የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
የኢትዮጵያ ምልክት ቋንቋ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • nwt ዘኁልቁ 1:1-36:13
  • ዘኁልቁ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ዘኁልቁ
  • አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ
አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ
ዘኁልቁ

ዘኁልቁ

1 ይሖዋም እስራኤላውያን ከግብፅ ምድር በወጡ በሁለተኛው ዓመት ሁለተኛ ወር፣ የመጀመሪያ ቀን+ ላይ በሲና ምድረ በዳ+ በመገናኛ ድንኳኑ+ ውስጥ ሙሴን አነጋገረው። እንዲህም አለው፦ 2 “የእስራኤልን ማኅበረሰብ* በሙሉ በየቤተሰባቸው፣ በየአባቶቻቸው ቤትና በስም በተዘረዘሩት ወንዶች ሁሉ ቁጥር መሠረት በግለሰብ ደረጃ ቁጠር።+ 3 አንተና አሮን ዕድሜያቸው 20 ዓመትና ከዚያ በላይ የሆናቸውን+ በእስራኤል ውስጥ ወደ ሠራዊቱ መቀላቀል የሚችሉትን ሁሉ በየምድባቸው* መዝግቡ።

4 “ከየነገዱ አንድ ሰው ውሰድ፤ እያንዳንዳቸውም ለየአባቶቻቸው ቤት መሪ ይሆናሉ።+ 5 ከአንተ ጋር የሚቆሙትም ወንዶች ስም የሚከተለው ነው፦ ከሮቤል ነገድ የሸደኡር ልጅ ኤሊጹር፣+ 6 ከስምዖን ነገድ የጹሪሻዳይ ልጅ ሸሉሚኤል፣+ 7 ከይሁዳ ነገድ የአሚናዳብ ልጅ ነአሶን፣+ 8 ከይሳኮር ነገድ የጹአር ልጅ ናትናኤል፣+ 9 ከዛብሎን ነገድ የሄሎን ልጅ ኤልያብ፣+ 10 ከዮሴፍ ወንዶች ልጆች ይኸውም ከኤፍሬም+ ነገድ የአሚሁድ ልጅ ኤሊሻማ፣ ከምናሴ ነገድ ደግሞ የፐዳጹር ልጅ ገማልያል፣ 11 ከቢንያም ነገድ የጊድኦኒ ልጅ አቢዳን፣+ 12 ከዳን ነገድ የአሚሻዳይ ልጅ አሂዔዜር፣+ 13 ከአሴር ነገድ የኦክራን ልጅ ፓጊኤል፣+ 14 ከጋድ ነገድ የደኡዔል ልጅ ኤሊያሳፍ+ 15 እንዲሁም ከንፍታሌም ነገድ የኤናን ልጅ አሂራ።+ 16 እነዚህ ከማኅበረሰቡ የተመረጡ ናቸው። እነሱም የአባቶቻቸው ነገዶች መሪዎች+ ማለትም የእስራኤል የሺህ አለቆች+ ናቸው።”

17 በመሆኑም ሙሴና አሮን በስም የተጠቀሱትን እነዚህን ወንዶች ወሰዱ። 18 እነሱም ዕድሜያቸው 20 ዓመትና ከዚያ በላይ+ የሆኑት በየስማቸው፣ በየቤተሰባቸውና በየአባቶቻቸው ቤት በግለሰብ ደረጃ እንዲመዘገቡ ለማድረግ በሁለተኛው ወር በመጀመሪያው ቀን ላይ መላውን ማኅበረሰብ ሰበሰቡ፤ 19 ይህን ያደረጉት ልክ ይሖዋ ሙሴን ባዘዘው መሠረት ነው። እሱም በሲና ምድረ በዳ መዘገባቸው።+

20 የእስራኤል የበኩር ልጅ+ ዝርያዎች የሆኑት የሮቤል ልጆች በየስማቸው፣ በየቤተሰባቸውና በየአባቶቻቸው ቤት በዝርዝር ተመዘገቡ። ወደ ሠራዊቱ መቀላቀል የሚችሉት ዕድሜያቸው 20 ዓመትና ከዚያ በላይ የሆኑት ወንዶች ሁሉ በግለሰብ ደረጃ ተቆጠሩ፤ 21 ከሮቤል ነገድ የተመዘገቡት 46,500 ነበሩ።

22 የስምዖን+ ዝርያዎች በየስማቸው፣ በየቤተሰባቸውና በየአባቶቻቸው ቤት በዝርዝር ተመዘገቡ። ወደ ሠራዊቱ መቀላቀል የሚችሉት ዕድሜያቸው 20 ዓመትና ከዚያ በላይ የሆኑት ወንዶች ሁሉ በግለሰብ ደረጃ ተቆጠሩ፤ 23 ከስምዖን ነገድ የተመዘገቡት 59,300 ነበሩ።

24 የጋድ+ ዝርያዎች በየስማቸው፣ በየቤተሰባቸውና በየአባቶቻቸው ቤት በዝርዝር ተመዘገቡ። ወደ ሠራዊቱ መቀላቀል የሚችሉት ዕድሜያቸው 20 ዓመትና ከዚያ በላይ የሆኑት ወንዶች ሁሉ ተቆጠሩ፤ 25 ከጋድ ነገድ የተመዘገቡት 45,650 ነበሩ።

26 የይሁዳ+ ዝርያዎች በየስማቸው፣ በየቤተሰባቸውና በየአባቶቻቸው ቤት በዝርዝር ተመዘገቡ። ወደ ሠራዊቱ መቀላቀል የሚችሉት ዕድሜያቸው 20 ዓመትና ከዚያ በላይ የሆኑት ወንዶች ሁሉ ተቆጠሩ፤ 27 ከይሁዳ ነገድ የተመዘገቡት 74,600 ነበሩ።

28 የይሳኮር+ ዝርያዎች በየስማቸው፣ በየቤተሰባቸውና በየአባቶቻቸው ቤት በዝርዝር ተመዘገቡ። ወደ ሠራዊቱ መቀላቀል የሚችሉት ዕድሜያቸው 20 ዓመትና ከዚያ በላይ የሆኑት ወንዶች ሁሉ ተቆጠሩ፤ 29 ከይሳኮር ነገድ የተመዘገቡት 54,400 ነበሩ።

30 የዛብሎን+ ዝርያዎች በየስማቸው፣ በየቤተሰባቸውና በየአባቶቻቸው ቤት በዝርዝር ተመዘገቡ። ወደ ሠራዊቱ መቀላቀል የሚችሉት ዕድሜያቸው 20 ዓመትና ከዚያ በላይ የሆኑት ወንዶች ሁሉ ተቆጠሩ፤ 31 ከዛብሎን ነገድ የተመዘገቡት 57,400 ነበሩ።

32 በኤፍሬም+ በኩል ያሉት የዮሴፍ ዝርያዎች በየስማቸው፣ በየቤተሰባቸውና በየአባቶቻቸው ቤት በዝርዝር ተመዘገቡ። ወደ ሠራዊቱ መቀላቀል የሚችሉት ዕድሜያቸው 20 ዓመትና ከዚያ በላይ የሆኑት ወንዶች ሁሉ ተቆጠሩ፤ 33 ከኤፍሬም ነገድ የተመዘገቡት 40,500 ነበሩ።

34 የምናሴ+ ዝርያዎች በየስማቸው፣ በየቤተሰባቸውና በየአባቶቻቸው ቤት በዝርዝር ተመዘገቡ። ወደ ሠራዊቱ መቀላቀል የሚችሉት ዕድሜያቸው 20 ዓመትና ከዚያ በላይ የሆኑት ወንዶች ሁሉ ተቆጠሩ፤ 35 ከምናሴ ነገድ የተመዘገቡት 32,200 ነበሩ።

36 የቢንያም+ ዝርያዎች በየስማቸው፣ በየቤተሰባቸውና በየአባቶቻቸው ቤት በዝርዝር ተመዘገቡ። ወደ ሠራዊቱ መቀላቀል የሚችሉት ዕድሜያቸው 20 ዓመትና ከዚያ በላይ የሆኑት ወንዶች ሁሉ ተቆጠሩ፤ 37 ከቢንያም ነገድ የተመዘገቡት 35,400 ነበሩ።

38 የዳን+ ዝርያዎች በየስማቸው፣ በየቤተሰባቸውና በየአባቶቻቸው ቤት በዝርዝር ተመዘገቡ። ወደ ሠራዊቱ መቀላቀል የሚችሉት ዕድሜያቸው 20 ዓመትና ከዚያ በላይ የሆኑት ወንዶች ሁሉ ተቆጠሩ፤ 39 ከዳን ነገድ የተመዘገቡት 62,700 ነበሩ።

40 የአሴር+ ዝርያዎች በየስማቸው፣ በየቤተሰባቸውና በየአባቶቻቸው ቤት በዝርዝር ተመዘገቡ። ወደ ሠራዊቱ መቀላቀል የሚችሉት ዕድሜያቸው 20 ዓመትና ከዚያ በላይ የሆኑት ወንዶች ሁሉ ተቆጠሩ፤ 41 ከአሴር ነገድ የተመዘገቡት 41,500 ነበሩ።

42 የንፍታሌም+ ዝርያዎች በየስማቸው፣ በየቤተሰባቸውና በየአባቶቻቸው ቤት በዝርዝር ተመዘገቡ። ወደ ሠራዊቱ መቀላቀል የሚችሉት ዕድሜያቸው 20 ዓመትና ከዚያ በላይ የሆኑት ወንዶች ሁሉ ተቆጠሩ፤ 43 ከንፍታሌም ነገድ የተመዘገቡት 53,400 ነበሩ።

44 ሙሴ ከአሮንና እያንዳንዳቸው የአባቶቻቸውን ቤት ከሚወክሉት ከ12 የእስራኤል አለቆች ጋር በመሆን የመዘገባቸው እነዚህ ናቸው። 45 በእስራኤል ውስጥ ወደ ሠራዊቱ መቀላቀል የሚችሉት ዕድሜያቸው 20 ዓመትና ከዚያ በላይ የሆኑት እስራኤላውያን ሁሉ በየአባቶቻቸው ቤት ተመዘገቡ፤ 46 የተመዘገቡትም ሰዎች ጠቅላላ ቁጥር 603,550 ነበር።+

47 ይሁን እንጂ ሌዋውያኑ+ ሌሎቹ እንደተመዘገቡት በየአባቶቻቸው ነገድ መሠረት አልተመዘገቡም።+ 48 ስለዚህ ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ 49 “የሌዊን ነገድ ብቻ አትመዝግብ፤ ቁጥራቸውም በሌሎቹ እስራኤላውያን ቁጥር ውስጥ እንዲካተት አታድርግ።+ 50 ሌዋውያኑን በምሥክሩ+ የማደሪያ ድንኳን፣ በዕቃዎቹ ሁሉና ከዚያ ጋር ተያያዥነት ባላቸው ነገሮች ሁሉ ላይ ሹማቸው።+ እነሱም የማደሪያ ድንኳኑንና ዕቃዎቹን በሙሉ ይሸከማሉ፤+ በዚያም ያገለግላሉ፤+ በማደሪያ ድንኳኑም ዙሪያ ይሰፍራሉ።+ 51 የማደሪያ ድንኳኑ ከቦታ ወደ ቦታ በሚንቀሳቀስበት ጊዜ ሁሉ ሌዋውያኑ ይንቀሉት፤+ የማደሪያ ድንኳኑ በሚተከልበት ጊዜም ሌዋውያኑ ይትከሉት። ያልተፈቀደለት ማንኛውም ሰው* ወደዚያ ቢቀርብ ይገደል።+

52 “እያንዳንዱ እስራኤላዊ በየተመደበበት ሰፈር ድንኳኑን ይትከል፤ እያንዳንዱም ሰው ሦስት ነገዶችን ባቀፈው ቡድኑ*+ ውስጥ በየምድቡ* ይስፈር። 53  በእስራኤል ማኅበረሰብ ላይ ቁጣ እንዳይወርድ ሌዋውያኑ በምሥክሩ የማደሪያ ድንኳን ዙሪያ ይስፈሩ፤+ ሌዋውያኑም የምሥክሩን የማደሪያ ድንኳን የመንከባከብ* ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል።”+

54 እስራኤላውያንም ይሖዋ ሙሴን ያዘዘውን ሁሉ አደረጉ። ልክ እንደዚያው አደረጉ።

2 ይሖዋ ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፦ 2 “እስራኤላውያን ሦስት ነገዶችን ላቀፈው ምድባቸው+ በተሰጠው ቦታ ይስፈሩ፤ እያንዳንዱም ሰው ለአባቶቹ ቤት በቆመው ዓርማ* አጠገብ ይስፈር። ፊታቸውን ወደ መገናኛ ድንኳኑ አድርገው ዙሪያውን ይስፈሩ።

3 “በስተ ምሥራቅ ፀሐይ በምትወጣበት አቅጣጫ በየምድቡ* የሚሰፍረው ሦስት ነገዶችን ያቀፈው የይሁዳ ምድብ ይሆናል፤ የይሁዳ ልጆች አለቃ የአሚናዳብ ልጅ ነአሶን+ ነው። 4 በሠራዊቱ ውስጥ የተመዘገቡትም 74,600 ናቸው።+ 5 ከእሱም ቀጥሎ የሚሰፍረው የይሳኮር ነገድ ይሆናል፤ የይሳኮር ልጆች አለቃ የጹአር ልጅ ናትናኤል+ ነው። 6 በሠራዊቱ ውስጥ የተመዘገቡትም 54,400 ናቸው።+ 7 ከዚያ ቀጥሎ የዛብሎን ነገድ ይስፈር፤ የዛብሎን ልጆች አለቃ የሄሎን ልጅ ኤልያብ+ ነው። 8 በሠራዊቱ ውስጥ የተመዘገቡትም 57,400 ናቸው።+

9 “በይሁዳ ምድብ በሠራዊቱ ውስጥ የተመዘገቡት በአጠቃላይ 186,400 ናቸው። መጀመሪያ ድንኳናቸውን ነቅለው የሚነሱት እነሱ ይሆናሉ።+

10 “ሦስት ነገዶችን ያቀፈው የሮቤል+ ምድብ በየምድቡ* በመሆን በስተ ደቡብ አቅጣጫ ይስፈር፤ የሮቤል ልጆች አለቃ የሸደኡር ልጅ ኤሊጹር+ ነው። 11 በሠራዊቱ ውስጥ የተመዘገቡትም 46,500 ናቸው።+ 12 ከእሱ ቀጥሎ የሚሰፍረው የስምዖን ነገድ ይሆናል፤ የስምዖን ልጆች አለቃ የጹሪሻዳይ ልጅ ሸሉሚኤል+ ነው። 13 በሠራዊቱ ውስጥ የተመዘገቡትም 59,300 ናቸው።+ 14 ከዚያ ቀጥሎ የጋድ ነገድ ይስፈር፤ የጋድ ልጆች አለቃ የረኡዔል ልጅ ኤሊያሳፍ+ ነው። 15 በሠራዊቱ ውስጥ የተመዘገቡትም 45,650 ናቸው።+

16 “በሮቤል ምድብ በሠራዊቱ ውስጥ የተመዘገቡት በአጠቃላይ 151,450 ናቸው፤ በሁለተኛ ደረጃ ድንኳናቸውን ነቅለው የሚነሱት እነሱ ናቸው።+

17 “የመገናኛ ድንኳኑ ከቦታ ወደ ቦታ በሚንቀሳቀስበት ጊዜ+ የሌዋውያኑ ሰፈር በሌሎቹ ሰፈሮች መሃል መሆን ይኖርበታል።

“እነሱም ልክ በሰፈሩበት ሁኔታ እያንዳንዳቸው ቦታቸውን ጠብቀው+ ሦስት ነገድ ባቀፈው ምድባቸው መሠረት መጓዝ ይኖርባቸዋል።

18 “ሦስት ነገዶችን ያቀፈው የኤፍሬም ምድብ በየምድቡ* በመሆን በስተ ምዕራብ አቅጣጫ ይስፈር፤ የኤፍሬም ልጆች አለቃ የአሚሁድ ልጅ ኤሊሻማ+ ነው። 19 በሠራዊቱ ውስጥ የተመዘገቡትም 40,500 ናቸው።+ 20 ከእሱም ቀጥሎ የምናሴ+ ነገድ ይስፈር፤ የምናሴ ልጆች አለቃ የፐዳጹር ልጅ ገማልያል+ ነው። 21 በሠራዊቱ ውስጥ የተመዘገቡትም 32,200 ናቸው።+ 22 ከዚያ ቀጥሎ የቢንያም ነገድ ይስፈር፤ የቢንያም ልጆች አለቃ የጊድኦኒ ልጅ አቢዳን+ ነው። 23 በሠራዊቱ ውስጥ የተመዘገቡትም 35,400 ናቸው።+

24 “በኤፍሬም ምድብ በሠራዊቱ ውስጥ የተመዘገቡት በአጠቃላይ 108,100 ናቸው፤ በሦስተኛ ደረጃ ድንኳናቸውን ነቅለው የሚነሱት እነሱ ናቸው።+

25 “ሦስት ነገዶችን ያቀፈው የዳን ምድብ በየምድቡ* በመሆን በስተ ሰሜን አቅጣጫ ይስፈር፤ የዳን ልጆች አለቃ የአሚሻዳይ ልጅ አሂዔዜር+ ነው። 26 በሠራዊቱ ውስጥ የተመዘገቡትም 62,700 ናቸው።+ 27 ከእሱም ቀጥሎ የሚሰፍረው የአሴር ነገድ ይሆናል፤ የአሴር ልጆች አለቃ የኦክራን ልጅ ፓጊኤል+ ነው። 28 በሠራዊቱ ውስጥ የተመዘገቡትም 41,500 ናቸው።+ 29 ከዚያ ቀጥሎ የንፍታሌም ነገድ ይስፈር፤ የንፍታሌም ልጆች አለቃ የኤናን ልጅ አሂራ+ ነው። 30 በሠራዊቱ ውስጥ የተመዘገቡትም 53,400 ናቸው።+

31 “በዳን ምድብ የተመዘገቡት በአጠቃላይ 157,600 ናቸው። ሦስት ነገዶችን ባቀፈው ምድባቸው መሠረት መጨረሻ ላይ ድንኳናቸውን ነቅለው የሚነሱት እነሱ ናቸው።”+

32 በአባቶቻቸው ቤት መሠረት የተመዘገቡት እስራኤላውያን እነዚህ ነበሩ፤ ወደ ሠራዊቱ ለመቀላቀል በሰፈሩ ውስጥ የተመዘገቡት በአጠቃላይ 603,550 ነበሩ።+ 33 ሌዋውያኑ ግን ልክ ይሖዋ ሙሴን ባዘዘው መሠረት ከሌሎቹ እስራኤላውያን ጋር+ አልተመዘገቡም።+ 34 እስራኤላውያንም ይሖዋ ሙሴን ያዘዘውን ሁሉ አደረጉ። እያንዳንዳቸው በየቤተሰባቸውና በየአባቶቻቸው ቤት በመሆን ሦስት ነገዶችን ባቀፈው ምድባቸው+ መሠረት የሰፈሩትም ሆነ ድንኳናቸውን ነቅለው የተነሱት በዚህ መንገድ ነው።+

3 ይሖዋ በሲና ተራራ+ ላይ ከሙሴ ጋር በተነጋገረ ጊዜ የአሮንና የሙሴ የቤተሰብ ሐረግ* ይህ ነበር። 2 የአሮን ወንዶች ልጆች ስም ይህ ነው፦ የበኩር ልጁ ናዳብ፣ አቢሁ፣+ አልዓዛርና+ ኢታምር።+ 3 የአሮን ወንዶች ልጆች ስም ይኸውም ካህናት ሆነው እንዲያገለግሉ የተሾሙት* ቅቡዕ የሆኑት ካህናት ስም ይህ ነበር።+ 4 ይሁንና ናዳብና አቢሁ በሲና ምድረ በዳ በይሖዋ ፊት ያልተፈቀደ እሳት ባቀረቡ ጊዜ በይሖዋ ፊት ሞቱ፤+ እነሱም ወንዶች ልጆች አልነበሯቸውም። አልዓዛርና+ ኢታምር+ ግን ከአባታቸው ከአሮን ጋር በክህነት ማገልገላቸውን ቀጠሉ።

5 ከዚያም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ 6 “የሌዊን ነገድ+ አምጥተህ በካህኑ በአሮን ፊት አቁመው፤ እነሱም ያገልግሉት።+ 7 ከመገናኛ ድንኳኑ ጋር በተያያዘ የሚያከናውኑትን አገልግሎት በመፈጸም ለእሱም ሆነ ለመላው ማኅበረሰብ ያለባቸውን ኃላፊነት በመገናኛ ድንኳኑ ፊት ይወጡ። 8 የመገናኛ ድንኳኑን ዕቃዎች በሙሉ በኃላፊነት መቆጣጠርና+ ከማደሪያ ድንኳኑ ጋር የተያያዘውን አገልግሎት በማከናወን ለእስራኤል ልጆች ያለባቸውን ኃላፊነት መወጣት ይኖርባቸዋል።+ 9 ሌዋውያኑን ለአሮንና ለወንዶች ልጆቹ ስጣቸው። እነሱ የተሰጡ ናቸው፤ ከእስራኤላውያን መካከል ለእሱ የተሰጡ ናቸው።+ 10 አሮንንና ወንዶች ልጆቹን ሹማቸው፤ እነሱም የክህነት ኃላፊነታቸውን ይወጡ፤+ ማንኛውም ያልተፈቀደለት ሰው* ወደ መቅደሱ ቢቀርብ ይገደል።”+

11 ይሖዋም ሙሴን እንዲህ አለው፦ 12 “በእስራኤላውያን በኩሮች ሁሉ* ምትክ ሌዋውያኑን ከእስራኤላውያን መካከል እወስዳለሁ፤+ ሌዋውያኑም የእኔ ይሆናሉ። 13 ምክንያቱም በኩር ሁሉ የእኔ ነው።+ በግብፅ ምድር ያለውን በኩር ሁሉ በመታሁበት ቀን+ በእስራኤላውያን መካከል ያለውን የሰውም ሆነ የእንስሳ በኩር ለራሴ ቀድሻለሁ።+ እነሱ የእኔ ይሆናሉ። እኔ ይሖዋ ነኝ።”

14 በተጨማሪም ይሖዋ በሲና ምድረ በዳ+ ሙሴን እንዲህ አለው፦ 15 “የሌዊን ወንዶች ልጆች በየአባቶቻቸው ቤቶችና በየቤተሰባቸው መዝግብ። አንድ ወርና ከዚያ በላይ የሆነውን ወንድ ሁሉ መዝግብ።”+ 16 በመሆኑም ሙሴ ይሖዋ በሰጠው መመሪያ መሠረት ልክ እንደታዘዘው መዘገባቸው። 17 የሌዊ ወንዶች ልጆች ስም ይህ ነው፦ ጌድሶን፣ ቀአትና ሜራሪ።+

18 የጌድሶን ወንዶች ልጆች ስም በየቤተሰባቸው ይህ ነበር፦ ሊብኒ እና ሺምአይ።+

19 የቀአት ወንዶች ልጆች በየቤተሰባቸው አምራም፣ ይጽሃር፣ ኬብሮንና ዑዚኤል ነበሩ።+

20 የሜራሪ ወንዶች ልጆች በየቤተሰባቸው ማህሊ+ እና ሙሺ+ ነበሩ።

የሌዋውያኑ ቤተሰቦች በየአባቶቻቸው ቤቶች እነዚህ ነበሩ።

21 የሊብናውያን+ ቤተሰብና የሺምአያውያን ቤተሰብ የተገኘው ከጌድሶን ነበር። የጌድሶናውያን ቤተሰቦች እነዚህ ነበሩ። 22 አንድ ወርና ከዚያ በላይ ሆኗቸው የተመዘገቡት ወንዶች በሙሉ ብዛታቸው 7,500 ነበር።+ 23 የጌድሶናውያን ቤተሰቦች የሰፈሩት ከማደሪያ ድንኳኑ በስተ ኋላ+ በስተ ምዕራብ አቅጣጫ ነበር። 24 የጌድሶናውያን የአባቶች ቤት አለቃ የላኤል ልጅ ኤሊያሳፍ ነበር። 25 የጌድሶን ልጆች+ በመገናኛ ድንኳኑ ውስጥ ያለባቸው ኃላፊነት ከማደሪያ ድንኳኑ፣ ከድንኳኑ ጨርቅ፣+ ከመደረቢያው፣+ ከመገናኛ ድንኳኑ መግቢያ መከለያ፣*+ 26 ከግቢው መጋረጃዎች፣+ በማደሪያ ድንኳኑ ዙሪያ በሚገኘው ግቢ መግቢያ ላይ ካለው መከለያ፣*+ ከመሠዊያው፣ ከድንኳኑ ገመዶችና ከእነዚህ ጋር ግንኙነት ካለው አገልግሎት ሁሉ ጋር የተያያዘ ነበር።

27 የአምራማውያን ቤተሰብ፣ የይጽሃራውያን ቤተሰብ፣ የኬብሮናውያን ቤተሰብና የዑዚኤላውያን ቤተሰብ የተገኘው ከቀአት ነበር። የቀአታውያን ቤተሰቦች እነዚህ ነበሩ።+ 28 አንድ ወርና ከዚያ በላይ የሆናቸው ወንዶች በሙሉ ብዛታቸው 8,600 ነበር፤ እነሱም ቅዱሱን ስፍራ የመንከባከብ ኃላፊነት ነበረባቸው።+ 29 የቀአት ወንዶች ልጆች ቤተሰቦች ከማደሪያ ድንኳኑ በስተ ደቡብ በኩል ሰፍረው ነበር።+ 30 የቀአታውያን ቤተሰቦች የአባቶች ቤት አለቃ የዑዚኤል+ ልጅ ኤሊጻፋን ነበር። 31 ኃላፊነታቸውም ከታቦቱ፣+ ከጠረጴዛው፣+ ከመቅረዙ፣+ ከመሠዊያዎቹ፣+ በቅዱሱ ስፍራ ለማገልገል ከሚጠቀሙባቸው ዕቃዎች፣+ ከመከለያውና*+ ከእነዚህ ጋር ግንኙነት ካለው አገልግሎት ሁሉ ጋር የተያያዘ ነበር።+

32 የሌዋውያኑ ዋና አለቃ የካህኑ የአሮን ልጅ አልዓዛር+ ሲሆን እሱም ከቅዱሱ ስፍራ ጋር በተያያዘ ኃላፊነት የተጣለባቸውን በበላይነት ይከታተል ነበር።

33 የማህላውያን ቤተሰብና የሙሻውያን ቤተሰብ የተገኘው ከሜራሪ ነበር። የሜራሪ ቤተሰቦች እነዚህ ነበሩ።+ 34 አንድ ወርና ከዚያ በላይ ሆኗቸው የተመዘገቡት ወንዶች በሙሉ ብዛታቸው 6,200 ነበር።+ 35 የሜራሪ ቤተሰቦች የአባቶች ቤት አለቃ የአቢሃይል ልጅ ጹሪኤል ነበር። እነሱም ከማደሪያ ድንኳኑ በስተ ሰሜን በኩል ሰፍረው ነበር።+ 36 የሜራሪ ወንዶች ልጆች የተጣለባቸው ኃላፊነት የማደሪያ ድንኳኑን ቋሚዎች፣+ አግዳሚ እንጨቶቹን፣+ ዓምዶቹን፣+ መሰኪያዎቹን፣ ዕቃዎቹን በሙሉ፣+ ከእነዚህ ጋር ግንኙነት ያለውን አገልግሎት ሁሉ+ 37 እንዲሁም በግቢው ዙሪያ ያሉትን ዓምዶች፣ መሰኪያዎቻቸውን፣+ የድንኳን ካስማዎቻቸውንና የድንኳን ገመዶቻቸውን በበላይነት መቆጣጠር ነበር።

38 በማደሪያ ድንኳኑ ፊት ለፊት በስተ ምሥራቅ አቅጣጫ ይኸውም በመገናኛ ድንኳኑ ፊት ፀሐይ በምትወጣበት አቅጣጫ የሰፈሩት ሙሴና አሮን እንዲሁም የአሮን ወንዶች ልጆች ነበሩ። እስራኤላውያንን ወክለው እንዲያከናውኑ የተጣለባቸው ግዴታም መቅደሱን የመንከባከብ ኃላፊነት ነበር። ማንኛውም ያልተፈቀደለት ሰው* ወደዚያ ቢቀርብ ይገደላል።+

39 ይሖዋ በሰጠው መመሪያ መሠረት ሙሴና አሮን በየቤተሰባቸው የመዘገቧቸው አንድ ወርና ከዚያ በላይ የሆናቸው ሌዋውያን ወንዶች በሙሉ 22,000 ነበሩ።

40 ከዚያም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ከእስራኤላውያን መካከል አንድ ወርና ከዚያ በላይ የሆናቸውን+ በኩር የሆኑ ወንዶች በሙሉ መዝግብ፤ ከቆጠርካቸውም በኋላ ስማቸውን በዝርዝር ጻፍ። 41 ከእስራኤላውያን መካከል በኩር በሆኑት ሁሉ ምትክ ሌዋውያኑን ለይልኝ፤+ የሌዋውያኑን የቤት እንስሳትም ከእስራኤላውያን የቤት እንስሳት መካከል በኩር በሆኑት ሁሉ ምትክ ለይልኝ፤+ እኔ ይሖዋ ነኝ።” 42 ከዚያም ሙሴ ልክ ይሖዋ ባዘዘው መሠረት ከእስራኤላውያን መካከል በኩር የሆኑትን ሁሉ መዘገበ። 43 አንድ ወርና ከዚያ በላይ ሆኗቸው በየስማቸው የተመዘገቡት በኩር የሆኑ ወንዶች ብዛታቸው 22,273 ነበር።

44 ይሖዋ እንዲህ በማለት ሙሴን ማነጋገሩን ቀጠለ፦ 45 “ከእስራኤላውያን መካከል በኩር በሆኑት ሁሉ ምትክ ሌዋውያኑን ለይ፤ የሌዋውያኑን የቤት እንስሳትም በቤት እንስሶቻቸው ሁሉ ምትክ ለይ፤ ሌዋውያኑ የእኔ ይሆናሉ። እኔ ይሖዋ ነኝ። 46 ቁጥራቸው ከሌዋውያኑ ቁጥር የበለጠውን 273+ እስራኤላውያን በኩሮች ለመዋጀት+ 47 ለእያንዳንዱ ግለሰብ እንደ ቋሚ መለኪያ ሆኖ በሚያገለግለው በቅዱሱ ስፍራ ሰቅል* መሠረት አምስት ሰቅል* ውሰድ።+ አንድ ሰቅል 20 ጌራ* ነው።+ 48 አንተም ገንዘቡን ቁጥራቸው ከሌዋውያኑ ቁጥር የተረፈውን ሰዎች ለመዋጀት የተከፈለ ዋጋ አድርገህ ለአሮንና ለወንዶች ልጆቹ ስጥ።” 49 በመሆኑም ሙሴ ቁጥራቸው ከሌዋውያኑ ቁጥር የተረፈውን ሰዎች ለመዋጀት የመዋጃውን ገንዘብ ሰበሰበ። 50 እሱም ገንዘቡን ይኸውም እንደ ቋሚ መለኪያ ሆኖ በሚያገለግለው በቅዱሱ ስፍራ ሰቅል መሠረት 1,365 ሰቅል ከእስራኤላውያኑ በኩሮች ላይ ወሰደ። 51 ከዚያም ሙሴ በይሖዋ ቃል* መሠረት ልክ ይሖዋ እንዳዘዘው የመዋጃውን ገንዘብ ለአሮንና ለወንዶች ልጆቹ ሰጣቸው።

4 ይሖዋም ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፦ 2 “ከሌዊ ልጆች መካከል የቀአትን ወንዶች ልጆች+ በየቤተሰባቸውና በየአባቶቻቸው ቤቶች መሠረት ቁጠሩ፤ 3 በመገናኛ ድንኳኑ ውስጥ እንዲሠራ በተመደበው ቡድን ውስጥ ያሉትን ዕድሜያቸው ከ30+ እስከ 50 ዓመት+ የሆኑትን ሁሉ ቁጠሩ።+

4 “የቀአት ወንዶች ልጆች በመገናኛ ድንኳኑ ውስጥ የሚያከናውኑት አገልግሎት ይህ ነው።+ ይህ እጅግ ቅዱስ የሆነ ነገር ነው፦ 5 ሰፈሩ በሚነሳበት ጊዜ አሮንና ወንዶች ልጆቹ መጥተው ታቦቱን+ የሚከልለውን መጋረጃ+ ያወርዱታል፤ የምሥክሩንም ታቦት በእሱ ይሸፍኑታል። 6 በላዩም ላይ ከአቆስጣ ቆዳ የተሠራ መሸፈኛ ይደርቡበታል፤ እንዲሁም ሙሉ በሙሉ ሰማያዊ የሆነ ጨርቅ ያለብሱታል፤ ለመሸከሚያ የሚያገለግሉትንም መሎጊያዎች+ በቦታቸው ላይ ያደርጓቸዋል።

7 “ገጸ ኅብስቱ የሚቀመጥበትንም ጠረጴዛ+ ሰማያዊ ጨርቅ ያለብሱታል፤ በላዩም ላይ ሳህኖቹን፣ ጽዋዎቹን፣ ጎድጓዳ ሳህኖቹንና ለመጠጥ መባ የሚሆኑትን ማንቆርቆሪያዎች ያስቀምጣሉ፤+ የዘወትሩም የቂጣ መባ+ ከላዩ ላይ አይነሳ። 8 ደማቅ ቀይ ጨርቅ ያለብሷቸዋል፤ ከአቆስጣ ቆዳ የተሠራ መሸፈኛም ይደርቡበታል፤ እንዲሁም ለመሸከሚያ የሚያገለግሉትን መሎጊያዎች+ በቦታቸው ላይ ያደርጓቸዋል። 9 ከዚያም ሰማያዊ ጨርቅ ወስደው የመብራቱን መቅረዝ+ ከመብራቶቹ፣+ ከመቆንጠጫዎቹና ከመኮስተሪያዎቹ+ እንዲሁም ዘወትር ዘይት እንዲኖር ለማድረግ ከሚያገለግሉት ዘይት የሚቀመጥባቸው ዕቃዎች ሁሉ ጋር ይሸፍኑታል። 10 መቅረዙን ከዕቃዎቹ ሁሉ ጋር ከአቆስጣ ቆዳ በተሠራ መሸፈኛ ይጠቀልሉታል፤ በመሸከሚያ ሳንቃ ላይም ያስቀምጡታል። 11 የወርቁን መሠዊያም+ ሰማያዊ ጨርቅ ያለብሱታል፤ ከአቆስጣ ቆዳ የተሠራ መሸፈኛም ይደርቡበታል፤ ለመሸከሚያ የሚያገለግሉትንም መሎጊያዎች+ በቦታቸው ላይ ያደርጓቸዋል። 12 ከዚያም በቅዱሱ ስፍራ ዘወትር የሚጠቀሙባቸውን መገልገያ ዕቃዎች በሙሉ+ ወስደው በሰማያዊ ጨርቅ ይጠቀልሏቸዋል፤ ከአቆስጣ ቆዳ የተሠራ መሸፈኛም ይደርቡባቸዋል፤ በመሸከሚያ ሳንቃ ላይም ያስቀምጧቸዋል።

13 “አመዱን* ከመሠዊያው ላይ ያስወግዱ፤+ መሠዊያውንም ሐምራዊ የሱፍ ጨርቅ ያልብሱት። 14 እንዲሁም በመሠዊያው ላይ ለማገልገል የሚጠቀሙባቸውን ዕቃዎች በሙሉ ይኸውም መኮስተሪያዎቹን፣ ሹካዎቹን፣ አካፋዎቹን፣ ጎድጓዳ ሳህኖቹንና የመሠዊያውን ዕቃዎች በሙሉ በላዩ ላይ ያደርጉበታል፤+ ከአቆስጣ ቆዳ የተሠራ መሸፈኛም ይደርቡበታል፤ ለመሸከሚያ የሚያገለግሉትንም መሎጊያዎች+ በቦታቸው ላይ ያደርጓቸዋል።

15 “አሮንና ወንዶች ልጆቹ ሰፈሩ ከመነሳቱ በፊት በቅዱሱ ስፍራ ያሉትን ነገሮችና የቅዱሱን ስፍራ ዕቃዎች በሙሉ ሸፍነው መጨረስ አለባቸው።+ ከዚያም የቀአት ወንዶች ልጆች ለመሸከም ይመጣሉ፤+ ሆኖም በቅዱሱ ስፍራ ያሉትን ነገሮች መንካት የለባቸውም፤ ከነኩ ግን ይሞታሉ።+ ከመገናኛ ድንኳኑ ጋር በተያያዘ እነዚህን ነገሮች የማከናወኑ ኃላፊነት* የተጣለው በቀአት ወንዶች ልጆች ላይ ነው።

16 “የመብራቱን ዘይት፣+ ጥሩ መዓዛ ያለውን ዕጣን፣+ ዘወትር የሚቀርበውን የእህል መባና የቅብዓት ዘይቱን+ የመቆጣጠሩ ኃላፊነት የካህኑ የአሮን ልጅ የአልዓዛር+ ነው። ቅዱሱን ስፍራና ዕቃዎቹን ጨምሮ የማደሪያ ድንኳኑን ሁሉና በውስጡ ያለውን ነገር በሙሉ የመቆጣጠሩ ኃላፊነት የእሱ ነው።”

17 በተጨማሪም ይሖዋ ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፦ 18 “የቀአታውያን+ ቤተሰቦች ነገድ ከሌዋውያን መካከል ተለይቶ እንዲጠፋ አታድርጉ። 19 እጅግ ቅዱስ ወደሆኑት ነገሮች+ በመቅረባቸው የተነሳ እንዳይሞቱ፣ ከዚህ ይልቅ በሕይወት እንዲኖሩ ይህን አድርጉላቸው። አሮንና ወንዶች ልጆቹ ገብተው ለእያንዳንዳቸው ሥራቸውንና የሚሸከሙትን ነገር ይመድቡላቸው። 20 ቅዱስ የሆኑትን ነገሮች ለአፍታ እንኳ ገብተው ማየት የለባቸውም፤ ካዩ ግን ይሞታሉ።”+

21 ከዚያም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ 22 “የጌድሶንን ወንዶች ልጆች+ በየአባቶቻቸው ቤቶችና በየቤተሰባቸው ቁጠር። 23 በመገናኛ ድንኳኑ ውስጥ እንዲያገለግል በተመደበው ቡድን ውስጥ ያሉትን ዕድሜያቸው ከ30 እስከ 50 ዓመት የሆኑትን ሁሉ መዝግብ። 24 የጌድሶናውያን ቤተሰቦች እንዲንከባከቡና እንዲሸከሙ+ የተመደቡት እነዚህን ነገሮች ነው፦ 25 እነሱም የማደሪያ ድንኳኑን የድንኳን ጨርቆች፣+ የመገናኛ ድንኳኑን ጨርቆች፣ መደረቢያውንና ከእሱ በላይ ያለውን ከአቆስጣ ቆዳ የተሠራ መደረቢያ+ እንዲሁም የመገናኛ ድንኳኑን መግቢያ መከለያ*+ ይሸከማሉ፤ 26 በተጨማሪም የግቢውን መጋረጃዎች፣+ በማደሪያ ድንኳኑና በመሠዊያው ዙሪያ ባለው ግቢ መግቢያ ላይ የሚገኘውን መከለያ፣*+ የድንኳን ገመዶቻቸውንና ዕቃዎቻቸውን በሙሉ እንዲሁም ለአገልግሎቱ የሚውሉትን ነገሮች ሁሉ ይሸከማሉ። የሥራ ምድባቸው ይህ ነው። 27 ጌድሶናውያን+ የሚያከናውኑትን አገልግሎትና የሚሸከሟቸውን ነገሮች ሁሉ የሚቆጣጠሩት አሮንና ወንዶች ልጆቹ ናቸው፤ እነዚህን ነገሮች ሁሉ የመሸከሙን ኃላፊነት ለእነሱ ትሰጣቸዋለህ። 28 የጌድሶናውያን ቤተሰቦች በመገናኛ ድንኳኑ ውስጥ የሚያከናውኑት አገልግሎት ይህ ነው፤+ ኃላፊነታቸውንም የሚወጡት በካህኑ በአሮን ልጅ በኢታምር+ አመራር ሥር ሆነው ነው።

29 “የሜራሪን ወንዶች ልጆችም+ በየቤተሰባቸውና በየአባቶቻቸው ቤት ትመዘግባቸዋለህ። 30 በመገናኛ ድንኳኑ እንዲያገለግል በተመደበው ቡድን ውስጥ ያሉትን ዕድሜያቸው ከ30 እስከ 50 ዓመት የሆኑትን ሁሉ ትመዘግባለህ። 31 በመገናኛ ድንኳኑ ከሚያከናውኑት አገልግሎት ጋር በተያያዘ የሚከተሉትን ነገሮች የመሸከም ኃላፊነት+ ተጥሎባቸዋል፦ የማደሪያ ድንኳኑን ቋሚዎች፣+ አግዳሚ እንጨቶቹን፣+ ዓምዶቹን፣+ መሰኪያዎቹን፣+ 32 በግቢው ዙሪያ ያሉትን ቋሚዎች፣+ መሰኪያዎቻቸውን፣+ የድንኳን ካስማዎቻቸውን፣+ የድንኳን ገመዶቻቸውን እንዲሁም ቁሳቁሶቻቸውንና ከዚህ አገልግሎት ጋር የተያያዙትን ነገሮች ሁሉ ይሸከማሉ። በኃላፊነት የሚሸከሙትንም ዕቃ በስም ጠቅሰህ ትመድብላቸዋለህ። 33 የሜራሪ ወንዶች ልጆች ቤተሰቦች+ በካህኑ በአሮን ልጅ በኢታምር አመራር ሥር ሆነው በመገናኛ ድንኳኑ የሚያገለግሉት በዚህ መሠረት ነው።”+

34 ከዚያም ሙሴ፣ አሮንና የማኅበረሰቡ አለቆች+ የቀአታውያንን ወንዶች ልጆች+ በየቤተሰቦቻቸውና በየአባቶቻቸው ቤት መዘገቡ፤ 35 በመገናኛ ድንኳኑ እንዲያገለግል በተመደበው ቡድን ውስጥ ያሉትን ዕድሜያቸው ከ30 እስከ 50 ዓመት የሆኑትን ሁሉ መዘገቡ።+ 36 በየቤተሰባቸው የተመዘገቡትም በአጠቃላይ 2,750 ነበሩ።+ 37 ከቀአታውያን ቤተሰቦች መካከል የተመዘገቡትና በመገናኛ ድንኳኑ የሚያገለግሉት በአጠቃላይ እነዚህ ነበሩ። ሙሴና አሮንም ይሖዋ በሙሴ አማካኝነት በሰጠው ትእዛዝ መሠረት መዘገቧቸው።+

38 የጌድሶን ወንዶች ልጆችም+ በየቤተሰባቸውና በየአባቶቻቸው ቤት ተመዘገቡ፤ 39 በመገናኛ ድንኳኑ እንዲያገለግል በተመደበው ቡድን ውስጥ ያሉት ዕድሜያቸው ከ30 እስከ 50 ዓመት የሆኑት ሁሉ ተመዘገቡ። 40 በየቤተሰቦቻቸውና በየአባቶቻቸው ቤት የተመዘገቡት በአጠቃላይ 2,630 ነበሩ።+ 41 በመገናኛ ድንኳኑ እንዲያገለግሉ የተመዘገቡት የጌድሶን ወንዶች ልጆች ቤተሰቦች በአጠቃላይ እነዚህ ነበሩ። ሙሴና አሮንም ይሖዋ በሰጠው ትእዛዝ መሠረት መዘገቧቸው።+

42 የሜራሪ ወንዶች ልጆች በየቤተሰባቸውና በየአባቶቻቸው ቤት ተመዘገቡ፤ 43 በመገናኛ ድንኳኑ እንዲያገለግል በተመደበው ቡድን ውስጥ ያሉት ዕድሜያቸው ከ30 እስከ 50 ዓመት የሆኑት ሁሉ ተመዘገቡ።+ 44 ከእነሱ መካከል በየቤተሰባቸው የተመዘገቡት በአጠቃላይ 3,200 ነበሩ።+ 45 ሙሴና አሮን ይሖዋ በሙሴ አማካኝነት በሰጠው ትእዛዝ መሠረት የመዘገቧቸው የሜራሪ ወንዶች ልጆች ቤተሰቦች እነዚህ ነበሩ።+

46 ሙሴ፣ አሮንና የእስራኤል አለቆች እነዚህን ሌዋውያን ሁሉ በየቤተሰባቸውና በየአባቶቻቸው ቤቶች መዘገቧቸው፤ 47 እነሱም ከ30 እስከ 50 ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሲሆን ሁሉም ከመገናኛ ድንኳኑ ጋር በተያያዘ እንዲያገለግሉና ሸክም እንዲሸከሙ ተመድበው ነበር።+ 48 የተመዘገቡትም በአጠቃላይ 8,580 ነበሩ።+ 49 እነሱም ይሖዋ በሙሴ በኩል ባስተላለፈው ትእዛዝ መሠረት ተመዝግበው ነበር፤ የተመዘገቡትም እያንዳንዳቸው በሚያከናውኑት አገልግሎትና በሚሸከሙት ሸክም መሠረት ነበር፤ እነሱም ልክ ይሖዋ ሙሴን ባዘዘው መሠረት ተመዘገቡ።

5 በተጨማሪም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ 2 “እስራኤላውያንን የሥጋ ደዌ ያለበትን፣+ ፈሳሽ የሚወጣውንና+ በሞተ ሰው* የረከሰን+ ማንኛውንም ሰው ከሰፈሩ እንዲያስወጡ እዘዛቸው። 3 ወንድም ሆነ ሴት አስወጧቸው። እኔ በመካከላቸው ስለምኖር*+ ሕዝቤ የሚኖርባቸውን ሰፈሮች እንዳይበክሉ+ ከሰፈሩ አስወጧቸው።” 4 በመሆኑም እስራኤላውያን እንደተባሉት አደረጉ፤ ሰዎቹንም ከሰፈሩ አስወጧቸው። እስራኤላውያን ልክ ይሖዋ ለሙሴ እንደነገረው አደረጉ።

5 ከዚያም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ 6 “እስራኤላውያንን እንዲህ በላቸው፦ ‘አንድ ወንድ ወይም አንዲት ሴት የሰው ልጆች ከሚፈጽሟቸው ኃጢአቶች ውስጥ የትኛውንም ቢሠሩና በይሖዋ ላይ ታማኝነት የጎደለው ድርጊት ቢፈጽሙ ይህን ያደረገው ሰው* በደለኛ ይሆናል።+ 7 እሱም* የሠራውን ኃጢአት መናዘዝና+ ለፈጸመው በደል ካሳ አድርጎ ሙሉ ዋጋውን መመለስ አለበት፤ የዚህን አንድ አምስተኛም ይጨምርበት፤+ በደል ለፈጸመበትም ሰው ይስጠው። 8 ሆኖም በደል የተፈጸመበት ሰው ቢሞትና ካሳውን የሚቀበልለት የቅርብ ዘመድ ባይኖረው ካህኑ የግለሰቡን በደል ከሚያስተሰርይበት አውራ በግ በስተቀር ካሳው ለይሖዋ ይመለስ፤ የካህኑም ይሆናል።+

9 “‘እስራኤላውያን ለካህኑ የሚያቀርቧቸው ቅዱስ መዋጮዎች+ በሙሉ የእሱ ይሆናሉ።+ 10 እያንዳንዱ ሰው የሚያቀርባቸው ቅዱስ የሆኑ ነገሮች የእሱ ይሆናሉ። እያንዳንዱ ሰው ለካህኑ የሚሰጠው ማንኛውም ነገር የካህኑ ይሆናል።’”

11 ይሖዋም ሙሴን እንዲህ አለው፦ 12 “እስራኤላውያንን እንዲህ በላቸው፦ ‘የአንድ ሰው ሚስት ከትክክለኛው መንገድ ዞር በማለት ለባሏ ታማኝ ሳትሆን ብትቀርና 13 ሌላ ወንድ ከእሷ ጋር የፆታ ግንኙነት ቢፈጽም፣+ ባሏ ግን ይህን ነገር ባያውቅና ጉዳዩ ተሰውሮ ቢቀር፣ ይህች ሴት በዚህ መንገድ ራሷን ብታረክስም የሚመሠክርባት ሰው ባይገኝና እጅ ከፍንጅ ባትያዝ፣ 14 ባሏም ሚስቱ ራሷን አርክሳ ሳለ የቅናት መንፈስ ቢያድርበትና የሚስቱን ታማኝነት ቢጠራጠር ወይም ደግሞ ራሷን ሳታረክስ የቅናት መንፈስ ቢያድርበትና ታማኝነቷን ቢጠራጠር 15 ሰውየው ሚስቱን ለእሷ ከሚቀርበው መባ ይኸውም ከአንድ አሥረኛ ኢፍ* የገብስ ዱቄት ጋር ወደ ካህኑ ያምጣ። ይህ የቅናት የእህል መባ ይኸውም በደል እንዲታወስ የሚያደርግ የእህል መባ ስለሆነ በላዩ ላይ ዘይት አያፍስበት ወይም ነጭ ዕጣን አያድርግበት።

16 “‘ካህኑ ሴትየዋን አምጥቶ ይሖዋ ፊት እንድትቆም ያደርጋል።+ 17 ከዚያም ካህኑ የተቀደሰ ውኃ በሸክላ ዕቃ ይወስዳል፤ ከማደሪያ ድንኳኑም ወለል ላይ ጥቂት አፈር ወስዶ ውኃው ውስጥ ይጨምረዋል። 18 ካህኑም ሴትየዋ በይሖዋ ፊት እንድትቆም ያደርጋል፤ ፀጉሯንም ይፈታል፤ ለመታሰቢያ የሚሆነውን የእህል መባ ይኸውም የቅናት የእህል መባውን+ በእጆቿ ላይ ያደርጋል፤ ካህኑም እርግማን የሚያመጣውን መራራ ውኃ በእጁ ይይዛል።+

19 “‘ካህኑም ሴትየዋን እንዲህ በማለት ያስምላታል፦ “በባልሽ ሥልጣን ሥር ሆነሽ ሳለ+ ሌላ ወንድ ከአንቺ ጋር የፆታ ግንኙነት ካልፈጸመ አንቺም ከትክክለኛው መንገድ ዞር ካላልሽና ካልረከስሽ እርግማን የሚያስከትለው ይህ ውኃ ምንም ጉዳት አያድርስብሽ። 20 ይሁንና በባልሽ ሥልጣን ሥር ሆነሽ ሳለ ራስሽን በማርከስ ከትክክለኛው መንገድ ዞር ብለሽ ከሆነና ከሌላ ወንድ ጋር የፆታ ግንኙነት ፈጽመሽ+ ከሆነ . . . ” 21 ካህኑም ሴትየዋን እርግማን ያለበት መሐላ ያስምላታል፤ እንዲህም ይላታል፦ “ይሖዋ ጭንሽ* እንዲሰልና* ሆድሽ እንዲያብጥ በማድረግ፣ ይሖዋ በሕዝብሽ መካከል የእርግማንና የመሐላ ምሳሌ ያድርግሽ። 22 እርግማን የሚያመጣው ይህ ውኃ ወደ አንጀትሽ ገብቶ ሆድሽን ያሳብጠው፤ መሃንም ያድርግሽ።” በዚህ ጊዜ ሴትየዋ “አሜን! አሜን!”* ትበል።

23 “‘ከዚያም ካህኑ እነዚህን እርግማኖች በመጽሐፍ ይጻፋቸው፤ በመራራውም ውኃ አጥቦ ያጥፋቸው። 24 እርግማን የሚያመጣውን መራራ ውኃም እንድትጠጣ ያድርግ፤ ውኃውም ወደ ሰውነቷ ገብቶ መራራ ሥቃይ ያስከትልባት። 25 ካህኑም የቅናት የእህል መባውን+ ከሴትየዋ እጅ ላይ ወስዶ በይሖዋ ፊት ወዲያና ወዲህ ይወዝውዘው፤ ወደ መሠዊያውም ያምጣው። 26 ካህኑም ከእህል መባው ላይ አንድ እፍኝ በመውሰድ የመባው መታሰቢያ አድርጎ በመሠዊያው ላይ ያጭሰው፤+ ከዚያ በኋላ ሴትየዋ ውኃውን እንድትጠጣ ያድርግ። 27 ውኃውን እንድትጠጣ በሚያደርግበትም ጊዜ ሴትየዋ ራሷን አርክሳና በባሏ ላይ ታማኝነት የጎደለው ድርጊት ፈጽማ ከሆነ እርግማን የሚያመጣው ውኃ ወደ ሰውነቷ ገብቶ መራራ ሥቃይ ያስከትልባታል፤ ሆዷም ያብጣል፤ ጭኗም* ይሰልላል፤* እሷም በሕዝቧ መካከል የእርግማን ምሳሌ ትሆናለች። 28 ይሁንና ሴትየዋ ራሷን ካላረከሰችና ንጹሕ ከሆነች እንዲህ ካለው ቅጣት ነፃ ትሆናለች፤ እንዲሁም መጸነስና ልጆች ማፍራት ትችላለች።

29 “‘እንግዲህ ቅናትን በተመለከተ ሕጉ ይህ ነው፤+ አንዲት ሴት በባሏ ሥልጣን ሥር ሆና ሳለ ከትክክለኛው መንገድ ዞር ብትልና ራሷን ብታረክስ 30 ወይም አንድ ሰው የቅናት መንፈስ ቢያድርበትና የሚስቱን ታማኝነት ቢጠራጠር ሕጉ ይህ ነው፤ እሱም ሚስቱ በይሖዋ ፊት እንድትቆም ያድርግ፤ ካህኑም ይህ ሕግ በሙሉ በእሷ ላይ እንዲፈጸም ያድርግ። 31 ሰውየው ከበደል ነፃ ይሆናል፤ ሚስቱ ግን ስለ በደሏ ትጠየቃለች።’”

6 በተጨማሪም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ 2 “እስራኤላውያንን እንዲህ በላቸው፦ ‘አንድ ወንድ ወይም አንዲት ሴት ለይሖዋ ናዝራዊ*+ ሆነው ለመኖር ልዩ ስእለት ቢሳሉ 3 ስእለት የተሳለው ሰው ከወይን ጠጅና ከሚያሰክር ሌላ መጠጥ መራቅ ይኖርበታል። የወይን ጠጅ ኮምጣጤ ወይም የማንኛውም ዓይነት የሚያሰክር መጠጥ ኮምጣጤ አይጠጣ።+ ከወይን ፍሬ የተዘጋጀን ማንኛውንም መጠጥ አይጠጣ፤ የወይን ፍሬም ሆነ ዘቢብ አይብላ። 4 ናዝራዊ ሆኖ በሚቆይበት ጊዜ ሁሉ ከወይን ተክል የተዘጋጀን ማንኛውንም ነገር፣ ያልበሰለውን የወይን ፍሬም ሆነ ግልፋፊውን ፈጽሞ መብላት የለበትም።

5 “‘ናዝራዊ ሆኖ ለመቆየት በተሳለበት ጊዜ ሁሉ ራሱን ምላጭ አይንካው።+ ለይሖዋ የተለየበት ጊዜ እስኪያበቃ ድረስ የራስ ፀጉሩን በማሳደግ ቅዱስ ሆኖ መገኘት ይኖርበታል። 6 ራሱን ለይሖዋ በለየበት ጊዜ ሁሉ ወደ ሞተ ሰው* አይቅረብ።* 7 ለአምላኩ ናዝራዊ መሆኑን የሚያሳየው ምልክት በራሱ ላይ ስላለ አባቱ ወይም እናቱ ወይም ወንድሙ ወይም እህቱ ቢሞቱ እንኳ በእነሱ ራሱን አያርክስ።+

8 “‘ናዝራዊ ሆኖ በሚቆይበት ጊዜ ሁሉ ለይሖዋ ቅዱስ ይሆናል። 9 ይሁንና አንድ ሰው ድንገት አጠገቡ ቢሞትና+ ለአምላክ የተለየ መሆኑን የሚያሳየውን ፀጉሩን ቢያረክስ* መንጻቱን በሚያረጋግጥበት ቀን ራሱን ይላጭ።+ በሰባተኛውም ቀን ፀጉሩን ይላጨው። 10 በስምንተኛውም ቀን ሁለት ዋኖሶችን ወይም ሁለት የርግብ ጫጩቶችን በመገናኛ ድንኳኑ መግቢያ ወደሚገኘው ካህን ያምጣ። 11 ካህኑም አንዱን የኃጢአት መባ ሌላኛውን ደግሞ የሚቃጠል መባ አድርጎ በማዘጋጀት ከሞተ ሰው* ጋር በተያያዘ ስለሠራው ኃጢአት ያስተሰርይለታል።+ ከዚያም በዚያ ቀን ራሱን ይቀድስ። 12 ናዝራዊ ሆኖ ለሚቆይበት ጊዜ እንደገና ራሱን ለይሖዋ ይለይ፤ አንድ ዓመት ገደማ የሆነው የበግ ጠቦት የበደል መባ አድርጎ ያምጣ። ሆኖም ናዝራዊነቱን ስላረከሰ የቀድሞዎቹ ጊዜያት አይታሰቡለትም።

13 “‘እንግዲህ ናዝራዊን በተመለከተ ሕጉ ይህ ነው፦ ናዝራዊ ሆኖ የሚቆይበትን ጊዜ ሲያጠናቅቅ+ ወደ መገናኛ ድንኳኑ መግቢያ እንዲመጣ ይደረግ። 14 በዚያም የሚከተሉትን ለይሖዋ መባ አድርጎ ያቅርብ፦ ለሚቃጠል መባ አንድ ዓመት ገደማ የሆነውን እንከን የሌለበት አንድ የበግ ጠቦት፣+ ለኃጢአት መባ አንድ ዓመት ገደማ የሆናትን እንከን የሌለባት አንዲት ጠቦት፣+ ለኅብረት መሥዋዕት እንከን የሌለበትን አንድ አውራ በግ፣+ 15 በዘይት ከተለወሰ የላመ ዱቄት የተዘጋጁ እርሾ ያልገባባቸው አንድ ቅርጫት የቀለበት ቅርጽ ያላቸው ዳቦዎችና ዘይት የተቀቡ ስስ ቂጣዎች* እንዲሁም የእህል መባዎቻቸውንና+ የመጠጥ መባዎቻቸውን።+ 16 ካህኑም እነዚህን በይሖዋ ፊት ያቀርባቸዋል፤ የሰውየውን የኃጢአት መባና የሚቃጠል መባም ያቀርባል። 17 አውራውንም በግ በቅርጫቱ ውስጥ ካሉት ቂጣዎች ጋር የኅብረት መሥዋዕት አድርጎ ለይሖዋ ያቀርበዋል፤ ካህኑም የእህል መባውንና+ የመጠጥ መባውን ያቀርበዋል።

18 “‘ከዚያም ናዝራዊው ያልተቆረጠውን ፀጉሩን*+ በመገናኛ ድንኳኑ መግቢያ ላይ ይላጭ፤ ናዝራዊ ሆኖ በቆየበት ጊዜ ያደገውን የራሱን ፀጉር ወስዶ ከኅብረት መሥዋዕቱ ሥር ባለው እሳት ውስጥ ይጨምረው። 19 ናዝራዊው የናዝራዊነት ምልክቱን ከተላጨ በኋላ ካህኑ የአውራውን በግ አንድ የተቀቀለ+ የፊት እግር፣ ከቅርጫቱም ውስጥ እርሾ ያልገባበት የቀለበት ቅርጽ ያለው አንድ ዳቦ እንዲሁም አንድ ስስ ቂጣ ወስዶ በናዝራዊው መዳፍ ላይ ያድርጋቸው። 20 ካህኑም እነዚህን የሚወዘወዝ መባ አድርጎ በይሖዋ ፊት ወዲያና ወዲህ ይወዝውዛቸው።+ ይህም ከሚወዘወዘው መባ ፍርምባና መዋጮ ሆኖ ከተሰጠው እግር ጋር ለካህኑ የተቀደሰ ይሆናል።+ ከዚህ በኋላ ናዝራዊው የወይን ጠጅ መጠጣት ይችላል።

21 “‘ስእለት የሚሳልን ናዝራዊ+ በተመለከተ ሕጉ ይህ ነው፦ ናዝራዊው ስእለት ከተሳለና በናዝራዊነት ከሚጠበቅበት በተጨማሪ ለይሖዋ መባ ለማቅረብ አቅሙ የሚፈቅድለት ከሆነ ለናዝራዊነቱ ሕግ ካለው አክብሮት የተነሳ ስእለቱን መፈጸም ይገባዋል።’”

22 ከዚያም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ 23 “አሮንንና ወንዶች ልጆቹን እንዲህ በላቸው፦ ‘የእስራኤልን ሕዝብ የምትባርኩት+ በዚህ መንገድ ነው። እንዲህ በሏቸው፦

24 “ይሖዋ ይባርክህ፤+ ደግሞም ይጠብቅህ።

25 ይሖዋ ፊቱን ያብራልህ፤+ ሞገሱንም ያሳይህ።

26 ይሖዋ ፊቱን ወደ አንተ ይመልስ፤ ሰላምም ይስጥህ።”’+

27 እኔም እንድባርካቸው+ ስሜን በእስራኤል ሕዝብ ላይ ያድርጉ።”+

7 ሙሴ የማደሪያ ድንኳኑን ተክሎ በጨረሰበት ቀን+ የማደሪያ ድንኳኑን ከቁሳቁሶቹ ሁሉና ከመሠዊያው እንዲሁም ከዕቃዎቹ ሁሉ+ ጋር ቀባው፤+ ደግሞም ቀደሰው። እነዚህን ነገሮች በቀባቸውና በቀደሳቸው+ ጊዜ 2 የእስራኤል አለቆች+ ማለትም የአባቶቻቸው ቤት መሪዎች መባ አቀረቡ። ምዝገባውን በበላይነት ሲቆጣጠሩ የነበሩት እነዚህ የየነገዱ አለቆች 3 ስድስት ባለ ሽፋን ሠረገሎችንና 12 በሬዎችን ይኸውም ሁለት አለቆች አንድ ሠረገላ፣ እያንዳንዳቸውም አንድ አንድ በሬ መባ አድርገው ወደ ይሖዋ ፊት አመጡ፤ እነዚህንም በማደሪያ ድንኳኑ ፊት አቀረቡ። 4 ይሖዋም ሙሴን እንዲህ አለው፦ 5 “በመገናኛ ድንኳኑ ለሚከናወነው አገልግሎት እንዲውሉ እነዚህን ከእነሱ ተቀበል፤ ለሌዋውያኑም ለእያንዳንዳቸው ለሥራቸው እንደሚያስፈልጋቸው ስጣቸው።”

6 ስለሆነም ሙሴ ሠረገሎቹንና ከብቶቹን ተቀብሎ ለሌዋውያኑ ሰጣቸው። 7 ለጌድሶን ወንዶች ልጆች ለሥራቸው እንደሚያስፈልጋቸው ሁለት ሠረገሎችና አራት በሬዎች ሰጣቸው፤+ 8 ለሜራሪ ወንዶች ልጆች ደግሞ በካህኑ በአሮን ልጅ በኢታምር አመራር ሥር ሆነው ለሚያከናውኑት ሥራ እንደሚያስፈልጋቸው አራት ሠረገሎችና ስምንት በሬዎች ሰጣቸው።+ 9 ለቀአት ወንዶች ልጆች ግን ምንም አልሰጣቸውም፤ ምክንያቱም ሥራቸው በቅዱሱ ስፍራ ከሚቀርበው አገልግሎት ጋር የተያያዘ+ ሲሆን ቅዱስ የሆኑትን ነገሮች የሚሸከሙት ደግሞ በትከሻቸው ነበር።+

10 አለቆቹም መሠዊያው በተቀባበት ዕለት በምርቃቱ*+ ላይ መባቸውን አቀረቡ። አለቆቹ መባቸውን በመሠዊያው ፊት ባቀረቡ ጊዜ 11 ይሖዋ ሙሴን “በየቀኑ አንድ አንድ አለቃ ለመሠዊያው ምርቃት የሚሆነውን መባውን ያቅርብ” አለው።

12 በመጀመሪያው ቀን መባውን ያቀረበው ከይሁዳ ነገድ የሆነው የአሚናዳብ ልጅ ነአሶን+ ነበር። 13 መባውም እንደ ቋሚ መለኪያ ሆኖ በሚያገለግለው በቅዱሱ ስፍራ ሰቅል*+ መሠረት 130 ሰቅል* የሚመዝን አንድ የብር ሳህንና 70 ሰቅል የሚመዝን አንድ የብር ጎድጓዳ ሳህን ሲሆን እያንዳንዳቸው ለእህል መባ የሚሆን በዘይት የተለወሰ የላመ ዱቄት የተሞሉ ነበሩ፤+ 14 እንዲሁም ዕጣን የተሞላ 10 ሰቅል የሚመዝን አንድ የወርቅ ጽዋ፣ 15 ለሚቃጠል መባ የሚሆን አንድ ወይፈን፣ አንድ አውራ በግና አንድ ዓመት ገደማ የሆነው ተባዕት የበግ ጠቦት፣+ 16 ለኃጢአት መባ የሚሆን አንድ የፍየል ጠቦት+ 17 እንዲሁም ለኅብረት መሥዋዕት+ የሚሆኑ ሁለት ከብቶች፣ አምስት አውራ በጎች፣ አምስት ተባዕት ፍየሎችና እያንዳንዳቸው አንድ ዓመት የሆናቸው አምስት ተባዕት የበግ ጠቦቶች አቀረበ። የአሚናዳብ+ ልጅ ነአሶን ያቀረበው መባ ይህ ነበር።

18 በሁለተኛውም ቀን የይሳኮር አለቃ የሆነው የጹአር ልጅ ናትናኤል+ መባ አቀረበ። 19 መባውም እንደ ቋሚ መለኪያ ሆኖ በሚያገለግለው በቅዱሱ ስፍራ ሰቅል+ መሠረት 130 ሰቅል የሚመዝን አንድ የብር ሳህንና 70 ሰቅል የሚመዝን አንድ የብር ጎድጓዳ ሳህን ሲሆን እያንዳንዳቸው ለእህል መባ የሚሆን በዘይት የተለወሰ የላመ ዱቄት የተሞሉ ነበሩ፤+ 20 በተጨማሪም ዕጣን የተሞላ 10 ሰቅል የሚመዝን አንድ የወርቅ ጽዋ፣ 21 ለሚቃጠል መባ የሚሆን አንድ ወይፈን፣ አንድ አውራ በግና አንድ ዓመት ገደማ የሆነው ተባዕት የበግ ጠቦት፣+ 22 ለኃጢአት መባ የሚሆን አንድ የፍየል ጠቦት+ 23 እንዲሁም ለኅብረት መሥዋዕት+ የሚሆኑ ሁለት ከብቶች፣ አምስት አውራ በጎች፣ አምስት ተባዕት ፍየሎችና እያንዳንዳቸው አንድ ዓመት የሆናቸው አምስት ተባዕት የበግ ጠቦቶች አቀረበ። የጹአር ልጅ ናትናኤል ያቀረበው መባ ይህ ነበር።

24 በሦስተኛውም ቀን የዛብሎን ልጆች አለቃ የሆነው የሄሎን ልጅ ኤልያብ+ 25 መባ አቀረበ፤ መባውም እንደ ቋሚ መለኪያ ሆኖ በሚያገለግለው በቅዱሱ ስፍራ ሰቅል+ መሠረት 130 ሰቅል የሚመዝን አንድ የብር ሳህንና 70 ሰቅል የሚመዝን አንድ የብር ጎድጓዳ ሳህን ሲሆን እያንዳንዳቸው ለእህል መባ የሚሆን በዘይት የተለወሰ የላመ ዱቄት የተሞሉ ነበሩ፤+ 26 በተጨማሪም ዕጣን የተሞላ 10 ሰቅል የሚመዝን አንድ የወርቅ ጽዋ፣ 27 ለሚቃጠል መባ የሚሆን አንድ ወይፈን፣ አንድ አውራ በግና አንድ ዓመት ገደማ የሆነው ተባዕት የበግ ጠቦት፣+ 28 ለኃጢአት መባ የሚሆን አንድ የፍየል ጠቦት+ 29 እንዲሁም ለኅብረት መሥዋዕት+ የሚሆኑ ሁለት ከብቶች፣ አምስት አውራ በጎች፣ አምስት ተባዕት ፍየሎችና እያንዳንዳቸው አንድ ዓመት የሆናቸው አምስት ተባዕት የበግ ጠቦቶች አቀረበ። የሄሎን ልጅ ኤልያብ+ ያቀረበው መባ ይህ ነበር።

30 በአራተኛውም ቀን የሮቤል ልጆች አለቃ የሆነው የሸደኡር ልጅ ኤሊጹር+ 31 መባ አቀረበ፤ መባውም እንደ ቋሚ መለኪያ ሆኖ በሚያገለግለው በቅዱሱ ስፍራ ሰቅል+ መሠረት 130 ሰቅል የሚመዝን አንድ የብር ሳህንና 70 ሰቅል የሚመዝን አንድ የብር ጎድጓዳ ሳህን ሲሆን እያንዳንዳቸው ለእህል መባ የሚሆን በዘይት የተለወሰ የላመ ዱቄት የተሞሉ ነበሩ፤+ 32 በተጨማሪም ዕጣን የተሞላ 10 ሰቅል የሚመዝን አንድ የወርቅ ጽዋ፣ 33 ለሚቃጠል መባ የሚሆን አንድ ወይፈን፣ አንድ አውራ በግና አንድ ዓመት ገደማ የሆነው ተባዕት የበግ ጠቦት፣+ 34 ለኃጢአት መባ የሚሆን አንድ የፍየል ጠቦት+ 35 እንዲሁም ለኅብረት መሥዋዕት+ የሚሆኑ ሁለት ከብቶች፣ አምስት አውራ በጎች፣ አምስት ተባዕት ፍየሎችና እያንዳንዳቸው አንድ ዓመት የሆናቸው አምስት ተባዕት የበግ ጠቦቶች አቀረበ። የሸደኡር ልጅ ኤሊጹር+ ያቀረበው መባ ይህ ነበር።

36 በአምስተኛውም ቀን የስምዖን ልጆች አለቃ የሆነው የጹሪሻዳይ ልጅ ሸሉሚኤል+ 37 መባ አቀረበ፤ መባውም እንደ ቋሚ መለኪያ ሆኖ በሚያገለግለው በቅዱሱ ስፍራ ሰቅል+ መሠረት 130 ሰቅል የሚመዝን አንድ የብር ሳህንና 70 ሰቅል የሚመዝን አንድ የብር ጎድጓዳ ሳህን ሲሆን እያንዳንዳቸው ለእህል መባ የሚሆን በዘይት የተለወሰ የላመ ዱቄት የተሞሉ ነበሩ፤+ 38 በተጨማሪም ዕጣን የተሞላ 10 ሰቅል የሚመዝን አንድ የወርቅ ጽዋ፣ 39 ለሚቃጠል መባ የሚሆን አንድ ወይፈን፣ አንድ አውራ በግና አንድ ዓመት ገደማ የሆነው ተባዕት የበግ ጠቦት፣+ 40 ለኃጢአት መባ የሚሆን አንድ የፍየል ጠቦት+ 41 እንዲሁም ለኅብረት መሥዋዕት+ የሚሆኑ ሁለት ከብቶች፣ አምስት አውራ በጎች፣ አምስት ተባዕት ፍየሎችና እያንዳንዳቸው አንድ ዓመት የሆናቸው አምስት ተባዕት የበግ ጠቦቶች አቀረበ። የጹሪሻዳይ ልጅ ሸሉሚኤል+ ያቀረበው መባ ይህ ነበር።

42 በስድስተኛውም ቀን የጋድ ልጆች አለቃ የሆነው የደኡዔል ልጅ ኤሊያሳፍ+ 43 መባ አቀረበ፤ መባውም እንደ ቋሚ መለኪያ ሆኖ በሚያገለግለው በቅዱሱ ስፍራ ሰቅል+ መሠረት 130 ሰቅል የሚመዝን አንድ የብር ሳህንና 70 ሰቅል የሚመዝን አንድ የብር ጎድጓዳ ሳህን ሲሆን እያንዳንዳቸው ለእህል መባ የሚሆን በዘይት የተለወሰ የላመ ዱቄት የተሞሉ ነበሩ፤+ 44 በተጨማሪም ዕጣን የተሞላ 10 ሰቅል የሚመዝን አንድ የወርቅ ጽዋ፣ 45 ለሚቃጠል መባ የሚሆን አንድ ወይፈን፣ አንድ አውራ በግና አንድ ዓመት ገደማ የሆነው ተባዕት የበግ ጠቦት፣+ 46 ለኃጢአት መባ የሚሆን አንድ የፍየል ጠቦት+ 47 እንዲሁም ለኅብረት መሥዋዕት+ የሚሆኑ ሁለት ከብቶች፣ አምስት አውራ በጎች፣ አምስት ተባዕት ፍየሎችና እያንዳንዳቸው አንድ ዓመት የሆናቸው አምስት ተባዕት የበግ ጠቦቶች አቀረበ። የደኡዔል ልጅ ኤሊያሳፍ+ ያቀረበው መባ ይህ ነበር።

48 በሰባተኛውም ቀን የኤፍሬም ልጆች አለቃ የሆነው የአሚሁድ ልጅ ኤሊሻማ+ 49 መባ አቀረበ፤ መባውም እንደ ቋሚ መለኪያ ሆኖ በሚያገለግለው በቅዱሱ ስፍራ ሰቅል+ መሠረት 130 ሰቅል የሚመዝን አንድ የብር ሳህንና 70 ሰቅል የሚመዝን አንድ የብር ጎድጓዳ ሳህን ሲሆን እያንዳንዳቸው ለእህል መባ የሚሆን በዘይት የተለወሰ የላመ ዱቄት የተሞሉ ነበሩ፤+ 50 በተጨማሪም ዕጣን የተሞላ 10 ሰቅል የሚመዝን አንድ የወርቅ ጽዋ፣ 51 ለሚቃጠል መባ የሚሆን አንድ ወይፈን፣ አንድ አውራ በግና አንድ ዓመት ገደማ የሆነው ተባዕት የበግ ጠቦት፣+ 52 ለኃጢአት መባ የሚሆን አንድ የፍየል ጠቦት+ 53  እንዲሁም ለኅብረት መሥዋዕት+ የሚሆኑ ሁለት ከብቶች፣ አምስት አውራ በጎች፣ አምስት ተባዕት ፍየሎችና እያንዳንዳቸው አንድ ዓመት የሆናቸው አምስት ተባዕት የበግ ጠቦቶች አቀረበ። የአሚሁድ ልጅ ኤሊሻማ+ ያቀረበው መባ ይህ ነበር።

54 በስምንተኛውም ቀን የምናሴ ልጆች አለቃ የሆነው የፐዳጹር ልጅ ገማልያል+ 55 መባ አቀረበ፤ መባውም እንደ ቋሚ መለኪያ ሆኖ በሚያገለግለው በቅዱሱ ስፍራ ሰቅል+ መሠረት 130 ሰቅል የሚመዝን አንድ የብር ሳህንና 70 ሰቅል የሚመዝን አንድ የብር ጎድጓዳ ሳህን ሲሆን እያንዳንዳቸው ለእህል መባ የሚሆን በዘይት የተለወሰ የላመ ዱቄት የተሞሉ ነበሩ፤+ 56 በተጨማሪም ዕጣን የተሞላ 10 ሰቅል የሚመዝን አንድ የወርቅ ጽዋ፣ 57  ለሚቃጠል መባ የሚሆን አንድ ወይፈን፣ አንድ አውራ በግና አንድ ዓመት ገደማ የሆነው ተባዕት የበግ ጠቦት፣+ 58 ለኃጢአት መባ የሚሆን አንድ የፍየል ጠቦት+ 59 እንዲሁም ለኅብረት መሥዋዕት+ የሚሆኑ ሁለት ከብቶች፣ አምስት አውራ በጎች፣ አምስት ተባዕት ፍየሎችና እያንዳንዳቸው አንድ ዓመት የሆናቸው አምስት ተባዕት የበግ ጠቦቶች አቀረበ። የፐዳጹር ልጅ ገማልያል+ ያቀረበው መባ ይህ ነበር።

60 በዘጠነኛውም ቀን የቢንያም ልጆች አለቃ+ የሆነው የጊድኦኒ ልጅ አቢዳን+ 61 መባ አቀረበ፤ መባውም እንደ ቋሚ መለኪያ ሆኖ በሚያገለግለው በቅዱሱ ስፍራ ሰቅል+ መሠረት 130 ሰቅል የሚመዝን አንድ የብር ሳህንና 70 ሰቅል የሚመዝን አንድ የብር ጎድጓዳ ሳህን ሲሆን እያንዳንዳቸው ለእህል መባ የሚሆን በዘይት የተለወሰ የላመ ዱቄት የተሞሉ ነበሩ፤+ 62 በተጨማሪም ዕጣን የተሞላ 10 ሰቅል የሚመዝን አንድ የወርቅ ጽዋ፣ 63 ለሚቃጠል መባ የሚሆን አንድ ወይፈን፣ አንድ አውራ በግና አንድ ዓመት ገደማ የሆነው ተባዕት የበግ ጠቦት፣+ 64 ለኃጢአት መባ የሚሆን አንድ የፍየል ጠቦት+ 65 እንዲሁም ለኅብረት መሥዋዕት+ የሚሆኑ ሁለት ከብቶች፣ አምስት አውራ በጎች፣ አምስት ተባዕት ፍየሎችና እያንዳንዳቸው አንድ ዓመት የሆናቸው አምስት ተባዕት የበግ ጠቦቶች አቀረበ። የጊድኦኒ ልጅ አቢዳን+ ያቀረበው መባ ይህ ነበር።

66 በአሥረኛውም ቀን የዳን ልጆች አለቃ የሆነው የአሚሻዳይ ልጅ አሂዔዜር+ 67 መባ አቀረበ፤ መባውም እንደ ቋሚ መለኪያ ሆኖ በሚያገለግለው በቅዱሱ ስፍራ ሰቅል+ መሠረት 130 ሰቅል የሚመዝን አንድ የብር ሳህንና 70 ሰቅል የሚመዝን አንድ የብር ጎድጓዳ ሳህን ሲሆን እያንዳንዳቸው ለእህል መባ የሚሆን በዘይት የተለወሰ የላመ ዱቄት የተሞሉ ነበሩ፤+ 68 በተጨማሪም ዕጣን የተሞላ 10 ሰቅል የሚመዝን አንድ የወርቅ ጽዋ፣ 69 ለሚቃጠል መባ የሚሆን አንድ ወይፈን፣ አንድ አውራ በግና አንድ ዓመት ገደማ የሆነው ተባዕት የበግ ጠቦት፣+ 70 ለኃጢአት መባ የሚሆን አንድ የፍየል ጠቦት+ 71 እንዲሁም ለኅብረት መሥዋዕት+ የሚሆኑ ሁለት ከብቶች፣ አምስት አውራ በጎች፣ አምስት ተባዕት ፍየሎችና እያንዳንዳቸው አንድ ዓመት የሆናቸው አምስት ተባዕት የበግ ጠቦቶች አቀረበ። የአሚሻዳይ ልጅ አሂዔዜር+ ያቀረበው መባ ይህ ነበር።

72 በ11ኛውም ቀን የአሴር ልጆች አለቃ የሆነው የኦክራን ልጅ ፓጊኤል+ 73 መባ አቀረበ፤ መባውም እንደ ቋሚ መለኪያ ሆኖ በሚያገለግለው በቅዱሱ ስፍራ ሰቅል+ መሠረት 130 ሰቅል የሚመዝን አንድ የብር ሳህንና 70 ሰቅል የሚመዝን አንድ የብር ጎድጓዳ ሳህን ሲሆን እያንዳንዳቸው ለእህል መባ የሚሆን በዘይት የተለወሰ የላመ ዱቄት የተሞሉ ነበሩ፤+ 74 በተጨማሪም ዕጣን የተሞላ 10 ሰቅል የሚመዝን አንድ የወርቅ ጽዋ፣ 75 ለሚቃጠል መባ የሚሆን አንድ ወይፈን፣ አንድ አውራ በግና አንድ ዓመት ገደማ የሆነው ተባዕት የበግ ጠቦት፣+ 76 ለኃጢአት መባ የሚሆን አንድ የፍየል ጠቦት+ 77 እንዲሁም ለኅብረት መሥዋዕት+ የሚሆኑ ሁለት ከብቶች፣ አምስት አውራ በጎች፣ አምስት ተባዕት ፍየሎችና እያንዳንዳቸው አንድ ዓመት የሆናቸው አምስት ተባዕት የበግ ጠቦቶች አቀረበ። የኦክራን ልጅ ፓጊኤል+ ያቀረበው መባ ይህ ነበር።

78 በ12ኛውም ቀን የንፍታሌም ልጆች አለቃ የሆነው የኤናን ልጅ አሂራ+ 79 መባ አቀረበ፤ መባውም እንደ ቋሚ መለኪያ ሆኖ በሚያገለግለው በቅዱሱ ስፍራ ሰቅል+ መሠረት 130 ሰቅል የሚመዝን አንድ የብር ሳህንና 70 ሰቅል የሚመዝን አንድ የብር ጎድጓዳ ሳህን ሲሆን እያንዳንዳቸው ለእህል መባ የሚሆን በዘይት የተለወሰ የላመ ዱቄት የተሞሉ ነበሩ፤+ 80 በተጨማሪም ዕጣን የተሞላ 10 ሰቅል የሚመዝን አንድ የወርቅ ጽዋ፣ 81 ለሚቃጠል መባ የሚሆን አንድ ወይፈን፣ አንድ አውራ በግና አንድ ዓመት ገደማ የሆነው ተባዕት የበግ ጠቦት፣+ 82 ለኃጢአት መባ የሚሆን አንድ የፍየል ጠቦት+ 83 እንዲሁም ለኅብረት መሥዋዕት+ የሚሆኑ ሁለት ከብቶች፣ አምስት አውራ በጎች፣ አምስት ተባዕት ፍየሎችና እያንዳንዳቸው አንድ ዓመት የሆናቸው አምስት ተባዕት የበግ ጠቦቶች አቀረበ። የኤናን ልጅ አሂራ+ ያቀረበው መባ ይህ ነበር።

84 የእስራኤል አለቆች መሠዊያው በተቀባበት ጊዜ ያቀረቡት የመሠዊያው ምርቃት መባ+ የሚከተለው ነው፦ 12 የብር ሳህኖች፣ 12 የብር ጎድጓዳ ሳህኖች፣ 12 የወርቅ ጽዋዎች፣+ 85 እያንዳንዱ የብር ሳህን 130 ሰቅል፣ እያንዳንዱም ጎድጓዳ ሳህን 70 ሰቅል ይመዝን ነበር፤ ዕቃዎቹ የተሠሩበት ብር በአጠቃላይ፣ እንደ ቋሚ መለኪያ ሆኖ በሚያገለግለው በቅዱሱ ስፍራ ሰቅል+ መሠረት 2,400 ሰቅል ነበር፤ 86 ዕጣን የተሞሉት 12 የወርቅ ጽዋዎች ሲመዘኑ እያንዳንዱ ጽዋ እንደ ቋሚ መለኪያ ሆኖ በሚያገለግለው በቅዱሱ ስፍራ ሰቅል መሠረት 10 ሰቅል ነበር፤ ጽዋዎቹ የተሠሩበት ወርቅ በአጠቃላይ 120 ሰቅል ነበር። 87 የእህል መባዎቻቸውን ጨምሮ ለሚቃጠል መባ የቀረቡት ከብቶች በአጠቃላይ 12 በሬዎች፣ 12 አውራ በጎችና እያንዳንዳቸው አንድ ዓመት የሆናቸው 12 ተባዕት የበግ ጠቦቶች ነበሩ፤ ለኃጢአት መባ የቀረቡት 12 የፍየል ጠቦቶች ነበሩ፤ 88 ለኅብረት መሥዋዕት የቀረቡት ከብቶች በአጠቃላይ 24 በሬዎች፣ 60 አውራ በጎች፣ 60 ተባዕት ፍየሎችና እያንዳንዳቸው አንድ ዓመት የሆናቸው 60 ተባዕት የበግ ጠቦቶች ነበሩ። መሠዊያው ከተቀባ+ በኋላ የቀረበው የመሠዊያው ምርቃት መባ+ ይህ ነበር።

89 ሙሴ ከአምላክ* ጋር ለመነጋገር ወደ መገናኛ ድንኳኑ በሚገባበት ጊዜ+ ሁሉ ከምሥክሩ ታቦት መክደኛ በላይ ድምፅ ሲያነጋግረው ይሰማ ነበር፤+ እሱም ከሁለቱ ኪሩቦች መካከል ያነጋግረው ነበር።+

8 ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ 2 “ለአሮን ‘መብራቶቹን በምታበራበት ጊዜ ሰባቱ መብራቶች በመቅረዙ ፊት ለፊት ላለው አካባቢ ብርሃን መስጠት ይኖርባቸዋል’ ብለህ ንገረው።”+ 3 አሮንም እንዲሁ አደረገ፤ ይሖዋ ሙሴን ባዘዘው መሠረት በመቅረዙ+ ፊት ለፊት ያለው አካባቢ ብርሃን እንዲያገኝ የመቅረዙን መብራቶች ለኮሳቸው። 4 የመቅረዙ አሠራር ይህ ነበር፦ አንድ ወጥ ከሆነ ወርቅ ተጠፍጥፎ የተሠራ ነበር፤ ግንዱም ሆነ የፈኩት አበቦቹ ወጥ ከሆነ ወርቅ ተጠፍጥፈው የተሠሩ ነበሩ።+ መቅረዙ የተሠራው ይሖዋ ለሙሴ ባሳየው ራእይ መሠረት ነበር።+

5 ይሖዋ ሙሴን ዳግመኛ እንዲህ አለው፦ 6 “ሌዋውያኑን ከእስራኤላውያን መካከል ወስደህ አንጻቸው።+ 7 እነሱንም የምታነጻቸው በሚከተለው መንገድ ነው፦ ከኃጢአት የሚያነጻ ውኃ እርጫቸው፤ እነሱም ሰውነታቸውን በሙሉ በምላጭ ይላጩ፤ እንዲሁም ልብሳቸውን ይጠቡ፤ ራሳቸውንም ያንጹ።+ 8 ከዚያም አንድ ወይፈንና+ አብሮት የሚቀርበውን በዘይት ከተለወሰ የላመ ዱቄት የተዘጋጀ የእህል መባ+ ይወስዳሉ፤ አንተም ለኃጢአት መባ+ እንዲሆን ሌላ ወይፈን ትወስዳለህ። 9 እንዲሁም ሌዋውያኑን በመገናኛ ድንኳኑ ፊት ታቀርባቸዋለህ፤ መላውን የእስራኤል ማኅበረሰብ ትሰበስባለህ።+ 10 ሌዋውያኑን በይሖዋ ፊት በምታቀርባቸው ጊዜ እስራኤላውያን በሌዋውያኑ ላይ እጆቻቸውን ይጫኑ።+ 11 አሮንም ከእስራኤላውያን መካከል ሌዋውያኑን እንደሚወዘወዝ መባ+ አድርጎ በይሖዋ ፊት ያቅርባቸው፤* እነሱም ለይሖዋ የሚቀርበውን አገልግሎት ያከናውናሉ።+

12 “ከዚያም ሌዋውያኑ በወይፈኖቹ ራስ ላይ እጆቻቸውን ይጭናሉ።+ ይህን ካደረጉ በኋላ ለእነሱ ማስተሰረያ እንዲሆኑ+ አንደኛውን ወይፈን የኃጢአት መባ ሌላኛውን ደግሞ የሚቃጠል መባ አድርገው ለይሖዋ ያቀርባሉ። 13 ሌዋውያኑንም በአሮንና በወንዶች ልጆቹ ፊት እንዲቆሙ ካደረግክ በኋላ እንደሚወዘወዝ መባ አድርገህ ለይሖዋ አቅርባቸው።* 14 ሌዋውያኑን ከእስራኤላውያን መካከል ለያቸው፤ ሌዋውያኑም የእኔ ይሆናሉ።+ 15 ከዚህ በኋላ ሌዋውያኑ በመገናኛ ድንኳኑ ለማገልገል ይመጣሉ። እነሱን የምታነጻቸውና እንደሚወዘወዝ መባ አድርገህ የምታቀርባቸው* በዚህ መንገድ ነው። 16 ምክንያቱም እነሱ የተሰጡ ይኸውም ከእስራኤላውያን መካከል ለእኔ የተሰጡ ናቸው። በእስራኤላውያን በኩሮች ሁሉ* ምትክ+ እነሱን ለራሴ እወስዳቸዋለሁ። 17 ምክንያቱም ሰውም ሆነ እንስሳ ከእስራኤላውያን መካከል በኩር የሆነ ሁሉ የእኔ ነው።+ በግብፅ ምድር ያለውን በኩር ሁሉ በመታሁበት ቀን እነሱን ለራሴ ቀድሻቸዋለሁ።+ 18 ሌዋውያኑን በእስራኤላውያን በኩር ሁሉ ምትክ እወስዳቸዋለሁ። 19 የእስራኤል ሕዝብ ወደ ቅዱሱ ስፍራ በመቅረቡ የተነሳ በመካከሉ መቅሰፍት እንዳይከሰት+ በእስራኤላውያን ምትክ በመገናኛ ድንኳኑ ያገለግሉና+ ለእነሱ ያስተሰርዩ ዘንድ ከእስራኤላውያን መካከል ሌዋውያኑን ለአሮንና ለወንዶች ልጆቹ የተሰጡ አድርጌ እሰጣቸዋለሁ።”

20 ሙሴ፣ አሮንና መላው የእስራኤል ማኅበረሰብ ሁሉ ለሌዋውያኑ እንዲሁ አደረጉ። እስራኤላውያንም ይሖዋ ሌዋውያኑን አስመልክቶ ሙሴን ያዘዘውን ሁሉ አደረጉ። 21 በመሆኑም ሌዋውያኑ ራሳቸውን አነጹ፤ ልብሶቻቸውንም አጠቡ፤+ በመቀጠልም አሮን እንደሚወዘወዝ መባ አድርጎ በይሖዋ ፊት አቀረባቸው።*+ ከዚያም አሮን እነሱን ለማንጻት ማስተሰረያ አቀረበላቸው።+ 22 ይህ ሁሉ ከሆነ በኋላ ሌዋውያኑ በመገናኛ ድንኳኑ በአሮንና በወንዶች ልጆቹ ፊት አገልግሎታቸውን ለመፈጸም ገቡ። ይሖዋ ሌዋውያኑን በተመለከተ ሙሴን ባዘዘው መሠረት እንዲሁ አደረጉላቸው።

23 በዚህ ጊዜ ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ 24 “ሌዋውያኑን በተመለከተ የተደረገው ዝግጅት የሚከተለው ነው፦ አንድ ወንድ ዕድሜው 25 ዓመትና ከዚያ በላይ ከሆነ በመገናኛ ድንኳኑ ከሚያገለግለው ቡድን ጋር ይቀላቀላል። 25 ዕድሜው 50 ዓመት ከሞላ ግን ከሚያገለግልበት ቡድን ጡረታ ይወጣል፤ ከዚያ በኋላ ማገልገል አይጠበቅበትም። 26 ይህ ሰው በመገናኛ ድንኳኑ ኃላፊነታቸውን እየተወጡ ያሉትን ወንድሞቹን ሊያገለግል ይችላል፤ ሆኖም በዚያ ማገልገል የለበትም። ሌዋውያኑንና የተጣለባቸውን ኃላፊነት በተመለከተ ማድረግ ያለብህ ይህን ነው።”+

9 ከግብፅ ምድር በወጡ በሁለተኛው ዓመት በመጀመሪያው ወር+ ይሖዋ ሙሴን በሲና ምድረ በዳ እንዲህ በማለት አነጋገረው፦ 2 “እስራኤላውያን የፋሲካን* መሥዋዕት+ በተወሰነለት ጊዜ ያዘጋጁ።+ 3 በዚህ ወር በ14ኛው ቀን አመሻሹ ላይ* በተወሰነለት ጊዜ አዘጋጁት። ደንቦቹን ሁሉና ሥርዓቱን ሁሉ ተከትላችሁ አዘጋጁት።”+

4 በመሆኑም ሙሴ እስራኤላውያን የፋሲካን መሥዋዕት እንዲያዘጋጁ ነገራቸው። 5 እነሱም በመጀመሪያው ወር ከወሩም በ14ኛው ቀን አመሻሹ ላይ* የፋሲካን መሥዋዕት በሲና ምድረ በዳ አዘጋጁ። እስራኤላውያንም ሁሉንም ነገር ይሖዋ ሙሴን ባዘዘው መሠረት አደረጉ።

6 የሞተ ሰው ነክተው* በመርከሳቸው+ የተነሳ በዚያ ቀን የፋሲካን መሥዋዕት ማዘጋጀት ያልቻሉ ሰዎች ነበሩ። በመሆኑም እነዚህ ሰዎች በዚያ ቀን ሙሴና አሮን ፊት ቀረቡ፤+ 7 እንዲህም አሉት፦ “እኛ የሞተ ሰው በመንካታችን* የተነሳ ረክሰናል። ይሁንና ከእስራኤላውያን ጋር መባውን በተወሰነለት ጊዜ ለይሖዋ እንዳናቀርብ የምንከለከለው ለምንድን ነው?”+ 8 በዚህ ጊዜ ሙሴ “ይሖዋ እናንተን በተመለከተ የሚሰጠውን ትእዛዝ እስክሰማ ድረስ እዚያ ጠብቁ”+ አላቸው።

9 ከዚያም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ 10 “እስራኤላውያንን እንዲህ በላቸው፦ ‘ከእናንተ ወይም ከመጪዎቹ ትውልዶቻችሁ መካከል ማንኛውም ሰው የሞተ ሰው በመንካቱ* ቢረክስ+ ወይም ሩቅ መንገድ ቢሄድ ለይሖዋ የፋሲካን መሥዋዕት ማዘጋጀት ይጠበቅበታል። 11 እነሱም በሁለተኛው ወር+ በ14ኛው ቀን አመሻሹ ላይ* ያዘጋጁት። ይህንም ከቂጣና ከመራራ ቅጠል ጋር ይብሉት።+ 12 ከእሱም ላይ እስከ ጠዋት ድረስ ምንም ማስተረፍ+ ወይም ከአጥንቱ ውስጥ አንዱንም መስበር+ የለባቸውም። ፋሲካን በተመለከተ የወጣውን ደንብ ሁሉ ተከትለው ያዘጋጁት። 13 ይሁንና አንድ ሰው ንጹሕ ሆኖ ሳለ ወይም ሩቅ መንገድ ሳይሄድ በቸልተኝነት የፋሲካን መሥዋዕት ሳያዘጋጅ ቢቀር፣ ያ ሰው* የይሖዋን መባ በተወሰነለት ጊዜ ስላላቀረበ ከሕዝቡ መካከል ተለይቶ እንዲጠፋ ይደረግ።+ ይህ ሰው ለሠራው ኃጢአት ይጠየቅበታል።

14 “‘በመካከላችሁ የሚኖር የባዕድ አገር ሰው ካለ እሱም ለይሖዋ የፋሲካን መሥዋዕት ማዘጋጀት አለበት።+ ይህን በፋሲካው ደንብና በወጣለት ሥርዓት መሠረት ማድረግ አለበት።+ ለሁላችሁም ማለትም ለባዕድ አገሩም ሰው ሆነ ለአገሬው ተወላጅ አንድ ዓይነት ደንብ ይኑር።’”+

15 የማደሪያ ድንኳኑ በተተከለበት ቀን+ ደመናው የማደሪያ ድንኳኑን ይኸውም የምሥክሩን ድንኳን ሸፈነው፤ ሆኖም ከምሽት ጀምሮ እስከ ጠዋት ድረስ በማደሪያ ድንኳኑ ላይ እሳት የሚመስል ነገር ታየ።+ 16 ሁልጊዜም እንዲህ ይሆን ነበር፦ ቀን ቀን ደመናው ድንኳኑን ይሸፍነው ነበር፤ ሌሊት ሌሊት ደግሞ እሳት የሚመስል ነገር ይታይ ነበር።+ 17 ደመናው ከድንኳኑ ላይ በሚነሳበት ጊዜ ሁሉ እስራኤላውያን ወዲያውኑ ተነስተው ይጓዙ ነበር፤+ ደመናው በሚቆምበት ቦታ ደግሞ እስራኤላውያን ይሰፍሩ ነበር።+ 18 እስራኤላውያን ተነስተው የሚጓዙት በይሖዋ ትእዛዝ ነበር፤ የሚሰፍሩትም በይሖዋ ትእዛዝ ነበር።+ ደመናው በማደሪያ ድንኳኑ ላይ በሚቆይባቸው ቀናት ሁሉ እነሱም በሰፈሩበት ቦታ ይቆዩ ነበር። 19 ደመናው በማደሪያ ድንኳኑ ላይ ረዘም ላሉ ቀናት በሚቆይበትም ጊዜ እስራኤላውያን ይሖዋን በመታዘዝ ባሉበት ይቆዩ ነበር።+ 20 አንዳንድ ጊዜ ደመናው በማደሪያ ድንኳኑ ላይ የሚቆየው ለጥቂት ቀናት ነበር። እነሱም የሚሰፍሩት በይሖዋ ትእዛዝ ነበር፤ ተነስተው የሚጓዙትም በይሖዋ ትእዛዝ ነበር። 21 አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ደመናው የሚቆየው ከምሽት እስከ ጠዋት ድረስ ብቻ ነበር፤ ጠዋት ላይ ደመናው ሲነሳ እነሱም ተነስተው ይጓዛሉ። ቀንም ሆነ ሌሊት ደመናው በሚነሳበት ጊዜ እነሱም ተነስተው ይጓዛሉ።+ 22 እስራኤላውያን ደመናው በማደሪያ ድንኳኑ ላይ እስካለ ድረስ ለሁለት ቀንም ይሁን ለአንድ ወር ወይም ረዘም ላለ ጊዜ በሰፈሩበት ይቆያሉ እንጂ ተነስተው አይጓዙም። ደመናው በሚነሳበት ጊዜ ግን ተነስተው ይጓዛሉ። 23 እነሱም የሚሰፍሩት በይሖዋ ትእዛዝ ነበር፤ ተነስተውም የሚጓዙት በይሖዋ ትእዛዝ ነበር። ይሖዋ በሙሴ አማካኝነት በሰጠው ትእዛዝ መሠረት ይሖዋ የጣለባቸውን ግዴታ ይወጡ ነበር።

10 ከዚያም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ 2 “ሁለት መለከቶችን+ ለራስህ ሥራ፤ ወጥ ከሆነ ብር ጠፍጥፈህ ሥራቸው፤ መለከቶቹንም ማኅበረሰቡን ለመሰብሰብና ሕዝቡ ከሰፈረባቸው ቦታዎች ተነስቶ እንዲሄድ ምልክት ለመስጠት ተጠቀምባቸው። 3 ሁለቱም መለከቶች ሲነፉ መላው ማኅበረሰብ በመገናኛ ድንኳኑ መግቢያ ላይ ወደ አንተ ይሰብሰብ።+ 4 አንዱ መለከት ብቻ ከተነፋ ግን የእስራኤል የሺህ አለቆች ብቻ ወደ አንተ ይሰብሰቡ።+

5 “ድምፁን እያለዋወጣችሁ መለከቱን ስትነፉ በስተ ምሥራቅ+ የሰፈሩት ተነስተው ይጓዙ። 6 ለሁለተኛ ጊዜ ድምፁን እያለዋወጣችሁ መለከቱን ስትነፉ በስተ ደቡብ+ የሰፈሩት ተነስተው ይጓዙ። ከመካከላቸው አንዱ ምድብ ተነስቶ በተጓዘ ቁጥር መለከቱን በዚህ መንገድ ይንፉ።

7 “ጉባኤውን አንድ ላይ በምትሰበስቡበት ጊዜ መለከቶቹን መንፋት+ ይኖርባችኋል፤ በዚህ ጊዜ ግን ድምፁን እያለዋወጣችሁ መንፋት የለባችሁም። 8 ካህናት የሆኑት የአሮን ወንዶች ልጆች መለከቶቹን ይንፉ፤+ መለከቶቹን በዚህ መንገድ መጠቀም በትውልዶቻችሁ ሁሉ ለእናንተ ዘላቂ ደንብ ሆኖ ያገለግላል።

9 “ግፍ ከሚፈጽምባችሁ ጨቋኝ ጠላት ጋር በምድራችሁ ጦርነት ብትገጥሙ በመለከቶቹ አማካኝነት የክተት ጥሪ አሰሙ፤+ አምላካችሁ ይሖዋም ያስባችኋል፤ ከጠላቶቻችሁም ያድናችኋል።

10 “እንዲሁም በደስታችሁ ወቅት+ ይኸውም በበዓላት ወቅቶችና+ የወር መባቻን ስታከብሩ በሚቃጠሉ መባዎቻችሁ+ እንዲሁም በኅብረት መሥዋዕቶቻችሁ+ ላይ መለከቶቹን ንፉ፤ እነሱም በአምላካችሁ ፊት ለእናንተ እንደ መታሰቢያ ሆነው ያገለግላሉ። እኔ አምላካችሁ ይሖዋ ነኝ።”+

11 በሁለተኛው ዓመት ሁለተኛ ወር፣ ከወሩም በ20ኛው ቀን+ ደመናው ከምሥክሩ የማደሪያ ድንኳን ላይ ተነሳ።+ 12 እስራኤላውያንም በወጣላቸው የጉዞ ቅደም ተከተል መሠረት ከሲና ምድረ በዳ ተነስተው መጓዝ ጀመሩ፤+ ደመናውም በፋራን ምድረ በዳ+ ቆመ። 13 ይሖዋ በሙሴ አማካኝነት በሰጠው ትእዛዝ መሠረት ተነስተው ሲጓዙ ይህ የመጀመሪያ ጊዜ ነበር።+

14 ሦስት ነገዶችን ያቀፈው የይሁዳ ልጆች ምድብ በየምድቡ* በመሆን በመጀመሪያ ተነስቶ ተጓዘ፤ የምድቡም አለቃ የአሚናዳብ ልጅ ነአሶን+ ነበር። 15 የይሳኮር ልጆች ነገድ ምድብ አለቃም የጹአር ልጅ ናትናኤል+ ነበር። 16 የዛብሎን ልጆች ነገድ ምድብ አለቃ የሄሎን ልጅ ኤልያብ+ ነበር።

17 የማደሪያ ድንኳኑ በተነቀለም ጊዜ+ የማደሪያ ድንኳኑን የሚሸከሙት የጌድሶን ወንዶች ልጆችና+ የሜራሪ ወንዶች ልጆች+ ተነስተው ተጓዙ።

18 ከዚያም ሦስት ነገዶችን ያቀፈው የሮቤል ምድብ በየምድቡ* በመሆን ተነስቶ ተጓዘ፤ የምድቡም አለቃ የሸደኡር ልጅ ኤሊጹር+ ነበር። 19 የስምዖን ልጆች ነገድ ምድብ አለቃ የጹሪሻዳይ ልጅ ሸሉሚኤል+ ነበር። 20 የጋድ ልጆች ነገድ ምድብ አለቃ የደኡዔል ልጅ ኤሊያሳፍ+ ነበር።

21 ከዚያም የመቅደሱን ዕቃዎች የሚሸከሙት ቀአታውያን+ ተነስተው ተጓዙ። እነሱ በሚደርሱበት ጊዜ የማደሪያ ድንኳኑ ተተክሎ ይቆያል።

22 ቀጥሎም ሦስት ነገዶችን ያቀፈው የኤፍሬም ምድብ በየምድቡ* በመሆን ተነስቶ ተጓዘ፤ የምድቡም አለቃ የአሚሁድ ልጅ ኤሊሻማ+ ነበር። 23 የምናሴ ልጆች ነገድ ምድብ አለቃ የፐዳጹር ልጅ ገማልያል+ ነበር። 24 የቢንያም ልጆች ነገድ ምድብ አለቃ የጊድኦኒ ልጅ አቢዳን+ ነበር።

25 ከዚያም ሦስት ነገዶችን ያቀፈው የዳን ልጆች ምድብ ለሁሉም ምድቦች የኋላ ደጀን በመሆን በየምድቡ* ተነስቶ ተጓዘ፤ የሠራዊቱም አለቃ የአሚሻዳይ ልጅ አሂዔዜር+ ነበር። 26 የአሴር ልጆች ነገድ ምድብ አለቃ የኦክራን ልጅ ፓጊኤል+ ነበር። 27 የንፍታሌም ልጆች ነገድ ምድብ አለቃ የኤናን ልጅ አሂራ+ ነበር። 28 እስራኤላውያን በየምድባቸው* በመሆን ተነስተው የሚጓዙበት የጉዞ ቅደም ተከተል ይህ ነበር።+

29 ከዚያም ሙሴ የአማቱን የምድያማዊውን የረኡዔልን*+ ልጅ ሆባብን እንዲህ አለው፦ “እንግዲህ እኛ ይሖዋ ‘ለእናንተ እሰጣችኋለሁ’+ ወዳለን ምድር ተነስተን መጓዛችን ነው። አንተም ከእኛ ጋር ና፤+ ይሖዋ ለእስራኤል መልካም ነገር ለማድረግ ቃል ስለገባ+ እኛም መልካም ነገር እናደርግልሃለን።” 30 እሱ ግን “አብሬያችሁ አልሄድም። እኔ ወደ አገሬና ወደ ዘመዶቼ እመለሳለሁ” አለው። 31 በዚህ ጊዜ እንዲህ አለው፦ “በምድረ በዳው የት መስፈር እንዳለብን ስለምታውቅ እባክህ ትተኸን አትሂድ፤ መንገድም ልትመራን* ትችላለህ። 32 ከእኛ ጋር የምትሄድ ከሆነ+ ይሖዋ የሚያደርግልንን መልካም ነገር ሁሉ እኛም በእርግጥ ለአንተ እናደርግልሃለን።”

33 በመሆኑም የሦስት ቀን መንገድ ለመጓዝ ከይሖዋ ተራራ+ ተነስተው ጉዞ ጀመሩ፤ የሦስት ቀኑን ጉዞ በሚጓዙበት ጊዜም የይሖዋ የቃል ኪዳን ታቦት+ ለእነሱ የማረፊያ ቦታ ለመፈለግ ከፊት ከፊታቸው ይሄድ ነበር።+ 34 ከሰፈሩበት ቦታ በሚነሱበት ጊዜ የይሖዋ ደመና+ ቀን ቀን በላያቸው ይሆን ነበር።

35 ታቦቱ በሚንቀሳቀስበት ጊዜ ሁሉ ሙሴ “ይሖዋ ሆይ፣ ተነስ፤+ ጠላቶችህ ይበታተኑ፤ የሚጠሉህም ሁሉ ከፊትህ ይሽሹ” ይል ነበር። 36 ታቦቱ በሚያርፍበትም ጊዜ “ይሖዋ ሆይ፣ በሺዎች ወደሚቆጠሩት ስፍር ቁጥር የሌላቸው እስራኤላውያን*+ ተመለስ” ይል ነበር።

11 በዚህ ጊዜ ሕዝቡ፣ ስለደረሰበት ችግር በይሖዋ ፊት ክፉኛ ማጉረምረም ጀመረ። ይሖዋ ይህን ሲሰማ ቁጣው ነደደ፤ ከይሖዋም የመጣ እሳት በእነሱ ላይ ተቀጣጠለ፤ በሰፈሩ ዳርቻ ያሉትን የተወሰኑ ሰዎችም በላ። 2 ሕዝቡ ወደ ሙሴ መጮኽ ሲጀምር ሙሴ ይሖዋን ተማጸነ፤+ እሳቱም ከሰመ። 3 ከይሖዋ የመጣ እሳት በእነሱ ላይ ስለነደደም የዚያ ቦታ ስም ታበራ* ተባለ።+

4 እስራኤላውያንም በመካከላቸው የነበረው ድብልቅ ሕዝብ*+ ሲስገበገብ+ ሲያዩ እንዲህ በማለት እንደገና ያለቅሱ ጀመር፦ “እንግዲህ አሁን የምንበላው ሥጋ ማን ይሰጠናል?+ 5 በግብፅ እያለን በነፃ እንበላው የነበረው ዓሣ እንዲሁም ኪያሩ፣ ሐብሐቡ፣ ባሮ ሽንኩርቱ፣ ቀይ ሽንኩርቱና ነጭ ሽንኩርቱ በዓይናችን ላይ ዞሯል!+ 6 አሁን ግን ዝለናል።* ከዚህ መና በስተቀር ሌላ የምናየው ነገር የለም።”+

7 መናው+ እንደ ድንብላል ዘር+ ነበር፤ መልኩም ሙጫ* ይመስል ነበር። 8 ሕዝቡም ሜዳ ላይ ወጥቶ መናውን ከለቀመ በኋላ በወፍጮ ይፈጨው ወይም በሙቀጫ ይወቅጠው ነበር። ከዚያም በድስት ይቀቅሉት ወይም እንደ ቂጣ ይጋግሩት ነበር፤+ ጣዕሙም በዘይት ተለውሶ እንደተጋገረ ጣፋጭ ቂጣ ነበር። 9 ሌሊት በሰፈሩ ላይ ጤዛ በሚወርድበት ጊዜ መናውም በላዩ ላይ ይወርድ ነበር።+

10 ሙሴም ሕዝቡ ይኸውም እያንዳንዱ ሰው በድንኳኑ ደጃፍ ላይ ሆኖ ከቤተሰቡ ጋር ሲያለቅስ ሰማ። ይሖዋም እጅግ ተቆጣ፤+ ሙሴም በጣም አዘነ። 11 ከዚያም ሙሴ ይሖዋን እንዲህ አለው፦ “አገልጋይህን የምታጎሳቁለው ለምንድን ነው? በፊትህ ሞገስ ያጣሁትና የዚህን ሁሉ ሕዝብ ሸክም በእኔ ላይ የጫንከው ለምንድን ነው?+ 12 ይህን ሁሉ ሕዝብ የፀነስኩት እኔ ነኝ? ለአባቶቻቸው ለመስጠት ቃል ወደገባህላቸው ምድር እንዳስገባቸው ‘የሚጠባን ሕፃን እንደሚታቀፍ ሞግዚት በጉያህ እቀፋቸው’ የምትለኝ የወለድኳቸው እኔ ነኝ?+ 13 ለዚህ ሁሉ ሕዝብ የሚሆን ሥጋ ከየት ነው የማመጣው? ይኸው እነሱ ‘የምንበላው ሥጋ ስጠን!’ በማለት እያለቀሱብኝ ነው። 14 ይህን ሁሉ ሕዝብ እኔ ብቻዬን ልሸከመው አልችልም፤ ከአቅሜ በላይ ነው።+ 15 እንዲህስ ከምታደርገኝ እባክህ አሁኑኑ ግደለኝ።+ በፊትህ ሞገስ አግኝቼ ከሆነ ከእንግዲህ መከራ እንዳይ አታድርገኝ።”

16 ይሖዋም መልሶ ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ከእስራኤል ሽማግሌዎች መካከል የሕዝቡ ሽማግሌዎችና አለቆች+ የመሆን ብቃት አላቸው የምትላቸውን 70 ሰዎች ሰብስብልኝ፤ እነሱንም ወደ መገናኛ ድንኳኑ ውሰዳቸውና በዚያ ከአንተ ጋር ይቁሙ። 17 እኔም ወርጄ+ በዚያ ከአንተ ጋር እነጋገራለሁ፤+ በአንተ ላይ ካለው መንፈስ+ ወስጄ በእነሱ ላይ አደርጋለሁ፤ እነሱም የሕዝቡን ሸክም ብቻህን እንዳትሸከም ይረዱሃል።+ 18 ሕዝቡንም እንዲህ በለው፦ ‘ሥጋ ስለምትበሉ ለነገ ራሳችሁን ቀድሱ፤+ ምክንያቱም በይሖዋ ፊት አልቅሳችኋል፤+ ደግሞም “የምንበላው ሥጋ ማን ይሰጠናል? በግብፅ የነበርንበት ሁኔታ የተሻለ ነበር”+ ብላችኋል። ይሖዋ በእርግጥ ሥጋ ይሰጣችኋል፤ እናንተም ትበላላችሁ።+ 19 የምትበሉትም ለአንድ ቀን ወይም ለ2 ቀን ወይም ለ5 ቀን ወይም ለ10 ቀን ወይም ለ20 ቀን አይደለም፤ 20 ከዚህ ይልቅ በአፍንጫችሁ እስኪወጣና እስኪያንገፈግፋችሁ+ ድረስ ወር ሙሉ ትበላላችሁ፤ ምክንያቱም በመካከላችሁ ያለውን ይሖዋን ትታችኋል፤ እንዲሁም “ከግብፅ የወጣነው ለምንድን ነው?” በማለት በፊቱ አልቅሳችኋል።’”+

21 ከዚያም ሙሴ እንዲህ አለ፦ “እኔ በመካከሉ የምገኘው ሕዝብ 600,000 እግረኛ ወንዶች+ ያሉበት ነው፤ አንተ ደግሞ ‘ሥጋ እሰጣቸዋለሁ፤ ወር ሙሉ እስኪጠግቡ ይበላሉ’ ትላለህ። 22 በጎቹና ከብቶቹ ሁሉ ቢታረዱ እንኳ ይበቃቸዋል? የባሕር ዓሣዎች ሁሉ ቢያዙስ ሊበቃቸው ይችላል?”

23 ከዚያም ይሖዋ ሙሴን “ለመሆኑ የይሖዋ እጅ አጭር ነው?+ እንግዲህ ያልኩት ነገር ይፈጸምልህ እንደሆነና እንዳልሆነ ታያለህ” አለው።

24 ሙሴም ወጥቶ የይሖዋን ቃል ለሕዝቡ ተናገረ። እንዲሁም ከሕዝቡ ሽማግሌዎች መካከል 70 ሰዎችን ሰብስቦ በድንኳኑ ዙሪያ እንዲቆሙ አደረገ።+ 25 ከዚያም ይሖዋ በደመና ወርዶ+ አነጋገረው፤+ በሙሴ ላይ ከነበረውም መንፈስ+ ወስዶ በ70ዎቹ ሽማግሌዎች ላይ አደረገ። እነሱም ወዲያው መንፈሱ እንዳረፈባቸው እንደ ነቢያት አደረጋቸው፤*+ ሆኖም ዳግመኛ እንደዚያ አልሆኑም።

26 በዚህ ጊዜ ከሰዎቹ መካከል ሁለቱ በሰፈሩ ውስጥ ቀርተው ነበር። ስማቸውም ኤልዳድና ሞዳድ ነበር። እነዚህ ሰዎች ምንም እንኳ ወደ ድንኳኑ ባይሄዱም ስማቸው ከተመዘገቡት ሰዎች መካከል ስለነበሩ መንፈሱ በእነሱም ላይ ወረደ። በመሆኑም እነሱም በሰፈሩ ውስጥ እንደ ነቢያት ሆኑ። 27 አንድ ወጣትም እየሮጠ በመሄድ “ኤልዳድና ሞዳድ በሰፈሩ ውስጥ እንደ ነቢያት እየሆኑ ነው!” ሲል ለሙሴ ነገረው። 28 በዚህ ጊዜ ከወጣትነቱ ጀምሮ የሙሴ አገልጋይ የነበረው የነዌ ልጅ ኢያሱ+ “ጌታዬ ሙሴ ሆይ፣ እነዚህን ሰዎች ከልክላቸው እንጂ!”+ ሲል ተናገረ። 29 ሙሴ ግን እንዲህ አለው፦ “ስለ እኔ ተቆርቁረህ ነው? አትቆርቆር፤ የይሖዋ ሕዝቦች በሙሉ ነቢያት ቢሆኑና ይሖዋ መንፈሱን ቢሰጣቸው እንዴት ደስ ባለኝ!” 30 በኋላም ሙሴ ከእስራኤል ሽማግሌዎች ጋር ወደ ሰፈሩ ተመለሰ።

31 ከዚያም ነፋስ ከይሖዋ ዘንድ ወጥቶ ድርጭቶችን ከባሕሩ እየነዳ በማምጣት በሰፈሩ ዙሪያ በተናቸው፤+ ድርጭቶቹም የአንድ ቀን መንገድ ያህል በአንድ በኩል፣ የአንድ ቀን መንገድ ያህል ደግሞ በሌላ በኩል በሰፈሩ ዙሪያ ሁሉ ተበትነው ነበር፤ መሬት ላይም ሁለት ክንድ* ከፍታ ያህል ተቆልለው ነበር። 32 ሕዝቡም በዚያን ዕለት ቀኑን ሙሉና ሌሊቱን ሙሉ እንዲሁም በማግስቱ ቀኑን ሙሉ ድርጭቶቹን ሲሰበስብ ዋለ። ከአሥር ሆሜር* ያነሰ የሰበሰበ አልነበረም፤ የሰበሰቧቸውንም በሰፈሩ ዙሪያ አሰጧቸው። 33 ሆኖም ሥጋውን ገና ሳያኝኩት፣ በጥርሳቸው መካከል እያለ የይሖዋ ቁጣ በሕዝቡ ላይ ነደደ፤ ይሖዋም ሕዝቡን ክፉኛ ፈጀ።+

34 እነሱም ሲስገበገቡ+ የነበሩትን ሰዎች በዚያ ስለቀበሯቸው የቦታውን ስም ቂብሮትሃታባ*+ አሉት። 35 ሕዝቡም ከቂብሮትሃታባ ተነስቶ ወደ ሃጼሮት+ ተጓዘ፤ በሃጼሮትም ተቀመጠ።

12 ሙሴ ኩሻዊት ሴት አግብቶ ስለነበር ባገባት ኩሻዊት ሴት+ የተነሳ ሚርያምና አሮን ይነቅፉት ጀመር። 2 እነሱም “ለመሆኑ ይሖዋ የሚናገረው በሙሴ አማካኝነት ብቻ ነው? በእኛስ በኩል አልተናገረም?”+ ይሉ ነበር። ይሖዋም ይህን ይሰማ ነበር።+ 3 ሙሴ በምድር ላይ ከነበሩ ሰዎች ሁሉ ይልቅ በጣም የዋህ ነበር።*+

4 ይሖዋም ድንገት ሙሴን፣ አሮንንና ሚርያምን “ሦስታችሁም ወደ መገናኛ ድንኳኑ ውጡ” አላቸው። በመሆኑም ሦስቱም ወጡ። 5 ይሖዋም በደመና ዓምድ ወርዶ+ በድንኳኑ መግቢያ ላይ በመቆም አሮንንና ሚርያምን ጠራቸው። በዚህ ጊዜ ሁለቱም ወደ ፊት ቀረቡ። 6 እሱም እንዲህ አለ፦ “እባካችሁ ቃሌን ስሙ። አንድ የይሖዋ ነቢይ በመካከላችሁ ቢኖር በራእይ አማካኝነት+ ራሴን አሳውቀው በሕልምም+ አነጋግረው ነበር። 7 አገልጋዬን ሙሴን በተመለከተ ግን እንዲህ አይደለም! እሱ በቤቴ ሁሉ ላይ አደራ የተጣለበት* ሰው ነው።+ 8 እኔ እሱን የማነጋግረው ፊት ለፊት*+ በግልጽ እንጂ በእንቆቅልሽ አይደለም፤ እሱም የይሖዋን አምሳል ያያል። ታዲያ አገልጋዬን ሙሴን ስትነቅፉት ምነው አልፈራችሁም?”

9 በመሆኑም የይሖዋ ቁጣ በእነሱ ላይ ነደደ፤ ትቷቸውም ሄደ። 10 ከዚያም ደመናው ከድንኳኑ ላይ ተነሳ፤ በዚህ ጊዜ ሚርያም በሥጋ ደዌ ተመታ እንደ በረዶ ነጭ ሆና ነበር።+ አሮንም ወደ ሚርያም ዞር ሲል በሥጋ ደዌ ተመታ አየ።+ 11 አሮንም ወዲያውኑ ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ይቅርታ አድርግልኝ ጌታዬ! እባክህ ይህን ኃጢአት አትቁጠርብን! የፈጸምነው የሞኝነት ድርጊት ነው። 12 እባክህ፣ ግማሽ አካሉ ተበልቶ የተወለደ ጭንጋፍ መስላ እንድትቀር አታድርግ!” 13 ሙሴም “አምላክ ሆይ፣ እባክህ ፈውሳት! እባክህ!” በማለት ወደ ይሖዋ ጮኸ።+

14 ይሖዋም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “አባቷ ፊቷ ላይ ቢተፋባት ለሰባት ቀን ተዋርዳ ትቆይ አልነበረም? አሁንም ከሰፈር ውጭ ለሰባት ቀን ተገልላ እንድትቆይ ይደረግ፤+ ከዚያ በኋላ እንድትመለስ ማድረግ ይቻላል።” 15 ስለዚህ ሚርያም ለሰባት ቀን ከሰፈሩ ውጭ ተገልላ እንድትቆይ ተደረገ፤+ ሕዝቡም ሚርያም ተመልሳ እንድትቀላቀል እስኪደረግ ድረስ ጉዞውን አልቀጠለም። 16 ከዚያም ሕዝቡ ከሃጼሮት+ ተነስቶ በፋራን ምድረ በዳ+ ሰፈረ።

13 ይሖዋም ሙሴን እንዲህ አለው፦ 2 “ለእስራኤላውያን የምሰጠውን የከነአንን ምድር እንዲሰልሉ ሰዎችን ላክ። ከእያንዳንዱ የአባቶች ነገድ አንድ አንድ ሰው ይኸውም ከመካከላቸው አለቃ+ የሆነውን ሰው ትልካለህ።”+

3 በመሆኑም ሙሴ ይሖዋ በሰጠው መመሪያ መሠረት ከፋራን ምድረ በዳ+ ላካቸው። ሰዎቹ በሙሉ የእስራኤላውያን መሪዎች ነበሩ። 4 ስማቸውም የሚከተለው ነው፦ ከሮቤል ነገድ የዛኩር ልጅ ሻሙአ፣ 5 ከስምዖን ነገድ የሆሪ ልጅ ሻፋጥ፣ 6 ከይሁዳ ነገድ የየፎኒ ልጅ ካሌብ፣+ 7 ከይሳኮር ነገድ የዮሴፍ ልጅ ይግዓል፣ 8 ከኤፍሬም ነገድ የነዌ ልጅ ሆሺአ፣+ 9 ከቢንያም ነገድ የራፉ ልጅ ፓልጢ፣ 10 ከዛብሎን ነገድ የሶዲ ልጅ ጋዲኤል፣ 11 ከዮሴፍ+ ነገድ መካከል ለምናሴ+ ነገድ የሱሲ ልጅ ጋዲ፣ 12 ከዳን ነገድ የገማሊ ልጅ አሚዔል፣ 13 ከአሴር ነገድ የሚካኤል ልጅ ሰቱር፣ 14 ከንፍታሌም ነገድ የዎፍሲ ልጅ ናህቢ 15 እንዲሁም ከጋድ ነገድ የማኪ ልጅ ጌኡዔል። 16 ሙሴ ምድሪቱን እንዲሰልሉ የላካቸው ሰዎች ስም ይህ ነው። ሙሴም ለነዌ ልጅ ለሆሺአ፣ ኢያሱ*+ የሚል ስም አወጣለት።

17 ሙሴ የከነአንን ምድር እንዲሰልሉ ሰዎቹን ሲልካቸው እንዲህ አላቸው፦ “በዚህ አድርጋችሁ ወደ ኔጌብ አቅኑ፤ ከዚያም ወደ ተራራማው አካባቢ ሂዱ።+ 18 ምድሪቱ ምን እንደምትመስል፣+ ነዋሪዎቿም ብርቱ ወይም ደካማ፣ ጥቂት ወይም ብዙ መሆናቸውን እዩ፤ 19 እንዲሁም ምድሪቱ መልካም ወይም መጥፎ መሆኗን ከተሞቹም በግንብ የታጠሩ ወይም ያልታጠሩ መሆናቸውን ተመልከቱ። 20 ምድሪቱም ለም* ወይም ደረቅ* መሆኗን፣+ በዚያም ዛፎች መኖር አለመኖራቸውን አጣሩ። እንዲሁም በድፍረት+ ከምድሪቱ ፍሬ ጥቂት ይዛችሁ ኑ።” ደግሞም ጊዜው የመጀመሪያው የወይን ፍሬ የሚደርስበት ወቅት ነበር።+

21 ስለዚህ ሰዎቹ ወጥተው ምድሪቱን ከጺን ምድረ በዳ+ አንስተው በሌቦሃማት*+ አቅራቢያ እስከምትገኘው እስከ ሬሆብ+ ድረስ ሰለሉ። 22 በኔጌብ በኩል ሽቅብ ሲወጡም ኤናቃውያኑ+ አሂማን፣ ሸሻይ እና ታልማይ+ ወደሚኖሩበት ወደ ኬብሮን+ ደረሱ። ኬብሮን የተቆረቆረችው በግብፅ ያለችው ጾዓን ከመቆርቆሯ ከሰባት ዓመት በፊት ነበር። 23 ወደ ኤሽኮል ሸለቆ*+ በደረሱ ጊዜ የወይን ዘለላዎችን ያንዠረገገ አንድ ቅርንጫፍ ከዚያ ቆረጡ፤ ከሰዎቹም መካከል ሁለቱ በዱላ ተሸከሙት፤ በተጨማሪም ጥቂት የሮማን ፍሬዎችንና የበለስ ፍሬዎችን ያዙ።+ 24 እስራኤላውያን ከዚያ በቆረጡት ዘለላ የተነሳ ያን ቦታ የኤሽኮል* ሸለቆ*+ ብለው ጠሩት።

25 ምድሪቱንም ሰልለው ከ40 ቀን+ በኋላ ተመለሱ። 26 በቃዴስ+ ባለው በፋራን ምድረ በዳ ወደሚገኙት ወደ ሙሴ፣ ወደ አሮንና ወደ መላው የእስራኤል ማኅበረሰብ ተመልሰው መጡ። ያዩትንም ሁሉ ለመላው ማኅበረሰብ ተናገሩ፤ የምድሪቱንም ፍሬ አሳዩአቸው። 27 ሙሴንም እንዲህ አሉት፦ “ወደላክኸን ምድር ገብተን ነበር፤ በእርግጥም ምድሪቱ ወተትና ማር የምታፈስ ናት፤+ የምድሪቱም ፍሬ+ ይህን ይመስላል። 28 ይሁንና በምድሪቱ የሚኖሩት ሰዎች ብርቱዎች ናቸው፤ በግንብ የታጠሩት ከተሞችም ቢሆኑ በጣም ታላላቅ ናቸው። ደግሞም ኤናቃውያንን በዚያ አይተናል።+ 29 አማሌቃውያን+ በኔጌብ+ ምድር ይኖራሉ፤ ሂታውያን፣ ኢያቡሳውያንና+ አሞራውያን+ ደግሞ በተራራማው አካባቢ ይኖራሉ፤ በባሕሩ አካባቢና+ በዮርዳኖስ ዳርቻ ደግሞ ከነአናውያን+ ይኖራሉ።”

30 ከዚያም ካሌብ “በድፍረት እንውጣ፤ ድል እንደምናደርግ ምንም ጥርጥር ስለሌለው ምድሪቱን እንወርሳለን” በማለት በሙሴ ፊት የቆመውን ሕዝብ ሊያረጋጋ ሞከረ።+ 31 ከእሱ ጋር የወጡት ሰዎች ግን “ሰዎቹ ከእኛ ይልቅ ብርቱዎች ስለሆኑ ወጥተን ልንዋጋቸው አንችልም” አሉ።+ 32 እንዲሁም የሰለሏትን ምድር በተመለከተ ለእስራኤላውያን እንዲህ የሚል መጥፎ ወሬ+ አወሩ፦ “በውስጧ ተዘዋውረን የሰለልናት ምድር ነዋሪዎቿን የምትበላ ምድር ናት፤ እዚያ ያየናቸውም ሰዎች በሙሉ እጅግ ግዙፎች ናቸው።+ 33 በዚያም ኔፍሊምን ይኸውም የኔፍሊም ዝርያ የሆኑትን የኤናቅን ልጆች+ አይተናል፤ እኛ ከእነሱ ጋር ስንነጻጸር በእኛም ሆነ በእነሱ ዓይን ልክ እንደ ፌንጣ ነበርን።”

14 ከዚያም ማኅበረሰቡ ሁሉ ድምፁን ከፍ አድርጎ ጮኸ፤ ሕዝቡም ሌሊቱን ሙሉ ሲጮኽና ሲያለቅስ አደረ።+ 2 እስራኤላውያንም በሙሉ በሙሴና በአሮን ላይ ያጉረመርሙ ጀመር፤+ መላው ማኅበረሰብ እንዲህ አላቸው፦ “ምነው በግብፅ ምድር ሳለን ሞተን ባረፍነው፤ ወይም ምናለ በዚህ ምድረ በዳ በሞትን! 3 ይሖዋ በሰይፍ እንድንሞት ወደዚህ ምድር ያመጣን ለምንድን ነው?+ እንግዲህ ሚስቶቻችንና ልጆቻችን ይማረካሉ።+ ታዲያ ወደ ግብፅ ብንመለስ አይሻለንም?”+ 4 እንዲያውም እርስ በርሳቸው “መሪ እንሹምና ወደ ግብፅ እንመለስ” ይባባሉ ጀመር።+

5 በዚህ ጊዜ ሙሴና አሮን በተሰበሰበው በመላው የእስራኤል ጉባኤ ፊት በግንባራቸው መሬት ላይ ተደፉ። 6 ምድሩን ከሰለሉት ሰዎች መካከል የነበሩት የነዌ ልጅ ኢያሱና+ የየፎኒ ልጅ ካሌብ+ ልብሳቸውን ቀደዱ፤ 7 ለመላው የእስራኤል ማኅበረሰብም እንዲህ አሉ፦ “ተዘዋውረን የሰለልናት ምድር እጅግ በጣም ጥሩ ምድር ናት።+ 8 ይሖዋ በእኛ ከተደሰተ ወተትና ማር ወደምታፈሰው ወደዚህች ምድር+ በእርግጥ ያስገባናል፤ ደግሞም ይህችን ምድር ይሰጠናል። 9 ብቻ እናንተ በይሖዋ ላይ አታምፁ፤ እንደ እንጀራ ስለምንጎርሳቸው የምድሪቱን ሕዝቦች አትፍሯቸው።+ ጥላቸው ተገፏል፤ ደግሞም ይሖዋ ከእኛ ጋር ነው።+ ፈጽሞ አትፍሯቸው።”

10 ይሁን እንጂ መላው ማኅበረሰብ በድንጋይ ሊወግራቸው ተማከረ።+ ሆኖም የይሖዋ ክብር በመገናኛ ድንኳኑ ላይ ለመላው የእስራኤል ሕዝብ ተገለጠ።+

11 ከዚያም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ይህ ሕዝብ የሚንቀኝ እስከ መቼ ነው?+ በመካከላቸው ይህን ሁሉ ተአምራዊ ምልክት እያሳየሁ የማያምኑብኝስ እስከ መቼ ነው?+ 12 እንግዲህ በቸነፈር እመታቸዋለሁ፤ ደግሞም እደመስሳቸዋለሁ፤ አንተን ግን ከእነሱ ይልቅ ታላቅና ኃያል ብሔር አደርግሃለሁ።”+

13 ሙሴ ግን ይሖዋን እንዲህ አለው፦ “እንዲህ ካደረግክ ይህን ሕዝብ በኃይልህ ከመካከላቸው ስታወጣ ያዩ ግብፃውያን መስማታቸው አይቀርም፤+ 14 እነሱ ደግሞ የሰሙትን ነገር ለዚህ ምድር ነዋሪዎች ይናገራሉ። እነሱም ቢሆኑ አንተ ይሖዋ በዚህ ሕዝብ መካከል እንዳለህና+ ፊት ለፊት+ እንደተገለጥክላቸው ሰምተዋል። አንተ ይሖዋ ነህ፤ ደመናህም በላያቸው ላይ ቆሟል፤ ቀን ቀን በደመና ዓምድ፣ ሌሊት ሌሊት ደግሞ በእሳት ዓምድ ከፊት ከፊታቸው ትሄዳለህ።+ 15 እንግዲህ ይህን ሕዝብ በሙሉ በአንዴ ብትፈጀው* የአንተን ዝና የሰሙ ብሔራት እንዲህ ማለታቸው አይቀርም፦ 16 ‘ይሖዋ ይህን ሕዝብ፣ ሊሰጠው ወደማለለት ምድር ሊያስገባው ስላልቻለ በምድረ በዳ ፈጀው።’+ 17 አሁንም እባክህ ይሖዋ እንዲህ በማለት ቃል በገባኸው መሠረት ኃይልህ ታላቅ ይሁን፦ 18 ‘ይሖዋ ለቁጣ የዘገየ፣ ታማኝ ፍቅሩ* የበዛ፣+ ስህተትንና መተላለፍን ይቅር የሚል፣ በደለኛውን ግን በምንም ዓይነት ሳይቀጣ የማያልፍ እንዲሁም አባቶች ለሠሩት ስህተት በልጆች፣ በሦስተኛና በአራተኛ ትውልድ ላይ ቅጣትን የሚያመጣ ነው።’+ 19 ይህን ሕዝብ ከግብፅ አንስቶ እስካሁን ድረስ ይቅር ስትለው እንደቆየህ ሁሉ አሁንም እባክህ፣ የዚህን ሕዝብ ስህተት ታላቅ በሆነው ታማኝ ፍቅርህ ይቅር በል።”+

20 ከዚያም ይሖዋ እንዲህ አለ፦ “ባልከኝ መሠረት ይቅር እላቸዋለሁ።+ 21 በሌላ በኩል ግን በሕያውነቴ እምላለሁ፣ መላዋ ምድር በይሖዋ ክብር ትሞላለች።+ 22 ይሁን እንጂ ክብሬንና በግብፅም ሆነ በምድረ በዳ የፈጸምኳቸውን ተአምራዊ ምልክቶች+ የተመለከቱት ሆኖም አሥር ጊዜ የተፈታተኑኝና+ ቃሌን ያልሰሙት+ ሰዎች አንዳቸውም ቢሆኑ 23 ለአባቶቻቸው የማልኩላቸውን ምድር ፈጽሞ አያዩም። አዎ፣ የናቁኝ ሰዎች አንዳቸውም ቢሆኑ ያን ምድር አያዩም።+ 24 አገልጋዬ ካሌብ+ ግን የተለየ መንፈስ እንዳለው ስላሳየና በሙሉ ልቡ ስለተከተለኝ ሄዶባት ወደነበረው ምድር በእርግጥ አስገባዋለሁ፤ ዘሮቹም ያቺን ምድር ይወርሳሉ።+ 25 አማሌቃውያንና ከነአናውያን+ በሸለቆው ውስጥ* ስለሚኖሩ በነገው ዕለት ተመልሳችሁ በቀይ ባሕር መንገድ ወደ ምድረ በዳው ሂዱ።”+

26 ከዚያም ይሖዋ ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፦ 27 “ይህ ክፉ ማኅበረሰብ በእኔ ላይ እንዲህ የሚያጉረመርመው እስከ መቼ ነው?+ እስራኤላውያን በእኔ ላይ የሚያጉረመርሙትን ሰምቻለሁ።+ 28 እንዲህ በሏቸው፦ ‘“በሕያውነቴ እምላለሁ” ይላል ይሖዋ፤ “እናንተው ራሳችሁ ስትናገሩ የሰማሁትን ነገር አደርግባችኋለሁ!+ 29 ሃያ ዓመትና ከዚያ በላይ ሆኗችሁ የተመዘገባችሁትና የተቆጠራችሁት ሁሉ አዎ፣ በእኔ ላይ ያጉረመረማችሁት+ ሁሉ ሬሳችሁ በዚህ ምድረ በዳ ይወድቃል።+ 30 ከየፎኒ ልጅ ከካሌብና ከነዌ ልጅ ከኢያሱ በስተቀር+ አንዳችሁም ብትሆኑ በዚያ እንደማኖራችሁ ወደማልኩላችሁ* ምድር አትገቡም።+

31 “‘“ለምርኮ ይዳረጋሉ ያላችኋቸውን ልጆቻችሁን+ ግን አስገባቸዋለሁ፤ እናንተ የናቃችኋትንም ምድር+ በሚገባ ያውቋታል። 32 የእናንተ ሬሳ ግን በዚህ ምድረ በዳ ይወድቃል። 33 እንግዲህ ልጆቻችሁ በምድረ በዳ ለ40 ዓመት እረኞች ይሆናሉ፤+ እነሱም የእናንተ የመጨረሻው ሬሳ በምድረ በዳ እስኪወድቅ ድረስ+ እናንተ ለፈጸማችሁት ታማኝነት የጎደለው ድርጊት* መልስ ይሰጣሉ። 34 እኔን መቃወም* ምን ማለት እንደሆነ እንድታውቁ ምድሪቱን በሰለላችሁባቸው 40 ቀናት+ ልክ ይኸውም አንዱ ቀን እንደ አንድ ዓመት ተቆጥሮ፣ ለሠራችኋቸው ስህተቶች ለ40 ዓመት+ መልስ ትሰጣላችሁ።

35 “‘“እኔ ይሖዋ ተናግሬአለሁ። በእኔ ላይ ተባብሮ በተነሳው በዚህ ክፉ ማኅበረሰብ ላይ በእርግጥ ይህን አደርጋለሁ፦ መጨረሻቸው በዚህ ምድረ በዳ ይሆናል፤ እዚሁም ይሞታሉ።+ 36 ምድሪቱን እንዲሰልሉ ሙሴ የላካቸውና ስለ ምድሪቱ መጥፎ ወሬ ይዘው በመምጣት መላው ማኅበረሰብ በእሱ ላይ እንዲያጉረመርም ያደረጉት ሰዎች+ 37 አዎ፣ ስለ ምድሪቱ መጥፎ ወሬ ይዘው የመጡት ሰዎች በይሖዋ ፊት ተቀስፈው ይሞታሉ።+ 38 ምድሪቱን ለመሰለል ከሄዱት ሰዎች መካከል የነበሩት የነዌ ልጅ ኢያሱና የየፎኒ ልጅ ካሌብ ግን በሕይወት ይኖራሉ።”’”+

39 ሙሴም ለእስራኤላውያን በሙሉ ይህን ሲነግራቸው ሕዝቡ እጅግ አዘነ። 40 ከዚያም በጠዋት ወደ ተራራው አናት ለመውጣት ተነሱ፤ እነሱም “ኃጢአት ስለሠራን ይሖዋ ወደተናገረለት ቦታ ለመውጣት ይኸው ዝግጁ ነን” አሉ።+ 41 ሙሴ ግን እንዲህ አለ፦ “የይሖዋን ትእዛዝ የምትጥሱት ለምንድን ነው? ይህ አይሳካላችሁም። 42 ይሖዋ ከእናንተ ጋር ስላልሆነ አትውጡ፤ በጠላቶቻችሁ ድል ትመታላችሁ።+ 43 ምክንያቱም አማሌቃውያንና ከነአናውያን በዚያ ይገጥሟችኋል፤+ እናንተም በሰይፍ ትወድቃላችሁ። ምክንያቱም ይሖዋን ከመከተል ዞር ስላላችሁ ይሖዋ ከእናንተ ጋር አይሆንም።”+

44 እነሱ ግን በትዕቢት ወደ ተራራው አናት ወጡ፤+ ሆኖም የይሖዋ የቃል ኪዳን ታቦትና ሙሴ ከሰፈሩ መካከል ንቅንቅ አላሉም።+ 45 ከዚያም በዚያ ተራራ የሚኖሩት አማሌቃውያንና ከነአናውያን ወርደው መቷቸው፤ እስከ ሆርማም ድረስ በታተኗቸው።+

15 በተጨማሪም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ 2 “እስራኤላውያንን እንዲህ በላቸው፦ ‘እንድትኖሩባት ወደምሰጣችሁ ምድር በምትገቡበትና+ 3 ይሖዋን ደስ የሚያሰኝ* መዓዛ+ እንዲሆን የሚቃጠል መባም+ ሆነ ለየት ያለ ስእለት ለመሳል የሚቀርብ መሥዋዕት ወይም የፈቃደኝነት መባ+ አሊያም በየወቅቱ በምታከብሯቸው በዓላት+ ላይ የሚቀርብ መባ፣ ከከብታችሁ ወይም ከመንጋችሁ በመውሰድ ለይሖዋ በእሳት የሚቃጠል መባ በምታቀርቡበት ጊዜ 4 መባውን የሚያቀርበው ሰው በአንድ አራተኛ ሂን* ዘይት የተለወሰ አንድ አሥረኛ ኢፍ* የላመ ዱቄትም+ የእህል መባ አድርጎ ለይሖዋ ማቅረብ ይኖርበታል። 5 እንዲሁም ከሚቃጠለው መባ ወይም ከተባዕት የበግ ጠቦት መሥዋዕቱ ጋር አንድ አራተኛ ሂን የወይን ጠጅ የመጠጥ መባ አድርገህ ማቅረብ አለብህ።+ 6 ወይም ከአውራ በግ ጋር በአንድ ሦስተኛ ሂን ዘይት የተለወሰ ሁለት አሥረኛ የኢፍ መስፈሪያ የላመ ዱቄት የእህል መባ አድርገህ አቅርብ። 7 እንዲሁም አንድ ሦስተኛ ሂን የወይን ጠጅ ይሖዋን ደስ የሚያሰኝ* መዓዛ ያለው የመጠጥ መባ አድርገህ ማቅረብ አለብህ።

8 “‘ሆኖም ከመንጋው መካከል አንድ ወይፈን የሚቃጠል መባ+ ወይም ለየት ያለ ስእለት+ ለመሳል የሚቀርብ መሥዋዕት አሊያም የኅብረት መሥዋዕት አድርገህ ለይሖዋ የምታቀርብ+ ከሆነ 9 ከወይፈኑ ጋር በግማሽ ሂን ዘይት የተለወሰ ሦስት አሥረኛ የኢፍ መስፈሪያ የላመ ዱቄት የእህል መባ+ አድርገህ ማቅረብ ይኖርብሃል። 10 እንዲሁም ይሖዋን ደስ የሚያሰኝ* መዓዛ ያለው የመጠጥ መባ+ እንዲሆን ግማሽ ሂን የወይን ጠጅ በእሳት የሚቃጠል መባ አድርገህ ማቅረብ አለብህ። 11 ለእያንዳንዱ በሬ ወይም ለእያንዳንዱ አውራ በግ ወይም ለእያንዳንዱ ተባዕት የበግ ጠቦት ወይም ለእያንዳንዱ ፍየል እንዲሁ መደረግ አለበት። 12 የምታቀርቡት ብዛቱ ምንም ያህል ይሁን ምን ለእያንዳንዱ እንደየብዛቱ እንዲህ ማድረግ ይኖርባችኋል። 13 የአገሩ ተወላጅ የሆነ እያንዳንዱ እስራኤላዊ ይሖዋን ደስ የሚያሰኝ* መዓዛ ያለው በእሳት የሚቃጠል መባ የሚያቀርበው በዚህ መንገድ ነው።

14 “‘ከእናንተ ጋር እየኖረ ያለ ወይም ለብዙ ትውልድ በመካከላችሁ ሲኖር የነበረ የባዕድ አገር ሰው ይሖዋን ደስ የሚያሰኝ* መዓዛ ያለው በእሳት የሚቃጠል መባ ቢያቀርብ ልክ እናንተ እንደምታደርጉት ያድርግ።+ 15 የጉባኤው ክፍል የሆናችሁት እናንተም ሆናችሁ አብሯችሁ የሚኖር የባዕድ አገር ሰው አንድ ዓይነት ደንብ ይኖራችኋል። ይህም በትውልዶቻችሁ ሁሉ ዘላቂ ደንብ ይሆናል። የባዕድ አገሩ ሰው በይሖዋ ፊት ልክ እንደ እናንተ ይታያል።+ 16 ለእናንተም ሆነ ከእናንተ ጋር ለሚኖር የባዕድ አገር ሰው አንድ ዓይነት ሕግና አንድ ዓይነት ድንጋጌ ይኑር።’”

17 ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ 18 “እስራኤላውያንን አናግራቸው፤ እንዲህም በላቸው፦ ‘ወደማመጣችሁ ምድር በምትገቡበትና 19 ከምድሪቱ ማንኛውንም ምግብ በምትበሉበት+ ጊዜ ለይሖዋ መዋጮ ማድረግ አለባችሁ። 20 ከተፈጨው የእህላችሁ በኩር+ ላይ የቀለበት ቅርጽ ያለው ዳቦ በማዘጋጀት መዋጮ ማድረግ ይኖርባችኋል። ይህን ማዋጣት የሚኖርባችሁ ከአውድማ ላይ የሚገኘውን መዋጮ በምታዋጡበት መንገድ ነው። 21 በትውልዶቻችሁ ሁሉ፣ ከተፈጨው የእህላችሁ በኩር ላይ የተወሰነውን ለይሖዋ መዋጮ አድርጋችሁ መስጠት ይኖርባችኋል።

22 “‘ምናልባት ስህተት ብትሠሩና ይሖዋ ለሙሴ የተናገራቸውን እነዚህን ትእዛዛት ሁሉ ሳትፈጽሙ ብትቀሩ 23 ይኸውም ይሖዋ ትእዛዙን ከሰጠበት ዕለት አንስቶ ሥራ ላይ የዋለውንና በትውልዶቻችሁ ሁሉ ጸንቶ የሚኖረውን ይሖዋ በሙሴ በኩል ያስተላለፈላችሁን ትእዛዝ ሁሉ ባትፈጽሙና 24 ይህን ያደረጋችሁት ደግሞ በስህተትና ማኅበረሰቡ ሳያውቅ ቢሆን መላው ማኅበረሰብ አንድ ወይፈን ይሖዋን ደስ የሚያሰኝ* መዓዛ ያለው የሚቃጠል መባ አድርጎ ያቅርብ፤ ከእሱም ጋር በተለመደው አሠራር መሠረት+ የእህል መባውንና የመጠጥ መባውን እንዲሁም አንድ የፍየል ጠቦት የኃጢአት መባ አድርጎ ያቅርብ።+ 25 ካህኑም ለመላው የእስራኤል ማኅበረሰብ ያስተሰርያል፤ ኃጢአቱም ባለማወቅ የተፈጸመ ስለሆነና ለሠሩትም ስህተት መባቸውን ለይሖዋ በእሳት የሚቃጠል መባ አድርገው ስላቀረቡ እንዲሁም በይሖዋ ፊት የኃጢአት መባቸውን ስላቀረቡ ይቅር ይባልላቸዋል።+ 26 ይህም ሕዝቡ ሁሉ ባለማወቅ የፈጸመው ስለሆነ መላው የእስራኤል ማኅበረሰብም ሆነ በመካከላቸው የሚኖር የባዕድ አገር ሰው ይቅር ይባላል።

27 “‘ማንኛውም ሰው* ባለማወቅ ኃጢአት ቢሠራ አንድ ዓመት ገደማ የሆናት አንዲት ፍየል የኃጢአት መባ አድርጎ ያቅርብ።+ 28 ከዚያም ባለማወቅ በይሖዋ ፊት ኃጢአት በመሥራት የተሳሳተው ሰው* ኃጢአቱ ይሰረይለት ዘንድ ካህኑ ማስተሰረያ ያቀርብለታል፤ ኃጢአቱም ይቅር ይባልለታል።+ 29 ባለማወቅ ከሚፈጸም ነገር ጋር በተያያዘ በእስራኤላውያን መካከል ለሚገኝ የአገሬው ተወላጅም ሆነ በመካከላቸው ለሚኖር የባዕድ አገር ሰው አንድ ዓይነት ሕግ ይኑራችሁ።+

30 “‘ይሁን እንጂ ሆን ብሎ ኃጢአት የሚሠራ ሰው*+ የአገሬው ተወላጅም ይሁን የባዕድ አገር ሰው ይሖዋን እንደተሳደበ ስለሚቆጠር ከሕዝቡ ተለይቶ እንዲጠፋ መደረግ አለበት። 31 የይሖዋን ቃል ስላቃለለና የእሱን ትእዛዝ ስለጣሰ ያ ሰው* ያለምንም ጥርጥር ተለይቶ እንዲጠፋ መደረግ አለበት።+ ጥፋቱ የራሱ ነው።’”+

32 እስራኤላውያን በምድረ በዳ ሳሉ አንድ ሰው በሰንበት ቀን እንጨት ሲለቅም አገኙ።+ 33 ሰዎቹም እንጨት ሲለቅም ያገኙትን ሰው ወደ ሙሴ፣ ወደ አሮንና ወደ መላው ማኅበረሰብ አመጡት። 34 ሰውየው ምን መደረግ እንዳለበት በግልጽ የተቀመጠ ነገር ስላልነበረ በጥበቃ ሥር እንዲቆይ አደረጉ።+

35 ይሖዋም ሙሴን “ሰውየው ያለምንም ጥርጥር መገደል አለበት፤+ መላው ማኅበረሰብም ከሰፈሩ ውጭ በድንጋይ ይውገረው”+ አለው። 36 ስለዚህ ይሖዋ ሙሴን ባዘዘው መሠረት መላው ማኅበረሰብ ሰውየውን ከሰፈሩ ውጭ አውጥቶ እስኪሞት ድረስ በድንጋይ ወገረው።

37 ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ 38 “እስራኤላውያን በትውልዶቻቸው ሁሉ በልብሳቸው ጫፍ ላይ ዘርፍ እንዲያደርጉ ንገራቸው፤ ልብሳቸውም ከዘርፉ በላይ ሰማያዊ ጥለት ይኑረው።+ 39 ‘ይህን ዘርፍ በልብሳችሁ ላይ አድርጉ፤ ምክንያቱም እሱን ስታዩ የይሖዋን ትእዛዛት ሁሉ ታስታውሳላችሁ፤ እንዲሁም ትፈጽማላችሁ።+ ወደ መንፈሳዊ ምንዝር የሚመራችሁን የገዛ ልባችሁንና ዓይናችሁን አትከተሉ።+ 40 ይህን መመሪያ የሰጠኋችሁ ትእዛዛቴን በሙሉ እንድታስታውሱና እንድትፈጽሙ ነው፤ ለአምላካችሁም የተቀደሳችሁ ትሆናላችሁ።+ 41 አምላካችሁ መሆኔን ለማስመሥከር ከግብፅ ምድር ያወጣኋችሁ እኔ አምላካችሁ ይሖዋ ነኝ።+ አዎ፣ እኔ አምላካችሁ ይሖዋ ነኝ።’”+

16 ከዚያም የሌዊ+ ልጅ፣ የቀአት+ ልጅ፣ የይጽሃር+ ልጅ ቆሬ+ ከሮቤል ልጆች አንዱ ከሆነው ከኤልያብ+ ልጆች ከዳታንና ከአቤሮን እንዲሁም ከሮቤል+ ልጆች አንዱ ከሆነው ከፐሌት ልጅ ከኦን ጋር በመሆን ተነሳ። 2 እነሱም ከማኅበረሰቡ አለቆች ይኸውም ከጉባኤው መካከል ከተመረጡት ታዋቂ የሆኑ 250 እስራኤላውያን ወንዶች ጋር በማበር በሙሴ ላይ ተነሱ። 3 እነሱም ሙሴንና አሮንን ለመቃወም+ ተሰብስበው መጡ፤ እንዲህም አሏቸው፦ “ምነው፣ አላበዛችሁትም እንዴ! መላው ማኅበረሰብ እኮ ቅዱስ ነው፤+ ሁሉም ቅዱስ ናቸው፤ ይሖዋም በመካከላቸው ነው።+ ታዲያ በይሖዋ ጉባኤ ላይ ራሳችሁን ከፍ ከፍ የምታደርጉት ለምንድን ነው?”

4 ሙሴ ይህን ሲሰማ ወዲያውኑ በግንባሩ ተደፋ። 5 ከዚያም ቆሬንና ግብረ አበሮቹን ሁሉ እንዲህ አላቸው፦ “ጠዋት ላይ ይሖዋ የእሱ የሆነውን፣+ ቅዱስ የሆነውንና ወደ እሱ መቅረብ የሚችለውን+ ሰው ያሳውቃል፤ እሱ የመረጠውም+ ሰው ወደ እሱ ይቀርባል። 6 ስለዚህ እንዲህ አድርጉ፦ ቆሬ፣ አንተም ሆንክ ግብረ አበሮችህ+ በሙሉ የዕጣን ማጨሻዎች+ ውሰዱ፤ 7 ከዚያም በነገው ዕለት እሳት ካደረጋችሁባቸው በኋላ በይሖዋ ፊት ዕጣን ጨምሩባቸው፤ ይሖዋ የሚመርጠውም ሰው፣+ እሱ ቅዱስ ይሆናል። እናንተ የሌዊ ልጆች፣+ በጣም አብዝታችሁታል!”

8 ከዚያም ሙሴ ቆሬን እንዲህ አለው፦ “እናንተ የሌዊ ልጆች፣ እባካችሁ አዳምጡ። 9 የእስራኤል አምላክ እናንተን ከእስራኤል ማኅበረሰብ+ መለየቱ እንዲሁም በይሖዋ የማደሪያ ድንኳን የሚከናወነውን አገልግሎት ትፈጽሙና በማኅበረሰቡ ፊት ቆማችሁ እነሱን ታገለግሉ ዘንድ ወደ እሱ እንድትቀርቡ መፍቀዱ እንደ ቀላል ነገር የሚታይ ነው?+ 10 ደግሞስ አንተንና የሌዊ ልጆች የሆኑትን ወንድሞችህን በሙሉ ወደ እሱ እንድትቀርቡ ማድረጉ ቀላል ነገር ነው? ታዲያ የክህነት አገልግሎቱንም ለመጠቅለል መሞከር ይገባችኋል?+ 11 ስለዚህ አንተም ሆንክ አብረውህ የተሰበሰቡት ግብረ አበሮችህ በሙሉ ይሖዋን እየተቃወማችሁ ነው። በአሮን ላይ የምታጉረመርሙት እሱ ምን ስለሆነ ነው?”+

12 ከዚያም ሙሴ የኤልያብን ልጆች ዳታንንና አቤሮንን+ አስጠራቸው፤ እነሱ ግን እንዲህ አሉ፦ “አንመጣም! 13 በምድረ በዳ ልትገድለን ወተትና ማር ከምታፈሰው ምድር ያወጣኸን አይበቃህም?+ አሁን ደግሞ በእኛ ላይ ፈላጭ ቆራጭ* ልትሆን ያምርሃል? 14 ደግሞም ወተትና ማር ወደምታፈስ ምድር+ አላስገባኸንም፤ ወይም እርሻና የወይን የአትክልት ቦታዎችን ርስት አድርገህ አልሰጠኸንም። ታዲያ የእነዚያን ሰዎች ዓይን ልታወጣ ነው? እኛ እንደሆነ አንመጣም!”

15 ስለዚህ ሙሴ እጅግ ተቆጣ፤ ይሖዋንም እንዲህ አለው፦ “የእህል መባቸውን አትመልከት። ከእነዚህ ሰዎች አንድ አህያ እንኳ አልወሰድኩም፤ አንዳቸውንም ቢሆን አልበደልኩም።”+

16 ከዚያም ሙሴ ቆሬን እንዲህ አለው፦ “አንተና ግብረ አበሮችህ በሙሉ ነገ በይሖዋ ፊት ቅረቡ፤ አንተም ሆንክ እነሱ እንዲሁም አሮን መቅረብ ይኖርባችኋል። 17 እያንዳንዱ ሰው የየራሱን የዕጣን ማጨሻ ይያዝ፤ በላዩም ላይ ዕጣን ያድርግበት፤ አንተንና አሮንን ጨምሮ እያንዳንዱ ሰው በይሖዋ ፊት የዕጣን ማጨሻውን ያቀርባል፤ ይህም በአጠቃላይ 250 የዕጣን ማጨሻዎች ማለት ነው፤ እያንዳንዱም የየራሱን የዕጣን ማጨሻ ይዞ ይቀርባል።” 18 ስለዚህ እያንዳንዳቸው የዕጣን ማጨሻቸውን ይዘው መጡ፤ በላዩም ላይ እሳትና ዕጣን አደረጉበት፤ ከዚያም ከሙሴና ከአሮን ጋር በመገናኛ ድንኳኑ መግቢያ ላይ ቆሙ። 19 ቆሬ፣ ግብረ አበሮቹ+ በመገናኛ ድንኳኑ መግቢያ ላይ ሙሴንና አሮንን በመቃወም እንዲሰበሰቡ ባደረገ ጊዜ የይሖዋ ክብር ለመላው ማኅበረሰብ ተገለጠ።+

20 በዚህ ጊዜ ይሖዋ ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፦ 21 “በአንዴ ጠራርጌ እንዳጠፋቸው ራሳችሁን ከዚህ ቡድን ለዩ።”+ 22 እነሱም በግንባራቸው መሬት ላይ ተደፍተው እንዲህ አሉ፦ “አምላክ ሆይ፣ አንተ የሰው ሁሉ መንፈስ* አምላክ ነህ፤+ ታዲያ አንድ ሰው በሠራው ኃጢአት የተነሳ በመላው ማኅበረሰብ ላይ ትቆጣለህ?”+

23 ከዚያም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ 24 “ለማኅበረሰቡ ‘ከቆሬ፣ ከዳታንና ከአቤሮን+ ድንኳኖች አካባቢ ራቁ!’ ብለህ ንገራቸው።”

25 ሙሴም ተነስቶ ወደ ዳታንና አቤሮን ሄደ፤ የእስራኤል ሽማግሌዎችም+ አብረውት ሄዱ። 26 ከዚያም ማኅበረሰቡን እንዲህ አላቸው፦ “በኃጢአታቸው ተጠራርጋችሁ እንዳትጠፉ እባካችሁ፣ ከእነዚህ ክፉ ሰዎች ድንኳኖች ራቁ፤ የእነሱ የሆነውን ማንኛውንም ነገር አትንኩ።” 27 እነሱም ወዲያውኑ ከቆሬ፣ ከዳታንና ከአቤሮን ድንኳኖች፣ ከዙሪያቸውም ሁሉ ራቁ፤ ዳታንና አቤሮንም ወጥተው ከሚስቶቻቸው፣ ከልጆቻቸውና ከሕፃኖቻቸው ጋር በድንኳኖቻቸው ደጃፍ ላይ ቆሙ።

28 ሙሴም እንዲህ አለ፦ “እነዚህን ነገሮች ሁሉ የማደርገው ከልቤ አመንጭቼ ሳይሆን* ይሖዋ ልኮኝ መሆኑን በዚህ ታውቃላችሁ፦ 29 እነዚህ ሰዎች እንደ ማንኛውም ሰው አሟሟት የሚሞቱ ከሆነና የሚደርስባቸውም ቅጣት በሌሎች ሰዎች ሁሉ ላይ የሚደርስ ዓይነት ከሆነ እኔን ይሖዋ አላከኝም ማለት ነው።+ 30 ሆኖም ይሖዋ በእነሱ ላይ እንግዳ የሆነ ነገር ቢያደርግና መሬት አፏን ከፍታ እነሱንም ሆነ የእነሱ የሆነውን ነገር ሁሉ ብትውጥ፣ በሕይወት እንዳሉም ወደ መቃብር* ቢወርዱ፣ እነዚህ ሰዎች ይሖዋን እንደናቁ በእርግጥ ታውቃላችሁ።”

31 እሱም ይህን ተናግሮ እንደጨረሰ፣ የቆሙባት ምድር ተሰነጠቀች።+ 32 ምድሪቱም አፏን ከፍታ እነሱን፣ ቤተሰቦቻቸውን፣ የቆሬ የሆነውን ማንኛውንም ሰውና+ ንብረታቸውን ሁሉ ዋጠች። 33 በዚህ መንገድ እነሱም ሆኑ የእነሱ የሆኑት ሁሉ በሕይወት እንዳሉ ወደ መቃብር* ወረዱ፤ ምድርም ተከደነችባቸው፤ ስለዚህ ከጉባኤው መካከል ጠፉ።+ 34 በዙሪያቸው የነበሩት እስራኤላውያን በሙሉ ጩኸታቸውን ሲሰሙ “ኧረ ምድሪቱ እኛንም እንዳትውጠን!” በማለት መሸሽ ጀመሩ። 35 ከዚያም ከይሖዋ ዘንድ እሳት መጥቶ+ ዕጣን ሲያጥኑ የነበሩትን 250 ሰዎች በላ።+

36 በዚህ ጊዜ ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ 37 “የዕጣን ማጨሻዎቹ+ ቅዱስ ስለሆኑ የካህኑ የአሮን ልጅ አልዓዛር ከእሳቱ ውስጥ እንዲያወጣቸው ንገረው። በተጨማሪም እሳቱን ራቅ አድርጎ እንዲበትነው ንገረው። 38 ኃጢአት በመሥራታቸው የተነሳ ሕይወታቸውን የከፈሉት* ሰዎች ይዘዋቸው የነበሩት የዕጣን ማጨሻዎች ቅዱስ ስለሆኑ ለመሠዊያው መለበጫ+ እንዲያገለግሉ በስሱ ይጠፍጠፉ፤ ምክንያቱም በይሖዋ ፊት ስላቀረቧቸው ቅዱስ ሆነዋል። ለእስራኤላውያንም ምልክት ሆነው ያገልግሉ።”+ 39 ስለሆነም ካህኑ አልዓዛር በእሳት የተቃጠሉት ሰዎች ያቀረቧቸውን የመዳብ የዕጣን ማጨሻዎች ወሰደ፤ ከዚያም መሠዊያውን ለመለበጥ በስሱ ጠፈጠፋቸው፤ 40 ይህን ያደረገውም ይሖዋ በሙሴ በኩል ለእሱ በነገረው መሠረት ነው። ይህም የአሮን ዘር ያልሆነ ማንኛውም ያልተፈቀደለት ሰው* በይሖዋ ፊት ዕጣን ለማጨስ እንዳይቀርብ+ እንዲሁም ማንም ሰው እንደ ቆሬና እንደ ግብረ አበሮቹ እንዳይሆን ለእስራኤላውያን ማሳሰቢያ እንዲሆን ነው።+

41 በማግስቱም መላው የእስራኤል ማኅበረሰብ “እናንተ ሰዎች የይሖዋን ሕዝብ ገድላችኋል” በማለት በሙሴና በአሮን ላይ ያጉረመርም ጀመር።+ 42 የእስራኤልም ማኅበረሰብ ሙሴንና አሮንን በመቃወም በተሰበሰበ ጊዜ ወደ መገናኛ ድንኳኑ ዞር ብሎ ሲመለከት፣ የመገናኛ ድንኳኑን ደመና ሸፍኖት አየ፤ የይሖዋም ክብር ተገለጠ።+

43 ሙሴና አሮንም ወደ መገናኛ ድንኳኑ ፊት መጡ፤+ 44 ይሖዋም ሙሴን እንዲህ አለው፦ 45 “በአንዴ እንዳጠፋቸው+ ራሳችሁን ከዚህ ማኅበረሰብ ለዩ።” እነሱም በዚህ ጊዜ በግንባራቸው መሬት ላይ ተደፉ።+ 46 ከዚያም ሙሴ አሮንን እንዲህ አለው፦ “የዕጣን ማጨሻ ውሰድና ከመሠዊያው ላይ እሳት አድርግበት፤+ በላዩም ላይ ዕጣን ጨምርበት፤ ፈጥነህም ወደ ማኅበረሰቡ በመሄድ አስተሰርይላቸው፤+ ምክንያቱም ይሖዋ ተቆጥቷል። መቅሰፍቱ ጀምሯል!” 47 አሮን ልክ ሙሴ እንዳለው ወዲያውኑ የዕጣን ማጨሻውን ይዞ ወደ ጉባኤው መካከል እየሮጠ ገባ፤ መቅሰፍቱ በሕዝቡ መካከል ጀምሮ ነበር። በመሆኑም ዕጣኑን በዕጣን ማጨሻው ላይ በማድረግ ለሕዝቡ ማስተሰረይ ጀመረ። 48 እሱም በሞቱትና በሕይወት ባሉት መካከል ቆመ፤ መቅሰፍቱም ቀስ በቀስ ቆመ። 49 በቆሬ ምክንያት የሞቱትን ሳይጨምር በመቅሰፍቱ የሞቱት ሰዎች ብዛት 14,700 ነበር። 50 በመጨረሻም አሮን በመገናኛ ድንኳኑ መግቢያ ላይ ወደነበረው ወደ ሙሴ ሲመለስ መቅሰፍቱ ቆሞ ነበር።

17 ይሖዋም ሙሴን እንዲህ አለው፦ 2 “እስራኤላውያንን አናግራቸው፤ ለእያንዳንዱ የአባቶች ቤት ከእያንዳንዱ የአባቶች ቤት አለቃ+ ላይ አንድ አንድ በትር ይኸውም በአጠቃላይ 12 በትሮችን ከእነሱ ላይ ውሰድ። የእያንዳንዳቸውንም ስም በየበትራቸው ላይ ጻፍ። 3 ለእያንዳንዱ የአባቶች ቤት መሪ የሚኖረው አንድ በትር ስለሆነ የአሮንን ስም በሌዊ በትር ላይ ጻፍ። 4 በትሮቹን ራሴን ዘወትር ለእናንተ በምገልጥበት+ በመገናኛ ድንኳኑ ውስጥ በምሥክሩ+ ፊት ለፊት አስቀምጣቸው። 5 ከዚያም እኔ የምመርጠው+ ሰው በትር ያቆጠቁጣል፤ እኔም እስራኤላውያን በእናንተ ላይ በማጉረምረም+ በእኔ ላይ እያሰሙ ያሉት ማጉረምረም+ እንዲያበቃ አደርጋለሁ።”

6 በመሆኑም ሙሴ እስራኤላውያንን አነጋገራቸው፤ አለቆቻቸውም በሙሉ በትሮቹን ይኸውም ለእያንዳንዱ የአባቶች ቤት አለቃ አንድ በትር ማለትም 12 በትሮችን ሰጡት፤ የአሮንም በትር ከእነሱ በትሮች ጋር ነበር። 7 ከዚያም ሙሴ በትሮቹን በምሥክሩ ድንኳን ውስጥ በይሖዋ ፊት አስቀመጣቸው።

8 በማግስቱም ሙሴ ወደ ምሥክሩ ድንኳን ሲገባ የሌዊን ቤት የሚወክለውን የአሮንን በትር አቆጥቁጦ፣ እንቡጥ አውጥቶ፣ አበባ አብቦና የደረሰ የአልሞንድ ፍሬ አፍርቶ አገኘው። 9 ከዚያም ሙሴ በትሮቹን በሙሉ ከይሖዋ ፊት አውጥቶ ወደ እስራኤል ሕዝብ ሁሉ አመጣቸው። እነሱም በትሮቹን አዩ፤ እያንዳንዱም ሰው የራሱን በትር ወሰደ።

10 ከዚያም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ለዓመፀኞቹ ልጆች+ ምልክት ሆኖ እንዲያገለግል+ የአሮንን በትር+ መልሰህ ምሥክሩ ፊት አስቀምጠው፤ ይህም የሚሆነው በእኔ ላይ ማጉረምረማቸውን እንዲተዉና እንዳይሞቱ ነው።” 11 ሙሴም ወዲያውኑ ይሖዋ እንዳዘዘው አደረገ። ልክ እንደተባለውም አደረገ።

12 ከዚያም እስራኤላውያን ሙሴን እንዲህ አሉት፦ “እንግዲህ መሞታችን ነው፤ በቃ ማለቃችን ነው፤ ሁላችንም ማለቃችን ነው! 13 ወደ ይሖዋ የማደሪያ ድንኳን የሚቀርብ ማንኛውም ሰው ይሞታል!+ በቃ በዚህ መንገድ ሁላችንም መሞታችን ነው?”+

18 ከዚያም ይሖዋ አሮንን እንዲህ አለው፦ “ከመቅደሱ+ ጋር በተያያዘ ለሚፈጸመው ማንኛውም በደል አንተ፣ ከአንተም ጋር ወንዶች ልጆችህና የአባትህ ቤት ተጠያቂ ትሆናላችሁ፤ ከክህነታችሁ ጋር በተያያዘ ለሚፈጸመው ማንኛውም በደል አንተ፣ ከአንተም ጋር ወንዶች ልጆችህ ተጠያቂ ትሆናላችሁ።+ 2 በተጨማሪም በምሥክሩ ድንኳን+ ፊት ከአንተ ጋር አብረው እንዲሆኑ እንዲሁም አንተንና ወንዶች ልጆችህን እንዲያገለግሉ+ ከአባትህ ነገድ ይኸውም ከሌዊ ነገድ የሆኑትን ወንድሞችህን አቅርባቸው። 3 ከአንተም ሆነ በአጠቃላይ ከድንኳኑ ጋር በተያያዘ የተጣለባቸውን ኃላፊነት ይወጡ።+ ይሁንና አንተም ሆንክ እነሱ እንዳትሞቱ ወደ ቅዱሱ ስፍራ ዕቃዎችና ወደ መሠዊያው አይቅረቡ።+ 4 እነሱም ከእናንተ ጋር በመሆን ከመገናኛ ድንኳኑና በድንኳኑ ከሚከናወነው አገልግሎት ሁሉ ጋር በተያያዘ የተጣለባቸውን ኃላፊነት ይወጣሉ፤ ያልተፈቀደለት ማንኛውም ሰው* ወደ እናንተ መቅረብ የለበትም።+ 5 እናንተም በእስራኤል ሕዝብ ላይ ዳግም ቁጣ እንዳይመጣ+ ከቅዱሱ ስፍራና ከመሠዊያው+ ጋር በተያያዘ የተጣለባችሁን ኃላፊነት ተወጡ።+ 6 እኔ ራሴ ወንድሞቻችሁ የሆኑትን ሌዋውያን ከእስራኤላውያን መካከል ወስጄ ለእናንተ ስጦታ አድርጌ ሰጥቻችኋለሁ።+ እነሱም በመገናኛ ድንኳኑ ውስጥ የሚከናወነውን አገልግሎት እንዲፈጽሙ ለይሖዋ የተሰጡ ናቸው።+ 7 ከመሠዊያውና በመጋረጃው ውስጥ ካለው+ ነገር ጋር የተያያዙትን የክህነት ሥራዎቻችሁን የማከናወኑ ኃላፊነት የተጣለው በአንተና በወንዶች ልጆችህ ላይ ነው፤ እናንተም ይህን አገልግሎት ታከናውናላችሁ።+ የክህነት አገልግሎቱን ለእናንተ ስጦታ አድርጌ ሰጥቻችኋለሁ፤ ወደዚያ የሚቀርብ ማንኛውም ያልተፈቀደለት ሰው* ይገደል።”+

8 በተጨማሪም ይሖዋ አሮንን እንዲህ አለው፦ “ለእኔ በሚቀርቡት መዋጮዎች+ ላይ እኔ ራሴ ኃላፊ አድርጌ ሾሜሃለሁ። እስራኤላውያን የሚያዋጧቸውን ቅዱስ ነገሮች ሁሉ ለአንተና ለወንዶች ልጆችህ ድርሻችሁ አድርጌ ሰጥቻችኋለሁ፤ ይህም ቋሚ ድርሻችሁ ነው።+ 9 በእሳት ከሚቀርቡት እጅግ ቅዱስ የሆኑ መባዎች ውስጥ የሚከተሉት የአንተ ይሆናሉ፦ ለእኔ የሚያመጡትን የእህል መባቸውን፣+ የኃጢአት መባቸውንና+ የበደል መባቸውን+ ጨምሮ የሚያቀርቡት ማንኛውም መባ የአንተ ይሆናል። ይህ ለአንተና ለወንዶች ልጆችህ እጅግ የተቀደሰ ነገር ነው። 10 እጅግ ቅዱስ በሆነ ስፍራ ብላው።+ እያንዳንዱ ወንድ ይብላው። ይህ ለአንተ የተቀደሰ ነገር ነው።+ 11 እስራኤላውያን ከሚወዘወዝ መባቸው+ ሁሉ ጋር መዋጮ አድርገው የሚያመጧቸው ስጦታዎች+ የአንተ ይሆናሉ። እነዚህን ለአንተ፣ ከአንተም ጋር ለወንዶች ልጆችህና ለሴቶች ልጆችህ ቋሚ ድርሻ አድርጌ ሰጥቻችኋለሁ።+ በቤትህ ያለ ማንኛውም ንጹሕ የሆነ ሰው ሊበላው ይችላል።+

12 “ለይሖዋ የሚሰጡትን ምርጥ የሆነውን ዘይት ሁሉ፣ ምርጥ የሆነውን አዲስ የወይን ጠጅና እህል ሁሉ ይኸውም የፍሬያቸውን በኩራት+ ለአንተ ሰጥቼሃለሁ።+ 13 በምድራቸው ላይ መጀመሪያ የደረሰው ለይሖዋ የሚያመጡት ፍሬ ሁሉ የአንተ ይሆናል።+ በቤትህ ያለ ማንኛውም ንጹሕ የሆነ ሰው ሊበላው ይችላል።

14 “በእስራኤል ውስጥ ቅዱስ ለሆነ ዓላማ የተለየ ማንኛውም ነገር* የአንተ ይሆናል።+

15 “ከሰውም ሆነ ከእንስሳ ለይሖዋ የሚያቀርቡት የእያንዳንዱ ሕይወት ያለው ነገር* በኩር ሁሉ+ የአንተ መሆን ይኖርበታል። ሆኖም ከሰው በኩር የሆነውን ሁሉ መዋጀት ይኖርብሃል፤+ እንዲሁም ርኩስ ከሆነ እንስሳ በኩር የሆነውን ሁሉ መዋጀት ይገባሃል።+ 16 አንድ ወርና ከዚያ በላይ ሲሆነው እንደ ቋሚ መለኪያ ሆኖ በሚያገለግለው በቅዱሱ ስፍራ ሰቅል*+ መሠረት በተተመነለት ዋጋ ይኸውም በአምስት የብር ሰቅል* ወጆ ልትዋጀው ይገባል። አንዱ ሰቅል 20 ጌራ* ነው። 17 በኩር የሆነውን በሬ፣ በኩር የሆነውን ተባዕት በግና በኩር የሆነውን ፍየል ግን መዋጀት የለብህም።+ እነዚህ የተቀደሱ ነገሮች ናቸው። ደማቸውን በመሠዊያው ላይ እርጨው፤+ ስባቸውን ደግሞ ለይሖዋ ደስ የሚያሰኝ* መዓዛ የሚሰጥ በእሳት የሚቀርብ መባ አድርገህ አጭሰው።+ 18 ሥጋቸው የአንተ ይሆናል። እንደሚወዘወዘው መባ ፍርምባና እንደ ቀኙ እግር ሁሉ ይህም የአንተ ይሆናል።+ 19 እስራኤላውያን ለይሖዋ የሚያዋጧቸውን ቅዱስ መዋጮዎች+ በሙሉ ለአንተ፣ ከአንተም ጋር ለወንዶች ልጆችህና ለሴቶች ልጆችህ ቋሚ ድርሻ አድርጌ ሰጥቻችኋለሁ።+ ይህም በይሖዋ ፊት ለአንተ፣ ከአንተም ጋር ለዘሮችህ የተገባ ዘላቂ የጨው ቃል ኪዳን* ነው።”

20 ይሖዋም በመቀጠል አሮንን እንዲህ አለው፦ “አንተ በምድራቸው ውርሻ አይኖርህም፤ በመካከላቸውም ርስት አይኖርህም።+ በእስራኤላውያን መካከል የአንተ ድርሻም ሆነ ውርሻ እኔ ነኝ።+

21 “እንግዲህ የሌዊ ወንዶች ልጆች ለሚያከናውኑት አገልግሎት ይኸውም በመገናኛ ድንኳኑ ለሚሰጡት አገልግሎት በእስራኤል ውስጥ ያለውን የማንኛውንም ነገር አንድ አሥረኛ ውርሻ አድርጌ እንደሰጠኋቸው+ ልብ በል። 22 ከእንግዲህ እስራኤላውያን ወደ መገናኛ ድንኳኑ መቅረብ አይችሉም፤ ከቀረቡ ግን ኃጢአት ሆኖባቸው ይሞታሉ። 23 በመገናኛ ድንኳኑ የሚቀርበውን አገልግሎት ማከናወን ያለባቸው ሌዋውያኑ ራሳቸው ናቸው፤ ሕዝቡ ለሚፈጽመው ስህተት ተጠያቂ የሚሆኑት እነሱ ናቸው።+ በእስራኤላውያን መካከል በውርስ የሚያገኙት ርስት አይኖራቸውም፤+ ይህም በትውልዶቻችሁ ሁሉ የሚቀጥል ዘላቂ ደንብ ነው። 24 ምክንያቱም የእስራኤል ሕዝብ መዋጮ አድርጎ ለይሖዋ የሚያዋጣውን አንድ አሥረኛ ለሌዋውያኑ ውርሻ አድርጌ ሰጥቻቸዋለሁ። እኔም ‘በእስራኤላውያን መካከል በውርስ የሚያገኙት ርስት አይኖራቸውም’ ያልኳቸው ለዚህ ነው።”+

25 ከዚያም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ 26 “ሌዋውያኑን እንዲህ በላቸው፦ ‘ከእስራኤላውያን ላይ ውርሻችሁ አድርጌ የሰጠኋችሁን አንድ አሥረኛ ከእነሱ እጅ ትቀበላላችሁ፤+ እናንተ ደግሞ የአንድ አሥረኛውን አንድ አሥረኛ ለይሖዋ መዋጮ አድርጋችሁ ትሰጣላችሁ።+ 27 ይህ ለእናንተ እንደ መዋጮ ይኸውም ከአውድማ እንደገባ እህል+ ወይም ከወይን መጭመቂያ አሊያም ከዘይት መጭመቂያ እንደተገኘ የተትረፈረፈ ምርት ተደርጎ ይታሰብላችኋል። 28 በዚህ መንገድ እናንተም ከእስራኤላውያን ከምትቀበሉት አንድ አሥረኛ ሁሉ ላይ ለይሖዋ መዋጮ ታዋጣላችሁ፤ ከእሱም ላይ የይሖዋን መዋጮ ለካህኑ ለአሮን ትሰጣላችሁ። 29 ከምትቀበሏቸው ስጦታዎች+ ሁሉ ላይ ምርጥ የሆነውን እንደ ቅዱስ ነገር አድርጋችሁ ለይሖዋ ሁሉንም ዓይነት መዋጮ ታዋጣላችሁ።’

30 “እንዲህም በላቸው፦ ‘ከስጦታዎቹ ላይ ምርጥ የሆነውን በምታዋጡበት ጊዜ ይህ ለእናንተ ለሌዋውያኑ ከአውድማ እንደገባ ምርት እንዲሁም ከወይን መጭመቂያ ወይም ከዘይት መጭመቂያ እንደተገኘ ምርት ተደርጎ ይታሰብላችኋል። 31 ይህ በመገናኛ ድንኳኑ ለምታከናውኑት አገልግሎት የተሰጠ ደሞዛችሁ ስለሆነ እናንተም ሆናችሁ ቤተሰባችሁ በየትኛውም ቦታ ልትበሉት ትችላላችሁ።+ 32 ከስጦታዎቹ ላይ ምርጥ የሆነውን መዋጮ እስካደረጋችሁ ድረስ ኃጢአት አይሆንባችሁም፤ የእስራኤላውያንን ቅዱስ ነገሮች ማርከስ የለባችሁም፤ እንዲህ ካደረጋችሁ ግን ትሞታላችሁ።’”+

19 ይሖዋ ሙሴንና አሮንን በድጋሚ እንዲህ አላቸው፦ 2 “ይሖዋ ያዘዘው የሕጉ ደንብ ይህ ነው፦ ‘እንከን የሌለባትና+ ቀንበር ተጭኖባት የማታውቅ በጥሩ ሁኔታ ላይ የምትገኝ አንዲት ቀይ ላም እንዲያመጡልህ ለእስራኤላውያን ንገራቸው። 3 ለካህኑ ለአልዓዛርም ስጡት፤ እሱም ከሰፈሩ ውጭ ይወስዳትና በፊቱ ትታረዳለች። 4 ከዚያም ካህኑ አልዓዛር ከደሙ ላይ በጣቱ ወስዶ ደሙን በቀጥታ ወደ መገናኛ ድንኳኑ ፊት ሰባት ጊዜ ይረጨዋል።+ 5 ከዚያም ላሟ ዓይኑ እያየ ትቃጠላለች። ቆዳዋ፣ ሥጋዋና ደሟ ከፈርሷ ጋር አብሮ ይቃጠላል።+ 6 ካህኑም የአርዘ ሊባኖስ እንጨት፣ ሂሶጵና+ ደማቅ ቀይ ማግ ወስዶ ላሟ የምትቃጠልበት እሳት ውስጥ ይጨምራል። 7 ከዚያም ካህኑ ልብሶቹን በውኃ ያጥባል፤ ገላውንም ይታጠባል፤ ከዚያ በኋላ ወደ ሰፈሩ መግባት ይችላል፤ ሆኖም ካህኑ እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል።

8 “‘ላሟን ያቃጠለውም ሰው ልብሶቹን በውኃ ያጥባል፤ ገላውንም በውኃ ይታጠባል፤ እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ይሆናል።

9 “‘ንጹሕ የሆነ ሰው የላሟን አመድ+ አፍሶ ከሰፈሩ ውጭ ባለ ንጹሕ ቦታ ያጠራቅመዋል፤ የእስራኤል ማኅበረሰብም ለማንጻት የሚያገለግለውን ውኃ+ ለማዘጋጀት እንዲውል አመዱን ያስቀምጠው። ይህ የኃጢአት መባ ነው። 10 የላሟን አመድ የሚያፍሰው ሰው ልብሶቹን ያጥባል፤ እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ይሆናል።

“‘ይህም ለእስራኤላውያንና በመካከላቸው ለሚኖር የባዕድ አገር ሰው ዘላቂ ደንብ ሆኖ ያገለግላል።+ 11 የሞተ ሰው* የነካ ማንኛውም ሰው ለሰባት ቀን ርኩስ ይሆናል።+ 12 ይህ ሰው በሦስተኛው ቀን ራሱን በውኃው ያንጻ፤ በሰባተኛውም ቀን ንጹሕ ይሆናል። በሦስተኛው ቀን ራሱን ካላነጻ ግን በሰባተኛው ቀን ንጹሕ አይሆንም። 13 የሞተ ሰው* የነካና ራሱን ያላነጻ ሰው ሁሉ የይሖዋን የማደሪያ ድንኳን አርክሷል፤+ ይህ ሰው* ከእስራኤል መካከል ተለይቶ እንዲጠፋ መደረግ አለበት።+ የሚያነጻው ውኃ+ ስላልተረጨበት ርኩስ ነው። አሁንም ከርኩሰቱ አልነጻም።

14 “‘አንድ ሰው በድንኳን ውስጥ ቢሞት ሕጉ ይህ ነው፦ ወደ ድንኳኑ የሚገባም ሆነ ቀድሞውኑም በድንኳኑ ውስጥ የነበረ ሰው ሁሉ ለሰባት ቀን ርኩስ ይሆናል። 15 መክደኛው ላዩ ላይ ያልታሰረ ክፍት ዕቃ ሁሉ ርኩስ ነው።+ 16 በሰይፍ የተገደለን ወይም በድንን ወይም አፅምን ወይም መቃብርን የነካ በሜዳ ላይ ያለ ማንኛውም ሰው ለሰባት ቀን ርኩስ ይሆናል።+ 17 ለረከሰውም ሰው ከተቃጠለው የኃጢአት መባ አመድ ላይ ወስደው በዕቃ በማድረግ ከወራጅ ውኃ የተቀዳ ውኃ ይጨምሩበት። 18 ከዚያም ንጹሕ የሆነ ሰው+ ሂሶጵ+ ወስዶ ውኃው ውስጥ ከነከረ በኋላ በድንኳኑ፣ በዕቃዎቹ ሁሉ፣ እዚያ በነበረው ሰው* ሁሉና አፅሙን ወይም የተገደለውን ሰው አሊያም በድኑን ወይም መቃብሩን በነካው ሰው ላይ ይረጨዋል። 19 ንጹሕ የሆነውም ሰው ውኃውን በረከሰው ሰው ላይ በሦስተኛው ቀንና በሰባተኛው ቀን ላይ ይረጨዋል፤ በሰባተኛውም ቀን ከኃጢአት ያነጻዋል፤+ ከዚያም ሰውየው ልብሶቹን ይጠብ፤ በውኃም ይታጠብ፤ ማታም ላይ ንጹሕ ይሆናል።

20 “‘ሆኖም የረከሰውና ራሱን ያላነጻው ሰው የይሖዋን መቅደስ ስላረከሰ ይህ ሰው* ከጉባኤው መካከል ተለይቶ እንዲጠፋ መደረግ አለበት።+ የሚያነጻው ውኃ ስላልተረጨበት ሰውየው ርኩስ ነው።

21 “‘ይህ ለእነሱ ዘላቂ ደንብ ሆኖ ያገለግላል፦ የሚያነጻውን ውኃ+ የሚረጨው ሰው ልብሶቹን ማጠብ ይኖርበታል፤ የሚያነጻውን ውኃ የሚነካውም ሰው እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል። 22 የረከሰው ሰው የሚነካው ማንኛውም ነገር ርኩስ ይሆናል፤ ይህን የነካ ሰውም* እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል።’”+

20 በመጀመሪያው ወር መላው የእስራኤል ማኅበረሰብ ወደ ጺን ምድረ በዳ መጣ፤ ሕዝቡም በቃዴስ+ ተቀመጠ። ሚርያም+ የሞተችውም ሆነ የተቀበረችው በዚያ ነበር።

2 በዚያ ለማኅበረሰቡ የሚሆን ውኃ አልነበረም፤+ ሕዝቡም ሙሴንና አሮንን በመቃወም በእነሱ ላይ ተሰበሰበ። 3 ሕዝቡም እንዲህ በማለት ከሙሴ ጋር ተጣላ፦+ “ምነው ወንድሞቻችን በይሖዋ ፊት በሞቱ ጊዜ እኛም ሞተን ባረፍነው ኖሮ! 4 እኛም ሆንን ከብቶቻችን እዚህ እንድናልቅ የይሖዋን ጉባኤ ወደዚህ ምድረ በዳ ያመጣችሁት ለምንድን ነው?+ 5 ከግብፅ አውጥታችሁ ወደዚህ መጥፎ ቦታ እየመራችሁ ያመጣችሁን ለምንድን ነው?+ ይህ ቦታ እህልም ሆነ በለስ፣ የወይን ፍሬም ሆነ ሮማን የሌለበት ነው፤ የሚጠጣ ውኃም የለም።”+ 6 ከዚያም ሙሴና አሮን ከጉባኤው ፊት ተነስተው ወደ መገናኛ ድንኳኑ መግቢያ በመሄድ በግንባራቸው መሬት ላይ ተደፉ፤ የይሖዋም ክብር ተገለጠላቸው።+

7 ከዚያም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ 8 “በትሩን ውሰድ፤ አንተና ወንድምህ አሮንም ማኅበረሰቡን ሰብስቡ፤ ዓለቱም ውኃውን እንዲሰጥ በእነሱ ፊት ተናገሩት፤ አንተም ከዓለቱ ውኃ ታፈልቅላቸዋለህ፤ ማኅበረሰቡም ሆነ ከብቶቻቸው እንዲጠጡም ትሰጣቸዋለህ።”+

9 ሙሴም ልክ እንደታዘዘው በትሩን ከይሖዋ ፊት ወሰደ።+ 10 ከዚያም ሙሴና አሮን ጉባኤውን በዓለቱ ፊት ሰበሰቡ፤ እሱም “እናንተ ዓመፀኞች ስሙ! ከዚህ ዓለት ለእናንተ ውኃ ማፍለቅ አለብን?” አላቸው።+ 11 ሙሴም ይህን ካለ በኋላ እጁን አንስቶ ዓለቱን ሁለት ጊዜ በበትሩ መታው፤ ውኃውም ይንዶለዶል ጀመር፤ ማኅበረሰቡና ከብቶቻቸውም ጠጡ።+

12 በኋላም ይሖዋ ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፦ “በእስራኤል ሕዝብ ፊት በእኔ ስላልታመናችሁና እኔን ስላልቀደሳችሁ ይህን ጉባኤ እኔ ወደምሰጠው ምድር ይዛችሁ አትገቡም።”+ 13 ይሖዋ በመካከላቸው ይቀደስ ዘንድ እስራኤላውያን ከእሱ ጋር የተጣሉባቸው የመሪባ*+ ውኃዎች እነዚህ ናቸው።

14 ከዚያም ሙሴ ለኤዶም ንጉሥ እንዲህ ብለው እንዲነግሩት ከቃዴስ መልእክተኞችን ላከ፦+ “ወንድምህ እስራኤል+ እንዲህ ይላል፦ ‘መቼም የደረሰብንን መከራ ሁሉ በሚገባ ታውቃለህ። 15 አባቶቻችን ወደ ግብፅ ወርደው ነበር፤+ እኛም በግብፅ ለብዙ ዓመታት* ኖርን፤+ ግብፃውያኑም በእኛም ሆነ በአባቶቻችን ላይ በደል ይፈጽሙብን ነበር።+ 16 በመጨረሻም ወደ ይሖዋ ጮኽን፤+ እሱም ጩኸታችንን ሰምቶ መልአክ በመላክ+ ከግብፅ አወጣን፤ ይኸው አሁን ድንበርህ ላይ ባለችው በቃዴስ ከተማ እንገኛለን። 17 እናም አሁን እባክህ በምድርህ እንለፍ። በየትኛውም እርሻ ወይም በየትኛውም የወይን ቦታ አቋርጠን አንሄድም፤ ከየትኛውም ጉድጓድ ውኃ አንጠጣም። ክልልህን አቋርጠን እስክናልፍ ድረስ ወደ ቀኝም ሆነ ወደ ግራ ዞር ሳንል በንጉሡ መንገድ እንሄዳለን።’”+

18 ኤዶም ግን “ክልላችንን አቋርጠህ ማለፍ አትችልም። እንዲህ ካደረግክ ወጥቼ በሰይፍ እገጥምሃለሁ” አለው። 19 እስራኤላውያንም መልሰው እንዲህ አሉት፦ “አውራ ጎዳናውን ይዘን እናቀናለን፤ እኛም ሆን ከብቶቻችን ከውኃህ ከጠጣን ዋጋውን እንከፍልሃለን።+ በእግራችን አልፈን ከመሄድ በስተቀር ሌላ ምንም ነገር አንፈልግም።”+ 20 እሱ ግን አሁንም “በዚህ ማለፍ አትችልም”+ ሲል መልስ ሰጠ። ከዚያም ኤዶም ብዙ ሕዝብና ኃያል ሠራዊት* ይዞ ሊገጥመው ወጣ። 21 በዚህ መንገድ ኤዶም እስራኤል በክልሉ እንዳያልፍ ከለከለ፤ ስለዚህ እስራኤል ከእሱ ተመለሰ።+

22 የእስራኤል ሕዝብ ይኸውም መላው ማኅበረሰብ ከቃዴስ ተነስቶ ወደ ሆር ተራራ+ መጣ። 23 ከዚያም ይሖዋ በኤዶም ምድር ወሰን ላይ ባለው በሆር ተራራ ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፦ 24 “አሮን ወደ ወገኖቹ ይሰበሰባል።*+ ሁለታችሁም ከመሪባ ውኃ ጋር በተያያዘ በሰጠሁት ትእዛዝ ላይ ስላመፃችሁ ለእስራኤላውያን ወደምሰጣት ምድር አይገባም።+ 25 አሮንንና ልጁን አልዓዛርን ይዘህ ወደ ሆር ተራራ ውጣ። 26 የአሮንን ልብስ አውልቀህ+ ልጁን አልዓዛርን+ አልብሰው፤ አሮንም በዚያ ይሞታል።”*

27 በመሆኑም ሙሴ ልክ ይሖዋ እንዳዘዘው አደረገ፤ እነሱም መላው ማኅበረሰብ እያየ ወደ ሆር ተራራ ወጡ። 28 ሙሴም የአሮንን ልብስ አውልቆ ልጁን አልዓዛርን አለበሰው። ከዚያም አሮን እዚያው ተራራው አናት ላይ ሞተ።+ ሙሴና አልዓዛርም ከተራራው ወረዱ። 29 መላው ማኅበረሰብም አሮን መሞቱን አየ፤ በዚህ ጊዜ የእስራኤል ቤት በሙሉ ለአሮን 30 ቀን አለቀሰለት።+

21 በኔጌብ የሚኖረው ከነአናዊው የአራድ ንጉሥ+ እስራኤላውያን በአታሪም መንገድ እየመጡ መሆናቸውን በሰማ ጊዜ በእነሱ ላይ ጥቃት ሰነዘረ፤ ከመካከላቸውም የተወሰኑትን በምርኮ ወሰደ። 2 ስለዚህ እስራኤል “ይህን ሕዝብ በእጄ አሳልፈህ የምትሰጠኝ ከሆነ ከተሞቻቸውን ጠራርጌ አጠፋለሁ” በማለት ለይሖዋ ስእለት ተሳለ። 3 በመሆኑም ይሖዋ የእስራኤልን ጩኸት ሰማ፤ ከነአናውያንንም በእጃቸው አሳልፎ ሰጣቸው፤ እነሱም ሕዝቡንና ከተሞቻቸውን ጠራርገው አጠፉ። ስለሆነም የቦታውን ስም ሆርማ*+ አሉት።

4 እስራኤላውያን ከሆር ተራራ+ በመነሳት በኤዶም ምድር ዞረው ለመሄድ ስላሰቡ የቀይ ባሕርን መንገድ ይዘው ተጓዙ፤+ ከጉዞውም የተነሳ ሕዝቡ* ዛለ። 5 ሕዝቡም እንዲህ በማለት በአምላክና በሙሴ ላይ ያማርር ጀመር፦+ “በምድረ በዳ እንድንሞት ከግብፅ ያወጣችሁን ለምንድን ነው? ምግብ የለ፣ ውኃ የለ፤+ ደግሞም ይህን የማይረባ ምግብ ጠልተነዋል።”*+ 6 በመሆኑም ይሖዋ በሕዝቡ ላይ መርዘኛ* እባቦችን ሰደደባቸው፤ እባቦቹም ሰዎቹን ስለነደፏቸው ብዙ እስራኤላውያን ሞቱ።+

7 ስለሆነም ሕዝቡ ወደ ሙሴ መጥቶ “በይሖዋና በአንተ ላይ በማማረራችን ኃጢአት ሠርተናል።+ እባቦቹን ከመካከላችን እንዲያስወግድልን ይሖዋን ተማጸንልን” አለ። ሙሴም ስለ ሕዝቡ ተማጸነ።+ 8 ከዚያም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ “የመርዛማ* እባብ ምስል ሠርተህ እንጨት ላይ ስቀለው። ማንኛውም ሰው በሚነደፍበት ጊዜ በሕይወት እንዲኖር ምስሉን ማየት አለበት።” 9 ሙሴም ወዲያው የመዳብ እባብ+ ሠርቶ እንጨት ላይ ሰቀለው፤+ አንድ ሰው እባብ ሲነድፈው ከመዳብ ወደተሠራው እባብ ከተመለከተ ይድን ነበር።+

10 ከዚህ በኋላ እስራኤላውያን ከነበሩበት ተነስተው በመጓዝ በኦቦት ሰፈሩ።+ 11 ከዚያም ከኦቦት ተነስተው በምሥራቅ አቅጣጫ በሞዓብ ፊት ለፊት በሚገኘው ምድረ በዳ በኢዬዓባሪም+ ሰፈሩ። 12 ከዚያ ተነስተው ደግሞ በዘረድ ሸለቆ*+ ሰፈሩ። 13 ከዘረድ ሸለቆ ተነስተው ከአሞራውያን ድንበር ጀምሮ ባለው ምድረ በዳ ውስጥ በሚገኘው በአርኖን ክልል+ ሰፈሩ፤ ምክንያቱም አርኖን በሞዓብና በአሞራውያን መካከል የሚገኝ የሞዓብ ድንበር ነው። 14 የይሖዋ የጦርነት መጽሐፍ እንዲህ በማለት የሚናገረው ለዚህ ነው፦ “በሱፋ የሚገኘው ዋሄብ፣ የአርኖን ሸለቆዎች* 15 እንዲሁም ኤር ወደሚገኝበት አቅጣጫ የሚዘረጋውና የሞዓብን ድንበር የሚያዋስነው የሸለቆዎች* ቁልቁለት።”*

16 ከዚያም ወደ በኤር ተጓዙ። ይሖዋ ሙሴን “ሕዝቡን ሰብስብ፤ እኔም ውኃ እሰጣቸዋለሁ” ያለው ይህን የውኃ ጉድጓድ አስመልክቶ ነው።

17 በዚህ ጊዜ እስራኤላውያን ይህን መዝሙር ዘመሩ፦

“አንተ ጉድጓድ፣ ውኃ አፍልቅ! እናንተም መልሱለት!*

18 መኳንንት ለቆፈሩት፣ በሕዝቡ መካከል ያሉ ታላላቅ ሰዎች ለማሱት፣

በገዢ ዘንግና በራሳቸው በትሮች ላዘጋጁት የውኃ ጉድጓድ ዘምሩለት።”

ከዚያም ከምድረ በዳው ተነስተው ወደ ማታናህ ተጓዙ፤ 19 ከማታናህ ተነስተው ደግሞ ወደ ናሃሊኤል፣ ከናሃሊኤልም ተነስተው ወደ ባሞት+ ተጓዙ። 20 ከባሞትም ተነስተው የሺሞንን*+ ቁልቁል ማየት ወደሚቻልበት በጲስጋ+ አናት ላይ ወደሚገኘውና በሞዓብ ክልል*+ ወዳለው ሸለቆ ተጓዙ።

21 እስራኤላውያን የአሞራውያን ንጉሥ ወደሆነው ወደ ሲሖን እንዲህ በማለት መልእክተኞችን ላኩ፦+ 22 “ምድርህን አቋርጠን እንድናልፍ ፍቀድልን። ወደ የትኛውም እርሻ ወይም ወደ የትኛውም የወይን ቦታ አንገባም። ከየትኛውም ጉድጓድ ውኃ አንጠጣም። ክልልህን አቋርጠን እስክናልፍ ድረስ በንጉሡ መንገድ ቀጥ ብለን እንሄዳለን።”+ 23 ሲሖን ግን እስራኤላውያን ክልሉን አቋርጠው እንዲያልፉ አልፈቀደላቸውም። ከዚህ ይልቅ ሲሖን ሕዝቡን ሁሉ ሰብስቦ እስራኤልን ለመውጋት ወደ ምድረ በዳው ሄደ፤ ያሃጽ በደረሰ ጊዜም ከእስራኤላውያን ጋር ውጊያ ገጠመ።+ 24 እስራኤላውያን ግን በሰይፍ ድል አደረጉት፤+ ምድሩንም ከአርኖን+ አንስቶ በአሞናውያን አቅራቢያ እስከሚገኘው እስከ ያቦቅ+ ድረስ ያዙ፤+ ሆኖም ያዜር+ የአሞናውያን ወሰን+ ስለሆነ ከዚያ አላለፉም።

25 በመሆኑም እስራኤላውያን እነዚህን ከተሞች ሁሉ ያዙ፤ ከዚያም በአሞራውያን+ ከተሞች ይኸውም በሃሽቦንና በሥሯ* ባሉት ከተሞች ሁሉ መኖር ጀመሩ። 26 ምክንያቱም ሃሽቦን የአሞራውያን ንጉሥ የሲሖን ከተማ ነበረች፤ እሱም ከሞዓብ ንጉሥ ጋር ተዋግቶ እስከ አርኖን ድረስ ያለውን ምድር ከእጁ ወስዶበት ነበር። 27 እንዲህ የሚለውን ቅኔ በመቀኘት የተሳለቁበት በዚህ የተነሳ ነው፦

“ወደ ሃሽቦን ኑ።

የሲሖን ከተማ ትገንባ፤ ጸንታም ትቁም።

28 እሳት ከሃሽቦን፣ ነበልባልም ከሲሖን ከተማ ወጥቷልና።

የሞዓብን ኤር፣ የአርኖንን ኮረብቶች ጌቶች በላ።

29 ሞዓብ ሆይ፣ ወዮልህ! እናንተ የከሞሽ+ ሕዝቦች ሆይ፣ ድምጥማጣችሁ ይጠፋል።

ወንዶች ልጆቹን ለስደት ይዳርጋል፤ ሴቶች ልጆቹንም ለአሞራውያን ንጉሥ ለሲሖን ምርኮኛ አድርጎ ይሰጣል።

30 በመሆኑም ጥቃት እንሰንዝርባቸው፤

ሃሽቦን እስከ ዲቦን+ ድረስ ይደመሰሳል፤

እስከ ኖፋ ድረስ እንደምስሰው፤

እስከ መደባም+ ድረስ እሳት ይዛመታል።”

31 ስለዚህ እስራኤላውያን በአሞራውያን ምድር መኖር ጀመሩ። 32 ከዚያም ሙሴ ያዜርን እንዲሰልሉ የተወሰኑ ሰዎችን ላከ።+ እነሱም በሥሯ* ያሉትን ከተሞች ተቆጣጠሩ፤ በዚያ የነበሩትንም አሞራውያን አባረሩ። 33 ከዚህ በኋላ ተመልሰው በባሳን መንገድ ወጡ። የባሳን ንጉሥ ኦግም+ ከሕዝቡ ሁሉ ጋር በመሆን ኤድራይ ላይ ጦርነት ሊገጥማቸው ወጣ።+ 34 ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ “እሱንም ሆነ ሕዝቡን ሁሉ እንዲሁም ምድሩን በእጅህ አሳልፌ ስለምሰጥህ አትፍራው፤+ አንተም በሃሽቦን ይኖር በነበረው በአሞራውያን ንጉሥ በሲሖን ላይ እንዳደረግከው በእሱም ላይ ታደርግበታለህ።”+ 35 በመሆኑም ኦግን ከወንዶች ልጆቹና ከሕዝቡ ሁሉ ጋር አንድም ሰው ሳያስቀሩ ሁሉንም ደመሰሱ፤+ ምድሩንም ወረሱ።+

22 እስራኤላውያንም ከዚያ ተነስተው በመጓዝ ከኢያሪኮ ማዶ በዮርዳኖስ አጠገብ በሚገኘው በሞዓብ በረሃማ ሜዳ ሰፈሩ።+ 2 የሴፎር ልጅ ባላቅ+ እስራኤላውያን በአሞራውያን ላይ ያደረጉትን ሁሉ አየ፤ 3 ሞዓብም ከሕዝቡ ብዛት የተነሳ በጣም ፈራ፤ በእርግጥም ሞዓብ በእስራኤላውያን ምክንያት በፍርሃት ታውኮ ነበር።+ 4 ስለዚህ ሞዓብ የምድያምን+ ሽማግሌዎች “በሬ በሜዳ ላይ ያለን ሣር ጠራርጎ እንደሚበላ ሁሉ ይህም ጉባኤ በዙሪያችን ያለውን ሁሉ ጠራርጎ ያጠፋል” አላቸው።

በዚያን ጊዜ የሴፎር ልጅ ባላቅ የሞዓብ ንጉሥ ነበር። 5 እሱም የቢዖርን ልጅ በለዓምን እንዲጠሩት መልእክተኞችን ላከ፤ በለዓም የሚኖረው በትውልድ አገሩ ባለው ወንዝ* ዳር በምትገኘው በጰቶር ነበር።+ እንዲህም ብለው እንዲነግሩት ላካቸው፦ “ከግብፅ ወጥቶ የመጣ አንድ ሕዝብ አለ። ይኸው የምድሪቱን* ገጽ* ሸፍኗል፤+ ደግሞም መጥቶ አፍንጫዬ ሥር ሰፍሯል። 6 እነሱ ከእኔ ይልቅ ኃያላን ስለሆኑ እባክህ መጥተህ ይህን ሕዝብ እርገምልኝ።+ ምናልባትም ድል አድርጌ ከምድሪቱ ላባርራቸው እችላለሁ፤ ምክንያቱም አንተ የባረክኸው ሁሉ የተባረከ፣ የረገምከውም ሁሉ የተረገመ እንደሚሆን በሚገባ አውቃለሁ።”

7 በመሆኑም የሞዓብ ሽማግሌዎችና የምድያም ሽማግሌዎች ለሟርት የሚከፈለውን ዋጋ ይዘው ወደ በለዓም+ ሄዱ፤ የባላቅንም መልእክት ነገሩት። 8 እሱም “እንግዲህ እዚህ እደሩና ይሖዋ የሚለኝን ማንኛውንም ነገር መልሼ እነግራችኋለሁ” አላቸው። ስለዚህም የሞዓብ መኳንንት በለዓም ዘንድ አደሩ።

9 ከዚያም አምላክ ወደ በለዓም መጥቶ+ “ከአንተ ጋር ያሉት እነዚህ ሰዎች እነማን ናቸው?” አለው። 10 በለዓምም እውነተኛውን አምላክ እንዲህ አለው፦ “የሞዓብ ንጉሥ የሴፎር ልጅ ባላቅ እንዲህ የሚል መልእክት ልኮብኛል፦ 11 ‘ከግብፅ ወጥቶ የመጣው ሕዝብ የምድሪቱን* ገጽ* ሸፍኗል። ስለዚህ መጥተህ እነሱን እርገምልኝ።+ ምናልባትም ድል አድርጌ ከምድሪቱ ላባርራቸው እችላለሁ።’” 12 ሆኖም አምላክ በለዓምን “ከእነሱ ጋር እንዳትሄድ። ሕዝቡ የተባረከ ስለሆነ እንዳትረግመው” አለው።+

13 በለዓም በጠዋት ተነስቶ የባላቅን መኳንንት “ይሖዋ ከእናንተ ጋር እንዳልሄድ ስለከለከለኝ ወደ አገራችሁ ሂዱ” አላቸው። 14 በመሆኑም የሞዓብ መኳንንት ተነስተው ወደ ባላቅ ተመለሱ፤ እንዲህም አሉት፦ “በለዓም ከእኛ ጋር ለመምጣት ፈቃደኛ አልሆነም።”

15 ሆኖም ባላቅ ከበፊቶቹ ይልቅ ቁጥራቸው የበዛና ይበልጥ የተከበሩ ሌሎች መኳንንት እንደገና ላከ። 16 እነሱም ወደ በለዓም መጥተው እንዲህ አሉት፦ “የሴፎር ልጅ ባላቅ እንዲህ ይላል፦ ‘እባክህ ወደ እኔ ከመምጣት ምንም ነገር እንዲያግድህ አትፍቀድ። 17 እኔም ከፍ ያለ ክብር አጎናጽፍሃለሁ፤ የምትለኝንም ሁሉ አደርጋለሁ። ስለሆነም እባክህ መጥተህ ይህን ሕዝብ እርገምልኝ።’” 18 ሆኖም በለዓም ለባላቅ አገልጋዮች እንዲህ የሚል መልስ ሰጣቸው፦ “ባላቅ በብርና በወርቅ የተሞላውን የገዛ ቤቱን ቢሰጠኝ እንኳ ከአምላኬ ከይሖዋ ትእዛዝ ወጥቼ ትንሽም ሆነ ትልቅ ምንም ነገር ማድረግ አልችልም።+ 19 ሆኖም እባካችሁ፣ ይሖዋ ሌላ የሚለኝ ነገር ካለ እንዳውቅ ዛሬም እዚህ እደሩ።”+

20 ከዚያም አምላክ በሌሊት ወደ በለዓም መጥቶ እንዲህ አለው፦ “እነዚህ ሰዎች የመጡት አንተን ለመጥራት ከሆነ አብረሃቸው ሂድ። ይሁንና የምትናገረው እኔ የምልህን ብቻ ነው።”+ 21 ስለዚህ በለዓም በጠዋት ተነስቶ አህያውን ከጫነ በኋላ ከሞዓብ መኳንንት ጋር ሄደ።+

22 ይሁን እንጂ በለዓም ጉዞ በመጀመሩ የአምላክ ቁጣ ነደደ፤ የይሖዋም መልአክ በለዓምን ሊቃወመው መንገዱ ላይ ቆመ። በዚህ ጊዜ በለዓም በአህያው ላይ ተቀምጦ እየተጓዘ ነበር፤ ሁለት አገልጋዮቹም አብረውት ነበሩ። 23 አህያዋም የይሖዋ መልአክ የተመዘዘ ሰይፍ በእጁ ይዞ መንገዱ ላይ መቆሙን ስታይ ከመንገዱ ወጥታ ወደ እርሻ ለመግባት ሞከረች። ሆኖም በለዓም አህያዋን ወደ መንገዱ ለመመለስ ይደበድባት ጀመር። 24 ከዚያም የይሖዋ መልአክ በዚህም በዚያም በኩል በግንብ በታጠሩ ሁለት የወይን እርሻዎች መካከል በሚገኝ ጠባብ መንገድ ላይ ቆመ። 25 አህያዋም የይሖዋን መልአክ ስታይ ግንቡን መታከክ ጀመረች፤ የበለዓምንም እግር ከግንቡ ጋር አጣበቀችው፤ በለዓምም እንደገና ይደበድባት ጀመር።

26 የይሖዋም መልአክ እንደገና አልፎ ወደ ቀኝም ሆነ ወደ ግራ መፈናፈን በማያስችል ጠባብ ቦታ ላይ ቆመ። 27 አህያዋም የይሖዋን መልአክ ስታይ በለዓም ላይዋ ላይ እንዳለ ተኛች፤ በዚህ ጊዜ በለዓም እጅግ ተቆጣ፤ አህያዋንም በዱላው ይቀጠቅጣት ጀመር። 28 በመጨረሻም ይሖዋ አህያዋ እንድትናገር አደረገ፤*+ እሷም በለዓምን “ሦስት ጊዜ እንዲህ የመታኸኝ ምን አድርጌህ ነው?”+ አለችው። 29 በለዓምም አህያዋን “ስለተጫወትሽብኝ ነዋ! በእጄ ሰይፍ ይዤ ቢሆንማ ኖሮ እገድልሽ ነበር!” አላት። 30 ከዚያም አህያዋ በለዓምን “እስከ ዛሬ ድረስ በሕይወትህ ሙሉ የተቀመጥክብኝ አህያህ አይደለሁም? ከዚህ በፊት እንዲህ አድርጌህ አውቃለሁ?” አለችው። እሱም “በጭራሽ!” አላት። 31 ከዚያም ይሖዋ የበለዓምን ዓይኖች ገለጠ፤+ እሱም የይሖዋ መልአክ የተመዘዘ ሰይፍ በእጁ ይዞ መንገዱ ላይ ቆሞ አየ። ወዲያውኑም በግንባሩ ተደፍቶ ሰገደ።

32 ከዚያም የይሖዋ መልአክ እንዲህ አለው፦ “አህያህን ሦስት ጊዜ እንዲህ አድርገህ የመታሃት ለምንድን ነው? መንገድህ ከፈቃዴ ጋር ስለሚቃረን እኔ ራሴ ከጉዞህ ልገታህ መጥቻለሁ።+ 33 አህያዋ አይታኝ ሦስቱንም ጊዜ ከፊቴ ዞር ለማለት ሞከረች።+ እሷ ከፊቴ ዞር ባትልማ ኖሮ ምን ይከሰት እንደነበር አስብ! ይሄን ጊዜ አንተን ገድዬህ አህያዋን በሕይወት በተውኳት ነበር።” 34 በዚህ ጊዜ በለዓም የይሖዋን መልአክ እንዲህ አለው፦ “ኃጢአት ሠርቻለሁ፤ ምክንያቱም አንተ እኔን ለማግኘት መንገድ ላይ እንደቆምክ አላወቅኩም ነበር። አሁንም ቢሆን መሄዴ ጥሩ መስሎ ካልታየህ እመለሳለሁ።” 35 ሆኖም የይሖዋ መልአክ በለዓምን “ከሰዎቹ ጋር መሄዱን እንኳ ሂድ፤ የምትናገረው ግን እኔ የምልህን ብቻ ነው” አለው። በመሆኑም በለዓም ከባላቅ መኳንንት ጋር ጉዞውን ቀጠለ።

36 ባላቅ የበለዓምን መምጣት ሲሰማ በክልሉ ወሰን ላይ በሚገኘው በአርኖን ዳርቻ ባለው በሞዓብ ከተማ ሊቀበለው ወዲያውኑ ወጣ። 37 ባላቅም በለዓምን እንዲህ አለው፦ “እንድትመጣ ልኬብህ አልነበረም? ታዲያ ወደ እኔ ያልመጣኸው ለምንድን ነው? ለመሆኑ እኔ አንተን ታላቅ ክብር ማጎናጸፍ የሚያቅተኝ ይመስልሃል?”+ 38 በለዓምም ባላቅን እንዲህ አለው፦ “ይኸው አሁን ወደ አንተ መጥቻለሁ። ይሁንና ያሻኝን መናገር የምችል ይመስልሃል? እኔ መናገር የምችለው አምላክ በአፌ ላይ የሚያደርገውን ቃል ብቻ ነው።”+

39 በመሆኑም በለዓም ከባላቅ ጋር ሄደ፤ ወደ ቂርያትሁጾትም መጡ። 40 ባላቅም ከብቶችንና በጎችን ሠዋ፤ የተወሰነውንም ለበለዓምና ከእሱ ጋር ለነበሩት መኳንንት ላከ። 41 ጠዋት ላይም ባላቅ በለዓምን ይዞት ወደ ባሞትበዓል ወጣ፤ እዚያ ሆኖ ሕዝቡን ሁሉ ማየት ይችል ነበር።+

23 ከዚያም በለዓም ባላቅን “እዚህ ቦታ ላይ ሰባት መሠዊያዎች ሥራልኝ፤+ እንዲሁም ሰባት በሬዎችና ሰባት አውራ በጎች አዘጋጅልኝ” አለው። 2 ባላቅም ወዲያውኑ በለዓም እንዳለው አደረገ። ባላቅና በለዓም በእያንዳንዱ መሠዊያ ላይ አንድ በሬና አንድ አውራ በግ አቀረቡ።+ 3 ከዚያም በለዓም ባላቅን እንዲህ አለው፦ “አንተ እዚህ የሚቃጠለው መባህ አጠገብ ቆይ፤ እኔ ግን ልሂድ። ምናልባት ይሖዋ ይገለጥልኝ ይሆናል። እሱ የሚገልጥልኝን ማንኛውንም ነገር እነግርሃለሁ።” በመሆኑም በለዓም ወደ አንድ ገላጣ ኮረብታ ሄደ።

4 በለዓምም ከአምላክ ጋር በተገናኘ ጊዜ+ “ሰባቱን መሠዊያዎች በመደዳ አቁሜያቸዋለሁ፤ በእያንዳንዱም መሠዊያ ላይ አንድ በሬና አንድ አውራ በግ አቅርቤያለሁ” አለው። 5 ይሖዋም በበለዓም አፍ ላይ ይህን ቃል አስቀመጠ፦+ “ወደ ባላቅ ተመለስና እንዲህ ብለህ ንገረው።” 6 በመሆኑም በለዓም ተመለሰ፤ እሱም ባላቅን ከሞዓብ መኳንንት ሁሉ ጋር በሚቃጠለው መባው አጠገብ ቆሞ አየው። 7 ከዚያም ይህን ምሳሌያዊ አባባል ተናገረ፦+

“የሞዓብ ንጉሥ ባላቅ ከአራም፣+

ከምሥራቅ ተራሮች አመጣኝ፤

‘ና፣ ያዕቆብን እርገምልኝ።

አዎ ና፣ እስራኤልን አውግዝልኝ’ አለኝ።+

 8 አምላክ ያልረገመውን እኔ እንዴት ልረግም እችላለሁ?

ይሖዋ ያላወገዘውንስ እኔ እንዴት ላወግዝ እችላለሁ?+

 9 ከዓለቶቹ አናት ላይ ሆኜ አያቸዋለሁ፤

ከኮረብቶቹም ላይ ሆኜ እመለከታቸዋለሁ።

በዚያ እንደ አንድ ሕዝብ ብቻቸውን ሰፍረዋል፤+

ከሌሎች ብሔራት እንደ አንዱ አድርገው ራሳቸውን አይቆጥሩም።+

10 ከብዛቱ የተነሳ እንደ አፈር የሆነውን ያዕቆብን ማን ሊቆጥረው ይችላል?+

የእስራኤልንስ ሩብ ማን ይቆጥረዋል?

የቅኖች ዓይነት አሟሟት ልሙት፤*

መጨረሻዬም እንደ እነሱ ይሁን።”

11 ባላቅም በለዓምን እንዲህ አለው፦ “እንዴት እንዲህ ታደርገኛለህ? እኔ እኮ ያመጣሁህ ጠላቶቼን እንድትረግምልኝ ነው፤ አንተ ግን ባረክሃቸው እንጂ ምንም አልፈየድክልኝም።”+ 12 እሱም መልሶ “እኔ መናገር ያለብኝ ይሖዋ በአፌ ላይ ያስቀመጠውን ብቻ አይደለም?” አለ።+

13 ከዚያም ባላቅ እንዲህ አለው፦ “እባክህ፣ እነሱን ማየት ወደምትችልበት ሌላ ቦታ አብረን እንሂድ። እርግጥ ሁሉንም አታያቸውም፤ የምታያቸው በከፊል ብቻ ነው። እዚያ ሆነህ እርገምልኝ።”+ 14 እሱም በጲስጋ አናት+ ላይ ወደሚገኘው የጾፊም ሜዳ ወሰደው፤ በዚያም ሰባት መሠዊያዎችን ሠርቶ በእያንዳንዱ መሠዊያ ላይ አንድ በሬና አንድ አውራ በግ አቀረበ።+ 15 በለዓምም ባላቅን “እኔ ከእሱ ጋር ለመገናኘት ወደዚያ ስሄድ አንተ እዚሁ የሚቃጠለው መባህ አጠገብ ቆይ” አለው። 16 ይሖዋም ከበለዓም ጋር ተገናኘ፤ በአፉም ላይ ይህን ቃል አስቀመጠ፦+ “ወደ ባላቅ ተመለስና እንዲህ ብለህ ንገረው።” 17 በመሆኑም በለዓም ወደ ባላቅ ተመለሰ፤ ባላቅንም በሚቃጠለው መባው አጠገብ ሲጠብቀው አገኘው፤ የሞዓብ መኳንንትም ከእሱ ጋር ነበሩ። ከዚያም ባላቅ “ለመሆኑ ይሖዋ ምን አለ?” ሲል ጠየቀው። 18 በለዓምም ይህን ምሳሌያዊ አባባል ተናገረ፦+

“ባላቅ ተነስ፤ አዳምጥ።

የሴፎር ልጅ ሆይ፣ ጆሮህን ስጠኝ።

19 አምላክ እንደ ሰው አይዋሽም፤+

እንደ ሰው ልጅም ሐሳቡን አይለውጥም።*+

እሱ ያለውን አያደርገውም?

የተናገረውንስ አይፈጽመውም?+

20 እንግዲህ የእኔ ተልእኮ መባረክ ነው፤

እሱ እንደሆነ ባርኳል፤+ እኔ ደግሞ ልለውጠው አልችልም።+

21 ያዕቆብን ለማጥቃት የታሰበን ማንኛውንም አስማታዊ ኃይል ዝም ብሎ አያልፍም፤

በእስራኤል ላይ ምንም ዓይነት ችግር እንዲደርስ አይፈቅድም።

አምላኩ ይሖዋ ከእነሱ ጋር ነው፤+

በመካከላቸውም እንደ ንጉሥ ከፍ ባለ ድምፅ ይወደሳል።

22 አምላክ ከግብፅ አውጥቷቸዋል።+

እሱም ለእነሱ ልክ እንደ ጎሽ ቀንዶች ነው።+

23 በያዕቆብ ላይ የሚሠራ ምንም ዓይነት ድግምት የለምና፤+

በእስራኤልም ላይ የሚሠራ ምንም ዓይነት ሟርት የለም።+

በዚህ ጊዜ ስለ ያዕቆብና ስለ እስራኤል

‘አምላክ ያደረገውን ተመልከቱ!’ ይባላል።

24 ልክ እንደ አንበሳ የሚነሳው ሕዝብ ይህ ነው፤

እሱም እንደ አንበሳ ተነስቶ ይቆማል።+

ያደነውን እስኪበላ፣

የተገደሉትንም ደማቸውን እስኪጠጣ ድረስ አይተኛም።”

25 ከዚያም ባላቅ በለዓምን “እንግዲያው ልትረግመው ካልቻልክ ልትባርከውም አይገባም” አለው። 26 በለዓምም መልሶ ባላቅን “‘እኔ የማደርገው ይሖዋ የሚናገረውን ብቻ ነው’ ብዬህ አልነበረም?” አለው።+

27 ባላቅም በለዓምን እንዲህ አለው፦ “እባክህ ና፤ እስቲ አሁንም ወደ ሌላ ቦታ ልውሰድህ። ምናልባትም እውነተኛው አምላክ እዚያ ሆነህ እሱን እንድትረግምልኝ ይፈቅድ ይሆናል።”+ 28 ስለዚህ ባላቅ በለዓምን፣ የሺሞንን* ፊት ለፊት ማየት ወደሚቻልበት ወደ ፌጎር አናት ወሰደው።+ 29 ከዚያም በለዓም ባላቅን “እዚህ ቦታ ላይ ሰባት መሠዊያዎች ሥራልኝ፤ እንዲሁም ሰባት በሬዎችና ሰባት አውራ በጎች አዘጋጅልኝ” አለው።+ 30 ባላቅም በለዓም እንዳለው አደረገ፤ ከዚያም በእያንዳንዱ መሠዊያ ላይ አንድ በሬና አንድ አውራ በግ አቀረበ።

24 በለዓምም ይሖዋ እስራኤልን መባረክ እንደወደደ* ሲያይ ዳግመኛ ድግምት ፍለጋ አልሄደም፤+ ከዚህ ይልቅ ፊቱን ወደ ምድረ በዳ አቀና። 2 በለዓም አሻግሮ ሲመለከት እስራኤል በየነገዱ እንደሰፈረ አየ፤+ ከዚያም የአምላክ መንፈስ በእሱ ላይ ወረደ።+ 3 በመሆኑም ይህን ምሳሌያዊ አባባል ተናገረ፦+

“የቢዖር ልጅ የበለዓም ቃል፣

ዓይኑ የተከፈተው የዚያ ሰው ቃል፣

 4 የአምላክን ቃል የሰማው፣

ሁሉን ቻይ የሆነውን አምላክ ራእይ ያየው

ዓይኖቹ ሳይከደኑ የሰገደው ሰው ቃል ይህ ነው፦+

 5 ያዕቆብ ሆይ፣ ድንኳኖችህ፣

እስራኤል ሆይ፣ የማደሪያ ድንኳኖችህ እንዴት ያማሩ ናቸው!+

 6 እንደ ሸለቆዎች፣*

በወንዝም ዳር እንዳሉ የአትክልት ስፍራዎች በረጅሙ ተዘርግተዋል።+

ይሖዋ እንደተከላቸው እሬቶች፣

በውኃም ዳር እንዳሉ አርዘ ሊባኖሶች ሆነዋል።

 7 ከሁለቱም አቁማዳዎቹ ውኃ ይንጠባጠባል፤

ዘሩም በብዙ ውኃዎች አጠገብ ተዘርቷል።+

ንጉሡም+ ከአጋግ+ የላቀ ይሆናል፤

መንግሥቱም ከፍ ከፍ ይላል።+

 8 አምላክ ከግብፅ አወጣው፤

ለእነሱ ልክ እንደ ጎሽ ቀንዶች ነው።

የሚጨቁኑትን ብሔራት ይበላል፤+

አጥንቶቻቸውንም ይቆረጣጥማል፤ በፍላጻዎቹም ያደቃቸዋል።

 9 አድብቷል፤ እንደ አንበሳም ተጋድሟል፤

እንደ አንበሳስ ማን ሊቀሰቅሰው ይደፍራል?

አንተን የሚባርኩህ የተባረኩ ናቸው፤

የሚረግሙህም የተረገሙ ናቸው።”+

10 በዚህ ጊዜ ባላቅ በበለዓም ላይ በጣም ተቆጣ። ባላቅም በንቀት እጆቹን አጨብጭቦ በለዓምን እንዲህ አለው፦ “የጠራሁህ ጠላቶቼን እንድትረግምልኝ ነበር፤+ አንተ ግን ይኸው ሦስቱንም ጊዜ ባረክሃቸው እንጂ ምንም የፈየድከው ነገር የለም። 11 በል አሁን ቶሎ ብለህ ወደ ቤትህ ሂድ። እኔ እንኳ ታላቅ ክብር ላጎናጽፍህ አስቤ ነበር፤+ ይሖዋ ግን ክብር ነፈገህ።”

12 በለዓምም ለባላቅ እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “ወደ እኔ ለላክሃቸው መልእክተኞች እንዲህ ብዬ ነገሬአቸው አልነበረም? 13 ‘ባላቅ በብርና በወርቅ የተሞላውን ቤቱን ቢሰጠኝ እንኳ ከይሖዋ ትእዛዝ ውጭ በገዛ ፈቃዴ* መልካምም ሆነ መጥፎ ነገር ማድረግ አልችልም። እኔ የምናገረው ይሖዋ የሚነግረኝን ብቻ ነው።’+ 14 እንግዲህ አሁን ወደ ሕዝቤ ልሄድ ነው። ይልቅስ መጥተህ ወደፊት* ይህ ሕዝብ በሕዝብህ ላይ የሚያደርገውን ልንገርህ።” 15 ስለዚህ ይህን ምሳሌያዊ አባባል ተናገረ፦+

“የቢዖር ልጅ የበለዓም ቃል፣

ዓይኑ የተከፈተው የዚያ ሰው ቃል፣+

16 የአምላክን ቃል የሰማው፣

የልዑሉን አምላክ እውቀት የሚያውቀው ሰው ቃል ይህ ነው፤

ዓይኖቹ ሳይከደኑ እየሰገደ ሳለ

ሁሉን ቻይ የሆነውን አምላክ ራእይ አየ፦

17 አየዋለሁ፣ አሁን ግን አይደለም፤

እመለከተዋለሁ፣ በቅርቡ ግን አይደለም።

ኮከብ+ ከያዕቆብ ይወጣል፤

በትረ መንግሥትም+ ከእስራኤል ይነሳል።+

የሞዓብን ግንባር፣*

የሁከት ልጆችንም ሁሉ ራስ ቅል ይፈረካክሳል።+

18 እስራኤል ጀግንነቱን ሲያሳይ

ኤዶም ርስቱ ይሆናል፤+

ሴይርም+ የጠላቶቹ ርስት ይሆናል።+

19 ከያዕቆብም አንዱ ድል እያደረገ ይወጣል፤+

የተረፉትንም የከተማዋን ነዋሪዎች ሁሉ ያጠፋል።”

20 አማሌቅንም ባየ ጊዜ እንዲህ ሲል ምሳሌያዊ አባባሉን መናገሩን ቀጠለ፦

“አማሌቅ ከብሔራት መካከል የመጀመሪያ ነበር፤+

ሆኖም በመጨረሻ ይጠፋል።”+

21 ቄናውያንንም+ ባየ ጊዜ እንዲህ ሲል ምሳሌያዊ አባባሉን መናገሩን ቀጠለ፦

“መኖሪያህ አስተማማኝ ነው፤ ጎጆህም በቋጥኝ ላይ የተሠራ ነው።

22 ሆኖም አንድ ሰው ቄይንን ያቃጥላታል።

አሦር ማርኮ እስኪወስዳችሁ ድረስ ምን ያህል ትቆዩ ይሆን?”

23 እሱም እንዲህ ሲል ምሳሌያዊ አባባሉን መናገሩን ቀጠለ፦

“አቤት! አምላክ ይህን በሚያደርግበት ጊዜ ማን ይተርፍ ይሆን?

24 ከኪቲም+ የባሕር ዳርቻ መርከቦች ይመጣሉ፤

አሦርንም ያጠቃሉ፤+

ደግሞም ኤቤርን ያሠቃያሉ።

ሆኖም እሱም ፈጽሞ ይጠፋል።”

25 ከዚያም በለዓም+ ተነስቶ ወደ ስፍራው ተመለሰ። ባላቅም መንገዱን ቀጠለ።

25 እስራኤላውያን በሺቲም+ ይኖሩ በነበረበት ጊዜ ሕዝቡ ከሞዓብ ሴቶች ጋር የፆታ ብልግና መፈጸም ጀመረ።+ 2 ሴቶቹም ለአማልክታቸው ወደተሠዉት መሥዋዕቶች ሕዝቡን ጠሩ፤+ ሕዝቡም ከመሥዋዕቱ መብላት እንዲሁም ለእነሱ አማልክት መስገድ ጀመረ።+ 3 ስለዚህ እስራኤል የፌጎርን ባአል በማምለክ ተባበረ፤*+ ይሖዋም በእስራኤል ላይ እጅግ ተቆጣ። 4 ይሖዋም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “እየነደደ ያለው የይሖዋ ቁጣ ከእስራኤል ላይ እንዲመለስ የዚህን ሕዝብ መሪዎች* ሁሉ ወስደህ በጠራራ ፀሐይ* በይሖዋ ፊት ስቀላቸው።” 5 ከዚያም ሙሴ የእስራኤልን ዳኞች+ “እያንዳንዳችሁ በፌጎር ባአል አምልኮ የተባበረውን* የየራሳችሁን ሰው ግደሉ” አላቸው።+

6 ሆኖም ልክ በዚህ ጊዜ አንድ እስራኤላዊ፣ ሙሴና በመገናኛ ድንኳኑ መግቢያ ላይ እያለቀሰ ያለው የእስራኤል ማኅበረሰብ በሙሉ እያዩት አንዲት ምድያማዊት ሴት+ ይዞ ወደ ወንድሞቹ መጣ። 7 የካህኑ የአሮን ልጅ፣ የአልዓዛር ልጅ ፊንሃስ+ ይህን ሲመለከት ከማኅበረሰቡ መሃል ወዲያው ብድግ ብሎ ጦር አነሳ። 8 ከዚያም እስራኤላዊውን ተከትሎ ወደ ድንኳኑ በመግባት ሁለቱንም ወጋቸው፤ እስራኤላዊውን ወጋው፤ እሷንም ሆዷ* ላይ ወጋት። በዚህ ጊዜ መቅሰፍቱ ከእስራኤል ልጆች ላይ ተወገደ።+ 9 በመቅሰፍቱ የሞቱት ሰዎች 24,000 ነበሩ።+

10 ከዚያም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ 11 “የካህኑ የአሮን ልጅ፣ የአልዓዛር ልጅ ፊንሃስ+ በመካከላቸው እኔን የሚቀናቀነኝን ማንኛውንም ነገር በቸልታ ባለማለፉ ቁጣዬ ከእስራኤል ሕዝብ ላይ እንዲመለስ አድርጓል።+ ስለዚህ እስራኤላውያንን እኔን ብቻ ለምን አላመለካችሁም ብዬ ጠራርጌ አላጠፋኋቸውም።+ 12 በዚህም የተነሳ ከእሱ ጋር የሰላም ቃል ኪዳን እንደምገባ ንገረው። 13 ይህም አምላኩን የሚቀናቀነውን ማንኛውንም ነገር በቸልታ ባለማለፉ+ እንዲሁም ለእስራኤል ሕዝብ በማስተሰረዩ ለእሱና ከእሱ በኋላ ለሚመጡት ዘሮቹ+ ዘላቂ የክህነት ቃል ኪዳን ሆኖ ያገለግላል።”

14 ከምድያማዊቷ ሴት ጋር የተገደለው ሟቹ እስራኤላዊ የስምዖናውያን አባቶች ቤት አለቃ የሆነው የሳሉ ልጅ ዚምሪ ነበር። 15 የተገደለችውም ምድያማዊት ሴት የጹር+ ልጅ ኮዝቢ ነበረች፤ ጹር በምድያም ካሉት የአባቶች ቤት ጎሳዎች የአንዱ መሪ ነበር።+

16 በኋላም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ 17 “ምድያማውያንን አንገላቷቸው፤ እንዲሁም ፍጇቸው፤+ 18 ምክንያቱም እነሱ ከፌጎርና+ ከእህታቸው ከኮዝቢ ጋር በተያያዘ በፈጸሙባችሁ ተንኮል የተነሳ አንገላተዋችኋል፤ ኮዝቢ ከፌጎር ጋር በተያያዘ የተከሰተው መቅሰፍት በመጣበት ዕለት+ የተገደለች የምድያማዊው አለቃ ልጅ ነች።”+

26 ከመቅሰፍቱ በኋላ+ ይሖዋ ሙሴንና የካህኑን የአሮንን ልጅ አልዓዛርን እንዲህ አላቸው፦ 2 “ከመላው የእስራኤል ማኅበረሰብ መካከል ዕድሜያቸው 20 ዓመትና ከዚያ በላይ የሆናቸውን በየአባቶቻቸው ቤት ቁጠሩ፤ በእስራኤል የጦር ሠራዊት ውስጥ ገብተው ማገልገል የሚችሉትን ሁሉ ቁጠሩ።”+ 3 በመሆኑም ሙሴና ካህኑ አልዓዛር+ ከኢያሪኮ ማዶ+ በዮርዳኖስ አጠገብ በሚገኘው የሞዓብ በረሃማ ሜዳ+ ላይ ለሕዝቡ እንዲህ ሲሉ ተናገሩ፦ 4 “ይሖዋ ሙሴን ባዘዘው መሠረት ዕድሜያቸው 20 ዓመትና ከዚያ በላይ የሆናቸውን ቁጠሩ።”+

ከግብፅ ምድር የወጡት የእስራኤል ልጆች የሚከተሉት ነበሩ፦ 5 የእስራኤል የበኩር ልጅ ሮቤል፤+ የሮቤል ልጆች+ እነዚህ ነበሩ፦ ከሃኖክ የሃኖካውያን ቤተሰብ፣ ከፓሉ የፓላውያን ቤተሰብ፣ 6 ከኤስሮን የኤስሮናውያን ቤተሰብ እንዲሁም ከካርሚ የካርማውያን ቤተሰብ። 7 የሮቤላውያን ቤተሰቦች እነዚህ ነበሩ፤ ከእነሱም መካከል የተመዘገቡት 43,730 ነበሩ።+

8 የፓሉ ልጅ ኤልያብ ነበር። 9 የኤልያብ ልጆች ደግሞ ነሙኤል፣ ዳታን እና አቤሮን ነበሩ። እዚህ ላይ የተጠቀሱት ዳታን እና አቤሮን ቆሬና ግብረ አበሮቹ+ በይሖዋ ላይ ባመፁበት ወቅት+ ከእነሱ ጋር በማበር በሙሴና በአሮን ላይ የተነሱ የማኅበረሰቡ ተወካዮች ነበሩ።+

10 ከዚያም ምድር አፏን ከፍታ ዋጠቻቸው። ቆሬም እሳት ወርዶ 250 ሰዎችን በበላ ጊዜ ከነግብረ አበሮቹ ሞተ።+ እነሱም የማስጠንቀቂያ ምሳሌ ሆኑ።+ 11 ይሁንና የቆሬ ልጆች አልሞቱም።+

12 የስምዖን ልጆች+ በየቤተሰባቸው እነዚህ ነበሩ፦ ከነሙኤል የነሙኤላውያን ቤተሰብ፣ ከያሚን የያሚናውያን ቤተሰብ፣ ከያኪን የያኪናውያን ቤተሰብ፣ 13 ከዛራ የዛራውያን ቤተሰብ እንዲሁም ከሻኡል የሻኡላውያን ቤተሰብ። 14 የስምዖናውያን ቤተሰቦች እነዚህ ሲሆኑ እነሱም 22,200 ነበሩ።+

15 የጋድ ልጆች+ በየቤተሰባቸው እነዚህ ነበሩ፦ ከጸፎን የጸፎናውያን ቤተሰብ፣ ከሃጊ የሃጋውያን ቤተሰብ፣ ከሹኒ የሹናውያን ቤተሰብ፣ 16 ከኦዝኒ የኦዝናውያን ቤተሰብ፣ ከኤሪ የኤራውያን ቤተሰብ፣ 17 ከአሮድ የአሮዳውያን ቤተሰብ እንዲሁም ከአርዔላይ የአርዔላውያን ቤተሰብ። 18 የጋድ ልጆች ቤተሰቦች እነዚህ ነበሩ፤ ከእነሱም መካከል የተመዘገቡት 40,500 ነበሩ።+

19 የይሁዳ ልጆች+ ኤር እና ኦናን ነበሩ።+ ሆኖም ኤር እና ኦናን በከነአን ምድር ሞቱ።+ 20 የይሁዳ ልጆች በየቤተሰባቸው እነዚህ ነበሩ፦ ከሴሎም+ የሴሎማውያን ቤተሰብ፣ ከፋሬስ+ የፋሬሳውያን ቤተሰብ እንዲሁም ከዛራ+ የዛራውያን ቤተሰብ። 21 የፋሬስ ልጆች እነዚህ ነበሩ፦ ከኤስሮን+ የኤስሮናውያን ቤተሰብ እንዲሁም ከሃሙል+ የሃሙላውያን ቤተሰብ። 22 የይሁዳ ቤተሰቦች እነዚህ ነበሩ፤ ከእነሱም መካከል የተመዘገቡት 76,500 ነበሩ።+

23 የይሳኮር ልጆች+ በየቤተሰባቸው እነዚህ ነበሩ፦ ከቶላ+ የቶላውያን ቤተሰብ፣ ከፑዋ የፑዋውያን ቤተሰብ፣ 24 ከያሹብ የያሹባውያን ቤተሰብ እንዲሁም ከሺምሮን የሺምሮናውያን ቤተሰብ። 25 የይሳኮር ቤተሰቦች እነዚህ ነበሩ፤ ከእነሱም መካከል የተመዘገቡት 64,300 ነበሩ።+

26 የዛብሎን ልጆች+ በየቤተሰባቸው እነዚህ ነበሩ፦ ከሰሬድ የሰሬዳውያን ቤተሰብ፣ ከኤሎን የኤሎናውያን ቤተሰብ እንዲሁም ከያህልኤል የያህልኤላውያን ቤተሰብ። 27 የዛብሎናውያን ቤተሰቦች እነዚህ ነበሩ፤ ከእነሱም መካከል የተመዘገቡት 60,500 ነበሩ።+

28 የዮሴፍ ልጆች+ በየቤተሰባቸው ምናሴና ኤፍሬም ነበሩ።+ 29 የምናሴ ልጆች+ እነዚህ ነበሩ፦ ከማኪር+ የማኪራውያን ቤተሰብ፤ ማኪር ጊልያድን ወለደ፤+ ከጊልያድ የጊልያዳውያን ቤተሰብ። 30 የጊልያድ ልጆች እነዚህ ነበሩ፦ ከኢዔዝር የኢዔዝራውያን ቤተሰብ፣ ከሄሌቅ የሄሌቃውያን ቤተሰብ፣ 31 ከአስሪዔል የአስሪዔላውያን ቤተሰብ፣ ከሴኬም የሴኬማውያን ቤተሰብ፣ 32 ከሸሚዳ የሸሚዳውያን ቤተሰብ እንዲሁም ከሄፌር የሄፌራውያን ቤተሰብ። 33 የሄፌር ልጅ ሰለጰአድ ሴቶች ልጆች ብቻ እንጂ ወንዶች ልጆች አልነበሩትም፤+ የሰለጰአድ ሴቶች ልጆች+ ስም ማህላ፣ ኖኅ፣ ሆግላ፣ ሚልካ እና ቲርጻ ነበር። 34 የምናሴ ቤተሰቦች እነዚህ ነበሩ፤ ከእነሱም መካከል የተመዘገቡት 52,700 ነበሩ።+

35 የኤፍሬም ልጆች+ በየቤተሰባቸው እነዚህ ነበሩ፦ ከሹተላ+ የሹተላውያን ቤተሰብ፣ ከቤኬር የቤኬራውያን ቤተሰብ እንዲሁም ከታሃን የታሃናውያን ቤተሰብ። 36 የሹተላ ልጆች እነዚህ ነበሩ፦ ከኤራን የኤራናውያን ቤተሰብ። 37 የኤፍሬም ቤተሰቦች እነዚህ ነበሩ፤ ከእነሱም መካከል የተመዘገቡት 32,500 ነበሩ።+ የዮሴፍ ልጆች በየቤተሰባቸው እነዚህ ነበሩ።

38 የቢንያም ልጆች+ በየቤተሰባቸው እነዚህ ነበሩ፦ ከቤላ+ የቤላውያን ቤተሰብ፣ ከአሽቤል የአሽቤላውያን ቤተሰብ፣ ከአሂራም የአሂራማውያን ቤተሰብ፣ 39 ከሼፉፋም የሼፉፋማውያን ቤተሰብ እንዲሁም ከሁፋም የሁፋማውያን ቤተሰብ። 40 የቤላ ልጆች አርድ እና ንዕማን ነበሩ፤+ ከአርድ የአርዳውያን ቤተሰብ፣ ከንዕማን ደግሞ የንዕማናውያን ቤተሰብ። 41 የቢንያም ልጆች በየቤተሰባቸው እነዚህ ነበሩ፤ ከእነሱም መካከል የተመዘገቡት 45,600 ነበሩ።+

42 የዳን ልጆች+ በየቤተሰባቸው እነዚህ ነበሩ፦ ከሹሃም የሹሃማውያን ቤተሰብ። የዳን ቤተሰቦች በየቤተሰባቸው እነዚህ ነበሩ። 43 ከሹሃማውያን ቤተሰቦች በሙሉ የተመዘገቡት 64,400 ነበሩ።+

44 የአሴር ልጆች+ በየቤተሰባቸው እነዚህ ነበሩ፦ ከይምናህ የይምናሃውያን ቤተሰብ፣ ከይሽዊ የይሽዋውያን ቤተሰብ፣ ከበሪአ የበሪአውያን ቤተሰብ፤ 45 ከበሪአ ልጆች፦ ከሄቤር የሄቤራውያን ቤተሰብ እንዲሁም ከማልኪኤል የማልኪኤላውያን ቤተሰብ። 46 የአሴር ሴት ልጅ ስም ሴራህ ነበር። 47 የአሴር ልጆች ቤተሰቦች እነዚህ ነበሩ፤ ከእነሱም መካከል የተመዘገቡት 53,400 ነበሩ።+

48 የንፍታሌም ልጆች+ በየቤተሰባቸው እነዚህ ነበሩ፦ ከያህጽኤል የያህጽኤላውያን ቤተሰብ፣ ከጉኒ የጉናውያን ቤተሰብ፣ 49 ከየጼር የየጼራውያን ቤተሰብ እንዲሁም ከሺሌም የሺሌማውያን ቤተሰብ። 50 የንፍታሌም ቤተሰቦች በየቤተሰባቸው እነዚህ ነበሩ፤ ከእነሱም መካከል የተመዘገቡት 45,400 ነበሩ።+

51 ከእስራኤላውያን መካከል የተመዘገቡት በጠቅላላ 601,730 ነበሩ።+

52 ከዚህ በኋላ ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ 53  “ምድሪቱ ለእነዚህ በስማቸው ዝርዝር መሠረት ርስት ሆና ትከፋፈል።+ 54 ተለቅ ላሉት ቡድኖች በዛ ያለ ውርሻ ትሰጣቸዋለህ፤ አነስ ላሉት ቡድኖች ደግሞ አነስ ያለ ውርሻ ትሰጣቸዋለህ።+ የእያንዳንዱ ቡድን ውርሻ በተመዘገቡት ሰዎች ብዛት ተመጣጥኖ መሰጠት አለበት። 55 ይሁን እንጂ ምድሪቱ መከፋፈል ያለባት በዕጣ ነው።+ ውርሻቸውንም ማግኘት ያለባቸው በአባቶቻቸው ነገዶች ስም መሠረት ነው። 56 እያንዳንዱ ውርሻ የሚወሰነው በዕጣ ሲሆን በኋላም ውርሻው እንደ ቡድኑ ትልቅነትና ትንሽነት ይከፋፈላል።”

57  ከሌዋውያኑ መካከል በየቤተሰባቸው የተመዘገቡት እነዚህ ነበሩ፦+ ከጌድሶን የጌድሶናውያን ቤተሰብ፣ ከቀአት+ የቀአታውያን ቤተሰብ እንዲሁም ከሜራሪ የሜራራውያን ቤተሰብ። 58 የሌዋውያን ቤተሰቦች እነዚህ ነበሩ፦ የሊብናውያን ቤተሰብ፣+ የኬብሮናውያን ቤተሰብ፣+ የማህላውያን ቤተሰብ፣+ የሙሻውያን ቤተሰብ+ እና የቆሬያውያን ቤተሰብ።+

ቀአት አምራምን ወለደ።+ 59 የአምራም ሚስት ስሟ ዮካቤድ ነበር፤+ እሷም የሌዊ ሚስት በግብፅ ለሌዊ የወለደችለት ናት። ዮካቤድም ለአምራም አሮንን፣ ሙሴንና እህታቸውን ሚርያምን ወለደችለት።+ 60 አሮንም ናዳብን፣ አቢሁን፣ አልዓዛርን እና ኢታምርን ወለደ።+ 61 ሆኖም ናዳብና አቢሁ በይሖዋ ፊት ያልተፈቀደ እሳት በማቅረባቸው ሞቱ።+

62 አንድ ወርና ከዚያ በላይ ሆኗቸው የተመዘገቡት ወንዶች በአጠቃላይ 23,000 ነበሩ።+ እነዚህ በእስራኤላውያን መካከል ርስት ስለማይሰጣቸው+ ከእስራኤላውያን ጋር አልተመዘገቡም።+

63 እነዚህም ሙሴና ካህኑ አልዓዛር ከኢያሪኮ ማዶ በዮርዳኖስ አጠገብ በሚገኘው የሞዓብ በረሃማ ሜዳ ላይ እስራኤላውያንን በመዘገቡበት ወቅት የመዘገቧቸው ናቸው። 64 ሆኖም ከእነዚህ መካከል ሙሴና ካህኑ አሮን እስራኤላውያንን በሲና ምድረ በዳ በቆጠሩበት ወቅት ተመዝግቦ የነበረ አንድም ሰው አልነበረም።+ 65 ምክንያቱም ይሖዋ እነሱን በተመለከተ “በእርግጥ በምድረ በዳው ላይ ያልቃሉ”+ በማለት ተናግሮ ነበር። በመሆኑም ከየፎኒ ልጅ ከካሌብና ከነዌ ልጅ ከኢያሱ በስተቀር አንድም የተረፈ ሰው አልነበረም።+

27 ከዮሴፍ ልጅ ከምናሴ ቤተሰቦች የምናሴ ልጅ፣ የማኪር ልጅ፣ የጊልያድ ልጅ፣ የሄፌር ልጅ የሆነው የሰለጰአድ ሴቶች ልጆች+ ቀረቡ። የሴት ልጆቹም ስም ማህላ፣ ኖኅ፣ ሆግላ፣ ሚልካ እና ቲርጻ ነበር። 2 እነሱም በመገናኛ ድንኳኑ መግቢያ በሙሴ፣ በካህኑ በአልዓዛር፣ በአለቆቹ+ እንዲሁም በመላው ማኅበረሰብ ፊት ቆመው እንዲህ አሉ፦ 3 “አባታችን በምድረ በዳ ሞተ፤ ይሁንና እሱ በይሖዋ ላይ ለማመፅ ከተባበሩት ከቆሬ ግብረ አበሮች+ አንዱ አልነበረም፤ እሱ የሞተው በራሱ ኃጢአት ነው፤ ወንዶች ልጆችም አልነበሩትም። 4 ታዲያ አባታችን ወንድ ልጅ ስለሌለው ብቻ ስሙ ከቤተሰቡ መካከል ለምን ይጥፋ? በአባታችን ወንድሞች መካከል ርስት ስጡን።” 5 ስለዚህ ሙሴ ጉዳያቸውን በይሖዋ ፊት አቀረበ።+

6 ከዚያም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ 7 “የሰለጰአድ ሴቶች ልጆች ትክክል ናቸው። በአባታቸው ወንድሞች መካከል ርስታቸውን ውርስ አድርገህ ልትሰጣቸው ይገባል፤ የአባታቸውም ውርስ ለእነሱ እንዲተላለፍ ማድረግ አለብህ።+ 8 እስራኤላውያንንም እንዲህ በላቸው፦ ‘አንድ ሰው ወንድ ልጅ ሳይወልድ ቢሞት ውርሱ ለሴት ልጆቹ እንዲተላለፍ ማድረግ አለባችሁ። 9 ሴት ልጅ ከሌለው ደግሞ ውርሱን ለወንድሞቹ ትሰጣላችሁ። 10 ወንድሞች ከሌሉት ውርሱን ለአባቱ ወንድሞች ትሰጣላችሁ። 11 አባቱ ወንድሞች ከሌሉት ውርሱን ከቤተሰቡ መካከል ቅርብ ለሆነው የሥጋ ዘመዱ ትሰጣላችሁ፤ እሱም ርስት አድርጎ ይወስደዋል። ይህም ይሖዋ ሙሴን ባዘዘው መሠረት ለእስራኤላውያን የተደነገገ ደንብ ሆኖ ያገለግላል።’”

12 ከዚያም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ወደዚህ ወደ አባሪም ተራራ+ ውጣና ለእስራኤላውያን የምሰጠውን ምድር ተመልከት።+ 13 ካየኸውም በኋላ እንደ ወንድምህ እንደ አሮን+ አንተም ወደ ወገኖችህ ትሰበሰባለህ፤*+ 14 ምክንያቱም ማኅበረሰቡ በጺን ምድረ በዳ ከእኔ ጋር በተጣላ ጊዜ ከውኃዎቹ ጋር በተያያዘ በፊታቸው ሳትቀድሱኝ በመቅረታችሁ ትእዛዜን ተላልፋችኋል።+ እነዚህም በጺን ምድረ በዳ+ በቃዴስ+ የሚገኙት የመሪባ ውኃዎች+ ናቸው።”

15 ከዚያም ሙሴ ይሖዋን እንዲህ አለው፦ 16 “የሰው* ሁሉ መንፈስ አምላክ የሆነው ይሖዋ በማኅበረሰቡ ላይ አንድ ሰው ይሹም፤ 17 እሱም የይሖዋ ማኅበረሰብ እረኛ እንደሌላቸው በጎች እንዳይሆን በፊታቸው የሚወጣና የሚገባ እንዲሁም እነሱን መርቶ የሚያወጣና የሚያስገባ ይሆናል።” 18 በመሆኑም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ “መንፈስ ያለበትን የነዌን ልጅ ኢያሱን ወስደህ እጅህን ጫንበት።+ 19 ከዚያም በካህኑ በአልዓዛርና በመላው ማኅበረሰብ ፊት አቁመው፤ በፊታቸውም ሹመው።+ 20 መላው የእስራኤል ማኅበረሰብ እንዲሰማውም+ ከሥልጣንህ* የተወሰነውን ስጠው።+ 21 እሱም በኡሪም+ አማካኝነት የይሖዋን ፍርድ በሚጠይቅለት በካህኑ በአልዓዛር ፊት ይቆማል። እሱም ሆነ ከእሱ ጋር ያሉት እስራኤላውያን እንዲሁም መላው ማኅበረሰብ በእሱ ትእዛዝ ይወጣሉ፤ በእሱ ትእዛዝ ይገባሉ።”

22 በመሆኑም ሙሴ ልክ ይሖዋ እንዳዘዘው አደረገ። ኢያሱንም ወስዶ በካህኑ በአልዓዛርና በመላው ማኅበረሰብ ፊት አቆመው፤ 23 ይሖዋ በሙሴ አማካኝነት በተናገረውም መሠረት+ እጆቹን በእሱ ላይ በመጫን ሾመው።+

28 በመቀጠልም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ 2 “እስራኤላውያንን እዘዛቸው፤ እንዲህም በላቸው፦ ‘ምግቤን ይኸውም መባዬን ለእኔ ማቅረባችሁን እንዳትዘነጉ። ደስ የሚያሰኝ* መዓዛ እንዲሰጡ በእሳት የሚቀርቡት መባዎቼ በተወሰነላቸው ጊዜ መቅረብ አለባቸው።’+

3 “እንዲህም በላቸው፦ ‘ለይሖዋ የምታቀርቡት በእሳት የሚቃጠል መባ ይህ ነው፦ በየቀኑ፣ አንድ ዓመት የሆናቸው እንከን የሌለባቸው ሁለት ተባዕት የበግ ጠቦቶችን የሚቃጠል መባ አድርጋችሁ ዘወትር አቅርቡ።+ 4 አንደኛውን ተባዕት የበግ ጠቦት ጠዋት ላይ፣ ሌላኛውን ተባዕት የበግ ጠቦት ደግሞ አመሻሹ ላይ* አቅርቡ፤+ 5 ከእነዚህም ጋር ተጨቅጭቆ በተጠለለ አንድ አራተኛ ሂን* ዘይት የተለወሰ አንድ አሥረኛ ኢፍ* የላመ ዱቄት የእህል መባ አድርጋችሁ አቅርቡ።+ 6 ይህም በሲና ተራራ ላይ በወጣው ደንብ መሠረት ደስ የሚያሰኝ* መዓዛ ያለው ዘወትር የሚቀርብ የሚቃጠል መባ+ ይኸውም ለይሖዋ በእሳት የሚቀርብ መባ ነው፤ 7 ከዚህም ጋር የመጠጥ መባውን ይኸውም ለእያንዳንዱ ተባዕት የበግ ጠቦት አንድ አራተኛ ሂን አቅርቡ።+ የሚያሰክረውን መጠጥ ለይሖዋ እንደሚቀርብ የመጠጥ መባ አድርጋችሁ በቅዱሱ ስፍራ አፍሱት። 8 ሌላኛውን ተባዕት የበግ ጠቦት ደግሞ አመሻሹ ላይ* አቅርቡት። ከእሱም ጋር ማለዳ ላይ የሚቀርበውን ዓይነት የእህል መባና ከእሱ ጋር አብሮ የሚቀርበውን ዓይነት የመጠጥ መባ ይሖዋን ደስ የሚያሰኝ* መዓዛ ያለው በእሳት የሚቃጠል መባ አድርጋችሁ ታቀርባላችሁ።+

9 “‘ይሁንና በሰንበት ቀን፣+ አንድ ዓመት የሆናቸውን እንከን የሌለባቸው ሁለት ተባዕት የበግ ጠቦቶች እንዲሁም በዘይት የተለወሰ ሁለት አሥረኛ የኢፍ መስፈሪያ የላመ ዱቄት የእህል መባ አድርጋችሁ ከመጠጥ መባው ጋር ታቀርባላችሁ። 10 ይህ ዘወትር ከሚቀርበው የሚቃጠል መባና ከመጠጥ መባው ጋር በየሰንበቱ የሚቀርብ የሚቃጠል መባ ነው።+

11 “‘በየወሩም* መባቻ ላይ ሁለት ወይፈኖች፣ አንድ አውራ በግ እንዲሁም እያንዳንዳቸው አንድ ዓመት የሆናቸው እንከን የሌለባቸው ሰባት ተባዕት የበግ ጠቦቶች ለይሖዋ የሚቃጠል መባ አድርጋችሁ ታቀርባላችሁ፤+ 12 ለእያንዳንዱ ወይፈን ሦስት አሥረኛ መስፈሪያ በዘይት የተለወሰ የላመ ዱቄት የእህል መባ+ አድርጋችሁ ታቀርባላችሁ፤ ለአውራው በግ ደግሞ ሁለት አሥረኛ መስፈሪያ በዘይት የተለወሰ የላመ ዱቄት የእህል መባ አድርጋችሁ ታቀርባላችሁ፤+ 13 ለእያንዳንዱም ተባዕት የበግ ጠቦት አንድ አሥረኛ መስፈሪያ በዘይት የተለወሰ የላመ ዱቄት የእህል መባ ይኸውም ደስ የሚያሰኝ* መዓዛ ያለው ለይሖዋ በእሳት የሚቀርብ የሚቃጠል መባ+ አድርጋችሁ ታቀርባላችሁ። 14 በተጨማሪም ከእነዚህ ጋር ለአንድ ወይፈን ግማሽ ሂን፣+ ለአውራው በግ አንድ ሦስተኛ ሂን+ እንዲሁም ለአንድ ተባዕት የበግ ጠቦት አንድ አራተኛ ሂን+ የወይን ጠጅ የመጠጥ መባ አድርጋችሁ አቅርቡ። ይህም ዓመቱን ሙሉ በየወሩ የሚቀርብ ወርሃዊ የሚቃጠል መባ ነው። 15 እንዲሁም ከዘወትሩ የሚቃጠል መባና አብሮት ከሚቀርበው የመጠጥ መባ በተጨማሪ አንድ የፍየል ጠቦት የኃጢአት መባ ሆኖ ለይሖዋ መቅረብ አለበት።

16 “‘በመጀመሪያው ወር ከወሩም በ14ኛው ቀን የይሖዋ ፋሲካ ይከበራል።+ 17 በዚሁ ወር በ15ኛው ቀን በዓል ይሆናል። ለሰባት ቀን ቂጣ ይበላል።+ 18 በመጀመሪያው ቀን ቅዱስ ጉባኤ ይሆናል። ምንም ዓይነት ከባድ ሥራ መሥራት የለባችሁም። 19 ሁለት ወይፈኖች፣ አንድ አውራ በግና እያንዳንዳቸው አንድ ዓመት የሆናቸው ሰባት ተባዕት የበግ ጠቦቶች ለይሖዋ በእሳት የሚቀርብ የሚቃጠል መባ አድርጋችሁ ታቀርባላችሁ። እንከን የሌለባቸውን እንስሳት ማቅረብ አለባችሁ።+ 20 ከእነዚህም ጋር ለአንድ ወይፈን ሦስት አሥረኛ መስፈሪያ፣ ለአውራው በግ ደግሞ ሁለት አሥረኛ መስፈሪያ በዘይት የተለወሰ የላመ ዱቄት የእህል መባ+ አድርጋችሁ አቅርቡ። 21 ለሰባቱ ተባዕት የበግ ጠቦቶች ለእያንዳንዳቸው አንድ አሥረኛ መስፈሪያ ታቀርባላችሁ፤ 22 እንዲሁም ለእናንተ ማስተሰረያ እንዲሆን አንድ ፍየል የኃጢአት መባ አድርጋችሁ አቅርቡ። 23 ለዘወትሩ የሚቃጠል መባ እንዲሆን ጠዋት ላይ ከሚቀርበው የሚቃጠል መባ በተጨማሪ እነዚህን ታቀርባላችሁ። 24 እነዚህንም በተመሳሳይ መንገድ በየቀኑ ለሰባት ቀን እንደ ምግብ፣ ይሖዋን ደስ የሚያሰኝ* መዓዛ እንዳለው በእሳት የሚቀርብ መባ አድርጋችሁ ታቀርባላችሁ። ይህም ከዘወትሩ የሚቃጠል መባና ከመጠጥ መባው ጋር ይቅረብ። 25 በሰባተኛው ቀን ቅዱስ ጉባኤ አድርጉ።+ ምንም ዓይነት ከባድ ሥራ መሥራት የለባችሁም።+

26 “‘መጀመሪያ የሚደርሰው ፍሬ በሚሰበሰብበት ቀን+ ለይሖዋ አዲስ የእህል መባ ስታቀርቡ+ በሳምንታት በዓላችሁ ላይ ቅዱስ ጉባኤ አድርጉ።+ ምንም ዓይነት ከባድ ሥራ መሥራት የለባችሁም።+ 27 ሁለት ወይፈኖች፣ አንድ አውራ በግ እንዲሁም እያንዳንዳቸው አንድ ዓመት የሆናቸው ሰባት ተባዕት የበግ ጠቦቶች ይሖዋን ደስ የሚያሰኝ* መዓዛ ያለው የሚቃጠል መባ አድርጋችሁ ታቀርባላችሁ፤+ 28 ከእነዚህም ጋር ለእያንዳንዱ ወይፈን ሦስት አሥረኛ መስፈሪያ፣ ለአውራው በግ ደግሞ ሁለት አሥረኛ መስፈሪያ በዘይት የተለወሰ የላመ ዱቄት የእህል መባ አድርጋችሁ ታቀርባላችሁ፤ 29 እንዲሁም ለሰባቱ ተባዕት የበግ ጠቦቶች ለእያንዳንዳቸው አንድ አሥረኛ መስፈሪያ በዘይት የተለወሰ የላመ ዱቄት ታቀርባላችሁ፤ 30 በተጨማሪም ለእናንተ ማስተሰረያ እንዲሆን አንድ የፍየል ጠቦት ታቀርባላችሁ።+ 31 ከዘወትሩ የሚቃጠል መባና ከእህል መባው በተጨማሪ እነዚህን ታቀርባላችሁ። እንስሳቱም እንከን የሌለባቸው መሆን አለባቸው፤+ ከመጠጥ መባቸውም ጋር መቅረብ ይኖርባቸዋል።

29 “‘በሰባተኛው ወር ከወሩም በመጀመሪያው ቀን ቅዱስ ጉባኤ አድርጉ። ምንም ዓይነት ከባድ ሥራ መሥራት የለባችሁም።+ ይህም መለከት የምትነፉበት ቀን ነው።+ 2 እናንተም አንድ ወይፈን፣ አንድ አውራ በግ እንዲሁም እያንዳንዳቸው አንድ ዓመት የሆናቸው ሰባት ተባዕት የበግ ጠቦቶች ይሖዋን ደስ የሚያሰኝ* መዓዛ ያለው የሚቃጠል መባ አድርጋችሁ ታቀርባላችሁ፤ ሁሉም እንከን የሌለባቸው መሆን ይኖርባቸዋል፤ 3 ከእነዚህም ጋር ለወይፈኑ ሦስት አሥረኛ የኢፍ መስፈሪያ፣ ለአውራው በግ ደግሞ ሁለት አሥረኛ መስፈሪያ በዘይት የተለወሰ የላመ ዱቄት የእህል መባ አድርጋችሁ ታቀርባላችሁ፤ 4 ለሰባቱ ተባዕት የበግ ጠቦቶች ለእያንዳንዳቸው አንድ አሥረኛ መስፈሪያ በዘይት የተለወሰ የላመ ዱቄት ታቀርባላችሁ፤ 5 እንዲሁም ለእናንተ ማስተሰረያ እንዲሆን አንድ ተባዕት የፍየል ጠቦት የኃጢአት መባ አድርጋችሁ ታቀርባላችሁ። 6 ይህም በተለመደው አሠራር መሠረት ከሚቀርቡት ከወርሃዊው የሚቃጠል መባና አብሮት ከሚቀርበው የእህል መባ፣+ ከዘወትሩ የሚቃጠል መባና አብሮት ከሚቀርበው የእህል መባ+ እንዲሁም ከመጠጥ መባዎቻቸው+ በተጨማሪ ደስ የሚያሰኝ* መዓዛ ያለው ለይሖዋ በእሳት የሚቀርብ መባ ነው።

7 “‘በዚሁ በሰባተኛው ወር በአሥረኛው ቀን ቅዱስ ጉባኤ አድርጉ፤+ ራሳችሁን አጎሳቁሉ።* ምንም ዓይነት ሥራ አትሥሩ።+ 8 አንድ ወይፈን፣ አንድ አውራ በግ እንዲሁም እያንዳንዳቸው አንድ ዓመት የሆናቸው ሰባት ተባዕት የበግ ጠቦቶች ደስ የሚያሰኝ* መዓዛ ያለው ለይሖዋ የሚቃጠል መባ አድርጋችሁ ታቀርባላችሁ፤ ሁሉም እንከን የሌለባቸው መሆን ይኖርባቸዋል።+ 9 ከእነዚህም ጋር ለወይፈኑ ሦስት አሥረኛ መስፈሪያ፣ ለአውራው በግ ደግሞ ሁለት አሥረኛ መስፈሪያ በዘይት የተለወሰ የላመ ዱቄት የእህል መባ አድርጋችሁ ታቀርባላችሁ፤ 10 እንዲሁም ለሰባቱ ተባዕት የበግ ጠቦቶች ለእያንዳንዳቸው አንድ አሥረኛ መስፈሪያ በዘይት የተለወሰ የላመ ዱቄት ታቀርባላችሁ፤ 11 ለማስተሰረያ ከሚሆነው የኃጢአት መባ፣+ ከዘወትሩ የሚቃጠል መባና አብሮት ከሚቀርበው የእህል መባ እንዲሁም ከመጠጥ መባዎቻቸው በተጨማሪ አንድ የፍየል ጠቦት የኃጢአት መባ አድርጋችሁ ታቀርባላችሁ።

12 “‘በሰባተኛው ወር በ15ኛው ቀን ቅዱስ ጉባኤ አድርጉ። ምንም ዓይነት ከባድ ሥራ አትሥሩ፤ ለሰባት ቀንም ለይሖዋ በዓል አክብሩ።+ 13 እንዲሁም 13 ወይፈኖች፣ 2 አውራ በጎችና እያንዳንዳቸው አንድ ዓመት የሆናቸው 14 ተባዕት የበግ ጠቦቶች የሚቃጠል መባ+ ይኸውም ይሖዋን ደስ የሚያሰኝ* መዓዛ ያለው በእሳት የሚቀርብ መባ አድርጋችሁ አቅርቡ፤ ሁሉም እንከን የሌለባቸው መሆን ይኖርባቸዋል።+ 14 ከእነዚህም ጋር ለ13ቱ ወይፈኖች ለእያንዳንዳቸው ሦስት አሥረኛ መስፈሪያ፣ ለ2ቱ አውራ በጎች ደግሞ ለእያንዳንዳቸው ሁለት አሥረኛ መስፈሪያ በዘይት የተለወሰ የላመ ዱቄት የእህል መባ አድርጋችሁ አቅርቡ፤ 15 እንዲሁም ለ14ቱ ተባዕት የበግ ጠቦቶች ለእያንዳንዳቸው አንድ አሥረኛ መስፈሪያ በዘይት የተለወሰ የላመ ዱቄት አቅርቡ፤ 16 ከዘወትሩ የሚቃጠል መባ እንዲሁም አብሮት ከሚቀርበው የእህል መባና የመጠጥ መባ በተጨማሪ አንድ የፍየል ጠቦት የኃጢአት መባ አድርጋችሁ አቅርቡ።+

17 “‘በሁለተኛው ቀን 12 ወይፈኖች፣ 2 አውራ በጎች እንዲሁም እያንዳንዳቸው አንድ ዓመት የሆናቸው 14 ተባዕት የበግ ጠቦቶች አቅርቡ፤ ሁሉም እንከን የሌለባቸው መሆን ይኖርባቸዋል፤+ 18 ለወይፈኖቹ፣ ለአውራ በጎቹና ለተባዕት የበግ ጠቦቶቹ በተለመደው አሠራር መሠረት በቁጥራቸው ልክ የእህል መባቸውንና የመጠጥ መባዎቻቸውን አቅርቡ፤ 19 ከዘወትሩ የሚቃጠል መባና አብሮት ከሚቀርበው የእህል መባ እንዲሁም ከመጠጥ መባዎቻቸው በተጨማሪ አንድ የፍየል ጠቦት የኃጢአት መባ አድርጋችሁ አቅርቡ።+

20 “‘በሦስተኛው ቀን 11 ወይፈኖች፣ 2 አውራ በጎች እንዲሁም እያንዳንዳቸው አንድ ዓመት የሆናቸው 14 ተባዕት የበግ ጠቦቶች አቅርቡ፤ ሁሉም እንከን የሌለባቸው መሆን ይኖርባቸዋል፤+ 21 ለወይፈኖቹ፣ ለአውራ በጎቹና ለተባዕት የበግ ጠቦቶቹ በተለመደው አሠራር መሠረት በቁጥራቸው ልክ የእህል መባቸውንና የመጠጥ መባዎቻቸውን አቅርቡ፤ 22 ከዘወትሩ የሚቃጠል መባ እንዲሁም አብሮት ከሚቀርበው የእህል መባና የመጠጥ መባ በተጨማሪ አንድ ፍየል የኃጢአት መባ አድርጋችሁ አቅርቡ።+

23 “‘በአራተኛው ቀን 10 ወይፈኖች፣ 2 አውራ በጎች እንዲሁም እያንዳንዳቸው አንድ ዓመት የሆናቸው 14 ተባዕት የበግ ጠቦቶች አቅርቡ፤ ሁሉም እንከን የሌለባቸው መሆን ይኖርባቸዋል፤+ 24 ለወይፈኖቹ፣ ለአውራ በጎቹና ለተባዕት የበግ ጠቦቶቹ በተለመደው አሠራር መሠረት በቁጥራቸው ልክ የእህል መባቸውንና የመጠጥ መባዎቻቸውን አቅርቡ፤ 25 ከዘወትሩ የሚቃጠል መባ እንዲሁም አብሮት ከሚቀርበው የእህል መባና የመጠጥ መባ በተጨማሪ አንድ የፍየል ጠቦት የኃጢአት መባ አድርጋችሁ አቅርቡ።+

26 “‘በአምስተኛው ቀን 9 ወይፈኖች፣ 2 አውራ በጎች እንዲሁም እያንዳንዳቸው አንድ ዓመት የሆናቸው 14 ተባዕት የበግ ጠቦቶች አቅርቡ፤ ሁሉም እንከን የሌለባቸው መሆን ይኖርባቸዋል፤+ 27 ለወይፈኖቹ፣ ለአውራ በጎቹና ለተባዕት የበግ ጠቦቶቹ በተለመደው አሠራር መሠረት በቁጥራቸው ልክ የእህል መባቸውንና የመጠጥ መባዎቻቸውን አቅርቡ፤ 28 ከዘወትሩ የሚቃጠል መባ እንዲሁም አብሮት ከሚቀርበው የእህል መባና የመጠጥ መባ በተጨማሪ አንድ ፍየል የኃጢአት መባ አድርጋችሁ አቅርቡ።+

29 “‘በስድስተኛውም ቀን 8 ወይፈኖች፣ 2 አውራ በጎች እንዲሁም እያንዳንዳቸው አንድ ዓመት የሆናቸው 14 ተባዕት የበግ ጠቦቶች አቅርቡ፤ ሁሉም እንከን የሌለባቸው መሆን ይኖርባቸዋል፤+ 30 ለወይፈኖቹ፣ ለአውራ በጎቹና ለተባዕት የበግ ጠቦቶቹ በተለመደው አሠራር መሠረት በቁጥራቸው ልክ የእህል መባቸውንና የመጠጥ መባዎቻቸውን አቅርቡ፤ 31 ከዘወትሩ የሚቃጠል መባ እንዲሁም አብረውት ከሚቀርቡት የእህል መባና የመጠጥ መባዎች በተጨማሪ አንድ ፍየል የኃጢአት መባ አድርጋችሁ አቅርቡ።+

32 “‘በሰባተኛው ቀን 7 ወይፈኖች፣ 2 አውራ በጎች እንዲሁም እያንዳንዳቸው አንድ ዓመት የሆናቸው 14 ተባዕት የበግ ጠቦቶች አቅርቡ፤ ሁሉም እንከን የሌለባቸው መሆን ይኖርባቸዋል፤+ 33 ለወይፈኖቹ፣ ለአውራ በጎቹና ለተባዕት የበግ ጠቦቶቹ በተለመደው አሠራር መሠረት በቁጥራቸው ልክ የእህል መባቸውንና የመጠጥ መባዎቻቸውን አቅርቡ፤ 34 ከዘወትሩ የሚቃጠል መባ እንዲሁም አብሮት ከሚቀርበው የእህል መባና የመጠጥ መባ በተጨማሪ አንድ ፍየል የኃጢአት መባ አድርጋችሁ አቅርቡ።+

35 “‘በስምንተኛው ቀን የተቀደሰ ጉባኤ አድርጉ። ምንም ዓይነት ከባድ ሥራ መሥራት የለባችሁም።+ 36 አንድ ወይፈን፣ አንድ አውራ በግ እንዲሁም እያንዳንዳቸው አንድ ዓመት የሆናቸው ሰባት ተባዕት የበግ ጠቦቶች የሚቃጠል መባ ይኸውም ይሖዋን ደስ የሚያሰኝ* መዓዛ ያለው በእሳት የሚቀርብ መባ አድርጋችሁ ታቀርባላችሁ፤ ሁሉም እንከን የሌለባቸው መሆን ይኖርባቸዋል፤+ 37 ለወይፈኑ፣ ለአውራው በግና ለተባዕት የበግ ጠቦቶቹ በተለመደው አሠራር መሠረት በቁጥራቸው ልክ የእህል መባቸውንና የመጠጥ መባዎቻቸውን አቅርቡ፤ 38 ከዘወትሩ የሚቃጠል መባ እንዲሁም አብሮት ከሚቀርበው የእህል መባና የመጠጥ መባ በተጨማሪ አንድ ፍየል የኃጢአት መባ አድርጋችሁ አቅርቡ።+

39 “‘እነዚህም የሚቃጠሉ መባዎች፣+ የእህል መባዎች፣+ የመጠጥ መባዎችና+ የኅብረት መሥዋዕቶች+ አድርጋችሁ ከምታቀርቧቸው የስእለት መባዎችና+ የፈቃደኝነት መባዎች+ በተጨማሪ በየወቅቱ በምታከብሯቸው በዓላት+ ላይ ለይሖዋ የምታቀርቧቸው ናቸው።’” 40 ሙሴም ይሖዋ ያዘዘውን ነገር በሙሉ ለእስራኤላውያን ነገራቸው።

30 ከዚያም ሙሴ የእስራኤላውያን የነገድ መሪዎችን+ እንዲህ አላቸው፦ “ይሖዋ የሰጠው ትእዛዝ ይህ ነው፦ 2 አንድ ሰው ለይሖዋ ስእለት ቢሳል+ ወይም ከአንድ ነገር ለመታቀብ በመሐላ ራሱን* ግዴታ ውስጥ ቢያስገባ+ ቃሉን ማጠፍ የለበትም።+ አደርገዋለሁ ብሎ የማለውን ነገር ሁሉ መፈጸም አለበት።+

3 “በአባቷ ቤት የምትኖር አንዲት ወጣት ለይሖዋ ስእለት ብትሳል ወይም ከአንድ ነገር ለመታቀብ ራሷን በመሐላ ግዴታ ውስጥ ብታስገባ 4 አባቷ ስእለት መሳሏን ወይም ከአንድ ነገር ለመታቀብ ራሷን* በመሐላ ግዴታ ውስጥ ማስገባቷን ሰምቶ ካልተቃወማት ስእለቶቿ በሙሉ ይጸናሉ፤ እንዲሁም ከአንድ ነገር ለመታቀብ በመሐላ የገባችው ማንኛውም ግዴታ ይጸናል። 5 ሆኖም አባቷ ስእለት መሳሏን ወይም ከአንድ ነገር ለመታቀብ ራሷን በመሐላ ግዴታ ውስጥ ማስገባቷን ሲሰማ ቢከለክላት ስእለቱ አይጸናም። አባቷ ስለከለከላት ይሖዋ ይቅር ይላታል።+

6 “ይሁን እንጂ ይህች ሴት ስእለት ተስላ ወይም ሳታስብበት ራሷን ግዴታ ውስጥ የሚያስገባ ቃል ተናግራ እያለ ባል ብታገባ፣ 7 ባሏም ይህን ቢሰማና በሰማበት ቀን ዝም ቢላት ስእለቶቿ ወይም ከአንድ ነገር ለመታቀብ በመሐላ የገባቻቸው ግዴታዎች ይጸናሉ። 8 ሆኖም ባሏ ይህን በሰማበት ቀን ቢከለክላት የተሳለችውን ስእለት ወይም ሳታስብበት ራሷን ግዴታ ውስጥ ያስገባችበትን ቃል ያፈርሰዋል፤+ ይሖዋም ይቅር ይላታል።

9 “ሆኖም አንዲት መበለት ወይም ከባሏ የተፋታች አንዲት ሴት ስእለት ብትሳል ራሷን ግዴታ ውስጥ ያስገባችባቸው ነገሮች በሙሉ ይጸኑባታል።

10 “ይሁን እንጂ አንዲት ሴት ስእለት የተሳለችው ወይም ከአንድ ነገር ለመታቀብ ራሷን በመሐላ ግዴታ ውስጥ ያስገባችው በባሏ ቤት እያለች ከሆነና 11 ባሏም ሰምቶ ይህን ካልተቃወማት ወይም ካልከለከላት የተሳለቻቸው ስእለቶች በሙሉ ወይም ከአንድ ነገር ለመታቀብ በመሐላ የገባቻቸው ግዴታዎች ሁሉ ይጸናሉ። 12 ይሁንና ባሏ የተሳለችውን ማንኛውንም ስእለት ወይም ከአንድ ነገር ለመታቀብ በመሐላ የገባችውን የትኛውንም ግዴታ በሰማበት ቀን ሙሉ በሙሉ ቢያፈርስባት ስእለቶቹ አይጸኑም።+ ባሏ ስእለቶቿን አፍርሷቸዋል፤ ይሖዋም ይቅር ይላታል። 13 የትኛውንም ስእለት ወይም ከአንድ ነገር ለመታቀብ በመሐላ የገባችውን ግዴታ አሊያም ራሷን* ለማጎሳቆል የገባችውን ቃል ባሏ ሊያጸናው ወይም ሊያፈርሰው ይችላል። 14 ሆኖም ባሏ ቀናት እያለፉ ሲሄዱ ጨርሶ ካልተቃወማት ስእለቶቿን በሙሉ ወይም ከአንድ ነገር ለመታቀብ በመሐላ የገባችውን ግዴታ ሁሉ አጽንቶታል ማለት ነው። ስእለት መሳሏን በሰማበት ቀን ስላልተቃወማት እንዳጸናቸው ይቆጠራል። 15 ስእለቶቹን ሰምቶ የተወሰኑ ቀናት ካለፉ በኋላ ስእለቶቹን ካፈረሰ ግን የእሷ በደል የሚያስከትላቸውን መዘዞች እሱ ይሸከማል።+

16 “ከባልና ከሚስት እንዲሁም ከአባትና በቤቱ ከምትኖር ወጣት ልጁ ጋር በተያያዘ ይሖዋ ለሙሴ የሰጣቸው ደንቦች እነዚህ ናቸው።”

31 ከዚያም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ 2 “ለእስራኤላውያን ምድያማውያንን+ ተበቀልላቸው።+ ከዚያ በኋላ ወደ ወገኖችህ ትሰበሰባለህ።”*+

3 በመሆኑም ሙሴ ሕዝቡን እንዲህ አላቸው፦ “ይሖዋ በምድያም ላይ የሚወስደውን የበቀል እርምጃ ለማስፈጸም ከምድያም ጋር ለሚደረገው ጦርነት* ከመካከላችሁ ወንዶችን አስታጥቁ። 4 ከሁሉም የእስራኤል ነገድ ከእያንዳንዱ 1,000 ወንዶችን ወደ ጦርነቱ ላኩ።” 5 ስለዚህ በሺዎች ከሚቆጠሩት እስራኤላውያን+ መካከል ከአንድ ነገድ 1,000 ወንዶች ተመርጠው በአጠቃላይ 12,000 ወንዶች ለጦርነቱ* ታጠቁ።

6 ከዚያም ሙሴ ከየነገዱ የተውጣጡትን አንድ አንድ ሺህ ወንዶች ወደ ጦርነቱ ላካቸው፤ ከእነሱም ጋር የሠራዊቱ ካህን የሆነውን የአልዓዛርን ልጅ ፊንሃስን+ ላከው፤ ቅዱስ የሆኑት ዕቃዎችና በጦርነት ጊዜ የሚነፉት መለከቶች+ በእሱ እጅ ነበሩ። 7 እነሱም ይሖዋ ሙሴን ባዘዘው መሠረት በምድያም ላይ ጦርነት ከፈቱ፤ ወንዶቹንም ሁሉ ገደሉ። 8 ከተገደሉትም መካከል ኤዊ፣ ራቄም፣ ጹር፣ ሁር እና ረባ የተባሉት አምስቱ የምድያም ነገሥታት ይገኙበታል። እንዲሁም የቢዖርን ልጅ በለዓምን+ በሰይፍ ገደሉ። 9 ሆኖም እስራኤላውያን የምድያምን ሴቶችና ትናንሽ ልጆች ማርከው ወሰዱ። በተጨማሪም የቤት እንስሶቻቸውን፣ ከብቶቻቸውን እንዲሁም ንብረታቸውን በሙሉ ዘረፉ። 10 ይኖሩባቸው የነበሩትን ከተሞችና ሰፈሮቻቸውን* ሁሉ በእሳት አቃጠሉ። 11 ሰውም ሆነ እንስሳ የማረኩትንና የዘረፉትን በሙሉ ወሰዱ። 12 ከዚያም የማረኳቸውን ሰዎችና የዘረፉትን ንብረት በኢያሪኮ፣ በዮርዳኖስ አጠገብ ባለው የሞዓብ በረሃማ ሜዳ+ ላይ ወደሚገኘው ሰፈር ወደ ሙሴ፣ ወደ ካህኑ አልዓዛርና ወደ እስራኤል ማኅበረሰብ አመጡ።

13 ከዚያም ሙሴ፣ ካህኑ አልዓዛርና የማኅበረሰቡ አለቆች በሙሉ ከእነሱ ጋር ለመገናኘት ከሰፈሩ ውጭ ወጡ። 14 ሆኖም ሙሴ ከጦርነቱ በተመለሱት የሠራዊቱ አዛዦች ይኸውም በሺህ አለቆቹና በመቶ አለቆቹ ላይ ተቆጣ። 15 እንዲህም አላቸው፦ “ሴቶቹን በሙሉ እንዴት ሳትገድሉ ተዋችኋቸው? 16 የበለዓምን ቃል ሰምተው እስራኤላውያን በፌጎር በተከሰተው ነገር+ የተነሳ በይሖዋ ላይ ታማኝነት የጎደለው ድርጊት እንዲፈጽሙ ያሳቷቸውና+ በዚህም ምክንያት በይሖዋ ማኅበረሰብ ላይ መቅሰፍት እንዲመጣ ያደረጉት እነሱ አይደሉም?+ 17 በሉ አሁን ከልጆች መካከል ወንዶቹን በሙሉ እንዲሁም ከወንድ ጋር የፆታ ግንኙነት የፈጸሙ ሴቶችን በሙሉ ግደሉ። 18 ሆኖም ከወንድ ጋር የፆታ ግንኙነት ፈጽመው የማያውቁትን ወጣት ሴቶች ሁሉ+ በሕይወት እንዲተርፉ ልታደርጉ ትችላላችሁ። 19 እናንተም ለሰባት ቀን ከሰፈሩ ውጭ ቆዩ። ከመካከላችሁ ሰው* የገደለም ሆነ የሞተ ሰው የነካ+ ማንኛውም ሰው በሦስተኛውና በሰባተኛው ቀን ራሱን ያንጻ፤+ እናንተም ሆናችሁ የማረካችኋቸው ሰዎች ራሳችሁን አንጹ። 20 ማንኛውንም ልብስ፣ ማንኛውንም ከቆዳ የተሠራ ነገር፣ ማንኛውንም ከፍየል ፀጉር የተሠራ ነገር እንዲሁም ማንኛውንም ከእንጨት የተሠራ ነገር ከኃጢአት አንጹ።”

21 ከዚያም ካህኑ አልዓዛር ወደ ጦርነቱ ሄደው የነበሩትን ወንዶች እንዲህ አላቸው፦ “ይሖዋ ሙሴን ያዘዘው የሕጉ ደንብ ይህ ነው፦ 22 ‘ወርቁን፣ ብሩን፣ መዳቡን፣ ብረቱን፣ ቆርቆሮውንና እርሳሱን ብቻ 23 ይኸውም እሳትን መቋቋም የሚችለውን ማንኛውንም ነገር በእሳት ውስጥ እንዲያልፍ አድርጉ፤ እሱም ንጹሕ ይሆናል። ያም ሆኖ ለማንጻት በሚያገለግለው ውኃ መንጻት አለበት።+ እሳትን መቋቋም የማይችሉ ነገሮችን በሙሉ በውኃ ውስጥ እንዲያልፉ ማድረግ አለባችሁ። 24 በሰባተኛውም ቀን ልብሶቻችሁን እጠቡ፤ ንጹሕም ሁኑ፤ ከዚያም ወደ ሰፈሩ መግባት ትችላላችሁ።’”+

25 ከዚያም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ 26 “የምርኮውን ብዛት ቁጠር፤ ሰዎችም ሆኑ እንስሳት የተማረኩትን ሁሉ ቁጠር፤ ይህንም ከካህኑ ከአልዓዛርና ከማኅበረሰቡ የአባቶች ቤት መሪዎች ጋር አድርግ። 27 ምርኮውንም በጦርነቱ ለተካፈሉት ተዋጊዎችና ለቀረው ማኅበረሰብ ሁሉ እንዲከፋፈል ለሁለት ክፈለው።+ 28 ለይሖዋም ግብር እንዲሆን በጦርነቱ ከተካፈሉት ተዋጊዎች ላይ ከሰውም ሆነ ከከብት፣ ከአህያም ሆነ ከመንጋ ከ500 አንድ ነፍስ* ውሰድ። 29 ለእነሱ ተከፍሎ ከተሰጣቸው ድርሻ ላይ ወስዳችሁ ለካህኑ ለአልዓዛር የይሖዋ መዋጮ አድርጋችሁ ስጡት።+ 30 ለእስራኤላውያን ተከፍሎ ከተሰጣቸው ድርሻ ላይ ደግሞ ከሰውም ሆነ ከከብት፣ ከአህያም ሆነ ከመንጋ እንዲሁም ከማንኛውም እንስሳ ከ50 አንድ ወስደህ ከይሖዋ የማደሪያ ድንኳን ጋር በተያያዘ ያለባቸውን ኃላፊነት+ ለሚወጡት ለሌዋውያኑ ስጥ።”+

31 በመሆኑም ሙሴና ካህኑ አልዓዛር ልክ ይሖዋ ሙሴን እንዳዘዘው አደረጉ። 32 በውጊያው የተካፈሉት ሰዎች ማርከው ካመጡት ምርኮ ውስጥ የቀሩት 675,000 በጎች፣ 33 72,000 ከብቶች 34 እንዲሁም 61,000 አህዮች ነበሩ። 35 ከወንድ ጋር የፆታ ግንኙነት ፈጽመው የማያውቁት ሴቶች*+ በአጠቃላይ 32,000 ነበሩ። 36 በውጊያው ለተሳተፉት ተከፍሎ የተሰጣቸው ድርሻ በአጠቃላይ 337,500 በግ ነበር። 37 ከበጎቹ መካከል ለይሖዋ ግብር ተደርገው የተሰጡት 675 ነበሩ። 38 ከብቶቹ ደግሞ 36,000 ነበሩ፤ ከእነሱም መካከል ለይሖዋ ግብር ተደርገው የተሰጡት 72 ነበሩ። 39 አህዮቹ 30,500 ነበሩ፤ ከእነሱም መካከል ለይሖዋ ግብር ተደርገው የተሰጡት 61 ነበሩ። 40 ሰዎቹ* ደግሞ 16,000 ነበሩ፤ ከእነሱም መካከል ለይሖዋ ግብር ተደርገው የተሰጡት 32 ሰዎች* ነበሩ። 41 ከዚያም ሙሴ ልክ ይሖዋ ባዘዘው መሠረት ግብሩን ለይሖዋ መዋጮ እንዲሆን ለካህኑ ለአልዓዛር ሰጠው።+

42 ሙሴም በጦርነቱ የተካፈሉት ሰዎች ካመጡት ላይ ከፍሎ ለእስራኤላውያን የሰጣቸው ድርሻ ይህ ነው፦ 43 ሙሴ ከፍሎ የሰጣቸው ድርሻ 337,500 በግ፣ 44 36,000 ከብት፣ 45 30,500 አህያ 46 እንዲሁም 16,000 ሰው* ነበር። 47 ከዚያም ሙሴ ልክ ይሖዋ ባዘዘው መሠረት ለእስራኤላውያን ተከፍሎ ከተሰጣቸው ድርሻ ላይ ከሰውም ሆነ ከእንስሳ ከ50 አንድ ወስዶ በይሖዋ የማደሪያ ድንኳን የተጣለባቸውን ኃላፊነት+ ለሚወጡት ሌዋውያን ሰጠ።+

48 ከዚያም በሠራዊቱ ክፍሎች ውስጥ የተሾሙት አዛዦች ይኸውም የሺህ አለቆቹና+ የመቶ አለቆቹ ወደ ሙሴ ቀርበው 49 እንዲህ አሉት፦ “እኛ አገልጋዮችህ በሥራችን ያሉትን ተዋጊዎች ቆጥረናል፤ ከመካከላችን አንድም የጎደለ የለም።+ 50 ስለዚህ እያንዳንዳችን በይሖዋ ፊት ለራሳችን* ማስተሰረያ እንዲሆኑልን፣ ያገኘናቸውን ነገሮች ይኸውም የወርቅ ጌጣጌጦችን፣ የእግር አልቦዎችን፣ የእጅ አምባሮችን፣ የማኅተም ቀለበቶችን፣ የጆሮ ጉትቻዎችንና ሌሎች ጌጣጌጦችን ለይሖዋ መባ አድርገን ማቅረብ እንፈልጋለን።”

51 በመሆኑም ሙሴና ካህኑ አልዓዛር ወርቁን ይኸውም ጌጣጌጡን ሁሉ ተቀበሏቸው። 52 ከሺህ አለቆቹና ከመቶ አለቆቹ ተቀብለው ለይሖዋ መዋጮ እንዲሆን የሰጡት ወርቅ በጠቅላላ 16,750 ሰቅል* ሆነ። 53  በሠራዊቱ ውስጥ ያሉት ወንዶች እያንዳንዳቸው ከምርኮው ላይ ድርሻቸውን ወስደው ነበር። 54 ስለዚህ ሙሴና ካህኑ አልዓዛር ወርቁን ከሺህ አለቆቹና ከመቶ አለቆቹ ተቀብለው በይሖዋ ፊት ለእስራኤል ሕዝብ ማስታወሻ* እንዲሆን ወደ መገናኛ ድንኳኑ አስገቡት።

32 የሮቤል ልጆችና+ የጋድ ልጆች+ እጅግ በጣም ብዙ ከብት ነበራቸው። እነሱም የያዜር+ እና የጊልያድ ምድር ለከብቶች የሚስማማ ስፍራ እንደሆነ አዩ። 2 በመሆኑም የሮቤል ልጆችና የጋድ ልጆች መጥተው ሙሴን፣ ካህኑን አልዓዛርንና የማኅበረሰቡን አለቆች እንዲህ አሏቸው፦ 3 “የአጣሮት፣ የዲቦን፣ የያዜር፣ የኒምራ፣ የሃሽቦን፣+ የኤልዓሌ፣ የሰባም፣ የነቦ+ እና የቤኦን+ ምድር 4 ይሖዋ በእስራኤል ማኅበረሰብ ፊት ድል ያደረገው+ ሲሆን ለከብቶች ምቹ ነው፤ አገልጋዮችህ ደግሞ ብዙ ከብት አላቸው።”+ 5 አክለውም እንዲህ አሉ፦ “እንግዲህ በፊትህ ሞገስ ካገኘን ይህ ምድር ለአገልጋዮችህ ርስት ተደርጎ ይሰጥ። ዮርዳኖስን እንድንሻገር አታድርገን።”

6 ከዚያም ሙሴ የጋድን ልጆችና የሮቤልን ልጆች እንዲህ አላቸው፦ “እናንተ እዚህ ተቀምጣችሁ ወንድሞቻችሁ ወደ ጦርነት እንዲሄዱ ትፈልጋላችሁ? 7 የእስራኤል ልጆች ይሖዋ ወደሚሰጣቸው ምድር እንዳይሻገሩ ተስፋ የምታስቆርጧቸው ለምንድን ነው? 8 አባቶቻችሁ ምድሪቱን እንዲያዩ ከቃዴስበርኔ በላክኋቸው ጊዜ ያደረጉት ይህንኑ ነበር።+ 9 ወደ ኤሽኮል ሸለቆ*+ አቅንተው ምድሪቱን ካዩ በኋላ የእስራኤልን ሕዝብ ይሖዋ ወደሚሰጠው ምድር እንዳይገባ ተስፋ አስቆረጡት።+ 10 በዚያ ቀን የይሖዋ ቁጣ ነደደ፤ እንዲህም ሲል ማለ፦+ 11 ‘ከግብፅ ምድር ከወጡት መካከል 20 ዓመትና ከዚያ በላይ የሆናቸው ለአብርሃም፣ ለይስሐቅና ለያዕቆብ የማልኩላቸውን+ ምድር አያዩም፤+ ምክንያቱም በሙሉ ልባቸው አልተከተሉኝም፤ 12 ይሖዋን በሙሉ ልባቸው ከተከተሉት+ ከቀኒዛዊው ከየፎኒ ልጅ ከካሌብና+ ከነዌ ልጅ ከኢያሱ+ በስተቀር አንዳቸውም ምድሪቱን አያዩም።’ 13 በመሆኑም የይሖዋ ቁጣ በእስራኤል ላይ ነደደ፤ በይሖዋ ፊት ክፉ ድርጊት የፈጸመው ያ ትውልድ በሙሉ እስኪያልቅ ድረስ+ ለ40 ዓመት በምድረ በዳ እንዲንከራተቱ አደረጋቸው።+ 14 እናንተ የኃጢአተኞች ልጆች ደግሞ ይኸው በአባቶቻችሁ እግር ተተክታችሁ ይሖዋ በእስራኤል ላይ ይበልጥ እንዲቆጣ ታደርጋላችሁ። 15 እንግዲህ እናንተ እሱን ከመከተል ዞር ካላችሁ እሱም እንደገና በምድረ በዳ ይተዋቸዋል፤ እናንተም በዚህ ሁሉ ሕዝብ ላይ ጥፋት ታመጣላችሁ።”

16 በኋላም ወደ እሱ ቀርበው እንዲህ አሉት፦ “እንግዲያው እዚሁ ለከብቶቻችን በድንጋይ ካብ በረት እንሥራ፤ ለልጆቻችንም ከተሞች እንገንባ። 17 ይሁን እንጂ ወደ ስፍራቸው እስክናስገባቸው ድረስ ለጦርነት ታጥቀን+ በእስራኤላውያን ፊት እንሄዳለን፤ በዚህም ጊዜ ልጆቻችን ከምድሪቱ ነዋሪዎች ተጠብቀው በተመሸጉት ከተሞች ውስጥ ይኖራሉ። 18 እኛም እያንዳንዱ እስራኤላዊ የራሱን ርስት እስኪያገኝ ድረስ ወደ ቤታችን አንመለስም።+ 19 እኛ ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ ባለው አካባቢ ርስት ካገኘን ከዮርዳኖስ ማዶና ከዚያ ባሻገር ባለው አካባቢ ከእነሱ ጋር ርስት አንካፈልም።”+

20 ሙሴም እንዲህ አላቸው፦ “ይህን ብታደርጉ ይኸውም በጦርነቱ ለመካፈል በይሖዋ ፊት ታጥቃችሁ ብትነሱ+ 21 እንዲሁም ጠላቶቹን ከፊቱ እስኪያስወግድ ድረስ+ እያንዳንዳችሁ የጦር መሣሪያችሁን ይዛችሁ በይሖዋ ፊት ዮርዳኖስን ብትሻገሩና 22 ምድሪቱ በይሖዋ ፊት እስክትገዛ ድረስ+ በዚያ ብትቆዩ፣ ከዚያ በኋላ መመለስ ትችላላችሁ፤+ በይሖዋም ሆነ በእስራኤላውያን ዘንድ ከበደል ነፃ ትሆናላችሁ። ከዚያም ይህች ምድር በይሖዋ ፊት የእናንተ ርስት ትሆናለች።+ 23 ይህን ባታደርጉ ግን በይሖዋ ላይ ኃጢአት ትሠራላችሁ። ለሠራችሁትም ኃጢአት ተጠያቂ እንደምትሆኑ እወቁ። 24 ስለዚህ ለልጆቻችሁ ከተሞችን መገንባትና ለመንጎቻችሁ በረት መሥራት የምትችሉ+ ቢሆንም የገባችሁትን ቃል መፈጸም ይኖርባችኋል።”

25 የጋድ ልጆችና የሮቤል ልጆችም ሙሴን እንዲህ አሉት፦ “እኛ አገልጋዮችህ ጌታችን እንዳዘዘን እናደርጋለን። 26 ልጆቻችን፣ ሚስቶቻችን፣ ከብቶቻችንና እንስሶቻችን በሙሉ በጊልያድ ከተሞች ውስጥ ይቆያሉ፤+ 27 ሆኖም እኛ አገልጋዮችህ ይኸውም በይሖዋ ፊት ጦርነት ለመግጠም የታጠቅን እያንዳንዳችን ልክ ጌታችን በተናገረው መሠረት እንሻገራለን።”+

28 በመሆኑም ሙሴ ለካህኑ ለአልዓዛር፣ ለነዌ ልጅ ለኢያሱና ለእስራኤል ነገዶች የአባቶች ቤት መሪዎች እነሱን በተመለከተ ትእዛዝ ሰጠ። 29 ሙሴም እንዲህ አላቸው፦ “የጋድ ልጆችና የሮቤል ልጆች ይኸውም በይሖዋ ፊት ለጦርነት የታጠቀ እያንዳንዱ ሰው ከእናንተ ጋር ዮርዳኖስን ከተሻገረ፣ ምድሪቱም በፊታችሁ ከተገዛች የጊልያድን ምድር ርስት አድርጋችሁ ትሰጧቸዋላችሁ።+ 30 ሆኖም የጦር መሣሪያ ታጥቀው ከእናንተ ጋር ካልተሻገሩ በከነአን ምድር በመካከላችሁ ይኖራሉ።”

31 በዚህ ጊዜ የጋድ ልጆችና የሮቤል ልጆች እንዲህ ሲሉ መለሱ፦ “ይሖዋ ለአገልጋዮችህ የተናገረውን እንፈጽማለን። 32 እኛ ራሳችን የጦር መሣሪያ ታጥቀን በይሖዋ ፊት ወደ ከነአን ምድር እንሻገራለን፤+ የምንወርሰው ርስት ግን ከዮርዳኖስ ወዲህ ያለውን ይሆናል።” 33 ስለዚህ ሙሴ ለጋድ ልጆችና ለሮቤል ልጆች+ እንዲሁም ለዮሴፍ ልጅ ለምናሴ ነገድ እኩሌታ+ የአሞራውያንን ንጉሥ የሲሖንን ግዛትና+ የባሳንን ንጉሥ የኦግን ግዛት+ ይኸውም በክልሎቹ ውስጥ የሚገኙ ከተሞች ይዞታ የሆነውን ምድር እንዲሁም በዙሪያው ባለው ምድር ያሉትን ከተሞች ሰጣቸው።

34 የጋድ ልጆችም ዲቦን፣+ አጣሮት፣+ አሮዔር፣+ 35 አትሮትሾፋን፣ ያዜር፣+ ዮግበሃ፣+ 36 ቤትኒምራ+ እና ቤትሃራን+ የተባሉትን የተመሸጉ ከተሞች ገነቡ፤ ለመንጎቹም በድንጋይ ካብ በረት ሠሩ። 37 የሮቤል ልጆች ደግሞ ሃሽቦንን፣+ ኤልዓሌን፣+ ቂርያታይምን፣+ 38 ስማቸው የተለወጠውን ነቦን+ እና በዓልመዖንን+ እንዲሁም ሲብማን ገነቡ፤ እነሱም መልሰው ለገነቧቸው ከተሞች አዲስ ስም አወጡላቸው።

39 የምናሴ ልጅ የማኪር+ ልጆች በጊልያድ ላይ ዘምተው ምድሪቱን ያዙ፤ በዚያም ይኖሩ የነበሩትን አሞራውያን አስወጧቸው። 40 በመሆኑም ሙሴ ጊልያድን ለምናሴ ልጅ ለማኪር ሰጠው፤ እሱም በዚያ መኖር ጀመረ።+ 41 የምናሴ ልጅ ያኢርም በእነሱ ላይ ዘምቶ የድንኳን ሰፈሮቻቸውን ያዘ፤ እነሱንም ሃዎትያኢር* ብሎ ጠራቸው።+ 42 ኖባህም ዘምቶ ቄናትንና በሥሯ* ያሉትን ከተሞች ያዘ፤ እነሱንም በራሱ ስም ኖባህ ብሎ ሰየማቸው።

33 የእስራኤል ሕዝብ በሙሴና በአሮን መሪነት+ በየምድቡ*+ በመሆን ከግብፅ ምድር በወጣ ጊዜ+ የተጓዘው በዚህ መልክ ነበር። 2 ሙሴም በጉዟቸው ላይ ሳሉ ያረፉባቸውን ቦታዎች ይሖዋ በሰጠው ትእዛዝ መሠረት ይመዘግብ ነበር፤ ከአንዱ ስፍራ ተነስተው ወደ ሌላው የተጓዙት በሚከተለው ሁኔታ ነበር፦+ 3 በመጀመሪያው ወር ከወሩም በ15ኛው ቀን+ ከራምሴስ ተነሱ።+ ልክ በፋሲካ በዓል+ ማግስት እስራኤላውያን ግብፃውያን ሁሉ እያዩአቸው በልበ ሙሉነት* ወጡ። 4 በዚህ ጊዜ ግብፃውያን ይሖዋ በመቅሰፍት የመታቸውን በኩሮቻቸውን ሁሉ እየቀበሩ ነበር፤+ ምክንያቱም ይሖዋ በአማልክታቸው ላይ የቅጣት እርምጃ ወስዶ ነበር።+

5 በመሆኑም እስራኤላውያን ከራምሴስ ተነስተው በሱኮት+ ሰፈሩ። 6 ከዚያም ከሱኮት ተነስተው በምድረ በዳው ዳርቻ ላይ በምትገኘው በኤታም ሰፈሩ።+ 7 በመቀጠልም ከኤታም ተነስተው በበዓልጸፎን+ ትይዩ ወደምትገኘው ወደ ፊሃሂሮት ተመለሱ፤ በሚግዶልም+ ፊት ለፊት ሰፈሩ። 8 ከዚያም ከፊሃሂሮት ተነስተው ባሕሩን በማቋረጥ+ ወደ ምድረ በዳው+ ሄዱ፤ በኤታም ምድረ በዳ+ የሦስት ቀን መንገድ ከተጓዙ በኋላ በማራ+ ሰፈሩ።

9 ከዚያም ከማራ ተነስተው ወደ ኤሊም መጡ። በኤሊም 12 የውኃ ምንጮችና 70 የዘንባባ ዛፎች ነበሩ፤ በመሆኑም በዚያ ሰፈሩ።+ 10 በመቀጠል ደግሞ ከኤሊም ተነስተው በቀይ ባሕር አጠገብ ሰፈሩ። 11 ከዚያ በኋላ ከቀይ ባሕር ተነስተው በሲን ምድረ በዳ ሰፈሩ።+ 12 ከሲን ምድረ በዳ ተነስተው ደግሞ በዶፍቃ ሰፈሩ። 13 በኋላም ከዶፍቃ ተነስተው በአሉሽ ሰፈሩ። 14 በመቀጠልም ከአሉሽ ተነስተው በረፊዲም+ ሰፈሩ፤ በዚያም ሕዝቡ የሚጠጣው ውኃ አልነበረም። 15 ከዚያ በኋላ ከረፊዲም ተነስተው በሲና ምድረ በዳ ሰፈሩ።+

16 ከሲና ምድረ በዳም ተነስተው በቂብሮትሃታባ+ ሰፈሩ። 17 ከዚያም ከቂብሮትሃታባ ተነስተው በሃጼሮት+ ሰፈሩ። 18 በኋላም ከሃጼሮት ተነስተው በሪትማ ሰፈሩ። 19 በመቀጠል ደግሞ ከሪትማ ተነስተው በሪሞንጰሬጽ ሰፈሩ። 20 ከዚያም ከሪሞንጰሬጽ ተነስተው በሊብና ሰፈሩ። 21 ከሊብናም ተነስተው በሪሳ ሰፈሩ። 22 በመቀጠልም ከሪሳ ተነስተው በቀሄላታ ሰፈሩ። 23 ከዚያም ከቀሄላታ ተነስተው በሸፈር ተራራ ሰፈሩ።

24 በኋላም ከሸፈር ተራራ ተነስተው በሃራዳ ሰፈሩ። 25 ከዚያም ከሃራዳ ተነስተው በማቅሄሎት ሰፈሩ። 26 ቀጥሎም ከማቅሄሎት ተነስተው+ በታሃት ሰፈሩ። 27 ከዚያ በኋላም ከታሃት ተነስተው በታራ ሰፈሩ። 28 ከዚያም ከታራ ተነስተው በሚትቃ ሰፈሩ። 29 በኋላም ከሚትቃ ተነስተው በሃሽሞና ሰፈሩ። 30 ከሃሽሞናም ተነስተው በሞሴሮት ሰፈሩ። 31 ከዚያም ከሞሴሮት ተነስተው በብኔያዕቃን+ ሰፈሩ። 32 በኋላም ከብኔያዕቃን ተነስተው በሆርሃጊድጋድ ሰፈሩ። 33 ከዚያም ከሆርሃጊድጋድ ተነስተው በዮጥባታ+ ሰፈሩ። 34 ከዮጥባታም ተነስተው በአብሮና ሰፈሩ። 35 ከዚያም ከአብሮና ተነስተው በዔጽዮንጋብር+ ሰፈሩ። 36 በኋላም ከዔጽዮንጋብር ተነስተው በጺን ምድረ በዳ+ በምትገኘው በቃዴስ ሰፈሩ።

37 ከቃዴስም ተነስተው በኤዶም ምድር ወሰን ላይ በሚገኘው በሆር ተራራ+ ሰፈሩ። 38 እስራኤላውያን ከግብፅ ምድር በወጡ በ40ኛው ዓመት በአምስተኛው ወር ከወሩም በመጀመሪያው ቀን ካህኑ አሮን ይሖዋ በሰጠው ትእዛዝ መሠረት ወደ ሆር ተራራ ወጣ፤ በዚያም ሞተ።+ 39 አሮን በሆር ተራራ ላይ በሞተበት ጊዜ ዕድሜው 123 ዓመት ነበር።

40 በከነአን ምድር በኔጌብ ይኖር የነበረው ከነአናዊው የአራድ ንጉሥ+ የእስራኤላውያንን መምጣት ሰማ።

41 ከጊዜ በኋላም ከሆር ተራራ+ ተነስተው በጻልሞና ሰፈሩ። 42 ከዚያም ከጻልሞና ተነስተው በጱኖን ሰፈሩ። 43 በመቀጠልም ከጱኖን ተነስተው በኦቦት+ ሰፈሩ። 44 ከኦቦትም ተነስተው በሞዓብ ድንበር+ ላይ በምትገኘው በኢዬዓባሪም ሰፈሩ። 45 በኋላም ከኢይም ተነስተው በዲቦንጋድ+ ሰፈሩ። 46 በመቀጠልም ከዲቦንጋድ ተነስተው በአልሞንዲብላታይም ሰፈሩ። 47 ከአልሞንዲብላታይም ተነስተው ደግሞ በነቦ+ ፊት ለፊት በአባሪም+ ተራሮች ሰፈሩ። 48 በመጨረሻም ከአባሪም ተራሮች ተነስተው በኢያሪኮ በሚገኘው በዮርዳኖስ አጠገብ ባለው የሞዓብ በረሃማ ሜዳ ሰፈሩ።+ 49 በሞዓብ በረሃማ ሜዳ ከቤትየሺሞት እስከ አቤልሺቲም+ በሚገኘው ስፍራ በዮርዳኖስ ወንዝ ዳርቻ ሰፈሩ።

50 ይሖዋ በኢያሪኮ በሚገኘው በዮርዳኖስ አጠገብ ባለው የሞዓብ በረሃማ ሜዳ ላይ ሙሴን እንዲህ አለው፦ 51 “እስራኤላውያንን ተናገራቸው፤ እንዲህም በላቸው፦ ‘እንግዲህ ዮርዳኖስን ተሻግራችሁ ወደ ከነአን ምድር ልትገቡ ነው።+ 52 የምድሪቱን ነዋሪዎች በሙሉ ከፊታችሁ አባሯቸው፤ የተቀረጹ የድንጋይ ምስሎቻቸውንም+ ሁሉ አጥፉ፤ ከብረት የተሠሩ ሐውልቶቻቸውንም*+ በሙሉ አስወግዱ፤ በከፍታ ቦታዎች ላይ ያሉ ቅዱስ ስፍራዎቻቸውን+ ሁሉ አፍርሱ። 53  ምድሪቱን ርስት አድርጌ ስለምሰጣችሁ ምድሪቱን ወርሳችሁ በዚያ ትኖራላችሁ።+ 54 ምድሪቱንም በየቤተሰባችሁ ውርስ አድርጋችሁ በዕጣ+ ተከፋፈሉ። ተለቅ ላለው ቡድን በዛ ያለውን፣ አነስ ላለው ቡድን ደግሞ አነስ ያለውን ውርስ አድርጋችሁ ስጡት።+ ሁሉም በወጣለት ዕጣ መሠረት የተሰጠውን ቦታ ይወርሳል። በየአባቶቻችሁ ነገዶች ርስታችሁን ውርስ አድርጋችሁ ትቀበላላችሁ።+

55 “‘የምድሪቱን ነዋሪዎች ከፊታችሁ ሳታባርሩ እዚያው ከተዋችኋቸው+ ግን ዓይናችሁ ውስጥ እንደገባ ጉድፍ እንዲሁም ጎናችሁ ላይ እንደተሰካ እሾህ ይሆኑባችኋል፤ ደግሞም በምትኖሩበት ምድር ያንገላቷችኋል።+ 56 እኔም በእነሱ ላይ ለማድረግ ያሰብኩትን በእናንተ ላይ አደርግባችኋለሁ።’”+

34 በተጨማሪም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ 2 “ለእስራኤላውያን ይህን መመሪያ ስጣቸው፦ ‘ወደ ከነአን ምድር ስትገቡ+ ርስት አድርጋችሁ የምትወርሷት ምድር ይኸውም የከነአን ምድር ከነወሰኖቿ ይህች ናት።+

3 “‘በስተ ደቡብ ያለው ወሰናችሁ ከጺን ምድረ በዳ ተነስቶ እስከ ኤዶም ጠረፍ ድረስ ይዘልቃል፤ በስተ ምሥራቅ ያለው ደቡባዊ ወሰናችሁ ደግሞ ከጨው ባሕር* ዳርቻ ጀምሮ ያለው ይሆናል።+ 4 ወሰናችሁ አቅጣጫውን በመቀየር ከአቅራቢም አቀበት+ በስተ ደቡብ አድርጎ እስከ ጺን ድረስ ይዘልቃል፤ መጨረሻውም ከቃዴስበርኔ+ በስተ ደቡብ ይሆናል። ከዚያም ወደ ሃጻርአዳር+ ይሄድና ወደ አጽሞን ይዘልቃል። 5 ወሰኑ አጽሞን ላይ ሲደርስ አቅጣጫውን ቀይሮ ወደ ግብፅ ደረቅ ወንዝ* ይሄዳል፤ መጨረሻውም ባሕሩ* ይሆናል።+

6 “‘ምዕራባዊ ወሰናችሁ ደግሞ ታላቁ ባሕርና* የባሕሩ ዳርቻ ይሆናል። ይህ ምዕራባዊ ወሰናችሁ ይሆናል።+

7 “‘ሰሜናዊ ወሰናችሁ የሚከተለው ይሆናል፦ ከታላቁ ባሕር አንስቶ እስከ ሆር ተራራ ድረስ ምልክት በማድረግ ወሰናችሁን ከልሉ። 8 ከሆር ተራራም አንስቶ እስከ ሌቦሃማት*+ ድረስ ወሰኑን ምልክት አድርጉ፤ የወሰኑም መጨረሻ ጼዳድ+ ይሆናል። 9 ወሰኑም እስከ ዚፍሮን ድረስ ይዘልቃል፤ መጨረሻውም ሃጻርኤናን+ ይሆናል። ይህ ሰሜናዊ ወሰናችሁ ይሆናል።

10 “‘ከዚያም በስተ ምሥራቅ በኩል ወሰናችሁን ከሃጻርኤናን አንስቶ እስከ ሸፋም ድረስ ምልክት አድርጉ። 11 ወሰኑም ከሸፋም አንስቶ ከአይን በስተ ምሥራቅ እስከሚገኘው እስከ ሪብላ ድረስ ይዘልቃል፤ ከዚያም ቁልቁል ወርዶ የኪኔሬትን ባሕር* ምሥራቃዊ ዳርቻ አቋርጦ ያልፋል።+ 12 ወሰኑ ወደ ዮርዳኖስ ይወርድና መጨረሻው ጨው ባሕር ይሆናል።+ እንግዲህ ምድራችሁ+ በዙሪያዋ ካሉት ወሰኖቿ ጋር ይህች ናት።’”

13 በመሆኑም ሙሴ እስራኤላውያንን እንዲህ ሲል አዘዛቸው፦ “ይሖዋ ለዘጠኙ ነገዶችና ለግማሹ ነገድ እንዲሰጥ ባዘዘው መሠረት ርስት አድርጋችሁ በዕጣ የምትከፋፈሏት+ ምድር ይህች ናት። 14 የሮቤላውያን ነገድ በየአባቶቻቸው ቤት፣ የጋዳውያን ነገድ በየአባቶቻቸው ቤት እንዲሁም የምናሴ ነገድ እኩሌታ አስቀድመው ርስታቸውን ወስደዋልና።+ 15 ሁለቱ ነገድና ግማሹ ነገድ በኢያሪኮ አቅራቢያ ከዮርዳኖስ ክልል በስተ ምሥራቅ በፀሐይ መውጫ አቅጣጫ ርስታቸውን አግኝተዋል።”+

16 በተጨማሪም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ 17 “ምድሪቱን ለእናንተ ርስት አድርገው የሚያከፋፍሏችሁ ካህኑ አልዓዛርና+ የነዌ ልጅ ኢያሱ+ ናቸው። 18 ምድሪቱን ርስት አድርጋችሁ ለማከፋፈል ከእያንዳንዱ ነገድ አንድ አንድ አለቃ ትወስዳላችሁ።+ 19 የሰዎቹም ስም የሚከተለው ነው፦ ከይሁዳ ነገድ+ የየፎኒ ልጅ ካሌብ፣+ 20 ከስምዖን ልጆች ነገድ+ የአሚሁድ ልጅ ሸሙኤል፣ 21 ከቢንያም ነገድ+ የኪስሎን ልጅ ኤሊዳድ፣ 22 ከዳን ልጆች ነገድ+ አንድ አለቃ ይኸውም የዮግሊ ልጅ ቡቂ፣ 23 ከዮሴፍ ልጆች+ መካከል ከምናሴ ልጆች ነገድ+ አንድ አለቃ ይኸውም የኤፎድ ልጅ ሃኒኤል፣ 24 ከኤፍሬም ልጆች ነገድ+ አንድ አለቃ ይኸውም የሺፍጣን ልጅ ቀሙኤል፣ 25 ከዛብሎን ልጆች ነገድ+ አንድ አለቃ ይኸውም የፓርናክ ልጅ ኤሊጻፋን፣ 26 ከይሳኮር ልጆች ነገድ+ አንድ አለቃ ይኸውም የአዛን ልጅ ፓልጢኤል፣ 27 ከአሴር ልጆች ነገድ+ አንድ አለቃ ይኸውም የሸሎሚ ልጅ አሂሑድ፣ 28 ከንፍታሌም ልጆች ነገድ+ አንድ አለቃ ይኸውም የአሚሁድ ልጅ ፐዳሄል።” 29 ይሖዋ በከነአን ምድር ለእስራኤላውያን መሬቱን እንዲያከፋፍሉ ያዘዛቸው እነዚህ ናቸው።+

35 ይሖዋ ሙሴን በኢያሪኮ በሚገኘው በዮርዳኖስ አጠገብ ባለው የሞዓብ በረሃማ ሜዳ+ ላይ እንዲህ አለው፦ 2 “እስራኤላውያንን ከሚወርሱት ርስት ላይ ለሌዋውያኑ መኖሪያ የሚሆኑ ከተሞችን እንዲሰጧቸው እዘዛቸው፤+ በከተሞቹም ዙሪያ ያለውን የግጦሽ መሬት ለሌዋውያኑ መስጠት አለባቸው።+ 3 ከተሞቹ ለእነሱ መኖሪያ፣ የግጦሽ ቦታዎቹ ደግሞ ለከብቶቻቸውና ለዕቃዎቻቸው እንዲሁም ለሌሎች እንስሶቻቸው ይሆናሉ። 4 ለሌዋውያኑ የምትሰጧቸው የከተሞቹ የግጦሽ ቦታዎች ከከተማው ቅጥር በሁሉም አቅጣጫ 1,000 ክንድ* ይሆናል። 5 ከተማውን መካከል ላይ በማድረግ ከከተማው ውጭ በምሥራቅ በኩል 2,000 ክንድ፣ በደቡብ በኩል 2,000 ክንድ፣ በምዕራብ በኩል 2,000 ክንድ እንዲሁም በሰሜን በኩል 2,000 ክንድ ለኩ። እነዚህም የከተሞቻቸው የግጦሽ መሬት ይሆናሉ።

6 “ለሌዋውያኑ የምትሰጧቸው ከተሞች ነፍስ ያጠፋ ሰው ሸሽቶ የሚሸሸግባቸውን+ 6 የመማጸኛ ከተሞችና+ ሌሎች 42 ከተሞችን ነው። 7 በጠቅላላ 48 ከተሞችን ከነግጦሽ መሬታቸው ለሌዋውያኑ ትሰጧቸዋላችሁ።+ 8 ከተሞቹን የምትሰጧቸው ከእስራኤላውያን ርስት ላይ ወስዳችሁ ነው።+ ተለቅ ካለው ቡድን ላይ ብዙ ትወስዳላችሁ፤ አነስ ካለው ቡድን ላይ ደግሞ ጥቂት ትወስዳላችሁ።+ እያንዳንዱ ቡድን በወረሰው ርስት መጠን ካሉት ከተሞች ላይ የተወሰኑትን ለሌዋውያኑ መስጠት ይኖርበታል።”

9 ይሖዋ በመቀጠል ሙሴን እንዲህ አለው፦ 10 “እስራኤላውያንን ተናገራቸው፤ እንዲህም በላቸው፦ ‘እንግዲህ ወደ ከነአን ምድር ለመግባት ዮርዳኖስን ልትሻገሩ ነው።+ 11 ሳያስበው ሰው የገደለ* ሰው ሸሽቶ የሚጠጋባቸው አመቺ የሆኑ የመማጸኛ ከተሞችን ለራሳችሁ ምረጡ።+ 12 እነዚህ ከተሞች ነፍስ ያጠፋው ሰው በማኅበረሰቡ ፊት ለፍርድ ከመቅረቡ በፊት+ እንዳይሞት ከደም ተበቃዩ+ የሚሸሸግባቸው ከተሞች ይሆኑላችኋል። 13 እናንተ የምትሰጧቸው ስድስቱ የመማጸኛ ከተሞች ለዚህ ዓላማ ያገለግላሉ። 14 የመማጸኛ ከተሞች ሆነው እንዲያገለግሉ ከዮርዳኖስ ወዲህ ሦስት ከተሞችን፣+ በከነአን ምድር ደግሞ ሦስት ከተሞችን+ ትሰጣላችሁ። 15 እነዚህ ስድስት ከተሞች ለእስራኤላውያንም ሆነ ለባዕድ አገር ሰው+ አሊያም በመካከላቸው ለሚኖር ሰፋሪ ሳያስበው ሰው የገደለ* ማንኛውም ሰው ሸሽቶ የሚጠጋባቸው ከተሞች ሆነው ያገለግላሉ።+

16 “‘ሆኖም ሰውየው ግለሰቡን በብረት መሣሪያ ቢመታውና ቢገድለው ይህ ሰው ነፍሰ ገዳይ ነው። ነፍሰ ገዳዩ ያለምንም ጥርጥር መገደል አለበት።+ 17 ሰውየው ግለሰቡን ሊገድለው በሚችል ድንጋይ ቢመታውና ቢገድለው ይህ ሰው ነፍሰ ገዳይ ነው። ነፍሰ ገዳዩ ያለምንም ጥርጥር መገደል አለበት። 18 ሰውየው ግለሰቡን ሊገድለው በሚችል ከእንጨት የተሠራ መሣሪያ ቢመታውና ቢገድለው ይህ ሰው ነፍሰ ገዳይ ነው። ነፍሰ ገዳዩ ያለምንም ጥርጥር መገደል አለበት።

19 “‘ነፍሰ ገዳዩን መግደል ያለበት ደም ተበቃዩ ይሆናል። ባገኘው ጊዜ እሱ ራሱ ይግደለው። 20 አንድ ሰው ሌላውን በጥላቻ ተገፋፍቶ ቢገፈትረው ወይም ተንኮል አስቦ* የሆነ ነገር ቢወረውርበትና ግለሰቡ ቢሞት+ 21 አሊያም በጥላቻ ተነሳስቶ በእጁ ቢመታውና ቢሞት መቺው ያለምንም ጥርጥር ይገደላል። እሱ ነፍሰ ገዳይ ነው። ደም ተበቃዩም ነፍሰ ገዳዩን ባገኘው ጊዜ ይገድለዋል።

22 “‘ይሁን እንጂ ሰውየው ግለሰቡን የገፈተረው በጥላቻ ተነሳስቶ ሳይሆን ሳያስበው ከሆነ ወይም ዕቃ የወረወረበት ተንኮል አስቦ* ካልሆነ+ 23 አሊያም ግለሰቡ ሳያየው ድንጋይ ቢጥልበትና ቢሞት ሆኖም ሰውየው ከግለሰቡ ጋር ጠላትነት ባይኖረውና ይህን ያደረገው እሱን ለመጉዳት አስቦ ባይሆን 24 ማኅበረሰቡ እነዚህን ደንቦች መሠረት በማድረግ በገዳዩና በደም ተበቃዩ መካከል ፍርድ ይስጥ።+ 25 ማኅበረሰቡም ነፍሰ ገዳዩን ከደም ተበቃዩ እጅ ታድጎ ሸሽቶበት ወደነበረው የመማጸኛ ከተማ ይመልሰው፤ እሱም በቅዱስ ዘይት የተቀባው+ ሊቀ ካህናት እስኪሞት ድረስ በዚያ ይቆይ።

26 “‘ይሁንና ገዳዩ ሸሽቶ ከገባበት የመማጸኛ ከተማ ወሰን ቢወጣና 27 ደም ተበቃዩም ገዳዩን ከመማጸኛ ከተማው ወሰን ውጭ አግኝቶ ቢገድለው በደም ዕዳ አይጠየቅም። 28 ምክንያቱም ሊቀ ካህናቱ እስኪሞት ድረስ በመማጸኛ ከተማው ውስጥ መቆየት ይገባዋል። ሊቀ ካህናቱ ከሞተ በኋላ ግን ገዳዩ ወደ ርስቱ መመለስ ይችላል።+ 29 እነዚህም በምትኖሩበት በየትኛውም ቦታ በትውልዶቻችሁ ሁሉ ፍርድ ለመስጠት እንደሚያገለግል ደንብ ይሁኗችሁ።

30 “‘ሰው* የገደለ ማንኛውም ሰው ምሥክሮች ከመሠከሩበት*+ እንደ ነፍሰ ገዳይ ተቆጥሮ ይገደል፤+ ይሁን እንጂ ማንም ሰው* አንድ ግለሰብ በሚሰጠው ምሥክርነት ብቻ በሞት መቀጣት የለበትም። 31 ሞት ለሚገባው ነፍሰ ገዳይ ሕይወት* ቤዛ አትቀበሉ፤ ምክንያቱም ያለምንም ጥርጥር መገደል አለበት።+ 32 እንዲሁም ሸሽቶ ወደ መማጸኛ ከተማው ለገባ ሰው* ሊቀ ካህናቱ ከመሞቱ በፊት ወደ ምድሩ ተመልሶ እንዲኖር ለማድረግ ቤዛ አትቀበሉ።

33 “‘ደም ምድሪቱን ስለሚበክል ያላችሁባትን ምድር አትበክሉ፤+ ደም ባፈሰሰው ሰው ደም ካልሆነ በስተቀር በምድሪቱ ላይ ለፈሰሰው ደም ስርየት ሊኖር አይችልም።+ 34 የምትኖሩባትን፣ እኔም የምኖርባትን ምድር አታርክሱ፤ እኔ ይሖዋ በእስራኤል ሕዝብ መካከል እኖራለሁና።’”+

36 ከዮሴፍ ልጆች ቤተሰቦች የምናሴ ልጅ፣ የማኪር ልጅ፣+ የጊልያድ ተወላጆች የአባቶች ቤት መሪዎች ወደ ሙሴና የእስራኤላውያን የአባቶች ቤት መሪዎች ወደሆኑት አለቆች ቀርበው ተናገሩ፤ 2 እንዲህም አሉ፦ “ይሖዋ ጌታዬን ምድሪቱን ለእስራኤላውያን ርስት አድርጎ በዕጣ እንዲያከፋፍል አዞት ነበር፤+ ደግሞም የወንድማችንን የሰለጰአድን ርስት ለሴቶች ልጆቹ እንዲሰጥ ይሖዋ ጌታዬን አዞት ነበር።+ 3 እነዚህ ሴቶች ከሌሎች የእስራኤል ነገዶች ባሎችን ቢያገቡ የእነሱ ውርስ ከአባቶቻችን ውርስ ላይ ተወስዶ በሚያገቡት ሰው ነገድ ውርስ ላይ ይጨመራል፤ በመሆኑም በዕጣ ከተሰጠን ውርስ ላይ ይቀነሳል። 4 የእስራኤል ሕዝብ የኢዮቤልዩ+ ዓመት በሚደርስበት ጊዜ የሴቶቹ ውርስ በሚያገቡት ሰው ነገድ ውርስ ላይ ለዘለቄታው ይጨመራል፤ በመሆኑም የእነሱ ውርስ ከአባቶቻችን ነገድ ውርስ ላይ ይቀነሳል።”

5 ከዚያም ሙሴ ይሖዋ በሰጠው ትእዛዝ መሠረት እስራኤላውያንን እንዲህ ሲል አዘዛቸው፦ “የዮሴፍ ልጆች ነገድ የተናገረው ነገር ትክክል ነው። 6 ይሖዋ የሰለጰአድን ሴቶች ልጆች በተመለከተ እንዲህ ሲል አዟል፦ ‘የፈለጉትን ሰው ማግባት ይችላሉ። ሆኖም ከአባታቸው ነገድ ቤተሰብ የሆነን ሰው ማግባት ይኖርባቸዋል። 7 የትኛውም የእስራኤላውያን ውርስ ከአንዱ ነገድ ወደ ሌላው ነገድ መተላለፍ የለበትም፤ ምክንያቱም እስራኤላውያን እያንዳንዳቸው የአባቶቻቸውን ነገድ ውርስ አጽንተው መያዝ አለባቸው። 8 እስራኤላውያን የቀደሙትን አባቶቻቸውን ውርስ ጠብቀው ማቆየት እንዲችሉ በእስራኤል ነገዶች መካከል ውርስ ያላት የትኛዋም ልጅ የአባቷ ነገድ ተወላጅ የሆነ ሰው ማግባት ይኖርባታል።+ 9 የትኛውም ውርስ ከአንዱ ነገድ ወደ ሌላው ነገድ መተላለፍ የለበትም፤ ምክንያቱም የእስራኤል ነገዶች እያንዳንዳቸው የየራሳቸውን ውርስ አጽንተው መያዝ አለባቸው።’”

10 የሰለጰአድ ሴቶች ልጆች ልክ ይሖዋ ሙሴን እንዳዘዘው አደረጉ።+ 11 ስለሆነም የሰለጰአድ ሴቶች ልጆች+ የሆኑት ማህላ፣ ቲርጻ፣ ሆግላ፣ ሚልካ እና ኖኅ የአባታቸውን ወንድሞች ልጆች አገቡ። 12 ውርሻቸው በአባታቸው ቤተሰብ ነገድ ሥር እንደሆነ እንዲቀጥል የዮሴፍ ልጅ የምናሴ ልጆች ቤተሰቦች የሆኑ ወንዶችን አገቡ።

13 ይሖዋ በኢያሪኮ በሚገኘው በዮርዳኖስ አጠገብ ባለው የሞዓብ በረሃማ ሜዳ ላይ ለነበሩት እስራኤላውያን በሙሴ አማካኝነት የሰጣቸው ትእዛዛትና ድንጋጌዎች እነዚህ ናቸው።+

ቃል በቃል “የእስራኤልን ወንዶች ልጆች።”

ቃል በቃል “በየሠራዊታቸው።”

ቃል በቃል “ባዕድ ሰው።” ሌዋዊ ያልሆነን ሰው ያመለክታል።

ወይም “አርማው።”

ቃል በቃል “በየሠራዊቱ።”

ወይም “የመጠበቅ፤ በማደሪያ ድንኳኑ ውስጥ የተሰጣቸውን አገልግሎት የመወጣት።”

ወይም “ምልክት።”

ቃል በቃል “በየሠራዊቱ።”

ቃል በቃል “በየሠራዊቱ።”

ቃል በቃል “በየሠራዊቱ።”

ቃል በቃል “በየሠራዊቱ።”

ቃል በቃል “ትውልድ።”

ቃል በቃል “እጃቸውን የተሞሉት።”

ቃል በቃል “ባዕድ ሰው።” ከአሮን ወገን ያልሆነን ሰው ያመለክታል።

ቃል በቃል “ማህፀን በሚከፍተው በኩር ሁሉ።”

ወይም “መጋረጃ።”

ወይም “መጋረጃ።”

ወይም “ከመጋረጃውና።”

ቃል በቃል “ባዕድ ሰው።” ሌዋዊ ያልሆነን ሰው ያመለክታል።

ወይም “በቅዱሱ ሰቅል።”

አንድ ሰቅል 11.4 ግራም ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።

አንድ ጌራ 0.57 ግራም ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።

ቃል በቃል “አፍ።”

ወይም “በስብ የራሰውን አመድ።” መሥዋዕት ሆነው በሚቀርቡት እንስሳት ስብ የራሰውን አመድ ያመለክታል።

ቃል በቃል “ሸክም።”

ወይም “መጋረጃ።”

ወይም “መጋረጃ።”

ወይም “ነፍስ።” የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

ወይም “ስለማድር።”

ወይም “ነፍስ።”

ቃል በቃል “እነሱም።”

አንድ አሥረኛ ኢፍ 2.2 ሊትር ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።

የመራቢያ አካላትን የሚያመለክት ይመስላል።

ወይም “እንዲመነምንና።” ዘር የማፍራት ችሎታ ማጣትን የሚያመለክት ሊሆን ይችላል።

ወይም “ይሁን! ይሁን!”

የመራቢያ አካላትን የሚያመለክት ይመስላል።

ወይም “ይመነምናል።” ዘር የማፍራት ችሎታ ማጣትን የሚያመለክት ሊሆን ይችላል።

በዕብራስይጥ ናዚር ሲሆን “ተነጥሎ የወጣ፤ ለአንድ ነገር የተወሰነ፤ ለአንድ ዓላማ የተለየ” የሚል ትርጉም አለው።

ወይም “ነፍስ።” የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

ወይም “የሞተ ሰው ወዳለበት ቦታ አይቅረብ።”

ወይም “የናዝራዊነት ራሱን ቢያረክስ።”

ወይም “ነፍስ።” የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

ወይም “የናዝራዊነት ራሱን።”

ወይም “በውሰናው።”

ወይም “በቅዱሱ ሰቅል።”

አንድ ሰቅል 11.4 ግራም ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።

ቃል በቃል “ከእሱ።”

ቃል በቃል “ይወዝውዛቸው።”

ቃል በቃል “ወዝውዛቸው።”

ቃል በቃል “የምትወዘውዛቸው።”

ወይም “ማህፀን በሚከፍተው በኩር ሁሉ።”

ቃል በቃል “ወዘወዛቸው።”

ወይም “የማለፍን።” የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

ቃል በቃል “በሁለቱ ምሽቶች መካከል።”

ቃል በቃል “በሁለቱ ምሽቶች መካከል።”

ወይም “በሰው ነፍስ።”

ወይም “እኛ በሰው ነፍስ።”

ወይም “ማንኛውም ሰው በነፍስ።”

ቃል በቃል “በሁለቱ ምሽቶች መካከል።”

ወይም “ነፍስ።”

ቃል በቃል “በየሠራዊቱ።”

ቃል በቃል “በየሠራዊቱ።”

ቃል በቃል “በየሠራዊቱ።”

ቃል በቃል “በየሠራዊቱ።”

ቃል በቃል “በየሠራዊታቸው።”

ዮቶርን ያመለክታል።

ወይም “ዓይናችን ሆነህ ልታገለግለን።”

ወይም “እልፍ አእላፋት እስራኤላውያን።”

“የሚነድ” የሚል ትርጉም አለው። የሚንቀለቀል፤ የሚንቦገቦግ መሆኑን ያመለክታል።

በመካከላቸው ያሉትን እስራኤላውያን ያልሆኑ ሰዎች የሚያመለክት ይመስላል።

ወይም “ነፍሳችን ዝሏል።”

ዘፍ 2:12 ላይ የሚገኘውን የግርጌ ማስታወሻ ተመልከት።

ወይም “ትንቢት መናገር ጀመሩ።”

አንድ ክንድ 44.5 ሴንቲ ሜትር ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።

አንድ ሆሜር 220 ሊትር ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።

“የመጎምጀት የመቃብር ስፍራ” የሚል ትርጉም አለው።

ወይም “ሙሴ ከማንኛውም ሰው ይልቅ በጣም ትሑት (ገር) ነበር።”

ቃል በቃል “ታማኝ መሆኑን ያስመሠከረ።”

ቃል በቃል “አፍ ለአፍ።”

ወይም “የሆሹአ።” “ይሖዋ አዳኝ ነው” የሚል ትርጉም አለው።

ቃል በቃል “የሰባች።”

ቃል በቃል “ያልሰባች።”

ወይም “በሃማት መግቢያ።”

ወይም “ደረቅ ወንዝ።”

“የወይን ዘለላ” የሚል ትርጉም አለው።

ወይም “ደረቅ ወንዝ።”

ቃል በቃል “እንደ አንድ ሰው ብታጠፋው።”

ወይም “ፍቅራዊ ደግነቱ።”

ወይም “በረባዳማው ሜዳ ላይ።”

ቃል በቃል “እጄን ወዳነሳሁበት።”

ቃል በቃል “ለዝሙት አዳሪነታችሁ።”

ወይም “እንደ ጠላት መመልከት።”

ወይም “የሚያረጋጋ፤ የሚያበርድ።” ቃል በቃል “እረፍት የሚሰጥ።”

አንድ ሂን 3.67 ሊትር ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።

አንድ አሥረኛ ኢፍ 2.2 ሊትር ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።

ወይም “የሚያረጋጋ፤ የሚያበርድ።” ቃል በቃል “እረፍት የሚሰጥ።”

ወይም “የሚያረጋጋ፤ የሚያበርድ።” ቃል በቃል “እረፍት የሚሰጥ።”

ወይም “የሚያረጋጋ፤ የሚያበርድ።” ቃል በቃል “እረፍት የሚሰጥ።”

ወይም “የሚያረጋጋ፤ የሚያበርድ።” ቃል በቃል “እረፍት የሚሰጥ።”

ወይም “የሚያረጋጋ፤ የሚያበርድ።” ቃል በቃል “እረፍት የሚሰጥ።”

ወይም “ነፍስ።”

ወይም “ነፍስ።”

ወይም “ነፍስ።”

ወይም “ነፍስ።”

ወይም “ጌታ።”

ቃል በቃል “የሥጋ ሁሉ መንፈስ።”

ወይም “እኔ እንዳሻኝ ሳይሆን።”

ወይም “ሲኦል።” የሰው ልጆችን ሁሉ መቃብር ያመለክታል። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

ወይም “ሲኦል።” የሰው ልጆችን ሁሉ መቃብር ያመለክታል። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

ወይም “በገዛ ነፍሳቸው ላይ ኃጢአት የሠሩት።”

ቃል በቃል “ባዕድ ሰው።”

ቃል በቃል “ባዕድ ሰው።” የአሮን ቤተሰብ ያልሆነን ሰው ያመለክታል።

ቃል በቃል “ባዕድ ሰው።” የአሮን ቤተሰብ ያልሆነን ሰው ያመለክታል።

በማይሻርና በማይዋጅ ሁኔታ ለአምላክ ቅዱስ ተደርጎ የተሰጠን ማንኛውንም ነገር ያመለክታል።

ቃል በቃል “የሥጋ ሁሉ።”

ወይም “በቅዱሱ ሰቅል።”

አንድ ሰቅል 11.4 ግራም ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።

አንድ ጌራ 0.57 ግራም ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።

ወይም “የሚያረጋጋ፤ የሚያበርድ።” ቃል በቃል “እረፍት የሚሰጥ።”

ዘላቂና የማይለወጥ ቃል ኪዳንን ያመለክታል።

ወይም “የማንኛውንም ሰው ነፍስ አስከሬን።” የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

ወይም “አስከሬን ይኸውም የማንኛውንም የሞተ ሰው ነፍስ።” የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

ወይም “ነፍስ።”

ወይም “ነፍስ።”

ወይም “ነፍስ።”

ወይም “ነፍስም።”

“ጠብ” የሚል ትርጉም አለው።

ቃል በቃል “ቀናት።”

ቃል በቃል “እጅ።”

ይህ ሞትን የሚያመለክት ቅኔያዊ አነጋገር ነው።

ቃል በቃል “በዚያ ይሰበሰባል፣ ይሞታልም።”

“ለጥፋት የተለየ” የሚል ትርጉም አለው።

ወይም “የሕዝቡ ነፍስ።”

ወይም “ነፍሳችን ተጸይፎታል።”

ወይም “የሚያቃጥሉ።”

ወይም “የሚያቃጥል።”

ወይም “ደረቅ ወንዝ።”

ወይም “ደረቅ ወንዞች።”

ወይም “የደረቅ ወንዞች።”

ቃል በቃል “አፍ።”

ወይም “ዘምሩለት።”

“በረሃውን፤ ምድረ በዳውን” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ቃል በቃል “ሜዳ።”

ወይም “በዙሪያዋ።”

ወይም “በዙሪያዋ።”

ኤፍራጥስን ወንዝ እንደሚያመለክት ከሁኔታው መረዳት ይቻላል።

ወይም “የመሬቱን።”

ቃል በቃል “ዓይን።”

ወይም “የመሬቱን።”

ቃል በቃል “ዓይን።”

ቃል በቃል “የአህያዋን አፍ ከፈተላት።”

ወይም “ነፍሴ የቅኖች ዓይነት አሟሟት ትሙት።”

ወይም “አይጸጸትም።”

“በረሃውን፤ ምድረ በዳውን” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ቃል በቃል “በይሖዋ ዓይን መልካም እንደሆነ።”

ወይም “ደረቅ ወንዞች።”

ቃል በቃል “ከልቤ አመንጭቼ።”

ወይም “በቀኖቹ መጨረሻ።”

ወይም “ሰሪሳራ።” በዓይንና በጆሮ መካከል ያለውን የአካል ክፍል ያመለክታል።

ወይም “ከፌጎር ባአል ጋር ተጣበቀ።”

ቃል በቃል “ራሶች።”

ቃል በቃል “በፀሐይ ፊት።”

ወይም “ከፌጎር ባአል ጋር የተጣበቀውን።”

“ብልቷ” ላቲን ቩልጌት። “ማህፀኗ” የሰብዓ ሊቃናት ትርጉም።

ይህ ሞትን የሚያመለክት ቅኔያዊ አነጋገር ነው።

ቃል በቃል “የሥጋ።”

ወይም “ከክብርህ።”

ወይም “የሚያረጋጋ፤ የሚያበርድ።” ቃል በቃል “እረፍት የሚሰጥ።”

ቃል በቃል “በሁለቱ ምሽቶች መካከል።”

አንድ ሂን 3.67 ሊትር ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።

አንድ አሥረኛ ኢፍ 2.2 ሊትር ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።

ወይም “የሚያረጋጋ፤ የሚያበርድ።” ቃል በቃል “እረፍት የሚሰጥ።”

ቃል በቃል “በሁለቱ ምሽቶች መካከል።”

ወይም “የሚያረጋጋ፤ የሚያበርድ።” ቃል በቃል “እረፍት የሚሰጥ።”

ቃል በቃል “በወሮቻችሁም።”

ወይም “የሚያረጋጋ፤ የሚያበርድ።” ቃል በቃል “እረፍት የሚሰጥ።”

ወይም “የሚያረጋጋ፤ የሚያበርድ።” ቃል በቃል “እረፍት የሚሰጥ።”

ወይም “የሚያረጋጋ፤ የሚያበርድ።” ቃል በቃል “እረፍት የሚሰጥ።”

ወይም “የሚያረጋጋ፤ የሚያበርድ።” ቃል በቃል “እረፍት የሚሰጥ።”

ወይም “የሚያረጋጋ፤ የሚያበርድ።” ቃል በቃል “እረፍት የሚሰጥ።”

ወይም “ነፍሳችሁን አጎሳቁሉ።” “ራስን ማጎሳቆል” በአብዛኛው መጾምን ጨምሮ የራስን ፍላጎት ከመፈጸም መቆጠብን የሚያሳዩ የተለያዩ ድርጊቶችን ሊያመለክት ይችላል።

ወይም “የሚያረጋጋ፤ የሚያበርድ።” ቃል በቃል “እረፍት የሚሰጥ።”

ወይም “የሚያረጋጋ፤ የሚያበርድ።” ቃል በቃል “እረፍት የሚሰጥ።”

ወይም “የሚያረጋጋ፤ የሚያበርድ።” ቃል በቃል “እረፍት የሚሰጥ።”

ወይም “ነፍሱን።”

ወይም “ነፍሷን።”

ወይም “ነፍሷን።”

ይህ ሞትን የሚያመለክት ቅኔያዊ አነጋገር ነው።

ወይም “ለሚገጥመው ሠራዊት።”

ወይም “ለሠራዊቱ።”

ወይም “በግንብ የታጠሩ ሰፈሮቻቸውን።”

ወይም “ነፍስ።”

የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

ወይም “ነፍሳት።”

ወይም “ነፍሳቱ።”

ወይም “ነፍሳት።”

ወይም “ነፍስ።”

ወይም “ለነፍሳችን።”

አንድ ሰቅል 11.4 ግራም ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።

ወይም “መታሰቢያ።”

ወይም “ደረቅ ወንዝ።”

“የያኢር የድንኳን መንደሮች” የሚል ትርጉም አለው።

ወይም “በዙሪያዋ።”

ቃል በቃል “በየሠራዊቱ።”

ቃል በቃል “ወደ ላይ በተዘረጋ እጅ።”

ወይም “ቀልጠው የተሠሩ ሐውልቶቻቸውንም።”

ሙት ባሕርን ያመለክታል።

የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

ታላቁን ባሕር፣ ሜድትራንያንን ያመለክታል።

ሜድትራንያንን ያመለክታል።

ወይም “ሃማት መግቢያ።”

ጌንሴሬጥ ሐይቅን ወይም ገሊላ ባሕርን ያመለክታል።

አንድ ክንድ 44.5 ሴንቲ ሜትር ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።

ወይም “ነፍስ መትቶ የገደለ።”

ወይም “ነፍስ መትቶ የገደለ።”

ቃል በቃል “አድብቶ።”

ቃል በቃል “አድብቶ።”

ወይም “ነፍስ።”

ቃል በቃል “በምሥክሮች አፍ።”

ቃል በቃል “ነፍስ።”

ወይም “ነፍስ።”

ቃል በቃል “ነፍስ።”

    የኢትዮጵያ ምልክት ቋንቋ ጽሑፎች (2011-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • የኢትዮጵያ ምልክት ቋንቋ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ