የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
የኢትዮጵያ ምልክት ቋንቋ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • nwt ኢሳይያስ 1:1-66:24
  • ኢሳይያስ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ኢሳይያስ
  • አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ
አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ
ኢሳይያስ

ኢሳይያስ

1 የይሁዳ ነገሥታት+ በሆኑት በዖዝያ፣+ በኢዮዓታም፣+ በአካዝና+ በሕዝቅያስ+ ዘመን የአሞጽ ልጅ ኢሳይያስ* ስለ ይሁዳና ስለ ኢየሩሳሌም ያየው ራእይ፦+

 2 ሰማያት ሆይ፣ ስሙ፤ ምድር ሆይ፣ አድምጪ፤+

ይሖዋ እንዲህ ሲል ተናግሯልና፦

“ወንዶች ልጆችን ተንከባክቤ አሳደግኩ፤+

እነሱ ግን በእኔ ላይ ዓመፁ።+

 3 በሬ ጌታውን፣

አህያም የባለቤቱን ጋጣ በሚገባ ያውቃል፤

እስራኤል ግን እኔን* አላወቀም፤+

የገዛ ሕዝቤም አላስተዋለም።”

 4 ኃጢአተኛ የሆነው ብሔር፣+

ከባድ በደል የተጫነው ሕዝብ፣

የክፉዎች ዘር፣ ብልሹ የሆኑ ልጆች ወዮላቸው!

እነሱ ይሖዋን ትተዋል፤+

የእስራኤልን ቅዱስ አቃለዋል፤

ጀርባቸውን ሰጥተውታል።

 5 በዓመፅ ላይ ዓመፅ የምትጨምሩት፣ አሁን ደግሞ ምናችሁ ላይ መመታት ፈልጋችሁ ነው?+

መላው ራስ ታሟል፤

መላው ልብም በበሽታ ተይዟል።+

 6 ከእግር ጥፍር አንስቶ እስከ ራስ ፀጉር ድረስ አንድም ጤነኛ የአካል ክፍል የለም።

በቁስልና በሰምበር ተሞልቷል፤ እንዲሁም ተተልትሏል፤

ቁስሉ አልታከመም* ወይም አልታሰረም አሊያም በዘይት አለዘበም።+

 7 ምድራችሁ ባድማ ሆኗል።

ከተሞቻችሁ በእሳት ጋይተዋል።

የባዕድ አገር ሰዎች ዓይናችሁ እያየ ምድራችሁን ይውጣሉ።+

ባዕዳን እንዳወደሙት ጠፍ መሬት ሆኗል።+

 8 የጽዮን ሴት ልጅ በወይን እርሻ ውስጥ እንዳለ መጠለያ፣*

በኪያር የእርሻ ቦታ እንዳለ ጎጆ፣

እንደተከበበችም ከተማ ተትታለች።+

 9 የሠራዊት ጌታ ይሖዋ ጥቂት ሰዎች ከጥፋት እንዲተርፉልን ባያደርግ ኖሮ

እንደ ሰዶም በሆንን፣

ገሞራንም በመሰልን ነበር።+

10 እናንተ የሰዶም+ አምባገነኖች፣* የይሖዋን ቃል ስሙ።

እናንተ የገሞራ+ ሰዎች፣ የአምላካችንን ሕግ* አዳምጡ።

11 “የመሥዋዕታችሁ ብዛት ለእኔ ምን ይጠቅመኛል?”+ ይላል ይሖዋ።

“የሚቃጠሉ የአውራ በግ መባዎችና+ የደለቡ እንስሳት ስብ+ በቅቶኛል፤

በወይፈኖች፣+ በበግ ጠቦቶችና በፍየሎች+ ደም+ ደስ አልሰኝም።

12 በፊቴ ለመቅረብ የምትመጡት፣+

ይህን እንድታደርጉ፣

የቤተ መቅደሴን ግቢ እንድትረግጡ ማን ጠይቋችሁ ነው?+

13 ከንቱ የሆኑትን የእህል መባዎች ከዚህ በኋላ አታምጡ።

ዕጣናችሁ በፊቴ አስጸያፊ ነው።+

የአዲስ ጨረቃ+ በዓልንና ሰንበትን+ ታከብራላችሁ፤ ስብሰባም+ ትጠራላችሁ።

በአንድ በኩል የተቀደሱ ጉባኤዎችን እያከበራችሁ በሌላ በኩል የምትፈጽሙትን አስማታዊ ድርጊት+ መታገሥ አልችልም።

14 የአዲስ ጨረቃ በዓሎቻችሁንና ሌሎች በዓሎቻችሁን ጠልቻለሁ።*

ለእኔ ሸክም ሆነውብኛል፤

እነሱንም ከመሸከሜ የተነሳ ዝያለሁ።

15 እጆቻችሁን ስትዘረጉ

ዓይኖቼን ከእናንተ እሰውራለሁ።+

ጸሎት ብታበዙም እንኳ+

አልሰማችሁም፤+

እጆቻችሁ በደም ተሞልተዋል።+

16 ታጠቡ፤ ራሳችሁንም አንጹ፤+

ክፉ ሥራችሁን ከፊቴ አስወግዱ፤

መጥፎ ድርጊት መፈጸማችሁን አቁሙ።+

17 መልካም ማድረግን ተማሩ፤ ፍትሕን ፈልጉ፤+

ጨቋኙ እንዲታረም አድርጉ፤

አባት የሌለውን ልጅ* መብት አስከብሩ፤

ለመበለቲቱም ተሟገቱ።”+

18 “ኑና በመካከላችን የተፈጠረውን ችግር ተወያይተን እንፍታ” ይላል ይሖዋ።+

“ኃጢአታችሁ እንደ ደም ቢቀላ

እንደ በረዶ ይነጣል፤+

እንደ ደማቅ ቀይ ጨርቅ ቢቀላም

እንደ ነጭ የሱፍ ጨርቅ ይሆናል።

19 እሺ ብትሉና ብትታዘዙ

የምድሪቱን መልካም ፍሬ ትበላላችሁ።+

20 እንቢ ብትሉና ብታምፁ ግን

ሰይፍ ይበላችኋል፤+

የይሖዋ አፍ ይህን ተናግሯልና።”

21 ታማኝ የነበረችው ከተማ+ እንዴት ዝሙት አዳሪ ሆነች!+

ፍትሕ የሞላባትና+

ጽድቅ የሰፈነባት ነበረች፤+

አሁን ግን የነፍሰ ገዳዮች ጎሬ ሆናለች።+

22 ብርሽ እንደ ዝቃጭ ሆኗል፤+

መጠጥሽ* በውኃ ተበርዟል።

23 አለቆችሽ ግትሮችና የሌባ ግብረ አበሮች ናቸው።+

ሁሉም ጉቦ የሚወዱና እጅ መንሻ የሚያሳድዱ ናቸው።+

አባት የሌለው ልጅ ፍትሕ እንዲያገኝ* አያደርጉም፤

የመበለቲቱም አቤቱታ ወደ እነሱ አይደርስም።+

24 ስለዚህ እውነተኛው ጌታ፣ የሠራዊት ጌታ ይሖዋ፣

የእስራኤል ኃያል አምላክ እንዲህ ይላል፦

“እንግዲያው ስሙ! ባላጋራዎቼን አጠፋለሁ፤

ጠላቶቼንም እበቀላለሁ።+

25 እጄን በአንቺ ላይ አነሳለሁ፤

በመርዝ የማጥራት ያህል ቆሻሻሽን አቅልጬ አወጣለሁ፤

ዝቃጭሽንም ሁሉ አስወግዳለሁ።+

26 መጀመሪያ ላይ እንደነበረው ፈራጆችሽን፣

እንደቀድሞውም አማካሪዎችሽን መልሼ አመጣለሁ።+

ከዚያ በኋላ የጽድቅ መዲና፣ የታመነች ከተማ ተብለሽ ትጠሪያለሽ።+

27 ጽዮን በፍትሕ፣

የሚመለሱት ነዋሪዎቿም በጽድቅ ይቤዣሉ።+

28 ዓመፀኞችና ኃጢአተኞች በአንድ ላይ ይደቅቃሉ፤+

ይሖዋን የሚተዉም ያከትምላቸዋል።+

29 እናንተ በተመኛችኋቸው ግዙፍ ዛፎች ያፍራሉና፤+

በመረጣችኋቸው የአትክልት ቦታዎች* የተነሳም ትዋረዳላችሁ።+

30 ቅጠሉ እንደጠወለገ ትልቅ ዛፍ፣+

ውኃም እንደሌለው የአትክልት ቦታ ትሆናላችሁና።

31 ብርቱውም ሰው እንደ ተልባ እግር* ይሆናል፤

የሥራውም ውጤት እንደ እሳት ብልጭታ ይሆናል፤

ሁለቱም አብረው ይቃጠላሉ፤

እሳቱንም ማጥፋት የሚችል ማንም የለም።”

2 የአሞጽ ልጅ ኢሳይያስ ስለ ይሁዳና ስለ ኢየሩሳሌም ያየው ይህ ነው፦+

 2 በዘመኑ መጨረሻ*

የይሖዋ ቤት ተራራ

ከተራሮች አናት በላይ ጸንቶ ይቆማል፤+

ከኮረብቶችም በላይ ከፍ ከፍ ይላል፤

ብሔራትም ሁሉ ወደዚያ ይጎርፋሉ።+

 3 ብዙ ሕዝቦችም ሄደው እንዲህ ይላሉ፦

“ኑ፤ ወደ ይሖዋ ተራራ፣

ወደ ያዕቆብ አምላክ ቤት እንውጣ።+

እሱ ስለ መንገዶቹ ያስተምረናል፤

በጎዳናዎቹም እንሄዳለን።”+

ሕግ* ከጽዮን፣

የይሖዋም ቃል ከኢየሩሳሌም ይወጣልና።+

 4 እሱ በብሔራት መካከል ይፈርዳል፤

ከብዙ ሕዝቦች ጋር በተያያዘም ሁሉንም ነገር ያቀናል።*

እነሱ ሰይፋቸውን ማረሻ፣

ጦራቸውንም ማጭድ ለማድረግ ይቀጠቅጣሉ።+

አንዱ ብሔር በሌላው ብሔር ላይ ሰይፍ አያነሳም፤

ከእንግዲህ ወዲህ ጦርነት አይማሩም።+

 5 እናንተ የያዕቆብ ቤት ሆይ፣ ኑ፤

በይሖዋ ብርሃን እንሂድ።+

 6 አንተ ሕዝብህን ይኸውም የያዕቆብን ቤት ትተሃል፤+

ምክንያቱም እነሱ ከምሥራቅ በመጡ ነገሮች ተሞልተዋል፤

እንደ ፍልስጤማውያን የአስማት ድርጊቶችን ይፈጽማሉ፤+

በባዕድ አገር ሰዎች ልጆችም ተጥለቅልቀዋል።

 7 ምድራቸው በብርና በወርቅ ተሞልታለች፤

ሀብታቸውም ገደብ የለውም።

ምድራቸው በፈረሶች ተሞልታለች፤

ሠረገሎቻቸውም ስፍር ቁጥር የላቸውም።+

 8 ምድራቸውም ከንቱ በሆኑ አማልክት ተጥለቅልቃለች።+

የገዛ እጃቸው ለሠራው፣

የገዛ ጣታቸውም ላበጀው ነገር ይሰግዳሉ።

 9 በመሆኑም ሰው አንገቱን ይደፋል፤ ኀፍረትም ይከናነባል፤

አንተም ይቅር ልትላቸው አትችልም።

10 ይሖዋ አስፈሪ ከመሆኑ የተነሳና

ከታላቅ ግርማው የተነሳ

በዓለት ውስጥ ተደበቅ፤ በመሬትም ውስጥ ተሸሸግ።+

11 ትዕቢተኛ ዓይኖች ይዋረዳሉ፤

እብሪተኛ ሰዎችም አንገታቸውን ይደፋሉ።*

በዚያም ቀን ይሖዋ ብቻ ከፍ ከፍ ይደረጋል።

12 ይህ ቀን የሠራዊት ጌታ የይሖዋ ነውና።+

ቀኑ ትዕቢተኛና ኩሩ በሆነው ሁሉ ላይ፣

ከፍ ባለውም ሆነ ዝቅ ባለው ሁሉ ላይ ይመጣል፤+

13 ታላላቅ በሆኑትና ከፍ ከፍ ባሉት አርዘ ሊባኖሶች ሁሉ ላይ

እንዲሁም በባሳን የባሉጥ ዛፎች ሁሉ ላይ፣

14 ታላላቅ በሆኑት ተራሮች ሁሉና

በረጃጅም ኮረብቶች ሁሉ ላይ፣

15 ረጅም በሆነ ማማ ሁሉና ጠንካራ በሆነ ግንብ ሁሉ ላይ፣

16 በተርሴስ መርከቦች+ ሁሉና

በሚያማምሩ ጀልባዎች ሁሉ ላይ ይደርሳል።

17 ትዕቢተኛ ሰው ይዋረዳል፤

እብሪተኞችም አንገታቸውን ይደፋሉ።*

በዚያም ቀን ይሖዋ ብቻ ከፍ ከፍ ይደረጋል።

18 ከንቱ የሆኑት አማልክት ሙሉ በሙሉ ይወገዳሉ።+

19 ይሖዋ ምድርን በሽብር ለማንቀጥቀጥ በሚነሳበት ጊዜ፣

አስፈሪ ከመሆኑ የተነሳና

ከታላቅ ግርማው የተነሳ+

ሰዎች በዓለት ዋሻዎችና

በጉድጓዶች ውስጥ* ይደበቃሉ።+

20 በዚያ ቀን፣ ሰዎች በፊታቸው ይሰግዱ ዘንድ

ለራሳቸው የሠሯቸውን ከንቱ የሆኑ የብርና የወርቅ አማልክት

ለአይጦችና* ለሌሊት ወፎች ይወረውራሉ፤+

21 ይሖዋ ምድርን በሽብር ለማንቀጥቀጥ በሚነሳበት ጊዜ፣

አስፈሪ ከመሆኑ የተነሳና

ከታላቅ ግርማው የተነሳ

በዓለት ዋሻዎችና

በቋጥኝ ስንጥቆች ውስጥ ይደበቃሉ።

22 ለራሳችሁ ስትሉ፣

ከአፍንጫው እንደሚወጣ እስትንፋስ በሆነ ሰው* አትታመኑ።

ለመሆኑ እሱ ያን ያህል ቦታ እንዲሰጠው የሚያደርግ ምን ነገር አለ?

3 እነሆ፣ እውነተኛው ጌታ፣ የሠራዊት ጌታ ይሖዋ

ኢየሩሳሌምና ይሁዳ ማንኛውም ዓይነት ድጋፍና አቅርቦት

ይኸውም የምግብና የውኃ አቅርቦት ሁሉ እንዲቋረጥባቸው ያደርጋል፤+

 2 ኃያሉን ሰውና ተዋጊውን፣

ዳኛውንና ነቢዩን፣+ ሟርተኛውንና ሽማግሌውን፣

 3 የሃምሳ አለቃውን፣+ ባለሥልጣኑንና አማካሪውን፣

በአስማት የተካነውንና በድግምት የላቀ ችሎታ ያለውን ያስወግዳል።+

 4 በእነሱ ላይ ልጆችን መኳንንት አድርጌ እሾማለሁ፤

ያልሰከነ* ሰውም ይገዛቸዋል።

 5 ሕዝቡ አንዱ ሌላውን፣

እያንዳንዱም ባልንጀራውን ይጨቁናል።+

ልጅ በሽማግሌ ላይ ጥቃት ይሰነዝራል፤

ተራው ሰውም የተከበረውን ይዳፈራል።+

 6 እያንዳንዱ ሰው በአባቱ ቤት የሚኖረውን ወንድሙን ይዞ

“አንተ ካባ አለህ፤ ስለዚህ በእኛ ላይ አዛዥ ሁን።

ይህን የፍርስራሽ ክምር ግዛ” ይለዋል።

 7 እሱ ግን በዚያ ቀን እንዲህ ሲል ይቃወማል፦

“እኔ ቁስላችሁን አላክምም፤*

በቤቴ ምግብም ሆነ ልብስ የለም።

በሕዝቡ ላይ አዛዥ አድርጋችሁ አትሹሙኝ።”

 8 ኢየሩሳሌም ተሰናክላለችና፤

ይሁዳም ወድቃለች፤

ምክንያቱም እነሱ በአንደበታቸውም ሆነ በሥራቸው ይሖዋን ይቃወማሉ፤

በክብራማው አምላክ ፊት* አሻፈረን ይላሉ።+

 9 የፊታቸው ገጽታ ይመሠክርባቸዋል፤

ደግሞም እንደ ሰዶም+ ኃጢአታቸውን በይፋ ይናገራሉ፤

ኃጢአታቸውን ለመደበቅ አይሞክሩም።

በራሳቸው ላይ ጥፋት ስለሚያመጡ ወዮላቸው!*

10 ለጻድቃን መልካም እንደሚሆንላቸው ንገሯቸው፤

ለሥራቸው ወሮታ ይከፈላቸዋል።*+

11 ለክፉ ሰው ወዮለት!

ጥፋት ይደርስበታል፤

በሌሎች ላይ ሲያደርግ የነበረው በራሱ ላይ ይደርሳልና!

12 የሕዝቤ አሠሪዎች ጨቋኞች ናቸው፤

ሴቶችም ይገዟቸዋል።

ሕዝቤ ሆይ፣ የሚመሯችሁ ሰዎች እንድትባዝኑና

በየትኛው መንገድ እንደምትሄዱ ግራ እንድትጋቡ እያደረጓችሁ ነው።+

13 ይሖዋ ለመክሰስ ተሰይሟል፤

በሕዝቦች ላይ ብያኔውን ለማሰማት ተነስቷል።

14 ይሖዋ የሕዝቡን ሽማግሌዎችና አለቆች ይፋረዳል።

“የወይኑን እርሻ አቃጥላችኋል፤

ከድሃው የዘረፋችሁት ንብረትም በቤታችሁ ይገኛል።+

15 ሕዝቤን የምታደቁት፣ የድሆችንም ፊት መሬት ላይ የምትፈጩት

እንዴት ብትዳፈሩ ነው?”+ ይላል ሉዓላዊው ጌታ፣ የሠራዊት ጌታ ይሖዋ።

16 ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “የጽዮን ሴቶች ልጆች ትዕቢተኛ ስለሆኑ፣

ራሳቸውን ቀና አድርገው* ስለሚራመዱ፣

በዓይናቸው እየተጣቀሱና እየተውረገረጉ በመሄድ

እግራቸው ላይ ያደረጉትን አልቦ ስለሚያቃጭሉ፣

17 ይሖዋ የጽዮንን ሴቶች አናት በቁስል ይመታል፤

ደግሞም ይሖዋ ግንባራቸውን ይገልጣል።+

18 በዚያ ቀን ይሖዋ ጌጦቻቸውን ሁሉ ይነጥቃል፦

አልቦውን፣ የፀጉር ጌጡን፣ የጨረቃ ቅርጽ ያለውን ጌጥ፣+

19 የጆሮ ጉትቻውን፣* አምባሩን፣ መከናነቢያውን፣

20 የራስ መሸፈኛውን፣ የሰንሰለት አልቦውን፣ ጌጠኛውን መቀነት፣*

የሽቶ ዕቃውን፣* ክታቡን፣

21 የጣት ቀለበቱን፣ የአፍንጫ ቀለበቱን፣

22 የክት ልብሱን፣ መደረቢያውን፣ ካባውን፣ የእጅ ቦርሳውን፣

23 የእጅ መስተዋቱን፣+ የበፍታ ልብሶቹን፣*

ጥምጥሙንና መከናነቢያውን ይወስድባቸዋል።

24 በበለሳን ዘይት+ መዓዛ ፋንታ የጠነባ ሽታ፣

በመታጠቂያ ፋንታ ገመድ፣

አምሮ በተሠራ ፀጉር ፋንታ መላጣነት፣+

ባማረ ልብስ ፋንታ ማቅ፣+

በውበትም ፋንታ ጠባሳ* ይሆናል።

25 ወንዶችሽ በሰይፍ፣

ኃያላኖችሽም በውጊያ ይወድቃሉ።+

26 የከተማዋም መግቢያዎች ያዝናሉ፣ ያለቅሳሉም፤+

እሷም ባዶዋን ቀርታ በሐዘን መሬት ላይ ትቀመጣለች።”+

4 በዚያን ቀን ሰባት ሴቶች አንድን ወንድ ይዘው እንዲህ ይሉታል፦+

“የራሳችንን ምግብ እንበላለን፤

የራሳችንንም ልብስ እንለብሳለን፤

ብቻ በእኛ ላይ የደረሰው ውርደት* እንዲወገድ+

በአንተ ስም እንድንጠራ ፍቀድልን።”

2 በዚያን ቀን፣ ይሖዋ እንዲያቆጠቁጥ ያደረገው ተክል ያማረና ክብር የተላበሰ ይሆናል፤ የምድሪቱም ፍሬ ከጥፋት ለተረፉት እስራኤላውያን የኩራት ምንጭና ውበት ይሆንላቸዋል።+ 3 በጽዮን የቀሩትና በኢየሩሳሌም የተረፉት ሁሉ ይኸውም በኢየሩሳሌም እንዲኖሩ የተመዘገቡት በጠቅላላ ቅዱሳን ተብለው ይጠራሉ።+

4 ይሖዋ በፍርድ መንፈስና በሚነድ* መንፈስ+ የጽዮንን ሴቶች ልጆች ቆሻሻ* አጥቦ ያስወግዳል፤+ የኢየሩሳሌምንም የደም ዕዳ ከመካከሏ አጥቦ ያነጻል፤ 5 ያን ጊዜ ይሖዋ በመላው የጽዮን ተራራ ላይና በመሰብሰቢያ ቦታዋ ላይ በቀን ደመናና ጭስ፣ በሌሊት ደግሞ የሚንበለበል የእሳት ብርሃን ይፈጥራል፤+ እንዲሁም ክብራማ በሆነው ቦታ ሁሉ ላይ መጠለያ ይኖራል። 6 ደግሞም በቀን ካለው ንዳድ ጥላ+ እንዲሁም ከውሽንፍርና ከዝናብ መጠጊያና መሸሸጊያ+ የሚሆን ዳስ ይኖራል።

5 እስቲ ለወዳጄ መዝሙር ልዘምር።

መዝሙሩ ስለ ወዳጄና ስለ ወይን እርሻው+ የሚገልጽ ነው።

ወዳጄ ለም በሆነ ኮረብታ ላይ የወይን እርሻ ነበረው።

 2 እሱም መሬቱን ቆፈረ፤ ድንጋዮቹንም አስወገደ።

ምርጥ የሆነ ቀይ ወይን ተከለ፤

በመካከሉ ማማ ገነባ፤

ድንጋይ ፈልፍሎም የወይን መጭመቂያ ጉድጓድ ሠራ።+

ከዚያም ‘ወይኑ ጥሩ ፍሬ ያፈራል’ ብሎ ይጠብቅ ጀመር፤

ይሁንና መጥፎ ፍሬ ብቻ አፈራ።+

 3 “እናንተ የኢየሩሳሌም ነዋሪዎችና የይሁዳ ሰዎች ሆይ፣

በእኔና በወይን እርሻዬ መካከል እስቲ ፍረዱ።+

 4 ለወይን እርሻዬ ከዚህ በላይ ላደርግለት የሚገባ

ምን ነገር አለ?+

‘ጥሩ ወይን ያፈራል’ ብዬ ስጠብቅ

መጥፎ ወይን ብቻ ያፈራው ለምንድን ነው?

 5 እንግዲህ በወይን እርሻዬ ላይ

ምን እንደማደርግ ልንገራችሁ፦

በዙሪያው ያለውን የቁጥቋጦ አጥር እነቅላለሁ፤

ለእሳትም ይማገዳል።+

የድንጋይ ቅጥሩን አፈርሳለሁ፤

በእግርም ይረጋገጣል።

 6 ቦታውን ጠፍ መሬት አደርገዋለሁ፤+

የወይን ተክሉ አይገረዝም እንዲሁም አይኮተኮትም።

ቁጥቋጦና አረም ይወርሰዋል፤+

ደመናቱም ዝናብ እንዳያዘንቡበት ትእዛዝ እሰጣለሁ።+

 7 የሠራዊት ጌታ የይሖዋ የወይን እርሻ የእስራኤል ቤት ነውና፤+

የይሁዳ ሰዎች እሱ ይወደው የነበረው የአትክልት ቦታ ናቸው።*

ፍትሕን ሲጠብቅ+

እነሆ፣ ግፍ ይፈጸማል፤

‘ጽድቅ ይሰፍናል’ ብሎ ሲጠብቅ

እነሆ፣ የጭንቅ ጩኸት ይሰማል።”+

 8 ቦታ እስኪጠፋ ድረስ

በቤት ላይ ቤት ለሚጨምሩና+

በመሬት ላይ መሬት ለሚይዙ ወዮላቸው!+

እናንተም በምድሪቱ ላይ ብቻችሁን ትቀመጣላችሁ።

 9 የሠራዊት ጌታ ይሖዋ ጆሮዬ እየሰማ እንዲህ ሲል ማለ፦

ብዙ ቤቶች ታላላቅና ያማሩ ቢሆኑም እንኳ

አንድም ነዋሪ የማይገኝባቸው

አስፈሪ ቦታዎች ይሆናሉ።+

10 ከአራት ሄክታር* የወይን እርሻ አንድ የባዶስ* መስፈሪያ ብቻ ይገኛል፤

ከአንድ የሆሜር* መስፈሪያ ዘርም አንድ የኢፍ* መስፈሪያ ብቻ ይገኛል።+

11 የሚያሰክር መጠጥ ለመጠጣት በማለዳ ለሚነሱ፣+

የወይን ጠጅ እስከሚያቃጥላቸው ድረስ እስከ ሌሊት ለሚያመሹ ወዮላቸው!

12 በግብዣቸው ላይ በገና፣ ባለ አውታር መሣሪያ፣

አታሞና ዋሽንት እንዲሁም የወይን ጠጅ አለ፤

እነሱ ግን ይሖዋ ያከናወነውን ተግባር አያስቡም፤

የእጁንም ሥራ አይመለከቱም።

13 ስለዚህ ሕዝቤ እውቀት በማጣቱ+

ተማርኮ ይወሰዳል፤

በመካከላቸው የሚገኙ የተከበሩ ሰዎች ይራባሉ፤+

ሕዝባቸውም እንዳለ በውኃ ጥም ይቃጠላል።

14 በመሆኑም መቃብር* ራሷን* አሰፋች፤

አፏንም ያለልክ ከፈተች፤+

የከተማዋ ውበት፣* የሚንጫጫው ሕዝቧና በውስጧ የሚፈነጥዙት ሰዎች

ወደዚያ ይወርዳሉ።

15 ሰውም አንገቱን ይደፋል፤

የሰው ልጅ ኀፍረት ይከናነባል፤

የትዕቢተኞችም ዓይን ይዋረዳል።

16 የሠራዊት ጌታ ይሖዋ በሚሰጠው ፍርድ* ከፍ ከፍ ይላል፤

ቅዱስ+ የሆነው እውነተኛው አምላክ በጽድቅ ራሱን ይቀድሳል።+

17 የበግ ጠቦቶችም በገዛ መሰማሪያቸው እንደተሰማሩ ሆነው ይግጣሉ፤

የባዕድ አገር ሰዎች፣ የሰቡ እንስሳት ይኖሩባቸው በነበሩ ወና የሆኑ ቦታዎች ይበላሉ።

18 በደላቸውን በአታላይ ገመድ የሚስቡ፣

ኃጢአታቸውንም በሠረገላ ገመድ የሚጎትቱ ወዮላቸው፤

19 “ሥራውን ያፋጥን፤

እናየውም ዘንድ ቶሎ ይምጣ።

እናውቀውም ዘንድ

የእስራኤል ቅዱስ አምላክ ዓላማ* ይፈጸም” የሚሉ ወዮላቸው!+

20 ጥሩውን መጥፎ፣ መጥፎውንም ጥሩ የሚሉ፣+

ጨለማውን በብርሃን፣ ብርሃኑን በጨለማ የሚተኩ

ጣፋጩን መራራ፣ መራራውን ጣፋጭ አድርገው የሚያቀርቡ ወዮላቸው!

21 በገዛ ዓይናቸው ጥበበኛ የሆኑና

በራሳቸው አመለካከት ልባም የሆኑ ወዮላቸው!+

22 የወይን ጠጅ በመጠጣት ረገድ ብርቱዎች የሆኑ፣

መጠጥ በመደባለቅም የተካኑ ወዮላቸው፤+

23 ጉቦ በመቀበል ክፉውን ከበደል ነፃ የሚያደርጉ፣+

ጻድቁንም ፍትሕ የሚነፍጉ ወዮላቸው!+

24 የእሳት ነበልባል ገለባን እንደሚበላ፣

የደረቀም ሣር በነበልባል በንኖ እንደሚጠፋ

የእነሱም ሥር ይበሰብሳል፤

አበባቸውም ልክ እንደ ዱቄት በየቦታው ይበናል፤

ምክንያቱም እነሱ የሠራዊት ጌታ የሆነውን የይሖዋን ሕግ* ለመቀበል አሻፈረን ብለዋል፣

የእስራኤል ቅዱስ የተናገረውንም ቃል ንቀዋል።+

25 የይሖዋ ቁጣ በሕዝቡ ላይ የነደደው በዚህ ምክንያት ነው፤

እሱም እጁን በእነሱ ላይ ይዘረጋል፤ ይመታቸዋልም።+

ተራሮችም ይናወጣሉ፤

አስከሬናቸውም በጎዳናዎች ላይ እንዳለ ቆሻሻ ይሆናል።+

ከዚህ ሁሉ የተነሳ ቁጣው አልተመለሰም፤

ይልቁንም እጁ ለመምታት ገና እንደተዘረጋ ነው።

26 በሩቅ ላለ ታላቅ ሕዝብም ምልክት* አቁሟል፤+

ከምድር ዳርቻ እንዲመጡ በፉጨት ጠርቷቸዋል፤+

እነሆም፣ ሕዝቡ በከፍተኛ ፍጥነት እየመጣ ነው።+

27 ከእነሱ መካከል የደከመም ሆነ የሚደናቀፍ አንድም ሰው የለም።

የሚያንጎላጅም ሆነ የሚተኛ የለም።

በወገባቸውም ላይ ያለው ቀበቶ አልተፈታም፤

እንዲሁም የጫማቸው ማሠሪያ አልተበጠሰም።

28 ፍላጻዎቻቸው ሁሉ የሾሉ፣

ደጋኖቻቸውም በሙሉ የተወጠሩ* ናቸው።

የፈረሶቻቸው ኮቴ እንደ ባልጩት ድንጋይ ነው፤

የሠረገሎቻቸውም መንኮራኩሮች* እንደ አውሎ ነፋስ ናቸው።+

29 ጩኸታቸው እንደ አንበሳ ነው፤

እንደ ደቦል አንበሳ ያገሳሉ።+

የጉርምርምታ ድምፅ እያሰሙ አድብተው ይይዛሉ፤

ከእጃቸውም የሚያስጥል ስለሌለ ተሸክመውት ይሄዳሉ።

30 በዚያም ቀን እንደ ባሕር ሞገድ

ያጉረመርሙበታል።+

ምድሪቷን ትኩር ብሎ የሚመለከት ማንኛውም ሰው የሚያስጨንቅ ጨለማ ያያል፤

ብርሃኑም እንኳ ከደመናው የተነሳ ጨልሟል።+

6 ንጉሥ ዖዝያ በሞተበት ዓመት+ ይሖዋን በረጅምና ከፍ ባለ ዙፋን ላይ ተቀምጦ አየሁት፤+ የልብሱም ዘርፍ ቤተ መቅደሱን ሞልቶት ነበር። 2 ሱራፌልም ከእሱ በላይ ቆመው ነበር፤ እያንዳንዳቸውም ስድስት ክንፎች ነበሯቸው። እያንዳንዱ* በሁለቱ ክንፍ ፊቱን ይሸፍን፣ በሁለቱ ክንፍ እግሩን ይሸፍን፣ በሁለቱ ክንፍ ደግሞ ይበር ነበር።

 3 አንዳቸውም ሌላውን እንዲህ ይሉ ነበር፦

“የሠራዊት ጌታ ይሖዋ ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ ነው።+

መላዋ ምድር በክብሩ ተሞልታለች።”

4 ከድምፁ ጩኸት* የተነሳ የበሩ መቃኖች ተናወጡ፤ ቤቱም በጭስ ተሞላ።+

 5 በዚህ ጊዜ እንዲህ አልኩ፦ “ወዮልኝ!

ከንፈሮቼ የረከሱብኝ ሰው ስለሆንኩና

የምኖረውም ከንፈራቸው በረከሰ ሕዝብ+ መካከል ስለሆነ

በቃ መሞቴ ነው፤*

ዓይኖቼ ንጉሡን፣ የሠራዊት ጌታ ይሖዋን ራሱን አይተዋልና!”

6 በዚህ ጊዜ ከሱራፌል አንዱ ወደ እኔ እየበረረ መጣ፤ እሱም ከመሠዊያው ላይ በጉጠት ያነሳውን ፍም+ በእጁ ይዞ ነበር።+ 7 አፌንም ነክቶ እንዲህ አለኝ፦

“እነሆ፣ ይህ ከንፈሮችህን ነክቷል።

በደልህ ተወግዶልሃል፤

ኃጢአትህም ተሰርዮልሃል።”

8 ከዚያም የይሖዋ ድምፅ “ማንን እልካለሁ? ማንስ ይሄድልናል?”+ ሲል ሰማሁ። እኔም “እነሆኝ! እኔን ላከኝ!” አልኩ።+

 9 እሱም መልሶ እንዲህ አለኝ፦ “ሄደህ ይህን ሕዝብ እንዲህ በለው፦

‘ደጋግማችሁ ትሰማላችሁ፣

ነገር ግን አታስተውሉም፤

ደጋግማችሁ ታያላችሁ፣

ነገር ግን ምንም እውቀት አታገኙም።’+

10 በዓይናቸው እንዳያዩ፣

በጆሯቸውም እንዳይሰሙ፣

ልባቸውም እንዳያስተውል፣

ተመልሰውም እንዳይፈወሱ

የዚህን ሕዝብ ልብ አደንድን፤+

ጆሯቸውንም ድፈን፤+

ዓይናቸውንም ሸፍን።”+

11 በዚህ ጊዜ “ይሖዋ ሆይ፣ እስከ መቼ ነው?” አልኩ። እሱም እንዲህ አለኝ፦

“ከተሞች እስኪፈራርሱና የሚኖርባቸው እስኪያጡ፣

ቤቶችም ሰው አልባ እስኪሆኑ፣

ምድሪቱም እስክትጠፋና ባድማ እስክትሆን ድረስ ነው፤+

12 ይሖዋም ሰዎችን ወደ ሩቅ ቦታ እስከሚሰድ፣+

የምድሪቱም በረሃነት በእጅጉ እስኪስፋፋ ድረስ ነው።

13 “ይሁንና በእሷ ውስጥ አንድ አሥረኛ ይቀራል፤ እሱም በድጋሚ ይቃጠላል፤ ከተቆረጡ በኋላ ጉቷቸው እንደሚቀር እንደ ትልቅ ዛፍና እንደ ባሉጥ ዛፍ ይሆናል፤ በምድሪቱ ላይ የቀረው ጉቶ የተቀደሰ ዘር ይሆናል።”

7 በዖዝያ+ ልጅ፣ በኢዮዓታም ልጅ በይሁዳ ንጉሥ በአካዝ ዘመን፣ የሶርያው ንጉሥ ረጺንና የእስራኤል ንጉሥ የሆነው የረማልያህ ልጅ ፋቁሄ+ ኢየሩሳሌምን ሊወጉ ወጡ፤ እሱ ግን ድል ሊያደርጋት አልቻለም።*+ 2 የዳዊት ቤት፣ “ሶርያ ከኤፍሬም ጋር ግንባር ፈጥራለች” የሚል ወሬ ደረሰው።

በዚህ ጊዜ የአካዝም ሆነ የሕዝቡ ልብ በነፋስ እንደሚናወጥ የዱር ዛፍ መናወጥ ጀመረ።

3 ከዚያም ይሖዋ ኢሳይያስን እንዲህ አለው፦ “እባክህ፣ አንተና ልጅህ ሸአርያሹብ*+ ከአካዝ ጋር ለመገናኘት ወደ አጣቢው እርሻ በሚወስደው መንገድ አጠገብ ወዳለው ወደ ላይኛው ኩሬ የውኃ መውረጃ ቦይ ጫፍ ውጡ።+ 4 እንዲህም በለው፦ ‘አይዞህ፣ ተረጋጋ። በእነዚህ ከእሳት ተርፈው በሚጤሱ ሁለት የግንድ ጉማጆች ማለትም በሶርያ ንጉሥ በረጺንና በረማልያህ+ ልጅ ኃይለኛ ቁጣ የተነሳ አትፍራ፤ ልብህም አይደንግጥ። 5 ሶርያ ከኤፍሬምና ከረማልያህ ልጅ ጋር እንዲህ ብላ አሲራብሃለች፦ 6 “በይሁዳ ላይ እንዝመትና እንበታትነው፤* በቁጥጥራችንም ሥር እናውለው፤* የታብኤልንም ልጅ እናንግሥበት።”+

7 “‘ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦

“ይህ ሴራ አይሳካም፤

ደግሞም አይፈጸምም።

 8 የሶርያ ራስ ደማስቆ፣

የደማስቆ ራስ ደግሞ ረጺን ነውና።

ኤፍሬም በ65 ዓመት ውስጥ

ብትንትኑ ወጥቶ ሕዝብ መሆኑ ይቀራል።+

 9 የኤፍሬም ራስ ሰማርያ+ ነው፤

የሰማርያም ራስ የረማልያህ ልጅ ነው።+

ጠንካራ እምነት ከሌላችሁ

ጸንታችሁ መቆም አትችሉም።”’”

10 ከዚያም ይሖዋ አካዝን እንዲህ አለው፦ 11 “አምላክህ ይሖዋ ምልክት እንዲያሳይህ ጠይቅ፤+ ምልክቱም እንደ መቃብር* ጥልቅ የሆነ ወይም እንደ ሰማይ ከፍ ያለ ሊሆን ይችላል።” 12 አካዝ ግን “አልጠይቅም፤ ይሖዋንም አልፈትንም” አለ።

13 ከዚያም ኢሳይያስ እንዲህ አለ፦ “የዳዊት ቤት ሆይ፣ እባካችሁ ስሙ። የሰውን ትዕግሥት መፈታተናችሁ አንሶ የአምላክንም ትዕግሥት ልትፈታተኑ ትፈልጋላችሁ?+ 14 በመሆኑም ይሖዋ ራሱ ምልክት ይሰጣችኋል፦ እነሆ፣ ወጣቷ* ትፀንሳለች፤ ወንድ ልጅም ትወልዳለች፤+ አማኑኤል* ብላም ትጠራዋለች።+ 15 ክፉውን መጥላትና መልካሙን መምረጥ በሚችልበት ጊዜ ቅቤና ማር ይበላል። 16 ልጁ ክፉውን መጥላትና መልካሙን መምረጥ ከመቻሉ በፊት በጣም የምትፈራቸው የሁለቱ ነገሥታት ምድር ጨርሶ የተተወ ይሆናል።+ 17 ይሖዋ፣ ኤፍሬም ከይሁዳ ከተለየበት+ ጊዜ ጀምሮ ታይቶ የማይታወቅ ዘመን በአንተ፣ በሕዝብህና በአባትህ ቤት ላይ ያመጣል፤ የአሦርን ንጉሥ ያመጣልና።+

18 “በዚያ ቀን ይሖዋ በግብፅ፣ ርቀው በሚገኙት የአባይ ጅረቶች ያሉትን ዝንቦች፣ በአሦርም ምድር ያሉትን ንቦች በፉጨት ይጠራል፤ 19 ሁሉም መጥተው ጥልቅ በሆኑ ሸለቆዎች፣* በየዓለቱ ንቃቃት፣ በቁጥቋጦዎች ሁሉና ውኃ ባሉባቸው ቦታዎች ሁሉ ላይ ይሰፍራሉ።

20 “በዚያም ቀን ይሖዋ በወንዙ* አካባቢ ከሚገኘው ቦታ በተከራየው ምላጭ ይኸውም በአሦር ንጉሥ+ አማካኝነት ራሱንና የእግሩን ፀጉር ይላጨዋል፤ ጢሙንም ሙልጭ አድርጎ ያስወግደዋል።

21 “በዚያም ቀን አንድ ሰው ከመንጋው መካከል አንዲት ጊደርና ሁለት በጎች በሕይወት ያተርፋል። 22 በብዛት ከሚገኘው ወተት የተነሳም ቅቤ ይበላል፤ በምድሪቱ መካከል የቀረው ሰው ሁሉ ቅቤና ማር ይበላል።

23 “በዚያ ቀን 1,000 የብር ሰቅል የሚያወጣ 1,000 የወይን ተክል ይገኝበት የነበረው ቦታ ሁሉ ቁጥቋጦና አረም ይወርሰዋል። 24 ምድሪቱ በቁጥቋጦና በአረም ስለምትሸፈን ሰዎች ወደዚያ የሚሄዱት ቀስትና ደጋን ይዘው ነው። 25 በአንድ ወቅት በመቆፈሪያ ተመንጥረውና ከአረም ጸድተው የነበሩ ተራሮች ሁሉ ቁጥቋጦና አረም ስለሚወርሳቸው ወደዚያ መሄድ ትፈራለህ፤ እነዚህ ቦታዎች በሬዎች የሚሰማሩባቸውና በጎች የሚፈነጩባቸው ይሆናሉ።”

8 ይሖዋ እንዲህ አለኝ፦ “አንድ ትልቅ ጽላት+ ወስደህ በብዕር* ‘ማኸር-ሻላል-ሃሽ-ባዝ’* ብለህ ጻፍ። 2 ታማኝ ምሥክሮች የሆኑት ካህኑ ኦርዮና+ የበራክዩ ልጅ ዘካርያስ ደግሞ የጽሑፍ ማረጋገጫ ይስጡኝ።”*

3 እኔም ከነቢዪቱ* ጋር ተገናኘሁ፤* እሷም ፀነሰች፤ በኋላም ወንድ ልጅ ወለደች።+ ከዚያም ይሖዋ እንዲህ አለኝ፦ “ስሙን ማኸር-ሻላል-ሃሽ-ባዝ ብለህ ጥራው፤ 4 ልጁ ‘አባዬ!’ እና ‘እማዬ!’ ብሎ መጥራት ከመቻሉ በፊት የደማስቆ ሀብትና የሰማርያ ምርኮ በአሦር ንጉሥ ፊት ይወሰዳል።”+

5 ይሖዋ በድጋሚ እንዲህ አለኝ፦

 6 “ይህ ሕዝብ ቀስ ብለው የሚወርዱትን የሺሎአ* ውኃዎች ንቆ+

በረጺንና በረማልያህ+ ልጅ ሐሴት ስላደረገ

 7 እነሆ፣ ይሖዋ ብርቱ የሆኑትንና ከፍተኛ መጠን ያላቸውን የወንዙን* ውኃዎች ይኸውም

የአሦርን ንጉሥና+ ክብሩን ሁሉ

በእነሱ ላይ ያመጣባቸዋል።

እሱም የውኃ መውረጃዎቹን ሁሉ ሞልቶ ይፈስሳል፤

ዳርቻዎቹንም ሁሉ ያጥለቀልቃል፤

 8 ይሁዳንም ጠራርጎ ይሄዳል።

አካባቢውን እያጥለቀለቀ በማለፍ እስከ አንገት ይደርሳል፤+

አማኑኤል*+ ሆይ፣ የተዘረጉት ክንፎቹ

ምድርህን ከዳር እስከ ዳር ይሸፍናሉ!”

 9 እናንተ ሕዝቦች፣ ጉዳት አድርሱባቸው፤ ሆኖም ድምጥማጣችሁ ይጠፋል።

ራቅ ባሉ የምድር ክፍሎች የምትኖሩ ሁሉ አዳምጡ!

ለውጊያ ተዘጋጁ፤* ነገር ግን ድምጥማጣችሁ ይጠፋል!+

ለውጊያ ተዘጋጁ፤ ነገር ግን ድምጥማጣችሁ ይጠፋል!

10 ዕቅድ አውጡ፤ ይሁንና ይጨናገፋል!

የፈለጋችሁትን ተናገሩ፤ ሆኖም አይሳካም፤

አምላክ ከእኛ ጋር ነውና!*+

11 ይሖዋ ብርቱ እጁን በእኔ ላይ አድርጎ የዚህን ሕዝብ መንገድ እንዳልከተል ለማስጠንቀቅ እንዲህ አለኝ፦

12 “ይህ ሕዝብ ‘ሴራ እንጠንስስ!’ ሲል እናንተ ‘በሴራው ተባበሩ!’ አትበሉ፤

እነሱ የሚያስፈራቸውን ነገር አትፍሩ፤

አትንቀጥቀጡለትም።

13 ቅዱስ አድርጋችሁ ልትመለከቱ የሚገባው የሠራዊት ጌታ ይሖዋን ነው፤+

ልትፈሩ የሚገባው እሱን ነው፤

እንዲሁም ልትንቀጠቀጡ የሚገባው ለእሱ ነው።”+

14 እሱ እንደ መቅደስ ይሆናል፤

ለሁለቱ የእስራኤል ቤቶች ግን

እንደሚያሰናክል ድንጋይና

እንደሚያደናቅፍ ዓለት፣+

ለኢየሩሳሌም ነዋሪዎችም

እንደ ወጥመድና እንደ አሽክላ ይሆንባቸዋል።

15 ከእነሱ መካከል ብዙዎቹ ይደናቀፋሉ፣ ይወድቃሉ፣ ይሰበራሉ፤

ወጥመድ ውስጥ ገብተው ይያዛሉ።

16 በጽሑፍ የሰፈረውን ማረጋገጫ* ጠቅልለው፤

ሕጉን* በደቀ መዛሙርቴ መካከል አሽገው!

17 እኔም ፊቱን ከያዕቆብ ቤት የሰወረውን+ ይሖዋን እጠባበቃለሁ፤*+ በእሱም ተስፋ አደርጋለሁ።

18 እነሆ፣ እኔና ይሖዋ የሰጠኝ ልጆች+ በጽዮን ተራራ ከሚኖረው ከሠራዊት ጌታ ከይሖዋ ለእስራኤል እንደተሰጡ ምልክቶችና+ ተአምራት ነን።

19 እነሱም “የሚያነበንቡትንና የሚያንሾካሹኩትን መናፍስት ጠሪዎች ወይም ጠንቋዮች ጠይቁ” ቢሏችሁ፣ አንድ ሕዝብ መጠየቅ ያለበት የራሱን አምላክ አይደለም? ስለ ሕያዋንስ ሙታንን መጠየቁ ተገቢ ነው?+ 20 ከዚህ ይልቅ ሕጉንና የማረጋገጫ ሰነዱን* መመርመር ይገባቸዋል!

ከዚህ ቃል ጋር የሚስማማ ነገር ሳይናገሩ ሲቀሩ ብርሃን አይበራላቸውም።*+ 21 እያንዳንዱም ተጎሳቁሎና ተርቦ በምድሪቱ ላይ ይንከራተታል፤+ ከመራቡና ከመበሳጨቱ የተነሳ ወደ ላይ እያየ ንጉሡንና አምላኩን ይረግማል። 22 ከዚያም ወደ ምድር ይመለከታል፤ የሚያየውም ነገር ጭንቀትና ጨለማ፣ ግራ የሚያጋባ ሁኔታ፣ አስቸጋሪ ወቅትና ብርሃን የሌለበት ፅልማሞት ብቻ ይሆናል።

9 ይሁን እንጂ ፅልማሞቱ ምድሪቱ በተጨነቀችበት ጊዜ እንደነበረው ይኸውም የዛብሎን ምድርና የንፍታሌም ምድር በተዋረዱበት ወቅት እንደነበረው እንደቀድሞው ዘመን አይሆንም።+ በኋለኛው ዘመን ግን ምድሩ ማለትም በባሕሩ አጠገብ የሚያልፈው መንገድ፣ በዮርዳኖስ ክልል የሚገኘው የአሕዛብ ገሊላ እንዲከበር ያደርጋል።

 2 በጨለማ ውስጥ ይሄዱ የነበሩ ሰዎች

ታላቅ ብርሃን አዩ።

ድቅድቅ ጨለማ ባጠላበት ምድር የሚኖሩ ሰዎችም

ብርሃን ወጣላቸው።+

 3 ሕዝቡን አብዝተሃል፤

ታላቅ ደስታ እንዲያገኝ አድርገሃል።

መከር በሚሰበሰብበት ጊዜ ሐሴት እንደሚያደርጉ፣

ምርኮንም ሲከፋፈሉ እንደሚደሰቱ ሰዎች

በፊትህ ደስ ይሰኛሉ።

 4 ምድያም ድል በተደረገበት ጊዜ እንደሆነው ሁሉ+

የሸክማቸውን ቀንበር፣ በትከሻቸው ላይ ያለውን በትር፣

የተቆጣጣሪያቸውንም ዘንግ ሰባብረሃልና።

 5 መሬቱ እስኪንቀጠቀጥ ድረስ በኃይል የሚረግጡ ሰልፈኞች ጫማ ሁሉ

እንዲሁም በደም የተጨማለቀ ልብስ በሙሉ

ለእሳት ማገዶ ይሆናል።

 6 ልጅ ተወልዶልናልና፤+

ወንድ ልጅም ተሰጥቶናል፤

ገዢነትም* በጫንቃው ላይ ይሆናል።+

ስሙ ድንቅ መካሪ፣+ ኃያል አምላክ፣+ የዘላለም አባትና የሰላም መስፍን ይባላል።

 7 በዳዊት ዙፋንና+ በመንግሥቱ ላይ ይቀመጣል፤

እየተጠናከረ የሚሄደው አገዛዙም* ሆነ

ሰላሙ ፍጻሜ አይኖረውም።+

ከአሁን ጀምሮ ለዘላለም

በማይናወጥ ሁኔታ ይመሠረታል፤+

በፍትሕና+ በጽድቅም+ ጸንቶ ይኖራል።

የሠራዊት ጌታ የይሖዋ ቅንዓት ይህን ያደርጋል።

 8 ይሖዋ በያዕቆብ ላይ ቃል ላከ፤

ቃሉም በእስራኤል ላይ ደረሰ።+

 9 ሕዝቡም ሁሉ ይኸውም የኤፍሬምና የሰማርያ ነዋሪዎች

ይህን ያውቃሉ፤

በትዕቢታቸውና በልባቸው እብሪት የተነሳ እንዲህ ይላሉ፦

10 “ጡቦቹ ወድቀዋል፤

እኛ ግን በጥርብ ድንጋይ እንገነባለን።+

የሾላ ዛፎቹ ተቆርጠዋል፤

እኛ ግን በአርዘ ሊባኖስ እንተካቸዋለን።”

11 ይሖዋ የረጺንን ባላጋራዎች በእሱ ላይ ያስነሳል፤

ጠላቶቹንም እርምጃ እንዲወስዱ ይቀሰቅሳቸዋል፤

12 ሶርያን ከምሥራቅ፣ ፍልስጤማውያንን ደግሞ ከምዕራብ* ያመጣበታል፤+

እነሱም አፋቸውን ከፍተው እስራኤልን ይውጡታል።+

ከዚህ ሁሉ የተነሳ ቁጣው አልተመለሰም፤

ይልቁንም እጁ ለመምታት ገና እንደተዘረጋ ነው።+

13 ሕዝቡ ወደመታቸው አልተመለሱምና፤

የሠራዊት ጌታ ይሖዋን አልፈለጉም።+

14 ይሖዋ ራስንና ጅራትን፣ ቀንበጥንና እንግጫን*

ከእስራኤል በአንድ ቀን ይቆርጣል።+

15 ሽማግሌውና የተከበረው ሰው ራስ ነው፤

የሐሰት መመሪያ የሚሰጠው ነቢይ ደግሞ ጅራት ነው።+

16 ይህን ሕዝብ የሚመሩት ሰዎች እንዲባዝን ያደርጉታል፤

በእነሱ የሚመራውም ሕዝብ ግራ ይጋባል።

17 ይሖዋ በወጣቶቻቸው የማይደሰተው ለዚህ ነው፤

በመካከላቸው ላሉት አባት የሌላቸው ልጆችና* መበለቶች ምሕረት አያሳይም፤

ምክንያቱም ሁሉም ከሃዲዎችና ክፉ አድራጊዎች ናቸው፤+

የሁሉም አፍ የማይረባ ነገር ይናገራል።

ከዚህ ሁሉ የተነሳ ቁጣው አልተመለሰም፤

ይልቁንም እጁ ለመምታት ገና እንደተዘረጋ ነው።+

18 ክፋት እንደ እሳት ይቀጣጠላል፤

ቁጥቋጦውንና አረሙንም ይበላል።

በደን ውስጥ ያለውን ጥሻ ያነደዋል፤

ጥሻው በሚቃጠልበት ጊዜም ጭሱ እየተትጎለጎለ ይወጣል።

19 ከሠራዊት ጌታ ከይሖዋ ቁጣ የተነሳ

ምድሪቷ በእሳት ተያያዘች፤

ሕዝቡም እሳት እንደሚበላው ማገዶ ይሆናል።

ማንም ሰው ወንድሙን እንኳ አይምርም።

20 አንዱ በቀኝ በኩል ይቆርጣል፤

ሆኖም ይራባል፤

ሌላው ደግሞ በግራ በኩል ይበላል፤

ሆኖም አይጠግብም።

እያንዳንዳቸው የገዛ ክንዳቸውን ሥጋ ይበላሉ፤

21 ምናሴ ኤፍሬምን፣

ኤፍሬም ደግሞ ምናሴን ይበላል።

በይሁዳም ላይ በአንድነት ይነሳሉ።+

ከዚህ ሁሉ የተነሳ ቁጣው አልተመለሰም፤

ይልቁንም እጁ ለመምታት ገና እንደተዘረጋ ነው።+

10 ጉዳት የሚያስከትሉ ሥርዓቶችን የሚያወጡ፣+

ሁልጊዜ ጨቋኝ ድንጋጌዎችን የሚያረቁ ወዮላቸው!

 2 የድሆችን አቤቱታ ላለመስማት፣

በሕዝቤም መካከል የሚገኙትን ምስኪኖች ፍትሕ ለመንፈግ ሕግ የሚያወጡ ወዮላቸው!+

መበለቶችን ይበዘብዛሉ፤

አባት የሌላቸውንም ልጆች* ይዘርፋሉ።+

 3 በምትመረመሩበት* ቀን፣+

ጥፋትም ከሩቅ በሚመጣበት ጊዜ ምን ይውጣችሁ ይሆን?+

እርዳታ ለማግኘት ወደ ማን ትሸሻላችሁ?+

ሀብታችሁንስ* የት ትተዉት ይሆን?

 4 በእስረኞች መካከል ተኮራምታችሁ ከመቀመጥና

በሞቱ ሰዎች መካከል ከመውደቅ በስተቀር የምታተርፉት ነገር የለም።

ከዚህ ሁሉ የተነሳ ቁጣው አልተመለሰም፤

ይልቁንም እጁ ለመምታት ገና እንደተዘረጋ ነው።+

 5 “የቁጣዬ በትር የሆነውንና+

ውግዘቴን የምገልጽበትን ዱላ በእጁ የያዘውን

አሦራዊ+ ተመልከት!

 6 ከሃዲ በሆነው ብሔር ላይ፣

እጅግ ባስቆጣኝም ሕዝብ ላይ እልከዋለሁ፤+

ብዙ ምርኮ እንዲወስድ፣ ብዙ ሀብት እንዲዘርፍና

ሕዝቡን በጎዳናዎች ላይ እንዳለ ጭቃ እንዲረጋግጥ አዘዋለሁ።+

 7 እሱ ግን እንዲህ ያለ ዝንባሌ አይኖረውም፤

ልቡም እንዲህ ለማድረግ አያቅድም፤

የልቡ ፍላጎት መደምሰስና

ጥቂት ሳይሆን ብዙ ብሔራትን ማጥፋት ነውና።

 8 እሱ እንዲህ ይላል፦

‘አለቆች ሆነው የሚያገለግሉኝ ሁሉ ነገሥታት አይደሉም?+

 9 ካልኖ+ እንደ ካርከሚሽ+ አይደለችም?

ሃማት+ እንደ አርጳድ+ አይደለችም?

ሰማርያስ+ እንደ ደማስቆ+ አይደለችም?

10 እጄ በኢየሩሳሌምና በሰማርያ ካሉት ይበልጥ በርካታ የተቀረጹ ምስሎች ያሏቸውንና

ከንቱ አማልክት የሚያመልኩትን መንግሥታት ይዟል!+

11 በሰማርያና ከንቱ በሆኑት አማልክቷ ላይ እንዳደረግኩት ሁሉ፣

በኢየሩሳሌምና በጣዖቶቿስ ላይ እንዲሁ አላደርግም?’+

12 “ይሖዋ በጽዮን ተራራና በኢየሩሳሌም የሚያከናውነውን ሥራ ሁሉ ሲያጠናቅቅ በእብሪተኛ ልቡ፣ በኩራቱና በትዕቢተኛ ዓይኑ የተነሳ የአሦርን ንጉሥ ይቀጣዋል።*+ 13 እሱ እንዲህ ይላልና፦

‘በእጄ ብርታትና በጥበቤ

ይህን አደርጋለሁ፤ እኔ ጥበበኛ ነኝና።

የሕዝቦችን ድንበር አስወግዳለሁ፤+

ሀብታቸውንም እዘርፋለሁ፤+

እንደ ኃያል ሰውም ነዋሪዎቹን በቁጥጥር ሥር አውላለሁ።+

14 ሰው እጁን ወደ ወፍ ጎጆ እንደሚሰድ፣

እጄ የሕዝቦችን ሀብት ይይዛል፤

አንድ ሰው የተተዉ እንቁላሎችን እንደሚሰበስብ

እኔም መላውን ምድር እሰበስባለሁ!

ክንፎቹን የሚያራግብ ወይም አፉን የሚከፍት አሊያም የሚጮኽ አይኖርም።’”

15 መጥረቢያ፣ በሚቆርጥበት ሰው ላይ ይኩራራል?

መጋዝ፣ በሚገዘግዝበት ሰው ላይ ራሱን ከፍ ከፍ ያደርጋል?

በትር፣+ የሚያነሳውን ሰው ወዲያና ወዲህ ማንቀሳቀስ ይችላል?

ወይስ ዱላ፣ ከእንጨት ያልተሠራውን ሰው ወደ ላይ ከፍ ማድረግ ይችላል?

16 ስለዚህ እውነተኛው ጌታ፣ የሠራዊት ጌታ ይሖዋ

በወፈሩት ሰዎች ላይ ክሳትን ይሰዳል፤+

ከክብሩም በታች እንደ እሳት ነበልባል የሚንቦገቦግ እሳት ያነዳል።+

17 የእስራኤል ብርሃን+ እንደ እሳት፣+

ቅዱስ አምላኩም እንደ ነበልባል ይሆናል፤

አረሙንና ቁጥቋጦውን በአንድ ቀን ያጋየዋል፤ ደግሞም ይበላዋል።

18 አምላክ የደኑንና የፍራፍሬ እርሻውን ክብር ፈጽሞ* ያጠፋል፤

ክብሩም እንደታመመ ሰው እየመነመነ ይሄዳል።+

19 በደኑ ውስጥ የሚተርፉት ዛፎች

ጥቂት ከመሆናቸው የተነሳ አንድ ትንሽ ልጅ ቆጥሮ ሊመዘግባቸው ይችላል።

20 በዚያ ቀን ከእስራኤላውያን መካከል የሚቀሩት፣

ከያዕቆብም ቤት የሚተርፉት ሰዎች

ከእንግዲህ ወዲህ፣ በመታቸው ላይ ፈጽሞ አይታመኑም፤+

ከዚህ ይልቅ የእስራኤል ቅዱስ በሆነው በይሖዋ ላይ

በታማኝነት ይደገፋሉ።

21 ጥቂት ቀሪዎች ይኸውም ከያዕቆብ ቤት የሚተርፉት ሰዎች

ወደ ኃያሉ አምላክ ይመለሳሉ።+

22 እስራኤል ሆይ፣

ሕዝብህ እንደ ባሕር አሸዋ ቢሆንም

ከእነሱ መካከል ጥቂት ቀሪዎች ይመለሳሉ።+

ጥፋት ተወስኗል፤+

ፍትሕም* ይውጣቸዋል።+

23 አዎ፣ ሉዓላዊው ጌታ፣ የሠራዊት ጌታ ይሖዋ የወሰነው ጥፋት፣

በመላ ምድሪቱ ላይ ይፈጸማል።+

24 ስለዚህ ሉዓላዊው ጌታ፣ የሠራዊት ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “በጽዮን የምትኖር ሕዝቤ ሆይ፣ በበትር+ ይመታህና ግብፅ እንዳደረገብህ+ ዱላውን በአንተ ላይ ያነሳ የነበረውን አሦርን አትፍራ። 25 ከጥቂት ጊዜ በኋላ ውግዘቱ ያበቃልና፤ ቁጣዬም እስኪጠፉ ድረስ በእነሱ ላይ ይነድዳል።+ 26 የሠራዊት ጌታ ይሖዋ በኦሬብ ዓለት ምድያምን ድል እንዳደረገ+ ሁሉ ጅራፉን በእሱ ላይ ያወዛውዛል።+ በትሩም በባሕሩ ላይ ይሆናል፤ በግብፅ ላይ እንዳደረገውም በትሩን ያነሳዋል።+

27 “በዚያ ቀን ሸክሙ ከትከሻህ ላይ፣+

ቀንበሩም ከአንገትህ ላይ ይወርዳል፤+

ከዘይቱም የተነሳ ቀንበሩ ይሰበራል።”+

28 በአያት+ ላይ መጥቷል፤

ሚግሮንን አቋርጦ አልፏል፤

በሚክማሽ+ ጓዙን ያስቀምጣል።

29 መልካውን* ተሻግረዋል፤

በጌባ+ ያድራሉ፤

ራማ ራደች፤ የሳኦል ከተማ ጊብዓ+ ሸሽታለች።+

30 የጋሊም ሴት ልጅ ሆይ፣ እሪታሽን አቅልጪው!

ላይሻ ሆይ፣ አዳምጪ!

ምስኪኗ አናቶት+ ሆይ፣ ጩኺ!

31 ማድመና ሸሽታለች።

የጌቢም ነዋሪዎች መሸሸጊያ ፈለጉ።

32 በዚሁ ቀን በኖብ+ ያርፋል።

በጽዮን ሴት ልጅ ተራራ፣

በኢየሩሳሌም ኮረብታ ላይ እጁን በዛቻ ያወዛውዛል።

33 እነሆ፣ እውነተኛው ጌታ፣ የሠራዊት ጌታ ይሖዋ

ቅርንጫፎችን በታላቅ ኃይል እየቆራረጠ ይጥላል፤+

ረጃጅሞቹ ዛፎች ይገነደሳሉ፤

ከፍ ያሉትም ይዋረዳሉ።

34 በደን ውስጥ ያለውን ጥሻ በብረት መሣሪያ* ይቆራርጣል፤

ሊባኖስም በኃያሉ እጅ ይወድቃል።

11 ከእሴይ+ ጉቶ፣ ቅርንጫፍ ይወጣል፤

ከሥሮቹም የሚወጣው ቀንበጥ ፍሬ ያፈራል።+

 2 በእሱም ላይ የይሖዋ መንፈስ፣+

የጥበብና+ የማስተዋል መንፈስ፣

የምክርና የኃይል+ መንፈስ፣

የእውቀትና ይሖዋን የመፍራት መንፈስ ያርፍበታል።

 3 ይሖዋን በመፍራትም ደስ ይሰኛል።+

ዓይኑ እንዳየ አይፈርድም

ወይም ጆሮው በሰማው ነገር ላይ ብቻ ተመሥርቶ አይወቅስም።+

 4 ለችግረኞች በትክክል* ይፈርዳል፤

በምድር ላሉ የዋሆች ጥቅም ሲል ሌሎችን ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ይወቅሳል።

በአፉም በትር ምድርን ይመታል፤+

በከንፈሩም እስትንፋስ* ክፉዎችን ይገድላል።+

 5 ጽድቅ የወገቡ መታጠቂያ፣

ታማኝነትም የጎኑ መታጠቂያ ይሆናል።+

 6 ተኩላ ከበግ ጠቦት ጋር የሚቀመጥበት ጊዜ ይኖራል፤+

ነብርም ከፍየል ግልገል ጋር ይተኛል፤

ጥጃ፣ አንበሳና* የሰባ ከብት አብረው ይሆናሉ፤*+

ትንሽ ልጅም ይመራቸዋል።

 7 ላምና ድብ አብረው ይበላሉ፤

ልጆቻቸውም አብረው ይተኛሉ።

አንበሳ እንደ በሬ ገለባ ይበላል።+

 8 ጡት የሚጠባ ሕፃንም በእባብ* ጉድጓድ ላይ ይጫወታል፤

ጡት የጣለውም ሕፃን እጁን በመርዘኛ እባብ ጎሬ ላይ ያደርጋል።

 9 በተቀደሰው ተራራዬ ሁሉ ላይ

ምንም ዓይነት ጉዳት ወይም ጥፋት አያደርሱም፤+

ምክንያቱም ውኃ ባሕርን እንደሚሸፍን

ምድርም በይሖዋ እውቀት ትሞላለች።+

10 በዚያን ቀን የእሴይ ሥር+ ለሕዝቦች ምልክት* ሆኖ ይቆማል።+

ብሔራት ከእሱ መመሪያ ይሻሉ፤*+

ማረፊያ ስፍራውም እጅግ የከበረ ይሆናል።

11 በዚያን ቀን ይሖዋ ዳግመኛ እጁን ዘርግቶ የተረፉትን የሕዝቡን ቀሪዎች ለሁለተኛ ጊዜ ከአሦር፣+ ከግብፅ፣+ ከጳትሮስ፣+ ከኢትዮጵያ፣*+ ከኤላም፣+ ከሰናኦር፣* ከሃማትና ከባሕር ደሴቶች+ መልሶ ይሰበስባል። 12 ለብሔራት ምልክት* ያቆማል፤ በየቦታው የተሰራጩትን እስራኤላውያንም መልሶ ያመጣቸዋል፤+ እንዲሁም የተበታተኑትን የይሁዳ ሰዎች ከአራቱም የምድር ማዕዘኖች ይሰበስባል።+

13 የኤፍሬም ቅናት ይወገዳል፤+

ይሁዳንም የሚጠሉ ይጠፋሉ።

ኤፍሬም በይሁዳ አይቀናም፤

ይሁዳም ኤፍሬምን አይጠላውም።+

14 በምዕራብ በኩል በፍልስጤም ተረተር* ላይ በድንገት ይወርዳሉ፤

ግንባር ፈጥረው በምሥራቅ የሚኖሩ ሕዝቦችን ይዘርፋሉ።

በኤዶምና+ በሞዓብ+ ላይ እጃቸውን* ይዘረጋሉ፤

አሞናውያንም ተገዢዎቻቸው ይሆናሉ።+

15 ይሖዋ የግብፅን ባሕረ ሰላጤ* ይከፍላል፤*+

በወንዙም*+ ላይ እጁን በዛቻ ያወዛውዛል።

በሚያቃጥል እስትንፋሱ* የወንዙን ሰባት ጅረቶች ይመታል፤*

ሰዎችም ከነጫማቸው እንዲሻገሩ ያደርጋል።

16 እስራኤል ከግብፅ ምድር በወጣበት ጊዜ እንደሆነው ሁሉ፣

ከሕዝቡ የተረፉት ቀሪዎችም+ ከአሦር የሚወጡበት ጎዳና+ ይኖራል።

12 በዚያ ቀን በእርግጥ እንዲህ ትላለህ፦

“ይሖዋ ሆይ፣ ተቆጥተኸኝ የነበረ ቢሆንም

ቁጣህ ቀስ በቀስ ስለበረደ

ደግሞም ስላጽናናኸኝ አመሰግንሃለሁ።+

 2 እነሆ፣ አምላክ አዳኜ ነው!+

በእሱ እታመናለሁ፤ ምንም የሚያስፈራኝ ነገር የለም፤+

ያህ* ይሖዋ ብርታቴና ኃይሌ ነው፤

ለእኔም አዳኝ ሆኖልኛል።”+

 3 ከመዳን ምንጮች

በደስታ ውኃ ትቀዳላችሁ።+

 4 በዚያም ቀን እንዲህ ትላላችሁ፦

“ይሖዋን አመስግኑ! ስሙን ጥሩ፤

ሥራውን በሕዝቦች መካከል አስታውቁ!+

ስሙ ከፍ ከፍ ማለቱን አውጁ።+

 5 አስደናቂ ነገሮችን+ ስላከናወነ ለይሖዋ የውዳሴ መዝሙር ዘምሩ።+

ይህም በመላው ምድር ይታወጅ።

 6 እናንተ የጽዮን ነዋሪዎች* ሆይ፣ ጩኹ፤ በደስታም እልል በሉ፤

የእስራኤል ቅዱስ በመካከላችሁ ታላቅ ነውና።”

13 የአሞጽ ልጅ ኢሳይያስ+ በራእይ ያየው በባቢሎን ላይ የተላለፈ ፍርድ፦+

 2 “በተራቆተ ዓለታማ ተራራ ላይ ምልክት* አቁሙ።+

ታላላቅ ሰዎች ወደሚገቡባቸው በሮች እንዲመጡ

ድምፃችሁን ከፍ አድርጋችሁ ጥሯቸው፤ እጃችሁንም አውለብልቡ።

 3 እኔ ለሾምኳቸው* ትእዛዝ ሰጥቻለሁ።+

ቁጣዬን ለመግለጥ

በኩራት ሐሴት የሚያደርጉትን ተዋጊዎቼን ጠርቻለሁ።

 4 ስሙ! በተራሮች ላይ እንደ ታላቅ ሕዝብ ድምፅ ያለ

የብዙ ሰዎች ድምፅ ይሰማል!

አዳምጡ! አንድ ላይ የተሰበሰቡ መንግሥታትና

ብሔራት+ ሁካታ ይሰማል!

የሠራዊት ጌታ ይሖዋ ሠራዊቱን ለጦርነት አሰልፏል።+

 5 ይሖዋና የቁጣው መሣሪያዎች

መላ ምድሪቱን ለመደምሰስ+

ከሩቅ አገር፣+

ከሰማያትም ዳርቻ እየመጡ ነው።

 6 የይሖዋ ቀን ቀርቧልና ዋይ ዋይ በሉ!

በዚያ ቀን ሁሉን ቻይ ከሆነው አምላክ ዘንድ ጥፋት ይመጣል።+

 7 ከዚህም የተነሳ እጆች ሁሉ ይዝላሉ፤

የሰዎችም ልብ ሁሉ በፍርሃት ይቀልጣል።+

 8 ሰዎቹ እጅግ ተሸብረዋል።+

ምጥ እንደያዛት ሴት

ብርክና ሥቃይ ይዟቸዋል።

እርስ በርሳቸው በታላቅ ድንጋጤ ይተያያሉ፤

ፊታቸው በጭንቀት ቀልቷል።

 9 እነሆ፣ የይሖዋ ቀን ምድሪቱን አስፈሪ ቦታ ለማድረግና

በምድሪቱ ላይ ያሉትን ኃጢአተኞች ለማጥፋት

በንዴትና በታላቅ ቁጣ

ጨካኝ ሆኖ እየመጣ ነው።+

10 የሰማያት ከዋክብትና የኅብረ ከዋክብት ስብስቦቻቸው*+

ብርሃን አይሰጡም፤

ፀሐይ ስትወጣ ትጨልማለች፤

ጨረቃም ብርሃኗን አትሰጥም።

11 ምድሪቱን ስለ ክፋቷ፣+

ክፉዎችንም ስለ በደላቸው እቀጣለሁ።

የእብሪተኞችን ኩራት አጠፋለሁ፤

የጨቋኞችንም ትዕቢት አዋርዳለሁ።+

12 ሟች የሆነውን ሰው ከጠራ ወርቅ፣

ሰዎችንም ከኦፊር ወርቅ+ ይበልጥ ብርቅ አደርጋለሁ።+

13 ስለዚህ የሠራዊት ጌታ የይሖዋ ቁጣ በሚነድበት ቀን፣

በታላቅ ቁጣ ሰማይን አናውጣለሁ፤

ምድርንም ከቦታዋ አናጋለሁ።+

14 እንደሚታደን የሜዳ ፍየል፣ እረኛም እንደሌለው መንጋ

እያንዳንዱ ወደ ወገኑ ይመለሳል፤

እያንዳንዱም ወደ አገሩ ይሸሻል።+

15 የተገኘ ሁሉ ይወጋል፤

የተያዘም ሁሉ በሰይፍ ይወድቃል።+

16 ልጆቻቸው ዓይናቸው እያየ ይጨፈጨፋሉ፤+

ቤታቸው ይዘረፋል፤

ሚስቶቻቸውም ተገደው ይደፈራሉ።

17 እነሆ፣ ለብር ደንታ የሌላቸውን፣

በወርቅም ደስ የማይሰኙትን

ሜዶናውያንን አስነሳባቸዋለሁ።+

18 ቀስታቸው ወጣቶችን ይፈጃል፤+

ለማህፀን ፍሬ አያዝኑም፤

ለልጆችም አይራሩም።

19 ከመንግሥታትም ሁሉ እጅግ የከበረችው፣*+

የከለዳውያን ውበትና ኩራት የሆነችው ባቢሎን፣+

አምላክ እንደገለበጣቸው እንደ ሰዶምና እንደ ገሞራ ትሆናለች።+

20 ከዚያ በኋላ የሚቀመጥባት አይኖርም፤

እንዲሁም ከትውልድ እስከ ትውልድ ድረስ የመኖሪያ ቦታ አትሆንም።+

በዚያም ዓረብ ድንኳኑን አይተክልም፤

እረኞችም መንጎቻቸውን በዚያ አያሳርፉም።

21 የበረሃ ፍጥረታት በዚያ ይተኛሉ፤

ቤቶቻቸው በጉጉቶች ይሞላሉ።

ሰጎኖች በዚያ ይኖራሉ፤+

የዱር ፍየሎችም* በዚያ ይፈነጫሉ።

22 የሚያላዝኑ ፍጥረታት በማማዎቿ፣

ቀበሮዎችም በሚያማምሩ ቤተ መንግሥቶቿ ውስጥ ሆነው ይጮኻሉ።

ጊዜዋ ቀርቧል፤ ቀኖቿም አይራዘሙም።”+

14 ይሖዋ ለያዕቆብ ምሕረት ያሳያልና፤+ እስራኤልንም እንደገና ይመርጠዋል።+ በምድራቸው ላይ ያሰፍራቸዋል፤*+ የባዕድ አገር ሰዎችም ከእነሱ ጋር ይሆናሉ፤ ከያዕቆብም ቤት ጋር ይጣበቃሉ።+ 2 ሕዝቦችም ይወስዷቸዋል፤ ወደ ገዛ ስፍራቸውም ይመልሷቸዋል፤ የእስራኤልም ቤት በይሖዋ ምድር ላይ ወንድና ሴት አገልጋዮቻቸው ያደርጓቸዋል፤+ ማርከው የወሰዷቸውንም ይማርካሉ፤ አስገድደው ያሠሯቸው የነበሩትንም* ይገዟቸዋል።

3 ይሖዋ ከሥቃይህ፣ ከጭንቀትህና በላይህ ተጭኖ ከነበረው ከባድ የባርነት ቀንበር ባሳረፈህ ቀን፣+ 4 በባቢሎን ንጉሥ ላይ እንዲህ ብለህ ትተርታለህ፦*

“ሌሎችን አስገድዶ ሲያሠራ የነበረው* እንዴት አበቃለት!

ጭቆናውስ እንዴት አከተመ!+

 5 ይሖዋ የክፉዎችን ዘንግ፣

የገዢዎችን በትር ሰብሯል፤+

 6 ሕዝቦችን ያለማቋረጥ በቁጣ ሲመታ የነበረውን፣+

ብሔራትን በማያባራ ስደት በቁጣ ሲገዛቸው የቆየውን ሰብሯል።+

 7 መላዋ ምድር አርፋለች፤ ከረብሻም ነፃ ሆናለች።

ሕዝቦች በደስታ እልል ብለዋል።+

 8 የጥድ ዛፎችና አርዘ ሊባኖሶች እንኳ ሳይቀሩ

በአንተ ላይ በደረሰው ነገር ሐሴት ያደርጋሉ።

‘አንተ ከወደቅክ ጀምሮ

ማንም ዛፍ ቆራጭ በእኛ ላይ አልተነሳም’ ይላሉ።

 9 “ከታች ያለው መቃብር* እንኳ

ወደዚያ በወረድክ ጊዜ አንተን ለመቀበል ሲል ተረበሸ።

በሞት የተረቱትን፣ ጨቋኝ የምድር መሪዎች* ሁሉ

በአንተ የተነሳ ቀሰቀሳቸው።

የብሔራትን ነገሥታት ሁሉ ከዙፋኖቻቸው ላይ አስነሳቸው።

10 ሁሉም እንዲህ በማለት ይናገራሉ፤ እንዲህም ይሉሃል፦

‘አንተም እንደ እኛው ደከምክ ማለት ነው?

አንተም እንደ እኛው ሆንክ?

11 ኩራትህና ባለ አውታር መሣሪያዎችህ የሚያሰሙት ድምፅ

ወደ መቃብር* ወረዱ።+

እጮች ከበታችህ እንደ አልጋ ተነጥፈውልሃል፤

የአልጋ ልብስህም ትሎች ናቸው።’

12 አንተ የምታበራ ኮከብ፣ የንጋት ልጅ ሆይ፣

እንዴት ከሰማይ ወደቅክ!

አንተ ብሔራትን ድል ያደረግክ፣

እንዴት ተቆርጠህ ወደ ምድር ወደቅክ!+

13 በልብህ እንዲህ ብለህ ነበር፦ ‘ወደ ሰማያት እወጣለሁ።+

ዙፋኔን ከአምላክ ከዋክብት በላይ ከፍ አደርጋለሁ፤+

በስተ ሰሜን ርቆ በሚገኘው

የመሰብሰቢያ ተራራም ላይ እቀመጣለሁ።+

14 ከደመናዎች ከፍታ በላይ እወጣለሁ፤

ራሴንም እንደ ልዑል አምላክ አደርጋለሁ።’

15 ከዚህ ይልቅ ወደ መቃብር፣*

ወደ ጥልቁም ጉድጓድ ትወርዳለህ።

16 የሚያዩህ አተኩረው ይመለከቱሃል፤

በሚገባም ይመረምሩሃል፤ እንዲህም ይላሉ፦

‘ምድርን ሲያንቀጠቅጥ፣

መንግሥታትንም ሲያናውጥ የነበረው ይህ ሰው አይደለም?+

17 ሰው የሚኖርበትን ምድር፣ ምድረ በዳ ያደረገው፣

ከተሞቹንም የገለበጠው፣+

እስረኞቹንም ወደ ቤታቸው እንዳይመለሱ የከለከለው እሱ አይደለም?’+

18 ሌሎቹ የብሔራት ነገሥታት ሁሉ፣

አንዳቸውም እንኳ ሳይቀሩ በክብር አንቀላፍተዋል፤

እያንዳንዳቸው በየመቃብራቸው* አርፈዋል።

19 አንተ ግን እንደተጠላ ቀንበጥ*

መቀበሪያ ሳታገኝ ተጥለሃል፤

በሰይፍ ተወግተው

ወደ ዓለታማ ጉድጓድ በወረዱ አስከሬኖች ተሸፍነሃል፤

እንደተረገጠም ሬሳ ሆነሃል።

20 ከእነሱ ጋር አብረህ በመቃብር አትቀበርም፤

የገዛ ምድርህን አጥፍተሃልና፤

የገዛ ሕዝብህንም ፈጅተሃል።

የክፉ አድራጊዎች ዘር ስም ዳግመኛ አይጠራም።

21 ተነስተው ምድሪቱን እንዳይወርሱና

ምድሪቱን በከተሞች እንዳይሞሏት

በአባቶቻቸው በደል የተነሳ

ልጆቹ የሚታረዱበትን ስፍራ አዘጋጁ።”

22 “በእነሱ ላይ እነሳለሁ”+ ይላል የሠራዊት ጌታ ይሖዋ።

“ከባቢሎን ስምን፣ ቀሪዎችን፣ ልጆችንና ዘርማንዘርን አጠፋለሁ”+ ይላል ይሖዋ።

23 “የጃርት መኖሪያና ረግረጋማ ቦታ አደርጋታለሁ፤ በጥፋት መጥረጊያም እጠርጋታለሁ”+ ይላል የሠራዊት ጌታ ይሖዋ።

24 የሠራዊት ጌታ ይሖዋ እንዲህ ሲል ምሏል፦

“ልክ እንዳሰብኩት ይሆናል፤

በወሰንኩትም መሠረት ይፈጸማል።

25 አሦራዊውን በምድሬ ላይ አደቀዋለሁ፤

በተራሮቼም ላይ እረግጠዋለሁ።+

ቀንበሩ ከላያቸው ላይ ይነሳል፤

ሸክሙም ከትከሻቸው ላይ ይወርዳል።”+

26 በመላው ምድር ላይ የተላለፈው ውሳኔ* ይህ ነው፤

በብሔራትም ሁሉ ላይ የተዘረጋው* እጅ ይህ ነው።

27 የሠራዊት ጌታ ይሖዋ ወስኗልና፤

ውሳኔውን ማን ሊያጨናግፍ ይችላል?+

እጁ ተዘርግቷል፤

ማንስ ሊያጥፈው ይችላል?+

28 ንጉሥ አካዝ በሞተበት+ ዓመት የሚከተለው ፍርድ ተላለፈ፦

29 “ፍልስጤማውያን ሆይ፣ የመቺያችሁ በትር ስለተሰበረ

አንዳችሁም ብትሆኑ ደስ አይበላችሁ።

ከእባቡ ሥር+ መርዘኛ እባብ ይወጣልና፤+

ዘሩም የሚበርና የሚያቃጥል እባብ* ይሆናል።

30 የችግረኞቹ የበኩር ልጆች ሲመገቡ፣

ድሆቹም ያለስጋት ሲተኙ፣

የአንተን ሥር ግን በረሃብ እገድላለሁ፤

ከአንተ የሚተርፈውም ይገደላል።+

31 አንተ በር ሆይ፣ አላዝን! አንቺ ከተማ ሆይ፣ ጩኺ!

ፍልስጤማውያን ሆይ፣ ሁላችሁም ተስፋ ትቆርጣላችሁ!

ከሰሜን ጭስ እየመጣ ነውና፤

አንዳቸውም ቢሆኑ ከሰልፉ ተነጥለው ወደ ኋላ አይቀሩም።”

32 ለብሔሩ መልእክተኞች ምን ብለው መመለስ ይገባቸዋል?

‘የጽዮንን መሠረት የጣለው ይሖዋ ነው፤+

በሕዝቡም መካከል ያሉት ችግረኛ ሰዎች እሷን መጠጊያ ያደርጋሉ’ ብለው ይመልሱላቸዋል።

15 በሞዓብ ላይ የተላለፈ ፍርድ፦+

የሞዓብ ኤር+ በሌሊት ስለወደመች

ጸጥ ረጭ ብላለች።

የሞዓብ ቂር+ በሌሊት ስለወደመች

ጸጥ ረጭ ብላለች።

 2 ወደ ቤቱ፣* ወደ ዲቦን፣+

ወደ ከፍታ ቦታዎቹም ለማልቀስ ወጥቷል።

ሞዓብ ስለ ነቦና+ ስለ መደባ+ ዋይ ዋይ ይላል።

ራስ ሁሉ ተመልጧል፤+ ጢምም ሁሉ ተላጭቷል።+

 3 በጎዳናዎቹ ላይ ማቅ ለብሰው ይታያሉ።

ሁሉም በጣሪያዎቻቸውና በአደባባዮቻቸው ላይ ዋይ ዋይ ይላሉ፤

እያለቀሱም ይወርዳሉ።+

 4 ሃሽቦንና ኤልዓሌ+ ያለቅሳሉ፤

ድምፃቸው እስከ ያሃጽ+ ድረስ ተሰምቷል።

ከዚህም የተነሳ የሞዓብ ተዋጊዎች ይጮኻሉ።

እሱም* ይንቀጠቀጣል።

 5 ልቤ ስለ ሞዓብ ያለቅሳል።

የሚሸሹት የሞዓብ ሰዎች እስከ ዞአርና+ እስከ ኤግላት ሸሊሺያ+ ድረስ ተሰደዱ።

እያለቀሱ የሉሂትን ዳገት ይወጣሉ፤

በደረሰባቸው ድንገተኛ ጥፋት የተነሳ ወደ ሆሮናይም በሚወስደው መንገድ ላይ ሲሄዱ ይጮኻሉ።+

 6 የኒምሪም ውኃዎች ደርቀዋልና፤

ለምለሙ የግጦሽ መስክ ደርቋል፤

ሣሩ ጠፍቷል፤ አንድም የለመለመ ነገር አይታይም።

 7 በመሆኑም ካከማቹት ንብረት ውስጥ የተረፈውን እንዲሁም ሀብታቸውን ተሸክመው

የአኻያ ዛፎች የሚገኙበትን ሸለቆ* ይሻገራሉ።

 8 ጩኸታቸው እስከ ሞዓብ ወሰን ድረስ አስተጋብቷል።+

ዋይታቸው እስከ ኤግላይም፣

እስከ በኤርዔሊም ድረስም ተሰምቷል።

 9 የዲሞን ውኃዎች በደም ተሞልተዋልና፤

በዲሞንም ላይ ተጨማሪ ነገሮች አመጣለሁ፦

በሚሸሹት ሞዓባውያንና

በምድሪቱ ላይ በሚቀሩት ሰዎች ላይ አንበሶች እሰዳለሁ።+

16 ከሴላ በምድረ በዳው በኩል አድርጋችሁ

በጽዮን ሴት ልጅ ተራራ ለሚገኘው

ለምድሪቱ ገዢ አውራ በግ ላኩ።

 2 የሞዓብ ሴቶች ልጆች በአርኖን+ መልካ*

ከጎጆው እንደተባረረ ወፍ ይሆናሉ።+

 3 “ምክር ለግሱ፤ ውሳኔውን ተግባራዊ አድርጉ።

እኩለ ቀን ላይ እንደ ምሽት ጨለማ ያለ ጥላ አጥሉ።

የተበተኑትን ሸሽጉ፤ የሚሸሹትንም አሳልፋችሁ አትስጡ።

 4 ሞዓብ ሆይ፣ የተበተኑት ሕዝቦቼ በአንተ ውስጥ ይኑሩ።

ከአጥፊው+ የተነሳ መሸሸጊያ ቦታ ሁንላቸው።

ጨቋኙ ፍጻሜው ይመጣል፤

ጥፋቱም ያበቃል፤

ሌሎችን የሚረግጡትም ከምድር ገጽ ይጠፋሉ።

 5 ከዚያም ዙፋን በታማኝ ፍቅር ጸንቶ ይመሠረታል።

በዳዊት ድንኳን ላይ በዙፋኑ የሚቀመጠው ታማኝ ይሆናል፤+

በትክክል ይፈርዳል፤ ጽድቅንም በቶሎ ያስፈጽማል።”+

 6 ስለ ሞዓብ ኩራት ይኸውም በጣም ኩሩ እንደሆነ ሰምተናል፤+

ስለ ትዕቢቱ፣ ስለ ኩራቱና ስለ ታላቅ ቁጣው ሰምተናል፤+

ይሁንና ድንፋታው ሁሉ ከንቱ ይሆናል።

 7 በመሆኑም ሞዓብ፣ ስለ ሞዓብ ዋይ ዋይ ይላል፤

አዎ፣ ሁሉም ዋይ ዋይ ይላሉ።+

የተመቱት ሰዎች ስለ ቂርሃረሰት+ የዘቢብ ቂጣ ያለቅሳሉ።

 8 በሃሽቦን+ እርከኖች ላይ የሚገኙት ተክሎች ጠውልገዋልና፤

የሲብማ+ የወይን ተክሎች ረግፈዋል፤

የብሔራት ገዢዎች ቀያይ ቅርንጫፎቹን* ረጋግጠዋል፤

እስከ ያዜር+ ደርሰዋል፤

በምድረ በዳውም ተንሰራፍተዋል።

ቀንበጦቹም ተዘርግተው እስከ ባሕሩ ድረስ ዘልቀዋል።

 9 ስለዚህ ስለ ያዜር እንዳለቀስኩት ለሲብማ የወይን ተክልም አለቅሳለሁ።

ሃሽቦንና ኤልዓሌ+ ሆይ፣ በእንባዬ አርሳችኋለሁ፤

ምክንያቱም የበጋ ፍሬና መከር በምትሰበስቡበት ወቅት የሚሰማው ጩኸት አብቅቷል።*

10 ሐሴትና ደስታ ከፍራፍሬ እርሻው ተወስዷል፤

በወይን እርሻዎቹም የደስታ ዝማሬ ወይም ጩኸት አይሰማም።+

ወይን የሚረግጥ ሰው ከእንግዲህ በወይን መጭመቂያው ውስጥ ወይን አይረግጥም፤

ጩኸቱን ሁሉ ጸጥ አሰኝቻለሁና።+

11 ከዚህም የተነሳ እንደሚርገበገብ የበገና ክር

ውስጤ ስለ ሞዓብ፣

አንጀቴም ስለ ቂርሃረሰት ይታወካል።+

12 ሞዓብ በከፍታ ስፍራው ላይ ራሱን ቢያደክምም እንኳ ዋጋ የለውም፤ ለመጸለይ ወደ መቅደሱ ቢመጣም ምንም ማድረግ አይችልም።+

13 ይሖዋ አስቀድሞ ስለ ሞዓብ የተናገረው ቃል ይህ ነው። 14 ደግሞም ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “ልክ እንደ ቅጥር ሠራተኛ የሥራ ዘመን፣* በሦስት ዓመት ጊዜ ውስጥ የሞዓብ ክብር በብዙ ብጥብጥ ይዋረዳል፤ የሚተርፉትም በጣም ጥቂትና እዚህ ግቡ የማይባሉ ይሆናሉ።”+

17 በደማስቆ ላይ የተላለፈ ፍርድ፦+

“እነሆ፣ ደማስቆ ከተማ መሆኗ ይቀራል፤

የፍርስራሽ ክምርም ትሆናለች።+

 2 የአሮዔር+ ከተሞች ወና ይሆናሉ፤

የመንጎች ማረፊያ ይሆናሉ፤

የሚያስፈራቸውም አይኖርም።

 3 የተመሸጉ ከተሞች ከኤፍሬም፣+

መንግሥትም ከደማስቆ ይወገዳል፤+

የተረፉት የሶርያ ሰዎች ክብርም

ልክ እንደ እስራኤላውያን ክብር ይጠፋል” ይላል የሠራዊት ጌታ ይሖዋ።

 4 “በዚያን ቀን የያዕቆብ ክብር ይከስማል፤

ጤናማ የሆነው ሰውነቱም* ይከሳል።

 5 አጫጁ በማሳ ውስጥ ያለውን እህል በሚሰበስብበትና

በእጁ ዛላውን በሚቆርጥበት ጊዜ እንደሚሆነው፣

ደግሞም ሰው በረፋይም ሸለቆ*+ እህል በሚቃርምበት ጊዜ እንደሚሆነው እንዲሁ ይሆናል።

 6 የወይራ ዛፍ ሲመታ

ከፍ ባለው ቅርንጫፍ ላይ ሁለት ወይም ሦስት የወይራ ፍሬዎች ብቻ፣

ፍሬ በሚይዙት ቅርንጫፎችም ላይ አራት ወይም አምስት ፍሬዎች ብቻ እንደሚቀሩ፣

በእሱም ላይ ቃርሚያ ብቻ ይቀራል”+ ይላል የእስራኤል አምላክ ይሖዋ።

7 በዚያም ቀን ሰው ወደ ሠሪው ይመለከታል፤ ዓይኖቹም የእስራኤልን ቅዱስ ትኩር ብለው ያያሉ። 8 የእጁ ሥራ+ ወደሆኑት መሠዊያዎች አይመለከትም፤+ ጣቶቹ የሠሯቸውን የማምለኪያ ግንዶችም* ሆነ የዕጣን ማጨሻዎች አተኩሮ አያይም።

 9 በዚያም ቀን፣ የተመሸጉ ከተሞቹ በጫካ እንዳለ የተተወ ቦታ፣+

በእስራኤላውያን ዘንድ እንደተተወ ቅርንጫፍ ይሆናሉ፤

ቦታው ጠፍ መሬት ይሆናል።

10 አንቺ፣* አዳኝ አምላክሽን ረስተሻልና፤+

መሸሸጊያ ዓለትሽንም+ አላስታወስሽም።

ያማሩ ተክሎችን ያለማሽውና

በመካከሉም የባዕድ* ቡቃያ የተከልሽው ለዚህ ነው።

11 በቀን በተክሎችሽ ዙሪያ አጥር ትሠሪያለሽ፤

በማለዳም ዘርሽ እንዲበቅል ታደርጊያለሽ፤

ይሁን እንጂ በበሽታና በማይሽር ሕመም ቀን አዝመራው ይጠፋል።+

12 አዳምጡ! እንደሚናወጥ ባሕር ያለ

የብዙ ሕዝቦች ትርምስ ይሰማል!

እንደ ኃይለኛ ውኃዎች ድምፅ ያለ

የሚያስገመግም የብሔራት ጫጫታ ይሰማል!

13 ብሔራት እንደ ብዙ ውኃዎች ድምፅ ያለ የሚያስገመግም ድምፅ ያሰማሉ።

እሱ ይገሥጻቸዋል፤ እነሱም ወደ ሩቅ ቦታ ይሸሻሉ፤

በተራራ ላይ እንዳለ በነፋስ እንደሚበን ገለባና

አውሎ ነፋስ እያሽከረከረ እንደሚወስደው ኮሸሽላ ይሆናሉ።

14 ሲመሽ ሽብር ይነግሣል።

ከመንጋቱም በፊት በዚያ አንዳቸውም አይገኙም።

የዘረፉን ሰዎች ድርሻ፣

የበዘበዙንም ሰዎች ዕጣ ይህ ነው።

18 በክንፋቸው ጥዝ የሚል ድምፅ የሚያሰሙ ጥቃቅን ነፍሳት ላሉባት

በኢትዮጵያ ወንዞች አካባቢ ለምትገኝ ምድር ወዮላት!+

 2 ይህች ምድር በባሕር ላይ፣

በደንገል ጀልባ ውኃዎችን አቋርጠው የሚሄዱ መልእክተኞችን እንዲህ በማለት ትልካለች፦

“እናንተ ፈጣን መልእክተኞች፣

ረጃጅም የሆኑና ለስላሳ ቆዳ ያላቸው ሰዎች ወደሚገኙበት ብሔር፣*

ከቅርብም ሆነ ከሩቅ ወደሚፈራ ሕዝብ፣+

ጥንካሬ ወዳለውና ድል አድራጊ ወደሆነው*

እንዲሁም መሬቱ በወንዞች ተጠርጎ ወደተወሰደበት ብሔር ሂዱ።”

 3 እናንተ በአገሪቱ የምትኖሩ ሁሉና እናንተ የምድር ነዋሪዎች ሁሉ፣

በተራሮች ላይ እንደሚቆም ምልክት* ያለ ነገር ትመለከታላችሁ፤

እንዲሁም ቀንደ መለከት ሲነፋ የሚሰማው ዓይነት ድምፅ ትሰማላችሁ።

 4 ይሖዋ እንዲህ ብሎኛልና፦

“በቀን ብርሃን እንዳለ የሚያጥበረብር ሐሩር፣

በመከርም ሙቀት እንዳለ የደመና ጠል፣

ጸጥ ብዬ ተቀምጬ ጽኑ ሆኖ የተመሠረተውን ስፍራዬን* እመለከታለሁ።

 5 ከመከር በፊት፣

አበባው በሚረግፍበትና የወይን ፍሬው በሚበስልበት ጊዜ

ቀንበጦቹ በማጭድ ይቆረጣሉና፤

ሐረጎቹም ተቆርጠው ይወገዳሉ።

 6 ሁሉም በተራሮች ላይ ላሉ አዳኝ አሞሮችና

ለምድር አራዊት ይተዋሉ።

አዳኝ አሞሮቹም እነሱን በመመገብ በጋውን ያሳልፋሉ፤

በምድር ላይ ያሉ አራዊትም ሁሉ እነሱን በመመገብ የመከሩን ወቅት ያሳልፋሉ።

 7 በዚያን ጊዜ ረጃጅም የሆኑና ለስላሳ ቆዳ ያላቸው ሰዎች የሚገኙበት ብሔር፣*

ከቅርብም ሆነ ከሩቅ የሚፈራው ሕዝብ፣

ጥንካሬ ያለው፣ ድል አድራጊ የሆነውና*

መሬቱ በወንዞች ተጠርጎ የተወሰደበት ብሔር

ለሠራዊት ጌታ ለይሖዋ ስጦታ ያመጣል፤

ስጦታውንም የሚያመጣው የሠራዊት ጌታ የይሖዋ ስም ወዳለበት ወደ ጽዮን ተራራ+ ነው።”

19 በግብፅ ላይ የተላለፈ ፍርድ፦+

እነሆ፣ ይሖዋ በፈጣን ደመና እየጋለበ ወደ ግብፅ እየመጣ ነው።

የግብፅ ከንቱ አማልክት በእሱ ፊት ይንቀጠቀጣሉ፤+

የግብፅም ልብ በውስጧ ይቀልጣል።

 2 “ግብፃውያንን በግብፃውያን ላይ አስነሳለሁ፤

እርስ በርሳቸውም ይጨራረሳሉ፤

እያንዳንዱ ወንድሙን፣ እያንዳንዱም ባልንጀራውን፣

ከተማም ከተማን፣ መንግሥትም መንግሥትን ይወጋል።

 3 የግብፅም መንፈስ በውስጧ ይረበሻል፤

ዕቅዷንም አፋልሳለሁ።+

እነሱም እርዳታ ለማግኘት ከንቱ ወደሆኑት አማልክት፣

ወደ ድግምተኞች፣ ወደ መናፍስት ጠሪዎችና ወደ ጠንቋዮች ይዞራሉ።+

 4 ግብፅ በኃይለኛ ገዢ እጅ እንድትወድቅ አደርጋለሁ፤

ጨካኝ ንጉሥም ይገዛቸዋል”+ ይላል እውነተኛው ጌታ፣ የሠራዊት ጌታ ይሖዋ።

 5 የባሕሩ ውኃ ይደርቃል፤

ወንዙም ይተናል፤ ጨርሶም ይደርቃል።+

 6 ወንዞቹም ይገማሉ፤

በግብፅ የሚገኙት የአባይ የመስኖ ቦዮች ይጎድላሉ፤ ይደርቃሉም።

ቄጠማውና እንግጫው ይበሰብሳል።+

 7 በአባይ ወንዝ መዳረሻ አካባቢ፣ በአባይ ዳር ያለው ተክል

እንዲሁም በአባይ ወንዝ አጠገብ ዘር የተዘራበት መሬት+ ሁሉ ይደርቃል።+

በነፋስ ተጠርጎ ይወሰዳል፤ ደብዛውም ይጠፋል።

 8 ዓሣ አጥማጆቹም ያዝናሉ፤

ወደ አባይ ወንዝ የዓሣ መንጠቆ የሚወረውሩም ሁሉ ያለቅሳሉ፤

በውኃው ላይ የዓሣ ማጥመጃ መረቦችን የሚጥሉም ይመናመናሉ።

 9 በተነደፈ የተልባ እግር+ የሚሠሩም ሆኑ

ነጭ ሸማ የሚሠሩ ሸማኔዎች ለኀፍረት ይዳረጋሉ።

10 የሽመና ባለሙያዎቿ ይደቆሳሉ፤

ቅጥር ሠራተኞቹ ሁሉ ያዝናሉ።*

11 የጾዓን+ መኳንንት ሞኞች ናቸው።

ጥበበኞች የሆኑ የፈርዖን አማካሪዎች የሚሰጡት ምክር ማስተዋል የጎደለው ነው።+

ፈርዖንን “እኔ የጥበበኞች ልጅ፣

የጥንት ነገሥታትም ዘር ነኝ”

እንዴት ትሉታላችሁ?

12 ጥበበኞችህ ታዲያ የት አሉ?+

የሠራዊት ጌታ ይሖዋ ስለ ግብፅ የወሰነውን የሚያውቁ ከሆነ ይንገሩህ።

13 የጾዓን መኳንንት የሞኝ ሥራ ሠርተዋል፤

የኖፍ*+ መኳንንት ተታለዋል፤

የነገዶቿ አለቆች ግብፅ እንድትባዝን አድርገዋል።

14 ይሖዋ በእሷ ላይ ግራ የመጋባት መንፈስ አፍስሷል፤+

የሰከረ ሰው በትፋቱ ላይ እንደሚንገዳገድ ሁሉ

እነሱም ግብፅ በሥራዋ ሁሉ እንድትባዝን አድርገዋል።

15 ግብፅ ለራስም ሆነ ለጅራት፣ ለቀንበጥም ሆነ ለእንግጫ*

ልታደርገው የምትችለው ምንም ነገር የለም።

16 በዚያ ቀን ግብፃውያን እንደ ሴቶች ይሆናሉ፤ የሠራዊት ጌታ ይሖዋ በእነሱ ላይ እጁን በዛቻ ስለሚያወዛውዝ ይንቀጠቀጣሉ፤ ይሸበራሉም።+ 17 የይሁዳም ምድር ግብፅን ታሸብራለች። ስለ ምድሪቱ ሲወራ የሚሰሙ፣ የሠራዊት ጌታ ይሖዋ በግብፃውያን ላይ ከወሰነው ውሳኔ የተነሳ በፍርሃት ይርዳሉ።+

18 በዚያ ቀን በግብፅ ምድር የከነአንን ቋንቋ የሚናገሩና+ ለሠራዊት ጌታ ለይሖዋ ታማኝ እንደሚሆኑ በመሐላ የሚያረጋግጡ አምስት ከተሞች ይኖራሉ። ከእነዚህም መካከል አንዷ ‘የማፍረስ ከተማ’ ተብላ ትጠራለች።

19 በዚያ ቀን በግብፅ ምድር መካከል ለይሖዋ መሠዊያ ይሠራል፤ በድንበሯም ላይ ለይሖዋ ዓምድ ይቆማል። 20 ይህም በግብፅ ምድር ለሠራዊት ጌታ ለይሖዋ ምልክትና ምሥክር ይሆናል፤ እነሱ ከጨቋኞቻቸው የተነሳ ወደ ይሖዋ ይጮኻሉና፤ እሱም የሚታደጋቸው አዳኝ፣ አዎ ታላቅ አዳኝ ይልክላቸዋል። 21 ይሖዋም በግብፃውያን ዘንድ የታወቀ ይሆናል፤ በዚያም ቀን ግብፃውያን ይሖዋን ያውቁታል፤ መሥዋዕትና ስጦታ ያቀርባሉ፤ ለይሖዋም ይሳላሉ፤ የተሳሉትንም ይፈጽማሉ። 22 ይሖዋ ግብፅን ይመታታል፤+ መትቶ ይፈውሳታል፤ እነሱም ወደ ይሖዋ ይመለሳሉ፤ እሱም ልመናቸውን ሰምቶ ይፈውሳቸዋል።

23 በዚያ ቀን ከግብፅ ወደ አሦር የሚወስድ አውራ ጎዳና ይኖራል።+ ከዚያም አሦር ወደ ግብፅ፣ ግብፅም ወደ አሦር ይመጣል፤ ግብፅና አሦርም በአንድነት አምላክን ያገለግላሉ። 24 በዚያ ቀን እስራኤል ሦስተኛ ወገን ሆና ከግብፅና ከአሦር ጋር ትተባበራለች፤+ በምድርም መካከል በረከት ትሆናለች፤ 25 የሠራዊት ጌታ ይሖዋ “ሕዝቤ ግብፅ፣ የእጄም ሥራ አሦር፣ ርስቴም እስራኤል የተባረኩ ይሁኑ”+ ብሎ ይባርካቸዋልና።

20 የአሦር ንጉሥ ሳርጎን የላከው ታርታን* ወደ አሽዶድ+ በመጣበት ዓመት አሽዶድን ወግቶ ያዛት።+ 2 በዚያን ጊዜ ይሖዋ የአሞጽ ልጅ በሆነው በኢሳይያስ በኩል እንዲህ ሲል ተናገረ፦+ “ሂድ፣ ማቁን ከወገብህ ላይ አስወግድ፤ ጫማህንም ከእግርህ ላይ አውልቅ።” እሱም እንደተባለው አደረገ፤ ራቁቱንና* ባዶ እግሩንም ተመላለሰ።

3 ከዚያም ይሖዋ እንዲህ አለ፦ “አገልጋዬ ኢሳይያስ በግብፅና+ በኢትዮጵያ+ ላይ ለሚደርሰው ነገር ምልክትና+ ማስጠንቀቂያ እንዲሆን ለሦስት ዓመት ራቁቱንና ባዶ እግሩን እንደተመላለሰ ሁሉ፣ 4 የአሦር ንጉሥም የግብፅን ምርኮኞችና+ የኢትዮጵያን ግዞተኞች፣ ልጆችንና ሽማግሌዎችን ሳይቀር መቀመጫቸውን ገልቦ ራቁታቸውንና ባዶ እግራቸውን እየነዳ ይወስዳቸዋል፤ የግብፅንም እርቃን ያጋልጣል።* 5 ተስፋቸውን በጣሉባት በኢትዮጵያና በሚኮሩባት* በግብፅ የተነሳ በፍርሃት ይርዳሉ፤ ብሎም ያፍራሉ። 6 በዚያም ቀን በዚህ የባሕር ዳርቻ የሚኖረው ሕዝብ ‘ተስፋ የጣልንበትን ይኸውም እርዳታ ለማግኘትና ከአሦር ንጉሥ ለመዳን የሸሸንበትን አገር ተመልከቱ! በዚህ ዓይነት እኛስ እንዴት እናመልጣለን?’ ማለቱ አይቀርም።”

21 በምድረ በዳው ባሕር* ላይ የተላለፈ ፍርድ፦+

ከደቡብ አቅጣጫ አውሎ ነፋሳት እየጠራረጉ እንደሚመጡ፣

ከምድረ በዳ ይኸውም አስፈሪ ከሆነው ምድር የሆነ ነገር እየመጣ ነው።+

 2 አንድ የሚያስጨንቅ ራእይ ተነገረኝ፦

ከሃዲው ክህደት ይፈጽማል፤

አጥፊውም ያጠፋል።

ኤላም ሆይ፣ ተነሺ! ሜዶን ሆይ፣ ክበቢ!+

እሷ ያስከተለችው ሲቃ ሁሉ እንዲያከትም አደርጋለሁ።+

 3 ከዚህም የተነሳ በጣም ተሠቃየሁ።*+

ልትወልድ እንደተቃረበች ሴት፣

ምጥ ያዘኝ።

እጅግ ከመጨነቄ የተነሳ መስማት ተሳነኝ፤

እጅግ ከመረበሼም የተነሳ ማየት አቃተኝ።

 4 ልቤ ደከመ፤ በፍርሃት ተንቀጠቀጥኩ።

የምናፍቀው የምሽት ድንግዝግዝታ ሽብር ለቀቀብኝ።

 5 ማዕዱን አሰናዱ፤ መቀመጫ ቦታዎቹን አዘጋጁ!

ብሉ፣ ጠጡ!+

እናንተ መኳንንት፣ ተነሱ፤ ጋሻውን ዘይት ቀቡ!

 6 ይሖዋ እንዲህ ብሎኛልና፦

“ሂድ፣ ጠባቂ አቁም፤ የሚያየውንም ነገር እንዲናገር አድርግ።”

 7 እሱም በፈረሶች የሚጎተቱ የጦር ሠረገሎች፣

በአህዮች የሚጎተቱ የጦር ሠረገሎች፣

በግመሎች የሚጎተቱ የጦር ሠረገሎች አየ።

ዓይኑን ተክሎ በከፍተኛ ትኩረት ተመለከተ።

 8 ከዚያም እንደ አንበሳ ጮኾ እንዲህ አለ፦

“ይሖዋ ሆይ፣ በየቀኑ በመጠበቂያው ግንብ ላይ ቆሜአለሁ፤

በየሌሊቱም በጥበቃ ቦታዬ ላይ ተሰይሜአለሁ።+

 9 እየመጣ ያለውን ነገር ተመልከት፦

ሰዎች በፈረሶች በሚጎተት የጦር ሠረገላ እየመጡ ነው!”+

ከዚያም ጮክ ብሎ እንዲህ አለ፦

“ወደቀች! ባቢሎን ወደቀች!+

የተቀረጹትን የአማልክቷን ምስሎች በሙሉ መሬት ላይ ጥሎ ሰባበረ!”+

10 እንደ እህል የተወቃኸው ሕዝቤ፣

የአውድማዬ ውጤት* ሆይ፣+

ከእስራኤል አምላክ፣ ከሠራዊት ጌታ ከይሖዋ የሰማሁትን ነግሬሃለሁ።

11 በዱማ* ላይ የተላለፈ ፍርድ፦

አንዱ ከሴይር ጠርቶኝ እንዲህ አለኝ፦+

“ጠባቂ ሆይ፣ ስለ ሌሊቱ ምን ትላለህ?

ጠባቂ ሆይ፣ ስለ ሌሊቱ ምን ትላለህ?”

12 ጠባቂውም እንዲህ አለ፦

“ሊነጋ ነው፤ ሆኖም ተመልሶ ይመሻል።

መጠየቅ ከፈለጋችሁ ጠይቁ።

ተመልሳችሁ ኑ!”

13 በበረሃማው ሜዳ ላይ የተላለፈ ፍርድ፦

እናንተ የዴዳን+ ተጓዥ ነጋዴዎች ሆይ፣

በበረሃማው ሜዳ በሚገኘው ዱር ሌሊቱን ታሳልፋላችሁ።

14 የተጠማውን ለመገናኘት ውኃ ይዛችሁ ኑ፤

እናንተ የቴማ+ ነዋሪዎች ሆይ፣

ለሚሸሸውም ሰው ምግብ አምጡ።

15 እነሱ ከሰይፍ፣ ከተመዘዘ ሰይፍ፣

ከተደገነ ቀስትና ከተፋፋመ ጦርነት ሸሽተዋልና።

16 ይሖዋ እንዲህ ብሎኛል፦ “እንደ ቅጥር ሠራተኛ የሥራ ዘመን፣* በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ የቄዳር+ ክብር ሙሉ በሙሉ ይጠፋል። 17 ከቄዳር ተዋጊዎች የሚተርፉት ቀስተኞች ጥቂት ይሆናሉ፤ የእስራኤል አምላክ ይሖዋ ይህን ተናግሯልና።”

22 ስለ ራእይ ሸለቆ* የተነገረ የፍርድ መልእክት፦+

ሁላችሁም ጣሪያ ላይ የወጣችሁት ምን ሆናችሁ ነው?

 2 አንቺ ሁከት የነገሠብሽ መዲና፣ የፈንጠዝያም ከተማ፣

በትርምስ ተሞልተሻል።

ነዋሪዎችሽ ያለቁት በሰይፍ

ወይም በጦርነት ተገድለው አይደለም።+

 3 አምባገነን መሪዎችሽ ሁሉ በአንድ ላይ ሸሽተዋል።+

ሆኖም ቀስት መጠቀም ሳያስፈልግ ተማርከዋል።

ወደ ሩቅ ቦታ ሸሽተው ቢሄዱም

የተገኙት ሁሉ ተማርከዋል።+

 4 ስለዚህ እንዲህ አልኩ፦ “ዓይናችሁን ከእኔ ላይ አንሱ፤

እኔም አምርሬ አለቅሳለሁ።+

የሕዝቤ ሴት ልጅ* ከደረሰባት ጥፋት የተነሳ

እኔን ለማጽናናት አትድከሙ።+

 5 ከሉዓላዊው ጌታ፣ ከሠራዊት ጌታ ከይሖዋ ዘንድ

በራእይ ሸለቆ

ግራ የመጋባት፣ የሽንፈትና የመደናገጥ ቀን ሆኗልና።+

ቅጥሩ ይፈርሳል፤+

ወደ ተራራውም ይጮኻሉ።*

 6 ኤላም+ ሰዎችን ባሳፈሩ ሠረገሎችና በፈረሶች* ላይ

የፍላጻ ኮሮጆዋን ይዛለች፤

ቂርም+ የጋሻውን ልባስ አወለቀች።*

 7 ምርጥ የሆኑት ሸለቆዎችሽ*

በጦር ሠረገሎች ይሞላሉ፤

ፈረሶቹም* የከተማዋ በር ላይ ይቆማሉ፤

 8 የይሁዳም መከለያ*+ ይወገዳል።

“አንተም በዚያ ቀን የደኑን የጦር መሣሪያ ግምጃ ቤት ትመለከታለህ፤ 9 እናንተም በዳዊት ከተማ ቅጥር ላይ ያሉትን በርካታ ክፍተቶች ትመለከታላችሁ።+ በታችኛውም ኩሬ ውኃ ታጠራቅማላችሁ።+ 10 የኢየሩሳሌምን ቤቶች ትቆጥራላችሁ፤ ቅጥሩንም ለማጠናከር ቤቶቹን ታፈርሳላችሁ። 11 በሁለቱ ቅጥሮች መካከል በድሮው ኩሬ ላለው ውኃ የሚሆን ማጠራቀሚያ ትሠራላችሁ፤ ይሁንና ይህን ወዳደረገው ታላቅ አምላክ አትመለከቱም፤ ከዘመናት በፊት ወደሠራውም አምላክ አታዩም።

12 በዚያም ቀን ሉዓላዊው ጌታ፣ የሠራዊት ጌታ ይሖዋ

እንድታለቅሱና እንድታዝኑ፣+

ፀጉራችሁን እንድትላጩና ማቅ እንድትለብሱ ይጠራችኋል።

13 ይሁን እንጂ ድግስና ፈንጠዝያ፣

ፍሪዳ መጣልና ሙክት ማረድ፣

ሥጋ መብላትና የወይን ጠጅ መጠጣት ሆኗል።+

‘ነገ ስለምንሞት እንብላ፣ እንጠጣ’ ትላላችሁ።”+

14 ከዚያም የሠራዊት ጌታ ይሖዋ በጆሮዬ ይህን ገለጠልኝ፦ “‘እናንተ እስክትሞቱ ድረስ ይህ በደል አይሰረይላችሁም’+ ይላል ሉዓላዊው ጌታ፣ የሠራዊት ጌታ ይሖዋ።”

15 ሉዓላዊው ጌታ፣ የሠራዊት ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “በቤቱ* ላይ ወደተሾመው ወደ መጋቢው ወደ ሸብና+ ሄደህ እንዲህ በለው፦ 16 ‘በዚህ ለራስህ የመቃብር ቦታ የወቀርከው፣ የአንተ የሆነ ምን ነገር ቢኖርህ ነው? በዚህስ የአንተ የሆነ ማን አለ? በከፍታ ቦታ የራሱን መቃብር ወቅሯል፤ ቋጥኝ ጠርቦ ለራሱ ማረፊያ ስፍራ* አዘጋጅቷል። 17 ‘አንተ ሰው፣ እነሆ፣ ይሖዋ በኃይል አሽቀንጥሮ ይጥልሃል፤ ጨምድዶም ይይዝሃል። 18 ጠቅልሎና አጡዞ እንደ ኳስ ወደ ሰፊ ምድር ይወረውርሃል። በዚያ ትሞታለህ፤ ያማሩ ሠረገሎችህም በዚያ ለጌታህ ቤት ውርደት ይሆናሉ። 19 እኔም ከሹመትህ እሽርሃለሁ፤ ከኃላፊነትህም አባርርሃለሁ።

20 “‘በዚያም ቀን አገልጋዬን የኬልቅያስን ልጅ ኤልያቄምን+ እጠራለሁ፤ 21 ቀሚስህን አለብሰዋለሁ፤ መታጠቂያህንም በደንብ አስታጥቀዋለሁ፤+ ሥልጣንህንም* በእጁ አሳልፌ እሰጠዋለሁ። እሱም ለኢየሩሳሌም ነዋሪዎችና ለይሁዳ ቤት አባት ይሆናል። 22 የዳዊትንም ቤት ቁልፍ+ በትከሻው ላይ አደርጋለሁ። እሱ የሚከፍተውን ማንም አይዘጋም፤ እሱ የሚዘጋውንም ማንም አይከፍትም። 23 በአስተማማኝ ቦታ ላይ እንደ ማንጠልጠያ እተክለዋለሁ፤ ለአባቱም ቤት እንደ ክብር ዙፋን ይሆናል። 24 በእሱም ላይ የአባቱን ቤት ክብር* በሙሉ፣ ልጆቹንና ዘሮቹን* ይኸውም ትናንሾቹን ዕቃዎች በሙሉ፣ ጎድጓዳ ሳህኖቹንና ትላልቆቹን እንስራዎች ሁሉ ይሰቅሉበታል።

25 “‘በዚያም ቀን’ ይላል የሠራዊት ጌታ ይሖዋ፣ ‘በአስተማማኝ ቦታ ላይ የተተከለው ማንጠልጠያ ይነቀላል፤+ ተቆርጦም ይወድቃል፤ በላዩ ላይ የተንጠለጠለው ሸክምም ወድቆ ይከሰከሳል፤ ይሖዋ ራሱ ተናግሯልና።’”

23 ስለ ጢሮስ የተነገረ የፍርድ መልእክት፦+

እናንተ የተርሴስ መርከቦች+ ዋይ ዋይ በሉ!

ወደቧ ወድሟልና፤ ወደ እሷ መግባት አይቻልም።

ከኪቲም+ አገር ወሬው ደርሷቸዋል።

 2 እናንተ በባሕር ዳርቻ የምትኖሩ ሰዎች፣ ጸጥ በሉ።

ባሕሩን አቋርጠው የሚመጡት የሲዶና+ ነጋዴዎች ሀብት በሀብት አድርገዋችኋል።

 3 የገቢ ምንጮቿ የሆኑት የሺሆር*+ እህልና*

የአባይ መከር በብዙ ውኃዎች ላይ ተጓጉዘው

የብሔራትን ትርፍ ያመጡላት ነበር።+

 4 አንቺ የባሕር ምሽግ ሲዶና ሆይ፣ እፈሪ፤

ምክንያቱም ባሕሩ እንዲህ ብሏል፦

“አላማጥኩም፤ አልወለድኩምም፤

ወጣት ወንዶችንም ሆነ ሴቶችን* አላሳደግኩም።”+

 5 ስለ ግብፅ በተነገረው ወሬ እንደሆነው ሁሉ+

ስለ ጢሮስም በሚነገረው ወሬ ሰዎች ጭንቅ ይይዛቸዋል።+

 6 ባሕሩን አቋርጣችሁ ወደ ተርሴስ ተሻገሩ!

እናንተ በባሕር ዳርቻ የምትኖሩ ሰዎች ዋይ ዋይ በሉ!

 7 ከጥንት ዘመን፣ ከድሮ ጀምሮ ሐሴት ታደርግ የነበረችው ከተማችሁ ይህች ናት?

በዚያ ትኖር ዘንድ እግሮቿ ወደ ሩቅ ቦታዎች ይወስዷት ነበር።

 8 ዘውድ በምታጎናጽፈው፣

እንዲሁም መኳንንት የሆኑ ነጋዴዎች፣

በመላውም ምድር ላይ የተከበሩ ሻጮችና ለዋጮች በነበሯት

በጢሮስ ላይ ይህን ውሳኔ ያስተላለፈው ማን ነው?+

 9 በውበቷ ሁሉ የተነሳ የሚሰማትን ኩራት ለማርከስ

እንዲሁም በመላው ምድር ላይ የተከበሩትን ሁሉ ለማዋረድ

ይህን ውሳኔ ያስተላለፈው የሠራዊት ጌታ ይሖዋ ራሱ ነው።+

10 የተርሴስ ሴት ልጅ ሆይ፣ እንደ አባይ ወንዝ ምድርሽን አጥለቅልቂ።

ከእንግዲህ ወዲያ መርከብ የሚሠራበት ቦታ* አይኖርም።+

11 አምላክ እጁን በባሕሩ ላይ ዘርግቷል፤

መንግሥታትን አንቀጥቅጧል።

ይሖዋ የፊንቄ ምሽጎች እንዲወድሙ ትእዛዝ አስተላልፏል።+

12 እሱም እንዲህ ይላል፦ “አንቺ የተጨቆንሽ የሲዶና ድንግል ሆይ፣

ዳግመኛ ሐሴት አታደርጊም።+

ተነሽ፣ ወደ ኪቲም+ ተሻገሪ።

እዚያም ቢሆን እረፍት አታገኚም።”

13 የከለዳውያንን+ ምድር ተመልከቱ!

በበረሃ የሚኖሩ እንስሳት መፈንጫ ያደረጓት

አሦራውያን+ ሳይሆኑ እነዚህ ሰዎች ናቸው።

ጥቃት ለመሰንዘር የሚያስችል ማማ አቁመዋል፤

የማይደፈሩ ማማዎቿን በማፈራረስ+

የፍርስራሽ ክምር አድርገዋታል።

14 እናንተ የተርሴስ መርከቦች፣

ምሽጋችሁ ስለወደመ ዋይ ዋይ በሉ።+

15 በዚያም ቀን ጢሮስ እንደ አንድ ንጉሥ ዕድሜ* ለ70 ዓመት የተረሳች ትሆናለች።+ በ70ኛው ዓመት ማብቂያ ላይ ጢሮስ እንዲህ ተብሎ እንደሚዘመርላት ዝሙት አዳሪ ትሆናለች፦

16 “አንቺ የተረሳሽ ዝሙት አዳሪ፣ በገና ይዘሽ በከተማው ውስጥ ተዘዋወሪ።

በገናሽንም ጥሩ አድርገሽ ተጫወቺ፤

እነሱም እንዲያስታውሱሽ

ብዙ ዘፈን ዝፈኚ።”

17 በሰባው ዓመት መጨረሻ ላይ ይሖዋ ትኩረቱን በጢሮስ ላይ ያደርጋል፤ እሷም ዳግመኛ ክፍያ መቀበሏን ትቀጥላለች፤ በመላው ምድር ላይ ካሉ የዓለም መንግሥታትም ጋር ታመነዝራለች። 18 ሆኖም ትርፏና የምትቀበለው ክፍያ ለይሖዋ የተቀደሰ ይሆናል። አይከማችም ወይም አይጠራቀምም፤ ምክንያቱም በይሖዋ ፊት የሚኖሩ ሰዎች እስኪጠግቡ ድረስ እንዲበሉና የሚያምር ልብስ እንዲለብሱ እሷ የምትቀበለው ክፍያ ለእነሱ ይሰጣል።+

24 እነሆ፣ ይሖዋ ምድሪቱን ወና እና ባድማ ያደርጋታል።+

ይገለብጣታል፤*+ ነዋሪዎቿንም ይበትናቸዋል።+

 2 በሁሉም ላይ ተመሳሳይ ነገር ይደርሳል፦

በሕዝቡ ላይ የሚሆነው በካህኑ፣

በአገልጋዩ ላይ የሚሆነው በጌታው፣

በአገልጋይዋ ላይ የሚሆነው በእመቤቷ፣

በገዢው ላይ የሚሆነው በሻጩ፣

በአበዳሪው ላይ የሚሆነው በተበዳሪው፣

በወለድ ተቀባዩ ላይ የሚሆነው በወለድ ከፋዩ ላይ ይደርሳል።+

 3 ምድሪቱ ሙሉ በሙሉ ወና ትሆናለች፤

ፈጽሞ ትበዘበዛለች፤+

ይሖዋ ይህን ቃል ተናግሯልና።

 4 ምድሪቱ ታዝናለች፤*+ ትከስማለች።

ፍሬያማዋ ምድር ትራቆታለች፤ ትጠፋለች።

የምድሪቱ ታላላቅ ሰዎች ይዝላሉ።

 5 ሕጎቹን ስለተላለፉ፣+

ሥርዓቱን ስለለወጡና+

ዘላቂውን* ቃል ኪዳን ስላፈረሱ+

ምድሪቱ በገዛ ነዋሪዎቿ ተበክላለች።+

 6 ስለዚህ እርግማኑ ምድሪቱን በላት፤+

በላይዋም የሚኖሩ ሰዎች በደለኞች ሆነው ተገኝተዋል።

የምድሪቱ ነዋሪዎች ቁጥር የመነመነው በዚህ ምክንያት ነው፤

የቀሩት ሰዎችም በጣም ጥቂት ናቸው።+

 7 አዲሱ የወይን ጠጅ ያለቅሳል፤* የወይን ተክሉም ይጠወልጋል፤+

በልባቸውም ሐሴት አድርገው የነበሩ ሁሉ ያዝናሉ።+

 8 አስደሳች የሆነው የአታሞ ድምፅ መሰማት አቁሟል፤

ይፈነጥዙ የነበሩት ሰዎች ድምፅ ጠፍቷል፤

ደስ የሚያሰኘው የበገና ድምፅ መሰማቱ ቀርቷል።+

 9 ዘፈን በሌለበት የወይን ጠጅ ይጠጣሉ፤

መጠጡም ለሚጠጡት ሰዎች መራራ ይሆናል።

10 የተተወችው ከተማ ፈራርሳለች፤+

እያንዳንዱ ቤት ማንም እንዳይገባበት ተዘግቷል።

11 በየጎዳናው ላይ የወይን ጠጅ ፍለጋ ይጮኻሉ።

ሐሴት ጨርሶ ጠፍቷል፤

ምድሪቱም ደስታ ርቋታል።+

12 ከተማዋ ፈራርሳለች፤

በሩም ተሰባብሮ የፍርስራሽ ክምር ሆኗል።+

13 የወይራ ዛፍ ሲራገፍ+ እንደሚቀር ፍሬ፣

ወይንም ተሰብስቦ ካበቃ በኋላ እንደሚቀር ቃርሚያ፣+

ሕዝቤም በምድሪቱና በሌሎች ሕዝቦች መካከል እንዲሁ ይሆናል።

14 ድምፃቸውን ከፍ ያደርጋሉ፤

በደስታ እልል ይላሉ።

ከባሕሩ* የይሖዋን ግርማ ያውጃሉ።+

15 ከዚህም የተነሳ በብርሃን ምድር*+ ለይሖዋ ክብር ይሰጣሉ፤

በባሕር ደሴቶችም የእስራኤልን አምላክ የይሖዋን ስም ከፍ ከፍ ያደርጋሉ።+

16 ከምድር ዳርቻ “ለጻድቁ ክብር* ይሁን!”+

የሚል ዝማሬ እንሰማለን።

እኔ ግን እንዲህ አልኩ፦ “አቅም አጣሁ፤ አቅም አጣሁ!

ወዮልኝ! ከሃዲዎች ክህደት ፈጽመዋል፤

ከሃዲዎች በማታለል ክህደት ፈጽመዋል።”+

17 አንተ የምድሪቱ ነዋሪ ሆይ፣ ሽብር፣ ጉድጓድና ወጥመድ ይጠብቅሃል።+

18 ከሚያሸብረው ድምፅ የሚሸሽ ሁሉ ጉድጓድ ውስጥ ይወድቃል፤

ከጉድጓዱም የሚወጣ ሁሉ በወጥመዱ ይያዛል።+

የሰማይ የውኃ በሮች ይከፈታሉና፤

የምድርም መሠረቶች ይናወጣሉ።

19 ምድሪቱ ተሰነጣጥቃለች፤

ምድሪቱ ተንቀጥቅጣለች፤

ምድሪቱ በኃይል ትናወጣለች።+

20 ምድሪቱ እንደሰከረ ሰው ትንገዳገዳለች፤

ነፋስ እንደሚወዘውዘው ጎጆም በነፋስ ወዲያና ወዲህ ትወዛወዛለች።

በደሏም በላይዋ ላይ እጅግ ከብዷል፤+

ዳግመኛም እንደማትነሳ ሆና ትወድቃለች።

21 በዚያን ቀን ይሖዋ በላይ፣ በከፍታ ቦታ ባለው ሠራዊት ላይ፣

እንዲሁም በታች፣ በምድር ባሉት ነገሥታት ላይ ትኩረቱን ያደርጋል።

22 እነሱም እንደ እስረኞች ጉድጓድ ውስጥ

አንድ ላይ ይታጎራሉ፤

በእስር ቤት ውስጥም ይዘጋባቸዋል፤

ከብዙ ቀናት በኋላ ጉዳያቸው ይታያል።

23 ሙሉ ጨረቃ ትዋረዳለች፤

የምታበራው ፀሐይም ታፍራለች፤+

የሠራዊት ጌታ ይሖዋ በጽዮን ተራራና+ በኢየሩሳሌም ነግሦአልና፤+

በሕዝቡ ሽማግሌዎች ፊት* ክብር ተጎናጽፏል።+

25 ይሖዋ ሆይ፣ አንተ አምላኬ ነህ።

ድንቅ ነገሮችን ስላደረግክና+

ከጥንት ዘመን ጀምሮ ያሰብካቸውን ነገሮች*+

በታማኝነትና+ እምነት በሚጣልበት መንገድ ስለፈጸምክ

ከፍ ከፍ አደርግሃለሁ፤ ስምህንም አወድሳለሁ።

 2 ከተማዋን የድንጋይ ቁልል፣

የተመሸገችውንም ከተማ የፍርስራሽ ክምር አድርገሃልና።

የባዕዳኑ ማማ፣ ከተማ መሆኑ አብቅቶለታል፤

ከተማዋ በምንም ዓይነት ዳግመኛ አትገነባም።

 3 ከዚህም የተነሳ ኃያል የሆነ ሕዝብ ያከብርሃል፤

የጨቋኝ ብሔራት ከተማም ትፈራሃለች።+

 4 ለችግረኛው ምሽግ ሆነሃልና፤

ለድሃውም ከደረሰበት ጭንቀት መሸሸጊያ፣+

ከውሽንፍርም መጠለያ፣

ከፀሐይ ንዳድም ጥላ ሆነሃል።+

የጨቋኞች ቁጣ ከግንብ ጋር እንደሚላተም ውሽንፍር በሚሆንበት ጊዜ ጥበቃ ታደርጋለህ፤

 5 ውኃ በተጠማ ምድር እንዳለ ሙቀት

የባዕዳንን ሁከት ጸጥ ታደርጋለህ።

በደመና ጥላ እንደሚበርድ ሙቀት፣

የጨቋኞችም ዝማሬ ጸጥ ረጭ ይላል።

 6 የሠራዊት ጌታ ይሖዋ በዚህ ተራራ+ ላይ ለሕዝቦች ሁሉ

ምርጥ ምግቦች* የሚገኙበት ታላቅ ግብዣ ያዘጋጃል፤+

ያረጀ የወይን ጠጅ ግብዣ፣

መቅኒ የሞላባቸው ምርጥ ምግቦች

እንዲሁም የተጣራና ጥሩ የወይን ጠጅ የሚቀርቡበት ታላቅ ግብዣ ያደርጋል።

 7 በዚህ ተራራ ላይ ሕዝቦችን ሁሉ የሸፈነውን ከፈን

እንዲሁም ብሔራትን ሁሉ ተብትቦ የያዘውን መሸፈኛ ያስወግዳል።*

 8 ሞትን ለዘላለም ይውጣል፤*+

ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ ከፊት ሁሉ እንባን ያብሳል።*+

በሕዝቡ ላይ የደረሰውን ነቀፋ ከመላው ምድር ያስወግዳል፤

ይሖዋ ራሱ ይህን ተናግሯልና።

 9 በዚያም ቀን እንዲህ ይላሉ፦

“እነሆ፣ አምላካችን ይህ ነው!+

እሱን ተስፋ አድርገናል፤+

እሱም ያድነናል።+

ይሖዋ ይህ ነው!

እሱን ተስፋ አድርገናል።

በእሱ ማዳን ደስ ይበለን፤ ሐሴትም እናድርግ።”+

10 የይሖዋ እጅ በዚህ ተራራ ላይ ያርፋልና፤+

ጭድ በፍግ ክምር ላይ እንደሚረገጥ

ሞዓብም በስፍራው እንዲሁ ይረገጣል።+

11 አንድ ዋናተኛ በሚዋኝበት ጊዜ በእጆቹ ውኃውን እንደሚመታ

እሱም እጁን ዘርግቶ ሞዓብን ይመታዋል፤

በእጆቹ በጥበብ በመምታት

ትዕቢቱን ያበርድለታል።+

12 የተመሸገውን ከተማ

ከረጃጅም የመከላከያ ግንቦችህ ጋር ያፈርሳል፤

ምድር ላይ ጥሎ ከአፈር ይደባልቀዋል።

26 በዚያ ቀን በይሁዳ ምድር ይህ መዝሙር ይዘመራል፦+

“ጠንካራ ከተማ አለችን።+

እሱ መዳንን፣ ቅጥሯና መከላከያ ግንቧ ያደርጋል።+

 2 ጻድቅ ብሔር ይኸውም በታማኝነት የሚመላለሰው ብሔር

እንዲገባ በሮቹን ክፈቱ።+

 3 ሙሉ በሙሉ በአንተ የሚመኩትን* ትጠብቃለህ፤

በአንተ ስለሚታመኑ+

ዘላቂ ሰላም ትሰጣቸዋለህ።+

 4 በይሖዋ ለዘላለም ታመኑ፤+

ያህ* ይሖዋ የዘላለም ዓለት ነውና።+

 5 ከፍ ባለ ቦታ የሚኖሩትን፣

ከፍ ያለችውንም ከተማ ዝቅ አድርጓልና።

ያዋርዳታል፤ ወደ ምድር ይጥላታል፤

ከአፈርም ይደባልቃታል።

 6 የጎስቋላ ሰው እግር፣

የችግረኞችም ኮቴ ይረግጣታል።”

 7 የጻድቅ ሰው መንገድ ቀና* ነው።

አንተ ቅን ስለሆንክ

የጻድቁን መንገድ ደልዳላ ታደርጋለህ።

 8 ይሖዋ ሆይ፣ የፍትሕ ጎዳናህን ስንከተል፣

ተስፋ የምናደርገው አንተን ነው።

ስምህና መታሰቢያህ የልባችን* ምኞት ነው።*

 9 ሁለንተናዬ* በሌሊት አንተን ለማግኘት ይጓጓል፤

አዎ፣ መንፈሴ አንተን በጥብቅ ትፈልጋለች፤+

በምድር ላይ በምትፈርድበት ጊዜ

የምድሪቱ ነዋሪዎች ስለ ጽድቅ+ ይማራሉና።

10 ክፉ ሰው ቸርነት ቢደረግለት እንኳ

ፈጽሞ ጽድቅን አይማርም።+

በቅንነት* ምድር እንኳ ክፋት ይሠራል፤+

የይሖዋንም ግርማ አያይም።+

11 ይሖዋ ሆይ፣ እጅህ ከፍ ብሏል፤ እነሱ ግን አላዩትም።+

ለሕዝብህ ያለህን ቅንዓት በምታሳይበት ጊዜ ያያሉ፤ ለኀፍረትም ይዳረጋሉ።

አዎ፣ ለጠላቶችህ የተዘጋጀው እሳት ይበላቸዋል።

12 ይሖዋ ሆይ፣ አንተ ሰላም ትሰጠናለህ፤+

ምክንያቱም የሠራነውን ነገር ሁሉ

ያከናወንክልን አንተ ነህ።

13 ይሖዋ አምላካችን ሆይ፣ ከአንተ ሌላ፣ ሌሎች ጌቶች ገዝተውናል፤+

እኛ ግን የአንተን ስም ብቻ እንጠራለን።+

14 እነሱ ሞተዋል፤ በሕይወትም አይኖሩም።

በሞት ተረተዋል፤ አይነሱም።+

ታጠፋቸውና ስማቸው ጨርሶ እንዳይነሳ ታደርግ ዘንድ

ትኩረትህን ወደ እነሱ አዙረሃልና።

15 ሕዝቡን አበዛህ፤ ይሖዋ ሆይ፣

ሕዝቡን አበዛህ፤

ራስህን አስከበርክ።+

የምድሪቱን ወሰን ሁሉ እጅግ አሰፋህ።+

16 ይሖዋ ሆይ፣ በተጨነቁ ጊዜ አንተን ፈለጉ፤

በገሠጽካቸው ጊዜ በሹክሹክታ ድምፅ በመጸለይ ልባቸውን አፈሰሱ።+

17 ይሖዋ ሆይ፣ ነፍሰ ጡር ሴት ልትወልድ ስትል

ምጥ እንደሚይዛትና በምጥ ጣር እንደምትጮኽ ሁሉ

እኛም በአንተ የተነሳ እንዲሁ ሆነናል።

18 አርግዘን ነበር፤ ደግሞም አምጠን ነበር፤

ይሁንና ነፋስን የወለድን ያህል ነበር።

ለምድሪቱ መዳን አላስገኘንም

እንዲሁም በምድሪቱ ላይ እንዲኖር የተወለደ አንድም ልጅ የለም።

19 “ሙታንህ ሕያዋን ይሆናሉ።

የእኔ አስከሬኖች ይነሳሉ።+

እናንተ በአፈር ውስጥ የምትኖሩ፣+

ተነሱ፤ በደስታም እልል በሉ!

ጠልህ እንደ ማለዳ ጠል ነውና፤*

ምድርም በሞት የተረቱት ዳግም ሕይወት እንዲያገኙ ታደርጋለች።*

20 ሕዝቤ ሆይ፣ ሂድ ወደ ውስጠኛው ክፍልህ ግባ፤

በርህንም ከኋላህ ዝጋ።+

ቁጣው* እስኪያልፍ ድረስ

ለጥቂት ጊዜ ተሸሸግ።+

21 እነሆ፣ ይሖዋ የምድሪቱ ነዋሪ የፈጸመውን በደል ለመፋረድ

ከመኖሪያ ቦታው ይመጣልና፤

ምድሪቱም በላይዋ የፈሰሰውን ደም ትገልጣለች፤

በላይዋም የተገደሉትን ከዚህ በኋላ አትደብቅም።”

27 በዚያን ቀን ይሖዋ፣ በፍጥነት እየተሳበ የሚሄደውን እባብ ሌዋታንን፣*

ደግሞም እየተጥመለመለ የሚጓዘውን እባብ ሌዋታንን

ትልቅ፣ ኃይለኛና ምሕረት የለሽ በሆነው ሰይፉ ይቀጣዋል፤+

በባሕር ውስጥ ያለውንም ግዙፍ ፍጥረት ይገድለዋል።

 2 በዚያ ቀን ለእሷ* እንዲህ ብላችሁ ዘምሩ፦

“የሚፈላ የወይን ጠጅ የሚመረትባት የወይን እርሻ!+

 3 እኔ ይሖዋ እጠብቃታለሁ።+

በየጊዜው ውኃ አጠጣታለሁ።+

ማንም ጉዳት እንዳያደርስባት

ሌት ተቀን እጠብቃታለሁ።+

 4 ከእንግዲህ አልቆጣትም።+

በውጊያው ላይ ቁጥቋጦና አረም ይዞ የሚገጥመኝ ማን ነው?

ሁሉንም በአንድ ላይ እረግጣቸዋለሁ፤ በእሳትም አቃጥላቸዋለሁ።

 5 አለዚያ ምሽጌን የሙጥኝ ይበል።

ከእኔ ጋር ሰላም ይፍጠር፤

አዎ፣ ከእኔ ጋር ሰላም ይፍጠር።”

 6 በመጪዎቹ ቀናት ያዕቆብ ሥር ይሰዳል፤

እስራኤል ያብባል እንዲሁም ይለመልማል፤+

ምድሩንም በምርት ይሞሉታል።+

 7 እሱ አሁን በተመታበት ሁኔታ መመታቱ ተገቢ ነው?

ወይስ የተገደሉበት ሰዎች በተፈጁበት መንገድ መገደሉ አስፈላጊ ነው?

 8 እሷን በምትልካት ጊዜ በአስደንጋጭ ጩኸት ትፋለማታለህ።

የምሥራቅ ነፋስ በሚነፍስበት ቀን በኃይለኛ አውሎ ነፋሱ ያስወግዳታል።+

 9 በመሆኑም የያዕቆብ በደል በዚህ መንገድ ይሰረይለታል፤+

ኃጢአቱ በሚወገድበት ጊዜ ፍሬው በሙሉ ይህ ይሆናል፦

የመሠዊያ ድንጋዮቹን ሁሉ

እንደደቀቀ የኖራ ድንጋይ ያደርጋል፤

የማምለኪያ ግንዶቹም* ሆኑ የዕጣን ማጨሻዎቹ አይተርፉም።+

10 የተመሸገችው ከተማ ትተዋለችና፤

የግጦሽ መሬቱም ወና ይሆናል፤ እንደ ምድረ በዳም የተተወ ይሆናል።+

በዚያ ጥጃ ይግጣል፤ ይተኛልም፤

ቅርንጫፎቿንም ይበላል።+

11 ቀንበጦቿ በሚደርቁበት ጊዜ

ሴቶች መጥተው ይሰብሯቸዋል፤

ከዚያም ማገዶ ያደርጓቸዋል።

ይህ ሕዝብ ማስተዋል ይጎድለዋልና።+

በዚህም ምክንያት ፈጣሪያቸው ምንም ምሕረት አያደርግላቸውም፤

ሠሪያቸውም ምንም ዓይነት ሞገስ አያሳያቸውም።+

12 በዚያም ቀን የእስራኤል ሕዝብ ሆይ፣ ሰው ዛፍ ላይ ያሉ ፍሬዎችን አርግፎ አንድ በአንድ እንደሚለቅም ሁሉ፣ ይሖዋም ከታላቁ ወንዝ* አንስቶ እስከ ግብፅ ደረቅ ወንዝ*+ ድረስ ባለው ቦታ ሁሉ የተበተናችሁትን ይሰበስባችኋል።+ 13 በዚያም ቀን ትልቅ ቀንደ መለከት ይነፋል፤+ በአሦር ምድር+ የጠፉትና በግብፅ ምድር+ የተበተኑት መጥተው በኢየሩሳሌም በሚገኘው ቅዱስ ተራራ ላይ ለይሖዋ ይሰግዳሉ።+

28 ጎልታ ለምትታየው* ለኤፍሬም+ ሰካራሞች አክሊል* ወዮላት!

ይህች የምታምር ጌጥ በወይን ጠጅ የተሸነፉ ሰዎች በሚኖሩበት

ለም ሸለቆ አናት ላይ የምትገኝ የምትጠወልግ አበባ ናት።

 2 እነሆ፣ ይሖዋ ጠንካራና ብርቱ የሆነውን ይልካል።

እሱም እንደ ነጎድጓዳማ የበረዶ ውሽንፍር፣ እንደ አጥፊ አውሎ ነፋስ፣

ኃይለኛ ጎርፍ እንደሚያስከትል ነጎድጓዳማ ውሽንፍር

በኃይል አሽቀንጥሮ ወደ ምድር ይጥላታል።

 3 ጎልተው የሚታዩት* የኤፍሬም ሰካራሞች ያደረጓቸው አክሊሎች

በእግር ይረገጣሉ።+

 4 ለም በሆነው ሸለቆ አናት ላይ የምትገኘውና

የምታምር ጌጥ የሆነችው የምትጠወልግ አበባ

ከበጋ በፊት፣ በመጀመሪያው ወቅት እንደምትበስል በለስ ትሆናለች።

ሰውም ባያት ጊዜ ቀጥፎ ወዲያውኑ ይውጣታል።

5 በዚያ ቀን የሠራዊት ጌታ ይሖዋ ከሕዝቡ መካከል ለተረፉት ሰዎች የሚያምር አክሊልና ውብ የአበባ ጉንጉን ይሆናል።+ 6 በፍርድ ወንበር ለተቀመጠውም የፍትሕ መንፈስ፣ የከተማዋ በር ላይ የሚሰነዘረውን ጥቃት ለሚመክቱም የብርታት ምንጭ ይሆናል።+

 7 እነዚህም ከወይን ጠጅ የተነሳ መንገድ ይስታሉ፤

ከሚያሰክር መጠጥ የተነሳም ይንገዳገዳሉ።

ካህኑና ነቢዩ ከጠጡት መጠጥ የተነሳ መንገድ ይስታሉ፤

ከወይን ጠጅ የተነሳ ግራ ይጋባሉ፤

ከሚያሰክር መጠጥ የተነሳም ይንገዳገዳሉ፤

የሚያዩት ራእይ መንገድ ያስታቸዋል፤

ፍርድ ሲሰጡም ይሳሳታሉ።+

 8 ገበታቸው ሁሉ በሚያስጸይፍ ትውከት ተሞልቷል፤

ያልተበላሸ ቦታም የለም።

 9 እነሱም እንዲህ ይላሉ፦ “እውቀትን የሚያካፍለው ለማን ነው?

መልእክቱንስ የሚያስረዳው ለማን ነው?

ገና ወተት ለተዉ፣

ጡትም ለጣሉ ሕፃናት ነው?

10 ‘በትእዛዝ ላይ ትእዛዝ፣ በትእዛዝ ላይ ትእዛዝ፣

በሥርዓት ላይ ሥርዓት፣ በሥርዓት ላይ ሥርዓት፣*+

እዚህ ጥቂት፣ እዚያ ጥቂት’ ነውና።”

11 ስለዚህ በሚንተባተቡ ሰዎች አንደበትና በባዕድ ቋንቋ ለዚህ ሕዝብ ይናገራል።+ 12 በአንድ ወቅት “ይህ የእረፍት ቦታ ነው። የዛለው እንዲያርፍ አድርጉ፤ ይህ የእፎይታ ቦታ ነው” ብሏቸው ነበር፤ እነሱ ግን ለመስማት ፈቃደኞች አልሆኑም።+ 13 የይሖዋም ቃል ለእነሱ

“በትእዛዝ ላይ ትእዛዝ፣ በትእዛዝ ላይ ትእዛዝ፣

በሥርዓት ላይ ሥርዓት፣ በሥርዓት ላይ ሥርዓት፣*+

እዚህ ጥቂት፣ እዚያ ጥቂት” ይሆንባቸዋል፤

በመሆኑም ሲሄዱ፣

ተሰናክለው ወደ ኋላ ይወድቃሉ፤

ደግሞም ይሰበራሉ፣ ይጠመዳሉ እንዲሁም ይያዛሉ።+

14 ስለዚህ እናንተ ጉረኞች፣

በኢየሩሳሌም የሚኖረው ሕዝብ ገዢዎች፣ የይሖዋን ቃል ስሙ፦

15 እናንተ እንዲህ ብላችኋልና፦

“ከሞት ጋር ቃል ኪዳን ገብተናል፤+

ከመቃብርም * ጋር ስምምነት አድርገናል።*

በድንገት የሚያጥለቀልቅ ጎርፍ ሲያልፍ

እኛን አይነካንም፤

ውሸትን መጠጊያችን አድርገናልና፤

በሐሰትም ውስጥ ተደብቀናል።”+

16 ስለዚህ ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦

“እነሆ፣ በጽዮን የመሠረት ድንጋይ ይኸውም የተፈተነ ድንጋይ፣+

አስተማማኝ መሠረት+ ሆኖ የተጣለ ክቡር የማዕዘን ድንጋይ+ አኖራለሁ።

በእሱ የሚያምን አይደናገጥም።+

17 እኔም ፍትሕን የመለኪያ ገመድ፣+

ጽድቅንም ውኃ ልክ* አደርጋለሁ።+

የውሸት መጠጊያውን፣ በረዶ ጠራርጎ ይወስደዋል፤

ውኃዎቹም መደበቂያ ቦታውን ያጥለቀልቁታል።

18 ከሞት ጋር የገባችሁት ቃል ኪዳን ይፈርሳል፤

ከመቃብርም * ጋር ያደረጋችሁት ስምምነት አይጸናም።+

በድንገት የሚያጥለቀልቀው ጎርፍ ሲያልፍ

ድምጥማጣችሁን ያጠፋል።

19 ጎርፉ ባለፈ ቁጥር

ጠራርጎ ይወስዳችኋል፤+

በየማለዳው እንዲሁም

በቀንና በሌሊት ያልፋልና።

የተነገረውን ነገር እንዲረዱ የሚያደርገው ሽብር ብቻ ነው።”*

20 እግር ተዘርግቶ እንዳይተኛ አልጋው አጭር ነውና፤

ተሸፋፍኖም እንዳይተኛ ጨርቁ በጣም ጠባብ ነው።

21 ይሖዋ ተግባሩን ይኸውም እንግዳ የሆነ ተግባሩን ያከናውን ዘንድ

እንዲሁም ሥራውን ይኸውም ያልተለመደ ሥራውን ይሠራ ዘንድ+

በጰራጺም ተራራ እንዳደረገው ይነሳልና፤

በገባኦን አቅራቢያ ባለው ሸለቆ* እንዳደረገውም ራሱን ያነሳሳል።+

22 እንግዲህ ፌዘኞች አትሁኑ፤+

አለዚያ እስራቱ ይበልጥ ይጠብቅባችኋል፤

ሉዓላዊው ጌታ፣ የሠራዊት ጌታ ይሖዋ

አገሪቱን በሙሉ* ለማጥፋት ያስተላለፈውን ፍርድ ሰምቻለሁና።+

23 ጆሯችሁን አዘንብሉ፤ ድምፄንም ስሙ፤

ለምናገረው ነገር ትኩረት ስጡ፤ በጥሞናም አዳምጡ።

24 ገበሬ ዘር ከመዝራቱ በፊት ቀኑን ሙሉ ሲያርስ ይውላል?

ደግሞስ ጓሉን ሲከሰክስና መሬቱን ሲያለሰልስ ይከርማል?+

25 ከዚህ ይልቅ መሬቱን ከደለደለ በኋላ

ጥቁር አዝሙድና ከሙን አይዘራም?

ስንዴውን፣ ማሽላውንና ገብሱንስ በቦታ በቦታቸው አይዘራም?

ደግሞስ አጃውን+ ዳር ላይ አይዘራም?

26 አምላክ ሰውን በትክክለኛው መንገድ ያስተምረዋል፤*

ደግሞም ይመራዋል።+

27 ጥቁር አዝሙድ በማሄጃ*+ አይወቃም፤

በከሙንም ላይ የመውቂያ መንኮራኩር* እንዲሄድ አይደረግም።

ጥቁር አዝሙድ በበትር፣

ከሙንም በዘንግ ይወቃል።

28 ሰው የዳቦ እህል እንዲደቅ ያደርጋል?

በጭራሽ፤ እስኪደቅ ድረስ አይወቃውም፤+

በፈረሶቹ የሚጎተተውን የመውቂያ መንኮራኩር በሚያስኬድበት ጊዜ፣

እህሉን አያደቀውም።+

29 ይህም የተገኘው፣ አስደናቂ ምክር* ካለውና

ታላላቅ ሥራዎችን ካከናወነው*

ከሠራዊት ጌታ ከይሖዋ ነው።+

29 “ለአርዔል፣* ዳዊት ለሰፈረባት ከተማ+ ለአርዔል ወዮላት!

በዓመት ላይ ዓመት ጨምሩ፤

ዓመታዊ በዓሎቻችሁን+ ማክበራችሁን ቀጥሉ።

 2 እኔ ግን በአርዔል ላይ የሚያስጨንቅ ነገር አመጣለሁ፤+

ለቅሶና ዋይታም ይሆናል፤+

እሷም ለእኔ፣ እንደ አምላክ የመሠዊያ ምድጃ ትሆናለች።+

 3 አንቺን ለማጥቃት በዙሪያሽ እሰፍራለሁ፤

በሹል እንጨት አጥርሻለሁ፤

በአንቺም ዙሪያ ቅጥር እገነባለሁ።+

 4 ትወድቂያለሽ፤ ትዋረጃለሽም፤

መሬት ላይ ሆነሽ ትናገሪያለሽ፤

የምትናገሪው ነገር በአፈር ይታፈናል።

ድምፅሽ እንደ መናፍስት ጠሪ ድምፅ

ከመሬት ይመጣል፤+

ቃልሽም ከአፈር ይጮኻል።

 5 የጠላቶችሽ* ሠራዊት እንደላመ ዱቄት ይሆናል፤+

የጨቋኞች መንጋ ተጠርጎ እንደሚሄድ ገለባ ይሆናል።+

ይህም ሳይታሰብ፣ በቅጽበት ይፈጸማል።+

 6 የሠራዊት ጌታ ይሖዋ ትኩረቱን ወደ አንቺ በማዞር

በነጎድጓድ፣ በምድር መናወጥ፣ በታላቅ ድምፅ፣

በውሽንፍር፣ በአውሎ ነፋስና በሚባላ የእሳት ነበልባል ያድንሻል።”+

 7 በዚያን ጊዜ አርዔልን የሚወጉ የብሔራት ሠራዊት ሁሉ፣+

ይኸውም ጦርነት የሚከፍቱባት ሁሉ፣

በእሷ ላይ ጥቃት ለመሰንዘር ማማዎችን የሚሠሩና

ጭንቀት ላይ የሚጥሏት ሁሉ

እንደ ሕልም፣ በሌሊትም እንደሚታይ ራእይ ይሆናሉ።

 8 አዎ፣ የተራበ ሰው በሕልሙ ሲበላ ቆይቶ

ሲነቃ ግን ረሃቡ እንደማይለቀው* ሁሉ፣

ደግሞም የተጠማ ሰው በሕልሙ ሲጠጣ ቆይቶ

ሲነቃ ግን ዝሎና ተጠምቶ እንደሚነሳ* ሁሉ እንዲሁ ይሆናል።

በጽዮን ተራራ ላይ ጦርነት የሚከፍቱ የብሔራት ሠራዊትም ሁሉ

ተመሳሳይ ነገር ይደርስባቸዋል።+

 9 ክው በሉ፤ ተደነቁም፤+

ዓይናችሁን ጨፍኑ፤ ዕውሮችም ሁኑ።+

በወይን ጠጅ አይሁን እንጂ ሰክረዋል፤

በሚያሰክር መጠጥ አይሁን እንጂ ተንገዳግደዋል።

10 ይሖዋ ኃይለኛ የእንቅልፍ መንፈስ አፍስሶባችኋልና፤+

ዓይኖቻችሁን ይኸውም ነቢያትን ጨፍኖባችኋል፤+

ራሶቻችሁን ይኸውም ባለ ራእዮችን ሸፍኖባችኋል።+

11 የሁሉ ነገር ራእይ እንደታሸገ መጽሐፍ ቃል ሆኖባችኋል።+ መጽሐፉን ማንበብ ለሚችል ሰው “እባክህ፣ ጮክ ብለህ አንብበው” ብለው ሲሰጡት “ታሽጓልና አልችልም” ይላል። 12 መጽሐፉንም ማንበብ ለማይችል ሰው “እባክህ፣ ይህን አንብበው” ብለው ሲሰጡት “ፈጽሞ ማንበብ አልችልም” ይላል።

13 ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “ይህ ሕዝብ ወደ እኔ የሚቀርበው በአፉ ብቻ ነው፤

በከንፈሩም ያከብረኛል፤+

ልቡ ግን ከእኔ እጅግ የራቀ ነው፤

እኔንም የሚፈራው፣ ሰዎች ያስተማሩትን ትእዛዛት በማክበር ነው።+

14 ስለዚህ እኔ በእነዚህ ሰዎች ላይ ዳግመኛ የሚያስደንቁ ነገሮች አደርጋለሁ፤+

በድንቅ ላይ ድንቅ ነገር እፈጽማለሁ፤

የጥበበኞቻቸውም ጥበብ ይጠፋል፤

የአስተዋዮቻቸውም ማስተዋል ይሰወራል።”+

15 ዕቅዳቸውን ከይሖዋ ለመሰወር* ከፍተኛ ጥረት ለሚያደርጉ ወዮላቸው!+

“ማን ያየናል?

ማንስ ያውቅብናል?” በማለት

ተግባራቸውን በጨለማ ቦታ ያከናውናሉ።+

16 እናንተ ሰዎች፣ ነገር ታጣምማላችሁ!*

ሸክላ ሠሪው እንደ ሸክላው ሊቆጠር ይገባል?+

የተሠራው ነገር ስለ ሠሪው

“እሱ አልሠራኝም” ማለቱ ተገቢ ነው?+

ደግሞስ ዕቃው ሠሪውን

“ማስተዋል የለውም” ይላል?+

17 በአጭር ጊዜ ውስጥ ሊባኖስ ወደ ፍራፍሬ እርሻነት ይለወጣል፤+

የፍራፍሬ እርሻውም እንደ ጫካ ይቆጠራል።+

18 በዚያ ቀን፣ መስማት የተሳናቸው ሰዎች የመጽሐፉን ቃል ይሰማሉ፤

የዓይነ ስውራኑም ዓይኖች ከጭጋግና ከጨለማ ተላቀው ያያሉ።+

19 የዋሆች በይሖዋ እጅግ ሐሴት ያደርጋሉ፤

በሰዎች መካከል ያሉ ድሆችም በእስራኤል ቅዱስ ደስ ይላቸዋል።+

20 ጨቋኙ ያከትምለታልና፤

ጉረኛውም ያበቃለታል፤

ሌሎችን ለመጉዳት አሰፍስፈው የሚጠባበቁ ሁሉ ይጠፋሉ፤+

21 ሌሎችን በውሸት ቃል በደለኛ የሚያደርጉ፣

በከተማዋ በር፣+ በተሟጋቹ* ላይ ወጥመድ የሚዘረጉና

መሠረተ ቢስ በሆነ ክስ ጻድቁን ሰው ፍትሕ የሚነፍጉ ይጠፋሉ።+

22 ስለዚህ አብርሃምን+ የተቤዠው ይሖዋ ለያዕቆብ ቤት እንዲህ ይላል፦

“ያዕቆብ ከእንግዲህ አያፍርም፤

ፊቱም ከእንግዲህ አይገረጣም።*+

23 የእጆቼ ሥራ የሆኑትን ልጆቹን

በመካከሉ በሚያይበት ጊዜ፣+

ስሜን ይቀድሳሉና፤

አዎ፣ የያዕቆብን ቅዱስ ይቀድሳሉ፤

የእስራኤልንም አምላክ ይፈራሉ።*+

24 በመንፈስ የባዘኑ ማስተዋል ያገኛሉ፤

የሚያጉረመርሙም የሚሰጣቸውን ትምህርት ይቀበላሉ።”

30 “ግትር ለሆኑ ልጆች ወዮላቸው”+ ይላል ይሖዋ፤

“በኃጢአት ላይ ኃጢአት ለመጨመር

የእኔን ሳይሆን የራሳቸውን ዕቅድ ይፈጽማሉ፤+

ደግሞም ኅብረት ይፈጥራሉ፤* ይህን የሚያደርጉት ግን በመንፈሴ አይደለም።

 2 በፈርዖን ጥበቃ ሥር* ለመሸሸግና

በግብፅ ጥላ ሥር ለመጠለል

እኔን ሳያማክሩ*+ ወደ ግብፅ ይወርዳሉ!+

 3 ይሁንና ፈርዖን የሚያደርግላችሁ ጥበቃ ለኀፍረት፣

በግብፅ ጥላ ሥር መጠለልም ለውርደት ይዳርጋችኋል።+

 4 መኳንንቱ በጾዓን+ ናቸውና፤

መልእክተኞቹም ሃኔስ ደርሰዋል።

 5 ምንም ሊጠቅማቸው በማይችል፣

እርዳታ በማይሰጥና ጥቅም በማያስገኝ፣

ይልቁንም ለውርደትና ለነቀፋ በሚዳርግ ሕዝብ

ሁሉም ኀፍረት ይከናነባሉ።”+

6 በደቡብ እንስሳት ላይ የተላለፈ ፍርድ፦

አንበሳ፣ አዎ የሚያገሳ አንበሳ ባለበት፣

እፉኝት እንዲሁም የሚበርና የሚያቃጥል እባብ* በሚገኙበት፣

አስጨናቂና አስቸጋሪ ሁኔታዎች በሞሉበት ምድር

ሀብታቸውን በአህያ ላይ፣

ቁሳቁሳቸውንም በግመል ሻኛ ላይ ጭነው ይሄዳሉ።

ሆኖም እነዚህ ነገሮች ለሕዝቡ ምንም ጥቅም አያስገኙለትም።

 7 ግብፅ የምትሰጠው እርዳታ ምንም እርባና የለውምና።+

ስለዚህ እሷን “ረዓብ፣+ ሥራ ፈታ የምትጎለት” ብዬ ጠርቻታለሁ።

 8 “በል ሂድ፤ ለመጪዎቹ ዘመናት፣

ቋሚ ምሥክር እንዲሆን

እነሱ ባሉበት በጽላት ላይ ጻፈው፤

በመጽሐፍም ላይ ክተበው።+

 9 እነሱ ዓመፀኛ ሕዝብ፣+ አታላይ ልጆችና+

የይሖዋን ሕግ* ለመስማት እንቢተኛ የሆኑ ልጆች ናቸውና።+

10 ባለ ራእዮችን ‘ከእንግዲህ ራእይ አትዩ’ ይላሉ፤

ነቢያትንም እንዲህ ይላሉ፦ ‘እውነተኛ ራእይ አትንገሩን።+

የሚጥም* ነገር ንገሩን፤ አሳሳች የሆነ ሕልም አልሙልን።+

11 ከመንገዱ ዞር በሉ፤ ጎዳናውንም ልቀቁ።

የእስራኤልን ቅዱስ በፊታችን አታድርጉ።’”+

12 ስለዚህ የእስራኤል ቅዱስ እንዲህ ይላል፦

“ይህን ቃል ስለናቃችሁ፣+

በማጭበርበርና በማታለል ስለታመናችሁ፣

በዚያም ላይ ስለተደገፋችሁ፣+

13 ይህ በደል እንደተሰነጠቀ ቅጥር፣

ሊወድቅ እንደተቃረበ ያዘመመ ረጅም ቅጥር ይሆንባችኋል።

ሳይታሰብ በድንገት ይፈርሳል።

14 ሸክላ ሠሪ እንደሠራው ትልቅ እንስራ ይሰባበራል፤

እንክትክቱ ከመውጣቱ የተነሳ ከምድጃ ፍም ለመውሰድ

ወይም ከረግረጋማ ቦታ* ውኃ ለመጨለፍ የሚያስችል

አንድም ገል አይገኝም።”

15 የእስራኤል ቅዱስ ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላልና፦

“ወደ እኔ በመመለስና በማረፍ ትድናላችሁ፤

ሳትረበሹ፣ ተማምናችሁ በመኖር ብርቱ መሆናችሁን ታሳያላችሁ።”+

እናንተ ግን ፈቃደኞች አልሆናችሁም።+

16 ይልቁንም “አይሆንም፣ በፈረሶች እንሸሻለን!” አላችሁ።

ደግሞም ትሸሻላችሁ።

“በፈጣን ፈረሶችም እንጋልባለን!” አላችሁ።+

ስለሆነም የሚያሳድዷችሁ ሰዎች ፈጣኖች ይሆናሉ።+

17 አንድ ሰው ከሚሰነዝረው ዛቻ የተነሳ ሺዎች ይሸበራሉ፤+

በተራራ አናት ላይ እንደተተከለ ምሰሶና

በኮረብታ ላይ እንደቆመ ለምልክት የሚያገለግል ግንድ ሆናችሁ እስክትቀሩ ድረስ፣

አምስት ሰዎች ከሚሰነዝሩት ዛቻ የተነሳ ትሸሻላችሁ።+

18 ይሁንና ይሖዋ ሞገስ ሊያሳያችሁ በትዕግሥት* ይጠባበቃል፤+

ምሕረት ሊያሳያችሁም ይነሳል።+

ይሖዋ የፍትሕ አምላክ ነውና።+

እሱን በተስፋ* የሚጠባበቁ ሁሉ ደስተኞች ናቸው።+

19 ሕዝቡ በጽዮን ይኸውም በኢየሩሳሌም በሚኖርበት ጊዜ+ ፈጽሞ አታለቅሱም።+ እርዳታ ለማግኘት በምትጮኹበት ጊዜ በእርግጥ ሞገስ ያሳያችኋል፤ ጩኸታችሁን እንደሰማም ይመልስላችኋል።+ 20 ይሖዋ የጭንቀትን ምግብና የጭቆናን ውኃ ቢሰጥህም+ እንኳ ታላቁ አስተማሪህ ከእንግዲህ ራሱን አይሰውርም፤ በገዛ ዓይኖችህም ታላቁን አስተማሪህን+ ታያለህ። 21 ወደ ቀኝ ወይም ወደ ግራ ዞር ብትል ጆሮህ ከኋላህ “መንገዱ ይህ ነው።+ በእሱ ሂድ” የሚል ድምፅ ይሰማል።+

22 የተቀረጹ ምስሎችህ የተለበጡበትን ብርና ከብረት የተሠሩ ሐውልቶችህ*+ የተለበጡበትን ወርቅ ታረክሳለህ። እንደ ወር አበባ ጨርቅ “ከዚህ ጥፉ!”* በማለት አሽቀንጥረህ ትጥላቸዋለህ።+ 23 እሱም መሬት ላይ ለምትዘራው ዘር ዝናብ ይሰጥሃል፤+ ምድሪቱም የምታፈራው እህል የተትረፈረፈና ምርጥ* ይሆናል።+ በዚያም ቀን ከብቶችህ ሰፊ በሆነ የግጦሽ መስክ ይሰማራሉ።+ 24 መሬቱንም የሚያርሱ ከብቶችና አህዮች በእንቧጮ* የተቀመመ እንዲሁም በላይዳና በመንሽ የተለየ ገፈራ ይበላሉ። 25 ብዙ እልቂት በሚደርስበትና ግንቦች በሚፈርሱበት ቀን፣ በረጅም ተራራና ከፍ ባለ ኮረብታ ሁሉ ላይ ጅረቶች ይፈስሳሉ፤+ የውኃ መውረጃ ቦዮችም ይኖራሉ። 26 የሙሉ ጨረቃ ብርሃንም እንደ ፀሐይ ብርሃን ይሆናል፤ ይሖዋ የሕዝቡን ስብራት* በሚጠግንበትና+ በእሱ ምት የተነሳ የደረሰባቸውን ከባድ ቁስል በሚፈውስበት ቀን+ የፀሐይ ብርሃን፣ እንደ ሰባት ቀን ብርሃን ሰባት እጥፍ ይደምቃል።+

27 እነሆ፣ የይሖዋ ስም በቁጣው እየነደደ

ጥቅጥቅ ካለ ደመና ጋር ከሩቅ ይመጣል።

ከንፈሮቹ በቁጣ ተሞልተዋል፤

ምላሱም እንደሚባላ እሳት ነው።+

28 መንፈሱ* እስከ አንገት ድረስ እንደሚደርስ የሚያጥለቀልቅ ወንዝ ነው፤

ብሔራትን በጥፋት ወንፊት* ይነፋቸዋል፤

በሕዝቦች መንጋጋም መንገድ እንዲስቱ የሚያደርግ ልጓም ይገባል።+

29 እናንተ ግን፣ ለበዓል በምትዘጋጁበት* ጊዜ+

በሌሊት እንደሚዘመረው ያለ መዝሙር ትዘምራላችሁ፤

ደግሞም ወደ እስራኤል ዓለት፣+ ወደ ይሖዋ ተራራ ሲጓዝ

ዋሽንት ይዞ* እንደሚሄድ ሰው

ልባችሁ ሐሴት ያደርጋል።

30 ይሖዋ ግርማ የተላበሰ ድምፁ+ እንዲሰማ ያደርጋል፤

የክንዱንም ብርታት ይገልጣል፤+

ይህን የሚያደርገው በሚነድ ቁጣ፣+ በሚባላ የእሳት ነበልባል፣+

ሳይታሰብ በሚወርድ ዶፍ፣+ ነጎድጓድ በቀላቀለ ውሽንፍርና በበረዶ ድንጋይ+ ታጅቦ ክንዱ ጥቃት ለመሰንዘር ወደ ታች በሚወርድበት ጊዜ ነው።

31 ከይሖዋ ድምፅ የተነሳ አሦር በሽብር ይናጣልና፤+

በበትርም ይመታዋል።+

32 ይሖዋ በጦርነት ክንዱን በእነሱ ላይ በሚያነሳበት ጊዜ+

በአሦር ላይ የሚያወርደው

የቅጣት በትር ሁሉ

በአታሞና በበገና የታጀበ ይሆናል።+

33 ቶፌቱ*+ ከወዲሁ ተዘጋጅቷልና፤

ለንጉሡም ተዘጋጅቶለታል።+

የእንጨት ክምሩ ጥልቀትና ስፋት ያለው እንዲሆን አድርጓል፤

ብዙ እሳትና እንጨትም አለ።

የይሖዋ እስትንፋስ ልክ እንደ ድኝ ጅረት

በእሳት ያያይዘዋል።

31 እርዳታ ለማግኘት ወደ ግብፅ ለሚወርዱ፣+

በፈረሶች ለሚመኩ፣+

ብዛት ባላቸው የጦር ሠረገሎችና

ብርቱ በሆኑ የጦር ፈረሶች* ለሚታመኑ ወዮላቸው!

ነገር ግን በእስራኤል ቅዱስ ተስፋ አያደርጉም፤

ይሖዋንም አይሹም።

 2 ይሁንና እሱም ጥበበኛ ነው፤ ጥፋትም ያመጣል፤

ቃሉንም አያጥፍም።

በክፉ አድራጊዎች ቤት ላይ፣

እንዲሁም መጥፎ ነገር የሚሠሩ ሰዎችን በሚረዱ ላይ ይነሳል።+

 3 ግብፃውያን ግን ተራ ሰዎች እንጂ አምላክ አይደሉም፤

ፈረሶቻቸው ሥጋ እንጂ መንፈስ አይደሉም።+

ይሖዋ እጁን ሲዘረጋ፣

እርዳታ የሚሰጥ ሁሉ ይሰናከላል፤

እርዳታ ተቀባዩም ሁሉ ይወድቃል፤

ሁሉም አንድ ላይ ይጠፋሉ።

 4 ይሖዋ እንዲህ ብሎኛልና፦

“አንበሳ ይኸውም ደቦል አንበሳ ባደነው እንስሳ ላይ ቆሞ እንደሚያገሳ፣

ብዙ እረኞች ተጠራርተው ሲመጡበትም

ጩኸታቸው እንደማያሸብረው፣

የሚያሰሙትም ሁካታ እንደማያስፈራው ሁሉ

የሠራዊት ጌታ ይሖዋም ለጽዮን ተራራና ለኮረብታዋ ሲል

ለመዋጋት ይወርዳል።

 5 ተወርውረው እንደሚወርዱ ወፎች፣ የሠራዊት ጌታ ይሖዋም እንዲሁ ኢየሩሳሌምን ይከልላታል።+

ይከልላታል፤ ደግሞም ያድናታል።

ከአደጋ ያስጥላታል፤ እንዲሁም ይታደጋታል።”

6 “የእስራኤል ሕዝብ ሆይ፣ እጅግ ወዳመፃችሁበት አምላክ ተመለሱ።+ 7 በዚያ ቀን እያንዳንዱ ሰው በገዛ እጆቻችሁ በኃጢአት የሠራችኋቸውን የማይረቡ የብር አማልክቱንና ከንቱ የሆኑ የወርቅ አማልክቱን ያስወግዳልና።

 8 አሦራዊውም የሰው ባልሆነ ሰይፍ ይወድቃል፤

የሰው ያልሆነም ሰይፍ ይበላዋል።+

እሱም ሰይፉን ፈርቶ ይሸሻል፤

ወጣቶቹም የግዳጅ ሥራ ይሠራሉ።

 9 ቋጥኙ እጅግ ከመፍራቱ የተነሳ ደብዛው ይጠፋል፤

መኳንንቱም ምልክት ሆኖ የሚያገለግለውን ምሰሶ ሲያዩ ይሸበራሉ” ይላል

ብርሃኑ* በጽዮን፣ እቶኑም በኢየሩሳሌም የሆነው ይሖዋ።

32 እነሆ፣ ንጉሥ+ ለጽድቅ ይነግሣል፤+

መኳንንትም ፍትሕ ለማስፈን ይገዛሉ።

 2 እያንዳንዱም ከነፋስ እንደ መከለያ፣*

ከውሽንፍር እንደ መሸሸጊያ፣*

ውኃ በሌለበት ምድር እንደ ጅረት፣+

በደረቅ ምድርም እንደ ትልቅ ቋጥኝ ጥላ ይሆናል።

 3 በዚያ ጊዜ፣ የሚያዩ ሰዎች ዓይኖች አይጨፈኑም፤

የሚሰሙ ሰዎችም ጆሮዎች በትኩረት ያዳምጣሉ።

 4 የችኩሎች ልብ እውቀትን ያሰላስላል፤

የሚንተባተብ ምላስም አቀላጥፎና አጥርቶ ይናገራል።+

 5 የማመዛዘን ችሎታ የጎደለው ሰው ከእንግዲህ ለጋስ አይባልም፤

ሥርዓት የሌለው ሰውም ትልቅ ሰው አይባልም፤

 6 የማመዛዘን ችሎታ የጎደለው ሰው የማይረባ ነገር ይናገራልና፤

ደግሞም በይሖዋ ላይ ክህደት ለመፈጸምና* የውሸት ቃል ለመናገር፣

እንዲሁም የተራበ ሰው የሚበላ ነገር እንዳያገኝና*

የተጠማ ሰው የሚጠጣ ነገር እንዳያገኝ ለማድረግ

ልቡ ክፋትን ያውጠነጥናል።+

 7 ሥርዓት የሌለው ሰው የሚጠቀምባቸው ዘዴዎች መጥፎ ናቸው፤+

ድሃው ትክክል የሆነውን ነገር በሚናገርበት ጊዜም እንኳ

የተጎሳቆለውን ሰው በውሸት ቃል ለማጥፋት

አሳፋሪ ለሆነ ምግባር ድጋፍ ይሰጣል።+

 8 ለጋስ ሰው ግን ስለ ልግስና ያስባል፤

ዘወትር የልግስና* ተግባር ለመፈጸም ይተጋል።

 9 “እናንተ ደንታ ቢስ ሴቶች፣ ተነሱ፤ ድምፄንም ስሙ!

እናንተ ግድየለሽ ሴቶች ልጆች፣+ የምናገረውን ነገር በትኩረት አዳምጡ!

10 እናንተ ግድየለሾች፣ ከአንድ ዓመት ብዙም ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ትሸበራላችሁ፤

ምክንያቱም የወይን ፍሬ የምትለቅሙበት ጊዜ ሲያልፍ የተሰበሰበ ፍሬ አይኖርም።+

11 እናንተ ደንታ ቢስ ሴቶች፣ ተንቀጥቀጡ!

እናንተ ግድየለሾች፣ ተሸበሩ!

ልብሳችሁን በሙሉ አውልቁ፤

በወገባችሁም ላይ ማቅ ታጠቁ።+

12 ስለ መልካሙ እርሻና ፍሬያማ ስለሆነው ወይን

በሐዘን ደረታችሁን ምቱ።

13 የሕዝቤን ምድር እሾህና አሜኬላ ይወርሱታልና፤

በደስታ ተሞልተው የነበሩትን ቤቶች ሁሉ፣

አዎ፣ በሐሴት ተሞልታ የነበረችውን ከተማ ይሸፍናሉ።+

14 የማይደፈረው ማማ ባዶ ሆኗልና፤

ሁካታ የነበረበት ከተማ ወና ቀርቷል።+

ኦፌልና+ መጠበቂያ ግንቡ ለዘለቄታው ጠፍ ሆነዋል፤

የዱር አህዮች መፈንጫና

የመንጎች መሰማሪያ ሆነዋል፤+

15 ይህም የሚሆነው መንፈስ ከላይ እስኪፈስብን፣+

ምድረ በዳውም የፍራፍሬ እርሻ እስከሚሆን፣

የፍራፍሬ እርሻውም እንደ ጫካ እስከሚቆጠር ድረስ ነው።+

16 ከዚያም በምድረ በዳ ፍትሕ ይሰፍናል፤

በፍራፍሬ እርሻም ጽድቅ ይኖራል።+

17 የእውነተኛ ጽድቅ ውጤት ሰላም፣+

የእውነተኛ ጽድቅ ፍሬም ዘላቂ ጸጥታና ደህንነት ይሆናል።+

18 ሕዝቤ ሰላማዊ በሆነ የመኖሪያ ስፍራ፣

አስተማማኝ በሆነ መኖሪያና ጸጥታ በሰፈነበት የማረፊያ ቦታ ይኖራል።+

19 ሆኖም በረዶው ጫካውን ያወድማል፤

ከተማዋም ሙሉ በሙሉ ትፈራርሳለች።

20 እናንተ በውኃዎች ሁሉ ዳር ዘር የምትዘሩ፣

በሬውንና አህያውንም የምትለቁ* ደስተኞች ናችሁ።”+

33 አንተ ሳትጠፋ የምታጠፋ፣+

ክህደት ሳይፈጸምብህ ክህደት የምትፈጽም ወዮልህ!

ማጥፋትህን እንዳጠናቀክ አንተም ትጠፋለህ።+

ክህደት መፈጸምህን እንዳበቃህ ትካዳለህ።

 2 ይሖዋ ሆይ፣ ሞገስ አሳየን።+

በአንተ ተስፋ አድርገናል።

በየማለዳው በክንድህ ደግፈን፤*+

አዎ፣ በጭንቅ ጊዜ አዳኛችን ሁን።+

 3 የድምፅህን ነጎድጓድ ሲሰሙ ሕዝቦች ይሸሻሉ።

በምትነሳበት ጊዜ ብሔራት ይበታተናሉ።+

 4 የማይጠግቡ አንበጦች በሚሰበሰቡበት ጊዜ እንደሚሆነው ከእናንተም የሚወሰደው ምርኮ እንዲሁ ይሰበሰባል፤

ሰዎች እንደ አንበጣ መንጋ ምርኮውን ይቀራመቱታል።

 5 ይሖዋ ከፍ ከፍ ይላል፤

በከፍታ ቦታ ይኖራልና።

ጽዮንን በፍትሕና በጽድቅ ይሞላል።

 6 እሱ የዘመንህ መተማመኛ ነው፤

የመዳን፣+ የጥበብና የእውቀት ብዛት እንዲሁም ይሖዋን መፍራት፣+

ይህ የእሱ ውድ ሀብት ነው።

 7 እነሆ፣ ጀግኖቻቸው በጎዳና ላይ ይጮኻሉ፤

የሰላም መልእክተኞቹም አምርረው ያለቅሳሉ።

 8 አውራ ጎዳናዎቹ ጭር ብለዋል፤

በመንገድ ላይ የሚጓዝ ሰው የለም።

እሱ* ቃል ኪዳኑን አፍርሷል፤

ከተሞቹን ንቋል፤

ሟች ለሆነው ሰው ደንታ የለውም።+

 9 ምድሪቱ አዘነች፤* ጠወለገችም።

ሊባኖስ ተዋረደ፤+ እንዲሁም በሰበሰ።

ሳሮን እንደ በረሃ ሆነች፤

ባሳንና ቀርሜሎስም ቅጠላቸውን አረገፉ።+

10 “አሁን እነሳለሁ” ይላል ይሖዋ፤

“አሁን ራሴን ከፍ ከፍ አደርጋለሁ፤+

አሁን ራሴን አከብራለሁ።

11 ደረቅ ሣር ትፀንሳላችሁ፤ ገለባንም ትወልዳላችሁ።

የገዛ መንፈሳችሁም እንደ እሳት ይበላችኋል።+

12 ሕዝቦችም እንደተቃጠለ ኖራ ይሆናሉ።

እንደተቆረጠ እሾህ በእሳት ይጋያሉ።+

13 እናንተ በሩቅ ያላችሁ፣ የማደርገውን ስሙ!

እናንተም በቅርብ ያላችሁ፣ ለኃይሌ እውቅና ስጡ!

14 በጽዮን ያሉ ኃጢአተኞች እጅግ ፈሩ፤+

ከሃዲዎቹም ብርክ ያዛቸው፦

‘ከእኛ መካከል የሚባላ እሳት ባለበት ቦታ መኖር የሚችል ማን ነው?+

ከእኛስ መካከል ከማይጠፋ የእሳት ነበልባል ጋር መኖር የሚችል ማን ነው?’

15 ዘወትር በጽድቅ የሚመላለስ፣+

ቅን+ የሆነውን ነገር የሚናገር፣

በማታለልና በማጭበርበር የሚገኝን ጥቅም የሚጠላ፣

ጉቦ ከመቀበል እጁን የሚሰበስብ፣+

ደም ለማፍሰስ የሚጠነሰስን ሴራ ላለመስማት ጆሮውን የሚደፍን

እንዲሁም ክፉ የሆነውን ላለማየት ዓይኑን የሚጨፍን ሰው፣

16 በከፍታ ቦታዎች ይኖራል፤

ዓለታማ ምሽጎች አስተማማኝ መጠጊያው ይሆናሉ፤

ምግቡም ይቀርብለታል፤

የውኃ አቅርቦትም ፈጽሞ አይቋረጥበትም።”+

17 ዓይኖችህ ንጉሡን ግርማ ተላብሶ ያዩታል፤

በሩቅ ያለችውን ምድር ያያሉ።

18 ሽብር የነበረበትን ወቅት በልብህ ታስታውሳለህ፦*

“ጸሐፊው የት አለ?

ግብር የመዘነው የት አለ?+

ማማዎቹንስ የቆጠረው የት አለ?”

19 የማይገባ ቋንቋ የሚናገረውንና*

ለመረዳት የሚያስቸግር ተብታባ አንደበት ያለውን+

ጋጠወጥ ሕዝብ ከእንግዲህ አታይም።

20 በዓሎቻችንን+ የምናከብርባትን ከተማ ጽዮንን ተመልከት!

ጸጥታ የሰፈነባት መኖሪያ፣

የማትነቃነቅ ድንኳን+ የሆነችውን ኢየሩሳሌምን ዓይኖችህ ያያሉ።

የድንኳን ካስማዎቿ ፈጽሞ አይነቀሉም፤

ከገመዶቿም አንዱ እንኳ አይበጠስም።

21 ይልቁንም ግርማ ሞገስ የተላበሰው ይሖዋ

በዚያ ስፍራ እንደ ወንዞችና እንደ ሰፋፊ ቦዮች ሆኖ ይጠብቀናል፤

በእነሱም ላይ ጠላት የሚያሰልፋቸው ባለ መቅዘፊያ ጀልባዎችም ሆኑ

ትላልቅ መርከቦች አያልፉም።

22 ይሖዋ ዳኛችን ነው፤+

ይሖዋ ሕግ ሰጪያችን ነው፤+

ይሖዋ ንጉሣችን ነው፤+

የሚያድነን እሱ ነው።+

23 ገመዶችህ ይላላሉ፤

የመርከቡን ምሰሶ አጽንተው ማቆምም ሆነ ሸራውን ወጥረው መያዝ አይችሉም።

በዚያን ጊዜ ብዛት ያለው ምርኮ ይከፋፈላል፤

አንካሶችም እንኳ ብዙ የሚበዘበዝ ነገር ያገኛሉ።+

24 በዚያም የሚቀመጥ* ማንኛውም ሰው “ታምሜአለሁ” አይልም።+

በምድሪቱ ላይ የሚቀመጡ በደላቸው ይቅር ይባልላቸዋል።+

34 እናንተ ብሔራት፣ ለመስማት ወደዚህ ቅረቡ፤

እናንተ ሕዝቦች፣ በትኩረት አዳምጡ።

ምድርና በውስጧ ያለው ነገር ሁሉ፣

ምድርና ከእሷ የሚገኘው ምርት ሁሉ ይስሙ።

 2 ይሖዋ በሁሉም ብሔራት ላይ ተቆጥቷልና፤+

በሠራዊታቸውም ሁሉ ላይ ተቆጥቷል።+

ፈጽሞ ያጠፋቸዋል፤

ለእርድም አሳልፎ ይሰጣቸዋል።+

 3 የተገደሉባቸው ሰዎች ይጣላሉ፤

የአስከሬኖቻቸውም ግማት ወደ ላይ ይወጣል፤+

ከደማቸውም የተነሳ ተራሮቹ ይሸረሸራሉ።*+

 4 የሰማያት ሠራዊት ሁሉ ይበሰብሳሉ፤

ሰማያትም እንደ መጽሐፍ ጥቅልል ይጠቀለላሉ።

ደርቆ እንደረገፈ የወይን ቅጠልና

ደርቆ እንደወደቀ በለስ

ሠራዊታቸውም ሁሉ ደርቀው ይረግፋሉ።

 5 “ሰይፌ በሰማያት በደም ትርሳለችና።+

በኤዶም ይኸውም እንዲጠፋ

ፍርድ ባስተላለፍኩበት ሕዝብ ላይ ትወርዳለች።+

 6 ይሖዋ ሰይፍ አለው፤ ሰይፉም በደም ትሸፈናለች።

በስብ፣+ በበግ ጠቦቶችና በፍየሎች ደም

እንዲሁም በአውራ በጎች ኩላሊት ስብ ትለወሳለች።

ይሖዋ በቦስራ መሥዋዕት፣

በኤዶምም ምድር

ታላቅ እርድ ያዘጋጃልና።+

 7 የዱር በሬዎች ከእነሱ ጋር ይወድቃሉ፤

ወይፈኖችም ከብርቱ ኮርማዎች ጋር ይወድቃሉ።

ምድራቸውም በደም ይሸፈናል፤

አፈራቸውም በስብ ይርሳል።”

 8 ይሖዋ የሚበቀልበት ቀን፣+

በጽዮን ላይ ለተፈጸመው በደል ቅጣት የሚያስፈጽምበት ዓመት አለውና።+

 9 በእሷ* የሚገኙት ጅረቶች ወደ ዝፍት ይለወጣሉ፤

አፈሯም ወደ ድኝ ይቀየራል፤

ምድሪቱም እንደሚቃጠል ዝፍት ትሆናለች።

10 እሳቱ በሌሊትም ሆነ በቀን አይጠፋም፤

ጭሷም ለዘላለም ይወጣል።

ከትውልድ እስከ ትውልድም እንደወደመች ትቀራለች፤

ለዘላለም ማንም በእሷ አያልፍም።+

11 ሻላና* ጃርት ይወርሷታል፤

ባለ ረጅም ጆሮ ጉጉቶችና ቁራዎችም በእሷ ውስጥ ይኖራሉ።

አምላክ፣ ምድሪቱ ባዶ እንደምትሆንና እንደምትጠፋ ለማሳየት

በመለኪያ ገመድና በቱንቢ* ይለካታል።

12 ከታላላቅ ሰዎቿ መካከል ለንግሥና የሚበቃ አንድም ሰው አይኖርም፤

መኳንንቷም ሁሉ ይጠፋሉ።

13 በማይደፈሩ ማማዎቿ ላይ እሾህ፣

በምሽጎቿም ላይ ሳማና ኩርንችት ይበቅላል።

የቀበሮዎች ማደሪያ፣+

የሰጎኖችም መኖሪያ ትሆናለች።

14 የበረሃ ፍጥረታት ከሚያላዝኑ እንስሶች ጋር ይገናኛሉ፤

የዱር ፍየልም* ባልንጀራውን ይጠራል።

የሌሊት ወፍ በዚያ ታርፋለች፤ ማረፊያ ስፍራም ታገኛለች።

15 ተወንጫፊ እባብ በዚያ ጎጆዋን ትሠራለች፤ እንቁላልም ትጥላለች፤

ከዚያም ትቀፈቅፋለች፤ በጥላዋም ሥር ትሰበስባቸዋለች።

ጭላቶችም ጥንድ ጥንድ ሆነው በዚያ ይሰበሰባሉ።

16 በይሖዋ መጽሐፍ ውስጥ ፈልጉ፤ ድምፃችሁንም ከፍ አድርጋችሁ አንብቡ፤

ከእነሱ መካከል አንዳቸውም አይጎድሉም፤

ሁሉም ተጓዳኝ አያጡም፤

ይህ ትእዛዝ የወጣው ከይሖዋ አፍ ነውና፤

አንድ ላይ የሰበሰባቸውም የእሱ መንፈስ ነው።

17 ዕጣ የጣለላቸው እሱ ነው፤

የተመደበላቸውን ቦታ የለካው የገዛ እጁ ነው።*

እነሱም ለዘለቄታው ይወርሱታል፤

ከትውልድ እስከ ትውልድም በዚያ ይኖራሉ።

35 ምድረ በዳውና ደረቁ ምድር ሐሴት ያደርጋል፤+

በረሃማው ቦታም ደስ ይለዋል፤ እንደ ሳሮን አበባም * ያብባል።+

 2 በእርግጥ ያብባል፤+

ሐሴት ያደርጋል፤ በደስታም እልል ይላል።

የሊባኖስ ክብር ይሰጠዋል፤+

የቀርሜሎስንና+ የሳሮንን+ ግርማ ይለብሳል።

የይሖዋን ክብር፣ የአምላካችንንም ግርማ ያያሉ።

 3 የደከሙትን እጆች አበርቱ፤

የሚብረከረኩትንም ጉልበቶች አጽኑ።+

 4 በጭንቀት የተዋጠ ልብ ላላቸው እንዲህ በሏቸው፦

“በርቱ፤ አትፍሩ።

እነሆ፣ አምላካችሁ ሊበቀል ይመጣል፤

አምላክ ብድራት ሊከፍል ይመጣል።+

እሱ መጥቶ ያድናችኋል።”+

 5 በዚያን ጊዜ የዓይነ ስውራን ዓይን ይገለጣል፤+

መስማት የተሳናቸው ሰዎች ጆሮም ይከፈታል።+

 6 በዚያን ጊዜ አንካሳ እንደ ሚዳቋ ይዘላል፤+

የዱዳም ምላስ በደስታ እልል ይላል።+

በምድረ በዳ ውኃ ይፈልቃልና፤

በበረሃማ ሜዳም ጅረት ይፈስሳል።

 7 በሐሩር የተቃጠለው ምድር ቄጠማ የሞላበት ኩሬ፣

የተጠማውም ምድር የውኃ ምንጭ ይሆናል።+

ቀበሮዎች ይኖሩበት የነበረው ጎሬ+

ለምለም ሣር፣ ሸምበቆና ደንገል ይበቅልበታል።

 8 በዚያም አውራ ጎዳና ይኖራል፤+

ደግሞም “የቅድስና ጎዳና” ተብሎ ይጠራል።

ንጹሕ ያልሆነ ሰው አይጓዝበትም።+

ጎዳናው፣ በመንገዱ ላይ ለሚሄዱት ብቻ ይሆናል፤

ሞኞችም አይሄዱበትም።

 9 በዚያ አንበሳ አይኖርም፤

አዳኝ አራዊትም ወደዚያ አይወጡም።

አንዳቸውም በዚያ አይገኙም፤+

የተቤዡት ብቻ በዚያ ይሄዳሉ።+

10 ይሖዋ የዋጃቸው ይመለሳሉ፤+ ወደ ጽዮንም በእልልታ ይመጣሉ።+

ፍጻሜ የሌለው ደስታን እንደ አክሊል ይጎናጸፋሉ።+

ደስታንና ሐሴትን ያገኛሉ፤

ሐዘንና ሲቃም ከዚያ ይርቃሉ።+

36 ንጉሥ ሕዝቅያስ በነገሠ በ14ኛው ዓመት የአሦር ንጉሥ+ ሰናክሬም በተመሸጉት የይሁዳ ከተሞች ሁሉ ላይ ዘምቶ ያዛቸው።+ 2 ከዚያም የአሦር ንጉሥ፣ ራብሻቁን*+ ከብዙ ሠራዊት ጋር ከለኪሶ፣+ በኢየሩሳሌም ወደሚገኘው ወደ ንጉሥ ሕዝቅያስ ላከው። እነሱም ወደ ልብስ አጣቢው እርሻ+ በሚወስደው አውራ ጎዳና ላይ በሚገኘው በላይኛው ኩሬ የውኃ መውረጃ ቦይ አጠገብ ቆሙ።+ 3 ከዚያም የቤቱ* ኃላፊ የሆነው የኬልቅያስ ልጅ ኤልያቄም፣+ ጸሐፊው ሸብና+ እንዲሁም ታሪክ ጸሐፊው የአሳፍ ልጅ ዮአህ ወደ እሱ መጡ።

4 ራብሻቁም እንዲህ አላቸው፦ “እስቲ ሕዝቅያስን እንዲህ በሉት፦ ‘ታላቁ ንጉሥ፣ የአሦር ንጉሥ እንዲህ ይላል፦ “ለመሆኑ እንዲህ እንድትተማመን ያደረገህ ምንድን ነው?+ 5 ‘የጦር ስልትና ለመዋጋት የሚያስችል ኃይል አለኝ’ ትላለህ፤ ይሁንና ይህ ከንቱ ወሬ ነው። ለመሆኑ በእኔ ላይ ለማመፅ የደፈርከው በማን ተማምነህ ነው?+ 6 እነሆ፣ ሰው ቢመረኮዘው እጁ ላይ ሊሰነቀርና ሊወጋው ከሚችለው ከዚህ ከተቀጠቀጠ ሸምበቆ፣ ከግብፅ ድጋፍ አገኛለሁ ብለህ ተማምነሃል። የግብፅ ንጉሥ ፈርዖን ለሚታመኑበት ሁሉ እንዲሁ ነው።+ 7 ‘እኛ የምንታመነው በአምላካችን በይሖዋ ነው’ የምትለኝ ከሆነ ደግሞ፣ ሕዝቅያስ ይሁዳንና ኢየሩሳሌምን ‘መስገድ ያለባችሁ በዚህ መሠዊያ ፊት ነው’+ ብሎ የእሱን ከፍ ያሉ የማምለኪያ ቦታዎችና መሠዊያዎች አስወግዶ የለም?”’+ 8 በል እስቲ፣ አሁን ከጌታዬ ከአሦር ንጉሥ+ ጋር ተወራረድ፦ ጋላቢዎች ማግኘት የምትችል ከሆነ 2,000 ፈረሶች እሰጥሃለሁ። 9 አንተ የምትታመነው በግብፅ ሠረገሎችና ፈረሰኞች ነው፤ ታዲያ ከጌታዬ አገልጋዮች መካከል ዝቅተኛ ደረጃ ያለውን አንዱን አለቃ እንኳ እንዴት መመከት ትችላለህ? 10 ለመሆኑ ይህን ምድር ለማጥፋት የመጣሁት ይሖዋ ሳይፈቅድልኝ ይመስልሃል? ይሖዋ ራሱ ‘በዚህ ምድር ላይ ዘምተህ አጥፋው’ ብሎኛል።”

11 በዚህ ጊዜ ኤልያቄም፣ ሸብና+ እና ዮአህ ራብሻቁን+ እንዲህ አሉት፦ “እባክህ፣ እኛ አገልጋዮችህ ቋንቋውን ስለምናውቅ በአረማይክ* ቋንቋ+ አናግረን፤ በቅጥሩ ላይ ያለው ሕዝብ በሚሰማው በአይሁዳውያን ቋንቋ አታነጋግረን።”+ 12 ራብሻቁ ግን እንዲህ አለ፦ “ጌታዬ ይህን ቃል እንድናገር የላከኝ ለጌታህና ለአንተ ብቻ ነው? ከእናንተ ጋር የገዛ ራሳቸውን እዳሪ ለሚበሉትና የገዛ ራሳቸውን ሽንት ለሚጠጡት በቅጥሩ ላይ ለተቀመጡት ሰዎች ጭምር አይደለም?”

13 ከዚያም ራብሻቁ ቆሞ ከፍ ባለ ድምፅ በአይሁዳውያን ቋንቋ+ እንዲህ አለ፦ “የታላቁን ንጉሥ፣ የአሦርን ንጉሥ ቃል ስሙ።+ 14 ንጉሡ እንዲህ ይላል፦ ‘ሕዝቅያስ አያታላችሁ፤ እሱ ሊታደጋችሁ አይችልምና።+ 15 ደግሞም ሕዝቅያስ “ይሖዋ በእርግጥ ይታደገናል፤ ይህችም ከተማ በአሦር ንጉሥ እጅ አትወድቅም” እያለ በይሖዋ እንድትታመኑ አያድርጋችሁ።+ 16 ሕዝቅያስን አትስሙት፤ የአሦር ንጉሥ እንዲህ ይላልና፦ “ከእኔ ጋር ሰላም ፍጠሩ፤ እጃችሁንም ስጡ፤* እያንዳንዳችሁም ከራሳችሁ ወይንና ከራሳችሁ በለስ ትበላላችሁ፤ ከራሳችሁም የውኃ ጉድጓድ ትጠጣላችሁ፤ 17 ይህም የሚሆነው መጥቼ የእናንተን ምድር ወደምትመስለው፣ እህልና አዲስ የወይን ጠጅ፣ ዳቦና የወይን እርሻ ወደሚገኝባት ምድር እስክወስዳችሁ ድረስ ነው።+ 18 ሕዝቅያስ ‘ይሖዋ ይታደገናል’ በማለት አያታላችሁ። ከብሔራት አማልክት መካከል ምድሩን ከአሦር ንጉሥ እጅ ያስጣለ አለ?+ 19 የሃማትና የአርጳድ+ አማልክት የት አሉ? የሰፋርዊም+ አማልክትስ የት አሉ? ሰማርያን ከእጄ ማስጣል ችለዋል?+ 20 ከእነዚህ አገሮች አማልክት ሁሉ ምድሩን ከእጄ ማስጣል የቻለ የትኛው ነው? ታዲያ ይሖዋ ኢየሩሳሌምን ከእጄ ሊያስጥላት ይችላል?”’”+

21 እነሱ ግን ንጉሡ “ምንም መልስ አትስጡት” ብሎ አዝዞ ስለነበር ዝም አሉ፤ አንድም ቃል አልመለሱለትም።+ 22 ይሁንና የቤቱ* አስተዳዳሪ የሆነው የኬልቅያስ ልጅ ኤልያቄም፣ ጸሐፊው ሸብና+ እንዲሁም ታሪክ ጸሐፊው የአሳፍ ልጅ ዮአህ ልብሳቸውን ቀደው ወደ ሕዝቅያስ መጡ፤ ራብሻቁ ያለውንም ነገሩት።

37 ንጉሥ ሕዝቅያስ ይህን እንደሰማ ልብሱን ቀደደ፤ ማቅ ለብሶም ወደ ይሖዋ ቤት ገባ።+ 2 ከዚያም የቤቱ* አስተዳዳሪ የሆነውን ኤልያቄምን፣ ጸሐፊውን ሸብናን እንዲሁም የካህናቱን ሽማግሌዎች ማቅ ለብሰው ወደ አሞጽ ልጅ ወደ ነቢዩ ኢሳይያስ+ እንዲሄዱ ላካቸው። 3 እነሱም እንዲህ አሉት፦ “ሕዝቅያስ እንዲህ ይላል፦ ‘ይህ ቀን የጭንቀት፣ የዘለፋና* የውርደት ቀን ነው፤ መውለጃዋ ደርሶ* ለማማጥ የሚያስችል አቅም እንዳጣች ሴት ሆነናል።+ 4 ምናልባት አምላክህ ይሖዋ፣ ሕያው የሆነውን አምላክ እንዲያቃልል+ ጌታው የአሦር ንጉሥ የላከውን የራብሻቁን ቃል ይሰማ ይሆናል፤ ደግሞም አምላክህ ይሖዋ፣ የተናገረውን ቃል ሰምቶ ተጠያቂ ያደርገው ይሆናል። ስለዚህ በሕይወት ለተረፉት ቀሪዎች+ ጸልይ።’”+

5 በመሆኑም የንጉሥ ሕዝቅያስ አገልጋዮች ወደ ኢሳይያስ ሄዱ፤+ 6 ኢሳይያስም እንዲህ አላቸው፦ “ጌታችሁን እንዲህ በሉት፦ ‘ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “የአሦር ንጉሥ አገልጋዮች+ እኔን በመሳደብ የተናገሩትን ቃል በመስማትህ አትፍራ።+ 7 እነሆ፣ በአእምሮው አንድ ሐሳብ አስገባለሁ፤* እሱም ወሬ ሰምቶ ወደ አገሩ ይመለሳል፤+ በገዛ አገሩም በሰይፍ እንዲወድቅ አደርጋለሁ።”’”+

8 ራብሻቁም የአሦር ንጉሥ ለኪሶን ለቆ እንደሄደ ሲሰማ ወደ ንጉሡ ተመለሰ፤ ከሊብናም ጋር ሲዋጋ አገኘው።+ 9 በዚህ ጊዜ ንጉሡ የኢትዮጵያው ንጉሥ ቲርሃቅ “ከአንተ ጋር ሊዋጋ ወጥቷል” የሚል ወሬ ሰምቶ ነበር። እሱም ይህን በሰማ ጊዜ ለሕዝቅያስ እንዲህ ብለው እንዲነግሩት በድጋሚ መልእክተኞች ላከ፦+ 10 “የይሁዳን ንጉሥ ሕዝቅያስን እንዲህ በሉት፦ ‘የምትታመንበት አምላክህ “ኢየሩሳሌም በአሦር ንጉሥ እጅ አትወድቅም” ብሎ አያታልህ።+ 11 እነሆ፣ የአሦር ነገሥታት ሌሎቹን አገሮች ሁሉ ፈጽመው በማጥፋት ያደረጉትን ነገር ሰምተሃል።+ ታዲያ አንተ ብቻ ከዚህ የምታመልጥ ይመስልሃል? 12 አባቶቼ ያጠፏቸውን ብሔራት አማልክታቸው ታድገዋቸዋል?+ ጎዛን፣ ካራን፣+ ረጼፍና በቴልአሳር የነበሩት የኤደን ሕዝቦች የት አሉ? 13 የሃማት ንጉሥ፣ የአርጳድ ንጉሥ፣ የሰፋርዊም+ ከተሞች ንጉሥ እንዲሁም የሄና እና የኢዋ ነገሥታት የት አሉ?’”

14 ሕዝቅያስ ደብዳቤዎቹን ከመልእክተኞቹ እጅ ተቀብሎ አነበበ። ከዚያም ወደ ይሖዋ ቤት ወጥቶ ደብዳቤዎቹን* በይሖዋ ፊት ዘረጋ።+ 15 ሕዝቅያስም ወደ ይሖዋ እንዲህ ሲል ጸለየ፦+ 16 “ከኪሩቤል በላይ* የምትቀመጥ፣ የእስራኤል አምላክ፣ የሠራዊት ጌታ ይሖዋ ሆይ፣+ የምድር መንግሥታት ሁሉ እውነተኛ አምላክ አንተ ብቻ ነህ። ሰማያትንና ምድርን ሠርተሃል። 17 ይሖዋ ሆይ፣ ጆሮህን አዘንብለህ ስማ!+ ይሖዋ ሆይ፣ ዓይንህን ገልጠህ እይ!+ ሰናክሬም ሕያው የሆነውን አምላክ ለማቃለል የላከውን ቃል ሁሉ ስማ።+ 18 ይሖዋ ሆይ፣ የአሦር ነገሥታት ሌሎቹን አገሮች ሁሉና የገዛ ራሳቸውን ምድር እንዳጠፉ አይካድም።+ 19 አማልክታቸውንም እሳት ውስጥ ጨምረዋል፤+ ምክንያቱም የሰው እጅ ሥራ፣ እንጨትና ድንጋይ እንጂ አማልክት አይደሉም።+ ሊያጠፏቸው የቻሉት በዚህ ምክንያት ነው። 20 አሁን ግን አምላካችን ይሖዋ ሆይ፣ የምድር መንግሥታት ሁሉ፣ አንተ ብቻ እውነተኛ አምላክ እንደሆንክ ያውቁ ዘንድ ይሖዋ ሆይ፣ ከእጁ አድነን።”+

21 ከዚያም የአሞጽ ልጅ ኢሳይያስ እንዲህ የሚል መልእክት ወደ ሕዝቅያስ ላከ፦ “የእስራኤል አምላክ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘የአሦርን ንጉሥ ሰናክሬምን በተመለከተ ወደ እኔ ስለጸለይክ፣+ 22 ይሖዋ በእሱ ላይ የተናገረው ቃል ይህ ነው፦

“ድንግሊቱ የጽዮን ልጅ ትንቅሃለች፤ ደግሞም ታፌዝብሃለች።

የኢየሩሳሌም ሴት ልጅ ራሷን ትነቀንቅብሃለች።

23 ያቃለልከውና+ የሰደብከው ማንን ነው?

ድምፅህን ከፍ ያደረግከው፣+

እብሪተኛ ዓይንህንም ያነሳኸው በማን ላይ ነው?

በእስራኤል ቅዱስ ላይ እኮ ነው!+

24 በአገልጋዮችህ በኩል ይሖዋን አቃለሃል፤+ እንዲህም ብለሃል፦

‘ብዛት ባላቸው የጦር ሠረገሎቼ፣

ወደ ተራሮች ከፍታ፣

ርቀው ወደሚገኙትም የሊባኖስ ስፍራዎች እወጣለሁ።+

ረጃጅሞቹን አርዘ ሊባኖሶች፣ ምርጥ የሆኑትንም የጥድ ዛፎች እቆርጣለሁ።

እጅግ ከፍ ወዳለው ማረፊያ ቦታ፣ በጣም ጥቅጥቅ ወዳለው ጫካ እገባለሁ።

25 ጉድጓድ ቆፍሬ ውኃ እጠጣለሁ፤

የግብፅን ጅረቶች* በእግሬ ረግጬ አደርቃለሁ።’

26 አልሰማህም? ይህ ከጥንት ዘመን ጀምሮ የተወሰነ* ነው።

ከድሮ ጀምሮ ይህን አስቤአለሁ።*+

አሁን እንዲፈጸም አደርጋለሁ።+

አንተም የተመሸጉትን ከተሞች የፍርስራሽ ክምር ታደርጋለህ።+

27 ነዋሪዎቻቸው አቅመ ቢስ ይሆናሉ፤

ይሸበራሉ፤ ደግሞም ያፍራሉ።

እንደ ሜዳ ተክል፣ እንደ ለምለም ሣር፣

እንዲሁም የምሥራቅ ነፋስ እንዳቃጠለው በጣሪያ ላይ የበቀለ ሣር ይሆናሉ።

28 ይሁንና መቼ እንደምትቀመጥ፣ መቼ እንደምትወጣና መቼ እንደምትገባ፣

እንዲሁም መቼ በእኔ ላይ እንደተቆጣህ በሚገባ አውቃለሁ፤+

29 ምክንያቱም በእኔ ላይ የተቆጣኸው ቁጣና+ ጩኸትህ ወደ ጆሮዬ ደርሷል።+

ስለዚህ ስናጌን በአፍንጫህ፣ ልጓሜንም+ በአፍህ አስገባለሁ፤

በመጣህበትም መንገድ እንድትመለስ አደርግሃለሁ።”

30 “‘ይህም ምልክት ይሆንሃል፦* በዚህ ዓመት የገቦውን እህል* ትበላላችሁ፤ በሁለተኛውም ዓመት ከዚያው ላይ የበቀለውን እህል ትበላላችሁ፤ በሦስተኛው ዓመት ግን ዘር ትዘራላችሁ፤ ታጭዳላችሁም፤ እንዲሁም ወይን ትተክላላችሁ፤ ፍሬውንም ትበላላችሁ።+ 31 ከይሁዳ ቤት ያመለጡትና በሕይወት የቀሩት ሰዎች+ ወደ ታች ሥር ይሰዳሉ፤ ወደ ላይም ያፈራሉ። 32 ከኢየሩሳሌም ቀሪዎች፣ ከጽዮን ተራራም በሕይወት የተረፉ ሰዎች ይወጣሉና።+ የሠራዊት ጌታ የይሖዋ ቅንዓት ይህን ያደርጋል።+

33 “‘ስለዚህ ይሖዋ ስለ አሦር ንጉሥ እንዲህ ይላል፦+

“ወደዚህች ከተማ አይመጣም፤+

ፍላጻም አይወረውርባትም፤

ጋሻም ይዞ አይመጣባትም፤

ከበባ ለማድረግም በዙሪያዋ የአፈር ቁልል አይደለድልም።”’+

34 ‘በመጣበት መንገድ ይመለሳል፤

ወደዚህች ከተማ አይገባም’ ይላል ይሖዋ።

35 ‘ስለ እኔና+ ስለ አገልጋዬ ስለ ዳዊት ስል+

ይህችን ከተማ እጠብቃታለሁ፤+ ደግሞም አድናታለሁ።’”

36 የይሖዋም መልአክ ወጥቶ በአሦራውያን ሰፈር የነበሩትን 185,000 ሰዎች ገደለ። ሰዎችም በማለዳ ሲነሱ ሬሳውን አዩ።+ 37 በመሆኑም የአሦር ንጉሥ ሰናክሬም ከዚያ ተነስቶ ወደ ነነዌ+ ተመለሰ፤ በዚያም ተቀመጠ።+ 38 ሰናክሬም በአምላኩ በኒስሮክ ቤት* እየሰገደ ሳለ አድራሜሌክና ሳሬጸር የተባሉት የገዛ ልጆቹ በሰይፍ መትተው ገደሉት፤+ ከዚያም ወደ አራራት+ ምድር ሸሽተው ሄዱ። ልጁም ኤሳርሃደን+ በእሱ ምትክ ነገሠ።

38 በዚያ ጊዜ ሕዝቅያስ በጠና ታሞ ሞት አፋፍ ደርሶ ነበር።+ የአሞጽ ልጅ ነቢዩ ኢሳይያስ+ መጥቶ እንዲህ አለው፦ “ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘ከሕመምህ አትድንም፤ መሞትህ ስለማይቀር ለቤተሰብህ መመሪያ ስጥ።’”+ 2 በዚህ ጊዜ ሕዝቅያስ ፊቱን ወደ ግድግዳው አዙሮ ወደ ይሖዋ መጸለይ ጀመረ፦ 3 “እባክህ ይሖዋ ሆይ፣ በታማኝነትና በሙሉ ልብ+ በፊትህ እንዴት እንደተመላለስኩ እንዲሁም በዓይኖችህ ፊት መልካም የሆነውን ነገር እንዳደረግኩ እንድታስታውስ አጥብቄ እለምንሃለሁ።”+ ሕዝቅያስም ምርር ብሎ አለቀሰ።

4 ከዚያም የይሖዋ ቃል እንዲህ ሲል ወደ ኢሳይያስ መጣ፦ 5 “ተመልሰህ ሄደህ ሕዝቅያስን እንዲህ በለው፦+ ‘የአባትህ የዳዊት አምላክ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “ጸሎትህን ሰምቻለሁ።+ እንባህንም አይቻለሁ።+ እነሆ በዕድሜህ* ላይ 15 ዓመት እጨምርልሃለሁ፤+ 6 አንተንና ይህችን ከተማ ከአሦር ንጉሥ እጅ እታደጋለሁ፤ ከተማዋንም እጠብቃታለሁ።+ 7 ይሖዋ የተናገረውን ቃል እንደሚፈጽም የሚያሳየው ይሖዋ የሰጠህ ምልክት ይህ ነው፦+ 8 በአካዝ ደረጃ* ላይ ወደ ታች የወረደውን የፀሐይ ጥላ ወደ ኋላ አሥር ደረጃ እንዲመለስ አደርገዋለሁ።”’”+ በመሆኑም ወደ ታች ወርዶ የነበረው የፀሐይ ጥላ አሥር ደረጃ ወደ ኋላ ተመለሰ።

9 የይሁዳ ንጉሥ ሕዝቅያስ ከሕመሙ ከዳነ በኋላ የጻፈው* ጽሑፍ፦

10 እኔ “በዕድሜዬ አጋማሽ ላይ

ወደ መቃብር* በሮች እገባለሁ።

ቀሪውን የሕይወት ዘመኔን እነፈጋለሁ” አልኩ።

11 እንዲህም አልኩ፦ “በሕያዋን ምድር ያህን፣* አዎ ያህን አላይም።

ሁሉም ነገር ከሕልውና ውጭ በሆነበት ስፍራ ከሚኖሩት ጋር በምሆንበት ጊዜ

የሰው ልጆችን አልመለከትም።+

12 መኖሪያዬ ልክ እንደ እረኛ ድንኳን

ተነቅሎ ተወስዶብኛል።+

ሕይወቴን እንደ ሸማኔ ጠቀለልኩ፤

ተሠርቶ ያለቀ ጨርቅ ከሽመና መሣሪያው ላይ እንደሚቆረጥ እኔንም ይቆርጠኛል።

ከማለዳ አንስቶ እስከ ምሽት ድረስ ትጨርሰኛለህ።+

13 እስከ ጠዋት ድረስ ራሴን አረጋጋለሁ።

አጥንቶቼን ሁሉ እንደ አንበሳ ይሰባብራል፤

ከማለዳ አንስቶ እስከ ምሽት ድረስ ትጨርሰኛለህ።+

14 እንደ ወንጭፊት ወይም እንደ ጭሪ* እጮኻለሁ፤+

እንደ ርግብ አልጎመጉማለሁ።+

ወደ ላይ ከመመልከቴ የተነሳ ዓይኖቼ ፈዘዙ፦+

‘ይሖዋ ሆይ፣ እጅግ ተጨንቄአለሁ፤

ድጋፍ ሁነኝ!’*+

15 እንግዲህ ምን ማለት እችላለሁ?

እሱ አናግሮኛል፤ ምላሽም ሰጥቷል።

ከደረሰብኝ አስከፊ ጭንቀት* የተነሳ

በሕይወት ዘመኔ ሁሉ በትሕትና* እመላለሳለሁ።

16 ‘ይሖዋ ሆይ፣ ሁሉም ሰው በእነዚህ ነገሮች* በሕይወት ይኖራል፤

በእነሱም የእኔ መንፈስ በሕይወት ይኖራል።

አንተ ጤናዬን ትመልስልኛለህ፤ በሕይወትም ታኖረኛለህ።+

17 እነሆ፣ ሰላም ከማግኘት ይልቅ በጣም ተመርሬ ነበር፤

አንተ ግን ለእኔ* ካለህ ፍቅር የተነሳ፣

ከጥፋት ጉድጓድ ጠበቅከኝ።+

ኃጢአቴን ሁሉ ወደ ኋላህ ጣልክ።*+

18 መቃብር* ከፍ ከፍ ሊያደርግህ አይችልምና፤+

ሞትም ሊያወድስህ አይችልም።+

ወደ ጉድጓድ የሚወርዱ በታማኝነትህ ተስፋ ሊያደርጉ አይችሉም።+

19 እኔ ዛሬ እንደማደርገው፣

አንተን ሊያወድስ የሚችለው ሕያው፣ አዎ ሕያው የሆነ ሰው ነው።

አባት ለልጆቹ ስለ አንተ ታማኝነት እውቀት ሊያካፍላቸው ይችላል።+

20 ይሖዋ ሆይ፣ አድነኝ፤

በሕይወታችን ዘመን ሁሉ በይሖዋ ቤት፣+

በባለ አውታር መሣሪያዎች መዝሙሮቼን እንዘምራለን።’”+

21 ከዚያም ኢሳይያስ “ሕመሙ እንዲሻለው የደረቀ የበለስ ጥፍጥፍ አምጡና እባጩ ላይ አድርጉለት” አለ።+ 22 ሕዝቅያስ “ወደ ይሖዋ ቤት እንደምወጣ ማወቅ የምችልበት ምልክት ምንድን ነው?” ብሎ ነበር።+

39 በዚያን ጊዜ የባቢሎን ንጉሥ፣ የባላዳን ልጅ ሜሮዳክባላዳን ሕዝቅያስ ታሞ እንደነበረና ከሕመሙ እንዳገገመ በመስማቱ ደብዳቤና ስጦታ ላከለት።+ 2 ሕዝቅያስም መልእክተኞቹን በደስታ ተቀበላቸው፤ ከዚያም ግምጃ ቤቱን ይኸውም ብሩን፣ ወርቁን፣ የበለሳን ዘይቱን፣ ሌላውን ምርጥ ዘይት፣ የጦር መሣሪያውን ሁሉና በግምጃ ቤቶቹ+ ውስጥ ያለውን ንብረት በሙሉ አሳያቸው። ሕዝቅያስ በቤቱም* ሆነ በግዛቱ ሁሉ ያላሳያቸው ምንም ነገር አልነበረም።

3 ከዚያ በኋላ ነቢዩ ኢሳይያስ ወደ ንጉሥ ሕዝቅያስ መጥቶ “እነዚህ ሰዎች ምን አሉ? የመጡትስ ከየት ነው?” ሲል ጠየቀው። ሕዝቅያስም “የመጡት ከሩቅ አገር፣ ከባቢሎን ነው” አለው።+ 4 ቀጥሎም “በቤትህ* ያዩት ነገር ምንድን ነው?” ሲል ጠየቀው። ሕዝቅያስም “በቤቴ* ያለውን ነገር ሁሉ አይተዋል። በግምጃ ቤቶቼ ውስጥ ካለው ንብረት ሁሉ ያላሳየኋቸው ምንም ነገር የለም” ሲል መለሰለት።

5 በዚህ ጊዜ ኢሳይያስ ሕዝቅያስን እንዲህ አለው፦ “የሠራዊት ጌታ የይሖዋን ቃል ስማ፤ 6 ‘እነሆ፣ በቤትህ* ያለው ሁሉና አባቶችህ እስካሁን ድረስ ያከማቹት ነገር ሁሉ ወደ ባቢሎን የሚጋዝበት ቀን ይመጣል። አንድም የሚቀር ነገር አይኖርም’+ ይላል ይሖዋ።+ 7 ‘ከአንተ ከሚወለዱት ከገዛ ልጆችህ መካከልም አንዳንዶቹ ይወሰዳሉ፤ በባቢሎን ንጉሥ ቤተ መንግሥትም ባለሥልጣናት ይሆናሉ።’”+

8 በዚህ ጊዜ ሕዝቅያስ ኢሳይያስን “የተናገርከው የይሖዋ ቃል መልካም ነው” አለው። አክሎም እንዲህ አለ፦ “ምክንያቱም በእኔ የሕይወት ዘመን* ሰላምና መረጋጋት* ይኖራል።”+

40 “አጽናኑ፣ ሕዝቤን አጽናኑ” ይላል አምላካችሁ።+

 2 “ለኢየሩሳሌም ልብ ተናገሩ፤*

የግዳጅ አገልግሎቷ እንዳበቃና

የበደሏ ዋጋ እንደተከፈለ ንገሯት።+

ለሠራችው ኃጢአት ሁሉ ከይሖዋ እጅ ሙሉ* ዋጋ ተቀብላለች።”+

 3 አንድ ሰው በምድረ በዳ እንዲህ ብሎ ይጮኻል፦

“የይሖዋን መንገድ ጥረጉ!*+

በበረሃ ለአምላካችን አውራ ጎዳናውን+ አቅኑ።+

 4 ሸለቆው ሁሉ ይሞላ፤

ተራራውና ኮረብታውም ሁሉ ዝቅ ይበል።

ወጣ ገባውም መሬት ይስተካከል፤

ጎርበጥባጣውም ምድር ሸለቋማ ሜዳ ይሁን።+

 5 የይሖዋ ክብር ይገለጣል፤+

ሥጋም ሁሉ በአንድነት ያየዋል፤*+

የይሖዋ አፍ ተናግሯልና።”

 6 አዳምጥ! አንድ ሰው “ጮክ ብለህ ተናገር!” አለ።

ሌላውም “ምን ብዬ ልናገር?” አለ።

“ሥጋ ሁሉ* ለምለም ሣር ነው።

ታማኝ ፍቅሩ ሁሉ እንደ ሜዳ አበባ ነው።+

 7 ለምለሙ ሣር ይደርቃል፤

አበባው ይጠወልጋል፤+

ምክንያቱም የይሖዋ እስትንፋስ* ይነፍስበታል።+

ሕዝቡ በእርግጥ ለምለም ሣር ነው።

 8 ለምለሙ ሣር ይደርቃል፤

አበባው ይጠወልጋል፤

የአምላካችን ቃል ግን ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።”+

 9 አንቺ ለጽዮን ምሥራች የምትነግሪ ሴት ሆይ፣+

ከፍ ወዳለ ተራራ ውጪ።

አንቺ ለኢየሩሳሌም ምሥራች የምትነግሪ ሴት ሆይ፣

ድምፅሽን በኃይል ከፍ አድርጊ።

ድምፅሽን ከፍ አድርጊ፤ አትፍሪ።

ለይሁዳ ከተሞች “እነሆ፣ አምላካችሁ” በማለት አስታውቂ።+

10 እነሆ፣ ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ በኃይል ይመጣል፤

ክንዱም ስለ እሱ ይገዛል።+

እነሆ፣ የሚከፍለው ወሮታ ከእሱ ጋር ነው፤

የሚመልሰውም ብድራት በፊቱ አለ።+

11 መንጋውን እንደ እረኛ ይንከባከባል።+

ግልገሎቹን በክንዱ ይሰበስባል፤

በእቅፉም ይሸከማቸዋል።

ግልገሎቻቸውን የሚያጠቡትን በቀስታ ይመራል።+

12 ውኃዎችን በእፍኙ የሰፈረ፣+

ሰማያትን በስንዝሩ* የለካ፣

የምድርን አፈር ሰብስቦ በመስፈሪያ የያዘ+

ወይም ተራሮችን በመለኪያ፣

ኮረብቶችንም በሚዛን የመዘነ ማን ነው?

13 የይሖዋን መንፈስ የለካ*

እንዲሁም አማካሪው ሆኖ ሊያስተምረው የሚችል ማን ነው?+

14 ማስተዋል ለማግኘት ከማን ጋር ተማከረ?

የፍትሕን መንገድ ያስተማረው

አሊያም እውቀትን ያካፈለው ማን ነው?

ደግሞስ የእውነተኛ ማስተዋልን ጎዳና ያሳየው ማን ነው?+

15 እነሆ፣ ብሔራት በገንቦ ውስጥ እንዳለች ጠብታ ናቸው፤

በሚዛንም ላይ እንዳለ አቧራ ይቆጠራሉ።+

እነሆ፣ ደሴቶችን እንደ ደቃቅ አፈር ያነሳቸዋል።

16 እሳት መንደዱን እንዲቀጥል ለማድረግ የሊባኖስ ዛፎች እንኳ አይበቁም፤*

በውስጡም ያሉት የዱር እንስሳት የሚቃጠል መባ ለማቅረብ በቂ አይደሉም።

17 ብሔራት ሁሉ በፊቱ የሌሉ ያህል ናቸው፤+

በእሱም ዘንድ ከምንም የማይቆጠሩና ዋጋ ቢስ ናቸው።+

18 አምላክን ከማን ጋር ታወዳድሩታላችሁ?+

ከየትኛውስ ምስል ጋር ታነጻጽሩታላችሁ?+

19 የእጅ ጥበብ ባለሙያ ብረት አቅልጦ ጣዖት* ይሠራል፤

አንጥረኛውም በወርቅ ይለብጠዋል፤+

የብር ሰንሰለትም ይሠራለታል።

20 አንድ ሰው መዋጮ አድርጎ ለመስጠት

የማይበሰብስ ዛፍ ይመርጣል።+

የማይወድቅ ምስል ቀርጾ እንዲያዘጋጅለት

በእጅ ጥበብ ሥራ የተካነ ባለሙያ ይፈልጋል።+

21 ይህን አታውቁም?

ደግሞስ አልሰማችሁም?

ከመጀመሪያ አንስቶስ አልተነገራችሁም?

የምድር መሠረት ከተጣለበት ጊዜ ጀምሮ የነበረውን ማስረጃስ አላስተዋላችሁም?+

22 እሱ ክብ* ከሆነችው ምድር በላይ ይኖራል፤+

በእሷም ላይ የሚኖሩት እንደ ፌንጣ ናቸው።

እሱ ሰማያትን እንደ ስስ ጨርቅ ይዘረጋል፤

እንደ መኖሪያ ድንኳንም ይወጥራቸዋል።+

23 ከፍተኛ ባለሥልጣናትን ያስወግዳል፤

የምድር ፈራጆችንም* እንዳልነበሩ ያደርጋል።

24 ገና እንደተተከለ፣

ገና እንደተዘራ፣

ግንዱም በአፈር ውስጥ ሥር እንዳልሰደደ ተክል ናቸው፤

ሲነፍስባቸውም ይደርቃሉ፤

ነፋስም እንደ ገለባ ጠራርጎ ይወስዳቸዋል።+

25 “እኩያው እሆን ዘንድ ከማን ጋር ታመሳስሉኛላችሁ?” ይላል ቅዱሱ።

26 “ዓይናችሁን ወደ ሰማይ አንስታችሁ ተመልከቱ።

እነዚህን ነገሮች የፈጠረ ማን ነው?+

እንደ ሠራዊት በቁጥር የሚመራቸው እሱ ነው፤

ሁሉንም በየስማቸው ይጠራቸዋል።+

ገደብ ከሌለው ብርቱ ጉልበቱና ከሚያስደምመው ኃይሉ+ የተነሳ

አንዳቸውም አይጎድሉም።

27 ያዕቆብ ሆይ፣ እስራኤልም ሆይ፣

‘መንገዴ ከይሖዋ ተሰውሯል፤

ከአምላክ ፍትሕ አላገኝም’ ለምን ትላለህ? ለምንስ እንዲህ ትናገራለህ?+

28 ይህን አታውቅም? ደግሞስ አልሰማህም?

የምድር ዳርቻዎች ፈጣሪ የሆነው ይሖዋ ከዘላለም እስከ ዘላለም አምላክ ነው።+

እሱ ፈጽሞ አይደክምም ወይም አይዝልም።+

ማስተዋሉ አይመረመርም።*+

29 ለደከመው ኃይል፣

ጉልበት ለሌላቸውም የተሟላ ብርታት* ይሰጣል።+

30 ወንዶች ልጆች ይደክማሉ፤ ደግሞም ይዝላሉ፤

ወጣቶችም ተደናቅፈው ይወድቃሉ፤

31 ይሖዋን ተስፋ የሚያደርጉ ግን ኃይላቸው ይታደሳል።

እንደ ንስር በክንፍ ወደ ላይ ይወጣሉ።+

ይሮጣሉ፣ አይዝሉም፤

ይሄዳሉ፣ አይደክሙም።”+

41 “እናንተ ደሴቶች፣ ዝም ብላችሁ አዳምጡኝ፤*

ብሔራትም ኃይላቸውን ያድሱ።

በመጀመሪያ ይቅረቡ፤ ከዚያም ይናገሩ።+

ለፍርድ አንድ ላይ እንሰብሰብ።

 2 ብሔራትን አሳልፎ ይሰጠውና

ነገሥታትን ድል ይነሳ ዘንድ+

ከፀሐይ መውጫ* አንዱን ያስነሳው፣+

በጽድቅ ወደ እግሩ የጠራው* ማን ነው?

በሰይፉ ፊት አቧራ የሚያደርጋቸው፣

በቀስቱ ፊት በነፋስ እንደተወሰደ ገለባ የሚያደርጋቸው ማን ነው?

 3 እግሩ ባልረገጠው መንገድ በመጓዝ

ምንም ነገር ሳያግደው እነሱን ያሳድዳል።

 4 ይህን የሠራና ያደረገ፣

ትውልዶቹንም ከመጀመሪያ አንስቶ የጠራ ማን ነው?

እኔ ይሖዋ የመጀመሪያው ነኝ፤+

ከመጨረሻዎቹም ጋር እኔ ያው ነኝ።”+

 5 ደሴቶች አይተው ፈሩ።

የምድር ዳርቻዎች ተንቀጠቀጡ።

ቀረቡ፤ ወደ ፊትም መጡ።

 6 እያንዳንዱም ባልንጀራውን ይረዳል፤

ወንድሙንም “አይዞህ፣ በርታ” ይለዋል።

 7 የእጅ ጥበብ ባለሙያውም አንጥረኛውን ያበረታታል፤+

በመዶሻ ብረቱን የሚያሳሳው

በመስፍ ላይ የሚቀጠቅጠውን ያበረታታዋል።

ብየዳውን በተመለከተ “ጥሩ ነው” ይላል።

ከዚያም ጣዖቱ እንዳይወድቅ አንድ ሰው በምስማር ይቸነክረዋል።

 8 “እስራኤል ሆይ፣ አንተ ግን አገልጋዬ ነህ፤+

ያዕቆብ ሆይ፣ አንተን መርጬሃለሁ፤+

የወዳጄ የአብርሃም ዘር ነህ፤+

 9 አንተን ከምድር ዳርቻዎች ወሰድኩህ፤+

እጅግ ርቀው ከሚገኙ ቦታዎችም ጠራሁህ።

እንዲህ ብዬሃለሁ፦ ‘አንተ አገልጋዬ ነህ፤+

እኔ መርጬሃለሁ፤ ገሸሽ አላደረግኩህም።+

10 እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ።+

እኔ አምላክህ ነኝና አትጨነቅ።+

አበረታሃለሁ፤ አዎ እረዳሃለሁ፤+

በጽድቅ ቀኝ እጄ አጥብቄ እይዝሃለሁ።’

11 እነሆ፣ በአንተ ላይ የተቆጡ ሁሉ ያፍራሉ፤ ይዋረዳሉም።+

ከአንተ ጋር የሚጣሉ ሁሉ እንዳልነበሩ ይሆናሉ፤ ይጠፋሉም።+

12 ከአንተ ጋር የሚፋለሙትን ሰዎች ትፈልጋቸዋለህ፤ ሆኖም አታገኛቸውም፤

ከአንተ ጋር የሚዋጉ ሰዎች እንደሌሉና ፈጽሞ እንዳልነበሩ ያህል ይሆናሉ።+

13 ‘አትፍራ። እረዳሃለሁ’ የምልህ

እኔ፣ አምላክህ ይሖዋ ቀኝ እጅህን ይዣለሁና።+

14 ትል* የሆንከው አንተ ያዕቆብ አትፍራ፤+

እናንተ የእስራኤል ሰዎች፣ እረዳችኋለሁ” ይላል የሚቤዥህ+ የእስራኤል ቅዱስ ይሖዋ።

15 “እነሆ፣ ማሄጃ፣ በሁለቱም በኩል የተሳሉ ጥርሶች ያሉት

አዲስ የመውቂያ መሣሪያ አድርጌሃለሁ።+

አንተም ተራሮቹን ረግጠህ ታደቃቸዋለህ፤

ኮረብቶቹንም እንደ ገለባ ታደርጋቸዋለህ።

16 ወደ ላይ ትበትናቸዋለህ፤

ነፋስም ይወስዳቸዋል፤

አውሎ ነፋስ ይበትናቸዋል።

በይሖዋ ደስ ይልሃል፤+

በእስራኤልም ቅዱስ ትኮራለህ።”+

17 “ችግረኞችና ድሆች ውኃ ይፈልጋሉ፤ ሆኖም አያገኙም።

ከመጠማታቸው የተነሳ ምላሳቸው ደርቋል።+

እኔ ይሖዋ እመልስላቸዋለሁ።+

እኔ የእስራኤል አምላክ አልተዋቸውም።+

18 በተራቆቱ ኮረብቶች ላይ ወንዞች እንዲፈስሱ አደርጋለሁ፤+

በሸለቋማ ሜዳዎች መካከል ምንጮችን አፈልቃለሁ።+

ምድረ በዳውን ቄጠማ የሞላበት ኩሬ፣

ውኃ የሌለበትንም ምድር የውኃ ምንጭ አደርጋለሁ።+

19 በበረሃ አርዘ ሊባኖስ፣

ግራር፣ አደስና ዘይት የሚሰጥ ዛፍ እተክላለሁ።+

በበረሃማ ሜዳ የጥድ ዛፍ፣

የአሽ ዛፍና* የፈረንጅ ጥድ በአንድነት እተክላለሁ፤+

20 ይህም የሚሆነው የይሖዋ እጅ ይህን እንዳደረገና

የእስራኤል ቅዱስ ይህን እንደፈጠረ

ሰዎች ሁሉ እንዲያዩና እንዲያውቁ፣

ልብ እንዲሉና በጥልቅ እንዲያስተውሉ ነው።”+

21 “ሙግታችሁን አቅርቡ” ይላል ይሖዋ።

“የመከራከሪያ ሐሳባችሁን አሰሙ” ይላል የያዕቆብ ንጉሥ።

22 “ማስረጃ አቅርቡ፤ እንዲሁም ወደፊት የሚሆኑትን ነገሮች ንገሩን።

በጥሞና እንድናስብባቸውና* ፍጻሜያቸውን እንድናውቅ

ስለቀድሞዎቹ* ነገሮች ንገሩን።

ወይም የሚመጡትን ነገሮች አሳውቁን።+

23 አማልክት መሆናችሁን እንድናውቅ

ወደፊት የሚሆነውን ነገር ንገሩን።+

አዎ፣ አይተን በአድናቆት እንድንዋጥ

መልካምም ሆነ ክፉ፣ የሆነ ነገር አድርጉ።+

24 እነሆ፣ እናንተ ጨርሶ ሕልውና የሌላችሁ ናችሁ፤

ምንም የምታከናውኑት ነገር የለም።+

እናንተን የሚመርጥ ሁሉ አስጸያፊ ነው።+

25 አንዱን ከሰሜን አስነስቻለሁ፤ እሱም ይመጣል፤+

የሚመጣው ከፀሐይ መውጫ*+ ሲሆን ስሜንም ይጠራል።

ጭቃውን እንደሚረግጥ ሸክላ ሠሪ

ገዢዎችን* እንደ ሸክላ አፈር ይረግጣቸዋል።+

26 እኛ እናውቅ ዘንድ ስለዚህ ነገር ከመጀመሪያው የተናገረ

ወይም ‘እሱ ትክክል ነው’ እንድንል ከጥንት ጀምሮ የተናገረ ማን ነው?+

በእርግጥ የተናገረ የለም!

ያሳወቀም የለም!

ከእናንተ አንዳች ነገር የሰማ የለም!”+

27 ከማንም በፊት ጽዮንን “ወደፊት የሚሆነውን ነገር ተመልከቺ!” ያልኩት እኔ ነኝ፤+

ለኢየሩሳሌምም ምሥራች ነጋሪ እልካለሁ።+

28 ሆኖም እኔ መመልከቴን ቀጠልኩ፤ አንድም ሰው አልነበረም፤

ከእነሱ መካከል ምክር የሚሰጥ አልነበረም።

እኔም መልስ እንዲሰጡ መጠየቄን ቀጠልኩ።

29 እነሆ፣ ሁሉም ቅዠት* ናቸው።

ሥራቸው ከንቱ ነው።

ከብረት የተሠሩት ምስሎቻቸው* ነፋስና መና ናቸው።+

42 እነሆ፣ ደግፌ የያዝኩት፣

ደስ የምሰኝበትና*+ የመረጥኩት+ አገልጋዬ!+

መንፈሴን በእሱ ላይ አድርጌአለሁ፤+

እሱ ለብሔራት ፍትሕን ያመጣል።+

 2 አይጮኽም ወይም ድምፁን ከፍ አያደርግም፤

ድምፁንም በጎዳና ላይ አያሰማም።+

 3 የተቀጠቀጠን ሸምበቆ አይሰብርም፤

የሚጨስንም የጧፍ ክር አያጠፋም።+

ፍትሕን በታማኝነት ያመጣል።+

 4 እሱ ፍትሕን በምድር ላይ እስኪያሰፍን ድረስ አይሰበርም ወይም ብርሃኑ አይደክምም፤+

ደሴቶችም ሕጉን* በተስፋ ይጠባበቃሉ።

 5 ሰማያትን የፈጠረውና የዘረጋው፣+

ምድርንና በውስጧ ያሉትን ነገሮች ሁሉ የሠራው፣+

በላይዋም ለሚኖሩ ሰዎች እስትንፋስን፣+

በእሷም ላይ ለሚመላለሱ መንፈስን የሰጠው+

እውነተኛው አምላክ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦

 6 “እኔ ይሖዋ በጽድቅ ጠርቼሃለሁ፤

እጅህን ይዣለሁ።

እጠብቅሃለሁ፤ እንዲሁም ለሰዎች ቃል ኪዳን፣

ለብሔራትም ብርሃን አድርጌ እሰጥሃለሁ፤+

 7 አንተም የዓይነ ስውራንን ዓይን ታበራለህ፤+

እስረኛውን ከወህኒ ቤት፣

በጨለማ ውስጥ የተቀመጡትንም ከእስር ቤት ታወጣለህ።+

 8 እኔ ይሖዋ ነኝ። ስሜ ይህ ነው፤

ክብሬን ለሌላ፣*

ምስጋናዬንም ለተቀረጹ ምስሎች አልሰጥም።+

 9 እነሆ፣ የቀደሙት ነገሮች ተፈጽመዋል፤

አሁን ደግሞ አዳዲስ ነገሮችን እናገራለሁ።

ገና ከመከሰታቸው በፊት ስለ እነሱ እነግራችኋለሁ።”+

10 እናንተ በባሕር ላይና በውስጡ ባሉት ፍጥረታት መካከል የምትጓዙ፣

እናንተ ደሴቶችና በእነሱ ላይ የምትኖሩ ሁሉ፣+

ለይሖዋ አዲስ መዝሙር ዘምሩ፤+

ከምድር ዳርቻም ውዳሴውን አሰሙ።+

11 ምድረ በዳውና በዚያ ያሉ ከተሞች፣

ቄዳር+ ያለችባቸውም ሰፈሮች ድምፃቸውን ከፍ ያድርጉ።+

ዓለታማ በሆኑ ቦታዎች የሚኖሩ ሰዎች በደስታ እልል ይበሉ፤

በተራሮችም አናት ላይ ሆነው ይጩኹ።

12 ለይሖዋ ክብር ይስጡ፤

በደሴቶችም ላይ ውዳሴውን ያውጁ።+

13 ይሖዋ እንደ ኃያል ሰው ይወጣል።+

እንደ ተዋጊ ቅንዓቱን ይቀሰቅሳል።+

ይጮኻል፤ አዎ፣ ቀረርቶ ያሰማል፤

ከጠላቶቹ ይበልጥ ኃያል መሆኑን ያሳያል።+

14 “ለረጅም ጊዜ ዝም አልኩ።

ጸጥ ብዬ ቆየሁ፤ ራሴንም ገታሁ።

ምጥ እንደያዛት ሴት

እቃትታለሁ፣ አለከልካለሁ እንዲሁም ቁና ቁና እተነፍሳለሁ።

15 ተራሮችንና ኮረብቶችን አወድማለሁ፤

ደግሞም በላያቸው ላይ ያለውን ተክል ሁሉ አደርቃለሁ።

ወንዞችን ደሴቶች* አደርጋለሁ፤

ቄጠማ የሞላባቸውንም ኩሬዎች አደርቃለሁ።+

16 ዓይነ ስውራንን በማያውቁት መንገድ እመራቸዋለሁ፤+

ባልለመዱት ጎዳናም እንዲሄዱ አደርጋቸዋለሁ።+

ጨለማውን በፊታቸው ብርሃን፣+

ወጣ ገባ የሆነውንም ምድር ደልዳላ ሜዳ አደርጋለሁ።+

ይህን አደርግላቸዋለሁ፤ ደግሞም አልተዋቸውም።”

17 በተቀረጸ ምስል የሚታመኑ፣

ከብረት የተሠሩትን ሐውልቶች* “እናንተ አምላኮቻችን ናችሁ” የሚሉ

ወደ ኋላ ይመለሳሉ፤ እጅግም ያፍራሉ።+

18 እናንተ ደንቆሮዎች፣ ስሙ፤

እናንተ ዕውሮች እዩ፤ ተመልከቱም።+

19 ከአገልጋዬ በቀር የታወረ፣

እንደምልከው መልእክተኛዬም ደንቆሮ የሆነ ማን አለ?

ብድራት እንደተከፈለው ሰው ዕውር የሆነ

ወይም እንደ ይሖዋ አገልጋይ የታወረ ማን ነው?+

20 ብዙ ነገሮች ብታዩም ልብ የምትሉት ነገር የለም።

ጆሮዎቻችሁን ብትከፍቱም ምንም አትሰሙም።+

21 ይሖዋ ለጽድቁ ሲል

ሕጉን* ታላቅና ክብራማ በማድረግ ደስ ተሰኝቷል።

22 ይህ ሕዝብ ግን የተበዘበዘና የተዘረፈ ነው፤+

ሁሉም ጉድጓድ ውስጥ ተይዘዋል፤ በእስር ቤትም ተሰውረዋል።+

የሚታደጋቸው በሌለበት ተበዝብዘዋል፤+

“መልሷቸው!” የሚል በሌለበትም ተዘርፈዋል።

23 ከእናንተ መካከል ይህን የሚሰማ ማን ነው?

በትኩረት የሚያዳምጥና ለወደፊቱ ጊዜ ትምህርት የሚወስድ ማን ነው?

24 ያዕቆብን ለዘረፋ፣

እስራኤልንም ለበዝባዦች አሳልፎ የሰጠ ማን ነው?

በእሱ ላይ ኃጢአት በመፈጸም የበደልነው ይሖዋ አይደለም?

እነሱ በመንገዱ ለመሄድ አልፈለጉም፤

ሕጉንም* አይታዘዙም።+

25 ስለዚህ ንዴቱን፣ ቁጣውንና የጦርነቱን መዓት

በእስራኤል ላይ አፈሰሰ።+

የጦርነቱም እሳት በዙሪያው ያለውን ሁሉ በላው፤ እሱ ግን አላስተዋለም።+

አቃጠለው፤ እሱ ግን ጨርሶ ልብ አላለም።+

43 አሁን ግን፣ ያዕቆብ ሆይ ፈጣሪህ፣

እስራኤልም ሆይ የሠራህ ይሖዋ+ እንዲህ ይላል፦

“እኔ ተቤዥቼሃለሁና+ አትፍራ።

በስምህ ጠርቼሃለሁ።

አንተ የእኔ ነህ።

 2 በውኃዎች መካከል ስታልፍ እኔ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፤+

በወንዞችም መካከል ስትሻገር አያሰምጡህም።+

በእሳት መካከል ስትሄድ አትቃጠልም፤

ነበልባሉም አይፈጅህም።

 3 እኔ ይሖዋ አምላክህ፣

የእስራኤል ቅዱስ፣ አዳኝህ ነኝና።

ግብፅን ለአንተ ቤዛ አድርጌ ሰጥቻለሁ፤

ኢትዮጵያንና ሴባን በአንተ ምትክ ሰጥቻለሁ።

 4 አንተ በዓይኔ ፊት ውድ ሆነሃልና፤+

የተከበርክም ነህ፤ እኔም ወድጄሃለሁ።+

ስለዚህ በአንተ ምትክ ሰዎችን፣

በሕይወትህም* ምትክ ብሔራትን እሰጣለሁ።

 5 እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ።+

ዘርህን ከምሥራቅ አመጣለሁ፤

ከምዕራብም እሰበስብሃለሁ።+

 6 ሰሜንን ‘ልቀቃቸው!’ እለዋለሁ፤+

ደቡብንም እንዲህ እለዋለሁ፦ ‘አታግታቸው።

ወንዶች ልጆቼን ከሩቅ፣ ሴቶች ልጆቼንም ከምድር ዳርቻ አምጣ፤+

 7 በስሜ የተጠራውን፣+

ለክብሬም የፈጠርኩትን፣

የሠራሁትንና ያበጀሁትን ሁሉ አምጣ።’+

 8 ዓይን ቢኖራቸውም ዕውር የሆኑትን፣

ጆሮ ቢኖራቸውም ደንቆሮ የሆኑትን ሰዎች አውጣ።+

 9 ብሔራት ሁሉ አንድ ቦታ ይሰብሰቡ፤

ሕዝቦችም በአንድነት ይሰብሰቡ።+

ከመካከላቸው ይህን ሊናገር የሚችል ማን አለ?

ወይስ የመጀመሪያዎቹን ነገሮች ሊነግሩን ይችላሉ?*+

ትክክል መሆናቸውን እንዲያረጋግጡ ምሥክሮቻቸውን ያቅርቡ፤

ወይም ሰምተው ‘ይህ እውነት ነው!’ ይበሉ።”+

10 “እናንተ ምሥክሮቼ ናችሁ”+ ይላል ይሖዋ፤

“አዎ፣ የመረጥኩት አገልጋዬ ናችሁ፤+

ይህም ታውቁና ታምኑብኝ ዘንድ*

ደግሞም እኔ ምንጊዜም ያው እንደሆንኩ ታስተውሉ ዘንድ ነው።+

ከእኔ በፊት አምላክ አልተሠራም፤

ከእኔም በኋላ የለም።+

11 እኔ፣ አዎ እኔ ይሖዋ ነኝ፤+ ከእኔ በቀር አዳኝ የለም።”+

12 “በመካከላችሁ ባዕድ አምላክ ባልነበረበት ጊዜ

የተናገርኩት፣ ያዳንኩትና ያሳወቅኩት እኔ ነኝ።+

ስለዚህ እናንተ ምሥክሮቼ ናችሁ” ይላል ይሖዋ፤ “እኔም አምላክ ነኝ።+

13 ደግሞም እኔ ምንጊዜም ያው ነኝ፤+

ከእጄም አንዳች ነገር ሊነጥቅ የሚችል የለም።+

እርምጃ በምወስድበት ጊዜ ሊያግድ የሚችል ማን ነው?”+

14 እናንተን የሚቤዠው+ የእስራኤል ቅዱስ ይሖዋ+ እንዲህ ይላል፦

“ለእናንተ ስል ወደ ባቢሎን እሰዳለሁ፤ የበሮቹንም መቀርቀርያዎች ሁሉ እጥላለሁ፤+

በመርከቦቻቸው ላይ ያሉት ከለዳውያንም በጭንቀት ይጮኻሉ።+

15 እኔ ይሖዋ የእናንተ ቅዱስ፣+ የእስራኤል ፈጣሪ፣+ ንጉሣችሁ ነኝ።”+

16 ይሖዋ ይኸውም

በባሕር መካከል መንገድ የሚያበጀው፣

በሚናወጡ ውኃዎችም መካከል ጎዳና የሚዘረጋው፣+

17 የጦር ሠረገላውንና ፈረሱን፣+

ሠራዊቱንና ኃያላን ተዋጊዎቹን በአንድነት የሚያወጣው አምላክ እንዲህ ይላል፦

“ይተኛሉ፤ አይነሱምም።+

እንደሚነድ የጧፍ ክር ተዳፍነው ይጠፋሉ።”

18 “የቀድሞዎቹን ነገሮች አታስታውሱ፤

ያለፈውንም ነገር አታውጠንጥኑ።

19 እነሆ፣ አዲስ ነገር አደርጋለሁ፤+

አሁንም እንኳ መከናወን ጀምሯል።

ይህን አታስተውሉም?

በምድረ በዳ መንገድ አዘጋጃለሁ፤+

በበረሃም ወንዞችን አፈልቃለሁ።+

20 የዱር አውሬ፣ ቀበሮዎችና

ሰጎኖች ያከብሩኛል፤

በምድረ በዳ ውኃ፣

በበረሃም ወንዞችን እሰጣለሁና፤+

ይህን የማደርገው የመረጥኩት ሕዝቤ+ እንዲጠጣ፣

21 ለራሴ የሠራሁትም ሕዝብ እንዲጎነጭ ነው፤

ሕዝቤ ውዳሴዬን እንዲያውጅ ይህን አደርጋለሁ።+

22 እስራኤል ሆይ፣ አንተ ግን የእኔ ነገር ስለታከተህ፣+

ያዕቆብ ሆይ፣ አልጠራኸኝም።+

23 ሙሉ በሙሉ የሚቃጠል መባ ለማቅረብ በግ አላመጣህልኝም፤

ወይም መሥዋዕቶች በማቅረብ አላከበርከኝም።

ስጦታ እንድታመጣልኝ አላስገደድኩህም፤

ነጭ ዕጣን አቅርብልኝ ብዬም አላሰለቸሁህም።+

24 በገንዘብህ ጠጅ ሣር* አልገዛህልኝም፤

በመሥዋዕቶችህም ስብ አላጠገብከኝም።+

ከዚህ ይልቅ ኃጢአትህን አሸክመኸኛል፤

በምትፈጽማቸውም በደሎች አሰልችተኸኛል።+

25 ስለ ራሴ ስል+ በደልህን* እኔ ራሴ እደመስሰዋለሁ፤+

ኃጢአትህንም አላስታውስም።+

26 እስቲ አስታውሰኝ፤ ጉዳያችንን አቅርበን እንሟገት፤

ትክክለኛ መሆንህን ለማረጋገጥ በበኩልህ ጉዳይህን ተናገር።

27 የመጀመሪያው አባትህ ኃጢአት ሠርቷል፤

የገዛ ቃል አቀባዮችህም* በእኔ ላይ ዓምፀዋል።+

28 ስለዚህ በቅዱሱ ስፍራ የሚገኙትን መኳንንት አረክሳለሁ፤

ያዕቆብንም ለጥፋት አሳልፌ እሰጠዋለሁ፤

እስራኤልንም ለስድብ እዳርገዋለሁ።+

44 “አሁን ግን፣ አገልጋዬ ያዕቆብ ሆይ፣

የመረጥኩህም እስራኤል ሆይ፣+ ስማ።

 2 የሠራህና ያበጀህ፣+

ከማህፀን* ጀምሮ የረዳህ

ይሖዋ እንዲህ ይላል፦

‘አገልጋዬ ያዕቆብ፣

የመረጥኩህም የሹሩን*+ ሆይ፣ አትፍራ።+

 3 ለተጠማው* ውኃ አፈሳለሁና፤+

በደረቁ ምድርም ላይ ጅረቶች እንዲፈስሱ አደርጋለሁ።

መንፈሴን በዘርህ ላይ፣

በረከቴንም በልጅ ልጆችህ ላይ አፈሳለሁ።+

 4 እነሱም በለምለም ሣር መካከል፣

በጅረቶችም ዳር እንዳሉ የአኻያ ዛፎች ይበቅላሉ።+

 5 አንዱ “እኔ የይሖዋ ነኝ” ይላል።+

ሌላውም ራሱን በያዕቆብ ስም ይጠራል፤

ሌላው ደግሞ በእጁ ላይ “የይሖዋ ነኝ” ብሎ ይጽፋል።

ደግሞም ራሱን በእስራኤል ስም ይጠራል።’

 6 የእስራኤል ንጉሥ+ የሆነውና እስራኤልን የተቤዠው+ ይሖዋ፣

የሠራዊት ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦

‘የመጀመሪያው እኔ ነኝ፤ የመጨረሻውም እኔ ነኝ።+

ከእኔ በቀር ሌላ አምላክ የለም።+

 7 እንደ እኔ ያለ ማን ነው?+

በድፍረት ይናገር፤ ያሳውቅም፤ ማስረጃውንም ለእኔ ያቅርብ!+

የጥንቱን ሕዝብ ካቋቋምኩበት ጊዜ ጀምሮ፣

በቅርቡ የሚከሰቱትንና

ወደፊት የሚሆኑትን ነገሮች ይናገሩ።

 8 ስጋት አይደርባችሁ፤

በፍርሃትም አትሽመድመዱ።+

አስቀድሜ ለእያንዳንዳችሁ አልነገርኳችሁም? ደግሞስ አላሳወቅኳችሁም?

እናንተ ምሥክሮቼ ናችሁ።+

ከእኔ ሌላ አምላክ አለ?

በፍጹም፣ ሌላ ዓለት የለም፤+ እኔ የማውቀው አንድም የለም።’”

 9 የተቀረጹ ምስሎችን የሚሠሩ ሁሉ ከንቱ ናቸው፤

የሚወዷቸውም ጣዖቶች ምንም ጥቅም የላቸውም።+

እንደ ምሥክሮቻቸው እነሱም* ምንም አያዩም፤ ምንም አያውቁም፤+

በመሆኑም ሠሪዎቻቸው ለኀፍረት ይዳረጋሉ።+

10 ለምንም የማይጠቅም አምላክ የሚሠራ

ወይም የብረት ምስል* የሚያበጅ ማን ነው?+

11 እነሆ፣ ባልደረቦቹ ሁሉ ያፍራሉ!+

የእጅ ጥበብ ባለሙያዎቹ ተራ ሰዎች ናቸው።

ሁሉም ተሰብስበው ይቁሙ።

በፍርሃት ይዋጣሉ፤ ሁሉም ያፍራሉ።

12 አንጥረኛ በመሣሪያው* ተጠቅሞ ብረቱን በከሰል ፍም ላይ ይሠራዋል።

ብርቱ በሆነው ክንዱ

በመዶሻ ቅርጽ ይሰጠዋል።+

ከዚያም ይርበዋል፤ ጉልበትም ያጣል፤

ውኃ ስለማይጠጣ ይደክማል።

13 እንጨት ጠራቢው በገመድ ይለካል፤ በቀይ ጠመኔም ንድፍ ያወጣል።

በመሮም ይጠርበዋል፤ በማክበቢያም ምልክት ያደርግበታል።

በሰው አምሳል ይቀርጸዋል፤+

የሰውንም ውበት ያላብሰዋል፤

ከዚያም ቤት ውስጥ* ያስቀምጠዋል።+

14 አርዘ ሊባኖስ የሚቆርጥ ሰው አለ።

እሱም አንድ የዛፍ ዝርያ ይኸውም የባሉጥ ዛፍ ይመርጣል፤

እስኪጠነክርለት ድረስ በጫካው ውስጥ ባሉት ዛፎች መካከል ይተወዋል።+

የላውሮ ዛፍ ይተክላል፤ ዝናብም ያሳድገዋል።

15 ከዚያም ሰው ለማገዶ ይጠቀምበታል።

የተወሰነውን እንጨት ወስዶ በማንደድ እሳት ይሞቃል፤

እሳት አያይዞም ዳቦ ይጋግራል።

ይሁንና አምላክ ሠርቶም ያመልከዋል።

የተቀረጸ ምስል ሠርቶበት በፊቱ ይደፋል።+

16 ግማሹን በእሳት ያነደዋል፤

በዚያም ላይ የሚበላውን ሥጋ ይጠብሳል፤ በልቶም ይጠግባል።

እሳቱንም እየሞቀ

“እሰይ! እሳቱን እያየሁ ሞቅኩ” ይላል።

17 የቀረውን ግን ምስል ይቀርጽበታል፤ አምላክ አድርጎም ይሠራዋል።

በፊቱም ተደፍቶ ይሰግድለታል።

“አንተ አምላኬ ነህና አድነኝ” ብሎ

ወደ እሱ ይጸልያል።+

18 ምንም አያውቁም እንዲሁም አያስተውሉም፤+

ምክንያቱም ዓይኖቻቸው ተጨፍነዋል፤ ማየትም አይችሉም፤

ልባቸውም ማስተዋል ጎድሎታል።

19 ቆም ብሎ በልቡ ያሰበ

ወይም እውቀትም ሆነ ማስተዋል ኖሮት እንዲህ ብሎ የተናገረ የለም፦

“ግማሹን እሳት አንድጄበታለሁ፤

በፍሙም ላይ ዳቦ ጋግሬአለሁ፤ ሥጋም ጠብሼ በልቻለሁ።

ታዲያ በቀረው እንጨት አስጸያፊ ነገር መሥራቴ ተገቢ ነው?+

ከዛፍ ለተቆረጠ እንጨት* መስገድ ይገባኛል?”

20 እሱ አመድ ይበላል።

የተታለለው የገዛ ልቡ አስቶታል።

ራሱን* ሊያድን አይችልም፤

ደግሞም “በቀኝ እጄ ያለው ውሸት አይደለም?” አይልም።

21 “ያዕቆብ ሆይ፣ አንተም እስራኤል ሆይ፣

አገልጋዬ ስለሆንክ እነዚህን ነገሮች አስታውስ።

እኔ ሠርቼሃለሁ፤ አንተ የእኔ አገልጋይ ነህ።+

እስራኤል ሆይ፣ አልረሳህም።+

22 በደልህን በደመና፣

ኃጢአትህንም ጥቅጥቅ ባለ ደመና እሸፍነዋለሁ።+

ወደ እኔ ተመለስ፤ እኔም እቤዥሃለሁ።+

23 እናንተ ሰማያት በደስታ እልል በሉ!

ይሖዋ እርምጃ ወስዷልና።

እናንተ ጥልቅ የምድር ክፍሎች በድል አድራጊነት ጩኹ!

እናንተ ተራሮች፣ አንተም ደን ሆይ፣

በውስጡም ያላችሁ ዛፎች ሁሉ በደስታ እልል በሉ!+

ይሖዋ ያዕቆብን ተቤዥቷልና፤

በእስራኤልም ላይ ግርማውን ገልጧል።”+

24 የተቤዠህና+ ከማህፀን ጀምሮ የሠራህ

ይሖዋ እንዲህ ይላል፦

“ሁሉንም ነገር የሠራሁ እኔ ይሖዋ ነኝ።

ብቻዬን ሰማያትን ዘረጋሁ፤+

ምድርንም ሠራሁ።+

ያኔ ከእኔ ጋር ማን ነበር?

25 የሆነ ያልሆነውን የሚቀባጥሩ ሰዎችን* ምልክቶች አከሽፋለሁ፤

ሟርተኞችንም ነፈዝ አደርጋለሁ፤+

ጥበበኞቹንም ግራ አጋባለሁ፤

እውቀታቸውንም ሞኝነት አደርጋለሁ፤+

26 የአገልጋዬን ቃል እውን አደርጋለሁ፤

የመልእክተኞቼንም ትንቢት ሙሉ በሙሉ እፈጽማለሁ፤+

ስለ ኢየሩሳሌም ‘የሰው መኖሪያ ትሆናለች’፤+

ስለ ይሁዳ ከተሞችም ‘ዳግም ይገነባሉ፤+

ፍርስራሾቿንም መልሼ እሠራለሁ’+ እላለሁ፤

27 ጥልቁን ውኃ ‘ደረቅ ሁን፤

ወንዞችህንም ሁሉ አደርቃለሁ’+ እላለሁ፤

28 ስለ ቂሮስ+ ‘እሱ እረኛዬ ነው፤

ፈቃዴንም ሁሉ ሙሉ በሙሉ ይፈጽማል’+ እላለሁ፤

ስለ ኢየሩሳሌም ‘ዳግም ትገነባለች’፤

ስለ ቤተ መቅደሱም ‘መሠረትህ ይጣላል’+ እላለሁ።”

45 ይሖዋ ለቀባው ለቂሮስ+ እንዲህ ይላል፦

ብሔራትን በፊቱ ለማስገዛት፣+

ነገሥታትን ትጥቅ ለማስፈታት*

እንዲሁም የከተማው በሮች እንዳይዘጉ

መዝጊያዎቹን በፊቱ ለመክፈት ስል

ቀኝ እጁን ለያዝኩት+ ለቂሮስ፦

 2 “እኔ በፊትህ እሄዳለሁ፤+

ኮረብቶቹንም ደልዳላ አደርጋለሁ።

የመዳብ በሮቹን እሰባብራለሁ፤

የብረት መቀርቀሪያዎቹንም እቆርጣለሁ።+

 3 በስምህ የምጠራህ+

እኔ የእስራኤል አምላክ ይሖዋ መሆኔን እንድታውቅ፣

በጨለማ ያለውን ውድ ሀብትና

ስውር በሆኑ ቦታዎች የተደበቀውን ውድ ሀብት እሰጥሃለሁ።+

 4 ለአገልጋዬ ለያዕቆብ፣ ለመረጥኩትም ለእስራኤል ስል

በስምህ እጠራሃለሁ።

አንተ ባታውቀኝም እንኳ የክብር ስም እሰጥሃለሁ።

 5 እኔ ይሖዋ ነኝ፤ ከእኔም ሌላ ማንም የለም።

ከእኔ በቀር ሌላ አምላክ የለም።+

አንተ ባታውቀኝም እንኳ አበረታሃለሁ፤*

 6 ይኸውም ከፀሐይ መውጫ እስከ ፀሐይ መግቢያ* ያሉ ሕዝቦች

ከእኔ በቀር ሌላ እንደሌለ እንዲያውቁ ነው።+

እኔ ይሖዋ ነኝ፤

ከእኔም ሌላ ማንም የለም።+

 7 ብርሃንን እሠራለሁ፤+ ጨለማንም እፈጥራለሁ፤+

ሰላምን አሰፍናለሁ፤+ ጥፋትንም እፈጥራለሁ፤+

እኔ ይሖዋ እነዚህን ነገሮች ሁሉ አደርጋለሁ።

 8 እናንተ ሰማያት፣ ከላይ አዝንቡ፤+

ደመናት ጽድቅን እንደ ዶፍ ያውርዱ።

ምድር ትከፈት፤ መዳንንም ታፍራ፤

ጽድቅንም በአንድነት ታብቅል።+

እኔ ይሖዋ ፈጥሬዋለሁ።”

 9 ከሠሪው ጋር ሙግት ለሚገጥም* ወዮለት!

እሱ መሬት ላይ በተጣሉ

ሌሎች ገሎች መካከል ያለ ተራ ገል ነውና።

ሸክላ፣ ሠሪውን* “የምትሠራው ምንድን ነው?” ይለዋል?+

የሠራኸውስ ነገር “እሱ እጅ የለውም” ይላል?*

10 አንድን አባት “ምን ልትወልድ ነው?” ብሎ ለሚጠይቅ፣

ሴትንም “ምን ልትወልጂ ነው?”* ለሚል ወዮለት!

11 የእስራኤል ቅዱስ፣+ ሠሪው የሆነው ይሖዋ እንዲህ ይላል፦

“ወደፊት ስለሚሆኑት ነገሮች ልትጠይቁኝ፣

ደግሞስ ልጆቼንና+ የእጆቼን ሥራ በተመለከተ ልታዙኝ ትፈልጋላችሁ?

12 እኔ ምድርን ሠርቻለሁ፤+ በላይዋም ላይ ሰውን ፈጥሬአለሁ።+

በገዛ እጆቼ ሰማያትን ዘርግቻለሁ፤+

ሠራዊታቸውንም ሁሉ አዛለሁ።”+

13 “እኔ አንድን ሰው በጽድቅ አስነስቻለሁ፤+

መንገዱንም ሁሉ ቀና አደርጋለሁ።

እሱ ከተማዬን ይገነባል፤+

በግዞት ያለውንም ሕዝቤን ያለዋጋ ወይም ያለጉቦ ነፃ ያወጣል”+ ይላል የሠራዊት ጌታ ይሖዋ።

14 ይሖዋ እንዲህ ይላል፦

“የግብፅ ትርፍ፣* የኢትዮጵያ ሸቀጦችና* ቁመተ ረጃጅሞቹ የሳባ ሰዎች

ወደ አንቺ ይመጣሉ፤ የአንቺም ይሆናሉ።

በሰንሰለት ታስረው ከኋላሽ ይሄዳሉ።

መጥተው ይሰግዱልሻል።+

ደግሞም በጸሎት ‘አምላክ በእርግጥ ከአንቺ ጋር ነው፤+

ከእሱም በቀር ሌላ የለም፤ ሌላም አምላክ የለም’ ይሉሻል።”

15 አዳኝ የሆንከው የእስራኤል አምላክ ሆይ፣+

በእርግጥ አንተ ራስህን የምትሰውር አምላክ ነህ።

16 ሁሉም ያፍራሉ፤ ይዋረዳሉም፤

ጣዖቶችን የሚሠሩ ሁሉ ውርደት ተከናንበው ይሄዳሉ።+

17 እስራኤል ግን በይሖዋ ዘላለማዊ መዳን ያገኛል።+

እናንተም ለዘላለም አታፍሩም ወይም አትዋረዱም።+

18 ሰማያትን የፈጠረው፣+ እውነተኛው አምላክ፣

ምድርን የሠራትና ያበጃት፣ አጽንቶም የመሠረታት፣+

መኖሪያ እንድትሆን እንጂ ለከንቱ* ያልፈጠራት+

ይሖዋ እንዲህ ይላልና፦

“እኔ ይሖዋ ነኝ፤ ከእኔም በቀር ሌላ የለም።

19 ስውር በሆነ ቦታ፣ ጨለማ በዋጠው ምድር አልተናገርኩም፤+

ለያዕቆብ ዘር

‘በከንቱ ፈልጉኝ’ አላልኩም።

እኔ ይሖዋ ጽድቅ የሆነውን እናገራለሁ፤ ቅን የሆነውንም አወራለሁ።+

20 ተሰብስባችሁ ኑ።

እናንተ ከብሔራት ያመለጣችሁ፣ በአንድነት ቅረቡ።+

የተቀረጹ ምስሎቻቸውን ተሸክመው የሚዞሩም ሆኑ

ሊያድናቸው ወደማይችል አምላክ የሚጸልዩ+ ምንም እውቀት የላቸውም።

21 ጉዳያችሁን ተናገሩ፤ እንዲሁም ሙግታችሁን አቅርቡ።

ተሰብስበው በአንድነት ይማከሩ።

ከረጅም ጊዜ በፊት ይህን አስቀድሞ የተናገረ ማን ነው?

ከጥንትስ ጀምሮ ይህን ያወጀ ማን ነው?

ይህን ያደረግኩት እኔ ይሖዋ አይደለሁም?

ከእኔ ሌላ አምላክ የለም፤

ከእኔ በቀር ጻድቅ አምላክና አዳኝ+ የሆነ ማንም የለም።+

22 የምድር ዳርቻዎች ሁሉ፣ ወደ እኔ ተመለሱ፤ ትድናላችሁ፤+

እኔ አምላክ ነኝና፤ ከእኔም በቀር ሌላ የለም።+

23 በራሴ ምያለሁ፤

ቃል ከአፌ በጽድቅ ወጥቷል፤

ደግሞም አይመለስም፦+

ጉልበት ሁሉ ለእኔ ይንበረከካል፤

ምላስም ሁሉ ታማኝ ለመሆን ይምላል፤+

24 እንዲህም ይላል፦ ‘በእርግጥም በይሖዋ ዘንድ እውነተኛ ጽድቅና ብርታት አለ።

በእሱ ላይ የተቆጡ ሁሉ ኀፍረት ተከናንበው ወደ እሱ ይመጣሉ።

25 የእስራኤል ዘር ሁሉ በይሖዋ ትክክለኛ ሆኖ ይገኛል፤+

በእሱም ይኮራል።’”

46 ቤል ያጎነብሳል፤+ ነቦ አንገቱን ይደፋል።

ጣዖቶቻቸው በደከሙ እንስሳት ላይ እንደሚጫን ከባድ ጭነት

በእንስሳት ይኸውም በጋማ ከብቶች ላይ ተጭነዋል።+

 2 አንገታቸውን ይደፋሉ፤ በአንድነት ያጎነብሳሉ፤

ጭነቱን* ማዳን አይችሉም፤

እነሱ ራሳቸውም ተማርከው ይወሰዳሉ።*

 3 “የያዕቆብ ቤት ሆይ፣ ከእስራኤልም ቤት የቀራችሁት ሁሉ፣+

ከተወለዳችሁበት ጊዜ አንስቶ የረዳኋችሁ፣ በማህፀን ከነበራችሁበት ጊዜም አንስቶ የተሸከምኳችሁ+ ስሙኝ።

 4 እስከ እርጅናችሁ ዘመን ድረስ እኔ ያው ነኝ፤+

ፀጉራችሁ እስኪሸብትም ድረስ እሸከማችኋለሁ።

ከዚህ ቀደም እንዳደረግኩት እሸከማችኋለሁ፣ እደግፋችኋለሁ እንዲሁም እታደጋችኋለሁ።+

 5 ከማን ጋር ታመሳስሉኛላችሁ? ከማንስ ጋር እኩል ታደርጉኛላችሁ?+

ወይስ እንመሳሰል ዘንድ ከማን ጋር ታነጻጽሩኛላችሁ?+

 6 ከኮሮጇቸው ወርቅ የሚዘረግፉ ሰዎች አሉ፤

ብሩን በሚዛን ይመዝናሉ።

አንጥረኛ ይቀጥራሉ፤ እሱም አምላክ አድርጎ ይሠራዋል።+

እነሱም በፊቱ ይደፋሉ፤ ደግሞም ያመልኩታል።*+

 7 አንስተው ትከሻቸው ላይ ያደርጉታል፤+

ተሸክመው ወስደው ቦታው ላይ ያኖሩታል፤ በዚያም ዝም ብሎ ይቆማል።

ካለበት ቦታ አይንቀሳቀስም።+

ወደ እሱ ይጮኻሉ፤ እሱ ግን አይመልስም፤

ማንንም ከጭንቀት ሊታደግ አይችልም።+

 8 ይህን አስታውሱ፤ ደግሞም አይዟችሁ።

እናንተ ሕግ ተላላፊዎች ይህን ልብ በሉ።

 9 ጥንት የተከናወኑትን የቀድሞዎቹን* ነገሮች፣

እኔ አምላክ* መሆኔንና ከእኔ ሌላ አምላክ እንደሌለ አስታውሱ።

እኔ አምላክ ነኝ፤ እንደ እኔም ያለ ማንም የለም።+

10 ከመጀመሪያ መጨረሻውን፣

ገና ያልተከናወኑትንም ነገሮች ከረጅም ጊዜ በፊት አስቀድሜ እናገራለሁ።+

እኔ ‘ውሳኔዬ* ይጸናል፤+

ደስ የሚያሰኘኝንም ነገር ሁሉ አደርጋለሁ’+ እላለሁ።

11 ከፀሐይ መውጫ* አዳኝ አሞራን፣+

ከሩቅ ምድርም ውሳኔዬን* የሚፈጽመውን ሰው እጠራለሁ።+

ተናግሬአለሁ፤ ደግሞም እፈጽመዋለሁ።

ይህን ለማድረግ አስቤአለሁ፤ አደርገዋለሁም።+

12 እናንተ ልበ ደንዳኖች፣*

እናንተ ከጽድቅ የራቃችሁ ሰዎች ስሙኝ።

13 ጽድቄን አምጥቻለሁ፤

ሩቅም አይደለም፤

ማዳኔም አይዘገይም።+

በጽዮን መዳን አስገኛለሁ፤ ለእስራኤልም ግርማዬን አጎናጽፋለሁ።”+

47 አንቺ ድንግል የባቢሎን ሴት ልጅ ሆይ፣+

ወርደሽ አፈር ላይ ተቀመጪ።

አንቺ የከለዳውያን ሴት ልጅ ሆይ፣

ዙፋን በሌለበት መሬት ላይ ተቀመጪ፤+

ከእንግዲህ ሰዎች ቅምጥልና ሞልቃቃ ብለው አይጠሩሽምና።

 2 ወፍጮ ወስደሽ እህል ፍጪ።

መሸፋፈኛሽን አንሺ።

ቀሚስሽን አውልቂ፤ ባትሽን ግለጪ።

ወንዞቹን ተሻገሪ።

 3 እርቃንሽ ይገለጣል።

ኀፍረትሽም ይታያል።

እኔ የበቀል እርምጃ እወስዳለሁ፤+ ማንም ሰው ሊያግደኝ አይችልም።*

 4 “እኛን የሚቤዠን

የእስራኤል ቅዱስ ነው፤+

ስሙም የሠራዊት ጌታ ይሖዋ ነው።”

 5 አንቺ የከለዳውያን ሴት ልጅ ሆይ፣

በዚያ ዝም ብለሽ ተቀመጪ፤ ወደ ጨለማም ግቢ፤+

ከእንግዲህ የመንግሥታት እመቤት* ብለው አይጠሩሽም።+

 6 ሕዝቤን ተቆጣሁ።+

ርስቴን አረከስኩ፤+

አሳልፌም በእጅሽ ሰጠኋቸው።+

አንቺ ግን ምሕረት አላሳየሻቸውም።+

በሽማግሌው ላይ እንኳ ሳይቀር ከባድ ቀንበር ጫንሽ።+

 7 አንቺም “ሁልጊዜ ብሎም ለዘላለም እመቤት* እሆናለሁ” አልሽ።+

እነዚህን ነገሮች ልብ አላልሽም፤

ነገሩ ምን ፍጻሜ እንደሚኖረው አላሰብሽም።

 8 በመሆኑም አንቺ ለሥጋዊ ደስታ ያደርሽ፣+

ተማምነሽ የተቀመጥሽና

በልብሽ “እኔ ነኝ፤ ከእኔም በቀር ሌላ የለም።+

መበለት አልሆንም።

በምንም ዓይነት የወላድ መሃን አልሆንም” የምትዪ ሴት ሆይ፣+ ይህን ስሚ።

 9 ሆኖም እነዚህ ሁለት ነገሮች ይኸውም

የወላድ መሃንነትና መበለትነት በአንድ ቀን በድንገት ይደርሱብሻል።+

በመተት ስለተሞላሽና ታላቅ ኃይል ባለው ድግምት ስለተዘፈቅሽ*+

እነዚህ ነገሮች ሁሉ በአንቺ ላይ ይደርሳሉ።+

10 አንቺ በክፋትሽ ታምነሻል።

“ማንም አያየኝም” ብለሻል።

ያሳቱሽ ጥበብሽና እውቀትሽ ናቸው፤

በልብሽም “እኔ ነኝ፤ ከእኔም በቀር ሌላ የለም” ትያለሽ።

11 ሆኖም ጥፋት ይመጣብሻል፤

ደግሞም ከዚህ ሊያስጥልሽ የሚችል ድግምት የለሽም።*

መከራ ይደርስብሻል፤ ልታስወግጂውም አትችዪም።

አይተሽው የማታውቂው ጥፋት በድንገት ይደርስብሻል።+

12 እንግዲያው ከልጅነትሽ ጀምሮ ስትደክሚበት የነበረውን

ድግምት ሁሉና ብዛት ያለው የጥንቆላ ድርጊት+ መፈጸምሽን ቀጥዪ።

ምናልባት ይጠቅምሽ ይሆናል፤

ሰዎችን ለማሸበር ይረዳሽ ይሆናል።

13 በመካሪዎችሽ ብዛት እጅግ ተዳክመሻል።

በሰማያት ያሉ ነገሮችን የሚያመልኩ፣* ከዋክብትን በትኩረት የሚመለከቱ፣+

አዲስ ጨረቃም ስትወጣ

በአንቺ ላይ ስለሚመጣው ነገር የሚተነብዩ ሰዎች፣

እስቲ አሁን ተነስተው ያድኑሽ።

14 እነሆ፣ እነሱ እንደ ገለባ ናቸው።

እሳት ያቃጥላቸዋል።

ራሳቸውን* ከነበልባሉ ኃይል ማዳን አይችሉም።

ይህ ሰዎች የሚሞቁት ፍምም ሆነ

በፊቱ ተቀምጠው የሚሞቁት እሳት አይደለም።

15 ከልጅነትሽ ጀምሮ አብረሻቸው ስትደክሚ የነበሩት

ድግምተኞች እንዲሁ ይሆኑብሻል።

እያንዳንዳቸው የመረጡትን አቅጣጫ ተከትለው ይባዝናሉ።*

አንቺን የሚያድን አይኖርም።+

48 እናንተ ራሳችሁን በእስራኤል ስም የምትጠሩ፣+

ከይሁዳ ምንጭ የፈለቃችሁ፣*

በእውነትና በጽድቅ ባይሆንም

በይሖዋ ስም የምትምሉና+

የእስራኤልን አምላክ የምትጠሩ

የያዕቆብ ቤት ሆይ፣ ይህን ስሙ።+

 2 እነሱ የቅድስቲቱ ከተማ ነዋሪ እንደሆኑ ይናገራሉና፤+

ስሙ የሠራዊት ጌታ ይሖዋ የሆነውን

የእስራኤልን አምላክ ድጋፍ ለማግኘት ይጥራሉ።+

 3 “ከብዙ ዘመን በፊት የቀድሞዎቹን* ነገሮች ነግሬአችኋለሁ።

ከአፌም ወጥተዋል፤

እንዲታወቁም አድርጌአለሁ።+

በድንገት እርምጃ ወሰድኩ፤ እነሱም ተፈጸሙ።+

 4 ምን ያህል ልበ ደንዳና እንደሆንክ፣

ይኸውም የአንገትህ ጅማት ብረት፣ ግንባርህም መዳብ መሆኑን ስለማውቅ፣+

 5 ከረጅም ጊዜ በፊት ነግሬሃለሁ።

‘ይህን ያደረገው የራሴ ጣዖት ነው፤

ይህን ያዘዘው የተቀረጸው ምስሌና ከብረት የተሠራው ምስሌ* ነው’ እንዳትል

ገና ከመፈጸሙ በፊት አሳውቄሃለሁ።

 6 አንተም ሰምተሃል፤ ደግሞም ይህን ሁሉ አይተሃል።

ይህን አታሳውቅም?*+

ከአሁን ጀምሮ አዳዲስ ነገሮችን፣

የማታውቃቸውን ጥብቅ ሚስጥሮች እነግርሃለሁ።+

 7 እነዚህ ነገሮች የተፈጠሩት ጥንት ሳይሆን ገና አሁን ነው፤

‘እነዚህንማ ከዚህ በፊት አውቃቸዋለሁ!’ እንዳትል፣

ከዛሬ በፊት ሰምተሃቸው አታውቅም።

 8 አዎ፣ አንተ አልሰማህም፤+ አላወቅክምም፤

ከዚህ በፊት ጆሮህ ክፍት አልነበረም።

በጣም አታላይ እንደሆንክና+

ከተወለድክበት ጊዜ ጀምሮ ዓመፀኛ ተብለህ እንደተጠራህ አውቃለሁና።+

 9 ይሁንና ስለ ስሜ ስል ቁጣዬን እቆጣጠራለሁ፤+

ስለ ውዳሴዬም ስል ራሴን እገታለሁ፤

ደግሞም አላጠፋህም።+

10 እነሆ፣ እንደ ብር ባይሆንም አንጥሬሃለሁ።+

እንደ ማቅለጫ ምድጃ ባለ መከራ ፈትኜሃለሁ።*+

11 ለራሴ ስል፣ አዎ ለራሴ ስል እርምጃ እወስዳለሁ፤+

ስሜ እንዲረክስ እንዴት እፈቅዳለሁ?+

ክብሬን ለማንም አልሰጥም።*

12 ያዕቆብ ሆይ፣ የጠራሁህም እስራኤል ሆይ፣ ስማኝ።

እኔ ምንጊዜም ያው ነኝ።+ የመጀመሪያው እኔ ነኝ፤ የመጨረሻውም እኔ ነኝ።+

13 የገዛ እጄ የምድርን መሠረት ጣለ፤+

ቀኝ እጄም ሰማያትን ዘረጋ።+

እነሱን ስጠራቸው በአንድነት ይቆማሉ።

14 ሁላችሁም አንድ ላይ ተሰብስባችሁ ስሙ።

ከመካከላቸው እነዚህን ነገሮች ያሳወቀ ማን ነው?

ይሖዋ ወዶታል።+

እሱ ደስ የሚያሰኘውን በባቢሎን ላይ ይፈጽማል፤+

ክንዱም በከለዳውያን ላይ ያርፋል።+

15 እኔ ራሴ ተናግሬአለሁ፤ እሱንም ጠርቼዋለሁ።+

አምጥቼዋለሁ፤ መንገዱም የተቃና ይሆናል።+

16 ወደ እኔ ቅረቡ፤ ደግሞም ይህን ስሙ።

ከመጀመሪያው አንስቶ በሚስጥር አልተናገርኩም።+

ከተፈጸመበት ጊዜ አንስቶ እኔ በዚያ ነበርኩ።”

አሁንም ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ፣ መንፈሱም * ልኮኛል።

17 የሚቤዥህ፣ የእስራኤል ቅዱስ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦+

“የሚጠቅምህን ነገር* የማስተምርህ፣+

ልትሄድበትም በሚገባህ መንገድ የምመራህ

እኔ ይሖዋ አምላክህ ነኝ።+

18 ትእዛዛቴን ብትሰማ ምንኛ መልካም ነው!+

እንዲህ ብታደርግ ሰላምህ እንደ ወንዝ፣+

ጽድቅህም እንደ ባሕር ሞገድ ይሆናል።+

19 ዘርህ እንደ አሸዋ፣

የአብራክህም ክፋዮች እንደ አሸዋ ቅንጣቶች ብዙ ይሆናሉ።+

ስማቸው ከፊቴ አይጠፋም ወይም አይደመሰስም።”

20 ከባቢሎን ውጡ!+

ከከለዳውያን ሽሹ!

ይህን በእልልታ አስታውቁ! አውጁትም!+

እስከ ምድር ዳርቻ እንዲሰማ አድርጉ።+

እንዲህም በሉ፦ “ይሖዋ አገልጋዩን ያዕቆብን ተቤዥቶታል።+

21 ባድማ በሆኑ ቦታዎች በመራቸው ጊዜ አልተጠሙም።+

ከዓለት ውስጥ ውኃ አፈለቀላቸው፤

ዓለቱን ሰንጥቆ ውኃ አንዶለዶለላቸው።”+

22 “ክፉዎች ሰላም የላቸውም” ይላል ይሖዋ።+

49 እናንተ ደሴቶች ስሙኝ፤

እናንተም በሩቅ ያላችሁ ብሔራት+ በጥሞና አዳምጡ።

ይሖዋ ከመወለዴ በፊት* ጠርቶኛል።+

በእናቴ ማህፀን ከነበርኩበት ጊዜ አንስቶ ስሜን ጠርቷል።

 2 አፌን እንደተሳለ ሰይፍ አደረገው፤

በእጁ ጥላ ሥር ሰወረኝ።+

የሾለ ፍላጻ አደረገኝ፤

በኮሮጆው ውስጥ ሸሸገኝ።

 3 እሱም “እስራኤል ሆይ፣ አንተ ግርማዬን የምገልጥብህ+

አገልጋዬ ነህ”+ አለኝ።

 4 እኔ ግን “የደከምኩት በከንቱ ነው።

ጉልበቴንም ያፈሰስኩት ከንቱ ለሆነና ምንም ፋይዳ ለሌለው ነገር ነው።

ሆኖም የሚዳኘኝ ይሖዋ ነው፤*

ደሞዜንም* የሚከፍለኝ አምላኬ ነው”+ አልኩ።

 5 የእሱ አገልጋይ እንድሆን ከማህፀን ጀምሮ የሠራኝ ይሖዋ፣

እስራኤል ወደ እሱ ይሰበሰብ ዘንድ

ያዕቆብን ወደ እሱ እንድመልስ አዞኛል።+

በይሖዋ ፊት እከብራለሁ፤

አምላኬም ብርታቴ ይሆናል።

 6 እንዲህም አለ፦ “የያዕቆብን ነገዶች ዳግመኛ ለማቋቋምና

ጥበቃ ያገኙትን እስራኤላውያን መልሰህ ለማምጣት

አገልጋዬ መሆንህ በቂ አይደለም።

የማዳን ሥራዬ እስከ ምድር ዳርቻ ይደርስ ዘንድ+

ለብሔራት ብርሃን አድርጌ ሰጥቼሃለሁ።”+

7 እስራኤልን የሚቤዠው፣ የእስራኤል ቅዱስ የሆነው ይሖዋ፣+ እጅግ ለተናቀውና*+ በሕዝብ ለተጠላው የገዢዎች አገልጋይ እንዲህ ይላል፦

“ታማኝ በሆነው በይሖዋ፣+

አንተንም በመረጠህ+ በእስራኤል ቅዱስ የተነሳ

ነገሥታት አይተው ይነሳሉ፤

መኳንንትም ይሰግዳሉ።”

 8 ይሖዋ እንዲህ ይላል፦

“ሞገስ* በማሳይበት ዘመን መልስ ሰጥቼሃለሁ፤+

በመዳንም ቀን ረድቼሃለሁ፤+

ለሰዎች ቃል ኪዳን አድርጌ እሰጥህ ዘንድ ጠብቄሃለሁ፤+

ይህም ምድሪቱን ዳግመኛ እንድታቋቁም፣

የወደመውን ርስታቸውን መልሰህ እንድታወርሳቸው፣+

 9 እስረኞቹን ‘ኑ ውጡ!’+

በጨለማ ያሉትንም+ ‘ራሳችሁን ግለጡ!’ እንድትል ነው።

በየመንገዱ ዳር ይመገባሉ፤

በተበላሹ መንገዶችም* ሁሉ አጠገብ መሰማሪያ ያገኛሉ።

10 አይራቡም፤ አይጠሙም፤+

ሐሩርም ሆነ ፀሐይ አያቃጥላቸውም።+

ምሕረት የሚያደርግላቸው ይመራቸዋልና፤+

የውኃ ምንጮች ወዳሉበትም ይወስዳቸዋል።+

11 ተራሮቼን ሁሉ መንገድ አደርጋለሁ፤

አውራ ጎዳናዎቼም ከፍ ያሉ ይሆናሉ።+

12 እነሆ፣ እነዚህ ከሩቅ ይመጣሉ፤+

እነሆም፣ እነዚህ ከሰሜንና ከምዕራብ፣

እነዚህ ደግሞ ከሲኒም ምድር ይመጣሉ።”+

13 እናንተ ሰማያት፣ እልል በሉ፤ አንቺም ምድር፣ ሐሴት አድርጊ።+

ተራሮች በደስታ እልል ይበሉ።+

ይሖዋ ሕዝቡን አጽናንቷልና፤+

ለተጎሳቆሉት ሕዝቦቹም ምሕረት ያሳያል።+

14 ጽዮን ግን “ይሖዋ ትቶኛል፤+

ይሖዋም ረስቶኛል”+ ትላለች።

15 እናት የምታጠባውን ልጇን ልትረሳ ትችላለች?

ከማህፀኗ ለወጣውስ ልጅ አትራራም?

እነዚህ ሴቶች ቢረሱ እንኳ እኔ ፈጽሞ አልረሳሽም።+

16 እነሆ፣ በእጄ መዳፍ ላይ ቀርጬሻለሁ።

ግንቦችሽ ምንጊዜም በፊቴ ናቸው።

17 ወንዶች ልጆችሽ ፈጥነው ይመለሳሉ።

ያፈራረሱሽና ያወደሙሽ አንቺን ለቀው ይሄዳሉ።

18 ዓይንሽን አንስተሽ ዙሪያሽን ተመልከቺ።

ሁሉም በአንድነት እየተሰበሰቡ ነው።+

ወደ አንቺም እየመጡ ነው።

“በሕያውነቴ እምላለሁ” ይላል ይሖዋ፣

“አንቺም ሁሉንም እንደ ጌጥ ትለብሻቸዋለሽ፤

እንደ ሙሽራም ትጎናጸፊያቸዋለሽ።

19 ስፍራዎችሽ ባድማና ወና፣ ምድርሽም የወደመ ቢሆንም+

አሁን በዚያ የሚኖሩ ሰዎች ቦታው በጣም ይጠባቸዋል፤+

የዋጡሽም+ ከአንቺ ይርቃሉ።+

20 የወላድ መሃን ከሆንሽ በኋላ የተወለዱት ወንዶች ልጆች፣

ጆሮሽ እየሰማ ‘ይህ ቦታ በጣም ጠቦናል።

የምንኖርበት በቂ ስፍራ ስጪን’ ይላሉ።+

21 አንቺም በልብሽ እንዲህ ትያለሽ፦

‘እኔ ልጆቼን በሞት ያጣሁና መሃን

እንዲሁም በምርኮ የተወሰድኩና እስረኛ የሆንኩ ሴት ሆኜ ሳለ

እነዚህን ልጆች የወለደልኝ ማን ነው?

ያሳደጋቸውስ ማን ነው?+

እነሆ፣ እኔ ብቻዬን ቀርቼ ነበር፤+

ታዲያ እነዚህ ከየት መጡ?’”+

22 ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦

“እነሆ፣ እጄን ለብሔራት አነሳለሁ፤

ምልክቴንም * ለሕዝቦች ከፍ አደርጋለሁ።+

ወንዶች ልጆችሽን በክንዳቸው* ይዘው ያመጧቸዋል፤

ሴቶች ልጆችሽንም በትከሻቸው ይሸከሟቸዋል።+

23 ነገሥታት ይንከባከቡሻል፤+

ልዕልቶቻቸውም ሞግዚቶችሽ ይሆናሉ።

በግንባራቸው ተደፍተው ይሰግዱልሻል፤+

የእግርሽንም አቧራ ይልሳሉ፤+

አንቺም እኔ ይሖዋ እንደሆንኩ ታውቂያለሽ፤

እኔን ተስፋ የሚያደርጉ አያፍሩም።”+

24 በምርኮ የተያዙ ሰዎች ከኃያል ሰው እጅ ሊወሰዱ ይችላሉ?

ወይስ በጨቋኝ እጅ የወደቁ ምርኮኞችን የሚታደጋቸው ይኖራል?

25 ይሖዋ ግን እንዲህ ይላል፦

“በኃያል ሰው የተማረኩ ሰዎችም እንኳ ከእጁ ላይ ይወሰዳሉ፤+

በጨቋኝ እጅ የወደቁ ሰዎችንም የሚታደጋቸው ይኖራል።+

አንቺን የሚቃወሙትን እቃወማለሁ፤+

ወንዶች ልጆችሽንም አድናቸዋለሁ።

26 በደል የሚፈጽሙብሽን የገዛ ሥጋቸውን እንዲበሉ አደርጋቸዋለሁ፤

ልክ እንደ ጣፋጭ ወይን ጠጅ የገዛ ደማቸውን ጠጥተው ይሰክራሉ።

ሰውም* ሁሉ እኔ ይሖዋ

አዳኝሽና+ የምቤዥሽ፣+

የያዕቆብም ኃያል አምላክ እንደሆንኩ ያውቃል።”+

50 ይሖዋ እንዲህ ይላል፦

“እናታችሁን በሰደድኳት ጊዜ የፍቺ የምሥክር ወረቀት+ ሰጥቻታለሁ?

እናንተንስ የሸጥኳችሁ ለየትኛው አበዳሪዬ ነው?

እነሆ፣ የተሸጣችሁት በገዛ ጥፋታችሁ+ ነው፤

እናታችሁም እንድትሄድ የተደረገው በገዛ በደላችሁ ነው።+

 2 ታዲያ በመጣሁ ጊዜ እዚህ ማንም ያልነበረው ለምንድን ነው?

በተጣራሁስ ጊዜ የሚመልስ ሰው የጠፋው ለምንድን ነው?+

እጄ አጭር ሆና እናንተን መዋጀት ተስኗታል?

ወይስ እናንተን ለመታደግ የሚያስችል ኃይል የለኝም?+

እነሆ፣ በተግሣጼ ባሕሩን አደርቃለሁ፤+

ወንዞችን በረሃ አደርጋለሁ።+

ዓሣዎቻቸው ውኃ ባለማግኘታቸው ይበሰብሳሉ፤

በውኃ ጥምም ይሞታሉ።

 3 ሰማያትን ጨለማ አለብሳለሁ፤+

ማቅንም መሸፈኛቸው አደርጋለሁ።”

 4 ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ፣ ለደከመው ትክክለኛውን ቃል በመናገር

እንዴት መልስ* መስጠት እንደምችል አውቅ ዘንድ+ የተማሩ ሰዎችን አንደበት* ሰጥቶኛል።+

በየማለዳው ያነቃኛል፤

እንደ ተማሪ አዳምጥ ዘንድ ጆሮዬን ያነቃል።+

 5 ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ ጆሮዬን ከፍቷል፤

እኔም ዓመፀኛ አልነበርኩም።+

ጀርባዬን አልሰጠሁም።+

 6 ለሚገርፉኝ ጀርባዬን፣

ጢም ለሚነጩም ጉንጮቼን ሰጠሁ።

ፊቴን፣ ከሚያዋርዱ ነገሮችና ከትፋት አልሰወርኩም።+

 7 ሆኖም ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ ይረዳኛል።+

ስለዚህ አልዋረድም።

ከዚህም የተነሳ ፊቴን እንደ ባልጩት አደረግኩ፤+

ለኀፍረት እንደማልዳረግም አውቃለሁ።

 8 ጻድቅ መሆኔን የሚመሠክርልኝ ቀርቧል።

ታዲያ ማን ሊከሰኝ* ይችላል?+

በአንድነት እንቁም።*

ከእኔ ጋር ሙግት ያለው ማን ነው?

እስቲ ወደ እኔ ይቅረብ።

 9 እነሆ፣ ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ ይረዳኛል።

ታዲያ ጥፋተኛ ነህ ሊለኝ የሚችል ማን ነው?

እነሆ፣ ሁሉም እንደ ልብስ ያረጃሉ።

ብል ይበላቸዋል።

10 ከመካከላችሁ ይሖዋን የሚፈራ፣

የአገልጋዩንም ድምፅ የሚሰማ ማን ነው?+

ብርሃን በሌለበት በድቅድቅ ጨለማ የሄደ ማን ነው?

በይሖዋ ስም ይታመን፤ በአምላኩም ይደገፍ።*

11 “እነሆ፣ እናንተ እሳት የምታያይዙ፣

የእሳት ፍንጣሪ የምታበሩ ሁሉ፣

በእሳታችሁ ብርሃን፣

ባያያዛችሁትም እሳት ብልጭታዎች መካከል ሂዱ።

ከእጄ የምትቀበሉት ይህ ነው፦

በከባድ ሥቃይ ትጋደማላችሁ።

51 “እናንተ ጽድቅን የምትከታተሉ፣

ይሖዋንም የምትፈልጉ ስሙኝ።

ተፈልፍላችሁ የወጣችሁበትን ዓለት፣

ተቆፍራችሁ የወጣችሁበትንም ካባ ተመልከቱ።

 2 አባታችሁን አብርሃምን፣

የወለደቻችሁንም* ሣራን+ ተመልከቱ።

እሱ በጠራሁት ጊዜ ብቻውን ነበርና፤+

እኔም ባረክሁት፤ ደግሞም አበዛሁት።+

 3 ይሖዋ ጽዮንን ያጽናናታልና።+

ፍርስራሾቿን ሁሉ ያጽናናል፤+

ምድረ በዳዋንም እንደ ኤደን፣+

በረሃማ ሜዳዋንም እንደ ይሖዋ የአትክልት ስፍራ ያደርጋል።+

በእሷም ውስጥ ሐሴትና ታላቅ ደስታ

እንዲሁም ምስጋናና ደስ የሚያሰኝ መዝሙር ይገኛሉ።+

 4 ሕዝቤ ሆይ፣ በጥሞና አዳምጡኝ፤

አንተም የእኔ ብሔር፣ ጆሮህን ስጠኝ።+

ሕግ ከእኔ ይወጣልና፤+

የፍትሕ እርምጃዬም ለሕዝቦች እንደ ብርሃን ጸንቶ እንዲቆም አደርጋለሁ።+

 5 ጽድቄ ቀርቧል።+

ማዳኔ ወደ እናንተ ይመጣል፤+

ክንዴም በሕዝቦች ላይ ይፈርዳል።+

ደሴቶች በእኔ ተስፋ ያደርጋሉ፤+

ክንዴንም* ይጠባበቃሉ።

 6 ዓይኖቻችሁን ወደ ሰማያት አንሱ፤

ወደታችም ወደ ምድር ተመልከቱ።

ሰማያት እንደ ጭስ በነው ይጠፋሉና፤

ምድርም እንደ ልብስ ታረጃለች፤

ነዋሪዎቿም እንደ ትንኝ ይረግፋሉ።

ማዳኔ ግን ለዘላለም ይኖራል፤+

ጽድቄም ፈጽሞ አይከስምም።*+

 7 እናንተ ጽድቅን የምታውቁ፣

ሕጌንም* በልባችሁ ያኖራችሁ ሰዎች፣+ ስሙኝ።

ሟች የሆኑ ሰዎች የሚሰነዝሩትን ትችት አትፍሩ፤

ስድባቸውም አያሸብራችሁ።

 8 ብል እንደ ልብስ ይበላቸዋልና፤

የልብስ ብል* እንደ ሱፍ ጨርቅ ይበላቸዋል።+

ሆኖም ጽድቄ ለዘላለም፣

ማዳኔም ከትውልድ እስከ ትውልድ ይኖራል።”+

 9 የይሖዋ ክንድ ሆይ፣+

ተነስ! ተነስ! ብርታትንም ልበስ!

ከረጅም ጊዜ በፊት፣ በጥንቶቹ ትውልዶች ዘመን እንደሆነው ተነስ።

ረዓብን*+ ያደቀከው፣

ግዙፉንም የባሕር ፍጥረት የወጋኸው አንተ አይደለህም?+

10 ባሕሩን፣ የተንጣለለውን የጥልቁን ውኃ ያደረቅከው አንተ አይደለህም?+

የተቤዠሃቸው ሰዎች እንዲሻገሩ ጥልቁን ባሕር መንገድ ያደረግከው አንተ አይደለህም?+

11 ይሖዋ የዋጃቸው ይመለሳሉ።+

በእልልታ ወደ ጽዮን ይመጣሉ፤+

ማብቂያ የሌለውንም ደስታ እንደ አክሊል ይጎናጸፋሉ።+

ሐሴት ያደርጋሉ፤ ታላቅ ደስታም ያገኛሉ፤

ሐዘንና ሲቃም ከእነሱ ይሸሻሉ።+

12 “የማጽናናችሁ እኔ ራሴ ነኝ።+

ሟች የሆነውን ሰው፣

እንደ ሣርም የሚጠወልገውን የሰው ልጅ የምትፈሪው ለምንድን ነው?+

13 ሰማያትን የዘረጋውንና+ የምድርን መሠረት የጣለውን

ሠሪህን ይሖዋን+ የምትረሳው ለምንድን ነው?

ደግሞም ጨቋኙ* ሊያጠፋህ የተዘጋጀ ይመስል

ከእሱ ቁጣ የተነሳ ቀኑን ሙሉ በፍርሃት ተውጠህ ነበር።

ታዲያ አሁን የጨቋኙ ቁጣ የት አለ?

14 በሰንሰለት ታስሮ ያጎነበሰው እስረኛ ቶሎ ይፈታል፤+

ሞትን አያይም፤ ወደ ጉድጓድም አይወርድም፤

የሚበላውም ነገር አያጣም።

15 ባሕሩን የማናውጥና ኃይለኛ ማዕበል የማስነሳ፣+

እኔ ይሖዋ አምላክህ ነኝ፤

ስሙ የሠራዊት ጌታ ይሖዋ ነው።+

16 ሰማያትን እዘረጋና የምድርን መሠረት እጥል ዘንድ፣+

ጽዮንንም ‘አንቺ ሕዝቤ ነሽ’+ እል ዘንድ

ቃሌን በአፍህ አኖራለሁ፤

በእጄም ጥላ እጋርድሃለሁ።+

17 ከይሖዋ እጅ የቁጣውን ጽዋ የጠጣሽ

ኢየሩሳሌም ሆይ፣ ተነሺ! ተነሺ! ቁሚ።+

ዋንጫውን ጠጥተሻል፤

የሚያንገዳግደውን ጽዋ ጨልጠሻል።+

18 ከወለደቻቸው ወንዶች ልጆች ሁሉ መካከል አንድም የሚመራት የለም፤

ካሳደገቻቸውም ወንዶች ልጆች ሁሉ መካከል እጇን ይዞ የወሰዳት ማንም የለም።

19 እነዚህ ሁለት ነገሮች ደርሰውብሻል።

ማን ያስተዛዝንሻል?

ጥፋትና ውድመት እንዲሁም ረሃብና ሰይፍ መጥቶብሻል!+

ማንስ ያጽናናሻል?+

20 ወንዶች ልጆችሽ ራሳቸውን ስተዋል።+

በመረብ እንደተያዘ የዱር በግ

በየመንገዱ ማዕዘን ላይ* ይተኛሉ።

የይሖዋ ቁጣ፣ የአምላክሽም ተግሣጽ ሙሉ በሙሉ ወርዶባቸዋል።”

21 ስለዚህ አንቺ የተጎሳቆልሽና ያለወይን ጠጅ የሰከርሽ ሴት ሆይ፣

እባክሽ ይህን ስሚ።

22 ለሕዝቡ የሚሟገተው ጌታሽና አምላክሽ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦

“እነሆ፣ የሚያንገዳግደውን ጽዋ፣+ ይኸውም ዋንጫውን፣

የቁጣዬን ጽዋ ከእጅሽ እወስዳለሁ፤

ከእንግዲህ ዳግመኛ አትጠጪም።+

23 ጽዋውን ‘በላይሽ ላይ እንድንሻገር አጎንብሺልን!’ ባሉሽ፣*

አንቺን በሚያሠቃዩት እጅ ላይ አደርገዋለሁ፤+

አንቺም ጀርባሽን እንደ መሬት፣

እንደሚሄዱበትም መንገድ አደረግሽላቸው።”

52 ጽዮን ሆይ፣+ ተነሺ! ተነሺ! ብርታትን ልበሺ!+

ቅድስቲቱ ከተማ ኢየሩሳሌም ሆይ፣ የሚያምሩ ልብሶችሽን ልበሺ!+

ከእንግዲህ ወዲህ ያልተገረዘና ርኩስ የሆነ ወደ አንቺ አይገባምና።+

 2 ኢየሩሳሌም ሆይ፣ አቧራሽን አራግፊ፤ ተነስተሽ ቦታሽን ያዢ።

ምርኮኛ የሆንሽው የጽዮን ሴት ልጅ ሆይ፣ አንገትሽ ላይ ያለውን ማሰሪያ ፍቺ።+

 3 ይሖዋ እንዲህ ይላልና፦

“ያለዋጋ ተሸጣችሁ ነበር፤+

ያለገንዘብም ትቤዣላችሁ።”+

 4 ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላልና፦

“በመጀመሪያ ሕዝቤ ባዕድ ሆኖ ለመኖር ወደ ግብፅ ወረደ፤+

ከዚያም አሦር ያላንዳች ምክንያት በጭቆና ገዛው።”

 5 “ታዲያ እዚህ ምን ማድረግ ይኖርብኛል?” ይላል ይሖዋ።

“ሕዝቤ የተወሰደው ያለዋጋ ነውና።

የሚገዟቸው በድል አድራጊነት ጉራ ይነዛሉ”+ ይላል ይሖዋ፤

“ስሜንም ቀኑን ሙሉ ያለማቋረጥ ያቃልላሉ።+

 6 በዚህ ምክንያት ሕዝቤ ስሜን ያውቃል፤+

በዚህም የተነሳ የተናገርኩት እኔ እንደሆንኩ በዚያ ቀን ያውቃሉ።

እነሆ፣ እኔ ነኝ!”

 7 ምሥራች ይዞ የሚመጣ፣+

ሰላምን የሚያውጅ፣+

የተሻለ ነገር እንደሚመጣ ምሥራች የሚያበስር፣

መዳንን የሚያውጅ፣

ጽዮንንም “አምላክሽ ነግሦአል!”+ የሚል በተራሮች ላይ እግሮቹ እንዴት ያማሩ ናቸው!

 8 ስሚ! ጠባቂዎችሽ ድምፃቸውን ከፍ ያደርጋሉ።

በአንድነት ሆነው እልል ይላሉ፤

ይሖዋ ጽዮንን መልሶ ሲሰበስብ በግልጽ* ያያሉና።

 9 እናንተ የኢየሩሳሌም ፍርስራሾች፣ ደስ ይበላችሁ፤ በአንድነትም እልል በሉ፤+

ይሖዋ ሕዝቡን አጽናንቷልና፤+ ኢየሩሳሌምንም ተቤዥቷል።+

10 ይሖዋ በብሔራት ሁሉ ፊት ቅዱስ ክንዱን ገልጧል፤+

የምድር ዳርቻዎችም ሁሉ የአምላካችንን የማዳን ሥራዎች* ያያሉ።+

11 እናንተ የይሖዋን ዕቃ የምትሸከሙ፣+

ገለል በሉ፣ ገለል በሉ፤ ከዚያ ውጡ፤+ ማንኛውንም ርኩስ ነገር አትንኩ!+

ከመካከሏ ውጡ፤+ ንጽሕናችሁን ጠብቁ።

12 ተደናግጣችሁ አትወጡም፤

ሸሽታችሁም አትሄዱም፤

ይሖዋ በፊታችሁ ይሄዳልና፤+

የእስራኤል አምላክም ደጀን ይሆናችኋል።+

13 እነሆ፣ አገልጋዬ+ ማንኛውንም ነገር የሚያከናውነው በጥልቅ ማስተዋል ነው።

ላቅ ያለ ቦታ ይሰጠዋል፤

ከፍ ከፍ ይላል፤ እጅግም ይከበራል።+

14 ብዙዎች በመገረም ትኩር ብለው እንዳዩት ሁሉ፣

(መልኩ ከማንኛውም ሰው የባሰ፣

ግርማ የተላበሰ ቁመናውም ከሰው ልጆች ሁሉ ይልቅ ተጎሳቁሎ ነበር)

15 እሱም ብዙ ብሔራትን+ ያስደንቃል።

ነገሥታት በእሱ ፊት አፋቸውን ይዘጋሉ፤*+

ምክንያቱም ያልተነገራቸውን ያያሉ፤

ወዳልሰሙትም ነገር ትኩረታቸውን ያዞራሉ።+

53 ከእኛ የሰማውን* ነገር ያመነ ማን ነው?+

የይሖዋስ ክንድ+ ለማን ተገለጠ?+

 2 እሱ በፊቱ* እንደ ቅርንጫፍ፣+ በደረቅ ምድር እንዳለ ሥር ይበቅላል።

የሚያምር ቁመናም ሆነ ግርማ ሞገስ የለውም፤+

ባየነውም ጊዜ መልኩ አልሳበንም።*

 3 ሰዎች የናቁትና ያገለሉት፣+

ሥቃይን ያየ፣* ሕመምንም የሚያውቅ ሰው ነበር።

ፊቱ የተሰወረብን ያህል ነበር።*

ሰዎች ናቁት፤ እኛም ከቁብ አልቆጠርነውም።+

 4 በእርግጥም እሱ ራሱ ሕመማችንን ተሸከመ፤+

ሥቃያችንንም ተቀበለ።+

እኛ ግን እንደተቀሰፈ፣ በአምላክ እንደተመታና እንደተጎሳቆለ አድርገን ቆጠርነው።

 5 እሱ ግን ስለ መተላለፋችን+ ተወጋ፤+

ስለ በደላችን ደቀቀ።+

በእሱ ላይ የደረሰው ቅጣት ለእኛ ሰላም አስገኘልን፤+

በእሱም ቁስል የተነሳ እኛ ተፈወስን።+

 6 ሁላችንም እንደ በጎች ተቅበዘበዝን፤+

እያንዳንዳችን በየራሳችን መንገድ ሄድን፤

ይሖዋም የሁላችንንም በደል እሱ እንዲሸከም አደረገ።+

 7 ግፍ ተፈጸመበት፤+ መከራም ለመቀበል ፈቃደኛ ሆነ፤+

ነገር ግን አፉን አልከፈተም።

እንደ በግ ለመታረድ ተነዳ፤+

በሸላቾቿ ፊት ዝም እንደምትል በግ፣

እሱም አፉን አልከፈተም።+

 8 ፍትሕ ተነፈገ፤* በአግባቡም ሳይዳኝ ተወሰደ፤

ትኩረት ሰጥቶ ትውልዱን በዝርዝር ለማወቅ* የሚሞክር ማን ነው?

ከሕያዋን ምድር ተወግዷልና፤+

በሕዝቤ መተላለፍ የተነሳ ተመታ።*+

 9 ምንም ዓይነት በደል* አልፈጸመም፤

እንዲሁም ከአንደበቱ የማታለያ ቃል አልወጣም፤+

ሆኖም በሚሞትበት ጊዜ የመቃብር ቦታው

ከክፉዎችና+ ከሀብታሞች*+ ጋር ይሆናል።*

10 ይሁንና እሱን ማድቀቅ የይሖዋ ፈቃድ ነበር፤* ለሕመም እንዲዳረግም ፈቅዷል።

ሕይወቱን* የበደል መባ አድርገህ የምታቀርበው ከሆነ+

ዘሩን ያያል፤ ዘመኑን ያስረዝማል፤+

እንዲሁም በእሱ አማካኝነት ይሖዋ ደስ የሚሰኝበት ነገር* ይከናወናል።+

11 በእሱ ላይ ከደረሰው ሥቃይ* የተነሳ፣ በሚያየው መልካም ነገር ይደሰታል።

ጻድቅ አገልጋዬ+ በእውቀቱ አማካኝነት

ብዙ ሰዎች ጻድቅ ሆነው እንዲቆጠሩ ይረዳል፤+

በደላቸውንም ይሸከማል።+

12 ስለዚህ ከብዙዎች ጋር ድርሻውን እሰጠዋለሁ፤

ምርኮውን ከኃያላን ጋር ይካፈላል፤

ሕይወቱን* እስከ ሞት ድረስ አፍስሷልና፤+

ከሕግ ተላላፊዎችም ጋር ተቆጥሯል፤+

የብዙ ሰዎችን ኃጢአት ተሸክሟል፤+

ስለ ሕግ ተላላፊዎችም ማልዷል።+

54 “አንቺ ያልወለድሽ መሃን ሴት፣ እልል በይ!+

አንቺ አምጠሽ የማታውቂ ሴት፣+ ደስ ይበልሽ፤ በደስታም ጩኺ፤+

የተተወችው ሴት ወንዶች ልጆች፣*

ባል ካላት ሴት* ወንዶች ልጆች ይልቅ በዝተዋልና”+ ይላል ይሖዋ።

 2 “የድንኳንሽን ቦታ አስፊ።+

ታላቅ የሆነውን የማደሪያ ድንኳንሽን ሸራዎች ዘርጊ።

ፈጽሞ አትቆጥቢ፤ የድንኳንሽን ገመዶች አስረዝሚ፤

ካስማዎችሽንም አጠንክሪ።+

 3 በቀኝም ሆነ በግራ ትስፋፊያለሽና።

ዘሮችሽ ብሔራትን ይወርሳሉ፤

ባድማ በሆኑትም ከተሞች ውስጥ ይኖራሉ።+

 4 ኀፍረት ስለማይደርስብሽ+ አትፍሪ፤+

ለሐዘን ስለማትዳረጊም አትሸማቀቂ።

በልጅነትሽ ዘመን የደረሰብሽን ኀፍረት ትረሺዋለሽና፤

መበለትነትሽ ያስከተለብሽን ውርደትም ከእንግዲህ አታስታውሽም።”

 5 “ታላቁ ሠሪሽ+ ባልሽ* ነውና፤+

ስሙም የሠራዊት ጌታ ይሖዋ ነው፤

የሚቤዥሽም+ የእስራኤል ቅዱስ ነው።

እሱም የምድር ሁሉ አምላክ ተብሎ ይጠራል።+

 6 ይሖዋ የተተወችና በሐዘን የተደቆሰች* ሚስት፣+

ደግሞም በልጅነቷ አግብታ፣ ከጊዜ በኋላ የተጠላች ሚስት እንደሆንሽ ቆጥሮ ጠርቶሻልና” ይላል አምላክሽ።

 7 “ለአጭር ጊዜ ተውኩሽ፤

ሆኖም በታላቅ ምሕረት መልሼ እሰበስብሻለሁ።+

 8 በቁጣ ጎርፍ ለጥቂት ጊዜ ፊቴን ከአንቺ ሰውሬ ነበር፤+

ሆኖም በዘላለማዊ ታማኝ ፍቅር ምሕረት አሳይሻለሁ”+ ይላል የሚቤዥሽ+ ይሖዋ።

 9 “ይህ ለእኔ እንደ ኖኅ ዘመን ነው።+

የኖኅ ውኃ ምድርን ዳግመኛ አያጥለቀልቅም ብዬ እንደማልኩ ሁሉ+

አንቺንም ከእንግዲህ ላለመቆጣትም ሆነ ላለመገሠጽ እምላለሁ።+

10 ተራሮች ከቦታቸው ሊወገዱ፣

ኮረብቶችም ሊናወጡ ይችላሉ፤

ይሁንና ታማኝ ፍቅሬ ከአንቺ አይለይም፤+

የሰላም ቃል ኪዳኔም አይናጋም”+ ይላል ምሕረት የሚያሳይሽ ይሖዋ።+

11 “አንቺ የተጎሳቆልሽ፣+ በአውሎ ነፋስ የተናወጥሽና ማጽናኛ ያላገኘሽ ሴት ሆይ፣+

እነሆ ድንጋዮችሽን በኃይለኛ ማጣበቂያ እገነባለሁ፤

መሠረትሽንም በሰንፔር እሠራለሁ።+

12 መጠበቂያ ማማዎችሽን በሩቢ ድንጋዮች፣

የከተማሽንም በሮች በሚያብረቀርቁ ድንጋዮች፣*

ወሰኖችሽንም ሁሉ በከበሩ ድንጋዮች እሠራለሁ።

13 ልጆችሽም* ሁሉ ከይሖዋ የተማሩ ይሆናሉ፤+

የልጆችሽም* ሰላም ብዙ ይሆናል።+

14 በጽድቅ ጽኑ ሆነሽ ትመሠረቺያለሽ።+

ጭቆና ከአንቺ ይርቃል፤+

ምንም ነገር አትፈሪም፤ የሚያሸብርሽም ነገር አይኖርም፤

ወደ አንቺ አይቀርብምና።+

15 ማንም ጥቃት ቢሰነዝርብሽ

እኔ አዝዤው አይደለም።

ጥቃት የሚሰነዝርብሽ ሁሉ ከአንቺ የተነሳ ይወድቃል።”+

16 “እነሆ፣ የከሰል እሳቱን በወናፍ የሚያናፋውን

የእጅ ጥበብ ባለሙያ የፈጠርኩት እኔ ነኝ፤

የሚያከናውነውም ሥራ የጦር መሣሪያ ያስገኛል።

ደግሞም ጥፋት እንዲያደርስ አጥፊውን ሰው የፈጠርኩት እኔ ራሴ ነኝ።+

17 አንቺን ለማጥቃት የተሠራ ማንኛውም መሣሪያ ይከሽፋል፤+

አንቺን ለመክሰስ የሚነሳን ምላስ ሁሉ ትፈርጂበታለሽ።

የይሖዋ አገልጋዮች ውርሻ* ይህ ነው፤

ጽድቃቸውም ከእኔ ዘንድ ነው” ይላል ይሖዋ።+

55 እናንተ የተጠማችሁ ሁሉ+ ኑ፤ ወደ ውኃው ኑ!+

እናንተ ገንዘብ የሌላችሁ ኑና ገዝታችሁ ብሉ!

አዎ፣ ኑና ያለገንዘብ፣ ያለዋጋም የወይን ጠጅና ወተት+ ግዙ።+

 2 ምግብ ላልሆነ ነገር ለምን ገንዘባችሁን ታወጣላችሁ?

እርካታ ለማያስገኝ ነገርስ ለምን ገቢያችሁን* ታባክናላችሁ?

እኔን በጥሞና አዳምጡ፤ መልካም የሆነውንም ብሉ፤+

ምርጥ ምግብ በመብላትም* ሐሴት ታደርጋላችሁ።*+

 3 ጆሯችሁን አዘንብሉ፤ ወደ እኔም ኑ።+

አዳምጡ፤ በሕይወትም ትኖራላችሁ፤*

ለዳዊት ካሳየሁት የማይከስም * ታማኝ ፍቅር+ ጋር በሚስማማ ሁኔታ

ከእናንተ ጋር የዘላለም ቃል ኪዳን አደርጋለሁ።+

 4 እነሆ፣ ለብሔራት ምሥክር፣+

መሪና+ አዛዥ+ አድርጌዋለሁ።

 5 እነሆ፣ የማታውቀውን ብሔር ትጠራለህ፤

የማያውቅህ ብሔርም ለአምላክህ ለይሖዋና ለእስራኤል ቅዱስ ሲል

ወደ አንተ ሮጦ ይመጣል፤+

ምክንያቱም እሱ ክብር ያጎናጽፍሃል።+

 6 ይሖዋን በሚገኝበት ጊዜ ፈልጉት።+

በቅርብም ሳለ ጥሩት።+

 7 ክፉ ሰው መንገዱን፣

መጥፎ ሰውም ሐሳቡን ይተው፤+

ምሕረት ወደሚያሳየው አምላካችን ወደ ይሖዋ ይመለስ፤+

ይቅርታው ብዙ ነውና።*+

 8 “ሐሳቤ እንደ ሐሳባችሁ፣

መንገዳችሁም እንደ መንገዴ አይደለምና”+ ይላል ይሖዋ።

 9 “ሰማያት ከምድር ከፍ እንደሚሉ

መንገዴ ከመንገዳችሁ፣

ሐሳቤም ከሐሳባችሁ ከፍ ያለ ነው።+

10 ዝናብና በረዶ ከሰማይ እንደሚወርድ፣

ምድርን በማራስ እንድታበቅልና እንድታፈራ፣

ለዘሪው ዘርን፣ ለበላተኛውም ምግብን እንድትሰጥ ሳያደርግ ወደመጣበት እንደማይመለስ ሁሉ፣

11 ከአፌ የሚወጣውም ቃሌ እንዲሁ ይሆናል።+

ደስ የሚያሰኘኝን ነገር* ያደርጋል፣+

የተላከበትንም ዓላማ በእርግጥ ይፈጽማል እንጂ

ያላንዳች ውጤት ወደ እኔ አይመለስም።+

12 በታላቅ ደስታ ትወጣላችሁና፤+

በሰላምም ትመለሳላችሁ።+

ተራሮቹና ኮረብቶቹ በደስታ በፊታችሁ እልል ይላሉ፤+

የሜዳም ዛፎች ሁሉ ያጨበጭባሉ።+

13 በቁጥቋጦ ፋንታ የጥድ ዛፍ ይበቅላል፤+

በሳማም ፋንታ የአደስ ዛፍ ይበቅላል።

የይሖዋ ስም እንዲገን ያደርጋል፤*+

እንዲሁም ፈጽሞ የማይጠፋ የዘላለም ምልክት ይሆናል።”

56 ይሖዋ እንዲህ ይላል፦

“ፍትሕን ጠብቁ፤+ ጽድቅ የሆነውንም አድርጉ፤

ማዳኔ በቅርቡ ይመጣልና፤

ጽድቄም ይገለጣል።+

 2 ይህን የሚያደርግ ሰው፣

ደግሞም ይህን አጥብቆ የሚይዝ፣

ሰንበትን የሚጠብቅና የማያረክስ፣+

እንዲሁም ከማንኛውም ዓይነት ክፋት እጁን የሚመልስ የሰው ልጅ ደስተኛ ነው።

 3 ከይሖዋ ጋር የሚቆራኝ የባዕድ አገር ሰው+

‘ይሖዋ ከሕዝቡ እንደሚለየኝ ጥርጥር የለውም’ አይበል።

ጃንደረባም ‘እነሆ፣ እኔ ደረቅ ዛፍ ነኝ’ አይበል።”

4 ይሖዋ እንዲህ ይላልና፦ “ሰንበቶቼን ለሚጠብቁ፣ ደስ የሚያሰኘኝን ነገር ለሚመርጡና ቃል ኪዳኔን አጥብቀው ለሚይዙ ጃንደረቦች፣

 5 በቤቴና በቅጥሮቼ ውስጥ

ከወንዶችና ከሴቶች ልጆች የሚሻል ነገር፣

ይኸውም የመታሰቢያ ሐውልትና ስም እሰጣቸዋለሁ።

ለዘላለም የማይጠፋ ስም እሰጣቸዋለሁ።

 6 እሱን ለማገልገል፣ የይሖዋን ስም ለመውደድና

የእሱ አገልጋዮች ለመሆን

ከይሖዋ ጋር የሚቆራኙትን የባዕድ አገር ሰዎች፣+

ሰንበትን የሚጠብቁትንና የማያረክሱትን፣

ቃል ኪዳኔንም አጥብቀው የሚይዙትን ሁሉ፣

 7 ቅዱስ ወደሆነው ተራራዬ አመጣቸዋለሁ፤+

በጸሎት ቤቴም ውስጥ እጅግ እንዲደሰቱ አደርጋቸዋለሁ።

የሚያቀርቧቸውም ሙሉ በሙሉ የሚቃጠሉ መባዎችና መሥዋዕቶች በመሠዊያዬ ላይ ተቀባይነት ያገኛሉ።

ቤቴም ለሕዝቦች ሁሉ የጸሎት ቤት ተብሎ ይጠራልና።”+

8 የተበተኑትን የእስራኤል ሰዎች የሚሰበስበው ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ+ እንዲህ ይላል፦

“አስቀድሞ ከተሰበሰቡት በተጨማሪ ሌሎችን ወደ እሱ እሰበስባለሁ።”+

 9 እናንተ በሜዳ ያላችሁ አራዊት ሁሉ፣

እናንተ በጫካ የምትኖሩ አራዊት ሁሉ፣ ኑና ብሉ።+

10 ጠባቂዎቹ ዕውሮች ናቸው፤+ አንዳቸውም አላስተዋሉም።+

ሁሉም መናገር የማይችሉ ውሾች ናቸው፤ መጮኽ አይችሉም።+

ተጋድመው ያለከልካሉ፤ እንቅልፍም ይወዳሉ።

11 በቀላሉ የማይጠግቡ* ውሾች ናቸው፤

ጠገብኩ ማለትን አያውቁም።

ማስተዋል የሌላቸው እረኞች ናቸው።+

ሁሉም በገዛ ራሳቸው መንገድ ሄደዋል፤

እያንዳንዳቸው አግባብ ያልሆነ ጥቅም ለማግኘት ይሻሉ፤ እንዲህም ይላሉ፦

12 “ኑ! የወይን ጠጅ ላምጣና

እስኪወጣልን ድረስ እንጠጣ።+

ነገም እንደ ዛሬ ይሆናል፤ እንዲያውም በጣም የተሻለ ይሆናል።”

57 ጻድቁ ሞቷል፤

ይህን ግን ማንም ልብ አይልም።

ታማኝ ሰዎች ተወስደዋል፤*+

ሆኖም ጻድቁ የተወሰደው

ከመከራ የተነሳ እንደሆነ* የሚያስተውል የለም።

 2 እሱ ሰላም ያገኛል።

በቅንነት የሚሄዱ ሁሉ አልጋቸው* ላይ ያርፋሉ።

 3 “ይሁንና እናንተ የአስማተኛዋ ወንዶች ልጆች፣

የአመንዝራና የዝሙት አዳሪ ልጆች፣

ኑ ወደዚህ ቅረቡ፦

 4 የምታሾፉት በማን ላይ ነው?

አፋችሁን የምትከፍቱትና ምላሳችሁን የምታወጡትስ በማን ላይ ነው?

እናንተ የዓመፅ ልጆች፣

የሐሰትም* ልጆች አይደላችሁም?+

 5 በትላልቅ ዛፎች መካከል፣

ቅጠሉ በተንዠረገገም ዛፍ ሥር ሁሉ በስሜት የተቃጠላችሁ፣+

በሸለቆዎች* ውስጥ፣ በቋጥኞች መካከል

ልጆችን የምታርዱ አይደላችሁም?+

 6 በሸለቆው* ውስጥ ያሉት ለስላሳ ድንጋዮች ድርሻዎችሽ ናቸው።+

አዎ፣ እነዚህ ዕጣ ፋንታዎችሽ ናቸው።

ለእነሱም ጭምር የመጠጥ መባ አፍስሰሻል፤ ስጦታም አቅርበሻል።+

ታዲያ እኔ በእነዚህ ነገሮች ደስ ልሰኝ ይገባል?*

 7 በረጅሙና ከፍ ባለው ተራራ ላይ አልጋሽን አነጠፍሽ፤+

መሥዋዕት ለማቅረብም ወደዚያ ወጣሽ።+

 8 ከበሩና ከመቃኑ ጀርባ የመታሰቢያ ምልክትሽን አደረግሽ።

እኔን ተውሽኝ፤ እርቃንሽንም ገለጥሽ፤

ወደ ላይ ወጣሽ፤ መኝታሽንም አሰፋሽ።

ከእነሱም ጋር ቃል ኪዳን ገባሽ።

በአልጋቸው ላይ አብረሽ መተኛት ወደድሽ፤+

የወንድ ብልትም* አፍጥጠሽ አየሽ።

 9 ዘይትና ብዛት ያለው ሽቶ ይዘሽ

ወደ ሜሌክ* ወረድሽ።

መልእክተኞችሽን ወደ ሩቅ ቦታ ላክሽ፤

በመሆኑም ወደ መቃብር* ወረድሽ።

10 ብዛት ያላቸውን መንገዶችሽን በመከተል ደከምሽ፤

ሆኖም ‘ተስፋ የለውም!’ አላልሽም።

ጉልበትሽ ታደሰ።

ተስፋ ያልቆረጥሽው* ለዚህ ነው።

11 መዋሸት የጀመርሽው+ ማን አስፈርቶሽ፣

ማንስ ስጋት አሳድሮብሽ ነው?

እኔን አላስታወስሽም።+

ልብ ያልሽውም ነገር የለም።+

እኔ ዝም አላልኩም? ደግሞስ ከመናገር አልተቆጠብኩም?*+

በመሆኑም እኔን አልፈራሽም።

12 ‘ጽድቅሽን’+ እና ሥራሽን+ እናገራለሁ፤

እነሱም አይጠቅሙሽም።+

13 እርዳታ ለማግኘት በምትጮኺበት ጊዜ

የሰበሰብሻቸው ጣዖቶች አይታደጉሽም።+

ነፋስ ሁሉንም ጠራርጎ ይወስዳቸዋል፤

እስትንፋስ ይዟቸው ይሄዳል፤

እኔን መጠጊያ የሚያደርግ ግን ምድሪቱን ይወርሳል፤

ቅዱስ ተራራዬም ርስቱ ይሆናል።+

14 እንዲህ ይባላል፦ ‘መንገድ ሥሩ! መንገድ ሥሩ! መንገዱን አዘጋጁ!+

ሕዝቤ ከሚሄድበት መንገድ ላይ ማንኛውንም እንቅፋት አስወግዱ።’”

15 ለዘላለም የሚኖረውና+ ስሙ ቅዱስ የሆነው፣+

ከፍ ከፍ ያለውና እጅግ የከበረው እንዲህ ይላልና፦

“ከፍ ባለውና ቅዱስ በሆነው ስፍራ እኖራለሁ፤+

ደግሞም የተሰበረ ልብ ካለውና መንፈሱ ከተደቆሰው ጋር እሆናለሁ፤

ይህም የችግረኞችን መንፈስ አነሳሳ ዘንድ፣

የተሰበረ ልብ ያላቸውንም አነቃቃ ዘንድ ነው።+

16 ለዘላለም አልቃወማቸውም፤

ወይም ለዘለቄታው አልቆጣም፤+

በእኔ የተነሳ የሰው መንፈስ፣

እኔ የሠራኋቸው እስትንፋስ ያላቸው ፍጥረታትም እንኳ ይዝላሉና።+

17 በማጭበርበር ጥቅም ለማግኘት ሲል በፈጸመው ኃጢአት እጅግ ተቆጣሁ፤+

በመሆኑም መታሁት፤ ፊቴን ሰወርኩ፤ ተቆጣሁም።

እሱ ግን እንደ ከዳተኛ የልቡን መንገድ ተከትሎ መሄዱን ገፋበት።+

18 መንገዶቹን አይቻለሁ፤

ሆኖም እፈውሰዋለሁ፤+ እንዲሁም እመራዋለሁ፤+

ለእሱም ሆነ ላዘኑ ወገኖቹ መጽናኛን እመልሳለሁ።”*+

19 “የከንፈሮችን ፍሬ እፈጥራለሁ።

በሩቅም ሆነ በቅርብ ያለው ዘላቂ ሰላም ያገኛል፤+

እኔም እፈውሰዋለሁ” ይላል ይሖዋ።

20 “ክፉዎች ግን ጸጥ ማለት እንደማይችል የሚናወጥ ባሕር ናቸው፤

ውኃውም የባሕር ውስጥ ዕፀዋትንና ጭቃን ያወጣል።

21 ክፉዎች ሰላም የላቸውም” ይላል አምላኬ።+

58 “ጉሮሮህ እስኪሰነጠቅ ጩኽ፤ ምንም አትቆጥብ!

ድምፅህን እንደ ቀንደ መለከት አሰማ።

ለሕዝቤ ዓመፃቸውን፣

ለያዕቆብ ቤት ኃጢአታቸውን አውጅ።+

 2 እነሱ በየዕለቱ እኔን ይፈልጉኛል፤

ጽድቅ ይሠራ የነበረ፣

የአምላኩንም ፍትሕ ያልተወ ብሔር የሆኑ ይመስል+

መንገዶቼን ማወቅ ደስ እንደሚያሰኛቸው ይገልጻሉ።

በጽድቅ እንድፈርድላቸው ይጠይቃሉ፤

ወደ አምላክ መቅረብ ደስ ያሰኛቸዋል፦+

 3 ‘ስንጾም የማታየው ለምንድን ነው?+

ራሳችንን* ስናጎሳቁል የማታስተውለውስ ለምንድን ነው?’+

በምትጾሙበት ቀን የራሳችሁን ጥቅም* ስለምታሳድዱና

ሠራተኞቻችሁን ስለምትጨቁኑ ነው።+

 4 ጾማችሁ በጭቅጭቅና በጥል ያበቃል፤

እንዲሁም ያለርኅራኄ በቡጢ ትማታላችሁ።

ዛሬ እንደምትጾሙት እየጾማችሁ ድምፃችሁ በሰማይ ሊሰማ አይችልም።

 5 እኔ የመረጥኩት ጾም እንዲህ ሊሆን ይገባል?

ሰው ራሱን* የሚያጎሳቁልበት፣

እንደ እንግጫ ራሱን የሚደፋበት፣

መኝታውን በማቅና በአመድ ላይ የሚያነጥፍበት ቀን መሆን አለበት?

እናንተ ጾም የምትሉት፣ ይሖዋንም ደስ የሚያሰኝ ቀን ብላችሁ የምትጠሩት ይህን ነው?

 6 አይደለም፤ እኔ የመረጥኩት ጾም ይህ ነው፦

የክፋትን የእግር ብረት እንድታስወግዱ፣

የቀንበርን ማሰሪያ እንድትፈቱ፣+

የተጨቆኑትን በነፃ እንድትለቁ፣+

ቀንበርንም ሁሉ እንድትሰብሩ ነው፤

 7 ምግብህን ለተራበው እንድታካፍል፣+

ድሆችንና ቤት የሌላቸውን ወደ ቤትህ እንድታስገባ፣

የተራቆተ ሰው ስታይ እንድታለብስ፣+

ለሥጋ ዘመድህም ጀርባህን እንዳትሰጥ ነው።

 8 በዚህ ጊዜ ብርሃንህ እንደ ንጋት ጮራ ይፈነጥቃል፤+

ፈውስህም ፈጥኖ ይመጣል።

ጽድቅህም በፊትህ ይሄዳል፤

የይሖዋም ክብር ደጀን ይሆንልሃል።+

 9 የዚያን ጊዜ ትጣራለህ፤ ይሖዋም ይመልስልሃል፤

እርዳታ ለማግኘት ትጮኻለህ፤ እሱም ‘አለሁልህ!’ ይልሃል።

ከመካከልህ ቀንበሩን ብታስወግድ

እንዲሁም ጣትህን መቀሰርና ተንኮል ያዘለ ንግግር መናገር ብትተው፣+

10 ለተራበው ሰው አንተ ራስህ* የምትፈልገውን ነገር ብታደርግለት፣+

የተጎሳቆሉትንም ብታረካ፣*

ያን ጊዜ ብርሃንህ በጨለማ እንኳ ቦግ ብሎ ይበራል፤

ጨለማህም እንደ ቀትር ብርሃን ይሆናል።+

11 ይሖዋ ምንጊዜም ይመራሃል፤

ደረቅ በሆነ ምድርም እንኳ ፍላጎትህን ያረካል፤*+

አጥንቶችህን ያበረታል፤

አንተም ውኃ እንደሚጠግብ የአትክልት ቦታና

ውኃው እንደማይቋረጥ ምንጭ ትሆናለህ።+

12 ከአንተም የተነሳ የጥንቶቹን ፍርስራሾች መልሰው ይገነባሉ፤+

ያለፉትን ትውልዶች መሠረቶች ታድሳለህ።+

አንተም የፈረሱትን* ግንቦች የሚያድስ፣

በመኖሪያ ቦታዎች አካባቢ የሚገኙ ጎዳናዎችን የሚጠግን ተብለህ ትጠራለህ።+

13 ሰንበትን በማክበር በተቀደሰው ቀኔ የራስህን ጥቅም* ከማሳደድ ብትቆጠብ፣*+

ሰንበትንም ሐሴት፣ የተቀደሰ የይሖዋ ቀንና ሊከበር የሚገባው ቀን ብለህ ብትጠራው+

እንዲሁም የራስህን ጥቅም ከማሳደድና ከንቱ ቃል ከመናገር ይልቅ ብታከብረው፣

14 ያን ጊዜ በይሖዋ ሐሴት ታደርጋለህ፤

ደግሞም በምድር ከፍ ያሉ ቦታዎች ላይ እንድትጋልብ አደርግሃለሁ።+

ከአባትህ ከያዕቆብ ርስት አበላሃለሁ፤*+

የይሖዋ አፍ ተናግሯልና።”

59 እነሆ፣ የይሖዋ እጅ ማዳን ይሳናት ዘንድ አላጠረችም፤+

ጆሮውም መስማት ይሳናት ዘንድ አልደነዘዘችም።*+

 2 ከዚህ ይልቅ ከአምላካችሁ ያለያያችሁ የገዛ በደላችሁ ነው።+

የፈጸማችሁት ኃጢአት ፊቱን እንዲሰውርባችሁ አድርጎታል፤

እናንተን ለመስማትም ፈቃደኛ አይደለም።+

 3 እጆቻችሁ በደም፣

ጣቶቻችሁም በበደል ተበክለዋልና።+

ከንፈሮቻችሁ ውሸት ይናገራሉ፤+ አንደበታችሁም ክፋትን ያጉተመትማል።

 4 ጽድቅን የሚጣራ ማንም የለም፤+

እውነትን ይዞ ፍርድ ቤት የሚቀርብ የለም።

በማይጨበጥ* ነገር ይታመናሉ፤+ ፍሬ ቢስ ነገሮችን ይናገራሉ።

ችግርን ይፀንሳሉ፤ የሚጎዳ ነገርም ይወልዳሉ።+

 5 የመርዘኛ እባብን እንቁላሎች ይቀፈቅፋሉ፤

የሸረሪት ድርም ያደራሉ።+

እንቁላሎቻቸውንም የሚበላ ሁሉ ይሞታል፤

እንቁላሉም ሲሰበር እፉኝት ይወጣል።

 6 የሸረሪት ድራቸው ልብስ ሆኖ አያገለግልም፤

በሚሠሩትም ነገር ራሳቸውን መሸፈን አይችሉም።+

ሥራቸው ጉዳት የሚያስከትል ነው፤

በእጃቸውም የዓመፅ ሥራ አለ።+

 7 እግሮቻቸው ክፋት ለመፈጸም ይሮጣሉ፤

ንጹሕ ደም ለማፍሰስም ይጣደፋሉ።+

የሚያስቡት ጎጂ ሐሳብ ነው፤

በመንገዳቸው ላይ ጥፋትና መከራ አለ።+

 8 የሰላምን መንገድ አያውቁም፤

በጎዳናቸውም ፍትሕ የለም።+

መንገዳቸውን ጠማማ ያደርጋሉ፤

በዚያም የሚሄድ ሁሉ ሰላምን አያውቅም።+

 9 ከዚህ የተነሳ ፍትሕ ከእኛ ራቀ፤

ጽድቅም ወደ እኛ አይደርስም።

ብርሃን ይሆናል ብለን በተስፋ ተጠባበቅን፤ ሆኖም ጨለማ ሆነ፤

ጸዳልን ተጠባበቅን፤ ሆኖም በጨለማ እንመላለሳለን።+

10 ልክ እንደ ዓይነ ስውራን ቅጥሩን እየዳበስን እንሄዳለን፤

ዓይን እንደሌላቸው ሰዎች እንደናበራለን።+

በምሽት ጨለማ እንደሚሆነው በቀትር ብርሃን እንሰናከላለን፤

በብርቱ ሰዎች መካከል እንደ ሙታን ነን።

11 ሁላችንም እንደ ድቦች እናጉረመርማለን፤

እንደ ርግቦችም በሐዘን እናልጎመጉማለን።

ፍትሕን በተስፋ ተጠባበቅን፤ ነገር ግን አላገኘንም፤

መዳንን ተጠባበቅን፤ ነገር ግን ከእኛ ርቋል።

12 ዓመፃችን በፊትህ በዝቷልና፤+

የሠራነው ኃጢአት ሁሉ ይመሠክርብናል።+

ዓመፃችን ከእኛ ጋር ነውና፤

በደላችንን በሚገባ እናውቃለን።+

13 ሕግ ተላልፈናል፤ ይሖዋንም ክደናል፤

ለአምላካችን ጀርባችንን ሰጥተናል።

ግፍንና ዓመፅን ተናግረናል፤+

በልባችን ውሸትን ፀንሰናል፤ እንዲሁም የሐሰት ቃላትን አጉተምትመናል።+

14 ፍትሕ ወደ ኋላ ተመልሷል፤+

ጽድቅም በሩቅ ቆሟል፤+

እውነት* በአደባባይ ተሰናክሏልና፤

ቀና የሆነውም ነገር ወደዚያ መግባት አልቻለም።

15 እውነት* ጠፍቷል፤+

ከክፋት የራቀ ሁሉ ለጥፋት ተዳርጓል።

ይሖዋ ይህን አየ፤ ደስም አልተሰኘም፤*

ፍትሕ አልነበረምና።+

16 እርዳታ የሚሰጥ ሰው እንደሌለ አየ፤

ጣልቃ የሚገባ ባለመኖሩም ተገረመ፤

በመሆኑም የገዛ ክንዱ መዳን አስገኘ፤*

የገዛ ጽድቁም ድጋፍ ሆነለት።

17 ከዚያም ጽድቅን እንደ ጥሩር ለበሰ፤

በራሱም ላይ የመዳንን* ቁር አደረገ።+

የበቀልንም ልብስ ለበሰ፤+

ቅንዓትንም እንደ ካባ* ተጎናጸፈ።

18 ላደረጉት ነገር ብድራት ይከፍላቸዋል፦+

ቁጣን ለባላጋራዎቹ፣ በቀልን ለጠላቶቹ ይከፍላል።+

ለደሴቶችም የሚገባቸውን ዋጋ ይከፍላቸዋል።

19 በፀሐይ መግቢያ ያሉ የይሖዋን ስም ይፈራሉ፤

በፀሐይ መውጫም ያሉ ክብሩን ይፈራሉ፤

እሱ የይሖዋ መንፈስ እንደሚነዳው

ኃይለኛ ወንዝ ሆኖ ይመጣልና።

20 “ጽዮንን፣ በደል መፈጸም ያቆሙትንም

የያዕቆብ ቤት ሰዎች የሚቤዥ+ ይመጣል”+ ይላል ይሖዋ።+

21 “በእኔ በኩል ከእነሱ ጋር የገባሁት ቃል ኪዳን ይህ ነው”+ ይላል ይሖዋ። “በአንተ ላይ ያለው መንፈሴና በአፍህ ያኖርኩት ቃሌ፣ ከአንተ አፍ ወይም ከልጆችህ* አፍ ወይም ከልጅ ልጆችህ* አፍ ከአሁን ጀምሮ ለዘላለም አይወሰዱም” ይላል ይሖዋ።

60 “አንቺ ሴት ሆይ፣ ተነሺ፣+ ብርሃን አብሪ፤ ብርሃንሽ መጥቷልና።

የይሖዋ ክብር በአንቺ ላይ ያበራል።+

 2 እነሆ፣ ጨለማ ምድርን፣

ድቅድቅ ጨለማም ብሔራትን ይሸፍናል፤

በአንቺ ላይ ግን ይሖዋ ያበራል፤

ክብሩም በአንቺ ላይ ይታያል።

 3 ብሔራት ወደ ብርሃንሽ፣+

ነገሥታትም+ አንጸባራቂ ወደሆነው ውበትሽ* ይመጣሉ።+

 4 ዓይንሽን አንስተሽ ዙሪያሽን ተመልከቺ!

ሁሉም አንድ ላይ ተሰብስበዋል፤ ወደ አንቺም እየመጡ ነው።

ከሩቅ ቦታ ወንዶች ልጆችሽ በመምጣት ላይ ናቸው፤+

ሴቶች ልጆችሽም ታዝለው እየመጡ ነው።+

 5 በዚያን ጊዜ ታያለሽ፤ ፊትሽም ይፈካል፤+

ልብሽ በኃይል ይመታል፤ በደስታም ይሞላል፤

ምክንያቱም የባሕር ብልጽግና ወደ አንቺ ይጎርፋል፤

የብሔራትም ሀብት ወደ አንቺ ይመጣል።+

 6 የግመል መንጋ ምድርሽን ይሸፍናል፤*

የምድያምና የኤፋ+ ግልገል ግመሎች ያጥለቀልቁሻል።

ሁሉም ወርቅና ነጭ ዕጣን ይዘው

ከሳባ ይመጣሉ።

የይሖዋንም ውዳሴ ያውጃሉ።+

 7 የቄዳር+ መንጎች ሁሉ ወደ አንቺ ይሰበሰባሉ።

የነባዮት+ አውራ በጎች ያገለግሉሻል።

እነሱም በመሠዊያዬ ላይ ተቀባይነት ያለው መሥዋዕት ይሆናሉ፤+

ክብራማ የሆነውንም ቤቴን* አሳምረዋለሁ።+

 8 እንደ ደመና፣ ወደ ቤታቸውም* እንደሚተሙ ርግቦች

እየበረሩ የሚመጡት እነዚህ እነማን ናቸው?

 9 ደሴቶች እኔን ተስፋ ያደርጋሉና፤+

የተርሴስ መርከቦችም ከሩቅ ወንዶች ልጆችሽን

ከነብራቸውና ከነወርቃቸው

ለአምላክሽ ለይሖዋ ስምና ለእስራኤል ቅዱስ ለማምጣት+

ቀዳሚ ሆነው* ይወጣሉ፤

እሱ ክብር* ያጎናጽፍሻልና።+

10 የባዕድ አገር ሰዎች ቅጥሮችሽን ይገነባሉ፤

ነገሥታታቸውም ያገለግሉሻል፤+

በቁጣዬ መትቼሻለሁና፤

በሞገሴ* ግን ምሕረት አሳይሻለሁ።+

11 በሮችሽ ሁልጊዜ ክፍት ይሆናሉ፤+

የብሔራትን ሀብት ወደ አንቺ ያመጡ ዘንድ

በሮችሽ ቀንም ሆነ ሌሊት አይዘጉም፤

ነገሥታታቸውም ቀዳሚ ይሆናሉ።+

12 አንቺን የማያገለግል ማንኛውም ብሔርም ሆነ ማንኛውም መንግሥት ይጠፋልና፤

ብሔራትም ፈጽመው ይደመሰሳሉ።+

13 የመቅደሴን ስፍራ አስውብ ዘንድ

የሊባኖስ ክብር፣+ ጥዱ፣ የአሽ ዛፉና* የፈረንጅ ጥዱ

በአንድነት ወደ አንቺ ይመጣሉ፤+

እግሬ የሚያርፍበትንም ስፍራ አከብራለሁ።+

14 የጨቋኞችሽ ወንዶች ልጆች መጥተው በፊትሽ ይሰግዳሉ፤

የሚያዋርዱሽ ሁሉ እግርሽ ሥር ይደፋሉ፤

ደግሞም የይሖዋ ከተማ፣

የእስራኤልም ቅዱስ አምላክ ንብረት የሆንሽ ጽዮን ብለው ይጠሩሻል።+

15 የተተውሽና የተጠላሽ፣ ማንም ሰው የማያልፍብሽ መሆንሽ ቀርቶ+

የዘላለም መኩሪያ፣

ከትውልድ እስከ ትውልድም የደስታ ምንጭ እንድትሆኚ አደርግሻለሁ።+

16 አንቺም የብሔራትን ወተት ትጠጫለሽ፤+

የነገሥታትን ጡት ትጠቢያለሽ፤+

እኔ ይሖዋ አዳኝሽ እንደሆንኩ፣

ደግሞም የያዕቆብ ኃያል አምላክ የሆንኩት እኔ እንደምቤዥሽ በእርግጥ ታውቂያለሽ።+

17 በመዳብ ፋንታ ወርቅ፣

በብረት ፋንታ ብር፣

በእንጨት ፋንታ መዳብ፣

በድንጋዮችም ፋንታ ብረት አመጣለሁ፤

ሰላምንም የበላይ ተመልካቾችሽ፣

ጽድቅንም አሠሪዎችሽ አድርጌ እሾማለሁ።+

18 ከዚህ በኋላ በምድርሽ ውስጥ ዓመፅ፣

ወይም በክልልሽ ውስጥ ጥፋትና ውድመት አይሰማም።+

ቅጥሮችሽን መዳን፣+ በሮችሽንም ውዳሴ ብለሽ ትጠሪያቸዋለሽ።

19 ከእንግዲህ ፀሐይ በቀን ብርሃን አትሆንልሽም፤

የጨረቃም ብርሃን ከእንግዲህ አያበራልሽም፤

ይሖዋ የዘላለም ብርሃን፣+

አምላክሽም ውበት ይሆንልሻልና።+

20 ፀሐይሽ ከእንግዲህ አትጠልቅም፤

ጨረቃሽም አትደበዝዝም፤

ይሖዋ የዘላለም ብርሃን ይሆንልሻልና፤+

የሐዘንሽም ጊዜ ያበቃል።+

21 ሕዝቦችሽም ሁሉ ጻድቃን ይሆናሉ፤

ምድሪቱን ለዘላለም ይወርሳሉ።

እነሱ፣ ውበት እጎናጸፍ ዘንድ የተከልኳቸው ችግኞች፣

የእጆቼም ሥራ ናቸው።+

22 ጥቂት የሆነው ሺህ፣

ትንሽ የሆነውም ኃያል ብሔር ይሆናል።

እኔ ይሖዋ፣ ይህን በራሱ ጊዜ አፋጥነዋለሁ።”

61 የሉዓላዊው ጌታ የይሖዋ መንፈስ በእኔ ላይ ነው፤+

ምክንያቱም ይሖዋ የዋህ ለሆኑ ሰዎች ምሥራች እንድናገር ቀብቶኛል።+

ልባቸው የተሰበረውን እንድጠግን፣

ለተማረኩት ነፃነትን እንዳውጅ

እንዲሁም ‘የእስረኞች ዓይን ይከፈታል’ ብዬ እንድናገር ልኮኛል፤+

 2 ይሖዋ በጎ ፈቃድ* የሚያሳይበትን ዓመት፣

አምላካችን የሚበቀልበትንም ቀን እንዳውጅ፣+

የሚያለቅሱትንም ሁሉ እንዳጽናና ልኮኛል፤+

 3 በጽዮን የተነሳ ላዘኑት

በአመድ ፋንታ የራስ መሸፈኛ፣

በሐዘን ፋንታ የደስታ ዘይት፣

በተደቆሰም መንፈስ ፋንታ የውዳሴ ልብስ እንድሰጥ ልኮኛል።

እነሱም ይሖዋ ራሱን ክብር ለማጎናጸፍ*

የተከላቸው ትላልቅ የጽድቅ ዛፎች ተብለው ይጠራሉ።+

 4 የጥንቶቹን ፍርስራሾች መልሰው ይገነባሉ፤

በቀድሞዎቹ ጊዜያት ባድማ የሆኑትን ቦታዎች ይሠራሉ፤+

የወደሙትን ከተሞች፣

ከትውልድ እስከ ትውልድም ፈራርሰው የቆዩትን ቦታዎች መልሰው ይገነባሉ።+

 5 “እንግዳ ሰዎች መጥተው መንጎቻችሁን ይጠብቃሉ፤

የባዕድ አገር ሰዎችም+ ገበሬዎቻችሁና የወይን አትክልት ሠራተኞቻችሁ ይሆናሉ።+

 6 እናንተም የይሖዋ ካህናት ተብላችሁ ትጠራላችሁ፤+

የአምላካችን አገልጋዮች ብለው ይጠሯችኋል።

የብሔራትን ሀብት ትበላላችሁ፤+

በእነሱም ክብር* ትኮራላችሁ።

 7 በኀፍረት ፋንታ እጥፍ ድርሻ ይኖራችኋል፤

በውርደትም ፋንታ በሚያገኙት ድርሻ በደስታ እልል ይላሉ።

አዎ፣ በምድራቸው እጥፍ ድርሻ ይወርሳሉ።+

የዘላለም ሐሴት የእነሱ ይሆናል።+

 8 እኔ ይሖዋ ፍትሕን እወዳለሁና፤+

ዝርፊያንና ክፋትን እጠላለሁ።+

ደሞዛቸውን በታማኝነት እሰጣቸዋለሁ፤

ከእነሱም ጋር ዘላለማዊ ቃል ኪዳን አደርጋለሁ።+

 9 ዘሮቻቸው በብሔራት፣

ልጆቻቸውም በሕዝቦች መካከል የታወቁ ይሆናሉ።+

የሚያዩአቸው ሁሉ

ይሖዋ የባረካቸው ዘሮች እንደሆኑ ይገነዘባሉ።”+

10 እኔ በይሖዋ እጅግ ደስ ይለኛል።

ሁለንተናዬ በአምላኬ ሐሴት ያደርጋል።*+

የመዳንን መጎናጸፊያ አልብሶኛልና፤+

የካህን ዓይነት ጥምጥም+ እንደሚያደርግ ሙሽራ፣

በጌጣጌጧም ራሷን እንዳስዋበች ሙሽሪት

የጽድቅ ቀሚስ አልብሶኛል።

11 ምድር ቡቃያዋን እንደምታበቅል፣

የአትክልት ቦታም በላዩ ላይ የተዘሩትን ዘሮች እንደሚያበቅል

ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋም

በብሔራት ሁሉ ፊት ጽድቅንና+ ውዳሴን ያበቅላል።+

62 ጽድቋ እንደ ደማቅ ብርሃን እስኪፈነጥቅ፣+

መዳኗም እንደ ችቦ እስኪቀጣጠል ድረስ

ለጽዮን ስል ጸጥ አልልም፤+

ለኢየሩሳሌምም ስል ዝም ብዬ አልቀመጥም።+

 2 “አንቺ ሴት ሆይ፣+ ብሔራት ጽድቅሽን፣

ነገሥታትም ሁሉ ክብርሽን ያያሉ።+

አንቺም የይሖዋ አፍ በሚያወጣልሽ

አዲስ ስም ትጠሪያለሽ።+

 3 በይሖዋ እጅ የውበት ዘውድ፣

በአምላክሽ መዳፍ የንጉሥ ጥምጥም ትሆኛለሽ።

 4 ከእንግዲህ የተተወች ሴት አትባዪም፤+

ምድርሽም ከእንግዲህ ባድማ ተብላ አትጠራም።+

ከዚህ ይልቅ “ደስታዬ በእሷ ነው” ተብለሽ ትጠሪያለሽ፤+

ምድርሽም “ያገባች ሴት” ትባላለች።

ይሖዋ በአንቺ ደስ ይለዋልና፤

ምድርሽም እንዳገባች ሴት ትሆናለች።

 5 አንድ ወጣት ድንግሊቱን እንደሚያገባ፣

ወንዶች ልጆችሽ አንቺን ያገባሉ።

አንድ ሙሽራ በሙሽራይቱ ሐሴት እንደሚያደርግ፣

አምላክሽም በአንቺ ሐሴት ያደርጋል።+

 6 ኢየሩሳሌም ሆይ፣ በቅጥሮችሽ ላይ ጠባቂዎች አቁሜአለሁ።

ቀኑንም ሆነ ሌሊቱን በሙሉ፣ መቼም ቢሆን ዝም ሊሉ አይገባም።

እናንተ ስለ ይሖዋ የምትናገሩ፣

ፈጽሞ አትረፉ፤

 7 ደግሞም ኢየሩሳሌምን አጽንቶ እስኪመሠርታት፣

አዎ፣ የምድር ምስጋና እስኪያደርጋት ድረስ ምንም እረፍት አትስጡት።”+

 8 ይሖዋ በቀኝ እጁ፣ ብርቱ በሆነውም ክንዱ እንዲህ ሲል ምሏል፦

“ከእንግዲህ እህልሽን ለጠላቶችሽ መብል እንዲሆን አልሰጥም፤

የደከምሽበትንም አዲስ የወይን ጠጅ የባዕድ አገር ሰዎች አይጠጡትም።+

 9 ሆኖም እህሉን፣ የሚሰበስቡት ሰዎች ይበሉታል፤ ይሖዋንም ያወድሳሉ፤

ወይኑንም፣ የሚለቅሙት ሰዎች ቅዱስ በሆኑት ቅጥር ግቢዎቼ ውስጥ ይጠጡታል።”+

10 በበሮቹ በኩል እለፉ፤ እለፉ።

ለሕዝቡ መንገዱን ጥረጉ።+

ሥሩ፤ አውራ ጎዳናውን ሥሩ።

ድንጋዮቹን አስወግዱ።+

ለሕዝቦችም ምልክት* አቁሙ።+

11 እነሆ፣ ይሖዋ እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ አውጇል፦

“ለጽዮን ሴት ልጅ

‘እነሆ፣ መዳንሽ ቀርቧል።+

እነሆ፣ የሚከፍለው ወሮታ ከእሱ ጋር ነው፤

የሚመልሰውም ብድራት በፊቱ አለ’ በሏት።”+

12 ቅዱስ ሕዝብ፣ ይሖዋ የተቤዣቸው+ ተብለው ይጠራሉ፤

አንቺም “እጅግ የምትፈለግ፣” “ያልተተወች ከተማ” ተብለሽ ትጠሪያለሽ።+

63 ይህ ከኤዶም የሚመጣው፣+

ደማቅ ቀለም ያለው* ልብስ ለብሶ ከቦስራ+ የሚገሰግሰው ማን ነው?

ይህ እጅግ ያማረ ልብስ ለብሶና

በታላቅ ኃይል ተሞልቶ የሚራመደው ማን ነው?

“በጽድቅ የምናገር፣

ለማዳን የሚያስችል ታላቅ ኃይል ያለኝ እኔ ነኝ።”

 2 መጎናጸፊያህ የቀላውና

ልብሶችህ በመጭመቂያ ውስጥ ወይን እንደሚረግጥ ሰው ልብስ የሆኑት ለምንድን ነው?+

 3 “በወይን መጭመቂያው ውስጥ ወይኑን ብቻዬን ረገጥኩ።

ከሕዝቦች መካከል ከእኔ ጋር ማንም አልነበረም።

በቁጣዬም ረጋገጥኳቸው፤

በታላቅ ቁጣዬም ጨፈላለቅኳቸው።+

ደማቸውም ልብሶቼ ላይ ተረጨ፤

ልብሴንም ሁሉ በከልኩ።

 4 የምበቀልበት ቀን በልቤ ውስጥ ነውና፤+

የምቤዥበትም ዓመት ደርሷል።

 5 ተመለከትኩ፤ ሆኖም እርዳታ የሚሰጥ አልነበረም፤

ማንም ድጋፍ ባለመስጠቱ ደነገጥኩ።

ስለዚህ ክንዴ መዳን* አስገኘልኝ፤+

የገዛ ቁጣዬም ድጋፍ ሆነልኝ።

 6 ሕዝቦችን በቁጣዬ ረጋገጥኩ፤

በታላቅ ቁጣዬም አሰከርኳቸው፤+

ደማቸውንም በምድር ላይ አፈሰስኩ።”

 7 ይሖዋ በምሕረቱና ታላቅ በሆነው ታማኝ ፍቅሩ

ለእኛ ባደረገልን ነገሮች ሁሉ+

ይኸውም ለእስራኤል ቤት ባደረጋቸው በርካታ መልካም ነገሮች የተነሳ

የይሖዋን የታማኝ ፍቅር መግለጫዎች፣

ደግሞም ሊወደሱ የሚገባቸውን የይሖዋን ሥራዎች እናገራለሁ።

 8 እሱ እንዲህ ብሏልና፦ “እነሱ በእርግጥ ሕዝቤ፣ የማይከዱ* ወንዶች ልጆች ናቸው።”+

ስለዚህ አዳኝ ሆነላቸው።+

 9 በጭንቃቸው ሁሉ እሱ ተጨነቀ።+

የግል መልእክተኛውም* አዳናቸው።+

እሱ በፍቅሩና በርኅራኄው ተቤዣቸው፤+

በቀድሞውም ዘመን ሁሉ አነሳቸው እንዲሁም ተሸከማቸው።+

10 እነሱ ግን ዓመፁ፤+ ቅዱስ መንፈሱንም አሳዘኑ።+

በዚህ ጊዜ ጠላት ሆነባቸው፤+

ደግሞም ተዋጋቸው።+

11 እነሱም የጥንቱን ዘመን፣

አገልጋዩ ሙሴ የኖረበትን ጊዜ አስታወሱ፦

“ከመንጋው እረኞች+ ጋር ከባሕሩ ያወጣቸው የት አለ?+

በእሱ ውስጥ ቅዱስ መንፈሱን ያኖረው፣+

12 የከበረ ክንዱ ከሙሴ ቀኝ እጅ ጋር እንዲሄድ ያደረገው፣+

ለራሱ ዘላለማዊ ስም ለማትረፍ+

ውኃዎቹን በፊታቸው የከፈለው፣+

13 አውላላ ሜዳ* ላይ እንዳለ ፈረስ፣

በሚናወጡ ውኃዎች* መካከል

ሳይደናቀፉ እንዲሄዱ ያደረገው የት አለ?

14 የከብት መንጋ ወደ ሸለቋማ ሜዳ ሲወርድ እንደሚሆነው፣

የይሖዋ መንፈስ አሳረፋቸው።”+

ለራስህ የከበረ* ስም ለማትረፍ ስትል+

ሕዝብህን የመራኸው በዚህ መንገድ ነው።

15 ከሰማይ ተመልከት፤

ከፍ ካለው የቅድስናና የክብር* መኖሪያህም ሆነህ እይ።

ቅንዓትህና ታላቅ ኃይልህ፣

የሚንሰፈሰፈው አንጀትህና+ ምሕረትህ የት አለ?+

እነዚህን ነገሮች ነፍገኸኛል።

16 አንተ አባታችን ነህና፤+

አብርሃም ባያውቀን፣

እስራኤልም ባያስታውሰን እንኳ

ይሖዋ ሆይ፣ አንተ አባታችን ነህ።

ስምህም ከጥንት ዘመን ጀምሮ “እኛን የተቤዠ” የሚል ነው።+

17 ይሖዋ ሆይ፣ ከመንገዶችህ ወጥተን እንድንቅበዘበዝ የፈቀድከው* ለምንድን ነው?

አንተን እንዳንፈራ ልባችን እንዲደነድን የፈቀድከው* ለምንድን ነው?+

ስለ አገልጋዮችህ፣

ርስትህ ስለሆኑትም ነገዶች ስትል ተመለስ።+

18 ቅዱስ ሕዝብህ ለጥቂት ጊዜ ወርሶት ነበር።

ጠላቶቻችን መቅደስህን ረግጠዋል።+

19 እኛ ለረጅም ጊዜ፣ ፈጽሞ እንዳልገዛኻቸው፣

ጨርሶ በስምህ እንዳልተጠሩ ሰዎች ሆነናል።

64 በአንተ የተነሳ ተራሮች ይናወጡ ዘንድ

ምነው ሰማያትን ቀደህ በወረድክ!

 2 እሳት ጭራሮን አቀጣጥሎ

ውኃን እንደሚያፈላ ሁሉ፣

ያን ጊዜ ጠላቶችህ ስምህን ያውቃሉ፤

ብሔራትም በፊትህ ይሸበራሉ!

 3 እኛ ፈጽሞ ያልጠበቅናቸውን እጅግ አስደናቂ ነገሮች ባደረግክ ጊዜ፣+

አንተ ወረድክ፤ ተራሮችም በፊትህ ተንቀጠቀጡ።+

 4 ከጥንት ዘመን ጀምሮ፣ እሱን በተስፋ ለሚጠባበቁት* ሲል እርምጃ የወሰደ

ከአንተ በቀር ሌላ አምላክ እንዳለ የሰማም ሆነ በጆሮው ያዳመጠ

ወይም በዓይኑ ያየ ማንም የለም።+

 5 ትክክል የሆነውን ነገር በደስታ ከሚያደርጉ፣+

አንተን ከሚያስቡና መንገዶችህን ከሚከተሉ ሰዎች ጋር ተገናኝተሃል።

እነሆ፣ ኃጢአት መሥራታችንን በቀጠልን ጊዜ ተቆጣህ፤+

ይህን ያደረግነውም ለረጅም ጊዜ ነው።

ታዲያ አሁን መዳን ይገባናል?

 6 ሁላችንም እንደረከሰ ሰው ሆነናል፤

የጽድቅ ሥራችንም ሁሉ እንደ ወር አበባ ጨርቅ ነው።+

ሁላችንም እንደ ቅጠል እንጠወልጋለን፤

በደላችንም እንደ ነፋስ ጠራርጎ ይወስደናል።

 7 ስምህን የሚጠራ የለም፤

አንተን የሙጥኝ ብሎ ለመያዝ የሚነሳሳ የለም፤

ፊትህን ከእኛ ሰውረሃልና፤+

በበደላችን የተነሳ እንድንመነምን* አድርገኸናል።

 8 አሁን ግን ይሖዋ ሆይ፣ አንተ አባታችን ነህ።+

እኛ ሸክላ ነን፤ አንተም ሠሪያችን ነህ፤*+

ሁላችንም የእጅህ ሥራ ነን።

 9 ይሖዋ ሆይ፣ እጅግ አትቆጣ፤+

በደላችንንም ለዘላለም አታስታውስ።

እባክህ ተመልከተን፤ እኛ ሁላችን ሕዝብህ ነንና።

10 የተቀደሱ ከተሞችህ ምድረ በዳ ሆነዋል።

ጽዮን ምድረ በዳ፣

ኢየሩሳሌምም ጠፍ ምድር ሆናለች።+

11 አባቶቻችን አንተን ያወደሱበት

የቅድስናና የክብር ቤታችን*

በእሳት ተቃጥሏል፤+

ከፍ አድርገን እንመለከታቸው የነበሩት ነገሮች በሙሉ ፈራርሰዋል።

12 ይሖዋ ሆይ፣ ይህ ሁሉ ሆኖ እያለ እርምጃ ከመውሰድ ትታቀባለህ?

ዝም ብለህስ ታያለህ? ደግሞስ ከልክ በላይ እንድንጎሳቆል ትፈቅዳለህ?+

65 “እኔን ላልጠየቁ ሰዎች ተገለጥኩ፤

ላልፈለጉኝ ሰዎች ተገኘሁ።+

ስሜን ላልጠራ ብሔር ‘እነሆኝ፤ እነሆኝ!’ አልኩ።+

 2 የራሳቸውን ሐሳብ እየተከተሉ፣+

መልካም ባልሆነ መንገድ ወደሚሄዱ+

ግትር ሰዎች ቀኑን ሙሉ እጆቼን ዘረጋሁ፤+

 3 እነሱ ዘወትር በፊቴ እኔን የሚያስከፋ ነገር ይፈጽማሉ፤+

በአትክልት ቦታዎች ይሠዋሉ፤+ በጡቦችም ላይ የሚጨስ መሥዋዕት ያቀርባሉ።

 4 በመቃብር መካከል ይቀመጣሉ፤+

በተሰወሩ ቦታዎችም* ውስጥ ያድራሉ፤

የአሳማ ሥጋ ይበላሉ፤+

ዕቃዎቻቸው ጸያፍ* በሆኑ ነገሮች መረቅ የተሞሉ ናቸው።+

 5 ‘እዚያው ባለህበት ሁን፤ አትጠጋኝ፤

እኔ ከአንተ ይልቅ ቅዱስ ነኝና’* ይላሉ።

እነዚህ ሰዎች በአፍንጫዬ እንዳለ ጭስ፣ ቀኑን ሙሉ እንደሚነድ እሳት ናቸው።

 6 እነሆ፣ በፊቴ ተጽፏል፤

እኔ ዝም አልልም፤

ከዚህ ይልቅ እንደ ሥራቸው እከፍላቸዋለሁ፤+

ብድራቱን ሙሉ በሙሉ እመልስባቸዋለሁ፤*

 7 ይህን የማደርገው እነሱ በሠሩት በደልና አባቶቻቸው በሠሩት በደል የተነሳ ነው”+ ይላል ይሖዋ።

“ምክንያቱም በተራሮች ላይ የሚጨስ መሥዋዕት አቅርበዋል፤

በኮረብቶችም ላይ አዋርደውኛል፤+

እኔም በመጀመሪያ፣ ዋጋቸውን ሙሉ በሙሉ እከፍላቸዋለሁ።”*

 8 ይሖዋ እንዲህ ይላል፦

“አዲስ ወይን፣ በወይን ዘለላ ውስጥ ሲገኝ

አንድ ሰው ‘በውስጡ ጥሩ ነገር* ስላለ አታጥፋው’ እንደሚል፣

እኔም ለአገልጋዮቼ ስል እንዲሁ አደርጋለሁ፤

ሁሉንም አላጠፋቸውም።+

 9 ከያዕቆብ ዘርን፣

ከይሁዳም ተራሮቼን የሚወርሰውን አወጣለሁ፤+

የመረጥኳቸው ምድሪቱን ይወርሳሉ፤

አገልጋዮቼም በዚያ ይኖራሉ።+

10 እኔን ለሚፈልገኝ ሕዝቤ፣

ሳሮን+ የበጎች መሰማሪያ፣

የአኮርም ሸለቆ*+ የከብቶች ማረፊያ ይሆናል።

11 እናንተ ግን ይሖዋን ከተዉት፣+

ቅዱስ ተራራዬን ከረሱት፣+

መልካም ዕድል ለተባለ አምላክ ማዕድ ካሰናዱት፣

ዕጣ ለተባለም አምላክ የተደባለቀ ወይን ጠጅ በዋንጫ ከሞሉት ሰዎች መካከል ናችሁ።

12 በመሆኑም ዕጣችሁ በሰይፍ መውደቅ ይሆናል፤+

ሁላችሁም ለመታረድ ታጎነብሳላችሁ፤+

ምክንያቱም ስጣራ አልመለሳችሁም፤

ስናገር አልሰማችሁም፤+

በዓይኔ ፊት ክፉ የሆነውን ነገር ማድረጋችሁን ቀጠላችሁ፤

እኔ የማልደሰትበትንም ነገር መረጣችሁ።”+

13 ስለዚህ ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦

“እነሆ፣ አገልጋዮቼ ይበላሉ፤ እናንተ ግን ትራባላችሁ።+

እነሆ፣ አገልጋዮቼ ይጠጣሉ፤+ እናንተ ግን ትጠማላችሁ።

እነሆ፣ አገልጋዮቼ ሐሴት ያደርጋሉ፤+ እናንተ ግን ኀፍረት ትከናነባላችሁ።+

14 እነሆ፣ አገልጋዮቼ ከልባቸው ደስታ የተነሳ እልል ይላሉ፤

እናንተ ግን ከልባችሁ ሐዘን የተነሳ ትጮኻላችሁ፤

መንፈሳችሁ ስለተሰበረም ዋይ ዋይ ትላላችሁ።

15 የተመረጡት አገልጋዮቼ ለእርግማን የሚጠቀሙበት ስም ትታችሁ ታልፋላችሁ፤

ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋም እያንዳንዳችሁን ይገድላችኋል፤

የራሱን አገልጋዮች ግን በሌላ ስም ይጠራቸዋል፤+

16 ስለዚህ በምድር ላይ በረከትን የሚሻ ሁሉ

በእውነት አምላክ* ይባረካል፤

በምድር ላይ መሐላ የሚምልም ሁሉ

በእውነት አምላክ* ይምላል።+

ቀደም ሲል የነበሩት የሚያስጨንቁ ነገሮች* ይረሳሉና፤

ከዓይኔ ይሰወራሉ።+

17 እነሆ፣ አዲስ ሰማያትና አዲስ ምድር እየፈጠርኩ ነውና፤+

የቀድሞዎቹ ነገሮች አይታሰቡም፤*

ወደ ልብም አይገቡም።+

18 በመሆኑም በምፈጥረው ነገር ለዘላለም ደስ ይበላችሁ፤ ሐሴትም አድርጉ።

እነሆ፣ ኢየሩሳሌምን ለደስታ፣

ሕዝቧንም ለሐሴት እፈጥራለሁና።+

19 እኔም በኢየሩሳሌም ደስ እሰኛለሁ፤ በሕዝቤም ሐሴት አደርጋለሁ፤+

ከዚህ በኋላ በውስጧ የለቅሶ ድምፅም ሆነ የጭንቅ ጩኸት አይሰማም።”+

20 “ከእንግዲህ በዚያ፣ ለጥቂት ቀን ብቻ የሚኖር ሕፃንም ሆነ

ዕድሜ የማይጠግብ አረጋዊ አይኖርም።

መቶ ዓመት ሞልቶት የሚሞት ማንኛውም ሰው ገና በልጅነቱ እንደተቀጨ ይቆጠራል፤

ኃጢአተኛው መቶ ዓመት ቢሞላውም እንኳ ይረገማል።*

21 ቤቶችን ይሠራሉ፤ በዚያም ይኖራሉ፤+

ወይንንም ይተክላሉ፤ ፍሬውንም ይበላሉ።+

22 እነሱ በሠሩት ቤት ሌላ ሰው አይኖርም፤

እነሱ የተከሉትንም ሌላ ሰው አይበላውም።

የሕዝቤ ዕድሜ እንደ ዛፍ ዕድሜ ይሆናልና፤+

የመረጥኳቸው አገልጋዮቼም በእጃቸው ሥራ የተሟላ እርካታ ያገኛሉ።

23 በከንቱ አይለፉም፤+

ወይም ለመከራ የሚዳረጉ ልጆች አይወልዱም፤

ምክንያቱም እነሱም ሆኑ ልጆቻቸው+

ይሖዋ የባረከው ዘር ናቸው።+

24 ገና ሳይጣሩ እመልስላቸዋለሁ፤

እየተናገሩ ሳሉ እሰማቸዋለሁ።

25 ተኩላና የበግ ግልገል በአንድነት ይበላሉ፤

አንበሳ እንደ በሬ ገለባ ይበላል፤+

የእባብም መብል አፈር ይሆናል።

በተቀደሰው ተራራዬ ሁሉ ላይ ምንም ዓይነት ጉዳትም ሆነ ጥፋት አያደርሱም”+ ይላል ይሖዋ።

66 ይሖዋ እንዲህ ይላል፦

“ሰማይ ዙፋኔ ነው፤ ምድር ደግሞ የእግሬ ማሳረፊያ ናት።+

ታዲያ እናንተ ምን ዓይነት ቤት ልትሠሩልኝ ትችላላችሁ?+

ደግሞስ የማርፍበት ቦታ የት ነው?”+

 2 “እነዚህን ነገሮች ሁሉ የሠራው እጄ ነው፤

ሁሉም ወደ ሕልውና የመጡት በዚህ መንገድ ነው” ይላል ይሖዋ።+

“እኔ የማየው ትሑት የሆነውን፣

መንፈሱ የተሰበረውንና በቃሌ የሚንቀጠቀጠውን* ሰው ነው።+

 3 በሬን የሚያርድ፣ ሰውን እንደሚገድል ነው።+

በግን የሚሠዋ፣ የውሻን አንገት እንደሚሰብር ነው።+

ስጦታ የሚሰጥ ሰው፣ የአሳማ ደም እንደሚያቀርብ ነው!+

ነጭ ዕጣንን የመታሰቢያ መባ አድርጎ የሚያቀርብ፣+ በአስማታዊ ቃላት እንደሚባርክ* ሰው ነው።+

እነሱ የራሳቸውን መንገድ መርጠዋል፤

በአስጸያፊ ነገሮችም ደስ ይሰኛሉ።*

 4 ስለዚህ እነሱን የምቀጣበትን መንገድ እፈልጋለሁ፤+

የፈሩትንም ያንኑ ነገር አመጣባቸዋለሁ።

ምክንያቱም ስጣራ መልስ የሰጠ ማንም አልነበረም፤

ስናገር የሰማ አንድም ሰው አልነበረም።+

በዓይኔ ፊት ክፉ የሆነውን ነገር ማድረጋቸውን ቀጠሉ፤

እኔ የማልደሰትበትንም ነገር መረጡ።”+

 5 እናንተ በቃሉ የምትንቀጠቀጡ* ሰዎች ሆይ፣ የይሖዋን ቃል ስሙ፦

“በስሜ የተነሳ የሚጠሏችሁና የሚያገሏችሁ ወንድሞቻችሁ፣ ‘ይሖዋ የተከበረ ይሁን!’ ብለዋል።+

ሆኖም አምላክ ይገለጣል፤ ደስታንም ያጎናጽፋችኋል፤

እነሱም ለኀፍረት ይዳረጋሉ።”+

 6 ከከተማዋ ሁካታ፣ ከቤተ መቅደሱም ድምፅ ይሰማል!

ይህም ይሖዋ ለጠላቶቹ የሚገባቸውን ብድራት በሚከፍላቸው ጊዜ የሚሰማ ድምፅ ነው።

 7 እሷ ገና ምጥ ሳይጀምራት ወለደች።+

ምጥ ሳይዛት በፊት ወንድ ልጅ ተገላገለች።

 8 እንዲህ ያለ ነገር ማን ሰምቶ ያውቃል?

እንዲህ ያሉ ነገሮችስ ማን አይቶ ያውቃል?

አገር በአንድ ቀን ይወለዳል?

ወይስ ብሔር በአንድ ጊዜ ይወለዳል?

ሆኖም ጽዮን እንዳማጠች ወዲያው ወንዶች ልጆቿን ወልዳለች።

 9 “ማህፀኑን ከከፈትኩ በኋላ ልጁ እንዳይወለድ አደርጋለሁ?” ይላል ይሖዋ።

“ወይስ ምጡ እንዲፋፋም ካደረግኩ በኋላ ማህፀኑን እዘጋለሁ?” ይላል አምላክሽ።

10 እናንተ የምትወዷት ሁሉ፣+ ከኢየሩሳሌም ጋር ሐሴት አድርጉ፤ ከእሷም ጋር ደስ ይበላችሁ።+

ለእሷ የምታዝኑ ሁሉ ከእሷ ጋር እጅግ ደስ ይበላችሁ፤

11 የሚያጽናኑ ጡቶቿን ትጠባላችሁና፤ ሙሉ በሙሉም ትረካላችሁ፤

እስኪበቃችሁም ድረስ ትጠጣላችሁ፤ በክብሯም ብዛት ሐሴት ታደርጋላችሁ።

12 ይሖዋ እንዲህ ይላልና፦

“እነሆ፣ ሰላምን እንደ ወንዝ፣+

የብሔራትንም ክብር እንደሚያጥለቀልቅ ጅረት አፈስላታለሁ።+

እናንተም ትጠባላችሁ፤ ጀርባዋም ላይ ታዝላችኋለች፣

ጭኗም ላይ ሆናችሁ ትዘላላችሁ።

13 እናት ልጇን እንደምታጽናና፣

እኔም እናንተን ሁልጊዜ አጽናናችኋለሁ፤+

በኢየሩሳሌምም ትጽናናላችሁ።+

14 እናንተ ይህን ታያላችሁ፤ ልባችሁም ሐሴት ያደርጋል፤

አጥንቶቻችሁ እንደ ሣር ይለመልማሉ።

የይሖዋም እጅ* በአገልጋዮቹ ዘንድ ትታወቃለች፤

ጠላቶቹን ግን ያወግዛቸዋል።”+

15 “ይሖዋ፣ ብድራቱን በታላቅ ቁጣ ለመመለስ፣

በእሳት ነበልባልም ለመገሠጽ+

እንደ እሳት ሆኖ ይመጣልና፤+

ሠረገሎቹም እንደ አውሎ ነፋስ ይመጣሉ።+

16 ይሖዋ በእሳት ፍርዱን ይፈጽማልና፤

አዎ፣ በሥጋ ለባሽ* ሁሉ ላይ በሰይፍ ፍርዱን ይፈጽማል፤

በይሖዋ እጅ የሚገደሉትም ብዙ ይሆናሉ።

17 ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “መሃል ላይ ያለውን ተከትለው ወደ አትክልት ቦታዎቹ*+ ለመግባት ሲሉ ራሳቸውን የሚቀድሱና የሚያነጹ፣ የአሳማ ሥጋና አስጸያፊ ነገር እንዲሁም አይጥ የሚበሉ ሁሉ+ በአንድነት ይጠፋሉ። 18 እኔ ሥራቸውንና ሐሳባቸውን ስለማውቅ፣ ከሁሉም ብሔራትና ቋንቋዎች የተውጣጡ ሰዎችን ለመሰብሰብ እመጣለሁ፤ እነሱም መጥተው ክብሬን ያያሉ።”

19 “በመካከላቸው ምልክት አቆማለሁ፤ ከተረፉት መካከል አንዳንዶቹን ወደ ብሔራት ይኸውም ወደ ተርሴስ፣+ ወደ ፑል እና ወደ ሉድ+ እልካለሁ። በቱባልና በያዋን+ ወዳሉት ቀስተኞች እልካቸዋለሁ። ስለ እኔ ወዳልሰሙ ወይም ክብሬን ወዳላዩ፣ ርቀው በሚገኙ ደሴቶች ውስጥ ወደሚኖሩ ሕዝቦችም እልካቸዋለሁ፤ እነሱም በብሔራት መካከል ክብሬን ያውጃሉ።+ 20 የእስራኤል ልጆች በንጹሕ ዕቃ ስጦታ ይዘው ወደ ይሖዋ ቤት እንደሚያመጡ፣ ወንድሞቻችሁን ሁሉ ለይሖዋ ስጦታ እንዲሆኑ ከየብሔራቱ በፈረሶች፣ በሠረገሎች፣ ጥላ ባላቸው ጋሪዎች፣ በበቅሎዎችና በፈጣን ግመሎች ጭነው ወደተቀደሰው ተራራዬ ወደ ኢየሩሳሌም ያመጧቸዋል”+ ይላል ይሖዋ።

21 “በተጨማሪም አንዳንዶቹን ካህናት፣ ሌሎቹን ደግሞ ሌዋውያን እንዲሆኑ እወስዳለሁ” ይላል ይሖዋ።

22 “እኔ የምሠራቸው አዲስ ሰማያትና አዲስ ምድር+ በፊቴ ጸንተው እንደሚኖሩ ሁሉ የእናንተም ዘርና ስማችሁ እንዲሁ ጸንቶ ይኖራል”+ ይላል ይሖዋ።

23 “ከአንዱ ወር መባቻ እስከ ሌላው ወር መባቻ እንዲሁም ከአንዱ ሰንበት እስከ ሌላው ሰንበት፣

ሰው* ሁሉ በፊቴ ለመስገድ* ይመጣል”+ ይላል ይሖዋ።

24 “እነሱም ሄደው በእኔ ላይ ያመፁትን ሰዎች ሬሳ ያያሉ፤

በእነሱ ላይ ያሉት ትሎች አይሞቱምና፤

እሳታቸውም አይጠፋም፤+

ለሰዎችም* ሁሉ አስጸያፊ ነገር ይሆናሉ።”

“የይሖዋ ማዳን” ማለት ነው።

ወይም “ጌታውን።”

ቃል በቃል “አልፈረጠም።”

ወይም “ዳስ።”

ወይም “ገዢዎች።”

ወይም “መመሪያ፤ ትምህርት።”

ወይም “ነፍሴ ጠልታለች።”

ወይም “ወላጅ አልባ የሆነውን ልጅ።”

ወይም “ከስንዴ የሚዘጋጀው ጠላሽ።”

ወይም “ወላጅ አልባ የሆኑ ልጆች ፍትሕ እንዲያገኙ።”

ከጣዖት አምልኮ ጋር ግንኙነት ያላቸውን ዛፎችና የአትክልት ቦታዎች የሚያመለክት ይመስላል።

ተቀጣጣይ የሆነ ገመድ መሰል ቃጫ።

ወይም “በመጨረሻዎቹ ቀኖች።”

ወይም “መመሪያ፤ ትምህርት።”

ወይም “ያስተካክላል።”

ወይም “ኀፍረት ይከናነባሉ።”

ወይም “ኀፍረት ይከናነባሉ።”

ወይም “በመሬት ጉድጓዶች ውስጥ።”

በልተው የማይጠግቡ ትናንሽ አጥቢ እንስሳት።

ወይም “እስትንፋሱ በአፍንጫው ላይ ባለች ሰው።”

ወይም “ወላዋይ።”

ወይም “ፈዋሻችሁ አልሆንም።”

ቃል በቃል “በክብሩ ዓይኖች ፊት።”

ወይም “ለነፍሳቸው ወዮ!”

ቃል በቃል “የሥራቸውን ፍሬ ይበላሉ።”

ቃል በቃል “አንገታቸውን (ጉሮሯቸውን) አስግገው።”

ወይም “ዶቃውን።”

ወይም “ድጉን።”

ቃል በቃል “የነፍስ ቤቶቹን።”

ወይም “የውስጥ ልብሶቹን።”

የአንድን ባሪያ ወይም እስረኛ ሰውነት በጋለ ብረት በመተኮስ የሚደረግን ምልክት ያመለክታል።

አለማግባታቸውና ልጅ አለመውለዳቸው ያስከተለባቸውን ውርደት ያመለክታል።

ወይም “በሚያስወግድ።”

ቃል በቃል “እዳሪ።”

ወይም “ተክል ናቸው።”

ቃል በቃል “አሥር ጥማድ ከሚያውል።”

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።

ወይም “ሲኦል።” የሰው ልጆችን ሁሉ መቃብር ያመለክታል። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

ወይም “ነፍሷን።”

ወይም “ታላላቅ ሰዎቿ።”

ወይም “በሚሰጠው ፍትሕ።”

ወይም “ውሳኔ፤ ምክር።”

ወይም “መመሪያ፤ ትምህርት።”

ወይም “ለምልክት የሚተከል ምሰሶ።”

ወይም “ፍላጻ ለማስፈንጠር የተዘጋጁ።”

ተሽከርካሪ እግር።

ቃል በቃል “እሱ።”

ቃል በቃል “ከጯኺው ድምፅ።”

ቃል በቃል “ጸጥ እንድል ተደርጌአለሁ።”

“እነሱ ግን ድል ሊያደርጓት አልቻሉም” ማለትም ሊሆን ይችላል።

“ቀሪዎች ብቻ ይመለሳሉ” የሚል ትርጉም አለው።

“እናሸብረው” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ወይም “ግንቦቹንም እንንደል።” ቃል በቃል “እንሰንጥቀውም።”

ወይም “ሲኦል።” የሰው ልጆችን ሁሉ መቃብር ያመለክታል። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

ወይም “ልጃገረዷ።”

“አምላክ ከእኛ ጋር ነው” የሚል ትርጉም አለው።

ወይም “ደረቅ ወንዞች።”

የኤፍራጥስን ወንዝ ያመለክታል።

ቃል በቃል “ሟች በሆነ ሰው ብዕር።”

“ወደ ምርኮው ፈጥኖ መሄድ፣ ወደ ብዝበዛው ፈጥኖ መምጣት” የሚል ትርጉም ሊኖረው ይችላል።

ወይም “ይመሥክሩልኝ፤ ቃላቸውን ይስጡልኝ።”

የኢሳይያስን ሚስት ታመለክታለች።

ቃል በቃል “ወደ ነቢዪቱ ቀረብኩ።”

ሺሎአ የውኃ ቦይ ነበር።

ኤፍራጥስን ያመለክታል።

ኢሳ 7:14ን ተመልከት።

ወይም “ታጠቁ።”

“አምላክ ከእኛ ጋር ነው” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል ኢማኑኤል የሚለው ነው። ኢሳ 7:14ንና 8:8ን ተመልከት።

ወይም “የምሥክርነት ቃል።”

ወይም “መመሪያውን፤ ትምህርቱን።”

ወይም “በጉጉት እጠብቃለሁ።”

ወይም “የምሥክርነት ቃሉን።”

ቃል በቃል “አይነጋላቸውም።”

ወይም “መንግሥትም፤ መስፍናዊ አገዛዝም።”

ወይም “መንግሥቱም፤ መስፍናዊ አገዛዙም።”

ቃል በቃል “ከኋላ።”

“የዘንባባ ቅርንጫፍንና ሸምበቆን” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ወይም “ወላጅ አልባ የሆኑ ልጆችና።”

ወይም “ወላጅ አልባ የሆኑ ልጆችን።”

ወይም “በምትቀጡበት።”

ወይም “ክብራችሁንስ።”

ቃል በቃል “እቀጣዋለሁ።”

ወይም “ከነፍስ እስከ ሥጋ።”

ወይም “ቅጣትም።”

ወንዝ ማቋረጥ የሚቻልበት ጥልቀት የሌለው የወንዝ ክፍል።

ወይም “በመጥረቢያ።”

ወይም “በጽድቅ።”

ወይም “መንፈስ።”

ወይም “ደቦል አንበሳና።”

“ጥጃና አንበሳ አብረው ይሰማራሉ” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ወይም “በጉበና።” በእስያና በአፍሪካ የሚገኝ እጅግ መርዘኛ የሆነ እባብ፤ ኮብራ።

ወይም “ለምልክት የሚተከል ምሰሶ።”

ወይም “ብሔራት እሱን ይፈልጉታል።”

ወይም “ከኩሽ።”

ባቢሎንን ያመለክታል።

ወይም “ለምልክት የሚተከል ምሰሶ።”

ቃል በቃል “ትከሻ።”

ወይም “ኃይላቸውን።”

ቃል በቃል “ምላስ።”

“ያደርቃል” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ኤፍራጥስን ያመለክታል።

ወይም “መንፈሱ።”

“ወንዙን መትቶ ሰባት ጅረት ያደርገዋል” ማለትም ሊሆን ይችላል።

“ያህ” የይሖዋ ስም አጭር መጠሪያ ነው።

ቃል በቃል “አንቺ የጽዮን ነዋሪ።” ሕዝቡ በጥቅሉ በአንስታይ ፆታ መጠራቱን ያሳያል።

ወይም “ለምልክት የሚተከል ምሰሶ።”

ቃል በቃል “ለቅዱሳኔ።”

ቃል በቃል “የእነሱ ከሲል።” ኦርዮንንና በዙሪያው ያሉትን የኅብረ ከዋክብት ስብስቦች ሊያመለክት ይችላል።

ወይም “የመንግሥታት ጌጥ የሆነችው።”

“ፍየል የሚመስሉ አጋንንትም” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ወይም “እረፍት ይሰጣቸዋል።”

ወይም “ተቆጣጣሪዎቻቸውንም።”

ወይም “ትሳለቃለህ።”

ወይም “ተቆጣጣሪው።”

ወይም “ሲኦል።” የሰው ልጆችን ሁሉ መቃብር ያመለክታል። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

ቃል በቃል “አውራ ፍየሎች።”

ወይም “ሲኦል።” የሰው ልጆችን ሁሉ መቃብር ያመለክታል። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

ወይም “ሲኦል።” የሰው ልጆችን ሁሉ መቃብር ያመለክታል። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

ቃል በቃል “በየቤታቸው።”

ወይም “ቅርንጫፍ።”

ቃል በቃል “በምድር ላይ የተመከረው ምክር።”

ወይም “ብሔራትንም ሁሉ ለመምታት የተዘጋጀው።”

ወይም “ተወርዋሪ መርዘኛ እባብ።”

ወይም “ቤተ መቅደሱ።”

ወይም “ነፍሱም።”

ወይም “ደረቅ ወንዝ።”

ወንዝ ማቋረጥ የሚቻልበት ጥልቀት የሌለው የወንዝ ክፍል።

ወይም “ቀይ የወይን ዘለላዎች የያዙ ቅርንጫፎቹን።”

“ምክንያቱም የበጋ ፍሬና መከር በምትሰበስቡበት ጊዜ የጦርነት ሁካታ መጥቷል” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ወይም “አንድ ቅጥር ሠራተኛ እንደሚያደርገው በጥንቃቄ ተቆጥሮ።” ይህም ልክ በሦስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ማለት ነው።

ቃል በቃል “የሥጋውም ውፍረት።”

ወይም “ረባዳማ ሜዳ።”

የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

ኢየሩሳሌምን ያመለክታል።

ወይም “የእንግዳ አምላክ።”

ቃል በቃል “ወደተመዘዘና ወደሚያብረቀርቅ ሕዝብ።”

ወይም “ሌሎችን ወደሚረግጥ ታላቅ ጥንካሬ ያለው ብሔር።”

ወይም “ለምልክት እንደሚተከል ምሰሶ።”

“ከተመሠረተው ስፍራዬ” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ቃል በቃል “የተመዘዘና የሚያብረቀርቅ ሕዝብ።”

ወይም “ሌሎችን የሚረግጥ ታላቅ ጥንካሬ ያለው ብሔርና።”

ወይም “የቅጥር ሠራተኞቹ ሁሉ ነፍስ ታዝናለች።”

ወይም “የሜምፊስ።”

“ለዘንባባ ቅርንጫፍም ሆነ ለሸምበቆ” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ወይም “የጦር አዛዥ።”

ወይም “ከውስጥ በለበሳት ልብስ ብቻና።”

ወይም “ደግሞም ግብፅን ያዋርዳል።”

ወይም “ውበቷን በሚያደንቁላት።”

የጥንቷን ባቢሎን ደቡባዊ ክፍል የሚያመለክት ሊሆን ይችላል።

ቃል በቃል “ዳሌዎቼ በሥቃይ ተሞሉ።”

ቃል በቃል “ወንድ ልጅ።”

“ዝምታ” የሚል ትርጉም አለው።

ወይም “አንድ ቅጥር ሠራተኛ እንደሚያደርገው በጥንቃቄ ተቆጥሮ።” ይህም ልክ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ማለት ነው።

ኢየሩሳሌምን የሚያመለክት ሳይሆን አይቀርም።

በሰውኛ ዘይቤ የተገለጸ ቅኔያዊ አነጋገር፤ አዘኔታን ወይም ርኅራኄን የሚያመለክት ሊሆን ይችላል።

እርዳታ ለማግኘት ወይም በጦርነት ወቅት የሚሰማን ጩኸት ሊያመለክት ይችላል።

ወይም “በፈረሰኞች።”

ወይም “ጋሻውን አዘጋጀች።”

ወይም “ረባዳማ ሜዳዎችሽ።”

ወይም “ፈረሰኞቹም።”

ወይም “መከላከያ።”

ወይም “በቤተ መንግሥቱ።”

ቃል በቃል “መኖሪያ።”

ወይም “ግዛትህንም።”

ቃል በቃል “ክብደት።”

ወይም “ቅርንጫፎቹን።”

ከአባይ ወንዝ ተገንጥሎ የሚወጣን ጅረት ያመለክታል።

ቃል በቃል “ዘርና።”

ቃል በቃል “ድንግሎችን።”

“ወደብ” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ቃል በቃል “ቀኖች።”

ወይም “ፊቷን ያዞራል።”

“ትደርቃለች” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ወይም “የጥንቱን።”

“ይደርቃል” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ወይም “ከምዕራብ።”

ወይም “በምሥራቅ።”

ወይም “ጌጥ።”

ቃል በቃል “በእሱ ሽማግሌዎች ፊት።”

ወይም “ምክሮች።”

ቃል በቃል “ቅባት የሞላባቸው ምግቦች።”

ቃል በቃል “ይውጣል።”

ወይም “ያስወግዳል።”

ወይም “ይጠርጋል።”

“የማይናወጥ ልብ ያላቸውን” ማለትም ሊሆን ይችላል።

“ያህ” የይሖዋ ስም አጭር መጠሪያ ነው።

ወይም “ደልዳላ።”

ወይም “የነፍሳችን።”

አምላክም ሆነ ስሙ እንዲታወስና እንዲታወቅ እንደሚጓጉ ያሳያል።

ወይም “ነፍሴ።”

ወይም “በጽድቅ።”

“እንደ ዕፀዋት (ልት) ጠል ነውና” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ወይም “በሞት የተረቱትን ትወልዳለች።”

ወይም “ውግዘቱ።”

የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

እዚህ ላይ በአንስታይ ፆታ የተገለጸችውና በወይን እርሻ የተመሰለችው እስራኤል ልትሆን ትችላለች።

የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

ኤፍራጥስን ያመለክታል።

የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

ወይም “ትዕቢተኛ ወይም ኩሩ ለሆነችው።”

ዋና ከተማዋን ሰማርያን የምታመለክት ልትሆን ትችላለች።

ወይም “ትዕቢተኛ ወይም ኩሩ የሆኑት።”

ወይም “በመለኪያ ገመድ ላይ መለኪያ ገመድ፣ በመለኪያ ገመድ ላይ መለኪያ ገመድ።”

ወይም “በመለኪያ ገመድ ላይ መለኪያ ገመድ፣ በመለኪያ ገመድ ላይ መለኪያ ገመድ።”

ወይም “ከሲኦልም።” የሰው ልጆችን ሁሉ መቃብር ያመለክታል። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

“ራእይ አይተናል” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ወይም “ቱምቢ።”

ወይም “ከሲኦልም።” የሰው ልጆችን ሁሉ መቃብር ያመለክታል። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

“የተነገረውን ነገር ሲረዱ በሽብር ይዋጣሉ” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ወይም “ረባዳማ ሜዳ።”

ወይም “መላዋን ምድር።”

ወይም “ሰውን . . . ይገሥጸዋል፤ ይቀጣዋል።”

ጥርስ መሳይ ጉጦች ያሉት የእህል መውቂያ።

ተሽከርካሪ እግር።

ወይም “ዓላማ።”

ወይም “ጥበቡ ታላቅ ከሆነው።”

“የአምላክ የመሠዊያ ምድጃ” የሚል ትርጉም ሊኖረው ይችላል፤ ኢየሩሳሌምን የሚያመለክት ይመስላል።

ቃል በቃል “የባዕዳን።”

ወይም “ነፍሱ ባዶ እንደምትሆን።”

ወይም “ነፍሱ በጥም እንደምትቃጠል።”

ወይም “ምክራቸውን ከይሖዋ ለመሰወር።”

ወይም “እንዴት ጠማሞች ናችሁ!”

ቃል በቃል “ወቀሳ በሚሰነዝረው።”

ውርደትና ኀፍረት እንደማይደርስበት ያመለክታል።

ወይም “ለእስራኤልም አምላክ አክብሮታዊ ፍርሃት ያሳያሉ።”

ቃል በቃል “የመጠጥ መባ ያፈሳሉ።” ስምምነት ማድረጋቸውን የሚያሳይ ሊሆን ይችላል።

ቃል በቃል “በፈርዖን ምሽግ።”

ወይም “ከአፌ መመሪያ ሳይጠይቁ።”

ወይም “ተወርዋሪ መርዘኛ እባብ።”

ወይም “መመሪያ፤ ትምህርት።”

ቃል በቃል “ለስላሳ።”

“ከውኃ ጉድጓድ” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ወይም “በእርግጠኝነት።”

ወይም “በጉጉት።”

ወይም “ቀልጠው የተሠሩ ሐውልቶችህ።”

“ቆሻሻ” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ቃል በቃል “የሰባና ቅባት የሞላበት።”

ጨው ጨው የሚል ጣዕም ያለው የዕፀዋት ዓይነት።

ወይም “ስንጥቅ።”

ወይም “እስትንፋሱ።”

ቃል በቃል “በከንቱነት ወንፊት።”

ወይም “ለበዓል ራሳችሁን በምትቀድሱበት።”

ወይም “የዋሽንት ድምፅ እየሰማ።”

እዚህ ላይ “ቶፌት” የሚለው ቃል እሳት የሚነድበትን ቦታ የሚያሳይ ምሳሌያዊ አገላለጽ ሲሆን ጥፋትን ያመለክታል።

ወይም “ፈረሰኞች።”

ወይም “እሳቱ።”

ወይም “መጠለያ።”

ወይም “እንደ መጠጊያ።”

ወይም “ፈሪሃ አምላክ የጎደለው ድርጊት ለመፈጸምና።”

ወይም “የተራበ ሰው ነፍስ የሚበላ ነገር እንዳታገኝና።”

ወይም “የተቀደሰ።”

ወይም “የምትፈቱ።”

ወይም “ብርታት ሁነን።”

ጠላትን ያመለክታል።

“ደረቀች” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ወይም “ታሰላስላለህ።”

ቃል በቃል “ቋንቋው ጥልቅ የሆነውንና።”

ወይም “የሚኖር።”

ወይም “ተራሮቹ በደም ይጥለቀለቃሉ።”

የኤዶም ዋና ከተማ የሆነችውን ቦስራን የሚያመለክት ሊሆን ይችላል።

ወይም “ገርጌሶና።” ጠፍጠፍ ያለ ረጅም መንቆር ያለው ትልቅ አሞራ።

ቃል በቃል “በድንጋዮች።”

“ፍየል የሚመስል ጋኔንም” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ቃል በቃል “በመለኪያ ገመድ ለክቶ አከፋፍሏቸዋል።”

ቃል በቃል “ሳፍሮንም።”

ወይም “የመጠጥ አሳላፊዎቹን አለቃ።”

ወይም “የቤተ መንግሥቱ።”

ወይም “በሶርያ።”

ቃል በቃል “ከእኔ ጋር ባርኩ፤ እንዲሁም ወደ እኔ ውጡ።”

ወይም “የቤተ መንግሥቱ።”

ወይም “የቤተ መንግሥቱ።”

ወይም “የስድብና።”

ቃል በቃል “ልጁ ወደ ማህፀኑ አፍ መጥቶ።”

ቃል በቃል “እነሆ፣ መንፈስ አስገባበታለሁ።”

ቃል በቃል “ደብዳቤውን።”

“በኪሩቤል መካከል” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ወይም “የግብፅን የአባይ የመስኖ ቦዮች።”

ቃል በቃል “የተደረገ።”

ወይም “ሠርቻለሁ።”

ለሕዝቅያስ የተነገረ ነው።

ሰብል በሚሰበሰብበት ጊዜ ማሳው ላይ ረግፎ እንደገና የሚበቅለውን እህል ያመለክታል።

ወይም “ቤተ መቅደስ።”

ቃል በቃል “በቀኖችህ።”

እነዚህ ደረጃዎች በፀሐይ ጥላ አማካኝነት ሰዓትን ለመቁጠር ያገለግሉ የነበረ ይመስላል።

ወይም “ያጠናቀረው።”

ወይም “ሲኦል።” የሰው ልጆችን ሁሉ መቃብር ያመለክታል። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

“ያህ” የይሖዋ ስም አጭር መጠሪያ ነው።

“ቁርዬ” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ቃል በቃል “ዋስ ሁነኝ።”

ወይም “ከነፍሴ ምሬት።”

ወይም “በዝግታ።”

የአምላክን ቃልና ተግባር ያመለክታል።

ወይም “ለነፍሴ።”

ወይም “ኃጢአቴን ሁሉ ከእይታህ አስወገድክ።”

ወይም “ሲኦል።” የሰው ልጆችን ሁሉ መቃብር ያመለክታል። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

ወይም “በቤተ መንግሥቱም።”

ወይም “በቤተ መንግሥትህ።”

ወይም “በቤተ መንግሥቴ።”

ወይም “በቤተ መንግሥትህ።”

ቃል በቃል “ቀኖች።”

ወይም “እውነት።”

ወይም “ኢየሩሳሌምን በሚያጽናና ቃል አናግሯት።”

ወይም “እጥፍ።”

ወይም “አዘጋጁ።”

ወይም “ሰዎችም ሁሉ በአንድነት ያዩታል።”

ወይም “ሰው ሁሉ።”

ወይም “መንፈስ።”

ጣቶች ሲዘረጉ ከአውራ ጣት ጫፍ እስከ ትንሿ ጣት ጫፍ ድረስ ያለውን ርዝመት ያመለክታል። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።

“የተረዳ” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ወይም “ሊባኖስ እንኳ በቂ ማገዶ ማቅረብ አትችልም።”

ወይም “ቀልጦ የተሠራ ሐውልት።”

ወይም “ድቡልቡል።”

ወይም “ገዢዎችንም።”

ወይም “ሊደረስበት አይችልም።”

ወይም “ብርቱ ጉልበት።”

ወይም “እናንተ ደሴቶች፣ በፊቴ ዝም በሉ።”

ወይም “ከምሥራቅ።”

እሱን እንዲያገለግል የጠራው ማለት ነው።

አቅመ ቢስና ትንሽ መሆኑን ያመለክታል።

እስከ 15 ሜትር የሚደርስ ርዝመት ያለው ትልቅ ዛፍ ነው። ቅጠሎቹ ፈዘዝ ያለ አረንጓዴ ቀለም ያላቸው ሲሆን ቅርንጫፎቹ ደግሞ አመድማ መልክ አላቸው።

ወይም “ልብ እንድናደርግና።”

ቃል በቃል “ስለ መጀመሪያዎቹ።”

ወይም “ከምሥራቅ።”

ወይም “የበታች ገዢዎችን።”

ወይም “ሁሉም ሕልውና የሌላቸው ነገሮች።”

ወይም “ቀልጠው የተሠሩት ሐውልቶቻቸው።”

ወይም “ነፍሴ ደስ የምትሰኝበትና።”

ወይም “መመሪያውን፤ ትምህርቱን።”

ወይም “ክብሬን ለማንም አላጋራም።”

ወይም “በባሕር አጠገብ ያለ መሬት።”

ወይም “ቀልጠው የተሠሩትን ሐውልቶች።”

ወይም “መመሪያውን፤ ትምህርቱን።”

ወይም “መመሪያውንም፤ ትምህርቱንም።”

ወይም “በነፍስህም።”

ወደፊት የሚመጡትን የመጀመሪያዎቹን ነገሮች የሚያመለክት ሊሆን ይችላል።

ወይም “ትታመኑብኝ ዘንድ።”

እዚህ ላይ የተጠቀሰው የዕብራይስጥ ቃል ጥሩ መዓዛ ያለውን ተክል ያመለክታል። ሆኖም የተክሉ ምንነት በእርግጠኝነት አይታወቅም።

ወይም “የዓመፅ ድርጊትህን።”

የሕጉን አስተማሪዎች የሚያመለክት ሊሆን ይችላል።

ወይም “ከተወለድክበት ጊዜ።”

“ቅን የሆነ” የሚል ትርጉም ያለው ሲሆን ለእስራኤል የተሰጠ የማዕረግ ስም ነው።

ወይም “ለተጠማው ምድር።”

ምስሎቹን ያመለክታል።

ወይም “ቀልጦ የተሠራ ሐውልት።”

ወይም “በገጀራው።”

ወይም “በአምልኮ ቦታው።”

ወይም “ከዛፍ ተቆርጦ ለደረቀ ጉማጅ።”

ወይም “ነፍሱን።”

ወይም “የሐሰተኛ ነቢያትን።”

ቃል በቃል “የነገሥታትን ዳሌዎች ለመፍታት።”

ቃል በቃል “በሚገባ አስታጥቅሃለሁ።”

ወይም “ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ።”

ወይም “ለሚከራከር።”

ወይም “ያበጀውን።”

“ወይስ ሸክላው ‘ሥራህ እጀታ የለውም’ ይላል?” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ወይም “ምን እያማጥሽ ነው?”

“የጉልበት ሠራተኞች” ማለትም ሊሆን ይችላል።

“ነጋዴዎችና” ማለትም ሊሆን ይችላል።

“ባዶ እንድትሆን” ማለትም ሊሆን ይችላል።

በእንስሶቹ ላይ የተጫኑትን ጣዖታት ያመለክታል።

ወይም “ነፍሳቸውም ተማርኮ ይወሰዳል።”

ቃል በቃል “ይሰግዱለታል።”

ቃል በቃል “የመጀመሪያዎቹን።”

ወይም “መለኮት።”

ወይም “ዓላማዬ፤ ምክሬ።”

ወይም “ከምሥራቅ።”

ወይም “ዓላማዬን፤ ምክሬን።”

ቃል በቃል “ኃይለኞች።”

“ለማንም አልራራም” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ወይም “ንግሥት።”

ወይም “ንግሥት።”

“መተት ብታበዢና ታላቅ ኃይል ያለው ድግምት ብትደግሚም” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ወይም “በድግምት እንዴት እንደምታርቂውም አታውቂም።”

“ሰማያትን የሚከፋፍሉ፤ ኮከብ ቆጣሪዎች” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ወይም “ነፍሳቸውን።”

ቃል በቃል “ወደየአካባቢያቸው ለመመለስ ይባዝናሉ።”

“ከይሁዳ ዘር የተገኛችሁ” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ቃል በቃል “የመጀመሪያዎቹን።”

ወይም “ቀልጦ የተሠራው ሐውልቴ።”

ቃል በቃል “አታሳውቁም?”

ወይም “መርምሬሃለሁ።” “መርጬሃለሁ” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ወይም “ክብሬን ለማንም አላጋራም።”

ወይም “ከመንፈሱ ጋር።”

ወይም “ለገዛ ጥቅምህ ስል።”

ቃል በቃል “ከማህፀን ጀምሮ።”

ወይም “ሆኖም ይሖዋ ፍትሕ ያሰፍንልኛል።”

ወይም “ወሮታዬንም።”

ወይም “በነፍስ ለተናቀውና።”

ወይም “በጎ ፈቃድ።”

“በተራቆቱ ኮረብቶችም” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ወይም “ለምልክት የሚተከል ምሰሶዬንም።”

ቃል በቃል “በእቅፋቸው።”

ቃል በቃል “ሥጋም።”

“ማበረታቻ” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ወይም “በሚገባ የሠለጠነ አንደበት።”

ወይም “ሊሟገተኝ።”

ወይም “ፊት ለፊት እንጋጠም።”

ወይም “ይመካ።”

ወይም “አምጣ የወለደቻችሁንም።”

ወይም “ኃይሌንም።”

ወይም “አይንኮታኮትም።”

ወይም “መመሪያዬንም፤ ትምህርቴንም።”

“ትል” ማለትም ሊሆን ይችላል።

የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

ወይም “እንዳትንቀሳቀስ ያገደህ።”

ቃል በቃል “በመንገዶቹ ሁሉ ራስ ላይ።”

ወይም “ነፍስሽን ‘በላይሽ ላይ እንድንሻገር አጎንብሺልን!’ ባሏት።”

ወይም “ዓይን በዓይን።”

ወይም “ድል።”

ወይም “በእሱ ፊት ዱዳ ይሆናሉ።”

“እኛ የሰማነውን” ማለትም ሊሆን ይችላል።

“በፊቱ” የሚለው ቃል፣ ማንኛውንም ተመልካች ወይም አምላክን ሊያመለክት ይችላል።

ወይም “እሱን እንድንፈልግ የሚያደርግ የተለየ መልክ አልነበረውም።”

ወይም “ሥቃይን የሚረዳ።”

“ሰዎች ፊታቸውን የሚያዞሩበት ዓይነት ሰው ነበር” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ወይም “ተጨቆነ።”

ወይም “ስለ አኗኗሩ በዝርዝር ለማወቅ።”

ወይም “ተገደለ።”

ወይም “ግፍ።”

ቃል በቃል “ከሀብታም ሰው።”

ወይም “በሚሞትበት ጊዜ ከክፉዎችና ከሀብታሞች ጋር እንዲሆን አንድ ሰው መቃብሩን ይሰጣል።”

ወይም “ይሁንና ይሖዋ እሱን በማድቀቅ ደስ ተሰኝቷል።”

ወይም “ነፍሱን።”

ወይም “የይሖዋ ፈቃድ።”

ወይም “በነፍሱ ላይ ከደረሰው ችግር።”

ወይም “ነፍሱን።”

ወይም “የተተወችው ሴት ልጆች።”

ወይም “ጌታ ካላት ሴት።”

ወይም “ጌታሽ።”

ቃል በቃል “መንፈሷ የተጎዳ።”

ወይም “በእሳት ድንጋዮች።”

ቃል በቃል “ወንዶች ልጆችሽም።”

ቃል በቃል “የወንዶች ልጆችሽም።”

ወይም “ርስት።”

ወይም “በብዙ ድካም ያገኛችሁትን ገንዘብ።”

ቃል በቃል “በስብ።”

ወይም “ነፍሳችሁም ምርጥ ምግብ በመብላት ሐሴት ታደርጋለች።”

ወይም “ነፍሳችሁም በሕይወት ትኖራለች።”

ወይም “እምነት የሚጣልበት፤ አስተማማኝ የሆነ።”

ወይም “በነፃ ይቅር ይላልና።”

ወይም “ፈቃዴን።”

ወይም “የይሖዋን ስም ያስጠራል።”

ወይም “ብርቱ ነፍስ ያላቸው።”

መሞትን ያመለክታል።

“ከመከራ እንዲተርፍ መሆኑን” ማለትም ሊሆን ይችላል።

መቃብርን ያመለክታል።

ወይም “የማታለልም።”

ወይም “በደረቅ ወንዞች።”

ወይም “በደረቁ ወንዝ።”

ወይም “ራሴን ላጽናና ይገባል?”

የጣዖት አምልኮን የሚያመለክት ሊሆን ይችላል።

“ወደ ንጉሡ” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ወይም “ሲኦል።” የሰው ልጆችን ሁሉ መቃብር ያመለክታል። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።

ቃል በቃል “ያልዛልሽው።”

ወይም “ነገሮችን አልደበቅኩም?”

ወይም “እሱንም ሆነ ያዘኑ ወገኖቹን በማጽናናት እክሳቸዋለሁ።”

ወይም “ነፍሳችንን።”

ወይም “ደስታ።”

ወይም “ነፍሱን።”

ወይም “የገዛ ነፍስህ።”

ወይም “የተጎሳቆሉትንም ነፍሳት ብታረካ።”

ወይም “ነፍስህን ያረካል።”

ቃል በቃል “ክፍተት ያላቸውን።”

ወይም “ደስ የሚያሰኝህን።”

ቃል በቃል “እግርህን ብትመልስ።”

ወይም “በአባትህ በያዕቆብ ርስት እንድትደሰት አደርጋለሁ።”

ቃል በቃል “አልከበደችም።”

ወይም “ባዶ በሆነ።”

ወይም “ሐቀኝነት።”

ወይም “ሐቀኝነት።”

ቃል በቃል “ይህም በዓይኖቹ ፊት መጥፎ ነበር።”

ወይም “ድል አስገኘለት።”

ወይም “የድልን።”

ወይም “እጅጌ እንደሌለው ቀሚስ።”

ቃል በቃል “ከዘርህ።”

ቃል በቃል “ከዘርህ ዘር።”

ወይም “ወደ ንጋትሽ ጸዳል።”

ቃል በቃል “ይሸፍንሻል።”

ወይም “የውበት ቤቴን።”

ወይም “ወደ ጎጇቸውም መግቢያ።”

ወይም “እንደቀድሞው።”

ወይም “ውበት።”

ወይም “በበጎ ፈቃዴ።”

እስከ 15 ሜትር የሚደርስ ርዝመት ያለው ትልቅ ዛፍ ነው። ቅጠሎቹ ፈዘዝ ያለ አረንጓዴ ቀለም ያላቸው ሲሆን ቅርንጫፎቹ ደግሞ አመድማ መልክ አላቸው።

ወይም “ሞገስ።”

ወይም “ራሱን ውበት ለማጎናጸፍ።”

ወይም “ሀብት።”

ወይም “ነፍሴ በአምላኬ ሐሴት ታደርጋለች።”

ወይም “ለምልክት የሚተከል ምሰሶ።”

“ደማቅ ቀይ” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ወይም “ድል።”

ወይም “የማይዋሹ።”

ወይም “በፊቱ ያለው መልአክም።”

ወይም “ምድረ በዳ።”

ወይም “በጥልቅ ውኃዎች።”

ወይም “ያማረ።”

ወይም “የውበት።”

ወይም “ያደረግከው።”

ቃል በቃል “ልባችንን ያደነደንከው።”

ወይም “እሱን በትዕግሥት ለሚጠባበቁት።”

ቃል በቃል “እንድንቀልጥ።”

ወይም “ያበጀኸንም አንተ ነህ።”

ወይም “የውበት ቤተ መቅደሳችን።”

“በመጠበቂያ ጎጆዎችም” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ወይም “ርኩስ።”

“ቅድስናዬን ወደ አንተ አስተላልፋለሁና” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ቃል በቃል “በጉያቸው አስታቅፋቸዋለሁ።”

ቃል በቃል “በጉያቸው አስታቅፋቸዋለሁ።”

ቃል በቃል “በረከት።”

ወይም “ረባዳማ ሜዳ።”

ወይም “ታማኝ በሆነው አምላክ።” ቃል በቃል “በአሜን አምላክ።”

ወይም “ታማኝ በሆነው አምላክ።” ቃል በቃል “በአሜን አምላክ።”

ወይም “ችግሮች።”

ወይም “አይታወሱም።”

“አንድ ሰው መቶ ዓመት ባይሞላው እንደተረገመ ይቆጠራል” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ወይም “ስለ ቃሌ የሚጨነቀውን።”

“ጣዖት እንደሚያወድስ” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ወይም “ነፍሳቸውም በአስጸያፊ ነገሮች ደስ ትሰኛለች።”

ወይም “ስለ ቃሉ የምትጨነቁ።”

ወይም “ኃይል።”

ወይም “በሰዎች።”

ጣዖት አምልኮ የሚካሄድባቸውን ልዩ የሆኑ የአትክልት ቦታዎች ያመለክታል።

ቃል በቃል “ሥጋ።”

ወይም “ለማምለክ።”

ቃል በቃል “ለሥጋም።”

    የኢትዮጵያ ምልክት ቋንቋ ጽሑፎች (2011-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • የኢትዮጵያ ምልክት ቋንቋ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ