠርጎ ይወስደዋል።+

22 ከነፋሱ ኃይል ለማምለጥ ሲፍጨረጨር፣+

ያለርኅራኄ ተወርውሮ ይመጣበታል።+

23 እጁን ያጨበጭብበታል፤

ደግሞም ካለበት ቦታ ሆኖ ያፏጭበታል።*+

28 “ብር የሚወጣበት ቦታ፣

ወርቅም የሚነጠርበት ስፍራ አለ፤+

 2 ብረት ከመሬት ውስጥ ይገኛል፤

መዳብም ከዓለት ቀልጦ ይወጣል።*+

 3 ሰው ጨለማን ያሸንፋል፤

ማዕድን* ለማግኘት

በጨለማና በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ እስከ ወሰኑ ድረስ ፍለጋ ያካሂዳል።

 4 ሰዎች ከሚኖሩበት ክልል ርቆ በሚገኝ ስፍራ፣

ሰዎች ከሚመላለሱበት አካባቢ ርቀው በሚገኙ የተረሱ ቦታዎች ጥልቅ ጉድጓድ ይቆፍራል፤

አንዳንድ ሰዎች በገመድ ወደዚያ ይወርዳሉ፤ ተንጠልጥለውም ይሠራሉ።

 5 በምድር ላይ እህል ይበቅላል፤

ከታች ግን ምድር በእሳት የሆነ ያህል ትታመሳለች።*

 6 በዚያ በድንጋዮቹ ውስጥ ሰንፔር ይገኛል፤

በአፈሩም ውስጥ ወርቅ አለ።

 7 ወደዚያ የሚወስደውን መንገድ የትኛውም አዳኝ አሞራ አያውቀውም፤

የጥቁር ጭልፊትም ዓይን አላየውም።

 8 ግርማ የተላበሱ አራዊት አልረገጡትም፤

ብርቱ አንበሳም በዚያ አላደባም።

 9 ሰው የባልጩት ድንጋይ በእጁ ይመታል፤

ተራሮችንም ከሥር መሠረታቸው ይገለብጣል።

10 በዓለት ውስጥ የውኃ ቦዮች ይሠራል፤+

ዓይኑም ውድ የሆኑ ነገሮችን ሁሉ ያያል።

11 ወንዞች የሚፈልቁባቸውን ቦታዎች ይገድባል፤

የተሰወረውንም ነገር ወደ ብርሃን ያወጣል።

12 ይሁንና ጥበብ የት ልትገኝ ትችላለች?+

ማስተዋል የሚገኘውስ ከየት ነው?+

13 ማንም ሰው ዋጋዋን አይገነዘብም፤+

በሕያዋንም ምድር ልትገኝ አትችልም።

14 ጥልቁ ውኃ ‘እኔ ውስጥ የለችም!’ ይላል፤

ባሕሩም ‘በእኔ ዘንድ አይደለችም!’ ይላል።+

15 እሷን በንጹሕ ወርቅ መግዛት አይቻልም፤

በብርም ልትለወጥ አትችልም።+

16 በኦፊር ወርቅም+ ሆነ

ብርቅ በሆነው ኦኒክስና በሰንፔር ልትገዛ አትችልም።

17 ወርቅና መስተዋት* ከእሷ ጋር ሊወዳደሩ አይችሉም፤

ምርጥ ከሆነ* ወርቅ በተሠራ ዕቃም እሷን መለወጥ አይቻልም።+

18 ዛጎልና ክሪስታል ጨርሶ አይወዳደሯትም፤+

ጥበብ በከረጢት ሙሉ ካለ ዕንቁ ትበልጣለችና።

19 የኢትዮጵያ* ቶጳዝዮን+ ከእሷ ጋር ሊወዳደር አይችልም፤

በንጹሕ ወርቅ እንኳ እሷን መግዛት አይቻልም።

20 ታዲያ ጥበብ ከየት ትመጣለች?

ማስተዋል የሚገኘውስ ከየት ነው?+

21 ከሕያዋን ፍጥረታት ሁሉ ዓይን ተሰውራለች፤+

በሰማያት ከሚበርሩ ወፎችም ተሸሽጋለች።

22 ጥፋትና ሞት፣

‘ወሬዋን ብቻ በጆሯችን ሰምተናል’ ይላሉ።

23 ወደ እሷ የሚወስደውን መንገድ የሚረዳው አምላክ ነው፤

መኖሪያዋን የሚያውቀው እሱ ብቻ ነው፤+

24 እሱ እስከ ምድር ዳርቻ ይመለከታልና፤

ከሰማያትም በታች ያለውን ሁሉ ያያል።+

25 የነፋስን ኃይል* በወሰነ ጊዜ፣+

ውኃዎችንም በለካ ጊዜ፣+

26 ለዝናብ ሥርዓትን ባወጣ ጊዜ፣+

ነጎድጓድ ለቀላቀለ ጥቁር ደመና መንገድን ባዘጋጀ ጊዜ፣+

27 ያኔ ጥበብን አያት፤ ደግሞም ገለጻት፤

መሠረታት፤ እንዲሁም መረመራት።

28 ሰውንም እንዲህ አለው፦

‘እነሆ፣ ይሖዋን መፍራት ጥበብ ነው፤+

ከክፉም መራቅ ማስተዋል ነው።’”+

29 ኢዮብ ንግግሩን* በመቀጠል እንዲህ አለ፦

 2 “የቀድሞዎቹን ወራት፣

አምላክ ለእኔ ጥበቃ ያደርግ የነበረበትን ዘመን ተመኘሁ!

 3 ያን ጊዜ መብራቱን በራሴ ላይ ያበራ፣

በእሱም ብርሃን፣ በጨለማ ውስጥ እሄድ ነበር፤+

 4 ያኔ የወጣትነት ብርታት ነበረኝ፤

አምላክ የቅርብ ወዳጄ ሆኖ በድንኳኔ ይገኝ ነበር፤+

 5 ሁሉን ቻይ አምላክ ከእኔ ጋር ነበር፤

ልጆቼም* በዙሪያዬ ነበሩ፤

 6 መንገዴ በቅቤ የራሰ ነበር፤

ዓለቱም ዘይት ያንዶለዱልልኝ ነበር።+

 7 ወደ ከተማዋ በር እሄድ፣+

በአደባባይዋም እቀመጥ ነበር፤+

 8 ወጣቶች ሲያዩኝ መንገድ ይለቁልኝ፣*

ሽማግሌዎችም እንኳ ተነስተው ይቆሙ ነበር።+

 9 መኳንንት ከመናገር ይቆጠቡ፣

እጃቸውንም በአፋቸው ላይ ይጭኑ ነበር።

10 የታላላቆቹ ሰዎች ድምፅ አይሰማም ነበር፤

ምላሳቸውም ከላንቃቸው ጋር ይጣበቅ ነበር።

11 ስናገር የሰማ ሁሉ ያሞግሰኝ፣

ያዩኝ ሰዎችም ይመሠክሩልኝ ነበር።

12 ለእርዳታ የሚጮኸውን ድሃ፣

አባት የሌለውን ልጅና ረዳት የሌለውን ሁሉ እታደግ ነበርና።+

13 ሊጠፋ ተቃርቦ የነበረው ይባርከኝ ነበር፤+

የመበለቲቱንም ልብ ደስ አሰኝ ነበር።+

14 ጽድቅን እንደ ልብስ ለበስኩ፤

የፍትሕ አቋሜ እንደ ቀሚስና* እንደ ጥምጥም ሆነልኝ።

15 ለዓይነ ስውሩ ዓይን፣

ለአንካሳውም እግር ነበርኩ።

16 ለድሃው አባት ነበርኩ፤+

የማላውቃቸውን ሰዎች ሙግት እመረምር ነበር።+

17 የክፉ አድራጊውን መንጋጋ እሰብር፣+

አድኖ የያዘውንም ከጥርሱ አስጥል ነበር።

18 እንዲህ እል ነበር፦ ‘በገዛ ቤቴ* እሞታለሁ፤+

የሕይወት ዘመኔም እንደ አሸዋ ይበዛል።

19 ሥሮቼ ወደ ውኃ ይዘረጋሉ፤

ጠልም ሌሊቱን ሙሉ በቅርንጫፎቼ ላይ ያድራል።

20 ክብሬ ሁልጊዜ ይታደሳል፤

በእጄም ያለው ደጋን ደጋግሞ ይወነጭፋል።’

21 ሰዎች በጉጉት ያዳምጡኝ፣

ምክሬንም ጸጥ ብለው ይጠባበቁ ነበር።+

22 እኔ ከተናገርኩ በኋላ የሚጨምሩት ነገር አልነበረም፤

ቃሌም በጆሯቸው ይንቆረቆር* ነበር።

23 ዝናብ እንደሚጠባበቁ ሰዎች እኔን ተጠባበቁ፤

ቃሌንም እንደ በልግ ዝናብ+ ጠጡ።

24 በፈገግታ ባየኋቸው ጊዜ ማመን አቃታቸው፤

የፊቴ ብርሃን ያጽናናቸው ነበር።*

25 እንደ መሪያቸው ሆኜ አመራር ሰጠኋቸው፤

በወታደሮቹ መካከል እንዳለ ንጉሥ፣+

ሐዘንተኞችንም እንደሚያጽናና ሰው ሆኜ ኖርኩ።+

30 “አሁን ግን ከእኔ በዕድሜ የሚያንሱ፣

በእኔ ላይ ይስቃሉ፤+

አባቶቻቸው መንጋዬን ከሚጠብቁ ውሾች ጋር እንዲሆኑ

ፈቃደኛ አልነበርኩም።

 2 የእጃቸው ብርታት ለእኔ ምን ይፈይድልኝ ነበር?

እነሱ ጉልበት ከድቷቸዋል።

 3 ከችጋርና ከረሃብ የተነሳ ዝለዋል፤

በወደመ እና ወና በሆነ ደረቅ ምድር

ያገኟትን ነገር ያላምጣሉ።

 4 በቁጥቋጦዎች አጠገብ ያለውን ጨው ጨው የሚል ተክል ይሰበስባሉ፤

ምግባቸው የክትክታ ዛፍ ሥር ነው።

 5 ከማኅበረሰቡ ተባረዋል፤+

ሰዎችም ሌባ ላይ እንደሚጮኹ ይጮኹባቸዋል።

 6 በሸለቆዎች* ተዳፋት ላይ፣

መሬት ላይ ባሉ ጉድጓዶች ውስጥና በዓለቶች መካከል ይኖራሉ።

 7 ከቁጥቋጦዎች ውስጥ ይጮኻሉ፤

በሳማዎችም መካከል ይከማቻሉ።

 8 ማመዛዘን የጎደላቸውና የአልባሌ ሰዎች ልጆች ናቸው፤

ከምድሪቱ ላይ ተባረዋል።*

 9 አሁን ግን በዘፈኖቻቸው ሳይቀር ይሳለቁብኛል፤+

የእነሱ መሳለቂያ* ሆኛለሁ።+

10 ይጸየፉኛል፤ ከእኔም ርቀዋል፤+

በፊቴ ከመትፋት ወደኋላ አይሉም።+

11 ምክንያቱም አምላክ ትጥቅ አስፈትቶኛል፤* ደግሞም አዋርዶኛል፤

እነሱ በፊቴ እንዳሻቸው ይሆናሉ።*

12 በቀኜ በኩል እንደ አድመኛ ተነስተውብኛል፤

እንድሸሽ አድርገውኛል፤

በመንገዴም ላይ ለጥፋት የሚዳርግ መሰናክል አስቀምጠዋል።

13 መንገዶቼን ያፈርሳሉ፤

መከራዬንም ያባብሳሉ፤+

የሚገታቸውም የለም።*

14 ሰፊ ክፍተት ባለው ቅጥር እንደሚመጣ ሰው መጡ፤

በፍርስራሹ መካከል እየገሰገሱ ገቡ።

15 በሽብር ተዋጥኩ፤

ክብሬ በነፋስ እንደሚወሰድ ተወስዷል፤

የመዳን ተስፋዬም እንደ ደመና እልም ብሎ ጠፍቷል።

16 አሁን ሕይወቴ* ከውስጤ ተሟጠጠች፤+

የጉስቁልና ዘመን+ ያዘኝ።

17 ከባድ ሕመም በሌሊት አጥንቶቼን ይበሳል፤*+

የሚመዘምዘኝ ሥቃይ እረፍት አይሰጠኝም።+

18 ልብሴ በታላቅ ኃይል ተበላሸ፤*

እንደ ልብሴ አንገትጌ አንቆ ያዘኝ።

19 አምላክ ጭቃ ውስጥ ጥሎኛል፤

አፈርና አመድ ሆንኩ።

20 እርዳታ ለማግኘት ወደ አንተ እጮኻለሁ፤ አንተ ግን አትመልስልኝም፤+

በፊትህ ቆምኩ፤ አንተ ግን ዝም ብለህ ታየኛለህ።

21 በጭካኔ በእኔ ላይ ተነሳህ፤+

በእጅህ ብርታት አጠቃኸኝ።

22 ወደ ላይ አንስተህ በነፋስ ወሰድከኝ፤

ከዚያም በአውሎ ነፋስ አንገላታኸኝ።*

23 በሕይወት ያለ ሁሉ ወደሚሰበሰብበት ቤት፣

ወደ ሞት እንደምታወርደኝ አውቃለሁና።

24 ይሁንና የተሰበረ ሰው አደጋ ደርሶበት ለእርዳታ ሲጮኽ፣

እጁን የሚያነሳበት ሰው አይኖርም።*+

25 መከራ ላይ ለወደቁ ሰዎች* አላለቀስኩም?

ለድሃውስ አላዘንኩም?*+

26 መልካም ነገር በተስፋ ብጠባበቅም ክፉ ነገር ደረሰ፤

ብርሃን ብጠባበቅም ጨለማ መጣ።

27 ውስጤ ያለማቋረጥ ተናወጠ፤

የጉስቁልናም ዘመን መጣብኝ።

28 በሐዘን ተውጬ እመላለሳለሁ፤+ የፀሐይ ብርሃንም የለም።

በጉባኤ መካከል ቆሜ እርዳታ ለማግኘት እጮኻለሁ።

29 የቀበሮዎች ወንድም፣

የሰጎንም ሴቶች ልጆች ባልንጀራ ሆንኩ።+

30 ቆዳዬ ጠቁሮ ተቀረፈ፤+

ከሙቀቱ* የተነሳ አጥንቶቼ ነደዱ።

31 በገናዬ ለሐዘን ብቻ ዋለ፤

ዋሽንቴም* ለለቅሶ ሆነ።

31 “ከዓይኔ ጋር ቃል ኪዳን ገብቻለሁ።+

ታዲያ ለድንግሊቱ ተገቢ ያልሆነ ትኩረት እንዴት እሰጣለሁ?+

 2 ለመሆኑ ከላይ ከአምላክ የማገኘው ድርሻ ምንድን ነው?

ከፍ ባለ ስፍራ ከሚኖረው ሁሉን ቻይ አምላክ የማገኘውስ ውርሻ ምንድን ነው?

 3 በደለኛ ሰው ጥፋት፣

ክፉ ነገር የሚያደርጉስ መቅሰፍት አይደርስባቸውም?+

 4 እሱ መንገዴን ሁሉ አያይም?+

እርምጃዬንስ ሁሉ አይቆጥርም?

 5 በውሸት ጎዳና ተመላልሼ* አውቃለሁ?

እግሬ ለማታለል ተጣድፎ ያውቃል?+

 6 አምላክ በትክክለኛ ሚዛን ይመዝነኝ፤+

ያን ጊዜ ንጹሕ አቋም* እንዳለኝ ይገነዘባል።+

 7 እርምጃዬ ከመንገዱ ወጣ ብሎ፣+

ወይም ልቤ ዓይኔን ተከትሎ፣+

አሊያም እጄ ረክሶ ከሆነ፣

 8 የዘራሁትን ዘር ሌላ ይብላው፤+

የተከልኩትም ይነቀል።*

 9 ልቤ ሌላ ሴት ከጅሎ፣+

በባልንጀራዬም ደጃፍ ላይ አድብቼ ከሆነ፣+

10 ሚስቴ ለሌላ ሰው እህል ትፍጭ፤

ሌሎች ወንዶችም ከእሷ ጋር ይተኙ።*+

11 ይህ አሳፋሪ ምግባር፣

ደግሞም በዳኞች ሊያስቀጣ የሚገባ በደል በሆነ ነበርና።+

12 ይህ የሚያጠፋና የሚደመስስ፣*

የፍሬዬንም ሥር ሁሉ የሚፈጅ* እሳት በሆነ ነበር።+

13 ወንድ ባሪያዬ ወይም ሴት ባሪያዬ በእኔ ላይ አቤቱታ* ባቀረቡ ጊዜ

ፍትሕ ነፍጌ ከሆነ፣

14 አምላክ ሲከራከረኝ* ምን ማድረግ እችላለሁ?

ሲጠይቀኝስ ምን መልስ እሰጣለሁ?+

15 እኔን በማህፀን ውስጥ የሠራኝ እነሱንስ አልሠራም?+

ከመወለዳችን በፊት* የሠራን እሱ ራሱ አይደለም?+

16 ድሃ የሆኑ ሰዎች የፈለጉትን ነገር ነፍጌ፣+

ወይም የመበለቲቱ ዓይን እንዲያዝን* አድርጌ ከሆነ፣+

17 ወላጅ አልባ ለሆኑ ልጆች ሳላካፍል፣

የራሴን ምግብ ብቻዬን በልቼ ከሆነ፣+

18 (ወላጅ አልባ የሆነውን ልጅ* ከወጣትነቴ ጀምሮ እንደ አባት ሆኜ አሳድጌዋለሁና፤

ከልጅነቴም* አንስቶ መበለቲቱን* ስመራት ቆይቻለሁ።)

19 ሰው የሚለብሰው አጥቶ በብርድ ሲያልቅ፣

ወይም ድሃው ሲታረዝ አይቼ ከሆነ፣+

20 ከጠቦቶቼ የተሸለተውን ፀጉር ለብሶ በሞቀው ጊዜ፣

ሳይባርከኝ ቀርቶ ከሆነ፣+

21 በከተማዋ በር+ ላይ የእኔን እርዳታ በሚፈልግ ወላጅ አልባ ልጅ ላይ*

እጄን በዛቻ አወዛውዤ ከሆነ፣+

22 ክንዴ* ከትከሻዬ ይውለቅ፤

ክንዴም ከክርኔ* ይሰበር።

23 ከአምላክ የሚመጣ ጥፋት ያስፈራኛልና፤

በግርማውም ፊት መቆም አልችልም።

24 ወርቅን መታመኛዬ አድርጌ፣

ወይም ምርጥ የሆነውን ወርቅ ‘አንተ መመኪያዬ ነህ!’ ብዬ ከሆነ፣+

25 ታላቅ ሀብት በማፍራቴ፣

እንዲሁም ብዙ ንብረት በማግኘቴ ደስ ብሎኝ ከሆነ፣+

26 ፀሐይ ስትፈነጥቅ፣*

ወይም ጨረቃ ግርማ ተላብሳ ስትሄድ አይቼ ከሆነ፣+

27 ልቤ በስውር ተታሎ፣

አፌም ለእነሱ አምልኮ ለማቅረብ እጄን ስሞ ከሆነ፣+

28 ይህ በዳኞች ሊያስቀጣ የሚገባ በደል በሆነ ነበር፤

በላይ ያለውን እውነተኛውን አምላክ መካድ ይሆንብኝ ነበርና።

29 ጠላቴ በደረሰበት ጥፋት ደስ ብሎኝ ያውቃል?+

ወይስ ክፉ ነገር ስለደረሰበት ሐሴት አድርጌ አውቃለሁ?

30 በእርግማን ሕይወቱን* በመሻት፣

አንደበቴ ኃጢአት እንዲሠራ አልፈቀድኩም።+

31 በድንኳኔ የሚኖሩ ሰዎች

‘እሱ ካቀረበው ምግብ* በልቶ ያልጠገበ ሰው ማግኘት የሚችል ማን አለ?’ አላሉም?+

32 አንድም እንግዳ* ደጅ አያድርም ነበር፤+

ቤቴን ለመንገደኛ እከፍት ነበር።

33 በደሌን በልብሴ ኪስ በመሸሸግ፣

እንደ ሌሎች ሰዎች ጥፋቴን ለመሸፋፈን ሞክሬ አውቃለሁ?+

34 የብዙ ሰዎችን ምላሽ በመፍራት፣

ወይም በሌሎች ቤተሰቦች ንቀት በመሸበር፣

ዝም ብያለሁ? ደግሞስ ወደ ውጭ መውጣት ፈርቻለሁ?

35 ምነው የሚሰማኝ ባገኘሁ!+

በተናገርኩት ነገር ላይ ስሜን አሰፍር ነበር።*

ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ መልስ ይስጠኝ!+

ምነው ከሳሼ ክሱን በሰነድ ላይ ባሰፈረ ኖሮ!

36 በትከሻዬ እሸከመው ነበር፤

እንደ አክሊልም በራሴ ላይ አስረው ነበር።

37 የወሰድኩትን እያንዳንዱን እርምጃ ባሳወቅኩት ነበር፤

እንደ አለቃ በልበ ሙሉነት ወደ እሱ እቀርብ ነበር።

38 እርሻዬ በእኔ ላይ ጮኻ፣

ትልሞቿም በአንድ ላይ አልቅሰው ከሆነ፣

39 ፍሬዋን ያለዋጋ በልቼ፣+

ባለቤቶቿንም* አሳዝኜ ከሆነ፣+

40 በስንዴ ፋንታ እሾህ፣

በገብስም ምትክ የሚገማ አረም ይብቀልብኝ።”

የኢዮብ ቃል እዚህ ላይ ተፈጸመ።

32 ኢዮብ ጻድቅ ነኝ የሚል ጽኑ እምነት ስለነበረው፣*+ እነዚህ ሦስት ሰዎች ለእሱ መልስ መስጠታቸውን አቆሙ። 2 ይሁን እንጂ ከራም ወገን የሆነው የቡዛዊው+ የባራክኤል ልጅ ኤሊሁ እጅግ ተቆጣ። ከአምላክ ይልቅ ራሱን* ጻድቅ ለማድረግ ስለሞከረ+ በኢዮብ ላይ ቁጣው ነደደ። 3 በተጨማሪም ሦስቱ የኢዮብ ወዳጆች መልስ መስጠት ባለመቻላቸው፣ ይልቁንም አምላክን ክፉ በማድረጋቸው+ በእነሱም ላይ እጅግ ተቆጣ። 4 ኤሊሁ በዕድሜ ይበልጡት ስለነበር፣ ተናግረው እስኪጨርሱ ድረስ ለኢዮብ ምንም መልስ ሳይሰጥ ሲጠብቅ ቆየ።+ 5 ኤሊሁ ሦስቱ ሰዎች መልስ መስጠት እንደተሳናቸው ባየ ጊዜ ቁጣው ነደደ። 6 በመሆኑም የቡዛዊው የባራክኤል ልጅ ኤሊሁ እንዲህ ሲል መናገር ጀመረ፦

“እኔ በዕድሜ ትንሽ ነኝ፤*

እናንተ ግን ትላልቆች ናችሁ።+

ለእናንተ ካለኝ አክብሮት የተነሳ ከመናገር ዝም አልኩ፤+

ደግሞም የማውቀውን ለመናገር አልደፈርኩም።

 7 እኔም ‘ዕድሜ ይናገር፤*

ረጅም ዘመንም ጥበብን ያሳውቅ’ ብዬ አስቤ ነበር።

 8 ሆኖም ለሰዎች ማስተዋል የሚሰጠው በውስጣቸው ያለው መንፈስ፣

ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ እስትንፋስ ነው።+

 9 ዕድሜ* በራሱ ሰውን ጥበበኛ አያደርገውም፤

ትክክለኛውን ነገር የሚያስተውሉትም በዕድሜ የገፉ ሰዎች ብቻ አይደሉም።+

10 ስለዚህ ‘እኔን ስማኝ፤

እኔም የማውቀውን እነግርሃለሁ’ አልኩ።

11 እነሆ፣ እናንተ የተናገራችሁትን በትዕግሥት ሳዳምጥ ቆይቻለሁ፤

የምትናገሩትን ነገር አውጥታችሁ አውርዳችሁ፣+

ሐሳባችሁን በምትገልጹበት ጊዜ በትኩረት ስሰማ ነበር።+

12 ልብ ብዬ አዳመጥኳችሁ፤

ሆኖም አንዳችሁም ኢዮብ መሳሳቱን ማስረዳት፣*

ወይም ላቀረበው የመከራከሪያ ሐሳብ መልስ መስጠት አልቻላችሁም።

13 ስለሆነም ‘እኛ ጥበብ አለን፤

እሱ መሳሳቱን የሚነግረው አምላክ እንጂ ሰው አይደለም’ አትበሉ።

14 እሱ በእኔ ላይ የተናገረው ነገር የለም፤

በመሆኑም እንደ እናንተ አልመልስለትም።

15 እነሱ ተሸብረዋል፤ መልስ መስጠትም ተስኗቸዋል፤

የሚናገሩትም ጠፍቷቸዋል።

16 እኔ ጠበቅኳቸው፤ እነሱ ግን ንግግራቸውን መቀጠል አልቻሉም፤

ከዚህ በላይ መልስ መስጠት አቅቷቸው ዝም ብለው ቆመዋል።

17 ስለዚህ እኔም መልስ እሰጣለሁ፤

የማውቀውንም እናገራለሁ፤

18 ብዙ የምናገረው ነገር አለኝና፤

በውስጤ ያለው መንፈስ ገፋፍቶኛል።

19 ውስጤ መተንፈሻ እንዳጣ የወይን ጠጅ፣

ሊፈነዳ እንደተቃረበ አዲስ አቁማዳ ሆኗል።+

20 እፎይታ እንዳገኝ እስቲ ልናገር!

አፌንም ከፍቼ መልስ እሰጣለሁ።

21 ለማንም ፈጽሞ አላዳላም፤+

ማንንም ሰው አልሸነግልም፤*

22 ሰውን መሸንገል አላውቅበትምና፤

እንደዛ ባደርግ ፈጣሪዬ ወዲያውኑ ባስወገደኝ ነበር።

33 “አሁን ግን ኢዮብ፣ እባክህ ቃሌን ስማ፤

የምናገረውንም ሁሉ አዳምጥ።

 2 እባክህ ልብ በል! አፌን እከፍታለሁ፤

አንደበቴም* ይናገራል።

 3 ቃሌ የልቤን ቅንነት ይገልጻል፤+

ከንፈሮቼም የማውቀውን ነገር በቅንነት ይናገራሉ።

 4 የአምላክ መንፈስ ሠራኝ፤+

ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ እስትንፋስም ሕይወት ሰጠኝ።+

 5 የምትችል ከሆነ መልስልኝ፤

የመከራከሪያ ሐሳብህን በፊቴ አቅርብ፤ ቦታህንም ያዝ።

 6 እነሆ፣ በእውነተኛው አምላክ ፊት እኔም እንደ አንተው ነኝ፤

እኔም የተሠራሁት ከሸክላ ነው።+

 7 ስለዚህ እኔን ፈርተህ ልትሸበር አይገባም፤

የማሳድርብህ ጫናም ሊደቁስህ አይገባም።

 8 ይሁንና የተናገርከውን ሰምቻለሁ፤

አዎ፣ እነዚህን ቃላት ስሰማ ቆይቻለሁ፦

 9 ‘ከበደል ነፃ ነኝ፤+

ንጹሕ ነኝ፤ ጥፋትም የለብኝም።+

10 አምላክ ግን እኔን ለመቃወም ምክንያት ይፈልጋል፤

እንደ ጠላቱ ይቆጥረኛል።+

11 እግሬን በእግር ግንድ ያስራል፤

መንገዴንም ሁሉ ይመረምራል።’+

12 ሆኖም እንዲህ ማለትህ ትክክል ስላልሆነ እመልስልሃለሁ፦

አምላክ ሟች ከሆነው ሰው እጅግ ይበልጣል።+

13 በአምላክ ላይ የምታጉረመርመው ለምንድን ነው?+

ለተናገርከው ሁሉ መልስ ስላልሰጠህ ነው?+

14 አምላክ ከአንዴም ሁለቴ ይናገራል፤

ይሁንና ማንም አያስተውለውም፤

15 ሰዎች ከባድ እንቅልፍ ሲይዛቸው፣

በአልጋቸውም ላይ ሆነው ሲያሸልቡ፣

በሕልም፣ በሌሊትም ራእይ ይናገራል።+

16 በዚያን ጊዜ ጆሯቸውን ይከፍታል፤+

መመሪያውንም እንዲገነዘቡ ያደርጋል፤*

17 ይህም ሰውን ከስህተት ይመልስ ዘንድ፣+

ደግሞም ሰውን ከኩራት ይጠብቅ ዘንድ ነው።+

18 አምላክ ነፍሱን* ከጉድጓድ* ያድናል፤+

ሕይወቱ በሰይፍ* እንዳይጠፋ ይታደገዋል።

19 ደግሞም ሰው በአልጋው ላይ ሳለ በሕመም፣

እንዲሁም አጥንቶቹ በሚያስከትሉበት ፋታ የሌለው ሥቃይ ተግሣጽ ይቀበላል፤

20 በመሆኑም ሁለመናው* መብል ይጸየፋል፤

ምርጥ የሆነ ምግብም ይጠላል።*+

21 ሥጋውም መንምኖ ይጠፋል፤

ተሸፍነው የነበሩት አጥንቶቹም ያገጣሉ።*

22 ነፍሱ* ወደ ጉድጓድ፣*

ሕይወቱም ሊያጠፏት ወደሚሹ ትቀርባለች።

23 ለሰው ትክክል የሆነውን ነገር የሚነግረው

አንድ መልእክተኛ፣*

ከሺዎች መካከል አንድ ጠበቃ ቢገኝለት፣

24 ያን ጊዜ አምላክ ሞገስ ያሳየዋል፤ እንዲህም ይላል፦

‘ወደ ጉድጓድ* ከመውረድ አድነው!+

ቤዛ አግኝቻለሁ!+

25 በወጣትነቱ ጊዜ ከነበረው የበለጠ ሥጋው ይለምልም፤*+

ብርቱ ወደነበረበት የወጣትነት ዘመኑም ይመለስ።’+

26 አምላክን ይለምናል፤+ እሱም ይቀበለዋል፤

በእልልታም የአምላክን ፊት ያያል፤

ደግሞም አምላክ የራሱን ጽድቅ፣ ሟች ለሆነው ሰው ይመልስለታል።

27 ግለሰቡም ለሰዎች እንዲህ ይላል፦*

‘ኃጢአት ሠርቻለሁ፤+ ትክክል የሆነውንም ነገር አጣምሜአለሁ፤

ሆኖም የእጄን አላገኘሁም።*

28 እሱ ነፍሴን* ወደ ጉድጓድ* ከመውረድ ታድጓታል፤+

ሕይወቴም ብርሃን ታያለች።’

29 በእርግጥም አምላክ እነዚህን ነገሮች ሁሉ፣

ከሁለቴም ሦስቴ ለሰው ያደርጋል፤

30 ይኸውም የሕይወት ብርሃን ይበራለት ዘንድ፣

እሱን ከጉድጓድ* ለመመለስ ነው።+

31 ኢዮብ፣ ልብ ብለህ ስማ! ደግሞም አዳምጠኝ!

ዝም በል፤ እኔም መናገሬን እቀጥላለሁ።

32 የምትለው ካለ መልስልኝ።

ትክክለኛነትህ እንዲረጋገጥ ማድረግ ስለምፈልግ ተናገር።

33 የምትለው ነገር ከሌለ ግን ስማኝ፤

ዝም በል፤ እኔም ጥበብን አስተምርሃለሁ።”

34 ኤሊሁም መልስ መስጠቱን በመቀጠል እንዲህ አለ፦

 2 “እናንተ ጥበበኞች፣ ቃሌን አዳምጡ፤

እናንተ ብዙ እውቀት ያላችሁ ስሙኝ።

 3 ምላስ* የምግብን ጣዕም እንደሚለይ ሁሉ፣

ጆሮም ቃላትን ያመዛዝናል።

 4 ትክክለኛ የሆነውን ነገር እናመዛዝን፤

መልካም የሆነውን ነገር በመካከላችን እንወስን።

 5 ኢዮብ እንዲህ ብሏልና፦ ‘እኔ ትክክል ነኝ፤+

አምላክ ግን ፍትሕ ነፍጎኛል።+

 6 ሊበየንብኝ የሚገባውን ፍርድ በተመለከተ እዋሻለሁ?

በደል ባልሠራም እንኳ በላዬ ላይ ያለው ቁስል የማይሽር ነው።’+

 7 ፌዝን እንደ ውኃ የሚጠጣ፣

እንደ ኢዮብ ያለ ሰው ማን ነው?

 8 ክፉ ድርጊት ከሚፈጽሙ ጋር ተወዳጅቷል፤

ከክፉዎችም ጋር ገጥሟል።+

 9 ኢዮብ ‘ሰው አምላክን ለማስደሰት መሞከሩ

ምንም ፋይዳ የለውም’ ብሏልና።+

10 ስለዚህ እናንተ አስተዋዮች* ስሙኝ፦

‘እውነተኛው አምላክ ክፉ ነገር ያደርጋል፤

ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ በደል ይፈጽማል’ ብሎ ማሰብ የማይመስል ነገር ነው!+

11 ለሰው እንደ ሥራው ይከፍለዋልና፤+

መንገዱም ያስከተለበትን መዘዝ እንዲቀበል ያደርገዋል።

12 በእርግጥም አምላክ ክፋት አይሠራም፤+

ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ፍትሕን አያዛባም።+

13 ምድርን እንዲገዛ ያደረገው ማን ነው?

በመላው ዓለም* ላይ የሾመውስ ማን ነው?

14 እሱ ትኩረቱን* በእነሱ ላይ ቢያደርግ፣

መንፈሳቸውንና እስትንፋሳቸውን ወደ ራሱ ቢሰበስብ፣+

15 ሰዎች* ሁሉ በአንድነት በጠፉ፣

የሰውም ዘር ወደ አፈር በተመለሰ ነበር።+

16 ስለዚህ ማስተዋል ካለህ ለዚህ ነገር ትኩረት ስጥ፤

የምናገረውንም በጥሞና አዳምጥ።

17 ፍትሕን የሚጠላ ሰው፣ ገዢ ሊሆን ይገባል?

ወይስ ጻድቅ የሆነውን ኃያል ሰው ትኮንነዋለህ?

18 ንጉሥን ‘የማትረባ ነህ፣’

ታላላቅ የሆኑ ሰዎችንስ ‘ክፉዎች ናችሁ’ ትላለህ?+

19 አምላክ ለመኳንንት አያዳላም፤

ሀብታሙንም ከድሃው* አስበልጦ አይመለከትም፤+

ሁሉም የእጁ ሥራዎች ናቸውና።+

20 እነሱ በእኩለ ሌሊት ድንገት ሊሞቱ ይችላሉ፤+

በኃይል ተንቀጥቅጠው ሕይወታቸው ያልፋል፤

ኃያላን የሆኑትም እንኳ ይወገዳሉ፤ ይሁንና ይህ የሚሆነው በሰው እጅ አይደለም።+

21 የአምላክ ዓይኖች የሰውን መንገድ ይመለከታሉና፤+

ደግሞም እርምጃውን ሁሉ ያያል።

22 ክፉ ድርጊት የሚፈጽሙ ሰዎች የሚደበቁበት

ጨለማም ሆነ ፅልማሞት የለም።+

23 አምላክ፣ ማንኛውም ሰው በፊቱ ለፍርድ እንዲቀርብ፣

የተወሰነ ጊዜ አልቀጠረምና።

24 ምርመራ ማድረግ ሳያስፈልገው ኃያላንን ይሰባብራል፤

በእነሱም ቦታ ሌሎችን ይተካል።+

25 እያደረጉ ያሉትን ያውቃልና፤+

በሌሊት ይገለብጣቸዋል፤ እነሱም ይደቅቃሉ።+

26 በክፋታቸው የተነሳ፣

ሁሉም ማየት በሚችልበት ቦታ ይመታቸዋል፤+

27 ምክንያቱም እሱን ከመከተል ወደኋላ ብለዋል፤+

መንገዶቹንም ሁሉ ችላ ብለዋል፤+

28 ድሃው ወደ እሱ እንዲጮኽ ያደርጋሉ፤

እሱም የምስኪኖችን ጩኸት ይሰማል።+

29 አምላክ ዝም ሲል ማን ሊወቅሰው ይችላል?

ፊቱን በሚሰውርበት ጊዜ ማን ሊያየው ይችላል?

ይህን ያደረገው በአንድ ብሔር ላይም ሆነ በአንድ ሰው ላይ ምንም ለውጥ አያመጣም፤

30 ይህም አምላክ የለሽ የሆነ* ሰው እንዳይገዛ፣+

ወይም በሕዝቡ ላይ ወጥመድ እንዳይዘረጋ ነው።

31 አምላክን እንዲህ የሚል ሰው ይኖራል?

‘የሠራሁት ጥፋት ባይኖርም ተቀጥቻለሁ፤+

32 ማየት የተሳነኝን ነገር አስተምረኝ፤

የሠራሁት ጥፋት ካለ ዳግመኛ አልሠራም።’

33 ፍርዱን አልቀበልም ስትል አንተ በምትፈልገው መንገድ ሊክስህ ይገባል?

መወሰን ያለብህ አንተ እንጂ እኔ አይደለሁም።

ስለዚህ አንተ በደንብ የምታውቀውን ነገር ንገረኝ።

34 አስተዋይ የሆኑ* ሰዎች፣

ደግሞም እኔን የሚሰሙ ጥበበኛ ሰዎች ሁሉ እንዲህ ይሉኛል፦

35 ‘ኢዮብ ያለእውቀት ይናገራል፤+

ቃሉም ማስተዋል የጎደለው ነው።’

36 ኢዮብ እስከ መጨረሻው ድረስ ይፈተን!*

እንደ ክፉ ሰዎች መልስ ሰጥቷልና።

37 በኃጢአቱ ላይ ዓመፅ ጨምሯል፤+

በፊታችን በንቀት አጨብጭቧል፤

በእውነተኛውም አምላክ ላይ ብዙ ነገር ተናግሯል!”+

35 ኤሊሁ እንዲህ ሲል መልስ መስጠቱን ቀጠለ፦

 2 “ትክክል እንደሆንክ በጣም እርግጠኛ ከመሆንህ የተነሳ

‘እኔ ከአምላክ ይበልጥ ጻድቅ ነኝ’ ትላለህ?+

 3 ደግሞም ‘ይህ ለአንተ* ምን ለውጥ ያመጣል?

ኃጢአት ብሠራ ኖሮ ከዚህ የከፋ ነገር ይደርስብኝ ነበር?’ ብለሃልና።+

 4 ለአንተና አብረውህ ላሉት ወዳጆችህ፣+

መልስ እሰጣለሁ።

 5 ቀና ብለህ ወደ ሰማይ እይ፤

ከአንተ ከፍ ያሉትን ደመናት በጥሞና ተመልከት።+

 6 ኃጢአት ብትሠራ እሱን ምን ትጎዳዋለህ?+

በደልህ ቢበዛ እሱን ምን ታደርገዋለህ?+

 7 ጻድቅ ብትሆን ለእሱ ምን ትጨምርለታለህ?

ከአንተ እጅ ምን ይቀበላል?+

 8 ክፋት ብትሠራ የምትጎዳው እንደ አንተ ያለውን ሰው ብቻ ነው፤

ጽድቅህም የሚጠቅመው የሰውን ልጅ ነው።

 9 ሰዎች ከባድ ጭቆና ሲደርስባቸው ይጮኻሉ፤

ከኃያል ሰው የሥልጣን ቀንበር* ለመገላገል ይጮኻሉ።+

10 ይሁንና ‘በሌሊት መዝሙር እንዲዘመር የሚያደርገው፣+

ታላቅ ፈጣሪዬ የሆነው አምላክ የት አለ?’ የሚል የለም።+

11 ከምድር እንስሳት+ ይበልጥ እኛን ያስተምረናል፤+

በሰማይ ከሚበርሩ ወፎችም በላይ ጥበበኞች አድርጎናል።

12 በክፉዎች ኩራት የተነሳ ሰዎች ይጮኻሉ፤

ሆኖም እሱ አይመልስላቸውም።+

13 በእርግጥ አምላክ ከንቱ ጩኸት* አይሰማም፤+

ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ትኩረት አይሰጠውም።

14 አላየሁትም ብለህ ቅሬታ እያሰማህ፣ አንተንማ እንዴት ይስማህ!+

ጉዳይህ በእሱ ፊት ነው፤ ስለዚህ እሱን በትዕግሥት ተጠባበቅ።+

15 ተቆጥቶ ተጠያቂ አላደረገህምና፤

በችኮላ ያደረግከውንም አልያዘብህም።+

16 ኢዮብ አፉን የሚከፍተው በከንቱ ነው፤

እውቀት ሳይኖረው ብዙ ይናገራል።”+

36 ኤሊሁ በመቀጠል እንዲህ አለ፦

 2 “አምላክን ወክዬ ገና የምናገረው ነገር ስላለ

ጉዳዩን በማብራራበት ጊዜ ትንሽ ታገሠኝ።

 3 ስለማውቀው ነገር በሰፊው እናገራለሁ፤

ፈጣሪዬ ጻድቅ እንደሆነም አስታውቃለሁ።+

 4 በእርግጥ የምናገረው ቃል ውሸት አይደለም፤

እውቀቱ ፍጹም የሆነው አምላክ+ በፊትህ ነው።

 5 በእርግጥ አምላክ ኃያል ነው፤+ ደግሞም ማንንም ገሸሽ አያደርግም፤

የማስተዋል ችሎታው* ታላቅ ነው።

 6 የክፉዎችን ሕይወት አይጠብቅም፤+

ጎስቋላው ግን ፍትሕ እንዲያገኝ ያደርጋል።+

 7 ዓይኖቹን ከጻድቃን ላይ አያነሳም፤+

ከነገሥታት ጋር በዙፋን ላይ ያስቀምጣቸዋል፤*+ እነሱም ለዘላለም ከፍ ከፍ ይላሉ።

 8 ይሁንና ሰዎች በሰንሰለት ቢታሰሩ፣

በመከራም ገመድ ቢጠፈሩ፣

 9 ከመታበያቸው የተነሳ ስለፈጸሙት ድርጊት

ይኸውም ስለ በደላቸው ይነግራቸዋል።

10 እርማት እንዲቀበሉ ጆሯቸውን ይከፍታል፤

ከክፋትም እንዲመለሱ ይነግራቸዋል።+

11 ቢታዘዙትና ቢያገለግሉት፣

የሕይወት ዘመናቸውን በብልጽግና ይፈጽማሉ፤

ሕይወታቸውም አስደሳች ይሆናል።+

12 ባይታዘዙ ግን በሰይፍ* ይጠፋሉ፤+

ያለእውቀትም ይሞታሉ።

13 በልባቸው አምላክ የለሽ* የሆኑ ቂም ይይዛሉ።

እሱ በሚያስራቸው ጊዜም እንኳ እርዳታ ለማግኘት አይጮኹም።

14 ገና ወጣት እያሉ ይሞታሉ፤*+

በቤተ መቅደስ ቀላጮች* መካከል ሕይወታቸውን ያሳልፋሉ።*+

15 ሆኖም አምላክ* የተጎሳቆሉ ሰዎችን ከጉስቁልናቸው ይታደጋቸዋል፤

ጭቆና በሚደርስባቸው ጊዜ ጆሯቸውን ይከፍታል።

16 እሱ ከመከራ መንጋጋ አስጥሎ+

የሚያጨናንቅ ነገር ወደሌለበት ሰፊ ስፍራ ያመጣሃል፤+

ማዕድህ ምርጥ በሆነ ምግብ የተሞላ ይሆናል፤ ይህ ደግሞ ያጽናናሃል።+

17 ፍርድ ሲበየንና ፍትሕ ሲሰፍን፣

በክፉዎች ላይ በሚፈጸመው ፍርድ ትረካለህ።+

18 ይሁንና ቁጣ ወደ ክፋት* እንዳይመራህ ተጠንቀቅ፤+

ጠቀም ያለ ጉቦም አያስትህ።

19 እርዳታ ለማግኘት መጮኽህ፣

ወይም የምታደርገው ማንኛውም ብርቱ ጥረት ከጭንቀት ነፃ ያደርግሃል?+

20 ሰዎች ካሉበት ስፍራ የሚጠፉበትን

የሌሊቱን ጊዜ አትናፍቅ።

21 ከጉስቁልና ይልቅ ይህን መርጠህ፣+

ወደ ክፋት እንዳትመለስ ተጠንቀቅ።

22 እነሆ፣ አምላክ በኃይሉ ከፍ ከፍ ብሏል፤

እንደ እሱ ያለ አስተማሪ ማን ነው?

23 እሱን መንገድ የመራው፣*

ወይም ‘የሠራኸው ነገር ትክክል አይደለም’ ያለው ማን ነው?+

24 ሰዎች በመዝሙር ያወደሱትን፣+

የእሱን ሥራ ከፍ ከፍ ማድረግ አትዘንጋ።+

25 የሰው ልጆች ሁሉ አይተውታል፤

ሟች የሆነ ሰው ከሩቅ ያያል።

26 አዎ፣ አምላክ እኛ ልናውቀው ከምንችለው በላይ ታላቅ ነው፤+

የዘመኑም ቁጥር ከመረዳት ችሎታ በላይ ነው።*+

27 እሱ የውኃ ጠብታዎችን ወደ ላይ ይስባል፤+

ጭጋጉም ወደ ዝናብነት ይለወጣል፤

28 ከዚያም ደመናት ያዘንባሉ፤+

በሰው ልጆችም ላይ ዶፍ ያወርዳሉ።

29 የደመናትን ንብርብር፣

ከድንኳኑም የሚሰማውን ነጎድጓድ+ ማን ሊያስተውል ይችላል?

30 መብረቁን*+ በላዩ ላይ እንዴት እንደሚዘረጋ፣

የባሕሩንም ወለል* እንዴት እንደሚሸፍን ተመልከት።

31 በእነዚህም ሕዝቦችን ያኖራል፤*

ምግብ አትረፍርፎ ይሰጣቸዋል።+

32 በእጆቹ መብረቁን ይሸፍናል፤

ወደ ዒላማውም ይሰደዋል።+

33 ነጎድጓዱ ስለ እሱ ይናገራል፤

ከብቶች እንኳ ሳይቀሩ ማን* እየመጣ እንዳለ ይጠቁማሉ።

37 “ከዚህም የተነሳ ልቤ ይመታል፤

ከስፍራውም ይዘላል።

 2 የድምፁን ጉምጉምታ፣

ከአፉም የሚወጣውን ነጎድጓድ በጥሞና ስሙ።

 3 ከሰማያት በታች ይልከዋል፤

መብረቁንም እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ይሰደዋል።+

 4 ከዚያም በኋላ ድምፅ ያስተጋባል፤

ግርማ በተላበሰ ድምፅ ያንጎደጉዳል፤+

ድምፁም በሚሰማበት ጊዜ አይከለክለውም።

 5 አምላክ በሚያስደንቅ ሁኔታ በድምፁ ያንጎደጉዳል፤+

እኛ መረዳት የማንችላቸውን ታላላቅ ነገሮች ያደርጋል።+

 6 በረዶውን ‘ወደ መሬት ውረድ፣’+

ዶፉን ዝናብም ‘በኃይል ውረድ’ ይለዋልና።+

 7 ሟች የሆነ ሰው ሁሉ ሥራውን እንዲያውቅ፣

አምላክ የእያንዳንዱን ሰው ሥራ ያስቆማል።*

 8 የዱር አራዊት ወደ ጎሬአቸው ይገባሉ፤

በዋሻዎቻቸውም ውስጥ ይቀመጣሉ።

 9 አውሎ ነፋስ ከማደሪያው ይነፍሳል፤+

ቅዝቃዜም ከሰሜን ነፋሳት ይመጣል።+

10 በአምላክ እስትንፋስ በረዶ ይገኛል፤+

የተንጣለሉትም ውኃዎች ግግር በረዶ ይሆናሉ።+

11 አዎ፣ ደመናትን እርጥበት ያሸክማቸዋል፤

በደመናት መካከል መብረቁን ይበትናል፤+

12 እሱ በመራቸው አቅጣጫ ይሽከረከራሉ፤

ሰዎች በሚኖሩበት* የምድር ገጽ ላይ እሱ ያዘዘውን ሁሉ ይፈጽማሉ።+

13 ለቅጣትም+ ሆነ* ለምድሩ ሲል

አሊያም ታማኝ ፍቅር ለማሳየት ይህ እንዲሆን ያደርጋል።+

14 ኢዮብ ሆይ፣ ይህን ስማ፤

ቆም ብለህ የአምላክን ድንቅ ሥራዎች በጥሞና አስብ።+

15 አምላክ ደመናትን እንዴት እንደሚቆጣጠር፣*

ከደመናውም እንዴት መብረቅ እንደሚያበርቅ ታውቃለህ?

16 ደመናት እንዴት እንደሚንሳፈፉ ታውቃለህ?+

እነዚህ፣ እውቀቱ ፍጹም የሆነው አምላክ ድንቅ ሥራዎች ናቸው።+

17 ምድር በደቡብ ነፋስ ጸጥ ስትል፣

ልብስህ የሚሞቀው ለምንድን ነው?+

18 እንደ ብረት መስተዋት ጠንካራ የሆኑትን ሰማያት፣

ከእሱ ጋር ልትዘረጋ* ትችላለህ?+

19 ለእሱ የምንለውን ንገረን፤

ጨለማ ውስጥ ስለሆን መልስ መስጠት አንችልም።

20 እኔ መናገር እንደምፈልግ ለእሱ ማሳወቅ ያስፈልጋል?

ወይስ እሱ ሊያውቀው የሚገባ ነገር የተናገረ ሰው አለ?+

21 በሰማይ ላይ ብርሃን ቢኖርም፣

ነፋስ ነፍሶ ደመናቱን ካልበተነ፣

ሰዎች ብርሃኑን* ማየት አይችሉም።

22 ከሰሜን ወርቃማ ጨረር ይወጣል፤

የአምላክ ግርማ+ አስፈሪ ነው።

23 ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ከመረዳት ችሎታችን በላይ ነው፤+

ኃይሉ ታላቅ ነው፤+

ደግሞም ፍትሑንና ታላቅ ጽድቁን አይጥስም።+

24 ስለዚህ ሰዎች ሊፈሩት ይገባል።+

ጠቢብ ነን ብለው ለሚያስቡ* ሁሉ ሞገስ አያሳይምና።”+

38 ከዚያም ይሖዋ ከአውሎ ነፋስ ውስጥ ለኢዮብ መለሰለት፦+

 2 “ሐሳቤን የሚሰውርና

ያለእውቀት የሚናገር ይህ ማን ነው?+

 3 እስቲ እንደ ወንድ ወገብህን ታጠቅ፤

እኔ እጠይቅሃለሁ፤ አንተም ንገረኝ።

 4 ምድርን በመሠረትኩ ጊዜ አንተ የት ነበርክ?+

ማስተዋል አለኝ የምትል ከሆነ ንገረኝ።

 5 የምታውቅ ከሆነ፣ መለኪያዎቿን የወሰነ፣

ወይስ መለኪያ ገመድ በላይዋ ላይ የዘረጋ ማን ነው?

 6 የምድር ምሰሶዎች የተተከሉት ምን ላይ ነው?

የማዕዘኗን ድንጋይ ያኖረስ ማን ነው?+

 7 አጥቢያ ከዋክብት+ በአንድነት እልል ሲሉ፣

የአምላክም ልጆች ሁሉ*+ በደስታ ሲጮኹ አንተ የት ነበርክ?

 8 ባሕሩ ከማህፀን አፈትልኮ በወጣ ጊዜ፣

በር የዘጋበት ማን ነው?+

 9 ደመና ባለበስኩት ጊዜ፣

በድቅድቅ ጨለማም በጠቀለልኩት ጊዜ፣

10 በላዩም ድንበሬን በወሰንኩ ጊዜ፣

መቀርቀሪያዎችና በሮች ባደረግኩለት ጊዜ፣+

11 ደግሞም ‘እስከዚህ ድረስ መምጣት ትችላለህ፤ ከዚህ ግን አታልፍም፤

የኩሩው ማዕበልህም ገደብ ይህ ነው’ ባልኩ ጊዜ+ አንተ የት ነበርክ?

12 ለመሆኑ ንጋትን አዘህ ታውቃለህ?

ወይስ ጎህ ስፍራውን እንዲያውቅ አድርገሃል?+

13 የማለዳ ብርሃን ወደ ምድር ዳርቻዎች እንዲሄድ፣

ክፉዎችንም ከላይዋ እንዲያራግፍ ያዘዝከው አንተ ነህ?+

14 ምድር ከማኅተም በታች እንዳለ የሸክላ ጭቃ ትለወጣለች፤

ገጽታዎቿም እንደሚያምር ልብስ ጎልተው ይታያሉ።

15 የክፉዎች ብርሃን ግን ከእነሱ ተወስዷል፤

ከፍ ያለው ክንዳቸውም ተሰብሯል።

16 ወደ ባሕሩ ምንጮች ወርደሃል?

ወይስ ጥልቁን ውኃ መርምረሃል?+

17 የሞት በሮች+ ተገልጠውልሃል?

የድቅድቅ ጨለማንስ* በሮች አይተሃል?+

18 ምድር ምን ያህል ሰፊ እንደሆነች አስተውለሃል?+

ይህን ሁሉ የምታውቅ ከሆነ ተናገር።

19 ብርሃን የሚኖረው በየት አቅጣጫ ነው?+

የጨለማ ስፍራስ የት ነው?

20 ወደ ክልሉ ልትወስደው ትችላለህ?

ወደ ቤቱስ የሚወስደውን ጎዳና ታውቃለህ?

21 በዚያን ጊዜ ተወልደህ ስለነበር፣

ዕድሜህም ትልቅ ስለሆነ* ይህን ሳታውቅ አትቀርም!

22 አመዳዩ ወደተከማቸበት መጋዘን ገብተሃል?+

የበረዶውንስ ግምጃ ቤት አይተሃል?+

23 ይህም ለመከራ ጊዜ፣

ለውጊያና ለጦርነት ቀን ያስቀመጥኩት ነው።+

24 ብርሃን* የሚሰራጨው ከየት አቅጣጫ ነው?

የምሥራቅስ ነፋስ በምድር ላይ የሚነፍሰው ከየት ነው?+

25 ለዶፍ መውረጃን፣

ነጎድጓድ ለቀላቀለ ጥቁር ደመናም መንገድን ያዘጋጀ ማን ነው?+

26 አንድም ሰው በሌለበት ቦታ፣

ሰውም በማይኖርበት ምድረ በዳ የሚያዘንበው፣+

27 የወደመውን ጠፍ መሬት የሚያረካው፣

ሣርንም የሚያበቅለው ማን ነው?+

28 ዝናብ አባት አለው?+

ጠልንስ የወለደው ማን ነው?+

29 በረዶ የሚወጣው ከማን ማህፀን ነው?

የሰማዩንስ አመዳይ የወለደው ማን ነው?+

30 ውኃዎች በድንጋይ የተሸፈኑ ያህል እንዲሆኑ፣

የጥልቁ ውኃም ገጽ ግግር በረዶ እንዲሆን የሚያደርገው ማን ነው?+

31 የኪማ ኅብረ ከዋክብትን* ገመድ ልታስር፣

ወይስ የከሲል ኅብረ ከዋክብትን* ገመድ ልትፈታ ትችላለህ?+

32 ኅብረ ከዋክብትን* በወቅቱ ልታወጣ፣

ወይስ የአሽ ኅብረ ከዋክብትን* ከነልጆቹ ልትመራ ትችላለህ?

33 ሰማያት የሚመሩባቸውን ሕጎች ታውቃለህ?+

ወይስ የሰማያትን* ሕጎች በምድር ላይ ተግባራዊ ማድረግ ትችላለህ?

34 ጎርፍ ይሸፍንህ ዘንድ፣

ድምፅህን ወደ ደመናት ማንሳት ትችላለህ?+

35 የመብረቅ ብልጭታዎችን መላክ ትችላለህ?

እነሱስ አንተ ጋ ቀርበው ‘ይኸው መጥተናል!’ ይሉሃል?

36 በደመናት ውስጥ* ጥበብ ያኖረው፣+

በሰማይ ለሚከናወነውስ ክስተት* ማስተዋልን የሰጠው ማን ነው?+

37 ደመናትን ለመቁጠር የሚያስችል ጥበብ ያለው ማን ነው?

ወይስ የሰማይን የውኃ ማሰሮዎች ሊደፋ የሚችል ማን ነው?+

38 አፈሩ ቦክቶ እንዲጋገር፣

የምድር ጓሎችም እንዲጣበቁ ሊያደርግ የሚችል ማን ነው?

39 ለአንበሳ አድነህ ግዳይ ልታመጣለት፣

ወይስ የተራቡ የአንበሳ ግልገሎችን ልታጠግብ ትችላለህ?+

40 እነሱ በዋሻቸው ውስጥ አድፍጠው፣

ወይም በጎሬአቸው አድብተው ሳለ ይህን ልታደርግ ትችላለህ?

41 ጫጩቶቿ ወደ አምላክ ሲጮኹ፣

የሚበሉትም አጥተው ሲቅበዘበዙ፣

ለቁራ መብል የሚያዘጋጅ ማን ነው?+

39 “የተራራ ፍየሎች የሚወልዱበትን ጊዜ ታውቃለህ?+

ርኤሞች* ግልገሎቻቸውን ሲወልዱ ተመልክተሃል?+

 2 የእርግዝናቸው ወራት ምን ያህል እንደሆነ መቁጠር ትችላለህ?

የሚወልዱበትን ጊዜስ ታውቃለህ?

 3 ግልገሎቻቸውን ተንበርክከው ይወልዳሉ፤

ከምጣቸውም ይገላገላሉ።

 4 ግልገሎቻቸው ይጠነክራሉ፤ በሜዳም ያድጋሉ፤

ይሄዳሉ፤ ወደ እነሱም አይመለሱም።

 5 የዱር አህያውን ነፃ የለቀቀው፣+

የዱር አህያውን ከእስራቱ የፈታውስ ማን ነው?

 6 በረሃማው ሜዳ ቤቱ፣

ጨዋማውም ምድር መኖሪያው እንዲሆን አደረግኩ።

 7 በከተማ ሁካታ ያፌዛል፤

የነጂውንም ጩኸት አይሰማም።

 8 መሰማሪያ ለማግኘት በኮረብቶች ላይ ይቅበዘበዛል፤

ማንኛውንም አረንጓዴ ተክል ይፈልጋል።

 9 የዱር በሬ አንተን ለማገልገል ፈቃደኛ ነው?+

በጋጣህ ውስጥ ያድራል?

10 የዱር በሬ ትልም እንዲያወጣልህ ልትጠምደው ትችላለህ?

ወይስ እየተከተለህ ሸለቆውን ያርሳል?*

11 በብርቱ ጉልበቱ ትታመናለህ?

ደግሞስ ከባዱን ሥራህን እንዲሠራልህ ታደርጋለህ?

12 እህልህን እንዲሰበስብልህ፣

በአውድማህም ላይ እንዲያከማችልህ በእሱ ትታመናለህ?

13 የሰጎን ክንፍ በደስታ ይርገበገባል፤

ይሁንና የራዛ*+ ዓይነት ክንፍና ላባ አላት?

14 እንቁላሎቿን መሬት ላይ ትጥላለች፤

በአፈርም ውስጥ ታሞቃቸዋለች።

15 እግር ሊሰብራቸው፣

የዱር አውሬም ሊረግጣቸው እንደሚችል አታስብም።

16 ልጆቿ የራሷ ያልሆኑ ይመስል ትጨክንባቸዋለች፤+

ድካሜ ሁሉ ከንቱ ይሆናል የሚል ስጋት አያድርባትም።

17 አምላክ ጥበብ ነስቷታልና፤*

ማስተዋልንም አልሰጣትም።

18 ተነስታ ክንፎቿን በምታርገበግብበት ጊዜ ግን፣

በፈረሱና በፈረሰኛው ላይ ትስቃለች።

19 ለፈረስ ጉልበት የምትሰጠው አንተ ነህ?+

አንገቱንስ የሚርገፈገፍ ጋማ ታለብሰዋለህ?

20 እንደ አንበጣ እንዲዘል ልታደርገው ትችላለህ?

የፉርፉርታው ግርማ አስፈሪ ነው።+

21 የሸለቆውን መሬት ይጎደፍራል፤ ደግሞም በኃይል ይዘላል፤+

ወደ ውጊያ ይገሰግሳል።*+

22 በፍርሃት ላይ ይስቃል፤ የሚያስፈራውም ነገር የለም።+

ሰይፍ አይቶም ወደኋላ አይልም።

23 ኮሮጆው በጎኑ ይንኳኳል፤

ጭሬውና ጦሩ ያብረቀርቃል።

24 በደስታ እየተርገፈገፈ ወደ ፊት ይሸመጥጣል፤*

የቀንደ መለከት ድምፅ ሲሰማ ያቅበጠብጠዋል።*

25 ቀንደ መለከቱ ሲነፋ ‘እሰይ!’ ይላል፤

ጦርነቱን ከሩቅ ያሸታል፤

ደግሞም የጦር አዛዦችን ጩኸትና ቀረርቶውን ይሰማል።+

26 ሲላ ክንፎቹን ወደ ደቡብ ዘርግቶ

ወደ ላይ የሚወነጨፈው በአንተ ማስተዋል ነው?

27 ወይስ ንስር ወደ ላይ የሚመጥቀው፣+

ጎጆውንም ከፍ ባለ ቦታ ላይ የሚሠራው+ አንተ አዘኸው ነው?

28 በገደል ላይ ያድራል፤

በገደሉ አፋፍ ላይ በሚገኝ ዓለታማ ምሽግ ውስጥ* ይኖራል።

29 በዚያም ሆኖ የሚበላውን ነገር ይፈልጋል፤+

ዓይኖቹም እጅግ ሩቅ ወደሆነ ቦታ ይመለከታሉ።

30 ጫጩቶቹም ደም ይጠጣሉ፤

በድን ባለበት ስፍራም ሁሉ ይገኛል።”+

40 ይሖዋ በመቀጠል ኢዮብን እንዲህ አለው፦

 2 “ስህተት የሚፈላልግ ሰው፣ ሁሉን ቻይ ከሆነው አምላክ ጋር ሊሟገት ይገባል?+

አምላክን መውቀስ የሚፈልግ እሱ መልስ ይስጥ።”+

 3 ኢዮብ ለይሖዋ እንዲህ በማለት መለሰ፦

 4 “እነሆ፣ እኔ የማልረባ ሰው ነኝ።+

ምን ልመልስልህ እችላለሁ?

እጄን በአፌ ላይ እጭናለሁ።+

 5 አንዴ ተናግሬአለሁ፤ ከአሁን በኋላ ግን የምሰጠው መልስ የለም፤

ሁለተኛ ጊዜም ተናገርኩ፤ ከዚህ በኋላ ግን አልናገርም።”

 6 ከዚያም ይሖዋ ከአውሎ ነፋስ ውስጥ ለኢዮብ መለሰለት፦+

 7 “እባክህ፣ እንደ ወንድ ወገብህን ታጠቅ፤

እኔ እጠይቅሃለሁ፤ አንተም ንገረኝ።+

 8 የእኔን ፍትሕ ትጠራጠራለህ?*

አንተ ትክክል ሆነህ ትገኝ ዘንድ እኔን ትኮንናለህ?+

 9 ክንድህ የእውነተኛውን አምላክ ክንድ ያህል ኃያል ነው?+

ወይስ ድምፅህ እንደ እሱ ድምፅ ሊያንጎደጉድ ይችላል?+

10 እስቲ ራስህን በክብርና በግርማ አስጊጥ፤

ደግሞም ታላቅነትና ሞገስ ተላበስ።

11 ቁጣህ ገንፍሎ ይፍሰስ፤

ትዕቢተኛውንም ሁሉ ተመልክተህ ዝቅ አድርገው።

12 ትዕቢተኛውን ሰው ሁሉ አይተህ አዋርደው፤

ክፉዎችንም በቆሙበት ስፍራ ጨፍልቃቸው።

13 ሁሉንም በአፈር ውስጥ ደብቃቸው፤

እነሱንም* በሰዋራ ቦታ እሰራቸው፤

14 ያን ጊዜ ቀኝ እጅህ ልታድንህ እንደምትችል፣

እኔ ራሴ አምኜ እቀበላለሁ።*

15 አንተን እንደፈጠርኩ፣ የፈጠርኩትን ብሄሞትን* ተመልከት።

እንደ በሬ ሣር ይበላል።

16 በወገቡ ውስጥ ያለውን ጉልበት፣

በሆዱም ጡንቻዎች ውስጥ ያለውን ኃይል ተመልከት!

17 ጅራቱን እንደ አርዘ ሊባኖስ ያጠነክረዋል፤

የወርቹም ጅማቶች እርስ በርስ የተጠላለፉ ናቸው።

18 አጥንቶቹ የመዳብ ቱቦዎች ናቸው፤

እግሮቹ እንደ ብረት ዘንጎች ናቸው።

19 እሱ ከአምላክ የፍጥረት ሥራዎች መካከል አውራ ነው፤

በሰይፍ ሊቀርበው የሚችለው ሠሪው ብቻ ነው።

20 የዱር እንስሳት ሁሉ የሚፈነጩባቸው ተራሮች

መብሉን ያበቅሉለታልና።

21 በውኃ ላይ በሚያድጉ ዕፀዋት ጥላ ሥር፣

ረግረጋማ በሆነ ቦታ በሚገኙ ቄጠማዎችም ሥር ይተኛል።

22 በውኃ ላይ የሚያድጉ ዕፀዋት በጥላቸው ይጋርዱታል፤

በሸለቆ* ውስጥ የሚገኙ የአኻያ ዛፎችም ይከቡታል።

23 ወንዙ ቢናወጥ አይፈራም።

ዮርዳኖስ+ ወደ እሱ ቢጎርፍ አይሸበርም።

24 ዓይኖቹ እያዩ ሊይዘው የሚችል አለ?

ወይስ በአፍንጫው መንጠቆ* ሊያስገባ የሚችል ይኖራል?

41 “ሌዋታንን*+ በመንጠቆ ልትይዘው፣

ወይስ ምላሱን በገመድ ልታስረው ትችላለህ?

 2 በአፍንጫው ገመድ* ልታስገባ፣

ወይስ መንጋጋዎቹን በሜንጦ* ልትበሳ ትችላለህ?

 3 እሱ እንድትምረው ይለማመጥሃል?

ወይስ በለሰለሰ አንደበት ያናግርሃል?

 4 ዕድሜ ልኩን ባሪያህ ታደርገው ዘንድ፣

ከአንተ ጋር ቃል ኪዳን ይገባል?

 5 ከወፍ ጋር እንደምትጫወተው ከእሱ ጋር ትጫወታለህ?

ወይስ ለትናንሽ ሴት ልጆችህ መጫወቻ እንዲሆን በውሻ ማሰሪያ ታስረዋለህ?

 6 ነጋዴዎች ይገበያዩበታል?

ለቸርቻሪዎችስ ያከፋፍሉታል?

 7 ቆዳውን ለአደን በሚያገለግል ጦር፣+

ራሱንስ በዓሣ መውጊያ ጭሬ ልትጠቀጥቅ ትችላለህ?

 8 እስቲ እጅህን አሳርፍበት፤

ግብግቡን መቼም አትረሳውም፤ ዳግመኛም እንዲህ ለማድረግ አይቃጣህም!

 9 እሱን በቁጥጥር ሥር አውላለሁ ማለት ከንቱ ልፋት ነው።

እሱን በማየትህ ብቻ እንኳ ብርክ ይይዝሃል።*

10 እሱን ለመተንኮስ የሚደፍር የለም።

ታዲያ እኔን ሊቋቋም የሚችል ማን ነው?+

11 ብድራት እመልስለት ዘንድ በመጀመሪያ አንዳች ነገር የሰጠኝ ማን ነው?+

ከሰማያት በታች ያለው ሁሉ የእኔ ነው።+

12 ስለ እግሮቹ፣ ደግሞም ስለ ኃይሉና

ግሩም በሆነ መንገድ ስለተሠራው አካሉ ከመናገር አልቆጠብም።

13 የላይኛውን ሽፋኑን የገፈፈ ማን ነው?

ወደተከፈቱ መንጋጋዎቹስ ማን ይገባል?

14 የአፉን* በሮች በኃይል ሊከፍት የሚችል ማን ነው?

በዙሪያው ያሉት ጥርሶቹ አስፈሪ ናቸው።

15 ጀርባው ላይ እርስ በርስ የተጣበቁ፣

በረድፍ የተቀመጡ ቅርፊቶች አሉ።*

16 ቅርፊቶቹ ግጥግጥ ያሉ ከመሆናቸው የተነሳ፣

በመካከላቸው አየር እንኳ ሊገባ አይችልም።

17 አንዳቸው ከሌላው ጋር የተጣበቁ ናቸው፤

እርስ በርስ የተያያዙ ናቸው፤ ሊለያዩም አይችሉም።

18 ፉርፉርታው የብርሃን ብልጭታ ያወጣል፤

ዓይኖቹም እንደ ማለዳ ጨረር ናቸው።

19 ከአፉ የመብረቅ ብልጭታዎች ይወጣሉ፤

የእሳት ፍንጣሪዎችም ይረጫሉ።

20 በእንግጫ እንደተቀጣጠለ ምድጃ፣

ከአፍንጫው ጭስ ይወጣል።

21 እስትንፋሱ ከሰል ያቀጣጥላል፤

ከአፉም ነበልባል ይወረወራል።

22 በአንገቱ ውስጥ ታላቅ ብርታት አለ፤

ሽብርም በፊቱ ይሮጣል።

23 የሥጋው ንብርብር እርስ በርስ የተጣበቀ ነው፤

ከቦታው እንደማይነቃነቅ ብረት ጠንካራ ነው።

24 ልቡ እንደ ድንጋይ የጠጠረ፣

አዎ፣ እንደ ወፍጮ ድንጋይ የጠነከረ ነው።

25 በሚነሳበት ጊዜ ኃያላን እንኳ ይርዳሉ፤

ውኃውን እየመታ ሲሄድ ያስደነብራል።

26 ሰይፍ፣ ጦር፣ መውጊያም ሆነ ፍላጻ ቢያገኙት

ሊያሸንፉት አይችሉም።+

27 ብረትን እንደ ገለባ፣

መዳብንም እንደበሰበሰ እንጨት ይቆጥራል።

28 ፍላጻ አያባርረውም፤

የወንጭፍ ድንጋይም ለእሱ እንደ ገለባ ነው።

29 ቆመጥን እንደ ገለባ ይቆጥረዋል፤

ጦር ሲሰበቅም ይስቃል።

30 ሆዱ እንደሾሉ የሸክላ ስብርባሪዎች ነው፤

እንደ ማሄጃ*+ በጭቃ ላይ ምልክት ትቶ ያልፋል።

31 ጥልቁን ውኃ እንደ ድስት ያፈላዋል፤

ባሕሩንም እንደ ቅባት መያዣ ይበጠብጠዋል።

32 በመንገዱ ላይ የሚያብረቀርቅ ፈለግ እየተወ ያልፋል።

ተመልካችም ጥልቁ ውኃ ሽበት ያለው ይመስለዋል።

33 በምድር ላይ ያለፍርሃት የተፈጠረ፣

እንደ እሱ ያለ ፍጡር የለም።

34 ትዕቢተኛ በሆነው ሁሉ ላይ በቁጣ ያፈጣል።

ግርማ በተላበሱ የዱር እንስሳት ሁሉ ላይ ንጉሥ ነው።”

42 ከዚያም ኢዮብ ለይሖዋ እንዲህ ሲል መለሰ፦

 2 “አንተ ሁሉን ነገር ማድረግ እንደምትችል፣

ደግሞም ያሰብከውን ነገር ሁሉ ማድረግ እንደማይሳንህ አሁን አወቅኩ።+

 3 አንተ ‘ያለእውቀት ሐሳቤን የሚሰውር ይህ ማን ነው?’ አልክ።+

በመሆኑም ስለማላውቃቸው እጅግ ድንቅ የሆኑ ነገሮች+

ማስተዋል በጎደለው መንገድ ተናግሬአለሁ።

 4 ‘እባክህ ስማኝ፤ እኔም እናገራለሁ።

እጠይቅሃለሁ፤ አንተም ትነግረኛለህ’ አልከኝ።+

 5 ጆሮዬ ስለ አንተ ሰምታ ነበር፤

አሁን ግን በገዛ ዓይኔ አየሁህ።

 6 ስለዚህ በተናገርኩት ነገር እጸጸታለሁ፤*+

በአፈርና በአመድ ላይ ተቀምጬም ንስሐ እገባለሁ።”+

7 ይሖዋ ከኢዮብ ጋር ተነጋግሮ ካበቃ በኋላ፣ ቴማናዊውን ኤሊፋዝን ይሖዋ እንዲህ አለው፦

“አገልጋዬ ኢዮብ እንዳደረገው ስለ እኔ እውነቱን ስላልተናገራችሁ+ በአንተና በሁለቱ ጓደኞችህ+ ላይ ቁጣዬ ነዷል። 8 አሁን ሰባት ኮርማዎችና ሰባት አውራ በጎች ይዛችሁ ወደ አገልጋዬ ወደ ኢዮብ ሂዱ፤ ለራሳችሁም የሚቃጠል መሥዋዕት አቅርቡ። አገልጋዬ ኢዮብም ለእናንተ ይጸልያል።+ እንደ ሞኝነታችሁ እንዳላደርግባችሁ የእሱን ልመና እቀበላለሁ፤* አገልጋዬ ኢዮብ እንዳደረገው ስለ እኔ እውነቱን አልተናገራችሁምና።”

9 በመሆኑም ቴማናዊው ኤሊፋዝ፣ ሹሃዊው በልዳዶስና ናአማታዊው ሶፋር ሄደው ይሖዋ እንዳዘዛቸው አደረጉ። ይሖዋም የኢዮብን ጸሎት ሰማ።

10 ኢዮብ ለጓደኞቹ ከጸለየ+ በኋላ ይሖዋ በኢዮብ ላይ የደረሰው መከራ+ እንዲያበቃ አደረገ፤ ደግሞም ብልጽግናውን መለሰለት።* ይሖዋ ለኢዮብ ቀድሞ የነበረውን እጥፍ አድርጎ ሰጠው።+ 11 ወንድሞቹና እህቶቹ ሁሉ እንዲሁም የቀድሞ ወዳጆቹ ሁሉ+ ወደ እሱ መጡ፤ በቤቱም ከእሱ ጋር ምግብ በሉ። ሐዘናቸውን ገለጹለት፤ እንዲሁም ይሖዋ በእሱ ላይ እንዲደርስበት ከፈቀደው መከራ ሁሉ አጽናኑት። እያንዳንዳቸውም የገንዘብ ስጦታና የወርቅ ጌጥ ሰጡት።

12 በመሆኑም ይሖዋ ከፊተኛው የኢዮብ ሕይወት ይልቅ የኋለኛውን አብዝቶ ባረከ፤+ ኢዮብም 14,000 በጎች፣ 6,000 ግመሎች፣ 1,000 ጥማድ ከብቶችና 1,000 እንስት አህዮች አገኘ።+ 13 ደግሞም ሌሎች ሰባት ወንዶችና ሦስት ሴቶች ልጆች ወለደ።+ 14 የመጀመሪያዋን ሴት ልጁን ይሚማ፣ ሁለተኛዋን ቃስያ፣ ሦስተኛዋን ደግሞ ቄሬንሃጱክ ብሎ ስም አወጣላቸው። 15 በምድሪቱ ሁሉ የኢዮብን ሴቶች ልጆች ያህል የተዋቡ ሴቶች አልነበሩም፤ አባታቸውም ከወንድሞቻቸው ጋር ርስት ሰጣቸው።

16 ከዚህ በኋላ ኢዮብ 140 ዓመት ኖረ፤ እስከ አራት ትውልድም ድረስ ልጆችንና የልጅ ልጆችን አየ። 17 በመጨረሻም ኢዮብ ሸምግሎና ዕድሜ ጠግቦ ሞተ።

“የጥላቻ ዒላማ” የሚል ትርጉም ሊኖረው ይችላል።

ወይም “ነቀፋ የሌለበትና ቅን ሰው።”

ቃል በቃል “500 ጥማድ ከብቶች።”

ቃል በቃል “እንስት አህዮች።”

ወይም “ወንዶች ልጆቹ ሁሉ በእያንዳንዳቸው ቤት በተራቸው።”

የአምላክ ልጆች የሆኑትን መላእክት የሚያመለክት የዕብራይስጥ ፈሊጣዊ አነጋገር ነው።

ቃል በቃል “(በአገልጋዬ በኢዮብ) ላይ ልብህን አኑረሃል?”

ኢዮብ 1:1 ላይ የሚገኘውን የግርጌ ማስታወሻ ተመልከት።

ወይም “በቁጥጥርህ ሥር።”

“መብረቅ ወረደ” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ወይም “በአምላክ ላይ አግባብ ያልሆነ ነገር አልተናገረም።”

የአምላክ ልጆች የሆኑትን መላእክት የሚያመለክት የዕብራይስጥ ፈሊጣዊ አነጋገር ነው።

ቃል በቃል “(በአገልጋዬ በኢዮብ) ላይ ልብህን አኑረሃል?”

ወይም “ነቀፋ የሌለበትና ቅን ሰው።”

ቃል በቃል “እንድውጠው።”

ወይም “ለነፍሱ።”

ወይም “በቁጥጥርህ ሥር።”

ወይም “ነፍሱን።”

ወይም “በከባድ ቁስል መታው።”

እዚህ ላይ የገባው የዕብራይስጥ ቃል የሥነ ምግባር ንጽሕናን፣ ሁለት ልብ አለመሆንንና እንከን የለሽ መሆንን ያመለክታል።

ወይም “ኢዮብን የሚያውቁት ሦስት ሰዎች።”

ወይም “ጨለማና የሞት ጥላ።”

አዞን ወይም በውኃ ውስጥ የሚኖርን ትልቅና ኃይለኛ የሆነ ሌላ እንስሳ እንደሚያመለክት ይታመናል።

“የፈራረሱ ቦታዎችን ለራሳቸው ከገነቡ” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ወይም “ነፍሳቸው ለተመረረችስ።”

ወይም “አክብሮታዊ ፍርሃት።”

ኢዮብ 2:9 ላይ የሚገኘውን የግርጌ ማስታወሻ ተመልከት።

ወይም “የሚሸርቡ።”

ወይም “የደቦል አንበሶች።”

ወይም “በመልእክተኞቹም።”

ሰብዓ ሊቃናት “ከቅዱሳን መላእክትስ” ይላል።

ወይም “ከአንተ ጋር ቃል ኪዳን ይጋባሉ (ስምምነት ያደርጋሉ)።”

ቃል በቃል “ሰላም።”

ወይም “በችኮላ፤ በግዴለሽነት።”

ጣዕም የሌለውና ዝልግልግ ፈሳሽ የሚወጣው ተክል።

ወይም “ነፍሴ ተጸይፋለች።”

ይህ አባባል ኢዮብ የደረሰበትን መከራ ወይም አጽናኞቹ የሰጡትን ምክር ሊያመለክት ይችላል።

ወይም “ሕይወቴን (ነፍሴን) ባራዝምስ።”

ወይም “በቡድን የሚጓዙ ሳባውያንም።”

ቃል በቃል “ከጨቋኞች እንድትዋጁኝ።”

ወይም “ትለውጣላችሁ።”

ወይም “እስከ ማለዳ ወጋገን።”

ቃል በቃል “መልካም ነገር።”

ወይም “ሲኦል።” የሰው ልጆችን ሁሉ መቃብር ያመለክታል። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

ወይም “በነፍሴ ምሬት።”

ወይም “ነፍሴ . . . መረጠች።”

ቃል በቃል “ከአጥንቶቼም።”

ቃል በቃል “ልብህን ታኖርበትም።”

ለአጭር ጊዜ እንኳ የማትተወኝ ለምንድን ነው? ማለት ነው።

ቃል በቃል “ወደ ዓመፃቸው እጅ ልኳቸዋል።”

ወይም “እሱ ስለ አንተ ይነሳል።”

ቃል በቃል “ከልባቸውም ቃል አውጥተው።”

ቃል በቃል “መንገዶቻቸው እንደዚህ ናቸው።”

ወይም “የከሃዲ።”

ቃል በቃል “ቤት።”

ወይም “የድንጋይ ቤት ይመለከታል።”

ወይም “በሚዋጥበት።”

ወይም “መንገዱ በዚህ ሁኔታ ያከትማል።”

ኢዮብ 2:9 ላይ የሚገኘውን የግርጌ ማስታወሻ ተመልከት።

ቃል በቃል “(የክፉ ሰዎችን) እጅ አይዝም።”

ወይም “አምላክን ፍርድ ፊት ማቅረብ ቢፈልግ።”

ወይም “ያስወግዳል።”

የታላቁ ድብ ኅብረ ከዋክብት (ኧርሳ ሜጀር) ሊሆን ይችላል።

የኦርዮን ኅብረ ከዋክብት ሊሆን ይችላል።

በቶረስ ኅብረ ከዋክብት የታቀፉ ፐልያዲስ የሚባሉ ከዋክብት ሊሆኑ ይችላሉ።

ቃል በቃል “የደቡቡን ውስጠኛ ክፍሎች።”

እጅግ ግዙፍ የሆነ የባሕር ፍጥረት ሊሆን ይችላል።

“ተሟጋቼን” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ቃል በቃል “ማን ሊጠራኝ።”

ወይም “ንጹሕ ብሆን እንኳ።”

ቃል በቃል “ጠማማ።”

ወይም “ንጹሕ ብሆን እንኳ።”

ወይም “ነፍሴን አላውቅም።”

ወይም “እንቀዋለሁ፤ እቃወመዋለሁ።”

ወይም “ንጹሕ አቋማቸውን የሚጠብቁትንም።”

ቃል በቃል “ፊቶች።”

ቃል በቃል “ክፉ።”

ወይም “በፖታሽ።”

ወይም “መካከለኛ የሚሆን።”

ቃል በቃል “እጁንም በሁለታችን ላይ የሚጭን።”

ቃል በቃል “በትሩን ከእኔ ላይ ቢያነሳ።”

ወይም “ነፍሴ ተጸየፈቻት።”

ወይም “በነፍሴ ምሬት።”

ወይም “እስትንፋሴን፤ ሕይወቴን።”

ቃል በቃል “ደግሞም እነዚህን ነገሮች በልብህ ውስጥ ሰወርክ።”

ወይም “ትንሽ እንድጽናና።”

ወይም “ጨለማና የሞት ጥላ ወዳለበት።”

ወይም “ጉረኛ ሰው ትክክለኛ ይሆናል?”

ወይም “ማስተዋል የታከለበት ጥበብ።”

ወይም “ሁሉን ቻይ የሆነውን አምላክ ገደብ ማወቅ።”

ወይም “ከሲኦልም።” የሰው ልጆችን ሁሉ መቃብር ያመለክታል። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

ወይም “የዱር አህያ ሰው ሆኖ በሚወለድበት ጊዜ።”

ወይም “የነፍስ ሞት።”

ቃል በቃል “ሰዎች እናንተ ናችኋ!”

ቃል በቃል “ልብ።”

ወይም “በሚያዳልጣቸው።”

ጣዖትን እንደሚያመለክት ይታመናል።

“ለምድር ተናገር” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ወይም “በሕይወት ያለ ነገር ሁሉ ነፍስ።”

ወይም “እስትንፋስ።”

ቃል በቃል “ላንቃ።”

ወይም “ማስተዋል የታከለበት ጥበብ።”

ወይም “ያላቸውን ሁሉ ይገፍፋል።”

ቃል በቃል “የብርቱዎችን መታጠቂያ ያላላል።”

ቃል በቃል “ልብ።”

ወይም “ለእሱ ታደላላችሁ?”

ወይም “የማይረሱ።”

ቃል በቃል “የአመድ ምሳሌዎች።”

ቃል በቃል “የጋሻ ጉብጉባቶቻችሁ።”

ቃል በቃል “ሥጋዬን ለምን በጥርሴ እሸከማለሁ?”

ወይም “ነፍሴንስ።”

ወይም “ስለ መንገዴ እሟገታለሁ።”

ወይም “ከሃዲ።”

“መሟገት የሚችል ካለ ዝም ብዬ ሞቴን እጠብቃለሁ” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ቃል በቃል “ሁለት ነገሮች ብቻ አታድርግብኝ።”

ቃል በቃል “እሱ።” ኢዮብን የሚያመለክት ሳይሆን አይቀርም።

ወይም “በጭንቀት የተሞላ።”

“ይቆረጣል” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ቃል በቃል “እኔንም . . . ታቀርበኛለህ።”

ወይም “በሲኦል።” የሰው ልጆችን ሁሉ መቃብር ያመለክታል። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

ወይም “ለማየት ትጓጓለህ።”

ወይም “ነፍሱ የምታዝነው።”

ወይም “እንደ ነፋስ በሆነ እውቀት።”

ወይም “በደልህ አፍህን ያሠለጥነዋል።”

ወይም “በመላእክቱ።”

ቃል በቃል “ዳቦ።”

ወይም “ለማሸነፍም።”

ቃል በቃል “ወፍራም የጋሻ ጉብጉባት።”

ምንም ዓይነት የማንሰራራት ተስፋ እንደሌለው ያመለክታል።

ቃል በቃል “ከእሱም።”

ወይም “የከሃዲዎች።”

ወይም “እንደ ነፋስ ያሉ።”

ወይም “የእናንተ ነፍስ በእኔ ነፍስ ቦታ ብትሆን ኖሮ።”

ወይም “ከእኔ ጋር የሚሰበሰቡትን።”

ወይም “ብርታቴንም።” ቃል በቃል “ቀንዴንም።”

ወይም “የሞት ጥላም።”

“እንቅልፍ አጥቶ ይመለከታል” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ወይም “በዓመፅ ተግባራቸው ላይ ተተከለች።”

ቃል በቃል “መተረቻ፤ ምሳሌ።”

ወይም “ከሃዲ።”

ወይም “ሲኦል።” የሰው ልጆችን ሁሉ መቃብር ያመለክታል። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

ወይም “መቃብሩን።”

ወይም “የሲኦል።” የሰው ልጆችን ሁሉ መቃብር ያመለክታል። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

ኢዮብንና እንደ እሱ ያሉትን ወይም ለእሱ አዘኔታ የሚያሳዩ ሰዎችን ሊያመለክት ይችላል።

“ርኩስ” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ወይም “ነፍስህን።”

ወይም “ያስነክሰዋል።”

ቃል በቃል “የሞት የበኩር ልጅ።”

ወይም “አስከፊ ወደሆነ ሞትም።”

ቃል በቃል “የእሱ ያልሆነ ነገር በድንኳኑ ውስጥ ይኖራል።”

ቃል በቃል “ስም አይኖረውም።”

ወይም “ለጊዜው በሚኖርበት ስፍራም።”

ወይም “እኔን የምታበሳጩኝ።” የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

ወይም “ሰደባችሁኝ።”

ወይም “ዘመዶቼ ትተውኛል።”

ቃል በቃል “ለማህፀኔም ወንዶች ልጆች።” እኔን የወለደችኝ ማህፀን (የእናቴ ማህፀን) ማለት ነው።

ቃል በቃል “በጥርሴ ቆዳ።”

ቃል በቃል “ሥጋዬን የማትጠግቡትስ።”

ወይም “የሚቤዠኝ።”

ወይም “ኩላሊቴ በውስጤ መሥራት አቆመ።”

ቃል በቃል “ማስተዋሌ ያስገኘው መንፈስ።”

ወይም “የሰው ልጅ፤ አዳም።”

ወይም “የከሃዲ።”

በእስያና በአፍሪካ የሚገኝ እጅግ መርዘኛ የሆነ እባብ፤ ኮብራ።

ወይም “ሐሞት።”

ቃል በቃል “ምላስ።”

ቃል በቃል “እሱ።”

ቃል በቃል “በእሱ የቁጣ ቀን።”

ቃል በቃል “የመንፈሴ።”

ወይም “ኃያል።”

ወይም “በእምቢልታም ድምፅ።”

ወይም “በቅጽበትም።” ያለምንም ሥቃይ ወዲያው መሞታቸውን ያመለክታል።

ወይም “ሲኦል።” የሰው ልጆችን ሁሉ መቃብር ያመለክታል። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

ወይም “ምክር፤ ዕቅድ።”

ወይም “ለሁለት ቢከፈል።”

ወይም “እሱን አንዳች ነገር ሊያስተምረው።”

ቃል በቃል “የአጥንቶቹ መቅኒም እርጥብ (ሆኖ)።”

ወይም “ነፍሱ እንደተመረረች።”

“በእኔ ላይ የኃይል እርምጃ ለመውሰድ” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ቃል በቃል “ምልክቶችስ።”

ወይም “የደረቅ ወንዝ።”

ቃል በቃል “የሰውን ዘር ሁሉ ከኋላው ይጎትታል።”

ወይም “ያስደስተዋል?”

ኢዮብ 2:9 ላይ የሚገኘውን የግርጌ ማስታወሻ ተመልከት።

ወይም “አክብሮታዊ ፍርሃት።”

ቃል በቃል “የተራቆቱትን ሰዎች ልብስ ትገፋለህ።”

ወይም “ወላጅ አልባ የሆኑ ልጆችን።”

ወይም “ሕይወታቸው በአጭሩ ተቀጭቷል።”

ቃል በቃል “በወንዝ።”

ወይም “ያልተጣራ ወርቅህን።”

ወይም “ደረቅ ወንዝ።”

ወይም “ያልተጣራ ወርቅና።”

ወይም “ቀና ብሎ የማያየውን።”

ወይም “ቅሬታዬ ቅጥ ያጣ ነው።”

ወይም “ከታዘዝኩት።”

ወይም “ነፍሱ . . . ከፈለገች።”

ወይም “ለእኔ የታዘዘውን።”

ይህ ቃል የፍርድ ቀኑን ያመለክታል።

“መኖ” ማለትም ሊሆን ይችላል።

“በእርከኖቹ መካከል ዘይት ይጨምቃሉ” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ወይም “የቆሰሉት ነፍሳት።”

“አምላክ ግን ማንንም ተጠያቂ አያደርግም” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ቃል በቃል “ሰርስረው።”

ቃል በቃል “እሱ በውኃ ላይ ፈጣን ነው።”

ወይም “ሲኦል።” የሰው ልጆችን ሁሉ መቃብር ያመለክታል። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

ቃል በቃል “ማህፀን።”

ቃል በቃል “እሱ።”

ቃል በቃል “እሱ።”

ቃል በቃል “በመንገዶቻቸው።”

ቃል በቃል “በከፍታዎቹ።”

ወይም “የጠራ።”

ወይም “ማስተዋል የታከለበት ጥበብህን።”

ወይም “ጥበብህን ሳትቆጥብ።”

ቃል በቃል “የማንስ እስትንፋስ (መንፈስ) ከአንተ ዘንድ ወጣ?”

ወይም “ሲኦል።” የሰው ልጆችን ሁሉ መቃብር ያመለክታል። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

ቃል በቃል “በእሱ።”

ወይም “አባዶንም።”

ቃል በቃል “ሰሜኑን።”

ቃል በቃል “በባዶ።”

ቃል በቃል “ክበብን።”

ቃል በቃል “ረዓብን።”

ወይም “በነፋሱ።”

ወይም “በፍጥነት የሚሳበውን።”

ቃል በቃል “ምሳሌውን።”

ወይም “ነፍሴን መራራ ባደረጋት።”

ኢዮብ 2:9 ላይ የሚገኘውን የግርጌ ማስታወሻ ተመልከት።

ወይም “ከእኔ አላርቅም! እጠብቃለሁ!”

ወይም “ስለ የትኛውም ቀኔ።”

ወይም “አይዘልፈኝም።”

ወይም “ከሃዲ።”

ወይም “ነፍሱን።”

“በአምላክ እጅ” ማለትም ሊሆን ይችላል።

“እጃቸውን ያጨበጭቡበታል፤ እንዲሁም ካሉበት ቦታ ሆነው ያፏጩበታል” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ቃል በቃል “(ከዓለት) ይፈስሳል።”

ቃል በቃል “ድንጋይ።”

ማዕድን የማውጣት ሥራን የሚያመለክት ይመስላል።

ይህ ቃል የገባው ማዕድኑን ለማመልከት ነው።

ወይም “ከጠራ።”

ወይም “የኩሽ።”

ቃል በቃል “ክብደት።”

ቃል በቃል “ምሳሌውን።”

ወይም “አገልጋዮቼም።”

ቃል በቃል “ራሳቸውን ይደብቁ።”

ወይም “እጅጌ እንደሌለው ቀሚስና።”

ቃል በቃል “በጎጆዬ።”

ቃል በቃል “ይንጠባጠብ።”

“የፊቴን ብርሃን አላጨለሙም” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ወይም “በደረቅ ወንዞች።”

ቃል በቃል “ተገርፈው (ተባረዋል)።”

ቃል በቃል “ምሳሌ፤ መተረቻ።”

ቃል በቃል “የደጋኔን አውታር አላልቶብኛል።”

ወይም “ልጓሙን ይፈታሉ።”

“የሚረዳቸው ሳይኖር መከራዬን ያባብሳሉ” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ወይም “ነፍሴ።”

ቃል በቃል “በሌሊት አጥንቶቼ ተቦርቡረዋል።”

“የደረሰብኝ ከባድ መከራ ሰውነቴን አበላሸው” ማለትም ሊሆን ይችላል።

“በኃይል አላትመህ በታተንከኝ” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ቃል በቃል “በፍርስራሽ ክምር (ላይ እጁን የሚያነሳ አይኖርም)።”

ወይም “የመከራ ቀን ለገጠማቸው ሰዎች።”

ወይም “ነፍሴስ ለድሃው አላዘነችም?”

“ከትኩሳቱ” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ወይም “እምቢልታዬም።”

“ከሚዋሹ ሰዎች ጋር ሄጄ” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ኢዮብ 2:9 ላይ የሚገኘውን የግርጌ ማስታወሻ ተመልከት።

ወይም “ዘሮቼም ይነቀሉ።”

ቃል በቃል “ሌሎች ወንዶችም በእሷ ላይ ይንበርከኩ።”

ቃል በቃል “በልቶ (ውጦ) የሚያወድም።”

ወይም “የሚነቅል።”

ወይም “ሙግታቸውን።”

ቃል በቃል “ሲነሳ።”

ቃል በቃል “በማህፀን ውስጥ።”

ቃል በቃል “እንዲደክም።”

ቃል በቃል “እሱን።”

ቃል በቃል “ከእናቴም ማህፀን።”

ቃል በቃል “እሷን።”

“በከተማዋ በር ላይ ደጋፊ እንዳለኝ አይቼ ወላጅ አልባ በሆነው ልጅ ላይ” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ወይም “ብራኳዬ።”

ወይም “ከመጋጠሚያው፤ ከላይኛው አጥንት።”

ቃል በቃል “ብርሃን (ሲፈነጥቅ)።”

ወይም “ነፍሱን።”

ቃል በቃል “ሥጋ።”

ወይም “የባዕድ አገር ሰው።”

ወይም “ፊርማዬ ይኸውና።”

ወይም “የባለቤቶቿንም ነፍስ።”

ወይም “በገዛ ዓይኑ ጻድቅ ስለነበር።”

ወይም “ነፍሱን።”

ቃል በቃል “ቀኖቼ ጥቂት ናቸው።”

ቃል በቃል “ቀኖች (ይናገሩ)።”

ወይም “ብዙ ቀን።”

ወይም “ኢዮብን መውቀስ።”

ወይም “ለማንም ሰው የማዕረግ ስም አልሰጥም።”

ቃል በቃል “ምላሴም ከላንቃዬ ጋር።”

ቃል በቃል “ማኅተም ያደርግባቸዋል።”

ወይም “ሕይወቱን።”

ወይም “ከመቃብር።”

ወይም “በመሣሪያ (በተወንጫፊ መሣሪያ)።”

ቃል በቃል “ሕይወቱ።”

ወይም “ነፍሱም ምርጥ የሆነ ምግብ ትጠላለች።”

ወይም “ይራቆታሉ።”

ወይም “ሕይወቱ።”

ወይም “መቃብር።”

ወይም “መልአክ።”

ወይም “ወደ መቃብር።”

ወይም “ጤናማ ይሁን።”

ቃል በቃል “(እንዲህ በማለት) ይዘምራል።”

“ደግሞም አልጠቀመኝም” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ወይም “ሕይወቴን።”

ወይም “ወደ መቃብር።”

ወይም “ነፍሱን ከመቃብር።”

ቃል በቃል “ላንቃ።”

ቃል በቃል “እናንተ ልብ (ያላችሁ ሰዎች)።”

ወይም “ሰው በሚኖርበት ምድር።”

ቃል በቃል “ልቡን።”

ቃል በቃል “ሥጋ።”

ወይም “የተከበረውን ከችግረኛው።”

ወይም “ከሃዲ።”

ቃል በቃል “ልብ (ያላቸው)።”

“አባቴ ሆይ፣ ኢዮብ እስከ መጨረሻው ድረስ ይፈተን” ማለትም ሊሆን ይችላል።

አምላክን የሚያመለክት ሳይሆን አይቀርም።

ቃል በቃል “ክንድ።”

ወይም “ውሸት።”

ቃል በቃል “የልቡ ኃይል።”

“ነገሥታትን በዙፋን ላይ ያስቀምጣል” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ወይም “በመሣሪያ (በተወንጫፊ መሣሪያ)።”

ወይም “ከሃዲ።”

ወይም “ነፍሳቸው ትሞታለች።”

ግብረ ሰዶማውያን ሆነው የሴት ዓይነት ሚና ያላቸውን ወንዶች ያመለክታል።

“ሕይወታቸው ይቀጫል” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ቃል በቃል “እሱ።”

ወይም “ይሁንና ቁጣ በንቀት ወደማጨብጨብ።”

“እሱን የተቸው፤ ተጠያቂ ያደረገው” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ወይም “አይመረመርም።”

ቃል በቃል “ብርሃኑን።”

ቃል በቃል “ሥር።”

“ለሕዝቦች ይሟገታል” ማለትም ሊሆን ይችላል።

“ምን” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ቃል በቃል “በሰው ሁሉ እጅ ላይ ማኅተም ያኖራል።”

ወይም “ፍሬያማ በሆነው።”

ቃል በቃል “ለበትርም ሆነ።”

ወይም “እንደሚያዝዝ።”

ወይም “ቀጥቅጠህ ልትሠራ።”

የፀሐይን ብርሃን ያመለክታል።

ቃል በቃል “በልብ ጥበበኛ ለሆኑ።”

የአምላክ ልጆች የሆኑትን መላእክት የሚያመለክት የዕብራይስጥ ፈሊጣዊ አነጋገር ነው።

ወይም “የሞት ጥላንስ።”

ቃል በቃል “ቀኖችህ (ብዙ ስለሆኑ)።”

“መብረቅ” ማለትም ሊሆን ይችላል።

በቶረስ ኅብረ ከዋክብት የታቀፉ ፐልያዲስ የሚባሉ ከዋክብት ሊሆኑ ይችላሉ።

የኦርዮን ኅብረ ከዋክብት ሊሆን ይችላል።

ቃል በቃል “ማዛሮትን።” በ2ነገ 23:5 ላይ የገባው ከዚህ ቃል ጋር ተዛማጅነት ያለው በብዙ ቁጥር የተሠራበት ቃል የዞዲያክ ኅብረ ከዋክብትን ያመለክታል።

የታላቁ ድብ ኅብረ ከዋክብት (ኧርሳ ሜጀር) ሊሆን ይችላል።

“የእሱን” ማለትም ሊሆን ይችላል።

“በሰው ውስጥ” ማለትም ሊሆን ይችላል።

“ለአእምሮ” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ቅርንጫፍ የሚመስሉ ቀንዶች ያሉት አጥቢ እንስሳ፤ ከአጋዘን ጋር ይመሳሰላል።

ወይም “የሸለቆውን ጓል ይከሰክሳል።”

ባለ ረጃጅም እግር ትልቅ አሞራ።

ቃል በቃል “(ጥበብን) እንድትረሳ አድርጓታል።”

ቃል በቃል “የጦር መሣሪያን ለመገናኘት ይወጣል።”

ቃል በቃል “ምድርን (መሬትን) ይውጣል።”

“ጆሮውን ማመን ያቅተዋል” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ቃል በቃል “በቋጥኝ ጥርስ ላይ።”

ወይም “ዋጋ ታሳጣለህ?”

ቃል በቃል “ፊታቸውንም።”

ወይም “አመሰግንሃለሁ።”

ጉማሬ ሊሆን ይችላል።

ወይም “በደረቅ ወንዝ።”

ቃል በቃል “ወጥመድ።”

አዞ ሊሆን ይችላል።

ቃል በቃል “እንግጫ።”

ቃል በቃል “በእሾህ።”

ወይም “ተርበትብተህ ትወድቃለህ።”

ቃል በቃል “የፊቱን።”

“ጀርባው ላይ ያሉት እርስ በርስ የተጣበቁና በረድፍ የተቀመጡ ቅርፊቶች እንዲታበይ ያደርጉታል” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ጥርስ መሳይ ጉጦች ያሉት የእህል መውቂያ።

ወይም “ቃሌን አስተባብላለሁ።”

ቃል በቃል “በእርግጥ ፊቱን ቀና አደርጋለሁ።”

ቃል በቃል “ይሖዋ የኢዮብን ምርኮ መለሰለት።”

    የኢትዮጵያ ምልክት ቋንቋ ጽሑፎች (2011-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • የኢትዮጵያ ምልክት ቋንቋ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ